የሚታዩ ሥርዓት አልበኝነቶችን መንግስት እንዲያስቆም ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ

Home Forums Semonegna Stories የሚታዩ ሥርዓት አልበኝነቶችን መንግስት እንዲያስቆም ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #7980
    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ – የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስነ-ሥርዓት በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የተከፈተ ሲሆን፥ ፕሬዝዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው በምክር ቤቶቹ በበጀት ዓመቱ ለማከናወን የታሰቡ ተግባራትን አንስተዋል።

    በንግግራቸው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ሀገሪቱ በሁለተኛው እድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP II) አሳካዋለሁ ያለቻቸውን ዕቅዶች በሀገሪቱ በተከሰተ ግጭት እና አለመረጋጋት ምክንያት ማሳካት አልተቻለም ብለዋል።

    ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች በሀገሪቱ ሲከሰቱ ከጅምራቸው እንዲቆሙ የማድረግ ውስንነት እንደነበርም ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ አንስተዋል። ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አደጋ ውስጥ ከቶታል። በቀጣይ ህልውናዋን ለማረጋገጥ የሚያስችል ወሳኝ የፖለቲካ ምዕራፍ ተጀምሯል ። በዚህ የለውጥ ሂደት የሕዝቡን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች የህግ የበላይነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ አቋም ተይዟል ብለዋል።

    ከቅርብ ወራት ጀምሮ በፖለቲካው ዘርፍ የታዩ ለውጦች ለወደፊት የሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ ትልቅ ሚና ይጫወታል። በስደት ላይ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር የተደረገው ሰላማዊ ድርድር ትልቅ ለውጥ የታየበት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነበር። እንደ ዶክተር ሙላቱ ገለፃ ለዚህ ፖለቲካዊ መሻሻል ምክር ቤቱ ያፀደቀው የምህረት አዋጅ ትልቁን ሚና ተጫውቷልም ነው ያሉት። የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በተደረገው ጅምር እንቅስቃሴ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ምሁራን፣ጦማሪ እና አክቲቪስቶች በነፃነት የመሥራት እድል ተፈጥሮላቸዋል።

    ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በተቃርኖ ውስጥ የነበሩት ሁለቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክረስቲያን ሲኖዶሶች ችግር ተፈትቶ ወደ አንድ እንዲመጡ መደረጉም የለውጡ አካል ነበር። ለረጅም ዓመታት አለመግባባት ውስጥ የነበሩት አትዮጵያ እና ኤርትራ መግባባታቸው በቀጠናው የነበረውን የድህነት እና ኋላቀርነት መገለጫ ማጥፋት ችሏል።

    ———————————————-

    ———————————————-

    በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በዜጎች ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ ኢትዮጵያ መታደግ ችላለች። ከሌሎች አጎራባች እና የውጭ ሀገራት ጋርም ጥብቅ የሆነ ወዳጅነት እንዲኖራት መደረጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመለከትነው የፖለቲካ ለውጥ ውጤት ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

    ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በመክፈቻ ንግግራቸው የዜጎችን ነፃነት እና መሰረታዊ መብቶች ከማስጠበቅ አንፃር የተሠራው ሥራ ውስን እንደነበር ተናግረዋል።

    በአሁኑ ወቅ የሕዝቡ የዴሞክራሲ እና የፖለቲካ ጥያቄዎች የጎለበተበት በመሆኑ መንግስት የፖለቲካ ማሻሻያ የሚያደርግበት ነው ። የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል መንግስት በበጀት ዓመቱ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራልም ብለዋል።

    አሁን በሀገሪቱ የተጋረጠው የሰላም መደፍረስ ሕዝቡን አደጋ ውስጥ አስገብቶታል። የህግ የበላይነትም ተጥሷል። ፕሬዝዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት እና የህግ የበላይነትን ለማስከበር መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል። የመገናኛ ተቋማት በማንኛውም የመገናኛ ዘዴ ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል።

    ተከስቶ የነበረው ሁከት እና አለመረጋጋት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አድርሷል።በስፋት እየታየ ያለውን የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ለመቀነስ እና የኢኮኖሚ ምህዳሩን ለማስፋት በዚህ የበጀት ዓመት በተጨባጭ እንደሚሠራም ተናግረዋል። መንግስት የተረጋጋ እና ቀጣይነት ያለው ማክሮ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ፅኑ አቋም እንዳለው አንስተዋል። ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችው ድርድር በዚህ ዓመት ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

    ከመክፈቻ ንግግሩ ለመረዳት እንደተቻለው የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግስት (ኢጋድ) በማጠናከር እና ወደ ተግባር ገብቶ ቀጠናዊ አገልግሎቱን እንዲያሰፋ ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ ትወጣለች።

    ሀገራችን በርካታ አለማቀፍ የስብሰባ መድረክ አገልግሎት እየተካሄደባት በመሆኑ የቪዛ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል። የሚሰጠው የቪዛ አገልግሎት ቀልጣፋ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አንስተዋል።

    የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ እንዲሁም የመስኖ እርሻን በማጠናከር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ይሠራል።
    የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ አዲሱን ፍኖተ-ካርታ መሰረት ያደረገ የሥርዓት ትምህርት ማሻሻያ የደረጋል። የሴቶች እና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በያዝነው በጀት ዓመት የጤና ተቋማት ግንባታ እና ቁሳቁስ አቅርቦት ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራል። አሁን የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ በሥርዓት አልበኞች ምክንያት እየታዩ ያሉ መፈናቀሎችን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በመክፈቻ ንግግራቸው አንስተዋል።

    ምንጭ፦ የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት

    ሙላቱ ተሾመ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.