Home › Forums › Semonegna Stories › ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Tagged: አቢሲንያ ባንክ, የኢትዮጵያ አየር መንገድ, የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን, ዳሸን ባንክ, ፀሐይ ባንክ
- This topic has 55 replies, 3 voices, and was last updated 8 months, 1 week ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
February 16, 2020 at 11:39 pm #13611SemonegnaKeymaster
የሀገሪቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሁነኛ ደጋፊ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2019 የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ሆነ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2019 የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ሆነ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊ የሆነው “በምርጥ የንግድ ባንክ” ምድብ ነው።
ባንኩ በተለያዩ ዘርፎች ከቀረቡ ባንኮች ጋር ተወዳድሮ ነው “ምርጥ ንግድ ባንክ” /Best Commercial Bank/ ሽልማት አሸናፊ መሆን የቻለው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ምርጥ ባንኮች ደረጃ እያገኘ የመጣ ሲሆን ለዚህ ዓለም አቀፍ ሽልማት ሲበቃ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ሽልማቱ ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ በሚያወጣቸው መስፈርቶች ተመሥርቶ የሚካሄድ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዚህ ሽልማት አሸናፊ ለመሆን ካስቻሉት መስፈርቶች መካከል ለበርካታ ዓመታት በትርፋማነት መቀጠሉ፣ ተደራሽነቱ በፍጥነት እያደገ መሄዱ፣ የደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ፣ ለልማት ሥራዎች የሚያስፈልግ የፋይናንስ አቅርቦት ማሳደጉ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣቱና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን በተሟላ ሁኔታ መስጠት መቻሉ እንደሆነም ተጠቅሷል።
ባንኩ የአገሪቱን ቁልፍ የልማት ሥራዎች እየደገፈና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የጤና፣ ትምህርት፣ አካባቢ ጥበቃና ሌሎችም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በግንባር ቀደምትነት ለመደገፍና በመሳተፍ ለአገራችን ልማት አጋር መሆኑን በተጨባጭ ያስመሰከረ መሆኑ ዓለም አቀፍ ሽልማቱን በቀዳሚነት እንዲያገኝ እንዳስቻለው ነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባጫ ጊና የገለፁት።
በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ከሆኑ ሥራዎች መካከል የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት ማሳደግ የሚያስችሉ ግዙፍ ኘሮጀክቶችን ፋይናንስ በማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲከናወኑ አድርጓል። ለኃይል ማመንጫ ኘሮጀክቶች በርካታ ገንዘብ በማቅረብ ግንባታዎች እንዲከናወኑ በማድረግ ላይ መሆኑም ነው የተገለፀው።
የሀገሪቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዋና ደጋፊ ከሆኑ ድርጅቶች መካከል ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፥ በየዓመቱ ለግብርና ግብዓቶች አቅርቦት፣ ለክልሎች ፋይናንስ ማቅረቡ፣ ለሀገር ውስጥ ከሚያቀርበው ከፍተኛ መጠን ካለው ብድር በተጨማሪ ለህብረተሰቡ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የመድኃኒት፣ የምግብ ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳርና ቅባት ሌሎች የፍጆታ እቃዎችና የፋብሪካ ግብአቶች ከውጪ እንዲገቡ በማገዝ እየሠራ መሆኑም ለአሸናፊነቱ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተገልጿል። አቶ ባጫ ጊና አክለውም ሽልማቱ ባንኩ በቀጣይ ያለውን አገልግሎት ለማሳደግና በሌሎች ዘርፎችም ተሸላሚ ለመሆን የሚያነሳሳ መሆኑን ገልፀዋል።
ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ በ2019 ካዘጋጃቸው የውድድር ምድቦች መካከል፦
- Best Commercial Bank – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣
- Best Islamic Bank – የአፍጋኒስታኑ Islamic Bank of Afghanistan፣
- Best Innovative Bank – የአርመኑ InecoBank፣
- Best Digital Bank – የቦትስዋናው FNB Botswana፣
- Best Customer Service Bank – የባህሬኑ BBK፣
- Best Retail Bank – የግብጹ National Bank of Egypt፣
ከአሸናፊ ምርጥ ዝርዝሮች መካከል ይጠቀሳሉ። በተለያዩ ዘርፎች ያሸነፉ የባንኮችን ዝርዝር ለማየት እዚህ ጋር ይጫኑ። ከዚህ ቀደም የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ከነበሩ ሀገራት መካከል ካናዳ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ፖርቹጋል፣ ህንድ፣ ኢንዶኒዥያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያ ይጠቀሳሉ።
ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ መቀመጫነቱ ለንደን ከተማ (እንግሊዝ) የሆነ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘገባዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የህትመት ድርጅት ነው።
February 22, 2020 at 6:46 pm #13677AnonymousInactiveየቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ‹‹ሸገር ባንክ›› የተሰኘ ባንክ ለመመሥረት እንቅስቃሴ ጀመሩ
አዲስ አበባ (ሪፖርተር ጋዜጣ)– የኦሮሚያ ክልልን በፕሬዚዳንት ከመመራት ባሻገር የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት ያስተዳደሩትና በስደት ከኢትዮጵያ ውጭ የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ‹‹ሸገር ባንክ›› የተባለ አዲስ ባንክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ በመጀመር የባንኩን የአክሲዮን ሽያጭ አስጀምረዋል።
አቶ ጁነዲን ‹‹ሸገር ባንክ›› በሚል መጠሪያ የሰየሙትን ባንክ ለማቋቋም የተሰባሰበውን አደራጅ ኮሚቴ በአስተባባሪነት እየመሩ ሲሆን፣ ባንኩን ለመመሥረት የሚያስፈልገውን ካፒታል ለማሟላት ከተለያዩ ባለሀብቶች ጋር ከመከሩና አክሲዮን የሚገዙ በርካቶችን ከጎናቸውን ካሰለፉ በኋላ ወደ ካፒታል ማሰባሰብ ሥራ መግባታቸው ይጠቀሳል።
ከሸገር ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ በተሠራጨው መረጃ መሠረት፣ እንደ ሕጉ አግባብ አንድ አክሲዮን የአንድ ሺሕ ብር ዋጋ ይኖረዋል። አንድ ባለአክሲዮን ከአሥር አክሲዮኖች ጀምሮ መግዛት ይችላል ተብሏል። ባንኩን በተያዘው ዓመት መጨረሻ ሥራ ለማስጀመር መታቀዱን ከአደራጅ ኮሚቴው ለመረዳት ተችሏል። ሸገር ባንክን ለመመሥረት አቶ ጁነዲን ጨምሮ 150 አደራጆች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ሲገለጽ፣ ካፒታል በማሰባሰቡ ረገድ ባንኩ ውጭ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሠራም ተጠቅሷል። የባንኩን አብላጫ ድርሻም በገጠሩ ኅብረተሰብ ላይ ትኩረት በማድረግ የአክሲዮን ሽያጩ እንደሚከናወን ይጠበቃል።
የ‹‹ሸገር ባንክ›› አደራጆች፣ ከባንኩ ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑና ታዋቂ ግለሰቦችን በማካተት ሐሙስ፣ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል የባንኩን አቅጣጫ የሚያመላክት ትንታኔ አቅርበዋል።
በዚሁ ወቅትም የባንኩ የአክሲዮን ሽያጭ እንደተጀመረ ተገልጾ፣ ከታዋቂ ግለሰቦች መካከል ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ አቶ ጁነዲን ሳዶ፣ አቶ ጌቱ ገለቴ፣ አቶ ድንቁ ደያስና ሌሎችም ተገኝተዋል። የተለያዩ ከተሞችን የሚያስተዳድሩ ኃላፊዎችና ከንቲባዎች እንዲሁም አባ ገዳዎች ተሳትፈዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ባንክ ለማቋቋም 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስፈልጋል። ይህንን ተከትሎም የሸገር ባንክ የተፈቀደ ካፒታል እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተገልጿል። የባንኩ አደራጆች ቢሮ ቦሌ መንገድ ላይ በሚገኘው ጌቱ ኮሜርሻል ሕንፃ ላይ መከፈቱም ታውቋል።
የሸገር ባንክ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጁነዲን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲያቅፍ እንደሚደረግ በተለይ ግን ለገበሬው ክፍልና በተለያዩ ከተሞች በአነስተኛ ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና ተደራሽ የፋይናንስ አቅርቦቶችን እንዲያገኙ ይታሰባል። ባንኩ የገጠሩን ክፍል ከከተማው ጋር በማስተሳሰር የገቢ ምንጩ እንዲሰፋ የማገዝ ዓላማ እንዳለውም አቶ ጁነይዲ ጠቅሰዋል።
ሙሉ ታሪኩን ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያንብቡ
February 27, 2020 at 1:10 am #13716SemonegnaKeymasterበዓመት 500 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት የሚያመርተው ፋብሪካ ዘንድሮ ሥራ ይጀምራል
ቡሬ (አዲስ ዘመን) – የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን ከ50 እስከ 60 በመቶ መሸፈን የሚያስችልና በቡሬ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የምግብ ዘይት ፋብሪካ ከሁለት እስከ አራት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ምርት ይገባል ተባለ። የውጭ ምንዛሬ በማዳን የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘግቧል።
በፌዴራልና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የካቲት ወር አጋማሽ፣ 2012 ዓ.ም. የተጎበኘው በኢትዮጵያዊ ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴ በመገንባት ላይ ያለው ፋብሪካው፤ የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን ከ50 እስከ 60 በመቶ ይሸፍናል ተብሏል።
በአገር ውስጥ ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ወደ ዘርፉ መግባታቸውን የገለጹት አቶ በላይነህ ክንዴ፥ ከአንድ ፋብሪካ በስተቀር ቀሪዎቹ እንደተገጣጠሙም ተናግረዋል። በዓመት 500 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም እንዳለውና አገር ውስጥ ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት እንደሚፈታም ተናግረዋል።
ድርጅቱ ላለፉት 13 ዓመታት ሰሊጥ ወደ ውጭ በመላክ ግንባር ቀደም እንደነበር በማስታወስ፥ በተደጋጋሚ በመንግሥትና በሕዝብ ይቀርብ የነበረው ጥያቄ እውን የሚያደርገው አቀነባብሮ የሚያቀርበው ፋብሪካ ዘንድሮ ወደ ምርት እንደሚገባ ነው ባለሀብቱ የተናገሩት። ማንኛውንም አይነት የቅባት እህሎችን እንደሚያጣራና በአሁኑ ወቅት ለአምስት መቶ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ወደ ምርት ሲገባ ቁጥሩ እስከ ሦስት ሺህ ከፍ እንደሚልም አብራርተዋል። ፋብሪካው በግብአትነት 20 ሚሊዮን ኩንታል እህል እንደሚያስፈልገው በመጠቆም፥ ከጉትን እስከ ጎንደር ጫፍ ያሉ አርሶ አደሮችም ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ በጋራ እንሠራለን ብለዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ፥ አሁን ባለው ሁኔታ የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ያለው የምግብ ዘይት ፋብሪካ አለ ማለት ይከብዳል፤ አብዛኛው የምግብ ዘይት ፍላጎት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች እየተሸፈነ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ የሚገነባው 50 በመቶ ፍላጎትን ከሸፈነ ቀሪውንም ሌሎች ወደ ምርት የሚገቡ ፋብሪካዎች ይሸፍኑታል ብለዋል። ፋብሪካዎች ማሽን ስላስገቡ ይጠናቀቃል ማለት አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የመብራት ችግር እንዳያስተጓጉል ጎን ለጎን እየተሠራ መሆኑንና ፋብሪካው ወደ ምርት ሲገባ የውጭ ምንዛሬ በማዳን በኩል ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የፕሮሞሽንና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይሄነው አለም፥ ባህር ዳር ዙሪያና ቡሬ ከተማም እንደቅደም ተከተላቸው ሰፊ የኢንቨስትመንት ማዕከል መሆናቸውን ተናግረዋል። ባለሀብቱ ትልቅ የዘይት ፋብሪካ እንዲተክሉ ያነሳሳቸው አካባቢው ትርፍ አምራች መሆኑ ነውም ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፥ ከሱዳን ጠረፍ እስከጃዊ አኩሪ አተር፣ ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ስንዴና በቆሎ በከፍተኛ ደረጃ ይመረታል፤ ፋብሪካው ምርቶቹን በግብአትነት በመጠቀም ዘይት በከፍተኛ ደረጃ በማምረት በዕቅዱ መሠረት የአገሪቱን ከ50 እስከ 60 በመቶ ፍላጎት እንደሚሸፍንም ተናግረዋል። ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃምና አዊ ደቡባዊ ጎንደር እስከ ሱዳን ጠረፍ ከፍተኛ ምርት በመኖሩ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት የግብርና ምርት አቀነባባሪዎች ትኩረታቸውን ወደ አካባቢዎቹ እንዲያርጉም ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማራ ድርጅት ሲሆን፤ በገላን ከተማ የጀመረው የመኪና መገጣጠሚያ፣ ሆቴልና እርሻ ሥራ ተጠቃሽ ናቸው። በቡሬ ከተማ በግንባታ ላይ ያለው የዘይት ፋብሪካ በ2006 ዓ.ም የተጀመረና በ30 ሄክታር ላይ ያረፈ ነው። የጀሪካን፣ የማሸጊያ፣ የሳሙና፣ የማርጋሪንና የካርቶንን ጨምሮ ሰባት የተለያዩ ፋብሪካዎችን ይዟል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
February 27, 2020 at 1:52 am #13721AnonymousInactiveእናት ባንክ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ዕውቅና አገኘ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– እናት ባንክ አክስዮን ማኅበር በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ዕውቅና አገኘ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ለእናት ባንክ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችለውን የዕውቅና ምስክር ወረቀት (certificate) በሰጠበት ወቅት ዋና ዳሬክተሩ ኢንጅነር ኡሌሮ ኡፒየው እንዳሉት፥ ባለስልጣኑ በምርት ገበያው ክፍያ የሚፈጽሙ ተቋማትን አፈጻጸማቸውን የመቆጣጠርና ዕውቅና የመስጠት ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው በመሆኑ እናት ባንክ ከምርት ገበያው ጋር የሚያደርገው የኤሌክትሮኒክስ የመረጃ ልውውጥ አስተማማኝ መሆኑ በመረጋገጡ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችል የዕውቅና ምስክር ወረቀት ሊያገኝ ችሏል። በዚህም ባለስልጣኑ ከባንኩ ጋር ለመሥራት የሚያስችለውን የሥራ ውል ስምምነት መፈራረሙን ተናግረዋል።
እናት ባንክ አክስዮን ማኅበር ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የተሰጠውን የዕውቅና ሰርተፍኬት በተረከበበት ወቅት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወንደወሰን ተሾመ እንዳሉት፥ የባንኩን የቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ለመሳተፍና የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ዕውቅና ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
እናት ባንክ በፌስቡክ ገጹ ላይ ያሰፈረው መግለጫ እንዲህ ይነበባል፦
“እንኳን ደስ አለን…
እናት ባንክ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ኢ.ሲ.ኤክስ) የክፍያ ፈፃሚ ባንክ በመሆን የክፍያ ሥርዓቱን መጀመር የሚስችለውን የዕውቅና ሰርተፊኬት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ተቀበለ። በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምትገበያዩ ደንበኞቻችን በዚሁ አጋጣሚ አገልግሎቱን ማግኘት እንደምትችሉ ስናሳውቅ ደስታ ይሰማናል።”የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሥራውን ሲጀምር ዕውቅና ተሰጥቷቸው በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ክፍያ ሲፈጸምባቸው የነበሩ ባንኮች ሁለት ብቻ የነበሩ ሲሆን፥ በሂደት ቁጥራቸው 15 መድረሱን አስታውሰው፥ እናት ባንክ ሲጨመር በድምሩ 16 መድረሳቸውን ተናግረዋል።
በገበያ ሥርዓቱ ውስጥ የክፍያ መፈጸሚያ ባንኮች ዋና ዋና ተግባራትና ኃላፊነቶች የምርት ገበያው አባላትና ደንበኞች በባንኮቹ ውስጥ ገንዘብ የሚሰባሰብበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ የምርት ገበያው የክፍያ መፈጸሚያ ተቋም በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ከግብይት በኋላ ገንዘብ ማዘዋወርና ስለ ወቅታዊ ደንበኞችና የአባላት የባንክ ሂሳብ ከባለስልጣኑ ጋር መረጃ መለዋወጥ መሆኑ ተገልጿል።
ከግል ባንኮች በርካታ ባለአክሲዮኖችን በመያዝ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው እናት ባንክ፥ በ2011 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 231.4 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ፣ የተጣራ ትርፉም 202 ሚሊዮን ብር መሆኑን አስታውቆ ነበር። ባንኩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች 45 ቅርንጫፎችን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ ይህንን የቅርንጫፍ ቁጥር በ2012 ሒሳብ ዓመት ወደ 70 ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን አምና ኅዳር ወር 2012 ዓ.ም. አስታውቆ ነበር።
March 1, 2020 at 3:04 am #13760SemonegnaKeymasterአቢሲንያ ባንክ በታላቁ የንግድ ሰው በሞላ ማሩ ስም ቅርንጫፍ ከፈተ፤ የባንኩ አሚን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለሁለተኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝቷል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ቅርንጫፎቹን በሀገር ባለውለታዎች ስም እየሰየመ የሚከፍተው አቢሲንያ ባንክ አሁን ደግሞ (በየካቲት ወር 2012 ዓም) በሀገራችን ስመ-ጥር የንግድ ሰው በሆኑት ሞላ ማሩ ስም አዲስ አበባ ውስጥ ከአብነት ወደ ተክለኃይማኖት በሚወስደው መንገድ ሞላ ማሩ አካባቢ <አቢሲንያ ባንክ ሞላ ማሩ ቅርንጫፍ> ከፍቶ ሙሉ የባንክ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ቀኛዝማች ሞላ ማሩ ከአባታቸው ከአቶ ማሩ ዶሬ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ዳዊቴ ሁሉቃ፥ በክስታኔ ጉራጌ፣ ዋጮ ፉሌ ቀበሌ፣ በመጋቢት ወር 1918 ዓ.ም. ተወለዱ። ከሊስትሮነት፣ ከጎዳና ንግድ፣ ከአልባሳት ሽያጭ የሥራ ዘርፍ ጀምሮ እስከ ቡና ንግድ፣ ለስላሳ መጠጦች፣ ዘይትና አረቂ ፋብሪካ ማቋቋም ድረስ የዘለቀ የንግድ ሥራ ታሪክ ባለቤት ናቸው። በተጨማሪም ቀኛዝማች ሞላ ማሩ በሆቴል ሥራ፣ በብሎኬት ፋብሪካ ሥራ፣ በእርሻ ሥራ፣ በድንጋይ መፍለጫ ካባ ሥራ እና ሌሎች በርካታ የሥራ ዘርፎች ውስጥ በመሳተፍ ከፍተኛ አበርክቶ ነበራቸው። በአጠቃላይ ቀኛዝማች ሞላ ማሩ በበርካታ የሥራ ዘርፎች ላይ በመሠማራት፤ የሥራ ፈጠራን (entrepreneurship) ወርድና ቁመት በዕውን ያሳዩ የሀገር ባለውለታ ናቸው።
በንግድና ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያከናወኗቸው ተግባራት ከራሳቸው ባለፈ ለሀገርና ሕዝብ ጠቃሚ መሆናቸውን ያመነበት የቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለሥላሴ መንግሥት፣ በ1964 ዓ.ም. የቀኛዝማችነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል።
ባለትዳርና የ6 ልጆች አባት የነበሩት ቀኛዝማች ሞላ ማሩ በ1972 ዓ.ም፣ በ54 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም አርአያነታቸው በርካቶችን እያነሣሣ ለትውልድ ይቀጥላል።
‘ቅርንጫፎቹን በሀገር ባለውለታዎች ስም እየሰየም ለትውልድ የሚዘክረው አቢሲንያ ባንክ በእኚህ የሀገር ባለውለታ ስም ቅርንጫፉን በመሰየሙ ከፍተኛ ደስታና ክብር ይሰማዋል’ – ይላል ባንኩ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ።
ከአቢሲንያ ባንክ ዘገባ ሳንወጣ፥ ባንኩ አሚን (Ameen) በተሰኘው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ለሁለተኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝቷል። ሽልማቱ መቀመጫውን ዱባይ ባደረገው አልሁዳ ኢስላሚክ ባንኪንግና ኢኮኖሚክስ (AlHuda Centre of Islamic Banking and Economics) በመባል የሚታወቀው ማዕከል ባዘጋጀው 2ተኛው “የአፍሪካ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትና ታክፉል ሽልማት 2020” (African Interest-Free Banking and Takaful Awards 2020) ፎረም ላይ ተበርክቷል። ሽልማቱ አቢሲንያ ባንክን “በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትና ፋይናንስ” የላቀ የገበያ አበርክቶ ተሸላሚ ሲያደርገው፥ የባንኩን አሚን ማዕከል ዳይሬክተር አቶ አብዱልቃድር ሬድዋንን “በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት አንጸባራቂ ሰብዕና እየገነባ የመጣ” በሚል የ2020 ተሸላሚ አድርጓል።
March 6, 2020 at 8:09 am #13819AnonymousInactiveአቶ አቤ ሳኖ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አቶ አቤ ሳኖ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ። አቶ አቤ ከየካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ነው ባንኩን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የተመደቡት።
የካቲት 26 ቀንም ከቀድሞ የባንኩ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባጫ ጊና እና ከሌሎች የባንኩ የሥራ አመራር አባላት ጋር ትውውቅና የሥራ ርክክብ አድርገዋል። በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት አቶ ባጫ ጊና በኃላፊነት ቆይታቸው የሥራ አመራሮችና ሠራተኞች ላደረጉላቸው እገዛና ትብብር ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፥ ከአዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ጋርም በትጋትና በትብብር በመሥራት ለተሻለ ውጤት እንዲሠሩም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ የተሾሙት የባንኩ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ሥራ የጀመሩበትና በወጣት እድሜያቸው በኃላፊነት መምራት ወደቻሉበት ባንክ መምጣታቸው የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት እንደሆነ ገልፀዋል። አቶ አቤ ሳኖ ከዚህ በፊት ከሁለት ዓመታት ከፍ ላለ ጊዜ ያህል (ከጥር ወር 1998 ዓም እስከ ኅዳር ወር 2001 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በፕሬዝዳንትት ማገልገላቸው ይታወሳል። የዚያን ጊዜ የአንጋፋው ባንክ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲሾሙ የ30 ዓመት ወጣት ነበሩ። ይህም ሁኔታም የሥራ ልምዳቸውን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት በዘርፉ በተሰማሩ ብዙ ግለሰቦች ዘንድ ጥርጣሬንና አግራሞትን ፈጥሮ ነበር።
አቶ አቤ አክለውም በድጋሚ ኃላፊነቱን ተረክበው እንዲሠሩ ምክንያት የሆናቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞችን ከልብ መውደዳቸውና ሠራተኛው ለእርሳቸው የነበረው አክብሮትና ፍቅር እንደሆነ ገልፀዋል። ባንኩ ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ከፍ ለማድረግ ከአመራሩና ሠራተኛው ጋር በመሆን የአቅማቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል።
ከሐምሌ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የባንኩ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ባጫ ጊና ሀገራቸውን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለማገልገል ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ነው አቶ አቤ ሳኖ ባንኩን እንዲመሩ በኃላፊነት የተመደቡት።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ሌሎች ዜናዎች፦March 20, 2020 at 3:01 am #13914AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራር አባላት ፊቤላ ኢንዱስትሪያል በማስገንባት ላይ የሚገኘውን ግዙፍ የምግብ ዘይት ፋብሪካን ጎበኙ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራር አባላት ፊቤላ ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በማስገንባት ላይ የሚገኘውን ግዙፍ የምግብ ዘይት ፋብሪካን ጎበኙ። ፋብሪካው በተያዘው በጀት ዓመት ተመርቆ ምርት እንደሚጀምር በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፋይናንስ በማድረግ እየተሳተፈበት የሚገኘውና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቡሬ ከተማ በኢትዮጵያዊው ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴ የተገነባው የዘይት ፋብሪካ በዓመት 500 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት የሚያመርት ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን ከ50 እስከ 60 በመቶ መሸፈን የሚያስችልና ለዘይት ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማዳን የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሚሰማሩና ለበርካቶች የሥራ ዕድል ለሚፈጥሩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ብድር የሚያቀርብ ሲሆን፥ በቡሬ ከተማ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ወጥቶበት በመገንባት ላይ ለሚገኘው የምግብ ዘይት ፋብሪካም ባንኩ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማቅረቡን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና የጉብኝት ቡድኑ አስተባባሪ አቶ ሙሉነህ አቦዬ ይገልፃሉ።
በቡሬ ከተማ በ30 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታው ተገባዶ የማሽን ተከላ ሥራው እየተጠናቀቀ የሚገኘው ይህ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ምርት እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን፥ ከ2500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
በአቶ በላይነህ ክንዴ በመገንባት ላይ ያለው ፋብሪካው፥ የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚሸፍን በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል። በሀገር ውስጥ ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ወደ ዘርፉ መግባታቸውን የገለጹት አቶ በላይነህ ክንዴ፥ ፋብሪካው ወደ ምርት ሲገባ የውጭ ምንዛሬ በማዳን በኩል ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
በመገንባት ላይ ያለው ትልቅ የምግብ ዘይት ፋብሪካ አካባቢው ከሱዳን ጠረፍ እስከጃዊ አኩሪ አተር፣ ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ስንዴና በቆሎ በከፍተኛ ደረጃ ትርፍ አምራች በመሆኑ ምርቶቹን በግብአትነት በመጠቀም የምግብ ዘይት በከፍተኛ ደረጃ በማምረት የአገሪቱን ከ50 እስከ 60 በመቶ ፍላጎት እንደሚሸፍንም ነው አቶ በላይነህ የጠቆሙት።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በቡሬ ከተማ በመገንባት ላይ ለሚገኙት ሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ፋይናንስ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙና በአምራች ኢንዱስትሪው ለተሰማሩ የግል ኢንቨስተሮች ፋይናንስ በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ይህን ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሙሉነህ አቦዬ አስታውቀዋል።
በቡሬ ከተማ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ምርት ለመግባት በዝግጅት ላይ ያለው ፊቤላ ኢንዳስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የዘይት ፋብሪካ በ2006 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን የጀሪካን፣ የማሸጊያ፣ የሳሙና፣ የማርጋሪንና የካርቶንን ጨምሮ ሰባት የተለያዩ ፋብሪካዎችን በውስጡ ይዟል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
April 2, 2020 at 4:00 pm #14046SemonegnaKeymasterቱሉሞዬ እና ኮርቤቲ የጂኦተርማል ፕሮጀክቶች የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ተከናወነ
አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የፈረንሳዩ ሜሪድየም (Meridiam) ኢንቨስትመንት ኩባንያ የከርሰ ምድር እንፋሎት ኃይል (geothermal energy) ማመንጫ ገንብቶ ኃይል ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።
በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በተካሄደው ስምምነት ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ በአፍሪካ የሜሪድየም ኢንቨስትመንት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የቱሉሞዬ ፕሮጀክት ሊቀመንበር ሚስተር ማቲው ፒለር (Mathieu Peller) እና የኮርቤቲ ተወካይ ናቸው።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት በኃይል ልማት ዘርፍ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጮችን በማስፋት የግል አልሚዎችን ማሳተፍ ተጀምሯል። አሁን የተፈረመው ስምምነትም ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ማሳያ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ ወደ ግንባታ እንዲገባ ከግል አልሚዎች ጋር ድርድር ሲያካሂዱ የቆዩትን አባላት አመስግነዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሸዴ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ስብጥሩን በማመጣጠን የሀገሪቱን ኢነርጂ የማምረት አቅም እንደሚያሳድግ በመግለፅ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚን የፈጠረ እንደሆነም ጠቁመዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ከሆነ ሥምምነቱ በሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ የግል አልሚዎችም ትልቅ ዕድል እንደሚከፍትላቸው አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ከኩባንያው ጋር የነበረው ድርድር ተጠናቆ ስምምነት ላይ መደረሱ እንዳስደሰታቸው ጠቅሰው የግል አልሚዎች ተሳትፎ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሚያደርገው የሃይል አቅርቦትና ስብጥር የሚግዝ መሆኑን በመግለጽ ሌሎችም የግል አልሚዎች በዚህ ረገድ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በአፍሪካ የሜሪድየም ኢንቨስትመንት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የቱሉሞዬ ፕሮጀክት ሊቀመንበር ሚስተር ማቲው ፒለር (Mathieu Peller) በበኩላቸው በአፍሪካ የሜሪድየም ኢንቨስመንት ኩባንያ ዋና መቀመጫን አዲስ አበባ ያደረጉት ኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሏት በመሆኑ ነው ብለዋል። አሁን ከጀመሩት የከርሰ ምድር እንፋሎት በተጨማሪ በትራንስፖርት እና በተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮችም መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ሰፊ ዕቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ቱሉሞዬ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን ግንባታውም በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታም 50 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን ግንባታውም እ.ኤ.አ. በ2023 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል። ሁለተኛውን ምዕራፍ ደግሞ 100 ሜጋ ዋት ለማመንጨት እ.ኤ.አ. ከ2023 በኋላ ገንብቶ ለማጠናቀቅ መታሰቡን ለማወቅ ተችሏል።
የፕሮጀክቱን ግንባታ የሚያከናውነው ቱሉሞዬ ጂኦተርማል ኩባንያ ሲሆን የቁፋሮውን ሥራ ደግሞ ኬንያ ጀነሬሽን የተባለ የኬንያ ሥራ ተቋራጭ የሚያከናውን ሲሆን ሚኪዳ የተባለ ሃገር በቀል ኩባንያም እንደሚሳተፍ ማወቅ ተችሏል።
ቱሉሞዬ እና ኮርቤቲ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪ እያንዳንዳቸው 800 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 1.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነም ነው በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የተጠቆመው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
May 16, 2020 at 4:06 am #14525AnonymousInactiveእናት ባንክ እና ዳሸን ባንክ የብድር ወለድ ስረዛ/እፎይታ እና የአገልግሎት ማሻሻያ አደረጉ
አዲስ አበባ (ፋና/ዋልታ) – እናት ባንክ ለተለያዩ የብድር ዘርፎች የብድር ወለድ ስረዛና የአገልግሎት ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ። ባንኩ በሰጠው መግለጫ ኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝነት በዓለምአቀፍ ደረጃ መሰራጨት ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በዓለም ማኅበረሰብ ላይ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን በማድረስ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሷል።
ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ የንግድ እንቅስቃሴና በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት በማድረስ ላይ መሆኑን ነው የገለጸው። በመሆኑም እናት ባንክ ይህንን ጉዳይ በከፋተኛ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ተበዳሪዎቹ የብድር ወለድ ስረዛና የተለያዩ የአገልግሎት ማሻሻያዎችን ማድረጉን ነው ያሳወቀው።
የማሻሻያው ዋና ዓላማም እየተከሰተ ያለውን ችግር በጋራ ለመወጣት፣ በደንበኞች የንግድ እንቅሳቃሴ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ፣ የብድር አመላለስን የተሻለ ለማድረግና የሀገራችን ኢኮኖሚ ሚዛናዊነቱን ጠብቆ ማስኬድ በሚቻልበት አካሄድ ባንኩ የራሱን ድርሻ ለመወጣት ታሳቢ ያደረገ ነው ብሏል ።
በዚህም መሠረት የብድር ወለድና አገልግሎት ክፍያን አስመልክቶ በሆቴልና ቱሪዝም የሥራ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞች ከግንቦት እስከ ሀምሌ የብድር ወለድ እንዳይከፍሉ መሰረዙን ገልጿል።
ከዚያም ባለፈ የብደር ማራዘሚያ ላይ የሚከፈለዉ የአገልግሎት ዋጋ፣ የኦቨር ድራፍት እድሳት ላይ የሚከፈለዉ የአገልግሎት ዋጋ፣ ብድራቸውን ከሚጠበቅባቸው የመክፈያ ጊዜ ቀድመው ለሚከፋሉ ደንበኞች ይጣል የነበረው ቅጣት እንዲሁም ውዝፍ የብድር ዕዳን አዘግይቶ ሲከፈል የሚጣል ቅጣት ሙሉ ለሙሉ መነሳቱንም ነው ያብራራው።
በዓለምአቀፍ ባንኪንግ ዙሪያም እናት ባንክ የተለያዩ ማሻሻያዎች ማድረጉን ገልጾ፥ በዚህም አስመጪዎች እቃ ወደ ሀገር ለማስገባት ለከፈቱት ሌተር ኦፍ ክሬዲት (LC) አሁን በዓለም ላይ ከተፈጠረዉ ችግር አኳያ አስቀድመዉ ለማራዘሚያ የሚጠየቁት የአገልግሎት ክፍያ ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳ መደረጉን አንስቷል።
በተያያዘም ከኮቪድ-19 ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ዕቃዎች ለሚያሰመጡ አስመጪዎች ባንኩ ሃምሳ በመቶ (50%) የአገልግሎትና የኮሚሽን ክፍያ መቀነሱን ነው የገለጸው።
እናት ባንክ ማኅብራዊ ኃላፊነትን ለመወጣትና ኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ለብሔራዊ የኮቪድ-19 ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የብር 2 ሚሊዮን ብርድጋፍ ከማበርከቱም ባለፈ የባንኩ ሠራተኞችና የደንበኞች ደኅንነት ከወረርሽኙ ለመጠበቅ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆኑን ከባንኩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
በተመሳሳይ ዜና፥ ዳሸን ባንክ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እንደሚያሳድርባቸዉ በጥናት በተለዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቹ የወለድ ቅናሽ፣ የብድር እፎይታና ማራዘሚያ ጊዜ ለመስጠት ወስኗል።
የኮቪድ-19 ስርጭት በተለይ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ እያስከተለ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በመገንዘብ ቀደም ሲል በሌሎች ተጎጂ መስኮች ላይ እንዳደረገው ሁሉ በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ ደንበኞቹ እየደረሰባቸዉ ያለዉን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመጋራት መወሰኑን ለዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን (ዋልታ) በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በዚህም መሠረት በአበባና አትክልት፣ በሆቴልና ማስጎብኘት (ቱሪዝም)፣ በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራቾች፣ በፋብሪካ ምርት (manufacturing)፣ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት እና ትምህርት ተቋማት ዘርፎች ለተሰማሩና በሥራ ላይ ላሉ ደንበኞች እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር (እ.አ.አ.) ከሰኔ 1 ቀን 2020 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የወለድ ቅናሽ፣ የብድር እፎይታና ማራዘሚያ ጊዜ ሰጥቷል።
ባንኩ በአበባና አትክልት ዘርፍ ለተሰማሩ ተበዳሪዎች ቀደም ሲል በዝቅተኛ ወለድ እያበደረ የነበረ ቢሆንም፥ ዘርፉ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዞ የደረሰበትን የኢኮኖሚ ጉዳት ከግምት ዉስጥ በማስገባት ከ 1 በመቶ እስከ 2 በመቶ ተጨማሪ ቅናሽ አድርጓል።
ከፈረንጆቹ ሰኔ 1 ጀምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ደንበኞች 7 በመቶ የወለድ ምጣኔ ብቻ እንዲከፍሉ ወስኗል። በተጨማሪም ተበዳሪዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት የ6 ወር የብድር እፎይታና እስከ 5 ዓመት የሚቆይ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ ፈቅዷል።
በሆቴልና ማስጎብኘት ዘርፍ የተሰማሩ ተበዳሪዎች እ.አ.አ. ከሰኔ 1 ቀን 2020 ጀምሮ የሚከፍሉት የወለድ ምጣኔ ወደ 7 በመቶ እንዲቀንስና ተበዳሪዎቹ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት የስድስት ወር የብድር እፎይታ ጊዜና እስከ 5 ዓመት ድረስ የሚቆይ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ እንያገኙ ለማድረግ ወስኗል።
በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራቾችም እንዲሁ እ.አ.አ. ከሰኔ 1 ቀን 2020 ጀምሮ የወለድ ምጣኔ ቅናሹ ተጠቃሚ ሆነው ለሶስት ወራት 7 በመቶ ብቻ ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል። ከዚህም ሌላ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረትም የሦስት ወር የብድር መክፈያ ዕፎይታ ጊዜና እስከ ሦስት ዓመት ያለምንም የብድር ማራዘሚያ ክፍያ እንዲስተናገዱ መደረጉን ባንኩ በመግለጫው አትቷል ።
በፋብሪካ ምርት (manufacturing)፣ በሕዝብ ማመላለሻ አዉቶብስና በትምህርት ዘርፎች የተሰማሩ ተበዳሪዎችም ጭምር በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ከሰኔ 1 ጀምሮ ለ 6 ወር የብድር መክፈያ እፎይታ ጊዜና እስከ 3 ዓመት ድረስ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ ለመስጠት ወስኗል።
በተጨማሪ ዳሸን ባንክ ከላይ ለተጠቀሱትና በቫይረሱ ስርጭት ይበልጥ ለኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንሚዳረጉ በጥናት ለተለዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተጨማሪ የወለድ ምጣኔ ማስተካከያ እንዲደረግላቸዉም ወስኗል። ከ17.5 በመቶ እስከ 18 በመቶ ወለድ ይከፍሉ የነበሩና በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ ደንበኞች የ1.5 በመቶ ወለድ ቅናሽ ተደርጎላቸዉ 16 በመቶና 16.5 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል ብሏል። ከ14 በመቶ እስከ 17 በመቶ ወለድ ይከፍሉ የነበሩ ደግሞ የ1 በመቶ ቅናሽ ተደርጎላቸዉ ከ13 በመቶ እስከ 16 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ተወስኗል ።
ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም የብድር አገልግሎት ማሻሻያ ዉሳኔዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከታወጀበት ጊዜ በፊት በተበላሸ ብድር ዝርዝር ዉስጥ ይገኙ የነበሩ ብድሮችን እንደማይጨምርም ዳሸን ባንክ አስታውቋል።
ምኝጮች፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት/ ዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት
May 23, 2020 at 12:36 am #14574AnonymousInactiveየኢትዮጵያ አየር መንገድ ለጭነት አገልግሎት ተግባር በ22 የመንገደኛ አውሮፕላኖቹ ላይ የምህንድስና ማስተካከያ /conversion/ አደረገ
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ አየር መንገድ) – እንደሚታወቀው የዓለማችንን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ያስቆመው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) ከሌሎች ዘርፎች በተለየ ሁኔታ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪውን ከ90 በመቶ በላይ እንዲቆም አድርጓል። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የመንገደኛ በረራዎቹን በተመሳሳይ ሁኔታ ከ90 በመቶ በላይ እንዲቆሙ በመደረጋቸው የተነሳ የአየር መንገዱን ህልውና የሚፈታተንና በታሪኩ የመጀመሪያ ከሆነው ዓለምአቀፋዊ ቀውስ ለመውጣት ሙሉ በሙሉ የሥራቴጂክ እቅድ ለውጥ በማድረግ የትኩረት አቅጣጫውን ወደ እቃ ጭነት ቢዝነስ በማዞር እየሠራ ነው። ከዚህም ጋር በተያያዘ በመላው ዓለም እየጨመረ ለመጣው የጭነት አገልግሎት (cargo service) ፍላጎት በነበሩት የጭነት ማመላለሻ አውሮፕላኖች አጠናክሮ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል። ይህንን አዲስ ስትራቴጂ በመጠቀም የጭነት ማጓጓዝ አቅሙን ለማሳደግ ተጨማሪ 22 የመንገደኛ አውሮፕላኖችን (passenger planes) የጭነት አገልግሎት እንዲሰጡ በውስጥ አቅም የምህንድስና ማስተካኪያ (conversion) ተደርጎባቸው በጭነት አገልግሎት ሥራ ላይ ይገኛሉ።
አየር መንገዱ በመንገደኛ አውሮፕላኖቹ ውስጥ የሚገኙ መቀመጫዎችን ከቦታቸው በማንሳት ስፍራው ለጭነት አገልግሎት እንዲውል ያደረገው ዓለምአቀፍ የአቪየሽንና የቴክኒክ ተቆጣጣሪ አካላት ያስቀመጧቸውን መስፈርቶች በመከተልና በማሟላት ነው። አየር መንገዱ የኮሮናን ቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ሕይወት አድን የሆኑ የሕክምና ቁሳቁሶችን በመላው አፍሪካ በማጓጓዝ ላይ ይገኛል። የአገልግሎት ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣትም በመንገደኛ አውሮፕላን የእቃ ማስቀመጫ ቦታ፣ እንዲሁም የአውሮፕላኖቹ ወንበሮች ሳይነሱ ጭነት በመጫን አገልግሎቱን በማቀላጠፍ ላይ ይገኛል።
አቶ ተወልደ ገብረማርያም፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የጭነት አገልግሎት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አስመልክተው፥ “የመንገደኛ አውሮፕላኖቻችንን ለጭነት አገልግሎት እንዲውሉ በማጥናትና በማስተካከል የምህንድስና ሥራ ላይ የተሳተፉትን የአየር መንገዳችን የአውሮፕላን ጥገና ክፍል /MRO/ ብቁ ባለሙያዎችን ከልብ አደንቃለሁ፤ አመሰግናለሁ። ይህ ተግባር በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የበርካታ ደንበኞቻችንን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችለንን የተሻለ አቅም ለመፍጠር ያስችለናል። በዓለማችን የሚገኙ ሕዝቦች የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመመከት የሚያስችላቸውን የሕክምና ቁሳቁስም ሆነ ሌሎች የመሠረታዊ ፍሎጎት ቁሶች በእጅጉ የሚፈልጉበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። በዚህ ታሪካዊና አስቸጋሪ ወቅት ይህንን ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ ለመዋጋት ዋነኛ ተዋንያን በመሆናችን ደስተኞች ነን። ከዚህም ጋር በተያያዘ አገልግሎታችንን አሁን ካለበት በላቀ ደረጃ ለማሳደግ የተለያዩ አማራጮችን በማጤን ላይ እንገኛለን።” ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈታኝ በሆነው በዚህ ወቅት የዓለምን ማኅበረሰብ ለማገልገል ባደረገው ጥረት ሕይወት አድን የሆኑ የሕክምና መሣሪያዎችን በበርካታ መጠንና ፍጥነት ያጓጓዘ ሲሆን፣ በዚህም አጠቃላይ የአገልግሎት ብቃቱን በማስመስከሩ ምስጋናና አድናቆት እየተቸረው ይገኛል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
May 24, 2020 at 3:15 am #14581AnonymousInactiveብርሃን ባንክ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለጉዳት የተጋለጡ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለመደገፍ የብድር ወለድ ቅናሽ አደረገ
ብርሃን ባንክ አክሲዮን ማኅበር (አ.ማ.) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ተጽዕኖን ለማቃለል በማሰብ ከ 0.5% እስከ 4% የሚደርስ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ ከግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ ከሜይ 18 ቀን 2020) ጀምሮ ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ። ጋዜጣዊ መግለጫው እንደሚያስረዳው፥ የወለድ ቅናሽ ማስተከካያው በተለያዩ ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ኮቪድ-19 ያስከተለውን ተጽዕኖ ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሲሆን፥ ሁሉም የብድር ዘርፎች ማለትም የግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ የአገር ውስጥ፣ ንግድና አገልግሎት፣ የወጪ ንግድ፣ ሕንፃና ግንባታ፣ የግል ብድር ዘርፎች የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ተጠቃሚ ሆነዋል።
የወለድ ምጣኔ ቅናሹ በተለይም በኮቪድ-19 ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ዘርፎች ከፍተኛውን የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። በዚህም መሠረት ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላኪ ዘርፍ የ4% የወለድ ምጣኔ ቅናሽ የተደረገ ሲሆን፤ እንዲሁም ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ደግሞ የ3.5% ቅናሽ ተደርጓል። በተጨማሪም ለእነዚህ የኢኮኖሚ ዘርፎች የስድስት ወራት የፍሬ ብድር እና የወለድ ክፍያ የእፎይታ ጊዜ ከግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ ከሜይ 18 ቀን 2020) ጀምሮ እንዲደረግላቸው ባንኩ ወስኗል። በሌላም በኩል ተበዳሪዎቻችን በኮቪድ-19 ጫና ምክንያት የብድር ክፍያ ማራዘሚያ ጥያቄ ቢያቀርቡ ጥያቄያቸው እንደሁኔታው እየታየ የሚስተናገድ ይሆናል።
ብርሃን ባንክ ይህንን የወለድ ምጣኔ ቅናሽ በማድረጉ በዓመት ሊያገኝ የሚችለውን ወደ ብር 100 ሚሊዮን የሚሆን የወለድ ገቢ የሚያሳጣው መሆኑ ታውቋል። ይህም ውሳኔ ከባንኩ እድሜ እና አቅም አንፃር ሲታይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ብሔራዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ባንኩ የበኩሉን አስተዋፅኦ ከማበርከት አንፃር የሚሄድበትን ርቀት እና ቁርጠኝነት ያመለክታል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) በሀገራችን ከተከሰተ ጀምሮ ብርሃን ባንክ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ሰፊውን ማኅበረሰብ እና የባንኩን ደንበኞች ማዕከል ያደረጉ በርካታ ተግባራትና ድጋፎች ከዚህ ቀደም ማከናወኑ ይታወቃል። ከዚህም አንፃር ቀደም ሲል የ Letter of Credit ማራዚሚያ ኮሚሽን ሙሉ በሙሉ ማንሣቱን፣ የብድር ማራዘሚያ ኮሚሽንና የተጨማሪ ወለድ ማንሣቱ፤ በአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች በ35 ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች የንፅህና አገልግሎት መስጫ የውሃ ታንከሮችን ማዘጋጀቱ እና እንዲሁም ለጤና ሚኒስቴር ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ብር 3 ሚሊዮን ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።
በመጨረሻም ብርሃን ባንክ ለወደፊቱም የወረርሽኙን ተጽዕኖ ለመቅረፍ ተመሳሳይ ድጋፎችን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አስታውቋል።
ምንጭ፦ berhanbanksc.com
May 30, 2020 at 3:29 am #14654AnonymousInactiveየሠራተኞቻቸውን ደመወዝ የቀነሱ እና ከሥራ ያሰናበቱ 14 ሆቴሎች ተለይተው ታወቁ – የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር
አዲስ አበባ (ኢፕድ) – የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን የሥራ መቀዛቀዝ ምክንያት በማድረግ የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ ያልከፈሉ፣ የቀነሱ እና ሠራተኞቻቸውን ከሥራ ያሰናበቱ 14 ሆቴሎች መለየታቸውን የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር የኮምኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እጅጉ እንደሻው ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደገለጹት፥ መንግሥት የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉን ለመደገፍ ድጎማ ቢያደርግም አንዳንድ ሆቴሎች ሠራተኞቻቸውን እያሰናበቱ፣ እንዲሁም ደመወዛቸውን እያስቀሩና እየቀነሱ ነው።
ሆቴሎችን መለየት የተቻለው ማኅበሩ በመሠረተው የቴሌግራም የመገናኛ ዘዴ መሆኑን ጠቁመው፥ ሠራተኞች የደረሰባቸውን ችግርና ሥራ የለቀቁበትን ደብዳቤ ይዘው መጥተዋል። ማኅበሩ የተገኙ የደብዳቤ ማስረጃዎችን በመያዝ ለኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር ኮንፌዴሬሽን ማሳወቁን አቶ እጅጉ አመልክተዋል።
“ተበድረን ለሠራተኛ አንከፍልም፤ መንግሥት እንደሚያደርግ ያድርጋችሁ” ያሉ ሆቴሎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ እጅጉ፥ መንግሥት ያወረደውን መመሪያና ድጎማ ተፈፃሚ የሚያደርጉ አሠራሮችን እንዲያመቻች አሳስበዋል።
እንደ አቶ እጅጉ ገለጻ፥ የሆቴል ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት አያገኙም፤ የሚከፈላቸው ደመወዝ በፊትም አነስተኛ ነበር። በዚህ ወቅት የደንበኛ ጉርሻም አያገኙም። የትራንስፖርት ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል:: ከአነስተኛ ደመወዛቸው ላይ ግብር ይቆረጥለታል:: በመሆኑም መንግሥት ለእንዲህ አይነት ሠራተኞች የግብር ቅናሽ ወይም ምኅረት እንዲያደርግላቸውና ሙሉ ደመወዛቸውን እንዲያገኙ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር ፀሐፊ አቶ ክፍሉ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው፥ ሆቴል ያለሠራተኛ ባዶ ህንፃ ማለት እንደሆነ ገልፀው፥ “የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜያዊ ነው፤ ነገ ያልፋል። ልምድ ያላቸውን የሆቴል ሠራተኞች ማሰናበት ለባለሀብቱም ለአገርም ክስረት ነው” ብለዋል።
የሆቴል ሠራተኛ ዲፕሎማት እንደመሆናቸው በአግባቡ ካልተያዙ የሠራተኞች ዕጣ ለባለሀብቱም እንደሚተርፍ አመልክተው፥ “በዚህ ወቅት የተባረረ ሠራተኛ ነገ ቀን ሲወጣ ‘ና!’ ቢባል የሚመጣበት ሞራል አይኖረውም። የሆቴል ሠራተኛ ደንበኛን የሚያረካው በደስታ ሲሠራ ነው” ሲሉም አቶ ክፍሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር የሥልጠና እና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ሥዩም እንደገለጹት፥ በሌሎች ሀገራት እንኳን ያልተደረገውን የኢትዮጵያ መንግሥት ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል። ይህ ዓይነት ድጋፍ በሌሎች ዘርፍ አልተደረገም። መንግሥት ያደረገው ድጋፍ ግን ከታች ባለው የአፈፃፀም ችግር ክፍተት ታይቶበታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
June 7, 2020 at 2:10 am #14736SemonegnaKeymasterሕብረት ባንክ አዲሱን መለያ እና አርማውን ይፋ አደረገ
ሕብረት ባንክ የተገነባበትን የሕብረትና የአካታችነት መርሁን የሚያጐላለትን አዲስ መለያ እና አርማ ይፋ አደረገ። ባንኩ አዲሱን መለያ ቀርጾ ያጠናቀቀው ዓለም-አቀፍ ደረጃ ያለውን የባንኩን የጨረታ መስፈርቶች በሟሟላት ከተመረጠው ስቱዲዩኔት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ከተሰኘ ሀገር በቀል አማካሪ ድርጅት ጋር በመሆን ነው። እንደ ምንጊዜውም ባንኩ እንዲህ ዓለም-አቀፋዊ ብቃት ካላቸው ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር በመሥራት ይህንን የመሰሉ ትልልቅ ፕሮጀክት ሊያሳካ ችሏል። በተመሳሳይ ሕብረት ባንክ በቅርቡ የኮርባንኪንግ እና የኦንላይን ፕላትፎርም በራሱ የየመረጃ ቴክኖሎጂ (information technology) ቡድን ማዘመኑ የሚታወስ ነው።
አዲሱ የባንኩ መለያ ሕብረት ባንክ ከደንበኞቹ፣ ከአጋሮቹና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትስስር እንዲያንፀባርቅ ሆኖ የተቀረፀ ሲሆን፤ በሕብረት እና በጋራ እድገት ላይ የተመሠረተ መስተጋብር ወይም “eco-system” ለመፍጠር ባንኩ የወሰደውን ቁርጠኝነትም ጭምር የሚያረጋግጥ ነው። ባንኩ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ “በእርግጥም የስኬታችን ምንጭ ደንበኞቻችን እና አጋሮቻችን ናቸው። ‘በሕብረት እንደግ’ የሚለው የባንካችን መሪ ቃልም ለዚህ እውነት እማኝ ነውና በጐላ እና በደመቀ መልኩ መገለጥ እና መታየት ይገባዋል” ብሏል።
መግለጫው ሲቀጥል እንደሚከተለው ይነበባል፦
ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አዲሱ የባንካችን መለያ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከቴክኖሎጂ ጋር ያለንን ቁርኝት ከግንዛቤ ውስጥ የከተተና፣ ከዚህ በስተጀርባ ውስብስብ የሚመስሉ አያሌ ጉዳዮች በመላ የሚቃለሉበትን መንገድ የሚጠቁም ብሎም ወደፊት ለመገስገስ የምንገባውን ቃልኪዳን የሚያረጋግጥ ነው።
ሕብረት ባንክ ያካበተውን የቴክኖሎጂ ብቃት፣ የደንበኞቹንና የአጋሮቹን አብሮነት እንዲሁም በፋይናንሱ ዘርፍ ያዳበረውን ልምድ በመሰነቁ የተሻለ ነገን በሕብረት ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ ጉልበት እንዳለው እሙን ነው።
አዲሱ የሕብረት ባንክ መለያ የተለያዩ ሕብረ ቀለማትን ያካተተ ሲሆን ይህም የሕብረትን ምንነት የሚያንጸባርቅ ነው። ቀለማቱ ዘመናዊነትን፣ ሙያዊ ጨዋነትንና፣ መስህብን በማመላከት ዕይታን የሚስቡና በቀላሉ ተለይተው የሚታወቁ ናቸው ።
የአዲሱ የባንካችን መለያ እና አርማ ፍሬ ሀሳብ ‹‹ሕብረት›› ከሚለው ስማችን የተወሰደ ሲሆን መልዕክቱም ትብብርን፣ ሕብርን፣ አብሮነትን፣ አጋርነትን፣ ቅንጅትንና መተጋገዝን የሚገልጽነው።
ይኽንን ምከግምት ውስጥ በማስገባት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ባንክ ስማችን በዓለም-አቀፍ ደረጃ “ሕብረት ባንክ” በሚለው ስያሜ ብቻ የሚወከል ስለሆነ እንደከዚህ ቀደሙ “ዩናይትድ ባንክ” የሚለውን የእንግሊዝኛ ትርጓሜ እንደአማራጭ ስያሜ በቀጣይ የማንጠቀም መሆኑን እናሳውቃለን። የአዲሱ መለያ ቃል-ኪዳንም (brand promise) “በሕብረት የተሻለ ነገን እንገነባለን” የሚል ነው። ይህም ቃልኪዳን ውስጣችንን የሚያነቃቃና ከጅምሩ የተመሰረትንለትንና አሁንም የምንጠቀምበትን መሪ ቃል (tag line) “በሕብረት እንደግ” የሚለውን በሕብረት የማደግ ዓላማ የሚያጸና ነው።
ምንጭ፦ ሕብረት ባንክ
June 21, 2020 at 12:51 am #14881AnonymousInactiveሲቢኢ ኑር (CBE Noor) ― የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ራሱን የቻለ ስያሜና አርማ ሥራ ላይ አዋለ
አዲስ አበባ (CBE) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ‘ሲቢኢ ኑር’ (CBE Noor) የተሠኘ ስያሜና አርማ ሥራ ላይ ማዋሉን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም በተዘጋጀ የማስተዋወቂያ መርሀ-ግብር ላይ ይፋ አድርገዋል።
ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በተጠናከረ መልኩ ለሕብረተሰቡ ለማዳረስ እየተገበረ ካለው መጠነ ሰፊ የማሻሻያ ተግባራት ጋር ተያይዞ አዲሱ ስያሜና አርማ ሥራ ላይ መዋሉን አቶ አቤ ሳኖ በመርሀ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።
አዲሱን ስያሜ እና አርማ በማዘጋጀት ሂደት በርካታ አማራጮች የቀረቡ መሆኑን አቶ አቤ አስታውሰው፥ ‘ኑር’ የሚለው አረብኛ ቃል ‘የብርሀን ፍንጣቂ’ የሚለውን ትርጓሜ የያዘ ሲሆን በአማርኛ መኖር የሚለውን መልካም ተስፋን የሚያመለክት በመሆኑ ለአገልግሎቱ ፈላጊዎች ተስፋን የሚሰጥ እንዲሁም ባንኩ ያለውን ራዕይ አመላካች ቃል ስለሆነ የባንኩ የሸሪዓ አማካሪዎችና የባንኩ ከፍተኛ የሥራ አመራር አስተያየት ሰጥተውበት ስያሜው መመረጡን ገልፀዋል።
ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ አቤ፥ በእምነታቸው ምክንያት ወለድ ለማይፈልጉ ደንበኞች አገልግሎቱን እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ባንኩ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን አክለው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. በ2011 ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱን ተከትሎ እ.ኤ.አ. ከህዳር 2013 ጀምሮ በተመረጡ 23 ቅርንጫፎች በተለየ መስኮት አገልግሎቱ መሰጠት መጀመሩን በንግግራቸው ያስታወሱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት፥ በአሁኑ ጊዜ በ1574 በላይ ቅርንጫፎች በመስኮት ደረጃ እንዲሁም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ ለመስጠት በተከፈቱ ከ53 በላይ ቅርንጫፎች አማካኝነት አገልግሎቱ በመሰጠት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
ባንኩ የሸሪዓ መርህን የሚከተሉ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን ለሕብረተሰቡ በማድረስ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ አቤ እ.ኤ.አ. ግንቦት 2020 መጨረሻ ድረስ በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 30.3 ቢሊዮን ብር መድረስ መቻሉን አመላክተዋል።
አቶ አቤ በገለፃቸው፥ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን የሚጠቀሙ ደንበኞች ብዛትን 2.7 ሚሊዮን መድረሱንና ባንኩ በተለያዩ የሥራ መስኮች ለተሰማሩ ደንበኞች 3 ቢሊዮን ብር የፋይናንስ አገልግሎት ማቅረቡን አስረድተዋል።
አቶ አቤ ባንኩ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት፣ ዕውቅናና አመኔታን ያተረፉ፣ በዘርፉ በቂ የትምህርት ዝግጅት፣ ጥልቅ ዕውቀትና የካበተ ልምድ ያላቸው አምስት አባላት ያሉት የሸሪዓ መማክርት ኮሚቴ እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ ሰይሟልም ነው ያሉት።
የሸሪዓ አማካሪዎችን መሰየሙ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን የሸሪዓ እሴትን በጠበቀ መልኩ ለመስጠት እንዳስቻለው የገለፁት አቶ አቤ የሸሪዓ መርህ መከበሩን የሚያረጋግጡ የውስጥ ቁጥጥር አሠራሮችን የመተግበር፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሂሳብ መዝገብ የመለየት እና መመሪያዎችን የማርቀቅ ተግባርም ማከናወኑን አክለው ገልፀዋል።
አቶ አቤ በንግግራቸው መጨረሻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ የተሻለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የማቅረብ ትልቅ አላማ እንዳለው እና በቀጣይ የቁጠባ እና የፋይናንስ አማራጮቹን በማስፋት፣ አዳዲስ አሠራሮችን በመተግበር እና ይበልጥ ዘመናዊ በማድረግ የባንክ አገልግሎቱን ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል አመቺና ተስማሚ በሆነ መልኩ ለማቅረብን ያለውን ቁርጠኝነት ገልፀው፥ ደንበኞችና መላው ሕብረተሰብ የወቅቱ የጤና ስጋት ከሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እራስንና ቤተሰብን በመጠበቅ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሆነዉ ሲቢኢ ኑር (CBE Noor) ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሸሪዓ መርህን በመከተል በሚሰጠው ‘ሲቢኢ ኑር’ (CBE Noor) በተሰኘው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት፦
-
- ከወለድ ነፃ የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት
- ለበይክ የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት (ለሀጅ እና ኡምራ ተጓዦች)
- ዘካ የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት (ዘካ ለሚያወጡ)
- የፋይናንስ አገልግሎት
- የዓለም አቀፍ ንግድ ድጋፍ
- የዳያስፖራ የቤት መግዣ/መሥሪያ ብድር እና
- ሌሎችንም አገልግሎቶች
ከ50 በላይ በሆኑ አገልግሎቱን ብቻ ለመሥጠት በተከፈቱ ቅርንጫፎች እና ከ1574 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎች በተለየ መስኮት ይሰጣል፡፡
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
June 25, 2020 at 4:09 am #14953AnonymousInactiveኢትዮጵያ ውስጥ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ
አዲስ አበባ (ፋና) – በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባውና በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርተው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ። በፋብሪካው ምርቃ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ፋብሪካው የዳቦ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን በምግብ ራሳችንን የመቻል ፍላጎታችንን፣ ከድህነት የመውጣት ጥማትን እና የብልፅግና ጎዳናን አመላካች ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ በ10 ወራት ፋብሪካ ገንብቶ ማጠናቀቅ የሚታሰብ አልነበረም፤ በተለይም ለሚድሮክ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ ሚድሮክ ከነበረበት ድክመት ተላቆ ፋብሪካውን በዚህ ፍጥነት ማጠናቀቅ መቻሉ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አክለውም መንግሥት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ስንዴን ከውጭ ማስገባት የማቆም ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፤ ለዚህም የሙከራ ምርቶች መጀመራቸውን አስታውቅዋል። ስንዴ ማምረት ብቻ ሳይሆን ምርቶቹን ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን፥ ለዚህም ለግሉ ዘርፍ ጥሪ መቅረቡን አስታውቅዋል።
መንግሥት ላቀረበው ጥሪ ሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ፈጣን ምላሽ መስጠታቸውን በመግለፅ፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ እውን እንዲሆን በማድረጋቸውም ምስጋናቸውን ያቀረቡላቸው ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሌም ከጎናቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል።
መሰል የዳቦ ማምረቻዎችን ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞችም ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን እና ለዚህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ከተሞች መሰል መለስተኛ የዳቦ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሯን አስታውቀዋል። በተጨማሪም የዱባይ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያንም ከፍ ያለ ፋብሪካ ቃል መግባታቸውን እና ይህም በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
እነዚህ አሁን የተገነቡ እና ወደ ፊት የሚገነቡ ፋብሪካዎች በቀን ዳቦ ለማግኘት ለሚያዳግታቸው ሕፃናት ዳቦ እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ።
“አዲስ አበባን፣ ክልሎችን፣ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን እንለውጣለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ “ኢትዮጵያ የጀመረችውን በሙሉ ታጠናቅቃለች፤ ይህም በየአደባባዩ እየጮኸች ሳይሆን ሪቫን እየቆረጠች ነው” ብለዋል።
ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማም፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተገንብቶ እውን እንዲሆን ለተሳተፉ አካላት መስጋና አቅርበዋል። የሸገር ዳቦ ፋብሪካ መገንባት የከተማውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ይቀንሳል ያሉት ኢ/ር ታከለ፥ በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎችን ጥያቄ የሚመልሱ ሥራዎችን በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱብንም አስታውቅዋል።
የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪ ሕዝብ በከፍተኛ ጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ አምርቶ ማቅረብ እንዲቻል ሸገር ዳቦ ፋብሪካን ገንብቶ ለፍሬ አብቅቷል ብለዋል።
በ41 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ፋብሪካው፥ የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካ፣ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ እና 120 ሺህ ኩንታል ስንዴ ማከማቸት የሚያስችል 4 ጎተራ እንዳለው አስታውቀዋል። በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካው በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርት መሆኑን እና በቀን በሶስት ፈረቃ እስከ 2 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርት መሆኑ ገልፀዋል።
ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ግንባታው በአጠቃላይ በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ መከናወኑን ያስታወቁት አቶ አብነት፥ አጠቃላይ ወጪውም በሚድሮክ እህት ኩባንያዎች የተሸፈነ መሆኑንም አስታውቅዋል። ፋብሪካው ከምርት እስከ ማከፋፈል ሂደት ቁጥራቸው 3 ሺህ 400 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።
ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.