Home › Forums › Semonegna Stories › የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች › የተሻሻለው የወሎ ቴሪሸሪ የህክምናና የማስተማሪያ ሆስፒታል ዲዛይን ለሕዝብ ይፋ ሆነ
የተሻሻለው የወሎ ቴሪሸሪ የህክምናና የማስተማሪያ ሆስፒታል ዲዛይን ለሕዝብ ይፋ ሆነ
ደሴ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – በጥቂት ሀገር ወዳድ ግለሰቦች ሀሳቡ ተጠንስሶ ሀገራዊ የሕዝብ ፕሮጀክት የሆነው የወሎ ልዕለ ህክምና የማስተማሪያ ሆስፒታል /ሦስተኛ ትውልድ ሆስፒታል/ (Wollo Tertiary Care and Teaching Hospital) ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በየጊዜው እየፈታ ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ተዳርሷል።
ይህንን የሕዝብ ፕሮጀክት ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ያለ በጀትና ዲዛይን በባለቤትነት የተረከበው ወሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሥራ ለመግባት ከሕዝብ የተሰበሰበውን በጀትና ዲዛይን ሊያስረክብ የሚችል አካል በመጥፋቱ ተቸግሮ ቆይቷል።
ዩኒቨርሲቲው የሕዝቡ ፍላጎትና ጥያቄዎች እየተበራከቱ ሲመጡበት የዋና ሆስፒታል ዲዛይን መረከብ እስኪችል ድረስ በራሱ ወጭ በ460 ሚሊዮን ብር የተማሪዎች መኖሪያ G+4 10 ህንጻዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል።
የሆስፒታሉን ዲዛይን የተረከበው አማካሪ ድርጅት ሰርቶ ማቅረብ ባለመቻሉ በ2011 ዓ.ም. አጋማሽ ዩኒቨርሲቲው ውለታውን በማቋረጥ ከአዲሱ የኤምቲቲ አማካሪ አርክቴክቶችና ምህንድስና ኃ/የተ/ የግል ኩባንያ (MTT Consulting and Architects and Engineers PLC) ድርጅት ጋር ውለታ በመፈጸም ዲዛይኑን ለአዲሱ ድርጅት አስረክቧል።
የኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት የተረከበው ዲዛይን ከዓለም የቴክኖሎጅ እድገትና ከዘመኑ የኪነ ህንጻ ጥበብ ጋር ሊዛመዱ በማይችሉ የመዋቅር፣ የኤሌክትሮ መካኒክ፣ የፍሳሽ ማስወገጃና መሰል በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት በመሆኑ የዲዛይን ማሻሻያዎችን ሠርቶ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።
የኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት የሆስፒታሉን ዲዛይን ከማሻሻሉም ባሻገር የሆቴል ቱሪዝምን ለማበረታታት ባለ 5 ኮኮብ ሆቴል፣ የባሕላዊ ህክምና መስጭያ ማዕከልና ከአካባቢው ባህልና ሥነ-ምህዳር ጋር የሚዛመዱ ተያያዥ ማዕከላትን የሆስፒታሉ አካል እንድሆኑ በማካተት ይፋ አድርጓል።
ይህንን ይፋ የሆነ የሆስፒታል ዲዛይን የተመለከቱት የደሴ ከተማ የሕዝብ ተወካዮች፣ የዘርፉ ባለሞያዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለሙያዎች በተሻሻለው ዲዛይን ላይ የተሰማቸውን ስሜት በመግለጽ ቢካተቱ ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን ዋናውን ሆስፒታል ወደ መሬት ለማውረድ ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች በመጥቀስ ዩኒቨርሲቲው የሕዝብን ስሜት ለመጠበቅ በራሱ የተጓዘውን ርቀት አብራርተዋል። ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ከሕዝብ የተሰበሰበውን አምስት ሳንቲም እንኳን እንዳልተረከቡ በመግለጽ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ አማካሪው ኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት የሀሳቡ ጠንሳሽ ዶ/ር በላይ አበጋዝን ጨምሮ በጤና ሚኔስተር፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በጥቁር አንበሳና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ያሉ የዘርፉ ምሁራንን በማሳተፍ ሆስፒታሉ እውን እንድሆን ለተሠራው ሥራ አመስግነዋል።
የኤምቲቲ አማካሪ ድርጅት በበኩሉ በሕዝብ የተነሱትን ጥያቄዎችና አስተያየቶች በማካተት ፕሮጀክቱ ወደ መሬት በቅርብ ቀን እንዲወርድ የቻለውን ሁሉ እንደሚሠራ ቃል ገብቷል።
ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ