የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች

Home Forums Semonegna Stories የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች

Viewing 15 posts - 16 through 30 (of 56 total)
  • Author
    Posts
  • #13250
    Semonegna
    Keymaster

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጥፋት ፈፅመው በተገኙ 77 ተማሪዎች ተማሪዎች ላይ ዛሬ እርምጃ ወሰደ

    ሐረማያ (ሰሞነኛ) – ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰኑት የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ መማር ማስተማርን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ችግሮች እንደጋጠማቸው ይታወቃል። በተለይ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለምንም ምክንያት ውድ የሆነው የሰው ሕይወት በሚያሳዝን ሁኔታ ጠፍቷል።

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ይህ እንዳይሆን ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ ቅንጅት በማድረግ ሲሠራ በመቆየቱ የሰው ሕይወት ባያልፍም የጥፋት አላማን አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጥቂት ተማሪዎች ግን ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲታወክ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ ህልውናን ጭምር አደጋ ውስጥ በመክተት የጥፋት ተልዕኮአቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። እነዚህ ለጥፋት የተሰማሩ ተማሪዎች ከጥፋታቸው እንዲመለሱና እንዲታረሙ ተደጋጋሚ ምክርና ጊዜ የተሰጣቸው ቢሆንም ከጥፋታቸው ሊታረሙ አልቻሉም።

    በመሆኑም የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ መማር ማስተማርን ለማስቀጠል እንዲቻል በተለያዩ ጊዜያት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራው እንዲስተጓጎል ምክንያት በሆኑ 77 ተማሪዎች ላይ እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን ለእርምጃው መወሰድ ምክንያቶች በዋናነት የሚከተሉትን ያካትታል፦

    • በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዳይኖር በተደራጀ ሁኔታ ሰላማዊ ተማሪ ላይ ጥቃት በማድረስ፣ ሕገ-ወጥ ሰልፍ በማደራጀት እና መማር ማስተማር እንዳይካሄድ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመፍጠር፣
    • በቡድን ተደራጅተው በማንነት ላይ የተመሠረተ ጥቃት ማድረስ ፣ የማሸማቀቅ እና የማስፈራራት ተግባርን በመፈፀም፣
    • በሕገ-ወጥ ሰልፍ በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ውድመት ማድረስ፥ ለምሳሌ፡- ታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ተቋም 3 (ሦስት) ተሸከርካሪዎችን አውድመዋል፤ የባንክ ኤቲኤም (ATM) ማሽን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ አድርገዋል፤ ዩኒቨርሲቲው ላይም ከፍተኛ ውድመት እንዲከሰት እሳት አቀጣጥለዋል።
    • የብሔር ግጭት የሚቀሠቅሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ንግግሮችን በማጉላት በተማሪዎች መሀከል የስጋት ድባብ እንዲነግስ ማድረግ እና ብሔርን መሠረት አድርጎ ተማሪን በመከፋፈል ትምህርት አቋርጠው እንዲበተኑ ማድረግ ይጠቀሳል።

    በዚሁ መሠረት ሰላማዊ ተማሪዎችን ሕይወት ለመጠበቅና ሰላማዊ የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማስቀጠል ሲባል እርምጃ ከተወሰደባቸው አጥፊ ተማሪዎች መካከል 2 (ሁለቱ) ሙሉ ለሙሉ እንዲሰናበቱ የተደረገ ሲሆን 75 ተማሪዎች ደግሞ ለ2 (ሁለት) ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ ተወስኗል።

    በተጨማሪም ሁለት መምህራን ተማሪዎችን በማስኮብለል ድርጊት ላይ ተሳትፈው በመገኘታቸው በደመወዝ ቅጣትና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

    ዩኒቨርሲቲው ድብቅ ዓላማን አንግበው በተለያዩ ማደነጋገሪያ ሽፋኖች የሚንቀሣቀሱ እና ተቋሙ የጥፋት ዓላማዎች ማራመጃ ሜዳ እንዲሆን ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚሠሩ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ በቀጣይ የማጣራት ሥራ የሚሠራ ሲሆን፥ እንደጥፋታቸው ደረጃ እና ጥልቀት ሕጋዊ እና ተቋሟዊ እርምጃ ለመውሰድ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ እያሳወቅን፥ ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው እና የሀገራቸው እና የዩኒቨርሲቲያቸው ሰላም የሚያሳስባቸው የአስተዳደር፣ ፀጥታ እና ማኅበረሰብ አካላት እንደተለመደው ከዩኒቨርሲቲው ጐን እንዲቆሙ በአክብሮት እንጠይቃለን። በተጨማሪም የተማሪ ቤተሰቦች ልጆቻችሁን በመምከር እንድታግዙን ዩኒቨርሲቲው ጠይቋል።

    ምንጭ፦ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ


    #13261
    Semonegna
    Keymaster

    በጋሞ ዞን ገረሴ ወረዳ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ የከበሩ ማዕድናት መገኘታቸውን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

    አርባ ምንጭ (አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ) – የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኤጀንሲ ጋር በ2010/11 በጀት ዓመት በጋሞ፣ በወላይታና በኮንሶ ዞኖች ያካሄደውን የማዕድን አለኝታ ጥናት ውጤት ታህሳስ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ለባለድርሻ አካላት ይፋ አድርጓል። በመርሀግብሩ ላይ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋሞ ዞን ገረሴ ወረዳ ከተሌ ቀበሌ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ የከበሩ ድንጋዮችና ማዕድናት መገኘታቸውን አስታውቋል።

    በክልሉ የሚገኘውን ማዕድን በዓይነት፣ በመጠንና በቦታ ለይቶ ለክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ለማሳወቅ ጥናቱ መከናወኑን የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ተናግረዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና የጥናት ቡድኑ አባል ረዳት ፕሮፈሰር ጎሳዬ ብርሃኑ እንደገለጹት፥ ጥናቱ በዋናነት ለሴራሚክ ኢንዱስትሪ የሚውሉ የከበሩ ድንጋዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ ባለሙያዎችን ባካተቱ 5 ቡድኖች ለ1 ዓመት ያህል የተከናወነ ሲሆን በጥናቱም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው “aquamarine”፣ “tourmaline” እና “garnet” የተሰኙ የከበሩ የድንጋይ ናሙናዎች እንዲሁም “feldspar” ማዕድን ውጤታማ ግኝት ተመዝግቧል። “Feldspar” ማዕድን ለሴራሚክ እና ብርጭቆ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን ማዕድን ሲሆን በአካባቢው ከ101 ሚሊየን ቶን በላይ ክምችት እንዳለ በጥናቱ ታውቋል።

    የአካባቢው ወጣቶች በመደራጀት አካፋ፣ ዶማና የመሳሰሉትን ባህላዊ መሣሪያዎች ተጠቅመው በተለይም “aquamarine” የተባለውን ማዕድን እያወጡ መሆኑን የጠቀሱት ረዳት ፕሮፈሰር ጎሳዬ፥ ይህም የማዕድኑን ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ነው ብለዋል። ማዕድናቱ ጥራታቸውን እንደጠበቁ እንዲወጡ የሚመለከተው አካል ለወጣቶቹ ሥልጠና ቢሰጥ መልካም መሆኑን ተናግረዋል።

    በጥናቱ የማዕድናቱ መገኛ፣ ጥራትና ክምችት በሚገባ የተዳሰሰ በመሆኑ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አዋጭ የማውጫ ዘዴ በመለየት ማዕድናቱ የሚወጡበትን ሁኔታ ቢያመቻች ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቅምና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ረዳት ፕሮፈሰር ጎሳዬ ገልጸዋል።

    የምርምር ውጤቱን የማኀበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እና የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዩኒቨርሲቲውን ወክለው ለኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኤጀንሲ ተወካይና ለደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አስረክበዋል።

    ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

    #13311
    Anonymous
    Inactive

    በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተፈጠረው የሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ከ640 በላይ ተማሪዎች፣ 40 መምህራን እና ከ240 በላይ የአስተዳደር ራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸው ተገለጸ

    አዲስ አበባ (ኢብኮ) – ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በነበሩ ከ640 በላይ ተማሪዎች፣ 40 መምህራን እና ከ240 በላይ የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች እንደተወሰደ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።

    በዩኒቨርሲቲዎች በተፈጠረ የሰላም እጦት 35 ሺህ ተማሪዎች ትምህርት ጥለው መውጣታቸውን የገለጸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፥ እነዚህን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል። የተማሪዎችን አደረጃጀት በኅብረ ብሔር ለማሰባጠር መታሰቡንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎች ሰላም ባጡባቸው ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ አካላት ጋር ግምገማ እና ምክክር እያደረገ ይገኛል።

    በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለማጣራት የተዋቀረው ኮሚቴ ባደረገው የመስክ ምልከታ ያዘጋጀው ሪፖርት በመድረኩ ላይ ቀርቧል። በቀረበው ሪፖርትም የዩኒቨርሲቲዎች የሰላም መታወክ የፖለቲካ አመራሮች ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንዳለ ተገልጿል።

    በተለያዩ ክልሎች ባሉ የተለያዩ የፖለቲካ አመራሮች የሚወጡ መግለጫዎች እና ከግቢ ውጭ ተማሪዎችን ሰብስቦ ተልእኮ የመስጠት ሥራዎች ለመማር ማስተማሩ መታወክ እንደ አንድ ምክንያት ተጠቁሟል። ተልእኮ የተቀበሉ ተማሪዎች መማር የሚፈልጉ ተማሪዎች ላይ የሥነ ልቦና፣ አካላዊ፣ የሕይወት እና ንብረት ጉዳት በማድረስ ግጭት እንደሚያነሳሱም ተጠቁሟል። በሚዲያዎች፣ በሶሻል ሚዲያዎች እና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተጋነኑ እና የተዛቡ መረጃዎች መሰራጨት፣ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ችግሮችን ውጫዊ ማድረግ ወይም ቸልተኝነትም ሌላው ለዩኒቨርሲቲዎች የሰላም እጦት የተነሣ ተግዳሮት ነው። በዩኒቨርሲቲዎች ያለው በቤተ ዘመድ የተሳሳበ የሠራተኛ አደረጃጀት እንዲሁ እንደ አንድ ችግር ተጠቅሷል።

    ችግር የፈጠሩ እና ምንም ዓይነት የሕግ እርምጃ ሳይወሰድባቸው በነፃ የሚለቀቁ እና እንዲማሩ የሚፈቀድላቸው ተማሪዎችም በዩኒቨርሲቲዎች ለሚታየው የሰላም እጦት ሌላው ምክንያት መሆናቸው ተጠቁሟል።

    በዩኒቨርሲቲ አመራሩ በኩል ውጫዊ ማስፈራሪያዎችን በመፍራት ውሳኔ ሰጭነት ላይ የሚታየውን ማፈግፈግ እንዲሻሻል እና ጠንካራ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተገልጿል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዩኒቨርሲቲዎች የሰላም እጦት

    #13337
    Anonymous
    Inactive
    • በሥራ ላይ ያለው ሥርዓተ-ትምህርት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በአዲስ ሥርዓተ-ትምህርት ይቀየራል።
    • በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ይበልጥ ተቀናጅቶ መሥራት አስፈላጊ ነው።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በአዲስ ሥርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የሚያስችሉ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

    በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው በጉዳዩ ዙሪያ በተዘጋጀ የባለሙያዎች ምክክር መድረክ ላይ እንደገለፁት ከ2012-2014 የትምህርት ዘመን በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የአስር ዓመታት ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቷል።

    በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት መቀየር ያስፈለገው በፍኖተ ካርታው ምክረ-ሃሳቦች መሠረት ችግሮች ስላሉበት ነው። በመሆኑም በመጭዎቹ ዓመታት በአዲስ የሚተካው ሥርዓተ-ትምህርት የተማሪዎችን ሥነ-ምግባር ጨምሮ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈታ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቃዋል።

    በአውደ-ጥናቱም ከሀገሪቱ ሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የትምህርት ቢሮ ባለሙያዎች፣ የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ሃላፊዎች፣ ከሁለተኛና ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራን፣ የመምህራን ኮሌጆችና ከአምስቱ የመምህራን ማሰልጠኛ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎችም ባለድርሻዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

    በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ወርቁ በበኩላቸው ሥርዓተ-ትምህርቱ እየተዘጋጀ ያለው ከፍኖተ ካርታው በተገኙ ምክረ ሃሳቦችና ጥቆማዎች (recommendations an suggestions) እንዲሁም የካንብሪጅ ኢንተርናሽናል አሰስመንትን (Cambridge Assessment International Education) ጨምሮ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻዎች በተገኙ ምክረ ሃሳቦችና ተጨማሪ አስተያየት መሠረት ነው።

    በምክክር መድረኩም የሥርዓተ-ትምህርት ማዕቀፍ፣ የእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት መርህ አቅጣጫ (position papers) እና ሌሎችም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ሰለሞን መግለፃቸውን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።

    ከሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ደግሞ፥ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ይበልጥ ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት፣ ከሌሎች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር በዘርፉ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሒዷል።

    በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም “በዘርፉ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን በተሟላ ሁኔታ ተተገብረው ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባር የተላበሱ ምሩቃን አፍርተን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን እያለፍን የሀገራችንን የማስፈጸም አቅም በመገንባት በብልጽግና ከፍታ ላይ ለማድረስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን እንሠራለን” ብለዋል።

    ሚኒስቴሩ በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ላይ የተቀመጡ ምክረ ሐሳቦችን መነሻ በማድረግ በነባሩ የትምህርት ሥርዓት ላይ ያለውን ጉድለት ለመሙላት እና ለማሻሻል አዳዲስ የለውጥ ኃሳቦችን በማካተት ከ2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ትግበራ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፥ ከነዚህም መካከል የከፍተኛ ትምህርትን ሥርዓተ ትምህርት የማሻሻል፣ የትምህርት አሠጣጥ ሥነ-ዘዴዎቹንና የትምህርቶቹንም ይዘት የመከለስና የኮርስ ካታሎግ (course catalog) የማዘጋጀት፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችንን በተልዕኮና በልህቀት ለይቶ የማደራጀት እንዲሁም አዳዲስ የሕግና የአሠራር ማዕቀፎችን የማውጣትና ነባሮቹንም የመከለስ ሥራዎች ይገኙበታል ብለዋል።

    እንደ ፕሮፌሰር ሂሩት ገለፃ፥ የምክክር መድረኩ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ሚኒስቴሩ በሚያከናውናቸው የለውጥ ሥራዎች ላይ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ስለሚያምንና በተለይም በቂ ግንዛቤ ያለውና የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ለለውጥ ሥራዎቻችን ስኬት ቁልፍ ስለሆነ ነው ሲሉ አስቀምጠዋል።

    ለሁለት ቀናት በቆየው የምክክር መድረክ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጉዳዮች፣ በፍኖተ ካርታ ምክረ-ሃሳብ መሠረት በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሴክተር የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ እንዲሁም በሰላማዊ መማር ማስተማር ዙሪያ የተሠሩ አንኳር ሥራዎች፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል።

    በመጨረሻም የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የልህቀት ማዕከል የሥራ እንቅስቃሴን የሚጎበኙ ይሆናል።

    ምንጮች፦ የትምህርት ሚኒስቴር/ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    ሥርዓተ-ትምህርት

    #13341
    Semonegna
    Keymaster

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) በትብብር ለመሥራት ስምምነት አደረገ

    ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አሜሪካን ሀገር ካምብሪጅ ከተማ ከሚገኘው ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) ከተሰኘው ዕውቅ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረመ።

    ሁለቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡትን ውል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችላቸውን የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች ማከናወንም ጀምረዋል።

    በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ሐብቴ ዱላ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ጋር የሚኖረው የትብብር ሥራ በዋናነት በኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ የሚሰጡትን የትምህርት ፕሮግራሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ የቤተ-ሙከራ ትምህርት ለማስደገፍ የሚያስችልና በመምህራንና በተማሪዎች የሚሠሩትን የምርምር ሥራዎች እና ፕሮጀክቶች ውጤታማነት ለማሻሻል ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

    እንዲሁም የትብብር ሥራው የኮሌጁን የመማር-ማስተማር ሥራ ለማዘመንና ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን ለማስጠበቅ የሚያግዘው ከመሆኑም ባሻገር በምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስኮች ለሚከናወኑ ሥራዎች ስኬታማነት የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ዶ/ር ሐብቴ አስረድተዋል።

    በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ኮርአብዛ ሸዋረጋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፥ ኢንስቲትዩቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በገባው ውል መሠረት በያዝነው የ2012 የትምህርት ዘመን ከሁለተኛው መንፈቀ-ዓመት /ሴሚስተር/ ጀምሮ ዓመታዊ ክፍያው ከ160 ሺህ በላይ የሆነውን የኦንላይን ትምህርት በነጻ በመስጠት የኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅን ተጠቃሚ ማድረግ ይጀምራል። ለዚህም ዕቅድ ተግባራዊነት ኢንሰቲትዩቱ ድጋፍ ሰጪ ቡድን ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በመላክ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።

    በዚህም መሠረት ድጋፍ ሰጪው ቡድን የኦንላይን ትምህርቱን ለመስጠት ወሳኝ የሆኑት የቤተ-ሙከራ ዕቃዎችን ይዞ በመምጣት ለዩኒቨርሲቲው በእርዳታ አበርክቷል። የተበረከቱት ዕቃዎች እስካሁን ድረስ በንድፈ-ሐሳብ /theory/ ብቻ ሲሰጡ የነበሩትን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ /artificial intelligence/፣ ሮቦቲክስ /robotics/ እና ተዛማጅ የትምህርት ዓይነቶች የማስተማር ዘዴ በተግባር የታገዘ አንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አቶ ኮርአብዛ ገልጸዋል።

    ድጋፍ ሰጪ ቡድኑ ለዩኒቨርሲቲው ያበረከታቸውን የቤተ-ሙከራ መሣሪያዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል ከኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅና ከኢንጅነሪንግና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ለተውጣጡ 10 መምህራን ከጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ያዘጋጀውን በኮምፒዩተር ፕሮግራም ቋንቋ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።

    በመጨረሻም ዶ/ር ሐብቴ አክለውም፥ ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመሥራት እንዲችሉ በማገናኘቱ ሥራ በአሜሪካ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሚና ከፍተኛ እንደነበረ በመግለፅ ይህንን የዜግነት ግዴታቸውን ለተወጡት የዲያስፖራ አባላት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እና በራሳቸው ስም አመስግነዋል።

    ምንጭ፦ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ

    #13406
    Anonymous
    Inactive
    • ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲውን የመማር-ማስተማር ሥራ አውከዋል ባላቸው 21 ተማሪዎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ወሰደ።
    • ዩኒቨርሲቲው “ንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል ደማቅ የኪነ ጥበብ ምሽት አካሂዷል።

    ባሕር ዳር (ሰሞነኛ) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን በማወክ በተለዩና ተጨባጭ ማስረጃ በተገኘባቸው 21 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ። በዩኒቨርሲቲው አንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ሙሉ በሙሉ መጀመሩንም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል።

    የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ፥ አራት ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት መታገዳቸውን እና በ21 ተማሪዎች ላይ ደግሞ ከአንድ ዓመት እገዳ ጀምሮ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል። ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት በመለየትና በማጣራት በቀጣይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

    የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ከመማር-ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን ተማሪዎችን በሥነ ምግባር በማነጽ ችግር ፈቺ ሆነው እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባም ዶ/ር ዘውዱ ተናግረዋል።

    ባለፉት ሳምንታት ተማሪዎች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ተደጋጋሚ ውይይትና ምክክር ቢደረግም ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በፖሊ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ፔዳና ይባብ ግቢዎች ትምህርት ተቋርጦ እንደነበር ተዘግቧል።

    ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳንወጣ፥ በዩኒቨርሲቲው ፔዳ ግቢ አዳራሽ “ንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲዉ ተማሪዎች፣ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ደማቅ የኪነ ጥበብ ምሽት ተካሂዷል።

    የኪነ ጥበብ ምሽቱን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲዉ የዉስጥ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ አክሎግ፥ በተማሪዎች አነሳሽነት እና በባህል ማዕከሉ ተባባሪነት ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን አመስግነዉ፤ መሰል ዝግጅቶች በሚኖሩበት ጊዜ የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንደማይለያቸዉ ጠቁመዋል። አክለዉም፥ የዉጭ ሀገራት ተሞክሮዎችን በመጥቀስ መሰል የኪነ ጥበብ ፕሮግራሞች በተማሪዎች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩ መዘውተር አለባቸው ብለዋል።

    በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዉ ለታዳሚዎች አነቃቂ ንግግር ያደረጉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዉ የሳይኮሎጅ መምህር አቶ ታምሩ ደለለኝ እንደተናገሩት፥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁለት ዋነኛ ችግሮችን ሊያስቡባቸው ይገባል ብለዋል። አንደኛው ስብዕናና ክህሎት በማይገነቡ ጊዜያዊ እርካታ ላይ በሚያተኩሩ ክዋኔዎች ለምሳሌ ቲሸርቶችን እያሳተሙ የቀለም ቀን (Color Day)፣ የሕፃናት ቀን (Baby Day)፣ የውሃ ቀን (Water Day) ወይም ሌሎች የመሳሰሉት ላይ ማተኮር ሲሆን፤ ሌላው እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣው ደግሞ ሰክኖ ከመወያየት ይልቅ አለመግባባትና ግጭት በስፋት መከሰት ናቸው። ከአለመግባባት እና ግጭት ጋር በተያያዘም ተማሪዎች በዙሪያቸው ያሉ ሌሎች ተማሪዎችን እንደ ተማሪ እንዲመለከቷቸውና እርስ-በእርስ እንዲተሳሰቡ መክረዋል። አቶ ታምሩ በመቀጠልም ተማሪዎች ትዕግስትና ማስተዋልን አጥብቀዉ በመያዝ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን ተጨማሪ ስንቅ የሚያገኙበት እንዲሆን እንዲያደርጉት አሳስበዋል።

    በኪነ ጥበብ ምሽቱ “የንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በጎ ሀሳብ አፍላቂ ተማሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን በቀጣይም መሰል ፕሮግራሞች በየ 3 ሳምንቱ እንደሚካሄዱ የዩኒቨርሲቲዉ የተማሪዎች ባህል ማዕከል ኃላፊ ተማሪ ተመስገን ሙሉቀን ተናግረዋል። በኪነ ጥበብ ምሽቱ በርካታ ታዳሚያን የተገኙ ሲሆን፥ በበመርሃ-ግብሩ መደሰታቸዉን ለመረዳት ተችሏል።

    በኪነ ጥበብ ምሽቱ በርካታ የግጥም ሥራዎችን ጨምሮ ‘በቃን’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ አዝናኝና አስተማሪ ጭዉዉት አንዲሁም ‘ከኛ ጓዳ’ የተሰኘ ተከታታይ የኮሜድ ሥራ ቀርቧል።

    ምንጮች፦ ፋና/ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

    #13437
    Anonymous
    Inactive

    የተሻሻለው የወሎ ቴሪሸሪ የህክምናና የማስተማሪያ ሆስፒታል ዲዛይን ለሕዝብ ይፋ ሆነ

    ደሴ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – በጥቂት ሀገር ወዳድ ግለሰቦች ሀሳቡ ተጠንስሶ ሀገራዊ የሕዝብ ፕሮጀክት የሆነው የወሎ ልዕለ ህክምና የማስተማሪያ ሆስፒታል /ሦስተኛ ትውልድ ሆስፒታል/ (Wollo Tertiary Care and Teaching Hospital) ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በየጊዜው እየፈታ ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ተዳርሷል።

    ይህንን የሕዝብ ፕሮጀክት ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ያለ በጀትና ዲዛይን በባለቤትነት የተረከበው ወሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሥራ ለመግባት ከሕዝብ የተሰበሰበውን በጀትና ዲዛይን ሊያስረክብ የሚችል አካል በመጥፋቱ ተቸግሮ ቆይቷል።

    ዩኒቨርሲቲው የሕዝቡ ፍላጎትና ጥያቄዎች እየተበራከቱ ሲመጡበት የዋና ሆስፒታል ዲዛይን መረከብ እስኪችል ድረስ በራሱ ወጭ በ460 ሚሊዮን ብር የተማሪዎች መኖሪያ G+4 10 ህንጻዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል።

    የሆስፒታሉን ዲዛይን የተረከበው አማካሪ ድርጅት ሰርቶ ማቅረብ ባለመቻሉ በ2011 ዓ.ም. አጋማሽ ዩኒቨርሲቲው ውለታውን በማቋረጥ ከአዲሱ የኤምቲቲ አማካሪ አርክቴክቶችና ምህንድስና ኃ/የተ/ የግል ኩባንያ (MTT Consulting and Architects and Engineers PLC) ድርጅት ጋር ውለታ በመፈጸም ዲዛይኑን ለአዲሱ ድርጅት አስረክቧል።

    የኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት የተረከበው ዲዛይን ከዓለም የቴክኖሎጅ እድገትና ከዘመኑ የኪነ ህንጻ ጥበብ ጋር ሊዛመዱ በማይችሉ የመዋቅር፣ የኤሌክትሮ መካኒክ፣ የፍሳሽ ማስወገጃና መሰል በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት በመሆኑ የዲዛይን ማሻሻያዎችን ሠርቶ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

    የኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት የሆስፒታሉን ዲዛይን ከማሻሻሉም ባሻገር የሆቴል ቱሪዝምን ለማበረታታት ባለ 5 ኮኮብ ሆቴል፣ የባሕላዊ ህክምና መስጭያ ማዕከልና ከአካባቢው ባህልና ሥነ-ምህዳር ጋር የሚዛመዱ ተያያዥ ማዕከላትን የሆስፒታሉ አካል እንድሆኑ በማካተት ይፋ አድርጓል።

    ይህንን ይፋ የሆነ የሆስፒታል ዲዛይን የተመለከቱት የደሴ ከተማ የሕዝብ ተወካዮች፣ የዘርፉ ባለሞያዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለሙያዎች በተሻሻለው ዲዛይን ላይ የተሰማቸውን ስሜት በመግለጽ ቢካተቱ ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል።

    የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን ዋናውን ሆስፒታል ወደ መሬት ለማውረድ ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች በመጥቀስ ዩኒቨርሲቲው የሕዝብን ስሜት ለመጠበቅ በራሱ የተጓዘውን ርቀት አብራርተዋል። ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ከሕዝብ የተሰበሰበውን አምስት ሳንቲም እንኳን እንዳልተረከቡ በመግለጽ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ አማካሪው ኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት የሀሳቡ ጠንሳሽ ዶ/ር በላይ አበጋዝን ጨምሮ በጤና ሚኔስተርበአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲበጥቁር አንበሳና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ያሉ የዘርፉ ምሁራንን በማሳተፍ ሆስፒታሉ እውን እንድሆን ለተሠራው ሥራ አመስግነዋል።

    የኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት በበኩሉ በሕዝብ የተነሱትን ጥያቄዎችና አስተያየቶች በማካተት ፕሮጀክቱ ወደ መሬት በቅርብ ቀን እንዲወርድ የቻለውን ሁሉ እንደሚሠራ ቃል ገብቷል።

    ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የወሎ ልዕለ ህክምና የማስተማሪያ ሆስፒታል


    #13554
    Semonegna
    Keymaster

    “እኔ ለወገኔ” የወሎ ዩኒቨርሲቲ የበጎ አድራጎት ማኅበር በደሴ ከተማ ድጋፍ አደረገ

    በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተመሰረተው “እኔ ለወገኔ” ማኅበር ድጋፍ ለሚሹ አቅመ ደካሞችና ሕፃናት የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል። በቀጣይም አረጋውያንን በማዕከል በማሰባሰብ በቋሚነት የሚጦሩበትና የጎዳና ተዳዳሪ ወጣትና ሕፃናትን ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት በማስገባት ለማስተማር ይሠራል።

    ደሴ (ኢዜአ) – በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተመሠረተው “እኔ ለወገኔ” የበጎ አድራጎት ማኅበር ከ700 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው አልባሳትና ቁሳቁሶችን አቅመ ደካሞችና ለዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ ድጋፍ ለሚሹ የደሴ ከተማ ኗሪዎች ድጋፍ አደረገ። የማህበሩ አባላት በተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ያሰባሰቡትን ቁሳቁስ በከተማዋ ለሚኖሩ አቅመ ደካሞችና ሕፃናት አሰራጭተዋል።

    የማኅበሩ አባል ተማሪ አቡሽ ግርማ እንዳለው የዛሬ ሁለት ዓመት የተመሠረተው “እኔ ለወገኔ” ማኅበር ደሴ ከተማ እና በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካሞችንና ችግረኛ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማገዝ ሥራ ተሰማርቷል። በዚህም ተማሪዎች ከባለሃብቶች፣ ፋብሪካዎችና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በማሰባሰብና ጫማ በመጥረግ ሥራ የሚያገኙትን ገንዘብ በመቆጠብ ለ300 አቅመ ደካሞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ድጋፍ አበርትቷል። ድጋፉ የተደረገውም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ ብርድ ልብስ፣ አንሶላ እና ሌሎች አልባሳት የመሳሰሉት ናቸው። በቀጣይም አረጋዊያንን በማዕከል በማሰባሰብ በቋሚነት የሚጦሩበትና የጎዳና ተዳዳሪ ወጣትና ሕፃናትን ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት በማስገባት ለማስተማር እንደሚሠሩ ተናግሯል።

    ሌላው የ3ኛ ዓመት የሥራ አመራር (management) ተማሪ ምትኩ ደጉ በበኩሉ፥ ቁሳቁሱንና አልባሳቱን ማሰባሰብ የተቻለው የትምህርት ጊዜያቸውን በማይነካ መልኩ በመንቀሳቀስ ነው። የኢትዮጵያውያን አኩሪ እሴት ከሆኑት መካከል መረዳዳትና መደጋገፍ መሆኑን በሌሎች ተማሪዎች ዘንድ ለማስረጽ ማኅበር መሥርተው መንቀሳቀሳቸውን አስረድቷል።

    የወሎ ዩንቨርሲቲ አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አማረ ምትኩ በበኩላቸው፥ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የሚያደርጉት የተለያየ በጎ ተግባር የሚደነቅ ነው። ዩኒቨርሲቲዎች በግጭት በሚታመሱበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የማኅበሩ አባላት ተማሪዎች በአንድ ላይ ሕብረተሰቡን አስተባብረውና የሌሎችን ጫማ ጠርገው ደካሞችን መደጋገፋቸው አርአያነት ያለው ተግባር ነው ብለዋል። አያይዘውም ፕሬዚዳንቱ በትውልዱ እየተሸረሸረ የመጣውን መረዳዳት፣ መተዛዘን እና የተገኘውን ተካፍሎ የመጠቀም ተግዳሮቶች ምላሽ የሰጠ ሊበረታታና ሊስፋፋ የሚገባው መልካም ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል። በቀጣይም ተማሪዎቹ ለሚያከናውኑት መልካም ምግባር ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

    የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አቶ ጸጋዬ ቢያድግልኝ እንደ ገለጹት፥ ረዳትና ተንከባካቢ ቤተሰብ ስለሌላቸው አንድ ሱሪና ጃኬት ለብሰው ለዓመታት ኖረዋል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አማካኝነት ብርድ ልብስ፣ ሱሪ፣ ሸሚዝና ጃኬት በማግኘታቸው እየቀያየሩ በመልበስ ንጽህናና ጤንነታቸውን ለመጠበቅ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

    ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    እኔ ለወገኔ ወሎ ዩንቨርሲቲ

    #13607
    Anonymous
    Inactive

    ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 221 የህክምና ዶክተሮችና ስፔሻሊስቶችን አስመረቀ

    ሀዋሳ (ኢዜአ) – የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምንጮች ብቻ ሳይሆኑ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ማፍሪያ ማዕከላት ጭምር መሆን እንዳለባቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሳሰቡ።

    ዩኒቨርሲቲው የካቲት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በአጠቃላይ 221 የጤና ባለሙያዎችን (192 የህክምና ዶክተሮችና 29 ስፔሻሊስት ዶክተሮችን) አስመርቋል። ከተመራቂዎች ውስጥ 22 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውም ተጠቁሟል።

    በምረቃ በዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ እንደገለፁት፥ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ፣ በህክምና ስፔሻሊስትና በሦስተኛ ዲግሪ በርካታ የትምህርት መስኮችን (ፕሮግራሞችን) በመክፈት ከ43 ሺህ 800 በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት መርሀ ግብሮች እያስተማረ ይገኛል። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅም የመምህራን ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

    ሀገሪቱ ካላት ውስን ሀብት ላይ አንድ አራተኛውን በጀት ለትምህርት ማዋሏን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፥ ተመራቂዎችም ያላቸውን ዕውቀት፣ ክህሎትና ጉልበት ላስተማራቸው ማኅበረሰብ በማበርከት ለሀገራቸው ዕድገት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

    ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምንጮች ብቻ ሳይሆኑ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ማፍሪያ ማዕከላትም ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ተመራቂዎች ራሳቸውን ከመጥፎ ምግባር በመቆጠብና ሙያው በሚጠይቀው ሥነ-ምግባር ህሙማንን በፍቅር ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

    በምረቃ በዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ፕሮፌሰር በየነ እንዳሉት፥ ሀገሪቱ ባለፉት ሃያና ሰላሳ ዓመታት ውስጥ በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ እመርታ በማስመዝገብ የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ታላላቅ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና መንግሥታት ዕውቅና ማግኘቷን ተናግረዋል።

    ይሁን እንጂ አሁንም የጤና ሽፋንን ከመጨመርና ጥራትና ፍትሐዊነት ያለው አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚጠይቅ የተናገሩት ፕሮፌሰር በየነ፥ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ጠንክረን በጋራና በትብብር መንፈስ መሥራት አለብን ብለዋል። የዛሬ ተመራቂዎችም የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋዎች መሆናቸውን በመረዳት ሀገራቸውን ማገልገል እናዳለባቸው ጠቁመዋል።

    በሙያቸው ገፍተው ዕውቀትና ክህሎታቸውን በማዳበርም የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡና ችግር ፈቺ በሆኑ ምርምሮች ውስጥ በመሳተፍ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለውን ፈርጀ ብዙ ለውጥ የማቀጣጠልና የማስቀጠል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል ።

    ከተመራቂዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳልያ ተሸላሚ የሆነው ዶ/ር አቤል ጌታቸው በሰጠው አስተያየት፥ የህክምና ትምህርት ጽናትን የሚጠይቅ መሆኑን ገልፆ ሁኔታዎችን በትዕግስት በማለፍ ለዚህ መብቃቱን ተናግሯል።

    የህክምና ሙያ በራሱ ለሰዎች ክብር መስጠትና ርህራሄ መላበስን የሚያስተምር እንደሆነ የተናገረው ዶ/ር አቤል፥ ያለአድሎ ሰብዓዊነትን በመላበስ ህብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን አስረድቷል።

    በውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻላይዝድ በማድረግ የተመረቀው ዶ/ር ሙባረክ ሁሴን በበኩሉ፥ የህክምና ሥነ-ምግባር ከሀሳብ ይልቅ በተግባር የሚገለፅ መሆኑንና ታካሚዎችን እንደ ቤተሰብ በማየት ያለአድሎ ለማገልገል መዘጋጀቱን ተናግሯል።

    የዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ዶክትሬት ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ለ11ኛ ዙር ሲሆን ስፔሻሊስት ሀኪሞችን ደግሞ ለ4ኛ ዙር መሆኑ ተዘግቧል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 221 የህክምና ዶክተሮችና ስፔሻሊስቶችን አስመረቀ

    #13682
    Semonegna
    Keymaster

    አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና ዶክተሮችን አስመረቀ
    ጅማ ዩኒቨርሲቲ 3ሺህ 185 ተማሪዎችን መተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል

    አዳማ (ኢዜአ) – አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌና ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና ስፔሻልስቶችን ጨምሮ በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን 140 ዶክተሮችን የካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ። ከተመራቂዎቹ መካከል ደቡብ ሱዳን የሕክምና ስፔሻልስቶች ይገኙበታል።

    በምረቃው ሥነ ሥርዓት የተገኙት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋሽ ስሜ እንደገለጹት፥ በክልሉ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ካንሰርና ስኳርን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች (noncommunicable diseases) እየተስፋፉ መጥተዋል። በክልሉ በሚገኙ የመጀመሪያና ሪፌራል ሆስፒታሎች የሕክምና መሣሪያና መድኃኒትን ጨምሮ የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች እጥረት መኖሩንም ተናግረዋል።

    ለዚህም አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ግንባር ቀደም መሆኑን ጠቅሰው ኮሌጁ የሰው ሕይወት ለማዳን የሚያስችል እውቅትና ክህሎት ለማስታጠቅ ተግባር ተኮር ስልጠናና ምርምር ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባው አቶ ነጋሽ ጠቁመዋል። ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመተርጎም ማህበረሰቡን በማገልገል ምሳሌ መሆን አለባቸው ብለዋል።

    የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መኮንን ፈይሳ በማህፀን፣ በውስጥ ደዌ፣ በህፃናትና በከፍተኛ ቀዶ ሕክምና እንዲሁም በጠቅላለ ሐክም ስፔሻልስቶችን እያሰለጠነ ነው፤ ዛሬ ለምረቃ የበቁት 140 የሕክምና ዶክተሮች አሁን በስፋት የሚስተዋለውን አጣዳፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

    በተለይ በክልሉ የመጀመሪያ፣ ስፔሻላይዝድና ሪፌራል ሆስፒታሎች የሚታዩትን የማህፀን፣በውስጥ ደዌ፣ የህፃናትና ከፍተኛ ቀዶ ሕክምና ያለው የከፍተኛ ሙያተኞች እጥረት የሚፈታ ነው ብለዋል – ዶ/ር መኮንን።

    ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ለህብረተሰቡ የጠቅላላ ሕክምና አገልግሎት፣ መካከለኛና ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ሕክምና በመስጠት ሙያዊ ብቃታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ በማለት አስረድተዋል።

    አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ከ400 በላይ አልጋ ያለው፣ ማስፋፊያ ግንባታ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከላት፣የተማሪዎች መኖሪያና መመገቢያ ህንፃዎች ከአንድ ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በመገንባት ለአገልግሎት ዝግጁ አድርጓል።

    ከተመራቂዎቹ መካከል በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ዶ/ር አያንቱ በቀለ በሰጠችው አስተያየት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን አሳሳቢ እየሆነ ያለው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደሆነ ገልጻ ባገኘሁ እውቀት የድርሻዬን እወጣለሁ በማለት ተናግራለች።

    ከከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ምርቃት ጋር በተያያዘ፥ ጅማ ዩኒቨርሲቲ 3ሺህ 185 ተማሪዎችን መተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል። የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ በምረቃው ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት “ዛሬ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ሀገራችሁ ከእናንተ ከምንግዜውም በላይ እንድታገለግሏት ትፍልጋለች” ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ያስመረቀው ከስድስት ኮሌጆች፣ ሁለት ኢንስቲትዩቶች እና ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት በተለያዩ ሙያዎች ስልጠናቸው ነው። ከተመራቂዎቹ መካከል 834 ሴቶች እንዲሁም 11 የሱማሌላንድና የሩዋንዳ ዜጎች ይገኙበታል። ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወጣጡ አንድ መቶ ስልሳ ስምንት ሰዎችን እያስተማረ እንደሚገኝም ተመልክቷል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ

    #13838
    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ያወጣው ወቅታዊ የአቋም መግለጫ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ ለመወሰንና ለማስወሰን አንዳንድ ሀገራት የተዛባ ውሳኔ እንዲሰጥ ጫና ለመፍጠር እየጣሩ ይገኛሉ። በአንድ ወቅት ተመሳሳይ የተዛባ ውሳኔ በ League of Nations ሲተላለፍ እ.ኤ.አ. በ1949 የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የሚከተለውን ብለው ነበር፡-

    ሀገሬ ኢትዮጵያ በዓለም ሸንጎ ላይ ፍርድ ተነፍጓት ስታዝን የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ለነፃነቷና ለመብቷ ከኮሎኒያልስት ጣሊያን ጋር በየጊዜው ስትዋጋ ያሸነፈችውም ብቻዋን ነው። የተጠቃችውም ብቻዋን ስለሆነ ሀገሬ መቼውንም በሚደርስባት አደጋ ከማንም እርዳታ አገኛለሁ ብላ አትጠብቅም። ዛሬም ሆነ ነገ ነፃነቷን ለመጠበቅ ታሪኳን ለማስከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ያለባት እሷ ራሷ ብቻ ናት!

    እንዳሉት ሁሉ፥ አሁንም ያለን ትውልዶች የተዛባውን ሚዛን ማስተካከል ያለብን እኛው ነን። እናም የአድዋውን ድል በተባበረው የአያቶቻችን ክንድ እዳሸነፍነው ሁሉ የሕዳሴውንም ግድብ በተባበረው አንድነታችን፣ ክንዳችን እና ሀብታችን ሠርተን የምንጨርሰው መሆናችንን እያረጋገጥን እኛ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች አቋማችንን በጋራ ስንገልፅ መነሻ ያደረግነው፡-

    • የግድቡ መገንባት በአገሪቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ልዩነት እንደሌለው፣
    • ኮሎኒያሊስቶች አፍሪካን እና ሀብቷን ለመቀራመት አውጥተውት የነበረና አሁን የሚያፍሩበት እ.ኤ.አ. የ1929 እና የ1959 ኢትዮጵያ ባልተወከለችበት በተደረገ ስምምነት የሕግ ተገዥ የምትሆንበት ሕጋዊም ሆነ አመክኗዊ ነገር የሌለ መሆኑን፣
    • የሀገራችን ምሁራን በሠሯቸው ጥናቶች ግድቡ የሚገነባው ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ ባልሆነ ቦታ ከመሆኑም በተጨማሪ ውሀው ግብፅ ወይም ሱዳን ላይ ቢከማች ኖሮ በትነት የሚባክነውን ውኃ ስለሚያስቀር ተመራጭ የሚያደርገው መሆኑን ነው።

    ከዚህ በላይ በቀረበው መነሻነትም እኛ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ባለ ስድስት ነጠብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

    1. የጀመርነውን እውን ለማድረግ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምናደርግ እናረጋግጣለን።
    2. የሕዳሴው ግድብ የአንድነታችን ተምሣሌት በመሆኑ በዘር፣ በኃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይኖር የመንግሥትን አቋም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደግፍ እንጠይቃለን።
    3. እኛ ጠግበን በብርሃን እየኖርን እናንተ በረሃብና በጨለማ ኑሩ የሚል ራስ ወዳድ አስተሳሰብን በፅኑ እናወግዛለን።
    4. እኛ የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውን የየድርሻቸውን እንዲወጡና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንደያሳድሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
    5. የአረብ ሊግ በኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ሰሞኑን የወሰደውን ኢ-ፍትሐዊ ውሣኔ እየተቃወምን የአፍሪካ ህብረት እንዲህ ዓይነት ጣልቃ ገብነትን እንዲቃወምና መርህን እና ሕግን መሠረት በማድረግ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም እንጠይቃለን።
    6. የአሜሪካ መንግሥት በታዛቢነት ገብቶ ሀብት እና የዲፕሎማሲያዊ ኃይሉን በመጠቀም ወደ አደራዳሪነት ራሱን ከማሸጋገር በላይ የወሣኝነት ሚና ያለው የሚመስል መግለጫ ማውጣቱን አጥብቀን እንቃወማለን።

    የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ

    የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች
    የካቲት 28 /2012 ዓ/ም
    ካፒታል ሆቴል
    አዲስ አበባ

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች

    #13866
    Semonegna
    Keymaster

    በ2013 ዓ.ም የጉራጊኛ ቋንቋ ከቅድመ መደበኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ እየተሠራ ነው

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ.ም. የጉራጊኛ ቋንቋ ከቅድመ መደበኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ እየሠራ መሆኑን ገለጸ። ዩኒቨርሲቲው ከ135 በላይ ለመድኃኒት የሚሆኑ እጽዋት ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

    ወልቂጤ (ኢዜአ) – ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአገር በቀል እውቀት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ጥሩውሃ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደተናገሩት፥ እስካሁን የጉራጊኛ ቋንቋ በትምህርት ቤት፣ በመሥሪያ ቤት እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ አልተካተተም። በቋንቋው ውስጥ የተለያየ የአነጋገር ዘዬ መኖር በትምህርት እንዳይሰጥ ካደረጉት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

    በዚህም አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጉራጊኛ ቋንቋን እየረሳ በመምጣቱ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር የፊደል ገበታ መቀረጹን ገልጸዋል። የተወሰኑ ፎነቲኮች በአማርኛ ፓወር ግዕዝ ላይ ባለመኖራቸው ዩኒቨርሲቲው “የተንቢ” የተሰኘ የኮምፒተር መተየቢያ አበልጽጓል።

    በጉራጊኛ ቋንቋ 13 የአነጋገር ዘዬ የሚገኝ ሲሆን በየትኛው መጀመር እንዳለበት ዩኒቨርሲቲው ለማኅበረሰቡ አማራጭ ሃሳቦችን ለማቅረብ ተዘጋጅቷል።

    ”የኮምፒተር መተየቢያና የፊደል ገበታን በማሰልጠን እንዲሁም ሌሎች ግብአቶች እንዲሟሉ በመጠቆም  የጉራጊኛ ቋንቋ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ ለማስቻል እየተሠራ ነው” ብለዋል አቶ ካሳሁን።

    በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ከ135 ዓይነት በላይ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ተክሎች ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ለዚህም የተፈጥሮ መድኃኒት ማምረት የሚያስችል የስልት ሰነድ (strategic document) እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

    እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ መድኃኒቱን ማምረት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው። በዚህም ንጥረ ነገሮችን የመሥራትና የአሠራር ዘዴ ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

    ምርምር እየተደረገባቸው ያሉ እጽዋት ለደም ብዛት፣ ጋንግሪን፣ አስም፣ አጥንት ካንሰርና ለሌሎች በሽታዎች ፈውስ ያስገኛሉ የተባሉ ናቸው።

    ቀደም ሲል ከእጽዋት የባህላዊ መድኃኒቶች ልኬት እንደማይታወቅ ያነሱት አቶ ካሳሁን፥ የፋርማሲና የኬሚስትሪ ባለሙያዎች ከአካባቢው የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር በምርምሩ እንዲሳተፉ ተደርጓል።

    በሌላ በኩል የማኅበረሰቡ ለበርካታ ዓመታት ይተዳደርበት የነበረው ባህላዊ የሕግና አስተዳደር ዘዴ እየቀነሰ በመምጣቱ መልሶ እንዲያንሰራራ ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው ምርምር እያደረገ ነው።

    ቋንቋና ሥነ-ጹህፍ፣ አገር በቀል መድኃኒት፣ አስተዳደርና ሕግ፣ ባህልና የማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኒቨርሲቲው ትኩረት ተሰጥቷቸው ምርምርና ጥናት እየተካሄደባቸው ነው።

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በደቡብ ክልል የሚገኝ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲሆን የተመሠረተው በ2004 ዓ.ም. ነው።

    ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጉራጊኛ ቋንቋ

    #13886
    Semonegna
    Keymaster

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 34 የሕክምና ዶክተሮችን ጨምሮ ለሁለተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 1233 ተማሪዎቸ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመርቋል።

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በዋና ግቢው እና በዱራሜ ካምፓስ 6 ኮሌጆች በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ እና በተከታታይ ትምህርት በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ነው ያስመረቀው።

    በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሳይንስና እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፥ ኢትዮጵያ ለእርሷ እና ለዜጎቿ ክብር እና ፍቅር ያለው ባለሙያ ያስፈልጋታል ብለዋል። አክለውም ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት በተገቢው ሁኔታ ለማኅበረሰብ ለውጥ እንዲያውሉት አሳስበዋል።

    ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ድጋፋቸውን በማጠናከር የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንዲያስረግጡም ዶ/ር ሳሙኤል ጠይቀዋል።

    የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሐብታሙ አበበ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። አሁን ላይ በሀገሪቱ በተለያየ መልኩ ከሚንፀባረቀው የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ኋላ ቀርነት በመራቅ ለኅብረተሰብ ዕድገት እና ብልፅግና እንዲረባረቡ ጠይቀዋል።

    በሌላ በኩል ደግሞ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም ያሰለጠናቸውን 33 የሕክምና ዶክተሮችን አስመረቀ።

    ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም (hybrid innovative curriculum) በሕክምና ዶክትሬት ያሰለጠናቸውን 33 ተማሪዎች በተመሳሳይ ቀን አስመርቋል።

    በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ለተማሪዎቹ የሥራ መመሪያ የሰጡት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ ተመራቂዎቹ ቃለመሀላ በገቡለት የሕክምና ሥነ-ምግባር በመታገዝ ቅን አገልጋዮች እንዲሆኑ አሳስበዋል። ከዚህም ባለፈ በተግባር በተደገፈው ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም የቀሰሙትን የሕክምና ትምህርት የሀገሪቱን ብሎም የዓለምን ሕዝብ ስጋት ላይ ከጣሉ ዘመን-ወለድ የጤና ችግሮች ኅብረተሰቡን ለመታደግ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጥሪ አቅርበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በውጤት በታገዘው የቅይጥ ፈጠራ-አከል ሥርዓት (ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም) ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸው በመሆናቸው ማኅበረሰቡን ከጤና እክሎች ከመታደግ ባለፈ በምርምር ዘርፍ በመሰማራት ለሀገር ብልፅግና የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ 26 የማስተርስ ዲግሪ (ሁለተኛ ዲግሪ) ተማሪዎችንም አስመርቋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ

    #13890
    Anonymous
    Inactive

    ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአርክቴክቸር ዘርፍ ለአምስት ዓመት ተኩል ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

    ኮምቦልቻ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – በወሎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘው ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (Kombolcha Institute of Technology) የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል ለአምስት ዓመት ተኩል ሲያስተምራቸው ከነበሩት ተማሪዎች ውስጥ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓም በዋለው ሴኔት ውጤታቸውን መርምሮ ሃያ ስድስት ተማሪዎችን በደማቅ ዝግጅት አስመርቋል።

    በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት፥ ኢትዮጵያ በኪነ ህንፃ ዘርፍ የቆየ ጥበብ ባለቤት መሆኗን አስታውሰው፤ ተማሪዎች በቆዩባቸው ዓመታት ከአካዳሚያዊ እውቀት ባለፈ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና ችረዋል።

    ዶ/ር መላኩ በመልዕክታቸው፥ በ2012 ዓ.ም. ከተመረቁት ሃያ ስድስት ተማሪዎች መካከል በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ሁለት ተማሪዎች በትምህርት ክፍሉ እና በማኔጅመንት ውሳኔ በተቋሙ ውስጥ በመምህርነት እንዲቀጠሩ መወሰኑን አብስረዋል።
    የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ ሲሸጋገሩ ያገኙትን እውቀት እና ልምድ በተግባር በማዋል ዘርፉ ላይ ትልቅ አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ እንደሚገባ አሳስበው፤ ምሩቃኑ በአገሪቱ ነባራዊ ሁናቴ ላይ በጎ አሻራ በማስቀመጥ የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት መቻል እንዳለባቸው ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል።

    ዶ/ር አባተ ኢትዮጵያ ከጣራ ወደ መሠረት እነዲሁም ከአንድ ፍልፍል ደንጋይ ህንፃ በማዋቀር የቀደመ የጥበብ ተምሳሌት መሆኗን አውስተው ተመራቂ ተማሪዎች ራሳቸወን በማብቃት በአለም ገበያ ጭምር ተወዳዳሪ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

    የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ የሱፍም በምረቃ ፕረግራሙ ወቅት በክብር እንግድነት ተገኝተው ለምሩቃኑ ንግግር አድርገዋል።

    በ2012 ዓ.ም. ትምህርት ዘመን ከአጠቃላይ ተመራቂዎች 3.67 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ኤደን ሽመልስ እና 3.54 ያመጣው ዳዊት ማለደ ወደ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መቀላቀላቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ በቆይታቸው ባገኙት እውቀትና ልምድ ተቋሙን እና አገራቸው ለማገልገል ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

    ከዚህ ጋር በተያያዘ፥ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስናና በሒሳብ የትምህርት መስኮች የተሻለ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች እንድኖሩ የSTEM ማዕከል በማቋቋም እየሠራ ይገኛል። ይህንን የSTEM ማዕከል በቴክኖሎጅ ለማደራጀት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር “የኮምፒዩተርና የኤሊክትሮኒክስ” ቤተ-ሙከራ ከፍቷል። ይህ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የSTEMpower ማበልጸጊያ “የኮምፒተርና የኤሌክትሮኒክስ ቤተ ሙከራ” በአሜሪካን STEMpower.org ከተሰኘ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ የተመሠረተ ነው። ማዕከሉ በዘመናዊና ደረጃቸውን በጠበቁ የቤተ-ሙከራ ማቴሪያሎች የተደራጀ እንዲሆን ድርጅቱ ሁሉንም መሣሪያዎች በቀጥታ ከውጭ እንድገቡ አድርጓል። ይህም የSTEM ማዕከል የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራንና ድጋፍ አድራጊው የSTEMpower.org ድርጅት ተወካይ ባሉበት “ማዕከሉ” በይፋ ተከፍቷል።

    ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት

    #13918
    Anonymous
    Inactive

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ በከሚሴ ከተማ ቅርንጫፍ (ካምፓስ) ለመክፈት ቦታ ተረከበ

    ከሚሴ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – ወሎ ዩኒቨርሲቲ ተደራሽነቱን በማስፋፋት የግቢ (የካምፓስ) ብዛቱን ሦስት ለማድረስ ከከሚሴ ከተማ አስተዳደር 100 ሄክታር መሬት ተርክቧል። በዚህም የቦታ ርክክብ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የኮሌጅ ዲኖችና ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል።

    የዩኒቨርሲቲው አመራሮች የከሚሴ ከተማ አስተዳደር በስጦታ ያበረከተውን ቦታ ከጎበኙ በኋላ ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል። በዚህም ውይይት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በከሚሴ በቀጣይ የሚከፈተው ኮሌጅ የከሚሴንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጥቅም፣ ፍላጎትና ሃብት መሰረት ያደረገ እንዲሆን በጥናት ላይ ተሞርኩዞ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱም የከሚሴ ከተማ አስተዳደር ላደረገው የቦታ ስጦታ ላቅ ያለ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ፥ ምክትል ፕሬዚዳንቶች በየዘርፋቸው ቦታውን ተረክቦ የከሚሴንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጥያቄዎች ለመመለስ በሎም የተሰማቸውን አስተያየት እንዲሰጡ አድርገዋል። ወሎ ዩኒቨርሲቲ በርካታ በሆኑ የቅድመና ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሆነ የገለጹት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር ብረሃን አስማሜ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የትምህርት ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ኮሌጆችን፥ ትምህርት ክፍሎችንና መርሀ-ግብሮችን (ፕሮግራሞችን) ለመክፈት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

    በምሥራቅ አማራ ጨፋ ሸለቆ ያለው ከፍተኛ የሃብት ክምችት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ተርፎ ለገበያ እንዲውል የምርምር ማዕከል በቦታው በመክፈት ሕዝባችንን ከድህነት የሚያወጡ የምርምር ሥራዎችን በማካሄድ ዕድሉን ለመጠቀም እንደሚሠሩ የተናገሩት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበራዊ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ኃይሉ ናቸው። የቦታው ሕጋዊ ሰነዶች በሙሉ በዩኒቨርሲቲው ስም ሆነው እንደተጠናቀቁ ተገቢውን የግንባታና ተቋሙን የማደራጀት ተግባራት እንደሚጀምሩ የገለጹት የዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አማረ ምትኩ፥ ዩኒቨርሲቲው ተደራሽነቱን በማስፋት የማኅበረሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ የአቅሙን ሁሉ ይሠራል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    በከሚሴና አካባቢ ያለውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍ ከክህሎት ስልጠና ጀምሮ በአዋጭ የሥራ መስኮች ወጣቱ እንዲሰማራ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የቢዝነስ ልማትና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ፕሬዝዳንቷ ዶ/ር አጸደ ተፈራ ሲገልጹ፥ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ በበኩላቸው የአካባቢውን ማኅበረሰብ ፍላጎት በማየት በኮምፒዩተር ሳይንስ መርሀ-ግብሮችን መክፈት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

    የኮሌጅ ዲኖችና ዳይሬክተሮች በጉብኝቱ ያዩትን፣ የተሰማቸውንና በቀጣይ በቦታው ቢሠራ ያሏቸውን አስተያየቶች ሰጥተዋል። ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት ከከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች የሥነ-ተዋልዶ፣ የመዝናኛ፣ የቤተ መጻሕፍትና ተዛማጅ የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን የሚሰጥበት ማዕከል ተቀብሎ ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወቅ ነው።

    ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከሚሴ ካምፓስ

Viewing 15 posts - 16 through 30 (of 56 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.