ኮሚሽኑ ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ አደረገ

Home Forums Semonegna Stories ኮሚሽኑ ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ አደረገ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #15617
    Semonegna
    Keymaster

    የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ አደረገ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ 184 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳያቸው በምርመራ እንዲጣራ እና ክስ እንዲመሠረት ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ስም ዝርዝራቸውን ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መላኩን አስታወቀ።

    ኮሚሽኑ ሀብትና ንብረት የማስመዝገብ ግዴታ ያለባቸውን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ በተለያየ ጊዜ በቴሌቪዥን፣ በሬድዮ እና በደብዳቤ ጥሪ ባስተላለፈው መሠረት አብዛኞቹ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ሀብትና ንብረታቸውን አስመዝግበዋል።

    ይሁን እንጂ በፌደራልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ 184 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ኮሚሽኑ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሀብትና ንብረታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም። ሀብትን ከማስመዝገብ ግዴታ ጋር ተያይዞ ፈቃደኛ ሆኖ ያልተገኙ አካላት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠባቂነት ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል በወጣው የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተደንግጓል።

    በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባ ሥራን በማካሄድ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነትና የግል ጥቅም ሳይቀላቀሉ በየራሳቸው መንገድ የሚመሩበትን ግልጽ ሥርዓት እንዲኖር እያደረገ ባለው ሂደት ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ እንዲሆኑ እያደረገ ሲሆን፥ በቀጣይም ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ በማይሆኑ የመንግሥት ተሿሚዎችና ሠራተኞች ላይ በሕጉ መሠረት ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን ያሳውቃል።

    ከባለስልጣናት ሀብት ምዝገባ ጋር በተያያዘ፥ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔና ምክትል አፈ-ጉባዔን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት ነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም የሀብት ምዝገባ እድሳት አካሂደዋል።

    በሀብት ምዝገባ እድሳቱ ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ እንደተናገሩት፥ የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል እየሠራቸው ካሉት በርካታ ሥራዎች መካከል የሀብት ምዝገባ ሥራ አንዱ ነው። የሀብት ምዝገባ ሥራ ሙስናን ለመከላከል ዓይነተኛ መሣሪያ እንደመሆኑ መጠን ሊደገፍና ሊጠናከር ይገባል ሲሉ አፈ-ጉባዔው አክለው ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁሉም አካላት ሀብታቸውን በማስመዝገብ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከከላከል የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባቸው አፈ-ጉባዔው አሳስበዋል።

    አፈ-ጉባዔዎቹን ጨምሮ የሀብት ምዝገባ እድሳት ያካሄዱ የምክር ቤቱ አባላት ሀብታቸውን ያሳደሱበትን ሰነዶች ለፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር አቶ ፀጋ አራጌ አስረክበዋል።

    ምንጭ፦ የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.