የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ተወሰነ
—–
የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ለጊዜው እንዲቋረጥ ውሳኔ መተላለፉን ውድድሩ በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. አስታወቀ።
የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ግንቦት 28 ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ በውድድሩ ከሚካፈሉ የእግር ኳስ ክለቡችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ፥ ውድድሮች በተገቢው መንገድ የሚካሄዱበት ዘላቂ መፍትሄ እስኪሰጥ ድረስ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ወሳኔ ላይ ደርሰዋል።
የተደረገውን የአስቸኳይ ስብሰባ ውሳኔ ተከትሎ ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ ለጊዜው እንዲሰረዝም ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ለፌዴሬሽኑ የሚቀርቡ የተለያዩ ጥያቄዎች በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ የውድድር ደንብ መሰረት እንዲታዩ ውሳኔ ተላልፏል።
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን