ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)

Home Forums Semonegna Stories ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)

Viewing 15 posts - 1 through 15 (of 36 total)
  • Author
    Posts
  • #15317
    Anonymous
    Inactive

    ቁጥጥር ወይ ድርድር! ― አብርሃ ደስታ

    በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና በፌደራል መንግሥት መካከል ውጥረት ነግሷል። የኦሮሚያ ጉዳይም አሳሳቢ ነው። በዚሁ ከቀጠልን የሀገር አንድነት እና የሕዝቦች ደህንነት አደጋ ላይ ይወድቃል።

    ምን መደረግ አለበት?

    ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ ችግሮች ቢኖርቡንም ለአሁኑ ወቅታዊውና አንገብጋቢው ውጥረት መንስዔ ከምርጫ መራዘም በኋላ የፌደራል መንግሥት ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር መነጋገር/ መወያየት ሲገባው “ሁሉም ነገር በሕግ አግባብ ይፈታል” ብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም ወደ መጠየቅ መጣደፉ ነው።

    መንግሥታዊ ተቋምና መዋቅር (government institutions and structure) እንዲሁም ሁነኛ የመንግሥትቁጥጥር (effective government control) በሌለበት ሀገር ሁሉም ነገር በሕግ አግባብ አይፈታም።

    የፌደራል መንግሥት “የፖለቲካ ውይይት አልቀበልም፤ ስልጣን ልትጋሩኝ ነው” ብሎ ወደ “ሕገ መንግሥት ትርጉም” ሮጦ ብቻውን ባይወስን ኖሮ፥ ብዙ ነገር ቀላል ይሆን ነበር። “ትርጉም” ከመጠየቁ በፊት “ይህን ውሳኔዬን የማይቀበሉ ቢኖሩስ? አመፅ ቢቀሰቀስስ?” ብሎ ማሰብ ነበረበት። በሁሉም አከባቢ “መንግሥታዊ ቁጥጥር” እንደሌለው እያወቀ!? ብቻውን ከመወሰኑ በፊት ከሌሎች ጋር መወያየት ቢችል ኖሮ ብዙ ችግሮቻችን መፍትሔ ያገኙ ነበር።

    አንድ መንግሥት መሥራት ያለበት የመጀመርያ ሥራ በሁሉም አከባቢ መንግሥታዊ መዋቅር ዘርግቶ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ነው። ለዚህም ጠንካራ እና ገለልተኛ የሆኑ (ለፖለቲካ ፓርቲ የማያዳሉ) መንግሥታዊ ተቋማት በመገንባት ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲኖረው ማሳየት አለበት። መንግሥት ይህን ባልሠራበት ወቅት ችግር የሚያጋጥም ከሆነ ግን በውይይት/ እውነተኛ ድርድር ነው መፈታት የሚችለው/ ያለበት።

    መንግሥት “መንግሥት” መሆን ካቃተው ዜጎች ዋስትና ያጣሉ። እናም ራሳቸው በራሳቸው ለመከላከል ይታጠቃሉ። ራሳቸው መልስ ይሰጣሉ፣ ይበቀላሉ። በዚህም ሕዝብ ይጎዳል፤ ሀገር ይፈርሳል። የህወሓት ወታደራዊ ትእይንት የምርጫ ጉዳይ አይደለም፤ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ዋስትና ማጣት ነው። የኦሮሞ ዓመፅ በመንግሥት ላይ እምነት ማጣት ነው። እንደ ውጤቱም እጅግ ዘግናኝ ክስተቶች አየን።

    ሀገር እንዲፈርስና ሕዝብ እንዲጎዳ አልፈልግም፤ ስለዚህ የፖለቲካ ችግሮቻችን ለመፍታት መደራደር ይኖርብናል። መንግሥት ከስልጣን በላይ የሀገር አንድነትና የሕዝቦች ደህንነት የሚያሳስበው ከሆነ ለእውነተኛ ድርድር ዝግጁ መሆን አለበት። አለበለዚያ ግን ችግሮቻችን ይቀጥላሉ።

    ወይ አልተደራደረ ወይ አልተቆጣጠረ?!

    አብርሃ ደስታ

    * አቶ አብርሃ ደስታ በትግራይ ክልል ውስጥ በዕድሜ አንጋፋነታቸው ሁለተኛ የሆነው ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲ እና ሉዓላዊነት (ዓረና ትግራይ) በመባል የሚጠራው የፖለቲካ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚታ አባል ናቸው። የፌስቡክ ገጻቸውን እዚህ ጋር ያገኙታል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ-ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    Abraha Desta አብርሃ ደስታ

    #15402
    Anonymous
    Inactive

    የአቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚስጥር ንግግር
    (ሙሉሸዋ አንዳርጋቸው)

    ኢትዮ 360 አቶ ሽመልስ አብዲሳ የዛሬ 7 ወር ገደማ በከፍተኛ ሚስጥር ይጠበቅ ብሎ በኦሮምኛ በስብሰባ ላይ የተናገረውን የኦሮሙማ ፕሮጄክት ለሕዝቡ ሰሞኑን ለቆታል

    መረጃውን ለኢትዮ 360 ማን ለምን እንዴት ሰጠ የሚለውን ለጊዜው ወደጎን ትተን፥ ኢትዮ 360 ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ተማክረው የኢትዮጵያን ህልውና ግምት ውስጥ በመክተት ነገሮች እስኪረጋጉ መረጃውን ከመልቀቅ በመቆጠባቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ይሄ ነው በተግባር ኢትዮጵያን ከሁሉም በላይ ማስቀደም። እንደ ጋዜጠኞች መረጃውን ማግኘት መቻላቸውም በራሱ በተጨማሪ ሊያስመሰግናቸው ይገባል።

    ወደ ሽመልስ ንግግር ፍሬ ነገር ስንገባ፥ አነ ሽመልስ አብዲሳ እና በጥቅሉ የኦሮሙማ አራማጆች ምን እንደሚያስቡ ማወቅ ተገቢውን የትግል ስልት ለመቀየስ በእጅጉ ይረዳል። ከዚህ በፊት ኦቦ ለማ መገርሳ ስለ ዲሞግራፊ ሃሳባቸው፣ አያቶላ ጃዋር ስለ 2ኛው የቄሮ ስውር መንግሥት፣ አሁን ደግሞ ሽመልስን በዚህ ረገድ እናመሰግናቸዋለን።

    ከዚህ ቀጥዬ የሽመልስን ንግግር ልፈትሸው እሞክራለሁ። እነ ሽመልስ አብዲሳ እና ኦሮሙማ አራማጆች ምን እንዳሰቡና ምን እንደሚፈልጉ ለሁላችንም ግልጽ ነው፤ ነገር ግን እግረ መንገዴን ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ መሆናቸውን ለማሳየት እሞክራለሁ። መደስኮርና በተግባር ማሳካት ትልቅ ልዩነት አላቸው።

    1. በመጀመርያ ይሄ ዲስኩር የተደረገው የዛሬ 7 ወር ገደማ መሆኑን ልብ እንበል። Fast forward ዛሬ ላይ ባጭሩ ኦሮሙማ አራማጆች ላይ የነበረው እንዳልነበረ ሆኗል። የ2ኛው መንግሥት መሪያቸው ጃዋር ታስሯል፤ ኦ ኤም ኤን (OMN) የሀገር ቤት መርዛማ ስርጭቱ ተዘግቷል፤ ቀላል የማይባሉ የኦሮሙማ አራማጆች ታስረዋል፤ የዲሞግራፊ ቅየሳ መሃንዲሱ ኦቦ ለማና የለገጣፎ/ሱሉልታ/ሰበታ አፈናቃይዋ ጠቢባ ሀሰን ሳይቀሩ ከፓርቲው ታግደዋል። ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ አባ ገዳዎች ከብት እያረዱ ሊያስማሟቸው ቢሞክሩም፥ ዛሬ ላይ የኦሮሙማ አራማጆች እርስ በእርስ ከመጨራረስ ምንም ምድራዊ ኃይል የሚያስቆማቸው ያለ አይመስልም። ዛሬ ላይ ለዐቢይ ከጃዋር በላይ፣ ለጃዋር ከዐቢይ በላይ ጠላት ከየትም አይመጣም። መሬት ላይ ያለው ሃቅ ይሄ ነው።
    2. ሽመልስ አብዲሳ እኛ ነን ትህነግን (የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር) በቁማር ጨዋታ ያባረርነው የሚለውን እስቲ እንፈትሸው።

    በረከት ስምዖን በቶሎ ካልተቀየርን አደጋው የከፋ ነው ብዬ ስለፈልፍ አልሰማ ብለውኝ፤ የጎንደር አመጽ ሲጀመር የኢህአደግ አመራሮች የምር መሆኑ ዘግይቶም ቢሆን ገባቸው አለ። በሕወሃት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የተጻፈው የኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞ መጽሐፍ ላይ የገዱ አንዳርጋቸው ቡድን ከትህነግ ጋር ለረጅም ጊዜ ፊት ለፊት ሲጋፈጥ እንደነበር ቀን፣ ቦታና አጀንዳ ጠቅሶ ያስረዳል። ዐቢይ ከመመረጡ በፊት የአማራ ሚዲያ ከትህነግ ቁጥጥር ውጪ ወጥቶ ተደማጭ ሚዲያ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ቴዲ አፍሮ በአዲስ አበባ በትህነግ የተከለከለውን ኮንሰርት ባህር ዳር በነጻነት ያውም በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሸብርቆ ማድረጉን እናውቃለን። ባህር ዳር እነ ለማ መገርሳን የጋበዛቸው፣ በሰላምም ቆይተው በሰላም እንዲመለሱ ያደረገው የገዱ አንዳርጋቸው ቡድን ነው። በትህነግ እነ ለማን ለማሰር ታስቦ ደመቀ እምቢ ብሎ ማስቀረቱን ሰምተናል።

    ጥሬ ሃቁ ይሄ ከሆነ እነ ሽመልስ ቁማር ከተጫወቱ፥ ባለቀ ሰዓት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ከውስጥ ደግሞ የገዱ ቡድን በዋናነት ገዝግዞ የጣሉትን ትህነግ፣ በቁማር ጨዋታ የገዱን ቡድን በልጠው ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት መግባታቸው ነው። የገዱ ቡድን ትልቁ ድክመቱ ባህር ዳር ከአዲስ አበባ ርቆ ተወሽቆ፣ ከመሃል ሀገር ስነ ልቦና መራቁና ስልጣን ይገባኛል የሚል ስነ ልቦና ስላልነበረው ነው።

    1. አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስለ ኦሮሙማ ፕሮጀክት የመጀመሪያው ተናጋሪ አይደሉም። በእርግጠኝነት የመጨረሻም ተናጋሪ አይሆኑም። ኦዴፓን (ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) ጨምሮ የኦሮሞ ፓርቲዎች በኦሮሙማ አራማጆች የተሞሉ ናቸው።

    አቶ ሽመልስ ከዚህ ቀደም የማናውቀውን ነገር ብዙም አልነገሩንም። ክብርና ምስጋና በዋናነት ለእስክንድር ነጋ ይግባውና፥ የኦሮሙማ ፕሮጀክትን ከስር ከስር እየተከታተለ አዲስ አበባ ውስጥ ስር እንዳይሰድ አጋልጧቸዋል። እስክንድር ተወልዶ ባያነሳ ብዕር፣ አዲስ አበባ ይሄኔ የኦሮሙማ መቀለጃ ትሆን ነበር። እስክንድርን ለምን እንዳሰሩት ይገባናል።

    1. የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግርና የኦሮሙማ አራማጆች ፍላጎት ላይ ምንም ብዥታ የለንም። ቢችሉ አማርኛን ሙሉ ለሙሉ ቢያጠፉና ኦሮምኛ ብቻ ቢነገር ደስተኞች ናቸው፤ ቅዠታቸው እዚህ ድረስ ነው። ሽመልስ አማርኛ ቋንቋ እንዲሞት፣ ኦሮምኛ ደግሞ እያደገ እንዲመጣ እንዳደረጉ፥ ኦሮምኛ ቋንቋ በ22% እንዳሳደጉ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በሀረሪ፣ በሶማሌ የኦሮሞኛ ቋንቋ እንዳሳደጉ ይናገራል። ለሽመልስ ጥያቄዬ ይሄን ሁሉ ያደረጉት በዚህ 2 ዓመት ውስጥ ነው? የመረጃው ምንጩ ምንድን ነው? ማስረጃ እስኪጠቀስ ድረስ እንደ ኦሮሙማ ምኞት ቢወሰድ የሚመረጥ ይመስለኛል።

    አቶ ሽመልስ አብዲሳ ብልጽግና ውስጥ የኦዴፓ ውክልና በምንወክለው ሕዝብ ብዛት መጠን እንዲሆን አድርገናል ይላል። በዚህ የተነሳ ኦሮሞ ያልሆነ ወይም ኦሮሞ ያልፈለገው ሊቀ-መንበርም ሆነ ምክትል ሊቀ-መንበር እንዳይወጣ አድርገን ብልጽግናን ሠርተናል ይላል። ሲጀምር ፓርቲዎቹ በሚወክሉት ሕዝብ ብዛት መጠን ድምጽ መኖሩን ከትህነግ በቀር ሁሉም ፓርቲዎች ይፈልጉትታል። ሲቀጥል ሽመልስ 40% ድምጽ አለን የሚለውን እውነት አድርገን እንውሰደውና፥ በየትኛው ቀመር ይሆን የተቀሩት 60% ድምፅ ካላቸው ፍላጎት ውጪ ኦዴፓዎች የፈለጉትን እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው? ወይስ የብልጽግና ደንብ ኦዴፓ ያልፈቀደው ሊቀ-መንበር ወይም ምክትል ሊቀ-መንበር መሆን እንደማይችል “veto power” ለኦዴፓ ይሰጣል? እንዴት አርገው ነው 30% የሕዝብ ብዛት ኢትዮጵያን በኦሮሙማ ቅድ መስፋት የሚቻልው? ሌላው ጉራጌው፣ አማራው፣ ሱማሌው፣ ደቡቡ፣ ትግሬው እሺ ብሎ ይገዛል ወይ?

    አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአዲስ አበባ በሕጋዊ መንገድ ይሁን ከሕግ ውጪም የኦሮሞን ቁጥር እንጨምራለን ይላል። መጀመርያ የለማ በአዲስ አበባ ዙርያ ሰፋሪዎች፣ ቀጥሎ ታከለ ኡማ በዚህ ጉዳይ ላይ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ መሬት ላይ ምን እያደረገ እንደሆነ እናውቃለን። አቶ ሽመልስ ምንም አዲስ ነገር እዚህ ላይ አልነገረንም።

    አዲስ አበባን ሌሎች ሁለት ወይም ሦስት ተጨማሪ የፌዴራል መቀመጫ ከተሞች በመጨመር እናዳክማታለን አለ። አቶ ሽመልስ አብዲሳ አዲስ አበባን ለማዳከም መወሰን ማለት “ፊንፊኔ ኬኛ” ቀረ እያለን እንደሆነ ገብቶታል? አዲስ አበባን ማዳከም እንደ ማውራት ቀላል ይሆን? ከተጨማሪ የፌዴራል ከተሞች ውስጥ ለምሳሌ አንዱ ናዝሬት የሁሉም ኢትዮጵያኖች ከተማ ቢሆን፣ “ናዝሬት ኬኛ” በኋላ ማለት ሊጀምሩ ይሆን?

    አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአሁኑ ወቅት በልበ-ሙሉነት እንደ ኦሮሚያ እየለማ ያለ ቦታ የለም ይላል። Really? የቄሮ እብደት ከጀመረ በኋላ ፋብሪካዎች በኦሮሞ አካባቢ ሲቃጠሉና ሲዘጉ አይደል እንዴ እያየን የለነው? አሁን እንኳን ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣… እንዳልነበሩ ሆነው አልወደሙም? ስንት ዓመት ይፈጅ ይሆን የተቃጠሉትን ከተሞች ያሉበት ቦታ ለመመለስ? በተጨማሪ “ፊንፊኔ ኬኛ” ብለው የኦሮሞ ባህል ማዕከል፣ የኦሮሞ መሥሪያ ቤቶች፣ቢሮዋች፣…. ሸገር ላይ ነው የሚሠሩት። ታዲያ እንዴት አድርገው ነው አዱ ገነትን መግደል የፈለጉት? በኦሮሞ አካባቢ አለመረጋጋትና በኦሮሙማ አራማጆች ድንቁርና እየተመነደጉ ያሉት ከተሞች ሌሎች ናቸው። በስታትስቲክስ የተደገፈ መረጃ እዚህ ላይ ለሽመልስ ማቅረብ ይቻላል።

    1. ማጠቃለያ
      የሽመልስና የቢጤዎቹ ኦሮሙማ አራማጆች ሴራ በንቃት ሁላችንም መከታተልና ማጋለጥ አለብን። ለሴራቸውም ማክሸፊያ በሕብረት መፈለግ አለበት። በተለይ ሌሎቹ የብልጽግና አባሎች ይሄንን የእነ ሽመልስን የኦሮሙማ ቅዠት በዋዛ ፈዛዛ ሊያልፉት አይገባም። ከስር ከስር እነ ሽመልስን እየተከታተሉ ማጋለጥና ማርከሻ መፈለግ አለባቸው። የእነ ሽመልስን እጅና እግር ለማሰር የብልጽግናን ደንብ መለወጥ ካለባቸው አይናቸውን ማሽት የለባቸውም። እንዲህ በማድረግ ነው የኦሮሙማ ቅዠታሞችን እሩቅ አሳቢ፣ ቅርብ አዳሪ አድርገን የምናስቀረው።

    ሙሉሸዋ አንዳርጋቸው

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ ሽመልስ አብዲሳ

    #15538
    Anonymous
    Inactive

    በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የታሪክ ዳራ፥ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ሀገር ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎች፣
    ያጋጠሙን የታሪክ ፈተናዎችና ያመለጡን ዕድሎች በብሔራዊ መግባባት መነፅር ሲታይ

    መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)
    ለብሔራዊ መግባባት ውይይት የቀረበ ጥናት
    ነሐሴ 2012

    አብዛኛዎቹ የሀገራችን የታሪክ ምሁራን የኢትዮጵያ ታሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ በአስረኛው ምዕተ ዓመት የንግስት ሳባ እና የንጉሥ ሰለሞን ግንኙነት በሚባለው ጊዜ ይጀምራል ይላሉ። ይህ ለአንዳንዶቹ የሚታመን ታሪክ ተደርጎ የሚወሰደው፤ ለሌሎች ደግሞ ተረት እንደነበረ የሚነገረው ክስተት የማስመሰያ ትርክቱ የእስራኤል አምላክ የቀባቸው ገዥዎች ተብሎ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ንጉሦቹ ቅቡልነትን አግኝተውበታል። በትርክቱም ሀገሪቷን እስከ 1966 ሕዝባዊ አብዮት ድረስ ያለ ብዙ ጭንቀት ገዝተውበታል።

    የዛሬይቱ ሰፊዋ ኢትዮጵያ እንደ ሕብረ ብሔራዊ የነገሥታት መንግሥት (multi-ethnic empire state) የተፈጠረችው በ2ኛው የ19ኛው ክፍለ ዘመን ግማሽ፤ የዘመነ መሳፍንት ከሚባለው ዘመን በኋላ ስለሆነና ዛሬም በጣም ሰፊ ቀውስ ውስጥ የከተተን ታሪካዊ ዳራም ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ፥ ጽሑፌም ከዘመናዊ ኢትዮጵያ መፈጠር ጋር በተፈጠሩ ችግሮች ላይ ያተኩራል።

    የዘመነ መሳፍንትን ክስተት በመለወጥ የተጀመረው የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ሕልም በግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ከሦስት እጥፍ በላይ የሰፋች ኢትዮጵያን መፍጠር ችሎዋል። ይህ የታሪክ ክስተት የሦስት ምኞቶች ዉጤት ነበር። እነዚህም፡-

    1ኛ/ ተበታትና የነበረችውን የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለማሰባሰብ የታለመ ምኞት፣
    2ኛ/ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦችን ጨምሮ ሰፊውን የደቡብ ክፍል የማስገበር ምኞት፣
    3ኛ/ አፍሪካን ለመቀራመት የመጡትን የአውሮፓ ሀገሮች ጋር የመፎካከር ምኞት ነበሩ።

    እነዚህን ሦስት ምኞቶች ለማሳካት የመጀመሪያ የሆነውን ሙከራ የጀመሩት እንደምታውቁት አፄ ቴዎድሮስ ነበሩ። ቴዎድሮስ ሕልሞቹን ለማሳካት ጠንካራና ሰፊ ሠራዊት ማደራጀት ነበረባቸው፤ ለዚህም ሰፊ መሬት የያዙትን ቄሶች መሬት መቀማትና ዘመናዊ መሣሪያን ከክርስቲያን አውሮፓ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ነበር። የአዉሮፓ መሪዎችን ማሳመን ሲያቅታቸው ደግሞ ሙያው የሌላቸውን አውሮፓዊያንን ሳይቀር በቤተ መንግሥታቸው ሰብስበው ከባድ የጦር መሣሪያ ውለዱ እስከማለት ደርሰዋል። ይህም ምኞታቸዉ ይሳካ ዘንድ በነበራቸዉ የጦር መሣሪያ የአካባቢ ገዥዎችንም ለማንበርከክ ተንቀሳቅሰዋል።

    ቄሶችን ለመግፋት ያደረጉት ሙከራ እግዚአብሔርን የካዱ ንጉሥ ተብሎ ተሰባከባቸዉ። የአውሮፓውያንን ዘመናዊ መሣሪያ ለማግኘት ገደብ ያለፈ ጉጉታቸው ከእንግሊዘኞች ጋር ያለጊዜ አላተማቸው። የየአከባቢውን ገዥዎች በጉልበት ለማንበርከክ እጅና አንገት በመቁረጥ የገፉበት ሙከራ ከእንግሊዞች ጋር ለመዋጋት የቁርጥ ቀን ሲመጣ፥ የትግራይ፣ የወሎ፤ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የጎንደር ገዥዎች ሁሉም በሚባልበት ደረጃ ካዷቸው። በአጭሩ የየአከባቢዉ ገዥዎች በእንግሊዞች እጅ መሞታቸውን ሲሰሙ ከማዘን ይልቅ ተገላገልን ያሉ ይመስላል። ለዚህም ይመስለኛል ዕውቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሴር ባህሩ ዘውዴ የቴዎድሮስን ሚና በተሻለ የታሪክ ሚዛን ላይ ለማስቀመጥ ሲሞክር፥ “የተወናበዱ የለዉጥ ነቢይ” (“confused prophet of change”) ያላቸዉ።

    በዚህ የቴዎድሮስ የታሪክ ሚና ላይ ብዙ ሰው ልብ የማያደርገውን የታሪክ ማስታወሻ አስቀምጬ ልለፍ። ይኼውም ቴዎድሮስ በጊዜው ለነበሩ የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት በፃፉት ደብዳቤ ውስጥ፥ “አባቶቼ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር “ጋሎችን” በሀገሬ ላይ ለቆ፣ እነሱ ጌቶች ሆነው፣ እኛ የእስራኤል ልጆች የነሱ አሽከሮች ሆነን እንኖር ነበር። አሁን እግዚአብሔር ከትቢያ አንስቶኝ የኢትዮጵያ ንጉሥ አድርጎኛል። እናንተ ከረዳችሁኝ በጋራ እየሩሳሌምንም ነፃ ልናወጣ እንችላለን” ማለታቸዉ ነዉ (ትርጉም የኔ ነው)። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ልበል፦

    1) “ጋሎቹ” የሚባሉት በዘመነ መሳፍንት የጎንደርን ቤተ መንግሥት በበላይነት ሲቆጣጠሩ የነበሩ የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውና እየሩሳሌም በጊዜው በእስላሞች እጅ የነበረች መሆንዋን ነው።
    2) ከዚህ አንጻር ማስታወስ የሚያስፈልገው ትልቁ ጉዳይ አፄ ቴዎድሮስ የብሔረሰብ (የዘር) ፖለቲካን በግልፅ የተናገሩ የመጀመሪያዉ የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ነው።

    ከቴዎድሮስ ሞት በኋላ ለሦስት ዓመታት በተክለጊዮርጊስ እና ካሣ (አማቾች የነበሩ ይመስለኛል) ከተካሄደው የሥልጣን ትግል በኋላ በአሸናፊነት የወጡት አፄ ዮሐንስ (ካሣ ምርጫ) ነበሩ። አፄ ዮሐንስ ከሀገር ውስጥ ከወሎ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከሸዋ ገዢዎች ጋር እየተጋጩ፥ ከውጭ ደግሞ ከጣሊያኖች፣ ከግብፆችና ከሱዳን መሐዲስቶች (ደርቡሾች ) ጋር ሲዋጉ በመጨረሻ በመሐዲስቶች እጅ ወድቋዋል።

    በአጭሩ ዮሐንስ ለትግራይ ሊሂቃን የኢትዮጵያ ማዕከል ነበርን፤ የአክሱም ሀቀኛ ወራሾች እኛ ነን የሚለውን የፖለቲካ ስሜት መፍጠር ቢችሉም፥ በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ የተለየ ሚና መጫወት አልቻሉም።

    በማያሻማ ቋንቋ፥ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዋናነት የተፈጠረችውና የዛሬው የታሪክ ጣጣችንም በዋናነት የተፈጠረው በአፄ ምኒልክ ነው። ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስን የሱዳን መሐዲስቶች እስኪገድሉላቸው ድረስ ከአውሮፓ መንግሥታት፥ በተለይም ከጣሊያን በገፍ ባገኙት የጦር መሣሪያ እነራስ ጎበና የመሳሰሉ የኦሮሞ የጦር መሪዎችን በመጠቀም በጊዜው ጠንካራ የሚባል ግዙፍ ሠራዊት መገንበት ችለዋል። ይህንን ግዙፍ ሠራዊትን ከዮሐንስ ጋር በመዋጋት ከማድከም ይልቅ፥ በአንድ በኩል ዮሐንስን እየገበሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያኔ የነበረችውን ኢትዮጵያ ሦስት እጅ እጥፍ የሆነ ሰፊ ግዛት መፍጠር ችሎዋል። በዚህም መጀመሪያ ሳይጠቀለሉ የቀሩትን የሸዋ ኦሮሞዎችን ጠቅልለው ያዙ። ከዚያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር (እ.አ.አ) በ1876 ጉራጌን ብዙ ሕይወት ከጠየቀ ጦርነት በኋላ አስገበሩ። ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ የምኒልክን የመስፋፋት ጦርነቶች እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል። ይኸውም በምኒልክና ጀኔራሎቹ ብዙ የግዛት መስፋፋት ጦርነቶችን ቢወጉም ሦስቱ ወሳኝ ጦርነቶች ነበሩ።

    አንደኛው በምዕራብ በኩል በእማባቦ (ዛሬ ሆሮ ጉዱሩ በሚባለው ላይ በጎበና መሪነት እ.አ.አ በ1882 የተዋጉት ጦርነት ነበር። ይህ ጦርነት ኦሮሞን ጨምሮ የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ዕድልና የጎጃም መሪዎች ከሸዋ ጋር የነበራቸውን ፉክክር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የወሰነና የሸዋንም የበላይነት ያረጋገጠ ነበር።

    ሌላው የምኒልክ ጦርነት በአርሲ ላይ እ.አ.አ በ1886 የተደመደመዉ ነው። አርሲዎች ከሌሎች የኦሮሞ አካባቢዎች በተለየ መንገድ ለአምስት ዓመታት በጀግንነት ተዋግተዋል። በመጨረሻም በራሳቸው በምኒልክ በተመራ ጦር የአውሮፓ መሣሪያ በፈጠረው ልዩነት ሊሸንፉ ችለዋል። ተመሳሳይ የመከላከል ጦርነት እንዳይገጥማቸው ይመስላል ምኒልክ ዛሬ አለ፣ የለም የሚባለውን የአኖሌ ዓይነት የጭካኔ በትር በአርሲዎች ላይ አሳርፈዋል። እዚህ ላይ ዛሬ እየተነጋገርንበት ላለው የብሔራዊ መግባባት መሳካት፥ የለም ከሚለው አጉል ክርክር ወጥተን የትናንትናውን የታሪክ ቁስላችንን በሚያክም መልኩ እንድናስተካክል መምከርን እወዳለሁ።

    ሦስተኛው የምኒልክ ትልቁ ጦርነት አሁንም በእሳቸው የተመራውና እ.አ.አ በ1887 የተካሄደው የጨለንቆ ጦርነት ነበር። የዚህ ጦርነት ውጤት በጊዜው የሀብታሟ የሐረር ከተማ መንግሥት (the Harari city-state) ጨምሮ ምስራቅ ኢትዮጵያ ያለ ደረሰኝ ምኒልክ እጅ የገባበት ሁኔታን ፈጥሯል። ከዚህም በኋላ ከፋን፣ ወላይታን፣ ወዘተ ለመያዝ ብዙ ደም የፈሰሰባቸው ጦርነቶች ነበሩ። እንደሚባለው በእንግሊዝ ተስፋፊዎችና በምኒልክ ኢትዮጵያ መካከል የመምረጥ ዕድል የገጠማቸው የቦረና ኦሮሞዎች፥ ‘ማንን ትመርጣላችሁ?’ ሲባሉ፥ የፊታወራሪ ሀብተጊዮርጊስ ፊትን አይተው፥ የእኛኑ ፊት የሚመስለው ይሻላል ብለው በሪፈረንደም (referendum) እየሰፋ በመጣው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ግዛት ውስጥ የተቀላቀሉበት ሁኔታም እንዳለ ይነገራል።

    እ.አ.አ በ1889 አፄ ዮሐንስ በመሐዲስቶች ሲገደሉ፥ ኦሮሞን ጨምሮ አብዛኛው ደቡብን የተቆጣጠሩት ምኒልክ ለሰሜኑ ወንድም መሪዎች ፈረንጆች እንደሚሉት “ካሮትና ዱላን ማስመረጥ” (carrot-and-stick approach) ብቻ በቂ ነበር። የሰሜኑ መሪዎች ምርጫም በማያሻማ መንገድ ካሮት ነበር። ስለካሮቱም በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ የኦሮሞ አከባቢዎችን ጨምሮ በደቡብ የተገኘውን እጅግ በጣም ሰፊ ግዛት ዉስጥ በታናሽ ወንድምነት ሹማቶችን መቀራመት ነበር።

    በብሔራዊ መግባባታችን ውይይት አንፃር በምኒልክ በተፈጠረው ሰፊ አፄያዊ ግዛት ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ወደ ማንሳቱ ልለፍ። አንደኛው ችግር ከላይ እንዳነሳሁት፥ በጉልበት የግዛት ፈጠራ ላይ አኖሌን የመሳሰሉ የታሪክ ጠባሳዎች መፈጠራቸው። ሁለተኛውና ዋናው ነገር ግን ከማቅናቱ ጋር የተፈጠረው የፖለቲካል ኤኮኖሚው ነው። ይህም በነፍጥ ላይ የተመሠረተዉ የፖለቲካ ኤኮኖሚ ዛሬም እያወዛገበን ያለው የነፍጠኛ ሥርዓት በሚባለው ላይ የተመሠረተዉ ነዉ። ለማቅናት የተሰማራው የፊውዳሉ ሥርዓት ሠራዊት የገባር ሕዝቦችን ነፃነት ቀምተዋል፤ መሬታቸዉን ዘርፈዋል፤ ሕዝቦችን በገዛ መሬታቸው ላይ ጭሰኛና አሽከር አድርገዋል፤ ቋንቋቸውን አፍነው በ’ስማ በለው’ ገዝቷቸዋል። በአጭሩ፥ እጅግ በጣም ዘግናኝና ጨካኝ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ጭነውባቸዋል። አንዳንዱ ነፍጠኛ በሃያ ሺዎች የሚቆጠር ጋሻ መሬትም ነበረው። ወረ-ገኑ የመሳሰሉ የቤተ መንግሥት መሬቶች እጅግ በጣም ብዙ ነበሩ። እዚህ ላይ ማስታወስ የሚያስፈልገው የሰሜንና የደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት ይዞታም በፍጹም የተለያዩ መሆናቸው ነው። አነሰም በዛ የሰሜኑ ገበሬ የዘር ግንዱን ቆጥሮ መሬት ያገኛል። መሬት አያያዙም የወል ነበር። ሌላው ቢቀር የሚገዛውም በራሱ ቋንቋ ነበር። በደቡቡ ያለው ግን የመሬት ሥርዓቱ የግል ሆኖ፥ ጭሰኝነት እጅግ የተንሠራፋበት ነበር። ሲሶ ለነጋሽ፣ ሲሶ ለቀዳሽ፣ ሲሶ ለአራሽ የሚባለው የኢትዮጵያ ነገሥታት የመሬት ፖሊሲ እጅግ በጣም ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሥራ ላይ የዋለው በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ላይ ነው።

    በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን “መሬት ላራሹ” እና “የብሔረሰቦች እኩልነት” የተባሉ ሕዝባዊ መፈክሮች የተወለዱት ከዚሁ ጨቋኝ ሥርዓት ነበር። ዛሬ የታሪክ ክለሳ ውስጥ ብንገባም፥ በእውነቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብራክ የወጡ ወጣቶች፥ እንዲያውም በወቅቱ ‘አማራ’ ከሚባለው ክፍል የሚበዙ ይመስለኛል፤ መፈክሮቹን በጋራ አስተጋብተዋል።

    ለማንኛውም ከብሔራዊ መግባባታችን አንፃር አንድ ነገር ግልፅ ላድርግ። ‘ነፍጠኛ’ የሚባለው ሥርዓት ገዝፎ የነበረ ሥርዓት መሆኑና፥ ይህም ሥርዓት ከደቡቡ አርሶ አደር የተሻለ ኑሮ የማይኖሩትን፥ ቢፈልጉ እንኳን የደቡቡን ገበሬ ለመዝረፍ አቅሙም ሆነ ዕድሉን ያልነበራቸውን የአማራ አርሶ አደርን አይጨምርም፤ መጨመሩም ጩቡ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ አንዳንድ የአማራ ሊሂቃን “እኔም ነፍጠኛ ነኝ” የሚለውን መፈክር ሲያሰሙ፥ ጥቅሙ ኦሮሞን ጨምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ከአማራ ሕዝብ ጋር ከማጋጨት የዘለለ የፖለቲካ ትርፍ የሚኖረው አይመስለኝም። ስለሆነም የምንችለውን ያክል ሁላችንም ከሁለቱም ጩቡዎች እንጠንቀቅ ዘንድ አደራ እላለሁ።

    ወደ ሌሎች ነጥቦች ከማለፌ በፊት በዋናናት በምኒልክ የተፈጠረችዉ ኢትዮጵያን ለማስተካከል ያቃታቸዉና መሪዎች ማለፍ ያልቻሉት የታሪክ ፈተና ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ በንጽጽር እንደ ታሪክ ቁጭት ማንሳትን እወዳለሁ። አፄ ቴዎድሮስ የሞቱት እ.አ.አ በ1868 ነበር። ጃፓንን ከታላላቅ የዓለም መንግሥታት ተርታ ያሰለፏት መጅ (Meiji) የሚባሉ የንጉሣውያን ቤተሰብ ወደ ሥልጣን የተመለሱት (The Meiji Restoration) በዚሁ ዓመተ ምኅረት ነበር። የጃፓን ንጉሣዊ ቤተሰቦች በሰላሳ ዓመታት ውስጥ በኢኮኖሚ የበለፀገች ታላቋ ጃፓንን ፈጠሩ። የጃፓኖች የሀገር ፍቅር ግንባታቻውም ባዶ አልነበረም። ትዝ እስከሚለኝ ድረስ አንድ የጃፓን ወታደር ንጉሤ የጃፓንን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መሸነፍ አልነገሩኝም ብሎ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ በፊሊፕንስ ይሁን፤ በኢንዲኔዢያ ጫካ ውስጥ ተገኝቷል። ለሀገር ፍቅር ሲባል እራስን በራስ ማጥፋት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በትናንሽ አይሮፕላኖችን የአሜሪካን መርከቦች ውሰጥ እየጠለቁ አጥፍቶ መጥፋትን የጀመሩት የጃፓን ካሚከዞች (Kamikaze) የሚበሉ ነበሩ። የኢትዮጵያ መሪዎች ግን በተመሳሳይ ጊዜ (እ.አ.አ 1868-1900) ድረስ ሀገሪቷን ከዓለም ጭራነት አላላቀቋትም። በነገራችን ላይ ጃፓንና ኢትዮጵያ በ1868 ላይ ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ነበሩ።

    ሌላው ንጽጽሬና የታሪክ ቁጭታችን መሆን ያለበት፥ ታላቋ ጀርመንን የፈጠሩት ቢስማርክ (Otto von Bismarck) እና ምኒልክ የአንድ ዘመን ሰዎች ነበሩ። ምንም ይሁን ምን እነ ቢስማርክ ዓለምን ሁለት ጊዜ ጦርነት ውስጥ መክተት የቻለች ኃያሏን ጀርመን ሲፈጥሩ፥ የኢትዮጵያ ገዥዎች ግን ኋላቀር ኢትዮጵያን ትተውልን ሄደዋል። በነገራችን ላይ ሀገር ትፈርሳለች ተብሎ ስለተሰጋ፥ የምኒልክ ሞት ለሕዝብ ይፋ የሆነው ከዓመታት በኋላ ነበር ይበላል።

    በአጠቃላይ ከብሔራዊ መግባባት ፈጠራችን አንፃር መረሳት የሌለበት ቁመነገር፥ በምኒልክና ጣይቱ የተመራው የአድዋው የጋራ ድል እንኳ ያልፈቱት የሚጋጩ ሦስት አመለካከቶች ዛሬም ከእኛ ጋር መኖራቸዉ ነዉ።

    አንደኛው፥ የሀገራችን ሀገረ-መንግሥት ግንባታ አንድ የነበሩና የተበታተኑ ሕዝቦችን አንድ ላይ መልሶ ያመጣ ነዉ የሚላዉ አመላካከት (reunification)፤
    ሁለተኛው፥ በአንድ ላይ ያልነበሩ ሕዝቦችን ወደ አንድ ማምጣት ነዉ የሚለዉ አመላካከት (unification and/or expansion)፤
    ሦስተኛው፥ ነፃ ሕዝቦችን ጨፍልቆ በኃይል ማቅናት ነዉ የሚላዉ አመላካከት (colonial thesis) ናቸው። የበለጠ ግልፅ ለማድረግ፥ የኢትዮጵያ አንድነት አጥባቂዎች ነን የሚሉ በዋናነት የምኒልክን ኃጢአቶች አይቀበሉም። እንደሚሉት እምዬ ምኒልክ በዓለም ከተደረጉት የሀገር ግንባታዎች ምን የተለየ ነገር ሠራ የሚለውን ሐሳብ ያራምዳሉ። ከዚያም አልፈዉ ምኒልክ የሠራዉ ሥራ ተለያይተዉ የነበሩትን የኢትዮጵያ ግዛቶችን መመለሰ ነበር ይላሉ። በአንፃሩ የኢትዮጵያ አንድነትን የማያጠብቁ ብሔረተኞች ደግሞ የአቶ ሌንጮ ለታን አባባል ለመጠቀም (አሁን አቋማቸዉ ያ መሆኑን አላዉቅም)፥ ሲያንስ “ኢትዮጵያዊ ለመሆን እንደራደራለን ሲበዛ ደግሞ ነፃ መንግሥታትን እስከ መፍጠር ድረስ እንሄደለን” የሚሉ ናቸው። በጥቅሉ እነዚህ አመለካከቶች በፖለቲካችን ለሚጋጩ ሕልሞቻችን መሠረት የሆኑና ካልተገደቡ የሥልጣን ሕልሞች ጋር ተደምሮ የብሔራዊ መግባባት ጥረታችንን የሚያወሳስቡ አመለካከቶች መሆናቸውን በውል መገንዘብ ያስፈልጋል።

    በእነምኒልክ የተፈጠረችዉን ኢትዮጵያን ለማስተካከል የተደረጉ ሙከራዎችና ያመለጡን ዕድሎች፡-

    1) የልጅ ኢያሱ ሙከራ

    ልጅ ኢያሱ የምኒልክ ልጅ ልጅ ሲሆን፥ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩ ዕድል የነበረውና ያንንም ልዩ ዕድል አውቆ ለመጠቀም ሲሞክር በወጣትነት ዕድሜው ላይ የተቀጨ መሪ ነበር። በብሔር ግንዱ ኦሮሞና አማራ የነበረ፣ በሃይማኖት ጀርባዉ ክርስቲያንና ሙስሊም የነበረ ሰዉ ነዉ። ከወሎም በመወለዱ፣ ትግራይንና ሸዋን ለማገናኘት የተሻለ ድልድይ ለመሆን ይችል ነበር። የሚገርመው ግን፥ የልጅ ኢያሱ ወንጀሎች የሚመነጩት እነዚህኑ አዎንታዊ እሴቶችን ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ለመጠቀም መሞከሩ ነበር። ለምሳሌ አንዳንድ የታሪክ ማስታወሻዎች እንደሚያስረዱት፥ አርሲዎች እንደልጃቸው ይመለከቱት ነበር ይባላል። ከሱማሌዎችና ከአፋሮች ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንደነበረው በቂ የሆነ የታሪክ ማስረጃ አለ። ከጎጃሙ ራስ ኃይሉና ከወለጋው ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ ጋር የጋብቻ ዝምድና እንደነበረው ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያንን ለማሠራት የሚጥረውን ያክል (ለምሳሌ የቀጨኔውን መድሃኔዓለምን እሱ ነው ያሠራው ይባላል) መስግዶችን ያሠራ ነበር። ከሥልጣን ላወረዱት የሸዋ ሊሂቃን ግን፤ አንዱና ትልቁ የልጅ ኢያሱ ወንጀል መስጊዶችን ማሠራቱ ነበር። የመጨረሻው ትልቁ ወንጀል ደግሞ ኢትዮጵያን ለመቀራመት ያንዣበቡ የቅኝ ገዥ ኃይሎች ከሰሜንና ምስራቅ ጣሊያን፣ በምዕራብ፣ በደቡብና በምስራቅ እንግሊዝ፣ በምስራቅ ፈረንሳይ የሦስትዮሽ ስምምነት (tripartite treaty) የሚባለውን እ.አ.አ በ1903 ፈርሞ የምኒልክን ሞት ይጠብቁ ከነበሩት መራቅና በአንደኛው የዓለም ጦርነት በአከባቢያችን ግዛት ካልነበራቸው ከነጀርመንና ቱርክ ጋር ለመደጋገፍ መሞከሩ ነበር።

    በጥቅሉ ከሁሉም በላይ ወንጀሎቹ ሰፊዋን ኢትዮጵያን የፈጠርን እኛ ነን የሚሉትን የሸዋ ልሂቃንን መጋፋቱ ነበር። በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ የኢያሱ ወንጀሎች የሸዋ ልጅ አለመሆኑ (የኢያሱ አባት ወሎ ነው)፣ ሐቀኛ የክርስቲያን ልጅ አለመሆኑ (አባቱ የግድ ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት መሐመድ ዓሊ ነበሩና) እንዲሁም የአውሮፓ የቅኝ ገዥ ኃይሎችን ማስቀየሙ ናቸው።

    እ.አ.አ በ1916 በመስቀል ቀን ኢያሱን ለማውረድ ሁሉም መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ተሰለፉ። ቄሶቹ ኢያሱ ሐቀኛ የክርስቲያን ልጅ አይደለም በማለት በማውገዝ፣ የሸዋ ሊሂቃን ሠራዊታቸውን በመሳለፍ፣ የአውሮፓዊያኑ መንግሥታት ምክርና ጥበባቸውን ይዘው ተሰለፉ። የአውሮፓዊያኑ ጥበብ የሚገርም ነበር፤ ኢያሱ በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ የእስልምና ምልክት የሆነውን ግማሽ ጨረቃ ለጥፎ ለቱርኮች ዲፕሎማት ሲሰጥ የሚያሳይ ፎቶ ሾፕ የሆነ ሥዕል (ፎቶ ሾፕም፣ የባንድራ ፖለቲካም በልጅ ኢያሱ ዘመንም ነበር) መፈንቅለ መንግሥት እንድያከሄዱ የሸዋ ሊሂቃንን መርዳት ነበር። እዚህ ላይ ለታሪክ ትዝብት አንድ ነገር ልብ በሉልኝ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሳስተምር፥ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ችግሮቻችንን በሚመለከት ፈተናም ፈትኜበታለሁ፤ የሸዋው ጦር መሪ የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የመፈንቅለ መንግሥቱም መሪ ነበሩ፤ ልጅ ኢያሱን ሲያወርዱ ባስተላለፉት መልዕክት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል።

    “He claims that he eats flesh of cattle slain by Muslims in order to extend frontiers and to win hearts. But these Somali and Muslims have already been brought to heel [and do not need such diplomacy]”

    በጥሬው ሲተረጎም፥ ግዛትን ለማስፋፋትና ልቦችን ለመሳብ ብዬ በሙስሊም የታረደውን የከብት ሥጋ እባላለሁ ይላል። ነገር ግን እነዚህን ሱማሌዎችና ሙስሊሞችን ቀድሞውኑ ስላንበረከክን እንዲህ ዓይነቱ ዲፕሎማሲ አያስፈልጋቸውም።

    ይህንን የሀብተጊዮርጊስን ንግግር በሚመለከት ሰፊውን ትንተና ለናንተ ትቼ፥ በዚህ ዓይነት የተዛባ አመለካከት ላይ የተገነባችውን ኢትዮጵያን አስተካክሎ በሰፊ መሠረት ላይ የተገነባችውን ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተደረገው የመጀመሪያ ሙከራ፥ ልጅ ኢያሱን ለሥልጣን ተብሎ በተጠነሰሰው ሤራ መውረዱን እንዳትረሱት አደራ ማለት እፈልጋለሁ። ያመለጠንን ዕድል ትርጉም ግን ለታሪክ መተውን አመርጣለሁ።

    2) ኢያሱን በወሳኝነት የተኩት ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ

    የሀገራችንን ሀገረ-መንግሥት ግንባታን በተሻለ መሠረት ላይ ለመገንባት ረጅም ጊዜ (ለ60 ዓመታት ገደማ አገሪቷን መርተዋል) በልጅነታቸው የተሻለ የፈረንጅ ዕውቀት የቀመሱና ከማንም የበለጠ ተደጋጋሚ ዕድል ያገኙ ነበሩ። ነገር ግን በእኔ ግምት ታሪክ የሰጣቸዉን ዕድል አልተጠቃሙበትም። ንጉሥ ኃይለ ሥላሴን የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ የታሪክ ሚዛን ላይ ቢያስቀጣቸውምና እኔም ቢሆን በዘመናዊ ትምህርትና በመሳሰሉት ላይ የነበራቸውን አሻራ ቀላል ነው ብዬ ባላስብም፥ ንጉሡ ሕይወት ዘመናቸውን በሙሉ የግል ዝናንና ሥልጣንን ማዕከል ማድረጋቸው ኢትዮጵያዉያንን የ20ኛው ክፍለ ዘመን ሕዝቦች ማድረግ አልተቻላቸውም። ስለዘር ግንዳቸው ሀሜቱ እንዳለ ሆኖ፥ ከኢያሱ በተሻለ ደረጃ ኦሮሞም፣ ጉራጌም አማራም ነበሩ። ይህንን ስረ ግንድ አልተጠቀሙም። በተለይ ኦሮሞ ከሚባል ሕዝብ ሲሸሹ እንደኖሩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ለማንኛዉም፤ አንድንድ ወሳኝ ነገሮችን እንመልከት።

    አምቦ 2ኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የሰማሁት ይመስለኛል፤ አንድ ጋዜጠኛ ካነበቡት መጽሐፍት ዉስጥ የትኛውን እንደሚያደንቁ ሲጠይቃቸው፥ ቀልባቸውን በጣም የሳበውና ብዙ ጊዜ ደጋግመው ያነበቡት በኒኮሎ ማኪያቬሊ (Niccolò Machiavelli) የተፃፈውን “The Prince” የተባለውን እንደነበረ ትዝ ይለኛል። ንጉሡ አብዘኛዉን የሕይወት ዘመናቸዉን የተመሩት በማኪያቬሊ ምክር ነበር ብዬ እጠረጥራለሁ። በማክያቬሊ ትምህርት በመመራትም የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን አንድ በአንድ አስወግደው ከአስራ አራት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1930 ጥቁር ማክያቬሊ ፈላጭ ቆራጭ ንጉሥ ሆነው ወጡ።

    እንደ ሀብተጊዮርጊስ ዓይነቱን እግዚአብሔር በጊዜ ሲገላገልላቸው፣ እንደ ጎንደሩ ራስ ጉግሳና ባለቤታቸው ንግስት ዘዉድቱን ያስወገዱበት የፖለቲካ ጥበብ፣ በጊዜው በርግጥም አስደናቂ ነበር። ይህ የንጉሡ ጥበብ፤ አርባ ዓመታትን ቆጥራ የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል የመጣቸውን ጣሊያንን ለመከላከል አልረዳም። መንግሥታቸዉንም፤ ሀገሪቷንም ለክፉ ቀን አላዘጋጁም።

    አድዋ ላይ ታሪካዊ ድል ያስገኙ ጀግኖችም የሉም። አንድ ለታሪክ የተረፉት ደጀዝማች ባልቻ ሣፎም በንጉሡ ዉሰኔ እስር ቤት ነበሩ። እዚህም ላይ አንድ የታሪክ ትዝብት አስቀምጬ ማለፍ እፈልጋለሁ። ኃይለ ሥላሴ ለሥልጣናቸዉ ብሎ የገፏቸው ብዙ የአከባቢ መሪዎች፥ ከትግራዩ ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳ ጀምሮ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የጅማ፣ የወለጋ ገዥዎች የጣሊያን ባንዳ ሆኑ። ከሚታወቁት ውስጥ ለታሪክ ‘ተፈሪ ሌላ፣ ሀገር ሌላ’ ብለው ሲዋጉ የሞቱት ደጃዝማች ባልቻ ብቻ ነበሩ። በንጉሡ ስህተት ሀገሪቷ ውድ ዋጋ ከፍላለች። ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት ጠዋትና ማታ ባንዳ፣ ባንዳ ሲሉ፥ ግብፅ ሱዳንን ይዛ የምር ከመጣች ሰው ያላሰበውን አሳስበው ለኪሳራ እንዳይዳርጉን የሚፈራው።

    ያም ሆነ ይህ፥ ኃይለ ሥላሴ ለጦርነት ያላዘጋጇትን ሀገር በክፉ ቀን ጥለው ሸሹ። ሐረርጌ ላይም የጂቡቲን ባቡር ሲሳፈሩ ከጦር ሜዳ መሸሻቸውን ለመሸፈን፥ ‘የት ይሄደሉ?’ ብሎ ለጠያቀቸዉ የፈንሳይ ጋዜጠኛ፡ “Je ne suis pas né soldat” (“ወታደር አይደለሁም”) ብለው ያለፉት። ለሳቸዉም ፍትሃዊ ለመሆን፥ የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ቢክዷቸውም በዓለም መንግሥታት ማኅበር ላይ የሚያስመካ ሥራ ሠርተዋል። ሆኖም ከጦር ሜዳ የመሸሻቸው ጉዳይ እስከ መንግሥታቸው ፍፃሜ ድረስ እንደ ጥቁር ነጥብ ስትከታላቸዉ ኖራለች። የአርበኞችም ሆነ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዋናው የተቃውሞ መፈክርም ይህች የሽሸት ጉዳይ ነበረች። ከጣሊያን ወረራ በኋላም ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ በሁለት መሠረታዊ ነገሮች ምክንያት፥ ጋዜጣቸውን “አዲስ ዘመን” ብለው እንደሰየሙ፥ በእርግጥም አዲስ ዘመን፤ ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ይፈጠራሉ ብሎ የጠበቁ ብዙ መሆናቸውን ብሎ መገመት አስቸጋሪ አይመስለኝም።

    ለአምስት ዓመታት በእንግሊዝ ሀገር በስደት ሲኖሩ ስለራሳቸው ስህተትም ሆነ የሰለጠነው ዓለም ንጉሦች እንዴት ሕዝቦቻቸውን እንደሚመሩና በዚያም ምክንያት በሕዝቦቻቸው ዘንድ ተከብረው እንዴት እንደሚኖሩ ተምረዋል ብሎ መጠበቅ ይቻል ነበር። ከሁሉም በላይ በጣሊያን ወረራ ምክንያት እሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ከገጠመው ውርደትና ኪሳራ ይማራሉ ተብሎ ይጠበቅም ነበር። ከሁሉም አልተማሩም። በባሰ ሁኔታና ፍጥነት ወደ ድሮአቸው ተመለሱ። ለዓቢይነት፥ አስተዳደራቸውን የተቃወሙ የራያ ገበሬዎችን (ቀዳማይ ወያኔ የሚባለዉ ነዉ) ከየመን በመጡ የእንግሊዝ አይሮፕላኖች አስደበደቡ። የሪፐብሊካን አስተሳሰብ ነበራቸው የሚባሉትን አርበኛ ደጃዝማች ታከለን (ደጃዝማች ታከለ ወልደሀዋርያት) አሰሩ። እኚህ ሰው ከተደጋጋሚ እስር በኋላ በመጨረሻም ሊይዟቸው ከተላኩ የንጉሡ ወታደሮች ጋር ሲዋጉ ሞቱ። ሌላው ስመጥር አርበኛ የነበሩ በላይ ዘለቀንም ያለርህራሄ ሰቀሉ።

    የአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ግልፅ ደብዳቤ እንኳን (አምባሳደር ብርሃኑ፤ በአሜሪካ አምባሳደር የነበሩና ንጉሡ የገፉበት መንገድ ዉሎ አድሮ ንጉሡንም ሆነ ሀገሪቷን ለዉርደት እንደሚያበቃ የመጀመሪያ የማስጠንቃቂያ ደወል በአደባባይ የሰጡ ባለስልጣን ነበሩ) አሠራራቸውን አላስለወጧቸውም።

    በፖለቲካ ሥርዓታቸው ላይ በተከታታይ ቦንቦች ፈነዱ። የመጀመሪያዉ ትልቁ ቦንብ በራሳቸው ቤተ መንግሥት ውስጥ የፈነዳው የነመንግሥቱ ንዋይ ያውም የእሳቸውን ክብርና ሞገስ ለመጠበቅ ከፈጠሩት የክብር ዘበኛ ጦር ነበር። ንጉሡ ከክስተቱ ከመማር ይልቅ ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይን በሞት ቀጡ፤ የታናሽ ወንድማቸውን ሬሳ እኔን ያየህ ተቀጣ በሚመስል መንገድ በስቅላት ቀጡ። የበሉበትን [ወጭት] ሰባሪዎች ናቸው ብለውም በአዝማሪ አዘለፏቸው።

    ማን እንደመከራቸው ባይታወቅም ትልቁን የመንግሥታቸውን የዲፕሎማሲ ውጤትን ያበላሸውና ለትልቅ ኪሳራ ያበቃንን የኤርትራን ፌዴሬሽንን አፈረሱ። ውጤቱም ሁላችንም እንደምናውቀው የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር መፈጠር ሆነ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ኦሮሞዎች የሜጫና ቱለማ ልማት ማኅበር በመፍጠራቸው ጠገቡ ተብሎ መሪዎቹ እነ መቶ አለቃ ማሞ መዘምር ተሰቀሉ፤ ኃይለማርያም ገመዳ እስር ቤት ውስጥ በተፈፀመበት ድብዳባ ሞተ። ጀኔራል ታደሰ ብሩ ሞት ተፈርዶባቸው በአማላጅ ወደ ሐረርጌ በግዞት ተላኩ። እኔ እስከ ማውቀው ድረስ ሁሉም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጥያቄ አልነበራቸውም። ውጤቱ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን መፍጠር ሆነ። በነገራችን ላይ በእነ ኤሌሞ ቅልጡ በኦነግ ስም የመጀመሪያዋ ጥይት የተተኮሰችው ጀኔራል ታደሰ ብሩ የታሰሩበት ሥፍራ ሐራርጌ ዉስጥ ነበር። በዚሁ ጊዜ ሰፋፊ ማኅበራዊ ፍትህን የሚጠይቁ ተከታታይ ጥያቄዎችም መቅረብ ጀመሩ። እ.አ.አ በ1965 የንጉሡ ፊውዳላዊ ሥርዓት የተመሠረተበት ላይ በመሬት ላራሹ ሰልፍ ድንገተኛ የፖለቲካ ቦንብ ፈነዳ። ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ እስከዛሬ ኢትዮጵያን እያመሰ ያለው በእነ ዋለልኝ መኮንን የብሔረሰቦች ጥያቄ ታወጀ። ይህችኛውን ንጉሡና ሥርዓቱ በቀላሉ የተመለከቷት አይመስልም። ንጉሡ የቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ፥ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዝደንት የነበረውን ጥላሁን ግዛዉን በማሰገደል “ልጆቼ” ከሚሏቸው ተማሪዎች ጋር ደም መቃባት ዉስጥ ገቡ። በዚህም የታሪክ ጎማው ወደፊት እንዳይሽከረከር ጣሩ።

    አሳዛኙ ጉዳይ መካሪዎቻቸውም ሆኑ እሳቸው አስተዳደራቸው ለሃያኛዉ ክፍለ ዘመን የማይመጥን መሆኑን፣ በጣም እወዳታለሁ የሚሏትም ኢትዮጵያ በታሪክ ፍራሽ ላይ ተኝታ የምትሸሞነሞን ሀገር መሆኗን አልተረዱም። የኤርትራ ግንባሮች ጥይትም ከረጅም ዘመን እንቅልፋቸው አላነቋቸውም። የባሌና የጎጃም ሕዝብ አመፅም አልቀሰቀሳቸውም። ለዓመታት የቆየው የተማሪዎች ንቅናቄ ጩኸትም አላነቃቸውም። ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በቀጥታ የወጡ የመኢሶንና የኢህአፓ የሶሻሊስት አብዮት ደወልም አላነቃቸውም። በመጨረሻም በመቶ ሺዎች የሚቆጠረው የወሎ ሕዝብ እልቂት እንኳን ከእንቅልፋቸዉ አላበነናቸውም።

    በነገራችን ላይ፥ ብልጡ ደርግ በጠዋቱ ሊያወርዳቸው፣ ማታ ያሳየው የወሎ ሕዝብ እልቂት፥ በአንድ በኩል የንጉሡ ውሻ በጮማ ሥጋ ሲጫወት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በረሃብ በተረፈረፈ ሕዝብ ውስጥ ሕፃን ልጅ የሞተች እናቷን ጡት ስታጠባ የሚያሳየዉን የጆናታን ዲምበልቢ (Jonathan Dimbleby, “The Unknown Famine”) ፊልም ነበር። ያንን ፊልም ደርግ በቅድሚያ ንጉሡና የኢትዮጵያ ሕዝብን እንዲያዩ ስለጋበዘ ቴሌቪዥን ያልነበረን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በስድስት ኪሎና አራት ኪሎ አካባቢዎች ያሉትን ቡና ቤቶችን አጣብበን ስንመለከት ነበር። የንጉሡ ደጋፊዎች እንኳ ጃኖሆይ እንዲህ ጨካኝ ነበሩ እንዴ? የሚሉትን ይዘን ወደ ዶርማችን እንደገባን ትዝ ይለኛል። ምናልባት ከእንቅልፋቸው የነቁት በማግስቱ የደርግ አባላቱ በኩምቢ ቮልስዋገን ከቤተ መንግሥታቸው ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ሲወስዷቸው በሠሩባቸው ድራማ ይመስለኛል። ብልጣብልጦቹ ደርጎች የተጠቀሙት ቮልስ መጀመሪያ መስኮቷ ዝግ ነበር ይባላል።

    ንጉሡ ከውጭ ብዙ ሰው ሲጮህ ተመልክተው፥ “እናንተ ልጆች የሚወደን ሕዝባችን ንጉሤን የት እየወሰዳችሁ ነው እያለ ነዉ” ሲሉ፥ ብልጦቹ ደርጎችም መስኮቱን ከፍተው የሕዝቡን ድምፅ ሲያሰሟቸው ጩኼቱ “ተፈሪ ሌባ፤ ተፈሪ ሌባ” የሚለውን ሰምተው፥ “አይ ኢትዮጵያ ይኼን ያክል በድዬሻለሁ እንዴ?” አሉ ይባላል። በዚህ ሽኝታቸው ድሮ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ዳቦ የሚጥሉላት ለማኝ ዳቦዋን ስትጠብቅ፥ ‘ንጉሡ ወረዱ፤ ንጉሡ ወረዱ’ ሲባል ሰምታ፥ ‘ለዚህ ያበቃኸኝ አንተ ነህ!’ ብላ በቮልሷ አቅጣጫ የወረወረችው ዳቦ ብቻ ነበር ይባላል። የንጉሡ ሬሳም ከ17 ዓመታት በኋላ ከመንግሥቱ ኃይለማርያም ሽንት ቤት ሥር ተቆፍሮ እንደተገኘ ይታወቃል። እዚህ ላይ ልብ አድርገን ማለፍ ያለብን የፖለቲካ ቁም ነገር ለ60 ዓመታት ገደማ (የአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ እንዳለ ሆኖ) በፈላጭ ቆራጭነት ኢትዮጵያን ሲገዙ የሀገረ መንግሥታቸው ግንባታ ፕሮጀክት በአጉል ምክርም ይሁን በራሳቸው ገታራ አቋም ከሽፎ ሽኝታቸው በለማኟ ዳቦ፣ ቀብራቸው ደግሞ በአሳደጓቸው ወታደሮች ሽንት ቤት ሥር መሆኑ ነው።

    3) አብዮቱ እና የደርግ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሙከራ

    አዲስቷን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሕዝባዊ አብዮቱ ልዩ ዕድል ፈጥሮ ነበር። አብዮቱ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የመጡ የአዲሱ ትዉልድ ምሁራን ድጋፍና ተሳትፎ ነበረው። እንደ አብዮቱ መሪ ወደፊት የመጣውን መንግሥቱ ኃይለማርያምም ‘ቪቫ መንግሥቱ፣ ቪቫ መንግሥቱ!’ ብለን ተቀብለን ነበር።

    የኢትዮጵያ አብዮትን አብዮት ያደረገው የጭሰኝነት ሥርዓትን ያስወገደውና የደርግ እርምጃ (ውለታው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ቢሆንም) እስከዛሬ በኢትዮጵያ የሕዝቦች የትግል ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ አለው ብዬ ባምንም፥ ነገሮችን በቶሎ የሚያዩ ወጣቶች “ተፈሪ ማረኝ፤ የደርጉ ነገር አላማረኝ ” ማለት የጀመሩት ብዙዉም ሳይቆዩ ነበር። በአጭሩ ለማስቀመጥ፥ የደርግ የሥልጣን ፍቅር፣ የመኢሶንና የኢህአፓ አሳዛኝ ክፍፍል፣ የኤርትራ ግንባሮችና የህወሓት የተናጠል የፖለቲካ ፕሮጀክቶች በአብዮቱ መፈንዳት የተፈጠረውን ልዩ ታሪካዊ ዕድል አምክኖታል።

    ደርግ መሃይምነትና የሥልጣን ፍቅር ስለተደባለቀበት፥ የሶሻሊስት አብዮቱን እንደሰው ማሰርና መግደል ወሰደው። በዚህ ሶቭዬት ህብረት ድረስ ሄዶ የሌኒን ሐውልት አይተው የመጡት ባለሥልጣኖቹ ስለሶሻሊዝም የተማርነው ከበሰበሰ ከቡርዧ ቤተ መፃሕፍት ሳይሆን ከምንጩ ከሌኒን ሀገር ነው እያሉ ተዘባበቱ። ካደሬዎቻቸው ድንቅ የሶሻሊስት ዕውቀታቸውን ከፍተኛነት ለማሰየት በሚመስል መንገድ የስታሊን ቀይ በትር ሥራ ላይ ይዋል አሉ። ደርግ የሱማሌ ወረራን፣ የኤርትራ ግንባሮችና የህወሓት እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ አንድነት እንዲነግድ ልዩ ሁኔታ ስለፈጠሩለት “አብዮታዊት እናት ሀገር፥ ወይም ሞት!” አለ።

    ከኤርትራ ግንባሮች እስከ ኢህአፓ እና መኢሶን (ኢጭአት/ ኦነግን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች እዚህ መሃል ናቸው) የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነትና የአብዮት ጠላቶች ሆነው ልዩ ልዩ ስሞች ተለጣፈበቸው። በአጭሩ የኢህአፓና መኢሶን መከፋፈልም ደርግን ብቻኛ የሀገር አንድነትና የአብዮት ተወካይ አደረገው። ሌሎች ዝርዝሮችን ትቼ ለኢትዮጵያ አንድነትና አብዮት ግንባታ ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን ላንሳ።

    የደርግ የመጀመሪያው ሊቀ መንበር አማን አንዶም የሚባሉ ኤርትራዊ ጀኔራል ነበሩ። የደርግ ሊቀ መንበር ተብሎ ከደርግ ውጭ የተመረጠትም ለኢትዮጵያ አንድነት ብሎ እስከ ሞቃዲሾ ድረስ ሄዶ ካልተዋጋሁ ብሎ ንጉሡን ያስቸገሩ መኮንን ስለነበሩ ነዉ። በወታደሮቹ ዘንድም ተወዳጅ ስለነበረ በራሳቸው በደርግ አባሎቹ ጥያቄ መጀመሪያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ከዚያም ከደርግ ውጭ የደርግ ሊቀ መንበር የሆነው የተመረጡትና በአደባባይ እስከሚታወቀውም በኢትዮጵያ አንደነት ላይም (መቼም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ልዩ ፍቅር አለን የሚሉ ብዙ ቢኖሩም፥ ፍቅራቸውን የሚለካልን መሣሪያ በሜዲካል ሳይንስ እስካሁን አልተፈጠረልንም) ምንም ዓይነት ጥያቄ ያልነበራቸውና የኤርትራን ችግር በሰላም ለመፍታት አሥመራ ድረስ ሄዶ ሕዝቡን ያወያዩ ነበሩ። ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አለኝ የሚሉ እነሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ግን ጠረጠሯቸዉ፤ በታንክ እቤታቸው ውስጥ ገደሉት። በእኔ ግምት ውጤቱ የኤርትራና የኢትዮጵያን አንድነት መግደል ነበር። በዚህም ኤርትራ የደም ምድር ሆነች። ዛሬ እንዲህ ልንሆን የፈሰሰው የሰው ደም ዋጋም ሆነ ለጠፋው ሀብትና ንብረት ሂሳብ ለፈረደበት ታሪክ መተው ይመረጣል።

    የብሔራዊ አንድነት መንግሥትን ልታመጡብኝ ብሎ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሁለተኛውን የደርግ ሊቀ መንበር የነበሩትን ጀኔራል ተፈሪ በንቲን ከደጋፊዎቻቸው የደርግ አባላት ጋር ረሸናቸው።

    ኮሎኔል አጥናፉ አባተንም ቅይጥ ኢኮኖሚ ልታመጣብን ነው ብሎ መንግሥቱ ኃይለማርያም በፀረ-አብዮታዊነት ረሸነዉ። በነገራችን ላይ የመጨረሻ ጭንቅ ሲመጣ መንግሥቱ ኃይለማርያም የአጥናፉን ቅይጥ ኢኮኖሚ ላይ ለመንጠላጠል ሞክሮ ነበር።

    በዛሬው የኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ልዩ ሥፍራ ያላቸው ጀኔራል ታደሰ ብሩ ለሁለተኛ ጊዜ ሞት ተፈርዶባቸው ተረሸኑ። እኔ መከታተል እስከቻልኩ ድረስ ታደሰ ብሩ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ፍጹም ጥያቄ ያልነበራቸው፤ ለኢትዮጵያ ብሎ ከሰላሌ ጫካ እሰካ ሞቃዲሾ ድረስ ተወስደው የታሰሩ እንግሊዞች ኢትዮጵያን ነፃ እናወጣለን ብለው ሲመጡ ከነሱ ጋር እየተዋጉ የመጡ አርበኛ ነበሩ። ከተራ ወታደርነት እስከ ጀኔራል ማዕረግ ድረስ ሀገራቸውን ያገለገሉም ነበሩ። እግር ጥሏቸው አብዮቱ ውስጥ የገቡት መንግሥቱ ኃይለማርያም ያላርህራሄ ገደሏቸዉ። በነገራችን ላይ ከጀኔራል ታደሰ ብሩ ጋር በፀረ አንድነት ክስ የተገደለ፣ ብዙ ሰው የማያስታውሰው መለስ ተክሌ የሚባል በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪ መሪዎች አንዱ የሆነ የትግራይ ተወላጅ ነበር (በጊዜዉ ከነበረዉ አቋም ተነስቼ፥ ይህ ሰው ቢቆይ ኖሮ የትኛው ድርጅት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ዶክተር አረጋዊን ደግሜ መጠየቄን አስታውሳለሁ)። ይህ ሰዉ ሌላ ተከታይ ቢያጣ ለሩብ ምዕተ ዓመት አከባቢ የምኒልክ ቤተ መንግሥትን ተቆጣጥሮ በፈላጭ ቆራጭነት ሀገሪቷን የገዛው ለገሠ ዜናዊ ስሙን አንስቶ ትግራይ በረሃ ገብቷል። ይህም ደርግ በኢትዮጵያ አንድነት ስም ያመጣብን የታሪክ ዕዳ ነው።

    በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳልነበራቸው በተሻለ የማውቃቸውን የመኢሶን መሪዎችን ላንሳ። ለሥልጣን ተብሎ በደርግና ብዙ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ዘንድ እንደ ኦሮሞ ድርጅት፥ በኦሮሞ ደግሞ እንደነፍጠኛ ድርጅት የሚታየው መኢሶን በዘመኑ በየትኛውም ሚዛን የተሻለ ትምህርት የነበራቸው መሪዎች ነበሩት፤ በስብጥራቸውም ኤርትራዊ የዘር ግንድ አላቸው ከሚባሉት ኅሩይ ተድላ እና አበራ የማነአብ እስከ ሲዳማው እሼቱ አራርሶ የነበሩበት ነው። ሽኩሪ የሚባል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አብረን የነበርነው ልጅ በስተቀር ሰፊ ተሳትፎ እንደልነበራቸዉ የማዉቀዉ የሱማሌ ምሁራንን ብቻ ነበር።

    የመጀመሪያዉ የመኢሶን ሊቀ መንበር የሰሜን ሸዋ አማራ ከሚባለው የተወለዱ፥ ዶ/ር ወርቁ ፈረደ፣ ሁለተኛው ኃይሌ ፊዳ፣ ሦስተኛው የወሎ አማራ ከሚባለው የመጡ ዶ/ር ከበደ መንገሻ ነበሩ። ሕብረ ብሔር ነን፤ ለሀገረ- መንግሥት ግንባታው የተሻለ ግንዛቤም እዉቀትም አለን ለሚሉ የመኢሶን ምሁራንም ደርጎች ርህራሄ አላደረጉም። በተለይ የመጀመሪያው የኦሮሞ የምሁር ትዉልድ የሚባሉት ኃይሌ ፊዳን ጨምሮ አብዱላህ ዩሱፍ፣ ዶ/ር ከድር መሀመድ፣ ዶ/ር ተረፈ ወልደፃዲቅ፣ ዶ/ር መኮንን ጆቴ የመሳሰሉት ሕበረ ብሔር በሚባለው መኢሶን ውስጥ አልቀዋል። በእኔ እምነት ብዙዎች ሊቀየሙኝ ቢችሉም፥ እንደስማቸው በኢትዮጵያ ምድር ሕብረ ብሔር የነበሩ ድርጅቶች መኢሶንና ኢህአፓ ብቻ ነበሩ። አላስፈላጊ ክርክር ዉስጥ ሳልገባ፥ እኔ እስከ ማምነው ድረስ ኢሠፓ የወታደሮች ፓርቲ ነበር። የኢህአዴግን ምንነት ለብልጽግና አበላት እተዋለሁ። የብልጽግናን ምንነት ደግሞ የታሪክ ፈተናዉን ሲያልፍ ብንነጋገርበት የተሻለ ይመስለኛል።

    ደርግ ሕበረ ብሔር ድርጅቶችን በቀላሉ አንድ በአንድ ቀርጥፎ በላቸው። ኢህአፓን ቁርስ አደረገ፤ መኢሶንን ምሳ አደረገ:: ብሔር ሆኖ ለመውጣት ገና ዳዴ የሚሉትን ወዝሊግንና ማሌሪድን እራት አደረጋቸው። ከደርግ ዱላ የተረፉት በደርግ አስተዋጽኦ ጭምር በተሸለ ሁኔታ ኃይል ሆነዉ የወጡት የብሔር ንቅናቄዎች ናቸው። ኢጭአት (የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል) ወደ ኦነግ ተጠቃልሎ ገብቶ ዛሬ የምናውቀው ኦነግን ፈጠረ። የሱማሌ ድርጅቶች ኦብነግ ዓይነትን ፈጠሩ። የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ቢያንስ ዋናው ክንፍ ዛሬ ሲአን (የሲዳማ አርነት ንቅናቄ) የሚለው ሆነ። አፋሮችም የአፋር ግራ ክንፍ አርዱፍ እያሉ በሕይወት ያሉ ድርጅቶች አሏቸው። በጣም የተሳካላቸው የብሔር ንቅናቄዎች በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ደርግን ለሁለት ቀብረው መንግሥታት ሆኑ።

    የደረግ ዘመንን ስናጠቃልል መረሳት የሌለባቸው ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች፥ ለሥልጣን ብሎ ደረግ ባካሄዳቸው ጦርነቶች፡-

    የሀገረ-መንግሥት ግንባታውን የበለጠ አወሳስቦ መሄዱን፣
    ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በፃፉት መጽሐፍ በትክክል እንዳስቀመጡት፥ ደርግ ትቶት የሄደው በደም እምባ የታጠበች ሀገር መሆንዋን፣
    በሀገር አንድነት ስም ባካሄደው ትርጉም-የለሽ ጦርነት የባከነው የሀገር ሀብት ብቻ ሳይሆን በዓለም ትልቋ ወደብ-አልባ ሀገር ኢትዮጵያን ትቶ መሄዱን ነዉ።

    ደርግ ለ17 ዓመታት የተጫወተዉ የአጥፍቶ መጥፋት ፖለቲካን እንደ ኑዛዜም፣ እንደ ቁጭትም የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ (ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርምም ሆነ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ እድፋቸውን ከታጠቡበት በጣም ይሻላል) በፃፉት መጽሐፍ ልዝጋ።

    የኢህአፓ ወጣቶችን የትግል ስሜት፣ የመኢሶን መሪዎች ዕውቀትና የእኛን የወታደሮቹን የሀገር ወዳድነት ብንጠቀምበት ኖሮ ሀገራችን እንዲህ አትሆንም ማለታቸውን እስር ቤት ሆኜ ማንበቤ ትዝ ይለኛል። ምክራቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይም የሚሆን ይመስለኛል። በነገራችን ላይ በታሪክ አጋጣሚ ወደ አስር ወሮች ገደማ በኢህአዴግ እስር ቤት የተኛሁበት አልጋ ኮ/ል ፍስሃ ደስታ ይተኙበት እንደነበረ ሰምቻለሁ።

    4) የኢህአዴግ ዘመን የሀገረ-መንግሥት ግንባታ

    ለአራተኛ ጊዜ የሀገራችን ፖለቲካን ማሰልጠንና የተሻለ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዕድል ያመለጠን የኢህአዴጉ ዘመን ነው (ይህ የመለስ እና የኃይለማርያም ዘመንን ይጨምራል)። የኢህአዴግ ዘመን ሌላው ቢቀር የብሔረሰቦች ጥያቄን ለሁሉም ሕዝቦች ተቀባይነት ባለው መንገድ ይመልሳል ብሎ (እኔን ጨምሮ) የጠበቁ ብዙ ናቸው። ይህም ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የተሻለ ዕድል ይፈጠራል ተብሎም ተገምቶ ነበር።

    ገና የሽግግር መንግሥቱ ሲመሠረት፥ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት እንደግል ሠርጋቸው የፈለጉትን ጠርተው፣ ያልፈለጉትን በመተው የሠሩት የፖለቲካ ቲያትር ጫካ ሆነው ስደግፋቸው ከነበሩት የኢህአዴግ መሪዎች ተለየሁ። እኔም ብቻ ሳልሆን ብዙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጓደኞቼ በዚህ ጊዜ የተለዩዋቸዉ ይመስለኛል። ኢህአዴግ መጀመሪያ በጦርኛነት፤ ቀጥሎ ደግሞ በዘመኑ ቋንቋ የሽብርተኝነት ታርጋ እየለጠፈ ለ27 ዓመታት ሕዝብና ሀገርን አመሰ። ዝርዝር ነገሮች ውስጥ ሳልገባ፥ በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች፤ በሲዳማ፣ በሀዲያ፤ በወላይታ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ ቁጥራቸውን የኢህአዴግ ባለሥልጣናት እንኳ የማያውቁት ሕይወት ጠፋ። የአፍሪካ መዲና የምትባለው አዲስ አበባ/ፊንፊኔም ሆነች የኢህአፓን ጠበል በቀመሱ ብአዴኖች የሚመራው የአማራ ክልልም ውሎ አድሮ ከኢህአዴግ ዱላ አልተረፉም።

    በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም (ነገርየው መሬት ላይ ሲፈተሽ፥ የአብዮታዊነትም የዴሞክራሲያዊነትም ባህርይ አልነበረውም) የተተበተበው የሞግዚት አስተዳደር እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት ሊሆን አልቻለም። የሕዝቦችን እራስን በራስ ማስተዳደር ጋር ምንም ግንኙነት ያልነበረው፥ ጆርጅ ኦርዌል የእንስሳት እርሻ (George Orwell, “Animal Farm”) በሚለዉ መጽሐፉ ላይ፥ ሁሉም እንስሶች እኩል ናቸው፤ አንዳንድ እንስሶች የበለጠ እኩል ናቸው “All animals are equal, but some are more equal than others” ከሚለው ያለፈ የፖለቲካ ፋይዳ አልነበረውም። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተብዬዎቹም ከ97ቱ በስተቀር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር ይቅርና ቅርጫ እንኳ ሊ ሆኑ አልቻሉም። ዉጤቱም ዴሞክራሲያዊ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዕድል መጨናገፉ ብቻም ሳይሆን ለ27 ዓመታት ውድ የሕይወት ዋጋ ጭምር ሲያስከፍለን ኖሯል። በዚህም ምክንያት የታሪክ ጣጣችንን አስተካክለን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም የመፍጠር ተስፋችን ሕልም ሆኖ ቀርቷል።

    5) በማምለጥ ላይ ያለ አዲስ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሙከራ

    አሁን እየገጠመን ያለውን የታሪክ ፈተናን ለማለፍ፥ ጨክነን በቁርጠኝኘት ብሔራዊ መግባባት ውስጥ መግባት ወይም ኢትዮጵያን እንደ ሀገረ-መንግሥት የምታበቃበት የሚጨምር ቀውስ ውስጥ መግባት ይመስለኛል። እዚህ ላይ የሌሎች ሀገሮችን ፖለቲካ በድኅረ ቅኝ ግዛት ዘመን ብቻ እንኳን በመቀኛት ብጀምር፥ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በቁርጠኝነት የሠሩት ተሳክቶላቸዋል። ያንን ያልቻሉት ወይ ፈርሰዋል ወይም አሁንም በቀውስ ውስጥ እየዳከሩ ነዉ። ቅኝታችንን በላቲን አሜሪካ ብንጀምር፥ ቀዉስ ገጥሟቸዉ አነ አርጀንቲና፣ ቺሌ፣ ፔሩ፣ ኒካራጓ፣ ኮሎምቢያ የመሰሰሉ ሀገሮች በተለያየ ደረጃ ፖለቲካቸውን ያስተካከሉ ሀገሮች ናቸው። ከ60 ዓመታት በላይ ለልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ሳትበገር በአሜሪካ አፍንጫ ሥር የኖረችው አስደናቂዋ ሶሻሊስት ኩባና በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት አሁን በሁለት ፕሬዝዳንቶች የምትገዛዋ ሶሻሊስት ቬኔዙዌላም በዚሁ ክፍለ ዓለም ይገኛሉ። በአውሮፓ ፖርቹጋል፣ ስፓኝ፣ ግሪክ፣ ፖለቲካቸዉን ማስተካከል ችለዋል። ዩጎዚላቪያ ውድ ዋጋ ብትከፍልም ከመፍረስ አልደነችም። ሶቭዬት ህበረትና (ግማሽ አውሮፓ ነች) ቼኮዝላቫኪያ በሰላማዊ መንገድ ፈርሰዋል። በኤዥያ፥ ኔፓል የፓለቲካ ችግርዋን በብሔራዊ መግባባት ስትፈታ፥ፓኪስታን፣ ቬየትናም፣ ካምቦዲያና ላኦስ ደግሞ ችግሮቻቸውን በጦርነት ፈተዋል። አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያና የመን አሁንም እየቀወሱ ነው። ወደ አፍሪካችን ስንመጣ፥ ደቡብ አፍሪካና ጋና ከመሳሰሉት በስተቀር አብዘኛዎቹ በይስሙላ ምርጫ ላይ የተመሠረቱ አምባገነን መንግሥታት ሲሆኑ፥ የአፍሪካ ሕብረትም የዲክታተሮች ማኅበር (trade union of dictators) ከመሆን አላለፈም (በኢህአዴግ ጊዜ የተከሰስኩበት አንዱ ወንጀሌ የአፍሪካ መሪዎችን ተሰደብክ የሚል ነበር)። ሱማሊያና ሊቢያ ፈረንጆች የወደቁ መንግሥታት (failed states) የሚሏቸው ሲሆኑ፤ ሩዋንዳ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ሌላ ቦንብ የምትጠብቅ ይመስለኛል።

    በዚህ የአፍሪካ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞ ውስጥ አንዱ የሚገርመኝ ላለፉት 60 ዓመታት ፖለቲካቸውን ማስተካከል አቅቷቸው በቀውስ ሲናጡ የኖሩ ሁለት ሀገሮች፥ በተፈጥሮ ፀጋ እጅግ ሀብታሟ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑቢሊክና የሦስት ሺህ ዓመታት ዕድሜ አለኝ የምትለዋ ድሃዋ ኢትዮጵያ መሆናቸው ነው።  ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ይህንኑ የሀገራችንን የፖለቲካ እንቆቅልሾችን የተከታተለ፣ ያጠና፣ ያስተማረና ብዙ ጽሑፎችን የፃፈበት ጆን ማርካከስ (John Markakis) የሚባል ፈረንጅ፥ የታሪክና ፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሴር “Ethiopia: The Last Two Frontiers” (የኢትዮጵያ፥ የመጨረሻዎቹ ሁለት ድንበሮች) ብሎ ፅፏል። ምሳ ጋብዞኝ መፅሐፉን ለዶ/ር ዓቢይ ስጥልኝ ብሎኝ፥ ዶ/ር ዓቢይ ያንብበው አያንብበው ባላውቅም፥ እሳቸውን ማግኘት ለሚችል ለኦፒድኦ ባለሥልጣን ልኬላቸው እንደነበርም አሰታዉሰለሁ። መፅሐፉ በአጭሩ የኢትዮጵያ መሪዎች የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የንጉሦቹ ሞዴል (the Imperial model) ፣ የደርግ የሶሻሊስት ሞዴልና የኢህአዴጉ ፌዴራሊስት ሞዴል በሙሉ ከሽፈዋል ይላል። የከሸፉበትም ዋናዉ ምክንያት የባለጊዜ ገዥዎችን ሥልጣን ለማሳካት የተገፋበት መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እኩልነት ያላጎናፀፈና የልማት ጥማታቸውንም ያላረካ በመሆኑ ነው ይላል።

    ይህ የፈረንጅ ምሁር እንዳለው፥ ፖለቲካችንን ማሰልጠን ባለመቻላችን ሚሊየኖች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ሚሊዮኖች ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፤ ሚሊዮኖችም ተሰደዋል። እኔም ከላይ ባነሳሁት ከዚሁ ምሑር ዕይታ ተነስቼ ሀገራችን ስለገባችበት የፖለቲካ ቅርቃርና በብሔራዊ መግባባት አንፃር ከቅርቃሩ ለማውጣት በሌኒን ቋንቋ ምን መደረግ አለበት (What is to be done?) የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ የሀገራችን ፖለቲካ እስከገባኝ ድረስ ልመልስ።

    1. መሠረታዊ ችግራችን በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣን ላይ የወጡ መሪዎቻችን ሀገርን የመምራት ሕልማቸው፤ ሥልጣንን ጨምድዶ ከመቆየት ሕልማቸው ጋር ሁሌ ስለሚጋጭባቸው ነው። ለሕዝብ አለን ከሚሉት ፍቅር የሥልጣን ፍቅራቸው ስለሚበልጥባቸው ነው። ለዚህ ነው ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የሚወደንና (ሕዝቡ ምን ያከል እንደሚወደቸዉ እንዴት እነዳወቁ ባናዉቅም) የምንወደው ሕዝባችን ሲሉ ኖረው ለ60 ዓመታት ገደማ የገዟትን ኢትዮጵያ ለ20ኛዉ ክፍለ ዘመን ሳያበቁ ከዓለም ሀገሮች ጭራ ደረጃ ትተዋት የሄዱት። የሕዝብ ፍቅራቸውንም ደረጃ በረሃብ በመቶ ሺህዎች ያለቀው የወሎ ሕዝብ ይመሰክራል። ይህን የመሳሰሉ የመሪዎቻችን ባዶ የሕዝብና የሀገር ፍቅር፥ የንጉሡ ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ፣ የመንግሥቱ ኃይለማርያም አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት የመለስ ዜናዊ በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገቡ ዜጎችን እፈጠራለሁ ወ.ዘ.ተ መሸፈን አይችልም። ለዚህ አሁን ያሉ መሪዎቻችንም ሆኑ ተስፈኛ መሪዎች ይህንን የታሪክ እውነታ በውል እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ።
    2. የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የተቀሩት ልሂቃን በተለያየ ደረጃ የሚጋጩ ሕልሞቻቸውን ይዘው መጓዛቸው ነው። ከመኢሶንና ኢህአፓ ዘመን እስከዛሬ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶቻችንና መሪዎቻቸው ይህንን እውነታ በውል መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የሕልሟን ጉዳይ በፈንጆቹ አባባል ከዜሮ ድምር ፖለቲካ (zero-sum game politics) የመውጣቱን ጉዳይና የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸዉን በገደብ የማድረጉን ነገር በጥብቅ እንዲያስቡበት እመክራለሁ። ዋና ጉዳያችን ሥልጣን ሆኖ ከፊንፊኔ እስከ መቀሌ ባንዳ፣ ባንዳ እየተባባሉ መካሰሱ ሕዝባችንን ከማደናገር በላይ ብዙ የፖለቲካ ትርፍ የለውም። ዛሬ በአሜሪካና በአውሮፓ በሚደረጉ ሰልፎች ላይ በአንድ እጅ እስክንድር ነጋ ይፈታ፣ በሌላ እጅ ጃዋር ሽብርተኛ ነው የሚሉት መፈክር ዓይነቶቹ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታችንም ሆነ ለብሔራዊ መግባባት ሥራችን ብዙ የሚጠቅሙ አይመስሉኝም። በእኔ በኩል እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ስላስቸገረኝ ነበር በ2008 በፃፍኩት መፅሐፍ ላይ ለቡዳ ፖለቲካችን መላ እንፈልግ ብቻ ሳይሆን የሚጋጩ ሕልሞች ሊታረቁ ወይስ ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ በሚል ግልፅ ጥያቄ የደመደምኩኝ። ለእኔ መፍትኼው ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ፈጠራ የሚሆን አዲስ ማኅበራዊ ውል (new social contract) ከመፈራረም ውጭ የተሻለ የማጂክ ፎርሙላ ያለን አይመስለኝም። ይህንን እውነታ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ያሉ የብልጽግና ወንድሞቻችንም ሆኑ ከአዲስ አበባ/ፍንፍኔም እስከ አውሮፓና አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ግፋ በለው የሚሉ ሁሉ እንዲረዱልኝ አደራ እላለሁ። በቅርብ ጊዜ በተፈጠረው ቀውስ በሁሉም በኩል ላለቁትም የተሻለ የሐዘን መግለጫ የሚሆነውና ዕንባቸውን የሚያብሰው የችግሮቻችን ምንጭ አዉቀን ዘለቂ መፍትኼ ስንፈልግ ይመስለኛል።
    1. ከላይ ካነሳኋቸው ሁለት ነጥቦች ጋር ተያይዞ ሺህ ጊዜ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እየተባለ በሕዝብ ላይ የሚሠራዉ የፖለቲካ ትያትር መቆም አለበት።
      የንጉሡ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የደርግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የኢህአዴግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ ሲያንሱ በዴሞክራሲ ስም የተቀለዱ  ቀልዶች፣ ሲበዙ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የተሠሩና ታሪክ ይቅር የማይላቸው ወንጀሎች ነበሩ። በሰለጠነው ዓለም የሕዝብን ድምፅ ከመስረቅ በላይ ወንጀል የለም። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን አስታውሼ ልለፈው። በ“ኢህአዴግ-1” ዘመን አቶ በረከት፥ “ኢህአዴግ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉትና በዝረራ ያሸንፋል” ብሎ ሲያስቸግረኝ፤ አቶ በረከት፥ “ኢህአዴግ ሁለት ምርኩዞች አሉት፤ አንደኛው ምርጫ ቦርድ ነው። ሁለተኛው ጠመንጃችሁ ነው። ሁለቱን ምርኩዞቻችሁን አስቀምጣችሁ ተቃዋሚዎችን ካሸነፋችሁ፥ እኔ በግሌ እናንተ የምትሉትን 20 ና 30 ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለሃምሳ ዓመታት እንድትገዙን እፈርምልሀለሁ” እንዳልኩት አሰታዉሰለሁ። በ“ኢህአዴግ-2” ጊዜ ደግሞ ዶ/ር ዓቢይ በጠሩት ድንገተኛ ስብሰባ ላይ ገለልተኛ የሆነው ጠቋሚ ኮሚቴ ስምንት ሰዎች አጣርቶ ስላቀረበ አራት ሰዎች መመረጥ ስላለባቸው በተጠቆሙት ሰዎች ላይ አስተያየት ስጡ አሉን። ሌሎች ስብሰባው ላይ የተገኙ የየድርጅት መሪዎች ያሉትን ብለዋል፤ እኔ ጨዋታው ስላላማረኝ፥ “አብዛኛዎቹን ዕጩዎች ብዙዎቻችን አናዉቃቸውምና ከየት እንደመጡ እንኳ ለማወቅ የ24 ሰዓት ጊዜ ስጡኝ” ብዬ አጥብቄ ጠየኩኝ። ዶ/ር አቢይ ‘አይቻልም’ አሉ። ነገ የምናገረው እንዳይጠፋኝና ለታሪክም ቢሆን ተአቅቦ (reservation) መዝግቡልኝ ማለቴ ትዝ ይለኛል። ምስክሮችም አሉኝ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች የምርጫ ጊዜውን ሰሌዳ ለማስተላለፍ በጠሩት የምክክር ስብሰባ ላይ እንደተናገርኩኝ፥ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት (divine intervention) ነው እንዳልኩኝ ምርጫው ባይተላለፍ ኖሮ የአዲሱ ምርጫ ቦርድ አካሄድ ሌላ ከበድ ቀውስ ሊያስከትል ይችል እንደነበረ ዛሬ ላይ ሆኜ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ይህንኑ ደግም ብዙ ጊዜ በታጋይነቷ ለምናውቃት ክብርት ብርቱካንም ጭምር መናገሬን አስታውሳለሁ።

    ስለሆነም የሚመጣውን ምርጫ አዲስቷን ዴሞክራትክ ኢትዮጵያ እንድትወለድበት ካላደረግን፥ የንጉሥ የማክያቬሊ ምክር፣ የመንግሥቱ ኃይለማርያም፣ የጆሴፍ ስታሊን ቀይ በትር፣ የመለስ ዜናዊ፣ የሊቀ መንበር ማኦ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ውሰት፣ ኢትዮጵያን ለመለወጥ የታሪክ ፈተናውን ለማለፍ እንዳላስቻላቸዉ፥ የዶ/ር ዓቢይም የመደመር የፖለቲካ ቀመር አዛውንቱ የፈረንጅ ምሁር የሚለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመጨረሻ ሁለት ድንበሮችን የሚያሻግረን አይመስለኝም። እሱን ካልተሻገርን ደግሞ ሁሌም እንደምለው ለሁላችንም የምትሆን ዴሞክራትክ ኢትዮጵያ የምትፈጠር አይመሰልኝም።

    ከማጠቃለሌ በፊት የብሔረታዊ መግባባቱ የፖለቲካ ጥረታችን ይሳካ ዘንድ መፍትሄ የሚሹ ቁልፍ ጉዳዮች ላስቀምጥ፦

    1. ያለ ሀገራዊ ስምምነት በዋናነት በአንድ ቡድን ሕልምና ፍላጎት (በተለይ የአንድ ቡድን ፍኖተ-ካርታ /road map/) የመመረቱ ጉዳይ ለዉጡን አጣብቂኝ ዉስጥ ማስገበቱን የማወቅ ጉዳይ፤
    2. ለውጡን ለማምጣት በዋናነት የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው ኃይሎች (ለምሳሌ እንደ ኦሮሞ ቄሮ ዓይነቶቹ) ወደ ዳር የመገፋታቸው ጉደይ፤
    3. ለውጡን እየመራ ያለው ከራሱ ከኢህአዴግ የወጣ ቡድን ቢሆንም፥ በለውጡ ምንነት፣ ፍጥነት፣ ስፋትና ጥልቀት ላይ የተለያዩ የኢህአዴግ ክንፎች ስምምነት ማጣታቸውና በዚህም ምክንያት እያመጣ ያለው አደገኛ ሁኔታ፤
    4. በሚጋጩ ሕልሞቻችን ምክንያት ላለፉት 50 ዓመታት መፍትሄ ያላገኘንለት የመከፋፈል ፖለቲካችን (political polarization) ጉዳይ፤
    5. ዴሞክራሲያዊ ለውጡ ለአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና የፓለቲካ ኃይሎች ተቀባይነት ያለዉ፣ ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን የጋራ ፍኖተ-ካርታ (roadmap) የመቀየስ አስፈላጊነት ጉዳይና፤ የተቀየሰዉን በጋራ ሥራ ላይ የማዋል ጉደይ፤
    6. ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማለት በእርግጥም በሕዝቦች ይሁንታ ላይ የተመሠረተ የፓለቲካ ጨዋታ መሆኑን የመረዳት ጉዳይ፤
    7. ሀገራችን እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ የፈድራል ሥርዓት ያስልጋታል ስንል፥ ከሕልሞቻችን በሻገር በሕዝቦቻችን ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የፖሊቲካ ሥርዓት መሆኑን የማረጋገጥ ጉዳይ፤
    8. ብሔራዊ መግባባቱ በተሻለ መንገድ የሚሳካው፥ በደቡብ አፍሪካ እና ኮሎምቢያ በመሰሰሉት ሀገሮች እንዳየነው የፖለቲካ እስረኞችንና የጫካ አማፅያንን መጨመርን የማስፈለጉ ጉዳይ፤
    9. የተሳካ ብሔራዊ እርቅን ለመምጣት ከሥልጣን በሻገር የምር የፖለቲካ ቁረጠኝነት (political will) የማስፈለጉ ጉዳይ፤
    10. ስለኢትዮጵያ አንድነት ያለን ግንዘቤ ከፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ እይታ የሰፋና ለሀገሪቷ ያለን ፍቅርም ገደብ የማድረጉ ጉደይ ናቸዉ።

    በመደምደሚያዬም፥ እዚህ ያደረሰንን የሀገራችንን ፖለቲካ ጉዞ ታሪክ ወደኋላ እያየሁ፥ የወደፊቱን የሀገራችንን ዕጣ ፈንታንም እያማተርኩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ለሁላችንም የታሪክ የግርጌ ማስታወሻ ልተዉ።

    በቅርብ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ኢትዮጵያን የሚያፈርሷት እኛን ቀድሞ ሲያፈርሱ ነው፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አይፈቀድላቸውም’ ሲሉ አዳምጫለሁ። ሀገርን ለመፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎች መጀመሪያኑ ፈቃድ ይጠይቃሉ፤ አይጠይቁም የሚለዉን ክርክር ውስጥ ሳልገባ፥ በጨዋ ቋንቋ ንግግራቸውን አልወደድኩላቸውም። ንግግራቸውንም ተከትሎ የኢሳት ቴሌቪዥን የፖለቲካ ተንታኞች የሚታወቁ የአዛውንት ምሁርን በመጥቀስ (ይህኑን ምሁር መንግሥቱ ሀይለማርያምም ያዉቃል ብለን ስለተሠሩ የንጉሡ ባለስልጣኖች ምክር ጠይቀነዉ፥ ጠመንጃዉ በእናንተ እጅ ነዉ፤ የምን ምክር ትጠይቁናላችሁ ብሎኛል ማለቱን አንብቤአለሁ) ዶ/ር ዓቢይ ጥሩ ይዘዋል፤ ሕጉንም ሰይፉንም እየተጠቀሙ ነው ያሉት የበለጠ ሥጋት ፈጥሮብኛል። እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሁላችንም ደጋግመን ማሰብ ያለብን ጨዋታው ከተበላሸ አብዛኛው ዓለምን በሰዓታት ውስጥ ወደ አመድነት የሚለወጥ ወይም ሕይወት-አልባ ሊያደርግ የሚችል የኒዩክሊየርር መሣርያ የታጠቀ፣ ነፍሷን ይማርና የሶቭዬት ህብረት ሠራዊት ዓይኑ እያየ ሀገራቸው መበቷን ነው። የሀገራችንን ፖለቲካ በጋራ አስተካክለን ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እግዚአብሔር ይርዳን እላለሁ።

    ዋቢ መፃሕፍት:

    1. Bahiru Zewde (1991) A History of Modern Ethiopia, 1885 -1991.
    2. Gebru Tareke (1996) Ethiopia: Power and Protest, Peasant Revolts in the Twentieth Century.
    3. John Markakis, (2011) Ethiopia: The Last Two Frontiers.
    4. Merera Gudina, (2002) Ethiopia: Competing Ethnic Nationalisms and the Quest for Democracy, 1960-2000.
    5. Teshale Tibebu, (1995), The Making of Modern Ethiopia, 1896-1974.

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forumsላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የታሪክ ዳራ… መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)

    #15549
    Semonegna
    Keymaster

    በሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጸመውን ግፍ እውነታ በመረጃ የማሳየትና ማስረዳት ግዴታ ሁላችንም አለብን
    (ነአምን ዘለቀ)

    ሰላም ወገኖቼ ኢትዮጵያውያን፦

    ሀገራችን ኢትዮጵያን ከምንም ችግር ለመታደግ የሚያስችል ከፍተኛ ብቃቱም የሀገር ፍቅሩም ያላችሁ አያሌ የኢትዮጵያ ልጆች በውጪው ዓለም ትኖራላችሁ። የኢትዮጵያ ችግር እንደሚያሳስባችሁና በጎዋ ደግሞ እንደሚያስደስታችሁም ግልጽ ነው። ነገር ግን አብዛኞቻችሁ በተለያየ ምክንያት የዳር ተመልካች መሆንን መምረጣችሁ ሀገራችንንና ወገኖቻችንን ብዙ ዋጋ እያስከፈለ እንደሆነ እያየን ነው። ሄዶ ሄዶ ያልተጠበቀና ከእስካሁኑም በከፋ ሁኔታ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ለማይወጡት አደጋ ለማጋለጥ እየተመቻቸን እንደሆነ ስጋቴን ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ።

    በኦሮሞ ጽንፍ ኃይሎች መሪነት የኢትዮጵያ ጥላቻ ያላቸው ባዕዳን እንዲሁም የህወሓት ዲያስፓራ ሚዲያዎችና ካድሬዎች በጋራ በመሆን የአሜሪካ፣ የካናዳንና የአውሮፓን የሕግ አውጪዎችና አስፈጻሚዎች በማወናበድ ጸረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ለማራመድ በስፋት ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ ። ይህም በሰፊው እየወሰዷቸው ካሉ በርካታ አፍራሽ እርምጃዎች እንዱ ብቻ ነው። እነኚህ ኃይሎች ያለማጋነን ላለፉት 27 ዓመታት የጸረ-ወያኔ ሁለንተናዊ የትግል ቆይታዬ ያላየሁትን ከፍተኛ የዓላማ አንድነት (unity of purpose)፣ ቅንጅትና መናበብ በመፍጠር ከዳር እሰከ ዳር እየሰሩ ለመሆናቸው ብዙ መረጃዎች ይገኛሉ።

    ከዚህ መልዕክት ጋር ያያያዝኩት የአሜሪካ ኮንግሬስ አባላት ለአሜሪካ ስቴት ሴክሬታሪ/የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ (Mike Pompeo) የጻፉት ደብዳቤ የዚህ ሴራ አንዱ ውጤት ነው። በተቀናጀ መልክ የሀገራችንን እውነታና ሂደት በማዛባት፣ የሃሰት ትርክቶችን በመደራረት የውጭ ኃይሎችንና መንግሥታትን ለማወናበድ ያለተቀናቃኝ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ይህን ማድረግ የቻሉት ደግሞ በእነሱ ጥንካሬ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት፣ ለፍትህ፣ ለሕዝብ እኩልነት፣ ለሕግ የበላይነት ቀናዊ የሆነው ኢትዮጵያዊ ጎራ (silent majority) የተበታተነ መሆኑና የሚያምንበትን የሀገርና ሕዝብ አንድነት እውን ለማድረግ የድርሻውን ለመወጣት ቁርጠኛ አለመሆኑ ነው።

    “ነፍጠኛን ምታ፣ አቃጥል፣ ግደል፤ ቁረጥ” የሚሉ ያልተቋረጡ የጥላቻ ዘመቻዎች በሶሻል ሚዲያና በኦኤምኤን (OMN) ሚዲያ እንደሚክያሄድ ታውቃላችሁ ብዬ አምናለሁ። የዚህ ዘመቻ ውጤትም ብዙ መቶ ወገኖቻችን በኦሮሞ ጽንፈኞች አርመኔያዊ በሆነ መንገድ መጨፍጨፍ ነው። ይህም ግፍ በቅድመ ጄኖሳይድ (pre-genocide) ደረጃ የሚመደብ የዘርና የሃይማኖት ተኮር ፍጅት ነው ማለት ከእውነቱ የራቀ አይደለም። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ይህን ሀቅ በመካድ አፈናቃይና ገዳዮቹ በተገላቢጦሽ ከሳሽ በመሆን “መንግሥት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚያደርገው አፈና” ያለ በማስመስል የተቀናጀ የሀሰት ትርክት በማሥራጨት ላይ ይገኛሉ። ዓላማቸውም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አመንስቲ (Amnesty) እና ሂውማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን፣ የአሜሪካ፣ የአውሮፓና፣ የካናዳ የሕግና የፓሊሲ አውጪዎችን ከጎናቸው ለማሰለፍ ሲሯሯጡ ይታያሉ።

    በአሜሪካና በአንዳንድ ሀገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ይህን የሀሰት ትርክት ለመለወጥ ጥረት ያደረጋሉ። ነገር ግን አብዛኞቹ ኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አደጋውን መመከት በሚቻልበት ልክ የአቅምና ፓለቲካ ቁርጠኝነት ይዘው ሲንቀሳቀሱ አይታዩም። ከዚህ ከተያያዙት የተመልካችነትና ተከላካይነት ውሱን እንቅስቃሴ አልፈው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና፣ የየሀገሩን የፓሊሲና የሕግ አውጪዎችን እውነታውን ለማስጨበጥ በቂና አጥጋቢ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

    ይህ በጽንፈኞች የተቀነባበረ ርብርብና ዘመቻ በጊዜ ካልተገታ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የያዘውን መንግሥት እየቦረቦረ እንዳያዳክመው ስጋት አለ። ከህወሓት እስከ ኦነግ ሽኔ በተለያዩ አፍራሽ ኃይሎች ተወጥሮ የሚገኘው በዶ/ር ዓብይ አህመድ የሚመራው መንግሥት ከተዳከመ ሀገሪቷን ለትርምስ፣ ለሁከትና ሌላም የከፋ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል። ስለዚህም እንደሕዝብና ሀገር ከፊታችን የተደቀነውን አደጋ በቀላሉ ማየት የለብንም።

    አደጋው በጣም የሚያስፈራው ደግሞ ቅራኔው በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ብቻ መሆኑ ቀርቶ የ27 ዓመቱ የጥላቻ ቅስቀሳ ስር ሰዶ ሕዝብ አቃቅሯል። በየጊዜው የምናየው ግድያ፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም የዚህ የጥላቻ ፖለቲካ ውጤት ነው። “ብሔር ለብሔር” ቅራኔዎችና ግጭቶችን እነማን ለምን ዓላማ ሲያራግቡ፣ ሲደግፉና ሲቆሰቁሱ እንደነበሩና ዛሬም ድረስ ያማያርፉበት፣ የሚተጉበት መሆኑን ሁላችንም የምናውቅም ይመስለኛል።

    እነዚህን የውስጣዊና የውጭ ከባድ አደጋዎች ድምር ለመግታትም በተደራጀ መልክ በካናዳ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ የተናበቡ ሥራዎች መሥራት ግድ ይላል። ለየሀገራቱ የሕግ አውጪ (lawmakers) እና የሥራ አስፈጻሚ/የፓሊሲ ወሳኞች (policymakers) በሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጸመውን ግፍ እውነታ በመረጃ የማሳየትና ማስረዳት ግዴታ ሁላችንም አለብን። ስለዚህም ሁላችንም በየሀገሩና በየከተማው መሰባሰብ፣ መነጋገር፣ መተባበር፣ መቀናጀትና ጠንካራ የአድቮኬሲ ቡድን (advocacy group) ማቋቋም ይኖርብናል። ከዛሬ ሁለት ወር በፊት ገደማ በሀገርና በሕዝብ ላይ የመጣው አደጋ አሳስቧቸው የተሰባሰቡ በርካታ ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፡ የፓለቲካ፣ የአድቮኬሲ፣ የድርጅታዊ ልምድና ተሞከሮ ያላቸው ኢትዮጵያውን የሚገኙበት ዓለም ኣቀፍ ኔትዎርክ እገዛ ያደርግላችኋል። ይህን መሰል እንቅስቃሴ የምታደርጉ ለማድረግ የተዘጋጃችሁ ሁሉ፣ አሰፈላጊውን የሰነድ፣ የምክር፣ የአቅጣጫ ድጋፍ ልናደርግላችሁ ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ስለሆን በውስጥ መስመር (messenger inbox) ልታገኙን ትችላላችሁ።

    ነአምን ዘለቀ
    bit.ly/NeaminZeleke

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ-ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    በሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጸመውን ግፍ እውነታ በመረጃ የማሳየትና ማስረዳት ግዴታ ሁላችንም አለብን

    #15559
    Semonegna
    Keymaster

    አቶ ልደቱ አያሌው ለፍርድ ቤት ያቀረበው የሕግ መከራከሪያ ነጥብና የፍትህ ሥርዓቱን ውድቀት ያሳየበት ልብ የሚነካ ንግግር*

    ክቡር ፍርድ ቤት፥

    ለመጀመሪያ ቀን በዚህ ችሎት ላይ ስገኝ ከችሎቱ ጀርባ የተፃፈውንና “ተልዕኳችን የሕግ የበላይነትን በማስከበር አርዓያ መሆን ነው” የሚለውን ሳነብ እና ከአሁን ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ ተከስሼ ነፃ ያወጡኝ ፍርድ ቤቶች በመሆናቸው እውነተኛ ፍትህ ከዚህ ችሎት አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። ዛሬ ግን በዚህ ችሎት ፊት የተገኘሁት ሕጋዊ ግዴታዬን ለመወጣትና ለችሎቱ ያለኝን አክብሮት ለመግለፅ እንጂ፥ ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ተስፋ በማድረግ አይደለም። ክቡር ፍርድ ቤት፥ ይህንን ማለት የተገደድኩት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው።

    1ኛ. ለፖሊስ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የሚሰጠው በምርመራ ሂደቱ ላይ ያሉት ለውጦች በዳኞች እየተመዘኑ ቢሆንም፥ እስካሁን በቀረብኩባቸው አራት ችሎቶች ጉዳዩን ያዩት አራት የተለያዩ ዳኞች በመሆናቸው ምንም ዓይነት የምርመራ ውጤት ለውጥ በሌለበት ሁኔታ ተከታታይ የጊዜ ቀጠሮ እየተሰጠብኝ ያለው ከሕጉ መንፈስ ውጭ በመሆኑ፤

    2ኛ. ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ቀጠሮ እንዳለኝ፣ በአሁኑ ወቅትም ከፍተኛ የልብ ህመም ታማሚ እንደሆንኩ፣ ከህመሜ ጋር በተያያዘም በኮቪድ-19 ቫይረስ ብጠቃ ህይወቴ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል የሕክምና መረጃ አቅርቤ እያለና በፖሊስ የቀረበብኝ ክስ የዋስትና መብት የማያስከለክል ሆኖ እያለ ያለ አግባብ የዋስ መብት ተከልክያለሁ። ክቡር ፍርድ ቤት፥ ከምገኝበት አሳሳቢ የጤና ችግር በእስር ላይ ከምገኝበት ለኮሮና እጅግ ተጋላጭ የሆነ እስር ቤት አንፃር የተከለከልኩት የዋስትና መብት ሳይሆን የሰው ልጅ መሠረታዊ መብት የሆነውን በህይወት የመኖር መብቴን ነው። ይህም የሚያሳየው ገና ወንጀለኛ ተብዬ ሳይፈረድብኝ የሞት ፍርድ የተፈረደብኝ መሆኔን ነው፤

    3ኛ. በዚህ በተከበረው ፍርድ ቤት ፊት አሁን እየተከራከርን ያለነው አንድ መንግሥት እና አንድ ዜጋ አይደለንም። በሕጉ መሠረት ከሳሽና ተከሳሽ ነን። ክቡር ፍርድ ቤቱ ለከሳሽና ለተከሳሽ መብት መከበር እኩል መቆም ሲገባው ሁል ጊዜ የከሳሽን ምክንያታዊ ያልሆነ ጥያቄ እየተቀበለ፥ በተቃራኒው ደግሞ የእኔን በመረጃ የተደገፈ ጥያቄ ውድቅ እያደረገ አድሏዊነት እየፈፀመብኝ በመሆኑ፤

    4ኛ. በአጠቃላይ በሀገር ደረጃ ያለውን ሁኔታ ስናይም፥ ፍትህ እየተሰጠ ያለው ከችሎት አደባባይ ሳይሆን ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት መሆኑን እያየን ነው። በወቅቱ የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በእስር ላይ የምንገኘው ዜጎች በብዙ ሺዎች የምንቆጠር ሆኖ እያለ፥ ልክ ሁላችንም አንድ ዓይነት ወንጀል እንደሠራንና ጉዳያችን በአንድ ዳኛና ችሎት ብቻ እየታየ እንደሆነ ሁላችንም የዋስ መብት ተነፍገን በተደራራቢ የጊዜ ቀጠሮ መብታችን በጅምላ እየተጣሰ ነው።

    ክቡር ፍርድ ቤት፥ እኛ ፍትህ የምንጠብቀው ከፍርድ ቤት እንጂ ከሳሻችን ከሆነው የአራት ኪሎ መንግሥት አይደለም። የአራት ኪሎ መንግሥት ኃላፊነት ሕግ ማስፈፀም ነው እንጂ ሕግ መተርጎም አይደለም። ክቡር ፍርድ ቤት፥ በአጠቃላይ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው አራት ነጥቦች የሚያሳዩት የሕግ ሳይሆን የፖለቲካ እስረኞች መሆናችንን ነው። አሁን በመጨረሻ ፖሊስ “የሽግግር መንግሥት ጥያቄ በማቅረብ መንግሥትን የመገልበጥ ሙከራ አድርጓል” በሚል ክስ ሲያቀርብብኝ መታየቱ ይህንን የሚያረጋግጥ ነው።

    በዚህ ሁኔታ እውነተኛ ፍትህ ይገኛል ብዬ ስለማልጠብቅ በጊዜ ቀጠሮ እየተመላለስኩ እኔና ጠበቃዬ አጉል ከምንጉላላ፥ ውድ የሆነው የፖሊስ እና የፍርድ ቤት ጊዜም ያለ አግባብ ከሚባክን- መቋጫ የሌለው የፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ እንዲቋረጥና ጉዳዩ የፖለቲካ ውሳኔ ሲሰጠውና ፖሊስ “ምርመራዬን ጨርሻለው” ባለ ጊዜ ከእስር ቤት ወደ ችሎት እንድቀርብ እንዲወሰን በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ።

    ምንጭ፦ ሀብታሙ አያሌው

    * አቶ ልደቱ አያሌው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ምክር ቤት ሲሆኑ፥ ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ፓርቲው በፕሬዝደንቱ አቶ አዳነ ታደሰ በኩል፥ አቶ ልደቱ አያሌው የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸውና ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንደታሰሩ ገልጾ ነበር። ይህንንም አስመልክቶ ፓርቲው ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ ልደቱ አያሌው

    #15604
    Anonymous
    Inactive

    የትግራይ ሕዝብ መከራ እንዲያበቃ ህወሓት ከነግሳንግሱ መወገድ አለበት!!
    በላይ አስመላሽ
    የተጋሩ አለማቀፍ ጥምረት ለአዎንታዊ ተግባር ድርጅት (OTNAA–Worldwide) አማካሪ በሰሜን አሜሪካ

    በትግራይ ምርጫ ምርጫ ሲባል እየሰማን ነው። ነገር ግን የትግራይ ሕዝብ በትግሉ ዋጋ የከፈለበትን የፍትህ፣ የነፃነት፣ የዲሞክራሲ፣ የሕግ ልዕልና፣ የሰላምና የዳቦ ጥያቄዎች ጭራሽ አልተመለሱም። ላለፉት 50 ዓመታት በትግራይ የተካሄዱት አምስት ተከታታይ ምርጫዎችም አንዲት ኢንች ለውጥ አላመጡም። አሁንም ከ50 ዓመት በኋላ የቀረበልን የምርጫ ድግስም ያው በተመሳሳይ ‘ወጮ ቢገለብጡት ወጮ’ ሆኖ ነው የተገኘው።

    በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ ድርብ ድርብርብ የ50 ዓመታት ሶቆቃ ሲታይ፦

    • አንድ ቀን እንኳን ተረጋግቶ የሚኖርበት እፎይታ ያላገኘ ሕዝብ ነው ያለው፤
    • አሁንም ራሱ አስመራጭ፣ ራሱ ተመራጭ፣ ራሱ መራጭ፣ ራሱ ዳኛና ራሱ ቀማኛ በሆነ ፈላጭ ቆራጭና አምባገነን የህወሓት ሥርዓት ስር ወድቆ እንደ ሞርኮኛ ተቆጥሮ በቁም እስር ላይ የሚኖር ሕዝብ ነው ያለው፤
    • አንድ ለአምስት በማደራጀት የዘመነ–ደደቢት በጫካ አገዛዝ መፈናፈኛ በማሳጣት በጅሆ (hostage) ተይዞ የሚገኝ ሕዝብ ነው ያለው፤
    • ለሚደርስበት በደል አቤት የሚልበት የዳኝነት ቦታ አጥቶ እንደ ህፃን ልጅ ‘አፍህን ያዝ!’ እየተባለ፣ እየተኮረኮመ የሚኖር፤ የፍትህ በር የተዘጋበት ሕዝብ ነው ያለው፤
    • እስካሁን ድረስ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል “ወራሪ ጠላት መጣብህ” እየተባለ በፍርሃት፣ በሽብርና በስጋት እንዲኖር የተፈረደበትና ጦርነት ያልተለየው ሕዝብ ነው ያለው፤
    • “አደንቁረህ ግዛ” በሚል የካድሬ ፈሊጥ፥ ህወሓት ሲኖር የሚኖር ህወሓት ሲጠፋ ደግሞ አብሮ የሚጥፋ በማስመሰል በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መለኮታዊ ምትሃት እየተመራ፣ ለጥቂት መሪዎች ዘላለማዊ ስልጣን ሲባል የደም ግብር እየገበረ እንዲኖር የተፈረደበት ሕዝብ ነው ያለው፤
    • በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ “ለያይተህና አናቁረህ ግዛ” በሚል ስትራተጂ፣ ሆን ተብሎ በአውራጃና በዘር በመከፋፈል ብሔራዊ ማንነቱን፣ ብሔራዊ እሴቱን፣ ወርቃዊ ባህሉን፣ ታሪኩንና አንድነቱን እንዲዳከም፣ እንዲበተንና እንዲፈርስ እየተደረገ የመጣ መሆኑን በዓይናችን ስናይ ቆይተናል፤ አሁንም እያየን ነው።

    ታዲያ ወገኖቼ ሆይ፦

    • ፍትህ በሌለባት ትግራይ – ፍትሓዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላልን?
    • ነፃነት በሌለባት ትግራይ – ነፃ ምርጫ ማካሄድ ይቻላልን?
    • የሕግ የበላይነት በማይከበርባት ትግራይ – ሕጋዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላልን?
    • በክተት አዋጅ ስር የህሊና ሰላም በሌለባት ትግራይ – ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላልን?
    • አማራጭ የሌለው ሕዝብ – ማን ከማን ነው የሚመርጠው?

    ስለሆነም፥ ዛሬ በትግራይ ምድር እየተካሄደ ያለው የውሸት የምርጫ ድራማ ያለፈውን የሃምሳ ዓመት ፍዳና መከራ እንደገና በትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ መልሶ የባርነት ቀንበር ለመጫን የሚደረግ ሩጫና እሽቅድድም መሆኑን ሳይታለም የተፈታ ነው።

    መፍትሄውስ ምን ይሁን? ፦

    1. የሁሉንም ችግሮች ምንጭ የሆነው፣ ያረጀ ያፈጀ አምባገነን የህወሓት ሥርዓት ያበቃለት ስለሆነ በፍጹም የመፍትሄና የለውጥ አካል መሆን አይችልም። ባህሪውም ፈጽሞ አይፈቅድለትም። ስለዚህ ህወሓት የሕዝቡን ደመ ነብስ የሆኑት የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የዳቦ ጥያቄዎች መመለስ የማይችል መሆኑን ላለፉት በርካታ ዓመታት በተግባር የተፈተነና የትግራይ ሕዝብን ትግል የነጠቀ ድርጅት ነው። መፍትሄውም ሥርዓቱን ከነግሳንግሱ በማስወገድ በአዲሱ ትውልድ መተካት ለትግራይ ሕዝብ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ሆኖ ይገኛል።

    ስለዚህ አሁን ያለው ምርጫ ለትግራይ ሕዝብ በሰላም ወይም በባርነት የመኖርና ያለመኖር ምርጫ ነው ሲባልም አንደኛው ምርጫ የበሰበሰውን አረሜኔ የህወሓት ሥርዓት ዳግም በመምረጥ በጅሆ ተይዘው እያለቀሱ፣ እርስ በርስ እየተናቆሩና ለጥቂት መሪዎች ንፁህ ደም እየገበሩ ባርነትን አሜን ብሎ በመቀበል በጦርነት፣ በሽብርና በስጋት ደመና ስር መኖር ነው። ሁለተኛውና ወሳኙ ምርጫ ደግሞ ከኋላ-ቀርና ከጨለማው አስከፊ የአገዛዝ ሥርዓት ወጥቶ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሰው በመሆን ከሁሉም ጋር በሰላም ተግባብቶና ተከባብሮ አብሮ መኖር ነው። ከሁለት መንገዶች አንዱን የመምረጥና ያለመምረጥ ደግሞ በትግራይ ሕዝብ እጅ ነው።

    ስለትግራይ ሕዝብ ሲነሳ በሚሊዮኖች ኢትዮጵያወያን ዘንድ አብረው የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ። የነቃ የተደራጀና የታጠቀ ሕዝብ እንዴት ጠላቱንና ወዳጁን ለይቶ ማወቅ ያቅቷል? የትግራይ ሕዝብ ለባዕድ ጠላት የማይንበረክክ፣ በሀገሩ፣ በማንነቱና በነፃነቱ የማይደራደር መሆኑን ለዘመናት የቆየ ታሪኩ ይመሰክርለታል። ይህ ከሆነ ሀቁ፥ የትግራይ ሕዝብ ዛሬ ዓለም በሰለጠነበት ዘመን ለሃምሳ ዓመታት ያህል የጥቂት ገዢዎች ምርኮኛና አገልጋይ ሆኖ ለመኖር በገዛ እጁ ለምን ፈቀደ? የትግራይ ሕዝብ ዘላለም የአንድ ኋላቀር ድርጅት የግል ንብረት ሆኖ በሞኖፓልና በጅሆ ተይዞ እንዲኖር በእግዚአብሔር ለህወሓት የተፈጠረ ሕዝብ ነውን? ትግራይ በተለይም በህወሓት ዘመን ከሌሎቹ 86 የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በተለየ መልኩ የአፈና ጉድጓድ፣ የዘር ጥላቻ ሞዴል፣ የጦርነት አውድማ፣ የግድያ ገሃነም፣ የለያይተህ ግዛ ተምሳሌትና የጭቁኖች የምድር ሲዖል ሆና እንድትታይ ያደረጋት ሚስጢሩ ምንድን ነው? በትግራይ ምድር ህወሓት በመፈጠሩ ከጦርነትና ከመፈናቀል አልፎ ለትግራይ ሕዝብ ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ በተለየ መልኩ ያስገኘለት ልዩ ጥቅም ምንድን ነው? እውነት ህወሓት ራሱን ያላዳነ ድርጅት በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪና መድኅን ሊሆን ይችላልን? የሚሉትንና ሌሎች ጥያቄዎች እስካሁን ድረስ መልስ ያላገኙ እንቆቁልሽ ሆነው ያሉት ናችው።

    1. ህወሓት በባህሪው ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ዲሞክራሲ ብቻ አይደለም። የትግራይ ሕዝብን ክብርና ማንነት የሚያሳንስ አምባገነን፣ ጠባብና ተራ ዘራፊ ድርጅትም ጭምር ነው። ይህን ያልኩበት ምክንያት ህወሓቶች ፊደል አልቆጠሩም ማለቴ አይደለም። ራሳችው ከሚያራምዱት አመለካከትና ከሚፈፅሙት ተግባር ተነስተን ስናያችው፦ ዲሞክራሲና የሰው ልጅ ነፃነት ቃሉ እንጂ በተግባር ምን ማለት እንደሆነ አያውቁትም። በዜጎች መካክል የአስተሳሰብ ልዩነት መኖር ማለት ለነሱ ጠላትነት እንጂ ለአንድ ሀገር የዲሞክራሲና የእድገት መሠረት መሆኑን አያውቁትም። ሕገ መንግሥት፣ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ተቋማት፣ አብያተ ምእመናንንም ሳይቀር የሚጠቀሙበት የሕዝብና የሀገር ደህንነት ለመጠበቅ ሳይሆን ለመጨቆኛና ለመዝረፊያ መሣሪያነት ነው።

    ከሁሉም በላይ ደግሞ ለምን በረሃ እንደወጡና ለምን እንደታገሉም አያውቁትም። ሁሉም እኩይ ተግባሮቻችው ልብ ብሎ ለተመለከተው የታገሉበትን ዓላማ የሚፃረሩ ናችው። እስካሁን ድረስ አእምሯችውና አስተሳሰባችው የተወቀረው በዘመነ-ደደቢት የነበረ ፅንፈኛ፣ አክራሪና [ትምክህታዊ] አመለካከት ነው። ጦርነት መለኮስ፣ ግጭት መፍጠር፣ ለያይቶና አደንቁሮ መግዛት፣ የውሸት መርዝ መርጨት፣ ሽብር መፍጠርና መዝረፍ የመሳሰሉትን አፍራሽ ተግባራት እንደ ሱስና እንደ ልዩ ሙያ አድርገው ሲከተሏችው የኖሩት የባህሪያቸው መገለጫዎች ናችው። አሁን ያለው የክተት አዋጅም የቆየ ባህሪያችው አንዱ አካል ነው፤ ጭር ሲል አይወዱም። በሕዝብና በሀገር ላይ የፈፀሙበትን ወንጀል ስለሚያውቁ ዙሪያችውን ሁሉ በጠላት የታጠረ መስሎ ይታያቿል። ከዚህ የተነሳ በሕዝቡ ላይ ምንም ዓይነት አሜኔታ የላችውም። ለዚህ ነው የትግራይ ሕዝብ ሌላ አማራጭ ነገር እንዳያስብ ነጋ ጠባ በክተት አዋጅ፣ በመግለጫ፣ በስብሰባ፣ በድጋፍ ሰልፍና በሽብር እንዲናጥ የሚያደርጉት።

    ህወሓቶች የዲሞክራሲ መሃይማንና የለውጥ ፀር ናቸው ከምንልበት አንዱ ህወሓት እስካሁን ድረስ ድሮ በዘመነ-ደደቢት የነበረ የአደረጃጀት ዓይነት “ነፃ አውጪ ግንባር” ነን ብለው ነው የሚያምኑት። ህወሓት ከሌሎች የፓለቲካ ፓርቲዎች እኩል መብትና ግዴታ ያለው ድርጅት አድርጎ አያስብም፤ አሁንም ‘የአንበሳ ድርሻ ያለኝ አውራ ፓርቲ ነኝ’ ብሎ ነው የሚያምነው። የትግራይ ሕዝብና ህወሓት የማይለያዩ አንድ ናቸው ብለው ነው የሚያምኑትና የሚያስተምሩት። በየዓመቱ የሚያከብሩት የህወሓት ልደት የትግራይ ሕዝብ ልደት ነው ብሎ ነው የሚያምኑትና የሚያስተምሩት። የህወሓት ከስልጣን መወገድ ማለት የትግራይ ሕዝብ ህልውና አብሮ ያከትማል ብሎ ነው የሚያምኑትና የሚያስተምሩት። የትግራይ ሕዝብ ሓቀኛ ታሪክና ህልውና ከደደቢት ይጀምራል ብሎ ነው የሚያምኑትና የሚያስተምሩት። መንግሥትና የፓለቲካ ድርጅት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽ ናችው ብለው ነው የሚያምኑትና የሚያስተምሩት። አደንቁሮና አደንዝዞ መግዛት ማለትም ትርጉሙ ይኸው ነው።

    ልብ በሉ!! ህወሓት በሚመራው መንግሥት ሁሉም ፓሊሲዎች፣ አደረጃጀቶች፣ ሕጎችና ጠቅላላ የምሕዳሩ መመሪያ ሥርዓት የሚቀዱት ከሀገርና ከሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም አኳያ ሳይሆን መነሻቸው ከላይ ከተጠቀሱት ኋላቀርና የድንቁርና አስተሳሰቦች የሚመነጩ ናችው። የትምህርት ሥርዓቱ፣ መምህርና ተማሪው በሙሉ በዚሁ ትውልድ ገዳይና አደንዛዥ በሆነው የድንቁርና አስተሳሰብ ነው ተቀርፀውና ተኮትኩተው ያደጉት። በወጣቱና በሕብረተሰቡ አካባቢም እስከታች ቤተሰብ ድረስ ወርዶ የዕለት ተዕለት መተዳደሪያውና የኑሮው አካል አድርጎ እንዲወስደው ይገደዳል። ከዚህ የተነሳም ሕዝቡ ህወሓትን እንደ አንድ ስጋ-ለበስ ሰዎች የተሰባሰቡበት የፓለቲካ ድርጅት ሳይሆን እንደ ረቂቃን መናፍስት አድርጎ እንደ ጣዖት እንዲያመልካችው ተደርጓል። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤትም በሕዝቡ ሥነ ልቦና ላይ የጣለው ጠባሳ አሳዛኝ ነው። ሕዝቡ እንዳያምፅ፣ በነፃ እንዳይደራጅና የፍትህ ጥያቄ እንዳያነሳ በተለያየ ደባ ለመብቱ የማይታገል የአካልና የህሊና እስረኛ ሆኖ እንዲኖር አድርገውታል።

    በሌላ በኩል ደግሞ ከህወሓት አስርቱ ትዕዛዛት ያፈነገጠ፣ የተለየ አመለካከት የያዘ ወይም ተቃዋሚ ነው ከተባለ ደግሞ ቅጣቱ ከቤተሰቡ ይጀምራል። ትዳር ይፈርሳል፤ ቤተሰብ ይበተናል። በሕብረተሰቡ ደረጃም እሳት እንዳታስጭሩ፣ ሲሞት እንዳትቀብሩ፣ ሻይ ቡና ኣንዳትሉ፣ ቤት እንዳታከራዩ፣ ወዘተ በሚል አሰቃቂና አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ማኅበራዊ ውግዘት ይታወጅበታል። በመንግሥት ደረጃም የመሥራት መብቱ፣ ሀብት የማፍራትና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ይከለከላል። የመጨረሻ ዕድሉም ሞት፣ ስደት፣ እስር ቤት ወይም የት እንደገባ በማይታወቅ መልኩ ተሰውሮ ይቀራል። ይህ ዓይነቱ ዘግናኝ ተግባር ለትግራይ ሕዝብ መናገር ማለት ለቀባሪ ማርዳት ነው የሚሆነው። ለዚህ ነው ህወሓት የሕብረተሰቡ ነቀርሳ ስለሆነ መወገድ አለበት የምንልበት ምክንያትም ተግባሩ ፀረ-ሰብዓዊ ፍጡር ስለሆነ ነው።

    ስለሆነም ለትግራይ ሕዝብ፣ ለትግራይ ምሁራን፣ ለትግራይ ወጣቶችና ታጋይ ኃይሎች በሙሉ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክትም አንድና አንድ ነው። የትግራይ ሕዝብን ለጥቃት፣ ለውርደት፣ ለስደትና ለረሃብ የዳረገው ከህወሓት በላይ ሌላ ጠላት የለውም። ትግራዋይ ትግራዋይን ለማጥፋት እርስ በርሱ እንደጠላት እየተፈራረጀና እየተባላ እንዲኖር እያደረገ ያለው ምንጩ ህወሓት ራሱ በፈጠረው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ደማዊ ሰርዓት ውጤት እንጂ ከአማራ ወይም ከውጭ የመጣ ጠላት አይደለም። በሀገሩ፣ በማንነቱና በነፃነቱ ኮርቶ ይኖር የነበረውና የጀግንነት የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት እየተባለ ይታወቅ የነበረውን ጀግናው የትግራይ ሕዝብ ዛሬ ትግራይን በጥላቻ የታጠረች የሽብር ደሴት ሆና እንድትቀር እያደረጋት ያለው ራሱ ህወሓት በፈጠረው የለያይተህ ግዛ መርዝ ያመጣው ጣጣ እንጂ፥ ከሌላ ጎረቤት ድንበርን ተሻግሮ የመጣብን ችግር አይደለም። ስለዚህ የችግሩ ምንጭም፣ የችግሩ ሰለባም እዚያው በትግራይ ምድር ላይ ነው ያለው። የችግሩን የመፍትሄ መድኃኒትም በራሱ በትግራይ ሕዝብ እጅ ላይ ነው ያለው።

    ለባዕዳን ወራሪዎችን ያልተንበረከከ ጀግና ሕዝብ ዛሬ እጃቸውን በደም የተነከሩ፣ ዓይናቸውን በፍቅረ-ንዋይ የታወሩ፣ አእምሯቸውን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምትሃት የደነዘዙ የህወሓት ጉግ ማንጉግ መሪዎችን መጫወቻ፣ ምርኮኛና የቁም እስረኛ ሆኖ ሲታይ እጅጉን ያሳዝነኛል፣ ያሳፍረኛል፣ ያስቆጣኛልም። ትናንት እንደነ ጀኔራል አሉላ አባ ነጋ፣ ሃፀይ ዮሐንስ፣ እንደነ ጀኔራል ሐየሎም አርኣያ፣ ዛሬም እንደነ ገብሩ አሥራት፣ አረጋሽ አዳነና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩትን ብሔራዊ ጀግኖች የተወለዱባት ትግራይ አሁን የህወሓት ፈርጣጭ መሪዎችን መሸሸጊያና መደበቂያ ሆና የውሸት ድራማ የሚሠራባት የትርምስ አውድማ ሆና ማየቱ ውርደትና ሀፍረት ከመሆኑም በላይ የትግራይ ሕዝብን ጨዋነት፣ የሞራል እሴትና ክብር የሚያሳንስ ነው።

    ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ መድኅን ህወሓት ሳይሆን ራሱ ሕዝቡ ነው። በአንፃሩ ህወሓትን ከሀገርና ከሕዝብ በላይ አድርጎ በማየት ጥቂት አምባገነን ገዢዎችን ከስልጣን ከማውረድ ይልቅ “የትግራይ ሕዝብ ይጥፋ፤ ሀገር ትፍረስ፤ ሚሊዮን ለጋ ወጣቶችን በማያውቁት ጉዳይ ወደ ጦርነት ይግቡ” ብሎ መንቀሳቀስ፣ የወንጀሉን ተባባሪ መሆን፣ ሕዝቡን ማስገደድና ማደናገር ማለት ያለፈውን የሃምሳ ዓመት ሶቆቃ መድገም ብቻ ሳይሆን፥ በታሪክም ሆነ በሕግ የሚያስጠይቅ የዘመናችን አስፀያፊና ወራዳ ተግባር ይሆናል።

    ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ ማለቂያ ከሌለው ጭቆና ተላቆ ዘላቂ ሰላምና እፎይታ ማግኘት የሚችለው የሁሉንም ችግሮች ምንጭ የሆኑትን የህወሓት መሪዎች ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለአንዴና ለመጨረሻ ከጀርባው አሽቀንጥሮ በመጣል ቦታውን ለባለተራው ለአዲሱ ታጋይ ትውልድ እንዲለቁ ሲያደርግ ብቻ መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል። ይህ ሁኔታ በዋዛ ፈዛዛ ለጥቂት መሪዎች ዋሻ ለመሆን ሲባል ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኝ ቀርቶ ወደ ሌላ የጥፋት ምዕራፍ ከተሸጋገረ ግን መዘዙ ከትግራይ አልፎ ሌላው ጎረቤትንም ጭምር ስለሚነካ የትግራይ ሕዝብ “ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል እየደማ ይኖራል” ነውና “ሳይቃጠል በቅጠል” ማለቱ ይበጃል እላለሁ።

    ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክትም ተመሳሳይ ነው። የሩቁን ትተን የትናንትናውን የሀምሳ ዓመት የትግል ታሪካችን መለስ ብለን ስንቃኝ በትክክል የሚያሳየን ስንተባበር እንደምናሸንፍ፣ ስንበታተንና ስንለያይ ግን እንደምንሸነፍ ነው። በሌላ አነጋገር፥ ተባብረን ታግለን ያገኘነውን ድል ገና እግር ሳይተክልና ለፍሬ ሳይበቃ ተበታትነን ስናፈርሰው ነው ታሪካችንን የሚያሳየን። ዛሬም ጨቋኞች፥ በተለይም ህወሓት ደካማ ጎናችንንና ኋላቀር የፓለቲካ ባህላችንን ከኛ በላይ ጠንቅቀው ስለሚረዱ እኛን መስለው እኛን ለማጥፋት ሲጠቀሙበት ቆይቷል። ለአርባና ለሀምሳ ዓመታት ያህል በዘር፣ በሀይማኖትና በቦታ እየተሸነሸነ ሲሠራበት የቆየውን የለያይተህ ግዛ ኢንጂነሪግ በያንዳንዳችን አእምሮ ውስጥ የጥላቻ መርዝን ተክሎ አልፏል።

    በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉት አንዳንድ አላስፈላጊ ግጭቶችም መነሻቸው የዚሁ የጥላቻው መርዝ ውጤቶች መሆናቸውን እሙን ነው። በተደረገው ትግል ህወሓትን ከመሀል ሀገር ተባርሮ ወደ ትግራይ በመሄዱ ብቻ እንደ ግብ ተወስዶ ለውጥ እንደ መጣና ትግሉ ያለቀ መስሏቸው የሚዝናኑና የሚኩራሩ ጥቂቶች አይደሉም። ነገር ግን ህወሓት ዘወር አለ እንጂ አልሸሸም። መልኩን፣ ስልቱንና ስትራተጂውን ቀየረ እንጂ አልጠፋም። ህወሓት የትግራይ ሕዝብን እንደምሽግ ተጠቅሞ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ አሁንም አለሁ አልሞትኩም እያለን ነው።

    ችግራችንን የህወሓት መኖርና አለመኖር ጉዳይ ብቻ አይደለም። ራሳችን በራሳችን ለመለወጥም አብዮት ያስፈልገናል። ሁልጊዜ ትግላችንን ውጤት አልባ ሆኖ እንዲቀር ከሚያደርጉት ጥቂት ምክንያቶች አንዱ ገና ያልተገነዘብናቸውና ያዝ ለቀቅ የምናደርጋችው መሠረታዊ ችግሮች ስላሉን ነው።

    አንደኛ – የጋራ ችግሮቻችንና የጋራ ጥቅሞቻችንን ምን እንደሆኑ ለይተን አላወቅንም፤
    ሁለተኛ – የሀገራችን እውነታና የሕዝባችንን የልብ ትርታ የተረዳ፣ የጠራ ራዕይና ዓላማ ያለው የመሪ ድርጅት ጥያቄ ገና አሁንም አልተመለሰም፤
    ሦስተኛ – ኢትዮጵያ ሦስት ሺህ ዓመት ያላት ነፃ ሀገር ናት ብለን እንፎክራለን እንጂ ሀገራዊ ንቃተ ህሊናችን ከ16ኛው የዘመነ መሳፍንት አስተሳሰብ ገና አልወጣንም፤
    አራተኛ – ከታሪካችንና ከውድቀታችን አንማርም፤
    አምስተኛ – ትልቁን ጉዳይ ትተን በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ነው የምንጣላውና የምናተኩረው።

    የሀገር ባለቤት መንግሥት ሳይሆን 110 ሚሊዮን ሕዝብ ነው። ሀገር ቢፈርስና ቢበታተን ተጠያቂ የሚሆነው መንግሥት ብቻ ሳይሆን ራሱ ሕዝቡም ጭምር መሆኑን በውል የሚገነዘብ ዜጋ ምን ያህል ነው? የሚለው አጠያያቂ ጉዳይ ነው። ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል። በእነዚህ ራሳችን በምንፈጥራችው ችግሮች ምክንያት ለነፃነታችን፣ ለመብታችን፣ ለአንድነታችንና ለህልውናችን ዘብ የማንቆም፣ ለአገዛዝና ለጭቆና የተመቸን እንድንሆን አድርጎናል። ውጤቱም ትግላችን በአቋራጭ እየተነጠቀ ሁሉ ጊዜ ታጥቦ ጭቃ ሆኖ እንዲቀር አድርጎታል። ይህ በመሆኑም የሕዝባችን የመከራ ዕድሜ እንዲራዘም ከማድረጉም በላይ ከነዚህ ችግሮች በይበልጥ የጠቀመው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን እንደ ህወሓት ለመሳሰሉት መሰሪ መሪዎችና ገዢዎች ነው።

    ስለሆነም ትግሉ ተጀመረ እንጂ አላለቀም። መፍትሄውም ችግሮችን በተለያየ ቦታ ብልጭ ባሉ ቁጥር ከቅርጫፋቸውና ከውጤታቸው ከመታገል ይልቅ በተባበረ ኃይል ግንዱን መገርሰስ ወይም ምንጩን ማድረቅ የትግላችን ተቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት። በመሆኑም የሁሉንም ችግሮች ምንጭ ከሆነው ህወሓት ጋር ተደራድሮ ወይም እሽሩሩ ብሎ በሀገራችን ምድር ላይ የተረጋጋ ሰላምና እድገት ይመጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። የህወሓት አምባገነንነት መነሻው ከራሱ ተፈጥራዊ ባህሪይ የሚመነጭ እንጂ በግምገማ ወይም በድርድር ሊስተካከል የሚችል አይደለም።

    ስለዚህ ተበታትነን በያለንበት ጊዜያችንና ጉልበታችንን ከማባክን ይልቅ ትግላችንን በተቀናጀ መልኩ ወደ አንድ የጋራ ጠላት ማነጣጠር አለበት። ዋናው ችግር ፈጣሪ ህወሓት ቁጭ ብሎ እያለ እሱ በሚሰጠን አጀንዳ እየተመራን ከውጤቱና ከቅርጫፉ ጋር እየታገልን ከመኖር ይልቅ አልፈን መገኘት አለብን። ከወደቁት ጋር እንካ ስላንቲያ ስንል ጠላቶቻችንን መልሰው እንዲጠናከሩ ዕድል ከመስጠት አልፎ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ፍፁም አይቻልም።

    የትግል አንድነታችን ይለምልም !!

    በላይ አስመላሽ
    የተጋሩ አለማቀፍ ጥምረት ለአዎንታዊ ተግባር ድርጅት (OTNAA–Worldwide) አማካሪ በሰሜን አሜሪካ

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    የትግራይ ሕዝብ መከራ እንዲያበቃ ህወሓት ከነግሳንግሱ መወገድ አለበት!!

    #15671
    Anonymous
    Inactive

    ኢንጂነር ታከለ ኡማ በአዲስ አበባ መሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላን በተመለከተ ላወጣው ጥናታዊ ሪፖርት የሰጡት ምላሽ

    በሀሰተኛ መረጃ ሀገር ማፍረስ ይቻል ይሆናል እንጂ ሀገር አይገነባም – የፖለቲካ ትርፍም የለውም!!

    ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ተገቢው ቦታ ላይ ባልገኝም፥ ከዚህ የመጓተት ፖለቲካ አስተሳሰብ መውጣት አለመቻል ግን ትልቅ ህመም እንደሆነ ይሰማኛል።

    የመሬት ወረራን በተመለከተ ከመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ እለት ድረስ ጠንካራ የሆነ እርምጃ ስንወስድበት የቆየንበት ጉዳይ ነው። በተለያዩ ጊዜዎች የወሰድናቸው እርምጃዎችም ህያው ምስክሮች ናቸው።

    እኛ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል እርምጃ ስንወስድ፥ የዛሬ ተቺዎች የሰብዓዊ መብት ተነካ፣ ዜጎች ተፈናቀሉ ብለው ዘመቻ ከከፈቱብን ውስጥ ነበሩ። ለ20ሺህ አርሶ አደሮች የተሰጡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በተመለከተም ከአንድ አመት ተኩል በፊት በካቢኔ የተወሰነና የተተገበረ ነው። በድብቅ የተተገበረም ሳይሆን በመንግሥት ሚዲያም በይፋ የተገለፀ ነበር።

    ከመሬታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ከወደቁ በራሳቸው መሬት ላይ በተሠራ ህንጻ ዘበኛ እና ተሸካሚ ሆነው ከቀሩ 67 ሺህ አባወራዎች መሃል የከፋ ችግር ላይ ለወደቁት 20 ሺህ ኮንዶሚንየም ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም። ስህተትም ከሆነ ለ67,000ውም አለመስጠታችን ነው። ከዚህ ውጭ በሕገ-ወጥ መንገድ የተሰጠ ምንም አይነት ቤት የለም።

    ይህ ሥራችን በተደጋጋሚ በይፋ ስንናገር እንደነበረው የምናፍርበት ሳይሆን የምንኮራበት ነው። በግፍ የተገፋን፣ በግፍ ከመሬቱ የተፈናቀለን አርሶ አደር መካስ ያኮራናል!

    በዙሪያዋ ካሉት አርሶ አደሮች ጋር በፍቅር ተሳስባ የምትኖር የተሰናሰለች ከተማ እንጂ በዙሪያዋ ካሉት ሕዝቦች ጋር የተቀያየመች ከተማ እንድትኖር አንሻም ነበርና። ይህ ደግሞ የከተማዋ ነዋሪዎች ፍላጎት መሆኑንም እንገነዘባለን።

    አንድም ቀን በግፍ ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የመቆርቆር ስሜት አሳይቶ የማያውቅ ቡድን ዛሬ የአርሶ አደሮችን ጉዳት ለተቀባይነት ማግኛ መጠቀሚያ ሲያደርገው ማየት ያሳዝናል። ነገር ግን በሀሰተኛ እና በተጋነነ መረጃ ጠንካራ መምሰል እንጂ መሆን አይቻልም።

    በሀሰተኛ መረጃ ድካማችንና ሥራችንን ለማጠልሸት ቢሞከርም ሥራችን ይናገራልና ፍርድ የሕዝብ ነው!

    ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ
    የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር
    (የቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ)

    ተያያዥ ጉዳዮች፦

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ

    #15682
    Anonymous
    Inactive

    ግልፅ ደብዳቤ ለኢንጂነር ታከለ ኡማ (ቢደርስም ባይደርስም)
    ወንድማገኘሁ አዲስ

    ሰላምታዬንና አክብሮቴን በማስቀደም የተከበሩ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በጥናት ደረስኩበት ብሎ ይፋ ላደረገው ሰነድ በሰጡት መልስ የተገነዘብኩት እንደ አንድ ተራ ዜጋ ላቀርብልዎት እወዳለሁ።

    ሲጀመር የሰጡት ርዕስ ራሱ ችግር እንዳለበት ይሰማኛል። ማስረጃ አጠናቅሬያለሁ ያለ ድርጅት መግለጫ ከማውጣቱ ሰነዱን ለሚመለከታቸው አቅርቦ ይመሩት የነበረው ፅሕፈት ቤት መልስ ስላልሰጠ። ኢዜማ ከዚህ ቢሮ መልስ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ አንደኛ መልሱን ሪፖርቱ ላይ ያካትት ነበር፤ አሳማኝ የሆኑ ጉዳዮች ከቀረቡም ፓርቲው ከሪፖርቱ ላይ የተወሰኑትን እንዲያርም ወይም እንዲያሻሽል ዕድሉ ክፍት ይሆን ነበር ብዬ አምናለሁ።

    በመቀጠልም ምላሽ ለመስጠት ተገቢው ቦታ ባልገኝም ሲሉ ተገቢው ቦታ ለመሆኑ የቱ ነው? ሰነዱ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ግለሰቦች አካላት እርስዎና እርስዎ ይመሩት የነበረው ተቋም በመሆናቸው መልስ እንዳይሰጡ ቦታ ምክንያት ይሆናል ብዬ አላስብም ።

    በመቀጠልም የመሬት ወረራን በተመለከተ ስልጣን ላይ ከወጣንበት የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ ቀን ድረስ ጠንካራ እርምጃዎች ስንወስድበት የነበረ ጉዳይ ነው ብለዋል።  ለእርስዎ አድልተን ያሉትን ብንቀበል እንኳን “የመሬት ወረራውን አስቆሙት ወይ? የኮንዶሚኒየሙን አድሎአዊ እደላ አስወገዱት ወይ ነው?” ጥያቄው በራስዎ አንደበት የሀይማኖት ተቋማት ሳይቀሩ በኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ሲወረሩና በመንግሥት አካላት ሲፈርሱ በተነሳብዎት ተቃውሞ ምክንያት እርስዎ ራስዎ ይቅርታ አልጠየቁም ወይ? ከፍተኛ የሆነ የመሬት ወረራ እንዳለ በይፋ አልተናገሩም ወይ? ባለፉበት ባገደሙበት ሁሉ የከተማዋን መሬት ለግለሰቦችና ለተቋማት ሲያድሉ አልነበር ወይ?

    ሌላው ክቡር ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ የተፈናቀሉትን አርሶ አደሮች በመታከክ እንደ ህወሀቶቹ የቀን ጅቦች ብሄርዎን ዋሻ ለማድረግ የሄዱበት መንገድ በጣም ከእርስዎ በጭራሽ ያልጠኩት ነበር። ለመሆኑ የትኛው የኢዜማ የመግለጫው ክፍል ላይ ነው “የተፈናቀሉት ገበሬዎች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ አይሆኑ” የሚለው። ማነው በቃለ መጠይቁስ ላይ “ለተፈናቀሉት ቤት አይሰጥ” ያለው? በእርስዎ የስልጣን ዘመን በገፍ ቤት የታደላቸው በሺዎች የሚቆጠሩት የኦሮሚያ ባለስልጣናት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ነበሩ ወይ? እስከ ልጅ ልጅ የሚሰጠው መሬት ፍትሀዊ ነበር ወይ? ለስፖርት ክለቦች የታደለውስ? ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው እኮ “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ድሆች ከዛሬ ነገ አንገታችንን ማስገቢያ፣ ልጆቻችንን ማሳረፊያ ቤት ልናገኝ ነው” በማለት ቤትን የህልውናቸውና የተስፋቸው ጥግ አርገው እየጠበቁ ሳለ ነው።

    “እኛ ሕጋዊ እርምጃ ስንወስድ የዛሬ ተችዎቻችን የሰብዓዊ መብት ተነካ፤ ዜጎች ተፈናቀሉ ብለው ዘመቻ የከፈቱብን አካላት ናቸው” ብለዋል። በመጀመሪያ ደረጃ እርምጃ ሲወሰድ የሰብዓዊ መብት መከበር አለበት የሚለው ዓለም-አቀፋዊ መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ ‘ዘመቻ’ ላሉት ቃል ግን ይቅርታ ያድርጉልኝና ማፈር ይኖርብዎታል። ለእርስዎም ሆነ ለመንግሥትዎ የኢዜማን ያክል ዕድል የሰጠ አንድም ድርጅት የለም። መወቀስ ካለበትም በሰጣችሁ ሰፊ ዕድልና በታገሳችሁ ልክ መሆን አለበት፤ ምንም እንኳን ሁለቱም ምክንያታዊ ናቸው ብዬ ባምንም።

    ሌላው እጅግ አስገራሚ የሆነው ደሞ “አንድም ቀን ለተናቀሉት የመቆርቆር ስሜት አሳይቶ የማያውቅ ድርጅት” ሲሉ የጠቀሱት ለመሆኑ ኢዜማ የጠቀሷቸው ዜጎች ሲፈናቀሉ ህልው ፓርቲ ነበር ወይ? ያፈናቀላቸው እኮ የራስዎ ድርጅት የዛሬው የኦሮሚያ ብልጽግና የትናንቱ ኦህዴድ ነበር! ተረሳ ክቡር ሚኒስትር? አርበኞች ግንቦት 7 (አግ7) እንዲሁም ከስመው ኢዜማን የመሠረቱት እኔ የማቃቸው ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ሁሉ እናንተ ስታፈናቅሉ እነሱ ከተፈናቃዮች ጎን ሆነው ድምፃቸውን ሲያሰሙ የነበሩ መሆናቸውን አስረግጬ መናገር እችላለሁ። እንደ አንድ ለወገኑ እንደሚቆረቆር ኢትዮጲያዊ እኔም ከእነሱ ባለሁበት ያቅሜን ስጮህ ነበር። ለምን ይዋሻል ኢንጂነር?!

    “የአርሶ አደሮችን ጉዳይ ለተቀባይነት ማግኛ” በማለት የፃፉት እና “መጀመሪያ ላይ በሀሰተኛ መረጃ ሀገር ማፍረስ እንጂ አይገነባም” ላሉት ደሞ ትንሽ ማለት አለብኝ። ለመሆኑ ኢዜማ እርስዎ ባሉት መልኩ ተቀባይነት ማግኘት እንደሚቻል ጠፍቶት ነው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹን ያጣው? ሌላው ቢቀር በእናት ድርጅትዎ መዋቅር በአብዛኛው ኦሮሚያና እርስዎ ሲያስተዳድሯት በነበረችው በአዲስ አበባ ከተማ በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ላይ ሲደርሱ የነበሩት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማስጮህ ብቻ ተከታይን ማፍራት አይቻልም ብለው ያስባሉ? ይልቅስ ከላይ እንደጠቀስኩት የተፈናቃዮችን ልብ በፀረ-ኢዜማ ትርክት ለማነፅና ጭፍን ተከታይ ለማፍራት የኳተኑት እርስዎ ራስዎ ነዎት። በነገራችን ላይ፥ ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ዕድል መስጠት ከመንግሥታዊ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ተግባራት ጋር ማበር አይደለም።

    ክቡር ኢንጂነር፥ አሁን ላይ በደንብ የገባኝ ከስልጣን ሲወርዱ፣ በሀሳብ መሟገት ሲያቅታቸውና ፖለቲካ ፊት ስትነሳቸው “ብሔርን መደበቂያ ዋሻ” ማድረግ በስፋት እየተዛመተ ያለ አስፈሪ ፖለቲካዊ ባህል መሆኑን ነው። እርስዎም ይሄን መንገድ በመከተል የእነ ሀይለመስቀል ሸኚን ፣ የእነ አቦይ ስብሀትን የእነ ልደቱ አያሌውን ዱካ እንደተከተሉ ተረድቻለሁ።

    የአሿሿምዎ ሂደት አጠያያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ ክቡር ሚኒስትር፥ እርስዎ የታላቋ አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ነበሩ። ሲያስተዳድሯት የነበረችው አዲስ አበባ ማለት የ AU፣ የ ECA እና የመሳሰሉት ታላላቅ ዓለም-አቀፋዊ ድርጅቶች መቀመጫና በዓለም ላይ 3ኛዋ ወይም 4ኛዋ የዲሎማሲና የፖለቲካ ከተማ እንደሆነች ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው። አሁንም ቢሆን ሚኒስትር እንጂ እንደኔ አክቲቪስት አይደሉም። ቢሆን ደስ የሚለኝ ‘ቀረበ’ የተባለውን ሰነድ በሚገባ ፈትሸው ተመጣጣኝ በሆነ አግባብ መልስ ቢሰጡ ነበር። ሰነዱን በሙሉም ሆነ በከፊል ወይም በተወሰነ ደረጃ ተቀብለው፥ ያም ካልሆነ ተቃውመው የነበሩበትንና ያሉበትን ወንበር የሚመጥን አጸፋ ይሰጣሉ ብዬ ጠብቄ ነበር። በእኔ በኩል ያደረጓቸውን በጎ ተግባራት በዜሮ የማጣፋ ሰው አይደለሁም። የዛሬው መልስዎ ስሜቴን በእጅጉ ቢበርዘውም ለበጎ ለበጎዎቹ ሥራዎችዎ ዛሬም ክብር እሰጣለሁ። ይሁን እንጂ በቀረበብዎ ክስ እና በሰጡት መልስ ምክንያት የተደበቀውን “ኢንጂነር ታከለ ኡማን” ማየቴን ደሞ አልሸሽግዎትም። አሁን ለደረስኩበት ግንዛቤ ትልቁ ግብአቴ ደግሞ እርስዎ ራስዎ የነገሩንን ጭምር በመካድዎ ነው። ይሄ ሁሉ ሆኖም የነበሩበትንና ያሉበትን ደረጃ የሚመጥን መልስ ካለ ለመስማት አሁንም ፍቃደኛ ነኝ።

    ክቡር ሚኒስትር፥ ስንብቴን አስቀድሜ እያቀረብኩ ደብዳቤዬን ከማጠናቀቄ በፊት እርስዎ ወይም ይመሩት የነበረው አስተዳደር ስለተሞገታችሁ ብቻ ሀገር እንደማትፈርስ በርግጠኝነት ልነግርዎ እወዳለሁ። ይልቅስ ሀገር የሚያፈርሰው የዜጎችን ድምፅ ለማፈን ይመሩት የነበረው ተቋም እየወሰደ ያለው ኢ-ሕገመንግሳታዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ እርምጃ ነው። የኢዜማ መግለጫዎች መታገድ የከንቲባ አዳነች አቤቤ ሳይሆን የእስዎ የሁለት ዓመታት የከንቲባነት ዘመን ውጤት ነው። የክብርት ከንቲባዋን ውጤት ደሞ ሰነባብተን እናየዋለን።

    አክባሪዎ ወንድማገኘሁ አዲስ

    ተያያዥ ጉዳዮች፦

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    ግልፅ ደብዳቤ ለኢንጂነር ታከለ ኡማ

    #15753
    Anonymous
    Inactive

    ዛሬ በይቅርታ ላይ ስናፌዝ ዋልን!
    በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

    የሀገሬ ሰዎች ለይቅርታ (ይቅርታ ለመጠየቅም፣ ይቅርታ ለማድረግም) ንፉግ ናቸው። “ሳላውቅ ያስቀየምኳቸሁ፣…” ብሎ ይቅርታ መጠየቅ። መጀመሪያ እስቲ አውቀን የበደልናቸውን ይቅርታ እንጠይቅ። አውቄ የበደልኩት የለም ለማለት ነው? በየአንዳንዳችን ልብ የበደል ቁልል አለ፤ ያንን ለመናድ መድፈር ነው ይቅርታ። የበደልከውን ሰው፥ “ይህን ስላደረግኩህ ይቅር በለኝ” ብለህ መጋፈጥ። በደለኛነትን ሸሽጎ በይቅርታ መንጻት አይቻልም።

    ይቅርታ በጅምላ አይሆንም። መሪዎች የገደሉትን፣ ያሰሩትን፣ ያፈረሱበትን፣ የወረሱትን፣… ወዘተ በስም እየጠሩ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው – እውን ይቅርታ ከፈለጉ። ጎንደር ላይ ወጣት ሲረሽን የነበረ፣ ተነስቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ የሚጠይቅበት ምክንያት የለም፤ የገደለውን ያስገደለውን በስም እየጠራ፣ የሟች ቤተሰቦች ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት። ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ስትላቀቅ የተደረገው ይኸውም ነው። በሀገር ላይ የተሠራ በደል ካለ (ለምሳሌ ኢትዮጵያን የባህር በር እንደማሳጣት ዓይነት) ሕዝብ ይቅርታ ይጠየቃል። አንድ ተማሪ የበደለ መምህር ክፍል ገብቶ “ያስቀየምኳችሁ ይቅርታ” ሲል፥ ‘ፐ! ይቅርታ ጠየቀ’ ይባልለታል። በፍጹም፤ ይቅርታ አልጠየቀም!! ስሙን ጠርቶ፣ የበደለውን ገልጾ ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት።

    ይቅርታ መጠየቅ ነው ወይንስ ማግኘት ቁም ነገሩ? እንዴ ይቅርታችንን ተበዳይ መቀበል አለመቀበሉን ማወቅ የለብንም? ካለብን ከበደልነው ጋር መጋፈጥ የግድ ነው። የጎረቤቴ ልጅ በተገደለ፣ በታሰረ እናት አባቱ እንጂ እኔን ማን ይቅርታ አድራጊ አደረገኝ?

    ደግሞ አንዳንዱ ይገርማል፤ እራሱን ከኢየሱስ መስቀል ላይ ሰቅሎ መሀሪ ይቅር ባይ መሆን ያምረዋል፤ ይቅርታ እኮ ዝቅ ማለት ነው። “ሳላውቅ በድያችኋለሁ፥ ይቅርታ አድርጉልኝ፤ እናንተ ግን አውቃችሁ በድላችሁኛል፥ ይሁንና ይቅር ብያችኋለሁ” ሲባል እኔ ንጹህ፣ እናንተ ኃጢአኞች ማለት እኮ ነው። እስቲ የሚከተለውን ይቅርታ እንመልከት።

    “… እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ባለማወቅ ለበደልኩት ለማንኛውም በደል ይቅርታን በትህትና እጠይቃለሁ። እኔንም ለበደሉኝ፣ ያለበደሌ ለከሰሱኝ፣ ያለተግባሬ መጥፎን ስም ሰጥተው ላሳጡኝ፤ ሕዝብን ለማገልገል በምተጋበት ወቅት አላስፈላጊ ጦርነትን በመክፈት ሲያደክሙኝና አላሠራ ሲሉኝ ለነበሩት ሁሉ ከልብ የሆነ ይቅርታን አድርጊያለሁ።

    አሁን እዚህ ውስጥ ምን የይቅርታ መንፈስ አለ? ይቅርታ ጠያቂው፣ አውቆ የበደለው አንድም ነገር የለም። እሱ ላይ የተደረገውን በደል ግን ሆን ተብሎ፣ ታቅዶ እንደተደረገ በዝርዝር ተቀምጧል። ምናለ የእነሱንም፥ ‹‹ሳታውቁ ለበደላችሁኝ›› ብሎ ቢያልፈው? ወይ የእሱንም (እሱ የበደለውንም፣ ያጠፋውንም) ቢዘረዝረው?

    እና እባካችን ያልደረስንበትን እንተወው፤ ቢያንስ ጽንሰ-ሀሳቡ ለልጆቻችን ይቀመጥ፤ እነሱ ይደርሱበት ይሆናል፤ የልጅ ልጆቻቸውም ቢሆኑ።

    በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)*

    * በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) ደራሲና ገጣሚ ሲሆኑ፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሂዩማኒቲስ፤ የቋንቋዎች ጥናት የጆርናሊዝምና የኮሚኒኬሽን ኮሌጅ ውስጥ ደግሞ መምህር ናቸው። ከዚህ ቀደም ለህትመት ከበቁላቸው ሥራዎች ውስጥ የማይፃፍ ገድል፣ የራስ ምስል፣ ያልተከፈለ ስለት፣ የወይራ ስር ጸሎት፣ የማይጻፍ ገድል፣ የተስፋ ክትባት፣ እና ፍካት ናፋቂዎች የጠቀሳሉ። በተጨማሪም በብሔራዊ ቲያትር ቀርቦ በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው “ደብተራው” የተሰኘው የሁለት ገጸባሕርያት ቲያትር (two-handler theater) ደራሲ ናቸው። በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ሊያገኟቸው ይችላሉ።

    ** ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    በድሉ ዋቅጅራ

    #15884
    Anonymous
    Inactive

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሆይ! እባክዎ፥ የሕዝብዎን የማመዛዘን አቅም አይናቁብን፤ የሚነግሩን አይመጥነንም
    አቶ ግርማ በቀለ – የኅብር ኢትዮጵያ ሊቀመንበርና የአብሮነት አመራር አባል

    አምና በተከልነው ችግኝ ሐረማያ ሐይቅ ዳግም ነፍስ ዘራ፤ አቢያታ ሐይቅ አንሰራራ፤…

    ሕዝብ የመንግሥትን ጥሪ (አምስት ቢሊዮን ችግኝ ተከላ፣ ሕዳሴ ግድብ፣ ማዕድ ማጋራት፣…) ሁሉ ተቀብሎ ከጎናችን በመቆሙ ያሰብነው ሁሉ ካቀድነው በላይ ተሳካ።…

    በዚህ ደረጃ ድጋፍ ያገኘ የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት አላውቅም።…

    የትግራይ ምርጫ የጨረቃ ምርጫ ነው፤ ከጨረቃ ቤት ጋር ይመሳሰላል፤ ሁለቱም ተኝተው አያድሩም።…

    እኔ ግን ከፖለቲካውም፣ ከማሳመኛ ፕሮፖጋንዳውም ከዚያ ሁሉ ንግግር የገረመኝን፥ በትምህርትም በተግባርም ጠንቅቄ የማውቀውን አንስቼ ትዝብቴን ላቅርብ። ስለ ሐረማያ ሐይቅ እንደገና ውሃመያዝ፣ የሞተው መዳን።

    የደረቀ ሐይቅን አምና በተተከለ ችግኝ ማዳን መቻሉን እናቆይና፥ በቅድሚያ መሠረታዊ ጥያቄዎችን እናንሳ። እውነት አምስት ቢሊዮን ችግኝ በአንድ ዓመት ማዘጋጀት ይቻላል? በስንት የችግኝ ማፊያ ጣቢያ? የዛፍ ችግኝ ወይስ የሽንኩርት፣ የቲማቲም፣ የቀይሥር፣… ችግኝ? አምስት ቢሊዮን የዛፍ ችግኝ ለማዘጋጀት ምን ያህል ጊዜ (የችግኙ ዘር ከተዘራበት ወደ መደበኛ ማሳ እስከሚዛወርበት)፣ ጉልበት (በችግኝ ማፊያ ጣቢያ ከተሰማራው በተጨማሪ፥ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የተሰማራው 25 ሚሊየን ሕዝብ ከሆነ እያንዳንዳችን 20 ችግኝ ተክለናል ማለት ነው)፣ ቁሳቁስ (ቦታ፣ ዘር፣ ፍግ/ኮምፖስት/፣ ፕላስቲክ፣…) ያስፈልጋል? እንደገና ይህን ሁሉ እንለፈውና፥ ሲጀመር ኢትዮጵያዊያን ዛፍ የተከልነው “ለእርሳቸው ያለንን ድጋፍ ለመግለጽ” መሆኑን መግለጽስ ለቀጣዩ ምን መልዕክት ያስተላልፋል? እኔ በግቢዬም፣ በአደባባይም የተከልኩት የፕሮግራሙን ዘላቂ ጥቅም በማመን እንጂ፥ እርስዎን ስለደገፍኩኝ አለመሆኑን ግልጽ ማድረግ እወዳለሁ።

    ጥያቄዬ አምና የተተከለ ችግኝ በዓመቱ የመሬትን የውሃ የመያዝ አቅም አሻሽሎ፣ የዛፍን ውሃ ትነት ምጣኔን ለውጦ፣ ጎርፍን አስቀርቶ፣ የአፈር ርጥበትን ጨምሮ፣… ውሃ አጠራቅሞ የደረቀን ሐይቅ ተመልሶ ነፍስ እንዲዘራ የማስቻል አቅም ያጎለብታል ወይስ እራሱን ከችግኝ ማፊያ ጣቢያው ከሚለየው አፈርና አየር ንብረት ጋር አዋዶና አዛምዶ፣ የቀረበትን እንክብካቤ አካክሶ ችግኙ መጽደቁ የሚመዘንበት ጊዜ ነው? የሚለው ነው። መልሱ በአጭሩ ችግኝ በተተከለ በዓመቱ ሐይቅ ሲያድን በዓለም ላይ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። መነሻዬንና እውነታውን ትንሽ ላብራራ።

    “ዛፍ በመትከላችን ሐረማያ ሐይቅ ዳግም ህይወት ዘራ፣ አቢያታ ሐይቅ አንሰራራ” ማለትዎ ሥልጣን የጉልበትም የዕውቀትም ምንጭ ነውና ዝም ብላችሁ ስሙ፤ ጸጥ ረጭ ብላችሁ አድምጡ፤ አትጠይቁ ካልተባለ በቀር፥ ለእንደ’ኔ ዓይነቱ የመጀመሪያ ዲግሪውን ሐረማያ ሐይቅ ዳር በግብርና /ዕጽዋት ሳይንስ ላገኘ (ፎረስትሪ /forestry/፣ አግሮፎረስትሪ /agroforestry/፣ ሲሊቪካልቸር /silviculture/፣ የዕጽዋትን ሥርዓተ-ህይወት በአጠቃላይ፣ የዛፍ ተክሎች ከችግኝነት አስከ ዛፍነት ያላቸውን ፍላጎትና ባህሪይ በተለይ፣…) ኮርሶች እንደተማረ፣ ከዚያም ከ12 ዓመታት በላይ በሀገሪቱ የግብርና ልማት ፕሮጀክት መሥሪያ ቤት በሰብል ምርት የፕሮጀክት ኤክስፐርትነት (የአፈርና ውሃ ጥበቃን እና የፕሮጀክት በአካባቢ/environment/ ላይ ያለውን ተጽዕኖ ትንተና ጨምሮ) ላገለገለ ሰው፣ የጣና በለስ ሰፈራ ፕሮግራም ላይ የአግሮ ኢንዱስትሪ (የዘር ማዘጋጃ ፕላንት /ፋብሪካና የዘር ስርጭት አመራርና ከዛፍ ችግኝ ማፊያና የመስኖ ግብርና ምርምር ጋር በቅርበት የሠራሁትን ጨምሮ) ክፍል እንደመራ፣ በፕሮጀክትና ልማት አመራር በርካታ ሀገራዊና ዓለምአቀፍ ሥልጠናዎች (የአካባቢ ተጽዕኖ ትንተና ጨምሮ) እንደተሳተፈና የተመሰከረለት የልማት አመራር አማካሪ ሆኖ 15 ዓመታት እንዳገለገለ፣ ይህን መቀበል እጅግ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን በእጅጉ እንድታዘብ አድርጎኛል። ይህን የሰማ ዓለም ምን ይለን ይሆን? ብዬ ሳስብ ስለእርስዎ በጣም፣ እጅግ በጣም አፍሬኣለሁ። ገበሬውማ ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከጥንት እስከዛሬ የህይወቱ መሠረት ነውና የሚኖረውን ትዝብት አልነግርዎትም።

    ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፥ እባክዎ! የሕዝብዎን የማመዛዘን አቅም አይናቁብን፤ የሚነግሩን አይመጥነንም። በማይጨበጥና በማይመጥነን ፕሮፖጋንዳ ተስፋችንን አያድርቁብን። ስለሀገራችን መጻኢ ዕድልና የገጠማትን የህልውና አደጋ መክተንና ቀልብሰን መጪውን ጊዜ በመተማመንና በመከባበር፣ ደንቃራዎችን ወደ መልካም ዕድል ለውጠን ተያይዘን ለመሻገር የሰነቅነውን ተስፋና የምናደርገውን ጥረት አያምክኑት። እባክዎ፥ ፈጣሪ በማያልቀው ይቅርባይነቱ በቸርነቱ የዘረጋልንን የምኅረት እጅ የርስዎ ድጋፍ ውጤት አድርገው “በቃችሁ” ብሎ ያዞረልንን ፊት እንዲያዞርብን አይትጉ፤ ቆም ብለው፣ ደግመው ያስቡ። አበቃሁ።

    አቶ ግርማ በቀለ /Girma Bekele/

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ ግርማ በቀለ ― ጠ/ሚ ዐቢይ ሆይ! እባክዎ፥ የሕዝብዎን የማመዛዘን አቅም አይናቁብን

    #15923
    Anonymous
    Inactive

    የገዳዮች ወንድማማችነት

    የገዳዮች ወንድማማችነት
    አገኘሁ አዳነ ድልነሳሁ

    ሰዎች በተለያየ ርዕሰ ነገር ወይም ዓላማ ይወዳጃሉ። የወዳጅነቱ ዓይነት የትየለሌ በመሆኑ ቆጥሬ አልዘልቀውም። በጥቅሉ ግን ማኅበራዊ ፋይዳው መልካም የሆነ ሕብረት ሲሆን ያ ጓድ የለውጥ ሠራዊት/ሐዋርያት “pioneers of change” የሚል ታሪካዊ ቅጽል ያገኛል። እንደሰንደቅ የሚውለበለብ ድል ባያቀዳጅም ዘወትራዊ ሕይወትን በድል የሚያሻግር መደበኛ ወንድማማችነትም ክብር ይገባዋል። ዓላማው በጉልህ የማይታየው የፈንጠዝያ ውድጅትንም ቢሆን የሚለካው አግኝቶ “ቢሰፍሩት” ዋጋው ከፍ ሳይል አይቀርም። ዝንጋኤ እስካላስከተለ ድረስ አብሮነት ደግ ነው።

    እኔን ግርም የሚለኝ የነፍሰ-ገዳዮች “ወንድማማችነት” (Fraternity of Assassins) ነው። ይህ ውድጅት በተለያየ ምክንያት ይመሠረታል። አንዳንዱ እጅግ እውቀታዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ እና ፍልስፍናዊ መሠረት ያለው ይመስላል። ይሁንና የዚህን ሕብረት መሠረት ቢያናጉት ከሆድ ወይም ከግላዊ ጥቅም የዘለለ ጉዳይ አታገኙበትም። ይህ ቡድን ለስሙ መጠርያ ተጨናቂ፣ ለቀለሙ ማማር ተብረቅራቂ፣ የሆዱን ጩኸት “በሕዝብ አለኝታነት” ደባቂ ነው። ይህን መልከ ቀናነት ለመቀዳጀት የታቀደ “እውነት”የሚመስል ቅደም ተከተላዊና ፈር ያለው ስልት ያዘወትራል። ይህ ውድጅት በነገረ ፆታ፣ በነገረ ወሲብ፣ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በፖለቲካ አቋም፣ በሙያ… በመሳሰለው ታላላቅ ሰብዓዊ ጉዳይ ሁሉ ልታይ፣ ልታይ ይላል፤ ሀገር ያውካል። ይህ ዓይነቱ ውድጅት ይሉኝታ ሲያልፍም አይነካው። እንደደጎች ሁሉ የዚህን ቡድን ደቀ-መዛሙርት በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።

    1. የጋራ የሆነችውን ሀገራችንን ጠፍጥፈው ዛሬ የሠሯት ይመስል፥ እኔ ብቻ አውቅልሻለሁ ይሏታል። መሽቶ እስኪነጋ “አያምኗትም”፤ ከቆሙበት ስፍራ በቀር ተጨማሪ ወይም የትየለሌ ግላዊም ቡድናዊም አንጻር፣ ምልከታ፣ አቋም፣ ወዘተ… እንዳለ አይረዱም። ቢረዱም ሌላው ሁሉ የማይረባና የተዋረደ ነው። በጉልህ የሚታያቸው “ከሀገር የሚሰፋው ሆዳቸው” ነው። ሀገር አፍ አውጥተሽ ተናገሪ ቢሏት ስለነዚህ ሰዎች ቃላት የሚያጥሯት ይመስለኛል።

    በሌላ ወገን እነዚህ ሰዎች በሰይፉ መታፈርያ ፍሬው አንዲት የግጥም አንጓ እንዲህ ይታዩኛል:-

    ይህ ዓለም ይህ ዓለም” ይላሉ፥
    ይህን ዓለም ሞልተው እንደኖሩ ሁሉ።

    ሀገሩ የማናየው፣ የማናውቀው፣ የማንሰፍረው፣ የማንለካው፣ የማንገምተው ጭምር ብዙ ጉዳይ አለው፤ ዓለም ሰፊ ነው። ይህን ሲያውቅ ሰው ትህትና ትዘልቀው ይመስለኛል።

    1. ጩኸት መቀማት ዓይነተኛ ጠባያቸው/ፍሬያቸው ነው። በዚህ ጠባያቸው “ራሳቸው ገርፈው ራሳቸው አልቃሽ” በመሆን ከፊት ተሰላፊ ናቸው።
    2. ስለመቃወም መቃወም የሚያስገኘውን ትርፍ ያሰላሉ። ጀብድ እንጂ ጀግንነት አያውቃችውም።
    3. ተቆርቋሪ ከሚመስለው የፊት ገፃቸው ባሻገር ድብቁ ህልማቸው ሆድ መሙላት ወይም ጥቅም ማሳደድ በመሆኑ ያቀዱት ሲከሽፍ ካሸናፊው ጎን ለመሰለፍ እፍረት አታውቃቸውም። የጠበቁት ጥቅም ካልተገኘ ጠላት ለመሆን እንዲሁ አይሰንፉም፤ ይቸኩላሉ።
    4. በእነሱ ዘንድ ወዳጅ ማለት ከጠባብ ሆዳቸው የመንጨ ደካማ ህልማቸውን የሚያገለግል እና ለሙት ህልማቸው ሕይወት መዝራት “ለምን? “ ሳይል የሚሰለፍ agent/object ነው።

    እነዚህ ሰዎች ውድጅት የሚያስፈልጋቸው የሰው ልጅ ለብቻው የማይገፋቸው በርካታ ሕይዎታዊ ጉዳዮች ስላሉት ነው። ወዳጅነት ለብቻ የማይገፋውን ለመግፋት የሚመሠርቱት ስላታዊ ኮንትራት ወይም ‘strategic alliances’ ነው። እንደተራራ የከበዳቸውን ሸክም ካራገፉ በኋላ ግን “ሆዳቸው አምላካቸው” ሆኖ ያርፈዋል።

    በተለምዶ “ባንዳነት” ለፍርፋሪ ተገዝቶ ከውጭ ጠላት ጋር በግልፅ በመወገን ሀገርን መጉዳት/መክዳት ብቻ የሚመስለው ብዙ የዋህ አለ። ነገር ግን ባንዳነት መጠነ ዙሪያው እጅግ ሰፊ ነው። የሀገርን ህልም ለግል ሆድ መሸቀጫ ማድረግ መጠኑም ልኩም ካቅም በላይ ነው።

    የገዳይ ወንድማማቾቹን መስፋፋት በማኅበራዊ ድረ-ገፆች፣ በቴሌቪዥን መስኮቶች፣ በሬዲዮና በመሰለው ሁሉ አዋጅ ነጋሪ ሆነው ማየት አዲስ አልሆን አለ፤ ተለመደ። የምናዋጣት ማንኛዋም “ቅንጣት” ነገ ለሚፈጠረው ሀገራዊ ግዙፍ ምስል አስተዋፅኦ ስላለው እየተስተዋለ ለማለት የተፃፈ። ምክሩ መካሪውን እንዲጨምር ይሁን አሜን!

    አገኘሁ አዳነ ድልነሳሁ

    አቶ አገኘሁ አዳነ ድልነሳሁ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፥ ቲያትርና ጥበባት ኮሌጅ ውስጥ በሚገኘው አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተርና መምህር ናቸው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    የገዳዮች ወንድማማችነት

    #16110
    Anonymous
    Inactive

    ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ለክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ
    ነጋችንን እንዳንፈራ ሕግ ተርጓሚው ይፈራ!

    ክብርት ፕሬዝደንት፥ እንደሚያውቁት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ባለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በጭፍን ከመደገፍ እና ከመቃወም ወጥቶ በምክንያት መቃወም እና መደገፍ የፖለቲካ ባህል፣ አስተሳሰብ እንዲገነባ የራሱን ሚና ሲጫወት የቆየ ፓርቲ ነው። ይሄ ስልጡን የፖለቲካ ባህል እንደምንፈልገው ፍሬ ባያፈራም ቀላል የማይባል የፖለቲካ ባህል ለውጥ ጭላንጭል አይተናል ብለን እናስባለን። ይህን አዲስ ባህል የፈጠረ ፓርቲ ግን ለሱ የሚመጥነውን ያህል ክብር ሊሰጠው ቀርቶ በየዘመኑ የመጡ ገዥዎች አና ጽንፈኛ ፖለቲከኞች በሴራ አላላውስ ብለውታል።

    ኢዴፓ ከለውጡ በፊት ባሉት ሁለት ዓመታት እና ከለውጡ ማግስት ባሉ ሁለት ዓመታት የተቀነባበረ በሚመስል ደረጃ ፓርቲያችንን የማዳከም እና ከፖለቲካው መድረክ እንዲገለል የማድረግ ከፍተኛ ደባ እየተሠራበት ይገኛል። ይህን በፓርቲው ህልውና ላይ የተቃጣውን መሠረተ ሰፊ የማፍረስ እርምጃ በተለያዩ መድረኮች እያሸነፍን እዚህ ብንደርስም፥ አሁንም ድረስ በግፍ የተነጠቅነውን የፓርቲውን ቢሮዎች፣ ንብረቶች ገንዘቦች እና ሰነዶች ለማስመለስ በፍትህ አደባባይ እየታገልን ነው። አሁንም በቢሮክራሲ ውጣ ውረድ እየተንገላታን ነው፤ ባለፉት አራት ዓመታት በፓርቲያችን ህልውና ላይ እየደረሰ ያለውን ፈተና እየታገልን ባለንበት ሁኔታ ይባስ ብሎ የአርቲስት ሃጫሉን ሞት ተከትሎ ሌላ የፖለቲካ ጫና እየደረሰብን ይገኛል። ይኸውም የፓርቲያችን ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ያለጥፋታቸው የፖለቲካ ጥቃት ሰለባ እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋልል። አቶ ልደቱ በወንጀል ድርጊት ውስጥ መሳተፋቸው በተጨባጭ ማስረጃ እስከተረጋገጠባቸው ድረስ አይያዙ አንልም፤ ለሕግ የበላይነት ሲታገል የኖረ ፓርቲ በዚህ ረገድ ምንም ብዥታ የለበትም። ነገም ከነገ ወዲያም ማንም በፖለቲካ ፓርቲ አመራርነትና አባልነት ስም ከሕግ ማምለጥ አለበት ብለን አናምንም፤ ነገር ግን ፖሊስ እርቸውን አስሮ ማስረጃ ሲፈልግ ሲታይ፣ ማስረጃ ማቅረብ ተስኖት ፍርድ ቤት ልቀቅ ብሎ ሲወስን እምቢኝ ካለ የታሰረው ወንጀል ሠርቶ ሳይሆን ለምን የተለየ አሰብክ ተብሎ እንደሆነ ድርጊቱ ያሳብቃል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ልደቱ መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በማቅረባቸውና በመቃወማቸው ብቻ እንደታሰሩ በፍትህ ሂደቱ ላይ የታዩትን ህጸጾች ስለታዘብኩ ነው ለእርስዎ አቤት ማለቴ። አቶ ልደቱ የሃጫሉን ሞት ተከትሎ ሁከት በተቀሰቀሰበት ሰዓት የፌዴራል ፖሊስ ለህይወትህ ያሰጋሃል ብሎ አጅቦ ከቢሾፍቱ ወደ አዲስ አበባ አምጥቷቸዋል። ይሄ ሆኖ ሳለ በፖሊስ የተከሰሱበት እና የተጠረጠሩበት ወንጀል የቢሾፍቱ ከተማ ወጣቶችን አደራጅተሃል፣ በገንዘብ ረድተሃል እና አስተባብረሃል ቢሆንም ተጨባጭ ማስረጃ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ሊያቀርብ አልቻለም። በኋላም የተሰጠውን የምርመራ ግዜ በመጨረሱና አቃቢ ሕግም ተጨማሪ የምርመራ ግዜ ባለመጠየቁ ፍርድ ቤቱ በነፃ አሰናብቷቸዋል። ነገር ግን ይህንን የፍርድ ቤት ውሳኔ ሰምቶ ፖሊስ መልቀቅ ሲገባው፥ ከ17ቀናት በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ አስሮ ሲያሰቃያቸው ቆይቷል። እኛም በፍትህ ሂደቱ ተስፋ ቆርጠን፣ አቶ ልደቱም ጠበቆቻቸውን አሰናብተው ፌደራል ላይ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ልንመሠርት ስንዘጋጅ ደግሞ ሌላ ክስ አዳማ ላይ ተከፈተባቸው።

    ይሄ ክስ በመጀመሪያው የቢሾፍቱ ከተማ የክስ መዝገብ ላይ ሕገ-ወጥ ሽጉጥ ተገኝቶባቸዋል ተብሎ ማስረጃ ቀርቦበት ውድቅ የተደረገ የክስ ጭብጥ ነው። የሆነው ሆኖ በሕገ-ወጥ መሣሪያ በመያዝ በሚል ምሥራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢከሰሱም ፍርድ ቤቱ የአቃቢ ሕግንና የጠበቆቻችንን የሕግ ክርከር መርምሮ አቶ ልደቱን በ100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ብር ዋስትና ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ወሰነ። እኛም 100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ብር አስይዘን ማስፈቻ ትዕዛዝ ለፖሊስ ብንወስድም አሁንም ፖሊስ ትዕዛዙን አልፈፅምም አለ። እኛም ትዕዛዙን ለሰጠው ፍርድ ቤት አቤት ብለን መልስ ሊነገረን ለበነጋታው ቀጠሮ ይዘን መጣን። ነገር ግን ማታ የአቶ ልደቱ ዋስትና እንደታገደ በመገናኛ ብዙኃን ሰማን። በዚህ ሁኔታ አቶ ልደቱ ከልብ ህመም ጋር ተያይዞ የልብ ቀዶ ጥገና ባደረጉበት አሜሪካ ቀጠሮአቸው እንዲያልፍ ተደርጎ፥ ከዚህ በተጨማሪ ካለባቸው የአስም ህመም የተነሳ ለኮሮና ተጋላጭ መሆናቸው በሐኪሞችም በፍርድ ቤቶቹም ታምኖበት ጭምር ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ የተደረገው ጥረት በፖሊስ እምቢተኝነት ህይወታቸው አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጓል። በሂደቱ ሁሉ አቶ ልደቱ እያቀረቡት ያለው ቅሬታ ሁሉ ተቀባይነት እያጣ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ እየተሻረ የፖለቲካ ውሳኔ አሸናፊ እየሆነ ይገኛል። አሁንም እንደቀጠለ ነው። እና በፍትህ አደባባይ አቶ ልደቱ ደግመው ደጋግመው ነፃ ቢሆኑም ፖሊስ አለቅም ማለቱን ሳይ ነው የአቶ ልደቱ እስር ሕግ ጥሰው ሳይሆን በፖለቲካ እስር ነው ብዬ በእርግጠኝነት መናገሬ፤ እንጂማ ሁለቴ ያሸነፈ አይደለም አንድ ግዜም ያሸነፈ ቤቱ እስር ቤት አይሆንም ነበር። ይሄ የሚያሳየው የፍትህ ሥርዓቱ ላይ የበዛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መኖሩን ነው።

    ክብርት ፕሬዝደንት፥ የፍትህ ተቋሙ በእርስዎ መመራት ሲጀምር በፍትህ መጓደል ላለፉት 27 ዓመታት ፍዳውን ሲያይ የነበረው ዜጋ እፎይ ይላል ብዬ በግሌ ተስፋ አድርጌ ነበር፤ ሕግ ተርጓሚው ከሕግ አስፈፃሚው ተፅዕኖ ወጥቶ የሚገባውን ክብር እና የሚወስነውም ውሳኔ በአስፈጻሚው አካል ሳይሸራረፍ ተፈፃሚ ይሆናል ብዬም ነበር። ፍትህ እና ርትዕ በእርስዎ አመራር ይሰፍናል ብዬ በእርስዎ የቀደመ ልምድ ፍፁም ተማምኜ የነበረ ቢሆንም እየሆነ ያለው የተገላቢጦሽ ነው። ፍትህ ከቀደመው ጊዜ በባሰ ችግር ውስጥ መውደቁን እኔ በግሌ በዚች ሁለት ወር በተግባር ባየሁት ነገር አረጋግጫለሁ። እርስዎ የተሰጠዎትን ኃላፊነት ያለምንም ፍርሃት እና ይሉኝታ ለመወጣት ከሞከሩ የፍትህ ሥርዓቱ ወደ መስመር ውስጥ መግባቱ አይቀርም፤ ግን ክብርት ፕሬዝደንት ለተቋማዊ ለውጥና ከታሪክ ተጠያቂነት ለመዳንም የበኩልዎን ይወጡ።

    ክብርት ፕሬዝደንት፥ ዜጋ በፍትህ ሥርዓቱ ተስፋ ሲቆርጥ ለሥርዓት አልበኝነት መንገድ ይከፈታል፤ የሞራል ልዕልና ቦታ አጥቶ ፍትህ በየአደባባዩ ትረገጣለች፤ ዜጋ በራሱ መንገድ ፍትህን ይፈልጋል፤ ፍትህን በራሱ ህሊና ተመርቶ ለመስጠት ይገደዳል። ያኔ እንደ ሀገር ዜጋው ወጥቶ የመግባት፣ ሠርቶ ሀብት ንብረት የማፍራት መብቱ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ እርስዎ የሚመሩት ተቋም ክብርና ሞገሱን ካጣ የሀገር ክብር እና ሞገስ ጠፍቶ እንደ ሀገር የመኖር ህልውናችንም አደጋ ውስጥ ይወድቃል። የመንግሥት መኖር ምልክት የሆነው ሕግና ሥርዓት ጠፍቶ ባለፈው እንዳየነው በየአካባቢው የደቦ ፍርድ ይነግሳል። አቶ ልደቱስ በፖለቲካው ባላቸው ተደማጭነት እና ተሰሚነት ድምፅ የሚሆናቸው ብዙ ነው። በዚህ ሁኔታ ተራው ዜጋ ምን ያህል በፍትህ ሥርዓቱ ፍዳውን ሊያይ እንደሚችል ተገንዝበውታል? ለእርስዎ ተቋም ክብር የሚመጥን የፍትህ ሥርዓት አለ ብለው ያምናሉ? አይመስለኝም ፍትህ እና ርትዕ እንዲሰፍን፣ እንዳይጓደል የበለጠ ሥራ በመሥራት የዳኞችን ክብር ያስመልሱ። ዳኞች የሚፈርዱት ፍርድ በአስፈፃሚው አካል ሲደፈጠጥ ማየት ያሳፍራል፣ ያሸማቅቃል ነገን እንድፈራ ያደርጋል። ነጋችንን እንዳንፈራ ሕግ ተርጓሚው ይፈራ! ስለዚህ ክብርት ፕሬዝደንት፥ ጉዳዩ የአቶ ልደቱን ጉዳይ የፍትህ መጓደል ብቻ አድርገው አይቁጠሩት። በህይወት የመኖር እና ያለመኖር የመብት ጥያቄ ነው እያቀረበ ያለው። በፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይሆን በአስፈፃሚው ጡንቻ በህይወቱ ላይ አንድ ነገር ቢደርስስ ማን ነው ተጠያቂው? በተለይ የሃጫሉን ሞት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የታዘብኩት ዜጎች ወደ ፍትህ ሳይቀርቡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እየተጉላሉ መሆኑን ነው። በየማጎሪያው እየተሰቃዩ ነው፤ የፍትህ ያለ እያሉ ነው። አሁንም እደግመዋለሁ ወንጀል የፈፀመ አይታሰር አልልም፤ ግን ከሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ ውጭ ዜጎች መጉላላት የለባቸውም፤ የተፋጠነ ፍትህ ይሰጣቸው፤ ሰብዓዊ መብታቸው ይጠበቅላቸው። ይህን በሁለት ወር ውስጥ የታዘብኩት ነው። ይህ የሚያሳየው የፍትህ መጓደል በሌሎች ክልሎች ላይም ቀላል በማይባል ደረጃ ችግሩ መኖሩን ነው። በቢሾፍቱና አዳማ ዋስትና ተፈቅዶላቸው ከወር በላይ ፖሊስ አለቅም በማለቱ በእስር የሚማቅቁ ብዙ ዜጎች እንዳሉ ያገኘኋቸው የሕግ ባለሙያዎች አጫውተውኛል። ፍትህ ተጠምተው በየእስር ቤቱ የሚሰቃዩ ብዙዎች ናቸው። ለፍትህ መከበር ሁሉም ሊጮህ ይገባል። ፍትህ በጉልበተኞች ጫማ ሲደፈጠጥ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሳልና!

    ክብርት ፕሬዝደንት መዓዛ፥ ይህችን ግልፅ አቤቱታዬን ሰምተው በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ነፍስ ይዘሩበታል፤ በየማጎሪያ ካምፑ ያሉ የብዙ ዜጎችን እንባ ያብሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አመሰግናለሁ።

    ከከበረ ሰላምታ ጋር!
    አዳነ ታደሰ
    የኢዴፓ ፕሬዝደንት

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    የጠቅላይ ፍርድ ቤት ክብርት ፕሬዝደንት መዓዛ አሸናፊ

    #16193
    Anonymous
    Inactive

    የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ! ኦሪት ዘህወሓት!
    (ታዬ ዳንደአ)

    የግራ አስተሳሰብ ሁሌ ግራ ተጋብቶ ግራ ያጋባል። ህወሓት የግራ ጁንታ መሆኑ ይታወቃል። የግራ ፖለቲካ ደግሞ ውሸት ሲደጋገም እውነት እንደሚሆን ያምናል። “መስከረም 25/30” የሚደጋገመዉ ለዚህ ይመስላል። ህወሓት ከፈረሶቹ ጋር ብቅ ጥልቅ እያለ ይፎክራል። በሕገ-መንግሥት እና በፌዴራሊዝም ስም ያለቃቅሳል። ከመስከረም 25/30 በኋላ መንግሥት ስለማይኖር “ባለአደራ መንግሥት ከሰማይ ይዉረድልኝ” ይላል። ኢትዮጵያን ወደ ሊቢያ ለመቀየር አቅዶ በሙሉ ኃይሉ ይንደፋደፋል! በእርግጥ ዋነኛ እቅዱ ሰኔ 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ተሞክሮ በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ከሽፏል! አሁን ቅዠትን እዉነት ለማድረግ በህወሓት አሻንጉሊቶች በከንቱ ዳንኪራ ይመታል። ይህ በአማርኛ ‘የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ’ ይባላል!

    የህወሓት ህልም ሩቅ ኖሯል። ኢትዮጵያዊያንን ከፋፍሎ እየገዛ ለመቶ ዓመታት ኢትዮጵያን የመጋጥ ግልፅ ዕቅድ እንደነበረዉ ይታወቃል። በዚሁ አግባብ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያዊያን ሰቆቃ ውስኪ እየተራጬ ሲንደላቀቅ ኖሯል። ያ ሁኔታ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ላይ አክትሟል። በኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመናት ትግልና በለውጥ አመራሩ ቆራጥ ውሳኔ የህወሓት ጉልበት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተንኮታኩቷል፤ ነገር ግን እዉነታዉ አልዋጥ ብሎታል። የቀን ቅዠት እዉን እየመሰለዉ አስቸግሮታል! ሁሌ ድምፂ ወያኔ ላይ ወጥቶ “ከመስከረም በኋላ ከኔ ውጭ ሌላ የለም” ይላል። “የለም! የለም!” እያለ ግልፅና ተጨባጭ እዉነታን መሰረዝ ይፈልጋል። መቼስ ከዚህ በላይ የሚገርም በዓለም ላይ ምን ይኖራል? ህወሓት ከነሙሉ ጥርሱና ጥፍሩ በነበረበት ወቅት ታግሎት ያቃተዉን ለዉጥ ከሬሳ ሳጥን ደጃፍ ሆኖ “የለም!” በማለት ብቻ ለመቀልበስ ይሞክራል!

    ዘንድሮ ‘ሰይጣን ለተንኮሉ ቅዱሳን መጽሐፍትን ይጠቅሳል’ የሚባለዉ በግልፅ መታየት ጀምሯል። ህወሓት በምክንያት የኢሬቻ 2013 ዋነኛ አቀንቃኝ ሆኖ ብቅ ብሏል። በኢሬቻ አስታኮ አዲስ አበባ ላይ ተጀምሮ አዲስ አበባ ላይ እንዲያልቅ ታቅዶ የከሸፈዉን ጦርነት ዳግም ለማወጅ ፈልጓል! ፍላጎቱን ለማሳካት ደግሞ በኦሮሞ ስም የሚነግዱ አሉላ የሚቀልባቸዉን ፈረሶች አዘጋጅቷል! በፈረሶቹ በኩል የኦሮሞ ወጣት ኢሬቻን አሳቦ በነቂስ በመዉጣት ሸገር ላይ እንዲረብሽ ይቀሰቅሳል። በዲጂታል ወያኔ ደግሞ “ኢሬቻ የሰይጠን አምልኮ ነዉ” እያለ በአማራ ስም ያሰራጫል። የኦሮሞን ሕዝብ ‘ጋኔን’ ያለዉ ህወሓት መሆኑ ግን ይታወቃል። በተጨማሪም “ኢሬቻ አዲስ አበባ ላይ መከበር የለበትም!” እያለ በሌላዉ አሻንጉሊቱ በኩል የሸገር ወጣቶችን ይቀሰቅሳል። ኢሬቻ 2009ን የዘነጋነዉ መስሎታል። ያኔ ቢሾፍቱ ላይ በአንድ ቀን ብቻ ከ700 በላይ የኢሬቻ ታዳሚ ኦሮሞዎች በወያኔ አግዓዚ ገደል ውስጥ ተጥለዉ ሞቷል። በዚያ ወሳኝ ወቅት “የኦሮሞ ደም ደሜ ነዉ” ያሉትን የጎንደር ወጣቶች ታሪክ መዝግቧል። ኢሬቻን መደገፍ እና ማሞገስ ከቁርጥ ቀን ወገኖች ያምራል! ዛሬ ወያኔ በግራና በቀኝ የሚያጫውታቸዉን አሻንጉሊቶች ማን ይሰማል?

    ታዲያ በመጨረሻ ምን ይሆናል? ውሾቹ እየጮሁ ግመሉ ይጓዛል! ባቡሩ ፍጥነቱን እና አቅጣጫዉን ጠብቆ ወደፊት ይገሰግሳል። ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት በከፈሉት ውድ ዋጋ የመጣዉ ለውጥ ከመስከረም 25/30 በኋላም ተጠናክሮ ይቀጥላል! የተቋማት ግንባታ እና ብሔራዊ ውይይት መሠረት ይይዛል። በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይፈጠራል። ህወሓት ሲያበላሸዉ የነበረዉ ብሔራዊ ምርጫም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልፅ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ይከወናል። የማይኖረዉ ህወሓት እና ተፅዕኖዉ ብቻ ይሆናል። ጓድ ህወሓት ቀስ እያለ ወደ መቃብሩ ጠጋ ጠጋ ይላል! በትግራይ ላይ ጠባሳ ሳይጥል፤ ማንም ሳይነካዉ ራሱን ችሎ ይሞታታል! የትግራይ ሕዝብም እንደወገኖች የነፃነትን አየር ይተነፍሳል! አሉላ ፈረሶቹን የሚቀልብበት መኖ ያጣል። በዚያዉ ጋብቻዉ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ይፈርሳል። አሻንጉሊትም አስታዋሽና አጫዋች ያጣል! የሴራና የሸር ሥራ ብኩን ይሆናል። የሌብነት፣ የውሸት፣ የፅንፈኝነት እና የክፋት ዘመን ያበቃል! እዉነት እና ዕዉቀት መርህና መመሪያ ይሆናል! የኢትዮጵያ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት እና ብልጽግና ደግሞ እየጎለበተ ይሄዳል! የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድማማችነትን መሠረታዊ መርሁ አድርጎ በድል ላይ ድል ይጎናጸፋል! ይህ ቃል ነዉ! ቃል ይነቅላል! ቃል ይተክላል! አሜን!!

    ታዬ ዳንደአ

    አቶ ታዬ ዳንደአ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ቃል አቀባይ ናቸው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ ታዬ ዳንደአ

    #16206
    Anonymous
    Inactive

    ህወሓት እና ISIS
    ታደሰ ብሩ ኬርሰሞ (ዶ/ር)

    ህወሓት እና ISIS
    ታደሰ ብሩ ኬርሰሞ (ዶ/ር)

    Islamic State of Iraq and Syria (ISIS) እስካሁን ከፍተኛው ደረጃ የደረሰ (አራተኛ ትውልድ/ 4th generation) የሽብር ድርጅት ነው። ISIS ቀድሞ ከነበሩት የሽብር ድርጅቶች በተለየ መንገድ ከሌሎች የሽብር ድርጅቶች ጋር አይጣላም፤ ይልቁንም ሌሎችን እያቀፈ፣ እያስተባበረ ራሱን ያባዛል። እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደኋላ ተመልሶ የኦቶማን ኢምፓየርን (Ottoman Empire)፤ ጥንታዊቷና ገናናዋን ሌቫንት (Levant/ የዛሬዎቹን ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ፣ እስራኤል) በማስታወስ የመካለኛው ምስራቅ፣ ሰሜንና ሰሜን ምስራቅ አፍሪቃ አገራት ሕዝቦች “በምዕራባዊያን ተበደልን፤ ተገፋን” ቁጭት ውስጥ እንዲገቡና ‘የጥንቱን ገናናነት ለማስመለስ’ ከጎኑ እንዲሰለፉ ያደርጋል። ISIS ብሶትንና ቁጭትን በመጠቀም ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የሕዝብ ድጋፍ የነበረው፤ በርካታ ወጣቶችንና ምሁራንን ያሰባሰበ ድርጅት ነበር፤ አሁንም ነው። ISIS አስደንጋጭና ዘግናኝ ርምጃዎችን በመውሰድ በሽብር ራሱን አግንኗል፤ ጭካኔ እንደ ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ጭምር ተጠቅሟል።

    ISIS በያዛቸው ቦታዎች የሕዝብ አስተዳደር ሥራዎችን ያከናውናል፤ ‘ልማትን’ ያፋጥናል፤ ግብር ይሰበስባል፤ ከመንግሥታትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ይዋዋላል፤ ይነግዳል… በዚህም ምክንያት ሽብርተኛ ከፊል መንግሥት (Terrorist Semi-State/ TSS) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በብዙ ሀገራት ትብብርና ርብርብ አቅሙ እንዲዳከም ባይደረግ ኖሮ ISIS በ2015 (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) በዓለም ላይ ጥሎ የነበረው ስጋት እጅግ ከፍተኛ ነበር። የዛሬ 5 ዓመት ከነበረው ቀነስ ይበል እንጂ ዛሬም ስጋቱ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም።

    በእኔ ግምት ህወሓት የአፍሪቃ ቀንድ ISIS የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው። የጥንታዊ የአክሱም ስልጣኔን ትርክት እየመገበ የትግራይ ወጣቶችን በቁጭትና ብሶት እያነሳሳ ነው። ለወደፊቱ ትልቅ ግዛትን (ኤርትራን፣ ከፊል አማራንና ከፊል አፋርን) እያመላከተ ለጊዜው በያዘው አነስተኛ ግዛት ውስጥ እንደ መንግሥት ከሌሎች መንግሥታትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ይዋዋላል፤ ‘ልማትን’ ያፋጥናል፤ ይደራደራል፥ ይነግዳል። ሌሎች አባሪ ድርጅቶችን በመላው ኢትዮጵያ እየፈለገ ያደራጃል፤ ያስተባብራል፣ ያሰለጥናል። ይህን በማድረጉም “ጥቂት” እየተባለ መናናቅ የማይገባው የሕዝብ ድጋፍ ያለው ድርጅት ነው። ልክ እንደ ISIS ሁሉ ህወሓትና አባሪዎቹ አስደንጋጭና ዘግናኝ ርምጃዎችን እየወሰዱ እያሸበሩን ነው። ህወሓትና አባሪዎቹ ሽብርን እንደ አዋጪ ታክቲክ እየተጠቀሙ ነው። በእኔ ግምት ህወሓት የአፍሪቃ ቀንድ ISIS የመሆን መንገዱን ጀምሮታል።

    ISIS በዓለም ላይ የጋረጠውን አደጋ ለመቋቋም የተደራጀ ርብርብ እንደተደረገ ሁሉ በህወሓት ምክንያት አደጋ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ ሁሉ መተባበር ይኖርባቸዋል። ህወሓት የሚፈጥረው አደጋ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአካባቢው አገሮች ሊተርፍ የሚችል መሆኑ የቀጠናው መንግሥታት እንዲረዱ መደረግ ይኖርበታል።

    ህወሓትን ማዳከም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ የሀገርና የሕዝብ ደህንነት ጉዳይ ነው የሚል ብርቱ እምነት አለኝ። ‘ህወሓትን ማዳከም’ ምን ማለት እንደሆነም ሊብራራ ይገባል። እኔ የህወሓት በማናቸውንም ደረጃ ካለ የመንግሥት ስልጣን መውጣት የመዳከው ማሳያ መሆን ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ። ህወሓት የክልል ይቅርና የዞን ስልጣን እንኳን ይዞ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ምርጫ ይደረጋል የሚል ግምት የለኝም። ህወሓት የክልል ስልጣን ይዞ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ይኖራል ማመን ሞኝነት ነው።

    ስለሆነም የፌደራል መንግሥቱ ቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት ህወሓትን ማዳከም ነው። ከትግራይ ጋር የሚዋሰኑ የክልል መንግሥታትና የፌደራል መንግሥት ተናበውና ተቀናጅተው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። ይህን በአፋጣኝ፣ በተጠናና በተደራጀ መንገድ መፈፀም ይኖርበታል፤ ለውጥ ፈላጊ ትግራዋይ ወገኖቻችን በዚህ ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።

    ታደሰ ብሩ ኬርሰሞ (ዶ/ር)

    ዶ/ር ታደሰ ብሩ ኬርሰሞ ነዋሪነቱ ለንደን፥ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሲሆን፤ እዚያው ለንደን በሚገኘው ግሪንዊች የሥራ አመራ ተቋም (Greenwich School of Management) ውስጥ በመምህርነት ይሠራል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    ዶክተር ታደሰ ብሩ ኬርሰሞ

    #16310
    Anonymous
    Inactive

    በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ ይቆጠራል
    አንዱዓለም አራጌ

    ከዚህ ቀደም በጣም በአመዛኙ የፓርቲዬን አቋም ካልሆነ በስተቀር እምብዛም የግል አቋሜን አንፀባርቄ አላውቅም።

    ብዙውን ጊዜ ተቋሞቻችን ሕጸጻቸውን እያረሙ ሁላችንም የምንደገፍባቸው ተቋማት እንዲሆኑ እድልም ሆነ ጊዜ መስጠት ተገቢ መሆኑን አምናለሁ። ይሁን እንጂ፥ ትናንት የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፍስና በስጋው ተወራርዶ መራር ሕዝባዊ ትግል ያደረገው ዝቅ ብለን የምንመለከተውን ዓይነት ግፍ ለማስተናገድ አለመሆኑ እሙን ነው።

    በ1993 ዓ.ም በጊዮርጊስ የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት በተለያዩ ሁለት ችሎቶች፣ በተመሳሳይ ዕለት፣ በተመሳሳይ ሰዓት የተፈፀሙ ሁለት ውሳኔወችን ለማስታወስ እወዳለሁ። አንደኛው ችሎት በሀቪየስ ኮርፐስ (habeas corpus) ክስ አማካኝነት፣ እነአቶ ታምራት ታረቀኝን ካሰረበት አምጥቶ ለፍርድ ቤቱ ያቀርብ ዘንድ ፓሊስን ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ቢያዝም፥ ትዕዛዙ ባለመፈፀሙ በወቅቱ የፍትህ ሚንስትር የነበሩት አቶ ወረደወልድ ወልዴ ታስረው እንዲቀርቡ ባዘዘው መሠረት ታስረው ቀረቡ። ፍርድ ቤቱም የአንድ ወር እሥራት ፈረደባቸው። በሌላ ደግሞ የዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ችሎት አቶ ስዬ አብርሃ ቀርበው የወ/ት ብርቱካን ችሎት አርነት ሰደዳቸው። ይሁን እንጂ ለቤታቸው ሊበቁ የተገባቸው አቶ ስዬ አብርሃ በአፈሙዝ አስገዳጅነት ወህኒ እንዲወርዱ ተገደዱ። ሚኒስትር ወረደወልድ ወልዴ ደግሞ ሳይገባቸው ለሞቀ ቤታቸው በቁ።

    ይህን የሃያ ዓመት ታሪክ ያለምክንያት አላነሳሁትም። ከእልህ አስጨራሽ ሕዝባዊ ትግል በኋላ የለውጥ ሽራፊ ለማየት ብንጓጓም ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ለከት ያጣ ግፍ እያስተናገድን ነው። በ”ለውጡ” የመጀመሪያ ወራት ሕዝቡ የተራበ አንጀቱን አስሮ ይስቅ የነበረው፣ ድጋፉንም የቸረው ከእንግዲህ በፍትህ፣ በእውነትና በእኩልነት የምጠግብበት ዘመን ጠባ ብሎ በማመኑ ይመስለኛል። ከፈጣሪ በታች ተስፋችን በእጃችን መሆኑ የቀትር ያህል ግልፅ ቢሆንም፣ ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ የፍትህን መጨንገፍን ሳይ ጥልቅ ሀዘን አልተሰማኝም ብል ግን እውነቱን አልናገርም።

    በቅርቡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሥራ አስፈፃሚ አባል ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ ፍርድ ቤት የዋስትና መብቷን ቢያከብርላትም፥ ፓሊስ ላለመልቀቅ ያሳየውን ዳተኝነት እናስታውሳለን። በተመሳሳይ የአሥራት ቴሌብዥን ጋዜጠኞችንም እንዲሁ በመከራ መልቀቁ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

    ዛሬ ብዕሬን እንዳነሳ ያደረገኝ ጉዳይ የአቶ ልደቱ አያሌው ጉዳይ ነው። ስለአቶ ልደቱ ከእኔ በላይ ብዙ ነገሮችን አጣቅሶ ማቅረብ የሚችል ሌላ ማን እንዳለ በእውነት አላውቅም። በፓርቲዬም ላይ ቢሆን በተደጋጋሚ ምን ያደርጉ እንደነበር ፈፅሞ ዘንግቼው አይደለም። አቋማቸው ከአቋሜ ስለገጠመም አይደለም። ይልቅስ አቶ ልደቱ እራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት በዚህ ሁኔታ አንዳች አሉታዊ ጉዳይ አንስቼ እሞግታቸው ዘንድ ፈፅሞ ህሊናዬ አይፈቅድልኝም።

    በተወሰነ መልኩ የቀደመውን ለአንባቢ ያስታወስኩትም ቢሆን፥ የቆምኩበትን የሀሳብ ማዕዘን ለማሳየት ይረዳኝ ዘንድ ግድ ሆኖብኝ እንጂ ምቾት ተሰምቶኝ አይደለም። ይልቅስ ከላይ ከፍ ብዬ ከጠቀስኳቸው ወገኖቻችንም በከፋ ሁኔታ የ“ፓሊስ ጢባጢቤ” መጫወቻ ሆነው ሳይ፥ እርሳቸውን የወጋ ጦር እኔንም እንደወጋኝ ተሰምቶኛል። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር እንዲለቀቁ ቢያዙም በፓሊስ እንቢተኝነት ግን በእስር ላይ ይገኛሉ። ውርደቱ፣ መረገጡ፣ ንቀቱና ኢፍትሃዊነቱ፣ የኢፍትሃዊነትን ስቃይ ለምናውቅ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ነው። በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ የሚጠራጠር ካለ እርሱ ፍፁም ማስተዋል የጎደለው ነው።

    በኢትዮጵያችን እየታየ ያለው ለከት ያጣ ግፍ ቅስም የሚሰብርና በምንም ዓይነት መንገድ ልንታገሰው የማይገባ ኢፍትሃዊ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ያዋረደ ወደር-አልባ የነውረኝነት ተግባርም ነው።

    በፈጣሪ እንደምትታመኑ ደጋግማችሁ የነገራችሁን ወገኖች፥ በሚፈፀመው ግፍ ፈጣሪ የሚደሰትበት ይመስላችኋል? የሚሠራውን ኢፍትሃዊነት በአስቸኳይ እስካላስቆማችሁ የፈጣሪም ሆነ የሕዝብም ቁጣ እሩቅ እንደማይሆን ለመናገር ነቢይነትን አይጠይቅም።

    Free Lidetu Ayalew
    አንዱዓለም አራጌ

    አቶ አንዱዓለም አራጌ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምክትል መሪ ሲሆኑ፤ ከዚያ በፊት ደግሞ የቀድሞው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ፕሬስ ሴክሬተሪ ነበሩ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ አንዱዓለም አራጌ

Viewing 15 posts - 1 through 15 (of 36 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.