Home › Forums › Semonegna Stories › ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን) › ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ለክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ
ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ለክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ
ነጋችንን እንዳንፈራ ሕግ ተርጓሚው ይፈራ!
ክብርት ፕሬዝደንት፥ እንደሚያውቁት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ባለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በጭፍን ከመደገፍ እና ከመቃወም ወጥቶ በምክንያት መቃወም እና መደገፍ የፖለቲካ ባህል፣ አስተሳሰብ እንዲገነባ የራሱን ሚና ሲጫወት የቆየ ፓርቲ ነው። ይሄ ስልጡን የፖለቲካ ባህል እንደምንፈልገው ፍሬ ባያፈራም ቀላል የማይባል የፖለቲካ ባህል ለውጥ ጭላንጭል አይተናል ብለን እናስባለን። ይህን አዲስ ባህል የፈጠረ ፓርቲ ግን ለሱ የሚመጥነውን ያህል ክብር ሊሰጠው ቀርቶ በየዘመኑ የመጡ ገዥዎች አና ጽንፈኛ ፖለቲከኞች በሴራ አላላውስ ብለውታል።
ኢዴፓ ከለውጡ በፊት ባሉት ሁለት ዓመታት እና ከለውጡ ማግስት ባሉ ሁለት ዓመታት የተቀነባበረ በሚመስል ደረጃ ፓርቲያችንን የማዳከም እና ከፖለቲካው መድረክ እንዲገለል የማድረግ ከፍተኛ ደባ እየተሠራበት ይገኛል። ይህን በፓርቲው ህልውና ላይ የተቃጣውን መሠረተ ሰፊ የማፍረስ እርምጃ በተለያዩ መድረኮች እያሸነፍን እዚህ ብንደርስም፥ አሁንም ድረስ በግፍ የተነጠቅነውን የፓርቲውን ቢሮዎች፣ ንብረቶች ገንዘቦች እና ሰነዶች ለማስመለስ በፍትህ አደባባይ እየታገልን ነው። አሁንም በቢሮክራሲ ውጣ ውረድ እየተንገላታን ነው፤ ባለፉት አራት ዓመታት በፓርቲያችን ህልውና ላይ እየደረሰ ያለውን ፈተና እየታገልን ባለንበት ሁኔታ ይባስ ብሎ የአርቲስት ሃጫሉን ሞት ተከትሎ ሌላ የፖለቲካ ጫና እየደረሰብን ይገኛል። ይኸውም የፓርቲያችን ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ያለጥፋታቸው የፖለቲካ ጥቃት ሰለባ እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋልል። አቶ ልደቱ በወንጀል ድርጊት ውስጥ መሳተፋቸው በተጨባጭ ማስረጃ እስከተረጋገጠባቸው ድረስ አይያዙ አንልም፤ ለሕግ የበላይነት ሲታገል የኖረ ፓርቲ በዚህ ረገድ ምንም ብዥታ የለበትም። ነገም ከነገ ወዲያም ማንም በፖለቲካ ፓርቲ አመራርነትና አባልነት ስም ከሕግ ማምለጥ አለበት ብለን አናምንም፤ ነገር ግን ፖሊስ እርቸውን አስሮ ማስረጃ ሲፈልግ ሲታይ፣ ማስረጃ ማቅረብ ተስኖት ፍርድ ቤት ልቀቅ ብሎ ሲወስን እምቢኝ ካለ የታሰረው ወንጀል ሠርቶ ሳይሆን ለምን የተለየ አሰብክ ተብሎ እንደሆነ ድርጊቱ ያሳብቃል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ልደቱ መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በማቅረባቸውና በመቃወማቸው ብቻ እንደታሰሩ በፍትህ ሂደቱ ላይ የታዩትን ህጸጾች ስለታዘብኩ ነው ለእርስዎ አቤት ማለቴ። አቶ ልደቱ የሃጫሉን ሞት ተከትሎ ሁከት በተቀሰቀሰበት ሰዓት የፌዴራል ፖሊስ ለህይወትህ ያሰጋሃል ብሎ አጅቦ ከቢሾፍቱ ወደ አዲስ አበባ አምጥቷቸዋል። ይሄ ሆኖ ሳለ በፖሊስ የተከሰሱበት እና የተጠረጠሩበት ወንጀል የቢሾፍቱ ከተማ ወጣቶችን አደራጅተሃል፣ በገንዘብ ረድተሃል እና አስተባብረሃል ቢሆንም ተጨባጭ ማስረጃ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ሊያቀርብ አልቻለም። በኋላም የተሰጠውን የምርመራ ግዜ በመጨረሱና አቃቢ ሕግም ተጨማሪ የምርመራ ግዜ ባለመጠየቁ ፍርድ ቤቱ በነፃ አሰናብቷቸዋል። ነገር ግን ይህንን የፍርድ ቤት ውሳኔ ሰምቶ ፖሊስ መልቀቅ ሲገባው፥ ከ17ቀናት በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ አስሮ ሲያሰቃያቸው ቆይቷል። እኛም በፍትህ ሂደቱ ተስፋ ቆርጠን፣ አቶ ልደቱም ጠበቆቻቸውን አሰናብተው ፌደራል ላይ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ልንመሠርት ስንዘጋጅ ደግሞ ሌላ ክስ አዳማ ላይ ተከፈተባቸው።
ይሄ ክስ በመጀመሪያው የቢሾፍቱ ከተማ የክስ መዝገብ ላይ ሕገ-ወጥ ሽጉጥ ተገኝቶባቸዋል ተብሎ ማስረጃ ቀርቦበት ውድቅ የተደረገ የክስ ጭብጥ ነው። የሆነው ሆኖ በሕገ-ወጥ መሣሪያ በመያዝ በሚል ምሥራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢከሰሱም ፍርድ ቤቱ የአቃቢ ሕግንና የጠበቆቻችንን የሕግ ክርከር መርምሮ አቶ ልደቱን በ100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ብር ዋስትና ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ወሰነ። እኛም 100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ብር አስይዘን ማስፈቻ ትዕዛዝ ለፖሊስ ብንወስድም አሁንም ፖሊስ ትዕዛዙን አልፈፅምም አለ። እኛም ትዕዛዙን ለሰጠው ፍርድ ቤት አቤት ብለን መልስ ሊነገረን ለበነጋታው ቀጠሮ ይዘን መጣን። ነገር ግን ማታ የአቶ ልደቱ ዋስትና እንደታገደ በመገናኛ ብዙኃን ሰማን። በዚህ ሁኔታ አቶ ልደቱ ከልብ ህመም ጋር ተያይዞ የልብ ቀዶ ጥገና ባደረጉበት አሜሪካ ቀጠሮአቸው እንዲያልፍ ተደርጎ፥ ከዚህ በተጨማሪ ካለባቸው የአስም ህመም የተነሳ ለኮሮና ተጋላጭ መሆናቸው በሐኪሞችም በፍርድ ቤቶቹም ታምኖበት ጭምር ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ የተደረገው ጥረት በፖሊስ እምቢተኝነት ህይወታቸው አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጓል። በሂደቱ ሁሉ አቶ ልደቱ እያቀረቡት ያለው ቅሬታ ሁሉ ተቀባይነት እያጣ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ እየተሻረ የፖለቲካ ውሳኔ አሸናፊ እየሆነ ይገኛል። አሁንም እንደቀጠለ ነው። እና በፍትህ አደባባይ አቶ ልደቱ ደግመው ደጋግመው ነፃ ቢሆኑም ፖሊስ አለቅም ማለቱን ሳይ ነው የአቶ ልደቱ እስር ሕግ ጥሰው ሳይሆን በፖለቲካ እስር ነው ብዬ በእርግጠኝነት መናገሬ፤ እንጂማ ሁለቴ ያሸነፈ አይደለም አንድ ግዜም ያሸነፈ ቤቱ እስር ቤት አይሆንም ነበር። ይሄ የሚያሳየው የፍትህ ሥርዓቱ ላይ የበዛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መኖሩን ነው።
ክብርት ፕሬዝደንት፥ የፍትህ ተቋሙ በእርስዎ መመራት ሲጀምር በፍትህ መጓደል ላለፉት 27 ዓመታት ፍዳውን ሲያይ የነበረው ዜጋ እፎይ ይላል ብዬ በግሌ ተስፋ አድርጌ ነበር፤ ሕግ ተርጓሚው ከሕግ አስፈፃሚው ተፅዕኖ ወጥቶ የሚገባውን ክብር እና የሚወስነውም ውሳኔ በአስፈጻሚው አካል ሳይሸራረፍ ተፈፃሚ ይሆናል ብዬም ነበር። ፍትህ እና ርትዕ በእርስዎ አመራር ይሰፍናል ብዬ በእርስዎ የቀደመ ልምድ ፍፁም ተማምኜ የነበረ ቢሆንም እየሆነ ያለው የተገላቢጦሽ ነው። ፍትህ ከቀደመው ጊዜ በባሰ ችግር ውስጥ መውደቁን እኔ በግሌ በዚች ሁለት ወር በተግባር ባየሁት ነገር አረጋግጫለሁ። እርስዎ የተሰጠዎትን ኃላፊነት ያለምንም ፍርሃት እና ይሉኝታ ለመወጣት ከሞከሩ የፍትህ ሥርዓቱ ወደ መስመር ውስጥ መግባቱ አይቀርም፤ ግን ክብርት ፕሬዝደንት ለተቋማዊ ለውጥና ከታሪክ ተጠያቂነት ለመዳንም የበኩልዎን ይወጡ።
ክብርት ፕሬዝደንት፥ ዜጋ በፍትህ ሥርዓቱ ተስፋ ሲቆርጥ ለሥርዓት አልበኝነት መንገድ ይከፈታል፤ የሞራል ልዕልና ቦታ አጥቶ ፍትህ በየአደባባዩ ትረገጣለች፤ ዜጋ በራሱ መንገድ ፍትህን ይፈልጋል፤ ፍትህን በራሱ ህሊና ተመርቶ ለመስጠት ይገደዳል። ያኔ እንደ ሀገር ዜጋው ወጥቶ የመግባት፣ ሠርቶ ሀብት ንብረት የማፍራት መብቱ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ እርስዎ የሚመሩት ተቋም ክብርና ሞገሱን ካጣ የሀገር ክብር እና ሞገስ ጠፍቶ እንደ ሀገር የመኖር ህልውናችንም አደጋ ውስጥ ይወድቃል። የመንግሥት መኖር ምልክት የሆነው ሕግና ሥርዓት ጠፍቶ ባለፈው እንዳየነው በየአካባቢው የደቦ ፍርድ ይነግሳል። አቶ ልደቱስ በፖለቲካው ባላቸው ተደማጭነት እና ተሰሚነት ድምፅ የሚሆናቸው ብዙ ነው። በዚህ ሁኔታ ተራው ዜጋ ምን ያህል በፍትህ ሥርዓቱ ፍዳውን ሊያይ እንደሚችል ተገንዝበውታል? ለእርስዎ ተቋም ክብር የሚመጥን የፍትህ ሥርዓት አለ ብለው ያምናሉ? አይመስለኝም ፍትህ እና ርትዕ እንዲሰፍን፣ እንዳይጓደል የበለጠ ሥራ በመሥራት የዳኞችን ክብር ያስመልሱ። ዳኞች የሚፈርዱት ፍርድ በአስፈፃሚው አካል ሲደፈጠጥ ማየት ያሳፍራል፣ ያሸማቅቃል ነገን እንድፈራ ያደርጋል። ነጋችንን እንዳንፈራ ሕግ ተርጓሚው ይፈራ! ስለዚህ ክብርት ፕሬዝደንት፥ ጉዳዩ የአቶ ልደቱን ጉዳይ የፍትህ መጓደል ብቻ አድርገው አይቁጠሩት። በህይወት የመኖር እና ያለመኖር የመብት ጥያቄ ነው እያቀረበ ያለው። በፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይሆን በአስፈፃሚው ጡንቻ በህይወቱ ላይ አንድ ነገር ቢደርስስ ማን ነው ተጠያቂው? በተለይ የሃጫሉን ሞት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የታዘብኩት ዜጎች ወደ ፍትህ ሳይቀርቡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እየተጉላሉ መሆኑን ነው። በየማጎሪያው እየተሰቃዩ ነው፤ የፍትህ ያለ እያሉ ነው። አሁንም እደግመዋለሁ ወንጀል የፈፀመ አይታሰር አልልም፤ ግን ከሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ ውጭ ዜጎች መጉላላት የለባቸውም፤ የተፋጠነ ፍትህ ይሰጣቸው፤ ሰብዓዊ መብታቸው ይጠበቅላቸው። ይህን በሁለት ወር ውስጥ የታዘብኩት ነው። ይህ የሚያሳየው የፍትህ መጓደል በሌሎች ክልሎች ላይም ቀላል በማይባል ደረጃ ችግሩ መኖሩን ነው። በቢሾፍቱና አዳማ ዋስትና ተፈቅዶላቸው ከወር በላይ ፖሊስ አለቅም በማለቱ በእስር የሚማቅቁ ብዙ ዜጎች እንዳሉ ያገኘኋቸው የሕግ ባለሙያዎች አጫውተውኛል። ፍትህ ተጠምተው በየእስር ቤቱ የሚሰቃዩ ብዙዎች ናቸው። ለፍትህ መከበር ሁሉም ሊጮህ ይገባል። ፍትህ በጉልበተኞች ጫማ ሲደፈጠጥ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሳልና!
ክብርት ፕሬዝደንት መዓዛ፥ ይህችን ግልፅ አቤቱታዬን ሰምተው በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ነፍስ ይዘሩበታል፤ በየማጎሪያ ካምፑ ያሉ የብዙ ዜጎችን እንባ ያብሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አመሰግናለሁ።
ከከበረ ሰላምታ ጋር!
አዳነ ታደሰ
የኢዴፓ ፕሬዝደንት
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።