የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል ― ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠር፣ እንዲሁም ሊያስከትል ይችል የነበረዉን ጉዳት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫዉቷል።
የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎ መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የታወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወረርሽኙ/ቫይረሱ ሊያስከትል ከሚችለዉ የከፋ ጉዳትን በመቀነስ በኩል ያበረከተዉ አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን በኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ ገልጸዋል።
የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በተለመደው የጤና አጠባበቅ ዘዴ እና አካሄድ ለመቆጣጠር አዳጋች በመሆኑ፥ ሀገራችንም የወረርሽኙን አደገኛነት በመገንዘብ ይህን ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እንዲቻል መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት በሥራ ላይ እንዲውል አድርጋለች።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ሦስት ደንቦችና ስድስት መመሪያዎችን በማውጣት የተለያዩ ክልከላዎችንና ግዴታዎችን በመደንገግ ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ ሲሆን ሥራውን የሚመሩ ከብሔራዊ ኮሚቴ ጀምሮ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ ባሉ አደረጃጀቶች የተለያዩ ኮሚቴዎችና ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ በማድረግ ሥራውን በተናበበና በተቀናጀ መልኩ እየሠሩ ይገኛሉ።
ከተቋቋሙት ንዑስ ኮሚቴዎች መካከል ከፌዴራል እስከ ክልል እና ወረዳ ባሉ አደረጃጀቶች የተቋቋመው የሕግ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ አንዱ ሲሆን፥ ይህ ንዑስ ኮሚቴ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሚመራ ሆኖ የወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕጎች ለሚመለከተው አካል በወቅቱ እንዲደርሱ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ሕጎቹ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሲያከናውን የቆየ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
ግንዛቤ ከተፈጠረ በኋላ ንቃተ ሕጉ በሕብረተሰቡ ላይ ያመጣዉን ለዉጥና አፈፃፀሙስ ምን ይመስላል የሚሉትን በመለየትና ወጣ ገባ የታየባቸዉን ጉዳዮች በመለየት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር መድረኮችን በመፍጠርና በቪዲዮ ኮንፈረንስና በፊት ለፊት ስልጠና በመታገዝ የተስተዋሉ ክፍተቶች ላይ ዉይይቶች እየተደረጉ አቅጣጫ እንዲሰጥባቸዉ የማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸዉን አክለዉ ገልጸዋል።
በአንዳንድ ክልሎች ወጣ ገባ አፈፃፀም መኖር እና ሕጉን አዉቆ መተግበር ላይ በማኅበረሱ ዘንድ የታዩት ቸልተኝነቶች የፈጠሩት አንዳንድ ክፍተቶች የተስተዋሉ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በላይሁን፥ ሆኖም ግን አዋጁ መታወጁ የኮሮና ወረርሽኝ ሊያደርሰዉና ሊያስከትለዉ ይችል ከነበረዉ የከፋ አደጋ ታድጎናል ሲሉ ተናግረዋል።
ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
