ኢዜማ በአባላቱ ላይ እየደረሰ ስላለው እስር እና እንግልት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አቤቱታውን አቀረበ

Home Forums Semonegna Stories የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች) ኢዜማ በአባላቱ ላይ እየደረሰ ስላለው እስር እና እንግልት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አቤቱታውን አቀረበ

#16189
Semonegna
Keymaster

ኢዜማ በአባላቱ ላይ እየደረሰ ስላለው እስር እና እንግልት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አቤቱታውን አቀረበ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ማክሰኞ፥ መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በተለያዩ ክልሎች በአባላቱና በደጋፊዎቹ ላይ እየተፈፀሙ ስላሉ እስር እና እንግልቶች ውይይት ካደረገ በኋላ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድብዳቤ እንዲፃፍ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ደብዳቤው እንደተፃፈና ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደተላከ የኢዜማ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ለዜጎች መድረክ ገለፁ።

ኃላፊው፥ ኢዜማ ምሥረታውን ካደረገበት ጊዜ አንስቶ እዚህም፣ እዚያም ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበርና አብዛኛዎቹ ቦታዎች ላይም የጸጥታ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል። ፓርቲያቸው በእነዚህ ችግሮች ውስጥ በማለፍ አባላቶቹን በማደራጀት መዋቅሮቹን ሲዘረጋ እንደነበር አውስተዋል። “በማደራጀት ሂደት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የጸጥታ ችግር ይገጥመን ነበር” ያሉት አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፥ የተለያዩ ኢ-መደበኛ የሆኑ አደረጃጀቶች መዋቅሮቻችንን እንዳንዘረጋ የተለያየ ጫና ያሳድሩብን ነበር ብለዋል።

“የተለያዩ ፈተናዎች ነበሩ፤ በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ታልፎ ነው እዚህ ደረጃ የተደረሰው። ለዚህም በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ አባሎቻችን ብዙ ዋጋ ከፍለዋል›› ያሉት ድርጅት ጉዳይ ኃላፊው፥ በአባላቶቻቸውና በደጋፊዎቻቸው ላይ የሚደርሰው እንግልት፣ እስር እና ጫና ከመቀነስ ይልቅ እየተባባሰ በመምጣቱ የተነሳ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ጉዳዩን እንዲመረምርና ችግሩ በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ መፃፍ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።

“አባላቶቻችሁ ሲታሰሩ አልያም እንግልት ሲደርስባቸው ብዙም ስትሉ አይደመጥም አሁን ምን ተፈጥሮ ነው ደብዳቤ ለመፃፍ የወሰናችሁት?” በሚል ከዜጎች መድረክ (በኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት የሚዘጋጅ ሳምንታዊ ጋዜጣ) ለተነሳላቸው ጥያቄ ኃላፊው ሲመልሱ፥ “የተለያዩ ፈተናዎች ሲገጥሙን ችግሩን ወደ አደባባይ በማውጣት ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት የለንም። አሁንም ቢሆን ችግሩን ከመፍታት አንጻር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቁጭ ብሎ በመነጋገር እንዲፈታ እንፈልጋለን። ከፖለቲካ አተያይ አንጻርም አባሌ ታስሯል እያሉ አባል ለማፍራት አይቻልም። እኛ ሰላማዊ የሆነ ምህዳር ተፈጥሮ ማንኛውም አካል ሳይፈራና ሳይሸማቀቅ በነፃ አባል እንዲሆን ነው የምንሻው። እዚህ ጋር አባሌ እንዲህ ሆኗል፤ እዚህ ጋር አባሌ ታስሯል እያሉ አባል ማፍራት ያሰቸግራል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፈን ነው እዚህ ደረጃ የደረስነው” ያሉት ድርጅት ጉዳይ ኃላፊው፥ ፓርቲያቸው በአሁኑ ሰዓት በመላው ኢትዮጵያ 280 ቢሮዎች እንዳሉትና 435 የምርጫ ወረዳ ላይ አደረጃጀቱን መዘርጋቱን ጠቁመዋል። ፓርቲያቸው ይህንን ሊያሳካ የቻለውም ችግሮች ሲከሰቱ ከመካሰስ ይልቅ በችግሮቹ ውስጥ መውጫን በመፈለግ ላይ በማተኮሩ የተነሳ መሆኑን ተናግረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለያዩ ክልሎች ላይ በሚገኙ አባላትና ደጋፊዎቻቸው ላይ የሚደርሰው እስራትና እንግልት እያየለ በመምጣቱ የተነሳ በደብዳቤ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኙት ለሚመለከተው አካል አቤቱታቸውን ማስገባታቸውን ኃላፊው አስረድተዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የኢዜማ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እየደረሰ ያለው እስር እና እንግልት እየጨመረ መምጣቱን የሚያነሱት የኢዜማ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፥ በቤንች ማጂ ዞን፣ ቴፒና ጋምቤላ ብቻ ከ30 በላይ አባላቶቻቸው ታስረው እንደሚገኙባቸው ገልፀዋል።

ምንጭ፦ ኢዜማ

ኢዜማ በአባላቱ ላይ እየደረሰ ስላለው እስር እና እንግልት ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አቤቱታውን አቀረበ