በ2013 ዓ.ም የጉራጊኛ የፊደል ገበታ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ መምህራን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ተሰጠ

Home Forums Semonegna Stories የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች በ2013 ዓ.ም የጉራጊኛ የፊደል ገበታ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ መምህራን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ተሰጠ

#15927
Anonymous
Inactive

በ2013 ዓ.ም የጉራጊኛ የፊደል ገበታ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ መምህራን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ተሰጠ

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከጉራጌ ዞን አስተዳደር በጋራ በመሆን የጉራጊኛ የፊደል ገበታ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ለማስተማር በዞኑ ከተለያዩ ወረዳዎች ለተዉጣጡ መምህራን ስልጠና የሰጠ ሲሆን፤ በቀጣይ የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርት፣ የሚዲያና የሥራ ቋንቋ ለማድረግ የፊደል ገበታዉ ለቅድመ መደበኛ ተማሪዎች መስጠት አጋዥ መሆኑ ተገልጿል።

በስልጠናዉ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል የሱፍ እንዳሉት፥ የሀገራችን ሕገ-መንግሥት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በቋንቋቸዉ የመናገር፣ የመፅሀፍ፣ ቋንቋቸዉን የማሳደግ መብት እንዳላቸዉ አስፍሯል። የቤተ-ጉራጌ ህጻናትም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ እንዲማሩ ለማድረግ ይሁንታ ያገኘዉን የጉራጊኛ የፊደል ገበታ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሄደበት ያለዉን መንገድ አበረታች ተግባር እንደሆነም አስታዉቀዋል። የጉራጊኛ የፊደል ገበታ የትምህርቱን መስክ መሣሪያ በማድረግና ወደ መሬት ለማውረድ የሰልጣኝ መምህራን ሚና የጎላ እንደሆነም አስረድተዋል።

ለህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት መስጠት አስፈላጊዉን የቤተሰብ ድጋፍ በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችላቸዉን ዕድል ለማስፋትና ሳይንሱን ይበልጥ ለመረዳት፥ እንዲሁም አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር የሚያስችላቸዉ ተመራጭ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ እንደሆነም አስታዉቀዋል።

በስልጠናዉ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ እንዳሉት፥ የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርት፣ የሚዲያ እና የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ለማድረግ የምሁራን ሚና የጎላ ነዉ። ቋንቋ የአንድ ማኅበረሰብ የማንነት መገለጫ እንደመሆኑ መጠን ዜጎች የራሳቸዉ ቋንቋ እንዲማሩ ሕገ-መንግሥቱ ላይ ተደንግጓል ብለዋል።

ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ መማር እንዲችሉ ለማድረግና የጉራጊኛ ቋንቋ በማልማት የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት ከቁጭት ባሻገር ወደ ተግባር አለመገባቱም አስታዉሰዉ፥ የተለያዩ ምሁራን መጽሐፍ በማዘጋጀት በጥናትና ምርምር ሁሉም የበኩሉን ቢያበረክትም ዉጤታማ እንዳልሆነም አንስተዋል።

ቋንቋዉን ለማልማት የኮምፒዩተር ቀመር (ሶፍትዌር) በመቅረጽ፣ ጥናትና ምርምር በማድረግ እና የተለያዩ ዕቅዶችን በማቀድ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ምሁራን እያደረጉት ያለዉን ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስረድተዋል።

በስልጠናዉ የተሳተፉ አንዳንድ መምህራን በሰጡት አስተያየት፥ የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን የበኩላቸዉን ሚና እንደሚወጡም አስረድተዋል።

በስልጠናዉ ያገኙት እዉቀት በመጠቀም የጉራጊኛ የፊደል ገበታዉ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ከማስተማር በተጨማሪ በሁሉም የትምህርት ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ቢሰጥ መልካም ነዉ ብለዋል።

በመጨረሻም ከሁሉም ወረዳዎች ከሚገኙ ሁለት ሞዴል ትምህርት ቤቶች አራት አራት መምህራን ስልጠና ተሰጥቷል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

የጉራጊኛ የፊደል ገበታ