Home › Forums › Semonegna Stories › ኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን እና ለመከለከል የሚደረገውን ጥረት ወቅታዊ መረጃ
- This topic has 16 replies, 3 voices, and was last updated 4 years, 4 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
February 3, 2020 at 1:38 pm #13505SemonegnaKeymaster
ዓለምን እጅግ ያሰጋው የኖቬል ኮሮና ቫይረስ የተጠቂዎች ቁጥር እጅግ አሻቅቧል፤ ቻይና ውስጥ በአንድ ቀን ብቻ 57 በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ሞተዋል። የተለያዩ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከዉሃን ከተማ ማስወጣት ጀምረዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኖቬል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ከታሕሳስ 21, 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቻይና ዉሃን (Wuhan) ግዛት የተከሰተ መሆኑን ካሳወቀ ጀምሮ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ደረስ (በኢትዮጵያ ቀንና ሰዓት አቆጣጠር እስከ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ) በአጠቃላይ 17,488 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 2,298 (13%) ታማሚዎች በሽታው ክፉኛ የጸናባቸው (in critical conditions) ናቸው። እስካሁን ድረስ በሽታው የተገኘባቸው የሀገራc ቁጥር ቻይናን ጨምሮ 24 የደረሰ ሲሆን፣ በበሽታው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 362 ደርሷል (361 የሞቱደርሷል ቻይና ውስጥ ሲሆን፣ አንዱ ብቻ ፊሊፒንስ ውስጥ ነው)። ሰኞ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ብቻ 57 በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ቻይና ውስጥ ሞተዋል።
በሀገረ ቻይና እንዲሁ ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተስፋፋባቸው ግዛቶች ምንም ዓይነት የመግባትና የመውጣት አንቅስቃሴ እንዳይደረግ ቢታገድም የስርጭቱ መጠን ከሚታሰበው ባላይ አሳሳቢ አየሆነ እንደመጣ ለማወቅ ተችሏል።
ይህ መላ ዓለምን እጅግ በሚያሰጋ ሁኔታ እየተስፋፋ እየተሰጨና፣ ብሎም ቻይና ውስጥ በበሽታው የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ያለው ኖቬል ኮሮና ቫይረስ ወደ ቻይና የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን (በተለይም የ አየር በረራዎችን) መቆጣጠር ጀምሯል። ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ብዙ ጎረቤት ሀገራት ከቻይና ጋር የሚያዋስናቸውን ድንበር ለመዝጋት የተገደዱ ሲሆን፤ ሌሎች ሃገራትም ወደቻይና የሚደረጉ ማንኛውም በረራዎችን ለማቆም እንደተገደዱ ነው። ለምሳሌ የጀርመኑ ግዙፍ አየርመንገድ ሉፍታንዛ ወደ ቻይና የሚያደርጋቸውን በረራዎች (ቢያንስ እስከ የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም.) ሙሉ ለሙሉ አቁሟል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (UAE) ወደ ዋና ከተማ ቤጂንግ ከሚደረጉ በረራዎች በስተቀር ሌሎች ወደ ቻይና የሚደረጉ ሁሉንም በረራዎች እንደምትሰርዝ አስታውቃለች። ካናዳ በበኩሏ ዜግቿን ኖቬል ኮሮና ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተነሳባት ሁቤይ (Hubei) ግዛት ከምትገኘው ዉሃን (Wuhan) ከተማ ማስወጣት ጀምራለ፤ ሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
ቫይረሱ በሀገራቸው በሚኖሩ ዜጎች ላይ መታያቱን ያረጋገጡት የጂ-7 (G-7) ሀገራትም (ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ) በችግሩ ላይ በትብብር በመሥራት ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የጀርመን የጤና ሚኒስቴር ጄንስ ፋህን በትላንትናው ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ተናግረዋል።
ወደ ሀገራችን ስንመለስ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለኖቬል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን ሰኞ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። እንደመግለጫው እየተወሰዱ ካሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ውስጥ ብሔራዊ ታስክ ፎርስ እና በኢንስቲትዩቱ ለኮሮና ቫይረስ ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጠው ማዕከል ሥራ ጀምረዋል። ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ፣ ከቦሌ አየር መንገድ፣ ከግልና ከመንግስት ጤና ተቋማት ለተውጣጡ ተሳታፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ተሰጥቷል። በተመሳሳይ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ለ200 የሚሆኑ የሆስፒታል አመራሮች እና ባለሞያዎች በጤና ሚኒስተር አማካኝነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል። በቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት እና 27 የተለያዩ የድምበር መግቢያ እና መውጫ ኬላዎች ላይ የሚደረገው የማጣራት ምርመራ በተጠናከረ ሁኔታ እየቀጠለ ይገኛል። የማጣራት ምርመራው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያላቸውን ተጓዦች የሚለይ ሲሆን ይሄም የቫይረሱ የበሽታ ምልክት የሚያሳዩትን ለመለየት ይረዳል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ አራት ሰዎች (አንድ ቻይናዊ እና ሦስት ኢትዮጵያውያን) በኖቬል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ተጠርጥረው፥ አንድ በአክሱም እና ሦስት በቦሌ ጨፌ በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፥ ናሙናቸው ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጅት ተጠናቋል።
የኖቬል ኮሮና ቫይረስ አስካሁን ድረስ ምንም አይነት ፈዋሽ መድኃኒት ወይም ክትባት ያልተገኘለት ሲሆን በዋናነት የመተንፈሻ አካላትን በማጥቃት ሰዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው። የኖቬል ኮሮና ቫይረስ እንደአውሮፓውያኑ በ2003 በቻይና ከተከሰተው “ሳርስ” በሽታ ጋር የመተንፈሻ አካልን በማጥቃት በኩል ተመሳሳይ ቢመስልም፤ የስርጭት መጠኑ እና የሚያደርሰው ጉዳት ግን እጅግ ከፍተኛ መሆኑ የሚለየው ጉዳይ ነው።
March 27, 2020 at 5:17 pm #13990SemonegnaKeymasterመንግሥት የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመግታት የሚወሰዱ አዳዲስ እርምጃዎችን ይፋ አደረገ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን ለመከላከል ከተቋቋመው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣ ኮሚቴ ጋር ያለውን የክንውን ሁኔታ እና ተጨማሪ መመሪያዎች እንዲሁም <ኮቪድ-19>ን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመግታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አስመልክቶ በኢንተርኔት አማካኝነት (virtually) ውይይት አድርገዋል።
እስከ ዛሬ መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ አጠቃላይ ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 በመጨመሩ፣ ቫይረሱ በፍጥነት እየተዛመተ እንዳይሄድ ለመግታት ሲባል በቂ የመከላከል ሥራዎች መሠራታቸውን ለማረጋገጥ፣ የፌደራል መንግሥት በስፋት የቅድመ-ጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ተመልክተዋል።
ከውይይቱ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሚከተሉትን ተጨማሪ ቁልፍ እርምጃዎች ይፋ ያደረጉ ሲሆን ጥሪም አቅርበዋል።
በዚህም መሠረት፦
- ከዛሬ (መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከሰዓት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚደርሱ እና ለለይቶ መከታተያ በተዘጋጁት ሆቴሎች ለመቆየት አቅም የሌላቸው መንገደኞች ወደ አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ተዛውረው ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ መንገደኞች ለ15 ቀናት ተለይተው እንዲቆዩ የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ የሚያደርጉ ይሆናል።
- ከዛሬ አንስቶ ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታት ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማትን ጨምሮ፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የሚቆዩ ይሆናል።
- በገበያ ስፍራዎች እና በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ በጥብቅ ተፈጻሚ ሊደረጉ ያስፈልጋል። የፌደራል መንግሥት አስከፊ ብሔራዊ አደጋ በሚከሰት ጊዜ ሀይማኖታዊ ስብሰባዎች እንዲቋረጡ የማድረግ ሕገመንግሥታዊ መብት አለው። ሆኖም፣ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን እርምጃዎች ተግባራዊ ከመደረጋቸው በፊት፣ ዜጎች የማኅበራዊ ርቀት መመሪያን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።
- ሁኔታው ተጨማሪ ድጋፍን የሚጠይቅ ከሆነ ሁሉም ጡረታ የወጡ እንዲሁም በትምህርት ላይ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ለብሔራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
- የተለያየ መጠን እና ዓይነት ያላቸው መገልገያዎችን የያዙ ከ134 በላይ ተቋማት ለለይቶ መከታተያ፣ ለይቶ ማቆያ እና ሕክምና እንዲሆኑ ተለይተዋል። ስለዚህ፣ መንግሥት ሁሉም ዜጎች እንደ አልጋዎች፣ ፍራሾች፣ አንሶላዎች፣ የመተንፈሻ ቬንትሌተሮች እና ሌሎች ከሕክምና ጋር ተያያዥነት ያላቸው እና የሌላቸው መገልገያዎችን ለማሰባሰብ በመሥራት ላይ የሚገኘውን የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ ያቀርባል።
- የማክሮ-ኢኮኖሚ ንዑስ ኮሚቴው ኢኮኖሚው ዘርፉን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጮችን ለመቀየስ በልዩ ልዩ ዘርፍ ከተሠማሩት አበይት የኢንደስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትን ሲያካሂድ ቆይቷል። ይህንኑ ተከትሎም፣ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የሚከተሉት እርምጃዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡-
-
- የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የገቢ ዕቃዎች እና ግብአቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ይደረጋል።
- የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት አስጠብቆ የመቀጠል እና ባንኮች በ<ኮቪድ-19> ቫይረስ ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታ እና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊየን ብር ለግል ባንኮች ይሰጣል።
- የውጪ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው እና የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ዕቃዎችን እና ግብዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ አስመጪዎች ባንኮች ቅድሚያ በመስጠት እንዲያስተናግዱ ይደረጋል።
- በፋይናንስ አገልግሎት የተነሳ ገጽ ለገጽ መገናኘት እና የብር ንክኪን ለመቀነስ እንዲቻል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሞባይል አማካኝነት የሚደረግ ክፍያ እና ገንዘብ የማስተላለፍ ጣሪያውን ከፍ ያደርጋል።
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለውጭ ገበያ በሚቀርብ አበባ ላይ የጣለው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ገደብ በጊዜያዊነት እንዲነሳ ተደርጓል። ኩባንያዎች የተሻለ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ የገቢዎች ሚኒስቴር የተጨማሪ እሴት ታክስ አመላለስ ሂደቱን በተለየ መልኩ እንዲያፋጥን ይደረጋል።
- የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የሸቀጦች እጥረት እና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር በንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ምንጭ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
March 28, 2020 at 3:02 pm #13999AnonymousInactiveየኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቋቋመው “ሰው ነኝ ሌሎችንም እረዳለሁ” የተባለው ኮሚቴ፣ በመንግሥት የተቋቋመው የአማካሪ ምክር ቤት እና ኢትዮጵያ ውስጥ በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ያሉበት ሁኔታ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ግለሰቦች “ሰው ነኝ ሌሎችንም እረዳለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚሠራ ኮሚቴ አቋቋሙ። ኮሚቴው መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የግንዛቤ ማስጨበጥና ሌሎች የእርዳታ ማሰባሰብ ሥራዎች ላይ እንደሚሠራ ነው ያስታወቀው።
ተነሳሽነቱን ወስዶ ኮሚቴውን ያዋቀሩት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ኦባንግ ሜቶ “ኮሮናቫይረስ ዘር፣ ቀለምና ሀይማኖት ሳይለይ የሰው ልጅን በስፋት እያጠቃ ይገኛል” ብለዋል።
ኮሮናቫይረስ የተከሰተባቸው አገሮች በራሳቸው መንገድ ችግሩን ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስታውሰው፥ ”እኛ ኢትዮጵያውያን የሌሎችን እርዳታ ሳንጠብቅ ስርጭቱን መግታት እንችላለን” ብለዋል አቶ ኦባንግ። “ይህ እውን እንዲሆን ግን ራሳችንን በመጠበቅ አንድ ሆነን መቆም ይገባል” በማለት ጨምረው አስገንዝበዋል።
ከአካለዊ ንክኪ ርቀን በመንፈስና ተግባር አንድ ሆነን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መግታት ይገባናል ሲሉ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ የኮሚቴው አባላትም ተናግረዋል።
ሙዚቀኛ ዘለቀ ገሰሰ፥ ወጣቶችን ኮሮና አይዝም የተባለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ማሰተካከልን እና ሕብረተሰቡ ሊያውቃቸው የሚገቡ ትክክለኛ መረጃዎች በኪነ-ጥበብ ለሕዝቡ ለማድረሰ እንደሚሠራ አሰታውቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጤና ሚኒስቴር የሚመራውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ለማጎልበትና ለማፍጠን በጤና ሙያ ማኅበራት የተመሠረተው የአማካሪ ምክር ቤት ሥራ ጀምሯል። ውጤታማ ሥራ ለመሥራትም በስድስት ግብረ ኃይሎች የተዋቀረ ሲሆን እነሱም፦
- ማኅበረሰቡን ስለ በሽታው መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች በሳይንሳዊ ዘዴ ማስተማርና ማንቃት፣
- ጤና ተቋማት የባለሙያውንና የታካሚውን ደኅንነት በጠበቀ መንገድ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ማዘጋጀት፣
- የሕክምና መሣሪያዎች መድኃኒቶችና ግባቶች አቅርቦት እንዲሻሻል ማድረግ፣
- የወረርሽኝ ስርጭት ቅኝትና በሽታው ከያዛቸው ሰዎች ጋር የተገናኙ ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት፣
- የወረርሽኙንመጠነስርጭት፣ማንንእንዲሚያጠቃ፣የትበብዛትእንደሚከሰት፣በጊዜሂደትያለውንለውጥናለወረርሽኙአጋላጭሁኔታዎችንማጥናትናበመረጃማጠናቀር፣እና
- ከወረርሽኙጋርተያይዘውየሚመጡየአዕምሮጤናእናየሥነ-ልቦናእናማኅበራዊጫናዎችንመፍታትናቸው።
ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሰጠው ወቅታዊ መግለጫ፥ ማንኛውም ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ መንገደኛ በሆቴል ውስጥ ለ14 ቀናት ተለይቶ እንዲቆይ በተወሰነው መሠረት እስካሁን ስድስት መቶ ሰላሳ ስድስት (636) መንገደኞች ወደ ሀገራችን የገቡ ሲሆን፥ በተመረጡ አስር ሆቴሎች ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ።
መንገደኞቹ ባሉባቸው ሁሉም ሆቴሎች የጤና ባለሙያዎችን በመመደብ የጤና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።
በሌላ በኩል ከላይ የተገለፀው ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስምንት መቶ ሰባ ሶስት (873) ሰዎች በቤታቸው ሆነው በስልክ ለ14 ቀን በጤና ባለሙያዎች የጤና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል። ከዘሁ ጋር በተያያዘ ለ14 ቀናት ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው የበሽታው ምልክት ያልታየባቸው ሁለት ሺ ዘጠና (2,090) ሰዎች ክትትላቸው እንዲረቋጥ ተደርጓል።
ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ የኮሮናቫይረስ በሽታ ምልክት ያሳዩ ሰባ ዘጠኝ (79) ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ሁሉም ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል።
በሀገራችን እስካሁን አሥራ ስድስት (16) ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው በላቦራቶሪ ምርመራ መረጋገጡ ኢንስቲትዩቱ እና የጤና ሚኒስቴር በመግለጫዎቻቸው ማሳወቃቸውን ተዘግቧል። ከእነዚህ አሥራ ስድስት (16) ታማሚዎች መካከል ሁለቱ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን አሥራ አራት (14) ታማሚዎች በለይቶ ሕክምና መስጫ ማዕከል የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ። የኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸውና የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ከሚገኙ ታማሚዎች ውስጥ አንድ (1) ታማሚ በድጋሚ በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ መሆናቸው የተረጋገጠ ቢሆንም ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት ተጨማሪ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው የሚቆዩ ይሆናል።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት/ የጤና ሚኒስቴር/ አኢጋን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
April 3, 2020 at 3:22 am #14054AnonymousInactiveየግብርና ሚኒስቴር የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል የሚደርገውን ጥረት ለመደገፍ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ (የግብርና ሚኒስቴር) – የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችል ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።
በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው የዓለማችን ሀገራት በፍጥነት እየተሰፋፋ ያለው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ የዓለም ስጋት ከሆነ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ሀገራትም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ይበጃል ያሉትን መፍትሄ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። በሽታው ወደ ሀገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የመከላከል ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ።
የግብርና ሚኒስቴርም ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ሀገራዊ ተልዕኮ ድርሻውን ለመወጣት በስሩ ያሉትን ተጠሪ ተቋማት በማስተባበር የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል ያስችል ዘንድ ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ማዕከል 1 ሚሊየን ብር እና የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራር አባላት የ1 ወር ሙሉ ደመወዝ 363,731 ብር በጠቅላላው 1,363,731 ብር ብሔራዊ የሀብት ማፈላለግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለሆኑት ለአምባሳደር ምስጋኑ አረጋ አስረክቧል።
ብሔራዊ የሀብት ማፈላለግ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እንደተናገሩት፥ በዜጎችና በሀገር ደህንነት ላይ ትልቅ ስጋት የደቀነው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት የድጋፍ አሰባሳብ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት የበኩላቸውን ድጋፍ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል። የግብርና ሚኒስቴር በስሩ የሚገኙትን ተጠሪ ተቋማት አመራር አባላት በማስተባበር የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ የመጀመሪያው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መሆኑንም አምባሳደሩ ገልፀዋል።
በመጨረሻም አምባሳደር ምስጋኑ ወረርሽኙ አስከፊ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ርብርብ ላይ የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ላበረከቱት የገንዘብ ድጋፍ በብሔራዊ የሀብት ማፈላለግ ኮሚቴው ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸው፥ ወደ ሀገራችን የገባውን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ለመከላከል እንዲያስችል የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ካበረከቱት የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ምርመራ ማዕከል የኮሮናቫይረስን ምርመራ ለመሥራት በተወሰነው መሠረት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀዋል።
ከግብርና ሚኒስቴር ዜና ሳንወጣ፥ ሚኒስቴሩ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታትና ለመከላከል የኬሚካል ርጭት ያካሄደ ሲሆን፤ የኮሮናቫይረስ (ኮቪዲ-19) ስርጭትን ለመግታትና ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል። በመሆኑም በዋናው መሥሪያ ቤት ግቢ የሚገኙ ቢሮዎችን፣ የደረጃ መወጣጫ ደጋፊ ብረቶች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የአጥር ግቢ በር፣ በአጠቃላይ ከሰው ጋር ንክኪ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚታሰቡ የግቢ ውስጥና ውጭ ቦታዎችን፣ የአጥር ብረቶችን፣ የመብራት ምሰሶዎችን፣ ወዘተ… መጋቢት 22 እና 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሠራተኛው ቢሮ ከመግባቱ በፊት እና በኋላ ተህዋስያንን በሚገል ኬሚካል /disinfectant/ ርጭት በማድረግ የሠራተኞችን ሕይወት ለሚታደግና የቫይረሱን ስርጭት የሚገታ ሥራ ሠርቷል።
ኮሮናቫይረስን (ኮቪዲ-19) ለመከላከል በግለሰብ ደረጃ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቢሮዎቻቸውን፣ ግቢያቸውንና አካባቢያቸውን ከቫይረሱ ነጻ ለማድረግ የተህዋስያን መከላከያ ኬሚካል መርጨት እንደሚገባቸውና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስተማሪያ ለማድረግ እየረጩ እንደሆነ በርጭቱ የተሳተፉ ሠራተኞች ተናግራዋል። ሌሎችም ሊተገብሩት የሚገባ በጎ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።
ምንጭ፦ የግብርና ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
April 7, 2020 at 4:55 pm #14103AnonymousInactiveየሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ (ሠ.ማ.ጉ.ሚ.) – ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ።
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር (ሠ.ማ.ጉ.ሚ.) ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ተጋላጭነት አላቸው ላላቸው አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።
በዚህም ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽና በስሩ ላሉት ብሔራዊ ማኅበራት ሁለት ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ብር፣ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር ሦስት መቶ ሺህ ብር እንዲሁም ለኢትዮጵያ አረጋውያን ብሔራዊ ማኅበር ስድስት መቶ ሀምሳ አንድ ሺህ አንድ መቶ አስራ ሰባት ብር ድጋፍ ተደርጓል።
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች እና ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አረጋውያን እንደሚገኙ ጠቁመው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነቱን በመወጣት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለኮሮና ቫይረስ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአቅም ግንባታ ማዕቀፍ ሲያደርግ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እንዲውል መወሰኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፥ ድጋፉ አዲስ አበባንና ክልሎችን ባቀፈ ሁኔታ የምግብ ፍጆታና የንፅህና መጠበቂያ እቃዎች አቅርቦት እንደሚሸፈንበት ተናግረዋል። በቀጣይም ከተለያዩ የልማት ድርጅቶችና የበጎ ፈቃድ ማኅበራት ጋር በመሆን ድጋፉ እንደሚቀጥል ዶ/ር ኤርጎጌ ተናግራዋል።
በዕለቱ ሌሎች የቁሳቁስ ድጋፎች የተደረጉ ሲሆን የአካል ጉተኞች የእንቅስቃሴ ችግርን ለመቅረፍ አሜሪካን አገር ከሚገኝ አጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ (Agape Mobility Ethiopia) ጋር በመተባበር ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት ወጪ 183 ዘመናዊ ዊልቸር (wheelchair) ርክክብ የተደረገ ሲሆን ፥ ድጋፉ በሱማሌ፣ ሀረርና ደቡብ ክልሎች ለሚገኙ የእንቅስቃሴ ችግር ላለባቸው አካል ጉዳተኞች የሚውል ይሆናል ተብሏል። በተጨማሪም በአፍሪኮም የቴክኖሎጂ ኩባንያ (AFRICOM Technologies Plc) እና ድርሻዬን ልወጣ የበጎ ፍቃደኞች የንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ ተደርጓል።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለወረርሽኙ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እንደሚጠበቅ የተናገሩት ማኅበራቱ ሚኒስቴር፥ መሥሪያ ቤቱ ላደረገው ድጋፍ ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።
እስከ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ በ አጠቃላይ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መካከል አንድ ግለሰብ በጽኑ ህሙማን ማቆያ ይገኛሉ። አራቱ ያገገሙ ሲሆን፤ ሁለቱ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ደግሞ ወደ ሀገራቸው ተሸኝተዋል።
ምንጭ፦ ሠ.ማ.ጉ.ሚ./ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
April 12, 2020 at 5:30 am #14161AnonymousInactiveየኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈፀሚያ ደንብ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል። በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው ረቂቅ አዋጅ ሚያዝያ 2 ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወቃል። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዋጁን ማስፈፀሚያ ደንብ አጠቃላይ ይዘት በሚመለከት ሚያዝያ 3 ቀን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 94 ንዑስ ቁጥር 4 መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብ ማውጣት እንዳለበት ይደነግጋል። በዚህም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን ማስፈፀሚያ ደንብ አጠቃላይ ዝርዝር በሚመለከት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል። ማስፈፀሚያ ደንቡ አጠቃላይ አራት ዋና ዋና ከፍሎች ያሉት ሲሆን ይሄውም ክልከላን የሚያስቀምጥ፣ ግደታዎችን የሚጥል፣ የአስፈፃሚ አካላትን ክንውን እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ክልከላን በሚመለከት ማንኛውም ሃይማኖታዊ ይሁን ፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ እድር፣ ደቦ፣ እቁብና ሌሎችም ከአራት (4) ሰው በላይ ስብሰባዎች ክልክል ናቸው። አራት ሰዎችም ቢሆኑ ሁለት የአዋቂ ሰው እርምጃ የጠበቀ መሆን እንዳለበት አቃቤ ህአቃቤ ሕጓ አብራርተዋል። ቀብርና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ሲኖሩ ግን እየታዩ ሊፈቀዱ የሚችሉበት አሠራር መኖሩን ጠቁመዋል። ታራሚዎች ከጠበቆቻቸው ጋር አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲገናኙ የሚፈቀድ ቢሆንም፥ ጥየቃ ለሚሄዱ ሰዎች የማይፈቀድ መሆኑ ተገልጿል።
በፖሊስ የተያዙ እስረኞችንም ስንቅ ከማቀበል በስተቀር መገናኘት የተከለከለ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል። በድንበር አካባቢ ከካርጎ፣ የደረቅና ፈሳሽ ጭነት አገልግሎቶች በስተቀር ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዝግ ተደርገዋል። የቤት ተከራዮች በራሳቸው ፍላጎት ካልወጡ በስተቀር ማስወጣትና ኪራይም አስገድዶ መቀበል/ ማስከፈል መጨመር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተከልክሏል። ሠራተኞችን መቀነስና የሥራ ቅጥር ውል ማቋረጥም መከልከሉን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል።
በዚህ ደንብ መሠረት ተማሪዎችና መምህራን በኦንላይን (online) ካልሆነ በአካል እንዲገናኙ አይፈቀድም። ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ የሕፃናትም ይሁን የሌሎች መጫወቻ ስፍራዎች እንዲሁም የእጅ መጨባበጥ ሰላምታ የተከለከለ ነው።
በትራንስፖርት ዘርፍም አገር አቋራጭ ካለው ወንበር ከ50 በመቶ በላይ ተሳፋሪ መጫን የተከለከለ መሆኑን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
ከኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ዜና ሳንወጣ፥ እስከዛሬ ሚያዝያ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ስዎች ቁጥር ሰባ አንድ (71) መድረሱን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም አስታውቋል። ከእነዚህ ተጠቂዎች መካከል ሦስቱ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ሀምሳ ስድስት (56) ታማሚዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ። ሁለት የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን፣ አስር (10) ሰዎች ደግሞ ከሕክምና በኋላ ከቫይረሱ ነፃ ሆነው አገግመዋል።
እስከዛሬ (ሚያዝያ 4 ቀን) ከሰዓት በኋላ ድረስ በዓለም ላይ በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ1.79 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከ109,200 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። በአጠቃላይ ቁጥራቸው 406,100 አካባቢ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ከኮቪድ-19 በሽታ ማገገማቸው ታውቋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
May 2, 2020 at 2:16 pm #14341AnonymousInactiveየኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ 111 የንጽህና መጠበቂያ አምራቾች ዘርፉን ተቀላቅለዋል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሀገሪቱ ከተከሰተ በኋላ ለ111 የንጽህና መጠበቂያ አምራቾች ፍቃድ መስጠቱን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን (የቀድሞው የኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ባለስልጣን (EFDA)) አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሄራን ገርባ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት፥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ በሕብረተሰቡ ዘንድ የንጽህና መጠበቂያ ቁሶች ፍላጎት ጨምሯል። በወቅቱ የፍላጎቱና የምርት መጠን ባለመመጣጠኑ በተለይም የሳኒታይዘር እና የአልኮል ምርት እጥረት አጋጥሞ ነበር።
ችግሩን ለመፍታት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በዘርፉ ከተሰማሩና ፍላጎት ካላቸው አምራቾች ጋር ውይይት ማካሄዱንም አስታውሰዋል። በዚህም አምራቾች ሳኒታይዘር እና አልኮል በስፋትና በጥራት እንዲያመርቱ የሚያስችል ስምምነት ተደርጎ ወደ ሥራ የገቡበት ሁኔታ መኖሩን ነው ዋና ዳይሬክተሯ የተናገሩት።
ባለስልጣኑም አምራቾቹ ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ ሳኒታይዘር እና አልኮል በስፋት እንዲያመርቱ ለማስቻል የሚያግዝ ጊዜያዊ መመሪያ አውጥቶ ተግባራዊ አድርጓል።
ዳይሬክተሯ እንዳሉት፥ መመሪያው አምራቹ ስለምርቱ ሁኔታና ጠቀሜታ የሚያቀርበው የቅድመ ተግባር ሀሳብ (proposal) በአጭር ጊዜ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችልና የፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱም ፈጣን እንዲሆን የሚያግዝ አሠራርን በውስጡ አካቶ የያዘ ነው። በዚህ መሠረት ዘርፉን በመቀላቀል የጥራትና የግብአት መስፈርቱን ላሟሉ 111 አምራች ፋብሪካዎች ወደምርት እንዲገቡ ፈቃድ መሰጠቱን ወ/ሮ ሄራን አስታውቀዋል።
“ፋብሪካዎቹ በአሁኑ ወቅት የሳኒታይዘር እና የአልኮል ምርቶቻቸውን በጥራትና በሚፈለገው መጠን በማምረት ለሕብረተሰቡ እያቀረቡ ይገኛሉም” ብለዋል ወ/ሮ ሄራን።
የምርቶቹን የጥራትና የደረጃ ሁኔታ ለመከታተልም በጊዜያዊነት የተዘጋጀው መመሪያ የቅኝት ሥራን የሚያከናውኑ አካላት ቅንጅታዊ አሠራርን ዝርዝር ሁኔታ ጭምር የሚዳስስ ነው። የቅኝት ሥራውን ከባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ሙያተኞች በተጨማሪ ከአዲስ አበባ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ ባለስልጣን እና ከጸጥታ አካላት የተወጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የሚሠሩበት ሁኔታም ተፈጥሯል።
ወ/ሮ ሄራን እንደገለጹት፥ የቅኝት ሥራው በገበያ ስፍራዎች፣ በሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ሱቆች፣ በሱፐር ማርኬቶችና በመድኃኒት ቤቶች የሚከናወን ነው። በተከናወነው የቅኝት ሥራም አጠራጣሪና ከደረጃ በታች የሆኑ፣ እውቅናና የንግድ ፈቃድ የሌላቸው እንዲሁም የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ ምርቶችን በፍተሻ መያዝ ተችሏል።
“በዚህም ባለስልጣኑ እነዚህን ምርቶች ከገበያ የመሰብሰብና የማስወገድ ሥራ እና አቅራቢዎቹንም ተጠያቂ የማድረግ ተግባር አከናውኗል” ይላሉ ወ/ሮ ሄራን። በቁጥጥር ሥራው እርምጃ ከተወሰደ በኋላ የተወሰኑ አምራቾች የምርት ጥራታቸውን በማሻሻል በአዲስ መልክ ወደ ምርት ለመግባት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
May 5, 2020 at 12:36 pm #14388AnonymousInactiveየኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከ220 በላይ የሕክምና መስጫ እና ለይቶ ማቆያ ማዕከላት ዝግጁ ተደርገዋል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ሰዎችን ሊይዙ የሚችሉ ከ220 በላይ የሕክምናና የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል።
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 የተቋማት ዝግጁነት ክፍል አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ መሠለ እንደገለጹት፥ የኮሮና ቫይረስ በቻይና ዉሃን ከተማ (Wuhan) ከተከሰተ ጀምሮ በሀገራችንም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል። ከዚህም ውስጥ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸውን ሰዎች የሕክምና መስጫ ማዕከል (treatment centers)፣ የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤታቸው እስኪታወቅ ተለይተው የሚቆዩበት (isolation centers) እንዲሁም ከመጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ማንኛውም ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ግለሰብ ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ መግባት እንዳለበት በተላለፈው ውሳኔ መሠረት የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን (quarantine centers) መለየትና ዝግጁ ማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ናቸው።
በዚህም መሠረት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባና በክልሎች ሙሉ በሙሉ ለኮሮና ቫይረስ ህሙማን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ጨምሮ ከ10,000 በላይ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ከ40 በላይ ማዕከሎች (treatment centers) ዝግጁ የሆኑ ሲሆን ከ15,000 በላይ ሰዎችን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ከ100 የሚበልጡ የለይቶ ማቆያዎች (isolation centers) እንዲሁም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከ80 በላይ የለይቶ ማቆያዎች (quarantine center) ተዘጋጅተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የኮቪድ-19 ብሔራዊ የድንገተኛ ማዕከል የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር የውሀ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን (sanitation and hygiene) ክፍል አስተባባሪ ወ/ሮ ኢክራም ሬድዋን እንደተናገሩት፥ ለኮሮና ቫይረስ (የኮቪድ-19) በሽታ በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት ያሉ የውሀ ሳኒቴሽንና ሀይጅን እንዲሁም ኢንፌክሽንን ከመከላከልንና መቆጣጠር አንፃር ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ለመሙላት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህም ከውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከውሀ ልማት ኮሚሽን እና ከአጋር ድርጅቶች በተደረጉ ድጋፎች ሲሆን፥ የውሀ መቆራረጥና እጥረት ያለባቸውን ተቋማት ክፍተት መሙላት፤ የውሀ አቅርቦት መቆራረጥን ለመቀነስ የውሀ ታንከሮችና ፓምፖችን መግጠም፣ ውሀን በከባድ መኪና (truck) ማቅረብ እንዲሁም የእጅ መታጠቢያ እጥረት ባለባቸው የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት ከእጅ ንክኪ የጸዱ በእግር መከፈት የሚችሉ ተንቀሳቃሽ የእጅ መታጠቢያዎች እንዲተከሉ ተደርጓል።
በተጨማሪም ለሁሉም ለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ እና በአዲስ አበባ ለሚገኙ የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት የፀረ-ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ባለሙያዎች ተመድበዋል። ለነዚህ ባለሙያዎችም የኮቪድ-19 የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፥ ባለሙያዎቹም በአጠቃላይ የሚከናወኑ ተግባራት ኢንፌክሽንን ከመከላከልና መቆጣጠር አንጻር በአግባቡ እየተካሄዱ መሆናቸውን በየዕለቱ ይከታላሉ ብለዋል።
በአጠቃላይ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚሠሩ ሥራዎች ባሻገር ሕብረተሰቡ የሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ለበሽታው ያለመስፋፋት ወሳኝ በመሆናቸው ሕብረተሰቡ ሳይዘናጋ የሚተላለፉ መልዕክቶችን እና መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 በመደወል ወይም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኢሜል አድራሻ ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ ኢንስቲትዩቱ ይጠይቃል።
May 13, 2020 at 2:28 am #14479AnonymousInactiveየኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለ18 ወራት የሚበቃ የመድኃኒት ክምችት መኖሩን ገለጸ
ለለይቶ ማቆያዎች የሕክምና ቁሳቁሶች ተሟልቶ እየቀረበ እንደሚገኝ ተጠቁሟልአዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለ18 ወራት የሚበቃ የመድኃኒት ክምችት ለመያዝ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ። በፌደራልና በክልል ደረጃ ለሚገኙ ለይቶ ማቆያዎች የሕክምና ቁሳቁሶች ተሟልቶ እየቀረበላቸው እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
በኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ አድና በሬ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፥ ኤጀንሲው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በሀገሪቱ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከወዲሁ ለ18 ወራት የሚበቃ የመድኃኒት ክምችት ለመያዝ እየሠራ ይገኛል።
እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ፤ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የመድኃኒት አቅርቦት ከውጭ የሚገባ በመሆኑ በሀገሪቱ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት አንዴ ከተከሰተ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለመመለስ ጊዜ ስለሚወስድ ችግሩን በፍጥነት ለመቅረፍ አዳጋች ያደርገዋል። ኤጀንሲው ችግሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቫይረሱ ወደ ሀገሪቱ ቢገባ በመድኃኒት አቅርቦቱ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽኖ ታሳቢ በማድረግ፥ ኮሚቴ ተቋቁሞ በመጋዘን ምን ያህል የመድኃኒት ክምችት እንዳለ፤ ከወርሃዊ ፍጆታው አንጻር በመጋዘንና በመጓጓዝ ላይ ያለው መድኃኒት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚበቃ፣ መጠናቸውን፣ የትኛው መድኃኒት ቀድሞ መግባት እንዳለበት፣ እስከ መቼ መድኃኒቶቹ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ቀደም ብሎ ጥናት ተደርጓል።
ወ/ሮ አድና ኮሚቴው ቫይረሱ በሀገሪቱ ከተከሰተ በኋላም ከተመላላሽ ታካሚዎች ባሻገር በተለይ ተከታታይ መድኃኒት የሚወስዱ ወገኖች እጥረት እንዳያጋጥማቸው፣ በመጋዘንና በመጓጓዝ ላይ ያለው መድኃኒት ለነዚህ ወገኖች አቅርቦት ሳይቆራረጥ ምን ያህል ጊዜ ሊያስኬድ ይችላል የሚለው ላይም በድጋሚ ጥናት ማካሄዱን ተናግረዋል።
ኤጀንሲው በጥናቱ መሠረት የመድኃኒቶቹን የአገልግሎት ዕድሜ ታሳቢ በማድረግ ለ18 ወራት የሚበቃ የመድኃኒት ክምችት ለመያዝ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ በተለይ የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የአስም፣ የልብ ህመምተኞች በተከታታይ ከሚወስዷቸው መድኃኒቶች በተጨማሪ ኤችአይቪ (HIV) በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች የሚወስዷቸው የፕሮግራም መድኃኒቶችን ለ18 ወራት የሚበቃ ክምችት ለመያዝ ታሳቢ ተደርጎ ግዢ እንዲፈጸም፣ በመጓጓዝ ላይ ያሉት በወቅቱ እንዲገቡና በመጋዘን ተከማችተው ያሉ መድኃኒቶችም በወቅቱ ወደ ጤና ተቋማቱ ተልከው ለህመምተኞች እንዲደርስ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ወ/ሮ አድና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በጤና ቀውስነቱ እስከመቼ ድረስ እንደሚቀጥል ስለማይታወቅ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረቱ ተከስቶ ችግር ውስጥ ከመገባቱ በፊት የመድኃኒት ክምችቱን ማሳደግ ላይ መሠራቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ጠቁመው፥ ቀደም ሲል በውል የታሰሩ የመድኃኒት ግዢዎች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ዋጋ ከመጨመር ባለፈ በውሉ መሠረት ድርጅቶቹ ለማቅረብ እያመነቱ በመሆኑ በተፈለገው መጠን መድኃኒቶቹን ለማከማቸት እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ የሕክምና ግብዓቶችን እያሠራጨ እንደሚገኝ ዳይሬክተሯ ገልጸው፥ ኤጀንሲው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት በፌዴራልና በክልል ደረጃ ለሚገኙ ለይቶ ማቆያዎች ሙሉ ለሙሉ የሕክምና ቁሳቁሶችን አሟልቶ እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
May 13, 2020 at 11:28 pm #14488AnonymousInactiveየፖሊስ የዘፈቀደ እስር በአስቸኳይ ሊቆም እና የታሰሩትም ሊለቀቁ ይገባል
Police Should Immediately Stop Arbitrary Arrests and Release those Detainedአዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን) – [በትላንትናው ዕለት (ግንቦት 5 ቀን 2012 ዓ.ም.)] በአዲስ አበባ ከተማ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የተገኙ ሰዎች በፖሊስ እየታሰሩ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ በሚዲያዎች የወጡ ዘገባዎችንና ለኮሚሽኑ የቀረቡ አቤቱታዎችን ተከትሎ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሚከተለውን ብለዋል።
“የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል አስፈላጊ የጤና መመርያ ሲሆን ሕብረተሰቡም ሊከተለው የሚገባ ነው። በእርግጥም የአስቸኳይ ጊዜ ደንቡ ማንኛውም ሰው እንደ ገበያ ቦታዎች፥ ሱቆች ፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ባሉ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች እና በሌሎች ሕዝብ በሚበዛባቸውና የአካል መራራቅን መጠበቅ በማይቻልባቸው አካባቢዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል። ከዚህ ውጪ ግን በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የተገኙ ሰዎች ላይ ሁሉ የሚደረግ የዘፈቀደ እስር ከሕግ ውጭ ከመሆኑም በላይ ለነገሩ ሁኔታ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ እና የታለመለትን አላማ የሚቃረን በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፤ በዚህ ሁኔታ የታሰሩ ሰዎችም በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል።”
[የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በመጋቢት ወር 20212 ዓ.ም. የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ለአምስት ወራት ተግባራዊ እየሆነ እንደሚቆይ ተነግሯል።]
ADDIS ABABA (Ethiopian Human Rights Commission) – Responding to media reports and complaints of arrests by police in the city of Addis Ababa on 13th May 2020 for not wearing face masks, Chief Commissioner of the Ethiopian Human Rights Commission (EHRC) Dr. Daniel Bekele said:
“Covering nose and mouth are recommended health measures to prevent the spread of COVID-19 and the public needs to follow these critical health directives. Indeed, the Emergency Regulations impose an obligation to wear face covering in public service areas such as markets, shops, transport services or other public spaces with large number of people where social distancing is not possible. Otherwise, arbitrary arrest of people on the streets is outside the regulation, disproportionate and counter-productive measure which should stop immediately and all those detained should be released immediately.”
[In the first week of April 2020, Ethiopia has declared a state of emergency in the country to help curb the spread of the coronavirus pandemic. The state of emergency is reported to stay in action for five months from its declaration.]
May 28, 2020 at 2:17 am #14632AnonymousInactiveኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም ሰው ከቤት ውጪ ሲሆን የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ (ጭንብል) እንዲያደርግ የግዴታ መመሪያ ተሰጠ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – በኢትዮጵያ ማንኛውም ሰው ከቤት ውጪ በሚሆንበት ጊዜ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ (ጭንብል) ማድረግ ግዴታ ሆነ። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በትላንትናው ዕለት (ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ.ም.) ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ መግለጫው ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ (ጭንብል) ከቤት ውጪ በሁሉም ቦታዎች ማድረግ ግዴታ እንደሆነ ያትታል። ሙሉ ጋዜጣዊ መግለጫው እንደሚከተለው ይነበባል።
ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ በመንግሥትና በባለድርሻ አካላት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ትዕዛዞች፣ ክልከላዎችና መልዕክቶች እየተላለፉ ነዉ። እነዚህን መልዕክቶችና ትእዛዞች ሰምቶ ለራስ በመፈጸምና ሌሎችን እንዲፈፅሙት በማድረግ በኩል በአንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሻሉ ሁኔታዎች ቢኖሩም ነገር ግን በርካታ በሚባለዉ ሕብረተሰቡ ዘንድ የመዘናጋት፣ የቸልተኝነትና በሽታዉን አስመልክቶ የሚሰጡ ትእዛዛቶች ወደ ጎን በመተዉ የሚሰጡ መግለጫዎችን የመላመድና ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታዎች እየተስተዋለ ይገኛል።
በቅርቡ በመንግሥት ተቋማት፣ በልማት ድርጅቶችና በግል ተቋማት ወሰጥ ያደረግነዉ ምልከታ ከቅደመ ጥንቃቄ ጋር በተያያዘ የመዘናጋት፣ ትኩረት ያለመሰጠት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል። ማኅበረሰባችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተለይም በግብይት ቦታዎችና በትራንስፖርት አገልግሎት መሰጫ አካባቢ እያሳየ ያለዉ መዘናጋትና ሕጎቹን ያለማክበር ጉዳይ አሳሳቢ ነዉ።
ይህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችን በተገኘበት እና የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ሰሞን የነበሩ ጥንቃቄዎች ጋር ሲነጻጸር እየቀነሰ መዘናጋት እየጨመረ ሲሆን፥ በተቃራኒዉ አሁንም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ እጅጉን አሳሳቢና ዋጋ የሚያስከፍል ጉዳይ እየሆነ ይገኛል።
መንግሥት በሽታዉን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመቀነስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዉጆ፣ ደንብና መመሪያዎችን በማዉጣት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ከዚህ ቀደም የወጡ መመሪያ ቁጥር 1/2012 እና መመሪያ ቁጥር 2/2012 ማሻሻያዎችን የያዘ መመሪያ ቁጥር 4/2012ን አፅድቆ ሥራ ላይ እንዲዉል አቅጣጫ ሰጥቷል። በዚሁ መሠረትም በመመሪያ ቁጥር 4 በኮድ 2 የቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረዉ ከፊል የእንቅስቃሴ ክልከላ፣ የማሰክ አጠቃቀም፣ በአገር አቋራጭ የሕዝብ ተሸከርካሪዎች ላይ እንዲሆም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች መግቢያና መዉጫ ስዓት ላይ ማሻሻያ አድርጓል።
የኮድ ሁለት የቤት ተሸከርካሪዎች ላይ መጣል ሚገባው የትራንስፖርት ሚኒስቴር በኩል የተደረገውን ጥናት መነሻ በማድረግ በከፊል በመገደብ ግለሰቦች ቤታቸዉ እንዲዉሉ በማድረግ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታሳቢ ተድርጎ በሙሉና በጎዶሎ መለያ ቁጥር ከፊል እገዳ ተጥሎ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ሆኖም የኮድ 2 ተሸከርካሪ ባለቤቶች በታሰበዉ መልኩ ቤታቸዉ ከመዋል ይልቅ የሕዝብ ትራንስፖርት በመጠቀም እና ታርጋዎችን እየቀያየሩ የመጠቀም ሁኔታ መታየቱ እንዲሁም ተራቸዉ ባልሆነ ቀን ቤታቸዉ ከመዋል ይልቅ በሰፊዉ የመንቀሳቀስ ሁኔታ የተስተዋለ መሆኑ ክልከላዉን መልክ መቀየር አሰፈላጊ ሆኗል። በመሆኑም በአጠቃላይ በኮድ ሁለት የቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረዉ ክልከላ ተነሰቶ አጠቃላይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ለመገደብ የሚያስችል አማራጭ ክልከላ እንድተገበር የሚኒስትሮች ኮሚቴ ወስኗል። የእንቅስቃሴ ገደብ መቀነሻ አሠራሮች አንዱ የሆነዉ በሀገር አቋራጭ ተሸከሪካሪዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ነው።
የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ለመገደብ አሰተዋጽኦ እንደሚያደረግ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የተደረገው ጥናት ያመላክታል። በዚሁ መሠረት አገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች መደበኛ የወንበር አቅማቸዉ ከ45 (አርባ አምስት) ሰዉ በላይ የሆነ ተሸከርካሪዎች የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ከመደበኛ ዋጋዉ 75% እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን መደበኛ የወንበር ቁጥራቸዉ እስከ (45) አርባ አምስት ሰዉ የሆኑ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ደግሞ 100% መሆኑ ተወሰኗል።
በተያያዘ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በተሻሻለዉ መመሪያ መሠረት የማስክ አጠቃቀምን አስመልክቶ ከቤት ዉጭ በማንኛዉም ቦታ የአፍ እና አፈንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግን ግዴታ እንዲሆን ወስኗል። የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በፋብሪካዎች የተሠራ ወይም ባህላዊ ጨርቅ ሊሆን ይችላል። ይህን ግዴታ በማሰፈጸም ረገድ የጸጥታ መዋቅሩ ኃላፊነት እንዳለበት ተወሰኗል።
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ መግቢያ ስዓት 1፡30 እንዲሆን የተቀመጠ ሲሆን መዉጫ ስዓቱም 9፡30 እንዲሆን ተደርጎ ተሸጋሽጓል። ይህም የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ ነው።
በአጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሁሉም ሕብረተሰብ ኃላፊነትና ግዴታ ያለበት በመሆኑ የሚታዩ መዘናጋቶችን እና ችላ ባይነትን በመቅረፍ ሁላችንም ህግና ሥርዓቱን ማክበር ግዴታ እንደሆነ በመገንዘብ መላዉ የሀገራችን ሕዝብ እራሱ፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሚያስከትለው ጉዳት ለአፍታም ሳይዘናጋ ለመጠበቅ ርብርብ እንዲያደረግ ጥሪያችንን እናቀረባለን።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያJune 4, 2020 at 12:26 am #14696SemonegnaKeymasterየኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከ220 በላይ የሕክምና መስጫ እና ለይቶ ማቆያ ማዕከላት ዝግጁ ተደርገዋል ― የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት) – በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ሰዎችን ሊይዙ የሚችሉ ከ220 በላይ የሕክምናና የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል።
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 የተቋማት ዝግጁነት ክፍል አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ መሠለ እንደገለጹት፥ የኮሮና ቫይረስ በቻይና ዉሃን ከተማ (Wuhan) ከተከሰተ ጀምሮ በሀገራችንም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል። ከዚህም ውስጥ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸውን ሰዎች የሕክምና መስጫ ማዕከል (treatment centers)፣ የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤታቸው እስኪታወቅ ተለይተው የሚቆዩበት (isolation centers) እንዲሁም ከመጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ማንኛውም ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ግለሰብ ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ መግባት እንዳለበት በተላለፈው ውሳኔ መሠረት የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን (quarantine centers) መለየትና ዝግጁ ማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ናቸው።
በዚህም መሠረት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባና በክልሎች ሙሉ በሙሉ ለኮሮና ቫይረስ ህሙማን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ጨምሮ ከ10,000 በላይ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ከ40 በላይ ማዕከሎች (treatment centers) ዝግጁ የሆኑ ሲሆን ከ15,000 በላይ ሰዎችን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ከ100 የሚበልጡ የለይቶ ማቆያዎች (isolation centers) እንዲሁም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከ80 በላይ የለይቶ ማቆያዎች (quarantine center) ተዘጋጅተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ብሔራዊ የድንገተኛ ማዕከል የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር የውሀ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን (WASH) ክፍል አስተባባሪ ወ/ሮ ኢክረም ሬድዋን እንደተናገሩት፥ ለኮሮና ቫይረስ (የኮቪድ-19) በሽታ በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት ያሉ የውሀ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን (WASH) እንዲሁም ኢንፌክሽንን ከመከላከልንና መቆጣጠር አንፃር ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ለመሙላት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህም ከውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከውሀ ልማት ኮሚሽን እና ከአጋር ድርጅቶች በተደረጉ ድጋፎች ሲሆን የውሀ መቆራረጥና እጥረት ያለባቸውን ተቋማት ክፍተት መሙላት፤ የውሀ አቅርቦት መቆራረጥን ለመቀነስ የውሀ ታንከሮችና ፓምፖችን መግጠም፣ ውሀን በትራክ ማቅረብ እንዲሁም የእጅ መታጠቢያ እጥረት ባለባቸው የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት ከእጅ ንክኪ የጸዱ በእግር መከፈት የሚችሉ ተንቀሳቃሽ የእጅ መታጠቢያዎች እንዲተከሉ ተደርጓል።
በተጨማሪም ለሁሉም ለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ እና በአዲስ አበባ ለሚገኙ የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት የፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ባለሙያዎች ተመድበዋል። ለነዚህ ባለሙያዎችም የኮቪድ-19 የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ባለሙያዎቹም በአጠቃላይ የሚከናወኑ ተግባራት ኢንፌክሽንን ከመከላከልና መቆጣጠር አንጻር በአግባቡ እየተካሄዱ መሆናቸውን በየዕለቱ ይከታላሉ ብለዋል።
በአጠቃላይ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚሰሩ ሥራዎች ባሻገር ህብረተሰቡ የሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ለበሽታው ያለመስፋፋት ወሳኝ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ የሚተላለፉ መልዕክቶችን እና መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 በመደወል ወይም በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኢሜል አድራሻ ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
June 18, 2020 at 12:00 am #14832SemonegnaKeymasterወሎ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ድጋፍ የተቋቋመው የባቲ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ተመረቀ
(ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – ከአፋር ክልልና ከጅቡቲ የሚመጡ መንገደኞችን ለይቶ በማቆየት የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል በባቲ ወረዳ የተቋቋመው የለይቶ ማቆያ ማዕከል (quarantine center) ተመርቋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ድጋፍ የተቋቋመው የባቲ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ከሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። ማዕከሉን የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የኦሮሚያ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር፣ የባቲ ወረዳና ከተማ አመራሮች፣ በጎ ፍቃደኞችና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ ተመርቋል።
የቅኝት አምባ፣ የወሎየነት ተምሳሌትና የንግድ የመተላለፊያ አውድ ባቲ በታሪክ አጋጣሚ ከጅቡቲ አፋርን አቋርጠው በሚመጡ መንገደኞች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መተላለፊያ ኮሪደር ልትሆን ትችላለች የሚል ስጋት ተጭኖባታል። ከጅቡቲና አፋር ክልል እያቋረጡ የሚመጡ መንገደኞች ምርመራና ክትትል ሳይደርግላቸው ከመሀል ሀገር እንዳይገቡ ለማድረግ የለይቶ ማቆያ ማዕከል በባቲ ወረዳ ማቋቋም ተገቢ መሆኑን በጥናት ለይተናል ያሉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን ባቲ ወረዳን ማዳን ወሎን፣ ሰሜን ሸዋን በአጠቃላይ ከቫይረስ ስርጭት ሀገርን መታደግ ነው ብለዋል።
አያይዘውም ፕሬዚዳንቱ የኦሮሚያ ብሄረሰብ ዞንና የባቲ ወረዳ አስተዳደር ዩኒቨርሲቲው የሰጣቸውን የለይቶ ማቆያ ቁሳቁስ በቀናት ውስጥ ሁሉን ነገር አዘጋጅተው ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጋቸው የአመራሩ፣ የኮሚቴውና የማኅበረሰቡ የቅንጅት ውጤት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በደሴና ኮምቦልቻ ካቋቋመው የለይቶ ማቆያ ማዕከል እኩል ግብአቶችንና ቁሳቁሶችን በማሟላት ሦስተኛው ማዕከል እንዲሆን የቻልነውን ሁሉ ለማድረግ እንሞክራለን ያለት የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አማረ ምትኩ (ዶ/ር) ባቲ ወረዳ ከጅቡቲና አፋር የሚመጡ የከባድ መኪና ሹፌሮችና መንገደኞች መተላለፊያ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ የወሎ ሕዝብ አምባሳደርነቱን በተግባር እያስመሰከረ ነው ያሉት የኦሮሚያ ብሔረሰብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሀሰን ዩኒቨርሲቲው የዞናችንን አቅም መሠረት ያደረጉ የልማት ሥራዎችን ከመሥራትና ከማስተዋወቅ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለከሚሴና ባቲ ወረዳዎች የለይቶ ማቆያ ማዕከሎች ያደረገው ድጋፍ በታሪክ የትውልድ ቅብብሎሽ የሚዘከር ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የባቲ ወረዳ ለይቶ ማቆያ ማዕከልን ለማቋቋም ከ5 መቶ ሺ ብር በላይ የሚያወጡ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ በፊት ዘግቦ ነበር።
ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
August 2, 2020 at 1:41 am #15252SemonegnaKeymasterየኮቪድ-19 ስርጭት ማሻቀብን ተከትሎ ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ይጀመራል – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሃምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ስርጭት እጅግ ማሻቀብን ተከትሎ ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ይጀመራል። የጽሕፈት ቤቱ መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኮቪድ-19 ስርጭት ማሻቀቡ ይስተዋላል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰብሳቢነት ሥራውን የሚከውነው እና ቫይረሱን የመከላከል ሥራዎችን የሚያስተባብረው የሚኒስቴሮች ኮሚቴ፥ ሃምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በወቅታዊው ሁኔታ ላይ ተወያይቷል። የጤና ሚኒስቴር እና የትምህርት ሚኒስቴር ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን አካሄድ በተመለከተ ገለጻ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስቴር ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፥ እስከ አሁን [ሃምሌ 25 ቀን] ድረስ በኢትዮጵያ 17,500 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 70 በመቶው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው። በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል፣ 84 በመቶው ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ሲሆን፣ ከመመርመራቸው በፊት በቫይረሱ የመያዝ ምልክቶች አልታዩባቸውም። ይህም ምልክት ሳይታይባቸው ቫይረሱን የሚያስተላልፉ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ያመላክታል።
የትምህርት ሚኒስቴር የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ ትምህርት ሁኔታዎችን መረጃ አጠቃልሎ አቅርቧል። በዚህም መሠረት፥ ትምህርት ቤቶች [በ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን] ተመልሰው ከመከፈታቸው በፊት ሊተኮርባቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን አመላክተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የቫይረሱ የስርጭት መጠን መቀነስ ዋነኛው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምርመራ መጠንን ከፍ ማድረግ የወረርሽኙን አካሄድ ለመረዳት ወሳኝ ተግባር መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል። ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ እንዲካሄድም አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ADDIS ABABA (Semonegna) – The Office of Prime Minister – Ethiopia issued a press statement on 1st August 2020 stating that the country will carry out nationwide mass testing of COVID-19 for one month amid the surge of COVID-19 cases in the country, especially in recent weeks. The press statement reads as follows.
Over the past couple of weeks there has been a noticeable increase in the number of positive COVID-19 cases. The ministerial committee overseeing prevention activities and chaired by Prime Minister Abiy Ahmed, met this afternoon to discuss the current status, where the Ministers of Health and Education presented on the international and domestic trends of the pandemic.
According to Ministry of Health reports, there are currently 17,500 positive COVID-19 cases confirmed [in the country] as of date with 70% located in Addis Ababa. While 84% of positive cases are above the age of 50 years, 92% of positive cases showed no symptoms prior to testing, which indicates the presence of many silent spreaders.
The Minister for Education, combining data for primary, secondary and tertiary education, highlighted that a number of issues need to be factored before considering opening schools [for the coming academic year], with declining rate of cases being the key number one factor to enable an opening decision.
Prime Minister Abiy Ahmed emphasized the critical importance of increased testing to understand the trends better for effective decision making, and gave direction for the launch of a one-month nationwide mass testing.
August 3, 2020 at 2:22 am #15267AnonymousInactiveጤናችን በእጃችን! ― 1.2 ሚሊዮን ሰዎችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚከላከል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ – በግል የንግድ ዘርፍ፣ በመንግሥት እና በመንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል የተመሠረተው ጥምረት ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ከፍተኛ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ለሚቀጥሉት ቀጣይ ወራት የሚሠራ እና እስከ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ሊኖረው የሚችል <ጤናችን በእጃችን!> የተሰኘው ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ። ፕሮጀክቱ የውሃ፣ የሳሙና እና ሌሎች ተመሳሳይ ተግዳሮቶች እጥረት የሚያጋጥማችውን እና በጣም ጥቅጥቅ ያሉ የመኖሪያ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎችን ለማገዝ ብሎም ራሳቸውን ከወረርሽኙ እንዲጠብቁ የሚያስችል ይሆናል።
የፕሮጀክቱ አባል የሆኑት አምራች ኩባንያዎች በፕሮጀክቱ የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ውስጥ ትርፍን መሰርት ያላደረገ ሥራ ለመሥራት እና ሠራተኞቻቸውን በሥራ መደብ ላይ ለማቆየት ተስማምተዋል። ይህንን ለማካካስ ጥምረቱ ለተሳታፊ ኩባንያዎች ወሳኝ ከሆኑ ጥሬ ዕቃዎች እና ከማምረት ጋር ለተያያዙ የክንዋኔ ወጪዎችን የሚሸፍን ይሆናል።
ጤናችን በእጃችን! ፕሮጀክት በይፋ መጀመርን ተከትሎ ይህ አዲስ ጥምረት የፊት ጭምብሎችን እና ሳሙናዎችን የማምረት እና ማሠራጨት፣ የውሃ ገንዳዎችን መትከል፣ ብሎም የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ የግንዛቤ ለውጥ ፈጣሪ ትምህርቶችን ለ1.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ከፍተኛ ተጋላጭ ተበለው ለተለዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመከላከል ሥራን በሚያጠናክር መልኩ የሚያደርስ ይሆናል።
ዳልበርግ ግሩፕ (Dalberg Group) እና ሮሃ ግሩፕ (Roha Group) የተባሉ የግል ድርጅቶች ተነሳሽነት በመውሰድ በሀገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የወረርሽኝ የመከላከል ብሔራዊ ምላሽ ላይ ዘላቂ ተፅዕኖ ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የግል እና የመንግሥት ተቋማት በጋራ በማደራጀት ወደ ሥራ ገብተዋል። የፕሮጀክቱ የሙከራ ጊዜ የሚያስፈልገውን 1 ሚሊዮን ዶላር በሮሃ ግሩፕ በኩል የተገኘ ሲሆን፥ ቀሪው 5 ሚሊዮን ዶላር ከለጋሽ ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚሰበሰብ ይሆናል። ጥምረቱ የንፅህና መጠበቂያ የሆኑ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ማምረትና በጣም ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በማከፋፈል በዓይነቱ ለየት ያለ የንግድ ሥራ ሞዴሎችንም ማስተዋወቅ ችሏል።
መንግሥት በበኩሉ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ለፕሮጀክቱ የሚመረቱ ዕቃዎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስን ያነሳ ሲሆን፥ ዓላማውም የግል ተቋማት በኮቪድ-19 ወረርሽኝላይ ለሚደረገው የመከላከል ሥራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበርክቱ ለማስቻል ነው።
ፕሮጀክቱ እስካሁን ድረስ 15 የሚሆኑ ሀገር በቀል በማምረቻ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ አነጋግሯል። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሴቭ ዘ ችልድረን (Save the Children) በጎ አድራጊ ድርጅት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት ውስጥ ብሎክን መሠረት ያደረገ የማኅበረሰብ አደረጃጀት ኤጀንሲ በከተማው ውስጥ የሚገኙ 24,934 አካባቢዎችን በመለየት የሚገኙበትን ጊዜያዊ ሁኔታ መረጃ ሰብስቦ አዘጋጅቷል። በተጨማሪም በ10 ክፍለ ከተማዎች የሚገኙ 121 ወረዳዎች ውስጥ 1,357 የተደራጁ ማዕከላትን በመጠቀም የፊት ጭንብሎችን እና ሳሙናዎችን ለከፍተኛ ተጋላጭ ተበለው ለተለዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚያከፋፍል ይሆናል።
በተጨማሪም ሴቭ ዘ ችልድረን (Save the Children) ለጥምረቱ የቴክኒክ ድጋፍ፣ መመሪያ እና የሕብረተሰቡ ተሳትፎን በተመለከተ ድጋፍ ይሰጣል። የሚሠራጨው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፀደቁ የእጅ መታጠብ፣ የፊት ጭንብል መልበስ እና አካላዊ ርቀት መጠበቅን የሚመለከቱ መልዕክቶችን ያካትታል። የሠራተኞቹን እና የሕብረተሰብ አካላትን ጤና እና ደህንነት ለመጠበቅ ከ260 በላይ የክፍለ ከተማና የወረዳ ቡድን አመራሮችም ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።
በተያያዘም ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቱ የሙከራ ጊዜውን ጨርሶ ሙሉ በሙሉ ከመጀመሩ በፊት የፈንድ አስተዳደርና የሥራ ሂደት ለመቆጣጠር የፕሮጀክቱን ውጤታማነት ለመገምገም ከጥምረቱ ጋር አብሮ የሚሠራ ይሆናል።
“የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማኅበረሰባችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል የበኩላችንን ማድረግ በመቻላችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል። ጥምረቱን የተቀላቀሉና ኃላፊነታቸውን በመወጣት አዳዲስ መፍትሄዎችን በማምጣት ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ አብረውን እየሠሩ ያሉትን አጋሮቻችንን እናመሰግናለን” ብለው የጥምረቱ መሥራቾች ተናግረዋል።
አክለውም ይህ ጥምረት ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚያስፈልገውን ቁሳቁሶች ብሎም የባህሪ ለውጥ ትምህርት ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን፥ ሌሎችም በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች እና ተቋማት ይህን ጥምረት በመቀላቀል የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።
ፍሰሃ አለማየሁ የፍሪ ዞን ኢንተርናሽናል (Free Zone International) ዋና ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው “የጥምረቱ አባል በመሆናችን የማምረት ሥራችን ሳይስተጓጎል በ ሀ ገራችን ውስጥ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመከላከል እንቅስቃሴ እንድንደግፍ አስችሎናል” ብለው ተናግረዋል።
ጤናችን በእጃችን!
ጤናችን በእጃችን! በዳልበርግ ግሩፕ እና በሮሃ ግሩፕ የተመሰረት የግል እና የመንግሥት ተቋማትን አንድ ላይ የያዘ ጥምረት ነው። በሀገራችን የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ሥራ ላይ ለውጥ ለማምጣት ሁለቱ ኩባንያዎች የግሉ ሴክተር አቅምን እና ብቃቶችን ለማደራጀት ተነሳሽነት ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል።፡
ጥምረቱ ተጋላጭ የሆኑትን የሕብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ባሉበት ቦታ መፍትሄ ለማቅረብ የሚቻልበትን መንገድ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በከፍተኛ አደጋ ላይ ከሚገኙ ንዑስ ምድቦች በተጨማሪ የህብረተሰባችንን ኢኮኖሚያዊ ጤና ለማረጋገጥ አካል የሆኑት የንግድ ድርጅቶችም የዚህ ጥምረት ትኩረት ናቸው። ስለሆነም ጤናችን በእጃችን! የተሰኘው ፕሮጀክት ከፍተኛ አደጋ ተጋላጭ ማኅበረሰቦችን የሚረዱ አስፈላጊ የንፅህና እና የመከላከያ ምርቶችን በማምረት እና በማሠራጨት ረገድ ልዩ የንግድ ሥራ ሞዴል በማስተዋወቅ የንግድ ተቋማት ይህ አስጨናቂ ጊዜ የፈጠረውን የገበያ እጦት ለመቋቋም የሚያስችላቸው መንገዶችን በማዘጋጀት የንግድ ድርጅቶች ወጪያቸውን ለመሸፈን እና ሠራተኞቻቸውን ለማቆየት የሚያስችል ይሆናል። https://www.tenachinbejachin.org
[caption id="attachment_15265" align="aligncenter" width="600"] ጤናችን በእጃችን! (Tenachin Bejachin!) Initiative[/caption]
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.