በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጫና ለመፍጠር የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ አስታወቀ

Home Forums Semonegna Stories በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጫና ለመፍጠር የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ አስታወቀ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #14889
    Anonymous
    Inactive

    በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) አስታወቀ

    አዲስ አበባ (ኢመደኤ) – የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ሰኔ 10፣ 12 ፣ 13 እና 14 ቀናት 2012 ዓ.ም. መቀመጫቸዉን ግብጽ ያደረጉ የሳይበር ወንጀለኞች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን አስታውቋል።

    የሳይበር ጥቃት ሙከራው የተቃጣው ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ (Cyber_Horus Group)፣ አኑቢስ ዶት ሃከር (AnuBis.Hacker) እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስድ (Security By-passed) በተባሉ የሳይበር አጥቂዎች አማካይነት መሆኑን ኤጀንሲው ገልጿል።

    ወንጀለኞቹ ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጁ የቆዩ እና ኤጀንሲው ሲከታተላችው የነበሩ ሲሆን፥ በይበልጥ አርብ ሰኔ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. እና ቅዳሜ ሰኔ 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ከፍተኛ የሚባል የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ማድረጋቸውን የገለጸው ኤጀንሲው፥ በዚህ ጊዜ ዉስጥ የ13 የመንግሥት፣ አራት መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን የድረ-ገጽን የማስተጓጎል ሙከራ ማድረጋቸውን አስታውቋል።

    የሳይበር ጥቃት ሙከራው በሀገሪቱ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች ድረ-ገጽ ላይ ያነጣጠረ ነበር።

    ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ፣ አኑቢስ ዶት ሃከር እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ የሳይበር ጥቃት አድራሽ ቡድኖች ኃላፊነቱን የወሰዱ ሲሆን፥ ዋና ዓላማቸዉም ከህዳሴው ግድብ ዙሪያ በተለይ በውሀ አሞላል ጋር በተያያዘ ሁሉን አቀፍ ተጽዕኖ በሀገሪቱ ላይ ለመፍጠር በማሰብ እንደፈጸሙት ገልጸዋል።

    የሳይበር ጥቃት የተሰነዘረባቸው ተቋማት አብዛኛዎቹ በድረ-ገጽ ግንባታ ሂደት ደvንነታችው ታሳቢ ያላደረጉ ተቋማት፤ በቀጣይነት የደኅንነት ፍተሻ ያላደረጉ እና ከፍተኛ የሳይበር ደኅንነት ተጋላጭነት የነበረባቸው መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አረጋግጧል።

    ኤጀንሲው አስቀድሞ ቅድመ ዝግጅት በማድረጉ ምክንያት እና ይህን መጠነ ሰፊ የሳይበር ጥቃት መከላከል ባይችል ኖሮ ጥቃቱ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖሊቲካዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበር የገለጸው ኤጀንሲው፥ በመከላከሉም ሊደርሱ የሚችሉ ከፍተኛ አደጋዎችን ማስወገድ መቻሉን እና ይህንንም ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት አሳውቋል።

    በቀጣይም መሰል ጥቃቶች በስፋት፤ በረቀቀ መንገድ እና ከተለያዩ ስፍራ ሊሰነዘር እንደሚችል ግምት ውስጥ በማስገባት፥ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት .et domain ከመጠቀማቸው በፊት የድረ-ገጻቸውን ደኅንነት አረጋግጠው እንዲጠቀሙ፤ ራሳቸውን ከሳይበር ደኅንነት ተጋላጭነት ለመከላከል እና አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚኖርባቸው ኤጀንሲው አሳስቧል።

    ተቋማት ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር ያለባቸውን የደኅንነት ተጋላጭነት መድፈን እንዳለባችው እና የተለያዩ የሳይበር ደኅንነት ጥቃት ሙከራ ሲያጋጥማቸውም ሆነ ሙያዊ ድጋፍ ሲያሻቸው ለኤጀንሲው በማሳወቅ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ አስታወቋል።

    የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ባለፉት ሁለት ቀናት ትብብር ላደረጉለት ተቋማት እና ግለሰቦች፥ በተለይ ለኢትዮ ቴሌኮም እና ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኤጀንሲው ምሰጋና አቅርቧል።

    ምንጭ፦ ኢመደኤ

    የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.