Search Results for 'ፌዴራል ፖሊስ'

Home Forums Search Search Results for 'ፌዴራል ፖሊስ'

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 26 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    የ6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ “ሰላምና ደህንነት” አስመልክቶ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

    የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ፥

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በቅድሚያ ለታሪካዊው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ እያለ የምርጫው ሂደት ተጀምሮ አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ በጨዋነትና በትዕግስት ላደረጋችሁት ድጋፍና ትብብር የላቀ ምስጋናውን እያቀረበ በቀሪው የምርጫ ሂደትም ምርጫውን የሚያደናቅፉ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ እንደተለመደው ሁሉ መረጃ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለፀጥታ እና ለደህንነት ኃይሉ በማድረግ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

    የተከበራችሁ የሀገራችን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፥

    የምርጫ ሕጉንና የሥነ-ምግባር ደንቡን አክብራችሁ እስከ አሁን ለምርጫው ሰላማዊነት የበኩላችሁን ገንቢ አስተዋፅኦ በማበርከታችሁ ኮሚሽኑ ምስጋናውን እያቀረበ በቀጣይም በሚኖረው የምርጫ ሂደት እስከመጨረሻው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ኮሚሽኑ አጥብቆ ይጠይቃል።

    የተከበራችሁ የፌዴራልና የክልል የፀጥታና የደህንነት አካላት፥

    መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ፍፁም ገለልተኛ ሆናችሁ ሌት ተቀን እያበረከታችሁት ላላችሁት አስተዋፅኦ ኮሚሽኑ ከልብ እያመሰገነ፤ በቀጣይ ለሚኖረው የድምፅ አሰጣጥና አጠቃላይ ለምርጫው ሂደት ስኬታማነት የተሰጣችሁን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነታችሁን ልክ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ እንድትወጡ ከአደራ ጭምር ያሳስባል፡፡

    ኮሚሽኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወሳኝ ምዕራፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት የምርጫ ሂደቶች ከሁከትና ብጥብጥ የጸዱ እንዲሆኑ ከፀጥታና የደህንነት መዋቅሩ ጋር የተቀናጀ የምርጫ ደህንነት ዕቅድ በማዘጋጀት፣ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ዕለት እና በድኅረ-ምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ የፀጥታ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመተንተን እና በመለየት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ሲሠራ ቆይቷል።

    ከዚህ አንፃር 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ማጠናቀቅ ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የሀገራችንን ታላቅነት ለመላው ዓለም የምናሳይበት ታላቅ ኩነት መሆኑንና ለገጽታችን ግንባታ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን የተረዳው ኮሚሸኑ የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ፀጥታውን ለማናጋት፣ የምርጫውን ሰላማዊነት ለማደፍረስና የሁከትና ብጥብጥ መንስዔ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ከወዲሁ በመረዳት ምንም ዓይነት ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በየትኛው አካባቢ እንዳይኖር ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የሀገራችን የፀጥታና የደህንነት መዋቅሮች በከፍተኛ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚያስችላቸው ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስምሪት ገብቷል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሕዝቡ እና ለሥራችን ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉት አስፈላጊ እና ወሳኝ የሆኑት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች በምርጫ ወቅት ያለ በቂ ምክንያት እንዳይቋረጡ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ኮሚሽኑ በአንክሮ ያሳስባል፡፡

    በመጨረሻም መላው የሀገራችን ሕዝብ እና የፀጥታ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመቀናጀት ይህንን ታሪካዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንድንወጣ ጥሪያችንን በከፍተኛ አክብሮት እያቀረብን፥ በድምጽ መስጫ ዕለትና በድኅረ-ምርጫ ወቅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በሕግ አግባብ ብቻ እንዲሆኑ ኮሚሽን በጥብቅ ያስታውቃል፡፡

    ኮሚሽኑ በድጋሚ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም አደረሳችሁ ይላል።

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
    ሰኔ 12 ቀን 2013 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ

    ምንጭ፦ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

    6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ -- ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

    Anonymous
    Inactive

    ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር አዲስ አበባ ከተማን ከማንኛውም የፀጥታ ስጋት የፀዳች ለማድረግ ባካሄደው የአንድ ሳምንት የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ውጤት ማስመዝገቡን ገለፀ።

    ኮሚሽኑ የፀጥታ ሥራውን በብቃት ለማከናወን የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅቶ የጋራ በማድረግ በተግባር ምዕራፉ የመጀመሪያ ሳምንት ባካሄደው ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ሂደት ባከናወናቸው ጠንካራ የወንጀል መከላከል ተግባራት

    1. በተደራጀ መንገድ ታቅደው የሚፈፀሙ የዘረፋና የግድያ ወንጀሎች፣
    2. የግል ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀም አፈና እና ግድያ፣
    3. የተሽከርካሪ ስርቆት፣
    4. ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን መቀነስ መቻሉን ገልጿል።

    ኮሚሽኑ እንደገለፀው በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 359 ተጠረጣሪዎች ተከታትሎ በሕግ ቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝና ከዚህ ውስጥ

    ትግራይ ላይ በተፈፀመው የጁንታው ጥቃት የተሳተፉና በተለያየ መንገድ አምልጠው ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት በተለያየ የወንጀል ተገባር ሲሳተፉ በተገኘ የሕዝብ ጥቆማ 135 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሰባት የኦነግ ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ በማጣራት ላይ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

    ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡን ከጎኑ በማሰለፍ በተቀናጀ የጋራ ኦፕሬሽን በተለያዩ በወንጀል የተጠረጠሩ የነፍስ ወከፍና የቡድን ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች፣ የሀገር ውስጥ ሀሰተኛ ገንዘብ እና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ተሽከርካሪዎች፣ በዘረፋና በግድያ ከተወሰዱ 10 ራይድ ተሽከርካሪዎች ስምንቱ እንደተያዙና የሁለቱ አካላቸው እንደተፈታ ፖሊስ ደርሶበት በቁጥጥር ስር አውሎ በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን አመልክቷል።

    ኮሚሽኑ ባካሄደው የጋራ ኦፕሬሽን የኑሮ ውድነት ለማባባስ እና የንግድ ስር-ዓቱን ለማዛባት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በዚህ ኦፕሬሽን በቀጥጥር ስር አውሎ ከእነሱም ብዛት ያላቸው ሸቀጦችና ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

    በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ባካሄደው በዚህ የጋራ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ንብረቶች መካከል በዝርፊያ የተወሰደ አንድ ሲኖ-ትራክ ከባድ መኪናንና ከግለሰቦች የተነጠቁና ከድርጅቶች የተዘረፉ ባርካታ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመያዝ ለባለ ንብረቶቹ ተመላሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ሐሰተኛ መታወቂያ በመቀያየርና በመጠቀም በተለያዩ የተሽከርካሪ መሸጫ ድርጅቶች እየተቀጠሩ ተሽከርካሪዎችን በሌሎች በማሰረቅ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች መያዛቸውንም ጨምሮ ገልጿል።

    በመጨረሻም ኮሚሽኑ ይህ ከጅምሩ ውጤት ያስመዘገበ የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ወደ ፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፆ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደህንነት አስተማማኝና ዘላቂ ይሆን ዘንድ የሰላሙ ባለቤት የሆነው መላው የከተማው ህዝብ ለሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሱ መረጃዎችን ባለመቀበልና ሀሰተኛ መረጃዎችንም ባለመጋራት እንዲሁም ለፖሊስ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በፍጥነት እንደተለመደው መረጃ በመስጠት እንዲተባበር እየጠየቀ ለዚህ ኦፕሬሽን መሳካት የከተማው ህዝብ ላደረገው ከፍተኛ አሰተዋጽኦ ኮሚሽኑ ሌሎች የፀጥታ ሀይሎችንም በመወከል የላቀ ምስጋና ያቀርባል።

    የኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
    መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ም

    የኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

    Anonymous
    Inactive

    ከትግራይ ክልል ሁኔታ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች አያያዝ

    አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እና የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው እስር ቤት የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በመገኘት በታሳሪዎች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል አድርገዋል።

    በጉብኝቱ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙትን እነ ዶ/ር አብረሃም ተከስተ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ አቶ ስብሀት ነጋ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ፣ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ፣ ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ፣ ሜ/ጀነራል ይርዳው ገብረመድኅን፣ ሜ/ጀነራል ገብረመድኅን ፍቃዱ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋን ጨምሮ በአጠቃላይ 21 ታሳሪዎች የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ ጎብኝተው ታሳሪዎችን አነጋግረዋል። እንዲሁም ከፖሊስ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

    በጉብኝቱም ታሳሪዎቹ በጥሩ አካላዊ ደኅንነት ላይ እንደሚገኙ፣ የሚገኙበት አካባቢና ክፍሎች ንፁህ እና ብዙም ያልተጨናነቁ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን ያላቸው መሆኑንና አጠቃላይ ሁኔታው ተቀባይነት ያለው መሆኑን ኮሚሽኑ ተመልክቷል። ሁሉም ከላይ የተጠቀሱት ታሳሪዎች ወደ ፌዴራል ፖሊስ እስር ቤት ከመጡ ወዲህ ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩንና ፖሊሶች በተገቢው የሙያ ሥነ ምግባር የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። የህክምና አገልግሎት ባለው አቅም እያገኙ እንደሆነ፣ ከቤተሰባቸው ተገናኝተው አቅርቦት እንደሚቀበሉ እና ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት መቻላቸውን አስረድተዋል። የተወሰኑ ታሳሪዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል በበረሀ ውስጥ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በሰብአዊ እንክብካቤ መያዛቸውን እና የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ከድንገተኛ አደጋና ጥቃት እንደጠበቋቸው ገልጸዋል።

    በሌላ በኩል ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን፣ በትግራይ ክልል ከመቀሌ ከተማ ሸሽተው ሲሄዱ በተያዙበት ጊዜ ስድብ፣ ድብደባ፣ ማስፈራራት እና ተኩስ እንደነበረና የአካል መቁሰል እንደደረሰባቸው፣ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም ነፃ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጋፋ መልኩ በሚዲያ አሰልፎ የማቅረብ እና የማንኳሰስ ሁኔታ እንደነበረ ያነሱ ታሳሪዎች አሉ። አብዛኞቹ ታሳሪዎች የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ  በተናጠል አለመቅረቡን እና የምርመራ ሂደቱ  በአፋጣኝ አለመታየቱን ገልጸው አቤቱታ አቅርበዋል። ታሳሪዎቹ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከጠበቆች ጋር የሚገናኙበት ጊዜ ማጠሩን አንስተዋል። በተጨማሪም የተወሰኑ ታሳሪዎች የራሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ ሒሳብ በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል።

    ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹ የሚገኙበት የአያያዝ ሁኔታ በተገቢው ደረጃ መሆኑን በማረጋገጥ፣ በታሳሪዎች የተነሱ አስተዳደር ነክ ጥያቄዎች ላይ ከእስር ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጓል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የወንጀል ምርመራውን በተቻለ ፍጥነት ማጠናቀቅ እና የሕግ አግባብ በሚፈቅደው መልኩ በዋስትና ሊለቀቁ የሚገባቸውን ታሳሪዎች መለየት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።

    ምንጭ፦ ኢሰመኮ

    ከትግራይ ክልል ሁኔታ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች አያያዝ

    Anonymous
    Inactive

    አሰቃቂ ጭፍጨፋ በመተከል ዞን ― የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ 

    ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፡ የሰዎች ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግሥት ግዴታ ነው።

    ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፥ መተከል ዞን፥ ቡለን ወረዳ፥ በኩጂ ቀበሌ ከለሊቱ 10፡00 ሰዓት ላይ የታጠቁ ኃይሎች በእንቅልፍ ላይ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ በለኮሱት እሳት እና በተኩስ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸው በክልሉ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መሄዱን እንደሚያሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ገለጸ።

    ኢሰመኮ የጥቃቱን ሂደት በተመለከተ ታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሚመለከታቸው አካላት እና ከተጎጂዎች ጋር በመነጋገር ሲከታተልና ሲያጣራ ቆይቷል። በኩጂ ቀበሌ ከወረዳው መቀመጫ ከሆነችው ቡለን ከተማ 90 ኪ.ሜ. ርቃ የምትገኝ ሲሆን የሺናሻ፣ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ይኖሩባታል። ለቀበሌው የተመደበ የፖሊስ ወይም የፀጥታ ኃይል አለመኖሩን ኮሚሽኑ በክትትሉ መሠረት ተረድቷል።

    ኮሚሽኑ ሁኔታውን እስካጣራበት ጊዜ ድረስ በቡለን ሆስፒታል 36 ተጎጂዎች እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን፥ አብዛኞዎቹ በጥይት ሌሎቹ በቀስት የቆሰሉ መሆናቸውን ኢሰመኮ በምልከታ አረጋግጧል። በተጨማሪም ሰዎች ጥቃት የደረሰባቸውን ሁኔታ የሚያሳዩና የሚረብሹ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች ለኮሚሽኑ ደርሰውታል። በሰው ሕይወት እና በአካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎችና የተሰበሰቡ ማሳዎች በእሳት ጋይተዋል። ቢያንስ 18 ያክል ነዶዎች ሲቃጠሉ ማየታቸውን አንድ ተጎጂ አስረድተዋል።

    በጨላንቆ እና ዶሼ ቀበሌዎች ቤቶች እየተቃጠሉ እንደሆነ ከአካባቢው ለኮሚሽኑ የተላኩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በድባጤ ወረዳ ዶንበን ቀበሌ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ከታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ቀዬአቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሆነም ኮሚሽኑ ተረድቷል።

    አካባቢውን በቅርበት እንዲጠብቅ የተመደበው ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማረጋጋት ተግባር ወደቦታው ተልከው የነበሩ አንድ የፌዴራል እና ሁለት የክልሉ አመራሮችን ለማጀብ በሚል አካባቢውን ለቅቆ መሄዱ ታውቋል። ጥቃቱ የጀመረው ይህንኑ ተከትሎ እንደሆነና ሌሊቱን የጀመረው ጥቃት እስከ ቀኑ አጋማሽ ድረስ መዝለቁንም ለማወቅ ተችሏል። ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች እንደሚሉት በጥቃቱ ከሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኛው የሺናሻ ተወላጆች ናቸው።

    ከዚህ ቀደም በነበሩ ጥቃቶች ፈጻሚዎቹ ከ”ጫካ” የሚመጡ ሰዎች የነበሩ ቢሆንም፥ በዚህኛው ጥቃት “በስምና በመልክ የሚያውቋቸው” የበኩጂ ቀበሌ ነዋሪዎች ጭምር መሳተፋቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ተጎጂዎች ገልጸዋል።

    ኢሰመኮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ተደጋጋሚነትና የክልሉን ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ አስመልክቶ የፌዴራሉንና የክልሉን መንግሥታት የተጠናከረ ትብብርና ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል፤ ይሁንና ጥቃቶቹ በመልክ እና በስፋት እየተባባሱ መጥተዋል።

    ስለሆነም፣ በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው እና ለተፈናቀሉ ሰዎች የሕክምና እና ሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም ተገቢው ማጣራትና ጥቃቱን ባለመከላከልም ሆነ በሌላ መልኩ ጥቃቱን የፈጸሙና ያባባሱ ሰዎችን ሕግ ፊት የማቅረቡ ሂደት ከወዲሁ እንዲጀመር ኮሚሽኑ ያሳስባል። በአካባቢው የሚገኘውን የፀጥታ ኃይልና መዋቅር የሰዎችን ደኅንነት ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በከፍተኛ ደረጃ በአፋጣኝ እንዲጠናከር ኢሰመኮ ጥሪ ያቀርባል።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
    ታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም.

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን

    Anonymous
    Inactive

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወሰነ

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወሰነ።

    ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲመለስ የተሰጠውን በቂ ዕድል መጠቀም ባለመቻሉ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ በሕገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወስኗል።

    ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በክልሉ በሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አስነዋሪ ጥቃት ፈጽሟል። በተጨማሪም በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በንፁሃን ዜጎችና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።

    የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 12 በአንድ የክልል መንግሥት ተሳትፎ ወይም ዕውቅና ሕገ-መንግሥቱን ወይም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት በተለይም፡

    (1) በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ ማድረግ፤

    (2) ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ክልል ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍታት፤

    (3) የፌዴራሉን ሰላምና ጸጥታ ማናጋት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ እንደሚቆጠር ተደንግጓል። ከዚህ ድንጋጌ አንጻር ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት የፈጸመው እና እየፈጸመ ያለው ድርጊት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ ተረጋግጧል።

    በዚሁ መሠረት የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) ማንኛውም ክልል ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ስልጣን እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 36 (1) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአንድ ክልል ውስጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ ሲያምን የፌዴራሉ መንግሥት ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዝ እንደሚችል እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 13 (4) ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ጣልቃ እንዲገባ ሊያዝ እንደሚችል በመደንገጉ ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ እና የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመፈጸም የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ስለሆነ ይህንን ድርጊት ማስቆም ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱና በአዋጆቹ የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት በመጠቀም ሕገ-መንግሥታዊ መፍትሔ መስጠት ያለበት ሆኖ በመገኘቱ፥ ጥቅምት 28 ቀን ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሚከተሉትንን ውሳኔዎች አሳልፏል።

    1. ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት ለማስቆም የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ትዕዛዝ ሰጥቷል፤ እንዲሁም ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 14 (2) መሠረት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተጣጣመ መልኩ አደጋውን ለማስወገድ እንዲቻል የፌደራል ፖሊስን ወይም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ወይንም ሁለቱንም በክልሉ እንዲያሰማራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፤
    2. ሕገ-ወጡን የክልሉ ምክር ቤት እና የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ታግዶ ለፌደራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነና በአዋጅ 359/1995 አንቀጽ 15 ላይ የተቀመጡት ስልጣንና ተግባራት የሚኖሩት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወስኗል። በዚሁ መሠረት የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ከሌሎች አግባብነት ካላቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በመተባበር ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል። በተጨማሪም ለክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካል የተሰጡትን ተግባሮች ይኖሩታል። በተለይም ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤

    ሀ) አስፈፃሚ አካሉን ይመራል፣ ያስተባብራል፤

    ለ) የጊዜያዊ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ይመድባል፤

    ሐ) ሕግና ሥርዓት መገበሩን ያረጋግጣል፤

    መ) አግባብ ባለው ህግ መሠረት በክልሉ ምርጫ የሚከናወንበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤

    ሠ) የክልሉን እቅድና በጀት ያፀድቃል፤

    ረ) በፌዴራል መንግሥቱ ሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል።

    1. ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን የምክር ቤቱ ውሳኔዎች አፈጻጸምና ክልሉ ስለሚገኝበት ሁኔታ በተመለከተ ክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ አስፈላጊነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ በማለት ወስኗል።

    በመጨረሻም፥ መላው የትግራይ ሕዝብና የሀገራችን ሕዝቦች ሕገ-ወጡ ቡድን የፈፀመውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊና አስነዋሪ ድርጊት በማውገዝ የሀገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር በሚል መርህ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ካለውና የኩራታችን ምንጭ ከሆነው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጨምሮ ከፌደራሉ መንግሥት እና ከሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጎን እንዲቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመተሳሰብ፣ አንዱ ለሌላው ጠበቃና ዋስትና በመሆን እኩይ ዓላማ ይዘው እርስ በርሳችንን በማጋጨት ሀገራችንን ለመበታተን ሌትተቀን የሚሠሩ ኃይሎችን ነቅተን በመጠበቅና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ረገድ ሁሉም ዘብ እንዲቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል።

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት

    Anonymous
    Inactive

    ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ለክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ
    ነጋችንን እንዳንፈራ ሕግ ተርጓሚው ይፈራ!

    ክብርት ፕሬዝደንት፥ እንደሚያውቁት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ባለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በጭፍን ከመደገፍ እና ከመቃወም ወጥቶ በምክንያት መቃወም እና መደገፍ የፖለቲካ ባህል፣ አስተሳሰብ እንዲገነባ የራሱን ሚና ሲጫወት የቆየ ፓርቲ ነው። ይሄ ስልጡን የፖለቲካ ባህል እንደምንፈልገው ፍሬ ባያፈራም ቀላል የማይባል የፖለቲካ ባህል ለውጥ ጭላንጭል አይተናል ብለን እናስባለን። ይህን አዲስ ባህል የፈጠረ ፓርቲ ግን ለሱ የሚመጥነውን ያህል ክብር ሊሰጠው ቀርቶ በየዘመኑ የመጡ ገዥዎች አና ጽንፈኛ ፖለቲከኞች በሴራ አላላውስ ብለውታል።

    ኢዴፓ ከለውጡ በፊት ባሉት ሁለት ዓመታት እና ከለውጡ ማግስት ባሉ ሁለት ዓመታት የተቀነባበረ በሚመስል ደረጃ ፓርቲያችንን የማዳከም እና ከፖለቲካው መድረክ እንዲገለል የማድረግ ከፍተኛ ደባ እየተሠራበት ይገኛል። ይህን በፓርቲው ህልውና ላይ የተቃጣውን መሠረተ ሰፊ የማፍረስ እርምጃ በተለያዩ መድረኮች እያሸነፍን እዚህ ብንደርስም፥ አሁንም ድረስ በግፍ የተነጠቅነውን የፓርቲውን ቢሮዎች፣ ንብረቶች ገንዘቦች እና ሰነዶች ለማስመለስ በፍትህ አደባባይ እየታገልን ነው። አሁንም በቢሮክራሲ ውጣ ውረድ እየተንገላታን ነው፤ ባለፉት አራት ዓመታት በፓርቲያችን ህልውና ላይ እየደረሰ ያለውን ፈተና እየታገልን ባለንበት ሁኔታ ይባስ ብሎ የአርቲስት ሃጫሉን ሞት ተከትሎ ሌላ የፖለቲካ ጫና እየደረሰብን ይገኛል። ይኸውም የፓርቲያችን ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ያለጥፋታቸው የፖለቲካ ጥቃት ሰለባ እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋልል። አቶ ልደቱ በወንጀል ድርጊት ውስጥ መሳተፋቸው በተጨባጭ ማስረጃ እስከተረጋገጠባቸው ድረስ አይያዙ አንልም፤ ለሕግ የበላይነት ሲታገል የኖረ ፓርቲ በዚህ ረገድ ምንም ብዥታ የለበትም። ነገም ከነገ ወዲያም ማንም በፖለቲካ ፓርቲ አመራርነትና አባልነት ስም ከሕግ ማምለጥ አለበት ብለን አናምንም፤ ነገር ግን ፖሊስ እርቸውን አስሮ ማስረጃ ሲፈልግ ሲታይ፣ ማስረጃ ማቅረብ ተስኖት ፍርድ ቤት ልቀቅ ብሎ ሲወስን እምቢኝ ካለ የታሰረው ወንጀል ሠርቶ ሳይሆን ለምን የተለየ አሰብክ ተብሎ እንደሆነ ድርጊቱ ያሳብቃል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ልደቱ መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በማቅረባቸውና በመቃወማቸው ብቻ እንደታሰሩ በፍትህ ሂደቱ ላይ የታዩትን ህጸጾች ስለታዘብኩ ነው ለእርስዎ አቤት ማለቴ። አቶ ልደቱ የሃጫሉን ሞት ተከትሎ ሁከት በተቀሰቀሰበት ሰዓት የፌዴራል ፖሊስ ለህይወትህ ያሰጋሃል ብሎ አጅቦ ከቢሾፍቱ ወደ አዲስ አበባ አምጥቷቸዋል። ይሄ ሆኖ ሳለ በፖሊስ የተከሰሱበት እና የተጠረጠሩበት ወንጀል የቢሾፍቱ ከተማ ወጣቶችን አደራጅተሃል፣ በገንዘብ ረድተሃል እና አስተባብረሃል ቢሆንም ተጨባጭ ማስረጃ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ሊያቀርብ አልቻለም። በኋላም የተሰጠውን የምርመራ ግዜ በመጨረሱና አቃቢ ሕግም ተጨማሪ የምርመራ ግዜ ባለመጠየቁ ፍርድ ቤቱ በነፃ አሰናብቷቸዋል። ነገር ግን ይህንን የፍርድ ቤት ውሳኔ ሰምቶ ፖሊስ መልቀቅ ሲገባው፥ ከ17ቀናት በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ አስሮ ሲያሰቃያቸው ቆይቷል። እኛም በፍትህ ሂደቱ ተስፋ ቆርጠን፣ አቶ ልደቱም ጠበቆቻቸውን አሰናብተው ፌደራል ላይ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ልንመሠርት ስንዘጋጅ ደግሞ ሌላ ክስ አዳማ ላይ ተከፈተባቸው።

    ይሄ ክስ በመጀመሪያው የቢሾፍቱ ከተማ የክስ መዝገብ ላይ ሕገ-ወጥ ሽጉጥ ተገኝቶባቸዋል ተብሎ ማስረጃ ቀርቦበት ውድቅ የተደረገ የክስ ጭብጥ ነው። የሆነው ሆኖ በሕገ-ወጥ መሣሪያ በመያዝ በሚል ምሥራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢከሰሱም ፍርድ ቤቱ የአቃቢ ሕግንና የጠበቆቻችንን የሕግ ክርከር መርምሮ አቶ ልደቱን በ100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ብር ዋስትና ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ወሰነ። እኛም 100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ብር አስይዘን ማስፈቻ ትዕዛዝ ለፖሊስ ብንወስድም አሁንም ፖሊስ ትዕዛዙን አልፈፅምም አለ። እኛም ትዕዛዙን ለሰጠው ፍርድ ቤት አቤት ብለን መልስ ሊነገረን ለበነጋታው ቀጠሮ ይዘን መጣን። ነገር ግን ማታ የአቶ ልደቱ ዋስትና እንደታገደ በመገናኛ ብዙኃን ሰማን። በዚህ ሁኔታ አቶ ልደቱ ከልብ ህመም ጋር ተያይዞ የልብ ቀዶ ጥገና ባደረጉበት አሜሪካ ቀጠሮአቸው እንዲያልፍ ተደርጎ፥ ከዚህ በተጨማሪ ካለባቸው የአስም ህመም የተነሳ ለኮሮና ተጋላጭ መሆናቸው በሐኪሞችም በፍርድ ቤቶቹም ታምኖበት ጭምር ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ የተደረገው ጥረት በፖሊስ እምቢተኝነት ህይወታቸው አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጓል። በሂደቱ ሁሉ አቶ ልደቱ እያቀረቡት ያለው ቅሬታ ሁሉ ተቀባይነት እያጣ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ እየተሻረ የፖለቲካ ውሳኔ አሸናፊ እየሆነ ይገኛል። አሁንም እንደቀጠለ ነው። እና በፍትህ አደባባይ አቶ ልደቱ ደግመው ደጋግመው ነፃ ቢሆኑም ፖሊስ አለቅም ማለቱን ሳይ ነው የአቶ ልደቱ እስር ሕግ ጥሰው ሳይሆን በፖለቲካ እስር ነው ብዬ በእርግጠኝነት መናገሬ፤ እንጂማ ሁለቴ ያሸነፈ አይደለም አንድ ግዜም ያሸነፈ ቤቱ እስር ቤት አይሆንም ነበር። ይሄ የሚያሳየው የፍትህ ሥርዓቱ ላይ የበዛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መኖሩን ነው።

    ክብርት ፕሬዝደንት፥ የፍትህ ተቋሙ በእርስዎ መመራት ሲጀምር በፍትህ መጓደል ላለፉት 27 ዓመታት ፍዳውን ሲያይ የነበረው ዜጋ እፎይ ይላል ብዬ በግሌ ተስፋ አድርጌ ነበር፤ ሕግ ተርጓሚው ከሕግ አስፈፃሚው ተፅዕኖ ወጥቶ የሚገባውን ክብር እና የሚወስነውም ውሳኔ በአስፈጻሚው አካል ሳይሸራረፍ ተፈፃሚ ይሆናል ብዬም ነበር። ፍትህ እና ርትዕ በእርስዎ አመራር ይሰፍናል ብዬ በእርስዎ የቀደመ ልምድ ፍፁም ተማምኜ የነበረ ቢሆንም እየሆነ ያለው የተገላቢጦሽ ነው። ፍትህ ከቀደመው ጊዜ በባሰ ችግር ውስጥ መውደቁን እኔ በግሌ በዚች ሁለት ወር በተግባር ባየሁት ነገር አረጋግጫለሁ። እርስዎ የተሰጠዎትን ኃላፊነት ያለምንም ፍርሃት እና ይሉኝታ ለመወጣት ከሞከሩ የፍትህ ሥርዓቱ ወደ መስመር ውስጥ መግባቱ አይቀርም፤ ግን ክብርት ፕሬዝደንት ለተቋማዊ ለውጥና ከታሪክ ተጠያቂነት ለመዳንም የበኩልዎን ይወጡ።

    ክብርት ፕሬዝደንት፥ ዜጋ በፍትህ ሥርዓቱ ተስፋ ሲቆርጥ ለሥርዓት አልበኝነት መንገድ ይከፈታል፤ የሞራል ልዕልና ቦታ አጥቶ ፍትህ በየአደባባዩ ትረገጣለች፤ ዜጋ በራሱ መንገድ ፍትህን ይፈልጋል፤ ፍትህን በራሱ ህሊና ተመርቶ ለመስጠት ይገደዳል። ያኔ እንደ ሀገር ዜጋው ወጥቶ የመግባት፣ ሠርቶ ሀብት ንብረት የማፍራት መብቱ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ እርስዎ የሚመሩት ተቋም ክብርና ሞገሱን ካጣ የሀገር ክብር እና ሞገስ ጠፍቶ እንደ ሀገር የመኖር ህልውናችንም አደጋ ውስጥ ይወድቃል። የመንግሥት መኖር ምልክት የሆነው ሕግና ሥርዓት ጠፍቶ ባለፈው እንዳየነው በየአካባቢው የደቦ ፍርድ ይነግሳል። አቶ ልደቱስ በፖለቲካው ባላቸው ተደማጭነት እና ተሰሚነት ድምፅ የሚሆናቸው ብዙ ነው። በዚህ ሁኔታ ተራው ዜጋ ምን ያህል በፍትህ ሥርዓቱ ፍዳውን ሊያይ እንደሚችል ተገንዝበውታል? ለእርስዎ ተቋም ክብር የሚመጥን የፍትህ ሥርዓት አለ ብለው ያምናሉ? አይመስለኝም ፍትህ እና ርትዕ እንዲሰፍን፣ እንዳይጓደል የበለጠ ሥራ በመሥራት የዳኞችን ክብር ያስመልሱ። ዳኞች የሚፈርዱት ፍርድ በአስፈፃሚው አካል ሲደፈጠጥ ማየት ያሳፍራል፣ ያሸማቅቃል ነገን እንድፈራ ያደርጋል። ነጋችንን እንዳንፈራ ሕግ ተርጓሚው ይፈራ! ስለዚህ ክብርት ፕሬዝደንት፥ ጉዳዩ የአቶ ልደቱን ጉዳይ የፍትህ መጓደል ብቻ አድርገው አይቁጠሩት። በህይወት የመኖር እና ያለመኖር የመብት ጥያቄ ነው እያቀረበ ያለው። በፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይሆን በአስፈፃሚው ጡንቻ በህይወቱ ላይ አንድ ነገር ቢደርስስ ማን ነው ተጠያቂው? በተለይ የሃጫሉን ሞት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የታዘብኩት ዜጎች ወደ ፍትህ ሳይቀርቡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እየተጉላሉ መሆኑን ነው። በየማጎሪያው እየተሰቃዩ ነው፤ የፍትህ ያለ እያሉ ነው። አሁንም እደግመዋለሁ ወንጀል የፈፀመ አይታሰር አልልም፤ ግን ከሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ ውጭ ዜጎች መጉላላት የለባቸውም፤ የተፋጠነ ፍትህ ይሰጣቸው፤ ሰብዓዊ መብታቸው ይጠበቅላቸው። ይህን በሁለት ወር ውስጥ የታዘብኩት ነው። ይህ የሚያሳየው የፍትህ መጓደል በሌሎች ክልሎች ላይም ቀላል በማይባል ደረጃ ችግሩ መኖሩን ነው። በቢሾፍቱና አዳማ ዋስትና ተፈቅዶላቸው ከወር በላይ ፖሊስ አለቅም በማለቱ በእስር የሚማቅቁ ብዙ ዜጎች እንዳሉ ያገኘኋቸው የሕግ ባለሙያዎች አጫውተውኛል። ፍትህ ተጠምተው በየእስር ቤቱ የሚሰቃዩ ብዙዎች ናቸው። ለፍትህ መከበር ሁሉም ሊጮህ ይገባል። ፍትህ በጉልበተኞች ጫማ ሲደፈጠጥ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሳልና!

    ክብርት ፕሬዝደንት መዓዛ፥ ይህችን ግልፅ አቤቱታዬን ሰምተው በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ነፍስ ይዘሩበታል፤ በየማጎሪያ ካምፑ ያሉ የብዙ ዜጎችን እንባ ያብሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አመሰግናለሁ።

    ከከበረ ሰላምታ ጋር!
    አዳነ ታደሰ
    የኢዴፓ ፕሬዝደንት

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    የጠቅላይ ፍርድ ቤት ክብርት ፕሬዝደንት መዓዛ አሸናፊ

    Anonymous
    Inactive

    በወቅታዊ ጉዳዮች ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መስከረም 9 እና 10 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ሕዝባችንን ባጋጠሙት ወቅታዊ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ላይ ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል።

    1] በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕዝባችን ላይ የተፈፀመውን የዘር ጥቃት በተመለከተ፦

    አብን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ከጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ማንነትን መሠረት አድርገው የተፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ተጨባጭ መረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል። በዚህም ከ160 በላይ ወገኖቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተጨፈጨፉ ተገንዝቧል።

    የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአማራው ሕዝብ ጥንተ ርስቱን ተነጥቆ፣ ሰብዓዊና ዜግነታዊ መብቱ ተገፎ ለሦስት አስርት ዓመታት ለዝርፊያ፣ ለመፈናቀል እና ለተደጋጋሚ የዘር ፍጅት የተጋለጠበት ነው። በተለይም “ለውጥ” እየተባለ በሚጠራው ባለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በክልሉ ውስጥ ባለው የአማራ ሕዝብ ላይ የሚደረገው የዘር ማጽዳትና ሰብዓዊ ጥቃት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሶ ቀጥሏል።

    ንቅናቄያችን ልክ ከሰኔ 22 እስከ 24 ቀን  2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአማራው ሕዝብ ላይ  የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ እንደገለገፀው ሁሉ በቤንሻንጉል ክልል የተፈፀመው ጥቃት ተራ የማኅበረሰቦች ግጭት ወይም የሽፍቶች ድርጊት ውጤት ሳይሆን በአማራ-ጠል ትርክት ላይ የተመሠረተ፣ ስልታዊ የሆነ እና በመንግሥታዊ መዋቅር ጭምር የተደገፈ የሽብርና የዘር ማጥፋት ድርጊት መሆኑን ያምናል።

    በዚህ አሰቃቂ ጥቃት የትህነግ ተቀጥላ የሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የቤንሻንጉል ክልል መንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ የአማራ ሕዝብንና የሀገሪቱን ሰላም ለማሳጣት የሚታትሩ ባዕዳንና ውስጣዊ ኃይሎች ያሰማሯቸው የሽብር ቡድኖች እጃቸው እንዳለበት አብን ያምናል።

    የጥቃቱ ፈፃሚዎች ለተከታታይ ቀናት ሕዝባችንን (አማራ/አገው) በማንነታቸው እየመረጡ በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በኃይል አሰባስበው ለጅምላ ጭፍጨፋ ሲያዘጋጁ የክልሉ መንግሥት መረጃ እና ጥሪ እየቀረበለት ባለመድረሱ፤ የፌዴራል መንግሥቱም ባለው የደኅንነት መረጃ ተመርኩዞ ጥቃቱን ለመከላከል ፈጥኖ እርምጃ ባለመውሰዱ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አብን በጥብቅ ያምናል።

    አብን በሕዝባችን ላይ ከእንግዲህ ማናቸውንም ዓይነት ማንነቱን መሠረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሊታገስ የማይችልበት ደረጃ መድረሱን እየገለፀ፤ ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተበጀለት ጉዳዩ  ከአማራው አልፎ ታላቅ ብሔራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል በመገንዘብ፦

    (ሀ) መሣሪያ የታጠቁ ገዳዮችን በመደገፍና እንዳላዩ በማለፍ ለጥቃቱ መዋቅራዊ ከለላ የሰጡና በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር የዘር ማጥፋቱ ተባባሪ የሆኑ የክልሉ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ፤

    (ለ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚኖረው ሕዝባችን አስተማማኝ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጥ፣ በየአካባቢያቸው የፖሊስና የደኅንነት መዋቅሮች ውስጥ የመሳተፍ መብታቸው እንዲከበር፣ በማኅበረሰብም ደረጃ ደህንነታቸውን የሚያስጠብቁበት አስቸኳይ መፍትኄ እንዲፈለግ፤

    (ሐ) የፌደራል መንግሥቱና ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በአማራው ሕዝብ ላይ በሚፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ላይ የያዘውን ዳተኝነት እንዲያቆምና ችግሩን ለመከላከልና ከመሠረቱ ለመቅረፍ ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስድ፤

    (መ) የአማራ ብልጽግና ፓርቲና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ላይ በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ ሁለት እጅግ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ሲፈፀሙ ወንጀሉን በስሙ ከመጥራት ጀምሮ ለችግሩ ዘላቂ መፍትኄ በመፈለግ ረገድ ያሳየው አቅም እና ፍላጎት ከደረጃ በታች መሆኑና ከእንግዲህም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ከዚህ አካል ሊመጣ እንደማይችል ሕዝባችን በግልፅ እንዲገነዘበው፤

    (ሠ) ሕዝባችን በተከታታይ ለዘር ማጥፋት እና ዘር ማጽዳት ጥቃቶች የተጋለጠበት የቤንሻንጉል ክልል አማራው ፍጹም ሥነ-ሕዝባዊ አብላጫ እያለው ፖለቲካዊ ውክልና በማጣቱ የተነሳ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ የክልሉ መዋቅር የነዋሪዎቹን መብቶች በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲከለስ ድርጅታችን አብን ያሳስባል።

    2] በአማራ ክልል የደረሰውን በጎርፍ የመጥለቅለቅ አደጋ በተመለከተ፦

    በአማራ ክልል በዘንድሮ ክረምት ዝናብ ምክንያት በተፈጠሩ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋዎች በአጠቃላይ በ6 ዞኖች በሚገኙ 36 ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 164 ቀበሌዎች በተለያዩ ደረጃዎች የሚገለፁ ጉዳቶች እንዳደረሱ ይታወቃል።

    በተለይ ደግሞ በማዕከላዊ ጎንደር በምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ፣ እንዲሁም በደቡብ ጎንደር በሊቦከምከም፣ ደራና ፎገራ ወረዳዎች በከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ በመጠቃታቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ይገኛሉ።

    አብን እነዚህ በጎርፍና በመጥለቅለቅ የተፈናቀሉ ወገኖች በአስቸኳይ የእለት እርዳታ እንዲያገኙ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ እየገለፀ፤ በመላው ዓለም የሚገኙ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣ መላው የአማራ ሕዝብና ኢትዮጵያውያን ወገኖች ለድጋፍ እጃቸውን እንዲዘረጉ ይጠይቃል።

    በጎርፉ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሊነሱ በሚችሉ የወባ እና ሌሎች ውሃ-ወለድ በሽታዎች ሕዝቡ እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ እንዲደረግ ይጠይቃል።

    ተጎጂዎች ሰብሎቻቸው እና ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው በመሆኑ አፋጣኝ ድጋፍ እና የመልሶ ማቋቋም ተግባራት እንዲከናወኑ፣ ለመጪው ዘመንም የሚያስፈልጋቸውን ሁለገብ እርዳታ የማዘጋጀት ሥራ እንዲሁም ለዘለቄታው በየዓመቱ የክረምት ወቅት ሊከሰቱ ከሚችሉ ተመሳሳይ አደጋዎች ለመጠበቅ ዘላቂ መፍትኄ እንዲፈለግ ይጠይቃል።

    በመጨረሻም በአማራ ሕዝብ ታላቅ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ አቅጣጫውን በመሳቱ በሕዝባችን ላይ ሥርዓት እና መዋቅር ሠራሽ ጥቃቶቹ ስጋት ደቅነውበት እንደቀጠሉ አብን ይገነዘባል።

    እጅግ ራስ-ወዳድ በሆነው ሰፊ የፖለቲካ ውቅር ውስጥ ጨካኞች እና ያልተገሩ ስብስቦች በአማራው ላይ ጥቃታቸውን ባስቀጠሉበት አግባብ፣ ለኩርፊያቸው እና ለደም ጥማታቸው አማራ ቋሚ ግብር ወይም ማስያዥያ የሚሆንበት የፖለቲካ ድባብ በትግላችን መገፈፍ ይኖርበታል።

    በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ያሉ ተዋንያንንና በቸልተኝነትና በሴራ ተባባሪ የሆኑ አካላትን ጭምር ለማጋለጥ እና በኃላፊነት እንዲጠየቁ ለማድረግ አብን እንደሚሠራ በአፅንዖት ለማስገንዘብ ይወዳል።

    በመጨረሻም አብን በቤንሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች በአሰቃቂ ሁኔታ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን ለመግለፅ ለመላው የአማራ ሕዝብና ለሕዝባችን ወዳጆች ከነገ ሰኞ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም  ጀምሮ እስከ ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ቀናት በምናደርገው ጥቁር የመልበስ እና ተያያዥ የሐዘን መግለጫ ሥርዓቶች እንዲካፈሉ አብን የአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል።

    አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) /NaMA/
    መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም
    አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    Anonymous
    Inactive

    በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል የተከሰተውን ግድያ እና መፈናቀል አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ

    አሶሳ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን /ኢሰመኮ/ (ኮሚሽኑ) በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የፀጥታ መደፍረሶችን ተከትሎ ያጋጠሙ ክስተቶች እጅግ አሳስበውታል።

    ኮሚሽኑ ከክልሉ ከመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ አጳር ቀበሌ እንዲሁም ከወንበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ እጅግ አሳሳቢ መረጃዎች እየደረሱት ነው። ኮሚሽኑ በጳጉሜ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲሁም ከጳጉሜ 2 አስከ መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም. መካከል ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግሥት ለማረጋጥ ችሏል።

    በቦታው ላይ ከሚገኝ አንድ መንግሥታዊ ምንጭ መረዳት እንደተቻለው፥ ቢያንስ በሁለት ዙር በደረሱ ጥቃቶች ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ ግድያዎች መፈፀማቸውን፤ እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን ኮሚሽኑ ማረጋገጥ ችሏል።

    የክልሉ መንግሥት እንደጠቆመው ከተፈናቃዮቹ መካከል 300 ያህል የሚሆኑት ወደ ቀያቸው የተመለሱ ሲሆን፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር አካባቢውን ለማረጋጋት እየሠሩ ነው።

    ስለሆነም ኮሚሽኑ፡-

    • በክልሉ ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ የደረሱትን ጥቃቶች፣ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ሙሉ በሙሉ ያወግዛል፤
    • በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በክልል የጸጥታ ኃይሎች ሰላምን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት ያበረታታል፤
    • በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥትና እንዲሁም ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው የቃል ኪዳን ሰነዶች ማለትም፡ በአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ በዓለምአቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች የተደነገጉትን በህይወት የመኖር መብቶች እንዲከበሩ ይጠይቃል፤
    • በክልሉ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ማጋጠማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፥ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ገለልተኛ፣ ፈጣን እና ውጤታማ ምርመራዎችን በማካሄድ ግድያው በተከሰተባቸው ሁኔታዎች ላይ የጥፋተኞችን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጡ ያሳስባል፤
    • የሚመለከታቸው የክልሉ መንግሥት አካላት ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ወደ ቀደመ ህይወታቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ጥሪ ያቀርባል፤
    • ኮሚሽኑ በተለይም መሰረታዊ የሆነው በህይወት የመኖር መብት ይረጋገጥ ዘንድ የሚመለከታቸው የክልሉ የመንግሥት አካላት እንዲሠሩ ያሳስባል።

    በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች እና ባለድርሻ አካላት ገንቢ ውይይት እንዲያደርጉ እና ከማንኛውም ዓይነት የሁከት ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጥሪውን ያቀርባል፤ እንዲሁም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት እና ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውን ሌሎች አግባብነት ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ የተቀመጡ መብቶችን እና ግዴታዎችን እንዲያከብሩ ኮሚሽኑ እየጠየቀ፥ በቀጣይም ጉዳዩን በንቃት እንደሚከታተለው ይገልፃል።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን /ኢሰመኮ/

    የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን

    Semonegna
    Keymaster

    የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ አደረገ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ 184 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳያቸው በምርመራ እንዲጣራ እና ክስ እንዲመሠረት ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ስም ዝርዝራቸውን ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መላኩን አስታወቀ።

    ኮሚሽኑ ሀብትና ንብረት የማስመዝገብ ግዴታ ያለባቸውን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ በተለያየ ጊዜ በቴሌቪዥን፣ በሬድዮ እና በደብዳቤ ጥሪ ባስተላለፈው መሠረት አብዛኞቹ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ሀብትና ንብረታቸውን አስመዝግበዋል።

    ይሁን እንጂ በፌደራልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ 184 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ኮሚሽኑ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሀብትና ንብረታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም። ሀብትን ከማስመዝገብ ግዴታ ጋር ተያይዞ ፈቃደኛ ሆኖ ያልተገኙ አካላት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠባቂነት ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል በወጣው የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተደንግጓል።

    በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባ ሥራን በማካሄድ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነትና የግል ጥቅም ሳይቀላቀሉ በየራሳቸው መንገድ የሚመሩበትን ግልጽ ሥርዓት እንዲኖር እያደረገ ባለው ሂደት ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ እንዲሆኑ እያደረገ ሲሆን፥ በቀጣይም ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ በማይሆኑ የመንግሥት ተሿሚዎችና ሠራተኞች ላይ በሕጉ መሠረት ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን ያሳውቃል።

    ከባለስልጣናት ሀብት ምዝገባ ጋር በተያያዘ፥ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔና ምክትል አፈ-ጉባዔን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት ነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም የሀብት ምዝገባ እድሳት አካሂደዋል።

    በሀብት ምዝገባ እድሳቱ ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ እንደተናገሩት፥ የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል እየሠራቸው ካሉት በርካታ ሥራዎች መካከል የሀብት ምዝገባ ሥራ አንዱ ነው። የሀብት ምዝገባ ሥራ ሙስናን ለመከላከል ዓይነተኛ መሣሪያ እንደመሆኑ መጠን ሊደገፍና ሊጠናከር ይገባል ሲሉ አፈ-ጉባዔው አክለው ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁሉም አካላት ሀብታቸውን በማስመዝገብ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከከላከል የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባቸው አፈ-ጉባዔው አሳስበዋል።

    አፈ-ጉባዔዎቹን ጨምሮ የሀብት ምዝገባ እድሳት ያካሄዱ የምክር ቤቱ አባላት ሀብታቸውን ያሳደሱበትን ሰነዶች ለፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር አቶ ፀጋ አራጌ አስረክበዋል።

    ምንጭ፦ የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን

    Anonymous
    Inactive

    ኢሰመኮ (ጋዜጣዊ መግለጫ) ― ኦሮሚያ፡ የሞት እና አካል ጉዳት አደጋ በተቃውሞ ሰልፎች 

    አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ለተቃውሞ በተጠሩ ሰልፎች ምክንያት የሚከሰተው የሰዎች ሕይወት መጥፋት በእጅጉ እንደሚያሳስበው እየገለጸ፥ የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ጥሪውን ያቀርባል።

    በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች በተለይም በአሳሳ፣ አሰቦት፣ አወዳይ፣ ባሌ ሮቤ፣ ጭሮ፣ ደንገጎ፣ ድሬ ጠያራ፣ ዶዶላ፣ ገለምሶ፣ ጊኒር፣ ሀሮማያ፣ ሂርና እና ሻሸመኔ የሞት ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ከተለያዩ ምንጮች መረጃ ደርሶታል፡፡ የሞት ጉዳቶቹ የደረሱት የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ በተጠሩ የተቃውሞ ሰልፎች እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

    “የመንግሥት አካላት የዜጎችን በሰላማዊ መልኩ ተቃውሞ የማሰማት መብት ማረጋገጥ እንዳለባቸው እና ሕግ የማስከበር ሥራ ተመጣጣኝነት እንዲጠብቅ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው”የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ እና ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ ገልፀዋል።

    የኦሮሚያ ክልል በዚህ ዓመት የተከሰቱ አሳዛኝ ግድያዎች ከፈጠሩት ሰቆቃ አሁንም ፈጽሞ አላገገመም። እነዚህ ከፍተኛ የመብት ጥሰት አዝማሚያዎች እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው አይገባም” በማለት አክለው ገልጸዋል።

    እስካሁን በአንዳንድ ሚዲያዎች የወጡ ሪፖርቶች እና በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ መረጃዎች የሞቱ ሰዎችን ቁጥር በሚመለከት የተለያየ አሃዝ አስቀምጠዋል። ኢሰመኮ የደረሰውን ሞትና ጉዳት መጠን ለማረጋገጥ ከየአካባቢው ነዋሪዎች፣ ምስክሮች፣ ሆስፒታሎች እና የአስተዳደር አካላት መረጃ በማሰባሰብ ላይ ይገኛል።

    ኢሰመኮ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ጉዳዩን ለማጣራት በአፋጣኝ ምርመራ እንዲጀምሩ ጥሪውን ያቀርባል።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች  ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
    ነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም.

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች  ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች  ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገ መንግሥት (ሰኔ 1986 ዓ.ም.) አዋጅ ቁጥር 210/1992 ኢትዮጵያ ውስጥ ለሁሉም ዜጎች ሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዲሠራ ሰኔ 27 ቀን 1992 .. የተመሠረተ ተቋም ነው።

    ተመሳሳይ ዜናዎች

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች  ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

    Anonymous
    Inactive

    የፖሊስ የዘፈቀደ እስር በአስቸኳይ ሊቆም እና የታሰሩትም ሊለቀቁ ይገባል
    Police Should Immediately Stop Arbitrary Arrests and Release those Detained

    አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን) – [በትላንትናው ዕለት (ግንቦት 5 ቀን 2012 ዓ.ም.)] በአዲስ አበባ ከተማ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የተገኙ ሰዎች በፖሊስ እየታሰሩ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ በሚዲያዎች የወጡ ዘገባዎችንና ለኮሚሽኑ የቀረቡ አቤቱታዎችን ተከትሎ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሚከተለውን ብለዋል።

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል አስፈላጊ የጤና መመርያ ሲሆን ሕብረተሰቡም ሊከተለው የሚገባ ነው። በእርግጥም የአስቸኳይ ጊዜ ደንቡ ማንኛውም ሰው እንደ ገበያ ቦታዎች፥ ሱቆች ፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ባሉ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች እና በሌሎች ሕዝብ በሚበዛባቸውና የአካል መራራቅን መጠበቅ በማይቻልባቸው አካባቢዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል። ከዚህ ውጪ ግን በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የተገኙ ሰዎች ላይ ሁሉ የሚደረግ የዘፈቀደ እስር ከሕግ ውጭ ከመሆኑም በላይ ለነገሩ ሁኔታ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ እና የታለመለትን አላማ የሚቃረን በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፤ በዚህ ሁኔታ የታሰሩ ሰዎችም በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል።

    [የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በመጋቢት ወር 20212 ዓ.ም. የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ለአምስት ወራት ተግባራዊ እየሆነ እንደሚቆይ ተነግሯል።]

    ADDIS ABABA (Ethiopian Human Rights Commission) – Responding to media reports and complaints of arrests by police in the city of Addis Ababa on 13th May 2020 for not wearing face masks, Chief Commissioner of the Ethiopian Human Rights Commission (EHRC) Dr. Daniel Bekele said:

    Covering nose and mouth are recommended health measures to prevent the spread of COVID-19 and the public needs to follow these critical health directives. Indeed, the Emergency Regulations impose an obligation to wear face covering in public service areas such as markets, shops, transport services or other public spaces with large number of people where social distancing is not possible. Otherwise, arbitrary arrest of people on the streets is outside the regulation, disproportionate and counter-productive measure which should stop immediately and all those detained should be released immediately.

    [In the first week of April 2020, Ethiopia has declared a state of emergency in the country to help curb the spread of the coronavirus pandemic. The state of emergency is reported to stay in action for five months from its declaration.]

    Semonegna.com

    የፖሊስ የዘፈቀደ እስር በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል

    Anonymous
    Inactive

    የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈፀሚያ ደንብ ይፋ ሆነ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል። በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው ረቂቅ አዋጅ ሚያዝያ 2 ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወቃል። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዋጁን ማስፈፀሚያ ደንብ አጠቃላይ ይዘት በሚመለከት ሚያዝያ 3 ቀን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

    በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 94 ንዑስ ቁጥር 4 መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብ ማውጣት እንዳለበት ይደነግጋል። በዚህም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን ማስፈፀሚያ ደንብ አጠቃላይ ዝርዝር በሚመለከት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል። ማስፈፀሚያ ደንቡ አጠቃላይ አራት ዋና ዋና ከፍሎች ያሉት ሲሆን ይሄውም ክልከላን የሚያስቀምጥ፣ ግደታዎችን የሚጥል፣ የአስፈፃሚ አካላትን ክንውን እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

    ክልከላን በሚመለከት ማንኛውም ሃይማኖታዊ ይሁን ፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ እድር፣ ደቦ፣ እቁብና ሌሎችም ከአራት (4) ሰው በላይ ስብሰባዎች ክልክል ናቸው። አራት ሰዎችም ቢሆኑ ሁለት የአዋቂ ሰው እርምጃ የጠበቀ መሆን እንዳለበት አቃቤ ህአቃቤ ሕጓ አብራርተዋል። ቀብርና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ሲኖሩ ግን እየታዩ ሊፈቀዱ የሚችሉበት አሠራር መኖሩን ጠቁመዋል። ታራሚዎች ከጠበቆቻቸው ጋር አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲገናኙ የሚፈቀድ ቢሆንም፥ ጥየቃ ለሚሄዱ ሰዎች የማይፈቀድ መሆኑ ተገልጿል።

    በፖሊስ የተያዙ እስረኞችንም ስንቅ ከማቀበል በስተቀር መገናኘት የተከለከለ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል። በድንበር አካባቢ ከካርጎ፣ የደረቅና ፈሳሽ ጭነት አገልግሎቶች በስተቀር ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዝግ ተደርገዋል። የቤት ተከራዮች በራሳቸው ፍላጎት ካልወጡ በስተቀር ማስወጣትና ኪራይም አስገድዶ መቀበል/ ማስከፈል መጨመር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተከልክሏል። ሠራተኞችን መቀነስና የሥራ ቅጥር ውል ማቋረጥም መከልከሉን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል።

    በዚህ ደንብ መሠረት ተማሪዎችና መምህራን በኦንላይን (online) ካልሆነ በአካል እንዲገናኙ አይፈቀድም። ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ የሕፃናትም ይሁን የሌሎች መጫወቻ ስፍራዎች እንዲሁም የእጅ መጨባበጥ ሰላምታ የተከለከለ ነው።

    በትራንስፖርት ዘርፍም አገር አቋራጭ ካለው ወንበር ከ50 በመቶ በላይ ተሳፋሪ መጫን የተከለከለ መሆኑን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።

    ከኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ዜና ሳንወጣ፥ እስከዛሬ ሚያዝያ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ስዎች ቁጥር ሰባ አንድ (71) መድረሱን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም አስታውቋል። ከእነዚህ ተጠቂዎች መካከል ሦስቱ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ሀምሳ ስድስት (56) ታማሚዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ። ሁለት የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን፣ አስር (10) ሰዎች ደግሞ ከሕክምና በኋላ ከቫይረሱ ነፃ ሆነው አገግመዋል።

    እስከዛሬ (ሚያዝያ 4 ቀን) ከሰዓት በኋላ ድረስ በዓለም ላይ በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ1.79 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከ109,200 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። በአጠቃላይ ቁጥራቸው 406,100 አካባቢ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ከኮቪድ-19 በሽታ ማገገማቸው ታውቋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ኮቪድ-19

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ጋዜጣዊ መግለጫ

    አዲስ አበባ፥ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም.
    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሸነር የእስረኞች ጉብኝት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን ስር በአደራ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ተጠርጣሪ ታሳሪዎችን ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጐብኝተዋል።

    ዋና ኮሚሸነሩ በዚህ ጉብኝታቸው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተማ ከተከሰተው የፖለቲካ ግድያ ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች በቁጥጥር ስር ከሚገኙ እስረኞች ውስጥ፥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር እና አባሎች ውስጥ እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ በለጠ ካሳን፤ ከባልደራስ ባለአደራ ምክር ቤት ንቅናቄ አባሎች ውስጥ እነ አቶ ኤልያስ ገብሩ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኰል እና አቶ መርከብ ኃይሌን፤ ከኢትዮጵስ ጋዜጣ ባልደረቦች አቶ ምሥጋና ጌታቸው እና አቶ አዳሙ ሁጁራን (አቶ አዳሙ በተጨማሪም የባልደራስ ባለአደራ ም/ቤት ንቅናቄም አባል ናቸው)፤ እንዲሁም «የተጠለፈው ትግል›› ከሚለው መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘም በእስር የሚገኙትን አቶ ፍሬው በቀለ፣ አቶ ሳሙኤል በቀለ፣ አቶ መለሰ ማሩ፣ አቶ ጋዲሳ ዳንኤል እና አቶ አማረ ተፈራን፤ በተጨማሪም የሟች ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋንና ሌሎች በርካታ ታሳሪዎችን በማነጋገር ጉዳያቸው ያለበትን ደረጃ እና የእስር ሆኔታቸውንም ተመልክተዋል።

    ዋና ኮሚሸነሩ ‹‹የሴቶች እስር ክፍሉ በአንፃራዊነት የተሻለ እና የጽዳት ደረጃው የተጠበቀ ሲሆን በሌላ በኩል ከ300 በላይ ታሳሪዎችን የያዘው የወንዶች እስር ቦታ እጅግ የተጨናነቀ፣ በውሃ መቋራረጥ እና በታሳሪው ብዛትም የጽዳት ደረጃው ዝቅተኛ ነው» ያሉ ሲሆን ታሳሪዎቹ በየእለቱ ከቤተሰብ፣ ወዳጅ እና የሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እንደሚችሉም ለማወቅ ችለዋል።

    በሌላ በኩል “ታሳሪዎቹ ከ 3–4 ወር ያህል የፖሊስ ምርመራን ለማጠናቀቅ በሚል በእስር የቆዩና በአሁኑ ወቅት በሕግ የሚፈቀደው የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በአብዛኛው የተጠናቀቀ እና ቀሪውም በመጠናቀቅ ላይ ያለ በመሆኑ ከዚህ በላይ ታሳሪዎቹ በእስር ሊቆዩ ስለማይገባ እንደየአግባቡ በዋስ ወይም ያለዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ተዓማኒ የሆነ ክስ በመደበኛው የወንጀል ሕግ መሰርት ሊቀርብ ይገባል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

    “ከአንድ መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘ የመጽሐፉ ፀሐፊ ነው ተብሎ ከተጠረጠረ ግለሰብ አንስቶ፣ የማታሚያ ቤቱ ባለቤት፣ የመጽሐፉ የፊት ገጽ ዲዛይን የሰራ ግለሰብ፣ የመጽሐፉ አከፋፋይ እና የመጽሐፉ የጐዳና ላይ ቸርቻሪ ሻጭ ሳይቀር እንዲሆም ሌሎች ታሳሪዎች ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጌዜ ፎቶ አንስተሃል በሚል የተያዘ ጋዜጠኛ ጭምር ለዚህን ያህል ጊዜ በእስር መቆየታቸው አሳሳቢ ሁኔታ በመሆኑ አፋጣኝ እልባት እና የዋስትና መብት መከበር ያስፈልገዋል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

    ክቡር ዋና ኮሚሽነሩ በተጨማሪም ለጉዳዮቹ ሁሉ ሕጋዊ እልባት ለማግኘት ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር በመነጋገር ኮሚሽኑ ክትትሉን እየቀጠለ መሆኑን አሳውቀዋል።

    ጉብኝቱ በዓለም ዓቀፍ የእስር ቤቶች ጉብኝት ደረጃ መሠረት ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የተደረገ ሲሆን የፖሊስ ኮሚሸኑ አመራሮች እና የጥበቃ ክፍል ኃላፊዎች ለዋና ኮሚሸነሩ ጉብኝቱ በማመቻቸት ኃላፊነታቸውን በመወጣታቸው ዋና ኮሚሸነሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    ምንጭ፦ የኮሚሽኑ ፌስቡክ ገጽ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን

    Anonymous
    Inactive

    ባህር ዳር (አብመድ)፦ ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ሹመታቸው የጸደቀላቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለምክር ቤት አባላትና ለሕዝቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    እንደ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንትነት ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ንግግር ያደረጉት አቶ ተመስገን በመልዕክታቸው የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ለግጭት ምክንያት ሳይሆኑ በሕግ እንዲመለሱ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

    በተጨማሪም የኢኮኖሚ ዕድገቱም ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ለኢንቨስትመንት ዕድገትም አትኩሮት እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል።

    አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስከትለውም “የሕግ የበላይነትን ማስፈንም ለነገ የምንለው ጉዳይ አይሆንም” ብለዋል ለአማራ ክልል ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት።

    ለመሆኑ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ ማን ናቸው?

    አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ብቸና ወረዳ ወይራ ቀበሌ ነው የተወለዱት። ከታችኛው የመንግሥት መዋቅር እስከ ፌዴራል ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎችም አገልግለዋል።

    በትምህርት ደረጃ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ ቀያቸው በጎተራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፤ የመለስተኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በብቸና በሚገኘው የበላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቁት። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከማይክሮሊንክ ኮሌጅ በሶፍትዌር ዘርፍ እና የሁለተኛ ዲግሪቸያውን ደግሞ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ (University of Greenwich) በለውጥ አመራርና አስተዳደር ተከታትለዋል።

    ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ በ አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና በፌደራል መንግስት ደረጃ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

    በአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የፀጥታ እና ቴክኖሎጂ አማካሪ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ሠርተዋል።

    ፌደራል መንግስት ደረጃ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (Information Network Security Agency) ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮ-ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በመሆንም አገልግለዋል።

    አቶ ተመስገን የሀገር መከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ፣ የኤሌክትሮኒክስ እና የቴክኒካል መረጃ መምሪያ ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል። በመከላከያ ሠራዊት ውስጥም እስከ ሻለቃነት ማዕረግ ደርሰዋል።

    የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ መሥራች ከመሆን ባለፈ በዚሁ መሥሪያ ቤት ከመምሪያ ኃላፊነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነትም አገልግለዋል። እስከ ዛሬ ድረስ ደግሞ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

    ምንጭ፦ የአማራ መገናኛ ብዙሀን ድርጅት (አብመድ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አቶ ተመስገን ጥሩነህ


    Semonegna
    Keymaster

    የገቢዎች ሚኒስቴር የተጠናከረ የጉምሩክ ስርዓት እና የተጠናከረ ኬላ ፍተሻ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚያዙ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችና የተለያዩ አገራት ገንዘቦችም (የገንዘብ ኖቶችም) ጨምረዋል

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ለሕገ-ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ዝውውር ስጋት ናቸው የተባሉ ቦታዎችን በመለየት ተጨማሪ 36 አዳዲስ የጉምሩክ ኬላዎች መቋቋማቸውን የኢፌዴሪ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

    አዳዲስ ኬላዎችን በመክፈት እንዲሁም ቦታቸው ትክክል ያልነበሩ ነባር ኬላዎችን ወደ ትክክለኛ ቦታ በመቀየር ሕገ-ወጥ የገንዘብና የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ይርጋ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ተናግረዋል።

    ችግሩን ለመከላከል በተደረው ጥናት በኬላዎች ላይ 1 ሺህ 400 የፖሊስ ኃይል እንደሚያስፈልግ በተጨማሪ ተገልጿል።

    ጥናቱን ተከትሎ ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ፣ ስምሪቱ በጉምሩክ ኮሚሽን የሆነ ጥሩ ሥነ ምግባር የተላበሰ፣ ለቦታው የሚመጥን የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ፖሊስ እንዲቋቋምና ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ዳይሬክተሩ አቶ አዲሱ ይርጋ ገልጸዋል።

    የተጠናከረ የጉምሩክ ስርዓት እና የተጠናከረ ኬላ ፍተሻ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚያዙ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችና ገንዘቦችም ጨምረዋል ነው የተባለው።

    የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጀላል አብዲ በበኩላቸው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ የራሳቸውን ገንዘብ ለማግኘት በሚንቀሳቀሱ ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ከተለያዩ አገራት (በተለይም ከጎረቤት አገራት) ወደ አገር ውስጥ ይገባል ብለዋል።

    የጦር መሣሪያዎቹን መዳረሻ ለማወቅ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም ከሁኔታ ግምገማ በመነሳት በአገር ውስጥ ጸጥታና የደህንነት ስጋት ያለ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ራሱን እና ንብረቱን ለመጠበቅ የጦር መሣሪያ ፍላጎት እንደ አንድ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የተለያየ ዓላማና ግብ ያላቸው የታጠቁ ቡድኖችም የጦር መሣሪያ መዳረሻ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል ዳይሬክተሩ።

    የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑ ይታዋሳል።

    ምንጭ፦ ኢቢሲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የገቢዎች ሚኒስቴር


Viewing 15 results - 1 through 15 (of 26 total)