የኢትዮጵያ መንግሥት የዓረብ ሊግ በሕዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አወገዘ

Home Forums Semonegna Stories የኢትዮጵያ መንግሥት የዓረብ ሊግ በሕዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አወገዘ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #13828
    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የዓረብ ሊግ በሕዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ቁልፍ ጉዳዮችን ሳያገናዝብ ለአንድ ወገን ያደላ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት አወገዘ።

    የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፥ የዓረብ ሊግ የሕግ አስፈፃሚ ምክር ቤት የካቲት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ የደረሰበት ውሳኔ የሚያሳዝን ሆኖ ያገኘው መሆኑን እና ኢትዮጵያ ውሳኔውን በፍጹም የማትቀበለው መሆኑን ገልጿል።

    ኢትዮጵያ የሱዳን መንግሥት በዓረብ ሊግ ለቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ድጋፍ ላለመስጠት የወሰደውን አቋም እንደምታደንቅ በመግለጫው ተጠቅሷል።

    ሱዳን የተቀነባበረውን እና የዓረብ ሊግን አቋም ባለመደገፍ የምክንያታዊነት እና የፍትሕ ድምፅ መሆኗን ዳግመኛ ማረጋገጧን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ በመርህ ላይ ለተመሠረተው እና የሁሉም ወገን አሸናፊነትን መሠረት ላደረገው የሱዳን አቋም ወደር የለሽ አድናቆቷን ገልጻለች።

    ኢትዮጵያ ከዓረብ ሊግ ሀገራት ሕዝቦች እና መንግሥታት ጋር በጋራ እሴት፣ ባሕል እና ልማድ ላይ የተመሠረተ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት እንዳላት በመግለጫው ተጠቁሟል።

    የዓረብ ሊግ የተለያዩ ሉዓላዊ ሀገራትን ያቀፈ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የሁሉንም ወገን ፍላጎት ያካተተ እና ሚዛናዊ መስመር መያዝ እንደሚጠበቅበት በመግለጫው ተጠቅሷል።

    ከዚህ መስመር በተቃረነ መልኩ የሚሠራ ከሆነ ግን የሊጉ ተዓማኒነት እና በዚህ እጅጉን በተሳሰረ ዓለም ውስጥ ሰላምን፣ መረጋጋትን እና ትብብርን ለማምጣት ያለው አቅም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ እንደሚሆን ተገልጿል።

    በተለያዩ ጊዜያት ስትገልጽ እንደነበረው ሁሉ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን “የአሁኑን እና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት የዓባይን ውኃ ሃብት የመጠቀም መብት አለኝ” የሚለውን የዘለቀ እና የማይናወጥ አቋም በድጋሚ ገልጻለች።

    የዓባይ ወንዝ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑም ኢትዮጵያ በሌሎች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ሳይደርስ ውኃውን በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ መንገድ የመጠቀም መርህን ተከትላ እንደምትሠራ ተገልጿል።

    በተጨማሪም ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል እና አሠራር ላይ መሠረታዊ መፍትሔ የሚሰጠውን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነትን ተከትላ እንደምትሠራም ማረጋገጧ ተገልጿል።

    የዓረብ ሊግ እውነተኛውን መንገድ ተከትሎ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የዘለቀ እና የጋራ እሴቶች ላይ የተመሠረተውን ግንኙነት መሠረት በማድረግ እንደሚሠራ ኢትዮጵያ እንደምትተማመን በመግለጫው ተጠቅሷል።

    ወዳጅነትን ማጠናከር እና ለጋራ ግቦች ተቀራርቦ መሥራት የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑም ነው የተገለጸው።

      • የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ያወጣውን መግለጫ (እንግሊዝኛ) ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ።

    ምንጭ:- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    Ethiopia rejects Arab League resolution on GERD የዓረብ ሊግ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.