Home › Forums › Semonegna Stories › ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Tagged: አቢሲንያ ባንክ, የኢትዮጵያ አየር መንገድ, የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን, ዳሸን ባንክ, ፀሐይ ባንክ
- This topic has 55 replies, 3 voices, and was last updated 9 months, 1 week ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
June 28, 2020 at 2:35 am #14974AnonymousInactive
የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባባር ኢትዮጵያን ማስቻል (Enabling Ethiopia) የተባለ የ5 ዓመት ፕሮጀክት ጀመረ
አዲስ አበባ – የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኢትዮጵያን ማስቻል (Enabling Ethiopia) የተባለ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባባር ጀመረ። የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በጋራ የጀመሩት የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ፈጠራን በማበረታታት፣ አካታችና አነቃቂነትን መሠረት በማድረግ ፖሊሲዎችን በማሻሻል በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ የሚደግፍ ነው። ለዚህ ፕሮጀክት ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የ11.8 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
“ኢትዮጵያን ማስቻል” (Enabling Ethiopia) ፕሮጀክት ሲቀረጽ የሀገሪቱን የ5 ዓመት የሥራ ፈጠራ መሪ ዕቅድ ለማሳካት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኖበት ነው። ፕሮጀክቱ ሀገሪቱን የሥራ ፈጠራ አጀንዳ እና የኮሚሽኑን አምስት ዓመት ስትራቴጂ ለመተግበር እንዲያግዝ ሆኖ የተቀረጸ ነው። እ.ኤ.አ በኦክቶበር 2019 የተጀመረው የኮሚሽኑ የአምስት ዓመት የሥራ ዕድል ፈጠራ መሪ ዕቅድ በግል ዘርፉና በፌደራል እንዲሁም በክልሎች ደረጃ ያሉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በተናበበ መልኩ አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብ፣ ኢንቨስትመንትን በማመቻቸት በ 2015 (እ.ኤ.አ) 14 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ ነው።
በዚህ ፕሮጀክት የረጅም ጊዜ ዕቅድ ለሥራ ፈጠራ ምቹ ምህዳር መፍጠር፣ አስፈላጊ የሰው ኃይል ካፒታልን ማዳበር እና ማክሮ ፖሊሲዎች ሥራ ፈጠራን እንዲያበረታቱ ማስቻል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራባቸዋል።
ኢትዮጵያን ማስቻል ለ50 ሺህ ሴቶችና ወጣቶች በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሥራ ዕድል በማመቻቸት የመሪ ዕቅዱን አፈጻጸም ያግዛል። በተጨማሪም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተገቢውን ትኩረት የሚሰጡ ማክሮ ፖሊሲዎች እንዲቀረጹና አፈጻጸማቸውም ቀልጣፋ እንዲሆን የአቅም ግንባታ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ፣ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ግንባታውን በማገዝ እንዲሁም ሃብት በማሰባሰብ ሥራዎች ላይ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል።
ኢትዮጵያን ማስቻል ትኩረት ላልተሰጣቸው የማኅበረሰብ አካላት ማለትም የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለሚሠሩት ሥራ ክፍያ የማያገኙ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች፣ ስደተኞችና አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት ዓላማ ያደረገ ነው። ፕሮጀክቱ የወጣቶችን ክህሎት ከማዳበር በተጨማሪ 200 ለሚሆኑ እምቅ ኃይል ያላቸው ሥራ ፈጣሪዎች ህልማቸውን እንዲያሳኩ ድጋፍ ያደርጋል።
“ኢትዮጵያን ማስቻል ስሙም እንደሚያመለክተው ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች መልካም አጋጣሚ ነው። በተለይም ትኩረት ያልተደረገባቸው ነገር ግን ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሥራ እንዲኖራቸውና ገቢ እንዲያገኙም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በተጨማሪም ፕሮጀክቱ አዳዲስ ዕድሎችን ለማመቻቸት እና ለሥራ ፈጣሪዎች ፣ ለድርጅቶችና ለግሉ ሴክተር እንቅፋቶችን ለማስወገድ ትኩረት ፈጠራ ትብብርና ልህቀትን በመጠቀም ለሴቶችና ለወጣቶች ደህንነቱ የተጠበቀ ፣ የተከበረ እና አስደሳች የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ይተጋል” በማለት ዶ/ር ኤፍሬም ተክሌ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ገልጽዋል።
ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መሪነት ሲሆን የፌዴራልና የክልል መንግሥታት፣ የኢንተርፕራይዝ ልማት አካላት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ተቋማትና የግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ነው።
“ይህ ፕሮጀክት በ2030 (እ.ኤ.አ) ለ10 ሚሊዮን ወጣቶች የተከበሩና አስደሳች የሥራ ዕድሎችን ለማመቻቸት ከተቀረጸው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ወጣት አፍሪካ በሥራ ላይ ፕሮጀክት ጋር አብሮ የሚሄድ ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር ባለን ትብብር የኢትዮጵያ ወጣቶች እድገት እንዲያስመዘግቡና የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በጉልህ እንዲታይላቸው የሚያደርግ ነው” በማለት አቶ አለማየሁ ኮንዴ ኮይራ፣ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ገልጸዋል።
- ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው ደንብ ቁጥር 435/2011 መሠረት ተጠሪነቱ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም ነው። ኮሚሽኑ በሁሉም የሥራ ዘርፎች የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳን የማስተዳደር ፣ የማቀናጀት እና የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን በዚህም በመላ ሀገሪቱ የሚፈጠሩ ሥራዎች ዘለቄታ ያላቸው እንዲሆኑ እ.ኤ.አ በ2020 ዓ.ም ሦስት ሚሊዮን ፣ በ2025 ዓ.ም 14 ሚሊዮን ፣ በ 2030 ደግሞ 20 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ በማመቻቸትና ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በፖሊሲና ስትራቴጂ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ክትትል እና አቅም ግንባታ፣ በትብብርና ኢንቨስትመንት፣ በኢኖቬሽንና በመረጃ ትንተና እና ሥርዓት ማበልጸግ ላይ ትኩረት በማድረግ እስከ ሚያዝያ 2012 (እ.ኢ.አ) ድረስ 2.4 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
ስለ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የበለጠ መረጃ ለማግኘት ድረ-ገጹንና ማኅበራዊ ሚድያዎቹን ይጎብኙ፦
https://www.jobscommission.gov.et
https://twitter.com/Jobs_FDRE
https://www.facebook.com/JobsCommissionFDRE/- ማስተርካርድ ፋውንዴሽን
ማስተርካርድ ፋውንዴሽን (Mastercard Foundation) ሁሉም ሰው የመማር እና የመበልፀግ ዕድል ሊያገኝ የሚችልበት ዓለም እንዲኖር ይመኛል። ለዚህም ፋውንዴሽኑን ዋነኛ ተልዕኮውን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ሰዎች የትምህርት ልህቀት እና የፋይናንስ አካታችነትን ማሻሻል ነው። በዓለማችን ካሉ ታላላቅ ፋውንዴሽኖች መሐከል አንዱ የሆነው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን አፍሪካ ላይ ዋነኛ ትኩረቱን ያደርጋል። እ.ኤ.አ በ2006 በማስተርካርድ ኢንተርናሽናል አማካኝነት ቢመሠረትም በአሁኑ ወቅት ራሱን በቻለ የቦርድ አመራር ስር ይተዳደራል። ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በቶሮንቶ፥ ካናዳ እንዲሁም በኪጋሊ፥ ሩዋንዳ ፅሕፈት ቤቶች አሉት።
ስለ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የበለጠ መረጃ ለማግኘት ድረገጹንና ማህበራዊ ሚድያዎቹን ይጎብኙ፦
http://www.mastercardfdn.org
http://twitter.com/MastercardFdnምንጭ፦ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን
July 18, 2020 at 4:30 am #15111AnonymousInactiveበሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቱሪስት ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ሄሎ ታክሲ በተባለ ድርጅት አማካኝነት በይፋ ተመርቀው ሥራ ጀመሩ
አዲስ አበባ (ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር) – ኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ የሚገጣጥማቸውና በሄሎ ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ታክሲዎች በሸራተን አዲስ ሆቴል በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው በይፋ ተመርቀዋል።
የኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሶሎሞን ሙሉጌታ፥ “ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ የቱሪዝም ሀብት ያላትና የተስፋ ምድር በመሆኗ ለቱሪስት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎችን ቀድመን ለማዘጋጀት ችለናል” ብለዋል።
የሄሎ ታክሲ መሥራችና ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሐንስ በበኩላቸው፥ “ሄሎ ታክሲ በቀጣይም ቱሪስቱን በአውሮፕላን ወደ ቱሪስት መዳረሻዎች ለማድረስና አመርቂ አገልግሎት ለመስጠት 50% ዝግጅቱን አጠናቋል” ብለዋል።
ሄሎ ታክሲ ከዚህ ቀደም 40 ታክሲዎችን አስመርቆ በይፋ ሥራ ያስጀመረ ሲሆን፥ አሁን ደግሞ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የቱሪስት ታክሲ ወደ አገልግሎት በማስገባት ሥራውን ጀምሯል። ሄሎ ታክሲ ከዚህ ቀደም በታክሲ አገልግሎት ተሰማርተው መኪኖቻቸው አሮጌ በመሆናቸው ከአገልግሎት ውጭ ለሆኑባቸው አሮጌውን መኪና በመቀበልና በአዲስ በመተካት የታክሲ ባለቤቶችን እየታደገ ያለ ድርጅት መሆኑም ተገልጿል። የተሰበሰቡ አሮጌ ታክሲዎችም ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመንጃ ፍቃድና ተግባራዊ የመኪና ጥገና መማሪያ እንዲሆኑ፤ ከዚያም ሲያልፍ የዋጋ ተመን ወጥቶላቸው ወደ ማቅለጫ ገብተውና ለውጭ ገበያ ተሽጠው ገቢ እንዲያስገኙ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስተር ክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው፥ “መንግሥት የታክሲ ሞተሮች ከቀረጥ ነጻ ሆነው ወደ ሀገራችን እንዲገቡ የወሰነው ግብር መሰብሰብ አቅቶት ሳይሆን፥ አሮጌ መኪኖችን በአዲስ ተተክተው የአየር ብክለት እንዲቀንስ፣ ሀገር ውስጥ ሲገጣጠሙም ተጨማሪ የሥራ ዕድል ስለሚፈጥሩ፣ ዜጎቻችንም በሀገራቸው ሠርተው እንዲከብሩ፣ ስርቆት የሚፀየፍ ጥሩ አገልጋይ እንድትሆኑ ነው” ብለዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም፥ ታክሲዎችን በአዲስ እንደቀየራችሁ ሁሉ አስተሳሰባችሁንና ሕይወታችሁን በመቀየር ለቱሪስቶቻችንም ቀድሞ መረጃ በመስጠት ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ የሀገራችንን ገፅታ እንድትገነቡ አሳስባለሁ ብለዋል።
የክህሎትና የአገልግሎት አሰጣጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለታክሲ ሹፌሮች ይሰጣል ያሉት ሚኒስትሯ፥ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሕጋዊ አሠራርን መከተል እና ለረዥም ዓመታት በአሮጌ መኪና ጭስ የተበከለችውን ሀገራችንን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብራችን ችግኝ በመትከልና በማልማት ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ ብለዋል።
በመጨረሻም ክብርት ወ/ሮ ቡዜና አልኸድር የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ፥ ለታክሲ አገልግሎት ማኅበራቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሳተፉ የችግኝ ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን፥ ከሄሎ ታክሲ ድርጅት ጋርም በቱሪስት የታክሲ አገልግሎት ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
የኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ተወካይ አቶ ሸምሰዲን አብዱራህማን በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ተደራሽ የሚሆኑ ለ110 ሥራ አጥ ወጣቶች በ100% ብድር የሚሰጡ ሄሎ ታክሲዎችን፣ አስር የቱሪስት አምቡላንሶችን፣ በ59 ቋንቋዎች የማስተርጎም ሥራ የሚሠሩ ሃምሳ ማሽኖችን ለክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው አስረክበዋል።
የሄሎ ታክሲ ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሐንስ በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ተደራሽ የሚሆኑ ለ250 ሰዎች አሮጌ ታክሲያቸውን ብቻ ሰጥተው አዲስ ታክሲ እንዲረከቡ የሚያስችል ስጦታ ያቀረቡ ሲሆን፥ የታክሲ ማኅበራትም ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የምስጋና ስጦታ ለክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው አበርክተዋል።
ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
July 29, 2020 at 2:17 am #15228SemonegnaKeymasterከ19.9 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 12 መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችል ውል ስምምነት ፊርማ ተካሄደ
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንአዲስ አበባ (ኢመባ) – የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን (ኢመባ) ከ19.9 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 12 መንገዶችን በአስፋልት ደረጃ ለመገንባት የሚያስችል ውል ስምምነት ፊርማ ከተለያዩ ሀገር በቀል እና የውጭ ተቋራጮች ጋር አካሄደ።
አሥራ ሁለቱ የሚፈረሙት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በደምሩ 825.23 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያላቸው ሲሆን፥ ለግንባታቸው የሚወጣው ወጪ የሚሸፈነው የአስሩን መንገዶች በኢትዮጵያ መንግሥት፣ የሁለቱን መንገዶች ደግሞ ከዓለም ባንክ (World Bank) በተገኘ ብድር ነው። የውል ስምምነት ከፈጸሙት የሥራ ተቋራጮች መካከል ስድስቱ አገር በቀል የሥራ ተቋራጮች ሲሆኑ፥ የተቀሩት አራቱ አለም አቀፍ የውጭ ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች ናቸው።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በሰጠው መግለጫ፥ መንገዶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ እንደመንገዶቹ ሁኔታ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር ጀምሮ እስከ አራት ዓመት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።
- የአስራ ሁለቱን የመንገድ ፕሮጀክቶች ዝርዝር እና እያንዳንዱን የመንገድ ፕሮጀክት ለመገንባት ያሸነፈውን ተቋራጭ ዝርዝር ለማየት እዚህ ጋር ይጫኑ።
የግንባታ ፕሮጀክቶቹ የመንገድ ግራና ቀኝ ትከሻን ጨምሮ በገጠር በአማካይ ከስምንት እስከ አስር ሜትር ስፋት ሲኖራቸው፥ በከተማ ውስጥ የሚገነቡት ምንገዶች ተጨማሪ ስፋት እንዲኖራቸው ተደርገው የሚገነቡ ይሆናል። በተጨማሪም ግንባታው የአነስተኛ፣ ከፍተኛ ፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎች እና ድልድዮችንም አካቷል።
የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከዚህ በፊት በአካባቢው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ የአካባቢው ሕብረተሰብ በቀላሉ ወደ ፈለገው ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ከዚህም ባለፈ አንድን ክልል ከሌላ ክልል፣ እንዲሁም በየክልሎቹ ውስጥ የሚገኙ ዞኖችንና ወረዳዎችን እርስ በእርስ የሚያስተሳስሩ ይሆናሉ። ከተፈረሙት መንገዶች መካከልም ወደ ጎረቤት አገር የሚያዘልቁ መንገዶችም በመኖራቸው አገራዊ ፋይዳቸው ላቅ ያለ እንደሚሆን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መግለጫ ያስረዳል።
መንገዶቹ የተሽከርካሪዎችን የጉዞ ጊዜና ወጪን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንሱ ከመሆኑም በተጨማሪ የምርትና የሸቀጥ ልውውጥ ያለምንም እንግልት በቀላሉ እንዲከናወን ከማድረግ አኳያ የተፈረሙት መንገዶች ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ያደርገዋል።
እነዚህ መንገዶች በአገሪቱ ካለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሁም መንግሥት ከያዘው የድህነት ቅነሳ ስልት (poverty reduction strategy) አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ይታመናል። ስለሆነም የመንገድ ኘሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቁ በአካባቢው የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጉዳዮች ከፍተኛ ትብብር እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ያሳስባል።
ምንጭ፦ ኢመባ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
August 3, 2020 at 11:28 pm #15283SemonegnaKeymasterከክረምቱ ወቅት መግባት ጋር ተያይዞ መንገዶች ላይ የሚደረጉ ማንኛውም ቁፋሮዎች እንደማይከናወኑ
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (አአመባ) አስታወቀአዲስ አበባ (አአመባ) – የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (አአመባ) የክረምት መግባት ጋር በተያያዘ በመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚካሄዱ የቁፋሮ ሥራዎችን ከግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማስቆሙን ገልፆ፥ ለተግባራዊነቱም የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
የክረምት ወራት መግባትን ተከትሎ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማትና ግለሰቦች ለተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚቀርቡለትን የመንገድ መሠረተ ልማት ቁፋሮ ፈቃድ ማቆሙ ይታወቃል።
ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የቁፋሮ ፈቃድ ይሰጥባቸው ከነበሩት ውስጥ የመጠጥ ውሃ ዝርጋታ፣ የዝናብ ውሃ ከቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ መስመር (drainage system) ጋር ይገናኝልኝ ጥያቄ፣ የፍሳሽ መስመር ለማገናኘት፣ የመግቢያ መውጫ ይከፈትልንና ከመሠረተ ልማት ዘርጊ ተቋማት የሚቀርቡ የመንገድ መቁረጥ ፈቃድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በክረምት የሚደረጉ ቁፋሮዎች በነዋሪው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ እክል እንዳይፈጥሩ፣ ከአደጋ ለመጠበቅና የትራፊክ ፍሰት እንዳይስተጓጎል የቁፋሮና የአስፋልት መቁረጥ ፍቃድ መስጠት እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማቆሙን አስታውቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት በቁጥር 443 የሚሆኑ ከተለያዩ አካላት የቀረቡለትን የመንገድ መቁረጥ ጥያቄ ፍቃድ ሰጥቷል። በተጨማሪም የመንገድ ሃብት ላይ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን በመፈጸም ጉዳት የሚያደርሱ አካላት ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የመንገድ መብት ጥሰቶችና ጉዳቶች ለመከላከል የሚያስችል አሠራርን በመዘርጋት እንቅስቃሴ እያደረግ ይገኛል።
በመንገድ ሀብት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቅረፍና መንገዶችን ለመንከባከብ ባለስልጣኑ ከመሠረተ ልማት ቅንጅት ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር እና ከመሠረተ ልማት ዘርጊ ተቋማትና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተናቦ በመሥራት ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት ፈሶባቸው የተገነቡ መንገዶችን ከሚደርስባቸው የተለያዩ የመንገድ መብት ጥሰቶችና ጉዳቶች ለመከላከል ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህም የመንገድ መሠረተ ልማቶች በሚፈለገው መጠን ከጉዳት ተጠብቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ከማስቻሉም ባለፈ የመንገዶችን የጥገና ወጪ በመቀነስ የጎላ አስተዋፅኦ አድርጓል።
በመጨረሻም ሕብረተሰቡ የተገነቡ እና በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከመንገድ መብት ጥሰቶችና ከሚፈፀሙ ሕገ-ወጥ ተግባራት በመከላከልና በመጠበቅ ከባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በጋራ እንዲሠሩ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከ375.2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የግንባታ ግብዓቶችን አምርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉንአስታውቋል።
ባለስልጣኑ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በ134.9 ሚሊዮን የካባ፣ በ73.7 ሚሊዮን ብር ሲሚንቶ፣ በ166.6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአስፋልት ምርቶችን አምርቶ ለተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ያሰራጨ ሲሆን፥ አጠቃላይም የዕቅዱን 89 በመቶ አፈፃፀም አስመዝግቧል።
በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በራስ አቅም ተመርተው ሥራ ላይ ከሚውሉ የተለያዩ ምርቶች መካከል፥ ገረገንቲ፣ ቤዝ ኮርስ (base course)፣ ሰብቤዝ (subbase)፣ ጠጠር፣ ነጭ ድንጋይ፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው ቱቦዎች፣ ሲሚንቶ ኮንክሪት፣ ከርብስቶን (curbstone)፣ የማንሆል ክዳን (manhole cover)፣ ፍርግርግ፣ ቦላርድ (bollard)፣ ታይልስ (tiles)፣ ባይንደር ሚክስ (binder mix)፣ ሰርፊስ ሚክስ (surface mix) የመሳሰሉት ይገኙበታል።
ባለስልጣኑ የግንባታ ግብዓቶችን በራሱ አቅም ማምረት መቻሉ በራሱ አቅም እየገነባቸው ለሚገኙ የግንባታና የጥገና ሥራዎች የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በቀጣይም የግብዓት ምርቶች እጥረት እንዳይፈጠርም አሁን ላይ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ሥራዎችን ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ ማሽነሪዎችን በመግዛት በትጋት እየሠራ ይገኛል።
ምንጭ፦ አአመባ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
August 5, 2020 at 12:13 am #15304SemonegnaKeymasterየፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስገነባቸው ቤቶች አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን)፦ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ አምስት ሳይቶች የሚያካሂደው የቤቶች ግንባታ አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክብሮም ገብረመድኅን በተለይ ለአዲስ ዘመን ዕለታዊ ጋዜጣ እንዳስታወቁት፥ የቤቶቹ ግንባታ በአቧሬ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ አካባቢ፣ በመካኒሳ፣ ብሪቲሽ ካውንስልና ቦሌ ላይ እየተካሄደ ነው፤ ህንፃዎቹም እስከ 10 ፎቅ የሚደርሱና ለቅይጥ አገልግሎት (ለንግድ እና ለመኖሪያ) በሚል እየተገነቡ ያሉ ናቸው።
ግንባታዎቹ እንደየቦታው ስፋት የተለያዩ ዓይነቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ መንታ /twin/ ተደርገው የሚገነቡም እንዳሉ ጠቁመዋል። የመካኒሳው፣ የጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ አካባቢውና የብሪቲሽ ካውንስሉ ፕሮጀክቶች ባለሁለት መንታ ግዙፍ ህንፃዎች መሆናቸውን አስታውቀው፥ የቦሌው አንድ ግዙፍ ህንፃ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ የግንኙነት ኃላፊው ገለጻ፥ አንዳንዶቹ ህንፃዎች ባለሰባት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ባለ 10 ወለሎች ሲሆኑ፥ እየተገነቡ ያሉት በከተማ አስተዳደሩ የየአካባቢው ፕላን መሠረት ነው። በአጠቃላይ ግን የንግድ ተቋማቱ ብዛት በካሬ ሆኖ ወደፊት የሚለይ ሲሆን፥ የተቀሩት ግን ለቀቅ ባለ /luxurious/ በሆነ መልኩ ወደ አንድ ሺ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቤቶች እየተገነቡ ነው።
በግንባታው ላይ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተደጋጋሚ ጉብኝት በማድረግ ክትትል እንደሚደረግ ጠቅሰው፥ የተቋሙ ማኔጅመንት ካውንስል /የስራ አመራር ኮሚቴው/፣ እንዲሁም የተቋሙ ቦርድ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የፓርላማው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴም ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረው፥ ሠራተኛው፣ ተቋራጮቹ፣ መሀንዲሶቹ እንዲሁ ሁሉም በጋራ በመረዳዳት መንፈስ እየተሠራ በመሆኑ አፈጻጸሙ ስኬታማ መሆን መቻሉን ተናግረዋል። የፓርላማ አባላት ፕሮጀክቶቹን እንደጎበኙትና በአፈጻጸሙም አድናቆቱ እንዳላቸው መግለጻቸውንም የግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል።
“በቀጣይ ደግሞ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩ ይጠበቃል” ያሉት የግንኙነት ኃላፊው፥ የአሁኖቹ ፕሮጀክቶች ልምድ የሚቀሰምባቸው፣ አቅም እና ካፒታል የሚሰባሰብባቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ኮርፖሬሽኑ ማኅበራዊ ኃላፊነቱንም እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለንግዱ ማኅበረሰብ 50 በመቶ የኪራይ ቅናሽ ማድረጉን አስታውሰዋል። ባለፉት አራት ወራት በኮቪድ-19 ምክንያት በየወሩ ከኪራይ መሰብሰብ የሚገባውን 60 ሚሊየን ብር ከተከራዮች አለመሰብሰቡን ተናግረዋል።
የግንኙነት ኃላፊው በዚህ ፈተና ውስጥ እንዴት ከማኅበረሰቡ ጎን መቆም አለብኝ ብሎ በማሰብ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው በአዲስ አበባና በድሬዳዋ የሚገኙ 18,153 የመኖሪያና የድርጅት ቤቶች ተከራይ ደንበኞች የኮቪድ-19 የኮረና ቫይረስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የፈጠረባቸውን ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ በመረዳት ኪራይ የመቀነስ ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውሰዋል። በኪራይ ዋጋ ቅነሳም በየወሩ ከአጠቃላይ ገቢው 50 በመቶውን እያጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ በወር ከሚያገኘው 120 ሚሊየን ብር ገቢ እየሰበሰበ ያለው 60 ሚሊየን ብር ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ከገባ አንስቶ ባሉት አራት ወራት ኮርፖሬሽኑ ማግኘት ከነበረበት 480 ሚሊየን ብር የሰብሰበው ግማሹን ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል። ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ብሔራዊ ንቅናቄ ሲቋቋም ድጋፍ ካደረጉት የመጀመሪያ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፥ በወቅቱም 10 ሚሊየን ብር መስጠቱንም ጠቅሰዋል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባና በድሬዳዋ 18,153 ቤቶች እንዳሉት ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከእነዚህ መካከል ወደ 6ሺ 500 አካባቢ የንግድና የድርጅት ሲሆኑ፥ የተቀሩት ደግሞ የመኖሪያ ቤቶች ናቸው። ኮርፖሬሽኑ በደንብ ቁጥር 398/2009 የተለያዩ ተግባርና ኃላፊነቶች ተሰጥተዉት በራሱ ገቢ እንዲተዳደር የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
August 9, 2020 at 8:08 pm #15354SemonegnaKeymasterኢትዮ ሊዝ ከሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የእርሻ ሜካናይዜሽን መሣሪያዎች ለገበሬዎች አስረከበ
አዲስ አበባ – በኢትዮጵያ በሊዝ ፋይናንስ ዘርፍ በመሰማራት የመጀመርያው የውጭ ኩባንያ የሆነው ኢትዮ ሊዝ የተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ 16 ኮምባይነሮችን ለአርሶ አደሮች እና ለማኅበራት አስረከበ። የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎቹን ወደ አገር ውስጥ ያስገባው የኢትዮጵያ መንግሥት በግብረናው ዘርፍ ለማዘመን የያዘውን ስትራቴጂ ለመደገፍ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ጋር ያደረውን ሰምምንት ተከትሎ ሲሆን፥ ስምምነቱም እነዚህን ውድ የሆኑ የግብርና ማቀነባበሪያ መሣሪያዎችን መግዛት የማይችሉትን አርሶ አደር ገበሬዎችን በአጭር ጊዜ ባለቤት የሚያደርግ ይሆናል።
በዚህኛው ዙር የተካሄደው ርክክብ እስካሁን ድረስ ያስረከባችውን የግብርና መሣሪያዎች ቁጥር ወደ አንድ መቶ ያደረሰ ሲሆን፥ አጠቃላይ ወጪያቸው ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው። ከእነዚህም በተጨማሪ ኩባንያው በመጪው መስከረም እና በጥቅምት ወራት (2013 ዓ.ም.) ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተጨማሪ መሣሪያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስፈልጉትን ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል።
የኢትዮ ሊዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ግሩም ፀጋዬ በርክክቡ ውቅት እንደተናግሩት፥ “በተከታታይ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባናቸው ያሉት የግብርና መሣሪያዎች ኩባንያችን የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ የማዘመን ዕቅድ ለማሳካት የበኩሉን እየሠራ እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን፥ በዚህም እንቅፋት የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጦት መፍታት ችለናል” በማለት አስረድተዋል።
አቶ ግሩም አክለውም፥ “ዘላቂነት ያለው ግብርናን ማዘመን ሥራ የአርሶ አደሩን አቅም በመገንባት ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወትና ምርታማነትን እና ገቢን ሊያሻሽል እንዲሁም የምግብ ዋስትናን እና አኗኗር ለማሻሻል ይረዳል” ብለዋል። የኢትዮ ሊዝ አርሶ አደሮች ከመደገፍ በተጨማሪ ለኦፕሬተሮች፣ ለረዳቶች ኦፕሬተሮች እና ለተለያዩ ባለሙያዎች፣ የሥራ ዕድልን የሚፈጥር እንደሆነ በሻሽመኔ ከተማ በተደረገው ርክክብ ላይ ተነግሯል።
አትዮ ሊዝ አፍሪካን አሴት ፋይናንስ ካምፓኒ (African Asset Finance Company/AAFC) በተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ በ400 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተ ኩባንያ ነው። ኩባንያው ለእርሻ፣ ለሕክምናና አምራች ኢንዱስትሪ የሚውሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች በኪራይ ለማቅረብ የሚያስችለውን የሥራ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም. አግኝቷል።
ኢትዮ ሊዝ የካፒታል እቃዎችን እንደአስፈላጊነቱ በመለየት እና በመግዛት፣ አስፈላጊ ጥገናዎችን እና አግባብነት ባለው ሁኔታ አገልግሎት ላይ መዋላቸውን የመቆጣጠር ኃላፊነት ይኖረዋል። በተጨማሪም ተከራዩ ወይንም አገልግሎቱን ያገኘው አካል መሣሪያዎችን መግዛት የሚችልበትን መንገድ ያመቻቻል። ኢትዮ ሊዝ ወደሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ፥ ለግብርና፣ ለጤና፣ ለኃይል አቅርቦት (energy)፣ ለምግብ ማቀነባበር (food processing) አገልግሎት ሰጪዎች የካፒታል እቃዎችን አቅርቧል። ድርጅቱ እስካሁን ከ60 በላይ ከሚሆኑ ደንበኞች ጋር የካፒታል እቃዎች አቅርቦት ስምምነት አድርጓል።
ስለ ኢትዮ ሊዝ
ኢትዮ ሊዝ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የሊዝ ፋይናንስ አቅራቢ ኩባንያ ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ እ.አ.አ በ2017 የአፍሪካ አሴት ፋይናንስ ኩባንያ አካል በመሆን ሥራው ጀምሯል። ኩባንያው በአፍሪካ የሊዝ አገልግሎት ያልተዳረሰባቸውን ገበያዎች ለማገልገልና አቅምን ያገናዘበ ብድር ለማቅረብ የሚሠራ ኩባንያ ነው። ለበለጠ መረጃ http://www.ethiolease.com ይጎብኙ።ስለ አፍሪካን አሴት ፋይናንስ ካምፓኒ (AAFC)
የአፍሪካ አሴት ፋይናንስ ኩባንያ (AAFC) ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ኒው ዮርክ በማድረግ በተለያዩ ሀገራት ያሉ ኩባንያዎች የፋይናንስ አቅርቦት አገልግሎት ይሰጣል። በመላው አፍሪካም የደንበኞችን ፍላጎትና አቅምን መሰረት ያደረገ የቁስ ውሰት አገልግሎቶችን ይሰጣል። ለበለጠ መረጃ http://www.aafc.com ይጎብኙ።August 11, 2020 at 11:31 pm #15378SemonegnaKeymasterየአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 በጀት ዓመት 715 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ማከናወኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት 715 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ማከናወኑን፣ 21 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቁንና አዳዲስና ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ማስጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ለአዲስ አድማስ ዕለታዊ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በበጀት ዓመቱ 706 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ለማከናወን አቅዶ 715 ኪ.ሜ. በማከናወን ከዕቅድ በላይ አፈፃፀም አስመዝግቧል። በዚሁ በጀት ዓመት ከተሠራው አጠቃላይ የመንገድ ሥራ ውስጥ 167 ኪ.ሜ. አዳዲስ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 544 ኪ.ሜ. ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎች ናቸው።
ባለስልጣኑ በግንባታ ላይ ከነበሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል 21 የሚሆኑትን በማጠናቀቅ አስመርቆ ለትራፊክ ክፍት ያደረገበት በጀት ዓመትም መሆኑን ጠቅሶ፥ በሁለት ዙር በይፋ የተመረቁት የመንገድ ግንባታዎች በድምሩ ከ33 ኪ.ሜ. በላይ ርዝመት እና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ ከ10 እስከ 30 ሜትር የጎን ስፋት ያላቸውና ለግንባታቸውም ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሆነባቸው መሆኑን አመልክቷል።
በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት በዓይነታቸው ለሀገሪቱም ሆነ ለመዲናዋ አዲስና ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ማስጀመሩንም የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታውሶ፥ ከእነዚህም መካከል የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት የተጀመረው የዊንጌት–ጀሞ ሁለት የፈጣን አውቶቡስ መንገድ እና የፑሽኪን አደባባይ–ጎተራ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት ገልጿል።
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው እና ከ90 ኪ.ሜ. በላይ ርዝመት ያላቸው 22 የመንገድ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውንም ባለስልጣኑ ጠቅሷል። በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት የተጀመሩት እነዚህ ታላላቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች በሁለት ዓመት ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ እንደሚገኝም ባለስልጣኑ ጠቁሟል።
በበጀት ዓመቱ በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ በርካታ ጉዳቶች መድረሳቸውንም አያይዞ የጠቀሰው ባለስልጣኑ፥ በ12 ወራት ውስጥ በተሽከርካሪ ግጭት ብቻ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ መድረሱንና ይህም በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ አመልክቷል።
በተሽከርካሪ ግጭት በብዛት ጉዳት ከደረሰባቸው የመንገድ ሀብቶች መካከል የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና ርቀት አመላካች ሰሌዳዎች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦች፣ ውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ክዳኖች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዘርዝሯል።
የወሰን ማስከበር ችግር፣ የተቋራጮች አቅም ውስንነት፣ የገልባጭ መኪና እና ግብዓት እጥረትና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራ ወቅት የገጠሙ ዋነኛ ፈተናዎች እንደነበሩም ባለስልጣኑ አስታውሶ፥ ችግሮቹን በመፍታት በአፈፃፀም ላይ ሊያሳድሩ የነበረውን ተፅዕኖ መቀነስ መቻሉን አስታወቋል። በበጀት ዓመቱ ለመንገድ ፕሮጀክቶች እና ለመደበኛ ሥራዎች አስከአሁን ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ባለስልጣኑ ጠቅሷል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
August 19, 2020 at 12:07 pm #15482AnonymousInactiveየማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ አስር የማዕድን ምርመራ እና ሁለት የማዕድን ምርት ፈቃዶችን ሰጥቷል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የማዕድናት ፍለጋ እና ልማት ለማካሄድ ፈቃድ ለጠየቁና የፈቃድ መውሰጃ መስፈርቶችን አሟልተው ለቀረቡ ለ12 የማዕድን ኩባንያዎች ፈቃድ ተሰጥቷል። ሁለቱ የምርት ፈቃዶች ሲሆኑ አስሩ የምርመራ ፈቃዶች ናቸው።
የምርት ፈቃድ የተሰጣቸው የባዛልት እና የዕምነበረድ ማዕድን ምርት ሲሆኑ ሌሎች አስር ኩባንያዎች ደግሞ በደለል ወርቅ፣ ወርቅ እና መሰል ማዕድናት፣ ብረት፣ ማንጋኔዝ፣ ክሮማይት፣ ብር እና ጀምስቶን ማዕድናት ምርመራዎች ናቸው።
ሁለቱ የምርት ፈቃዶች ለኢንቨስትመንት 270,186,310.00 (ሁለት መቶ ሰባ ሚሊዮን አንድ መቶ ሰማንያ ስድስት ሺ ሶስት መቶ አስር) ብር የተመዘገበ ካፒታልና ለ187 ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሲሆን፥ የምርመራ ፈቃዶች ደግሞ 131,935,555.00 ብር (አንድ መቶ ሰላሳ አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ መቶ ሰላሳ አምስት ሽህ ዘጠኝ አምስት መቶ አምሳ አምስት) ብር የተመዘገበ ካፒታል እና በምርመራ ወቅት በድምሩ ለ293 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። ምርመራ ሂደታቸውን በስኬት አጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡም ከሥራ ዕድል ፈጠራ እስከ ውጭ ምንዛሬ ግኝትና ማዳን ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ።
የምርመራ ፈቃዱ የውሉ ስምምነት ፊርማው ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ እንደ የፍቃድ ዓይነት ከ1 ዓመት እስከ 3 ዓመት የሚፀና ሆኖ፥ የፈቃድ ዘመኑም ሲጠናቀቅ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረትና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሲያምንበት ሊታደስ የሚችል ነው።
ስምምነቱን በፈቃድ ሰጪው መሥሪያ ቤት በኩል የፈረሙት ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ (የማዕድን ዘርፍ) ሲሆኑ፥ በባለፈቃዶቹ በኩል የፈቃድ ወሳጅ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ናቸው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ለወጠነችው የኢንዱስትሪያዊነት መዋቅራዊ ሽግግር የኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚፈልገውን የማዕድናት ግብዓት ለሟሟላት በሁሉም ዓይነት የዘርፉ ሃብቶቻችን ላይ በስፋት እየተሠራ ይገኛል።
ዛሬ ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች የምርትም ሆነ የምርመራ ሥራቸውን ሲያከናውኑ በፌደራልና በክልል የማዕድን አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን መሠረት አድርጎ በጥንቃቄ በትጋትና ቅልጥፍና በተሞላበት ሁኔታ በማዕድን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተቀባይነት ባለው የአሠራር ዘዴ ለማከናወን በስምምነቱ ውስጥ የተካተተ ሲሆን፥ ተመጣጣኝ ዕውቀት፣ ችሎታና ልምድ ላላቸው ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ቅድሚያ የሥራ ዕድል ለመስጠትና ለሥራው አስፈላጊ የሆነውን ሥልጠና የመስጠት ግዴታ አለባቸው።
የአካካቢ ጥበቃን (environmental protection) በተመለከተ የሠራተኞቹን፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጤንነትና ደህንነት በማይጎዳና ብክለት በማያስከትል መልኩ የምርት ሥራውን ለማከናወን ውል የተፈፀመ ሲሆን፥ ሥራውን ሲያቋርጥ በተፈጥሮ አካባቢ ላይ፣ በሰው ሕይወትና ንብረት እንዲሁም ዕፅዋት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ማናቸውም ቅሪቶችና ግንባታዎችን ያስወግዳል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የፕሮጀክቶችን ውልና አፈጻጸም በየጊዜው እየገመገመ በገቡት ውል መሰረት ሥራቸውን በአግባቡ የሚያከናውኑትን የመደገፍና የማበረታታት፣ በውላቸው መሠረት የማይሠሩትን ደግሞ ፍቃድ የመሰረዝና ሌሎች ሕጋዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዜና ሳንወጣ፥ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ኢ/ር ታከለ ኡማ ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዕለቱ አስር ሹመቶችን በሰጡበት ጊዜ፥ የሚኒስቴሩ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሁነው ተሹመዋል። በዕለቱ የተሰጡት አስር ሹመቶች የሚከተሉት ናቸው።
- ዶ/ር ቀንዓ ያደታ – የመከላከያ ሚኒስትር
- ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ – ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
- ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ – የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር
- ኢንጂነር ታከለ ኡማ – የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር
- አቶ ተስፋዬ ዳባ – ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
- አቶ ዮሐንስ ቧያለው – የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር
- አቶ ንጉሡ ጥላሁን – የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር
- አቶ እንደአወቅ አብቴ – የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር
- አቶ ፍቃዱ ጸጋ – ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
- ፕ/ር ሂሩት ወልደማርያም – በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ በመሆን መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅሕፈት ቤት አስታውቋል።
August 22, 2020 at 2:05 am #15517AnonymousInactiveቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ በ3 ቢሊዮን ብር ለሚያስገነባው ገርጂ የመኖሪያ መንደር ከተቋራጮች ጋር ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ (ኢብኮ)፦ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በሶስት ቢሊዮን ብር ለሚያስገነባው ዘመናዊ መንደር (ገርጂ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክት/ Gerji Village Project) ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ተቋራጮች ጋር ነሐሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ስምምነት ፈፅሟል። ኮርፖሬሽኑ ስምምነቱም ያደረገው ከኮሪያ፣ ከህንድ እና ከኢትዮጵያዊያን የህንጻ ተቋራጮች መሆኑን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ዘግቧል።
ገርጂ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክትን ይፋ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስተሩ የካቢኔ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቦርድ ኃላፊ ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳ ናቸው።
በስምምነቱ መሠረት ገርጂ የመኖሪያ መንደር ውስጥ በሚቀጥሉት 18 ወራት ውስጥ 510 መኖሪያ ቤቶች ይገነባሉ። የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች ባለ 10 ወለል የሚኖራቸው 16 ህንጻዎች መሆናቸው ተገልጿል።
ገርጂ የመኖሪያ መንደር ሲጠናቀቅ በከተማዋ የሚታዩ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን በተወሰነ መልኩ የሚያቃልል መሆኑን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ረሻድ ከማል ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ገልጸዋል።
ግንባታው በዘመናዊ መንገድ የሚገነባ በመሆኑ የግንባታ ወጪውንም ሆነ ጊዜውን የሚያቀላጥፍ መሆኑ ተመክቷል፤ አንድ የህንጻ ወለልን በአምስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ የሚያጠናቅቅ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል።
አዲአ አበባ ውስጥ ሲ.ኤም.ሲ ከሚገኘው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የመኖሪያ መንደር ልምድ ተወስዶ፥ በሦስት ሔክታር ላይ የሚገነባው የገርጂ የመኖሪያ መንደር ሲጠናቀቅ ዘመናዊነትን የተላበሰ የመኖሪያ መንደር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የመኖሪያ መንደሩ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ይውሏል ተብሏል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከ28 ዓመት በኋላ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ወደ ቤቶች ግንባታ ራሱን በመመለስ፣ በተለያዩ ስምንት የግንባታ ቦታዎች ቤቶችን እየገነባ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ረሻድ ከማል በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ገቢውን እያሳደገ ሰፊ የቤት አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ይሠራልም ብለዋል አቶ ረሻድ።
ምንጭ፦ ኢብኮ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ሌሎች ዜናዎች
August 26, 2020 at 12:14 am #15578AnonymousInactiveየአቫካዶ ልማት አብዮት ተጀመረ ― ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ (ግብርና ሚኒስቴር)፦ “የሆርቲከልቸር ልማት በማሳለጥ የውጪ ንግዱን ለማሳደግ መጪ ጊዜ የሆርቲከልቸር ነው!” በሚል መርህ ታልሞ እየተሠራ ነው። የኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስቴር በሰብል ልማት የተጀመረውን የኩታ-ገጠም (cluster) አመራርት ላይ የታየውን ውጤታማ ሥራ በፍራፍሬ ላይም ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በፍራፍሬ ልማት ላይ የኩታ-ገጠም (cluster) አመራረት ስልት ተግባራዊ በማድረግ የአርሶ አደሩን ገቢ ለማሳደግ እና ከሀገር-አቀፍ እስከ ዓለም-አቀፍ ገበያ ተፈላጊነት ያለውን አቮካዶን በጥራት በማምረት ተወዳዳሪ ለመሆን እየተሠራ ነው። በዘርፉ የአረንጓዴ አብዮት እንዲመጣ እየሠራ እንደሚገኝ በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲከልቸር (horticulture) ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ወንዳለ ሀብታሙ ገልጸዋል። ዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ የሚገኝ፣ የውጪ ንግድ (export) በማሳደግ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እያሳደገና የአርሶ አደሩን የሥነ-ምግብ ችግር ከመቅረፍ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ዘርፍ በመሆኑ ለማስፋት እየተሠራ እንዳለ አክለው ገልጸዋል።
ይህንኑ አጠናክሮ ለመሄድ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን በአደኣ ወረዳ ከዚህ ቀደም በጤፍ አምራችነት ይታወቅ የነበረው አሁን ደግሞ ወረዳው ካለው 70 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ተቀንሶ 600 ሄክታር መሬት ላይ የአቫካዶ ኩታ-ገጠም (avocado cluster) ለመፍጠር በሰፊው እየተሠራበት እንደሆነ ታውቋል። ከዚህ ውስጥ ከ400 ሄክታር በላይ ላይ 1300 አርሶ አደሮች የተሳተፉበት የአቮካዶ ልማት እየተከሄደ ነው።
አቶ ከፍያለው ለማ የምሥራቅ ሸዋ ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ደንካካ እና ኡዴ የተባሉ ሁለት ቀበሌዎች ለአቮካዶ ኩታ-ገጠም (cluster) ልማት ከተመረጡ ቀበሌዎች መካከል መሆኑን ገልጸው በክላስተሩ የአቮካዶ ችግኝ ተከላ ከሀምሌ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህንን የአቦካዶ ልማት ኩታ-ገጠም የሚያጠናክር የአቮካዶ ችግኝ ተከላ የተካሄደው የግብርና ሚኒስተር ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ ባለሙያዎች፣ የኦሮሚያ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የምስራቅ ሸዋ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ኃላፊዎች የአካባቢው አርሶ አደሮችና የኢትዮጵያ ሆርቲከልቸር ልማትና ኤክስፖርት ማኅበር (EHPEA) ተወካዮች በተገኙበት ነው። በአደአ ወረዳ የተጀመረው አቮካዶን በኩታ-ገጠም ማልማት ሥራ ለሀገሪቷ የአቮካዶ ኤክስፖርት እድገትተስፋ ሰጭ እንደሆነ ለማየት ተችሏል።
በችግኝ ተከላ የተሳተፉ አካላትም አምና ተተክለው የጸደቁ አቮካዶ ማሳዎች ጉብኝተው ከገበያ የማስተሳሰር ሥራ ከወዲሁ ታስቦ መሠራት እንደሚገባ አስተያየት በመስጠት የችግኝ ተከላና የአቮካዶ ልማት ኩታ-ገጠም ጉብኝት ተጠናቅቋል።
በተያያዘ ዜና፥ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀዝቃዛ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በባቡርና በመርከብ አቀናጅታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምራለች። አቮካዶ የጫነ የመጀመሪያው ኮንቴነር ነሐሴ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሞጆ ደረቅ ወደብ ወደ አውሮፓ ለሙከራ ተልኳል።
የትራንስፖርት ሚኒስቴሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ ምርቶቹ ለውጭ ገበያ መቅረባቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ምርቶቻቸውን ለዓለም-አቀፍ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ አንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። እንዲሁም ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ዕድል በመፍጠር ረገድም ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በቀጣይም አርሶ አደሩ የግብርና ምርቶቹን ጥራታቸውን እንደጠበቁና ሳይበላሹ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንተጋለን ብለዋል። ለዚህም የባቡርና መርከብ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ምርቱ በሚመረትበት ሥፍራ በትኩስነቱ እንዲመጣ የማቀዝቀዣ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች እንደሚቀርቡ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ገልጸዋል። በዚህም ቀጣይነት ያለው የምርት አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነትና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
ምንጭ፦ ግብርና ሚኒስቴር / የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
September 3, 2020 at 1:03 am #15697AnonymousInactiveየገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ
ከ919 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለፀየኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ባልደረሰባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት መርሀ ግብርን (National Electrification Program) በመተግበር በስፋት እየሠራ ይገኛል።
መርሀ ግብሩ እስካሁን ብዛት ያላቸው የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፤ በቀጣይም ፍትሃዊ ተደራሽነትን ባማከለ መልኩ ሰፊ ሥራዎች እንደሚያከናውን ተገልጷል።
የሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ሁሴን መሀመድ እንደገለፁት፥ ፅ/ቤቱ ከተመሠረተበት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል ባልደረሰባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ኃይል የማዳረስ ሥራ ሲሠራ መቆየቱንና ከ2010 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም መባቻ ድረስ ከ63 ሺህ 900 በላይ አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ኃይል በማዳረስ የደንበኞች ቁጥር ለመጨመር ቁልፍ ሚና ያለው ይህ መርሀ ግብር፥ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ6 ሺህ 759 በላይ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን ኃላፊው ገልፀዋል። ከ1998 ዓ.ም በፊት ተጠቃሚ የነበሩት የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን ብዛት ሲታይ ግን ከ667 የማያላፉ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ኃላፊው አክለውም፥ ፕሮግራሙ በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት በአዲስና በመልሶ ግንባታ 405 የገጠር ከተሞችና መንደሮች በማገናኘት ከ32 ሺህ በላይ ደንበኞችን ኃይል ለማዳረስ አቅዶ፤ 325 የሚሆኑት የገጠር ከተሞችና መንደሮች በማገናኘት 25 ሺህ 232 አዳዲስ ደንበኞች የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ለዚህም ከመንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ 919 ሚሊዮን 277 ሺህ 349 ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ለዕቃ አቅርቦት ግዥ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የኃይል ማሠራጫ ዕቃዎች በተለይ የትራንስፎርመር እና የኮንዳክተር እጥረት በዋናነት የመርሀ ግብሩ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ተጠቅሷል።
በመጨረሻም በያዝነው በጀት ዓመት ፕሮግራሙ 450 የገጠር ከተሞችና መንደሮች በማገናኘት 54 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እየሠራ መሆኑን አቶ ሁሴን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመላው ሀገሪቱ ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማሳደግ በ”ብርሃን ለሁሉ” (Lighting to All) መርሀ ግብር እ.ኤ.አ በ2025 ከዋናው የኃይል ግሪድ 65 በመቶ እና ከግሪድ ውጪ በተለያዩ የኃይል አማራጮች 35 በመቶ የሚሆነውን ሕብረተስብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስትራቴጂ ቀይሶ በመንቀሳቀስ መሆኑ ይታወቃል።
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዜና ሳንወጣ፥ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ከ2.8 ቢሊዮን ኪሎ ዋትስ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነት መቀነስ መቻሉን አስታውቋል። ተቋሙ እንዳለው በ2012 በጀት ዓመት ቴክኒካልና ቴክኒካል ያልሆነ የኃይል ብክነትን ለመከላከል ባደረገው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ 2,823,055,758.11 ኪሎ ዋትስ የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነት ወይም በገንዘብ 1,113,863,407.24 ብር ከብክነት ማዳን ችሏል።
ተቋሙ የኃይል ብክነቱን መቀነስ የቻለው የኤሌክትሪክ ስርቆትን በመከላከል፣ በትክክል የማይሠሩ፣ የተቃጠሉ፤ የቆሙ ቆጣሪዎች በወቅቱ እንዲቀየሩ በማድረግ፣ የታሪፍ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውን ደንበኞች የታሪፍ ለውጥ በማድረግ፣ ቢል የማይወጣላቸው ደንበኞችን ወደ ሲስተም እንደገቡ በማድረግ፣ ያልተፈቀደ የኃይል ጭነት በመቆጣጠር፣ ከቆጣሪው ልኬት ውጪ የተገጠመ አውቶማቲክ ፊዩዝን (automatic fuse) በመቀየር፣ የዝቅተኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ደንበኞች የተገኘ የማባዣ ስህተት በማስተካከል፣ የገቢ ደረሰኝ የሌላቸው እንዲኖራቸው በማድረግ እና የመሳሰሉ ቴክኒካል ያልሆነ የኃይል ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት ነው።
ተቋሙ ቴክኒካል የኃይል ብክነትን ለመቀነስም የ2000 Common Meter Reading Instrument (CMRI) በተስተካከለው software design መጫን፣ የደንበኞች ቆጣሪ ቅያሪ ሥራ፣ የ383 የደንበኞችን መረጃ ወደ አዱሱ ሲሰተም (SAP) ማዛወርና የመሳሰሉ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን በ2013 በጀት ዓመትም ሊከሰቱ የሚችሉ ቴክኒካልና ቴክኒካል ያልሆኑ የኃይል ብክነቶችን ለመቀነስ ሰፊ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሰቀሰ በይገኛል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
September 5, 2020 at 1:43 am #15721SemonegnaKeymasterበግማሽ ቢሊዮን ብር የተገነባው ኃይሌ ሪዞርት አዳማ ተመረቀ
ተቃጥለው የነበሩ የሻሸመኔ እና ዝዋይ የኃይሌ ሪዞርቶችና ሆቴሎች ወደሥራ እንደሚመለሱም ተገለጸአዳማ (አዲስ ዘመን) – በአዳማ ከተማ በ500 ሚሊዮን ብር በሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ “ኃይሌ ሪዞርቶች እና ሆቴሎች” (Haile Resorts & Hotels) ኢንቨስትመንት የተገነባው ዘመናዊው ኃይሌ ሪዞርት አዳማ ተመረቀ።
ነሐሴ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የሆቴሉ ባለቤት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እንደገለጸው፥ አዲሱ ኃይሌ ሪዞርት አዳማ በአጠቃላይ 300 ለሚሆኑ ዜጎችና የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር ከፍተኛ ጥረት ባለው አገልግሎት ሕብረተሰቡን ለማገልገል የቆመ ነው ብሏል።
ለሀገር ጎብኚዎች በምቹ የቦታ አቀማመጡና ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ ሆቴሉን ተመራጭ እንደሚያደርገው የጠቆመው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ፥ ሪዞርቱ 106 የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች፣ ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁ የመመገቢያ አዳራሾች እንዲሁም ባሮችና ሌሎች ደረጃቸውን የጠበቁ የስብሰባ አዳራሾች እንዳሉትም ገልጿል።
“ኃይሌ ሪዞርቶች እና ሆቴሎች” ድርጅት ፈተናዎች ቢገጥሙትም በምሥራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ ለመሆን ተጨማሪ ሪዞርቶችን ለመክፈት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን የጠቆመው ሻለቃ ኃይሌ፥ በቅርቡም በአዲስ አበባ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በኮንሶ፣ በደብረ ብርሃን፣ በጎርጎራ እና በተቀሩት የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ሆቴሎችና ሪዞርቶችን ከፍቶ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሠራ መሆኑንም ተናግሯል።
በቅርቡ የቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸው የሻሸመኔ እና ዝዋይ የኃይሌ ሪዞርቶችና ሆቴሎች በቅርቡ ወደ ቀደመ ሥራቸው እንደሚመለሱም አትሌት ኃይሌ ተናግሯል። መንግሥት ለሪዞርቶቹ ከለላ ከመስጠት አልፎ ሥራ በማስጀመር ሂደቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲደርግም ጠይቋል።
ሪዞርቶችና ሆቴሎች ለአንድ ሀገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የላቀ ድርሻ እንዳላቸው የጠቀሰው ሻለቃ ኃይሌ፥ በእነዚህ መሠረተ ልማቶች ላይ አሉታዊ ክፍተት ሲያጋጥም መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ችግሩን ካልፈታው ኢንቨስትመንቱ ሊጎዳ እንደሚችል ጠቁሟል። ውድመት የደረሰባቸው ሁለቱ ሪዞርቶችና ሆቴሎችም የሕዝብ ገንዘብ በመሆናቸው በአስቸኳይ ወደሥራ እንደሚመለሱ አመላክቷል።
እንደሻለቃ አትሌት ኃይሌ፥ ገለፃ በተለይ ኃይሌ ሪዞርት ዝዋይ በፍጥነት ወደሥራ እንዲመለስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ በእነዚህ ሪዞርቶች እና ሆቴሎች ውስጥ ሲሠሩ የነበሩና በአሁኑ ወቅት ከሥራ ውጪ የሆኑ ሠራተኞችን ወደሥራ ለመመለስ ከመንግሥት እገዛ ይጠበቃልም ብሏል። የሆቴሎቹን መከፈት እውን ለማድረግ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋርም እየሠራ መሆኑን ተናግሯል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
September 9, 2020 at 1:51 am #15790AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበረራ ትኬትን በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ዘዴ አማካኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ስምምነት አደረገ
ደንበኞች የ‘ጉዞጎ’ (GuzoGo) መተግበሪያን በመጠቀም የሀገር ውስጥ እና ዓለምአቀፍ የበረራ ትኬቶችን መግዛት የሚችሉበት አሠራር ተዘርግቷል
አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሶልጌት ትራቭል (Solgate Travel) የበረራ ትኬት ሽያጭ በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሥርዓት ለማከናወን የሚያስችላቸውን ስምምነት ነሐሴ 29 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደ ይፋዊ ሥነ-ሥርዓት ፈጽመዋል።
በስምምነቱ መሠረት ደንበኞች የሲቢኢ ብር (CBE Birr) እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁሉም ቅርንጫፎች አማካኝነት ክፍያቸውን መፈፀም የሚያስችል የ‘ጉዞጎ’ (GuzoGo) መተግበሪያን በመጠቀም የሀገር ውስጥ እና ዓለምአቀፍ የበረራ ትኬቶችን መግዛት የሚችሉበት አሠራር መዘርጋቱን ነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ዮሐንስ ሚሊዮን የገለፁት።
ደንበኞች በረራቸውን ለማስመዝገብና የትኬት ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለው የ‘ጉዞጎ’ (GuzoGo) የሞባይል መተግበሪያን ከድረ-ገጽ በማውረድና የሞባይል ስልካቸው ላይ በመጫን አገልግሎቱን ማግኘት ያስችላልም ነው የተባለው።
በስልካቸው ላይ የጉዞጎ መተግበሪያን ያልጫኑ፣ ለቸኮሉ ወይም በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች መጠቀም ላልቻሉ ተጓዦች ወደ 7473 የጥሪ ማዕከል በመደወል የጉዞ ቦታ ማስያዝና ትኬት መቁረጥ የሚቻልበት አሠራር መዘርጋቱም ነው የሶልጌት ትራቭል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራው የገለጹት። ወደ 7473 የስልክ ጥሪ ማእከል በመደወል የሚፈልጉትን በረራ በማስመዝብ ክፍያቸውን በሲቢኢ ብር ወይም በባንኩ ቅርንጫፎች በማከናወን የትኬት ግዥ መፈጸም እንደሚችሉ አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል።
በቀጣይ ደንበኞች አገልግሎቱን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሞባይል እና የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎቶች አማካኝነት ማግኘት የሚችሉበት አሠራር በቅርቡ የሚተገበር መሆኑን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን ተጓዥ ደንበኞች ‘የጉዞጎ’ (GuzoGo) መተግበሪያን በመጠቀም የሀገር ውስጥ የሆቴል ክፍል ማስያዝ (reservation) የሚችሉበት አገልግሎቱን ለመጀመር መዘጋጀታቸውን ነው የጉዞጎ ሥራ አስኪያጅ አቶ በእርሱፈቃድ ጌታቸው በስምምነት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የገለጹት።
-
- ‘የጉዞጎ’ (GuzoGo) መተግበሪያን እዚህ ጋር በመጫን ማግኘት ይችላሉ
ሶልጌት ትራቭል የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ዘዴን በመተግበር የአየር ትኬት ሽያጭ አገልግሎት ለመስጠት ኢትዮጵያ ውስጥ በረራ ካላቸው 10 አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኤመሬትስ (Emirate)፣ ሉፍታንዛ (Lufthansa)፣ ኳታር ኤርዌይስ (Qatar Airways)፣ ተርኪሽ ኤርላይንስ (Turkish Airlines)፣ ኬንያን ኤርዌይስ (Kenyan Airways)፣ ፍላይ ዱባይ (Fly Dubai)፣ ገልፍ ኤር (Gulf Air)፣ ኢጅፕትኤር (EgyptAir) እና ሳኡዲያ (Saudia) አየር መንገዶች ጋር እየሠራ በመሆኑ አገልግሎቱን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርገው ኃላፊዎቹ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶልጌት ትራቭል ጋር የፈጸመው ስምምነት የባንኩን ደንበኞች የዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት አካል ሲሆን፥ ባንኩ ከውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት፣ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ ከመልቲቾይስ ኢትዮጵያ፣ ከክፍለ ከተሞች፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎች የመንግሥትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር በተለያዩ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ዘዴዎች አገልግሎቱን እያቀረበ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
September 14, 2020 at 2:26 am #15832AnonymousInactiveበኢትዮጵያ አዲስ የ200 ብር ኖት ይፋ ተደረገ፤ ነባሮቹ የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ኖቶችም ተቀይረዋል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ዓይነቶች (የገንዘብ ኖቶች) ሙሉ ለሙሉ መለውጧን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ። በተጨማሪም አዲስ የ200 ብር ኖት መቅረቡንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። እንዲሁም የ5 ብር ገንዘብ ኖት ባለበት ቀጥሎ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሣንቲም እንደሚቀየርም ተገልጿል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፥ ነባሮቹን የገንዘብ ኖቶች በመተካት ለግብይት የሚሆን አዲስ የገንዘብ ኖት መጠቀም እንደምትጀምር መስከረም ሦስት ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ተደርጓል።
እነዚህ አዲስ የገንዘብ ኖቶች ለሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍን፣ ሙስናን እና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠርና ለመቀልበስ ይረዳሉ ብለዋል።
በአዲሶቹ የገንዘብ ኖቶች ላይ የተካተቱት ምስጢራዊ ምልክቶችና መለያዎች የገንዘብ ኖቶቹን አመሳስሎ ለማተም የሚደረጉ ሕገ ወጥ ጥረቶችንም ለማስቀረት እንደሚያግዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት (እንግሊዝኛ) እንዲህ ይነበባል፦
“Ethiopia today unveils new Birr notes for 10, 50 & 100 denominations, with introduction of a new Birr 200 note. The new notes will curb financing of illegal activities; corruption & contraband. Enhanced security features on the new notes will also cease counterfeit production.”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የገንዘብ (የብር) ኖቶች ለውጡን ተከትሎ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ዝግጅት ተደርጓል። በተለያዩ ጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያ የብር ኖቶች ክምችት መኖሩን የጠቀሱት ዶ/ር ይናገር፥ ለብር ለውጡ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል። ለዚህም ከጸጥታና የደህንነት አካላት ጋር በመነጋገር የመቆጣጠርና የማምከን ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል። በተለይ በድንበር አካባቢ የሚገኙ ባንኮችም በብር ኖቶች ለውጡ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እንዳይጋለጡ ጥብቅ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
ዶ/ር ይናገር የብር ኖቶች ቅያሬውን ለማከናወን ማንኛውም ግለሰብ የብር ኖቶቹን ራሱ በባንክ መቀየር ሲገባው፥ በሌላ ግለሰብ (በውክልና) የገንዘብ ኖት ለውጥ ማከናወን የማይችል መሆኑንም ተናግረዋል።
በ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን የብር ኖት መታተሙንና የመጠባበቂያ ክምችት እንዲኖር ተጨማሪ የብር ኖቶች እየታተሙ መሆኑን ዶ/ር ይናገር አመልክተዋል። ባለፉት ጥቂት ወራት አዳዲሶቹን የብር ኖቶች ወደ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የማጓጓዝ ሥራ መሠራቱንና አሮጌውን ገንዘብ መቀየር የሚያስችል በቂ ክምችት እንዳለ ገልጸዋል።
ካፒታል ኢትዮጵያ ሳምንታዊ ጋዜጣ በግንቦት ወር 2012 ዓም እንደዘገበው፥ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር (EBA) በነበሩት የብር ኖቶች ላይ ለውጥ እንዲደረግ መጠየቁን ገልጾ ነበር። ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ በብር ኖቶች መበላሸት ምክንያት ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ ከባንክ አገልግሎት ውጪ እንደሆነ በመጥቀስ፥ የሚታየውን የብር ኖቶች ከገበያ/ ከአገልግሎት ውጪ መሆን ችግር ለመቅረፍ የብር ኖቶችን መቀየር አስፈላጊነት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ (NBE) አስገንዝቦ ነበር።
ሌሎች ዜናዎች፦
- የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስገነባቸው ቤቶች አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ገለጸ
- ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ በ3 ቢሊዮን ብር ለሚያስገነባው ገርጂ የመኖሪያ መንደር ከተቋራጮች ጋር ስምምነት ተፈራረመ
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበረራ ትኬትን በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ዘዴ አማካኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ስምምነት አደረገ
- በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቱሪስት ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ሄሎ ታክሲ በተባለ ድርጅት አማካኝነት በይፋ ተመርቀው ሥራ ጀመሩ
- ግማሽ ቢሊዮን ብር የተገነባው ኃይሌ ሪዞርት አዳማ ተመረቀ፤ ተቃጥለው የነበሩ የሻሸመኔ እና ዝዋይ የኃይሌ ሪዞርቶችና ሆቴሎች ወደሥራ እንደሚመለሱም ተገለጸ
September 20, 2020 at 11:04 pm #15954AnonymousInactiveወልቂጤ ከተማ ውስጥ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው ባሮክ ሆቴል ተመርቆ ሥራ ጀመረ
የዞኑ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳዳር አስታውቋል።ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – በወልቂጤ ከተማ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ባሮክ ሆቴል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የጉራጌ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ዘግቧል። ባሮክ ሆቴል ባዘጋጀው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች ተገኘተዋል።
በሆቴሉ ምረቃዉ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ለአንድ ከተማ እድገትና ለዉጥ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ሚና የጎላ መሆኑን በማስገንዘብ እንደተናገሩት፥ የዞኑ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ከመቼዉም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ አጽንኦት ተሰጥቶ እየተሠራ ነዉ።
በተለይም ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የኢንቨስትመንት ልማት ሥራዎችን ለማሳደግ እንደ ክፍተት የሚስተዋሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በተደረገዉ እንቅስቃሴ አሁን ላይ ባለሀብቶች በዞኑ ኢንቨስት እያደረጉ ይገኛል።
ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሂደቶችም መኖራቸዉንም አቶ መሀመድ ጠቁመዉ፥ በቀጣይ በዘላቂነት የዞኑ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ከባለሀብቶች ጋር እየተሠራ ያለዉን ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመግለጽ፤ ባለሀብቶች በዞኑ ባሉ የልማት አማራጮች እንዲሰማሩ አስፈላጊዉን ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ገብረመስቀል፥ በበኩላቸዉ ከዚህ ቀደም በከተማዉ ኢንቨስት ለማድረግ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ባለሀብቶች በማበረታታት ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሠራ ነዉ ብለዋል።
ከተማዉን ለማልማት የሚመጡ ባለሀብቶች አስፈላጊዉን ድጋፍ በማድረግ ከዞኑ መንግሥት ጋር በመሆን እየተሠራ መሆኑም በመጠቆም፤ በአሁኑ ሰዓት በሆቴል ዘርፍ የተሰማራዉን ባርክ ሆቴል አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ለሌሎች ባለሀብቶች የሚያበረታታ መሆኑም አቶ እንዳለ ጠቅሰዋል።
ሌሎች በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር በተገቢው መንገድ ተቀብሎ እንደሚያስተናግዳቸው በመግለጽ፥ “ኑ! ተደጋግፈን አብረን እንልማ” የሚል ጥሪ አሰተላልፈዋል።
የባሮክ ሆቴል ባለቤት አቶ አሰፋ በቀለ በበኩላቸው ሆቴሉ ተጠናቆ አገልግሎት መሰጠት በመጀመሩ ደሰተኛ መሆናቸዉም አስረድተዋል። ሆቴሉ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 50 ሚሊየን ብር እንደሚፈጅም ተናግረዉ በሆቴሉም ከ50 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርም አስረድተዋል ።
ባሮክ ሆቴል 39 አልጋዎችና አንድ የስብሰባ አዳራሽ ያካተተ መሆኑን የገለጹት የሆቴሉ ባለቤት አቶ አሰፋ፥ በአካባቢያቸዉ በማልማታቸዉ ደስተኛ መሆናቸዉ እንዲሁም ለተደረገላቸዉ ድጋፍ የከተማ አስተዳደሩና የዞኑ መንግሥት አመስግነዋል።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
- ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.