Search Results for 'ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ'

Home Forums Search Search Results for 'ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ'

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 19 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት ዘርፎች ያስተማራቸውን 659 ተማሪዎችን አስመረቀ

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በቅድመ- እና ድኅረ- ምረቃ መርሀግብሮች ያሰለጠናቸውን 659 ተማሪዎችን ጳጉሜን 3 ቀን 2012 ዓ.ም አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ለ12ኛ ዙር ለምረቃ ካበቃቸው ተማሪዎች መካከል 515 ወንዶች ሲሆኑ 144 ደግሞ ሴቶች ናቸው።

    ዩኒቨርሲቲው በእጽዋት ሳይንስ፣ በእንስሳት ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሥራ አመራር (Management)፣ እንዲሁም በጂኦግራፊና አካባቢ-ነክ ጥናቶች (Environmental Studies) በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስተምሮ አስመርቋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። እንደ ዶ/ር አህመድ ገለጻ፥ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለውጤት አብቅቷል።

    እንደ ተጠባባቂ ፕሬዝደንቱ ገለጻ፥ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው ዓመት በ46 የመጀመሪያ ዲግሪና በ23 የሁለተኛኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ከ17ሺ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

    በጥናትና ምርምር ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጭብጦች 18 የምርምር ንድፈ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል – ዶ/ር አህመድ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልም ከ3 ሺህ ሊትር በላይ የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሽ (ሳኒታይዘር) በማምረት አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጓልሲሉ አስረድተዋል።

    የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍቅሬ አማን በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስተላለት መልዕክት፥ እንዳሉት የዘንድሮው የምረቃ በዓል ለዓለማችን፣ ብሎም ለሀገራችን ህዝቦች የኮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት ተመራቂዎች የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማጠናቀቅ ለውጤት በመብቃታቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸዋል።

    ሀገራችን በመደመር ፍልስፍና ከነበረችበት ችግር ወጥታ ወደ ብልጽግና ጎዳና እየተጓዘች ባለችበት በዚህ የይቅርታና የምኅረት ወር በሆነችው በጳጉሜ ወር ተማሪዎች ለምረቃ በመብቃታቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞውን ሚዛን ተፈሪ ግብርና ኮሌጅ መሠረት አድርጎ በደቡብ ክልል ሚዛን ተፈሪ እና ቴፒ ከተሞች በ1999 ዓ.ም የተቋቋመ ዩኒቨርሲቲ ነው።

    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ

    Anonymous
    Inactive

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 419 ተማሪዎችን አስመረቀ

    ደሴ (ኢዜአ/ወ.ዩ.) – ወሎ ዩኒቨርሲቲ (ወ.ዩ.) በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በሁለተኛ ዲግሪ (Masters program) ያሰለጠናቸውን 350 ወንድ 69 ሴት በድምሩ 419 ተማሪዎችን ነሐሴ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ተማሪዎቹ ባሉበት ቦታ በኦንላይን (online) አስመረቀ።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በምረቃው ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተናገሩት ተቋሙ በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ቢያስመርቁም ዘንድሮ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። በወቅታዊ የወረርሽኝ ምክንያት የመማር ማስተማሩ ሥራ ቢቋረጥም አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ተማሪዎችን በማስተማር የጀመሩትን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ መደረጉን አስታውቀዋል።

    ተማሪዎች በመደበኛ፣ በማታ እና ሳምንታዊ መረሃ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን አመልክተው ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመረቁት መካከል 69 ሴቶች እንደሚገኙበት ዶ/ር አባተ ገልጸዋል።

    ዶ/ር አባተ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ዓለም በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በተናወጠበት እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተከሄደበት ዓመት መመረቃቸው ታሪካዊና ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል። አያይዘውም፥ ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ዕቅዱን በአዲስ መልክ በማዋቀር ሀገር-በቀል እውቀቶችን ከምርምር ጋር በማቀናጀት ለውጥ በሚያስመዘግብ መልኩ ለመሥራት የተዘጋጀ በመሆኑ፥ ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በሚሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምረው አዳዲስ ምርምሮችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር የመሥራት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።

    ተመራቂዎች በትምህርት ቆታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር ቀይረው ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከሉም የድርሻቸውን እንዲወጡ ዶ/ር አባተ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ ነሐሴ 2 ቀን ያስመረቃቸው ተማሪዎች 12ኛ ዙር ሲሆኑ፥ በሕግ፣ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ፣ ማኅበራዊ ሳይንስ፣ የተፈጥሮ ቀመር፣ ቢዝነስ እና ምህንድስና የሰለጠኑ ናቸው።

    የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ምሩቃን በቆይታቸው በቀሰሙት እውቀት በታማኝነት እኩል ሕብረተሰቡን ሊያገለግሉ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ የአንድነትና የሰላም እሴት ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍም በእውቀት ላይ የተመሠረተ እገዛ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አቶ አበበ አመልክተዋል።

    ከተመራቂዎች መካከል መላኩ በላይ በሰጠው አስተያየት ምንም እንኳ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) በትምህርቱ ዘርፍ ጫና ቢያሳድርም፥ በቴክኖሎጂ ታግዘው በዕለቱ ለመመረቅ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በተማረበት ሕክምና እና ጤና ሳይንስም ሕብረተሰቡን በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ጠቁሞ፥ “በተለይ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የድርሻዬን እወጣለሁ” በማለት አክሏል።

    ሌላዋ የፕሮጀክት አመራር (project management) ተመራቂ ገነት ኪሮስ በበኩሏ፥ በሙያዋ ሕዝቡን በማገልገል የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ተናግራለች። ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን የሚያስጨንቅበት ቢሆንም በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ታግዛ ለዚህ በመብቃቷ መደሰቷን ገልጻለች።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ወሎ ዩኒቨርሲቲ (ወ.ዩ.)

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አስመረቀ

    Semonegna
    Keymaster

    ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎቹን አስመረቀ፤ ለመጪው የትምህርት ዘመን የቅድመ ሥራዎች ላይ ውይይት አድርጓል።

    ደብረ ብርሀን (ኢዜአ/ሰሞነኛ) – ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች በ2ኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን 61 ተማሪዎች ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ።

    የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጀ አንዳርጌ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በትምህርት ዘርፉ ላይ በርካታ እንቅፋቶች አጋጥመዋል። የመማር ማስተማሩ እንዲቋረጥ በመደረጉም ተማሪዎችን አቅም በፈቀደ መንገድ በቴክኖሎጂ ለማገዝ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል። በተለይም የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በቴክኖሎጂ እንዲከታተሉ በማድረግ ለምረቃ ቀናቸው ማድረስ መቻሉን ገልፀዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ ያስመረቃቸው ተማሪዎችም በቀን፣ በማታ እና በሳምንታዊ የትምህርት ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ተከታትለው ማጠናቀቅ የቻሉ መሆናቸውን ዶ/ር ደረጀ ተናግረዋል።

    ተመራቂዎቹ በጤና፣ በግብርና እና ተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ቀመር እና የቢዝነስ የትምህርት መስክን ጨምሮ በ21 የትምህርት ዘርፎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው ተብሏል። ዩኒቨርሲቲው ለ12ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከልም 52ቱ ሴቶች መሆናቸውን ዶ/ር ደረጀ አስታውቀዋል።

    አሁን ላይ ሀገሪቱ የተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች ውስጥ መሆኗን አመልክተው፥ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገሪቱ ከገጠማት ችግር ፈጥና እንድትወጣ በቆይታቸው ወቅት ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ዶ/ር ደረጀ አሳስበዋል።

    በአካውንቲንግና ፋይናስ የትምህርት ዘርፍ 3.91 በማምጣት የተመረቁት አቶ ገብረሀና ደበበ በበሰጡት አስተያየት በተመረቁበት ዘርፍ ሕዝባቸውን እና ሀገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

    በእናቶች እና ሕፃናት ጤና የተመረቁት ወ/ሮ ዘነቡ አጎናፍር በበኩላቸው፥ ሕብረተሰቡን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።

    ሐምሌ 21 ቀን በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት በኮሮና ቨይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተወካይ ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት ብቻ ተገኝተው የምረቃ መረሐ ግብሩን ተከታትለዋል።

    ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሳንወጣ፥ ዩኒቨርሲቲው ለ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ውይይት አድርጓል።

    የ2013 ዓ.ም. የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ዕቅድ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ ተዘጋጅቶ ለውይይት ቀርቦ ነበር። በፕሬዝዳንቱ የቀረበው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በ5 ዋና ዋና ዘርፎች ተከፍለዋል። በአስተዳደር፣ በፕ/ጽ/ቤት፣ በአካዳሚክ፣ በጥናትና ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት እና በቢዝነስና ልማት ዘርፍ የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎችን በጥልቀት የመረመረ እቅድ እንደነበረ ለማየት ተችሏል።

    ዶ/ር ንጉስ ታደሰ እንዳቀረቡት፥ በእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ዝርዝር እና የአፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳን አስቀምጠዋል። የቀጣይ የዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስኮች ተለይተው ጥናት ተካሂዷል ብለዋል። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ያለው የግንባታ ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱና እያለቁ መሆናቸውንም ዶ/ር ንጉስ ገልጸዋል።

    በዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች ላይ መከናወን አለባቸው ከተባሉት ዋና ዋና ተግባራት መካከል፥ ለሀኪም ግዛው መታሰቢያ ሆስፒታልና ለአዲሱ ማስተማሪያ ካምፓስ የውስጥ ቁሳቁሶችን ማሟላት፣ የአፕላይድ ዩኒቨርሲቲ (applied university) ደረጃን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል (center of excellence) የሚያዘጋጅ ቡድን ማዋቀርና ወደ ሥራ ማስገባት፤ የምኒልክ የቴክኖሎጂ ካምፓስን የዲዛይን፣ የካሳ ክፍያና ሌሎች ሥራዎች መሥራት፣ የአካዳሚክ አመራሩን መገምገምና ጊዜያቸው ያጠናቀቁ አመራሮች በአዲስ መተካት፣ የተጀመሩትን የጥናትና ምርምር ሥራ ማስቀጠል፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተዘጋጀውን የኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ በቁሳቁስና በሰው ኃይል ማሟላት እና በ2013 ዓ.ም ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ሙሉ ዝግጅት ማድረግና የተስተጓጎለውን ትምህርት በአጭር ጊዜ ለማካካስ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።

    በመቀጠልም በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በዕቅዱ ላይ ቢካተቱ ያሏቸውን ሀሳቦችና ትኩረት የሚያሻቸውን ነጥቦች ላይ ሀሳብና አስተያየት ሰጥተዋል።

    የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው፥ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የተያያዙ ምርምሮች እየተካሄዱ እንደሆነና የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርን ለ3ኛ ጊዜ ለማምረት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ቀድሞ ይከናወኑ የነበሩ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል።

    የአስተዳርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጄ አጅቤ እንዳሉት፥ በዝግጅት ምዕራፍ እቅድ በየሥራ ዘርፉ የተዘረዘሩት ዋና ዋና ተግባራትን እያንዳንዱ የሥራ ክፍል ተወያይቶ ለተግባራዊነቱ እንዲሰራ ሁሉም አመራር የሚጠበቅበትን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ አሳስበዋል።

    ምንጮች፦ ኢዜአ/ ዩኒቨርሲቲው

    ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ባሕር ዳር (ሰሞነኛ) – ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ አቶ አየነው በላይን በመተካት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ።

    ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአሜሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኖርዝ ቴክሳስ (The University of North Texas) ተከታትለዋል። በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ አት ኦስተን (The University of Texas at Austin) እና በሌሎችም በተመራማሪነት ማገልገላቸውም ታውቋል። የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በአሜሪካና ካናዳ ማቅረባቸውም በግለ ታሪካቸው ተብራርቷል።

    ዶክተር መሐሪ የተለያዩ ዓለማቀፍ የሙያ ማኅበራት አባል መሆናቸውም ነው የተገለጸው። የአሜሪካ የስታትስቲክስ ማኅበር (American Statistical Association)፣ የአሜሪካ የትምህርት ጥናት ማኅበር (American Educational Studies Association)፣ የተቋማዊ ጥናት ማኅበር፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥናት ማኅበር፣ የደቡብ ምዕራብ የትምህርት ጥናት ማኅበርና የቴክሳስ የትምህር ጥናት ማኅበር አባል እንደሆኑም ነው የተገለጸው።

    ከ13 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምርና የተለያዩ ትምህርቶችን በማስተማር እንደቆዩም ተገልጿል፤ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በኃላፊነት ደረጃ ማገልገላቸውም ነው የተነገረው።

    ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስን ልምዳቸውንና የአመራር ብቃታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ታኅሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ማካሄድ በጀመረው መደበኛ ጉባኤው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾሟቸዋል።■

    ከአማራ ክልል ሳንወጣ፥ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው የበላይ ባለ ኮኮብ 5 ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ፕላን በዘርፉ ባለሙያዎች ተገመገመ። የፕሮጀክቱ ዲዛይንና አማካሪ የሆኑት አቶ ነቢዩ ሰለሞን እንዳብራሩት፥ ሆቴሉ በ3,690 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደሚያርፍ፣ 3 ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ 120 የመኝታ ክፍሎች፣ 2 ሬስቶራንቶች፣ ባር፣ ጂም እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች እንደሚኖሩት፣ ዲዛይኑ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

    የደብረ ብርሃን ከተማ ህንጻ ሹም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አምሳሉ መኮንን በበኩላቸው በቀረበው ዲዛይን መሠረት ገንቢ አስያየት በመስጠት ሆቴሉ ከታሰበው በላይ ተሻሽሎና ዳብሮ እንዲሠራ ባለሙያዎች የድርሻቸውን አንዲወጡ አሳስበዋል።

    የውይይቱ ተሳታፊዎችም የቡና ስኒ በዲዛይኑ ላይ መካተቱ ከደብረብርሃን ጋር ምን ያገናኘዋል? የሠራተኞች ማረፊያ ክፈል፣ ሕፃናት መዝናኛ፣የመዋኛ ገንዳ መካተት አለበት የሚሉና እና ሌሎችም በርካታ ሀሳብ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። በመድረኩ ከደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ፣ ከኢንቨስትመንት፣ ከህንጻ ሹም፣ ከህንጻ ዲዛይን አማካሪዎች፣ ከባህል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች የመጡ የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

    የበላይ ባለ 5 ኮኮብ ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ከ2 መቶ ሚሊየን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለት የመሠረት ድንጋው ሲጣል መገለጹ የሚታወስ ነው።

    ምንጮች፦ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ዶክተር መሐሪ ታደሰ

    Semonegna
    Keymaster

    በአሁኑ ጊዜ የግዕዝ ቋንቋን ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚሰጥባቸው መካከል መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ደሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዲ.ሪ.) ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከብሔራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ፣ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ቅዱስ ያሬድ ጥንታዊ ብራና ጽሑፎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ከሰኔ 1-2 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ “ግዕዝ እና ሥነ-ፈውስ” በሚል መሪ ቃል በመቐለ ከተማ ለሚካሄደው 5ኛውን የግዕዝ ጉባኤ ቀንን አስመልክቶ መረጃውን አስቀድሞ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጋዜጣዊ መግለጫ በሚኒስቴሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንቦት 26 ቀን 20011 ዓ.ም. ተሰጥቷል።

    ጋዜጣዊ መግለጫውን በጥምረት የሰጡት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቋንቋና የባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው፣ የብሔራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ቅዱስ ያሬድ ጥንታዊ ብራና ጽሑፎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሐጎስ አብርሃ ናቸው።

    እንደኃላፊዎቹ መግለጫ፥ በግዕዝ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶች በርካታ በመሆናቸው ልንማርበት፣ ልንጠቀምበትና ልትውልድ በማሸጋገር ወደ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ማምራት ይቻላል። በመሪ ቃሉ “ግዕዝ እና ሥነ-ፈውስ” ስንል እንደየባህሉ ሥነ-ልቦናን፣ ፀሎትን፣ ሥነ-ቃልን ለማወቅና መዳንን የሚያበረታታታ ሀገር በቀል ዕውቀት መሆኑንማወቅ ስላለብን፣ ብሎም ስለግዕዝ ያለንን ግንዛቤ ለማስፋት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

    እንዲሁም በሀገራችን በርካታ ጥንታዊ የጽሑፍ ሀብቶቻችን የምናገኝበት በግዕዝ ቋንቋ የተፃፉ በመሆኑ፣ ጥንታዊ የስልጣኔ መገለጫ ሆኖ የሚያገለግል ነው። በአሁኑ ጊዜ የግዕዝ ቋንቋን ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚሰጥባቸው መካከል መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ደሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በሀገራችን በግዕዝ ቋንቋ በተሠሩ ሥራዎች ላይ እስካሁን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት 750,000 በብራና ላይ የተፃፉ መጽሕፍት መኖሩ ታውቋል።

    ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    መቐለ ዩኒቨርሲቲ


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ አሠራሩን ለማዘመን የሚያግዙ ሀሳቦች ላይ ከእንግሊዝ ቤተ መዛግብት ኃላፊዎች ጋር ምክክር አደረገ።

    በምክክሩ የቤተመዛግብት እና ቤተ መፃሕፍት አያይዝን ለማዘመን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የእንግሊዙ አቻ ተቋም ልምድ ምን እንደሆነ ያወያየ ምክክር ሚያዚያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በኤጀንሲዉ የቪዲዮ ኮንፈረንስ አዳራሽ ተካሄደ። ለውይይቱ መክፈቻ የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ የኩኖአምላክ መዝገቡ ለእንግዶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ኢትዮጵያ የብዙ መዛግብቶች መገኛና ባለቤት ብትሆንም እንኳን ያላትን ሀብት ለራሷም ለዓለምም ለማበርከት የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እጥረት እንዳለባት በማንሳት ይህንን ክፍተት የእንግሊዝ ቤተ መዛግብት የቴክኖሎጂ ሽግግር እገዛ አንዲያደርግላቸዉ ጠይቀዋል።

    በመቀጠል በእንግሊዝ ቤተ መዛግብት የኤሲያና የአፍሪካ የመዛግብት ስብስብ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሊዊሳ ኤሌና ሜንጎሊ (Luisa Elena Mengoni, Head of Asian and African Collections at the British Library) እንዳሉት በሁለቱ ሀገራት ዉስጥ ያሉ ተመራማሪዎች፣ ደራሲያን፣ እንዲሁም ሌሎች ፀሐፍት የእርስ በእርስ የልምድ ልዉዉጥ እንዲያደርጉ መንገዱን ማመቻቸት ለስነ-ፅሑፍ እድገት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

    አቶ ክርስቲያን ጄንሰን (Kristian Jensen) የእንግሊዝ ቤተ መዛግብት ኃላፊ እንዲህ አይነት የምክክር መድረኮች ክፍተቶችን ለመለየትና መፍትሔ ለማበጀት እንደሚጠቅሙና ቀጣይነት እዲኖራቸዉ በተለይም የሥነ-ፅሑፍ ታሪኳ ከአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሀገር ቤተ መፅሐፍቷና ቤተ መዛግብቷን በማዘመን ረገድ የእንግሊዝ ቤተመዛግብት እንደሚያግዝ ተናግረዉ፥ ኃላፊዉ የማይክሮ ፊልም (የመፅሐፍት ላይ ፅሑፎችን ወደ ሶፍት ኮፒ የሚቀይር መሣሪያ) በእርዳታ መስጠቷ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር በዶ/ር ሂሩት ካሳዉ በኩል ለኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ለአቶ የኩኖአምላክ መዝገቡ ርክክብ ከተደረገ በኋላ ባህላዊ የቡና ጠጡ ሥነ-ስርዓት ተከናዉኖ ዝግጅቱ ተጠናቋል።

    ምንጭ፦ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ቤተ መዛግብት


    Semonegna
    Keymaster

    ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው አቤ ደንጎሮ ሆስፒታል የተመላላሽ፣ የአስተኝቶ ማከም፣ የወሊድ አገልግሎት፣ የቀዶ ሕክምና፣ የድንገተኛ ሕክምና፣ የራጅ፣ የላቦራቶሪና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አሉት።

    ነቀምት (ኢዜአ) – ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤ ደንጎሮ ወረዳ ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው አቤ ደንጎሮ ሆስፒታል መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። ሆስፒታሉ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ እንዳስደሰታቸው አንዳንድ የወረዳው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

    የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ደረጃ ዱጉማ በምርቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው አቤ ደንጎሮ ሆስፒታል የተመላላሽ፣ የአስተኝቶ ማከም፣ የወሊድ አገልግሎት፣ የቀዶ ሕክምና፣ የድንገተኛ ሕክምና፣ የራጅ፣ የላቦራቶሪና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አሉት።

    ሆስፒታሉ በአቤ ደንጎሮ ወረዳና በአካባቢው በሚገኙ ተጎራባች ወረዳዎች ለሚገኙ ከ400 ሺህ ለሚበልጡ ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ የሕክምና መሳሪያዎችና የሰው ኃይል የተሟላለት መሆኑንም አመልክተዋል።

    የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትና የማኅበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው ሆስፒታሉ የህዝቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የመለሰና የሕዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል። ህብረተሰቡ ሆስፒታሉ የራሱ ሀብትና ንብረት መሆኑን ተረድቶ እንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠብቀው እንደሚገባ አሳስበዋል።

    ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች በበኩላቸው ሆስፒታሉ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

    ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል የቱሉ ዋዩ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ እቴነሽ ደገፉ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው ለበርካታ ዓመታት የጤና ተቋማት ባለመኖሩ በተለይ በእናቶችና ህጻናት ህይወት ላይ አደጋ ይደርስ እንደነበር አስታውሰዋል። የወረዳው ህዝብ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ሻምቡና ነቀምቴ ሆስፒታሎች በመጓዝ ለወጪና እንግሊት ሲጋለጥ መቆየቱንም ጠቁመዋል። በአካባቢያችን ደረጃውን የተጠበቀ ሆስፒታል መገንባቱ ወጪና እንግልትን ከማስቀረቱም በላይ የእናቶችና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

    ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ደቻሣ ገለታ ወረዳው ከነቀምቴና ሻምቡ ሆስፒታሎች በብዙ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ስለሚገኝ በተለይ በወሊድ ጊዜ የበርካታ እናቶችና ህፃናት ህይወት ሲያልፍ መቆየቱን አመልክተዋል። የሆስፒታል መገንባት የአካባቢውን ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የመለሰና የህብረተሰቡን የጤና ችግር የሚፈታ በመሆኑ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    አቤ ደንጎሮ ሆስፒታል


    Semonegna
    Keymaster

    “የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማምጣት ቸርነት አይደለም። ነገር ግን ለአንድ ሀገር ህልውና በመሆኑ አንዱ ሰጭ ሌላው ተቀባይ በሆነ መልኩ ሳይሆን ሰብዓዊ ወይም ሰዋዊ መብትም ጭምር ነው።” ዶ/ር አልማዝ አፈራ

    ደብረ ብርሃን (ሰሞነኛ) – የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን “የላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲተው ከፍተኛ አመራሮች ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የዞን ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች መምሪያ ኃላፊዎችና የሊግ ተወካዮች በተገኙበት መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

    በበዓሉ ላይ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር ወ/ሮ ኃይማኖት ቢችል እንደገለጹት የሴቶችን ቀን ስናከብር በሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆና ለማስወገድ የተደረገውን የትግል እንቅስቃሴና ውጤታማነት ለመዘከር፣ ሴቶች ከነበረባቸው ጭቆና ተላቀው በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በስነ-ልቦናዊ እና ፖለቲካዊ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚቻልበትን ሁነት ለመዘከር መሆኑን አንስተዋል። እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፥ በዓሉ ሴቶች ውጤታማ የሆኑባቸውን ሥራዎች በመዘከር ለማበረታታት ያስችላል ብለዋል።

    የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ በዓሉን በንግግር ሲከፍቱ፥ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማምጣት ቸርነት አይደለም። ነገር ግን ለአንድ ሀገር ህልውና በመሆኑ አንዱ ሰጭ ሌላው ተቀባይ በሆነ መልኩ ሳይሆን ሰብዓዊ ወይም ሰዋዊ መብትም ጭምር ነው ብለዋል። ፕሬዚዳንቷ አክለው እንደገለጹት፥ ሴት የቤተሰብና የሀገር መሠረት ስለሆነች እኛ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰቦች ከዘር፣ ከጾታና ከሀይማኖት አድሎ በጸዳ መልኩ መሥራትና መታገል እንዲሁም በግልፅ ብቻ ሳይሆን በረቀቀ ዘዴ ጭምር የሚደረጉ ጾታዊ ትነኮሳዎችን ለመዋጋት መሥራት አለብን ብለዋል።

    የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የግብርና ምርምር ፕሮጀክት ተመረቀ

    በበዓሉ ላይ ሁለት ጥናታዊ ጽሁፎች የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እና እናትነት /Motherism/ በሚሉ ርዕሶች በዶ/ር ሰርካለም ይገረሙ እና በመ/ር ጌትነት ጥበቡ ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል። በውይይቱም የቀረቡት ጽሁፎች አስተማሪ በመሆናቸው ለተግባራዊነታቸው ሁሉም አካል ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ተጠቁሟል።

    በመጨረሻም አርዓያ ለሆኑ ሴት መምህራንና በ2011 ዓ.ም የመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ከ1ኛ-3ኛ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች የእወቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል። አቶ ደረጀ አጅቤ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ተወካይ የማበረታቻ ሽልማቱን ከሰጡ በኋላ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ሴቶች ቤተሰባቸውን ይመራሉ፣ ያስተዳድራሉ፤ ለዚህም መስዋዕትነት ይከፍላሉ። አመራር ለመሆን ሴቶች ራሳቸው መስዋዕትነት መክፈል ይኖርባቸዋል። ሴቶችን አመራር ስናደርጋቸው ምቹ የሥራ ቦታና ሁኔታ ልንፈጥርላቸው ይገባል ብለዋል።

    ምንጭ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሴቶች ቀን


    Semonegna
    Keymaster

    የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ ተከትሎ የአዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የጠቅላይ ሚኒስትር የመሠረተ ልማት እና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር አምባቸው መኮንን ርዕስ መስተዳደር ሆነው ተሹመዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መልቀቂያ ጥያቄ አቀረቡ። ርዕሰ መስተዳድሩ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው ጥያቄውን ያቀረቡ ሲሆን፥ ምክር ቤቱም ጥያቄያቸውን ተቀብሏል። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)በበኩሉም የርዕሰ መስተዳድሩን ጥያቄ መቀበሉን የ አማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግበዋል።

    አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ለሦስተኛ ዙር በርዕሰ መስተዳድርነት ተመርጠው ሲያገለግሉ እንደነበር ይታወሳል። በአጠቃላይም ከታህሳስ ወር 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመሆን አገልግለዋል።

    አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “ታላቁን የአማራ ሕዝብ ለመምራት ዕድል የሰጠኝን ፓርቲዬን አመሠግናለሁ፤ በስልጣን ዘመኔ በሰጠኋቸው ውሳኔዎች ያስከፋኋችሁ ካላችሁ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ወኔና ጉልበት ሆኖኝ የኖረውን የአማራ ሕዝብ አመሠግናለሁ፤ ለአዲሱ ርዕሰ መስተዳድርም መልካም የሥራ ዘመን እመኛለሁ” ብለዋል በመሰናበቻ ንግግራቸው።

    የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ ተከትሎ ምክር ቤቱ የአዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑትን ዶ/ር አምባቸው መኮንንን ርዕስ መስተዳደር አደርጎ ሾሟል። ዶ/ር አምባቸው ከአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን የመሠረተ ልማት እና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር በመሆን እያገለገሉ ነበር።

    እድገታቸው ጋይንት፣ ጎንደር ውስጥ የሆነው ዶ/ር አምባቸው መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በተለያዩ የመንግስት ቦታዎች ለ28 ዓመታት ሠርተዋል።

    ዶ/ር አምባቸው ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፣ ቀጥሎም ደቡብ ኮርያ ከሚገኘው ከኮርያ የልማት ኢንስቲትዩት (Korea Development Institute) በፐብሊክ ፖሊሲ የማስተርስ ዲግሪ፣ ከዚያም እንግሊዝ ሀገር ካንተርበሪ ከተማ ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬንት (University of Kent) ሌላ ማስተርስ ዲግሪ እና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ዶ/ር አምባቸው መኮንን


    Semonegna
    Keymaster

    የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ በዚህ ፕሮጀክት የተሳተፉ ተመራማሪዎችን ያሉትን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ለዚህ በመብቃታቸው ምስጋና ቸረዋቸዋል።

    ደብረ ብርሃን (ሰሞነኛ)– የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ከኢፌዴሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ይምሎ ቀበሌ በተቀናጀ የአሳ፣ የዶሮ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ሲያካሂድ የቆየውን የምርምር ፕሮጀክት አጠናቆ ለዞኑ አስተዳደርና ለአካበቢው ማኅበረሰብ አስረከበ።

    በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ወቅት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህርና መሪ ተመራማሪ ዶ/ር ገዛኸኝ ደግፌ እንደተናገሩት ምርምሩ በትንሽ ቦታ አሳን፣ ዶሮንና አትክልትን አቀናጅቶ ማልማት የሚያስችል የቴክኖሎጅ ዕውቀትን በመጠቀም የአሳ፣ የዶሮና የአትክልት ልማቱን አቀናጅቶ መሥራት እንደሚቻል ነው ብለዋል። በዚህም የዶሮ ኩስን ለአሳዎች ምግብ እንዲውል እንዲሁም “vermicompost” ቆሻሻን ወደ ጠቃሚ ነገርነትና ማዳበሪያነት የሚቀይሩ ትሎችን ለዶሮዎችና ለአሳ ምግብነት እንዲውል የሚያስችል እንደሆነ አብራርተዋል።

    በምስራቅ ጎጃም ዞን ስንዴ አምራች ወረዳዎች ለገበሬዎች የቀረቡላቸው ኮምባይነሮች በምርታቸው ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ እያደረጉ ነው

    አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳደሪ እንዳሉት ይህ ለምርቃት የበቃው የምርምር ሥራ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዞኑ ከሚያከናውናቸው ምርምሮች አንዱ ሲሆን ፣ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፈጻሚነትና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ የተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ዋና አስተዳዳሪው አክለው እንዳስታወቁት ይህንን ምርምር በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለማስፋፋት ትልቅ ኃላፊነትና አደራ የተጣለባቸው መሆኑን አውስተው ለተግባራዊነቱም እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

    የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ባደረጉት ንግግር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ከሚደግፋቸው በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በሚባል ደረጃ ከ60 በላይ ምርምሮች መካከል የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አንዱና ውጤታማው በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በሚችሉ ትናንሽ ፕሮጀክቶች በመደገፍ የሀገራችንን ልማት ማረጋገጥ ይኖርብናል ብለዋል። ይህን ፕሮጀከት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች እንዲተላለፍ ማኑዋልና ስታንዳርድ ተዘጋጅቷል። የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርም በአማራ ክልል ለሚገኙ ሁሉም ዞኖች እንዲያደርስ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሰራጭ አናደርጋለን ብለዋል።

    ዶ/ር አልማዝ አፈራ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት በበኩላቸው በዚህ ፕሮጀክት የተሳተፉ ተመራማሪዎችን ያሉትን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ለዚህ በመብቃታቸው ምስጋና ቸረዋቸዋል። እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለፃ፥ በሀገራችን እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ሥራ-አጥ ወጣቶች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን እንደነዚህ ዓይነት የምርምር ሥራዎች ደግሞ ወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ በማድረግ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል። ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲም ብዙ የምርምር ውጤቶች ያሉት ሲሆን እነዚህን ምርምሮች ወደ ፕሮጀክት መቀየር የሚያስችል ተሞክሮ ስለሆነ ይህ ትልቅ ማሳያ ይሆነናል ብለዋል። በመጨረሻም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርንና የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳደርን ላደረጉት ድጋፍና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

    ምንጭ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የግብርና ምርምር ፕሮጀክት


    Anonymous
    Inactive

    ተረፈ-ምርትን በመጠቀም ማምረት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
    —–

    ቆሻሻና አነስተኛ ውሃን በመጠቀም የአሳና ዶሮ ምግብ፣ ማዳበሪያ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በቀላሉ ማምረት የሚያስችል የተቀናጀ የግብርና ዘዴ የምርምር ፕሮጀክት ተጠናቆ ወደ ስራ ሊገባ ነው፡፡

    በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለ3 ዓመታት ባደረገው ምርምር አርሶ አደሩ በአነስተኛ የጓሮ መሬትና ውስን የጉድጓድ ውሃ በማዘጋጀት ዘርፈ ብዙ ምርት መሰብሰብ የሚቻልበት ፕሮጀክት ተጠናቆ ለትግበራ ተዘጋጅቷል፡፡

    ምርምሩ በተደረገበት በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ይምሎ ቀበሌ የተደራጁ ወጣቶችን በማሳተፍ ውጤታማ የአሳ፣ የዶሮ፣ የማዳበሪያ፣ የሙዝና የሸንኮራ አገዳ ምርቶችን በአነስተኛ መሬት ላይ ማሳካት ተችሏል፡፡

    በፕሮጀክቱ ምረቃ ላይ የተገኙት የአ.ፌ.ዴ.ሪ. ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ይህን ፕሮጀክት ትልቅ የሚያደርገው ወጣቶች በአነስተኛ ወጪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊጠቀሙበት የሚችሉበት መሆኑ ነው ብለዋል፡፡

    ሚኒስትሩ የፕሮጀክቱን የአተገባበር ሰነድ ለዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ለአቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ አስረክበዋል፡፡

    ምንጭ፦ ዋልታ ሚዲያ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – STEMpower የተሰኘ መቀመጫውን USA (ሳሌም፥ ማሳቹሴትስ፣ አሜሪካ) ያደረገ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ትምህርቶችን በዩኒቨርሲቲዎች እየረዳ የሚገኝ ሲሆን በአገራችን 13 ማዕከላትን ከፍቶ በትብብር እየሠራና እየረዳ ይገኛል።

    ድርጅቱ የድጋፍ አድማሱን በማስፋት በኢትዮጵያ ተጨማሪ 10 ማዕከላትን (ሰባት ማዕከላትን በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሶስቱን በተለያዩ ከተሞች እ.አ.አ. በ2019) ለመክፈት ከኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የትብብር ስምምነት የካቲት 14 ቀን 2011ዓ.ም. ተፈራርመዋል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር) STEMpower ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶችን ለማበልጸግ እያደረገ ያለውን ትብብር በማመስገን፥ ዩኒቨርሲቲዎችም ዕድሉን በመጠቀም በአግባቡ ማዕከላቱን ማሳለጥ እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማሪያ ክፍሎቹ ውስጥ ዲጂታል ሰሌዳዎችን መጠቀም ጀመረ።

    የሳንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) በበኩላቸው ለሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲአዲግራት ዩኒቨርሲቲአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ) ማዕከሉን በመጠቀም በአካባቢዎቻቸው ያሉትን የማኅበረሰብ ችግሮች መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

    የSTEMpower አስተባባሪ ዳይሬክተርና ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ቅድስት ገብረአምላክ፥ “STEMpower ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ከድርጅቱ አመሠራረት ጀምሮ ዓላማውን፣ አሁን ያለበት ሁኔታ እና የወደፊት ዕቅድ አጭር ማብራሪያ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል። ለወደፊትም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በስፋት እንደሚሠሩ ፣ በ2040 የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት እንደሆነ ገልጸዋል።

    አገራችን ኢትዮጵያ የራሷን የሆነ ጥንታዊ ታሪክና ባህል ያላት አገር እንደመሆኗ ድርጅቱ በማኅበራዊ ሳይንስ ላይም ትኩረት እንዲያደርግ ከተሳታፊዎቹ አስተያየት ተሰንዝሯል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ማዕከሎቹ በከፍተኛ ትምህርት እና በሳይንስ ትምህርቶች አከባቢ የሚስተዋሉትን ችግሮች በመቅረፍ የአገሪቱን ብልጽግና ከማረጋገጥ ረገድ መልካም ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    STEMpower


    Semonegna
    Keymaster

    የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ያዘጋጁት የዘንድሮው ውድድር ለ2ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፥ በባለፈው ዓመት የተመረጠችው ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል በተካሄደው የቁንጅና ውድድር ላይ ተሳትፋ 3ኛ ደረጃ መውጣቷም ተገልጿል።

    ደብረ ብርሃን (ሰሞነኛ)– በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ‹‹ቱሪዝም ለአካባቢ እንክብካቤና ለማኅበረሰብ አቅም መጎልበት›› በሚል መሪ ቃል ሲከበር የቆየው የቱሪዝም ሳምንት ጥር 24/2011 ዓ/ም የቁንጅና ውድድር በማካሄድ ተጠናቀቀ።

    በውድድሩም ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ያብፀጋ አይነኩሉ ከሁለተኛ ዓመት የሎጅስቲክና ሰፕላይ ቼን ማኔጅመንት (Logistics and Supply Chain Management) ትምህርት ክፍል ተመርጣለች። በሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ኤልሳቤጥ ደስታ የ3ኛ ዓመት የባዮቴክኖሎጂ (Biotechnology) እና በሦስተኛነት ደረጃ ተማሪ ትንሳኤ ፀጋዬ አንደኛ ዓመት የሳይኮሎጂ (Psychology) ትምህርት ክፍል እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።

    VIDEO: The Yellow Movement AAU: Speaking up for women and girls – empowering women (Ethiopia)

    የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ተወካይ ዶ/ር ጌትነት አሸናፊ በፕሮግራሙ መዝጊያ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ከሳምንት በፊት ጀምሮ በዩኒቨርስቲው ግቢና ውጪ ያለውን አካባቢ በማጽዳት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ ተግባራት በማከናወን የቆዩ መሆናቸውን በመግለፅ ላደረጉት በጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።

    የቱሪዝም ማኔጅመንት የትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አብርሃም ኪዳኔ እንደገለፁት የዘንድሮው ውድድር ለ2ኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፥ በባለፈው ዓመት የተመረጠችው ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል በተካሄደው የቁንጅና ውድድር ላይ ተሳትፋ 3ኛ ደረጃ በመውጣቷ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘች መሆኗን ተናግረዋል።

    በመጨረሻም ለጓሳ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ መታሰቢያነት ‹‹ቱሪዝም ለአካባቢ እንክብካቤና ለማህበረሰብ አቅም መጎልበት›› በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የቱሪዝም ሳምንት 8 /ስምንት/ ተወዳዳሪዎችን ያሳተፈው የቁንጅና ውድድር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የወጡትን አሸናፊዎችን በመምረጥና እውቅና በመስጠት በዓሉ ተጠናቋል።

    ምንጭ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በ2006 ዓ.ም. በሰባት የየመገናኛ ብዙሃን (ሚዲያ) እና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተቋቋመው ጉዞ ዓድዋ፥ አንድ ሺሕ አስር ኪሎሜትሮችን የሚሸፍን፣ ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ተነስቶ መዳረሻውን የዓድዋ ድል አምባ ተራሮች ጫፍ ላይ የሚያደርግ ረዥም የእግር ጉዞ ነው። ላለፉት ስድስት ዓመታት ከጥር ወር ጀምሮ የዓድዋ ድል በዓል እስከ ሚከበርበት የካቲት 23 ቀን ድረስ ከስድስት ሳምንታት ላላነሰ በየዓመቱ ሳይቋረጥ የቆየው ጉዞ ዓድዋ፥ ዘንድሮ የኢትዮጵያዊነቱ ስሜት እጅግ ጎልቶ በጉዞው ላይ የሚሳተፉት ቁጥርም ጨምሯል። በዘንድሮው ጊዞ ዓድዋ 44 ተጋዦች ከአዲስ አበባ እና 4 ተጓዦች ከሐረር በአጠቃላይ 48 ተጓዦች ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀን ከአዲስ አበባ ተነስተዋል።

    የመላው አፍሪቃውያን ድል እስከመባል የደረሰው ታላቁ የዓድዋ ድል፥ የግዝፈቱን ያህል ክብር እና መታወሻ ሥነሥርዐት ሳይኖረው እየተከታተለ ከመጣው ትውልድ ጋር የበዓሉ አከባበር ዐውድ እየወረደ ጭራሽ እየተዘነጋ እና እየደበዘዘ መሔድ ያሳሰባቸው የጉዞ ዓድዋ መሥራቾች ትውልዱ ትኩረት ሰጥቶ የድሉን መንፈስ እንዲጋራ ለማድረግ ይህንን የጉዞ ሐሳብ አመንጭተዋል።

    ◌ የጉዞ ዓድዋ ተጓዦችና የኢትዮጵያዊያን አስተያየት

    በዚህም የተነሣ ጉዞ ዓድዋ ባለፉት ስድስት ዓመታት ብቻ ከታለመው ዓላማ አንጻር ከፍተኛ የሆነ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ የዓድዋ ድል በዓል ቀድሞ ከነበረበት አከባበር የላቀ ተሳትፎ ያለው የድል በዓል እንዲሆን አስተዋጽዖ ለማድረግ ተችሏል።

    ጉዞውን ከማካሔድ በተጓዳኝ በየመንገዱ ተንቀሳቃሽ የመጻሕፍት ንባብ መሰናዶ በማካሔድ በየዓመቱ የሚጓዙ አባላትን በዓድዋ ጦርነት እና ድል ዙሪያ በቂ የሆነ ግንዛቤ እና ዕውቀት የማጋራት ዝግጅቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል። ከአንድ ወር በላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን የሚሰጠው የጉዞው የዕለት ተእለት ውሎ፣ በዓሉ ከመድረሱ አስቀድሞ በበርካታው ሕዝባችን ላይ የካቲት 23 ዕለትን በጉጉት የመጠበቅ ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል።

    ◌ የዓድዋ ድል በዓል በጎሰኞች ዓይን የዲያቆን ዳንኤል ክብረት መጣጥፍ

    ከዚህ ቀደም የድል በዓሉ በብቸኝነት ከሚከበርባቸው የአዲስ አበባ እና የዓድዋ ከተሞች በተጨማሪ ከ28 በላይየሚሆኑ የክልል ከተሞች እና በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸው የገጠር ወረዳዎች ተጓዥ ቡድኑ በየደረሰበት በሚኖሩ ደማቅ አቀባበሎች ላይ በሚሰጡ የግንዛቤ መስጫ መልዕክቶች ስለ ዓድዋ ድል ታሪክ ግንዛቤ በመሰጠቱ የበዓሉአከባበር ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛል። የጉዞ ዓድዋ ትሩፋቶች፦

    • በዓድዋ ከተማ ውስጥ በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የነበረው የዓድዋ ድል በዓል አከባበር ሥነ ሥርዐትበየዓመቱ እንዲካሔድ አስችሏል።
    • የበዓሉ አከባበር በፌደራል መንግሥት ደረጃ እንዲከበር ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል።
    • ከ120 ዓመታት በፊት መቀሌ ከተማ በሚገኘው የእንዳየሱስን ምሽግ ለማስለቀቅ ከጣሊያን ጦር ጋር ሲዋጉ ሕይወታቸው ያለፉ ጀግና ኢትዮጵያውያን አጽም የትም ተበታትኖ በመቅረቱ፥ ጉዞ ዓድዋ በአሁኑ ሰዓት የቦታው አስተዳዳሪ የሆነውን የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በማንቃት፤ የካቲት 26 ቀን 2008 ዓ. ም አጽማቸውን አሰባስቦ በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል። ከዚህም ባሻገር በዓመቱ የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ወጪ “የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን መታሰቢያ ሙዚየም” የተሰኘ ጣራ አልባ ቤተ መዘክር በእንዳየሱስ ታሪካዊ ምሽግ ላይ ተገንብቶ ለመመረቅ በቅቷል።
    • የዓድዋ ጦርነት መንስዔ የሆነው የዉጫሌ ውል የተፈረመበት “ይስማ ንጉሥ” የተባለው ታሪካዊ ቦታ ተከልሎ ጥበቃ እንዲደረግለት በማድረግ ጉዞ ዓድዋ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ከዚህም በተጨማሪ ውሉ በተፈረመበት ዕለት ሚያዝያ 25 ቀን በየዓመቱ፤ ምሁራዊ ተዋስዖ የሚደረግባቸው መድረኮች በመፍጠር፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት ባበረከተው የላቀ አስተጽዖ የአምባሰል ወረዳ የዓድዋ ድልን ለመዘከርና ቦታውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ያለመቋሚ ቤተ መዘክር በቦታው ላይ እንዲገነባ የሚያስችል የ19 ሚልዮን ብር የበጀት ድጋፍ ከአማራ ክልል መንግሥት እንዲያገኝ ጉዞ ዓድዋ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
    • ለበርካታ ዓመታት አገልግሎቱ ተዘግቶ የቆየው በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የትውልድ መንደር “አንጎለላ” የሚገኘው የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ መታሰቢያ ክሊኒክ እንዲከፈት ከፍተኛ ቅስቀሳ በማድረግ፤ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድጋፍ ክሊኒኩ ታዳጊ የጤና ጣቢያ ሆኖ በድጋሚ አገልግሎት እንዲሰጥ ጉዞ ዓድዋ አስተዋጽዖ ካደረጉ መካከል ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውቷል።
    • የዓድዋ ጀግና የሆኑት ራስ አሉላ አባ ነጋ የቀብር ቦታ በሆነው የአባ ገሪማ ገዳም ውስጥ ለሁለቱም ጾታዎች ጉብኝት ምቹ በሆነ ቦታ ላይ ሐውልት እንዲቆምላቸው ጉዞ ዓድዋ ባመቻቸው ዕድል በአንድ ባለ ሀብት ሐውልታቸው ተሠርቶ ለምረቃ በቅቷል።
    • በየዓመቱ በሚካሔዱ ጉዞዎች ከዓድዋ ድል ጋር ግንኙነት ያላቸው ቦታዋችን እና ልዩ ታሪካዊ መረጃዎችን በምስል እና በጽሑፍ በመሰብሰብ ለጥናትና ምርምር አስተዋጽዖ ማበርከት የሚችሉ የታሪክ ግብዓቶችን በማደራጀት በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በተለይም የማኅበራዊ ድረ ገጽን በመጠቀም ቅርሶችን የማስተዋወቅና የመጠበቅ ሥራዎችንበ መሥራት ላይ ይገኛል።

    የጉዞ ዓድዋ ማኅበር የዓድዋ ድል በዓል በኢትዮጵያውያን እንዲሁም በጥቁር አፍሪካውያን ዘንድ የሚገባውን ክብር እንዲያገኝ ላደረገው ጥረት፣ ከላይ ለተጠቀሱት እና በየዓመቱ በሚያደርጋቸው እጅግ አመርቂ ክንዋኔዎች ምክንያት በ2009 ዓም በቅርስና ባሕል ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ተሸላሚ ሆኗል።

    ላይ የሚሳተፉ ተጓዦች በጉዞአቸው ላይ የሚያደርጓቸውን የተለያዩ ክንዋኔዎችና የሚዘግቧቸውን ታሪክ ተኮር ዘገባዎች ለመከታተል የማኅበሩን የፌስቦክ ገጽ ይጎብኙ።

    ◌ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በደብረ ብርሃን ከተማ ሃውልት ሊቆምላቸው ነው

    ምንጭ፦ በጎ ሰው ሽልማት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ጉዞ ዓድዋ


    Semonegna
    Keymaster

    የከተማዋን የቱሪዝም ዕድገት ከፍ ለማድረግ የዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ምኒልክ ሃውልቶችን የከተማ አስተዳደሩ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ያስገነባል። ስለሆነም የሁለቱ ታላላቅ መሪዎች ሃውልት በከተማዋ እንዲቆም እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ከ6 መቶ ዓመታት በላይ ባስቆጠረችው የድሮዋ ደብረ ኤባ የዛሬዋ ደብረ ብርሃን ከተማ ለዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ሃውልት ሊቆምላቸው እንቅስቃሴ መጀመሩን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

    የከተማዋ ምክትል ከንቲባ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃን ገብረሕይወት ጥር 9 ቀን 2011 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ በሰጡት መግለጫ ደብረ ብርሃን ከተማን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ እየሠራ ነው፤ ከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግም ከተማ አስተዳደሩ ባዛሮችን በተለያዩ ጊዚያት እንደሚያካሂድ ተገልጿል።

    የከተማዋን የቱሪዝም ዕድገት ከፍ ለማድረግ የዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ምኒልክ ሃውልቶችን የከተማ አስተዳደሩ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ያስገነባል። ስለሆነም የሁለቱ ታላላቅ መሪዎች ሃውልት በከተማዋ እንዲቆም እንቅስቃሴ እየተደረገ ነውም ተብሏል።

    ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ በከተማዋ ለሚኖሩ ዜጎች የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን ፈጥሯል

    ከተማ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየሠራ እንደሆነም አስታውቋል። ደብረ ብርሃን ከተማ በዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ መመሥረቷ ይታወቃል።

    አጼ ዘርአ ያዕቆብ

    አጼ ዘርአ ያዕቆብ በዘውድ ስማቸው ቆስጠንጥንዮስ ከአባታቸው ቀዳማዊ ዳዊት እና ከእናታቸው ንግስትክብረ እግዚ እ.ኤ.አ. በ1399 ከአዋሽ ወንዝ አጠቀብ ትገኝ በነበረው ትልቅ ተብላ በምትጠራው መንደር የድሮው ፈታጃር ክፍለ ሀገር ተወለዱ። የነገሡበትም ዘመን እ.ኤ.አ. ከ 1434 እስከ 1468 (እስከሞቱበት ጊዜ) ነበር። ያረፉትም በደጋ ደሴት፣ ጣና ሃይቅ ነው።

    ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ

    ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ከአባታችው ከሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴና ከእናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አድያም እ.ኤ.አ. ነሐሴ 17 ቀን 1844 ደብረ ብርሃን አካባቢ አንጎለላ ከሚባል ሥፍራ ተወልደው፤ በአንጎለላ መቅደላ ኪዳነ ምኅረት ቤተ ክርስቲያን ክርስትና ተነሱ። የነገሡበትም ዘመን እ.ኤ.አ. ከ 1889 እስከ 1913 (እስከሞቱበት ጊዜ) ነበር። ያረፉትም ተዓካ ነገሥት ለማርያም ወደብረ መንክራት ስዕል ቤት ኪዳነ ምኅረት ገዳም (አዲስ አበባ) ነው።

    ምንጭ፦ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ሃውልት


Viewing 15 results - 1 through 15 (of 19 total)