የአድዋ ድል በዓል ― እኛ አንድ እንጂ 80 ኢትዮጵያ የለችንም!

Home Forums Semonegna Stories የአድዋ ድል በዓል ― እኛ አንድ እንጂ 80 ኢትዮጵያ የለችንም!

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #13756
    Anonymous
    Inactive

    የአድዋ ድል በዓል ― እኛ አንድ እንጂ 80 ኢትዮጵያ የለችንም!
    አቶ ኦባንግ ሜቶ
    ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ሊቀመንበር መሥራችና ፕሬዝደንት

    እንኳን ለ124ኛው የአድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ ስለድል ስናወራ ጀግንነት እና አሸናፊነት ሰውነታችንን ይወረዋል፤ ግን ጀግንነት የቱ ነው? አሸናፊነትስ ምንድን ነው?

    ትናንት አባቶቻችን የጠላትን ጦር አሸንፈዋል፤ እኛ ግን ዛሬ እራሳችንን ማሸነፍ አቅቶናል። ለሰላም አልተሸነፍንም፤ ለፍቅር እጅ አልሰጠንም፤ ታዲያ ከአበቶቻችን ተረክበን ያስቀጠልነው ጀግንነት የቱ ነው? የኛ ዘመን ድል የቱ ጋር ነው ያለው?

    ሁላችንም የአድዋ ድልን ስናስብ እና አክብረነውም ስንውል ታሪክ ነጋሪ ብቻ ሳንሆን ታሪክን በአሸናፊነት ደጋሚ፥ ብሎም አዲስን ታሪክ ሠሪ መሆን አለብን እንጂ ታሪክን የኋሊት የምናስኬድና ጀግኖች አባቶቻችን ከጠላት ኃይል ጋር ተናንቀውና ሕይወታቸውን ሰውተው ዛሬ ድል አያልን በኩራት የምናከብረውን ነፃነትና በብዙ ተጋድሎ ያስረከቡንን ሀገር አኛ እርስ በእርሳችን ተገዳድለን፣ በዘር መከፋፈል ግጭት ተላልቀን መጨረሻው ያላማረ ከንቱ ትውልድ መሆን የለብንም። የጀግኖች አባቶቻችን የነፃነት አንባ የሆነችውን ሀገር በነፃ ጦር ሰይሰበቁና ሜዳ ሳይዋደቁ ‘እንካችሁ ሀገራችንን ውሰዱ፤ ነፃነታችንን ግፈፉ፤ በዓለም ላይ በጀግኖች አባቶቻችን ደም ደምቆ የተፃፈውን ታሪካችንን አጥፉ!’ ብለን እርስ በርሳችን እየተገዳደልን ‘የእሳት ልጅ አመድ’ እንዲሉት ልንሆን አይገባንም። ሀሳቤን ወደመጠቅሉ ስመጣ ዛሬ ሦስት ነገር ብቻ ነው ልላችሁ የምፈልገው፦

    • አድዋ ትላንት! አድዋ ዛሬ! አድዋ ነገስ! ለእኛ እና ለልጆቻችን ምንድን ነው? ሁሌም ለሁላችንም አንድ ዓይነት ትርጉም ነው ሊኖረው የሚገባው – እሱም ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት የማይለየው ፍፁም የሆነ አንድነት ፍቅርና ሰላም ሁሌም ድል ሁሌም ማሸነፍ ብቻ ነው።
    • ትላንትና አባቶቻችን አንድ ብቻ ነበሩ፤ ዛሬም እኛ አንድ ነን፤ የነገውም ትውልድ አንድ ብቻ ይሆናል። እኛ አንድ እንጂ 80 ኢትዮጵያ የለችንም።
    • ትላንትና አባቶቻችን አሸናፊና ጀግና ብቻ ነበሩ፤ ዛሬም እኛ አሸናፊና ጀግና ብቻ ነን፤ የነገውም ትውልድ አሸናፊና ጀግና ብቻ ይሆናል። ጥላቻን፣ ክፋትን፣ መለያየትን ያሸነፈ ለሰላምና ለፍቅር ለአንድነት የተሸነፈ፣ ሃገሩንና ነፃነቱን ለማንም አሳልፎ የማይሰጥ ትውልድ ባለድል ነው። ቅድም ያልኩትን አሁንም እደግመዋለው – እኛ አንድ እንጂ 80 ኢትዮጵያ የለችንም። ስለዚህ ዛሬ ሁላችን በአድዋ ድል ስም ለራሳችን ቃል አነገባለን።

    “ጀግኖች አባቶቻንች በፅኑ ተጋድሎ ያወረሱንን ሀገርና ነፃነት እኛ እርስ በእርሳችን ተገዳድለን በነፃ ለጠላት ላንሰጥ ቃል እንገባለን” ቃላችሁን እንደምትጠብቁ አምናለሁ አመሰግናለሁ።

    መልካም የአድዋ ድል በዓል
    ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር።
    አቶ ኦባንግ ሜቶ

    የአድዋ ድል በዓል

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.