በፌዴራል ፖሊስ አባላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የሶስት ፖሊሶች ሕይወት ጠፋ

Home Forums Semonegna Stories በፌዴራል ፖሊስ አባላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የሶስት ፖሊሶች ሕይወት ጠፋ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #7874
    Semonegna
    Keymaster

    በፌዴራል ፖሊስ አባላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የሶስት ፖሊሶች ሕይወት ጠፋ ― የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ዛሬ [መስከረም 24 ቀን 2011 ዓም] ማለዳ በአዲስ አበባ ቦሌ ወሎ ሰፈር አካባቢ በፖሊስ አባላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የሶስት ፖሊሶች ሕይወት መጥፋቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

    ምክትል ጀኔራል ኮሚሽነር መላኩ ፋንታ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት በፌዴራል ፖሊስ አባላቱ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት አንድ አባል በያዘው መሳሪያ በከፈተው ተኩስ ሁለት ፖሊሶችን ገድሏል።

    ድርጊቱን የፈጸመውን አባል በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት ተደርጎ ባለመሳካቱ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ሲባልም እርምጃ ተወስዶበታል።

    ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ ወደፎቁ የላይኛው ክፍል በመውጣት ላይ ሳለ በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ሲከታተሉት የነበሩትን ስድስት የስራ ባልደረቦቹን በመተኮስ አቁስሏቸዋል።

    ለጥበቃ በታጠቀው ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ተኩሱን እንደከፈተ የተረጋገጠው ይህ የፖሊስ አባል አለቆቹን ከገደለ በኋላ ተጨማሪ መሳሪያ ከባልደረቦቹ በመቀማት ሊይዙት በመጡት የጸጥታ ሃይሎች ላይ እስከ ማለዳ ደረስ ሲተኩስ ቆይቷል።

    አለመግባባቱ የተከሰተበት ስፍራ በርካታ ነዋሪዎች የሚገኙበት የመኖሪያ አፓርተማ በመሆኑ ፖሊስ በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረጉን ምክትል ጀኔራል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

    ”አባሉ በሥራ ቦታ ላይ መጥቶ ምድብ ቦታው ላይ ከነበሩ አባላት ጋር የሥራ ርክክብ ሲያደርጉ ግጭት ተፈጥሮ የከፋ ችግር እንዳያደርስ ምክር ቢሰጠውም መቀበል አልቻለም፤ በያዘው መሳሪያ የሥራ ጓዶቹ በሆኑ ሁለት ፖሊሶች ላይ የሞት አደጋ አድርሷል” ብለዋል።

    በተደረገው መከላከል የከፋ አደጋ ሳይደርስ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ መደረጉንና ፖሊስ በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል ሥራ መሥራቱንም አክለዋል።

    አባሉ ተደጋጋሚ የስነ-ምግባር ችግር ባይመዘገብበትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚደረግ የሥራ ግምገማ ሊያርማቸው የሚገቡ ጉዳዮችን እንዲያስተካክል ቢነገረውም ያልተቀበለው በመሆኑ የዛሬውን ችግር ሊፈጥር እንደቻለ ምክትል ጀኔራል ኮሚሽነር መላኩ ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና ARTS TV

    የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.