አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና ዶክተሮችን አስመረቀ

Home Forums Semonegna Stories የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና ዶክተሮችን አስመረቀ

#13682
Semonegna
Keymaster

አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና ዶክተሮችን አስመረቀ
ጅማ ዩኒቨርሲቲ 3ሺህ 185 ተማሪዎችን መተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል

አዳማ (ኢዜአ) – አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌና ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና ስፔሻልስቶችን ጨምሮ በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን 140 ዶክተሮችን የካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ። ከተመራቂዎቹ መካከል ደቡብ ሱዳን የሕክምና ስፔሻልስቶች ይገኙበታል።

በምረቃው ሥነ ሥርዓት የተገኙት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋሽ ስሜ እንደገለጹት፥ በክልሉ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ካንሰርና ስኳርን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች (noncommunicable diseases) እየተስፋፉ መጥተዋል። በክልሉ በሚገኙ የመጀመሪያና ሪፌራል ሆስፒታሎች የሕክምና መሣሪያና መድኃኒትን ጨምሮ የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች እጥረት መኖሩንም ተናግረዋል።

ለዚህም አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ግንባር ቀደም መሆኑን ጠቅሰው ኮሌጁ የሰው ሕይወት ለማዳን የሚያስችል እውቅትና ክህሎት ለማስታጠቅ ተግባር ተኮር ስልጠናና ምርምር ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባው አቶ ነጋሽ ጠቁመዋል። ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመተርጎም ማህበረሰቡን በማገልገል ምሳሌ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መኮንን ፈይሳ በማህፀን፣ በውስጥ ደዌ፣ በህፃናትና በከፍተኛ ቀዶ ሕክምና እንዲሁም በጠቅላለ ሐክም ስፔሻልስቶችን እያሰለጠነ ነው፤ ዛሬ ለምረቃ የበቁት 140 የሕክምና ዶክተሮች አሁን በስፋት የሚስተዋለውን አጣዳፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

በተለይ በክልሉ የመጀመሪያ፣ ስፔሻላይዝድና ሪፌራል ሆስፒታሎች የሚታዩትን የማህፀን፣በውስጥ ደዌ፣ የህፃናትና ከፍተኛ ቀዶ ሕክምና ያለው የከፍተኛ ሙያተኞች እጥረት የሚፈታ ነው ብለዋል – ዶ/ር መኮንን።

ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ለህብረተሰቡ የጠቅላላ ሕክምና አገልግሎት፣ መካከለኛና ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ሕክምና በመስጠት ሙያዊ ብቃታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ በማለት አስረድተዋል።

አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ከ400 በላይ አልጋ ያለው፣ ማስፋፊያ ግንባታ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከላት፣የተማሪዎች መኖሪያና መመገቢያ ህንፃዎች ከአንድ ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በመገንባት ለአገልግሎት ዝግጁ አድርጓል።

ከተመራቂዎቹ መካከል በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ዶ/ር አያንቱ በቀለ በሰጠችው አስተያየት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን አሳሳቢ እየሆነ ያለው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደሆነ ገልጻ ባገኘሁ እውቀት የድርሻዬን እወጣለሁ በማለት ተናግራለች።

ከከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ምርቃት ጋር በተያያዘ፥ ጅማ ዩኒቨርሲቲ 3ሺህ 185 ተማሪዎችን መተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል። የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ በምረቃው ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት “ዛሬ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ሀገራችሁ ከእናንተ ከምንግዜውም በላይ እንድታገለግሏት ትፍልጋለች” ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ያስመረቀው ከስድስት ኮሌጆች፣ ሁለት ኢንስቲትዩቶች እና ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት በተለያዩ ሙያዎች ስልጠናቸው ነው። ከተመራቂዎቹ መካከል 834 ሴቶች እንዲሁም 11 የሱማሌላንድና የሩዋንዳ ዜጎች ይገኙበታል። ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወጣጡ አንድ መቶ ስልሳ ስምንት ሰዎችን እያስተማረ እንደሚገኝም ተመልክቷል።

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ