Home › Forums › Semonegna Stories › የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ
Tagged: የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 19, 2019 at 2:19 am #12330SemonegnaKeymaster
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ባለፉት ሁለት ቀናት ሲያካሂድ በቆየው ስብሰባ አሁን የደረስንበትን የትግል ምዕራፍ እና በፓርቲው ውስጥ የሚስተዋሉ ጥንካሬዎችና ጉድለቶችን በጥልቀት በመገምገም የፓርቲው ውስጣዊ ክፍተቶችን ለመቅረፍና በቀጣይ ጊዜ የሚደረገውን ትግል ስኬታማ ለማድረግ የሚያግዙ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል።
ሰሞኑን የድርጅታችን ሊቀመንበር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማትን ማሸነፋቸውን ተከትሎ መላው የኦሮሞ ሕዝብና የአገራችን ሕዝቦች ያሳዩትን ድጋፍና የደስታ መግለጫ ፓርቲያችን በልዩ አድናቆት ይመለከተዋል። ይህ ዓለም አቀፍ ሽልማትም የድርጅቱ አመራርና የሕዝባችን የትግል ውጤት እንደሆነም ያምናል። በጋራ በምናስመዘግባቸው የድል ምዕራፎች በዚህ መልኩ የሚታዩ ድጋፎችና የደስታ መግለጫዎችም ለፓርቲው ቀጣይ የትግል አቅም እንዲሆን ይሠራል።
ትላንት እንደ ፓርቲ ታግለን ድል እያስመዘገብን ዛሬ የደረስነው ከኦሮሞ ሕዝብና ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመሆን ነው። አሁንም የኦሮሞ ሕዝብና የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ይዘን በድል እንደምንሻገር ጥርጥር የለንም። የፓርቲያችንን የትግል እርምጃዎች እየቆጠሩ የሚያኮርፉና ስጋት የሚገባቸው ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ ብዥታን የሚፈጥሩ መረጃዎችን በማሠራጨት ላይ ይገኛሉ። እኛ ደግሞ ባካበትነው የትግል ባህል ሕዝባችንን ይዘን የነሱን የውሸት ፕሮፖጋንዳና የማፍረስ ህልማቸውን የምናመክን መሆናችንን እንገልጻለን።
በዚሁ መሠረት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፉት ሁለት ቀናት ስብሰባው ባካሄደው ግምገማ ላይ ተመስርቶ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ኦዴፓ ሕዝብ ውስጥ ተወልዶ ያደገ የትግል ፓርቲ ነው። በትግል ጉዞው ውስጥ በሕዝቡ ጥያቄና ፍላጎት ላይ በመመስረት ራሱን በማየትና በመገንባት ዛሬ ላይ ደርሷል። ፓርቲው ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባው ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በየደረጃው ባለ መዋቅር ላይ የአመለካከት አንድነት ጉድለትን ከመሰረቱ በመቅረፍ የሕዝቡን ጥያቄ በተሟላ ሁኔታ እየመለሰ መሄድ አሁን የደረስንበት የትግል ምዕራፍ የሚፈልገው መሆኑ ላይ ስምምነት ተደርሷል።
እንደ ፓርቲና እንደ መንግስት የሚሰጥን ተልዕኮ በተቆርቋሪነትና በሕዝብ ወገንተኝነት መወጣትና በተጠያቂነት መንፈስ መንቀሳቀስን በተመለከተ ክፍተት እንዳለ ተመልክቷል። በመሆኑም ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ በአመለካከትና በተግባር አንድነት እንዲሁም በተጠያቂነት መንፈስ የሕዝባችንን ጥያቄና ፍላጎት መመለስ ወሳኝ መሆኑ ላይ ከመግባባት ተደርሷል። የውስጠ ፓርቲ የአመለካከትና የተግባር አንድነትን በማጠናከር እስካሁን ምላሽ የተሰጠባቸው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎችን እንደ መነሻ፣ምላሽ ያላገኙትን ደግሞ በተለየ ሁኔታ በመመልከት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቆጥረው ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚታገል አቅጣጫ አስቀምጧል።
ብዙ ብሄር ብሄረሰቦች፣ብዙ ቋንቋና ባህሎች በሚገኙበት አገር ውስጥ የፌዴራሊዝም ሥርዓት አማራጭ የሌለው ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት የብዝሃነትን ውበት በመንከባከብ የአገራችንና የሕዝባችን የጋራ ባህሎች መገንባትን የምናረጋግጥበት ወሳኝ መሳሪያ ነው። ስለሆነም የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ትክክለኛና እውነተኛ የብዝሃነት ፌዴራሊዝም ሥርዓትን በኢትዮጵያ ተግባራዊ በማድረግ የአገራችንን ሕዝቦች እኩልነትና ነጻነት ለማረጋገጥ የማያወላዳ አቋም እንዳለው በድጋሚ ያረጋግጣል።
ይሁን እንጂ ባለፉት ጊዜያት በአፈጻጸም የታዩ ተግባራት የፌዴራሊዝም ሥርዓትን የአስተዳደር ባህልና እሴትን የሚቃረኑ ብዙ ተግባራት ሲፈጸሙ ቆይተዋል። በግምገማ መድረካችን እንዳየነው ባለፉት ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሁሉንም ሕዝቦች በፍትሃዊነት እንደማያሳትፍ እውነተኛ ዴሞክራሲ በውስጡ ያልተረጋገጠ እንደሆነ ያሳያሉ።
ከዚህም ሌላ የሕዝቡ ጥቅሞችና ፍላጎቶች የመንግስትን ስልጣን እጃቸው ባስገቡት ጥቂቶች ሲጋጥ እንደነበረ ይታወቃል። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እነዚህ ድክመቶች ታርመው እውነተኛ የብዝሃነት ፌዴራሊዝም ሥርዓት መሬት እንዲይዝ የጀመረውን ትግል በማስቀጠል ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በነጻነት፣ በእኩልነት፣ በወንድማማችነትና በብልፅግና የሚኖሩባትን አገር ለመገንባት ጠንክሮ እንደሚሠራ ይገልጻል።
በሌላ በኩል ትላንት ትክክለኛው የፌዴራሊዝም ሥርዓት መሬት እንዳይይዝ ሕዝቡን የማይወክሉ ጥቂት ቡድኖች በያዙት የመንግስት ስልጣን ሕገመንግስቱንና የፌዴራሊዝም ስርዓቱን ሲጥሱ የነበሩ ቡድኖች ዛሬ ራሳቸውን ለሕገመንገስቱ የቆሙና የፌዴራሊዝም ሥርዓት ጠበቃ እንደሆኑ አድርገው በሕዝቡ ውስጥ ብዥታን ለመፍጠር የሚነዙት የውሸት ፕሮፖጋንዳ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ኦዴፓ ለማስገንዘብ ይወዳል።
የኢህአዴግ ዉስጣዊ ሪፎርም የፓርቲዉን የትግል አካሄድ፤ የህብረተሰቡን ጥያቄና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነዉ። ይህም በሐዋሳ ከተማ በተደረገዉ የፓርቲዉ 11ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ በምሁራን ተጠንቶ እንዲቀርብና ዉሳኔ እንዲያገኝ አቅጣጫ የተሰጠበት ነዉ። የህዝቡ ጥያቄና የፓርቲዉ ዉስጣዊ ዉሳኔዎች በጥቅሉ ሲታይ ፓርቲዉ በአደረጃጀቱ ፤ በዴሞክራሲዊነቱና፤ በአሳታፊነቱ እራሱን እንዲያይ የተሻለ ዕድል የፈጠረ ነዉ። የተደረገዉ ጥናትም የኢህአዴግ አመሠራረት ዴሞክራሲያዊና አቃፊ ያልሆነ፤ የሀገር ግንባታ አቅምን የሚሸረሽር ፣ ገሚሱን የሀገሪቱ ህዝቦች ወደ ጎን በመተዉ በጥቂት ቡድኖች የሚወሰን መሆኑ ተለይቷል።
የኢህአዴግ አወቃቀር ሲመራበት የነበረዉ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሕዝብን ዉሳኔ ሰጪነት የሚገድብ ስለሆነ ለደረስንበት የትግል መድረክ የሚመጥን አይደለም። ባለፉት ጊዜያት የነበረዉን የዝርፊያ መዋቅር ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፤ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች ሲፈፀሙበት የነበረዉን መዋቅር በማፈራረስ፤ ዴሞክራሲና ነፃነት የሰፈነባትና የበለፀገች ሀገር ለመገንባት በኢህአዴግ አወቃቀር ላይ ሪፎርም ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ኦዴፓ ያምናል።
በብዙ ጉድለቶች የታጠረዉ የኢህአዴግ አወቃቀር የኦሮሞንና የአገራችን ህዝቦችን ጥያቄና ፍላጎት ለመመለስ ያልተመቻቸ መሆኑን የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተንትኖ ተግባብቶበታል። በዚሁ መሠረት ኢህአዴግን በማደስ፤ በዘመነ አሠራርና ስርአት የሚመራ ፓርቲ በመፍጠር፤ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሐሳብን በማስወገድ በመደመር ፅንሰ ሀሳብ ለመተካት ውይይት እየተደረገ መሆኑ የታወቃል።
የመደመር ፅንሰ ሀሳብ ያለፉትን ስኬቶች ይበልጥ በማጎልበት የሚታዩትን ጉድለቶች ከመሰረቱ በመፍታት የአዲሱን ትዉልድ መብትና ጥቅም የሚያረጋግጥ መሆኑን ኦዴፓ ያምናል። በዚሁ መሰረት የኢህአዴግ ሪፎርም ጉዳይ እዉነተኛ የፌደራሊዝም ሥርዓት ዴሞክራሲዊ ብሄርተኝነትና ሀገራዊ አንድነት ሚዛኑን ጠብቆ ብዝሀነት የሰፈነባትና የበለፀገች ሀገር በመገንባት የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ የተመረጠ ዘዴ መሆኑን በማመን ለስኬታማነቱ ለመሥራት ወስኗል።
በመጨረሻም የደረስንበት የትግል ምዕራፍ የተወሳሰበ ቢሆንም የፓርቲዉን ዉስጣዊ ድክመት በመቅረፍ ሰፊዉን ሕዝብ ከጎኑ በማሰለፍ ከፊት ለፊቱ የሚጠብቀዉን ፈተና በማሸነፍ አዲስ ታሪክ እንዲመዘገብ ለማድረግ የጀመረዉ ትግል ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አዲፒ የገልፃል።
በኦዴፓ ሲወሰኑ የነበሩ ዉሳኔዎችና ሲቀመጡ የነበሩ አቅጣጫዎች ህዝባችንን ድል እያጎናፀፉ ለዚህ ምእራፍ አድርሰዉናል። አሁን የተቀመጡ አቅጣጫዎችም ህዝባችን በመስዋዕትነት የተጎናፀፋቸዉን ድሎች ጠብቆ እንዲያቆያቸዉና ተጨማሪ ድሎችን የሚያጎናፅፉት መሆኑን ተረድቶ ለአፈጻጸማቸዉ በጋራ መረባረብ ይጠበቅበታል። ትውልድ አያሌ መስዋዕትነት የከፈለበት የሕዝባችን ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ እንዲያገኙ ከምንጊዜዉም በበለጠ የሚታገል መሆኑን ኦዴፓ በድጋሚ ያረጋግጣል።
ተባብረን ከሠራን የማንወጣው ችግር አይኖርም!!
ጥቅምት 2012 ዓ.ም.
የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ -
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.