Home › Forums › Semonegna Stories › ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Tagged: አቢሲንያ ባንክ, የኢትዮጵያ አየር መንገድ, የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን, ዳሸን ባንክ, ፀሐይ ባንክ
- This topic has 55 replies, 3 voices, and was last updated 8 months, 1 week ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 13, 2020 at 2:04 am #16325AnonymousInactive
ኩታ ገጠም እርሻ ― ከዕቅድ በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ያስቻለ ተሞክሮ
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ ወቅታዊ መረጃ እንደሚያመለክተው፥ በዘንድሮው የምርት ዘመን በተለያዩ አካባቢዎች የተተገበረው ኩታ ገጠም እርሻ በሰብል ለመሸፈን ከታቀደው በላይ መሬት መሸፈን ተችሏል፤ ኩታ ገጠም እርሻ በመጠቀም ከሚታረሰው መሬት የሚገኘው ምርትም እያደገ ነው።
በሚኒስቴሩ የሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደሚሉት፥ በተያዘው የምርት ዘመን ኩታ ገጠም እርሻ በ300 ወረዳዎች፣ በ31 ክላስተሮች ላይ አየተካሄደ ነው። ከተገኙ ውጤታማ ተሞክሮዎችም በመነሳት ክልሎች ክላስተሮችን የጨመሩበት ሁኔታ አለ።
በምርት ዘመኑ ኩታ ገጠም እርሻ ለመጠቀም ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስ ታቅዶ እንደነበረ ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፥ ክልሎች የራሳቸውን ሰብሎችና ክላስተሮች የጨመሩበት ሁኔታ በመፈጠሩ፥ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ በላይ 3.79 ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል። በሰብል ዓይነትም እንደ ክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ ተጨማሪ ሰብል እና አትክልቶች ተካተዋል።
በክላስተር ደረጃ ይህን ያህል ምርት ይገኛል ተብሎ የተያዘ ዕቅድ የለም ያሉት አቶ ኢሳያስ፥ በሀገር-አቀፍ ደረጃ በመኽር እርሻ በአጠቃላይ 12.85 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ግብ መያዙን አመልክተዋል።
በክላስተር ማረስ (ኩታ ገጠም እርሻ ለመጠቀም) የዛሬ 10 ዓመት እንደተጀመረ አቶ ኢሳያስ አስታውሰው፥ ሥራው በአግባቡ ከገበያ ጋር የተሳሰረ ባለመሆኑ ውጤታማ መሆን ሳይችል መቅረቱን ያስታውሳሉ። አሁን የተጀመረው የክላስተር አሠራር ገበያ-መር መሆኑን ጠቅሰው፥ የገበያው ሁኔታ በሁለት መልኩ እንደሚታይም አመልክተዋል።
አንደኛው የሚያመርተው የሰብል ዓይነት በአካባቢው በቂ ገበያ አለው ወይ ለሚለው ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ከአካባቢው ባለፈ ምርቱ በገበያ ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን ተፈላጊነት ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉ ያብራራሉ። ከዚህም ባለፈው ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን፣ የገቢ ምርት መተካትንና የመሳሰሉትን ሀገራዊ የመንግሥት መርሀግብሮች ታሳቢ ተደርጎ እንደሚሠራም አብራርተዋል።
ኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነቱ እየጨመረ መምጣቱን ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፥ የጤፍ ምርታማነት ከአራት ዓመት በፊት ከነበረበት በሄክታር 16.64 ኩንታል ወደ 18.5 ኩንታል፣ ስንዴ ከ26.7 ወደ 29.71 ኩንታል፣ በቆሎ ከ36.75 ኩንታል ወደ 42.39 ኩንታል ማደጉን አስታወቀዋል። የምርት እድገቱ በኩታ ገጠም እርሻ የመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኩታ ገጠም እርሻ ገበያ-መር በሚል ከሁለት ዓመት በፊት ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በ178 ወረዳዎች መጀመሩን አስታውሰው፥ እርሻው ሁለት ሚሊዮን ሄክታር አካባቢ በሚጠጋ መሬት ላይ መጀመሩን፤ በወቅቱም በክላስተር ደረጃ በሄክታር በአማካይ 35 ኩንታል ማግኘት መቻሉን ጠቁመዋል። ከዚያ በፊት በአማካይ ይገኝ የነበረው 27 ኩንታል እንደነበር ያስታውሳሉ።
አሁን ደግሞ የአምስት ዓመት ዕቅድ 500 ወረዳዎችን ያካተተ 31 ክላስተሮችን የያዘ የኩታ ገጠም እርሻ ለማካሄድ መታቀዱን አቶ ኢሳያስ ጠቅሰው፥ የተገኙ ውጤታማ ተሞክሮዎችን በማየት የእርሻ መሬት መጨመሩን አመልክተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው፥ ኩታ ገጠም እርሻ ሲባል እንደ ስሙ የተቀራራበ እርሻ ማለት ሳይሆን ብዙ ሰው መሬቱን አንድ ላይ በተመሳሳይ ሰብል አልርቶ፣ በተመሳሳይ ግብዓት ተጠቅሞ፣ ተመሳሳይ እንክብካቤ አድርጎ የተሻለ ገቢ እና ምርት ማግኘት የሚችልበት አሠራር መሆኑን ይናገራሉ።
ኩታ ገጠም እርሻ የማምረት አቅምን ተመሳሳይ በማድረግ ምርታማነት እንዲያድግ የሚደረግበት መሆኑን ጠቅሰው፥ አርሶ አደሮች የኩታ ገጠም እርሻን ከምርታማነት መጨመርና ገበያውን በጋራ ከማግኘት አኳያ በመመልከት ጥቅሙን እየተረዱት መምጣቸውን ይናገራሉ። ይህን ተከትሎም በፍላጎታቸው መሬታቸውን በኩታ ገጠም ማልማት ውስጥ እያስገቡ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ዶ/ር ማንደፍሮ ሁሉም ቦታ በእዚህ ደረጃ ከሠራ ግብርናው ወደ ኮሜርሻል እርሻ እየተቀየረ እንደሚሄድ እምነታቸው ነው።
ዶ/ር ማንደፍሮ የኩታ ገጠም እርሻው ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ለዚህም የኮንትራት እርሻ ፖሊሲ በግብርና ሚኒስቴር ደረጃ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፥ ፖሊሲው አንዴ መገምገሙንና ቶሎ ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይናገራሉ።
መሬትን በጋራ አድርጎ የማምረቱ እና የመከፋፈሉ ሥራ እስከአሁን በመተማመን ላይ ተመሥርቶ ሲሠራ መቆየቱን አስታውቀው፥ ሁሉም ሰው ለጥቅምም ለግዴታም ተገዢ የሚሆንበት ሕግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። “አንዱ ከዚያ ውስጥ ቢያፈነግጥ በሕግ ማዕቀፍ ልትከሰውና ልታሸንፈው የሚያስችል ደንብና መመሪያ መኖር አለበት” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የጋራ ተጠያቂነት መኖር እንዳለበትም ገልጸዋል።
ማሳ በዘር ከተሸፈነ በኋላ አላርስም፣ አልኮተኩትም… የሚል ቢያጋጥም ችግሩን ለመፍታት የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፥ በዚህ ፖሊሲ ላይ በቀጣይም ውይይት ይካሄድበታል ይላሉ። በዘርፉ ባለሙያ ብቻ ሳይሆን የሕግ ሰዎችና ሌሎች ተዋንያንም እንደሚሳተፉበትም አመልክተዋል።
ግብርናውን በማዘመን በኩል በመንግሥት ዋስትና ለአርሶ አደሮች ትራክተሮች የሚቀርቡበት ሁኔታ እንዳለ ሚኒስትር ዴኤታ ጠቅሰው፥ ይህም ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልገው ነው ያስገነዘቡት። ለትራክተር የወጣው ወጪ ሳይከፈል ከቀረ መንግሥት ‘እኔ እከፍላለሁ’ እያለ ለአርሶ አደሩ ትራክተር እያቀረበ መሆኑን አስታውቀው፥ ይህ ሥራ ተግዳሮት እንዳይገጥመው ለማድረግ አሁን የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
“አርሶ አደሮች በጋራ ሆነው አንድ ትራክተር መግዛት እንዲችሉ፤ አንድም ሰው አቅሙ ካለው መግዛት እንዲችል የሕግ ማዕቀፍ ይፈልጋል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ “እነዚህን በደንብና በመመሪያ ካጠናከርናቸው ዘላቂነት ያለው ለውጥ ሊታይ ይችላል” ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
November 18, 2020 at 2:42 am #16733AnonymousInactiveበተለያዩ ወንጀል ተግባራት ውስጥ ስለመሳተፋቸው ምርመራ ለመጀመር የሚያስችል በቂ ማስረጃ የተገኘባቸው የህወሓት ድርጅቶች ሀብቶቻቸው ታገዱ
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የዘር-ተኮር ጥቃት እና የሽብር ድርጊት እንዲፈጸም የገንዘብ ድጋፍ በማቅረብ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ከሚንቀሳቀሰው የትህነት/ ህወሓት ኃይል ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በመመሳጠር እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የተሳተፉ ስለመሆናቸው እና በግብር-ስወራ እና የሙስና ወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ስለመሳተፋቸው ምርመራ ለመጀመር የሚያበቃ በቂ ማስረጃ የተገኘባቸውን ከታች ስማቸው የተጠቀሱትን ድርጅቶች የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በባንክ ያላቸውን ገንዘብ ጨምሮ ከህዳር 07 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እንዲታገዱ አድርጓል።
እግዱ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ድርጅቶቹ ሀብታቸውን ለማሸሽ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆኑ በቂ ማስረጃ የቀረበ በመሆኑ ንበረቶቹ ሳይሸሹ ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ውሳኔ እስኪሰጥባቸው ማቆየት ተገቢ መሆኑ ስለታመነበት ነው ሲል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አሳውቋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል የመመርመር እና ሀብትን የማስመለስ ሥራውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ የታገዱት ንብረቶች እንዳይጎዱ እና እንዳይባክኑ ጠብቆ የሚያቆይ የንብረት አስተዳዳሪ የሚሾም ሲሆን፥ አስተዳዳሪው ሥራውን ተቀብሎ ማስተዳደር እስኪጀምር ድረስ የድርጅቶቹ አስተዳዳሪዎች ንበረቱን በሚገባ የመጠበቅ ኃላፊነት እንደለባቸው አስታውቋል።
በቀጣይ የምርመራ እና ክስ ሂደቱን ተከታትሎ ለሕዝቡ እንደሚያሳውቅም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመግለጫው አትቷል። ሀብታቸው የታገደባቸው የህወሓት ድርጅቶች ከዚህ በታች ስማቸው የተዘረዘሩት ናቸው።
- ሱር ኮንስትራክሽን
- ጉና የንግድ ሥራዎች ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ትራንስ ኢትዮጵያ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ሰላም የሕዝብ ማመላለሻ አክሲዮን ማኅበር
- ሜጋ ማተሚያ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ኤፈርት ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ኤፈርት ኤሌክትሪካል ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ኤፈርት ዲዛይን እና ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ኢዛና ማዕድን ልማት ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ቬሎሲቲ አፖራልዝ ካምፓኒስ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- መሰቦ ቢውልዲንግ ማቴሪያል ፕሮዳክሽን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ሳባ ዳይሜንሺናል ስቶን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ
- ሼባ ታነሪ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ኤ.ፒ ኤፍ
- ሜጋ ኔት ኮርፖሬሽን
- እክስፕረስ ትራንዚት ሰርቪስ
- ደሳለኝ ካትሪናሪ
- ሼባ ታነሪ ፋክተሪ አክሲዮን ማኅበር
- ህይወት አግሪካልቸር መካናይዜሽን
- ህይወት እርሻ ሜካናይዜሽን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- አልመዳ ጋርመንት ፋክተሪ
- መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ
- ደደቢት ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማኅበር
- አዲስ ፋርማሲቲካልስ ፕሮዳክሽን
- ትግራይ ዴቨሎፕመንት ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ስታር ፓርማሲቲካልስ ኢፖርተርስ
- ሳባ እምነበረድ አክሲዮን ማኅበር
- አድዋ ፍሎር ፋክተሪ
- ትካል እግሪ ምትካል/ ትግራይ/ ት.እ.ም.ት/
- ብሩህ ተስፋ ፕላስቲክ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ደሳለኝ የእንስሳ መድኃኒት አስመጪና አከፋፋይ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ማይጨውፓርትክል ቦርድ ፋክተሪ
ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
December 10, 2020 at 5:22 am #16950AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡታጅራ ከተማ ወስጥ ያስገነባውን የባንኩ ዲስትሪክት ህንፃ ሳይጠናቀቅ በመተው
ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዛወር መደረጉ አግባብነት የሌለው ነው ተባለየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጉራጌ ማኅበረሰብን ነዋሪዎችን እና አጎራባች ከተሞችን ታሳቢ በማድረግ በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የባንኩን ዲስትሪክት ለመክፈት ከውሳኔ ደረሶ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከጫፍ ሲደርስ ዲስትሪክቱን ወደሌላ አካባቢ ማዛወሩ ተገቢ አለመሆኑ ተገለፀ።
የጉራጌ ማኅበረሰብ ከጥንት ጀምሮ እሴቱ የሆነውን የቁጠባ ባህል ፍላጎት እና የልማት ተነሳሽነት ተከትሎ የቡታጅራ ከተማ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከተማዋ መሀከል ላይ ዋናውን መስመር ተከትሎ ባንኩ ቅርንጫፍ እንዲከፍት ቦታውን አመቻችቶ ባቀረበው መሠረት ቅርንጫፉን ከፍቶ አሁን አራት አድርሷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡታጅራ ከተማ ቅርንጫፍ ባለበት ስፍራ ለጉራጌ ማኅበረሰብ በዞኑ ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች እና ለአጎራባች ከተሞች የሚያገለግል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲስትሪክት ለመክፈት ከውሳኔ በመድረስ፥ ህንፃም ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከጫፍ ባደረሰበት ሰዓት ማዕከሉን ወደ ሌላ አካባቢ ማዛወሩ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ማኅበረሰቡ ቅሬታውን እያቀረበ ይገኛል።
የባንኩ ማኔጅመንት ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መሠረት ለጉራጌ እና ለአካባቢው ከተሞች በማዕከልነት የባንኩ ዲስትሪክት አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበት ውሳኔ በማሳለፍ በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የጀመረውን የዲስትሪክት መቀመጫነት ወደ ሌላ አካባቢ ማዛወሩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የማይመጥን ውሳኔ መሆኑን ማኅበረሰቡ ያነሳል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአመራር (ማኔጅመንት) አባላትም የመጀመሪያ ውሳኔያቸውን በማጽናት በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የባንኩን ዲስትሪክት በማስቀጠል ባለበት የማያጸኑ ከሆነ የዞኑን ማኅበረሰብ በባንኩ ላይ ያለውን ደንበኝነት የሚሸረሽርና ደንበኝነታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርም ከግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ መሆኑን ማኅበረሰቡ ይገልፃል።
ባንኩ የራሱ የሆነ አሠራር አለው በማንኛውም ዓይነት በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት ውሳኔውን በመሻር ዲስትሪክቱን ማዛወሩ ቅቡልነት የሌለው አሠራር መሆኑን በማስገንዘብ፤ ባንኩ በመጀመሪያው (በቀደመው) ወሳኔው ፀንቶ በተጀመረበት ስፍራ ማስቀጠል እንደሚገባም በመግለጽ ማኅበረሰቡ ያሳስባል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ የጉራጌና የአካባቢዋ ማኅበረሰብም የኢትዮጵያ አንድ አካል ነው፤ ልማትም ይሻል፤ የዚህን ማኅበረሰብ ስሜት ከግምት ውስጥ ባለማስገባት የተጀመረና ለማጠናቀቅ ከጫፍ የደረሰን ልማት ማዛወር በምንም ዓይነት አስተሳሰብም ሆነ አመለካከት ተቀባይነት የሌለው ውሳኔ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ሲል ማኅበረሰቡ ይገልጻል።
May 24, 2021 at 10:33 pm #19442AnonymousInactiveቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አ ገልግሎት ምረቃ በተመለከተ የቀረበ ጋዜጣዊ መግለጫ ― ኢትዮቴሌኮም
ኩባንያችን “ቴሌብር” የተሰኘ፣ ለማኅበረሰባችን ምቹ እና ሁሉን አካታች የሆነ የገንዘብ ማስተላለፊያ እና የመገበያያ ዘዴ የሆነውን፣ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎቱን (mobile money service) ለመጀመር አስፈላጊ ዝግጅቶችን አጠናቆ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም አገልግሎቱ መጀመሩን ሲያበስር በታላቅ ደስታ ነው!
በሀገራችን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውና በኩባንያችን የሚሰጥ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ከተደራሽነትና ለአጠቃቀም እጅግ ቀላል ከመሆኑ አኳያ ለማኅበረሰባችን የብስራት ዜና ሲሆን፤ ሕዝባችንን ለማገልገል ካለን ጽኑ ፍላጎት አንጻር ለኩባንያችን ትልቅ ስኬት ነው።
የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በሀገራችን ያለውን የፋይናንስ አካታችነት ክፍተት በማጥበብ፣ ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣንና ቀላል በሆነ ዘዴ እንዲሁም በአነስተኛ የግብይት ወጪ የተሻለ የፋይናንስ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታን ያመቻቻል። የፋይናንስ አካታችነት /financial inclusion/ ሁሉንም የፋይናንስ አገልግሎቶች ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ ፅንሰ ሀሳብ ሲሆን፤ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ዓይነተኛ መፍትሔ ነው። ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ጤናማ የገንዘብ ፍሰት ከመፍጠሩም ባሻገር፥ ቁጠባን በማሳደግ፣ ድህነትን በመቀነስ፣ ሥራ ፈጣሪነትንና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት እንዲሁም ገንዘብ የሚታተምበትን ወጪ በመቀነስና ኢኮኖሚን በማሳደግ የሕዝባችንን ሁለንተናዊ እድገትና ተጠቃሚነትን ያሳድጋል።
ኩባንያችን ለቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ የዘረጋውን መጠነ ሰፊ መሠረተ ልማት በመጠቀም ወደ ደንበኞቹ ቅርብ ከመሆኑ አኳያ ለኅብረተሰባችን ተጨማሪ እና ከፍተኛ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር አገልግሎት ማስጀመሩ በሀገራችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም ለኅብረተሰባችን የዕለት ተዕለት ኑሮ መሻሻል ጉልህ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።
ኩባንያችን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትና ተያያዥ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ለውድ ደንበኞቹና ለሁሉም ማኅበረሰብ ለማቅረብ የፍቃድ ጥያቄውን ካቀረበበት ወቅት ጀምሮ ሰፊ የዝግጅት ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን፤ በተለይም በኢንዱስትሪው የተመረጠና የተሻለ የሞባይል ገንዘብ ቴክኖሎጂን ሥራ ላይ ለማዋል፣ ተገቢ ፖሊሲዎችን እና አሠራሮችን ለመተግበር፣ ሰፊውን ወኪል ኔትወርክ (ngent network) ለማንቀሳቀስ እና ከቴሌኮም እና ከፋይናንስ ኢንዱስትሪዎች የተሻሉ ልምዶችን በመቀመር በቂ ዝግጅት በማድረግ በዋናነት የባንክ አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችና በገጠር የሚገኙ ዜጎችን የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ጥረቶችን በማድረግ ለዛሬው ስኬት በቅቷል።
አገልግሎቱን ለማኅበረሰባችን በማቅረብ ሂደት ውስጥ በርካታ ተቋማት የሚሳተፉ ሲሆን፤ በተለይም በሀገራችን ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፋይናንስ እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች እንዲሁም አገልግሎቱን ለደንበኞቻችን ቅርብ ለማድረግ የሚያስችሉ ከኩባንያችን ጋር ልዩ ውል ያላቸው ዋና ወኪሎች /master agents/ እና በእነዚህ ዋና ወኪሎች የተመለመሉ እስካሁን ባለው ከ1,600 በላይ ወኪሎች /agents/ ዋነኛ ተሳታፊዎች ናቸው። የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ የወኪሎችን ቁጥር በየወሩ በማሳደግ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ15ሺህ በላይ ለማድረስ እየተሠራ ይገኛል።
ቴሌብርን በመጠቀም ገንዘብ ከማስተላለፍ፣ ከመቀበልና ከመክፈል በተጨማሪ ግብይት ለመፈጸም የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ከተለያዩ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር አብረን እየሠራን ሲሆን፤ ለአብነት ያህል ውሀና ፍሳሽ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ገቢዎች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ ነዳጅ ማደያዎች፣ እርዳታ ድርጅቶች፣ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ የህትመት ሚዲያዎች እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚገኙበት ሲሆን አገልግሎቱ ክፍያ መቀበልና መፈጸም ያስችላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ደንበኞቻችን ከውጭ ሀገር የሚላክላቸውን ገንዘብ ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን በመጠቀም በቀላሉና በአነስተኛ ወጪ ለመቀበል የሚያስችላቸው አገልግሎት ለማስጀመር ከዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር የኢንቴግሬሽን ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፤ ኩባንያችን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ፈቃድ ካገኘ አጭር ጊዜ ከመሆኑ አኳያ ከድርጅቶቹ ጋር ያሉ ሂደቶችና ፎርማሊቲዎችን አጠናቆ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አገልግሎቱን መስጠት ይጀምራል።
በቀጣይም ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለማኅበረሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸው እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የሞባይል አነስተኛ ብድር፣ የቁጠባ አገልግሎትና ተያያዥ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበርና አስፈላጊ ቅደመ ሁኔታዎችን በማሟላት የሚያስጀምር ይሆናል።
የቴሌብር አገልግሎት በሀገራችን የፋይናንስ አገልግሎት ላይ የሚታየውን ውስንነት ወይም የፋይናንስ አካታችነት ክፍተት በማጥበብ ሰፊ ሚና የሚጫወት ሲሆን አሁን ላይ 35% ብቻ የሆነውን የፋይናንስ አካታችነት ወደ 60% ለማሳደግ ግብ አስቀምጠን እየሠራን ሲሆን በተለይም ከኮቪድ-19 ጋር በተገናኘ የገንዘብ ንክኪን ለመቀነስ የቴሌብር አገልግሎት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች ያሉት አገልግሎት ሲሆን በተለይም የሀገራችንን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ጉልህ ሚና ለመጫወት በዘርፉ ላይ ድርሻና ሚና ያላቸውን አካላት በማሳተፍ ተቀናጅቶ በመሥራት በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ከ40% እስከ 50% ያህሉን ጠቅላላ የሀገራችን የኢኮኖሚ ግብይትና የገንዘብ ፍሰት በቴሌብር እንዲከናወን አቅደን እየሠራን እንገኛለን።
በዚህ አጋጣሚ ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የበለጠ ፍሬ እንዲያፈራና የሀገራችንን የዲጅታል ፋይናንስ ፍላጎት ለማሟላት እና ዲጅታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት ከግብ ለማድረስ በኢኮሲስተሙ ሚና ያላቸው ባለድርሻ አካላት በተለይም የፋይናንስ ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶችና አገልግሎት ሰጭ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆናችሁ ተቋማት አብራችሁን እንድትሠሩ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን።
July 6, 2021 at 10:51 pm #19844AnonymousInactiveአዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ. በ2020/21 የሂሣብ ዓመት ብር 5.58 ቢሊዮን ዓመታዊ ትርፍ አስመዘገበ
አዲስ አበባ (አዋሽ ባንክ) – ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የግል ባንኮች የመሪነት ስፍራውን ይዞ የቆየው አዋሽ ባንክ አሁን በተገባደደው የሂሣብ ዓመትም በዋና ዋና የባንኪንግ ዘርፎች የመሪነት ስፍራውን ይዞ መቀጠሉን ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው ዓመታዊ የበጀት መዝጊያ ስብሰባ ላይ አስታውቋል።
ባንኩ በተጠናቀቀው ሂሣብ ዓመት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የተቀማጭ ሂሣብ መጠን በማስመዝገብ በባንኩም ሆነ በግል ባንኮች ታሪክ የመጀመሪያው የሆነውን ውጤት አስመዝግቧል። የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ሂሣብ ኤልሲ ማርጅንን (letter of credit margin) ጨምሮ ብር 107.7 ቢሊዮን ሲሆን፣ ይህም አሀዝ ከባለፈው ሂሣብ ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የብር 33.8 ቢሊዮን /የ46 በመቶ/ ዕድገት አሣይቷል።
አዋሽ ባንክ ባሣለፍነው የሂሣብ ዓመት 100 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቶ ለአገልግሎት ማብቃት የቻለ ሲሆን፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የተቀማጭ ሂሣብ ደንበኞችን በማፍራት ጠቅላላ የተቀማጭ ሂሣብ ደንበኞቹን ከ5 ሚሊዮን በላይ ማድረስ ችሏል። የቅርንጫፎች መስፋፋት ሕብረተሰባችን በየአካባቢው የባንክ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ከማስቻሉም በተጨማሪ አዳዲስ ደንበኞች የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። አዋሽ ባንክ ሕብረተሰቡ በቦታና በጊዜ ሳይገደብ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የኤቲኤም (ATM)፣ የሞባይል እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባደረገው ጥረት እ.ኤ.አ. ሰኔ 2021 መጨረሻ ላይ 4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አድርጓል። ይህም መንግሥት የፋይናንስ አካታችነትን እና ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ብርቱ ጥረት አጋዥ እንደሆነ ይታመናል።
አዋሽ ባንክ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው ብድር መጠን በ2020/21 የሂሣብ ዓመት መጨረሻ ላይ የብር 30 ቢሊዮን /የ53 በመቶ/ እድገት በማሣየት ብር 87.1 ቢሊዮን ደርሷል።
በውጭ ምንዛሪ ረገድም በ2020/21 የሂሣብ ዓመት ከተለያዩ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ከ906 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማግኘት የቻለ ሲሆን፤ ይህም አሀዝ ከአምናው ተመሣሣይ ጊዜ አንጻር የ37 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ አሳይቷል። ለዚህም ዋና ዋና ምክንያቶች የአለም ኢኮኖሚ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ ማገገም፣ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማደግ እና ባንኩ የወሰዳቸው የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎች ናቸው።
አዋሽ ባንክ ከዛሬ 5 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ታሪክ ከብር 1 ቢሊዮን በላይ ያልተጣራ ትርፍ አስመዝግቦ ታሪክ እንደሠራው ሁሉ ባሳለፍነው በጀት ዓመትም ከብር 5.58 ቢሊዮን በላይ ያልተጣራ ትርፍ በማስመዝገብ ሌላ ታሪክ ሠርቷል። ለዚህም ዋናው ምክንያት የባንኩ ገቢ አምና ከነበረበት ከብር 10.2 ቢሊÄን ወደ ብር 13.7 ቢሊዮን ማደጉ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ባንኩ በተቀማጭ ሂሣብ፣ በብድር እና በትርፋማነት ብቻ ሳይሆን በተከፈለ ካፒታል መጠኑም የመሪነት ሥፍራውን እንደያዘ ቀጥሏል። የአዋሽ ባንክ የተከፈለ ካፒታል በዓመቱ በብር 2.23 ቢሊዮን ያደገ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. ሰኔ 2021 መጨረሻ ላይ ብር 8.2 ቢሊዮን ደርሷል። ይህ መጠን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሁሉም ነባር የግል ባንኮች ለወደፊቱ በ5 ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲደርሱበት ካስቀመጠው የ5 ቢሊዮን ብር መጠን በእጅጉ የላቀ ነው። አዋሽ ባንክ በአሁኑ ጊዜ በ566 ቅርንጫፎች እና ከ12 ሺህ በላይ በሆኑ ሠራተኞች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት የሚታወቀው አዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ. በ2020/21 የሂሣብ ዓመት በተለያዩ የማኅበረሰብ ልማት ሥራዎች እና በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከብር 30 ሚሊዮን በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።
ምንጭ፦ awashbank.com
July 12, 2021 at 3:51 am #19905AnonymousInactiveአቢሲንያ ባንክ እጅግ በተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ስም ቅርንጫፍ ከፈተ
አዳዲስ ቅርንጫፎችን በሀገር ባለውለታዎች ስም እየሰየመ የሚከፍተው አቢሲንያ ባንክ፥ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ዕንቁዎች በመጀመሪያ ረድፍ ላይ በተቀመጡትና ስማቸውን በወርቅ ቀለም ባጻፉት ታላቁ የኪነ ጥበብ ሊቅ፥ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ስም ቅርንጫፉን ከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በአንኮበር ከተማ፣ ከአቶ ተክሌ ማሞና ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ጥቅምት 13 ቀን፥ 1925 ዓ.ም. ተወለዱ። ዘመኑ ፋሺስት ጣልያን ሀገራችንን በግፍ የወረረበት ዘመን በመሆኑ፣ አፈወርቅ ተክሌ በጨቅላ እድሜያቸው በሰው፣ በንብረትና ባህል ላይ የደረሰው ጥፋት በአእምሮአቸው ታትሞ ቀረ። ለዛም ይመስላል በ1940 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ታላቋ ብሪታንያ፥ ለንደን ተጉዘው፣ የሥዕልን ጥበብ ተምረው ከተመለሱ በኋላ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላት እየተዘዋወሩ ታሪክን፣ የብሔረሰቦችን ባህልና ወግ ሲያጠኑ የከረሙት።
በ1944 ዓ.ም. በሃያ ሁለት ዓመት እድሜአቸው የመጀመሪያ የሆነው የሥዕል አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቀረቡ። ከአውደ ርዕይ ባገኙት ገቢ፣ ወደተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በመዘዋወር የሥዕል ጥበብን ቀሰሙ። የኢትዮጵያ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትን አጠኑ። ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በኢትዮጵያ የመስታወት ስዕልን (stained glass art) ያስተዋወቁ ቀዳሚው የጥበብ ሰው ናቸው። በዚህ ጥበብ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን መስኮቶች በመሥታወት ሥዕላት አስጊጠዋል። በሐረር ከተማ የአፄ ኃይለ ሥላሴ አባት የራስ መኮንን ሐውልትን ገንብተዋል።
ሥራዎቻቸው በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ እጅግ ዝናን ያተረፉ በመሆናቸው በርካታ ሽልማቶችን አስገኝተውላቸዋል። በ1971 ዓ.ም. የአልጀርስ የጥበብ ፌስቲቫል የወርቅ ሽልማት፤ በፈረንሳይ በተደረገው የሥዕል ውድድር አንደኛ በመውጣት የኖቤል የሎሬት ክብር መዓረግ በማግኘት ኢትዮጵያን አስጠርተዋል። በ2000 ዓ.ም. የዓለም ሎሬትነት ክብርን በዋሽንግተን ዲሲ በተደረው 27ኛው ዓለም አቀፍ የጥበብና መገናኛ ብዙኃን የሚሊንየም ኮንግረስ (27th International Millennium Congress on the Arts and Communication) ከአሜሪካ ባዬግራፊካል ኢንስቲትዩት ተቀዳጅተዋል፤ በ2004 ዓ.ም. በአየርላንድ ለጥበብ ዕድገት ለዓለም ላበረከቱት አስተዋጽዖ “የዳቬንቺ አልማዝ ሽልማት” እና “የጀግና ክብር ኒሻን” ተበርክቶላቸው።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ሚያዝያ 2 ቀን፣ 2004 ዓ.ም. በስጋ ሞት ቢለዩንም፥ እነሆ በራሳቸው ቀለምና በሀገርኛ ሥራዎቻቸው በዓለም መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ስም ከፍ በማድረጋቸው፥ ለእኚህ የሀገር ዋልታ አቢሲንያ ባንክ አዲስ የከፈተውን ቅርንጫፍ በስማቸው ሰይሞ ዘክሯል።
አቢሲንያ ባንክ ብዙ መሰናክሎች ሳይበግራቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የሥራ መስኮች ማለትም፥ በመንግሥት አስተዳደር፣ ሀገርን በመጠበቅ፣ በታሪካዊ ኩነቶች፣ ቅርስ በማሰባሰብ፣ በስፖርት፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በቴአትር፣ ሙዚቃ፣ ፋይናንስና አገልገሎት፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎች፣ በማስታወቂያ ሞያ፣ በንግድ ሥራና በመሳሰሉት ዘርፎች ስሟን ከፍ ላደረጉ ባለውለታዎች በስማቸው ቅርንጫፎችን በመሰየም እየዘከራቸው ይገኛል። ይህም ለሀገራችን ዘመን አይሽሬ አበርክቶ ያደረጉ ባለውለታዎችን ስማቸውንና መልካም ተግባራቸውን በመዘከር ለቀጣዩ ትውልድ ለማሳወቅና አርዓያ እንዲሆን በማመን ጭምር ነው።
ምንጭ፦ አቢሲንያ ባንክ
July 3, 2022 at 1:54 am #48207SemonegnaKeymasterዳሸን ባንክ ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል አስመረቀ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ታሪክ ውስጥ የአዲስ ዘመን ጅማሮ ተደርጎ ሊወሰዱ የሚችሉትን የኤሌክትሮኒክ ክፍያ እና የሞባይል ካርድ አገልግሎቶች በማስተዋወቅ ረገድ ፈር ቀዳጅ የሆነው ዳሸን ባንክ፣ ዘመናዊና በግል የፋይናንስ ተቋም ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን Tier III የውሂብ/የመረጃ ማዕክል (data center) አስመረቀ።
ዳሸን ባንክ ያለውን የመረጃ ቴክኖሎጂ (information technology /IT/) ለማሳደግ በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነና፤ ለመረጃ ቴክኖሎጂ (IT) መሠረተ ልማትና ግንባታ ብቻ በ2014 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በጀት በመመደብ እየሠራ መሆኑን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ለኢትዮጵያ ሪፖርተር ጋዜጣ አብራርተዋል። አሁን የተመረቀውን የውሂብ/የመረጃ ማዕከል (data center) ለመገንባት ባንኩ በአጠቃላይ 230 ሚሊዮን ብር ማውጣቱን አቶ አስፋው ጨምረው ገልጸዋል።
የመረጃ ማዕከሉ ከፍተኛ ኃይል ያላቸውን ከ1,000 ያላነሱ ሰርቨሮችና ሌሎች ተያያዥ የኔትወርክ መሣሪያዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ነው። በጥገና ወቅትም መደበኛ የባንኩን ሥራ ሳያቋርጥ ዓመቱን ሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው።
የመረጃ ማዕከሉ በአካባቢው የሚስተዋሉ የተለያዩ ክስተቶችን በመለየት ለማዕከሉ ዋና የመቆጣጠሪያ ክፍል መረጃ ማስተላለፍ የሚችል ሲሆን፣ ችግር ሲከሰትም ችግሩን በመለየት ስጋቶችን ለማስቀረት በሚችል ዓለማቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ ቴክኖሎጂ የተሟላ ነው።
ይህ የመረጃ ማዕከል ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ከየትኛውም ቦታ ማግኘት የሚያስችልና ባንኩ የተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶችን ያለምንም ችግር ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያግዘው ይሆናል። በተጨማሪም ባንኩ በዲጂታል ዘርፍ አዳዲስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅና የአገልግሎቱንም ደህንነትና ጥራት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ሁነኛ ሚና ይኖረዋል።
ይህ ማዕከል የዳሸን ባንክን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር በሥራ ላይ ለሚገኙ እና ወደ አገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ለሚቀላቀሉ የአገር ዉስጥም ሆነ የዉጭ ባንኮች እንዲሁም ለሌሎች ተቋማት አገልግሎት መስጠት የሚችል አቅም ያለዉ ነዉ።
በመረጃ ማዕከሉ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ የባንኮች ሥራ አስፈፃሚዎች፣ የተለያዩ ድርጅት ኃላፊዎች፣ የባንኩ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የባንኩ የበላይ አመራሮች፣ ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ቀደምት እና እጅግ አትራፊ ከሆኑት የግል ባንኮች አንዱ የሆነው ዳሸን ባንክ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ450 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፥ በባለፈው (2013) የበጀት ዓመት ከግብር በፊት 2.4 ቢሊየን ብር ትርፍ አስመዝግቧል። ባንኩ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ሲኖሩት፤ የአሞሌ (በስልክ የባንክ አገልግሎት) ተጠቃሚቾ ቁጥርም ከ2.4 ሚሊየን በላይ ነው። የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ደግሞ ከ94 ቢሊዮን ብር በላይ ነው።
July 5, 2022 at 2:48 am #48299SemonegnaKeymasterቡና ባንክ የውጭ ምንዛሪ በባንክ ያከናወኑ ደንበኞቹን ሸለመ
- የዕጣ አሸናፊ ደንበኞች ከዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል እስከ ሞባይል ስልክ ቀፎዎች ባለቤት የሚያደርጋቸው ዕጣ ወጥቶላቸዋል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ቡና ባንክ ጥቁር ገበያ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳደረውን ተጽዕኖ ለመከላከል በማቀድ የውጭ ገንዘብን በሕጋዊ መንገድ መመንዘርን ለማበረታታት የቀረጸው “የውጭ ገንዘብ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” አስረኛ ዙር መርሃግብር በይፋ በተካሄደ የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ተጠናቋል።
ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ በተካሄደው የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓትም 1ኛ ዕጣ የዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል አሸናፊው ቁጥር 0004079 መሆኑ ተረጋግጧል ።
ባንኩ ላለፉት ወራት ያካሄደው ይኸው የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ መርሃግብር “በቡና ይቀበሉ፣ በቡና ይመንዝሩ፣ ከቡና ይሸለሙ” በሚል መርህ የተካሄደ ሲሆን፥ ደንበኞች ከውጭ ሀገር ከወዳጅ ዘመዶቻቸው በተለያዩ ገንዘብ ማስተላለፊያ ድርጅቶች በኩል ገንዘብ ሲላክላቸውና በቡና ባንክ በኩል ሲቀበሉ እንዲሁም የውጭ ሀገር ገንዘብ በቡና ባንክ ሲመነዝሩ ዕድለኛ የሚሆኑበት የሎተሪ መርሃግብር ነው፡፡
በዚሁ የሎተሪ ዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ወቅት አንደኛ ዕጣ የሆነውን የ2021 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር መኪና ጨምሮ ዘመናዊ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ ፍሪጆች፣ የውሃ ማጣሪያዎች፣ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥኖችና ስማርት ስልኮች ለ30 ዕድለኞች ደርሰዋል፡፡
ወደሀገራችን ከሚመጣው የውጭ ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት ይልቅ በተለያየ ምክንያት ወደጥቁር ገበያ የሚገባ በመሆኑ፥ ሀገሪቱ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሚገጥማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል።
የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንድ ሀገር ለሚያስፈልጋት ማናቸውም የንግድ ልውውጥ ተግባር ከፍተኛ እንቅፋት የሚፈጥር ሲሆን፥ በዚህም ሳቢያ የሚከሰት የገቢ ንግድ መቀዛቀዝ፣ የሸቀጦች ዋጋ መጨመርን ብቻ ሳይሆን የአስፈላጊ ግብዓቶችን እጥረት በመፍጠር የኑሮ ውድነትን ያባብሳል፤ ዜጎችም በመሠረታዊ ግብዓቶች እጥረት ለችግር እንዲጋለጡ ምክንያት ይሆናል።
የውጭ ገንዘቦች ምንዛሪና መቀበል ሂደት በባንክ ብቻ እንዲተገበርና ከጥቁር ገበያ ተጽዕኖ እንዲላቀቅ ፣ በውጤቱም ሀገርና ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል ቡና ባንክ የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት በተከታታይ ዙሮች ለውጭ ገንዘብ ተቀባዮችና መንዛሪዎች የማበረታቻ ሽልማት በማዘጋጀት የዘመቻ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።
እስካሁን ባንኩ በአስር ዙር ባካሄደው “የውጭ ገንዘብ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” መርሃግብር በርካቶች በሕጋዊ መንገድ የውጭ ገንዘብ እንዲመነዝሩ ከማስቻሉ ባሻገር፥ ወደጥቁር ገበያ የሚገባውን የውጭ ገንዘብ መጠን ለመቀነስ የበኩሉን አስተዋጽዖ አበርክቷል።
ቡና ባንክ ባለፉት አስር ዙሮች ባካሄደው የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ መርሀግብር ካገኛቸው ልምዶች በመነሳት የባንኩን ደንበኞች የበለጠ ለማበረታታትና ለማትጋት አሥራ አንደኛ ዙር የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ መርሃግብሩን በቅርቡ ይጀምራል፡፡
አንድ ሀገር በምጣኔ ሃብት ጎልብታ ዜጎቿን ተጠቃሚ ማድረግ የምትችለው ጤናማ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ማስፈን ስትችል ሲሆን የገንዘብ ዝውውር ደግሞ በኢኮኖሚው ውስጥ ገንቢ ሚና እየተወጣ እንዲቀጥል ለማድረግ ባንኮች የማይተካ ድርሻ አላቸው።
ቡና ባንክም በየጊዜው በሚያካሂደው ጥናት ብዙኃኑን ሕብረተሰብ ወደባንክ ሥርዓት እንዲገባ፣ በዚህም የቁጠባ ባህሉን በማሳደግ ህይወቱን እንዲያሻሽል ለማስቻል የተለያዩ አገልግሎቶችን እየቀረጸ ለጥቅም ሲያውል ቆይቷል። በዚህም ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት ወደራዕዩ ስኬት የሚያደርገውን ግስጋሴ ቀጥሏል።
ከ13 ሺህ በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች የተቋቋመው ቡና ባንክ 343 በደረሱ ቅርንጫፎቹ በመላው ኢትዮጲያ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ የግል ባንክ ነው።
ምንጭ፦ ቡና ባንክ
July 31, 2022 at 1:08 am #49077SemonegnaKeymasterየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 890.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ
በሲቢኢ ኑር አገልግሎት ተጨማሪ 17.5 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ተሰበሰበአዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 (2021/22) በጀት ዓመት 154.9 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘቡን 890.1 ቢሊዮን ብር ማድረሱን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ አስታውቀዋል።
የ2014 (2021/22) በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማውን ከሐምሌ 21 እስከ ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲሱ የዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ያካሄደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአጠቃላይ ከዕቅድ በላይ ወይም ተቀራራቢ አፈጻጸም ያስመዘገበበት ዓመት መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት ካቀረቡት ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ 27.5 ቢሊየን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን፤ ይህም ከዕቅዱ 16.3 በመቶ፣ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ43.9 በመቶ ብልጫ እንደሚያሳይ አቶ አቤ ገልጸዋል።
ባንኩ 179.2 ቢሊዮን ብር ብድር ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች መስጠቱን ያስረዱት አቶ አቤ፥ 120.6 ቢሊዮን ብርም ከተሰጡ ብድሮች መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል።
የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተ፥ ከተለያዩ ዘርፎች 2.6 ቢሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ በመንግስት ትኩረት ለተሰጣቸው ለተለያዩ የገቢ እቃዎች እና ለሌሎችም 7.7 ቢሊዮን ዶላር ባንኩ መክፈሉንም ነው አቶ አቤ የገለጹት።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ሀብት 1.2 ትሪሊዮን ብር መድረሱንም አቶ አቤ ካቀረቡት ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
የባንኩን አገልግሎት ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት በበጀት ዓመቱ 124 አዳዲስ ቅርንጫፎች የተከፈቱ ሲሆን፤ የባንኩ አጠቃላይ የቅርንጫፍ ብዛትም 1824 ደርሷል።
የደንበኞችን በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶች ተጠቃሚነት በማሳደግ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስ ባንኩ በሚያደርገው ጥረት በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ የሒሳብ እንቅስቃሴዎች ውስጥ 35 በመቶ የሚሆነው በዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች መከናወኑን አቶ አቤ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ተጨማሪ 2.9 ሚሊዮን አዳዲስ ሒሳቦች መከፈታቸውነ የገለጹት አቶ አቤ፥ የባንኩ አጠቃላይ የገንዘብ አስቀማጮች ብዛት 35.9 ሚሊዮን መድረሱንም ጨምረው ገልጸዋል።
ባንኩ በተለያዩ ዓለም አቀፋዊም ሆነ ሀገራዊ ፈተናዎች ወስጥ አልፎ አበረታች ወጤት ማስመዝገቡን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሪክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ባንኩ እያካሄደ ባለው የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተናግረዋል።
ከባንኩ ጋር በተያያዘ ዜና፥ በሲቢኢ ኑር አገልግሎት (የሸሪዓ መርህን የተከተለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት) ተጨማሪ 17.5 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡን ባንኩ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲቢኢ ኑር (CBE Noor) በተባለው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 69.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን በሪፖርታቸው የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ፣የአስቀማጭ ደንበኞች ቁጥርም ከ5 ሚሊዮን በላይ መድረሱን አሳውቀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኑር በሚል ስያሜ የሸሪአ መርህን ተከትሎ በሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 69.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን በሪፖርታቸው የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ፥ የአስቀማጭ ደንበኞች ቁጥርም ከ5 ሚሊዮን በላይ መድረሱን አሳውቀዋል።
የተገኘው ውጤት ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያማከለ አገልግሎት ለመስጠት ባንኩ እያደረገ ያለው ጥረት ፍሬ ማፍራቱን የሚያሳይ ነው ያሉት አቶ አቤ፥ ባንኩ በሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት 9.3 ቢሊዮን ብር የፋይናንሲንግ አገልግሎት መስጠቱንም ነው አክለው የገለፁት።
August 7, 2022 at 12:14 am #49307SemonegnaKeymasterአዋሽ ባንክ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
አዋሽ ባንክ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የብር 5 ሚሊየን ድጋፍ አደረገ
አቶ ሰለሞን ሶካ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ
አዋሽ ባንክ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ሐምሌ 26 ቀን፥ 2014 ዓ.ም በጋራ አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱን የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው እና የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ፈርመውታል።
በስምምነቱ መሠረት ኢመደአ የሀገሪቱን የሳይበር ደኅንነት ለማረጋገጥ ለሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ ሥራዎች የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ በአዋሽ ባንክ የሚደረግ ሲሆን፤ በሌላም በኩል የባንኩን የኢንፎርሜሽንና ኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማት ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ድጋፍና እገዛ በኢመደአ በኩል እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።
የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ኢመደአ የፋይናንስ ሴክተሩን ጨምሮ ቁልፍ የሀገራችንን ተቋማት የሳይበር ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚሠራቸው ሥራዎች ከፍተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ ለኢመደአ መደረጉን ጠቅሰዋል። በቀጣይም የሁለቱ ተቋማት የትብብርና የቅንጅት ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው፥ ጠንካራ ሀገር መገንባት የሚቻለው ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ሲቻል መሆኑን በማስታወስ፥ ኢመደአ የሀገራችንን የሳይበር ደኅንነት የማስጠበቅ ዋና ተልዕኮውን ለማሳካት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ ይሠራል ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ ከአዋሽ ባንክ ጋር የተደረገው የጋራ የመግባቢያ ስምምነት ፊርማም የአስተዳደሩ የትብብርና የቅንጅት ሥራ አንዱ አካል እንደሆነ መግለጻቸን አዋሽ ባንክ በሰጠው መግለጫ ላይ አስፍሯል።
ከአዋሽ ባንክ ሳንወጣ፥ ባንኩ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ጸጋዬ ማሞ እንደገለጹት፥ የክልሉ መንግሥት ተልዕኮዎችን ለማስፈጸም የአጋሮችን ድጋፍ በመጠየቅ ሃብት የማሰባሰብ ሥራ መሠራቱን የገለፁ ሲሆን፤ አዋሽ ባንክ ላደረገው ድጋፍ በክልሉ መንግሥት ስም በማመስገን በክልሉ ባንኩ ለሚሠራቸው ሥራዎች የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።የአዋሽ ባንክ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን ዋና ዳይሬክተር አቶ ይርጋ ይገዙ በበኩላቸው፥ የአዋሽ ባንክ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን ክልላዊና ሀገራዊ ጥሪዎችን በመቀበል ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ለመነሻ የሚሆን የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ፥ አቶ ሰለሞን ሶካ ከሐምሌ 27 ቀን፥ 2014 ዓ.ም ጀምሮ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር በመሆን በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) መሾማቸውን ተቋሙ ዘግቧል።
አቶ ሰለሞን ሶካ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርን ከመሠረቱት ቀደምት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ ከቴክኒካል ባለሙያነት ጀምሮ እስከ ምክትል ዳይሬክተርነት ለ10 ዓመታት ያክል ተቋሙን አገልግለዋል። በ2008 ዓ.ም ተቋሙን ከለቀቁ በኋላም “ቴክ ማሂንድራ” (Tech Mahindra) በተባለ የህንድ የመረጃ ቴክኖሎጂ አገልግሎት እና አማካሪ ድርጅት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ለስድስት ዓመታት ሠርተዋል።
አቶ ሰለሞን ሶካ “ቴክ ማሂንድራ” ውስጥ ከ6 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ኢመደአ በመመለስ ከኅዳር ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው ከሐምሌ 27 ቀን፥ 2014 ዓ.ም ጀምሮ የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾመዋል ።
አቶ ሰለሞን ሶካ ከማይክሮ ሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ (Microlink Information Technology College) በሶፍትዌር ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ የማስተርስ ዲግሪያቸው ደግሞ ከቻይና ኤሌክትሮኒክ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (University of Electronic Science and Technology of China – UESTC) በኮምፒውተር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አግኝተዋል።
የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ የደቡብ ክልል ኮንሶ ዞንን ወክለው ተወዳድረው በማሸነፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን የምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል።
September 5, 2022 at 11:26 pm #50485SemonegnaKeymasterጥቁር ገበያ ላይ የአንድ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ90 ብር በላይ ደርሷል
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቁር ገበያ ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ90 ብር በላይ መድረሱን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።
ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ዋና የዶላር ምንጭ የሆነውን ሕገ ወጥ የሃዋላ እንቅስቃሴ ነው ያለው ብሄራዊ ባንክ ዝውውሩ የሚከናወንባቸውን የሒሳብ ቁጥሮችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ባላገሩ ቴሌቭዥን ዘግቧል።
ከብር አንፃር የዶላር ዋጋ ዕለት ከዕለት እየጨመረ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ መደበኛ ባልሆነው የሃዋላ ምንዛሬ (ጥቁር ገበያ) ባለፉት ጥቂት ቀናት ዶላር ከፍተኛ ጭማሬ ማሳየቱን የባላገሩ ዘጋቢ ባደረገው ቅኝት ተረድቷል።
ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ አንድ ዶላር ጥቁር ገበያ ላይ ከ85 እስከ 87 ብር ድረስ በመመንዘር ላይ እንደሚገኝ እና በተለያዩ ሁኔታዎች ይህ ዋጋ እስከ 92 ብር ድረስ ከፍ እንደሚል ባላገሩ ቴሌቪዥን ብሔራዊ ቴያትር አካባቢ ከሚገኙት የጥቁር ገበያ መንዛሪዎች መረዳት ችሏል፡፡
በመደበኛው የምንዛሬ ገበያ አንድ ዶላር በ53 ብር አከባቢ እየተመነዘረ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድረ ገጽ ያሳያል። በአሁኑ ጊዜ በጥቁር ገበያ እና መደበኛ ገበያው መካከል ያለው ልዩነት ከ26 ብር በላይ ሆኗል።
የዶላር ዋጋ መጨመሩ በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው ዋጋ ንረት ላይ የራሱን የሆነ ጫና የሚያሳድር መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ዶ/ር አጥላው ዓለሙ ያነሳሉ፡፡ የውጭ ምንዛሬ ጥቁር ገበያ ላይ በዚህ ያህል መናር የሀገሪቱ ወጪ እና ገቢ ንግድ አለመመጣጠን መሠረታዊ ምክንያት መሆኑን ዶ/ር አጥላው ገልጸዋል፡፡
ሀገሪቱ በቂ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ባለመቻሏ ነጋዴው ማኅበረሰብ በቂ ዶላር በባንክ ቤቶች በኩል ማግኘት አለመቻሉን ዶ/ር አጥላው አንስተዋል፡፡ በዚህም ምርት ከውጭ የሚያስገቡ ነጋዴዎች የጥቁር ገበያውን እንደ ዋና የውጭ ምንዛሬ ምንጭነት እየተጠቀሙበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱን እንዳሳደገው አብራርተዋል፡፡
የጥቁር ገበያውን ለመቆጣጠር በዋናነት የባንኮችን የዶላር ክምችት ማሳደግ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ያነሱ ሲሆን፤ ለዚህም ምርትን በማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፍቃዱ ድጋፌ ከሰሞኑ ሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል ዳግም ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በተለይም ጥቁር ገበያ ላይ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን የገቡበትን ጦርነት ተከትሎ የዓለም ምርት ዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት መጨመሩንና ይህን ተከትሎ በጥቁር ገበያ የምንዛሬ ዋጋ እድገት ማሳየቱን ምክትል ገዥው አብራርተዋል፡፡
በዓለም ገበያ ላይ የዩሮ ዋጋ እየቀነሰ መምጣቱን ያነሱት አቶ ፍቃዱ፥ በተቃራኒው የአሜሪካ ዶላር ፍላጎቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ዋና የዶላር ምንጭ የሆነውን ሕገ ወጥ የሃዋላ መሆኑን ያነሱት አቶ ፍቃዱ፥ ባንኩ የዚህ እንቅስቃሴ ማካሄጃ የሒሳብ ቁጥሮችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፤ በቅርቡም በዚህ እንቅስቃሴ ላይ ሲሳተፉ በተገኙ የሒሳብ ቁጥሮች ላይ እርምጀ እንደሚወሰድ ጨምረው አንስተዋል፡፡
በመደበኛ የዶላር ምንዛሬ ገበያውም ላይም ቢሆን ባለፉት ስድስት ወራት በአንድ ዶላር የምንዛሬ ዋጋ ላይ የ2 ብር ከ60 ሳንቲም ጭማሪ እንደተደረገበት ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ምንጭ፦ ባላገሩ ቴሌቭዥን
September 16, 2022 at 4:29 pm #50978SemonegnaKeymasterየኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንትንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ (tax incentive) ተግባራዊ ተደረገ
አዲስ አበባ (የገንዘብ ሚኒስቴር) – የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን እና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር መስከረም 6 ቀን፥ 2015 ዓ.ም. አስታውቋል።
በዚህም የታክስ ማሻሻያ (tax incentive) ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝቅተኛ የጉምሩክ ታሪፍ የሚጣልባቸው ሲሆን፥ ከተጨማሪ እሴት ታክስ / ቫት/ (value added tax /VAT/)፣ ከኤክሳይዝ ታክስ (excise tax) እና ከሰር ታክስ (surtax) ነፃ እንደሚደረጉም ታውቋል።
የታክስ ማሻሻያው ዓላማ በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር በፖሊሲ ማዕቀፍ ከአካባቢ ደኅንነት ጋር የሚስማማ (environmentally friendly) ለማድረግ፣ በሕብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል፣ በአየር ንብረትና በብዝኃ ህይወት (climate and biodiversity) ላይ ተጽዕኖ የማያሳርፍ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በአግባቡ የሚጠቀም የመጓጓዣ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሆን፥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ እንዲቀርቡ ለማስቻልም ነው።
በታክስ ማሻሻያው መሠረት የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም ሙሉ በሙሉ ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ አውቶሞቢሎች ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በከፊል ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም 5 በመቶ (5%) የጉምሩክ ቀረጥ (custom duty) ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን፥ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ያለቀላቸው የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ሲገቡ ደግሞ 15 በመቶ (15%) የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን፥ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተወስኗል ሲል የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ የመለክታል።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሽከርካሪና የተሽከርካሪ ባለቤቶችን ቁጥር ለመጨመር መንግሥት ተሽከርካሪ በማምርት ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶችን ከመሳብና በተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው ታክስ ላይ ማሻሻያ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በጣም ዝቅተኛ ተሽከርካሪዎች ካሏቸው ሀገራት አንዷ ስትሆን፥ የእ.ኤ.አ 2019 ዓ.ም መረጃ እንደሚያሳየው፥ በአማካይ ሁለት መኪኖች ለአንድ ሺህ ሰዎች (2 cars to 1000 people) ነው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ተሽከርካሪዎቾ ቁጥር 600,000 አካባቢ ሲሆን፥፥ ከእነዚህ ውስጥ 84 በመቶ (84%) የሚሆኑት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ናቸው። አብዛኞቹ ተሽከርካሪዎችም ከውጭ ሀገር ሲገቡ ያገለገሉ (secondhand) ሲሆኑ፥ አብዛኛዎቹም የሚመጡት ከገልፍ (Gulf) ሃገራት ከፍተኛ ቀረጥ (ታክስ) ተከፍሎባቸው ነው ሲል ከጥቂት ዓመታት በፊት ቢቢሲ ዘግቦ ነበር።
October 6, 2022 at 11:57 pm #52639SemonegnaKeymasterሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በባህር ዳር ከተማ፣ በጣና ሐይቅ እና ሐዋሳ ሐይቅ ሦስት ሆቴሎችን ሊከፍት ነው
/MIDROC Investment Group to open three international brand hotels in Bahir Dar, Lake Tana, and Lake Hawassa/ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ “ፕሮቴያ ማርዮት”ን በባህር ዳር ከተማ፣ በጣና ሀይቅ እና በሀዋሳ ሀይቅ ደግሞ “ፎር ፖይንትስ ባይ ሸራተን”ን ለመክፈት የሚያስችሉ ሦስት የፍራንቻይዝ ስምምነቶችን ከማርዮት ኢንተርናሽናል ጋር ተፈራረመ።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከማርዮት ኢንተርናሽናል ጋር በባህር ዳር የሚገኘውን ጣና ሆቴል እና ሀዋሳ የሚገኘውን ፕሮግረስ ኢንተርናሽናል ሆቴልን ሁለቱንም በ“ፎር ፖይንት ባይ ሸራተን” ብራንድ እንዲሁም የብሉ ናይል (አቫንቲ) ሪዞርትን በ“ፕሮቴያ ማርዮት” ብራንድ ለመክፈት ነው ስምምነቱን ያደረገው።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኩል ስምምነቱን የተፈራረሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ጀማል አህመድ እና የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሰለሞን ዘውዱ ናቸው፡፡ ሚስተር ከሪም ቼሎት፣ ሚስተር ጁጋል ኩሻላኒ እና ሚስተር ኤድዋርድ ኤድዋርት ሳንቼዝ ደግሞ በማርዮት ኢንተርናሽናል በኩል ስምምነቱን ፈርመዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድም ከማርዮት ኢንተርናሽናል ጋር ስምምነት በማድረጋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ፥ “ከዚህ ዝነኛ ብራንድ ጋር የረጅም ጊዜ አጋርነታችንን እያሰፋን በመምጣችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል።
ማርዮትን ወክለው የተናገሩት ሚስተር ከሪም ቼሎት በበኩላቸው ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር ያላቸውን አጋርነት በማሳደጋቸው እና በኢትዮጵያ ያላቸውን ተሳትፎ በማስፋታቸው ደስታ እንደተሰማቸው አስረድተዋል።
ሁለቱ ወገኖች ባለፈው በፈረንጆቹ ህዳር 2021 በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት አጠገብ የሚገኘውን የዌስቲን ሆቴል ለማስተዳደር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
ምንጭ፦ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ
MIDROC Investment Group to open three international brand hotels in Bahir Dar, Lake Tana, and Lake Hawassa
MIDROC Investment Group signs three franchise agreements with Marriott International to open Protea by Marriott in Bahir Dar, Four Points by Sheraton at Lake Tana as well as another Four Points by Sheraton at Lake Hawassa, Ethiopia.
MIDROC Investment Group has signed an agreement with Marriott International to open the Tana Hotel located in Bahir Dar and Progress International Hotel located in Hawassa, both with Four Points by Sheraton, and Blue Nile (Avanti) Resort, located in Bahir Dar to Protea by the Marriott brand.
Mr. Jamal Ahmed, CEO, and Mr. Solomon Zewdu, D/CEO of the Hospitality Cluster, signed the agreement on the Midroc Investment Group side. On the other hand, Mr. Karim Cheltout, Mr. Jugal Khushalani, and Mr. Edward Edwart Sánchez signed the agreement on Marriott International’s side.
Mr. Jamal Ahmed, CEO of the Investment Group, said that we are excited to work with Marriott International as we continue to expand our long-standing partnership with this famous brand.
Mr. Karim Chelout of The Marriot said with this significant project, we are thrilled to grow our partnership with MIDROC Investment Group and expand our presence in Ethiopia.
It is recalled that the two parties signed to manage the Westin Addis Hotel located next to the African Union Headquarters in Addis Ababa in last November 2021.
Source: MIDROC Investment Group
October 14, 2022 at 6:54 pm #52939SemonegnaKeymasterበ2014 ዓ.ም 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቤቶች ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል — የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ቤቶች ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፥ በተለያዩ አካባቢዎች ከዋናው የኤሌክትሪክ መሥመር ውጪ ያሉ (ኦፍግሪድ/off-grid) የተሠሩ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.3 ሚሊዮን ቤቶችን ተጠቃሚ አድርገዋል።
ከኦፍ ግሪድ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎቹ በተጨማሪ የቤት ለቤት የፀሐይ ኃይል ቁሶች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ይህ ሥራ በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የ2014 ዓ.ም በተለይ በኢነርጂው ዘርፍ ትልቅ የማምረት አቅም የተፈጠረበት ዓመት መሆኑን የጠቁመው ሚኒስቴሩ፥ ሆኖም እምርታ እየታየበት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ሊያዳርሳቸው የማይችላቸው የተንጠባጠቡ መንደሮችን የፀሐይ ኃይል እንደ አማራጭ እንደሚወሰድም ገልፀዋል።
እስካሁን በተጠኑ ጥናቶችና ባለው ነባራዊ እውነታ በሀገሪቱ ያሉ የኢነርጂ ምንጮች የመጀመሪያው ውሃ፣ ቀጥሎ ደግሞ የፀሐይ ኃይል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ከውሃ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማሳደግ ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን ሶላር ኢነርጂን (solar energy) በመጠቀም የሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከፍ ለማድረግ እየሠራች የምትገኘው ሥራ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሕብረተሰቡ በመንግሥት በኩልና በግሉ ከሚያገኛቸው የፀሐይ ኃይል አገልግሎቶች በተጨማሪ በተበታተነ መልኩ ያሉ መንደሮችን ለማገልገል የተገነቡ የውሃ ተቋማት ከሚጠቀሙት ጄነሬተር ኃይል በፀሐይ ኃይል በሚሠሩ ኢነርጂዎች እንዲጠቀሙ እንደሚደረግም ገልፀዋል።
ሕብረተሰቡ በግሉ የፀሐይ ኃይልን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀይሩ መሣሪያዎችን መጠቀም መጀመሩ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ፥ መንግሥት ይህንን ለመደገፍ በአግባቡ የማይሠሩና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የሶላር ኢነርጂ መሣሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በትኩረት መሥራቱንም ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የተበታተኑ መንደሮችን ከዋናው የኤሌክትሪክ መሥመር ውጭ በሆነ መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በ2015 ዓ.ም አነስተኛ የሆኑ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን ዲዛይን ማድረግ ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
በተለይ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል ብዙ ወንዞች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፥ ወንዞቹን ለኃይል ማመንጫነት በመጠቀም ዜጎችን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ፥ ሀገሪቱ ካላት ወንዞች አብዛኞቹ ያሉበት ተፋሰስ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ምቹ መሆናቸው መረጋገጡንና በትናንሽ ወንዞች እንኳ ብዙ የኃይል እጥረቶች መፍታት እንደሚቻልም አብራርተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በባዮጋዝ (biogas) አጠቃቀም ረገድም ሕብረተሰቡ ግንዛቤ አግኝቶ እንዲጠቀም ለማስቻል ጥረት መደረጉን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ በዚህም ብዙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በዘርፉ በመቀላቀል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፤ ጥረቱ በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
November 18, 2022 at 1:22 am #54201SemonegnaKeymasterበኢትዮ-ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በይፋ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ተጀመረ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና የኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያ ኅዳር 8 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በይፋ የኤሌክትሪክ ሽያጭ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በማስተላለፊያ መስመሩ ላይ ኃይል የማስተላለፍ የሙከራ ሥራ ከጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ ሲከናወን መቆየቱንም ኩባንያው አስታውሷል።
ኅዳር 8 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በይፋ ኃይል ማስተላለፍ የጀመረው የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት (500 kilovolt) የማስተላለፊያ መስመር በዓመት እስከ አንድ መቶ ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማስገባት አቅም ያለው ሲሆን፤ ከኬንያ አልፎ ከታንዛኒያ እስከ ደቡብ አፍሪካ ላሉት ሀገራት እስከ ሁለት ሺህ ሜጋ ዋት (2000 MW) ኤሌክትክ የማስተላለፍ አቅም አለው፡፡
የኢትዮ-ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ኮንቨርተር ጣቢያ ፕሮጀክት ለአማካሪ ድርጅቱ፣ ለካሳ ክፍያና የተሰረቁ መሰረተ ልማቶችን ለመተካት የወጣውን ወጪ ጨምሮ ወደ አምስት መቶ ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡
ከዚህ ውስጥ 214 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላሩ ለኮንቨርተር ስቴሽኑና ለግራውንድ ኤሌክትሮድ መስመር የግንባታ ሥራ እንዲሁም 120 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ለማስተላለፊያ መስመሩ የዋለ ነው፡፡
የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር የግንባታ ሥራ “China Electric Power Equipment and Technology Co. Ltd (CET)” በተሰኘ የቻይና ኩባንያ የተከናወነ ሲሆን፤ የኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያውና የግራውንድ ኤሌክትሮድ መስመሩ ደግሞ ሲመንስ (Siemens AG) በተሰኘው የጀርመን ኩባንያ ተከናውኗል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል የተዘረጋው የማስተላለፊያ መስመር እና የፕሮቴክሽንና የዳታ ኮሙዩኒኬሽን መስመር (ኦፕቲካል ግራውንድ ፋይበር) 440 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን 994 የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የብረት ታወሮች አሉት።
ኢትዮጵያ የምታስተላልፈው ኃይል ያልተቆራረጠና አስተማማኝ እንዲሆን የሚያግዙ ተግባራትን ያጠናቀቀች ሲሆን በኬንያ በኩል ተመሳሳይ ሥራዎች ተሰርተው በቅርቡ ወደተግባር እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡
የማስተላለፊያ መስመሩ ከደቡብ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የወላይታ፣ ጋሞ እና ኮንሶ ዞን እንዲሁም ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የቦረና ዞን አቋርጦ ነው ወደ ኬንያ ኃይል የሚያስተላልፈው።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከሱዳን እና ከጅቡቲ ጋር የኃይል ሽያጭ እያካሔደች ሲሆን ከሶማሌ ላንድ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማለች።
ባለፈው ዓመት ለሱዳን እና ለጅቡቲ ኤክስፖርት ከተደረገው የኤሌክትሪክ ኃይል 95 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.