ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲውን አውከዋል ባላቸው ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ

Home Forums Semonegna Stories የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲውን አውከዋል ባላቸው ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ

#13406
Anonymous
Inactive
  • ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲውን የመማር-ማስተማር ሥራ አውከዋል ባላቸው 21 ተማሪዎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ወሰደ።
  • ዩኒቨርሲቲው “ንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል ደማቅ የኪነ ጥበብ ምሽት አካሂዷል።

ባሕር ዳር (ሰሞነኛ) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን በማወክ በተለዩና ተጨባጭ ማስረጃ በተገኘባቸው 21 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ። በዩኒቨርሲቲው አንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ሙሉ በሙሉ መጀመሩንም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል።

የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ፥ አራት ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት መታገዳቸውን እና በ21 ተማሪዎች ላይ ደግሞ ከአንድ ዓመት እገዳ ጀምሮ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል። ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት በመለየትና በማጣራት በቀጣይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ከመማር-ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን ተማሪዎችን በሥነ ምግባር በማነጽ ችግር ፈቺ ሆነው እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባም ዶ/ር ዘውዱ ተናግረዋል።

ባለፉት ሳምንታት ተማሪዎች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ተደጋጋሚ ውይይትና ምክክር ቢደረግም ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በፖሊ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ፔዳና ይባብ ግቢዎች ትምህርት ተቋርጦ እንደነበር ተዘግቧል።

ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳንወጣ፥ በዩኒቨርሲቲው ፔዳ ግቢ አዳራሽ “ንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲዉ ተማሪዎች፣ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ደማቅ የኪነ ጥበብ ምሽት ተካሂዷል።

የኪነ ጥበብ ምሽቱን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲዉ የዉስጥ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ አክሎግ፥ በተማሪዎች አነሳሽነት እና በባህል ማዕከሉ ተባባሪነት ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን አመስግነዉ፤ መሰል ዝግጅቶች በሚኖሩበት ጊዜ የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንደማይለያቸዉ ጠቁመዋል። አክለዉም፥ የዉጭ ሀገራት ተሞክሮዎችን በመጥቀስ መሰል የኪነ ጥበብ ፕሮግራሞች በተማሪዎች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩ መዘውተር አለባቸው ብለዋል።

በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዉ ለታዳሚዎች አነቃቂ ንግግር ያደረጉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዉ የሳይኮሎጅ መምህር አቶ ታምሩ ደለለኝ እንደተናገሩት፥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁለት ዋነኛ ችግሮችን ሊያስቡባቸው ይገባል ብለዋል። አንደኛው ስብዕናና ክህሎት በማይገነቡ ጊዜያዊ እርካታ ላይ በሚያተኩሩ ክዋኔዎች ለምሳሌ ቲሸርቶችን እያሳተሙ የቀለም ቀን (Color Day)፣ የሕፃናት ቀን (Baby Day)፣ የውሃ ቀን (Water Day) ወይም ሌሎች የመሳሰሉት ላይ ማተኮር ሲሆን፤ ሌላው እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣው ደግሞ ሰክኖ ከመወያየት ይልቅ አለመግባባትና ግጭት በስፋት መከሰት ናቸው። ከአለመግባባት እና ግጭት ጋር በተያያዘም ተማሪዎች በዙሪያቸው ያሉ ሌሎች ተማሪዎችን እንደ ተማሪ እንዲመለከቷቸውና እርስ-በእርስ እንዲተሳሰቡ መክረዋል። አቶ ታምሩ በመቀጠልም ተማሪዎች ትዕግስትና ማስተዋልን አጥብቀዉ በመያዝ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን ተጨማሪ ስንቅ የሚያገኙበት እንዲሆን እንዲያደርጉት አሳስበዋል።

በኪነ ጥበብ ምሽቱ “የንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በጎ ሀሳብ አፍላቂ ተማሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን በቀጣይም መሰል ፕሮግራሞች በየ 3 ሳምንቱ እንደሚካሄዱ የዩኒቨርሲቲዉ የተማሪዎች ባህል ማዕከል ኃላፊ ተማሪ ተመስገን ሙሉቀን ተናግረዋል። በኪነ ጥበብ ምሽቱ በርካታ ታዳሚያን የተገኙ ሲሆን፥ በበመርሃ-ግብሩ መደሰታቸዉን ለመረዳት ተችሏል።

በኪነ ጥበብ ምሽቱ በርካታ የግጥም ሥራዎችን ጨምሮ ‘በቃን’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ አዝናኝና አስተማሪ ጭዉዉት አንዲሁም ‘ከኛ ጓዳ’ የተሰኘ ተከታታይ የኮሜድ ሥራ ቀርቧል።

ምንጮች፦ ፋና/ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ