Home › Forums › Semonegna Stories › ሰሞነኛ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮችና ክለቦችን የተመለከቱ ዜናዎች
- This topic has 8 replies, 3 voices, and was last updated 2 years, 6 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
July 6, 2019 at 5:07 am #11316AnonymousInactive
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወሰናቸውን ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎችን እንዲመረምር እና ያላአግባብ የተወሰነበትን ፎርፌ እንዲያነሳ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የጠየቀ ሲሆን፥ ያቀረባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።
አዲስ አበባ – የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮቸ ራሱን ማግለሉን አስታወቀ።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ የቅዱስ ጊዮርጊስን የሜዳ ተጠቃሚነት ለማሳጣት ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ሊያደርገው የነበረን ጨዋታ በዝግ ወይም አዳማ ከተማ ላይ ተጫወቱ በማለት ሁለት ጊዜ እንዲቋረጥ አድርጎል ብሏል።
ይህን ጨዋታ ከዚህ በፊት የተቋረጡ የሌሎች ክለቦች ጨዋታወችን ባስተናገደበት ሁኔታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን አላስተናገደም ሲል በፌዴሬሽኑ ላይ ቅሬታውን አቅርቧል።
እንዲሁም በ29ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የተሰጠው ፎርፌ አግባብነት የሌለውና አድሏዊ መሆኑንም ነው በመግለጫው ያመላከተው።
አዲስ ከመጡት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በመተባበር፣ በመቻቻል እና በመተጋገዝ ለመሥራት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷልም ነው ያለው።
በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የወሰናቸውን ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎችን እንዲመረምር እና ያላአግባብ የተወሰነበትን ፎርፌ እንዲያነሳ የጠየቀ ሲሆን፥ ያቀረባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ. / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- ኢትዮጵያ ቡና የአዲስ አበባ ዋንጫ አሸናፊ ሆነ
- ከመጣንበት መንገድ በላይ የሚቀረን ይከብዳል!! (ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች)
- የኢትዮጵያ ቡና ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር አዳማ ላይ አልጫወትም አለ፤ በዒድ አል ፈጥር ምክንያት ጨዋታው በድጋሚ ተራዝሟል
July 7, 2019 at 2:08 am #11320AnonymousInactiveፌዴሬሽኑ ዛሬም የሸገር ክለቦችን በአደባባይ እየናቀ ነው
(ከቡና ሠማይ ሥር)
—–ኳስ ክብ መሆኗን የፌዴሬሽን ወንበር ላይ ከተቀመጡ በኋላ ያወቁት የኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኝ አመራሮች በዘር ተቧድነው በደካማ ውሳኔቸው የእግር ኳሱን የቁልቁሊት ጉዙ እያፈጠኑት ይገኛሉ።
ይህ አዲስ አበባ ጠል የሆነው እግር ኳስ ፌዴሬሽን አምና የኤሌትሪክ እግር ኳስ ክለብን በግፍ ከሊጉ ያሰናበተው ፌዴሬሽን ዘንድሮ ደግሞ የግፍ አርጩሜውን መከላከያ እግር ኳስ ክለብ ላይ አሳርፏል።
የስሑል ሽረ እና የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ (ወልዋሎ ዓ. ዩ.) ጨዋታ ከነመከላከያ እና ከደቡብ ፖሊስ ጋራ የመትረፍ እና የመውረድ አደጋ ውስጥ ያለው። ስሑል ሽረ ቀደም ብሎ እንዲጫወት እንዲሁም እስከ 71ኛው ደቂቃ ድረስ በወልዋሎ ዓ. ዩ. አንድ ለዜሮ ሲመራ የነበረው ስሑል ሽረ ደጋፊው ሜዳ ውስጥ ገብቶ ለአርባ አምስት ደቂቃ ያህል ጨዋታውን ካቋረጠ በኋላ ዋና አሰልጣኙ ዮሃንሰ ሳህሌ ጨዋታውን እንዳይመራ በማድረግ ውጤቱን በግፍ ነጥቋል። በየጨዋታው ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ በመመደብ ጨዋታውን በአምስት ካሜራ እና በሦስት ኮሜሽነር ሲቆጣጠር የነበረው ፌዴሬሽን ጉዳዩን ባላየ በማለፍ መከላከያን ከሊጉ እንዲወረድ አድርጓል።
በሸገር ክለቦች ላይ ግፍ መሥራት የማይሰለቸው ፌዴሬሽን የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን የዋንጫ ፉክክር ውስጥ እያለ ቀሪ ጨዋታዬን ሳልጫወት ወደ ጎንደር በማቅናት ከፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ጋር አልጫወትም በማለት ተገቢ ጥያቄ እያቀረበ ቢገኝም ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ‘ምን ታመጣላቹ!?’ በሚል በእብሪት በተሞላበት እና ባላዋቂነት ውሳኔ ፎርፌ በመስጠት ዛሬም ለሸገር ክለብ ያለውን ንቀት አሳይቷል።
አሁን ከዚህ በብሄር ከተደራጀው ሊግ እና በዘር ከተቧደነው ፌዴሬሽን ጋር አብሮ መቀጠል የማያዋጣበት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረስን ይመስለኛል ስለዚህ የከተማውን ሊግ ሳይውል ሳያድር ይፋ ማድረግ ምርጫ የሌለው መፍትሄ ነው።
የአዲስ አበባ ክለቦች መግለጫ ከማውጣት እና የአንድ ሰሞን አጀንዳ ከመሆን በዘለለ አትኩሮት በመስጠት የተሻለ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
እግር ኳስ ሳይገባው እግር ኳስ ላይ ከተቀመጠ አመራር ጋራ መለያያት ይመጨረሻው አማራጭ ነው።
(ከቡና ሠማይ ሥር)July 7, 2019 at 11:46 pm #11326AnonymousInactiveመቐለ 70 እንደርታ የ2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሆነ
—–አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – መቐለ 70 እንደርታ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ዛሬ ድሬ ዳዋ ከነማን 2ለ1 በመርታት ዋንጫ አንስቷል።
ከስሑል ሽረ ጋር የተገናኘው ፋሲል ከነማ 1ለ1 በሆነ አቻ ግብ ሲለያይ መቐለ 70 እንደርታ ድሬ ዳዋን 2ለ1 በሆነ ልዩነት በመርታት ነው አሸናፊ የሆነው።
መቐለ 70 እንደርታ ከድሬ ዳዋ ከነማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ለመቐለ 70 እንደርታ ኦሴይ ማውሊ (በጨዋታው የመጀመርያ የመጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት) እና አማኑኤል ገብረሚካኤል (በሀምሳ አራተኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት) ሲሆኑ፤ ለድሬ ዳዋ ከነማ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ኤልያስ ማሞ (በሰባ ዘጠነኛው ኛው ደቂቃ ላይ) ነበር።
መቀመጫውን መቐለ ከተማ ያደረገውና ራሱን በአዲስ መልክ በ2000 ዓ.ም. ካዋቀረ በኋላ በ 2010 ዓ.ም. ፕሪምየር ሊጉን የተቀላቀለው መቐለ 70 እንደርታ የእግር ኳስ ክለብ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሲያሸንፍ ለመጀመርያ ጊዜው ነው።
በፕሪምየር ሊጉ ማጠናቀቂያ ዕለት (ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም.) በተካሄዱ ጨዋታዎች ደደቢትን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ 5ለ2 በሆነ ሰፊ ልዩነት ረቷል። ሲዳማ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 3 ለ0፣ ኢትዮጵያ ቡና ከመከላከያ 3ለ4፣ ጅማ አባጅፋር ከደቡብ ፖሊስ 3ለ2 እና አዳማ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ 0ለ3 ተለያይተው የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጠናቋል።
https://semonegna.com/wp-content/uploads/2019/07/Mekelle-70.jpg
September 5, 2019 at 11:36 pm #11890AnonymousInactiveኢትዮጵያ ቡና ክለብ ካሳዬ አራጌን በይፋ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ
አዲስ አበባ (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ነሃሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ ሾሟል።
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ እና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በዕለቱ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተካሄደ ዝግጅት በይፋ የፊርማ ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል። በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይም የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት መቶ አቀላ ፈቃደ ማሞ፣ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ስንታየሁ በቀለ እና የደጋፊ ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ክፍሌ አማረ ተገኝተዋል።
በስምምነቱ መሠረትም አሳልጣኝ ካሳዬ አራጌ ክለቡን ለ4 ዓመታት በአሰልጣኝነት የሚመራ ሲሆን፥ በውሉ መሠረት የመጀመሪያው ዓመት ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደሚሠራ ተገልጿል። በቀሪዎቹ 3 ዓመታት ግን ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን ይዞ መጨረስ እንዳለበት ቅድመ ሁኔታ በውሉ ላይ ተቀምጧል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይም የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወደ ቡና መምጣት የቀድሞ የክለቡን አጨዋወት እንደሚመልስ ተስፋ እንደጣለ ተነግሯል። አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ባሳለፈው የተጫዋችነት ጊዜ ይለብስ የነበረው 15 ቁጥር ማልያም በወቅቱ በነበረው መልክ ታትሞ ተበርክቶለታል።
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የሥራ አመራር ቦርድ አዲስ የአሰልጣኝ ቅጥርን የሚያከናውን የእግር ኳስ ኦፕሬሽንና ቴክኒክ አስተዳደር ኮሚቴ አዋቅሮ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወሳል።
የክለቡን የጨዋታ ዘይቤ ይረዳል በሚል የቀድሞውን የክለቡን ኮከብ ካሳዬ አራጌን በአሰልጣኝነት እንዲመረጥ በወሰነው መሰረትም ምርጫው ተካሂዷል።
ካሳዬ አራጌ በዕለቱም በይፋ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ በመሆን የፈረመ ሲሆን፥ በቀጣይ የውድድር ዘመንም ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት የሚመራ ይሆናል።አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከ1979 እስከ 1994 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቡናን በመሃል ሜዳ ተጫዋችነት ያገለገለ ሲሆን፥ ከተጫዋችነት ዘመኑ በኋላም ለ1 ዓመት ከ6 ወር ገደማ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝነት መርቷል። ከኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ጋር በነበረው የ1 ዓመት ከግማሽ ቆይታው የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ከክለቡ ጋር ማንሳት እንደቻለ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ
December 10, 2019 at 2:02 pm #12911SemonegnaKeymasterየኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና አሞሌ ዲጂታል ዋለት ድርጅት የአዲስ አበባ ስታዲየም የትኬት ሽያጭን በጋራ ለማከናወን ስምምነት አደረጉ
—–አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና አሞሌ ዲጂታል ዋለት ድርጀት (ዳሸን ባንክ) [Amole Digital Wallet] የአዲስ አበባ ስታዲየም የትኬት ሽያጭን በዘመናዊ መንገድ ለማከናወን የሚያስችላቸውን ስምምነት በተወካዮቻቸው ተፈራርመዋል። በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ስታዲየም የመግቢያ ትኬቶች በሙሉ በአሞሌ የገንዘብ መቀበያዎች ማለትም በሁሉም የፖስታ ቤቶች፣ ሸዋ ሱፐር ማርኬት፣ ህዳሴ ቴሌኮም እና ዳሽን ባንክ (በሁሉም ቅርንጫፎች) እና አሞሌ በሚያዘጋጃቸው ሌሎች ተቋማት የሚከናወን ይሆናል።
በዚህም መሠረት ስፖርት ክለቡ አዲስ አበባ ስታድየም ውስጥ ለሚያደርጋቸው ውድድሮች የእጅ በእጅ የትኬት ሸያጭ በየትኛዎቹም የስታዲየሙ በሮች እንደማይከናወን ክለቡ አስታውቋል።
ክለቡ በተጨማሪ እንዳስታወቀው፥ የዓመት የስታዲየም ቅድመ-ክፍያ ሲከፍሉ የነበሩ 289 ደንበኞች አሁንም በቅድሚያ ቦታቸውን ማስከበር የሚችሉ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለሁሉም በስታዲየሙ ለሚደረጉ ውድድሮች አጠቃላይ ሲጠየቅበት የነበረው የክፍያ ሂደትም ማስተካከያ ተደርጎበታል። ይህም የዓመት ክፍያ ከሁለቱ የከተማው ቡድኖች የደርሶ-መልስ ውድድር ውጪ የሚፈልጉትን ቡድን የዓመት ክፍያ መክፈል የሚያስችል ማሻሻያን ማድረግ ተችሏል።
በመሆኑም የዓመት ክፍያው 9,000 (ዘጠኝ ሺህ) ብር ሲሆን ይህም የሁለቱንም ቡድኖች ሙሉ ጨዋታዎችን (30 ጨዋታዎች) ለመመልከት የሚያስፈልግ የብር መጠን ነው። ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ ብቻ ለመመልከት የፈለገ ተመልካች የ14 ጨዋታዎች 4,200 (አራት ሺህ ሁለት መቶ) ብር የሚከፍል ሲሆን የሁለቱን የከተማው ደርቢ ጨዋታዎችን እንደ ማንኛውም ተመልካች ከአሞሌ የገንዘብ መቀበያዎች ገዝቶ የሚገባ ይሆናል። ከሌሎች የዓመት ክፍያ ከሌላቸው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናል። ሁለቱም የከተማው ቡድኖች ጨዋታዎች በሁለቱ ክለቦች ስምምነት የሚፈፀም ይሆናል።
በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ስታዲየም የመግቢያ ዋጋ የሚከተለው ይሆናል
- ክቡር ትሪቡን፦ 300 ብር
- ጥላ ፎቅ፦ 200 ብር
- ከማን አንሼ ባለ ወንበር፦ 100 ብር
- ከማን አንሼ ወንበር የሌለው፦ 50 ብር
- ካታንጋ፦ 30 ብር
- ሚስማር ተራ እና የንጋት ኮከብ፦ 20 ብር
የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብዓመታዊ የክቡር ትሪቢዩን የመግቢያ ትኬቶች ከኅዳር 27 ቀን 2019 ዓ.ም. ጀምሮ ጀምሮ እየተሸጠ ይገኛል።
ስለ አሞሌ ዲጂታል ዋለት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
January 29, 2020 at 12:34 am #13455SemonegnaKeymasterየኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተረከቡ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አስረከበ።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በርካታ ደጋፊዎችን በመያዝና የአዲስ አበባ ከተማ ተወካዮች በመሆን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ እየሳተፉ ለሚገኙት ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታውን ያስረከቡት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሁለቱ ክለቦች ከወራት በፊት የስታድየም እና ሁለገብ የስፖርት ማዕከል መገንቢያ የሚሆኑ የመሬት ይዞታዎችን እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር።
የሁለቱ ክለቦች የቦርድ የሥራ አመራሮች፣ የደጋፊ ማኅበር ተወካዮች፣ የክለቦቹ ደጋፊዎች እና የከተማ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በከንቲባው ጽሕፈት ቤት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ምክትል ከንቲባው ባደረጉት አጠር ያለ ንግግር ሁለቱን ክለቦች መደገፍ እና የከተማዋን አብዛኛውን ወጣቶች ፍላጎት መደገፍ ተገቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል። ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ እንደገለጹት፥ ሁለቱ ክለቦች የከተማዋ አምባሳደር ከመሆናቸውም ባለፈ በስፖርታዊ ጨዋነት እና በከተማዋ ሁለንተናዊ ሰላምን በማረጋገጥ፣ ወንድማማችነትን በመስበክ የበኩላቸው ሚና እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ሁለቱ ክለቦች በከተማዋ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጎለብት እና ወጣቱ ጊዜውን አልባሌ ስፍራ በመዋል ወይም አልባሌ ሥራ በመሥራት እንዳያሳልፍና እንዲቆጠብ ለሚያርጉት አዎንታዊ ተግባር የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ኢንጂነር ታከለ ተናግረዋል።
‘የከተማው አስተዳደር ከሁለቱ ክለቦች ጋር መሥራት ግዴታው ነው፤ የስታድየም ማስፋፊያ የመሬት ይዞታውን ከመስጠት ባሻገርም ክለቦቹ ለሚያከናውኗቸው ግንባታዎች በመዋዕለ አቅም ለመደገፍም አስተዳደሩ ዝግጁ ነው። ለክለቦቹ ከመሬት ይዞታው በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ስር ከሚገኙ የወጣት ማዕከላት መካከል ሁለት የወጣት ማዕከላትን ለሁለቱ ክለቦች በመስጠት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለቦች እንዲያስተዳድሯቸው በስጦታ ለመስጠት ዕቅድ አለው” ብለዋል ኢንጂነር ታከለ።
የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አመራሮችም በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ ለስታዲየም መገንቢያ የቦታ ይዞታ መረጋገጫ ከመስጠት ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረጉ በደጋፊዎቻቸው እና በእግር ኳስ ክለቦቹ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
August 22, 2020 at 1:12 am #15511SemonegnaKeymasterየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በቀጥታ ለሚያሠራጩ የሚዲያ ተቋማት ሊሸጥ መሆኑ ተገለጸ
የሀገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት በ2013 በጀት ዓመት በሚያከናውኗቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሁለት ውይይት አካሂደዋልአዲስ አበባ (ሰሞነኛ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የኢትዮጵያን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በቴሌቭዥን ማስተላለፍ ለሚችሉ የሚዲያ ተቋማት ሊሸጥ መሆኑ ታውቋል።
የፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒው በቀጣይ የሚካሄደውን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በቀጥታ የቴሌቭዥን ሥርጭት የማስተላለፍ ፈቃድ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ የሚዲያ ተቋማት ለመሸጥ ጨረታ ሊያወጣ መሆኑ ተሰምቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ሊግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የፕሪሚየር ሊግ ውድድሩን ስም ለመሸጥ በሚቀጥለው ሳምንት ጨረታ እንደሚያወጣ ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ከቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት እና ከውድድር ስያሜ ሽያጭ የሚያገኘው ገቢ የካምፓኒውን እና የተወዳደዳሪ ክለቦችን የገንዘብ (financial) አቅም ያሳድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።
ከስፖርቱ ዜና ሳንወጣ፥ የሀገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት በ2013 በጀት ዓመት በሚያከናውኗቸው ጉዳዮች ዙሪያ ለሁለት ቀናት የተካሄደው ውይይት ተጠናቋል። በውይይቱ ላይ ከተነሱት ጉዳዮች ዋነኛው በጥናት ተለይቶ የወጣውን የስፖርት ማሻሻያ መርሀ ግብር (Sport Reform Program) ተግባራዊ በማድረግ ሕዝባዊ አደረጃጀቱን የማጠናከር ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ ተገልጿል።
የሀገራችን ስፖርት ፖሊሲ ስፖርቱን በበላይነት የመምራት ኃላፊነት በዋናነት ለሕዝባዊ የስፖርት አደረጃጀቶች ይሰጣል። ፖሊሲው ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት ያለው እና ጠንካራ አደረጃጀት ሊፈጠር እንደሚገባ ጨምሮ ያስቀምጣል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ 20 ፌዴሬሽኖች ፣ ዘጠኝ ማኀበራት (associations) እንዲሁም ሁለት ኮሚቴዎች በአጠቃላይ 31 የስፖርት ማኀበራት ከኢፊድሪ ስፖርት ኮሚሽን እውቅና ወስደው የተመዘገቡበትን የስፖርት ዓይነት ለማሳደግ እና ለማስፋፋት እንዲሁም ውጤት ለማስመዝገብ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ የስፖርት ማኀበራት በ2013 በጀት ዓመት በሚያከናውኗቸው ዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ ነሐሴ 12 እና 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ዕቅዳቸውን አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።
በቀረበው ዕቅድም የስፖርት ማኀበራቱ እራሳቸውን በሰው ኃይል እና በገንዘብ (personnel and finance) ከማጠናከር፣ አደረጃጀታቸውን ከማስፋፋትና የተደራጁትንም በመደገፍ ረገድ ሊሠሯቸው ያሰቧቸውን ተግባራት አቅርበዋል። እንዲሁም የታዳጊ ወጣቶች ስልጠናን ከማስፋፋት እና ተተኪዎችን ከማፍራት፣ የባለሙያዎችን (ዳኞች እና አሰልጣኞች) አቅም ከመገንባት አንፃር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ አብራርተዋል።
በተጨማሪም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠውን እና ወደ በ2021 ይካሄዳል ተብሎ በሚታሰበው ቶክዮ ኦሎምፒክ እና ፓራሊምፒክ ለመሳተፍ እና ውጤት ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅት መጀመራቸውን ገልፀዋል። በሌላ በኩል የስፖርት ማኀበራት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅተው አቅርበዋል።
በቀረበው ዕቅደም ወረረሽኙ በስፖርቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን የተገለፀ ሲሆን፥ በተለይ ስፖርቱን የሕይወታቸው መሠረት እና መተዳደሪያቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ የስፖርት ቤተሰቦች ክፉኛ መጎዳታቸውን አንስተዋል። በተጨማሪም ውድድርና ስልጠናዎች በመቆማቸው ከውድድር ገቢ፣ ከስፖንሰርሺፕ፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገኙ ገቢዎች በመቆማቸው መቸገራቸውን እና መንግሥትም ችግሩን ተረድቶ አፋጣኝ መፍትሔ ሊፈልግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የቀረበውን ዕቅድ ያዳመጡት የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር የስፖርት ማኀበራት በጥናት ተለይቶ የተዘጋጀውን የስፖርት ማሻሻያ መርሀ ግብር (Sport Reform Program) ጋር ራሳቸውን በማስተዋወቅ እና የእቅዳቸው አካል በማድረግ ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ሕዝባዊ አደራጀቱን የማጠናከር ሥራ በ2013 በጀት ዓመት ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራ ሥራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን፥ በተለይ አመራሩ ወደ ማኀበሩ ሲመጣ ስፖርቱን ሊቀይርና ሊያሻግር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በሕዝባዊ አደረጃጀቱ ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር በመዘርጋት፣ ደንብ እና መመሪያን መሠረት በማድረግ በነፃነት የሚሠራበት ተቋም መገንባት እንደሚያስፈልግ ለዚህም በቅንጅትና በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል።
የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ በበኩቸው በመድረኩ የስፖርት ማኀበራት በ2012 ዓ.ም ያከናወኗቸውን ተግባራት፣ ያጋጠሟቸውን ችግሮች እና ጥንካሬና ድክመታቸውን የተገንዘብንበት ነበር ብለዋል። ያቀረቡት ዕቅድም ኮሚሽኑ ካስቀመጠላቸው አቅጣጫ እና ከራሳቸውን ነባራዊ ቁመና ጋር በማጣጣም የስፖርት ልማትን፣ ውድድርን፣ ስልጠናን እና አደረጃጀትን መሠረት ያደረገ ዕቅዱም በበጀት የተደገፈ እንደሆነ ጠቁመዋል። በመሆኑም የታቀደው ዕቅድ ተግባራዊ እንዲሆን እና ወደ ውጤት ለመቀየር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ትልቅ ስጋት ቢሆንም፥ ለዕቅዱ ተግባራዊነት ኮሚሽኑ በሰው ኃይል እና በገንዘብ አቅሙ በፈቀደ መጠን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ዱቤ ጅሎ አስታውቀዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችል ሰነድ በማዘጋጀት ለመንግሥት ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን
December 29, 2020 at 2:15 am #17168AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የዘላቂ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በባለአክሲዮን ብዛት ከቀዳሚ ባንኮች ተርታ የሚመደበው ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ እና በደጋፊ ቁጥር ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የዘላቂ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ።
ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ እና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በሁሉም ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የጋራ ስምምነት ተፈራርመው ወደሥራ መግባታቸውን ይፋ ያደረጉት ታኅሣሥ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በሃያት ሪጀንሲ አዲስ አበባ ሆቴል በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ስምምነቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፥ ባንኩም ሆነ ክለቡ የሚጋሩት ስም የሁሉም ኢትዮጲያዊ ከመሆኑ ባሻገር ሕዝባዊ መሠረት ያላቸው መሆናቸው አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ መለያቸው ነው ተብሏል።
ስምምነቱ የተፈረመው በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ እና በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ሲሆን፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የባንኩና የክለቡ የሥራ አመራር አባላት ተገኝተዋል። በስምምነቱ መሠረትም ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የአምስት ሚሊዮን ብር የአንድ ዓመት ስፖንሰርሺፕ ክፍያ የሚከፍል ሲሆን ስምምንቱም በየዓመቱ የሚታደስ ይሆናል።
በስምምነቱ መሠረት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የባንኩን አርማ በተጫዋቾች ቲሸርትና ላይ በማሳየት ባንኩን ያስተዋውቃል። በተጨማሪም በሜዳውም ይሁን ያለሜዳው ጨዋታ በሚኖረው ወቅት የባንኩ ቢልቦርድ ማስታወቂያ በጨዋታው ሜዳ አካባቢ እንዲቀመጥ ያደርጋል። ክለቡ በተቻለው መጠን የባንኩን ብራንድ እና አገልግሎቶች እንዲያስተዋውቅም በስምምነቱ ተካትቷል።
ስምምነቱ ከዚህ በተጨማሪ የስፖርት ክለቡ የባንክ ሂሳቡን በባንኩ እንዲከፍት ከማድረግ ጀምሮ የክለቡ አባላትና ደጋፊዎች የባንኩ ደንበኛ እንዲሆኑ ማድረግን የመሳሰሉ የባንክ አገልግሎቶችን ከባንኩ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ተብሏል።
እንደስምምነቱ ቡና ባንክ በበኩሉ የስፖርት ክለቡ ደጋፊዎች ማኅበር ወርሃዊ የአባልነት መዋጮአቸውን በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሠራር በመታገዝ በባንኩ በኩል እንዲከፍሉ የሚያስችላቸው አሠራር ይዘረጋል፤ በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ የክለቡ አባላትም የባንክ አገልግሎት እገዛ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ቡና ባንክ እና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እንደስማቸው አንድ መሆን የጋራ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ሌሎች በርካታ ሥራዎችንም በጥምረት ለመሥራት መስማማታቸውን ነው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ያበሰሩት።
ከተመሠረተ 11 ዓመታት የሆነውና ከ13 ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የእግር ኳስ ስፖርቱን በመደገፍና በዓለም አደባባይ አርማውን በማስተዋወቅ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የተሰለፈ ባንክ ሆኗል። ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ከ582 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉንም በዚያው ሳምንት አሳውቋል። የባንኩ ሀብት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የ4.4 ቢሊዮን ብር ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ጠቅላላ ሀብቱም ወደ 18.9 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ ከባንኩ ጠቅላላ ሀብት ውስጥ የተጣራ ብድር 60.9 በመቶውን በመሸፈን ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል ሲል ባንኩ የ2012 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አሳውቋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ
July 9, 2022 at 5:07 am #48425SemonegnaKeymasterየ2014 ዓ.ም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከቦች ተሸለሙ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የ2014 ዓ.ም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመዝጊያ እና የውድድር ዓመቱ ምርጦች ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ሰኔ 30 ቀን፥ 2014 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል። በሥነ-ሥርዓቱም ላይ በውድድር ዓመቱ በየዘርፉ ምርጥ ብቃት ያሳዩ ኮከቦች ተለይተው ተሸልመዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የውድድር ዓመቱ ኮከብ ተጫዋቾችን ይፋ ያደረጉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ሲሆኑ፥ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጫዋች ጋቶች ፓኖም የውድድር ዓመቱ ኮከብ ተጫዋች በመሆን ተመርጧል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለብ (ፈረሰኞቹ) ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ቻምፒዮንነት ክብራቸው ተመልሰው አስራ አምስተኛውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ባነሱበት በዘንድሮው የውድድር ዓመት አስደናቂ ብቃቱን በማሳየት ለክለቡ ስኬት ትልቅ ሚና የነበረው ጋቶች ፓኖም ከክብር እንግዳው እጅ የ210 ሺህ ብር እና የማስታወሻ ዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል።
በተመሳሳይ ፈረሰኞቹ ገና በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ አካባቢ አዲስ ከቀጠሯቸው ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ጋር መለያየታቸውን ተከትሎ የውድድር ዓመቱን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ፈረሰኞቹን እየመራ ለቻምፒዮንነት ክብር ያበቃው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የውድድር ዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ በመሆን ተመርጧል። በዚህም ከክብር እንግዳው የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አሥራት ኃይሌ የ200 ሺህ ብር እና የክብር ዋንጫውን ተቀብሏል።
የ2014 ዓ.ም የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመባል የዋንጫ እና የአንድ መቶ ሀምሳ ሺህ ብር ተሸላሚም የቅዱስ ጊዮርጊሱ ቻርለስ ሉክዋጎ ሆኗል። ዩጋንዳዊው የግብ ጠባቂ በተወካዩ አማካኝነት ሽልማቱን ከቀድሞ ግብ ጠባቂ በለጠ ወዳጆ እጅ ተቀብሏል። የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች የሆነው የሲዳማ ቡናው ተጫዋች ይገዙ ቦጋለ የዋንጫ እና የ2 መቶ ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል። ይገዙ ቦጋለ በውድድር ዓመቱ ለክለቡ ምርጥ አቋም በማሳየት አስራ ስድስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ነው ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለው።
የውድድር ዓመቱ ምርጥ ዋና ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው (ዶ/ር) ሆኖ ሲመረጥ፥ የ105 ሺህ ብር እና የዋንጫ ሽልማት ከቀድሞ ዳኛ ኃይለመላክ ተሰማ እጅ ተቀብሏል። በተመሳሳይ የውድድር ዓመቱ ምርጥ ረዳት ዳኛ በመሆን ትግል ግዛው የ105 ሺህ ብር እና የዋንጫ ሽልማቱን ከቀድሞ ዳኛ ይግዛው ብዙአየሁ ተቀብሏል።
የውድድር ዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው ዓመቱን በሀዋሳ ከተማ ጀምሮ በጅማ አባጅፋር ያገባደደው አልዓዛር ማርቆስ ከክብር አንግዳው የቀድሞ የፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች አንዋር ያሲን እጅ የ105 ሺህ ብር እና የዋንጫ ሽልማቱን ተረክቧል።
በ2014 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ለእያንዳንዳቸው ከሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ዘጠና ስድስት ሺህ ሦስት መቶ ሰባ ሦስት (7,696,373) ብር እስከ አስር ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ዘጠና አራት ሺህ ስምንት መቶ አስራ ዘጠኝ (10,994,819) ብር ተበርክቶላቸዋል።
በተጨማሪም ውድድሮቹን በማስተናገድ ላይ ለነበሩት ለአምስቱም ስታድየሞች ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ሚሊዮን ብር ተበርክቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ዓመቱን በደማቅ ሁኔታ በማጠናቀቁ እንዲሁም በኮከብነት ለተሸለሙት በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ሲል ልባዊ ደስታውን ገልጿል።
ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ዕለታዊ ጋዜጣ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.