Home › Forums › Semonegna Stories › ከመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ ሰሞነኛ ዜናዎችና መግለጫዎች
Tagged: መከላከያ ሚኒስቴር, መከላከያ ሠራዊት, የፌዴሬሽን ምክር ቤት, ፌዴራል ፖሊስ
- This topic has 13 replies, 2 voices, and was last updated 1 year, 7 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 31, 2020 at 2:47 am #16558AnonymousInactive
ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ
(የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮን በተመለከተ)
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ፌዴራዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 87 በተደነገጉ ግልጽ መርሆዎች መከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 1100/2011 በተሰጡት ግዳጆች መሠረት ዝርዝር ተልዕኮዎችን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ደንቦች እና መመሪያዎችን በማውጣት፥ በሀገራችን ላይ የተቃጡ የውጭና የውስጥ ጥቃቶችን በመመከት የሀገራችንን ሉዓላዊነት አስከብሯል። የሕዝብንም ሰላም በማስጠበቅ ላይ ይገኛል።
መከላከያ ሠራዊቱ የአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ሰላም የእኛም ሰላም ነው በሚል መርህ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ተሰማርቶ ዛሬም ግዳጁን በአስደናቂ ሁኔታ በመወጣት ላይ ይገኛል።
ከሁሉም በላይ የዓለም ሕዝቦችና የቀጠናችን ብሎም የሀገራችን ዋነኛ ጠላት የሆነውን አሸባሪነት ለመዋጋት በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ የመሸገውን የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን በመመከት ቀጠናችን ሰላም የሰፈነበትና የተረጋጋ እንዲሆን መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ነው።
በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ አለመረጋጋቶችን ከሌሎች የሀገራችን የፀጥታ ኃይሎች፣ ከክልል መስተዳድሮች፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና በዋነኝነት ከሕዝባችን ጋር በመተባባር ችግሩን ለመቅረፍ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲመጣ ሠርቷል፤ አሁንም በመሥራት ላይ ይገኛል። በዚህ ተግባሩ ሠራዊታችን በደረሰበት ቦታ ሁሉ ሕዝብ ከፍተኛ የሰላም አየር የሚተነፍስ እና እፎይታ የሚሰማው መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ህያው ምስክር ናቸው።
ከእነዚህ የሠራዊቱ አኩሪ ድሎች የምንረዳው ነገር ቢኖር፥ ሠራዊታችን ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል በአንድ ጊዜ ግዳጆችን መወጣት የሚችል፣ ለፈተናዎች የማይበገር፣ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለሕዝቦች ሰላም ሲል ማንኛውንም መስዋዕትነት ከመክፈል ወደኋላ የማይል ሕዝባችን የሚመካበት ሠራዊት መሆኑን ነው።
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥
የመከላከያ ሠራዊታችን የተጋድሎና የአሸናፊነት ገድሉ በወታደራዊ ስምሪት እና የግዳጅ አፈጻጸም ላይ ብቻ ሳይገደብ የሕዝብ ችግር ችግሬ ነው የሚል የሕዝቦች ደህንነትና ኋላ ቀርነት የሚያንገበግበውና የሚቆጨው ያለውን ሁሉ ለመስጠት ወደኋላ የማይል፣ የሕዝባችን አለኝታ የሆነ የልማትና የሰላም ሠራዊት ነው።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአንድነትና የጥንካሬ መለያ የሆነውን ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት ሠራዊቱ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለግድቡ ግንባታ ከወር ደመወዙ በማዋጣት በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ አስተዋጽኦ ከማበርከት አልፎ፤ በግድቡ ላይ ሊሰነዘር የሚችል ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ለመመከት ሌት ተቀን ዘብ ቆሞ በመጠበቅ ላይ ይገኛል።
መከላከያ ሠራዊታችን ከራሱ በፊት ለሕዝቡና ለሀገር የሚለውን እሴት መሠረት በማድረግ የሀገራችን ሕዝቦች ለገጠማቸው ሰው-ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን አብነት የሚሆን ተግባር እየፈጸመ ይገኛል።
በጎርፍ አደጋ ዜጎች የሚደርስባቸውን አደጋ ለመቀነስ፣ በደም ልገሳ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ፣ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ተሰማርቶ በማገዝ፣ በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነውን ኮቪድ-19 በሽታን ለመከላከል፣ ከደመወዙ ቀንሶ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ በማድረግ፣ ገበታ ለሀገር ፕሮጀከት እውን እንዲሆን የወር ደመወዙን በማዋጣት እና በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰተውን የአንበጣ ወረርሽኝ ከሕዝቡ ጋር በመሆን በመከላከል ከፍተኛ ጥረት ያደረገና በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህ ሕዝባዊነቱን ያስመሰከረ ተግባሩን ከመጀመሪያውኑ ሠራዊቱ የታነጸበት መሠረታዊ ባህሪው መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ የሚያውቀው ሃቅ ነው።
መከላከያ ሠራዊታችን ሀገራዊ ግዳጆቹን ሲወጣና ሕዝባዊ ተግባራቱን ሲያከናውን የሚገጥሙትን ችግሮች ሁሉ በመቋቋም ፈተናዎችን በጽናት ተጋፍጦ በማለፍና ውድ ህይወቱን መስዋዕት በማድረግም ጭምር መሆኑ በሕዝባችን የሚታወቅ ሃቅ ነው።
ይሁን እንጂ ሠራዊቱ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ሰላም የማረጋገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮውን በጀግንነትና በቁርጠኝነት እየተወጣ ባለበት በዚህ ሰዓት የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት የማይፈልጉ ቡድናዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የሠራዊቱን ስምና ዝና በማጠልሸት በመርህና በሕግ ላይ ያልተመሠረተ የትችት ናዳ በማውረድ ላይ የሚገኙ ቢሆንም፥ ሠራዊቱ ይህን የፀረ-ሰላም ኃይሎች አጀንዳ በውል በመገንዘብ ትኩረቱን ግዳጁ ላይ ብቻ በማድረግ እየሰራ ይገኛል።
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥
ሰሞኑን በተለያዩ የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊ የአቋም መግለጫ በሚል ርዕስ ስር መግለጫ ያወጣው አካል ሠራዊቱን የሚመለከቱ ጉዳዮች የተካተቱበት ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶ አሰራጭቷል።
በዚህ መግለጫ 1ኛ ተራ ቁጥር ላይ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 87(5) ድንጋጌ መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባር ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በሆነ አኳኋን እንደሚያከናውን የተደነገገውን መርህ በሚጥስ መልኩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ተወያይተው ከሚሰጡት መፍትሄ ውጭ መከላከያ የአደረጃጃት፣ የስምሪትና የቁጥጥር ተግባሩን መፈጸም አይችልም በማለት መከላከያ በተቋማዊ ዕቅዱ እንዲሁም ወቅታዊና ሀገራዊ የደህንነት ስጋቶችን መነሻ አድርጎ ግዳጁን እንዳይፈጽም በሚገድብ አኳኋን የተዛባ ይዘት ያለው መግለጫ አውጥቷል።
በዚህ መግለጫ ተራ ቁጥር 5 ላይ ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የወደቀ በዝምታ እንዳለፈና የሕገ-ወጥ የፖለቲካ ኃይሎች ጥቅም አስጠባቂ ኃይል መሆኑን የሚገልጽ መልዕክት በመግለጫ ላይ ተካቷል።
እውነታው የመከላከያ ሠራዊታችን የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ተሰማርቶ አስፈላጊ ተገቢና ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ይህንን በተጻረረ መልኩ ሠራዊቱ ሕዝብን እየጨፈጨፈ ነው በማለት የመከላከያ ኃይሉን የማይመጥን፣ ተቋሙ ለሀገርና ለሕዝብ የከፈለውን እና እየከፈለ ያለውን ክብር መስዋዕትነት የሚያንኳስስ ሀገራዊ ተልዕኮውን እና አኩሪ ታሪኩን የሚያጠልሽ መልዕክት ይህ አካል ባወጣው መግለጫ ተስተጋብቷል።
ይህንኑ መግለጫ ተከትሎ አንዳንድ ግለሰቦች እና ባለስልጣናት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይህ አካል መከላከያን በሚመለከት ያወጣውን መግለጫ በማስተጋባት ፍጹም የሠራዊቱን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ በማራከስ ተግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ።
ይህ ተግባር መከላከያ ሠራዊቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እና በትግራይ ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከክልሉ ሕዝብ ጋር ከፍተኛ ጥረት በሚያደርግበት የክልሉ ሕዝብ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ትርጉም ባለው ደረጃ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን እያስመሰከረ ባለበት እና አጠቃላይ በክልሉ ያለውን ስምሪት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዓላማ አድርጎ ግዳጁን ለመወጣት ዝግጁነቱን ባረጋገጠበት ወቅት የሠራዊቱን ተልዕኮ የሚገድብ መግለጫ ማውጣቱ አግባብነት የጎደለው ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህ መግለጫ የሠራዊቱን ተልዕኮ ያላገናዘበ፣ ግዳጁንም ተንቀሳቅሶ እንዳይፈጽም የሚያስተጓጉል ሀገራዊና ክልላዊ ተግባሮቹንም በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያደናቅፍ ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ ነው።
ከዚህ በፊትም እነዚህ አካላት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች በማስተላለፍ ላይ የነበሩ ቢሆንም ለሕዝቦች ክብር እና ጥቅም ሲባል በከፍተኛ ኃላፊነት መንፈስ ለማለፍ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። መላው የሀገራችን ሕዝቦች እንደሚገነዘቡት የመከላከያ ሠራዊታችን የማንም ፖለቲካ ኃይል፣ ክልል ወይንም ቡድን ጉዳይ አስፈጻሚ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነታቸውን እንዲያስከብርላቸው፣ ሰላምና ደህንነታቸውን እንዲያረጋግጥላቸው የገነቡት ጠንካራ፣ ብሔራዊና ሀገራዊ ተቋም ነው።
ስለሆነም የሠራዊቱን አደረጃጀት፣ ስምሪትና የግዳጅ አፈጻጸም የሚመለከቱ ጉዳዮችን ሠራዊቱ በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠለትን መርህና በአዋጅ የተሰጠውና ግዳጅና ተልዕኮ መሠረት በማድረግ ተግባራቱን በራሱ የሚወስን እንጅ የሠራዊቱን አጠቃላይ ተልዕኮ እኔ ነኝ የምወስንልህ በሚል አግባብ ይህ አካል የሰጠው መግለጫ የሠራዊቱን ገለልተኝነት የሚጋፋ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መግለጫ ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህ ወቅት የሀገራችን ሕዝቦች እንደ ሀገር የገጠማቸውን ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች በመመከት ሰላማቸውን ለማረጋገጥና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት የሀገራችንን እድገት የማይፈልጉ አካላት በተለይ ከሕዳሴ ግድባችን ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግልጽ በሚጻረር መልኩ በእጅ አዙር እና በቀጥታ ጥቃት የሚፈጽሙበትና አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሀገራችንን ወደለየለት ትርምስ ለማስገባት ዓላማ አድርገው በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች በዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ እና የማፈናቀል ወንጀል በመፈጸም ላይ የሚገኙ መሆኑ ይታወቃል።
መከላከያ ሠራዊት ከሕዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ የደህንነት ስጋቶችን ለመመከት የሚያስችል ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ባለበት እና በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተከሰቱ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ለማስቆም አስቸጋሪ የአየር ፀባይ እና መልክዓ ምድራዊ ቦታዎች ዘልቆ ሰፊ ስምሪት በማድረግ፣ ክቡር መስዋዕትነትን በመክፈል የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ጥረት በሚያደርግበት በዚህ ወቅት መግለጫውን ያወጣው አካል የሠራዊቱን ወርቃማ ዕድል በሚያጎድፍ መልኩ ሠራዊቱን በሚመለከት ያሰራጨው መልዕክት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ጉዳዩ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር በቀጥታ የሚቃረን፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስምሪት እና ተልዕኮ በምንም መልኩ በአንድ አካል ወይም ቡድን ስር የማይወድቅ ሕጋዊና ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ አግባብ ብቻ የሚመራ መሆኑን እያስታወቅን፤ መግለጫውን ያወጣው አካል ስህተቱን በይፋ እንዲያርም አጥብቀን እንጠይቃለን። ማንኛውም አካል የሠራዊቱን ተልዕኮ በሚያደናቅፍ አግባብ መግለጫ ከመስጠት እና አላስፈላጊ መልዕክት ከማስተላለፍ እንዲቆጠብም እናሳስባለን።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሀገርና ሕዝብ የሰጠንን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ በገባነው ቃልኪዳን መሠረት ከማንኛውም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ በመሆን፣ ክቡር የሆነውን ህይወታችንን በመክፈል ጭምር የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሰላም ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአስተማማኝ ቁመና ላይ የምንገኝ መሆኑን ለመላው ሕዝባችን እያረጋግጥን የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም እንደወትሮው ሁሉ ከጎናችን ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን።
መላው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አባላት፥
እኛ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በተጋድሎና በድል የደመቀ አንፀባራቂ ታሪክ ያለን ሠራዊት ነን። በከፍተኛ ሕዝባዊ ወገንተኝነትና ፅናት ምድራዊ ፈተና ተቋቁመን እና ጥሰን በማለፍም ለሀገራችን እና ለሕዝባችን ሰላም፣ ደህንነትና ልማት ስንል ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት እየከፈልን አልፈናል። በቀጣይም ከዚህ ጉዟችን ሊያደናቅፉን የሚጥሩ፣ ከተልዕኳችን ሊገድቡን ከሚሞክሩና አንድነታችንን ሊሸረሽሩ በሚታክቱ ማንኛውም ዓይነት ኃይሎች ሴራ ሳንገታ ደማቅ ታሪክ መሥራታችንን እንቀጥላለን።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር
ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያNovember 7, 2020 at 1:18 am #16662SemonegnaKeymasterበወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
አዲስአበባ
ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ምበሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ መሠረት የተለያዩ የፖለካ አካላት ወደ ሀገር መግባታቸው፣ በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ችግሮች እንዳያጋጥማቸውና ደህንነታቸውን በመጠበቅና የፈለጉትን ሀሳብ እንዲገልጹ በቂ ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው በመግለጫቸው አስታውሰዋል።
በፌደራልና በክልል የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መንግሥት ባደረገላቸው ምኅረትና ይቅርታ እንዲፈቱ መደረጋቸውን እንደ ትልቅ ሥራ መወሰድ አለበት ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ሚዲያዎችም የተለያየ ሀሳብ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉና ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ጉዳዮችን ለመንግሥት እንዲያደርሱ ነፃነታቸውን በመጠበቅ በኩል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
ከሕዳሴ ግድብ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ተቀዛቅዞ የነበረ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥልና የተጀመረ የልማት ሥራ እንዲቋጭ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በፖሊስ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በብሔራዊ መረጃና ደህንነትና በሌሎች የጸጥታ አካላት የተከናወኑ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎችን በበጎ የሚወሰዱ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ግን በሰላማዊ መንገድ ጥሪ ከተደረገላቸው አካላት መካከል ሰላማዊ መንገዱን በመተው ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ አካላት እንዳሉ የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በተለይ የኦኔግ ሸኔ ቡድን በምዕራብ ወለጋና በሌሎች አካባቢዎች እንቅስቃሴ በማድረግ ሕብረተሰቡን በመግደል፣ በማገት፣ ንብረት በማውደምና ሌሎች የተለያዩ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል።
በተማሪዎች ጠለፋ ላይም በመሰማራት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳና በቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ አካባቢ የኦኔግ ሸኔ አባላትና ህወሓት በተቀናጀ መንገድ የሕዝብ ግዲያ በመፈጸም የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደነበር ለማየት ተችሏል ብለዋል ኮሚሽነር ጄነራሉ።
ኮሚሽነር ጄነራሉ አያይዘውም የህወሓት ጽንፈኛው ኃይል ከእነዚህ ከፍተኛ ጥፋቶች ኋላ ተሰማርቶ ሲሠራ እንደነበረ በተለያዩ ጊዜ ባደረግናቸው ምርመራዎች ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የህወሓት ጽንፈኛ ኃይል ከፌደራል መንግሥት ጋር ለመሥራት ያለመፈለግ፣ ሕገ-ወጥ ምርጫ ማከናወን፣ የሠራዊት አባላትን ለውጊያ በሚመጥን መንገድ ማዘጋጀት፣ የፌደራል መንግሥትን ሕገ-ወጥ ነው በማለት ባገኘው ሚዲያ በሙሉ ማሰራጨትና ሌሎች ለጸጥታ ሥራ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን ሲያከናውን መቆየቱንም ኮሚሽነር ጄነራሉ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የህወሓት ጽንፈኛ ቡድንና የኦኔግ ሸኔ ታጣቂው ኃይል በተደራጀ መንገድ ከውጭና ከሀገር ውስጥ የሚደረግላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ በመጠቀም ለሁለት ዓመታት የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍል ሲያተራምሱ መቆየታቸውን ለማረጋገጥ እንደተቻለም ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ተናግረዋል።
በሁሉም አካባቢ የተፈጸሙ የጸጥታ ችግሮች ሲያደራጁና ሲመሩ የነበሩ መሆናቸውን ምርመራዎቻችንና የተለያዩ መረጃዎቻችን አረጋግጧል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ የተለያዩ ፍንዳታዎችን በመፈጸም፣ የግድያ ሙከራዎችን ማከናወን፣ ንብረት ማውደም፣ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨትና በቤተ-እምነቶች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደነበራቸውም ኮሚሽነር ጄነራሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
አሁንም በትግራይ ክልል ጦርነት ከፍተው ባሉበት ወቅት በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎችና ትላልቅ ከተሞች ላይ ጥቃት ለማድረስ ያሰማሩት ኃይል እንዳለ ተደርሶበታል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ይሄ ኃይል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ አካላት ባደረጉት ስምሪት ግማሹ የተያዘ ሲሆን ግማሹ ደግሞ በቅርብ ቀን ከተደበቀበት በማውጣት በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወን ተነግሯል።
የፌደራል ፖሊስ ባለው ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ መሠረት በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢ በመሰማራት የሕብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታን የሚጠብቅ ኃይል መሆኑን በመግለጽ በትግራይ ክልልም በ22 ትልልቅ ተቋማት ላይ በመሰማራት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ተቋም ነው ብለዋል።
የፌደራል ፖሊስ አባላት ኤርፖርቶችን፣ ዲፖዎችን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ጣቢያዎችን፣ ቴሌኮምን፣ ቤተ መንግሥትን፣ ትላልቅ ግድቦችንና ኬላዎችን ጨምሮ ሌሎች የሕዝብና የመንግሥት ተቋማትን በመጠበቅ ተገቢውን አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ሲሰጡ መቆየታቸውንና በትግራይ ውስጥ ለሚሰሩ የልማት ሥራዎችን ከሕብረተሰቡ ጎን በመሰለፍ በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ እንደነበር ተገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ ኃይል ሕብረተሰቡን ሲያግዝ በነበረበት ወቅት ህወሓት ከፍተኛ ኃይል በመመደብ ጥቃት እንደሰነዘረባቸውና የንብረት ዝርፊያ መፈጸሙን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በአንዳንድ አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ሠራዊትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ላይ ሆነው ሊወረው የመጣውን ኃይል ተከላክሏል ብለዋል።
መውጫና መግቢያ መንገዶችን ለሠራዊቱ በማሳየት የትግራይ ሕዝብ ሊያጠቃው የመጣውን አካል መከላከል መቻሉና ከሰሜን እዝ ጋር በመሆን ጽንፈኛውን ተዋጊ ኃይል በመመከትና በመምታት የራሱን ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል ተብሏል።
ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የፈፀመው ይሄ አስነዋሪ ድርጊት ታሪክ፣ ሕግና ህሊና ይቅርታ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ኮሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው፥ ሠራዊቱንና ሕዝቡን የደፈሩበት ሂደት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋልም ብለዋል።
ለውጊያ ሳይሆን ለጥበቃ ሥራ የተሰማራ የፌደራል ፖሊስ ኃይል በታጠቀና ለውጊያ በተዘጋጀ ኃይል ተከቦ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ መውሰድ አጅግ አሳፋሪ መሆን በመግለጽ ሕግ የማስከበር ሂደታችን በድል በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የፌደራልና የክልል ፖሊስ እንዲሁም ሕዝባዊ አደረጃጀት ያላቸው የሚኒሻ አባላት በጋራ በመደራጀት አካባቢያቸውን በአግባቡ መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፤ ለተለያየ እኩይ ተግባር የተሰማሩ ሃይሎችን በየአካባቢው በቂ ጥናት በማድረግ በቁጥጥር ስር ማዋል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች የነበሩ የጥፋት ሙከራዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ሠራዊቱ በአንድ ረድፍ በመሰለፍ ይህንን ችግር ለመከላከል ላሳየው ከፍተኛ ጽናት አድናቆታቸውን በመግለጽ አሁንም ከኢንቨስትመንት ጀምሮ ለትልልቅ የኢንዱስትሪ መንደሮች ተረባርበን አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን መከላከል አለብን ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት በሚሰጠው መመሪያ መሠረት መፈጸም ከሠራዊቱ አባላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ ሕብረተሰቡ በዲጂታል ወያኔ የሚሠራጩ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በጋራ መከላከል እንዳለበትና በየቀኑ ከመንግሥት የሚሰጠውን መግለጫ ብቻ መከታተል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
መንግሥት ለሚያቀርበው ጥሪ ሕብረተሰቡ በቂ ዝግጅት በማድረግ እኩይ ተግባር ለመፈጸም የተሰማራ ኃይል በመከታተል መጠቆምና ማጋለጥ እንዳለበትም ኮሚሽነር ጄነራሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተሰጡ አድራሻዎች መሠረት በዚህ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ1,500 በላይ የሚደርሱ ጥቆማዎች መድረሳቸውንና በዚህም ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ በሌሎችም መሰል ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የተጀመረው ጸረ-ሰላም ኃይልን የማጥራት ሂደት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ለሰላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ ግንባታ በማዞር ጥረት የምናደርግበት ጊዜ እንዲሆንም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ተመኝተዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን
November 7, 2020 at 3:21 am #16667AnonymousInactiveየፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወሰነ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወሰነ።
ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲመለስ የተሰጠውን በቂ ዕድል መጠቀም ባለመቻሉ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ በሕገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወስኗል።
ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በክልሉ በሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አስነዋሪ ጥቃት ፈጽሟል። በተጨማሪም በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በንፁሃን ዜጎችና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።
የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 12 በአንድ የክልል መንግሥት ተሳትፎ ወይም ዕውቅና ሕገ-መንግሥቱን ወይም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት በተለይም፡
(1) በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ ማድረግ፤
(2) ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ክልል ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍታት፤
(3) የፌዴራሉን ሰላምና ጸጥታ ማናጋት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ እንደሚቆጠር ተደንግጓል። ከዚህ ድንጋጌ አንጻር ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት የፈጸመው እና እየፈጸመ ያለው ድርጊት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ ተረጋግጧል።
በዚሁ መሠረት የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) ማንኛውም ክልል ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ስልጣን እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 36 (1) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአንድ ክልል ውስጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ ሲያምን የፌዴራሉ መንግሥት ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዝ እንደሚችል እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 13 (4) ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ጣልቃ እንዲገባ ሊያዝ እንደሚችል በመደንገጉ ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ እና የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመፈጸም የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ስለሆነ ይህንን ድርጊት ማስቆም ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱና በአዋጆቹ የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት በመጠቀም ሕገ-መንግሥታዊ መፍትሔ መስጠት ያለበት ሆኖ በመገኘቱ፥ ጥቅምት 28 ቀን ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሚከተሉትንን ውሳኔዎች አሳልፏል።
- ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት ለማስቆም የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ትዕዛዝ ሰጥቷል፤ እንዲሁም ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 14 (2) መሠረት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተጣጣመ መልኩ አደጋውን ለማስወገድ እንዲቻል የፌደራል ፖሊስን ወይም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ወይንም ሁለቱንም በክልሉ እንዲያሰማራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፤
- ሕገ-ወጡን የክልሉ ምክር ቤት እና የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ታግዶ ለፌደራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነና በአዋጅ 359/1995 አንቀጽ 15 ላይ የተቀመጡት ስልጣንና ተግባራት የሚኖሩት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወስኗል። በዚሁ መሠረት የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ከሌሎች አግባብነት ካላቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በመተባበር ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል። በተጨማሪም ለክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካል የተሰጡትን ተግባሮች ይኖሩታል። በተለይም ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤
ሀ) አስፈፃሚ አካሉን ይመራል፣ ያስተባብራል፤
ለ) የጊዜያዊ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ይመድባል፤
ሐ) ሕግና ሥርዓት መገበሩን ያረጋግጣል፤
መ) አግባብ ባለው ህግ መሠረት በክልሉ ምርጫ የሚከናወንበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤
ሠ) የክልሉን እቅድና በጀት ያፀድቃል፤
ረ) በፌዴራል መንግሥቱ ሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል።
- ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን የምክር ቤቱ ውሳኔዎች አፈጻጸምና ክልሉ ስለሚገኝበት ሁኔታ በተመለከተ ክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ አስፈላጊነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ በማለት ወስኗል።
በመጨረሻም፥ መላው የትግራይ ሕዝብና የሀገራችን ሕዝቦች ሕገ-ወጡ ቡድን የፈፀመውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊና አስነዋሪ ድርጊት በማውገዝ የሀገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር በሚል መርህ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ካለውና የኩራታችን ምንጭ ከሆነው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጨምሮ ከፌደራሉ መንግሥት እና ከሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጎን እንዲቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመተሳሰብ፣ አንዱ ለሌላው ጠበቃና ዋስትና በመሆን እኩይ ዓላማ ይዘው እርስ በርሳችንን በማጋጨት ሀገራችንን ለመበታተን ሌትተቀን የሚሠሩ ኃይሎችን ነቅተን በመጠበቅና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ረገድ ሁሉም ዘብ እንዲቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት
November 19, 2020 at 3:24 am #16739AnonymousInactiveየሀገር ክህደት ወንጀል በፈጸሙ 76 ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ላይ
የመያዣ ትዕዛዝ መውጣቱ ተገለፀ ― የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንአዲስ አበባ (የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን) – በትግራይ ክልል በሚገኘው በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም ሀገር የማፍረስ ሴራ አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩና የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸሙ የጁንታው ህወሓት ወንበዴ ቡድን የበላይ አመራሮችን አድኖ ለሕግ ለማቅረብ ከሳምንት በፊት ማለትም ህዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደወጣባቸው መገለፁ ይታወቃል።
በተመሳሳይም ከጁንታው የህወሓት ቡድን አባላት ጋር እየተገናኙ ሀገር በማፍረስ ሴራ ውስጥ በመሳተፍ የሀገር ክህደት ወንጀል በፈፀሙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት እንዲሁም በፖሊስ አመራሮች ላይ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ያስታወሰው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ፥ ከጁንታው የህወሓት የጥፋት ቡድን ሀገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራ እጃቸውን ባስገቡና በሀገር ክህደት ወንጀል የተሳተፉ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በዚህም መሠረት በሀገር መከላከያ ሠራዊት በሥራ ላይ ያሉና በጡረታ የተሰናበቱ ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት የተጣለባቸውን ሕዝባዊና ሀገራዊ አደራና ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው እና የጁንታው የህወሓት ቡድን የሴራ አካል በመሆን የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችንም አድኖ ለሕግ ለማቅረብ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጠባቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ በመጣልና ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ ወንጀል ውስጥ በመሳተፍ የሚፈለጉትና የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸው በሥራ ላይ ያሉና በጡረታ የተሰናበቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው።
- ሜጀር ጀነራል ማህሾ በየነ
- ሜጀር ጀነራል ሀለፎም እጂጉ
- ብርጋዴል ጀነራል ፍትዊ ፀሃዬ ገብረእግዚአብሔር
- ብርጋዴል ጀነራል ግደይ ሀይሉ ገብረእግዚአብሔር
- ብርጋዴል ጀነራል ወልደጊዮርጊስ
- ብርጋዴል ጀነራል አብዲሳ ፍላንሳ
- ብርጋዴል ጀነራል ጉሽ ገብሬ
- ብርጋዴል ጀነራል ከበደ ፍቃዱ
- ብርጋዴል ጀነራል ገብረጊዮርጊስ
- ብርጋዴል ጀነራል ህንፃ ወልደጊዮርጊስ
- ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳይ
- ኮሎኔል ንጉሴ ገብሩ
- ኮሎኔል መብራቱ አሰፋ /አልማዝ/
- ኮሎኔል ዘገየ ንጉስ
- ኮሎኔል ያለም
- ኮሎኔል መብራቱ ተድላ
- ኮሎኔል ነጋሽ መብራቱ
- ኮሎኔል ተክሉ በላይ
- ኮሎኔል ጥጋቡ መለስ
- ኮሎኔል ግርማ ተካ
- ኮሎኔል ሙሉጌታ ገብረክርስቶስ ነጋሽ
- ኮሎኔል አራሞ ገብረመድህን
- ኮሎኔል ተስፋዬ ገብረመድህን
- ኮሎኔል ግርማል አለማየሁ
- ኮሎኔል ነጋሽ አለፎም
- ኮሎኔል ተስፋዬ ምሩፅ
- ኮሎኔል ካሳየ አሰፋ
- ኮሎኔል ነጋሲ ታደሰ ስዩም
- ኮሎኔል ኪሮስ ሓጎስ ገ/ዝጋብሔር
- ኮሎኔል ሙርፅ ገብረሊባኖስ አብርሃ
- ኮሎኔል ሓ/ስላሴ ኪሮስ ተስፋይ
- ኮሎኔል ምሩፅ በርሔ /ተወርወር/
- ኮሎኔል ኃይለሥላሴ አሰፋ
- ኮሎኔል ደርበው ኃጎስ
- ኮሎኔል ወልዴ ሀጎስ
- ኮሎኔል ንጉሴ አማረ
- ኮሎኔል ነጋሲ ታደሰ
- ኮሎኔል ባራኪ /ወዲ ራያ/
- ኮሎኔል ከበደ ገብረሚካኤል
- ኮሎኔል ፀጋ ብርሀን ገብረእዜር
- ኮሎኔል ዘሩ ሀ/መለኮት
- ኮሎኔል ኃይለ መዝገብ
- ኮሎኔል አርአያ ገብሩ ግደይ
- ኮሎኔል የማነ ገብረሚካኤል
- ኮሎኔል ዘሩ መረሳ
- ኮሎኔል ልጃለም ገብረህይወት
- ኮሎኔል ፍሰሀ ግደይ
- ኮሎኔል ገብረመስቀል ወልደገብርኤል
- ኮሎኔል ወልዱሀጎስ ገብሩ
- ኮሎኔል ገብረሚካኤል ሀጎስ
- ኮሎኔል ስብሀቱ መብራቱ
- ኮሎኔል ጣሰው ወ/ጊዮርጊስ
- ኮሎኔል ገብረእግዚያብሔር አለምሰገድ
- ኮሎኔል ነጋሲ ታደሰ
- ኮሎኔል ተክለ በላይ
- ሌተናል ኮሎኔል ተወልደ አብርሃ ወልደሚካኤል
- ሌተናል ኮሎኔል ሙዘይ ተሰማ ስዩም
- ሌተናል ኮሎኔል ሀዲሽ ገብረፃድቅ አለማየሁ
- ሌተናል ኮሎኔል ፍስሃ በየነ ገብረኪዳን
- ሌተናል ኮሎኔል ምሩፅ ወልደአረጋይ ገብረመስቀል
- ሌተናል ኮሎኔል ሙሩፅ በርሀ ኣበራ
- ሌተናል ኮሎኔል ፀሀዬ ሀጎስ
- ሌተናል ኮሎኔል ሀጎስ ኪሮስ
- ሌተናል ኮሎኔል ገብረ ህንፃ ሀዲሽ
- ሌተናል ኮሎኔል ፈለቀ አይጠገብ
- ሻለቃ አስገዶም መስፍን
- ሻምበል ባሻ ሙእዝ መልካም
- ሻምበል አርአያ ተክለሀይማኖት
- ሻምበል ተስፋ ህይወት
ናቸው። ከላይ ስማቸው የተዘረዘረው ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እሴቶች መካከል ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም የሚለውን ወደ ጎን በመተው የወንበዴው ጁንታ ህወሓት የጥፋት ቡድን የሴራ አካል በመሆን በወንጀል የሚፈለጉ መሆናቸውን ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በመግለጫው አሳውቋል።
በመሆኑም መላው የሀገራችን ሕዝቦች፥ በተለይም ደግሞ የትግራይ ሕዝብ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትና ሚሊሻዎች እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሠራዊት፤ የሀገራችን የፖሊስ ሠራዊና የደህንነት ተቋማት እነዚህን የጁንታውን የህወሓት የጥፋት ቡድን ተፈላጊዎች አድኖ ለሕግ ለማቅረብ እየተደረገ ባለው ጥረት በያላችሁበት የድርሻችሁን እንድትወጡ በማለት ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል። በቀጣይም በጁንታው የህወሓት የጥፋት ቡድን ሀገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራ እንዲሁም በሀገር ክህደት ወንጀል የተሳተፉትንና በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃና መዋቅር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራውም ሆነ በጉዳዩ ዙሪያ ተከታታይ መረጃዎችን በመገናኛ ብዙሃን በኩል ለሕብረተሰቡ ይፋ የማድረግ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን
December 8, 2020 at 3:21 am #16928AnonymousInactiveበሀገር ላይ የፈጸሙ ወንጀሎች ስለሚያስከትሉት ቅጣት የወንጀል ሕግ ምን ይላል?
“የሀገር መከላከያ ኃይልን መጉዳት ከአምስት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት፣ እንዲሁም ነገሩ እጅግ ከባድ በሆነ ጊዜ
በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ያስቀጣል።”መንግሥት የሕዝቦቹን ሰላም እና ደህንነት የመጠበቅ እንዲሁም ሕግን የማስከበር ኃላፊነት የሚወጣ ቢሆኑም በተለያዩ ሁኔታዎች በሀገር ላይ ወንጀሎች ሊፈጸሙ ይችላሉ። የእነዚህ ወንጀሎች መፈፀም በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ሰላም፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ህይወት ላይ ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ በመሆኑም መንግሥት የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ አስቀድሞ የመከላከል፤ ተፈጽመው ሲገኙም ሕግን የማስከበር ኃላፊነት አለበት። በሀገር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ሦስተኛ መፅሐፍ በመንግሥት፣ በሀገርና በዓለም አቀፍ ጥቅሞች ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች በሚል ስር ተካቶ ይገኛል።
በዚህ አጭር የንቃተ ሕግ ፅሁፍ በሀገር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የሚያስከትሉትን የወንጀል ቅጣት እንዳስሳለን። በሕገ-መንግሥትና በሕገ-መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 238 ስር እንደተደነገገው ማንም ሰው በኃይል፣ በዛቻ፣ በአድማ ወይም ሕገ-ወጥ በሆነ ማናቸውም መንገድ የፌደራሉን ወይም የክልልን ሕገ-መንግሥት ያፈረሰ፣ የለወጠ ወይም ያገደ እንደሆነ ወይም በፌደራሉ ወይም በክልል ሕገ-መንግሥት የተቋቋመውን ሥርዓት ያፈረሰ ወይም የለወጠ እንደሆነ ከሦስት ዓመት እስከ 25 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስርት ይቀጣል። ወንጀሉ ሲፈፀም በሕዝብ ደህንነት ወይም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ደርሶ እንደሆነ አድራጊው በዕድሜ ልክ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል።
የሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣንን ተግባራዊነት ማሰናከል ሌላው በወንጀል ሕጉ የወንጀል ድርጊት ተብሎ የተፈረጀ ተግባር ሲሆን ማንም ሰው በኃይል ሥራ፣ በዛቻ፣ ወይም ሕገ-ወጥ በሆነ ሌላ ማናቸውም መንገድ በፌደራል ወይም በክልል ሕገ-መንግሥት ስልጣን የተሰጠውን አካል ወይም ባለስልጣን ተግባሩን እንዳያከናውን ያደናቀፈ፣ የከለከለ ወይም አስገድዶ ውሳኔ እንዲሰጥ ያደረገ እንደሆነ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል።
የጦር መሣሪያ ይዞ በማመፅ፣ ወይም የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግሥት ላይ የሚደረግ ወንጀል (የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240) — ማንም ሰው አስቦ በሕገ-መንግሥት በተቋቋሙት አካላት ወይም ባለስልጣናት ላይ ሕዝብ፣ ወታደሮች ወይም ሽፍቶች የትጥቅ አመፅ እንዲያነሱ ያደራጀ ወይም የመራ እንደሆነ ወይም ዜጎችን ወይም በሀገር ነዋሪ የሆኑትን በማስታጠቅ ወይም አንዱ ወገን በሌላው ላይ የጦር መሣሪያ እንዲያነሳ በማነሳሳት የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲነሳ ያደረገ እንደሆነ ከ10 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።እንዲሁም ድርጊቱ በሕዝብ ደህንነት ወይም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ይስከተለ እንደሆነ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል።
የሀገሪቱን የፖለቲካ የግዛት አንድነት በመንካት የሚደረግ ወንጀል (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 241) — ማንም ሰው በኃይል ወይም በሌላ ማናቸውም ሕገ-መንግሥትን የሚፃረር መንገድ፣ በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር፣ የሀገሪቱን ሕዝቦች አንድነት እንዲፈርስ ወይም ፌዴሬሽኑ እንዲከፋፈል ወይም ከፌዴሬሽኑ ግዛት ከፊሉ እንዲገነጠል የሚያደርግ ተግባር የፈፀመ እንደሆነ ከ10 ዓመት እስከ 20 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ በእድሜ ልክ እስራት ወይ በሞት ይቀጣል።
የሀገሪቱን መንግሥት እንዲሁም የሀገሪቱን ምልክቶችና በመንግሥት የታወቁ ሌሎች ምልክቶችን መድፈር — ማንም ሰው በንግግር ወይም በአድራጎት ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኋን በአደባባይ የሀገሪቱን መንግሥት ያዋረደ፣ የሰደበ፣ ስሙን ያጠፋ ወይም በሀሰት የወነጀለ እንደሆነ ከሦስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ወይም ከ500 ብር በማያንስ መቀጮ ይቀጣል (የወንጀል ሕግ አንቀፅ 244/1)። እንዲሁም በተንኮል፣ በንቀት ወይም ይህንን በመሳሰለ በማናቸውም ሀሳብ በግልጽ የታወቀውን አንድ የሀገር ምልክት፥ ማለትም የፌደራላዊት ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን ወይም አርማን እንዲሁም የክልላዊ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማን ወይም አርማን በአደባባይ የቀደደ፣ ያቃጠለ፣ ያጠፋ፣ ያበላሸ፣ የሰደበ ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኋን ያዋረደ እንደሆነ ከሦስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል (የወንጀል ሕግ አንቀፅ 244/2)። በሀገር ነፃነት ላይ የሚደረግ ወንጀል ማንም ሰው፡-
- የሀገሪቱን ነፃነት አደጋ ላይ ለመጣል ወይም ሀገሪቱ ሉአላዊቷን እንድታጣ፣
- የሀገሪቱን ነፃነት አደጋ ላይ ለመጣል የውጪ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ በመገፋፋት፣ ወይም
- የውጪ መንግሥት የጠላትነት ድርጊት በሀገሪቱ ላይ እንዲፈጽም ወይም ከውጪ ሀገር መንግሥት ጋር ጦርነት እንድትዋጋ ወይም የጠላትነት ድርጊት እንድትፈጽም፣ በጠላትነት እንድትከበብ ወይም እንድትያዝ በማሰብ ማናቸውም ድርጊት ያደረገ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ 25 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት፤ ወይም ነገሩ ከባድ ሲሆን በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል (የወንጀል ሕግ 246)።
የሀገር መከላከያ ኃይልን መጉዳት (የወንጀል ሕግ አንቀፅ 247/ሀ/ለ/ሐ እና መ) — የሀገር መከላከያ ኃይልን መጉዳት በሀገር ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች አንዱ ሲሆን ማንም ሰው አስቦ፡-
ሀ/ ወታደራዊ ፀባይ ያለውን ወይም ለሀገር መከላከያ እንዲሆን የታቀደውን ማናቸውንም የኢኮኖሚ ድርጅት፣ የመከላከያ ሥራ ተቋም ወይም ሥፍራ፣ የመገናኛ ወይም የመጓጓዣ ዘዴ፣ ሥራ፣ ማከማቻ፣ የጦር መሣሪያ ወይም ቁሳቁስ አሳልፎ በመስጠት፣ በማፍረስ፣ የተንኮል ሥራ በመፈፀም ወይም ለአገልግሎት እንዳይውል በማድረግ፣
ለ/ ጠላት ለሆነ ለውጪ ሀገር መንግሥት ወታደሮች በማቅረብ ወይም የኢትዮጵያ ዜጎች ለዚሁ ለጠላት ሀገር በወታደርነት እንዲያገለግሉ በመመልመል ወይም በማግባባት ወይም ራሱ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለዚሁ ዓይነት የጠላት ሀገር መንግሥት በመሰለፍ፣
ሐ/ የጦር ወታደሩ የጦር አገልግሎት ከመፈፀም እምቢተኛ እንዲሆን፣ ወታደራዊ አመፅ እንዲያስነሳ ወይም እንዲከዳ በግልፅ በማነሳሳት ወይም የጦር ወታደርነት ግዴታ ያለበት ሰው ከእነዚህ ወንጀሎች አንደኛውን እንዲፈፅም በመገፋፋት ወይም እንዲነሳሳ በማድረግ፣ ወይም
መ/ ለሀገር መከላከያ የሚያገለግሉትን ወታደራዊ የጥንቃቄ እርምጃዎች በማሰናከል፣ በማበላሸት ወይም በማናቸውም ሌላ ዘዴ የተንኮል ድርጊት በመፈፀም በኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ 25 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት ወይም ነገሩ እጅግ ከባድ በሆነ ጊዜ በተለይም በጦርነት ወይም ጦር አስጊ በሆነበት ጊዜ እንደሆነ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል።
ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
March 28, 2021 at 2:31 am #18804AnonymousInactiveከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር አዲስ አበባ ከተማን ከማንኛውም የፀጥታ ስጋት የፀዳች ለማድረግ ባካሄደው የአንድ ሳምንት የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ውጤት ማስመዝገቡን ገለፀ።
ኮሚሽኑ የፀጥታ ሥራውን በብቃት ለማከናወን የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅቶ የጋራ በማድረግ በተግባር ምዕራፉ የመጀመሪያ ሳምንት ባካሄደው ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ሂደት ባከናወናቸው ጠንካራ የወንጀል መከላከል ተግባራት
- በተደራጀ መንገድ ታቅደው የሚፈፀሙ የዘረፋና የግድያ ወንጀሎች፣
- የግል ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀም አፈና እና ግድያ፣
- የተሽከርካሪ ስርቆት፣
- ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን መቀነስ መቻሉን ገልጿል።
ኮሚሽኑ እንደገለፀው በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 359 ተጠረጣሪዎች ተከታትሎ በሕግ ቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝና ከዚህ ውስጥ
ትግራይ ላይ በተፈፀመው የጁንታው ጥቃት የተሳተፉና በተለያየ መንገድ አምልጠው ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት በተለያየ የወንጀል ተገባር ሲሳተፉ በተገኘ የሕዝብ ጥቆማ 135 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሰባት የኦነግ ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ በማጣራት ላይ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡን ከጎኑ በማሰለፍ በተቀናጀ የጋራ ኦፕሬሽን በተለያዩ በወንጀል የተጠረጠሩ የነፍስ ወከፍና የቡድን ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች፣ የሀገር ውስጥ ሀሰተኛ ገንዘብ እና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ተሽከርካሪዎች፣ በዘረፋና በግድያ ከተወሰዱ 10 ራይድ ተሽከርካሪዎች ስምንቱ እንደተያዙና የሁለቱ አካላቸው እንደተፈታ ፖሊስ ደርሶበት በቁጥጥር ስር አውሎ በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ባካሄደው የጋራ ኦፕሬሽን የኑሮ ውድነት ለማባባስ እና የንግድ ስር-ዓቱን ለማዛባት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በዚህ ኦፕሬሽን በቀጥጥር ስር አውሎ ከእነሱም ብዛት ያላቸው ሸቀጦችና ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ባካሄደው በዚህ የጋራ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ንብረቶች መካከል በዝርፊያ የተወሰደ አንድ ሲኖ-ትራክ ከባድ መኪናንና ከግለሰቦች የተነጠቁና ከድርጅቶች የተዘረፉ ባርካታ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመያዝ ለባለ ንብረቶቹ ተመላሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ሐሰተኛ መታወቂያ በመቀያየርና በመጠቀም በተለያዩ የተሽከርካሪ መሸጫ ድርጅቶች እየተቀጠሩ ተሽከርካሪዎችን በሌሎች በማሰረቅ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች መያዛቸውንም ጨምሮ ገልጿል።
በመጨረሻም ኮሚሽኑ ይህ ከጅምሩ ውጤት ያስመዘገበ የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ወደ ፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፆ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደህንነት አስተማማኝና ዘላቂ ይሆን ዘንድ የሰላሙ ባለቤት የሆነው መላው የከተማው ህዝብ ለሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሱ መረጃዎችን ባለመቀበልና ሀሰተኛ መረጃዎችንም ባለመጋራት እንዲሁም ለፖሊስ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በፍጥነት እንደተለመደው መረጃ በመስጠት እንዲተባበር እየጠየቀ ለዚህ ኦፕሬሽን መሳካት የከተማው ህዝብ ላደረገው ከፍተኛ አሰተዋጽኦ ኮሚሽኑ ሌሎች የፀጥታ ሀይሎችንም በመወከል የላቀ ምስጋና ያቀርባል።
የኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ምApril 19, 2021 at 12:56 am #19091AnonymousInactiveከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በሀገራችን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ የተሰጠ መግለጫ
በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት በንጹሃን ዜጎች ላይ የህይወት እና ንብረት አደጋ ባደረሱ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ መወሰድ ተጀምሯል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊታችን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ትግራይ ክልል ውጤታማ ሕግ የማስከበር ተልእኮውን በጀግንነት በመፈጸም ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች የጸጥታ ችግሮች እየተስተዋሉ ይገኛሉ።
እነዚህ ሆን ተብሎ የሠራዊታችንን ሕገ-መንግሥታዊ ተልእኮ ለማስተጓጎል ታስበው የተሠሩ የጥፋት ሴራዎች፣ በሰላም ወዳዱ ሕዝባችን እና በመከላከያ ሠራዊታችን የተቀናጀ ሥራ ሊከሽፉ ችለዋል።
አንደኛ በመተማ መስመር ለዘመናት አብረው በኖሩ የቅማንት እና የአማራ ተወላጆች መካከል የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን የፈዴራል እና የክልል የጸጥታ ኃይሎች ከኅብረተሰቡ እና ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ጋር የተቀናጀ ሥራ በመሥራት የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ።
ሁለተኛ፥ በወለጋ ቡሬ መስመር፣ በጊዳ አያና፣ አንገር ጉቴ አዋሳኝ አከባቢዎች ለረዥም ጊዜ አብሮ በኖሩ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎችን ሆን ብሎ ለማጋጨት ታስቦ የተደረገው ሙከራ በአከባቢው ኅብረተሰብ ትብብር ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ተችሏል።
ሦስተኛ፥ የሀገራችንን የገቢ እና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴን ለመገደብ በማሰብ፣ በሱማሌ እና የአፋር ኢሳ ሕዝቦችን ለማጋጨት የተሴረው ሴራ በሰላም ወዳዱ ሕዝባችን የተቀናጀ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር ለመዋል ችሏል።
አራተኛ፥ ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች በተለይም በዚህ ሁለት ሶስት ቀን በአጣዬ ከተማ እና በአከባቢው በታጠቁ ኃይሎች በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ውድመት፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፥ በዚህ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች መጽናናትን ይመኛል።
በዚህ የጸጥታ ችግር ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና መሣርያ ይዘው በጸጥታ አካላት ላይ ተኩስ የከፈቱ፣ የሠራዊቱን እንቅስቃሴ የገደቡ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ሠራዊታችን እርምጃ መውሰድ መጀመሩን እየገለጽን፤ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ የኅብረሰተሰቡን ሰላም በማወክ ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል።
በዚህም መሠረት፥ በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከክልል እና ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጨምሮ ሶስቱንም ዞኖች ያካተተ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል። ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ጸጥታ በማደፍረስ ሥራ ላይ በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ሥራን ይሠራል።
በዚህም መሠረት የአከባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ሲባል የሚከተሉት ክልከላዎች የተደረጉ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ይገልጻል።
1ኛ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ አዋሳኝ ወረዳዎች መንገድ ላይ፣ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ውስጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
2ኛ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ አብያተ ክርስቲያናትን እና የመንግሥት ተቋማትን፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤትን እና ንብረት ማውደም ወይም ለዚህ ተግባር በተናጠልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
ከላይ የተዘረዘሩትን እና ቀጣይ በኮማንድ ፖስቱ ለኅብረተሰቡ የሚገለጹ ክልከላዎችን ተላልፎ የተገኘ የፖለቲካ ድርጅት፣ የመንግሥት መዋቅር እና በድኖች ላይ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑ መታወቅ አለበት።
በመጨረሻም መላው ኅብረተሰባችን እንደ ወትሮው ሁሉ ከጸጥታ ተቋማት ጎን በመሰለፍ ለገሀራችን ሰላም እና ደህንነት የበኩሉን ገንቢ ሚና እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር
ሚያዝያ 10፥ ቀን 2013 ዓ.ም.June 19, 2021 at 4:46 pm #19705AnonymousInactiveየ6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ “ሰላምና ደህንነት” አስመልክቶ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ
የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ፥
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በቅድሚያ ለታሪካዊው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ እያለ የምርጫው ሂደት ተጀምሮ አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ በጨዋነትና በትዕግስት ላደረጋችሁት ድጋፍና ትብብር የላቀ ምስጋናውን እያቀረበ በቀሪው የምርጫ ሂደትም ምርጫውን የሚያደናቅፉ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ እንደተለመደው ሁሉ መረጃ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለፀጥታ እና ለደህንነት ኃይሉ በማድረግ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የተከበራችሁ የሀገራችን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፥
የምርጫ ሕጉንና የሥነ-ምግባር ደንቡን አክብራችሁ እስከ አሁን ለምርጫው ሰላማዊነት የበኩላችሁን ገንቢ አስተዋፅኦ በማበርከታችሁ ኮሚሽኑ ምስጋናውን እያቀረበ በቀጣይም በሚኖረው የምርጫ ሂደት እስከመጨረሻው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ኮሚሽኑ አጥብቆ ይጠይቃል።
የተከበራችሁ የፌዴራልና የክልል የፀጥታና የደህንነት አካላት፥
መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ፍፁም ገለልተኛ ሆናችሁ ሌት ተቀን እያበረከታችሁት ላላችሁት አስተዋፅኦ ኮሚሽኑ ከልብ እያመሰገነ፤ በቀጣይ ለሚኖረው የድምፅ አሰጣጥና አጠቃላይ ለምርጫው ሂደት ስኬታማነት የተሰጣችሁን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነታችሁን ልክ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ እንድትወጡ ከአደራ ጭምር ያሳስባል፡፡
ኮሚሽኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወሳኝ ምዕራፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት የምርጫ ሂደቶች ከሁከትና ብጥብጥ የጸዱ እንዲሆኑ ከፀጥታና የደህንነት መዋቅሩ ጋር የተቀናጀ የምርጫ ደህንነት ዕቅድ በማዘጋጀት፣ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ዕለት እና በድኅረ-ምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ የፀጥታ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመተንተን እና በመለየት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ሲሠራ ቆይቷል።
ከዚህ አንፃር 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ማጠናቀቅ ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የሀገራችንን ታላቅነት ለመላው ዓለም የምናሳይበት ታላቅ ኩነት መሆኑንና ለገጽታችን ግንባታ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን የተረዳው ኮሚሸኑ የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ፀጥታውን ለማናጋት፣ የምርጫውን ሰላማዊነት ለማደፍረስና የሁከትና ብጥብጥ መንስዔ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ከወዲሁ በመረዳት ምንም ዓይነት ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በየትኛው አካባቢ እንዳይኖር ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የሀገራችን የፀጥታና የደህንነት መዋቅሮች በከፍተኛ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚያስችላቸው ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስምሪት ገብቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሕዝቡ እና ለሥራችን ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉት አስፈላጊ እና ወሳኝ የሆኑት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች በምርጫ ወቅት ያለ በቂ ምክንያት እንዳይቋረጡ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ኮሚሽኑ በአንክሮ ያሳስባል፡፡
በመጨረሻም መላው የሀገራችን ሕዝብ እና የፀጥታ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመቀናጀት ይህንን ታሪካዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንድንወጣ ጥሪያችንን በከፍተኛ አክብሮት እያቀረብን፥ በድምጽ መስጫ ዕለትና በድኅረ-ምርጫ ወቅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በሕግ አግባብ ብቻ እንዲሆኑ ኮሚሽን በጥብቅ ያስታውቃል፡፡
ኮሚሽኑ በድጋሚ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም አደረሳችሁ ይላል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
ሰኔ 12 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባJuly 18, 2021 at 4:54 am #19946AnonymousInactiveየኢፌዴሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር በ2013 በጀት ዓመት በባህል ኢንዱስትሪ ልማት ዋና ዋና ክንውኖች
ሐምሌ 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ- በባህል ፖሊሲ፣ በቋንቋ ፖሊሲ በባህል እሴቶችና ሀገር በቀል ዕውቀቶች፣ በዕደ ጥበብ ማበልፀግና የገበያ ትስስር ስትራቴጂዎችና አዘገጃጀት ሂደት እና አተገባበር ላይ ከ10 ክልሎች እና ከ2 የከተማ መስተዳድር ለተውጣጡ 53 የባህል ዘርፍ ሙያተኞች እና አስፈጻሚዎች ስልጠና ተሰጥቷል።
- ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ለባህል ተቋማት በሲኒማ ቤት፣ በቴአትር ቤት እና ቤተ መፃሕፍት ላይ የደረጃ ሰነድ (standard) ተዘጋጅቷል።
- በኪነጥበብ እና በሥነ ጥበብ ተቋማት ዘርፍ ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የማበረታቻ ሽልማት የሚሰጥበትን አሰራር ሥርዓት በመዘርጋት የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የሽልማትና ዕውቅና መርሃ ግብር በሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በድርሰት፣ በሰርከስ፣ በስዕልና ቅርፃ ቅርፅ፣ በፋሽን ዲዛይን፣ በውዝዋዜ እና በፊልም 2013ዓ.ም የሽልማትና ዕውቅና ለመስጠት ሥራዎች ተሠርተዋል።
- ኢትዮጵያ ያላትን ሀብትና የተፈጥሮ ፀጋ ለማስተዋወቅ እንዲሁም ወደ ኢንቨስትመንት አማራጭ ለመለወጥ ያለመ “የኢትዮጵያ ሳምንት” በወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል። ክልሎች ልዩ መገለጫችን ነው ያሉትን ባህላቸውን በተለያዩ ቅርፃ ቅርፆች፣ በተንቀሳቃሽ ምስሎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ጭፈራዎችን በማቅረብ ተከብሯል።
- የባህል ኢንዱስትሪ መረጃዎችን ለማዘመንና ወጥነት ያላቸው እንዲሆኑ ለማስቻል ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ጋር በጋራ በመሆን የመረጃ ቋት (ዳታቤዝ) በማዘጋጀት የ2013 ዓ.ም የባህል ኢንዱስትሪ ተቋማትና ሙያተኞች መረጃ ተደራጅተዋል።
- በባህል ዘርፍ (በባህል፣ በፊልም፣ በቋንቋ ፖሊሲዎችና በእደ ጥበብ ልማት በሀገር በቀል እውቀቶች)፣ በጎጂና መጤ ባህላዊ ድርጊቶች እና ባህል ዘርፍ ተቋማት አከፋፈት የኮቪድ 19 ጥንቃቄና ደህንነት መመሪያን ማስተዋወቅ ሥራ ለ7 ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ለ52 አሰልጣኞች የማስተዋወቅ ሥራ ተሠርቷል።
- ከሙያ ማኅበራት ጋር በመተባበር በኮቪድ ወቅት ጥንቃቄና ደህንነትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ የወረርሽኙን አስከፊነት የጥንቃቄ ትኩረትን የሚያስገነዝብና ከ100 በላይ ማስታወቂያዎች (ስፖት) በተለያዩ ሚዲያዎች ተለቋል።
- የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የባህል ዘርፍ አገልግሎት ተቋማትን ሥራ ለማስጀመር እንዲቻል ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የአሠራር መመሪያ ተዘጋጅቷል።
- ለክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም የባህል ጥበባት ዘርፍ ለባለድርሻ አካላት በሁለት ዙር መድረክ ሥልጠና ተሰጥቷል።
- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ የተመለከቱት ሥዕል ኤግዚቪሽን ለሶሰት ቀናት ለሕዝብ ዕይታ ቀርቧል።
- በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በተዘጉ ወቅት በቤት ተቀምጠው የነበሩ ተማሪዎች እና ሕፃናት የተሳተፉበት የኪነ ጥበብ ፈጠራ ውድድር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የአንድ ወር የቴሌቪዥን ፕሮግም ተሠርቷል።
- ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በተደረገ ዘመቻ ለተሳተፉ አካላትና መመሪያውን ተግባራዊ ላደረጉ ለሁለት ክልልና ለአንድ ከተማ መስተዳድር በድምሩ ለ25 ተቋማት እውቅና የመሥጠት ሥራዎች ተከናውነዋል።
- የባህል ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተመለከተ 6 የአሰራር ሥርዓት ሰነዶችና መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል።
- ከዩኔስኮ በተገኘው ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ኤክስፐርቶቸች ድጋፍ በመታገዝ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የፈልም ፖሊሲ ማስተገበሪያ (የተቋም ማቃቋሚያ ሰነድ እና የፈልም ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስትራተጂ) ፕሮጀክት እየተከናወነ ነው።
- የ2005 የዩኔስኮ ኮንቬንሽን ስምምነት መሠረት የ2020 (2012 ዓ.ም.) የሚቀርበውን በየአራት ዓመታቱ የሚዘጋጀውን ሪፖርት ለማጠናቀቅ እንዲቻል ሀገራዊ ኮሚቴውን በማስተባበር በወቅቱ ገቢ ለማድረግ ተችሏል።
ምንጭ፦ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር
July 19, 2021 at 4:07 am #19953AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የልጆች የሳይንስ ማዕከል አስመረቀ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የልጆች የሳይንስ ማዕከል አስመርቋል። አካዳሚዉ ከጀርመን የባህል ተቋም በኢትዮጵያ (Goethe-Institut Ethiopia) እና ጀርመን ሀገር ከሚገኘው ፌኖሜንታ ሳይንስ ማዕከል (Phänomenta e.V. Science Center) ጋር በመተባበር ማቋቋሙም ተገልጿል።
በማዕከሉ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ይህንኑ በማጠናከር የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑትን ሕፃናት በሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀት ተኮትኩተው እንዲያድጉና ለሀገራቸዉ ሁሉ አቀፍ ልማትና ብልጽግና ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ በሀገራችን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የልጆች የሳይንስ ማዕከል ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ማቋቋሙ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የሳይንስ አካዳሚዉ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረማርያም ባደርጉት ንግግር፥ አካዳሚው የሳይንስ ዕውቀትንና ባሕልን ለማሳደግ እንዲሁም ሕፃናት በተመቻቹ የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች እየተዝናኑ ስለሳይንስና ቴክኖሎጂ ፅንሰ-ሐሳብና አሠራር ዕውቀት እንዲያገኙና ለዘርፉ ያላቸው ዝንባሌ እንዲያድግ ታቅዶ መቋቋሙን አብራርተዋል።
አካዳሚዉ በዋናነት የሳይንስ ዕውቀትንና ባሕልን የማሳደግና የማስፋፋት፤ እንዲሁም ለመንግሥትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ምክር የመስጠት ዓበይት ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸዉን ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሆነም ገልጸዋል።
የማዕከሉ ግንባታ ከተጀመረ በ3 ዓመት የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ለግንባታው የጀርመን ባህል ማዕከል 1.5 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ መንግሥት የሳይንስ ዘርፍን ለማጠናከር ከሰጠው 40 ሚሊዮን ብር 7.3 ሚሊዮን እና የጀርመኑ ፌኖሜንታ የሳይንስ ማዕከል 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር ፅጌ አያይዘዉ አገራችን ወቅቱ በሚፈልገው የእድገት አቅጣጫና ፍጥነት እንድትጓዝ ለማድረግ የሳይንስ እውቀት ማበልፀጊያ ተቋማት ግንባታ የሳይንስ ማህበረሰብ ምስረታና የአገር በቀል እውቀት አጣምሮ መስራት እንዳለበት ገልጸዉ ለዚህ አላማ ስኬት የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የጀርመን የባህል ተቋም እና ጀርመን ሀገር የሚገኘው ፌኖሜንታ ሳይንስ ማዕከል ላደረጉት ቴክኒካዊና ፋይናንስ ድጋፍ በራሳቸውና በአካዳሚው ሥም ምስጋና አቅርበዋል።
የጀርመን የባህል ተቋም እና ጀርመን ሀገር የሚገኘው ፌኖሜንታ ሳይንስ ማዕከልን ወክለዉ በምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉ ተወካዮቻቸዉ በተለያየ የእድሜ ደረጃና የትምህርት እርከን ላይ የሚገኙ የማኀረሰቡን አካላት ግንዛቤ ለማሳደግና የሳይንስ እውቀትን ለማስረፅ ማዕከሉ ጉልህ ሚና እንደሚኖረዉ ገልጸዋል።
የሳይንስ አካዳሚው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ባስተላለፉት መልእክት የበርካታ አገር በቀል እውቀቶች፣ የጥንታዊ ታሪክ ቅርሶችና የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤቶች በመሆናችን እነዚህን በሳይንሳዊ መንገዶች በማዘመን ለህብረተሰባችን ህይወት መሻሻል የጀመርናቸዉን ዉጥን ተግባራት ከግብ ለማድረስ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ብርቱ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ
July 9, 2022 at 3:57 am #48417SemonegnaKeymasterበአዲስ አበባ 25 ሺህ 491 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች በዕጣ ተላለፉ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ14ኛ ዙር የ20/80 እና የ3ኛ ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ሐምሌ 1 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ተካሂዷል። በዚህም በድምሩ 25 ሺህ 491 የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ዕድለኞች ተለይተዋል።
በዕለቱ የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ አዲስ የመረጃ መያዣ እና ዕጣ ማውጫ የቴክኖሎጂ ሥርዓት በጥቅም ላይ መዋሉ ተገልጿል። ይህንን ተከትሎም የቤት ተጠቃሚዎች በአዲሱ ሲስተም በቀጥታ የወጣውን የአሸናፊዎችን ሙሉ መረጃ በ‘ኦንላይን’ ማረጋገጥ እንደሚችሉም ተገልጿል።
በማዘጋጃ ቤት አዳራሽ በተካሄደው የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች፣ ቤት ፈላጊዎች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለቤት ፈላጊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት በማስተላለፍ የዕጣ አወጣጥ መርሐ ግብሩን አስጀምረዋል።
በብዙ ፈተናዎች መካከል ውስጥ ሆነንም ቢሆን ግንባታቸው የተጓተቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ በቅተናል ነው ያሉት ከንቲባዋ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ “የከተማ አስተዳደራችን የከተማዋን የቤት ችግር ለመፋታት የተለያዩ የቤት ልማት አዳዲስ አማራጮችን በመዘርጋት የጀመረውን ርብርብ አጠናክሮ ይቀጥላል።” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልገዋል።
በተጨማሪም ከንቲባዋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ለረጅም ዓመታት በትዕግስት ገንዘባችሁን እየቆጠባችሁ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን በጉጉት የተጠባበቃችሁ የቤት ባለእድለኞች በሙሉ፤ እንኳን ደስ አላችሁ! የከተማ አስተዳደሩ የተረከበውን በርካታ ውስብስብ ችግሮች የነበሩባቸው ቤቶች እንዲሁም በተረከብነው ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ እዳ ተስፋ ባለመቁረጥ ይልቁንም በቁጭትና እልህ ሌት ተቀን በመረባረብ ከ21 ቢሊየን ብር በላይ በጀት በመጠቀም ለዛሬ ውጤት በመብቃታችን መላውን የከተማ በተለይም የቤቶች ልማትና የቤቶች ኮርፖሬሽን አመራሮችና ሰራተኞች፤ ኮንትራክተሮች፤የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፤ እና ሌሎች ለዚህ ስራ ስኬታማነት ሚናችሁን የተወጣችሁ በሙሉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ! የከተማዋን የቤት ችግር ለመፍታት የተለያዩ የቤት ልማት አዳዲስ አማራጮችን በመዘርጋት የጀመረውን ስራ አጠናክረን የምንቀጥል ሲሆን የከተማችን ነዋሪዎች እንደ ሁልጊውም ከጎናችን በመሆን ጉዞ ከጫፍ እንድናደርስ ጥሪዬን ማስተላለፍ እወዳለሁ!”
የከተማ አስተዳደሩ ለቤቶቹ መሠረታዊ ግንባታ የሚሆን ወደ 21 ቢሊዮን ብር በማውጣት ሥራውን ሲያከናውን መቆየቱንና ለበርካቶችም የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አክለዋል።
በዕጣው የተካተቱት በ1997 እና በ2005 ዓ.ም ተመዝግበው እስከ የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በአማካይ ለ60 ወራት የቆጠቡ የ20/80 እና 40 በመቶ እና ከዚያ በላይ የቆጠቡ የ40/60 ቤት ፈላጊዎች ናቸው ተብሏል።
በዚሁ መሠረት በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 27 ሺህ 195 እና በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 52 ሺህ 599 በአጠቃላይ 79 ሺህ 794 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ ሆነው በዕጣ እንዲካተቱ ተደርጓል ነው የተባለው።
በዕለቱ ዕለት ዕጣ የወጣባቸው ቤቶች የሚገኙባቸው ሳይቶችም በ40/60 መርሃ ግብር የተገነቡ ቤቶች አያት 2፣ ቦሌ በሻሌ እና ቡልቡላ ሎት 2 እንዲሁም በ20/80 መርሃ ግብር የተገነቡ ቤቶች በረከት፣ ቦሌ አራብሳ (ሳይት 3፣5፣6)፣ ወታደር፣ የካ ጣፎ፣ ጀሞ ጋራ፣ ጎሮ ሥላሴ፣ ፉሪ ሃና እና ፋኑኤል መሆናቸው ተገልጿል።
ሐምሌ 1 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የተላለፉ የጋራ መኖርያ ቤቶችን የተመለከቱ መረጃዎች፡-
- አሁናዊ የአንድ ካሬ የቤት ማስተላለፊያ ዋጋ፦ የሥራ አመራር ቦርዱ ታህሳስ 5 ቀን 2014 ዓ.ም በወሰነው መሠረት አሁን በሥራ ላይ ያለው አሁናዊ የአንድ ካሬ ማስተላለፊያ ዋጋ፡-
-
- 20/80 ቤት ልማት ፕሮግራም 7,997.17 ብር
- 40/60 ቤት ልማት ፕሮግራም 11,162.97 ብር ነው።
- ለዕጣ የቀረቡ ቤቶች የሚገኙባቸው ሳይቶች፣ የቤት ዓይነትና ብዛት በተመለከተ
- የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም — አያት 2፤ ቦሌ በሻሌ፤ ቡልቡላ ሎት 2 ሲሆኑ
- የ20/80 ቤት ልማት ፕሮግራም — በረከት፣ ቦሌ አራብሳ (ሳይት 3፣ 5፣ 6)፣ ወታደር፣ የካ ጣፎ፣ ጀሞ ጋራ፣ ጎሮ ስላሴ፣ ፉሪ ሃና እና ፋኑኤል
- በቤት ዓይነትና ብዛት ሲታይ
- በ20/80 የቤቱ ብዛት ስቱዲዮ ፡-3318 ባለአንድ መኝታ ፡- 7171 ባለሁለት መኝታ፤- 8159 በድምሩ 18648 ናቸው።
- በ40/60 ባለአንድ መኝታ፤- 1870 ባለሁለት መኝታ 4220 እና ባለሶስት መኝታ 753 በአጠቃላይ በድምሩ 25491 ቤቶች ናቸው።
- በዚህ ዙር ለዕጣ የቀረቡ ቤቶች የግንባታ አፈጻጸም ሁኔታ በጋራ መኖሪያና ንግድ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ በወጣ መመሪያ ቁጥር 3/2011 በሥራ አመራር ቦርድ በማስወሰን
- የ20/80 ከ96% በላይ፣ በ40/60 ከ87% በላይ የግንባታ አፈጻጸም ያላቸው ቤቶች ለዕጣ ቀርበዋል።
- የዚህ ዙር የዕጣ ተሳታፊዎች ሁኔታ (የቤት ፈላጊ ተመዝጋቢ ሁኔታ) የ20/80 ነባር ተመዝጋቢዎች (1997) በመመሪያው መሠረት ዝቅተኛውን የ60 ወራት ቁጠባ መጠን ያሟሉ ለእጣ ውድድር ብቁ የሆኑ እስከ የካቲት 21 2014 ዓ.ም ድረስ እና የ40/60 40% እና ከዚያ በላይ ቁጠባ ያላቸው እስከ የካቲት 21 2014 ዓ.ም የቆጠቡ ናቸው።
- በዕጣ ውስጥ የተካተቱት ተመዝጋቢዎችን በተመለከተ ከባንክ በተገኘው መረጃ መሠረት በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 27,195 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 52,599 በአጠቃላይ 79,794 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ ሆነው በዚህ ዙር ዕጣ እንዲካተቱ ተደርጓል። የዕጣ ተሳታፊዎች ሁኔታ ለዕጣ ከቀረቡ የቤት ዓይነቶች አኳያ በዝርዝር ሲታይ
- በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚደረጉ ማህበረሰብ ክፍሎችን በተመለከተ በመመሪያ ቁጥር 3/2011 በተገለጸው መሠረት ከ20/80 ነባር ተመዝጋቢዎች (1997) እና 40/60 ተመዝጋቢዎች ውስጥ
- መንግሥት ሠራተኞች 20 በመቶ፣
- ሴቶች 30 በመቶ፣
- አካል ጉዳተኞች 5 በመቶ እና አጠቃላይ ተመዝጋቢዎች 45 በመቶ በዕጣ የቤት ተጠቃሚዎች የሚለዩ ይሆናሉ።
- በከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክቱን ለመኖር ብቁ ለማድረግ ና ቤቶቹን ለማጠናቀቅ ከባንክ ቦንድ ብድር ብር 18.7 ቢሊዮን እና ለመሠረተ ልማት ግንባታ ከመደበኛ በጀት ብር 2.871 ቢሊዮን በድምሩ ብር 21.571 ቢሊዮን በሥራ ላይ ውሏል።
- በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 27,195 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 52,599 በአጠቃላይ 79,794 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ ሆነው በዚህ ዙር ዕጣ እንዲካተቱ ተደርጓል።
- በዚህ ዙር ከተላለፉ ቤቶች ውስጥ ከዚህ በፊት በማጣራት ሂደት የተገኙ ቤቶች ለልማት ተነሺ ሲስተናገዱበት ቆይተው የቀሩት ተካተዋል።
- የቤት ልማት ፕሮግራም ከጀመረበት አንስቶ በ17 ዓመታት ውስጥ ለህብረተሰቡ ማቅረብ የተቻለው 300 ሺህ ያህል ቤቶችን ብቻ ነው።
- የቤት ዕጣ አወጣጡ እንደ ቅደም ተከተል ሲሆን በ20/80 ፕሮግራም የ97 ተመዝጋቢዎች ቅድሚያ አግኝተዋል።
- የባለ ሦስት መኝታ ቤት በተመለከተ ፕሮግራሙ ባለፈው ዙር በቦርድ ውሳኔ በመዘጋቱ በቀጣይ በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱ ይሆናል።
July 13, 2022 at 2:05 pm #48569SemonegnaKeymasterሰሞኑን የወጣው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውድቅ ተደረገ፤ ዕጣ አወጣጡ ላይ ችግር የፈጠሩ ባለሙያዎችም በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰሞኑን የወጣው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውደቅ መደረጉን አስታውቋል። ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም የወጣው የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣን አስተዳደሩ ውድቅ ማድረጉን ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስታወቁት።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ የተፈጠረው ስህተት ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ ታስቦ የተሠራ የፖለቲካ ሸፍጥ መሆኑን በመግለጽ፥ በጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ የተፈጠረውን ስህተት በተመከለተ ሐምሌ 6 ቀን፥ 2014 ዓ.ም መግለጫ ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ነዋሪዎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት በ14ኛው ዙር የ20/80 እንዲሁም የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለ25 ሺህ 491 እድለኞች ዕጣ ማውጣቱ ይታወሳል።
በመረጃ መረብ ደኅንነት አስተዳደር (Information Network Security Agency /INSA/) አስተባባሪነት የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ዕጣው የወጣበት መንገድ/ሂደት (system) ሙያዊ ሂደትን ያልተከተለ መሆኑን አረጋግጧል። ዕጣው የወዳበት ሂደት ሲበለጽግ ቅድመ ማበልጸግ፣ በማበልጸግ ወቅት፣ ከበለጸገ በኋላ ያሉ የኦዲትና የማረጋገጥ የኢንዱስትሪ ሂደቶችን የተከተለ አይደለም ተብሏል።
የአጣሪ ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ በኃይሉ አዱኛ ሙሉ ሂደቱ በአንድ ግለሰብ ብቻ የተከናወነና በሚመለከተው የመረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ያልጸደቀ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል። ሂደቱ የደኅንነት ፍተሻን ያላለፈ፣ የበለጸገበትና ዕጣው የወጣበት መንገድ ትክክለኛ አካሄድ ያልተከተለ እንዲሁም የኢንተርኔት ግንኙነት ያለው መሆኑ ተዓማኒነቱን ያጎድለዋል ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት፥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ ማውጣት ሂደቱ ግልጽና ፍትሃዊ እንዲሆን ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ተገንብቷል። ይሁን እንጂ በግለሰብ አመራርና ባለሙያዎች አማካኝነት የቴክኖሎጂ ውንብድና ተፈጽሞ ለዓመታት ካለው ቀንሶ የቆጠበውን ሕብረተሰብና ከተማ አስተዳደሩን ያሳዘነ ድርጊት መፈጸሙን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባገኘው መረጃ መሠረት ለዕጣው ብቁ የሆኑ 79 ሺህ ዜጎች ቢሆኑም ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ግን በሲስተሙ ላይ 93 ሺህ ተጨማሪ ሰዎች በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲካተቱ ማድረጋቸውን ነው ከንቲባዋ የገለጹት። ይህም ሆኖ ዝናብና ቁር ሳይበግረው ወጥቶ የመረጠ፣ በሕግ ማስከበርና ህልውና ዘመቻ ከተማውን የጠበቀ እንዲሁም የኑሮ ውድነት ሳይበግረው ቤት ለማግኘት የቆጠበን ሕዝብ ከመጭበርበር ታድገነዋል ብለዋል።
በወቅቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዕጣው የሚካተቱት ሰዎች የተጣራ መረጃ ይዘን ነበር ያሉት ከንቲባዋ፥ በዕለቱ የሚያጠራጥሩ ነገሮች ስለነበሩና ጥቆማም ስለደረሰን ዕጣው በወጣ በሰዓታት ልዩነት ኮሚቴ በማዋቀር ምርምራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
ቴክኖሎጂው በመረጃ መረብ ደኅንነት አስተዳደር (INSA) ያልተረጋገጠ፣ በግለሰቦች ግንኙነት ብቻ የተፃፈ ደብዳቤ እንዲሁም ማንም ሊያስተካክለው የሚችል በግለሰቦች ሲነካካ የነበረ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል። በመሆኑም የአዲስ አበባን ሕዝብ የማይመጥን በጥቂት ግለሰቦች የተቀነባበረ የቴክኖሎጂ ውንብድና ስለተፈጸመ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም የወጣው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ሙሉ በሙሉ ውድቅ መደረጉን ገልጸዋል።
ከንቲባዋ አክለውም፥ በጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ ማውጣት ሂደት ከሕዝቡ ጋር በማቃቃር የከተማ አስተዳደሩን እምነት ለማሳጣት ታስቦ የተዘጋጀ የፖለቲካ ሸፍጥ መሆኑን በመግለጽ፥ በዚህ ሂደት የወጣው ዕጣ ውድቅ ከመሆኑም ባሻገር በቅርቡ የመረጃ መረብ ደኅንነት አስተዳደር (INSA) የተረጋገጠ ቴክኖሎጂ በመፍጠር ዕጣ እንዲወጣ ይደረጋል ብለዋል።
የመረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ላይ የተፈፀመው ተግባር የቴክኖሎጂ ውንብድና መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም ከዚህ ስህተት በመማር ሲስተም ሲበለጽግ ምስጢራዊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ልማት ሂደቶችን ማለፍ ይኖርበታል ብለዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ላይ ችግር በመፍጠር እርምጃ የተወሰደባቸው አመራሮችና ባለሙያዎች ዝርዝር ስም ዝርዝር ይፋ ሆኗል።
- ዶ/ር ሙሉቀን ሃብቱ:- ቢሮ ኃላፊ ከኃላፊነቱ የተነሳ
በቁጥጥር ስር የዋሉ፡-
- አብርሀም ሰርሞሎ:- የዘርፉ ምክትል ቢሮ ኃላፊ
- መብራቱ ወልደኪዳን:- ዳይሬክተር
- ሀብታሙ ከበደ:- ሶፍትዌር ባለሙያ
- ዮሴፍ ሙላት:- ሶፍትዌር ባለሙያ
- ጌታቸው በሪሁን:- ሶፍትዌር ባለሙያ
- ቃሲም ከድር:- ሶፍትዌር ባለሙያ
- ስጦታው ግዛቸው:- ሶፍትዌሩን ያለማ
- ባየልኝ ረታ፡- ሶፍትዌር ተቆጣጣሪ
- ሚኪያስ ቶሌራ፡- የቤቶች የመረጃ ቴክኖሎጂ (IT) ባለሙያ
- ኩምሳ ቶላ ፡- የቤቶች የመረጃ ቴክኖሎጂ (IT) ዳይሬክተር
April 8, 2023 at 4:37 am #56597SemonegnaKeymasterየአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሠጠው መግለጫ
የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ ያልከፈለው ዋጋ የለም፡፡
የኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጽናትም ሲል ከመክፈል የሚሰስተው ዋጋ የለም፡፡ በመሆኑም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ መላው የክልሉ ሕዝብ በሀገር ሕልውና እና በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ላይ ያለው አቋም የጊዜ እና የሁኔታዎች መፈራረቅን ተከትሎ የማይለዋወጥ ጽኑ ሀቅ ስለመሆኑ በታሪክና በዜጎች ህሊና እንዳይፋቅ ሆኖ የተከተበ እውነታ ነው፡፡
ስለሆነም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልላችን ውስጥ የሚተለሙም ሆነ የሚፈጸሙ ማንኛውም ዓይነት ተግባራት ከዚህ ብሔራዊ መዳረሻ አንጻር የሚቃኙ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ማንኛውም ዓይነት ተቋማዊ መዋቅሮች የሚደራጁበትም አልፋ እና ኦሜጋዊ አመክንዮ ይኸው ነው፡፡
ከሰሞኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዋና አጀንዳ ከሆኑት ብሔራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውና በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን መልሶ የማደራጀት ተግባር ዋነኛ እና ብቸኛ ምክንያትም ዓላማው የኢትዮጵያን ሕልውናን የበለጠ የማበርታት የጋራ ግብን ያነገበ፣ በተሟላ ሀገራዊ ጥናት ላይ የተመሠረተ፣ የሕዝቦችን አንድነትንና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተተለመ እንዲሁም የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን እውን ለማድረግ በሁሉም ክልሎች ታምኖበት የተገባበት ወሳኝ ተግባር ነው።
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በክልሉ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የአማራ ክልልን ሕዝብ ሠላም እና ጸጥታን ለማስከበር በቅንነትና በቆራጥነት አገልግሏል፡፡
ከክልል አቀፍ ውለታው ባሻገር በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ ተጋርጦ የነበረን ከፍተኛ አደጋ ለመቀልበስ ሲል ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በመሆን በኢትዮጵያዊነት የላቀ ሥነ-ልቦናዊ ከፍታ ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት ከፍሎ ኢትዮጵያና አትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣን አደጋ በታማኝነት አምክኗል፡፡ ይህ አኩሪ ገድልና ውለታ ሁልጊዜም በታሪክና በትውልድ ልቦና ውስጥ እየተዘከረና ጽንቶ የሚኖር ታላቅ ተግባር ነው፡፡
ይህን መሰሉን ብሔራዊ ውለታ የበለጠ ለማጎልበትና ለማስፋት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አማራ ክልል ጨምሮ በሁሉም ክልላዊ መንግሥታት ውስጥ የሚገኙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን ያሰባሰበ በጥናት ላይ የተመሠረተ መልሶ የማደራጀት ሥራ በሁሉም ክልሎች በየደረጃው ካለው የፀጥታ አመራር፣ የመንግሥት አመራር፣ የልዩ ኃይል አመራርና አባላት፣ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት የተደረገበትና እየተደረገበት ያለ በሂደት ላይ የሚገኝ የጋራ ሀገራዊ ተግባር ነው።
ይህ የልዩ ኃይል ፖሊስ አደረጃጀቶችን መልሶ የማደረጃት ወይም የሪፎርም ሥራ በሁሉም የፌደራልና ክልላዊ መንግሥታት መሪዎች የጋራ ስምምነትና እንደ አንድ ሀገር አንድ ጠንካራ የፌደራልና የክልል የፀጥታ መዋቅር እንዲኖረን ታስቦ የተለያዩ አማራጮች ለልዩ ኃይል አባላቶቻችን ያቀረበ እና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በኩር ያደረገ ሀገር አቀፍ ታሪካዊ ተግባር ነው፡፡ ተግባሩም ለሁሉም ክልል የልዩ ኃይል አደረጃጀቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራልና የክልል መደበኛ ፖሊስ፣ የፌደራልና የክልል የማረሚያ ቤቶችን ፖሊስ አባል እንዲሆኑ አማራጮች ያቀረበ ብሔራዊ ተግባር ነው።
በቅርቡ በመንግሥት የተጀመረው የልዩ ኃይል ፖሊሶች የሪፎርም ተግባር እውነታዉ ከላይ በተቀመጡት አማራጮች ለሁሉም ክልሎች የልዩ ኃይል አባላት እንደየፍላጎታቸው በቀረቡት አማራጮች እንዲካተቱ ታሳቢ ያደረገ የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላትን የማጠናከር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኝ ብሔራዊ ተግባር ነው።
ይሁን እንጂ እውነታዉ ይሄ ሆኖ ሳለ አንዳንድ አካላት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን አየር ላይ እንዲበተን እየተደረገ ነው የሚል ከእውነት የራቀ ፍፁም በተሳሳተ መንገድ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የአማራን ሕዝብ ውስጣዊ ሰላምና አንድነት የሚያደፈርስ፣ የልዩ ኃይሉን አንድነት የሚረብሽ፣ ባልተገባ መንገድ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ። ድርጊቱም ሕዝባችንና የልዩ ኃይል አባሎቻችንን በተጨባጭ እየረበሸ ይገኛል።
ስለሆነም መላው የልዩ ኃይል አባላትና መላው የክልሉ ሕዝብ እንዲገነዘቡት የምንፈልገው መንግሥት ይህንን የመልሶ ማደራጀት ሥራ የሚከውነው የልዩ ኃይላችንን የሰው ኃይል ለበለጠ ፋይዳ ላለው ተልዕኮ መልሶ የማደራጀትና ብቁ የማድረግ ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ የማዘጋጀት ተግባር እንጅ በመልሶ ማደራጀቱ ሂደት ምንም ዓይነት የሚበተንም ኃይል የሌለ መሆኑን ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል።
ስለሆነም መላው የአማራ ሕዝብ በአንዳንድ አፍራሽ የሚዲያ ቡድኖች በሚነዛው አሉቧልታ ሳይታለልና ሳይደናገር እንደ አንድ ሕዝብ ያለውን ታሪኩን እና ሥነ ልቦናውን በሚመጥነው የኢትዮጵያዊነት ላዕላዊ ማእቀፍ ጥላ ስር በመሰባሰብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የማጽናት ሂደትን እንዲደግፍ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
የተከበራችሁ የክልላችን ሕዝቦች፥ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ መብትና ጥቅም የሚጋፋ የትኛውንም ዓይነት ውሳኔ ተግባራዊ እንደማያደርግ ሕዝባችን ሊያውቀው ይገባል።
የተከበራችሁ የክልላችን የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት እንዲሁም መላው ሕዝባችን፥ ለራሳቸው ጥቅምና ፖለቲካዊ ዓላማ ሲሉ ክልላችንን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ከሚሠሩ አካላት ራሳችሁን በመጠበቅ የክልላችን የፀጥታ ኃይል ብቁ ዘቦች ሁናችሁ ሰላምና ፀጥታን በማስጠበቅ ሥራችሁ እንድትተጉ እያሳሰብን የተጀመረውን ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ሥራ መላው ሕዝባችንንና ልዩ ኃይላችንን በማወያየት እና በመተማመን የሚፈፀም በመሆኑ በየካምፓችሁ ወይም በየተመደባችሁበት የሥራ ቦታ ተረጋግታችሁ በትግስት እንድትጠብቁ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
መጋቢት 29/2015 ዓም
ባሕር ዳር፥ ኢትዮጵያምንጭ፦ የክልሉ ሕዝብ ግንኙነት
April 20, 2023 at 12:44 am #56748SemonegnaKeymaster“መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣት አገልግሎት አሰጣጡ ምቹ ባለመሆኑ ለእንግልት ተዳርገናል” ― ተገልጋዮች
“በጉዳዩ ላይ በቅርቡ መግለጫ እሰጣለሁ” ― የኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲአዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣት ከፍተኛ መጉላላት እየደረሰባቸው መሆኑን ተገልጋዮች ቅሬታ አቀረቡ። የኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በበኩሉ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለቀረበለት ተደጋጋሚ ጥያቄ በጉዳዩ ላይ በቅርቡ መግለጫ እሰጣለሁ ከማለት ውጪ መረጃ ሊሰጥ አልቻለም።
በአዲስ አበባ መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣትም ሆነ ለማደስ ወደተቋሙ የሚሄዱ ተገልጋዮች በተቋሙ ባለው ምቹ ያልሆነ አሠራር ምክንያት ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ይገልጻሉ። ተገልጋዮቹ እንደሚሉት በተቋሙ አገልግሎቱን ለማግኘት ከሌሊት 9፡00 ሰዓት ጀምሮ ተሰልፎ ወረፋ ከመጠበቅ ጀምሮ ፓስፖርቱ አልቆም ለማግኘት ያለው ሂደት ውስብስብና ለከፍተኛ እንግልት የሚዳርግ ነው።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ፓስፖርት አገልግሎትን ለማግኘት በኦንላይን (online) አማካኝነት ምዝገባ የሚካሄድ ቢሆንም፥ ከዚያ በኋላ በተቀጠሩበት ዕለት ሌሊት ወጥቶ ወረፋ መጠበቅ፣ ከዚያም በኋላ ሂደቱን ሲያልፉ ፓስፖርት ለማግኘት ያለው አሠራር ተገልጋይን የሚያማርር ነው።
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መዲና ጂብሪል፥ ለልጆቻቸው ፓስፖርት ለማውጣት በስም ዝርዝር ምደባ መሠረ ከካዛንቺስ ፖስታ ቤት እንዲወስዱ የተገለጸላቸው ቢሆንም፥ ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ ከፖስታ ቤቱ አልደረሰም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል።
ወደ ኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ተመልሰው መጠየቅ እንዳለባቸው የተነገራቸው ወይዘሮ መዲና፥ ከዋናው መሥሪያ ቤት ወደፖስታ ቤት በየጊዜው እያመላለሷቸው መቸገራቸውን በምሬት አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈ በኢምግሬሽን መግቢያ በሮች ላይ ጥበቃዎችና ተራ አስከባሪዎች ወደ ውስጥ እንዳታስገቡ የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶናል በሚል ተገልጋዮችን ለመምታት የሚጋበዙ መሆናቸውን ገልጸው፤ በዚህም የሚመለከተውን አካል ለመጠየቅም ሆነ ለማነጋገር እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።
ችግሩን በተመለከተ ለማን አቤት ይባላል የሚሉት ወይዘሮ መዲና፥ ዜጎችን የሚያጉላሉ አሠራሮችን ማስተካከልና አገልግሎቱን የተሟላ ማድረግ ይገባል ብለዋል። መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣት አስፈላጊውን ማስረጃ ከሰጠችና ከተመዘገበች አንድ ወር ከአሥራ አምስት ቀን እንደሆናት የምትገልጸው ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወይዘሪት ሰናይት ንጉሴ ነች።
የአስቸኳይ ፓስፖርት ከመከልከሉ በፊት መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት በመሄድ ማመልከቷን ትገልጻለች። ኦርጅናል የልደት ካርድ፤ መታወቂያና የትምህርት ማስረጃዎችን እንዲሁም አስፈላጊውን መረጃ ሁሉ አሟልቻለሁ። አሻራ የሰጠሁ ቢሆንም ማስረጃውን አጣርተን እንጠራሻለን የሚል ምላሽ ቢሰጠኝም እስካሁን ምላሽ አላገኘሁም ትላለች።
እኔ ሻይና ቡና በመሸጥ የምተዳደር ነኝ። በሕጋዊ መንገድ ወደ ሌላ አገር ሄጄ ለመሥራት ብዩ ፓስፖርት ለማውጣት ፈልጊያለሁ ስትል ሁኔታዋን አስረድታለች።፡ ከለሊቱ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ ተራ ለመያዝ ወደኢምግሬሽን የምትሄድ መሆኑን በመግለጽ፤ እንግልቱ ግን ወደ ኢምግሬሽን በተደጋጋሚ የሄደች ቢሆንም ሳንደውል ለምን ትመጫለሽ የሚል ምላሽ እንደተሰጣትና፤ ጉዳዩን ለተቋሙ ቅሬታ ሰሚዎች ያቀረበች ቢሆንም ምንም ማድረግ እንደማይችሉ እንደተነገራት አስረድታለች።
የጅማ ከተማ ነዋሪው አቶ አብዲሳ ታደሰ በበኩላቸው፥ በከተማው የኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በተደጋጋሚ ያቀረበው የፓስፖርት ይሰጠኝ ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ወደዋናው መሥርያ ቤት ቢመጡም እዚህም ምላሽ ሊያገኝ እንዳተሰጣቸው ይገልጻሉ።
አቶ አብዲሳ አስፈላጊ ናቸው የተባሉ መረጃዎችን ሁሉ ይዘው መቅረባቸውን በመጥቀስ ከጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱን ሳያገኙ እየተጉላሉ መሆኑን ገልጸዋል። የፓስፖርት ሂደቱን ሲጀምሩ በሦስት ወር እንደሚሰጣቸው የተነገራቸው ቢሆንም በተቀጠሩበት ቀን ፓስፖርቱን መውሰድ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።
የቅርጫፉን ኃላፊ ስለጉዳዩ ማነጋገሩን የሚገልጸው አቶ አብዲሳ፥ ፖስታ ቤት ሂድ በማለት እንደመለሱለት ቢናገርም ፖስታ ቤት ግን ፓስፖርቱን ሊያገኝ እንዳልቻለ አስረድቷል። በዚህ የተነሳ ወደውጭ አገር ለመሄድ ያሰበውን የቪዛ ዕድል ማጣቱን በምሬት ገልጿል።
ችግሩ ከዋናው መሥሪያ ቤት ነው የሚል ምላሽ እንደተሰጠው ጠቁሞ፤ በወቅቱ ወደአዲስ አበባ ኢምግሬሽን ለመምጣት የመሸኛ ደብዳቤ እንዲሰጡት በጠየቀበት ወቅት ተጨማሪ 600 ብር በድጋሚ መክፈል እንደሚጠበቅበት የተገለጸለት መሆኑን አስረድቷል።
የፓስፖርት አገልግሎትለማግኘት እየተጉላሉ የሚገኙ ዜጎች ቀልጣፋ አሠራር እንዲፈጠርና በኢሚግሬሽን አገልግሎትና በፖስታ ቤቶች መካከል ተገቢው መናበብ ሊፈጠር ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ የኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲን በስልክና በደብዳቤ በተደጋጋሚ በመጠየቅ ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ኤጀንሲው በጉዳዩ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ በቃል ደረጃ ቢያሳውቅም ይህን ዜና የዘገበው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ወደህትመት እስከገባበት ሰዓት ድረስ ምንም ዓይነት መግለጫ እንዳልተሰጠ ማረጋገጥ ተችሏል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.