በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሪፈራልና ማስተማሪያ ሆስፒታል የእድሳት ግንባታ ሥራ በይፋ ተጀመረ

Home Forums Semonegna Stories ትምህርት፣ ጤና እና ሕብረተሰብ ― ሰሞነኛ ዜናዎች፣ መረጃዎች በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሪፈራልና ማስተማሪያ ሆስፒታል የእድሳት ግንባታ ሥራ በይፋ ተጀመረ

#48575
Semonegna
Keymaster

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሪፈራልና ማስተማሪያ ሆስፒታል የእድሳት ግንባታ ሥራ በይፋ ተጀመረ

ሰሞነኛ (ዲላ ዩኒቨርሲቲ) – በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሪፈራልና ማስተማሪያ ሆስፒታል የእድሳት ግንባታ ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሄደ። የእድሳት ሥራው መጀመሩን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ይፋ አድርገዋል።

ዶ/ር ችሮታው ባደረጉት ንግግር፥ ሆስፒታሉ ያሉበትን መሠረታዊ ችግሮች በትኩረት መፍታት ከተቋሙ ዋና ዋና ተግባራት አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለያዩ ሀገራዊና ተቋማዊ ምክንያቶች ግንባታው ቶሎ ያልተጠናቀቀውን አዲሱን የሕክምና እና ማስተማሪያ ሆስፒታል ለማጠናቀቅ ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ ነባሩን ሆስፒታል በልዩ ሁኔታ እድሳት አድርጎ ለታካሚሆችና ለአካሚዎች ጭምር በሚመጥን ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ነባሩ ሆስፒታል አሁን ባለበት ደረጃ የጌዴኦ ዞንን እና አጎራባች አካባቢዎችን ማኅበረሰቦች የሕክምና ፍላጎት ለማስተናገድ ችግሮች እንዳሉ የሚታወቅ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ችሮታው፥ ስለሆነም በሆስፒታሉ ሥራ አመራር ቦርድ ታምኖበት አጠቃላይ የእድሳት ሥራው መንግሥት በሚፈቅደው የፋይናንስ ሂደት አልቆ ዛሬ [ሐምሌ 5 ቀን፥ 2014 ዓ.ም] በይፋ እንዲጀመር ተደርጓል ብለዋል።

ዶ/ር ችሮታው አክለውም፥ እንደ ሀገር ከፍተኛ የሆነ የግንባታ ዘርፉ መቀዛቀዝ ውስጥ ቢሆንም ሆስፒታሉ ካለበት ደረጃ እንዲሁም ከሕብረተሰቡ የሕክምና አገልግሎት አንገብጋቢ ጥያቄ አንፃር አዲሱ እንሰኪጠናቀቅ ነባሩን ሆስፒታል በልዩ ሁኔታና በጥራት አድሶ ጥቅም ላይ ማዋል በትኩረት የሚሠራ ነው ብለዋል። ለዚህም ሥራውን በተቀላጠፈ እና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ አድሶ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚመለከተው ሁሉ በርብርብ እንደሚሠራ ተገልጿል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው፥ ሆስፒታሉ ለጌዴኦ ዞን ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ክልሎች ጭምር አገልግሎት ሰጪ በመሆኑ “መከፈል ያለበት መስዋዕትነት ሁሉ ተከፍሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ እድሳቱ እንዲጠናቀቅ ቦርዱም ሆነ የዞን አመራሩ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል። የሥራ ተቋራጭ ድርጅቱ የተጣለበት ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፥ የዩኒቨርሲቲው አመራር፣ የዞኑና አካባቢው አመራር እንዲሁም ሕብረተሰቡ በጋራ ተባብረው ውጤታማ የሆነ እድሳት እንዲከናወን ይሠራሉ ብለዋል።

የዲላ ከተማ ከንቲባና የሆስፒታሉ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋፅዮን ዳካ በበኩላቸው፥ ሆስፒታሉ ብዙ ማኅበረሰብ የሚገለገልበት ሆኖ ሳለ ከጊዜ ወደ ጊዜ አገልግሎት አሰጣጡ እየተዳከመ ከአቅም በታች የሆነ አገልግሎት እየሰጠ መጥቷል፤ ስለሆነም ከዚህ ችግር እንዲወጣ እና ሕብረተሰቡ ማገኘት ያለበትን አገልግሎት የመስጠት አቅሙን በተሻለ ለመመለስ በርብርብ ይሠራል ብለዋል።

የእድሳት ሥራውን ለማከናወን ውል የወሰደው ደሳለኝ አሥራደ ህንጻ ሥራ ተቋራጭ የተባለ ድርጅት ሲሆን ተወካዩ አቶ ፍጹም እምሩ ሆስፒታሉ ከአምስት ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚታከምበት ብቸኛ የዞኑ ሆስፒታል እንደመሆኑ የእድሳት ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ተወካዩ አክለውም የተሻለ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በመመደብ በተሻለ ጥራትና በተፋጠነ ጊዜ ግንባታውን አጠናቀው በማስረከብ ሕብረተሰቡ እና ዩኒቨርሲቲው የጣሉብንን አደራ እንወጣለን ነው ያሉት።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክት ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር በፍቃዱ መኩሪያ በዕለቱ የእድሳት ግንባታውን አስመልክቶ ባቀረቡት ገለፃ የሆስፒታሉን አጠቃላይ ገፅታ በከፍተኛ ጥንቃቄ ጥናት ተደርጎ ዲዛይን ተሠርቷል ብለዋል።

ይሄው የእድሳት ዲዛይን ለጤና ሚኒስቴር ቀርቦ ከተገመገመ በኋላ የሚጠበቀውን ደረጃ ማሟላቱ በመረጋገጡ የእድሳት ግንባታው መፈቀዱን ገልፀው፣ በጥናቱ የተለየቱን ችግሮች የሚፈታ እድሳት እንደሚሠራ እና የተወሰኑ ተጨማሪ አዳዲስ ግንባታዎችም እንደተካተቱ አስረድተዋል።

በእድሳት ግንባታ ሥራ ማስጀመሪያ መርሃግብሩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሆስፒታሉ የሥራ አመራር ቦርድ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲውና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሆስፒታሉ ማኅበረሰብ አካላት የተገኙ ሲሆን ግንባታው መጀመሩን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ይፋ አድርገዋል።

ምንጭ፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሆስፒታል እድሳት ተጀመረ