Home › Forums › Semonegna Stories › 2ተኛው “አረንጓዴ አሻራ” ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 4 years, 5 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
June 11, 2020 at 2:10 am #14775SemonegnaKeymaster
2ተኛው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን፣ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የ2012 ዓ.ም የ5 ቢሊዮን የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አርብ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀዋሳ ከተማ በታቦር ተራራ በይፋ ተጀምሯል።
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስጀመሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እየሠራች እንደሆነ ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 84 በመቶ መፅደቁን አስታውሰው፥ ዘንድሮ የታቀደውን 5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ግቡን ለማሳካት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ግቡን ማሳካት ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
በዘንድሮ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በደቡብ ክልል በ227 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 1.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፥ ወይራ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ እና የአበሻ ፅድ የመሳሰሉት ሃገር በቀል ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በዓለም ለ47ተኛ ጊዜ በሀገራችን ለ27ተኛ ጊዜ የሚከበረው የአለም የአካባቢ ቀንም (World Environment Day) “አካባቢን መጠበቅ የብዝሃ-ህይወትን በመጠበቅ ነው” በሚል መሪ-ቃል ከ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ጋር እየተከበረ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው መሪ ቃል “ለተፈጥሮ ጊዜ እንስጥ” (‘Time for Nature’) የሚል ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት “40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ቃል ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል አቅዳ 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞች ተተክሎ የዓለም ክብረ ወሰን መያዟ የሚታወስ ነው።
አምና 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በአጠቃላይ 4.7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከል የተቻለ ሲሆን 23 ሚሊዮን ሕዝብ መሳተፉም ይታወሳል። በቀጣም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በየዓመቱ የሚካሄድ ይሆናል ተብሏል።
ምንጭ፦ የግብርና ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
June 15, 2020 at 10:54 am #14801AnonymousInactiveየተፈጥሮ ሳይንስ እና ግብርና ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ተገለጸ።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአገራችን አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ዕለት የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የአረንጓዴ አሻራ ቀን በሚል ችግኝ የመትከል ማዕድ የማጋራትና ደም የመለገስ መርሃ-ግብሮች ተከናውነዋል።
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአሰላ ከተማ የሚገኘው አርሲ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት መርሃ-ግብሩን ያስጀመሩት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት፥ የተፈጥሮ ሳይንስ እና የግብርና ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።
በቅድመ ተከላ፣ በተከላ ወቅትና ድኅረ ተከላ መደረግ ያለባቸውን እንክብካቤዎችን እና ጥንቃቄዎችን በማስተማርና እንዲሁም እንደየአከባቢው የአየር ንብረት ሁኔታ ተስማሚ የሆኑትን ችግኞች እንዲባዙ ጥናትና ምርምር ከማድረግና ማማከር በተጨማሪ ከሌላው ጊዜ በበለጠ ችግኞችን አባዝተው ለአከባቢው ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
አያይዘውም በየአከባቢው ያለው የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማኅበረሰቡ እንዲሁም ሌሎችም ኢትዮጵያውያን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን እየተጠነቀቁ በዚሁ ምክንያት ለተቸገሩ ወገኖቻቸው ማዕድ እንዲያጋሩ እና ደም በመለገስም ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት እንዲታደጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲውን ሦስቱን ግቢዎች ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመሆን የጎበኙ ሲሆን፥ በጉብኝቱ ከሰባ ዓመታት በፊት በስዊድን ድጋፍ የተቋቋመውና በዩኒቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የግብርና ምርምር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ እና የጤና ሳይንስ ኮሌጁም የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን ለመከላከል የሚያመስገን ሥራ እየሠራ መሆኑም ተገልጿል።
ፕሮፌሰር አፈወርቅ በማዕድ ማጋራት ዩኒቨርሲቲው የሚደግፈውን አፎምያ የአረጋውያን መርጃ ማኅበር የጎበኙ ሲሆን በጉብኝቱ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው የዱቄትና ዘይት ድጋፍ አድርጓል።
ከአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ጋር በተያያዘ፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ ከድምጻውያን ጋር በመሆን በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ሚሊኒየም ፓርክ ውስጥ (የካ ተራራ) ችግኞችን ተክለዋል።
ከንቲባው በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዓለም-አቀፍ ስጋት የሆንውን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን ከመከላከል በተጓዳኝ ነዋሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው ችግኞች እንዲተክሉ አሳስበዋል። ችግኝ ከመትከል ባለፈም ችግኞች በየጊዜው መንከባከብም ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ሕብረት ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ ሕብረተሰቡ ችግኞች ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በመረዳት በራሱ ተነሳሽነት መትከልና መንከባከብ ይገባል ብለዋል። ሕብረቱም የተከላቸውን ችግኞች ለመንከባከብም ቃል ገብተዋል።
በሥፍራው ተገኝቶ አረንጓዴ አሻራ በማኖሩ ደስተኝነቱን የገለጸውና ተግባሩ መቀጠል አለበት ያለው ድምፃዊ ነዋይ ደበበ ነው።
”ንጹህ አየር ለሰው ልጅ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን ችግኝ መትከል ግዴታ ነው። በዚህም ቦታ ተገኝቼ አረንጓዴ አሻራ በማኖሬ ደስተኛ ነኝ” ሲል የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሣ ተናግሯል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰባት ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዷል። በአገር አቀፍ ደረጃ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፤ ከሚተከሉት መካከል ለጥምር ግብርና የሚሆኑ የፍራፍሬ ችግኞች ይገኙበታል።
ምንጮች፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.