Home › Forums › Semonegna Stories › የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች › ወሎ ዩኒቨርሲቲ በከሚሴ ከተማ ቅርንጫፍ (ካምፓስ) ለመክፈት ቦታ ተረከበ
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በከሚሴ ከተማ ቅርንጫፍ (ካምፓስ) ለመክፈት ቦታ ተረከበ
ከሚሴ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – ወሎ ዩኒቨርሲቲ ተደራሽነቱን በማስፋፋት የግቢ (የካምፓስ) ብዛቱን ሦስት ለማድረስ ከከሚሴ ከተማ አስተዳደር 100 ሄክታር መሬት ተርክቧል። በዚህም የቦታ ርክክብ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የኮሌጅ ዲኖችና ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል።
የዩኒቨርሲቲው አመራሮች የከሚሴ ከተማ አስተዳደር በስጦታ ያበረከተውን ቦታ ከጎበኙ በኋላ ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል። በዚህም ውይይት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በከሚሴ በቀጣይ የሚከፈተው ኮሌጅ የከሚሴንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጥቅም፣ ፍላጎትና ሃብት መሰረት ያደረገ እንዲሆን በጥናት ላይ ተሞርኩዞ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱም የከሚሴ ከተማ አስተዳደር ላደረገው የቦታ ስጦታ ላቅ ያለ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ፥ ምክትል ፕሬዚዳንቶች በየዘርፋቸው ቦታውን ተረክቦ የከሚሴንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጥያቄዎች ለመመለስ በሎም የተሰማቸውን አስተያየት እንዲሰጡ አድርገዋል። ወሎ ዩኒቨርሲቲ በርካታ በሆኑ የቅድመና ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሆነ የገለጹት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር ብረሃን አስማሜ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የትምህርት ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ኮሌጆችን፥ ትምህርት ክፍሎችንና መርሀ-ግብሮችን (ፕሮግራሞችን) ለመክፈት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።
በምሥራቅ አማራ ጨፋ ሸለቆ ያለው ከፍተኛ የሃብት ክምችት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ተርፎ ለገበያ እንዲውል የምርምር ማዕከል በቦታው በመክፈት ሕዝባችንን ከድህነት የሚያወጡ የምርምር ሥራዎችን በማካሄድ ዕድሉን ለመጠቀም እንደሚሠሩ የተናገሩት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበራዊ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ኃይሉ ናቸው። የቦታው ሕጋዊ ሰነዶች በሙሉ በዩኒቨርሲቲው ስም ሆነው እንደተጠናቀቁ ተገቢውን የግንባታና ተቋሙን የማደራጀት ተግባራት እንደሚጀምሩ የገለጹት የዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አማረ ምትኩ፥ ዩኒቨርሲቲው ተደራሽነቱን በማስፋት የማኅበረሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ የአቅሙን ሁሉ ይሠራል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በከሚሴና አካባቢ ያለውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍ ከክህሎት ስልጠና ጀምሮ በአዋጭ የሥራ መስኮች ወጣቱ እንዲሰማራ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የቢዝነስ ልማትና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ፕሬዝዳንቷ ዶ/ር አጸደ ተፈራ ሲገልጹ፥ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ በበኩላቸው የአካባቢውን ማኅበረሰብ ፍላጎት በማየት በኮምፒዩተር ሳይንስ መርሀ-ግብሮችን መክፈት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የኮሌጅ ዲኖችና ዳይሬክተሮች በጉብኝቱ ያዩትን፣ የተሰማቸውንና በቀጣይ በቦታው ቢሠራ ያሏቸውን አስተያየቶች ሰጥተዋል። ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት ከከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች የሥነ-ተዋልዶ፣ የመዝናኛ፣ የቤተ መጻሕፍትና ተዛማጅ የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን የሚሰጥበት ማዕከል ተቀብሎ ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወቅ ነው።
ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ