Home › Forums › Semonegna Stories › ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን) › በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ ይቆጠራል
በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ ይቆጠራል
አንዱዓለም አራጌ
ከዚህ ቀደም በጣም በአመዛኙ የፓርቲዬን አቋም ካልሆነ በስተቀር እምብዛም የግል አቋሜን አንፀባርቄ አላውቅም።
ብዙውን ጊዜ ተቋሞቻችን ሕጸጻቸውን እያረሙ ሁላችንም የምንደገፍባቸው ተቋማት እንዲሆኑ እድልም ሆነ ጊዜ መስጠት ተገቢ መሆኑን አምናለሁ። ይሁን እንጂ፥ ትናንት የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፍስና በስጋው ተወራርዶ መራር ሕዝባዊ ትግል ያደረገው ዝቅ ብለን የምንመለከተውን ዓይነት ግፍ ለማስተናገድ አለመሆኑ እሙን ነው።
በ1993 ዓ.ም በጊዮርጊስ የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት በተለያዩ ሁለት ችሎቶች፣ በተመሳሳይ ዕለት፣ በተመሳሳይ ሰዓት የተፈፀሙ ሁለት ውሳኔወችን ለማስታወስ እወዳለሁ። አንደኛው ችሎት በሀቪየስ ኮርፐስ (habeas corpus) ክስ አማካኝነት፣ እነአቶ ታምራት ታረቀኝን ካሰረበት አምጥቶ ለፍርድ ቤቱ ያቀርብ ዘንድ ፓሊስን ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ቢያዝም፥ ትዕዛዙ ባለመፈፀሙ በወቅቱ የፍትህ ሚንስትር የነበሩት አቶ ወረደወልድ ወልዴ ታስረው እንዲቀርቡ ባዘዘው መሠረት ታስረው ቀረቡ። ፍርድ ቤቱም የአንድ ወር እሥራት ፈረደባቸው። በሌላ ደግሞ የዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ችሎት አቶ ስዬ አብርሃ ቀርበው የወ/ት ብርቱካን ችሎት አርነት ሰደዳቸው። ይሁን እንጂ ለቤታቸው ሊበቁ የተገባቸው አቶ ስዬ አብርሃ በአፈሙዝ አስገዳጅነት ወህኒ እንዲወርዱ ተገደዱ። ሚኒስትር ወረደወልድ ወልዴ ደግሞ ሳይገባቸው ለሞቀ ቤታቸው በቁ።
ይህን የሃያ ዓመት ታሪክ ያለምክንያት አላነሳሁትም። ከእልህ አስጨራሽ ሕዝባዊ ትግል በኋላ የለውጥ ሽራፊ ለማየት ብንጓጓም ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ለከት ያጣ ግፍ እያስተናገድን ነው። በ”ለውጡ” የመጀመሪያ ወራት ሕዝቡ የተራበ አንጀቱን አስሮ ይስቅ የነበረው፣ ድጋፉንም የቸረው ከእንግዲህ በፍትህ፣ በእውነትና በእኩልነት የምጠግብበት ዘመን ጠባ ብሎ በማመኑ ይመስለኛል። ከፈጣሪ በታች ተስፋችን በእጃችን መሆኑ የቀትር ያህል ግልፅ ቢሆንም፣ ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ የፍትህን መጨንገፍን ሳይ ጥልቅ ሀዘን አልተሰማኝም ብል ግን እውነቱን አልናገርም።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሥራ አስፈፃሚ አባል ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ ፍርድ ቤት የዋስትና መብቷን ቢያከብርላትም፥ ፓሊስ ላለመልቀቅ ያሳየውን ዳተኝነት እናስታውሳለን። በተመሳሳይ የአሥራት ቴሌብዥን ጋዜጠኞችንም እንዲሁ በመከራ መልቀቁ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
ዛሬ ብዕሬን እንዳነሳ ያደረገኝ ጉዳይ የአቶ ልደቱ አያሌው ጉዳይ ነው። ስለአቶ ልደቱ ከእኔ በላይ ብዙ ነገሮችን አጣቅሶ ማቅረብ የሚችል ሌላ ማን እንዳለ በእውነት አላውቅም። በፓርቲዬም ላይ ቢሆን በተደጋጋሚ ምን ያደርጉ እንደነበር ፈፅሞ ዘንግቼው አይደለም። አቋማቸው ከአቋሜ ስለገጠመም አይደለም። ይልቅስ አቶ ልደቱ እራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት በዚህ ሁኔታ አንዳች አሉታዊ ጉዳይ አንስቼ እሞግታቸው ዘንድ ፈፅሞ ህሊናዬ አይፈቅድልኝም።
በተወሰነ መልኩ የቀደመውን ለአንባቢ ያስታወስኩትም ቢሆን፥ የቆምኩበትን የሀሳብ ማዕዘን ለማሳየት ይረዳኝ ዘንድ ግድ ሆኖብኝ እንጂ ምቾት ተሰምቶኝ አይደለም። ይልቅስ ከላይ ከፍ ብዬ ከጠቀስኳቸው ወገኖቻችንም በከፋ ሁኔታ የ“ፓሊስ ጢባጢቤ” መጫወቻ ሆነው ሳይ፥ እርሳቸውን የወጋ ጦር እኔንም እንደወጋኝ ተሰምቶኛል። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር እንዲለቀቁ ቢያዙም በፓሊስ እንቢተኝነት ግን በእስር ላይ ይገኛሉ። ውርደቱ፣ መረገጡ፣ ንቀቱና ኢፍትሃዊነቱ፣ የኢፍትሃዊነትን ስቃይ ለምናውቅ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ነው። በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ የሚጠራጠር ካለ እርሱ ፍፁም ማስተዋል የጎደለው ነው።
በኢትዮጵያችን እየታየ ያለው ለከት ያጣ ግፍ ቅስም የሚሰብርና በምንም ዓይነት መንገድ ልንታገሰው የማይገባ ኢፍትሃዊ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ያዋረደ ወደር-አልባ የነውረኝነት ተግባርም ነው።
በፈጣሪ እንደምትታመኑ ደጋግማችሁ የነገራችሁን ወገኖች፥ በሚፈፀመው ግፍ ፈጣሪ የሚደሰትበት ይመስላችኋል? የሚሠራውን ኢፍትሃዊነት በአስቸኳይ እስካላስቆማችሁ የፈጣሪም ሆነ የሕዝብም ቁጣ እሩቅ እንደማይሆን ለመናገር ነቢይነትን አይጠይቅም።
Free Lidetu Ayalew
አንዱዓለም አራጌ
አቶ አንዱዓለም አራጌ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምክትል መሪ ሲሆኑ፤ ከዚያ በፊት ደግሞ የቀድሞው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ፕሬስ ሴክሬተሪ ነበሩ።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።