ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ

Home Forums Semonegna Stories ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • Author
    Posts
  • #13202
    Semonegna
    Keymaster

    ባሕር ዳር (ሰሞነኛ) – ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ አቶ አየነው በላይን በመተካት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ።

    ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአሜሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኖርዝ ቴክሳስ (The University of North Texas) ተከታትለዋል። በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ አት ኦስተን (The University of Texas at Austin) እና በሌሎችም በተመራማሪነት ማገልገላቸውም ታውቋል። የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በአሜሪካና ካናዳ ማቅረባቸውም በግለ ታሪካቸው ተብራርቷል።

    ዶክተር መሐሪ የተለያዩ ዓለማቀፍ የሙያ ማኅበራት አባል መሆናቸውም ነው የተገለጸው። የአሜሪካ የስታትስቲክስ ማኅበር (American Statistical Association)፣ የአሜሪካ የትምህርት ጥናት ማኅበር (American Educational Studies Association)፣ የተቋማዊ ጥናት ማኅበር፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥናት ማኅበር፣ የደቡብ ምዕራብ የትምህርት ጥናት ማኅበርና የቴክሳስ የትምህር ጥናት ማኅበር አባል እንደሆኑም ነው የተገለጸው።

    ከ13 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምርና የተለያዩ ትምህርቶችን በማስተማር እንደቆዩም ተገልጿል፤ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በኃላፊነት ደረጃ ማገልገላቸውም ነው የተነገረው።

    ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስን ልምዳቸውንና የአመራር ብቃታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ታኅሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ማካሄድ በጀመረው መደበኛ ጉባኤው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾሟቸዋል።■

    ከአማራ ክልል ሳንወጣ፥ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው የበላይ ባለ ኮኮብ 5 ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ፕላን በዘርፉ ባለሙያዎች ተገመገመ። የፕሮጀክቱ ዲዛይንና አማካሪ የሆኑት አቶ ነቢዩ ሰለሞን እንዳብራሩት፥ ሆቴሉ በ3,690 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደሚያርፍ፣ 3 ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ 120 የመኝታ ክፍሎች፣ 2 ሬስቶራንቶች፣ ባር፣ ጂም እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች እንደሚኖሩት፣ ዲዛይኑ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

    የደብረ ብርሃን ከተማ ህንጻ ሹም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አምሳሉ መኮንን በበኩላቸው በቀረበው ዲዛይን መሠረት ገንቢ አስያየት በመስጠት ሆቴሉ ከታሰበው በላይ ተሻሽሎና ዳብሮ እንዲሠራ ባለሙያዎች የድርሻቸውን አንዲወጡ አሳስበዋል።

    የውይይቱ ተሳታፊዎችም የቡና ስኒ በዲዛይኑ ላይ መካተቱ ከደብረብርሃን ጋር ምን ያገናኘዋል? የሠራተኞች ማረፊያ ክፈል፣ ሕፃናት መዝናኛ፣የመዋኛ ገንዳ መካተት አለበት የሚሉና እና ሌሎችም በርካታ ሀሳብ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። በመድረኩ ከደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ፣ ከኢንቨስትመንት፣ ከህንጻ ሹም፣ ከህንጻ ዲዛይን አማካሪዎች፣ ከባህል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች የመጡ የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

    የበላይ ባለ 5 ኮኮብ ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ከ2 መቶ ሚሊየን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለት የመሠረት ድንጋው ሲጣል መገለጹ የሚታወስ ነው።

    ምንጮች፦ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ዶክተር መሐሪ ታደሰ

    #16366
    Anonymous
    Inactive

    ዶክተር ድረስ ሣህሉ ጎሹ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ

    ባህር ዳር (ሰሞነኛ)– የባህር ዳር ከተማ ምክር ቤት ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ዶክተር ድረስ ሣህሉ ጎሹን የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በማድረግ በሙሉ ድምፅ ሹሟል።

    በባህር ዳር ከተማ ምክር ቤት በከተማው የተቀዳሚ ከንቲባነት የተሾሙት ዶክተር ድረስ ሣህሉ ጎሹ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በምድረ ፅፍ እና አካባቢ ጥናት (geography and environmental study) ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፤ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአመራር እና መልካም አስተዳደር (leadership and good governance) ከኢትዮጵያ ሲቪል ሠርቪስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። በመቀጠልም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሥራ አመራር (management)  ቻይና ከሚገኘው ኋጆንግ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂያገኙ ዩኒቨርሲቲ (Huazhong University of Science and Technology) ሲሆን፥ ሁሉንም የትምህርት ደረጃዎች በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ ናቸው።

    ዶክተር ድረስ ሣህሉ የአማራን ሕዝብና መንግሥት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ ባሉ የተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች በውጤታማነት እና በታማኝነት ያገለገሉ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል በዞን ደረጃ የምዕራብ ጎጃምዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም የዞኑ የሕዝብ ግንኙነትና የከተማ አደረጃጀት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ የምሁራን ተሳትፎና አደረጃጀት ዘርፍ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል። በአጠቃላይ የዶክተር ድረስ ሣህሉ የሥራ ልምድ የሚከተለውን ይመስላል፦

    • በምስራቅ ጎጃም ዞን በደባይ ጥላት ግን እና በባሶ ሊበን ወረዳ የደን እርቻ ልማት (agro forestry) እና የመሬት አስተዳደር ባለሙያ በመሆን ለአራት ዓመታት አገልግለዋል፤
    • በምስራቅ ጎጃም ዞን በባሶ ሊበን ወረዳ የአስተዳደር እና ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፤
    • በአነደድ ወረዳ የግብርና ኃላፊ፣ የመሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የሕዝብ ተሳትፎና አደረጃጃት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፤
    • በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፤
    • በጃቢ ጠህናን ወረዳ የመሬት አስተዳደር ጽኅፈት ቤት ኃላፊና የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።
    • የምዕራብ ጎጃም ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ፣ የሕዝብ ግንኙነትና የከተማ አደረጃት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፤
    • በአማራ ክልል የምሁራን ተሳትፎና አደረጃጀት ዘርፍ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።

    ዘገባው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት እና የአማርኛ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ቤት ነው።

    ዶክተር ድረስ ሣህሉ ጎሹ

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.