Search Results for 'ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ'

Home Forums Search Search Results for 'ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ'

Viewing 9 results - 1 through 9 (of 9 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    በ2013 ዓ.ም የጉራጊኛ የፊደል ገበታ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ መምህራን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ተሰጠ

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከጉራጌ ዞን አስተዳደር በጋራ በመሆን የጉራጊኛ የፊደል ገበታ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ለማስተማር በዞኑ ከተለያዩ ወረዳዎች ለተዉጣጡ መምህራን ስልጠና የሰጠ ሲሆን፤ በቀጣይ የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርት፣ የሚዲያና የሥራ ቋንቋ ለማድረግ የፊደል ገበታዉ ለቅድመ መደበኛ ተማሪዎች መስጠት አጋዥ መሆኑ ተገልጿል።

    በስልጠናዉ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል የሱፍ እንዳሉት፥ የሀገራችን ሕገ-መንግሥት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በቋንቋቸዉ የመናገር፣ የመፅሀፍ፣ ቋንቋቸዉን የማሳደግ መብት እንዳላቸዉ አስፍሯል። የቤተ-ጉራጌ ህጻናትም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ እንዲማሩ ለማድረግ ይሁንታ ያገኘዉን የጉራጊኛ የፊደል ገበታ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሄደበት ያለዉን መንገድ አበረታች ተግባር እንደሆነም አስታዉቀዋል። የጉራጊኛ የፊደል ገበታ የትምህርቱን መስክ መሣሪያ በማድረግና ወደ መሬት ለማውረድ የሰልጣኝ መምህራን ሚና የጎላ እንደሆነም አስረድተዋል።

    ለህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት መስጠት አስፈላጊዉን የቤተሰብ ድጋፍ በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችላቸዉን ዕድል ለማስፋትና ሳይንሱን ይበልጥ ለመረዳት፥ እንዲሁም አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር የሚያስችላቸዉ ተመራጭ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ እንደሆነም አስታዉቀዋል።

    በስልጠናዉ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ እንዳሉት፥ የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርት፣ የሚዲያ እና የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ለማድረግ የምሁራን ሚና የጎላ ነዉ። ቋንቋ የአንድ ማኅበረሰብ የማንነት መገለጫ እንደመሆኑ መጠን ዜጎች የራሳቸዉ ቋንቋ እንዲማሩ ሕገ-መንግሥቱ ላይ ተደንግጓል ብለዋል።

    ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ መማር እንዲችሉ ለማድረግና የጉራጊኛ ቋንቋ በማልማት የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት ከቁጭት ባሻገር ወደ ተግባር አለመገባቱም አስታዉሰዉ፥ የተለያዩ ምሁራን መጽሐፍ በማዘጋጀት በጥናትና ምርምር ሁሉም የበኩሉን ቢያበረክትም ዉጤታማ እንዳልሆነም አንስተዋል።

    ቋንቋዉን ለማልማት የኮምፒዩተር ቀመር (ሶፍትዌር) በመቅረጽ፣ ጥናትና ምርምር በማድረግ እና የተለያዩ ዕቅዶችን በማቀድ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ምሁራን እያደረጉት ያለዉን ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስረድተዋል።

    በስልጠናዉ የተሳተፉ አንዳንድ መምህራን በሰጡት አስተያየት፥ የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን የበኩላቸዉን ሚና እንደሚወጡም አስረድተዋል።

    በስልጠናዉ ያገኙት እዉቀት በመጠቀም የጉራጊኛ የፊደል ገበታዉ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ከማስተማር በተጨማሪ በሁሉም የትምህርት ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ቢሰጥ መልካም ነዉ ብለዋል።

    በመጨረሻም ከሁሉም ወረዳዎች ከሚገኙ ሁለት ሞዴል ትምህርት ቤቶች አራት አራት መምህራን ስልጠና ተሰጥቷል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

    የጉራጊኛ የፊደል ገበታ

    Semonegna
    Keymaster

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት ዘርፎች ያስተማራቸውን 659 ተማሪዎችን አስመረቀ

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በቅድመ- እና ድኅረ- ምረቃ መርሀግብሮች ያሰለጠናቸውን 659 ተማሪዎችን ጳጉሜን 3 ቀን 2012 ዓ.ም አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ለ12ኛ ዙር ለምረቃ ካበቃቸው ተማሪዎች መካከል 515 ወንዶች ሲሆኑ 144 ደግሞ ሴቶች ናቸው።

    ዩኒቨርሲቲው በእጽዋት ሳይንስ፣ በእንስሳት ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሥራ አመራር (Management)፣ እንዲሁም በጂኦግራፊና አካባቢ-ነክ ጥናቶች (Environmental Studies) በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስተምሮ አስመርቋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። እንደ ዶ/ር አህመድ ገለጻ፥ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለውጤት አብቅቷል።

    እንደ ተጠባባቂ ፕሬዝደንቱ ገለጻ፥ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው ዓመት በ46 የመጀመሪያ ዲግሪና በ23 የሁለተኛኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ከ17ሺ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

    በጥናትና ምርምር ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጭብጦች 18 የምርምር ንድፈ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል – ዶ/ር አህመድ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልም ከ3 ሺህ ሊትር በላይ የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሽ (ሳኒታይዘር) በማምረት አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጓልሲሉ አስረድተዋል።

    የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍቅሬ አማን በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስተላለት መልዕክት፥ እንዳሉት የዘንድሮው የምረቃ በዓል ለዓለማችን፣ ብሎም ለሀገራችን ህዝቦች የኮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት ተመራቂዎች የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማጠናቀቅ ለውጤት በመብቃታቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸዋል።

    ሀገራችን በመደመር ፍልስፍና ከነበረችበት ችግር ወጥታ ወደ ብልጽግና ጎዳና እየተጓዘች ባለችበት በዚህ የይቅርታና የምኅረት ወር በሆነችው በጳጉሜ ወር ተማሪዎች ለምረቃ በመብቃታቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞውን ሚዛን ተፈሪ ግብርና ኮሌጅ መሠረት አድርጎ በደቡብ ክልል ሚዛን ተፈሪ እና ቴፒ ከተሞች በ1999 ዓ.ም የተቋቋመ ዩኒቨርሲቲ ነው።

    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ

    ዲላ/አርባ ምንጭ (ኢዜአ/አ.ም.ዩ) – ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1,043 ተማሪዎችን ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ።

    በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫላ ዋታ እንደገለጹት ከተመራቂዎቹ መካከል 283 በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው። ቀሪዎቹ በምስክር ወረቀት የተመረቁ መሆኑን አስረድተዋል።

    ተመራቂዎቹ ትምህርታቸውን በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሲከታተሉ እንደቆዩ አመልክተው፥ በተለይ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት የክፍል ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከልን ጨምሮ በተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ዶ/ር ጫላ ገልጸዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ኡዴሳ ክዮላ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ በቀጣይ በሚሰማሩበተ የሥራ መስክ ሀገርና ሕዝብ የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና ታታሪነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

    ከተመራቂዎቹ መካከል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቱን የተከታተለው ቅዱስ ይገረሙ በሰጠው አስተያየት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በሰለጠነበት በ“ሶፍትዌር ዲዛይን” ዘርፍ በመሰማራት እራሱንና ሀገሩን ለመጥቀም እንደሚሠራ ተናግሯል።

    በሁለተኛ ዲግሪ ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ የተመረቀው ዋቆ ጥላሁን በበኩሉ በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀት በመጠቀም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንደሚጥር ገልጿል።

    የሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች የሚያስተምራቸው ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉት በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።

    ከተማሪዎች ምርቃት ጋር በተያያዘ፥ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለ33ኛ ጊዜ አስመርቋል።

    ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በመደበኛ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,326 ተማሪዎች ቅዳሜ ነሐሴ 30/2012 ዓ/ም በተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው በስድስት የተለያዩ ካምፓሶች በ76 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ99 የ2ኛ ዲግሪ እና በ21 የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች በአጠቃላይ ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሀግብሮች በማስተማር ላይ ይገኛል። ተቋሙ ባለፉት 33 ዓመታት በልዩ ልዩ የምህንድስና፣ የሕክምናና የጤና፣ የግብርና፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ የማኅበራዊ እንዲሁም የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ዘርፎች 56,958 ምሩቃንን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ጉልህ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

    አክለውም በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛው አጋማሽ ላይ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሁሉም ደረጃዎች በመማሪያ ክፍል ሆኖ የመማር ማስተማር ሂደት የተቋረጠ ቢሆንም፥ ዩኒቨርሲቲዎች ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጥናትና ምርምር ሥራቸውን ሲሠሩ የቆዩ ተማሪዎች አስፈላጊውን የምረቃ መስፈርት በማጠናቀቅ ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ዓመታት በተከፈቱ የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች ላይ የማጠናከር ሥራ የሚሠራ ሲሆን፥ ዩኒቨርሲቲው በ2013 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ኛ ዲግሪ የሚያስመርቅ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደተናገሩት፥ የመማር ግቡ ከግለሰብ ህይወት እስከ ሀገር ድረስ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ምቹና ተስማሚ አኗኗርን ለመፍጠር የለውጥና የዕድገት ጎዳናን መከተል ነው። በመሆኑም የዕለቱ ተመራቂዎች ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ እንድትደርስ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲሉ አሳስበዋል። በተጨማሪም ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል። ሀገሪቱ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እየተሻገረች የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን ፈተናዎቹን በብቃት መክተን ወደ መልካም ዕድል መቀየር ይጠበቅብናል ብለዋል።

    በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እና የሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር በለጠ ይልማ የእጩ ምሩቃን መግለጫ በመስጠት አስመርቀዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በክብር እንግድነት፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

    ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ (አ.ም.ዩ)

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

    Anonymous
    Inactive

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀግብሮች ያስተማራቸውን ከ900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ

    ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – የሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀግብሮች ያስተማራቸውን 929 ተማሪዎች ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ለሰባተኛ ጊዜ ባካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት አስመርቋል።

    በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እንዳሉት፥ እውቀትና ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለአንድ ሀገር እድገትና ቀጣይነት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። በዚህ ረገድ ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርት በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ማስፋፋት ወሳኝ ነው ብለዋል።

    ዶ/ር ሙሉ አክለውም፥ መንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሀገራችንን ሕዝብ ህይወት ቀላልና ዘመናዊ በማድረግ ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በማመን በየዓመቱ ከፍተኛውን የሀገሪቱን በጀት ለትምህርት መድቦ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

    ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ሃሳቦችን በማፍለቅና በመተግበር መልካም አርአያ የሚሆኑ ዜጎችን ማፍሪያ፣ የዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችና ቴክኖሎጂዎች መፍለቂያ፣ የባህላዊ እሴቶቻችን መጎልበቻ፣ የሕዝቦች የመተሳሰብ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ባህል የሚቀመርባቸው ማዕከላት እንዲሆኑ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል – ዶ/ር ሙሉ።

    ሚኒስትር ዴኤታው ሰላም በምንም ነገር የማይተካ መሆኑን ገልጸው፥ ተመራቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉና በህይወት ጎዳናቸው ከጽዩፍ አስተሳሰብና እና ድርጊት ተጠብቀው በተሰማሩበት መስክ የችግሮች መፍትሄ በመሆን ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ዶ/ር ሙሉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ተመራቂዎች ሀገራችሁንና ሕዝባችሁን በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ በመሰማራት ታታሪ፣ የሀገራችሁን ሁለንተናዊ እድገት እና ብልጽግና የምታረጋግጡ ሰላም ወዳድ እንድትሆኑ አደራ እላለሁ ብለዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በምርምር፣ በማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎት (community-based service) እና መማር-ማስተማር መስክ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ኮቪድ-19 ከመጣ በኋላ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን በማዋጣት አቅመ ደካሞችን መርዳታቸውን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ከ3,000 ሊትር በላይ ሳኒታይዘር፣ 4,000 የፊት ጭንብል (face-mask)፣ 1800 ብሊች (bleach) የማምረት ሥራዎችን ሠርቶ በጉራጌ ዞን ለሚገኙና በሥራ ጸባያቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ ተቋማት ማበርከቱን ጠቁመዋል። ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የለይቶ ማቆያ ማዕከል (quarantine center) ሆኖ በማገልገል ላይም ይገኛል ብለዋል።

    በምርምር ረገድም ድርቅን በመቋቋም የሚታወቀውን ቆጮን ጨምሮ በተለያየ መልኩ ለምግብነት የሚውለውን እና የአከባቢው ማኅበረሰብ የኑሮ አለኝታ የሆነውን የእንሰት ተክል እንዳይጠፋ፣ እንዲሁም ዝርያው እንዲጠበቅና እንዲሻሻል የእንሰት ማዕከል በማደራጀት ዝርያዎችን የማሰባሰብ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    ዶ/ር ፋሪስ ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ ተማሪዎች ሥራ ወዳድና ታታሪ፣ በሕግ የበላይነት ላይ የማትደራደሩ፣ የጥላቻን ዘር የማትዘሩ በጥላቻ ሳይሆን የተዘራውን ክፉ አረም በፍቅርና አብሮነት የምትነቅሉ በሥነ-ምግባር የታነጻችሁ ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳትሆኑ አሻጋሪ ናችሁ ብለዋል።

    በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የዛሬው ምረቃ ሥነ ሥርዓት የተሳተፉት በክረምትና በማታ መርሀግብሮች በአምስት ኮሌጆች ስር በሚገኙ 15 ትምህርት ክፍሎች ከዓለምአቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) በፊት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወንድ 597፣ ሴት 143፤ በድምሩ 840 የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች እና በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጆች ስር በሚገኙ አራት ትምህርት ክፍሎች ከወረርሽኙ በኋላም በቴክኖሎጂ አማራጮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ በመደበኛና በማታው የድኅረ ምረቃ መርሀግብሮች ወንድ 81፣ ሴት 8፤ በድምሩ 89 ምሩቃን ናቸው።

    በ2004 ዓ.ም በ13 የትምህርት መስኮች 595 መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ጊዜ በስምንት ኮሌጆችና አንድ ትምህርት ቤት በቅድመ ምረቃ 50 መርሀግብሮች እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ እና 12 ፕሮግራሞች በጠቅላላው ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ፣ በማታና በክረምት መርሃ ግብሮች እያስተማረ ይገኛል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    በ2013 ዓ.ም የጉራጊኛ ቋንቋ ከቅድመ መደበኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ እየተሠራ ነው

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ.ም. የጉራጊኛ ቋንቋ ከቅድመ መደበኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ እየሠራ መሆኑን ገለጸ። ዩኒቨርሲቲው ከ135 በላይ ለመድኃኒት የሚሆኑ እጽዋት ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

    ወልቂጤ (ኢዜአ) – ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአገር በቀል እውቀት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ጥሩውሃ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደተናገሩት፥ እስካሁን የጉራጊኛ ቋንቋ በትምህርት ቤት፣ በመሥሪያ ቤት እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ አልተካተተም። በቋንቋው ውስጥ የተለያየ የአነጋገር ዘዬ መኖር በትምህርት እንዳይሰጥ ካደረጉት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

    በዚህም አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጉራጊኛ ቋንቋን እየረሳ በመምጣቱ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር የፊደል ገበታ መቀረጹን ገልጸዋል። የተወሰኑ ፎነቲኮች በአማርኛ ፓወር ግዕዝ ላይ ባለመኖራቸው ዩኒቨርሲቲው “የተንቢ” የተሰኘ የኮምፒተር መተየቢያ አበልጽጓል።

    በጉራጊኛ ቋንቋ 13 የአነጋገር ዘዬ የሚገኝ ሲሆን በየትኛው መጀመር እንዳለበት ዩኒቨርሲቲው ለማኅበረሰቡ አማራጭ ሃሳቦችን ለማቅረብ ተዘጋጅቷል።

    ”የኮምፒተር መተየቢያና የፊደል ገበታን በማሰልጠን እንዲሁም ሌሎች ግብአቶች እንዲሟሉ በመጠቆም  የጉራጊኛ ቋንቋ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ ለማስቻል እየተሠራ ነው” ብለዋል አቶ ካሳሁን።

    በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ከ135 ዓይነት በላይ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ተክሎች ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ለዚህም የተፈጥሮ መድኃኒት ማምረት የሚያስችል የስልት ሰነድ (strategic document) እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

    እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ መድኃኒቱን ማምረት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው። በዚህም ንጥረ ነገሮችን የመሥራትና የአሠራር ዘዴ ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

    ምርምር እየተደረገባቸው ያሉ እጽዋት ለደም ብዛት፣ ጋንግሪን፣ አስም፣ አጥንት ካንሰርና ለሌሎች በሽታዎች ፈውስ ያስገኛሉ የተባሉ ናቸው።

    ቀደም ሲል ከእጽዋት የባህላዊ መድኃኒቶች ልኬት እንደማይታወቅ ያነሱት አቶ ካሳሁን፥ የፋርማሲና የኬሚስትሪ ባለሙያዎች ከአካባቢው የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር በምርምሩ እንዲሳተፉ ተደርጓል።

    በሌላ በኩል የማኅበረሰቡ ለበርካታ ዓመታት ይተዳደርበት የነበረው ባህላዊ የሕግና አስተዳደር ዘዴ እየቀነሰ በመምጣቱ መልሶ እንዲያንሰራራ ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው ምርምር እያደረገ ነው።

    ቋንቋና ሥነ-ጹህፍ፣ አገር በቀል መድኃኒት፣ አስተዳደርና ሕግ፣ ባህልና የማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኒቨርሲቲው ትኩረት ተሰጥቷቸው ምርምርና ጥናት እየተካሄደባቸው ነው።

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በደቡብ ክልል የሚገኝ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲሆን የተመሠረተው በ2004 ዓ.ም. ነው።

    ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጉራጊኛ ቋንቋ

    Anonymous
    Inactive

    ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 221 የህክምና ዶክተሮችና ስፔሻሊስቶችን አስመረቀ

    ሀዋሳ (ኢዜአ) – የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምንጮች ብቻ ሳይሆኑ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ማፍሪያ ማዕከላት ጭምር መሆን እንዳለባቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሳሰቡ።

    ዩኒቨርሲቲው የካቲት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በአጠቃላይ 221 የጤና ባለሙያዎችን (192 የህክምና ዶክተሮችና 29 ስፔሻሊስት ዶክተሮችን) አስመርቋል። ከተመራቂዎች ውስጥ 22 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውም ተጠቁሟል።

    በምረቃ በዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ እንደገለፁት፥ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ፣ በህክምና ስፔሻሊስትና በሦስተኛ ዲግሪ በርካታ የትምህርት መስኮችን (ፕሮግራሞችን) በመክፈት ከ43 ሺህ 800 በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት መርሀ ግብሮች እያስተማረ ይገኛል። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅም የመምህራን ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

    ሀገሪቱ ካላት ውስን ሀብት ላይ አንድ አራተኛውን በጀት ለትምህርት ማዋሏን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፥ ተመራቂዎችም ያላቸውን ዕውቀት፣ ክህሎትና ጉልበት ላስተማራቸው ማኅበረሰብ በማበርከት ለሀገራቸው ዕድገት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

    ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምንጮች ብቻ ሳይሆኑ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ማፍሪያ ማዕከላትም ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ተመራቂዎች ራሳቸውን ከመጥፎ ምግባር በመቆጠብና ሙያው በሚጠይቀው ሥነ-ምግባር ህሙማንን በፍቅር ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

    በምረቃ በዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ፕሮፌሰር በየነ እንዳሉት፥ ሀገሪቱ ባለፉት ሃያና ሰላሳ ዓመታት ውስጥ በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ እመርታ በማስመዝገብ የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ታላላቅ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና መንግሥታት ዕውቅና ማግኘቷን ተናግረዋል።

    ይሁን እንጂ አሁንም የጤና ሽፋንን ከመጨመርና ጥራትና ፍትሐዊነት ያለው አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚጠይቅ የተናገሩት ፕሮፌሰር በየነ፥ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ጠንክረን በጋራና በትብብር መንፈስ መሥራት አለብን ብለዋል። የዛሬ ተመራቂዎችም የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋዎች መሆናቸውን በመረዳት ሀገራቸውን ማገልገል እናዳለባቸው ጠቁመዋል።

    በሙያቸው ገፍተው ዕውቀትና ክህሎታቸውን በማዳበርም የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡና ችግር ፈቺ በሆኑ ምርምሮች ውስጥ በመሳተፍ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለውን ፈርጀ ብዙ ለውጥ የማቀጣጠልና የማስቀጠል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል ።

    ከተመራቂዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳልያ ተሸላሚ የሆነው ዶ/ር አቤል ጌታቸው በሰጠው አስተያየት፥ የህክምና ትምህርት ጽናትን የሚጠይቅ መሆኑን ገልፆ ሁኔታዎችን በትዕግስት በማለፍ ለዚህ መብቃቱን ተናግሯል።

    የህክምና ሙያ በራሱ ለሰዎች ክብር መስጠትና ርህራሄ መላበስን የሚያስተምር እንደሆነ የተናገረው ዶ/ር አቤል፥ ያለአድሎ ሰብዓዊነትን በመላበስ ህብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን አስረድቷል።

    በውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻላይዝድ በማድረግ የተመረቀው ዶ/ር ሙባረክ ሁሴን በበኩሉ፥ የህክምና ሥነ-ምግባር ከሀሳብ ይልቅ በተግባር የሚገለፅ መሆኑንና ታካሚዎችን እንደ ቤተሰብ በማየት ያለአድሎ ለማገልገል መዘጋጀቱን ተናግሯል።

    የዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ዶክትሬት ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ለ11ኛ ዙር ሲሆን ስፔሻሊስት ሀኪሞችን ደግሞ ለ4ኛ ዙር መሆኑ ተዘግቧል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 221 የህክምና ዶክተሮችና ስፔሻሊስቶችን አስመረቀ

    Anonymous
    Inactive

    የተሻሻለው የወሎ ቴሪሸሪ የህክምናና የማስተማሪያ ሆስፒታል ዲዛይን ለሕዝብ ይፋ ሆነ

    ደሴ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – በጥቂት ሀገር ወዳድ ግለሰቦች ሀሳቡ ተጠንስሶ ሀገራዊ የሕዝብ ፕሮጀክት የሆነው የወሎ ልዕለ ህክምና የማስተማሪያ ሆስፒታል /ሦስተኛ ትውልድ ሆስፒታል/ (Wollo Tertiary Care and Teaching Hospital) ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በየጊዜው እየፈታ ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ተዳርሷል።

    ይህንን የሕዝብ ፕሮጀክት ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ያለ በጀትና ዲዛይን በባለቤትነት የተረከበው ወሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሥራ ለመግባት ከሕዝብ የተሰበሰበውን በጀትና ዲዛይን ሊያስረክብ የሚችል አካል በመጥፋቱ ተቸግሮ ቆይቷል።

    ዩኒቨርሲቲው የሕዝቡ ፍላጎትና ጥያቄዎች እየተበራከቱ ሲመጡበት የዋና ሆስፒታል ዲዛይን መረከብ እስኪችል ድረስ በራሱ ወጭ በ460 ሚሊዮን ብር የተማሪዎች መኖሪያ G+4 10 ህንጻዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል።

    የሆስፒታሉን ዲዛይን የተረከበው አማካሪ ድርጅት ሰርቶ ማቅረብ ባለመቻሉ በ2011 ዓ.ም. አጋማሽ ዩኒቨርሲቲው ውለታውን በማቋረጥ ከአዲሱ የኤምቲቲ አማካሪ አርክቴክቶችና ምህንድስና ኃ/የተ/ የግል ኩባንያ (MTT Consulting and Architects and Engineers PLC) ድርጅት ጋር ውለታ በመፈጸም ዲዛይኑን ለአዲሱ ድርጅት አስረክቧል።

    የኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት የተረከበው ዲዛይን ከዓለም የቴክኖሎጅ እድገትና ከዘመኑ የኪነ ህንጻ ጥበብ ጋር ሊዛመዱ በማይችሉ የመዋቅር፣ የኤሌክትሮ መካኒክ፣ የፍሳሽ ማስወገጃና መሰል በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት በመሆኑ የዲዛይን ማሻሻያዎችን ሠርቶ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

    የኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት የሆስፒታሉን ዲዛይን ከማሻሻሉም ባሻገር የሆቴል ቱሪዝምን ለማበረታታት ባለ 5 ኮኮብ ሆቴል፣ የባሕላዊ ህክምና መስጭያ ማዕከልና ከአካባቢው ባህልና ሥነ-ምህዳር ጋር የሚዛመዱ ተያያዥ ማዕከላትን የሆስፒታሉ አካል እንድሆኑ በማካተት ይፋ አድርጓል።

    ይህንን ይፋ የሆነ የሆስፒታል ዲዛይን የተመለከቱት የደሴ ከተማ የሕዝብ ተወካዮች፣ የዘርፉ ባለሞያዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለሙያዎች በተሻሻለው ዲዛይን ላይ የተሰማቸውን ስሜት በመግለጽ ቢካተቱ ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል።

    የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን ዋናውን ሆስፒታል ወደ መሬት ለማውረድ ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች በመጥቀስ ዩኒቨርሲቲው የሕዝብን ስሜት ለመጠበቅ በራሱ የተጓዘውን ርቀት አብራርተዋል። ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ከሕዝብ የተሰበሰበውን አምስት ሳንቲም እንኳን እንዳልተረከቡ በመግለጽ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ አማካሪው ኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት የሀሳቡ ጠንሳሽ ዶ/ር በላይ አበጋዝን ጨምሮ በጤና ሚኔስተርበአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲበጥቁር አንበሳና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ያሉ የዘርፉ ምሁራንን በማሳተፍ ሆስፒታሉ እውን እንድሆን ለተሠራው ሥራ አመስግነዋል።

    የኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት በበኩሉ በሕዝብ የተነሱትን ጥያቄዎችና አስተያየቶች በማካተት ፕሮጀክቱ ወደ መሬት በቅርብ ቀን እንዲወርድ የቻለውን ሁሉ እንደሚሠራ ቃል ገብቷል።

    ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የወሎ ልዕለ ህክምና የማስተማሪያ ሆስፒታል


    Anonymous
    Inactive
    • ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲውን የመማር-ማስተማር ሥራ አውከዋል ባላቸው 21 ተማሪዎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ወሰደ።
    • ዩኒቨርሲቲው “ንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል ደማቅ የኪነ ጥበብ ምሽት አካሂዷል።

    ባሕር ዳር (ሰሞነኛ) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን በማወክ በተለዩና ተጨባጭ ማስረጃ በተገኘባቸው 21 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ። በዩኒቨርሲቲው አንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ሙሉ በሙሉ መጀመሩንም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል።

    የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ፥ አራት ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት መታገዳቸውን እና በ21 ተማሪዎች ላይ ደግሞ ከአንድ ዓመት እገዳ ጀምሮ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል። ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት በመለየትና በማጣራት በቀጣይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

    የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ከመማር-ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን ተማሪዎችን በሥነ ምግባር በማነጽ ችግር ፈቺ ሆነው እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባም ዶ/ር ዘውዱ ተናግረዋል።

    ባለፉት ሳምንታት ተማሪዎች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ተደጋጋሚ ውይይትና ምክክር ቢደረግም ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በፖሊ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ፔዳና ይባብ ግቢዎች ትምህርት ተቋርጦ እንደነበር ተዘግቧል።

    ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳንወጣ፥ በዩኒቨርሲቲው ፔዳ ግቢ አዳራሽ “ንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲዉ ተማሪዎች፣ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ደማቅ የኪነ ጥበብ ምሽት ተካሂዷል።

    የኪነ ጥበብ ምሽቱን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲዉ የዉስጥ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ አክሎግ፥ በተማሪዎች አነሳሽነት እና በባህል ማዕከሉ ተባባሪነት ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን አመስግነዉ፤ መሰል ዝግጅቶች በሚኖሩበት ጊዜ የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንደማይለያቸዉ ጠቁመዋል። አክለዉም፥ የዉጭ ሀገራት ተሞክሮዎችን በመጥቀስ መሰል የኪነ ጥበብ ፕሮግራሞች በተማሪዎች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩ መዘውተር አለባቸው ብለዋል።

    በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዉ ለታዳሚዎች አነቃቂ ንግግር ያደረጉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዉ የሳይኮሎጅ መምህር አቶ ታምሩ ደለለኝ እንደተናገሩት፥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁለት ዋነኛ ችግሮችን ሊያስቡባቸው ይገባል ብለዋል። አንደኛው ስብዕናና ክህሎት በማይገነቡ ጊዜያዊ እርካታ ላይ በሚያተኩሩ ክዋኔዎች ለምሳሌ ቲሸርቶችን እያሳተሙ የቀለም ቀን (Color Day)፣ የሕፃናት ቀን (Baby Day)፣ የውሃ ቀን (Water Day) ወይም ሌሎች የመሳሰሉት ላይ ማተኮር ሲሆን፤ ሌላው እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣው ደግሞ ሰክኖ ከመወያየት ይልቅ አለመግባባትና ግጭት በስፋት መከሰት ናቸው። ከአለመግባባት እና ግጭት ጋር በተያያዘም ተማሪዎች በዙሪያቸው ያሉ ሌሎች ተማሪዎችን እንደ ተማሪ እንዲመለከቷቸውና እርስ-በእርስ እንዲተሳሰቡ መክረዋል። አቶ ታምሩ በመቀጠልም ተማሪዎች ትዕግስትና ማስተዋልን አጥብቀዉ በመያዝ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን ተጨማሪ ስንቅ የሚያገኙበት እንዲሆን እንዲያደርጉት አሳስበዋል።

    በኪነ ጥበብ ምሽቱ “የንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በጎ ሀሳብ አፍላቂ ተማሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን በቀጣይም መሰል ፕሮግራሞች በየ 3 ሳምንቱ እንደሚካሄዱ የዩኒቨርሲቲዉ የተማሪዎች ባህል ማዕከል ኃላፊ ተማሪ ተመስገን ሙሉቀን ተናግረዋል። በኪነ ጥበብ ምሽቱ በርካታ ታዳሚያን የተገኙ ሲሆን፥ በበመርሃ-ግብሩ መደሰታቸዉን ለመረዳት ተችሏል።

    በኪነ ጥበብ ምሽቱ በርካታ የግጥም ሥራዎችን ጨምሮ ‘በቃን’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ አዝናኝና አስተማሪ ጭዉዉት አንዲሁም ‘ከኛ ጓዳ’ የተሰኘ ተከታታይ የኮሜድ ሥራ ቀርቧል።

    ምንጮች፦ ፋና/ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) በትብብር ለመሥራት ስምምነት አደረገ

    ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አሜሪካን ሀገር ካምብሪጅ ከተማ ከሚገኘው ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) ከተሰኘው ዕውቅ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረመ።

    ሁለቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡትን ውል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችላቸውን የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች ማከናወንም ጀምረዋል።

    በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ሐብቴ ዱላ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ጋር የሚኖረው የትብብር ሥራ በዋናነት በኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ የሚሰጡትን የትምህርት ፕሮግራሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ የቤተ-ሙከራ ትምህርት ለማስደገፍ የሚያስችልና በመምህራንና በተማሪዎች የሚሠሩትን የምርምር ሥራዎች እና ፕሮጀክቶች ውጤታማነት ለማሻሻል ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

    እንዲሁም የትብብር ሥራው የኮሌጁን የመማር-ማስተማር ሥራ ለማዘመንና ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን ለማስጠበቅ የሚያግዘው ከመሆኑም ባሻገር በምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስኮች ለሚከናወኑ ሥራዎች ስኬታማነት የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ዶ/ር ሐብቴ አስረድተዋል።

    በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ኮርአብዛ ሸዋረጋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፥ ኢንስቲትዩቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በገባው ውል መሠረት በያዝነው የ2012 የትምህርት ዘመን ከሁለተኛው መንፈቀ-ዓመት /ሴሚስተር/ ጀምሮ ዓመታዊ ክፍያው ከ160 ሺህ በላይ የሆነውን የኦንላይን ትምህርት በነጻ በመስጠት የኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅን ተጠቃሚ ማድረግ ይጀምራል። ለዚህም ዕቅድ ተግባራዊነት ኢንሰቲትዩቱ ድጋፍ ሰጪ ቡድን ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በመላክ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።

    በዚህም መሠረት ድጋፍ ሰጪው ቡድን የኦንላይን ትምህርቱን ለመስጠት ወሳኝ የሆኑት የቤተ-ሙከራ ዕቃዎችን ይዞ በመምጣት ለዩኒቨርሲቲው በእርዳታ አበርክቷል። የተበረከቱት ዕቃዎች እስካሁን ድረስ በንድፈ-ሐሳብ /theory/ ብቻ ሲሰጡ የነበሩትን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ /artificial intelligence/፣ ሮቦቲክስ /robotics/ እና ተዛማጅ የትምህርት ዓይነቶች የማስተማር ዘዴ በተግባር የታገዘ አንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አቶ ኮርአብዛ ገልጸዋል።

    ድጋፍ ሰጪ ቡድኑ ለዩኒቨርሲቲው ያበረከታቸውን የቤተ-ሙከራ መሣሪያዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል ከኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅና ከኢንጅነሪንግና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ለተውጣጡ 10 መምህራን ከጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ያዘጋጀውን በኮምፒዩተር ፕሮግራም ቋንቋ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።

    በመጨረሻም ዶ/ር ሐብቴ አክለውም፥ ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመሥራት እንዲችሉ በማገናኘቱ ሥራ በአሜሪካ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሚና ከፍተኛ እንደነበረ በመግለፅ ይህንን የዜግነት ግዴታቸውን ለተወጡት የዲያስፖራ አባላት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እና በራሳቸው ስም አመስግነዋል።

    ምንጭ፦ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ

Viewing 9 results - 1 through 9 (of 9 total)