Search Results for 'የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ'

Home Forums Search Search Results for 'የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ'

Viewing 5 results - 1 through 5 (of 5 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የዘላቂ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በባለአክሲዮን ብዛት ከቀዳሚ ባንኮች ተርታ የሚመደበው ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ እና በደጋፊ ቁጥር ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የዘላቂ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ።

    ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ እና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በሁሉም ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የጋራ ስምምነት ተፈራርመው ወደሥራ መግባታቸውን ይፋ ያደረጉት ታኅሣሥ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በሃያት ሪጀንሲ አዲስ አበባ ሆቴል በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ስምምነቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፥ ባንኩም ሆነ ክለቡ የሚጋሩት ስም የሁሉም ኢትዮጲያዊ ከመሆኑ ባሻገር ሕዝባዊ መሠረት ያላቸው መሆናቸው አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ መለያቸው ነው ተብሏል።

    ስምምነቱ የተፈረመው በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ እና በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ሲሆን፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የባንኩና የክለቡ የሥራ አመራር አባላት ተገኝተዋል። በስምምነቱ መሠረትም ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የአምስት ሚሊዮን ብር የአንድ ዓመት ስፖንሰርሺፕ ክፍያ የሚከፍል ሲሆን ስምምንቱም በየዓመቱ የሚታደስ ይሆናል።

    በስምምነቱ መሠረት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የባንኩን አርማ በተጫዋቾች ቲሸርትና ላይ በማሳየት ባንኩን ያስተዋውቃል። በተጨማሪም በሜዳውም ይሁን ያለሜዳው ጨዋታ በሚኖረው ወቅት የባንኩ ቢልቦርድ ማስታወቂያ በጨዋታው ሜዳ አካባቢ እንዲቀመጥ ያደርጋል። ክለቡ በተቻለው መጠን የባንኩን ብራንድ እና አገልግሎቶች እንዲያስተዋውቅም በስምምነቱ ተካትቷል።

    ስምምነቱ ከዚህ በተጨማሪ የስፖርት ክለቡ የባንክ ሂሳቡን በባንኩ እንዲከፍት ከማድረግ ጀምሮ የክለቡ አባላትና ደጋፊዎች የባንኩ ደንበኛ እንዲሆኑ ማድረግን የመሳሰሉ የባንክ አገልግሎቶችን ከባንኩ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

    እንደስምምነቱ ቡና ባንክ በበኩሉ የስፖርት ክለቡ ደጋፊዎች ማኅበር ወርሃዊ የአባልነት መዋጮአቸውን በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሠራር በመታገዝ በባንኩ በኩል እንዲከፍሉ የሚያስችላቸው አሠራር ይዘረጋል፤ በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ የክለቡ አባላትም የባንክ አገልግሎት እገዛ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

    ቡና ባንክ እና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እንደስማቸው አንድ መሆን የጋራ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ሌሎች በርካታ ሥራዎችንም በጥምረት ለመሥራት መስማማታቸውን ነው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ያበሰሩት።

    ከተመሠረተ 11 ዓመታት የሆነውና ከ13 ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የእግር ኳስ ስፖርቱን በመደገፍና በዓለም አደባባይ አርማውን በማስተዋወቅ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የተሰለፈ ባንክ ሆኗል። ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ከ582 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉንም በዚያው ሳምንት አሳውቋል። የባንኩ ሀብት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የ4.4 ቢሊዮን ብር ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ጠቅላላ ሀብቱም ወደ 18.9 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ ከባንኩ ጠቅላላ ሀብት ውስጥ የተጣራ ብድር 60.9 በመቶውን በመሸፈን ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል ሲል ባንኩ የ2012 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አሳውቋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ

    ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ

    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተረከቡ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አስረከበ።

    በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በርካታ ደጋፊዎችን በመያዝና የአዲስ አበባ ከተማ ተወካዮች በመሆን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ እየሳተፉ ለሚገኙት ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታውን ያስረከቡት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሁለቱ ክለቦች ከወራት በፊት የስታድየም እና ሁለገብ የስፖርት ማዕከል መገንቢያ የሚሆኑ የመሬት ይዞታዎችን እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር።

    የሁለቱ ክለቦች የቦርድ የሥራ አመራሮች፣ የደጋፊ ማኅበር ተወካዮች፣ የክለቦቹ ደጋፊዎች እና የከተማ  የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በከንቲባው ጽሕፈት ቤት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ምክትል ከንቲባው ባደረጉት አጠር ያለ ንግግር ሁለቱን ክለቦች መደገፍ እና የከተማዋን አብዛኛውን ወጣቶች ፍላጎት መደገፍ ተገቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል። ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ እንደገለጹት፥ ሁለቱ ክለቦች የከተማዋ አምባሳደር ከመሆናቸውም ባለፈ በስፖርታዊ ጨዋነት እና በከተማዋ ሁለንተናዊ ሰላምን በማረጋገጥ፣ ወንድማማችነትን በመስበክ የበኩላቸው ሚና እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ሁለቱ ክለቦች በከተማዋ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጎለብት እና ወጣቱ ጊዜውን አልባሌ ስፍራ በመዋል ወይም አልባሌ ሥራ በመሥራት እንዳያሳልፍና እንዲቆጠብ ለሚያርጉት አዎንታዊ ተግባር የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ኢንጂነር ታከለ ተናግረዋል።

    ‘የከተማው አስተዳደር ከሁለቱ ክለቦች ጋር መሥራት ግዴታው ነው፤ የስታድየም ማስፋፊያ የመሬት ይዞታውን ከመስጠት ባሻገርም ክለቦቹ ለሚያከናውኗቸው ግንባታዎች በመዋዕለ አቅም ለመደገፍም አስተዳደሩ ዝግጁ ነው። ለክለቦቹ ከመሬት ይዞታው በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ስር ከሚገኙ የወጣት ማዕከላት መካከል ሁለት የወጣት ማዕከላትን ለሁለቱ ክለቦች በመስጠት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለቦች እንዲያስተዳድሯቸው በስጦታ ለመስጠት ዕቅድ አለው” ብለዋል ኢንጂነር ታከለ።

    የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አመራሮችም በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ ለስታዲየም መገንቢያ የቦታ ይዞታ መረጋገጫ ከመስጠት ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረጉ በደጋፊዎቻቸው እና በእግር ኳስ ክለቦቹ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች


    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና አሞሌ ዲጂታል ዋለት ድርጅት የአዲስ አበባ ስታዲየም የትኬት ሽያጭን በጋራ ለማከናወን ስምምነት አደረጉ
    —–

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና አሞሌ ዲጂታል ዋለት ድርጀት (ዳሸን ባንክ) [Amole Digital Wallet] የአዲስ አበባ ስታዲየም የትኬት ሽያጭን በዘመናዊ መንገድ ለማከናወን የሚያስችላቸውን ስምምነት በተወካዮቻቸው ተፈራርመዋል። በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ስታዲየም የመግቢያ ትኬቶች በሙሉ በአሞሌ የገንዘብ መቀበያዎች ማለትም በሁሉም የፖስታ ቤቶች፣ ሸዋ ሱፐር ማርኬት፣ ህዳሴ ቴሌኮም እና ዳሽን ባንክ (በሁሉም ቅርንጫፎች) እና አሞሌ በሚያዘጋጃቸው ሌሎች ተቋማት የሚከናወን ይሆናል።

    በዚህም መሠረት ስፖርት ክለቡ አዲስ አበባ ስታድየም ውስጥ ለሚያደርጋቸው ውድድሮች የእጅ በእጅ የትኬት ሸያጭ በየትኛዎቹም የስታዲየሙ በሮች እንደማይከናወን ክለቡ አስታውቋል።

    ክለቡ በተጨማሪ እንዳስታወቀው፥ የዓመት የስታዲየም ቅድመ-ክፍያ ሲከፍሉ የነበሩ 289 ደንበኞች አሁንም በቅድሚያ ቦታቸውን ማስከበር የሚችሉ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለሁሉም በስታዲየሙ ለሚደረጉ ውድድሮች አጠቃላይ ሲጠየቅበት የነበረው የክፍያ ሂደትም ማስተካከያ ተደርጎበታል። ይህም የዓመት ክፍያ ከሁለቱ የከተማው ቡድኖች የደርሶ-መልስ ውድድር ውጪ የሚፈልጉትን ቡድን የዓመት ክፍያ መክፈል የሚያስችል ማሻሻያን ማድረግ ተችሏል።

    በመሆኑም የዓመት ክፍያው 9,000 (ዘጠኝ ሺህ) ብር ሲሆን ይህም የሁለቱንም ቡድኖች ሙሉ ጨዋታዎችን (30 ጨዋታዎች) ለመመልከት የሚያስፈልግ የብር መጠን ነው። ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ ብቻ ለመመልከት የፈለገ ተመልካች የ14 ጨዋታዎች 4,200 (አራት ሺህ ሁለት መቶ) ብር የሚከፍል ሲሆን የሁለቱን የከተማው ደርቢ ጨዋታዎችን እንደ ማንኛውም ተመልካች ከአሞሌ የገንዘብ መቀበያዎች ገዝቶ የሚገባ ይሆናል። ከሌሎች የዓመት ክፍያ ከሌላቸው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናል። ሁለቱም የከተማው ቡድኖች ጨዋታዎች በሁለቱ ክለቦች ስምምነት የሚፈፀም ይሆናል።

    በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ስታዲየም የመግቢያ ዋጋ የሚከተለው ይሆናል

    • ክቡር ትሪቡን፦ 300 ብር
    • ጥላ ፎቅ፦ 200 ብር
    • ከማን አንሼ ባለ ወንበር፦ 100 ብር
    • ከማን አንሼ ወንበር የሌለው፦ 50 ብር
    • ካታንጋ፦ 30 ብር
    • ሚስማር ተራ እና የንጋት ኮከብ፦ 20 ብር

    የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብዓመታዊ የክቡር ትሪቢዩን የመግቢያ ትኬቶች ከኅዳር 27 ቀን 2019 ዓ.ም. ጀምሮ ጀምሮ እየተሸጠ ይገኛል።

    ስለ አሞሌ ዲጂታል ዋለት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    አሞሌ ዲጂታል ዋለት

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወሰናቸውን ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎችን እንዲመረምር እና ያላአግባብ የተወሰነበትን ፎርፌ እንዲያነሳ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የጠየቀ ሲሆን፥ ያቀረባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።

    አዲስ አበባ – የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮቸ ራሱን ማግለሉን አስታወቀ።

    የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ የቅዱስ ጊዮርጊስን የሜዳ ተጠቃሚነት ለማሳጣት ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ሊያደርገው የነበረን ጨዋታ በዝግ ወይም አዳማ ከተማ ላይ ተጫወቱ በማለት ሁለት ጊዜ እንዲቋረጥ አድርጎል ብሏል።

    ይህን ጨዋታ ከዚህ በፊት የተቋረጡ የሌሎች ክለቦች ጨዋታወችን ባስተናገደበት ሁኔታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን አላስተናገደም ሲል በፌዴሬሽኑ ላይ ቅሬታውን አቅርቧል።

    እንዲሁም በ29ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የተሰጠው ፎርፌ አግባብነት የሌለውና አድሏዊ መሆኑንም ነው በመግለጫው ያመላከተው።

    አዲስ ከመጡት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በመተባበር፣ በመቻቻል እና በመተጋገዝ ለመሥራት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷልም ነው ያለው።

    በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የወሰናቸውን ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎችን እንዲመረምር እና ያላአግባብ የተወሰነበትን ፎርፌ እንዲያነሳ የጠየቀ ሲሆን፥ ያቀረባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።

    ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ. / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    —–
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ


    Semonegna
    Keymaster

    ለግንቦት 27 ቀን ተወስኖ የነበረውን የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ በድጋሚ ወደ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ ተወስኗል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ግንቦት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት ጨዋታ የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ሊያካሂዱት የነበረው ጨዋታ በጸጥታ ስጋት ምክንያት (የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባደረገው ውሳኔ መሰረት) ውድድሩ ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወቃል።

    የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ጨዋታ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውቆ ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የላከው መግለጫ (በዋና ሥራ አስኪያጁ በተፃፈ ደብዳቤ) እንደሚያመለክተው ፌዴሬሽኑ ለግንቦት 27 ያወጣዉን ፕሮግራም እንደሚቃወመው አስታውቋል። በተጨማሪም ክለቡ ደብዳቤ ላይ በ27ኛ ሳምንት በሜዳው ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር ያለዉን ጨዋታ በሜዳዉና በደጋፊው ፊት እንዲካሄድም ጠይቋል።

    የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውሳኔውን በዚህ ብቻ ሳያበቃ ግንቦት 26 ቀን ለመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ሆቴል ከቀኑ 9:00 ሰዓት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ክለቡ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ ስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (Court of Arbitration for Sport) እንደሚወስደዉም ይፋ አድርጓል።

    እንደገና ግንቦት 26 ቀን የዒድ አል ፈጥር በዓል ማክሰኞ ግንቦት 27 ቀን እንደሚውል ከታወቀ በኋላ ለግንቦት 27 ቀን ተወስኖ የነበረውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በድጋሚ ወደ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ ተወስኗል።

    የኢትዮጵያ ቡና የጻፈው ደብዳቤ

    ጉዳዩ፦ የተላለፈብንን ውሳኔ ስለመቃወም።

    ክለባችን በ25/09/2011 ከመቀሌ 70 እንደርታ ቡድን ጋር በሊጉ 27ኛ ጨዋታ ለውድድር ተዘጋጅቶ መቅረቡ ይታወቃል።

    ሆኖም በእኛ በኩል ምንም ዓይነት ጥፋት ሳንፈጽም የዕለቱ ውድድር ሳይጀምር መሰረዙ ተገልፆልናል።

    በማግስቱ ጨዋታው በወጣበት ፕሮግራም በአስተናጋጅነታችን፣ በሜዳችን የሚካሄድበት ፕሮግራም ይላክልናል ብለን ስንጠብቅ በ26/9/2011 ዓም ውድድሩ በ27/9/2011 በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም በዝግ ስታድየም እንደሚካሔድ የሚገልፅ ደብዳቤ ደረሰን።

    ከፍተኛ ወጪ አውጥተን ወደ መቀሌ በመጓዝና በከተማችንም ቡድናችን በማዘጋጀት ያወጣነው ወጪ ከግምት ሳይገባ የዚህ ዓይነት ውሳኔ መስጠቱ በእጅጉ አሳዛኝ ነው።

    በሌላ በኩ እኛ መቀሌ ለውድድር ሄደን የደረሰብንን በደለ በቃልና በተጨማሪም በፅሁፍ 3 ጊዜ ወሳኔ እንዲሰጠን ስንጠይቅ ምንም ሳይወሰን ዛሬ በእኛ ላይ በምሽት ስብሰባ ተደርጎ የተሰጠው ወሳኔ በእጅጉ ያሳዘነነ ከመሆኑም በላይ፥ ክለባችን ከሜዳው የሚያገኘውን ገቢ በማቋረጥ፣ ወደ አዳማ ጉዞ የምናወጣው ወጪ፣ የከተማዋን ነዋሪና ደጋፊ ሞራል የሚነካ ሁኔታን በመፍጠር ተጫዋቾቻችንን ላላስፈላጊ እንግልት ከመዳረግ በተጨማሪ የሞራልና አካል ድክመት የሚፈጥር በመሆኑ ክለባችን አይቀበለውም።

    ስለሆነም በጋራ ያቋቋምነው ፌዴሬሽን ለሊግ ኮሚቴ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ የዝግ ስታድየም ጨዋታ ውሳኔ መስጠት ያለበት የፍትህ አካል መሆኑ እየታወቀ፥ ሊግ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳነ ሕገ ወጥ ስለሆነ በአስቸኳይ ተሽሮ በሜዳችን፣ ለተመልካች ክፍት በሆነ ስታድየማችን እንድንጫወት ይደረግ ዘንድ እየጠየቅን፥ ከዚህ ውጭ ያለ አማራጭ ክለባችንን የሚጎዳ ስለሆነ የማንቀበለው መሆኑን እንገልፃለን።

    የክለቡ ማኅተም
    የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ፊርማ

    የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያሳለፈው አዲስ ውሳኔ

    የ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ ግንቦት 29/2011ዓ.ም ይካሄዳል።

    በ27ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ግንቦት 25/2011ዓ.ም ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ በጸጥታ ስጋት ምክንያት ጨዋታው መሰረዙ ይታወቃል፤ የሊግ ኮሚቴ ጨዋታው በጸጥታ ስጋት ምክንያት አለመካሄዱን ተከትሎ ግንቦት 27/2011ዓ.ም. በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ያለ ተመልካች /በዝግ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል፤ ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ውሳኔውን በመቃወም ደብዳቤ ያስገባ ሲሆን ጉዳዩን የተመለከተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀደም ሲል የተሰረዘው ጨዋታ ከመንግስት ጸጥታ ኃይል በደረሰ መረጃ የደኅንነት ስጋት በስታዲየም እንዳለ በማሳወቁ በመሆኑ እና አሁንም በድጋሚ በተደረገው ውይይት ይህ ጉዳይ በጥብቅ ሊታይ የሚገባው በመሆኑ እና የመንግስት የጸጥታ ሀይልም የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ባሉበት ጨዋታው መካሄድ የሌለበት መሆኑን በጥብቅ አስገንዝቦናል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታን ግንቦት 27/2011ዓ.ም. ለማካሄድ የዒድ አል ፈጥር በዓል ስለሆነ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሐሙስ ግንቦት 29/2011ዓ.ም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በ9 ሰዓት ያለ ተመልካች በዝግ ይካሄዳል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ


Viewing 5 results - 1 through 5 (of 5 total)