Home › Forums › Semonegna Stories › የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን አስመልክቶ የአቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና የጠ/ሚ አብይ አህመድ መልዕክት
Tagged: Haacaaluu Hundeessaa, ሃጫሉ ሁንዴሳ, ሽመልስ አብዲሳ, አብይ አህመድ, አዳነች አቤቤ
- This topic has 7 replies, 2 voices, and was last updated 4 years, 4 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
June 29, 2020 at 11:33 pm #14988AnonymousInactive
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል መሪ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያስተላለፉት መልዕክት
አዲአ አበባ (EBC) – የታዋቂዉና ተዋዳጁ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ አስመልክቶ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስትዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሀዘናቸውን ገለፁ።
በአዲስ አበባ ከተማ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ጀግናችን፣ የቅርብ አካላችን የትግልና የለዉጥ ምልክት የሆነዉ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት መመታቱን ሰምቻለሁ ሲሉ አሳዛኙ ዜና እንዴት እንደደረሳቸው አስረድተዋል። ሕይወቱንም ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም ሕይወቱ ሊተርፍ አለመቻሉንም ነው ያስታወቁት።
በአርቲስቱ ህልፈተ ሕይወት እንደ ግለሰብና እንደ አብሮ አደግ አብሮም እንደኖረ ሰዉ እንደ ታጋይና የትግል አጋር እንደ የችግር ጊዜ ጀግና ትልቅ ሀዘን ተሰምቶኛል ብለዋል ርዕሰ መስተዳደሩ።
ሃጫሉ ሁንዴሳ አርቲስት ብቻ ሳይሆን ታጋይም ነዉ ያሉት ርዕሰ መስትዳደሩ፥ ለእኔ ደግሞ ወንድሜም መካሪዬም ነዉ። ይህንን ጀግና ነዉ ያጣነዉ ብለዋል አቶ ሽመልስ።
የዚህ ጀግና ግድያም እንደቀላል እና ለቀላል ነገር የተፈጸመ ወንጀል አይደለም። ታስቦበት እና ታቅዶበት የተፈጸመ ድርጊት ነዉ። ይሄ ምንም ጥርጥር የለዉም ሲሉም ነው አቶ ሽመለስ የገለጹት። በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ የተወሰኑት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለጹት ርዕሰ መስትዳደሩ፥ ምርመራም እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።
የጸጥታ አካላት በሁሉም አቅጣጫ ተሰማርቷል። የዚህ ግድያ ዓላማም ሕዝብና ሕዝብን በማጋጨት፣ ሀገር ለማፍረስ፣ ሲዝቱ የነበሩ ኃይሎች ድርጊት ነው ብለዋል።
ከለዉጡ ወዲህ እንደዚህ ዓይነት ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል። አብዛኛዎቹን በማክሸፍ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ብሔር ብሔረሰቦች አንድ ላይ ቆመዋል። አሁን ያለዉን ለዉጥ ለማደናቀፍ ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል ሲሉ አስረድተዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ እንደገለጹት፥ ይህንን ለማክሸፍ የኦሮሚያ ፖሊስና የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይሎችም ትልቅ ሥራ ሠርተዋል ብለዋል። ዛሬ ደግሞ ይህንን የግድያ ወንጀል በመፈጸም ብሄር ብሄረሰቦችን ለማጋጨት ሀገር ለማፍረስ፣ አቅደዉ እንደተነሱ ጥርጥር የለዉም ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች እርስ በርስ በመደማመጥ፣ አንድላይ በመቆም ጀግናችን የከፈለለትን መስዋዕትነት፣ ይህ ለዉጥ እንዲሳካ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሁሉም ሰዉ በእርጋታ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ እንድንሻገር ጥሪ አቅርበዋል።
መንግሥታዊ መዋቅሩም ይህንን አደጋ ለመታደግ በአንድነት ሊቆም ይገባል ብለዋል አቶ ሽመልስ አብዲሳ። ለቤተሰቦቹ ፣ ለኦሮሞ ሕዝብና ለመላዉ የሀገራችን ሕዝቦች መጽናናትን እንደሚመኙ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገልጸዋል።
ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተወዳጁና ጀግናው አርቲስት ሃጫሉ ሞት የተሰማቸውን ከባድ ሀዘን ገልፀዋል።
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፥ “ሃጫሉ ቢሞትም መሞት የማይችል ሥራ ሠርቷል። ማንም ይሁን ማን ሃጫሉን የገደለው ሰው ከሕግ ማምለጥ አይችልም። የእኩይ እና አስነዋሪ ሥራውን ዋጋ በሕግ ያገኛል። የአርቲስት ሃጫሉን ነብስ ፈጣሪ በገነት ያኑር! ለቤተሰቡና ለመላው ሕዝባችን ፈጣሪ ትዕግስቱን፣ ብርታትና መጽናናትን ይስጠን!” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባስተላለፉት የሐዘን መልእክት ደግሞ፥ “ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች፥ ውድ ሕይወት አጥተናል። የዚህ ድንቅና አንፀባራቂ ወጣት አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሕይወት መቀጠፍ ከተሰማ ጀምሮ በከባድ ሀዘን ውስጥ ለምንገኝ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁ ። የዚህን ክፉ ድርጊት ሙሉ የፖሊስ ምርመራ ሪፖርት እየተጠባበቅን እንገኛለን። የድርጊቱን መጠን በመረዳት በሀገራችን ውስጥ ስለሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ትኩረት ሰጥተን የምንከታተልበት ወቅት ላይ ነን። ሀዘናችንን ራሳችንን በመጠበቅ እና ተጨማሪ ወንጀልን በመከላከል እንግለፅ” ብለዋል።
July 10, 2020 at 3:45 pm #15060AnonymousInactiveአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ተያዙ፤ ኦነግ ሸኔ ከተባለው ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ዋነኛ የተባሉ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሐምሌ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. አስታውቋል። ሦስተኛው ተጠርጣሪ ደግሞ እየተፈተለገ ነው ብሏል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክብርት አዳነች አቤቤ ሐምሌ 3 ቀን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አንደኛው ተጠርጣሪ ጥላሁን ያኒ የተባለ ሃጫሉ የተገደለበት ገላን የተባለዉ የአዲስ አበባ አካባቢ ነዋሪ እንደሆነ አስታዉቀዋል። በግድያው ተባባሪ የተባለዉ ሁለተኛ ተጠርጣሪ አብዲ ዓለማየሁም በቁጥጥር ስር መዋሉን ክብርት አዳነች ተናግረዋል።
ዋነኛ የተባለው ተጠርጣሪ ጥላሁን ያኒ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል መሣሪያውን የተኮሰው እሱ መሆኑን እና ተልዕኮውንም ከኦነግ ሸኔ መቀበሉን ማመኑ ተገልጿል። ጥላሁን ያኒ ለፖሊስ በሰጠው የእምነት ቃል ድርጊቱን የፈፀመው “ኦነግ ሸኔ” ከተባለው ክንፍ በተሰጠው ተልኮ መሆኑን መግለፁን፤ ተልኮውን የሰጡት ግለሰቦችም ሁለት መሆናቸውን አምኖ መቀበሉን ክብርት አዳነች አስረድተዋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ክብርት ሕግ አዳነች አቤቤ አያይዘው እንደገለጹትም ከበደ ገመቹ የተባለ ሦስተኛ ተጠርጣሪ እስካሁን በቁጥጥር ስር እንዳልዋለ እና በፖሊስ እየተፈለገ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኦነግ ሸኔ እያለ የሚጠራቸውና ራሱን “የኦሮሞ ነፃነት ጦር” ብለው በሎ የሚጠራው (ከዋናው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተከፍሎ ጫካ የቀረው) ቡድን ሀገር ወስጥ በተደጓጋሚ ጥቃት እያደረሰ ለንጹሃን ዜጎች ሞት፤ መቁሰል እና ለንብረት መጥፋት ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል። ለምሳሌ የካቲት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል የቡራዩ ከተማ ፖሊስ አዛዥን የገደለውና የካቲት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በአምቦ ከተማ ውስጥ ለድጋፍ ሰላማዊ ሠልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ ቦምብ በመወርወር የአካል ጉዳት ያደረሰው ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን መሆኑን የኦሮሚያ ክልል አስታውቆ ነበር።
በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም. ደግሞ የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ሠራተኛ የነበሩት አቶ አብዱላሂ ሳጆር ከአሶሳ ወደ ነቀምት ለሥራ ጉዳይ በመሄድ ላይ እያሉ ዛሬ በታጣቂዎች መገደላቸውን፤ ጥቃቱንም የፈጸመው ትጥቅ ያልፈታው ኦነግ ሸኔ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት አስታውቆ ነበር።
በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ ዞኖች በመንቀሳቀስ የሰላማዊ ሰዎችን ኖሮ እና እንቅስቃሴ የሚያውከውን የኦነግ ሸኔ ቡድን ድርጊት በማውገዝ የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብና ምስራቅ ወለጋ እንዲሁም ቡሎ በደሌ የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎች ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓም የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደው ነበር። በሰላማዊ ሰልፉም ላይ ነዋሪዎቹ ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን እንደማይወክላቸው፣ ይልቁንም የሕዝቡን ሰላም እያደፈረሰ መሆኑን ገልጸው ነበር።
July 15, 2020 at 3:06 pm #15093AnonymousInactiveየሕግ የበላይነትን ማስከበር እና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ የሀገር ህልውና መሠረት ነው!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ ምግለጫበቅርቡ በልጃችን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና ይህን ተከትሎ በሀገራችን በደረሰው የንፁሃን ዜጎች ሞትና የንብረት ውድመት የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለፅን ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በድጋሚ መፅናናትን እንመኛለን።
በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ምክንያት ሁላችንም ሀዘን እና የልብ ስብራት ውስጥ እንዳለን፥ ግድያውን ተከትሎ የደረሰው የበርካታ ዜጎቻችን ሞትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ሀዘናችንን እጅግ መራር አድርጎታል። የአርቲስቱ ግድያ እና እሱን ተከትሎ በብዙ ዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ የደረሰው ጥፋት እጅግ አሳሳቢ፣ አሳፋሪ እንዲሁም በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተወገዘ እና በሀገራችን በምንም ዓይነት ሊደገም የማይገባው ድርጊት ነው።
ኢትዮጵያውያን ከአምባገነናዊ አገዛዝ ነፃ ለመውጣትና የሚመጥነንን ሕዝባዊ አስተዳደር ለመትከል ረጅም ጊዜያትን በትግል አሳልፈናል፣ ብዙ ዋጋም ተከፍሏል። ዋጋ የተከፈለባቸው ሙከራዎች የከሸፉ ቢሆኑም በዚህ ሁሉ የታሪክ ውጣ ውረድ ግን የሀገር ህልውና በዚህ መልኩ ተፈትኖ አያውቅም።
ሀገራችን ከነችግሮቿ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ያላት፣ የምናወሳቸው እና የምንዘክራቸው ዛሬ ላለው ትውልድ መኩሪያ እና መመኪያ የሆኑ የማንነታችን መገለጫዎች የሞሉባት ሀገር ናት። በአንድ ወቅት አርቲስ ሃጫሉ እንደተናገረው ኢትዮጵያችን በብዙ የማንነት ቀለማት ኅብር የተዋበች ሀገር ናት። ኢትዮጵያዊነታችን በልዩነት ውስጥ የተጋመደ አንድነት መሆኑ ሃቅ ሆኖ እያለ የዘውግ ማንነት እና የቋንቋ ልዩነቶችን እየመዘዙ በሀገር አንድነት ላይ አደጋ መጣል ማንም አሸናፊ ወደማይሆንበት የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንደሚከተን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ግልፅ ሆኗል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት አስርተ ዓመታት በተለይም በሕወሃት/ኢህአዴግ ከፋፋይ አገዛዝ ስር ያሳለፈችው የፖለቲካ ትርክት ምን ያህል አደገኛ እንደነበር በግልፅ አይተናል። የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ምንም እንኳን ያረጀና በሕዝብ ትግል የተሸነፈ ቢሆንም፤ የተከላቸው መርዘኛ ቅራኔዎች በአጭር ጊዜ የሚነቀሉ አልሆኑም። እያየን ያለነው የንፁሃን ዜጎች ሕይወት መቀጠፍ እና በረጅም ጊዜ ድካም የተገነቡ ሀብቶች ውድመት የዚሁ አገዛዝ ቅሪቶች እንጂ የኢትዮጵያዊያን እሴቶች አለመሆናቸውን እንገነዘባለን።
በሰሞነኛው ብጥብጥ የደረሰው የበርካታ ዜጎች ሕይወት መቀጠፍና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እጅግ አስከፊና የትውልዱ ማፈሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ በዘውግ ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አካሄድ ወደ መቀመቅ እየወሰደን እንደሆነ ሕዝብና መንግሥት ከበቂ በላይ ትምህርት አግኝተዋል ብለን እናምናለን። በኢዜማ እምነት እውነተኛ ፌዴራሊዝም ሁሉም ራሱን በራሱ የማስተዳደር እና በመረጠው የመተዳደር መብት እንደሆነ እያስረገጥን ፖለቲካችን ከዘውግ እና ከሃይማኖት ካልተላቀቀ በስተቀር መጨረሻችን እጅግ አደገኛ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ስንገልፅ ነበር። በዘውግ እና በሃይማኖት ልዩነት ላይ የተንጠለጠለ የፖለቲካ አካሄድ ወደ መጠፋፋት እየወሰደን መሆኑን በመገንዝብ በማስተዋል እና በመረጋጋት እንድንጓዝ፤ በአንድ ሀገር ለውጥን ማዋለድ ብዙ ትግልና መስዋትነትን የሚጠይቅ እንደዚሁም ከፍተኛ ትዕግስትና ማስተዋል የሚሻ መሆኑን በተደጋጋሚ ስንገልፅ ብንቆይም ይህ አቋማችን ባንዳንድ ወገኖች እንደመለሳለስ ሲቆጠር ቆይቷል።
ሰሞኑን በተከሰተው ቅስም-ሰባሪ ጥፋት በሀገራችን ፖለቲካ የሚከተሉትን አበይት ነጥቦች በተለየ እንድንታዘብ አስገድዶናል። እነዚህም፦
- በድንገት የሚፈጠር ነውጥ ሀገራችንን ከማትወጣው የከፋ አዘቅት ውስጥ ሊያስገባት እንደሚችል፣
- በዘውግ እና በሃይማኖት ላይ የሚሰበክ የፖለቲካ ትርክት፤ ከዚህ ትርክት ተነስቶ የሚቆሠቆሰው ፍጹም ስሜታዊ ጥላቻ እና ጥላቻው የሚቀሰቅሰው የደቦ እንቅስቃሴ፤ የሰውን ልጅ ከሰብዓዊነት ማማ አውርዶ ወደ አውሬነት ሊቀይረው እንደሚችል ተገንዝበናል። በሌላ መልኩ ደግሞ በዚህ ዓይነት ፍጹም ስሜታዊ ሁኔታም ውስጥ ብሔራቸውን እና ሃይማኖታቸውን ተሻግረው፤ ለሰብዓዊነት እና ለጋራ ህልውናችን ዘብ ቆመው፤ በሁከቱ ምክንያት ለችግር የተዳረጉ ዜጎችን በመሸሸግ እና በማስጠለል የንፁሀንን ነፍስ የታደጉ የምንኮራባቸው ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን፣ ይህንን የመሰለው ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያዊያን እሴት ቢፈተንም በዚህ ዘመንም መቀጠሉን፣
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር እንደገለፁት፥ ችግር ፈጣሪዎች በመንግሥት አስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች ጭምር መሆናቸውን፤
- ችግሩ በተከሰተበት ጊዜ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የዜጎች ሕይወት በአደባባይ ሲቀጠፍ፣ የሀገር ሃብት ሲወድም አይተው እንዳላዩ የማለፍ ሁኔታ እንደነበር፤ የዚያኑ ያክል ደግሞ የሕግና የሞራል ኃላፊነታችውን በመወጣት እየሞቱና እየቆሰሉ ማኅበረሰቡን ከጥቃት የተከላከሉ ብዙ የጸጥታ ኃይሎችን ያየንበት መሆኑ፣
- በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ በወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ውድቀት ማግስት የፀጥታ ኃይሎች ባልተደራጁበት እና ከፍተኛ የመንግሥት አስተዳደር ክፍተት በነበረበት ወቅት ነዋሪው ለሰላምና መረጋጋት አኩሪ አሰተዋፅኦ እንዳበረከተ ሁሉ፥ ዛሬም ሕዝባችን በመኖሪያ ቀዬው ራሱን በማደራጀት ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ንብረቱን እና አካባቢውን ለመጠበቅ ያሳየው ቁርጠኝነት እጅግ የሚመሰገን ተግባር ሆኖ ጎልቶ መታየቱ፤
ከሰኔ 22 በኋላ በጉልህ የታዘብናቸው ክስተቶች ነበሩ።
በቅርቡ የተከሰተው እና የሀገርን አንድነት የተፈታተነው አውዳሚ ክስተት ለጊዜውም ቢሆን መክሸፉ ችግሩ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ አግኝቷል ማለት አይደለም። የሀገራችንን አንድነት የሚፈታተኑ ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። በዚህ ጊዜ እንደ ተፎካካሪ ድርጅቶችም ሆነ እንደ ዜጎች ያለብን ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማወቅና በተግባር ለማሳየት መዘጋጀት ይጠበቅብናል። የሀገርን አንድነት እና ሰላም ባጭር ጊዜ፤ ለዘላቂው ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ምሥረታ፤ ከምሩ የቆመ መንግሥት እስካለን ድረስ (በተለያዩ የፖለቲካ እና የፖሊሲ አመለካከት የምናምን የፖለቲካ ድርጅቶችና ዜጎች ብንሆንም እንኳን) ይህን ማዕከላዊ መንግሥት ለማዳከም፤ በዚህም የተለያዩ የጦር አበጋዞች የሚርመሰመሱበት የእርስበርስ ግጭት ውስጥ ሊዳርጉን የሚፈልጉ ኃይሎች የሚያደርጉትን ዘመቻ በማስቆም በኩል ሙሉ ትብብር ማድረግ እንዳለብን ልናውቅ ይገባል። በእነኝህ አንኳር ጉዳዮች ላይ የምንስማማ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ ሌሎች የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት እና አባላት ለሀገራችን መኖር እና ለሕዝቧ ሰላም ባንድነት በተግባር መቆም እንደሚኖርብን መገንዘብ ያለብን ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ኢዜማ በሀገር አንድነትና በማኅበረሰባችን ሰላም ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ድርድር መኖር የለበትም ብሎ ያምናል። እነኝህን ሁለት መሠረታዊ እሴቶች በዋናነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ደግሞ ሀገራዊ መንግሥቱ ነው። ያለ ሀገር ፖለቲካም ሆነ ዴሞክራሲ ትርጉም የላቸውም። ለዘላቂው የሀገር አንድነት እና ሰላም ከዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መኖር፤ ከፍትህ መኖር፤ ከዜጎች እኩልነት መረጋገጥ ወዘተ… ጋር በጥብቅ የተቆራኙ መሆናቸውን እናምናለን። ስለሆነም ሁሉም የሀገራችን ዜጎች ይህን ፈታኝ ጊዜ በትግስት፣ በማስተዋልና በጥንቃቄ እንዲሻገሩት እና የሀገራችንን አንድነት እና ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሁላችንም ያለብንን ኃላፊነትና ድርሻ የመወጣት ግዴታ እንዳለብን በማሰብ ኢዜማ በሚከተሉት ወሳኝ ነጠቦች ላይ በድርጅታችን መርሆዎች ላይ የተመሠረተ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፤
- የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጥረት በመሆኑ በተለይም ፈታኝ ጊዜያትን ያሳለፈው፣ ከፍጥረታት ልቆ የቆየው እና ተፈጥሮን ገርቶ ትውልድን ማስቀጠል የቻለው በተለያዩ ማኅበራዊ አደረጃጀቶች አቅም ፈጥሮ በመተጋገዝ ነው። በአደረጃጀቱ አያሌ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ተቋቁሞ አሳልፏል፤ ከእነዚህም አደረጃጀቶች መካከል «መንግሥት» ትልቁ የሰው ልጅ አደረጃጀት ሲሆን በውስጡ በርካታ አደረጃጀቶችን እንደያዘ ግልፅ ነው።
የእነዚህ አደረጃጀቶች ዋና መሠረት ደግሞ የቆየው ማኅበራዊ አደረጃጀት ነው። በሀገራችንም በርካታ የቆዩ የአደረጃጀት ዓይነቶች አሉ። ይህንን ማጠናከር የሀገርን ህልውና እና የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በእጅጉ ይረዳል የሚል እምነት አለን። ማኅበራዊ ፍትህ በነገሰባቸው በርካታ ሀገራት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ነፃ ማኅበራዊ አደረጃጀቶች አሉ። እኛም ሀገር ሰሞኑን በተፈጠረው ችግር ሕዝቡ በየመኖሪያ ቀዬው ተደራጅቶ ሰላሙን ሲያስከብር ተመልክተናል። በተለይም በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ ከተሞች የታየው አደረጃጀት ትልቅ ትምህርት ሰጪ ነበር። አዲስ አበባ ከተማ ሁሉንም የሀገራችንን ማኅበረሰቦች አቅፋ የምትኖር፤ በዓለማችን በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የዲፕሎማቲክ ከተሞች አንዷ እንደመሆንዋ በውስጧ ያቀፈቻቸው ዜጎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱባትና ልዩልዩ አስተሳሰቦችና እምነቶች ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ ናት። ይህን መሰሉ ማኅበራዊ እሴት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እናምናለን። ይሁን እንጂ ሰሞነኛው ክስተት እንደሀገር ለከፍተኛ ውርደት የዳረገን የታሪካችን ማፈሪያ ሆኖ አልፏል። በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሕዝብ ዘመኑን በሚመጥን እና በሠለጠነ መንገድ በዘውግ ማንነት፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳያደርግ በመደራጅት ቤተሰቡን እና አካባቢውን ከጥፋት ከመከላከሉም ባሻገር ከተማዋን እጅግ ከከፋ ውድመት ታድጓታል። ለዚህም አክብሮት እና ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን።
ይህን ዓይነቱ መሰባሰብ ለወቅታዊ ችግሮች ብቻ ሳይሆን ለዘላቂውም ጭምር ጠቀሜታው የጎላ ስለሆነ የማኅበረሰቡ የቆዩ አደረጃጀቶች እንዲበረታቱ መሥራት ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር አሁን እየታዩ ያሉ አደረጃጀቶችን በየአካባቢው በሕዝብ በሚመረጡ አካላት ማጠናከር፣ እውቅና መስጠት እና የፀጥታ ጉዳይን በሚመለከት አደራጃጀቶቹን ከማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ እና የመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር የማጣመሩን ተግባር መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተቻለ ፍጥነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። አደረጃጀቶቹ የጋራ ደኅንነትን ከመጠበቅ በተጨማሪ የከተማዋ ምልክት የሆነውን ሁሉም ዓይነት ማንነቶች ተከብረውባት፣ ዜጎች ተጋግዘው እና ተባብረው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን በቀጣይነት ለማረጋገጥም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አደራ እንላለን።
እነዚህ አደረጃጀቶች በሌሎች ኃይሎች እንዳይጠለፉ እና ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ደኅንነታቸውን ከመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ጋር እንዲያስጠብቁ ከማስቻል ያፈነገጠ ዓላማ ማስፈፀሚያ መሣሪያ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባም ልናሳስብ እንወዳለን።
- የደኅንነት እና የፀጥታ ተቋማት ዋና ተግባር የሀገርን ደኅንነት እና የሕዝብን ሰላም ማስጠበቅ ነው። ሰሞኑን ሀገራችን በገባችበት ችግር ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጡ የነበሩ የፀጥታ ተቋማት ኃላፊዎች ችግሩ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ የዘገዩት በሆደ-ሰፊነት የፖለቲካውን ምህዳር ለማስፋት መንግሥት በያዘው አቋም ምክንያት መሆኑን ሲገልፁ ሰምተናል። ይህ ተቋማዊ ኃላፊነታቸውን የዘነጋ አካሄድ እና አገላለፅ በቶሎ ሊታረም ይገባል። የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት ለከፋ አደጋ ዳርጎ ሆደ-ሰፊነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ መነገር የለበትም። ይህንን የማድረግ መብትም ሆነ የሕግ ድጋፍም የላቸውም። የፀጥታ ተቋማት በየደረጃው ተቀናጅተው በመሥራት እና ሀገርን እና ዜጎችን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጥቃት መታደግ ነው ዋና ተልዕኳቸው። በተለይም በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ሕዝብን በማስተባበር አደጋ ከመድረሱ ቀድሞ የማክሸፍ ሥራ በመሥራት፤ አንዴ ከተፈጠረ ደግሞ በፍጹም ቁርጠኝነት ሀገርን እና ሰላማዊ ሕዝብን ከጥቃት መከላከል የፀጥታ አካላት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ተግባር እንደሆነ በአንክሮ እንገልፃለን።
- ለዘመናት የታገልንለት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ሀገርን እና ሕዝብን ለአደጋ እስከሚያጋልጥ ልቅነት ድረስ መሆን እንደሌለበት ደጋግመን ስንገልጽ ቆይተናል። አሁን እንደምናየው የግል የብዙሃን መገናኛዎች የተወሰኑት በፓርቲ ልሳንነት፣ የተወሰኑት ደግሞ በጥቅም አሳዳጅነት ሀገርን እና ዜጎችን አደጋ ላይ ሲጥሉ ሥልጣን የተሰጠው አካል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ነበረበት፤ አለበትም። ከዚህ አንፃር የግል ብዙሃን መገናኛዎች የሀገሪቱን ሕግና የሙያውን ሥነ-ምግባር ጠብቅው እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን። በሌላ በኩል የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ደግሞ ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ በተለይም የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቃለመጠይቆችን ብቻ በማስተናገድ መሪ አዘጋገብ እና ፍረጃ ውስጥ መግባታቸው የዜጎችን በፍርድ ቤት ጥፋተኛነታቸው እስኪረጋገጥ ድረስ እንደነፃ የመታየት መብት የሚጋፋ እና የፍትህ ተቋማቱን አካሄድ የሚያዛባ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲያርሙት እናሳስባለን። የመገናኛ ብዙሃን እንዲመሠረት የምንፈልገውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መርህ የተከተሉ፣ የሕዝብ መረጃ ማሳወቂያ፣ ማስተማሪያ እና ማረጋጊያ መሆን እንሚገባቸውም በአፅንዖት እንገልፃለን። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የብዙሃን መገናኛ ተቋማትን በቅርበት እየተከታተለ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድም አበክረን እናሳስባለን።
- የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት ለዘላቂ ሀገራዊ መረጋጋት መሠረት መሆኑን እናምናለን። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚመሠረተውም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማለትም በእውነተኛ ውይይትና ድርድር ብቻ ነው።
ይህንን ለማድረግም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ዘመናዊ፣ የሠለጠነ ፖለቲካ እና የጨዋታ ሜዳውን ሕግ ያከበረ አካሄድ መከተል ይገባናል። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደምም ሆነ ሰሞኑን የተከሰተው የመገዳደልና የመጠፋፋት ፖለቲካ ወደ ሰለጠነ ፖለቲካ የሚወስደን ሳይሆን ከዚህ ቀደም ዋጋ ወደከፍልንባቸው የተወሳሰቡ ችግሮች ውስጥ መልሶ የሚዘፍቀን አካሄድ ነው። በዚህ ረገድ የሁሉም ድርሻ አስፈላጊ ቢሆንም በሀገር አንድነት፣ በሰላማዊ እና በሠለጠነ የፖለቲካ ትግል እንዲሁም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግርን ከሚያምኑ ወገኖች ጋር ለሚደረግ ውይይት ገዢው ፓርቲ ወሳኝ ድርሻ አለው። በአንድ በኩል የሀገርን ህልውና እና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቁን አጠናክሮ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ሽግግር እውን ለማድረግ የሚያስችል እና ለሁሉም ተሰፋ የሚሰጥ የባለድርሻዎች ውይይት ሳይውል ሳያድር እንዲጀመር እንጠይቃለን።
- የሙያ እና የሲቪክ ማኅበራት በአጠቃላይ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፤ በተለይ ደግሞ እንደኛ ሀገር ፖለቲካችንን ሰቅዞ ከያዘው የዘውግ ፖለቲካ ወደ ጤናማ የሀሳብ ፖለቲካ በማሸጋገር እንቅስቃሴ ውስጥ የሚኖራቸው ሚና እጅግ የጎላ እና ሚዛንን ማስጠበቅ የሚያስችል እንደሚሆን ይታመናል። ባለፉት 27 ዓመታት በሀገራችን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሙያ ማኅበራት በገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ ስር የወደቁ እና ተዳክመው የቆዩ መሆናቸውን እንረዳለን።
ረጅም ጊዜ ከቆየ አምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግር ውስጥ ለረጅም ጊዜ የተጠራቀሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሁሉ በቶሎ እንዲፈቱ መጓጓት እና ዜጎች ጥያቄዎቻቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን የሚያቀርቡበት እና እንዲመለስላቸው ጫና ለማሳደር ኃይልን የቀላቀለ መንገድ መከተላቸው ትልቅ ተግዳሮት ይፈጥራል። የሙያ እና የሲቪክ ማኅበራት ራሳቸውን ከነበረባቸው ጭቆና ነፃ አውጥተው እና ተጠናክረው የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር እና ተደራሽ የሆኑ ብዙሃን መገናኛዎችን በመጠቀም ስለ ሰላማዊ ተቃውሞን የማሰሚያና ጫና የማሳደሪያ መንገዶች በሰፊው በማስተማር ከሕዝብና ከእውነት ጎን ቆመው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሀገር መረጋጋት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን።
- በሀገራችን በተደጋጋሚ ጊዜ ፖለቲካዊ ሽፋን እየተሰጣቸው ከተነሱ ረብሻዎች ጋር በተያያዘ በርካታ የንፁሃን ዜጎች ሕይወት በከንቱ ሲቀጠፍ እና የግል ባለሃብቶችም ንብረት በሚያሳዝን ሁኔታ ሲወድም እየተመለከትን ነው። እነዚህ ረብሻዎች እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱም የሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ አደጋ እንዳያደርሱ መቆጣጠር እና የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ዋነኛ የመንግሥት ሥራ በመሆኑ፣ መንግሥት ይህን ኃላፊነቱን በሚገባ ሳይወጣ ቀርቶ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ ወጥቶ ይቅርታ መጠየቅ እና ከዚህ በኋላ እንደዚህ ዓይነት ጥፋት በፍፁም እንደማይደገም ቃል ሊገባ እና ሊያረጋግጥ ይገባዋል።
መንግሥት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ እና የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ጉዳይ ባስቸኳይ አጣርቶ ፍትህ እንዲያገኙ ሊያደርግ ይገባል። እንደዚሁም የሀገራችን ኢኮኖሚ ዳዴ በሚልበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ባለሀብቶች አንጡራ ሃብታቸውን አፍስሰው የገነቧቸው መሠረተ ልማቶች እንደዘበት ወድመው፣ ተቃጥለው እና ሠራተኞች ተበትነው ማየቱ እጅግ ያሳዝናል። በቀጣይም ሃብታቸውን አፍስስው ሊያለሙ የሚችሉ ባለሃበቶችም ዋስትና ስለማይኖራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን ከማፍሰስ ይታቀባሉ። ከዚህ አንፃር በሰሞኑ ክስተት ቤት ንብረታቸውና ትልልቅ የንግድ ተቋሞቻቸው ለወደመባቸው ዜጎች መንግሥት ተገቢውን ካሳ ከፍሎ እንዲያቋቁማቸው አበክረን እንጠይቃለን።
በመጨረሻም አሁን ያለንበት ሁኔታ ለሀገራችን እጅግ ፈታኝ መሆኑ ግልፅ ነው። ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ከዕለት ዕለት እየተስፋፋ መጥቷል። ከአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም በተለይም ከህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ ግብፅ የፈጠረችው እሰጥአገባ ያመጣው ጫና ከሀገራችን አልፎ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ መነጋገሪያ ሆኗል። ኢትዮጵያውያንም በእነዚህ አንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምንግዜውም በላይ በጋራ መቆም የሚገባን ትክክለኛው ሰዓት ላይ እንገኛለን።
በመሆኑም የውስጥ ልዩነቶቻችንን በሰለጠነ ፖለቲካ አሰታርቀን እንደሀገር የተደቀኑብንን ተደራራቢ ፈተናችዎች በፅናት ማለፍ ካልቻልን ለትውልድ የምትሆን ሀገር ማሻገር ይቅርና እኛ ራሳችን ከማንወጣው የከፋ አዘቅት ውስጥ ገብተን እንደምንዳክር መረዳት ይኖርብናል። ስለሆነም የሕግ የበላይነትን በማክበር፣ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት በመተባበር እና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት አሁን ካለንበት ውስብስብ ችግር ወጥተን ሀገራችንን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጋራ እንድናሻግር ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ሐምሌ 6 ቀን 2012 ዓ.ም.July 18, 2020 at 12:25 am #15107AnonymousInactiveበየአካባቢያችን የሚገኙ የግጭት ነጋዴዎችን በጋራ እንክላከል ― የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
በሀገራችን በየአካባቢው የሚገኙ የግጭት ነጋዴዎችን በጋራ እንከላከል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥሪውን አቀረበ። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን ዙሪያ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል።
ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል:-
የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፥
ክቡራትና ክቡራን፥ባለፈው ሰሞን የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ግጭት ጠማቂዎች ባስነሱት ሁከት አያሌ ወገኖቻችን ሕይወታቸው አልፏል፤ የጸጥታ አካላት ተገድለዋል። በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የግለሰቦች፣ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ወድሟል።
በቅድሚያ በሁከቱ ሕይወታቸው ላለፈው ወገኖቼ የተሰማኝን ሀዘን መግለጽ እወዳለሁ። ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እመኛለሁ። መንግሥት ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን የተጎዱትን ለማቋቋም እንደሚሠራ፤ ወንጀለኞቹንም ለፍርድ የማቅረቡን ሂደትና የሕግ የበላይነትን ማስከበሩን እንደሚቀጥል በዚሁ አጋጣሚ በድጋሚ ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ።
ሁላችንም እንደምናውቀው የፖለቲካ መዝገበ ቃላችን የተሞላው ‹ምታው፣ ደምስሰው፣ ቁረጠው እና ፍለጠው› በሚሉ የሞት ቃላት ሲሆን፥ በመሳደድና ማሳደድ ዙሪያ መሽከርከር ከጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል። “ድርጊት ሲደጋገም ልማድ ይሆናል” እንዲሉ አሁን ያለው የፖለቲካ ባህላችን የተቀዳው ባንድ ወቅት እንደቀልድ በጀመርናቸው የሴራ፣ የመገዳደልና በጎራ ተከፋፍሎ ድንጋይ የመወራወር አጉል ልማዳችን ነው። በየአጋጣሚው ሲነገር፣ ሲጻፍና ሲዜም የኖረው ይሄ የተበላሸ ፖለቲካችን በትውልድ ጅረት ተንከባልሎ እነሆ ዛሬ ላይ ደርሷል።
ይሄው እኛም እንደ መልካም ውርስ የመጠላለፍና የመገዳደል ባህልን ተቀብለን የየዕለት ኑሯችን በቆምንበት መርገጥ፣ ዛሬም ነገም አንድ ቦታ መሽከርከር ሆኗል። ሀገራችንን ወደፊት ለማራመድ የምንሻ ከሆነ ይሄንን ክፉ ውርስ አሽቀንጥረን መጣል ይኖርብናል፤ በመጥፎ ባህል ያደፈ ካባችንን አውልቀን በምትኩ በጋራ የምንበለጽግበትን ካባ ልንደርብ ይገባል። ለውጥ ሰዎችን በሰዎች፣ መሪዎችን በመሪዎች የመቀየር ሂደት ብቻ አይደለም። የተበላሸውን የፖለቲካ ሥነ ልቡና፣ የፖለቲካ ባህልና የፖለቲካ ሥርዓት ጭምር በአዲስ የመቀየር ጉዞ ነው። ተቋሞቻችንን፣ የእርስ በርስ ግንኙነታችንና የፖለቲካ ቋንቋችንን ጭምር መለወጥ ይገባናል። ይሄን ማድረግ ከቻልን እንደሀገርና እንደ ሕዝብ ወደ ምናስበው የብልጽግና ሠገነት እንሻገራለን። ካልሆነም የኋቀርነት አዘቅት ውስጥ ስንደፋደፍ ዘላለም መኖራችን ነው።
ሁላችንም ልብ ካልን ምንጊዜም ከመከራ የሚያተርፉ አካላት በዙሪያችን እንዳሉ እንረዳለን። የከብት እልቂት ለገበሬ መከራ ቢያመጣም ለጅብ ግን ሠርግና ምላሽ ነው። የዶሮ እልቂት ለባለቤቱ ኪሳራ ለሸለምጥማጥ ደግሞ ትርፍ ነው። የሁለት በጎች ጠብ ጥቅም ካስገኘ የሚጠቀመው ተኩላውን ነው። የሁለት ርግቦች ግብግብ አንጋጦ ለሚጠብቃቸው ድመት በረከት ነው። ምንም መልፋት ሳይጠበቅባቸው ድመቱና ተኩላው በርግቦቹና በበጎቹ ጸብ ምክንያት በቀላሉ ሆዳቸውን ይሞላሉ። በተመሳሳይ በሰዎች ጸብም የሚያተርፉ ሞልተዋል። በእኛም ሀገር አሉ። አሁንም እርስ በእርሳችን እያጋጩን ከፍተኛ ጥቅም የሚያገኙት እነዚሁ ከቅርብም ከሩቅም ሆነው የሚጠብቁ የግጭት ነጋዴዎች ናቸው።
ለለውጥ ስንታገል ዋነኛው ዱላ የሚሠነዘርብን ከመከራችን ሲያተርፉ ከነበሩ አካላት እንደሆነ ግልጽ ነው። በሁላችንም ቤት ለዘመናት የተዘራ የልዩነት መርዝ አለ። አሁን እዚህም እዚያም ሲፈነዳ የምናየው እሱን ነው። ፈንጂው ዛሬ ቢፈነዳም ከተቀበረ ግን ቆይቷል። የግጭት ፈንጁ ምን እንደሆነ፣ የት የት እንደተቀበረ፣ በማን እንደተቀበረ ማወቅ ለአንድ አካል የሚተው የቤት ሥራ ሳይሆን የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። ማወቅም ብቻውን በቂ አይደለም፤ አንድ በአንድ እየተቀለቀመ መክሸፍ ይኖርበታል። ሕዝብ እንዲበጣበጥ፣ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳ፣ አንዱ ሌላውን እንዲገድል፣ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያውያንን ንብረት እንዲያወድሙ፣ የጥላቻና የሞት ድግስ ቅስቀሳዎች በየሚዲያው እንዲካሄዱ የሚያደርጉት ፈንጂ ቀባሪዎቹ የግጭት ነጋዴዎች ናቸው። አንዳንዶች ከእነሱ ጋር ተባብረው በሕዝብ ላይ ፈንጅዎቹን ያፈነዳሉ። ሳያውቁ ቆመውበት የሚፈነዳባቸውም ይኖራሉ። አንዳቸውም ጉዳትን እንጂ ጥቅም አያስገኙልም። ከእንግዲህ ይበቃል፤ በጉያችን ይዘን ዘወትር መሰቃየት የለብንም።
የሀገሬ ልጆች፥
አንገትን እንደ ሰጎን አሸዋ ውስጥ በመቅበር መፍትሔ የምናገኝበት ጊዜ ላይ አይደለንም። አጥፊዎቹን ፊት ለፊት እስካልተጋፈጥናቸው ድረስ የሚያደርሱትን ችግር በመሸሽ ብቻ አናመልጠውም። ላለማየት ጭንቅላትን ጎሬ ውስጥ በመቅበር ዘላቂ መፍትሔ ይገኛል ማለት ዘበት ነው። ዛሬ ጎረቤታችንን የጎበኘ እሳት ነገ ቤታችንን ማንኳኳቱ አይቀርም። ተነጣጥሎ አንድ ባንድ ማገዶ ከመሆን ይልቅ ተባብሮ የተለኮሰውን እሳት እስከወዲያኛው ማሰናበት ይበጃል። ለዚያም ነገሮችን በጥንቃቄ መመልከት፣ ትዕግሥትና አርቆ አስተዋይነት በተሞላበት መልኩ መገምገምና ጥበብ ባለው ሁኔታ ተንቀሳቅሶ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።
ማን ነው በየአካባቢያችን ሰላም እየነሣን ያለው? ከእነማን ጋር ሆኖ ነው የሚበጠብጠን? ለምንድን ነው የሚበጠብጠን? ጥቂት ነውጠኞች የጫሩት እሳት ብዙኃኑን ሲለበልብ ለምንድን ነው እኛስ ማስቆም ያልቻልነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። እሳት ለኳሾቹ እነማን እንደሆኑ፣ ማገዶ እያቀበሉ እሳቱን የሚያባብሱት እነማን እንደሆኑ፣ ዳር ቆመው የሚያዩትና አብረው የሚሞቁት ጭምር እነማን እንደሆኑ ልናውቅ ይገባል። በመንግሥት በኩል እነዚህን ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመርመርና አስፈላጊውን ሕግ የማስከበር ርምጃ ለመውሰድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቁርጠኞች ነን።
እሳቱን ማጥፋት ሲገባቸው በቸልታ የሚያልፉት ሰዎች በአንድም በሌላም መንገድ መከራችንን የሚያበዙብን መሆናቸው አያጠያይቅም። የሚወድመው የሀገር ሀብት፣ የሚሞተው የሁላችንም ወገን ነውና ሕጋዊና ሞራላዊ ኃላፊነት እያለባቸው አይተው እንዳላዩ የሚያልፉ አካላት ፈጽሞ ከተጠያቂነት አያመልጡም።
የተጋረጠብን ችግር እስከወዲያኛው እንዲወገድ ወላጆች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የየአካባቢው የባህልና የሐሳብ መሪዎች አስተዋጽኦችሁ ከፍተኛ ከመሆኑ አኳያ ያለማመንታት ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። ከምንም በላይ ሕዝባችን አስፈላጊውን ሁሉ ከማድረግ መቆጠብ እንደሌለበት ሊታወቅ ይገባል። እያንዳንዱ ዜጋ ጥፋተኞቹ በማስረጃ ለፍርድ እንዲቀርቡ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት አለበት፤ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር ተባብሮ መሥራት፣ የመንደሩንና የከተማውን ሰላምና ልማት ተደራጅቶ መጠበቅ አለበት። በየአካባቢው የተለየ እንቅስቃሴ ስናይ ለምን? ብለን ልንጠይቅ፤ እነማን እንደሆኑ ልናውቅ፤ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን አጥፊዎችን ለሕግ ልናቀርብ ይገባል። ጎረቤቶቻችንን፣ የልማት ተቋማትን፣ የንግድ ድርጅቶችን፣ ሕዝባዊ ንብረቶችን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን፣ የእምነት ተቋማትን፣ የትምህርትና የጤና ተቋማትን በጋራ እስካልጠበቅናቸው ድረስ ነገ የጉዳቱ የመጀመሪያ ሰለባዎች እኛው ስለመሆናችን ነጋሪ አያሻንም።
ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ጠባሳ እንዲቀመጥብን መፍቀድ የለብንም። የትላንቶቹ ጠበሳ ስላቆዩልን እኛ የዛሬዎቹ ምን ያህል አበሳ እያጨድን እንደሆነ ሁላችንም የሚገባን ይመስለኛል፤ ስለሆነም ከዚህ ስህተት ተምረን ዳግም አበሳው ወደ ልጆቻችን እንዳይሻገር ማድረግ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። በጉያችን ታቅፈናቸው የሚዘርፉን፣ የሚያቃጥሉን፣ የሚያበጣብጡንና የሚያገዳድሉን ሰዎች የጊዜ ጉዳይ እንጂ የእጃቸውን ማግኘታቸው፤ ከእነሱ አልፎ በልጆቻቸው በኩል ብድሩን መክፈላቸው አይቀሬ ነው።
ውድ ኢትዮጵያውያን፥
ሀገሩንና ሕዝቡን እንደሚወድ ዜጋ ከእያንዳንዳችን ሁለት ነገሮች ይጠበቁብናል። ከተጎዱ ወገኖቻችን ጎን መቆምና አለኝታነታችንን ማሳየት አለብን። የቦታ መቀያየር ይሆናል እንጂ እኛም አንድ ቀን በተጎጂዎች ቦታ የማንቆምበት ምንም ምክንያት የለም። ስለሆነም በሞራል፣ በኢኮኖሚና በባህላዊ መንገድ ደግፈን ተጎጂዎችን ወደነበሩበት እንመልሳቸው። የተቃጠለና የወደመ ንብረታቸውን ለመተካት አጋርነታችን እናሳያቸው፤ ቁስላቸው ጠገግ እስኪል እናክማቸው፤ የፈረሰ ቤታቸውን እንገንባላቸው። የማይተካ ሕይወታቸውን ለተነጠቁ ዜጎቻችን ጸሎት፣ ለሟች ቤተሰቦች መጽናናት እንዲያገኙ እናድርግ። በሁሉም ዘርፍ ያሉ መሪዎች ለዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ሆነው መልካም አርአያነታቸውን እንደሚያስመሰክሩ እተማመናለሁ።
ሰላማችንን ለማስጠበቅ ደፋ ቀና ሲሉ የተሰዉት ፖሊሶችና የጸጥታ አስከባሪዎች ያለእነሱ ትጋትና መሥዕዋትነት የሚደርሰውን አደጋ በቀላሉ መቆጣጠር ባልቻልን ነበር። ለሀገርና ለሕዝብ ደኅንነት ሲሉ የቆሰሉና የሞቱ የሕግ አስከባሪዎች የከፈሉት የሕይወት ዋጋ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ በክብር የሚታተም ስለመሆኑ አልጠራጠርም። ለሟች ቤተሰቦቻቸው፣ ለወላጅና ለልጆቻቸው ጭምር ተገቢውን ክብር እንሰጣለን።
በመንግሥት በኩል ዐቅም በፈቀደ መጠን የተጎዱትን ንጹሃን ዜጎችና የሕግ አስከባሪዎች ለመደገፍና ለማቋቋም ይሠራል። በሌላ በኩል የችግሩን ነዳፊዎች፣ ጠንሳሾች፣ ተልዕኮ ተቀባዮችና ፈጻሚዎችን በየደረጃው መርምሮና አጣርቶ ለሕግ ያቀርባል። ይሄን መሰል ክስተት ዳግም እንዳይፈጠርም ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የጸጥታ አካላት ሥምሪትን አጠናክሮ ይቀጥላል።
ከዚህ በተረፈ ሁላችንም ውድመትና ጥፋት ከእንግዲህ በሀገራችን ላይ እንዳይደገም አምርረን እምቢ ማለት ይኖርብናል። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ለፖለቲካ ትርፋቸው ሲሉ በየሚዲያው ‹በለው፣ በለው› የሚሉ አካላትን አሁን በግልጽ ነቅሰናቸዋል። በየአካባቢያችን የሚገኙትን የግጭት ነጋዴዎች በሚገባ አውቀናቸዋል። መረባቸውን እየበጣጠስነው ነው። ለጊዜው የተደበቁ የሚመስላቸውም በቅርቡ አደባባይ ይወጣሉ። እሳቱን ለኩሰው ጢሱ እንዳይሸታቸው መሸሽ፤ ፈንጂውን ወርውረው ፍንጣሪ ሳይነካቸው እስከመጨረሻው ማምለጥ አይችሉም። ሰላም ወዳዱ ሕዝባችን በእሳት እየተቃጠለና ሕይወቱን እየተነጠቀ ከእንግዲህ ይቀጥላል ማለት ዘበት ነው። አብሮነትን የሚፈልገው ዜጋችን፣ ለማደግና ለመበልጸግ ሌት ተቀን ደፋ ቀና የሚለው ሕዝባችን እየተጎዳ የግጭት ነጋዴዎቹ በምቾት አይቆዩም።
በሕዝብ መከራ ካላተረፍን ለሚሉ፤ በምስኪን ዜጎች ሞት ሥልጣን ለመያዝ ለሚቋምጡ ራስ ወዳዶች ‹አሻንጉሊት› መሆን ከእንግዲህ ይበቃል። ሰላማችንና ልማታችን፣ ዕድገታችንና ብልጽግናችን ደንታቸው ከሆኑ አካላት ጋር አበሳን እንጂ መልካም ነገርን ስለማናጭድ ከጉያችን ፈልቅቀን ብቻቸውን ይቆማሉ። ምክር ካልመለሳቸው መከራውን ፈልገዋልና በሚገባቸው መንገድ እንዲጓዙ እንተዋቸዋለን።
ክቡራትና ክቡራን፥
የሐሳብ ልዩነት ጌጥ እንጂ እርግማን አይደለም። የተሰማንን መግለጽና ጥያቄዎቻችንን ያለ ስጋት ማንሳት እስካዛሬ የታገልንለት ወሳኙ መብታችን ነው። የዚያኑ ያህል በሀገራችን ነገሮች በሥርዓት እንዲከናወኑ፣ የአንዱ ጥቅም የሌሎችን መብት እንዳይጋፋ እና ዜጎች ሰላምና ደኅንነታቸው ተጠብቆላቸው በሀገራችን እንዲኖሩ ማስቻል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት ነው። ኃይል እስካልተቀላቀለበት ድረስ የሐሳብ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ለዘመናት የታገንለትን መብት ከማጎናጸፍ ባለፈ የሌሎች ዜጎችን ሰላምና ደኅንነት እንዲጠበቅ ያደርጋል። ሐሳብ የሚሞገተውም የሚሸነፈውም በሌላ ሐሳብ እንጂ በጉልበት፣ በነውጥና በአመጽ አይሸነፍም፤ ተሸንፎም አያውቅም። መነጋገር፣ መከራከርና መወያየት እንጂ መጠፋፋት ሥልጣኔን አምጥቶ እንደማያውቅ ማገናዘቢያ አዕምሮ ያለው ሰው ሁሉ በቀላሉ የሚረዳው ሐቅ ነው። ወገኖቼ፣ ሌላው መታወቅ ያለበት ጉዳይ የምንገኝበት ወቅት ብዙ ጊዜ የማይሰጡ ፈተናዎች ከፊታችን የተደቀኑበትና ወሳኝ ድሎችን የምናሳካበት ወቅት እንሆነ ሊረሳ አይገባም። የግብርና ሥራችን ሳይስተጓጎል መከናወን አለበት። ምርታማነትን በመጨመር ከውጭ የምናስመጣውን የምግብ እህል ጭምር ሊተካ በሚቻልበት አኳኋን ሥራችንን መቀጠል ይኖርብናል። ከገጠር ግብርናችን በተጨማሪ የከተማ ግብርና ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ። አምራች ኢንዱስትሪው የኮሮና ወረርሽኝን ሁለንተናዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ ምርቶችን ለማምረት ሌት ተቀን መድከም አለበት። ከዚሁ ጎን ለጎን እየተባባሰ የመጣውን የኮሮና ወረርሽኝ ተቋቁመን ለመዝለቅ የጥንቃቄ፣ የምርመራና የሕክምና ተግባሮቻችንን ሳንዘናጋ እንፈጽማለን። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታችንን እያጠናቀቅን በዕቅዱ መሠረት የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት ሥራችንን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እናከናውናለን። በዚህ ክረምት ለመትከል ያቀድነው የአምስት ቢሊዮን ችግኞች “የአረንጓዴ አሻራ” መርሐ ግብርም ጥንቃቄ ባልተለየው መልኩ ተግባራዊ እናደርጋለን።
ምንም እንኳን ዛሬ የደረሰብን ፈተና ቢያሳምመንም የምንሠራው ለሀገር ነውና የነገውን ማየት አለብን። ሕዝብና ሀገር ይቀጥላሉ። ትውልድ ይቀጥላል። የተሻለ ትውልድ ፈጥረን የተሻለች ሀገር ማስረከብ ደግሞ ከእኛ የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው። ነገሮች ወደ በጎ እልህና ቁጭት እንጂ ወደ መጥፎ ቁዘማና ትካዜ ሊወስዱን አይገባም። ችግሮች ትምህርት እንጂ እሥር ቤት ሊሆኑብን አይገባም። ሕዝብ መሥራት ያለበትን በአግባቡ ከሠራ፤ መንግሥትም ያለበትን ኃላፊነት በብቃት ይወጣል። ከከባድ ክረምት ማዶ መልካም አዲስ ዘመን ቆሞ እንደሚጠብቀን ሁሉ የሌሊቱን ግርማ የሚያሸንፍና ጽልመቱን የሚደመስስ የብርሃን ጸዳል ማልዶ ወደኛ እንደሚገሠግሥ ሁላችንም እናውቃለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም.July 19, 2020 at 1:49 am #15118AnonymousInactiveበኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር እና ድሬ ዳዋ ከተሞች በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. የተፈጸመውን ፍጅት ለመጣራት መረጃ ለመሰብሰብ የተላለፈ ጥሪ
ሰላም ኢትዮጵያውያን ወገኖች፥
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመሠረተው የኢትዮጵያውያን ለሰላም፣ ለፍትህና፣ ለአንድነት ኔትወርክ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የሕግ ባለሞያዎች ቡድን የራሱን መግለጫ እንደሚያወጣ በገለጸው መሠረት፥ የሕግ ባለሞያዎች የሚገኙበት ቡድን በኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር እና ድሬ ዳዋ ከተሞች በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. የተፈጸመውን ፍጅት ለመጣራት መረጃ ለመሰብሰብ የተላለፈ ጥሪ እቅርቧል። ይህን ጥሪ ሀገር ቤት ለሚገኙ ወገኖች በማስተላለፍ ሁሉም ዜጎች እንዲተባበሩ ጥሪውን ያስተላልፋል።
በኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር እና ድሬ ዳዋ ከተሞች በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. የተፈጸመውን ፍጅት
ለመጣራት መረጃ ለመሰብሰብ የተላለፈ ጥሪበሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. የተፈጸመውን የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር እና ድሬ ዳዋ ከተሞች ሰፊ ተቃውሞ መቀስቀሱ ይታወሳል። እነዚህ ተቃውሞዎች በአብዛኛው በታዋቂው የባህልና የፖለቲካ ትግል ፋና ወጊ በነበረው ሃጫሉ ግድያ የሕብረተሰቡን ድንጋጤ ያንጸባረቁና ሰላማዊ ነበሩ። ሆኖም በተወሰኑ አካባቢዎች፣ የተወሰኑ ቡድኖች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የኃይል እርምጃ ወስደዋል። በዚህ እርምጃም የተወሰኑ የብሔርና የሃይማኖት ቡድን አባላት እና ጎረቤቶቻቸውን ለማዳን የተንቀሳቀሱ ንጹሃን የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሕይወት መጥፋት፣ አካል መጉደልና ንብረት ውድመት ደርሷል። የተለያዩ የዜና ማስራጫ ዘገባዎች እንድሚያስረዱት የኃይል እርምጃው በድንገት በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ የተፈጸሙ እርምጃዎች አለመሆናቸውን ነው። ጥቃቶቹ በመረጃ፣ በሰው ኃይልና በገንዘብ በቂ ዝግጅት ተደርጎባቸው በእቅድ፣ በመዋቅርና በሰፊው በኦሮሚያ ክልል ነዋሪ በሆኑ የተወሰኑ የብሔርና የሃይማኖት ቡድኖች አባላት ላይ ያነጣጠሩ ይመስላሉ። የእነዚህ ጥቃቶች እጅግ አሳሳቢ የሚያደርጋቸው ነገር ውሰጥ አንዱ በመንግሥት የጸጥታ ኃይልና አስተዳደራዊ መዋቅር ድጋፍ የተፈጸሙ መሆናቸው ነው።
ስለሆነም የእነዚህ ጥቃቶች ሁኔታና ያደረሱት የጉዳት ዓይነትና መጠን እውነቱ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው። እንደዚህ ያለ ፍጅት እንዳይደገም እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። በዚህ ድርጊት የተሳተፈ ወይም ድርጊቱ እንዲፈጸም ያደራጀ፣ የቀሰቀሰ፣ በገንዘብ የደገፈ ማንኛውም ሰው ተጠያቂ መሆን ይኖርበታል። በወንጀሎቹ ጉዳት ደረሰባቸውን ወገኖች የፍትሕ ጥያቄ በከንቱ እንዳይቀር ወንጀለኞቹን ተጠያቂ ማድረግ፤ እንዲሁም ተጎጂዎቹን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊ ነው።
እውነትን የማግኝትና ፍትሕን የማረጋገጥ ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም። እነዚህን አሰቃቂ ወንጀሎችን የመመርመርና የመሰነድ ሥራ ሙያዊና ተዓማኝነት ባለው መለኩ መከናወን አስፈላጊነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም።
እነዚህን ጉዳዮች ከግምት በማስገባት፥ በሰሜን አሜሪካ በጥብቅና (ሕግ) ሙያ በተሰማሩ ባለሙያዎች የሚመራ የበጎ ፋቃደኞች ቡድን የሰኔውን ጥፋቶች (ፍጅት) በሚመለከት መረጃ በማሰባሰብ የተሟላ ሪፖርት ለማዘጋጀት ተቋቁሟል። ይህ ሪፖርት ለወንጀሎቹ ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች፣ ቡድኖች ተቋማት ከፍትህ እንዳያመልጡ ለሚደረገው ጥረት ይረዳል።
የዚህ ቡድን አባላት ከማንኛውም ድርጅት ጋር ንክኪ ያለን አለመሆኑን እየገለጽን፥ የዓላማችን ደጋፊ ከሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት ድጋፍ ለመቀበል ግን ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።
በዚህም መሠረት፥ ማንኛውም ወንጀሎቹን በቀጥታ የተመለከተ ወይም ስለወንጀሎቹ አስተማማኝ መረጃ ያለው ሰው ምስክርነት እንድትሰጠን(ጭን) ወይም የሰነድ ወይም የኦዶቪዡዋል ማስረጃዎችን እንድትልክልን(ኪልን) ጥሪ እናቀርባለን። ምስክርነት የሚሰጠን ወይም ሌሎች ዓይነት ማስረጃዎችን የሚሰጠን ሰው ራሱ(ሷ) ተጎጂ የሆነ(ች) ወይም የተጎጂው(ዋ) የቤተሰብ አባል፣ ዘመድ፣ ጓዳኛ፣ ጎረቤት ወይም መንደርተኛ የሆነ(ች) መሆን አለበት(ባት)። የምስክሮችን ማንነት በሚስጥር የሚያዝ ሆኖ፥ በሪፖርቱ ላይ ሊጠቀስ የሚችለው በግልጽ በተሰጠ የምስክሩ ፈቃድ ብቻ ይሆናል።
ምስክርነት ለመሰጠት በቡድናችን የኢሜል አድራሻ forallethiopia@gmail.com ያሳውቁን። ከቡድናችን አንዱ አባል በስልክ ወይም እርስዎ በሚመርጡት የመገናኛ መንገድ ግንኙነት በማድረግ የምስክርነት ቃልዎን እንቀበላለን።
በተጨማሪም የፎቶና የቪዲዮ ማስረጃዎችንም በኢሜል አድራሻችን forallethiopia@gmail.com የምንቀበል መሆኑን እንገልጻለን። ማንኛውም የምንሰበስበው ማስረጃ እውነተኝነትና አስተማማኝነትን የምናጣራ መሆናችንን እንገልጻለን።
ይህንን መልዕክት በእንግሊዝኛ ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ።
በኦሮሚያ ክልልና አዲስ አበባ ከተማ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. የተፈጸመውን ፍጅትን የሚያጣራ – በሰሜን አሜሪካ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን
ሐምሌ 11 ቀን፥ 2012 ዓ.ም.[caption id="attachment_15116" align="aligncenter" width="600"] Call for evidence regarding June/July 2020 massacre in Oromia, Addis Ababa, Harar and Dire Dawa[/caption]
July 27, 2020 at 2:59 am #15206AnonymousInactiveበሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ የተሰጠ መግለጫ ― በድር ኢትዮጵያ
ለረጅም ዘመናት በታሪክ እንደምንረዳዉ በኢትዮጵያ ሕብረተሰቡ በጥሩ ማኅበራዊ ሁኔታ በመቀራረብ፣ በመተሳሰብ፣ በመቻቻል እና በመሳሰሉ ሁኔታዎች ተሳስሮ በጋራ ይኖር እንደነበር በሰፊዉ ሲተረክ ይታወሳል። ይኸዉ ማኅበራዊ ኑሮአቸዉንም ሀይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ አካባቢና መሰል ጉዳዮች ሳይገድባቸዉ ሕዝቦች አንድነታቸዉን ጠብቀዉ ኖረዋል፤ ምንም እንኳን በነበሩ መንግሥታት በኩል ይደረጉ የነበሩ ልዩነቶች፣ ጫናዎች፣ ጭቆናዎች እንደተጠበቁ ሆነዉ ማለታችን ነዉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የተለያዩ የልዩነት ክስተቶች ቢንጸባረቁም ሕዝቡ ግን ችግሮቹን ወደ ጎን በማድረግ ከሀይማኖት ዉጭ እንዲሆኑ ትግል ሲያደርግ ቢቆይም፥ በአሁኑ ወቅት ግን ይዘቱን ቀይሮ የመጣዉ ለችግሮች ሁሉ መነሻዉ ሀይማኖት እንደሆነ የሚዘምሩ አካላት እየተበራከቱ ይገኛል።
የታዋቂዉ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በግፍ መገደልን ተከትሎ በሀገሪቱ በተከሰተዉ አለመግባባትና ብጥብጥ የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ህይወት እጅግ አሰቃቂ በሆነ መልኩ አልፏል። ለሟቾች ነብስ ይማር እያልን ለቤተሰቦቻቸዉና ለመላዉ ኢትዮጵያዉያን መጽናናትን እንመኛለን። በሌላ መልኩ ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉ ንጹሀን ዜጎች እንዲሁም የወደመዉ የሀገር ንብረት ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር የጉዳዩ አስከፊነት ስፋቱን ይጠቁማል።
መንግሥት ባለበት ሀገር እንደዚህ አይነት ልቅ የሆነ ሥርዓተ-አልበኝነት ሲፈጠር መንግሥት አለን? ያስብላል። መንግሥት ሆይ የታሰሩ አካላት ፈጣን ፍትህ እንዲያገኙና መፈታት ያለባቸዉ አካላትም ያለምንም መጉላላት በሕግ የበላይነት መፍትሄ ሊቸራቸዉ ይገባልም እያልን፥ በሌላ መልኩም የጥላቻ ንግግር የሚያስተጋቡ አካላትን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የማስቆም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አደራ እንላለን።
ችግሩ የተከሰተበትን መንስኤ በማጥናት መፍትሄ መሻት ሲገባ፥ አንዳንድ የግል ዓላማ ያላቸውና እስላም-ጠል የሆኑ ጽንፈኛ አካላት የጉዳዩን አቅጣጫ ለማስቀየር የተለያዩ የዜና ማሰራጫ ዘዴዎችን በመጠቀም ጸረ-ሰላም ብሎም ጸረ-ኢስላም የሆነ ፕሮፓጋንዳቸዉን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ። በእምነት ተቃርኖ የማያዉቀዉ የሀገራችን አማኞች በእምነታቸዉ ከተመጣባቸዉ ሁሌም ቢሆን ወደ ኋላ የማይሉ እንደሆነ ስለሚያዉቁ በሌሎች ነገሮች ሁሉ ሞክረዉ አልሳካ ቢላቸዉ መጨረሻ ላይ ሕዝቡን በእምነት ለማጋጨት ሌት ተቀን እየዳከሩ ይገኛሉ።
በድር ኢትዮጵያ የማንኛዉም ቤተ-እምነት ወይም ተቋም ሲደፈር በጽኑ ተቃዉሞዉን ያሰማል። የእምነት ተቋማት ሊከበሩ ስለሚገባም ጭምር ነዉ። አንዱ ተቋም ከአንዱ አይበልጥም፤ የትኛዉም ተቋም ከማንኛዉም አያንስም፤ በእምነት ተቋምነታቸዉ ሁሉም እኩል ናቸዉ። ይህንን መገንዘብ የተሳናቸዉ የጽንፍ አራማጆች ግን በእምነቶች መካከል ጣልቃ በመግባት እኔ አዉቅልሀለሁ አባዜያቸዉን በመንዛት ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ለማሸማቀቅ በሚያስችል ደረጃ የችግሩ አካል ለማድረግ ብዙ ለፍተዋል፤ ሆኖም ግን አይሳካላቸዉም። ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የማንም አካል ተቀጥላ ሆኖም አያዉቅም፤ መብቱን ለማስከበር ደግሞ ማንም ሊነግረዉ አይችልም፤ በቂ ተሞክሮም አለዉ።
በሀገሪቱ የመጣዉን አንጻራዊ ለዉጥ ያልተዋጠላቸዉ ለዉጡን ለመቀልበስና ዳግም ላይመለስ ያከተመዉን የአጼዎችን ስርዓት ለማንገስ ለሚድሁ ያለን ምክረ-ሀሳብ ሀገራችን በተያያዘችዉ የለዉጥ ጎዳና የሚያራምዳት እንጂ ለነዉጥ የሚዳርጋትን ስለማትሻ ከእኩይ ተግባራችሁ እንድትቆጠቡ እያልን የሰላም ሰባኪ በመምሰል በሕዝቡ መካከል አሉባልታ የሚነዙና ጽንፈኝነትን የሚያራምዱ አካላት ከሚያስቡት ባልታሰበ መልኩ በተቃራኒዉ ብዙ አላስፈላጊ ዋጋ ሊያስከፍላቸዉ ይችላልና ለሀገሪቱ ሉዓላዊነት ለሕዝቦቿ አንድነት እንዲሁም ለሰላም ሲባል ቆም ብላችሁ እንድታስቡ መልካም መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን።
በአማራ ክልል በሞጣ የሚገኙ አራት መስጂዶችን አቃጥሎ የሙስሊም ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በመለየት በማዉደምና ንብረታቸዉን በመዝረፍ እሳት እየሞቁ ይጨፍሩ የነበሩትን የሥነ ምግባር ሞራል የጎደላቸዉን ኢስላም-ጠል ጽንፈኞችን ለመገሰጽ እንኳ የሞራል ብቃት ያጡ አካላት አሁን በሀገሪቱ በተከሰተዉ ብጥብጥ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሞተበትና ንብረቱ የወደመበት ሆኖ ሳለ የግል ድብቅ አጀንዳቸዉን ለማሳካት በበሬ ወለደ ትርክታቸዉ የእምነት ጥቃት አድርጎ ክፍፍልን መዝራት ፍጹም ተቀባይነት የሌለዉ እኩይ ተግባር ነዉ።
ስለዚህ እየተካሄደ ያለዉ አላስፈላጊ ቅስቀሳ ሕዝቡን ከማበጣበጥ፣ ሀገር ከማፈራረስ እና በሕዝቦች መካከል ሊፈታ የማይችል ጠባሳ ከማኖር ውጭ እንደ ሀገር እና ሕዝብ የማያስተሳስር ለሰላምና ፍትህ ያልቆመ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እንደ እምነትም ቢሆን በየትኛዉም የእምነት አስተምህሮት የማይደገፍ አጸያፊ ተግባር መሆኑን በመረዳት ሁሉም ሊገነዘበዉ የሚገባና ማንኛዉም አካል ከዚህ መሰል ሂደት ጥፋትን እንጂ ትርፋማነትን ማሰብ እንደማይገባ በቅጡ መገንዘብ ያሻል።
በመጨረሻም ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ የምናስተላልፈዉ መልእክት ኢስላም ሰላም እንደመሆኑ መጠን፥ ለሰላም መከፈል የሚገባዉ ዋጋም እንደተጠበቀ ሆኖ፥ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠናክሮ መገኘት እና በጽንፈኞች ለሚሰነዘሩብን የዉሸት ፕሮፓጋንዳ ለኛ አዲስ ባለመሆኑ ትኩረት ባለመስጠት የሚቃጣብንን በጥበብ፣ በሰከነ መንፈስ እንደ ሀገር በማሰብ የመመከት ኃይል ማዳበር ለሰላም ዘብ መቆም ግድ ይላል እንላለን።
ሀገራችንን ፈጣሪ አላህ (ሱ.ወ) በሰላም ይጠብቅልን።
በድር ኢትዮጵያ
ሰሜን አሜሪካ
24 ጁላይ 2020August 17, 2020 at 2:01 pm #15452AnonymousInactiveበእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የቀዳሚ ምርመራ ሂደት በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግበዛሬው ዕለት (ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም.) አቶ ጃዋር መሃመድ ጨምሮ ስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ የዐቃቤ ሕግ የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት የተያዘው ቀጠሮ አቶ ጃዋር መሐመድ አሞኛል በማለታቸው ተስተጓጉላል። ከዚህም የተነሳ ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹን የመስማት ሂደቱን ለማካሄድ ለሦስተኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በዚህ አጋጣሚ ለሕዝብ እና ጉዳዩን ለሚከታተሉ ሁሉ ግልጽ ለማድረግ የምንፈልገው፥ እነ አቶ ጃዋር መሃመድ በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ስር እንደመሆናቸው፥ ጤናቸውን ለመጠበቅ ባለው አሠራር አስፈላጊውን የጤና ክትትል እና አገልግሎት የሚያገኙ እና እያገኙ ያሉ ሲሆን ጤናቸውም በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል።
ለዚህም ማሳያ ከተደረገላቸው የሕክምና በተጨማሪ ዛሬ (ነሐሴ 11) በዋለው ችሎት ምስክር መሰማት እንዳይጀምር የተለያዩ ምክንያቶችን እያነሱ ለረጀም ሰዓት ሲከራከሩ ከቆዩ በኃላ በክርክሩ ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቶ ምስክር መሰሚያ ሰዓት ሲደርስ ወጣ ገባ ማለታቸው የሚፈለገው የምስክሮችን የማሰማት ሂደቱን ለማስተጓጎል እና በግብረ አበሮቻቸው ሁከት እና አመጽ ለመቀስቀስ ነው።
የተጠርጣሪው ግብረ አበሮች በተለያየ መንገድ ምስክሮችን በማስፈራራት የፍትህ ሂደቱ እንዲስተጓጎል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑም ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ፍጹም አግባብነት በሌላቸው መነሻዎች እና በተለያየ ሰበቦች ምስክሮች በቀዳሚ ምርመራ የሚሰሙበተ ሂደት እንዲራዘም እና እንዲሰናከል ለማድረግ ጥረት እያደረጉ በመሆኑ እንደ ወትሮም ሁሉ ተቋማችን ለምስክሮች ተገቢውን የሕግ ጥበቃና ከለላ የሚያደረግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንፈልጋለን።
ከምንም በላይ በተለያዩ ጥቃቅን ጉዳዮች አላግባብ ከሚቀርቡ አቤቱታ እና ይግባኞች ጀምሮ፣ አልተዘጋጀንም ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን፣ ዳኛው ፌገግ ብሏል እና ይቀየርልን በማለት በሰበብ አስባቡ የፍርድ ሂደቱን ለማደናቀፍ በተጠርጣሪዎቹ በኩል የሚደረግ ጥረት እንዳለ ግልጽ ሆኗል። ይህን እውነታ ሕዝቡም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት እንዲገነዘቡ እና በአፋጣኝ ፍትህ እንዲረጋገጥ ከምናደርገው ጥረት ጎን እንዲሰለፉ ጥሪያችንን እያቀረብን፥ ማንም ይሁን ማን ከሕግ በላይ መሆን የማይቻል መሆኑን በአጽንኦትት ለመግለጽ እንወዳለን።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባተያያዥ ዜናዎች
August 26, 2020 at 11:33 pm #15591AnonymousInactiveበስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።
የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ እና ግድያውን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ ዞኖች
ተቀነባብረው በተፈጸሙ ጥቃቶች የተጎዱ ኦርቶዶክሳውያንን መርዳትንና መልሶ ማቋቋምን አስመልክቶ
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ“አማን አማን እብለክሙ ከመ ትበክዩ ወትላህዉ አንትሙ፤ ወዓለምሰ ይትፌሣሕ፤ ወአንትሙሰ ተኃዝኑ፤ ወኃዘንክሙ ፍሥሐ ይከውነክሙ = እውነት እውነት እላችኋለኹ፤ እናንተ ታለቅሳላችኹ፤ ሙሾም ታወጣላችኹ፤ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችኹ፤ ነገር ግን ኃዘናችኹ ወደ ደስታ ይለወጣል።” (ዮሐ.16፥20) ሃጫሉ ሁንዴሳ ስመ ጥምቀቱ ኃይለ ገብርኤል፣ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በአዲስ አበባ መገደሉ ይታወሳል። ቤተ ክርስቲያን፥ በዚያ ድንገተኛ የልጇ ግድያ ከባድ ኃዘን ተሰምቷታል። ኾኖም፣ በግድያው የተሰማትን ኃዘን ለመወጣት ጊዜ ሳይሰጣት፣ ኃዘንተኛነቷ ተረስቶ እና እንደ ጠላት ተቆጥራ፣ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በክርስቲያን ልጆቿ ላይ ዘግናኝ ፍጅት እና መከራ ተፈጸመባቸው።
በኦርቶዶክሳዊነታቸው ብቻ በአሠቃቂ መልኩ በገጀራ ተቀሉ፤ በቆንጨራ ተቆራረጡ፤ በጦር ተወግተው በጩቤ ተዘከዘኩ፤ በሜንጫ ተተለተሉ፤ በዱላ ተቀጥቅጠው እና በደንጊያ ተወግረው ተገደሉ፤ አስከሬናቸው በጎዳና እየተጎተተ ሲንገላታ ዋለ፤ ለቀናት በየቦታው ወድቆ የቆየው የሰውነት ክፍላቸው ለከርሠ አራዊት ሲሳይ ኾነ፤ ሴቶች፥ በልጆቻቸው፣ በአባቶቻቸው እና በባሎቻቸው ፊት ተደፈሩ፤ ለዘመናት የደከሙበት ቤት ንብረታቸው፣ በጥናት እና በጥቆማ እየተለየ ከተዘረፈ በኋላ ቀሪው ጋዝ እየተርከፈከፈበት በእሳት እየጋየ ወደመ፤ ብዙዎች ከሞቀ ቀዬአቸው ተፈናቅለው የክረምቱን ጨለማ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን በሚገኙ መቃብር ቤቶች እና አዳራሾች፣ በልዩ ልዩ መንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም፣ በግሰለቦች ቤቶች ተጠልለው ለማሳለፍ ተገደዱ፤ ለአስከፊ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቡናዊ ቀውሶች ተዳረጉ።
ቤተ ክርስቲያናችን፣ ይህንኑ የተቀነባበረ ጥቃት እንደሰማች፣ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በቋሚ ሲኖዶስ የሐዘን መግለጫ አውጥታለች፤ በአገር ውስጥ እና በውጭ በሐዘንና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ስታመለክት ከርማለች፤ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም፥ “አጥፊዎችን አንታገሥም፤ ተገቢውን ፍትሕ እንሰጣለን፤ የተጎዱትን እንክሳለን፤” ብለው ቃል የገቡትን ይፈጽሙ እንደ ኾነ በማለት በትዕግሥት ጠብቃ ነበር። ኾኖም፣ ዜጎችን ከጥቃት አስቀድሞ የመከላከል እና የመጠበቅ፣ ፍትሕን የማስፈንና ተጎጂዎችን በአግባቡ የመካስ ሓላፊነታቸውን በወቅቱ እና በብቃት ሲወጡ አላየችም።
በጉዳዩ ላይ የተወያየው ቋሚ ሲኖዶስም፣ በየሥፍራው በአካል ተገኝቶ የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ዐቢይ ኮሚቴ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እንዲቋቋም መመሪያ ሰጥቷል። በዚኽም መሠረት ዐቢይ ኮሚቴው፣ ተጎጂዎችን፥ በጊዜያዊነት ለመርዳት እና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ንኡሳን ኮሚቴዎችን አደራጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል።
ዐቢይ ኮሚቴው ባወጣው መርሐ ግብር፣ የሥራው መጀመሪያ ያደረገው፣ ጥቃቱ የተፈጸመባቸውን አካባቢዎች በዝርዝር በመለየት፣ ተጎጅዎችን የማጽናናት እና መረጃ የማሰባሰብ ጉዞ ማካሔድ ነበር። ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ መንፈሳውያን ማኅበራትንና በርካታ የብዙኃን መገናኛዎችን ጨምሮ 260 ያኽል ልኡካን የተሳተፉበት ይኸው ጉዞ፣ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች ውስጥ በስድስት አህጉረ ስብከት የሚገኙ 25 ወረዳዎችን የሸፈነ ነበር።
የዐቢይ ኮሚቴው ልኡካን፣ ተጎጂዎችንና በማነጋገር እና ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች በመጎብኘት ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ የልጃችን የኃይለ ገብርኤልን ግድያ ተከትሎ፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ የመንግሥትን መዋቅር ተገን ያደረጉ የእምነት እና የብሔር ጽንፈኞች አስቀድመው ከተደራጁ ኀይሎች ጋራ በመቀናጀት የፈጸሙት ስልታዊ እና አረመኔያዊ ጥቃት ዋና ዒላማ፣ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን እንደነበሩ ተረጋግጧል።
ከሰኔ 22 ቀን ምሽት ጀምሮ እስከ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ሦስት ተከታታይ ቀናት በተፈጸመው በዚያ ጥቃት፥ ከ67 በላይ ምእመናን በግፍ እና በአሠቃቂ ኹኔታ ተገድለዋል፤ 38 ምእመናን ቋሚ(ከባድ)፣ 29 ምእመናን ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከሰባት ሺሕ በላይ ምእመናን ከመኖሪያቸው ከመፈናቀላቸው ባሻገር፣ በተለያየ ደረጃ ለሚገለጽ ሥነ ልቡናዊ እና ሥነ አእምሯዊ ቀውስ ተዳርገዋል፤ ከአምስት ቢልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረታቸውንም በዘረፋ እና በቃጠሎ ማጣታቸውን፣ ከዐቢይ ኮሚቴው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
የጥቃቱን አስከፊነት በዚኽ መልኩ የተረዳው ዐቢይ ኮሚቴው፣ ተጎጅዎችን በአፋጣኝ ባሉበት ለመርዳት እና በዘላቂነት ለማቋቋም ይቻል ዘንድ፣ አደረጃጀቱን በዐዲስ መልክ በማጠናከር ተልእኮውን በአጭር ጊዜ ለማከናወን የሚያስችለውን ስልት ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የጉዳቱን መጠን በነፍስ ወከፍ ደረጃ የመለየት ሥራ እየሠራ ሲኾን፣ በዚኽም መነሻነት፣ ርዳታው በቀጥታ ለተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዲደርስ ይደረጋል፤ በዘላቂነት ለማቋቋምም ኹኔታዎችን ያመቻቻል።
ዐቢይ ኮሚቴው፣ በጉዳት ጥናት መረጃው መሠረት፣ ጊዜያዊ ርዳታን ከማድረስ እና ከመልሶ ማቋቋም ባሻገር፣ መንግሥት በአስቸኳይ ሊፈጽማቸው የሚገቡ ተግባራት አሉ ብሎ ያምናል፤ እነዚኽም፤
- ተጎጅዎች በሃይማኖታቸው በደረሰባቸው ስልታዊ እና ዘግናኝ ጥቃት የተነሣ፣ በከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ላይ እንደሚገኙ በቀረበው ሪፖርት እና ማስረጃ አረጋግጠናል። በወቅቱ ያሉበት ኹኔታ፣ ለኮሮና ቫይረስ እና ለሌሎችም ተላላፊ በሽታዎች የሚያጋልጣቸው እንደኾነ ለመታዘብ ተችሏል። በመኾኑም፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የፌዴራል መንግሥት፣ የኦርቶዶክሳውያን ኢትዮጵያውያንን በሕይወት የመኖር እና ሀብት የማፍራት ሰብዓዊ እና ዜግነታዊ መብቶችን በማስከበር፣ የደኅንነት እና የኑሮ ዋስትና በአፋጣኝ እንዲያረጋግጥላቸው ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች።
- መንግሥት፥ ጥቃቱን ያቀዱትን፣ የፈጸሙትንና ያስተባበሩትን ኀይሎች እንዲሁም፣ የተጣለባቸውን ሓላፊነት ወደ ጎን በማለት ጥቃቱን በዝምታ የተመለከቱትን በመዋቅሩ ውስጥ ያሉትን ሹማምንት እና የጸጥታ አካላት የኾኑ አጥፊዎችን፣ በቁጥጥር ሥር በማዋል እና በሕግ ተጠያቂ በማድረግ ፍትሕ ርትዕ እስከ መጨረሻው እንዲያሰፍን ታሳስባለች። በዚኽ ረገድ፣ መንግሥት፣ ከጥቃቱም በኋላ ቢኾን፣ ሕግን ለማስከበር እያደረገ ያለውን ጥረት፣ ቤተ ክርስቲያን በቅርበት የምትከታተለውና የምታደንቀውም ነው፤ ለውጤታማነቱም፣ ማናቸውንም የበኩሏን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾኗን ትገልጻለች።
- በአሳዛኝ ኹኔታ በደል እና ግፍ የተፈጸመባቸው ኾነው እያለ፣ በጥቃቱ ምንም ሱታፌ የሌላቸው ንጹሐን ዜጎች፣ በኦርቶዶክሳዊነታቸው ብቻ ታስረው እየተንገላቱ በመኾኑ፣ ጉዳያቸው በጥንቃቄ ታይቶ ከእስር እንዲፈቱ ታሳስባለች።
- አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የፖሊቲካ ፓርቲዎች፥ የግፉዓን ሰማዕታቱን መጠቃት፣ አላግባብ ለቡድናዊ እና ፖሊቲካዊ ትርፍ በመጠቀም በሐዘናችን ከመሣለቅ እንዲቆጠቡ፤ መንግሥትም፣ ተገቢውን ክትትል በማድረግ እንዲያስታግሥ ቤተ ክርስቲያን አበክራ ታሳስባለች።
- ከወርኀ ሰኔው ጥቃት በፊትም ኾነ በኋላ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎችም ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ በተደጋጋሚ እየደረሱ የሚገኙ ስልታዊ የኾኑ ግልጽ ተጽዕኖዎች እና ጥቃቶች፣ በዐይነት እና በመጠን እየጨመሩ መጥተዋል። አብዛኞቹ የክልል መንግሥታት፣ ለውይይት ባሳዩት በጎ ፈቃድ፣ ጥቃቱንና ተጽዕኖውን በተወሰነ ደረጃ ለመግታት ቢቻልም፣ በተለይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የወቅቱ አስተዳደር ግን፣ የቀረበለትን በጋራ ችግሮችን የመፍታት ጥያቄ ችላ በማለት እና ባለመቀበል ቤተ ክርስቲያናችንን በተደጋጋሚ አሳዝኗታል። በክልሉ የተወሰኑ አህጉረ ስብከት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያገደው ሕገ ወጥ ቡድን፣ ለቤተ ክርስቲያን በሕግ የተሰጧትን መብቶች ከመጋፋት ጀምሮ የአስተዳደር መዋቅሯን እስከ ማፍረስ የተዳፈረው፣ ክልላዊ መንግሥቱ ለቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠት በሚያሳየው ቸልተኝነት እንደ ኾነ ለመረዳት አያዳግትም። በመኾኑም፣ የትላንቱን ችግር ለማከም፣ ይልቁንም ነገ በከፋ መልኩ ሊመጣ ያለውን ለማስቀረት እንዲቻል፣ በጋራ ከመሥራት ውጪ መፍትሔ የለም፤ ብለን እናምናለን። ስለዚህ ክልላዊ መንግሥቱ፣ ጥያቄያችንን ተቀብሎ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ እንዲኾን ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች።
- በ2012 ዓ.ም. መባቻ፣ በአንድ ቀን 97 ዜጎች እና ምእመናን ካለቁበት የወርኀ ጥቅምቱ ጥቃት እንዲሁም የወርኀ ጥር የበዓለ ጥምቀት አከባበር ወቅት ከተፈጸሙ ግድያዎች እና ዘረፋዎች ጀምሮ፣ በልዩ ልዩ የአገራችን አካባቢዎች፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየደረሱ ያሉ ግፎችንና በደሎችን መንግሥት አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብ፣ ውጤቱንም በይፋ ለሕዝብ እንዲገልጽ ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ትጠይቃለች።
- ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፣ ለአገር ሰላም እና ለሕዝብ አንድነት ባበረከተችው አስተዋፅኦ፣ በገነባችው የተቀደሰ ባህል እና ባወረሰችው ዘርፈ ብዙ እሴት፣ በኢትዮጵያውያን ኹሉ ልትከበር እና ልትወደድ የሚገባት ናት። ከሞላው ጸጋዋ እና በረከቷ ያልተቋደሰ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ተብሎ የማይገመት በመኾኑ፣ የኹሉ እናት እና ባለውለታ ናት ብለን እናምናለን።
ኾኖም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሱ ያሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ አብዝቶ እንደሚነገረው፣ “በሽግግር ወቅት የሚያጋጥሙ” ተብለው ብቻ የሚታለፉ ሳይኾኑ፣ የተሳሳቱ ርእዮተ ዓለማዊ ትርክቶችንና ጂኦ-ፖለቲካዊ ዳራዎችን መነሻ በማድረግ በተቀነባበረ እና በተደራጀ ስልት የሚፈጸሙ ኦርቶዶክሳውያንን የ‘ማጽዳት’ እንቅስቃሴዎች እንደኾኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየኾነ መምጣቱን ቤተ ክርስቲያናችን ትገነዘባለች፤ በአጭር ጊዜ ሳይታረም በዚኹ ከቀጠለም፣ የከፋ ፍጻሜ ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ ታስገነዝባለች።
ስለዚህም፣ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት፥ በእኒህ ስሑት አስተሳሰቦች እና ሐሳዊ ትርክቶች ማሕቀፍ፣ ኾነ ተብሎ የሚፈጸም ኦርቶዶክሳውያንን የማሣቀቅ እና የማዳከም ሃይማኖት ተኮር ጥቃትን አስቀድሞ በመከላከል፣ ፍትሕን በማስፈን፣ ተጎጂዎችን በአግባቡ በመካስ እና በማቋቋም፣ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በአጽንዖት ታሳስባለች።
የተወደዳችኹ ተጎጂ ምእመናንና ምእመናት የመንፈስ ልጆቻችን፤
የግፍ ጥቃቱ የደረሰባችኹና በአሁኑ ወቅት በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን አዳራሾች እና በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ተጠልላችኹ እንደምትገኙ ይታወቃል። ይህ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችኹ የተቀበላችኹት መከራ፣ በቤተ ክርስቲያናችን የሰማዕታት መዝገብ በወርቅ ቀለም ተጽፎ የሚኖር ነው። በግፈኞች ፊት ለማዕተበ ክርስትናችኹ ታምናችኹ ባሳያችኹት ጽናት እና በከፈላችኹት መሥዋዕት፣ የአገራችኹን ህልውና እና አንድነት ታድጋችኋል፤ የቤተ ክርስቲያናችኹን ልዕልና አስመሰክራችኋል። ይኸውም፣ ለትውልድ አብነት ኾኖ በምሳሌነት ሲነገር የሚኖር በመኾኑ፣ እናት ቤተ ክርስቲያናችኹ ኮርታባችኋለች። ለወደፊትም፣ መላው ኢትዮጵያውያንና ኦርቶዶክሳውያን፣ በሚያስፈልጋችኹ ኹሉ ከጎናችኹ ይቆማሉ፤ ብቻችኹን እንዳልኾናችኹም ቤተ ክርስቲያን ታረጋግጥላችኋለች። ዛሬ ባገኛችኹ መከራ ግፍ አድራሾች ቢደሰቱም፣ በጊዜው ጊዜ ፍትሕን በሕግ ተጎናጽፋችኹ እንባችኹ እንደሚታበስ እና ኃዘናችኹ ወደ ደስታ እንደሚለወጥ ቤተ ክርስቲያናችን ታምናለች።
በአገር ውስጥ እና በውጭ የምትገኙ የተወደዳችኹ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
አሠቃቂው ጥቃት ከደረሰበት ሰዓት ጀምሮ፣ በኢትዮጵያዊ ነባር አስተምህሮ እና የአብሮነት ባህል እርስ በርስ በመረዳዳት፣ ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ያሳደረው ከባድ የኑሮ ጫና ሳይበግራችኹ እና ርቀት ሳይገድባችኹ የጥቃቱን ሰለባዎች ለመታደግ እና መልሶ ለማቋቋም ያደረጋችኹትንና በማድረግ ላይ ያላችኹትን ልዩ ልዩ አስተዋፅኦ፣ ቤተ ክርስቲያናችን በከፍተኛ አንክሮ ትመለከታዋለች፤ የጎሣ እና የእምነት ልዩነት ሳይገድባችኹ እስከ ሞት ደርሳችኹ ላደረጋችኹት ሰብዓዊ እና ኢትዮጵያዊ ርዳታ እና ድጋፍ፣ ልዑል እግዚአብሔር ዋጋችኹን ይከፍላችኹ ዘንድ ዘወትር ትጸልያለች።
በሌላ በኩል፣ በክርስቲያናዊ የትብብር መንፈስ፣ በኦርቶዶክሳውያን ላይ የደረሰው ጉዳት ተሰምቷችኹ፣ ጥቃቱን በማውገዝ አጋርነታችኹን በመግለጫ እና በልዩ ልዩ ድጋፎች ላሳያችኹ የዓለም ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የከበረ ምስጋናዋን ታቀርብላችኋለች።
አሁንም፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተጠናክሮ የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ተጎጅዎችን ለመርዳት እና በዘላቂነት ለማቋቋም እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ፥ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በሞያ እንድትድገፉ፤ እንዳስፈላጊነቱም በቀጣይነት ለሚያስተላልፈው ጥሪ ንቁ ምላሽ ለመስጠት እንድትዘጋጁ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን። በዚኹ አጋጣሚ፣ በአገር ውስጥ እና በውጭ የምትኖሩ ምእመናን፥ ድጋፍ እና አስተዋፅኦ ማድረግ ያለባችኹ፣ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው የርዳታ አሰባሳቢ አካል በከፈታቸው የባንክ ሒሳብ ቁጥሮች ብቻ መኾኑን እናስታውቃለን።
ቸሩ እግዚአብሔር፥ ለአገራችንና ለዓለም ሰላምን፣ ለሕዝባችን አንድነትን፣ በግፍ ለተገደሉት ልጆቻችን ዕረፍተ ነፍስንና ለቤተ ክርስቲያናችን መጽናናትን እንዲሰጥልን እንለምናለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት~~~
ዐቢይ ኮሚቴው የከፈታቸው የባንክ ሒሳብ ቁጥሮች፡–
በኦርቶዶክሳዊነታቸው ምክንያት በግፍ ለተፈናቀሉ ክርስቲያኖች መርጃ እና ማቋቋሚያ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጭር ቁጥር፦ 8080
ሕብረት ባንክ የሒሳብ ቁጥር፦ 1601811299653018
ወጋገን ባንክ የሒሳብ ቁጥር፦ 0837771210101
ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የሒሳብ ቁጥር፦ 3359601000003
ዓባይ ባንክ የሒሳብ ቁጥር፦ 146211349291701ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.