እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገች

Home Forums Semonegna Stories እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገች

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #7911
    Semonegna
    Keymaster

    እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ትምህርት ጥራት ያደረገችው ድጋፍ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ተማሪዎችንና 120,000 አስተማሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የእንግሊዟ ተወካይ ሚስስ ሃርየት ባልድዊን አስታውቀዋል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ)–እንግሊዝ ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ትምህርት ጥራትና ኢንቨስትመንት መሰረተ ልማት የሚውል 6 ነጥብ 31 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለመስጠት ተስማማች።

    ስምምነቱ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በአፍሪካ የእንግሊዝ ሚኒስትር ዲኤታ (Minister of State at the Foreign Office) ሚስስ ሃርየት ባልድዊን (Harriett Baldwin) መካከል መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ተፈርሟል።

    ኢትዮጵያ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እያከናወነች ያለውን ተግባር የሚያግዝና ለኢንቨስትመንት መሰረተ ልማትና አቅም ግንባታ የሚውል 176 ሚሊዮን ዩሮ ወይም የ6 ነጥብ 31 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ነው ስምምነት የተደረገው።

    ከዚህ ውስጥ 110 ሚሊዮን ዩሮ ወይንም 3 ነጥብ 94 ሚሊዮን ብር ለአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም 66 ሚሊዮን ዩሮ ወይንም 2 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር ለኢንቨስትመንት መሰረተ ልማት የሚውል ነው።

    ለአጠቃላይ ትምህርት ጥራት የተደረገው ድጋፍ በአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና ሶማሌ ክልሎች በቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ጨምሮ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

    ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ እንደገለጹት የድጋፍ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በትምህርት ጥራትና ኢንቨስትመንት መስኮች እየሠራች ላለው ተግባር የራሱ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።

    የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተደረገው ድጋፍ በታዳጊ ክልሎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት፣ ጠንካራ የትምህርት አመራሮችን ለመፍጠርና ተጠያቂነትን ለማስፈን ይውላልም ብለዋል።

    እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ቀሪው 66 ሚሊዮን ዩሮ ወይንም 2 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር ለመንግስት ኢንቨስትመንትና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙያዊ ድጋፍና የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት የሚውል ነው።

    የተፈረመው የድጋፍ ስምምነት የሁለቱን አገራት ጠንካራ ግንኙነት እንደሚያሳይ በመግለጽም ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታከናውነው ሁሉን አቀፍ ልማት እንግሊዝ ድጋፏን እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

    ሚስስ ሃርየት ባልድዊን በበኩላቸው የኢትዮጵያን ፈጣን እድገት ለማሳካት እንግሊዝ በትብብር ትሰራለች ብለዋል።

    ሚስስ ሃርየት በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ትምህርት ጥራት ያደረገችው ድጋፍ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ተማሪዎችንና 120,000 አስተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

    በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በኢኮኖሚው መስክ ለውጥ ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረት እውን እንዲሆን ሙያዊና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ በጋራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

    እንግሊዝ ዶ/ር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ጀምሮ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሰላም ታደንቃለችም በማለት አክለዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገች

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.