ማኅበረ ቅዱሳን ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ደብዳቤ ጻፈ

Home Forums Semonegna Stories ማኅበረ ቅዱሳን ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ደብዳቤ ጻፈ

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • Author
    Posts
  • #12714
    Semonegna
    Keymaster

    ‘አገር የሆነች ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ የመንግሥት ግዴታ መሆኑን’ በማሳሰብ ማኅበረ ቅዱሳን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ደብዳቤ ጻፈ። የደብዳቤው ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ይነበባል።

    ለክቡር ዶክተር ዐቢይ አህመድ
    የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ጠቅላይ ሚኒስትር
    አዲስ አበባ
    ጉዳዩ፡- በተለያዩ አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች እንዲቆሙ ስለመጠየቅ

    ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ፡- አስቀድመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ የሀገር ግንባታ የነበራትን ታላቅ ሚና ተገንዝበው ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ሰላም ያረጉትን አስተዋጽኦ ሳናመሰግን አናልፍም።

    ይሁንና በአሁኑ ወቅት ይህን ደብዳቤ ለእርስዎ ለመጻፍ ያነሳሳን ዐቢይ ጉዳይ በሀገራችን በየጊዜው ድንገት በሚፈጠሩ ሁከቶችና ብጥብጦች ሁሉ ምክንያት ተፈልጎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ካህናቶቿና ተከታዮቿ ምእመናን የአደጋ ሰለባ እንዲሆኑ እየተደረገ መምጣቱ በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢና አፋጣኝ መፍትሔ በመንግሥት ሊሰጠው የሚገባው ሆኖ አግኝተነዋል።

    በየትኛውም ዓለም የሚኖሩ የእምነት ተቋማት ለሀገር ግንባታና ዕድገትም ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው። እንደዚሁ ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ የማይተካ ሚና እንደ ነበራት ግልጽ ነው። በሥነ ጥበብ፣ በኪነ ሕንፃ፣ በሥነ ሥዕል፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሕግ ቀረጻና ሀገራዊ ክብርና እሴትን በማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና የተጫወተች መንፈሳዊ ተቋም ናት። በረከታቸው ይደርብንና በሕይወት የተለዩን ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በተለያዩ ጽሑፎቻቸውና አባባሎቻቸው እንዳስቀመጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ጽሑፍ ከነፊደሉ፣ ነጻነት ከነክብሩ፣ ዘመን ከነቀመሩ፣ ሀገር ከነድንበሩ፣ አንድነት ከነጥብዓቱ ያስረከበች የኢትዮጵያ ባለውለታ ናት። ቀደም ሲል በክቡርነትዎም አንደበት እንደተነገረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሀገር ባለውለታ ከማለት ይልቅ ራሷን ሀገር አድርጎ መግለጽ የውለታዋን ታላቅነት በተሻለ ሁኔታ ያሳያል። ይህን የምታደርገው ደግሞ የሀገሪቱን ከፍተኛ ቁጥር የያዘ ሕዝብ የምትመራ እንደመሆኗ እንደ ሀገር ስለምታስብና ለሀገር ልማትና እድገት ትኩረት ሰጥታ ስለምትሠራ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም ።

    ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡-

    ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ያበረከተችው አስተዋጽኦና ውለታ ይህ ሆኖ ሳለ ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ እየተፈጸመባት ያለው ግፍ ከበጎነቷ በተቃራኒ ከመሆኑም በላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ በይዘቱ እየባሰና እየጨመረ በዐይነቱም ለመናገር እስከሚሰቀጥጥ ድረስ ዘግናኝ እየሆነ መጥቷል። ይህ ግፍ የተጀመረው ዛሬ ባይሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያጋጠሙ ያሉ ተደጋጋሚና ቀን ቆጥረው የሚፈጸሙ ጥቃቶች በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተበረታቱባት ይገኛሉ። በተለይም ጽንፍ የረገጠው የዘውግ ፖለቲካ ርእዮተ ዓለምና ኢትዮጵያን በጠላትነት የፈረጁ “የውጭ አካላትን” ሽፋን ያደረገ እንቅስቃሴ ግብ ቤተ ክርስቲያንን የማጥፋትና ለሀገር አንድነትና ነጻነት ያላትን ሚና መቀነስ እንደሆነ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ከሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዘው የመጡ የብዙ አካላት ፍላጎቶችም እንዲህ ዐይነት ቀውሶች እንዲፈጠሩ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም እንረዳለን። በሀገር ውስጥም የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት በሚለው ሃሳብ ላይ ዋልታ ረገጥ የሆነ አመለካከት በሚያራምዱ አካላት መካከል ያለው ውጥረትም ቀላል እንዳልሆነ እንገምታለን።

    ይህም ሁሉ ሆኖ መንግሥት ችግሩን ለመፍታትና ምላሽ ለመስጠት ያሳየውን በጎና ቅን ሙከራዎችን ግን ሳንጠቅስ አናልፍም። ነገር ግን አሁንም ቤተ ክርስቲያን የጥፋት መልእክተኞች የጥቃት ዒላማ ሆና ትገኛለች። በዚህ ረገድ የሕግ የበላይነት ኖሮ ፍትሕ ማግኘት አለመቻል ከመንግሥትም በቂ ከለላ ሳታገኝ መቅረቷ በኦርቶዶክሳውያን አእምሮ ብሶትና እሮሮ ያስነሳ በመንግሥትም ላይ ትልቅ ጥርጣሬን የሚያጭር እየሆነ መጥቷል። ለዚህም በምሳሌነት ቀደም ያለውን እንኳ ትተን የቅርቡን ብናይ በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ በተነሳው ውዝግብና ከአክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ጥበቃ መነሣት ውዝግብ ጋር ተያይዞ በተቀሰቀሰው ረብሻ በቤተ ክርስቲያን፤ በአገልጋዮችና በምእመናን የተፈጸመውን ጥቃትና የደረሰውን ዕልቂት ማስታወስ ይበቃል። በአጠቃላይ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በጅግጅጋና አካባቢው ከተፈጸመው ጥቃት እስከ አሁን ቤተ ክርስቲያን ብዙ መከራን አስተናግዳለች። እርስዎ ከመጡ ጀምሮ በተረጋገጠ መረጃ መሠረት በትንሹ 25 አብያተ ክርስቲያን ተቃጥለዋል። ጅግጅጋ፣ ጅማ፣ ሲዳማ፣ ከሚሴ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ባሌና አርሲ በተፈጸሙ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ካህናትና ምእመናን በአሰቃቂ ሁኔታ በድንጋይ ተቀጥቅጠው፣ በእሳት ተቃጥለውና በገጀራ ተቆራርጠው ሕይወታቸውን አጥተዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሕፃናትንና አሮጊቶችን ጨምሮ ብዙ ሴቶች ተደፍረዋል። የብዙ ክርስቲያኖች ቤቶች ተቃጥለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸውና ከሀብት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በተለያዩ የሥነ ልቡና ጫናዎች ውስጥ ወድቀው በፍርሃትና በሥጋት የሚኖሩት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

    ቀደም ሲልም የቤተክርስቲያን መቃጠልና ጥቃት ይቁም ብለው የተሰባሰቡና ለክቡርነትዎ ቀርበው ሃሳባቸውን ገልጸው እርስዎም በሰጡት ምላሽ ከክልሎች ጋር በመወያየት ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። ብዙ ክልሎችም አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ግን ጉዳዩ ላይ ትኩረት አልሰጠም፤ ፍላጎትም አላሳየም። አሁን እንደሚታዩት አብዛኞቹ ችግሮች የተፈጸሙትና በመፈጸምም ላይ የሚገኙት በዚሁ ክልል ውስጥ ነው። ይህን የምንጠቅሰው ስለማያውቁት ሳይሆን እንዲህ ዐይነቶች ጥቃቶች እየተፈጸሙ በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ ሳይወሰድ ሲቀርና የዜጎች የደኅንነት ዋስትና አለመረጋገጥ ምን ማለት እንደሆነ ምንስ ያህል ከባድ እንደሆነ በኋላ የሚያስከትለውም አደጋ ከባድ እንደሆነ ለማሳሰብ ጭምር ነው።

    በያዝነው ወርኃ ኅዳር ደግሞ የጥቃት ዒላማ ተረኛ የሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ናቸው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዙ ፍላጎቶች የሚስተናገዱባቸው፣ የሀሳብ ፍጭቶች የሚካሔዱባቸውና፣ ማኅበራዊ መስተጋብሮች የሚፈጸሙባቸው የልሕቀት ማእከላት ናቸው። በአግባቡ ከተያዙ ሀገርን ከድህነት የሚያወጡና ለሀገር ፈውስ የሚሆኑ ሊቃውንት የሚወጡባቸው፣ በአግባቡ ካልተያዙና ለጥፋ መልእክተኞች መሣሪያ ከሆኑ ግን ሀገርን የሚያጠፉ ትምህርትን በአግባቡ ያልተጠቀሙበት የጥፋት ዐርበኞች የሆኑ ትውልዶች የሚፈሩባቸው እንደሚሆኑ የታመነ ነው። ይህን እውነት ከግንዛቤ አስገብተን ስንመለከተው ለሀገር የሚበጅ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ለሕዝብ የሚቆረቆር የተማረ ዜጋ ማፍራት የሚቻለው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተረጋጋ የመማር ማስተማር ከባቢያዊ ሁኔታ መፍጠር ከቻሉ ብቻ ነው። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ አጥልቶ የሚታየው የጥቃት ድባብ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲማሩ ልጆቻቸውን የላኩ ወላጆችንም ሆነ ተማሪዎችን በተረጋጋ መንፈስ እንዲኖሩ የሚፈቅድ አይደለም። በአንዳንድ ቦታ አልፎ አልፎ እየተከሰቱ ያሉ አደጋዎችና ሁከቶች ወላጆችን ለከፍተኛ ሥጋትና ጭንቀት እየዳረጋቸው ነው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተፈጸመ ያለው ጥቃትም ሃይማኖትን ማእከል ያደረገ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል። ስለሆነም መንግሥት በአጥፊዎች ላይ ርምጃ አለመውሰድን እንደ “ትዕግሥት” በመቁጠር ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በዝምታ መመልከቱ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ነውና የዜጎችን የመኖር መብትና የደኅንነት ዋስትና ማረጋገጥን መንግሥት በአግባቡ እንዲተገብረው እንጠይቃለን። ሰሞኑን እንደተመለከትነው ጥቃቶችና ግጭቶችን በእንጭጩ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይወጡ መቆጣጠር እየተቻለ ከትኩረት ማነስ ምክንያት ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ በምሥራቅና ምዕራብ ሐራርጌ ምእመናንና አብያተ ክርስቲያናት በሁለት ቀናት ብቻ የደረሰውን ጥፋት ዘርዝረን የማንጨርሰው ሆኖብናል።

    በመሆኑም በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች በሚዲያ እንደተገለጸው ከመንግሥት አቅም በላይ ካልሆኑ በአጭር ጊዜ ችግሮቹ እልባት እንዲያገኙ መደረግ አለበት፣ ካልተቻለ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተወሰነ ጊዜ ተዘግተው የማረጋጋት ሥራዎችን ሠርቶ እንደገና ማስጀመር እንደ አማራጭ መፍትሔ መታየት ይገባዋል ብለን እናምናለን። ከዚህም በተጨማሪ ጥቃቶችን እየፈጸሙና እያስፈጸሙ ባሉ አጥፊዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ በግልጽና ሁሉንም ዜጋ በሚያሳምን መልኩ መውሰድ ለዜጎች ደኅንነት ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን። ችግሩ አልፎ አልፎ ከኦርቶዶክሳውያን ውጭ የሚገኙትንም የሚያካትት ቢሆንም አሁን ግልፅ ሆኖ ግን የሚታየው ኦርቶዶክሳውያኑ ላይ እጅግ ያነጣጠረ የሰፋና የከፋም ነው። አስቸኳይ መፍትሔ ካልተገኘለትም ‘’ኦርቶዶክሳውያኑ በሁሉም አካባቢ የጥቃት ዒላማ ተደርገን እየተቆጠርን ያለነው እኛን ነን’’ በማለት የራሳቸውን ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ከፍተኛ መተላለቅንም ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ የመንግሥት ሚዲያዎች አደጋዎችን በትክክል እንደመዘገብ እውነትን ማስተባበልና የተሳሳተ መረጃ ማስተላለፋቸው ደግሞ አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ ሆነ ተብሎ የሚወሰድ ርምጃና በአብዛኛውም ምእመንም ዘንድ መንግሥታዊ ሽፋን ያለው ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጎታል። በአጠቃላይ የችግሮቹ ሂደት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ጉዳዮች ከመፈጠራቸው በፊት መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እየጠየቅን በጉዳዩ ዙሪያ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ሆኑ ሃይማታዊ ተቋማት ሊሳተፉባቸው በሚገባቸው ኃላፊነቶች ሁሉ የድርሻችን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።

    እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!
    ማኅበረ ቅዱሳን (EOTCMK)

    ማኅበረ ቅዱሳን

    #15391
    Anonymous
    Inactive

    ኦርቶዶክሳዊ እንደ ወንጀለኛ የሚቆጠርበት ክልል
    (ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት)

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያም በኦርቶዶክስ ታሪክ ውስጥ ያላቸው ውሕደት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ እንደማለት ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ እና ቅርስ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኗ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ ሀገር መሆኗን እኛ ብቻ ሳንሆን ምዕራባውያን ጸሐፊዎችም የመሰከሩት እውነታ ነው። ኢትዮጵያ እና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፍጹም አንድነት ሲገለጡ ኖረዋል።

    ካለፉት 40 ዓመታት በኋላ ግን ለዘመናት የኖረው እውነት ተገፍቶና ተሽሮ ቤተ ክርስቲያኗን የማይወክል የሐሰት ትርክት ሲነገር ኖሯል። ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗን በጠላትነት በመፈረጅ “ቀና እንዳትል አከርካሪዋን ሰብረነዋል” ብለው በአደባባይ እስከ መናገር ደረሱ። አብያተ ክርስቲያናትን ለመቃጠል፣ ክርስቲያኖችን ለሞት፣ ለስደት፣ ለመፈናቀል እንዲሁም ለንብረት ውድመት ተዳረጉ። በሁለተኛው እና በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ያለፉበትን ሰማዕትነት እና ትላንት በሌላው ዓለም ስንሰማውና በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ ስናየው የነበረው አሰቃቂ ግድያ ኦርቶዶክስ በመሆናቸው ብቻ በሀገራችን ተፈጽሞ የሞትን ጽዋ ተጎነጩ ።

    በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያት ስበከት ወደ ዓለም ሁሉ መድረሷ እና በሰማዕታት ደም መጽናቷ ይታወቃል። ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ማታ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ምክንያት በማድረግ አስቀድመው አቅደውት የነበረውን ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት እኩይ ድርጊት በአሰቃቂ ሁኔታ ፈጽመውታል፤ ቤት ንብረታቸውን አቃጥለዋል። ቅዱስ ሲኖዶስ የተረፉትን ክርስቲያኖች ለማጽናናት እና የደረሰውን ጉዳት ለማየት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተመራ የሀገር ሽመግሌዎች እና የማኅበራት የተካተቱበት በሦስት አቅጣጫ ጉዞ አድርጓል። ልዑኩ በሦስት ተከፍሎ ጉዞ ካደረገባቸው መካከል ይህ ዘገባ በምዕራብ አርሲ እና በምሥራቅ ሸዋ የተደረገውን የሚያስገነዝብ ነው። የማጽናናት እና የተበተኑን ለመሰብሰብ ታልሞ በተካሔደው ሐዋርያዊ ጉዞ ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት የደረሰውን ጉዳት እንደሚከተለው እናቀርባለን። ከሐምሌ 24-26 በተደረገው ሐዋርያዊ ጉዞ የተመለከትናቸው ዝዋይን፣ አዳሚ ቱሉን፣ አርሲ ነገሌን ፣ ኩየራን፣ ፍልቻን፣ ሻሸመኔን፣ አዳባን ፣ ሄረሮን፣ አሳሳን፣ ሽሬን፣ ቆሬን እና ኮፈሌን ነው።

    ዝዋይ
    በዝዋይ ከተማ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ አምስት ኦርቶዶክሳውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ተቆራርጠው በመገደል ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። ገዳዮቹ ጭካኔያቸውን የሰማዕታቱን አስከሬን በመሬታችን አይቀበርም በማለት አንገላተዋል። የኦርቶዶክሳውያን የንግድ ቦታቸው እና የመኖሪያ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ በእሳት ጋይቷል። በሁሉም ከተሞች እና ወረዳዎች የክርስቲያኖች የንግድ ቦታቸው እና የመኖሪያ ቤቶቻቸው ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ሲሆን፥ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ክርስቲያኖቹ “ላዩ ሣር ውስጡ ባህር” በሚባልለት ክረምት በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ተጠልለው በብርድ ይሰቃያሉ።

    ፍልቻ
    በፍልቻ ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን በዱላ ተደብድበው፣ ቤታቸው ሙሉ ለሙሉ መቃጠሉን ለማየት ችለናል። በዚሁ ደብር አገልጋይ የሆኑትን ካህን እና ከዘጠና ዓመት በላይ የሆናቸውን የዕድሜ ባለጸጋ ገፍትረው ጥለው ‘እስከ ዛሬ አንተ አጥምቀሃል፤ ዛሬ እኛ እናጥምቅህ’ በማለት በባልዲ ውሃን እየደፉ እንዳሰቃዩዋቸው ነግረውናል።

    ሻሸመኔ
    በሻሸመኔ የሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አባላት ሆቴሎቻቸው እና ትምህርት ቤታቸው በእሳት ጋይቷል። ወ/ሮ ሜሮን የተባለች የ፱ ወር ነፍሰ-ጡር ልብሷን በመቅደድ እና ቢላን ሆዷ ላይ በማድረግ ክርስቲያን እንደማይወለድ ስላስፈራሯት የተፈጸመባት ድርጊት ጭንቀት እና ቅዠት ዳረጓት ሕይወቷ ዐልፏል።

    በጠቅላላው በሻሸመኔ የተፈጸመውን ውድመት መልሶ ለማልማት ከፍተኛ ገንዘብን እና ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ጥፋት ፈጻሚዎች አሁን ድረስ የማስፈራራት እና ክርስቲያኖችን የማሳቀቅ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን ተጎጂዎች ተናግረዋል። የሻሸመኔ ውድመትና ጥቃት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በተሰገሰጉ ባለሥልጣናት እና በፓሊስ ቸልተኝነት የተፈጠረ በመሆኑ ዘወትር በታሪክ ሲታወስ ይኖራል።

    አዳባ
    የክርስቲያኖች ቤት ተቃጥሏል፤ አንድ ወጣት ክርስቲያንም በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል። ወጣቱ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ታርዶ የተሰዋ ሲሆን፥ ቤተሰብም ‘አስከሬኑን አታነሱም’ ተብለው እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት ዝናብ እና ፀሐይ ተፈራርቆበታል። በተጨማሪም የወጣቱን ደም ውሾች ሲልሱት ቤተሰብ በመመልከቱ ለአእምሮ መረበሽ ተዳርገዋል። በመጨረሻም ለአራት በመሆን የሰማዕቱን አስከሬን አንሥተው ለመቅበር ችለዋል። ንብረቶቻቸው እና ቤቶቻቸው የተቃጠለባቸው ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ተጠልለዋል። የተጎዱትን ምእመናንን የሚመግቡት አስተባባሪዎች ታስረው እንደ ነበር ለማወቅ ተችሏል።

    አሳሳ
    በአሳሳ እና ሄረሮም የክርስቲያኖች ቤት እና ንብረት ሙሉ ለሙሉ የወደመ ሲሆን፥ በአሳሳ አራት ሰዎች፣ በሄረሮ አንድ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈውና ታርደው ተገድለዋል። በሽሬ፣ በቆሬ እና በኮፈሌ የሚገኙ ክርስቲያኖችም የተጎዱ ሲሆን፥ ለዘመናት ያፈሩት ቤት ንብረት ሙሉ ለሙሉ ወድሟል። ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ በየአብያተ ክርስቲያኑ በመቃብር ቤትና በደጀ ሰላም ለመጠለል ተግድደዋል። ለዓመታት የቀጠለው ኦርቶዶክሳውያንን የማሳደድ እና የማጥፋት ድርጊት እልባት ባለማግኘቱ፥ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የክርስቲያኖችን ደኅነነት ማስጠበቅ ባለመቻላቸው ዛሬም ድረስ ጭንቀት ፈጥሮባቸዋል። ዛሬም የማስፈራርያና የውጡልን ዛቻው እነደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።

    መንግሥት መቆጣጠር እና የኦርቶዶክሳውያንን ደኅንነት ማስጠበቅ ለምን ተሳነው?

    በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚፈጸሙ ጥቃቶች ማቆም እና ኦርቶዶክሳውያንን መታደግ ያልተቻለበት ምክንያት ጥቃቱ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ኃላፊዎች ይመራ እና ከለላ ይደረግለት ስለነበር ነው። የሚፈጸምን ወንጀል ማቆም የተሳነው የጸጥታ አካል ‘ትዕዛዝ አልተሰጠኝም’ በማለት ኦርቶዶክሳውያን ሲጨፈጨፉ እና ሀብት ንብረታቸው ሲወድም ይመለከት ነበር።

    መፍትሔ

    መንግሥት ኃላፊነቱን በመወጣት ሕግ ማስከበር ይኖርበታል። የሰዎችን የመኖር ተፈጥሯዊም ሕገ መንግሥታዊ መብት ማስጠበቅ አለበት። ወንበዴዎችን ተከታትሎ በመያዝ የጀመረውን ሥርዓት የማስጠበቅና ሕግ የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል፣ የኦርቶዶክሳውያንን ስጋት ማቃለል ኖርበታል፤ ለተፈናቀሉ እና ሀብት ንብረት ለወደመባቸው ወገኖች ተገቢው ካሳ በመስጠት መልሶ ማቋቋም ይኖርበታል፤ በፍጥነት በመሥራት የእኩይ ተግባር ተቃዋሚነቱን ማሳየት ይገባዋል። ይህ ካልተደረገ ኦርቶዶክሳዊ መሆኑ እንደ ወንጀለኛ እየተቆጠረ ሲሳደድ ይኖራል።

    ኦርቶዶክሳዊ ኅብረት እንዲጠናከር እና እራስን የመጠበቅ የመከላከል ሥራ ተግባር እንዲፈጽም ማንቃት ያስፈልጋል። በየአካባቢው የሚኖረው ክርስቲያን ቅንጅት የመፍጠር እና የመሳተፍ ግዴታ ይኖርበታል።

    በመጨረሻም፡-

    የተፈጸመው ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት ተግባር መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል። ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸምብን መንቃት ይኖርብናል። የተጠናከረ ጥበቃ በማድረግ ወገኖቻችንን መታደግ ግድ ይለናል። ወደ ፊት ለሚፈጸመው ጥቃት መንግሥት ኃለፊነቱን እንዲወስድ ማድረግ ይገባል።

    ይቆየን…

    መጋቤ ሥርዓት ዮሴፍ ዓባይ
    ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

    ጴጥሮሳውያን የቤተክርስቲያን መብትና ክብር አስጠባቂ ኅብረት

     

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.