Home › Forums › Semonegna Stories › ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን) › ገዳዮችና አስገዳዮች ሆይ! በጭራሽ አይሳካላችሁም!!! ― መቅደስ ፀጋዬ
ገዳዮችና አስገዳዮች ሆይ! በጭራሽ አይሳካላችሁም!!!
(መቅደስ ፀጋዬ)
ገዳዮችና አስገዳዮች ሆይ! በጭራሽ አይሳካላችሁም!!!
የሞታችሁ፣ የቆሰላችሁና በገዛ ሀገራችሁ የተፈናቀላችሁ ወገኖቼ!!!
ህመማችሁ ህመሜ፣ ሞታችሁ ሞቴ ነው!!! አቤት ስንቱን የጭካኔ ዓይነት ዓየን!!! አማራ በመሆናችሁ ብቻ ይህንን ግፍ የተቀበላችሁ ወገኖቼ፥ ነፍሳችሁን እግዚአብሔር አምላክ በገነት ያኑረው!!! በየዋሁ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን ይህን በደል እግዚአብሔር ያያል። ከሰው በላይ የእርሱን ፍርድና ከለላነት እንጠብቃለን!!! እስትንፋሴ እስክታልፍ በሀገሬ ተስፋ አልቆርጥም!!!
ገዳዮችና አስገዳዮች ሆይ! በጭራሽ አይሳካላችሁም!!!
ሕዝባችን ተባብሮና ተከባብሮ ብቻ ሳይሆን ተዛምዶና ተዋሕዶ ለዘመናት የኖረ ሕዝብ በመሆኑ ምን ያክል የላቀ ሰላማዊ ሕዝብ እንደሆነ ያስመሰከረ ሕዝብ ነው። የናንተ ምኞት ግን አሁን እየታየ ያለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ግድያና ማፈናቀል በሕዝቦች መካከል የተፈጠረ መስሎ እንዲታየን ማድረግና እርስ በርሳችን መተላለቅ እንድንጀምር መሆኑን እናውቃለን። በጭራሽ አይሳካላችሁም!!! እንእደናንተ ምኞትና ጥረት ቢሆን ኖሮ ሀገራችን የአንዲት ጀንበር እድሜ ባልኖራት ነበር፤ ግን አልተሳካላችሁም!! አይሳካላችሁምም!!
የምወዳችሁ ወገኖቼ፥
ይህ ወቅት በውስጣችን ብዙ ልዩነቶች ያሉበትና የውጭ ጠላቶቻችን ደግሞ ያለንበትን ሁኔታ እንደጥሩ አጋጣሚ ለመጠቀም እየተሯሯጡ ያለበት ጊዜ እንደሆነ ሁላችንም እንደምንገነዘበው እምነት አለኝ። ታዲያ ጠላቶቻችን የሚያተርፉት እርስ በርሳችን መበላላት የጀመርን ቀን ሲሆን፥ የሚከስሩት ደግሞ በትዕግስትና በፍጹም ሰላማዊነት ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ማለፍ ስንችል ብቻ ነው። ዓላማቸው እርስ በርሳችን እንድንጫረስ ነው ካልን፥ ድላችን ደግሞ አንድነታችንንና ሰላማችንን ጠብቀን መቆየታችን ላይ ነው የሚሆነው። ስለዚህ እያንዳንዳችን ሀገራችንን የምንወድ ዜጎች ሁሉ የአካባቢያችንን ሰላም በንቃት ከመጠበቅ ባሻገር፥ ተቃውሞዎቻችንንና ቁጣችን እንኳ ሳይቀር የሀገራችንን ሰላምና አንድነት በማያናጋ መልኩ ማድረግ እንዳለብን መረዳት ያስፈልገናል። ሰላም ላይ የሚደረሰው በሰላም መንገድ ብቻ ስለሆነ።
ከመንግሥት በኩል ደግሞ እጅግ ፈጣንና የሚታይ እርምጃ ሲወሰድ ማየት እንፈልጋለን።
ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ይጠብቅልን!!
መቅደስ ፀጋዬ
መቅደስ ፀጋዬ ኢትዮጵያ ውስጥ ዝናን ካተረፉ የፊልም ባለሙያዎች አንዷ ስትሆን፥ የተለያዩ ፊልሞችን ፕሮዲዩስ ከማድረግና በተለያዩ ፊልሞች ላይ ከመተወን በተጨማሪ (ትስስር፣ የ አዳም ገመና፣ ዘራፍ፣ የከረመ…) ራሷ የመሠረተችውና በዋና ሥራ አስኪያጅነት የምትመራው መቅዲ ፕሮዳክ ሽን በተመልካች ዘንድ ተወዳጅ የነበሩትን ሞጋቾች እና ግማሽ ጨረቃ የተሰኙ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማዎችን፥ እንዲህም መቅዲ ሾው የተሰኘ የቴሌቭዥን ሳምንታዊ መርሀግብር አቅርቧል።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።