ማኅበረ ቅዱሳን ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ደብዳቤ ጻፈ

Home Forums Semonegna Stories ማኅበረ ቅዱሳን ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ደብዳቤ ጻፈ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #15391
    Anonymous
    Inactive

    ኦርቶዶክሳዊ እንደ ወንጀለኛ የሚቆጠርበት ክልል
    (ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት)

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያም በኦርቶዶክስ ታሪክ ውስጥ ያላቸው ውሕደት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ እንደማለት ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ እና ቅርስ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኗ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ ሀገር መሆኗን እኛ ብቻ ሳንሆን ምዕራባውያን ጸሐፊዎችም የመሰከሩት እውነታ ነው። ኢትዮጵያ እና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፍጹም አንድነት ሲገለጡ ኖረዋል።

    ካለፉት 40 ዓመታት በኋላ ግን ለዘመናት የኖረው እውነት ተገፍቶና ተሽሮ ቤተ ክርስቲያኗን የማይወክል የሐሰት ትርክት ሲነገር ኖሯል። ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗን በጠላትነት በመፈረጅ “ቀና እንዳትል አከርካሪዋን ሰብረነዋል” ብለው በአደባባይ እስከ መናገር ደረሱ። አብያተ ክርስቲያናትን ለመቃጠል፣ ክርስቲያኖችን ለሞት፣ ለስደት፣ ለመፈናቀል እንዲሁም ለንብረት ውድመት ተዳረጉ። በሁለተኛው እና በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ያለፉበትን ሰማዕትነት እና ትላንት በሌላው ዓለም ስንሰማውና በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ ስናየው የነበረው አሰቃቂ ግድያ ኦርቶዶክስ በመሆናቸው ብቻ በሀገራችን ተፈጽሞ የሞትን ጽዋ ተጎነጩ ።

    በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያት ስበከት ወደ ዓለም ሁሉ መድረሷ እና በሰማዕታት ደም መጽናቷ ይታወቃል። ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ማታ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ምክንያት በማድረግ አስቀድመው አቅደውት የነበረውን ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት እኩይ ድርጊት በአሰቃቂ ሁኔታ ፈጽመውታል፤ ቤት ንብረታቸውን አቃጥለዋል። ቅዱስ ሲኖዶስ የተረፉትን ክርስቲያኖች ለማጽናናት እና የደረሰውን ጉዳት ለማየት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተመራ የሀገር ሽመግሌዎች እና የማኅበራት የተካተቱበት በሦስት አቅጣጫ ጉዞ አድርጓል። ልዑኩ በሦስት ተከፍሎ ጉዞ ካደረገባቸው መካከል ይህ ዘገባ በምዕራብ አርሲ እና በምሥራቅ ሸዋ የተደረገውን የሚያስገነዝብ ነው። የማጽናናት እና የተበተኑን ለመሰብሰብ ታልሞ በተካሔደው ሐዋርያዊ ጉዞ ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት የደረሰውን ጉዳት እንደሚከተለው እናቀርባለን። ከሐምሌ 24-26 በተደረገው ሐዋርያዊ ጉዞ የተመለከትናቸው ዝዋይን፣ አዳሚ ቱሉን፣ አርሲ ነገሌን ፣ ኩየራን፣ ፍልቻን፣ ሻሸመኔን፣ አዳባን ፣ ሄረሮን፣ አሳሳን፣ ሽሬን፣ ቆሬን እና ኮፈሌን ነው።

    ዝዋይ
    በዝዋይ ከተማ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ አምስት ኦርቶዶክሳውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ተቆራርጠው በመገደል ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። ገዳዮቹ ጭካኔያቸውን የሰማዕታቱን አስከሬን በመሬታችን አይቀበርም በማለት አንገላተዋል። የኦርቶዶክሳውያን የንግድ ቦታቸው እና የመኖሪያ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ በእሳት ጋይቷል። በሁሉም ከተሞች እና ወረዳዎች የክርስቲያኖች የንግድ ቦታቸው እና የመኖሪያ ቤቶቻቸው ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ሲሆን፥ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ክርስቲያኖቹ “ላዩ ሣር ውስጡ ባህር” በሚባልለት ክረምት በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ተጠልለው በብርድ ይሰቃያሉ።

    ፍልቻ
    በፍልቻ ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን በዱላ ተደብድበው፣ ቤታቸው ሙሉ ለሙሉ መቃጠሉን ለማየት ችለናል። በዚሁ ደብር አገልጋይ የሆኑትን ካህን እና ከዘጠና ዓመት በላይ የሆናቸውን የዕድሜ ባለጸጋ ገፍትረው ጥለው ‘እስከ ዛሬ አንተ አጥምቀሃል፤ ዛሬ እኛ እናጥምቅህ’ በማለት በባልዲ ውሃን እየደፉ እንዳሰቃዩዋቸው ነግረውናል።

    ሻሸመኔ
    በሻሸመኔ የሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አባላት ሆቴሎቻቸው እና ትምህርት ቤታቸው በእሳት ጋይቷል። ወ/ሮ ሜሮን የተባለች የ፱ ወር ነፍሰ-ጡር ልብሷን በመቅደድ እና ቢላን ሆዷ ላይ በማድረግ ክርስቲያን እንደማይወለድ ስላስፈራሯት የተፈጸመባት ድርጊት ጭንቀት እና ቅዠት ዳረጓት ሕይወቷ ዐልፏል።

    በጠቅላላው በሻሸመኔ የተፈጸመውን ውድመት መልሶ ለማልማት ከፍተኛ ገንዘብን እና ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ጥፋት ፈጻሚዎች አሁን ድረስ የማስፈራራት እና ክርስቲያኖችን የማሳቀቅ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን ተጎጂዎች ተናግረዋል። የሻሸመኔ ውድመትና ጥቃት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በተሰገሰጉ ባለሥልጣናት እና በፓሊስ ቸልተኝነት የተፈጠረ በመሆኑ ዘወትር በታሪክ ሲታወስ ይኖራል።

    አዳባ
    የክርስቲያኖች ቤት ተቃጥሏል፤ አንድ ወጣት ክርስቲያንም በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል። ወጣቱ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ታርዶ የተሰዋ ሲሆን፥ ቤተሰብም ‘አስከሬኑን አታነሱም’ ተብለው እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት ዝናብ እና ፀሐይ ተፈራርቆበታል። በተጨማሪም የወጣቱን ደም ውሾች ሲልሱት ቤተሰብ በመመልከቱ ለአእምሮ መረበሽ ተዳርገዋል። በመጨረሻም ለአራት በመሆን የሰማዕቱን አስከሬን አንሥተው ለመቅበር ችለዋል። ንብረቶቻቸው እና ቤቶቻቸው የተቃጠለባቸው ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ተጠልለዋል። የተጎዱትን ምእመናንን የሚመግቡት አስተባባሪዎች ታስረው እንደ ነበር ለማወቅ ተችሏል።

    አሳሳ
    በአሳሳ እና ሄረሮም የክርስቲያኖች ቤት እና ንብረት ሙሉ ለሙሉ የወደመ ሲሆን፥ በአሳሳ አራት ሰዎች፣ በሄረሮ አንድ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈውና ታርደው ተገድለዋል። በሽሬ፣ በቆሬ እና በኮፈሌ የሚገኙ ክርስቲያኖችም የተጎዱ ሲሆን፥ ለዘመናት ያፈሩት ቤት ንብረት ሙሉ ለሙሉ ወድሟል። ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ በየአብያተ ክርስቲያኑ በመቃብር ቤትና በደጀ ሰላም ለመጠለል ተግድደዋል። ለዓመታት የቀጠለው ኦርቶዶክሳውያንን የማሳደድ እና የማጥፋት ድርጊት እልባት ባለማግኘቱ፥ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የክርስቲያኖችን ደኅነነት ማስጠበቅ ባለመቻላቸው ዛሬም ድረስ ጭንቀት ፈጥሮባቸዋል። ዛሬም የማስፈራርያና የውጡልን ዛቻው እነደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።

    መንግሥት መቆጣጠር እና የኦርቶዶክሳውያንን ደኅንነት ማስጠበቅ ለምን ተሳነው?

    በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚፈጸሙ ጥቃቶች ማቆም እና ኦርቶዶክሳውያንን መታደግ ያልተቻለበት ምክንያት ጥቃቱ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ኃላፊዎች ይመራ እና ከለላ ይደረግለት ስለነበር ነው። የሚፈጸምን ወንጀል ማቆም የተሳነው የጸጥታ አካል ‘ትዕዛዝ አልተሰጠኝም’ በማለት ኦርቶዶክሳውያን ሲጨፈጨፉ እና ሀብት ንብረታቸው ሲወድም ይመለከት ነበር።

    መፍትሔ

    መንግሥት ኃላፊነቱን በመወጣት ሕግ ማስከበር ይኖርበታል። የሰዎችን የመኖር ተፈጥሯዊም ሕገ መንግሥታዊ መብት ማስጠበቅ አለበት። ወንበዴዎችን ተከታትሎ በመያዝ የጀመረውን ሥርዓት የማስጠበቅና ሕግ የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል፣ የኦርቶዶክሳውያንን ስጋት ማቃለል ኖርበታል፤ ለተፈናቀሉ እና ሀብት ንብረት ለወደመባቸው ወገኖች ተገቢው ካሳ በመስጠት መልሶ ማቋቋም ይኖርበታል፤ በፍጥነት በመሥራት የእኩይ ተግባር ተቃዋሚነቱን ማሳየት ይገባዋል። ይህ ካልተደረገ ኦርቶዶክሳዊ መሆኑ እንደ ወንጀለኛ እየተቆጠረ ሲሳደድ ይኖራል።

    ኦርቶዶክሳዊ ኅብረት እንዲጠናከር እና እራስን የመጠበቅ የመከላከል ሥራ ተግባር እንዲፈጽም ማንቃት ያስፈልጋል። በየአካባቢው የሚኖረው ክርስቲያን ቅንጅት የመፍጠር እና የመሳተፍ ግዴታ ይኖርበታል።

    በመጨረሻም፡-

    የተፈጸመው ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት ተግባር መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል። ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸምብን መንቃት ይኖርብናል። የተጠናከረ ጥበቃ በማድረግ ወገኖቻችንን መታደግ ግድ ይለናል። ወደ ፊት ለሚፈጸመው ጥቃት መንግሥት ኃለፊነቱን እንዲወስድ ማድረግ ይገባል።

    ይቆየን…

    መጋቤ ሥርዓት ዮሴፍ ዓባይ
    ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

    ጴጥሮሳውያን የቤተክርስቲያን መብትና ክብር አስጠባቂ ኅብረት

     

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.