Search Results for 'ሙዚቃ'

Home Forums Search Search Results for 'ሙዚቃ'

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 25 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    “የደጋ ሰው” በተሰኘው የሙዚቃ ስብስብ ላይ ሙያዊ ውይይት ተከናወነ

    በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ-ጥበባት ማዕከል አዘጋጅነት “የደጋ ሰው” በተሰኘው የሙዚቃ ስብስብ ላይ ሙያዊ ውይይት ተካሂዷል።

    በውይይቱ ላይ አጠቃላይ ሙያዊ ትንታኔውን የሙዚቃ ባለሙያና የሙዚቃ ሃያሲ አቶ ሰርጸ ፍሬስብሃት ያቀረቡ ሲሆን፥ የሙዚቃው አቀናባሪና ፕሮዲዩሰር ኢዩኤል መንግሥቱ እና ድምጻዊቷ የማርያም ቸርነት (የማ) የሙዚቃ ስብስቡን ሥራ ታሪክና ውጣ ውረድ አብራርተዋል።

    አቶ ሰርጸ ፍሬስብሃት ሙዚቃው የዓለም ሙዚቃ ዘውግ (World music genre) ላይ የሚመደብ ምርምራዊ ሥራ መሆኑን አመላካች፣ አስረጅ እና ታሪካዊ ዳራዎችን በመጥቀስ ያብራሩ ከመሆኑም ባሻገር፥ እስካሁን በዓለም ሙዚቃ ዘውግ ከተሠሩ የኢትዮጵያዊያን ሙዚቃዎች ውስጥ የቀለለ ዕድል በሌለበት በጥረትና ትጋት የተፈጠረ የጥበብ ሥራ መሆኑን አብራርተዋል።

    ከዚህ አስቀድሞ በየዓለም ሙዚቃ ዘውግ (World music genre) አስቴር አወቀ፣ እጅጋየሁ ሽባባው፣ ምንይሹ ክፍሌ፣ ዣን ስዩም ሔኖክን የመሰሉ ከያንያን በውጭ ሀገር ከመኖራቸውና ለወርልድ ሙዚቃ ካላቸው ተጋላጭነት አንጻር በመመዘንም “የደጋ ሰው” የሙዚቃ ስብስብ በተለየ ሁኔታ በምርጫና በጥረት የተሠራ ሥራ መሆኑን አቶ ሰርጸ አብራርተዋል።

    የሙዚቃ ስብስቡ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ሙዚቀኞች ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር የተጣመሩበት እና በአቀናባሪው ምርጫና ትጋት ወደ እውንነት የተቀየረ መሆኑ ተገልጿል።

    የሙዚቃው አቀናባሪ እና ፕሮዲዩሰር ኢዩኤል መንግሥቱ ሥራው በቦኬ ማኅበረሰብ ሙዚቃ በመሳብ እና ምርምሮችን በማስፋት ሀገር በቀል የሙዚቃ ቅንጣቶችን ከዓለም አቀፍ የሙዚቃ እሳቤዎች ጋር በመቀየጥ የባሕል ውህደትና ቅንብር ለመፍጠር የተሠራ ሥራ መሆኑን የሙዚቃ ስብስቡን ታሪክ አስረድተዋል።

    ድምጻዊቷ የማርያም ቸርነት ከእንግሊዝኛ የሙዚቃ ድምጻዊነት በሽግግር ወደእንዲህ አይነት የባሕል ቅይጥ እና ዓለማቀፋዊ መልክ ወዳለው ሥራ የተሻገረችበትን መልክ ሆኔታዎች አንስታ ገልጻች። “የደጋ ሰው” የሙዚቃ ስብስብ ከሰባት ሀገራት፣ ከሃያ በላይ ሙዚቀኞች የተሳተፉበት ሙዚቃ ስብስብ ሲሆን፥ በሙዚቃ ድርሰት፣ በሁለት የዘፈን ግጥሞች፣ በቅንብር እና በፕሮዲዩሰርነት ኢዩኤል መንግሥቱ፣ ጎላ ጎሕ (የብዕር ስም) ስምንት የሙዚቃ ግጥሞችን በማበርከት፣ አንጋፋው ይልማ ገብረአብ አንድ የሙዚቃ ግጥም ድርሰት በመስጠት የተሳተፉበት ስብስብ ነው።

    በውይይቱ ላይ በርካታ ታዳምያን ተገኝተው ስለሙዚቃ ሥራው የተሰማቸውን ስሜት እና በቀረቡት መነሻ ሃሳቦች ላይ ጥያቄና ማብራሪያ በማቅረብ ጠንካራ ተሳትፎ አድርገዋል።

    በውይይቱም ላይ ከሙዚቃው ድርሰትና ቅንብር በተጨማሪ የተለየ ሆኖ በሀሳብ ላይ ትኩረት አድርጎ ስለመጣው የሙዚቃው ግጥሞች በርካቶች አድናቆታቸውን ሰጥተዋል። በሌላም በኩል ምርምርና የሥነ-ጥበብን ከፍታ ይዘው ለሚመጡ አድካሚና ውድ ሥራዎች አድማጩ ሊሰጠው ስለሚገባው ትኩረት በማንሳት ጠንካራ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

    በዝግጅቱም ላይ ከራያ ማኅበረሰብ የተላኩ ወኪሎች በቦታው ተገኝተው ለድምጻዊቷ፣ ሙዚቃው አቀናባሪና ገጣሚ እንዲሁም በሥራው ላይ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ለየማርያም ቸርነትም የራያ ባሕል ልብስ ስጦታ አበርክተዋል።

    የካቲት 2 ቀን፥ 2016 ዓ.ም በ “ነገረ መጻሕፍት” ዝግጅት የገብረሕይወት ባይከዳኝ “ሕዝብና የመንግሥት አስተዳደር” መጽሐፍ የታተመበትን 100ኛ ዓመት በማስመልከት ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ጋር በሚደረገው ውይይት ላይ እንድትገኙ ከወዲሁ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋብዟል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    Anonymous
    Inactive

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በድምቀት አስመረቀ፤ ለቴዲ አፍሮ የክብር ዶክትሬት ሰጠ

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 24 ቀን፥ 2013 ዓ.ም በድምቀት አስመረቀ። በዚህ ደማቅ የምረቃ ሥነ ሥርዓት የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የበዓሉ ልዩ የክብር እንግዳ የተከበሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት አጸደወይን፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ሞላ መልካሙ፣ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርሀኑ ፈይሳ፣ የቀድሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ፕ/ር መንገሻ አድማሱ፣ የተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተመራቂ ወላጆችና ቤተሰቦች እንዲሁም የዕለቱ ተመራቂዎች ተገኝተዋል።

    በዓመቱ በዩኒቨርሲቲው በተካሄደው በዚህ በሁለተኛው ዙር የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሀግብሮች ወንድ 4153፣ ሴት 2421 በአጠቃላይ 6574 ተማሪዎችን በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ፣ በሦስተኛና በስፔሻሊቲ የትምህርት ደረጃዎች አስመርቋል፤ እንዲሁም ለአንጋፋው የሙዚቃ ሰው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ሰጥቷል።

    የነገ የሀገራችን ተስፋ የሆኑ የዕለቱ ተመራቂዎች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ፈታኝ ሁኔታዎችን ሁሉ በጽናትና በታላቅ ጀግንነት ተቋቁመው ለዚህች ልዩ ቀን በመድረሳቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት አጸደወይን አስተላልፈዋል። ተመራቂዎቻችን ወረርሽኙ የፈጠረውን አዲስ ሁኔታ በመቋቋም ለዚህ መብቃታቸውም ልጆቻችን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን ተፈትነው ማለፍ እንደሚችሉ ከወዲሁ ያረጋገጠ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ሲሉም አክለዋል።

    ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹትም በጎርፍ መጥለቅለቅ ለተጎዱ ዩኒቨርሲቲው የቻለው ድጋፍ አድርጓል፤ የወረታ ግብርና ኮሌጅን የሳተላይት ማዕከል አድርጎ ከፍቷል፤ 6ኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድ ብዙ ሠርቷል፤ እንቦጭን ለማስወገድ በርካታ ጥረት አድርጓል፤ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማርና ሀገራዊ ትስስርን የመፍጠር ሥራ ተሠርቷል፤ በማይካድራና ሌሎች አካባቢዎች በተደረጉ ዘር-ተኮር ጥቃቶች ላይ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን ጥናቶች እየተካሄዱ ነው፤ የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ይገኛል፤ እንዲሁም በገበታ ለሀገር መርሀ ግብር ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በዲዛይን ሥራ እና የጎርጎራ ከተማን መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። በአጠቃላይ 54 የሚሆኑ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች መተግበራቸውን የገለፁት ዶ/ር አሥራት አፀደወይን፥ በዚህ አመርቂ ተግባሩም ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ እውቅናና ሽልማቶች ከተለያዩ አካላት እንደተበረከቱለት በመክፈቻ ንግግራቸው አንስተዋል። “ከአባይ ወንዝ የምንቀዳው ፍቅር እንጅ ጥላቻ እንዳልሆነ ለተመራቂ ልጆቻችን በጓዳም በአደባባይም ነግረን አሳድገናቸዋል” በማለትም አለመግባባቶች በሰላም ይፈቱ ዘንድ በአባይ ተፋሰስ ለሚገኙ ሀገራት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የበዓሉ ልዩ የክብር እንግዳ የተከበሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ እንደአድዋ በአንድ ያቆመን የአባይን ግድብን የውሃ ሙሌት በድል ባከናወንበት ወቅት በመካሄዱ የዛሬውን ምረቃ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። የራሳችንን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀማችንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማፍለቅና መጠቀም ባለመቻላችን በድህነት እንኖራለን፤ ለዚህ ደግሞ በእውቀት የተደራጀ ኃይል ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፥ ስለሆነም ለትምህርት ትልቅ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል። ተመራቂዎች በትምህርት ህይወታቸው ያገኙትን እውቀት በራስ በመተማመን ስሜት ከሁሉም ጋር በመከባበርና በመሥራት ታላቅ የሆነችውን ሀገር ታላቅነቷን ማስጠበቅ እንደሚችሉ ያላቸውን የጸና እምነት በመግለጽ ለተመራቂዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ አያይዘውም የግድቡ ሥራ ሀገር አቀፍና አለማአቀፍ ትኩረትና ድጋፍ እንዲያገኝና በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረገው ጉልህ ሚና ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ እውቅና ሰጥተዋል። ሁሉም ሰው በተሰማራበት ሥራ መልካም ውጤት በማስመዝገብ ራስንም፣ ሀገርንም የሚያስከብር መሆኑን ከድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ሁሉ ሊማር ይገባል በማለት ለአርቲስት ቴዎድሮስ፣ ለተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

    ምንጭ፦ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለቴዲ አፍሮ የክብር ዶክትሬት ሰጠ

    Anonymous
    Inactive

    የኢፌዴሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር በ2013 በጀት ዓመት በባህል ኢንዱስትሪ ልማት ዋና ዋና ክንውኖች
    ሐምሌ 2013 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ

    • በባህል ፖሊሲ፣ በቋንቋ ፖሊሲ በባህል እሴቶችና ሀገር በቀል ዕውቀቶች፣ በዕደ ጥበብ ማበልፀግና የገበያ ትስስር ስትራቴጂዎችና አዘገጃጀት ሂደት እና አተገባበር ላይ ከ10 ክልሎች እና ከ2 የከተማ መስተዳድር ለተውጣጡ 53 የባህል ዘርፍ ሙያተኞች እና አስፈጻሚዎች ስልጠና ተሰጥቷል።
    • ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ለባህል ተቋማት በሲኒማ ቤት፣ በቴአትር ቤት እና ቤተ መፃሕፍት ላይ የደረጃ ሰነድ (standard) ተዘጋጅቷል።
    • በኪነጥበብ እና በሥነ ጥበብ ተቋማት ዘርፍ ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የማበረታቻ ሽልማት የሚሰጥበትን አሰራር ሥርዓት በመዘርጋት የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የሽልማትና ዕውቅና መርሃ ግብር በሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በድርሰት፣ በሰርከስ፣ በስዕልና ቅርፃ ቅርፅ፣ በፋሽን ዲዛይን፣ በውዝዋዜ እና በፊልም 2013ዓ.ም የሽልማትና ዕውቅና ለመስጠት ሥራዎች ተሠርተዋል።
    • ኢትዮጵያ ያላትን ሀብትና የተፈጥሮ ፀጋ ለማስተዋወቅ እንዲሁም ወደ ኢንቨስትመንት አማራጭ ለመለወጥ ያለመ “የኢትዮጵያ ሳምንት” በወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል። ክልሎች ልዩ መገለጫችን ነው ያሉትን ባህላቸውን በተለያዩ ቅርፃ ቅርፆች፣ በተንቀሳቃሽ ምስሎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ጭፈራዎችን በማቅረብ ተከብሯል።
    • የባህል ኢንዱስትሪ መረጃዎችን ለማዘመንና ወጥነት ያላቸው እንዲሆኑ ለማስቻል ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ጋር በጋራ በመሆን የመረጃ ቋት (ዳታቤዝ) በማዘጋጀት የ2013 ዓ.ም የባህል ኢንዱስትሪ ተቋማትና ሙያተኞች መረጃ ተደራጅተዋል።
    • በባህል ዘርፍ (በባህል፣ በፊልም፣ በቋንቋ ፖሊሲዎችና በእደ ጥበብ ልማት በሀገር በቀል እውቀቶች)፣ በጎጂና መጤ ባህላዊ ድርጊቶች እና ባህል ዘርፍ ተቋማት አከፋፈት የኮቪድ 19 ጥንቃቄና ደህንነት መመሪያን ማስተዋወቅ ሥራ ለ7 ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ለ52 አሰልጣኞች የማስተዋወቅ ሥራ ተሠርቷል።
    • ከሙያ ማኅበራት ጋር በመተባበር በኮቪድ ወቅት ጥንቃቄና ደህንነትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ የወረርሽኙን አስከፊነት የጥንቃቄ ትኩረትን የሚያስገነዝብና ከ100 በላይ ማስታወቂያዎች (ስፖት) በተለያዩ ሚዲያዎች ተለቋል።
    • የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የባህል ዘርፍ አገልግሎት ተቋማትን ሥራ ለማስጀመር እንዲቻል ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የአሠራር መመሪያ ተዘጋጅቷል።
    • ለክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም የባህል ጥበባት ዘርፍ ለባለድርሻ አካላት በሁለት ዙር መድረክ ሥልጠና ተሰጥቷል።
    • በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ የተመለከቱት ሥዕል ኤግዚቪሽን ለሶሰት ቀናት ለሕዝብ ዕይታ ቀርቧል።
    • በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በተዘጉ ወቅት በቤት ተቀምጠው የነበሩ ተማሪዎች እና ሕፃናት የተሳተፉበት የኪነ ጥበብ ፈጠራ ውድድር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የአንድ ወር የቴሌቪዥን ፕሮግም ተሠርቷል።
    • ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በተደረገ ዘመቻ ለተሳተፉ አካላትና መመሪያውን ተግባራዊ ላደረጉ ለሁለት ክልልና ለአንድ ከተማ መስተዳድር በድምሩ ለ25 ተቋማት እውቅና የመሥጠት ሥራዎች ተከናውነዋል።
    • የባህል ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተመለከተ 6 የአሰራር ሥርዓት ሰነዶችና መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል።
    • ከዩኔስኮ በተገኘው ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ኤክስፐርቶቸች ድጋፍ በመታገዝ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የፈልም ፖሊሲ ማስተገበሪያ (የተቋም ማቃቋሚያ ሰነድ እና የፈልም ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስትራተጂ) ፕሮጀክት እየተከናወነ ነው።
    • የ2005 የዩኔስኮ ኮንቬንሽን ስምምነት መሠረት የ2020 (2012 ዓ.ም.) የሚቀርበውን በየአራት ዓመታቱ የሚዘጋጀውን ሪፖርት ለማጠናቀቅ እንዲቻል ሀገራዊ ኮሚቴውን በማስተባበር በወቅቱ ገቢ ለማድረግ ተችሏል።

    ምንጭ፦ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር

    የኢፌዴሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር

    Anonymous
    Inactive

    አቢሲንያ ባንክ እጅግ በተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ስም ቅርንጫፍ ከፈተ

    አዳዲስ ቅርንጫፎችን በሀገር ባለውለታዎች ስም እየሰየመ የሚከፍተው አቢሲንያ ባንክ፥ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ዕንቁዎች በመጀመሪያ ረድፍ ላይ በተቀመጡትና ስማቸውን በወርቅ ቀለም ባጻፉት ታላቁ የኪነ ጥበብ ሊቅ፥ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ስም ቅርንጫፉን ከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

    አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በአንኮበር ከተማ፣ ከአቶ ተክሌ ማሞና ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ጥቅምት 13 ቀን፥ 1925 ዓ.ም. ተወለዱ። ዘመኑ ፋሺስት ጣልያን ሀገራችንን በግፍ የወረረበት ዘመን በመሆኑ፣ አፈወርቅ ተክሌ በጨቅላ እድሜያቸው በሰው፣ በንብረትና ባህል ላይ የደረሰው ጥፋት በአእምሮአቸው ታትሞ ቀረ። ለዛም ይመስላል በ1940 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ታላቋ ብሪታንያ፥ ለንደን ተጉዘው፣ የሥዕልን ጥበብ ተምረው ከተመለሱ በኋላ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላት እየተዘዋወሩ ታሪክን፣ የብሔረሰቦችን ባህልና ወግ ሲያጠኑ የከረሙት።

    በ1944 ዓ.ም. በሃያ ሁለት ዓመት እድሜአቸው የመጀመሪያ የሆነው የሥዕል አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቀረቡ። ከአውደ ርዕይ ባገኙት ገቢ፣ ወደተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በመዘዋወር የሥዕል ጥበብን ቀሰሙ። የኢትዮጵያ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትን አጠኑ። ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በኢትዮጵያ የመስታወት ስዕልን (stained glass art) ያስተዋወቁ ቀዳሚው የጥበብ ሰው ናቸው። በዚህ ጥበብ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን መስኮቶች በመሥታወት ሥዕላት አስጊጠዋል። በሐረር ከተማ የአፄ ኃይለ ሥላሴ አባት የራስ መኮንን ሐውልትን ገንብተዋል።

    ሥራዎቻቸው በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ እጅግ ዝናን ያተረፉ በመሆናቸው በርካታ ሽልማቶችን አስገኝተውላቸዋል። በ1971 ዓ.ም. የአልጀርስ የጥበብ ፌስቲቫል የወርቅ ሽልማት፤ በፈረንሳይ በተደረገው የሥዕል ውድድር አንደኛ በመውጣት የኖቤል የሎሬት ክብር መዓረግ በማግኘት ኢትዮጵያን አስጠርተዋል። በ2000 ዓ.ም. የዓለም ሎሬትነት ክብርን በዋሽንግተን ዲሲ በተደረው 27ኛው ዓለም አቀፍ የጥበብና መገናኛ ብዙኃን የሚሊንየም ኮንግረስ (27th International Millennium Congress on the Arts and Communication) ከአሜሪካ ባዬግራፊካል ኢንስቲትዩት ተቀዳጅተዋል፤ በ2004 ዓ.ም. በአየርላንድ ለጥበብ ዕድገት ለዓለም ላበረከቱት አስተዋጽዖ “የዳቬንቺ አልማዝ ሽልማት” እና “የጀግና ክብር ኒሻን” ተበርክቶላቸው።

    እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ሚያዝያ 2 ቀን፣ 2004 ዓ.ም. በስጋ ሞት ቢለዩንም፥ እነሆ በራሳቸው ቀለምና በሀገርኛ ሥራዎቻቸው በዓለም መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ስም ከፍ በማድረጋቸው፥ ለእኚህ የሀገር ዋልታ አቢሲንያ ባንክ አዲስ የከፈተውን ቅርንጫፍ በስማቸው ሰይሞ ዘክሯል።

    አቢሲንያ ባንክ ብዙ መሰናክሎች ሳይበግራቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የሥራ መስኮች ማለትም፥ በመንግሥት አስተዳደር፣ ሀገርን በመጠበቅ፣ በታሪካዊ ኩነቶች፣ ቅርስ በማሰባሰብ፣ በስፖርት፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በቴአትር፣ ሙዚቃ፣ ፋይናንስና አገልገሎት፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎች፣ በማስታወቂያ ሞያ፣ በንግድ ሥራና በመሳሰሉት ዘርፎች ስሟን ከፍ ላደረጉ ባለውለታዎች በስማቸው ቅርንጫፎችን በመሰየም እየዘከራቸው ይገኛል። ይህም ለሀገራችን ዘመን አይሽሬ አበርክቶ ያደረጉ ባለውለታዎችን ስማቸውንና መልካም ተግባራቸውን በመዘከር ለቀጣዩ ትውልድ ለማሳወቅና አርዓያ እንዲሆን በማመን ጭምር ነው።

    ምንጭ፦ አቢሲንያ ባንክ

    አቢሲንያ ባንክ አፈወርቅ ተክሌ ቅርንጫፍ

    Anonymous
    Inactive

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 5117 ተማሪዎች አስመረቀ

    ባሕር ዳር (ሰሞነኛ)– ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን መመረቅ የነበረባቸው እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት መቋረጡን ተከትሎ የዘገዩ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ 4203፣ በሁለተኛ ዲግሪ 759፣ በሦስተኛ ዲግሪ 10፣ በስፔሻሊቲ 40፣ በፒጂዲቲ ቅድመ ምረቃ (post graduate diploma in teaching/PGDT) 105፤ በአጠቃላይ 1623 ሴት፣ 3494 ወንድ ተማሪዎችን፥ በድምሩ 5117 ተማሪዎችን ጥር 29 ቀን 2013 ዓ.ም. የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በክብር እንግድነት በተገኙበት አስመርቋል።

    የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፥ “የዘንድሮ ተማራቂዎችን እንደተማሪ በርካታ መሰናክሎችን አልፈው ለዛሬው ቀን በመብቃታቸው ‘ከመወርቅ’ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግሮች በመከራ ጊዜ እንደ ወርቅ ነጥራችሁ በመውጣታችሁና ለዚህ ታሪካዊ ቀን እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል። ዶ/ር ፍሬው አክለወም፥ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆንና በሀገራችን ካሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ግምባር ቀደም እንዲሆን ላገዙት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በከተማዋ ውስጥ ላሉ የወጣት አደረጃጀቶችና ለሌሎች አጋር ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ተመራቂዎች ዓለምን እየፈተነ ባለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ውስብስብ ችግሮችን አልፈው መመረቅ መቻላቸው ታሪካዊ ተመራቂዎች መሆናቸውን አውስተው፤ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገርና ቤተሰብ የጣለባቸውን አደራ በአግባቡ እንዲወጡ፣ በሰለጠኑበት የትምህርት መስክ ጠንክረው በመሥራት ሀገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው፥ ተመራቂ ተማሪዎች ‘ሀገሬ ምን አደረገችልኝ?’ ሳይሆን ‘ለሀገሬ ምን አደረኩላት?’ ብሎ ራስን መጠየቅ እና በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ጥልቅ ዕውቀት ተጠቅመው በኮሮናቫይረስ ወረርሽ የቀዘቀዘውን ኢኮኖሚ እንዲሻሻል በማገዝ በሀገር ግንባታ ላይ የበኩላችውን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለባሕር ዳር ከተማ ብሎም ለክልሉ እንደ ዓይን ብሌን የሚታይ ግዙፍ የዕውቀት ማዕከል መሆኑንም ተናግረዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ በመመረቂያ ፕሮጀክቶች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የምስክር ወረቀት እና የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሁም በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የወርቅ ዋንጫ ተሸልመዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ክብርት ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ፣ የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨረሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ ፣ የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋም ድርጅት (አመልድ) ዋና ዳይሬክተር እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

    የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ባማረው እና በተዋበው የዩኒቨርሲቲው ስታዲየም በፖሊስ ማርሽ ባንድ በቀረበ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መዝሙር እና በሙሉ ዓለም የባህል የሙዚቃ ባንድ በቀረቡ የተለያዩ ባህላዊ ውዝዋዜዎች እና ዘመናዊ ሙዚቃዎች በመታጀብ ደምቆ ውሏል።

    ምንጭ፦ ዩኒቨርሲቲው

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 5117 ተማሪዎች አስመረቀ

    Semonegna
    Keymaster

    በጉራጌ ዞን የመስቀል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ተጀመረ
    (የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ)

    በሀገራችን በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት መካከል የመስቀል በዓል አንዱ ነው። የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው እንደመሆኑ፥ በየዓመቱ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል። የዘንድሮውን የዋዜማ ዝግጅት በዞኑ ቸሃ ወረዳ የጠናቃ ቀበሌ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ከመስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በድምቀት መከበር ተጀምሯል።

    በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል ታዳሚዎችን እንኳን አደረሳችሁ በማለት “የመስቀል በዓል የኛነታችን መገለጫ ነው፤ የመስቀል በዓል ትውፊታዊም መንፈሳዊም ነው። በመስቀል በዓል የእርስ በእርስ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የሰላም እንዲሆን የመልካም ምኞት ማብሰሪያ አበባ የሚሰጣጡበት ጊዜ ነው። እንዲሁም በሥራም ሆነ በሌላ አጋጣሚ ተራርቆ የቆየ ሰው የሚገናኝበት፣ ዘመድ ከዘመዱ የሚጠያየቅበት፣ የሚረዳዳበት እንዲሁም አዲስ ጎጆ የሚቀለስበት ጊዜ መሆኑ ማኅበረሰባችን ልዩ ቦታ ይሰጠዋል። አያይዘውም በበዓሉ ባህላዊ እሴቶቻችንን በደንብ አልምተን እንደ አንድ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ በማድረግ ለሀገራዊ ብልጽግናችን መሠረት የምንጥልበት ነው ብለዋል።

    የመስቀል በዓል ከሀይማኖታዊ ክዋኔ ባሻገር ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር ቢሆንም መስቀል በጉራጌ በተለየ የአከባበር ሁኔታ ይከበራል ብለዋል – አቶ መሐመድ።

    እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ እንደ መስቀል ያሉ ቱባ ባህሎቻችን ታሪካቸው ሳይሸራረፍ ለትውልድ በማስተላለፍ ዘረኝነት፣ ጥላቻና ቂም በቀል በማስወገድ የሀገራችን ብልፅግና ለማረጋገጥ  ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

    መርሀ-ግብሩን በጋራ ያዘጋጁት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ የጉራጌ ዞን አስተዳደር እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በመተባበር ሲሆን፥ የዚህ ክብረ በዓል አከዋወን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት /UNESCO/ ከማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ ባህላዊ እሴቶች (“intangible heritages of Ethiopia”) ተርታ መመዝገቡን በማስመልከት ሲሆን፥ በአከባበሩ ሥርዓት ውስጥ ያሉት ትውፊቶች በትውልድ ቅብብሎሹ ውስጥ ተጠብቀው ያለ ምንም ተፅዕኖ ክዋኔዎቹ እየቀጠሉ እንዲሄዱ የማስተማር ዓላማ ያለው እንደሆነ ተነግሯል።

    በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክተር ወ/ሮ እስከዳር ግሩም በበኩላቸው፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊና ታሪካዊ ሀብት ባለቤት ብትሆንም በተገቢው ማልማትና ማስተዋወቅ ባለመቻላችን ከዘርፉ የምናገኘው ገቢ እንዳላደገ ገልጸዋል።

    አንድነታችን አጠናክረን ሀብቶቻችን ማልማት፣ መጠበቅና መንከባከብ አለብን። ይህ ደግሞ የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ያደርገዋል። በተጨማሪም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ይቻላል ብለዋል።

    የቸሀ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፈለቀ የመስቀል በዓል በጉራጌ ሁሉም በድምቀት ከማክበር ባለፈ የጉራጌ እሴት የሚገለፅበት በመሆኑ የረጅም ጊዜ ቅድመ ዝግጅት እንደሚደረግበት በማስታወስ፤ በዓሉንም በድምቀት ለማክበር ሁሉም የቤተሰብ አባል የድርሻውን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚከበር ገልጸዋል።

    ለበዓሉ ማብሰሪያ የጉራጌ ዞን የባህል ቡድንም ያሰናዳቸውን ሙዚቃዊ ክዋኔዎች እንደነ “ጊቻዌ፣ ጊቻዌ”፣ “አዳብና” የመሳሰሉት ተውኔታዊ ክዋኔዎች በሴቶችና ወንዶች የታየበት፣ የሥራ ባህልን፣ ሠርቶ ማደግን የሚያወድሱ፣ የሚያስተምሩ ማሳያዎች፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ በአንድነት በአብሮነት ባህላዊ እሴቶች የሚጎለብቱበት ተውኔታዊ ትዕይንቶች የተንፀባረቁበት ነበር።

    የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ

    Anonymous
    Inactive

    የተፈጥሮ ሳይንስ እና ግብርና ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ተገለጸ።

    በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአገራችን አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።

    የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ዕለት የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የአረንጓዴ አሻራ ቀን በሚል ችግኝ የመትከል ማዕድ የማጋራትና ደም የመለገስ መርሃ-ግብሮች ተከናውነዋል።

    ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአሰላ ከተማ የሚገኘው አርሲ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት መርሃ-ግብሩን ያስጀመሩት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት፥ የተፈጥሮ ሳይንስ እና የግብርና ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።

    በቅድመ ተከላ፣ በተከላ ወቅትና ድኅረ ተከላ መደረግ ያለባቸውን እንክብካቤዎችን እና ጥንቃቄዎችን በማስተማርና እንዲሁም እንደየአከባቢው የአየር ንብረት ሁኔታ ተስማሚ የሆኑትን ችግኞች እንዲባዙ ጥናትና ምርምር ከማድረግና ማማከር በተጨማሪ ከሌላው ጊዜ በበለጠ ችግኞችን አባዝተው ለአከባቢው ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

    አያይዘውም በየአከባቢው ያለው የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማኅበረሰቡ እንዲሁም ሌሎችም ኢትዮጵያውያን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን እየተጠነቀቁ በዚሁ ምክንያት ለተቸገሩ ወገኖቻቸው ማዕድ እንዲያጋሩ እና ደም በመለገስም ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት እንዲታደጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲውን ሦስቱን ግቢዎች ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመሆን የጎበኙ ሲሆን፥ በጉብኝቱ ከሰባ ዓመታት በፊት በስዊድን ድጋፍ የተቋቋመውና በዩኒቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የግብርና ምርምር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ እና የጤና ሳይንስ ኮሌጁም የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን ለመከላከል የሚያመስገን ሥራ እየሠራ መሆኑም ተገልጿል።

    ፕሮፌሰር አፈወርቅ በማዕድ ማጋራት ዩኒቨርሲቲው የሚደግፈውን አፎምያ የአረጋውያን መርጃ ማኅበር የጎበኙ ሲሆን በጉብኝቱ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው የዱቄትና ዘይት ድጋፍ አድርጓል።

    ከአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ጋር በተያያዘ፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ ከድምጻውያን ጋር በመሆን በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ሚሊኒየም ፓርክ ውስጥ (የካ ተራራ) ችግኞችን ተክለዋል።

    ከንቲባው በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዓለም-አቀፍ ስጋት የሆንውን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን ከመከላከል በተጓዳኝ ነዋሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው ችግኞች እንዲተክሉ አሳስበዋል። ችግኝ ከመትከል ባለፈም ችግኞች በየጊዜው መንከባከብም ያስፈልጋል ብለዋል።

    የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ሕብረት ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ ሕብረተሰቡ ችግኞች ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በመረዳት በራሱ ተነሳሽነት መትከልና መንከባከብ ይገባል ብለዋል። ሕብረቱም የተከላቸውን ችግኞች ለመንከባከብም ቃል ገብተዋል።

    በሥፍራው ተገኝቶ አረንጓዴ አሻራ በማኖሩ ደስተኝነቱን የገለጸውና ተግባሩ መቀጠል አለበት ያለው ድምፃዊ ነዋይ ደበበ ነው።

    ”ንጹህ አየር ለሰው ልጅ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን ችግኝ መትከል ግዴታ ነው። በዚህም ቦታ ተገኝቼ አረንጓዴ አሻራ በማኖሬ ደስተኛ ነኝ” ሲል የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሣ ተናግሯል።

    በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰባት ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዷል። በአገር አቀፍ ደረጃ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፤ ከሚተከሉት መካከል ለጥምር ግብርና የሚሆኑ የፍራፍሬ ችግኞች ይገኙበታል።

    ምንጮች፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አረንጓዴ አሻራ

    Anonymous
    Inactive

    ቅኔ ነው ሀገር ― የሦስት ሙዚቃዊ ዘመናት አንጋፋ እና ወጣት ድምፃውያንን እንዲሁም ታላላቅ የሙዚቃ ሊቃውንትን ያገናኘ ልዩ ኦርኬስትራዊ ኅብረ ዝማሬ!!!

    • ከ1950ዎቹ እና 60ዎቹ አንጋፋ ድምጻውያን መካከል አንዱ የሆነው ጥዑመ ልሳኑ ድምጻዊ ታደለ በቀለ (ከሥራዎቹ በጥቂቱ፦ “አላስቀየምኳትም”፣ “ዉብ ዓይናማ” /ከሒሩት በቀለ ጋር/፣ “ሸንኮርዬ” /ከወይንሸት ሙሉነህ ጋር/)፣
    • ከ1970ዎቹ እና 80ዎቹ የወጣትነት ዘመናቸው እስከ ዛሬ ዝናቸው እንደተጠበቀ እዚህ የደረሱት ድምጻውያኑ ንዋይ ደበበ (ከብዙ ሥራዎቹ በጥቂቱ፦ “የፍቅር ገዳም”፣ “አልዋሽም”፣ “ብትከዳኝ ታዘብኳት”፣ “ማዕበል ነው”፣ “ሸጊት ከሐረር፣ ሸጋው ከሐረር” /ከሀመልማል አባተ ጋር/) እና ጸጋዬ እሸቱ (ከብዙ ሥራዎቹ በጥቂቱ፦ “ሰንደቅ ዓላማ”፣ “ያይኔ አበባ”፣ “አላስገድድሽም”፣ “አንቺ ቅናተኛ”፣ “እናት ወደር የላት”፣ “ለሰርጓ ተጠራሁ”)፣
    • ከ1990ዎቹ አይረሴ አልበሞቹ ጀምሮ እስከ ዛሬ ተወዳጅ የኾነው ድምጻዊ ኃይልዬ ታደሰ (ከብዙ ሥራዎቹ በጥቂቱ፦ “ሁሌ ሁሌ”፣ “እንደአፍሽ ያድርገው”፣ “እሷን ብቻ”፣ “በዘመኔ”፣ “ልትሄድ ነው”፣ “ይሞታል ወይ”)፣
    • የሙዚቃ ልኬት በልዩ አጨዋወት እና ድንቅ ብቃት የታየበት እንዲሁም ብዙዎች ለመስማት የጓጉለት ሠርፀ ፍሬስብሐት (በኢትዮጵያን አይድል [Ethiopian Idol] ውድድር ላይ እጅግ ላቀ ባለ የዳኝነት ሙያው አንቱታን ያተረፈ)፣
    • ከወጣቶቹ፣ ከዘመነኞቹ ከወደፊት የሙዚቃ ተስፋዎቹ ከሚካኤል ለማ ደምሰው፣ ከየማርያም ቸርነት (የሚ)፣ ከማኅሌት ነጋሽ ፣ ከማስተዋል ዕያዩ እና ከይድነቃቸው ገለታ ጋር በአንድነት “ቅኔ ነው ሀገር” የተሰኘ ድንቅ ኅብረ ዝማሬ አቅርበዋል።

    ድርሰት፣ ቀረፃ፣ ቅንብር፣ ፕሮዳክሽን እና ዳይሬክቲንግ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህሩ በወጣቱ ድንቅ ሙዚቀኛ በኢዩኤል መንግሥቱ ውብ ሆኖ ተሰናድቷል።

    የሙዚቃው የድምጽ ውኅደት በታላቁ ሙዚቀኛ በአበጋሱ ክብረወርቅ ሺዎታ ተከውኗል።

    በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነት፥ ዶ/ር ዕዝራ አባተ፣ ረ/ፕ ኃይሉ ዓለማየሁ፣ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሰላማዊት አራጋው፣ ታዋቂው ሳክስፎኒስት አክሊሉ ወልደ ዮሐንስ (ጆኒ)፣ ኤፍሬም ውብሸት፣ ዳዊት ፍሬው ኃይሉ፣ ኢዩኤል መንግሥቱ፣ ለታሪክ ጥላሁን ፣ ሚሊዮን አብርሀም፣ ቴዎድሮስ አበራ፣ ዳዊት ቦስኮ እና ሌሎች በርካታ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች በሥራው ላይ ግሩም አጨዋወት ተሳትፈዋል።

    ሀገር ሰምና ወርቅ ያላት ቅኔ ናት። የቅኔዋን “ወርቅ” የምናገኘው፣ “ሰው በሌለበት ሰው ሆነን ስንገኝ ነው፤” ሰውነት፣ ሀገር መውደድ፣ ሰው ሆኖ መገኘት… የዘመናችን እና የወቅቱ ትልቅ “የመሆን አለመሆን” (to be or not to be) ‘ሐምሌታዊ’ (ሼክስፒሪያን) ጥያቄ ስለመሆኑ ኅብረ ዝማሬው ይነግረናል።

    ይህን ምርጥ የትብብር ውጤት የሆነውን ሙዚቃ ለማድመጥ/ ለመመልከት (ምነው ሸዋ ቲዩብ) እዚህ ጋር ይጫኑ

    ሠርፀ ፍሬስብሐት እንደጻፈው

    ቅኔ ነው ሀገር

    Semonegna
    Keymaster

    ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ «ባላገሩ አይድል» በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይተላለፍ በነበረ የሙዚቃ ዉድድር ከዓመታት በፊት አሸናፊ ነበር። ዉድድሩ ሲጠናቀቅም ለአሸናፊዉ የሙዚቃ አልበም ማዘጋጀት የሽልማቱ አካል ስለነበር፤ በዉድድሩ ዳዊት ፅጌ ያሳየዉ ድንቅ ችሎታ በሙዚቃ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አልበሙ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎት ነበር።

    እናም እንደተጠበቀዉ በቅርቡ «የኔ ዜማ» በሚል መጠሪያ የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሙን (debut album) ለአድናቂዎቹ እንካችሁ ብሏል። የአልበሙን መለቀቅ ተከትሎ በኢትዮጵያ ሙዚቃ አድማጮችና አድናቂዎች ዘንድ በብዛት መነጋጋሪያ የሆነው ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጀርመኑ የዶይቸ ቬለ ሬድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍል ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል።

    አሥራ አራት የሙዚቃ ሥራዎች የተካተቱበት የድምፃዊ ዳዊት ፅጌ «የኔ ዜማ» አልበም ዉድድሩን ካሸነፈ ከአራት አመታት በኋላ የወጣ በመሆኑ የሙዚቃ አልበሙ ዘግይቷል የሚሉ ብዙዎች ናቸዉ። የዶይቸ ቬለ ጋዜጠኛም ለዳዊት በመጀመሪያ ያነሳችለት ይህንኑ ጥያቄ ነበር።

    በዉድድሩ የተለያዩ አንጋፋና ወጣት ድምፃዉያንን ሙዚቃ ይጫወት ስለነበር የአራት ዓመት ቆይታዉ የራሱን የሙዚቃ ቀለም ፈልጎ ለማግኘት የጣረበት እንደነበርም ድምፃዊዉ ገልጿል። ለዚህም አንጋፋዉ የሙዚቃ ሰዉ አበበ መለሰ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎለታል።

    በዳዊት ፅጌ «የኔ ዜማ» አልበም የ«ባላገሩ አይድል» አዘጋጅ የነበረውና የእውቁ የሙዚቃ ባለሙያ የአብርሃም ወልዴ አሻራ ያረፈበት ሲሆን፥ «ባላገሩ » ቁጥር አራት በዚህ አልበም ተካቷል። «አስመሪኖ»በሚለዉ ዜማዉ ደግሞ ፀሀይቱ ባራኪን የመሳሰሉ አንጋፋ የኤርትራ ድምፃዉያን ተዘክረዉበታል። (አብርሃም ወልዴ ከተለያዩ ድምጻውያን ጋር በመተባበር “ባላገሩ” በሚል ርዕስ ከዚህ በፊት አራት ሥራዎችን ሠርቷል። የመጀመሪያው ባላገሩ ፩ ድምፃዊ ደሳለኝ መልኩ፣ ሁለተኛው ባላገሩ ፪ ድምፃውያን ኤፍሬም ታምሩ እና ጎሳዬ ተስፋዬ (በኅብረት)፣ ሦስተኛው ባላገሩ ፫ ድምፃዊ መስፍን ዘበርጋ /ጉራጊኛ/ ናቸው።)

    «ባላገሩ አይድል» በሚለዉ የሙዚቃ ዉድድር በነበረዉ ቆይታ በሙዚቃ አፍቃሪዎች ልብ ዉስጥ ትልቅ ቦታ ይዞ የቆየዉ ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ፤ በቅርቡ ያወጣዉ አዲሱ አልበም በአድማጩ ዘንድ ጥሩ ምላሽ እየተቸረዉ መሆኑን በቃለ ምልልሱ ላይ ገልጿል። ከአዲሱ የሙዚቃ አልበሙ ዉስጥም «ልቤ ሰዉ ይወዳል» ለሚለዉ ሙዚቃዉ የተለየ ስሜት አለዉ።

    ከዶይቸ ቬለ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ሙሉውን እዚህ ጋር በማስፈንጠር መስማት ይችላሉ።

    ልቤ ሰው ይወዳል (ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ)

    ልቤ ሰው ይወዳል (2x)
    ልቤ ሰው ይወዳል ወድያው ይላመዳል፣
    የቀረበኝ ሁሉ ወዳጅ ይመስለዋል፤
    ይላመዳል ሰው ያምናል ይወዳል፣
    ይሄ ልቤ ሰው ያምናል ይወዳል፤
    ይመስለዋል ወዳጅ ይመስለዋል፣
    ይሄ ልቤ ሰው ያምናል ይወዳል።

    አይቶ አለመራመድ እግሩን ቢያስነክሰው፣
    በማጣት ቢያሳሹት እንዴት ይድናል ሰው?
    በእሳት ከነደደ አመድ መች ይገዳል?
    ሰው ሁሉ እንደዚህ ነው አጥፊውን ይወዳል። (2x)

    አንዳንዴ እንዲ ነው አንዳንዴ እንዲ ነው፣
    ሰው ወዶ ሰው መጥላት ለካስ ፈተና ነው።
    ጥርስ አልሰንፍ አለ እንጂ ቀድሞ ለመሳቁ፣
    እኔን ባይ አይጠፋም ተገፍተው ስወድቁ።

    ልቤ ሰው ይወዳል ወድያው ይላመዳል፣
    የቀረበኝ ሁሉ ወዳጅ ይመስለዋል፤
    ይላመዳል ሰው ያምናል ይወዳል፣
    ይሄ ልቤ ሰው ያምናል ይወዳል፤
    ይመስለዋል ወዳጅ ይመስለዋል፣
    ይሄ ልቤ ሰው ያምናል ይወዳል።

    ቀን ይዞ ቢጠልቅም ወዳጅ እንደጀንበር፣
    ሰው ጨረቃ አያጣም ባመሸበት ሀገር፤
    ልቤ አይጉደል እንጂ በሰው ያለ ተስፋ፣
    በመጪው ይካሳል በሄደው የከፋ። (2x)፤

    አንዳንዴ እንዲ ነው፥ አንዳንዴ እንዲ ነው፣
    ሰው ወዶ ሰው መጥላት ለካስ ፈተና ነው።
    አንዳንዴ እንዲህ፥ ነው አንዳንዴ፣
    ሰው ወዶ ሰው መጥላት አይለምደውም ሆዴ።

    አረ አይጣል ነው (8x)

    አንዳንዴ እንዲ ነው፥ አንዳንዴ እንዲ ነው፣
    ሰው ወዶ ሰው መጥላት ለካስ ፈተና ነው።

    ደሃ አይጣላ ከውሃ (ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ)

    አንዲት ሴት ነበረች የቤት ሠራተኛ፣
    ቀን ስትደክም ውላ ሌሊ’ትን የማት’ተኛ፤
    ኑሮዋ ሆነና የአርባ ቀን ዕድሏ፣
    ልጅ እያጠባች ነው የተለያት ባሏ፤
    ለአንድ ልጇ ስትል በነፃ እየሠራች፣
    ደሞዟን ሳትል ለፍታ ያሳደገች።
    እንደወጣ ቢቀር ያ’ ባሏ ያ’ ጎበዝ፣
    ስትረግም ትኖራለች ያሻገረውን ወንዝ።

    ለራሷ’ምትቀምሰው ’ምትልሰው ሳይኖራት፣
    ምን ልታጠባው ነው የምትወልደው ሲሏት፤
    ልጅ ስህተት አይደለም ከመጣ በኋላ፣
    ብላ ተስፋ ቆርጣ ሄደች ዳግም ጥላ።
    ሀገር ጥላ ጠፍታ ተሰዳ በርቁ፣
    ትኑር ትሙት እንኳን አንዳቸው ሳያውቁ፤
    ስንት ዘመን አልፎ ናፍቃ ብትመለስ፣
    ይኸው ፊት አስነሳት የታቀፈችው ነፍስ።
    ምን አለ ብትተወው የባሏን እሮሮ፣
    ያሻገረውን ወንዝ መርገም በእንጉርጉሮ።
    ወንዙን አለችው ብላ ጠጋ፣
    ለአንተም አለ በጋ!!
    እሷም አለችው ብላ ጠጋ፣
    ለአንተም አለ በጋ!!

    ከሀገር ሀገር ስትዞር ተሸክማ ጓዟን፣
    ስንት አሳር አይታለች ለማሳደግ ልጇን፤
    እረፍት እንኳን ሳታውቅ በነፃ እየሠራች፣
    ወዟን አራግፋ ነው ለፍታ ያሳደገች።

    ታድያ አንድ ቀን ጥዋት ማለዳ ተነስታ፣
    ቅጠል ጠርጋ መጥታ ሳታርፍ እንኳን ላፍታ፤
    ልጇን በአንቀልባ አዝላው ውሃ ልትቀዳ፣
    ከለመደችው ወንዝ መሸት ሲል ወርዳ፤
    ጎንበስ ባለችበት በድካም ስሜቷ፣
    አመለጣት ልጇ አይ እድሏ ሀብቷ፤
    ደራሽ ወሰደባት የት ገባ ጸሎቷ?
    የምትወደው ልጇን ሆነ የውሃ ሽታ!

    ምን ያደርግላታል ብታለቅስ ብትረግመው፣
    ከውሃ ተጣልታ የትም ለማትደርሰው?
    እሷም አለችው ብላ ጠጋ፣
    ለአንተም አለ በጋ!!
    እሷም አለችው ብላ ጠጋ፣
    ለአንተም አለ በጋ!!

    ድሃ አይጣላ ከውሃ! (5x)
    ድሃ ኣኣኣ አይጣላ ከውሃ!! (8x)

    ምንጭ፦ ዶይቸ ቬለ ሬድዮ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ዳዊት ፅጌ የኔ ዜማ


    Semonegna
    Keymaster

    ብርሃን ባንክ የ10ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓሉን ሲያከብር ለኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ሕፃናት መርጃ ድርጅት የ3 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ክፍል የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ብርሃን ባንክ የ10ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓሉን ህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች በስካይላይት ሆቴል በደማቅ ሁኔታ አክብሯል። በዝግጅቱ ባንኩ ለአገልሎት ክፍት ከሆነበት ከከፈረንጆች ጥቅምት (October) ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ያሉ የተለያዩ ዋነኛ ስኬቶቹን በማወደስ፣ የወደፊት ጊዜያትን ደግሞ በጠንካራ አቅም ሊጓዝ እንዳቀደ ነው ያስረዳው። የእለቱ ዝግጅት በሦስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያነጣጠረ ሆኖ በተለያዩ መርሃግብሮች በስኬት ተጠናቅቋል።

    ከተለያዩ የህትመት እና ኤሌክተሮኒክስ ሚዲያ ተቋማት ተጋብዘው በቀረቡ የሚዲያ አካላት በተዘጋጀው የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እና የባንኩ ፕሬዚዳንት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ እስከ 11፡45 ድረስ ተከናውኗል። በማስከተልም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ወንበሮቻቸውን እንደያዙ በመድረኩ ላይ በእውቅ የሙዚቃ ተጫዋቾች አማካኝነት ድንቅ የሆነ የቫዮሊን የሙዚቃ ኮንሰርት ለታዳሚያኑ ቀርቧል። ይህንንም ተከትሎ በአርቲስት ሃረገወይን አሠፋ የመድረክ አጋፋሪነት ለእንግዶቹ የሚቀርበው የአዳራሽ ውስጥ ዝግጅቱ በይፋ ተጀመረ። አርቲስት ሃረገወይን የባንኩን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካቀረበች እና አጠር ያለ የ10 ዓመታት የባንኩን የአመሰራረት አፅመ ታሪክ በአጭሩ አቅርባ መድረኩን እንዲረከቧት እና የእለቱን የክብር እንግዶች ወደ መድረክ እንዲጋብዙ የባንኩን ፕሬዚዳንት አቶ አብሃም አላሮን ወደ መድረኩ ጋበዘች።

    የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አብሃም አላሮ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት እንዲያስተላልፉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ የሆኑትን ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ወደ መድረክ ጋብዘው ገዥው ባንኩ በርካታ ባለአክሲዮኖችን በመያዝ ቀዳሚው የንግድ ባንክ መሆኑን ገልፀው ለመላው የባንኩ ማህበረሰብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አቅርበዋል። በማስከተልም የቀረበው የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጉማቸው ኩሴ የእንኳን አደረሳችሁ እና እንኳን ደስ ያላችሁ መልክት ሲሆን፥ ሰብሳቢው በመልዕከታቸው የባንኩን ስኬቶች በማወደስ ቀጣይ ሥራዎችን በተሻለ አቅም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ እምነታቸውን ገልፀዋል። ይህ ዝግጅት እንዲህ ባለው መልኩ ቀጥሎ በባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም አላሮ አጠር ያለ የኢትዮጵያ ባንኮችን ታሪክ እና እድገት እንዲሁም ብርሃን ባንክ በ10 ዓመታት ዕድሜው ያሳየውን የአፈፃፀም ጉዞን የሚያሳይ ጥናት ቀርቧል። ፕሬዚዳንቱ ባንኩ ከምሥረታው ጀምሮ በተለያዩ ልኬቶች ያስመዘገባቸው ስኬቶቹ እጅግ አመርቂ እና ፍሬያማ የሚባሉ መሆናቸውን አብራርተው በቀጣይም እነኚህ ስኬቶቹ በላቀ መልኩ አሸብርቀው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

    በማስከተል የቀረበው ለባንኩ መመሥረት እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ባንኩን ከምሥረታው ጀምሮ ላገዙ መሥራቾች፣ አመራሮች እንዲሁም ላለፉት አስር ዓመታት በባንኩ ላገለገሉ ሠራተኞች የእውቅና እና የምስጋና ስጦታዎችን የማበርከት ሥነ-ሥርዓት ነበር። ከምስጋና የምስክር ወረቀት (certificate) ጀምሮ 13 ሠራተኞቹን ጨምሮ ለተለያዩ ባለድርሻዎች በወርቅ በተሠሩ ስጦታዎች ተበርክቶላቸዋል። ይህንኑ መርሀ ግብር ተከትሎ ብርሃን ባንክ ለኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ሕፃናት መርጃ ድርጅት የ3 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ክፍል 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። ይህንኑ ስጦታ የማዕከላቱ ተጠሪዎች ዶክተር ሄለን በፈቃዱ (የልብ ሕሙማን ህፃናት ድርጅትን በመወከል) እና ዶክተር ብሩክ ላምቢሶ (የአጥንት ህክምና ክፍልን በመወከል) ከባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እጅ ተቀብለዋል። ይሀንን ስጦታ ሲቀበሉም ድጋፉ በሚደረግላቸው እና የህክምና ወጪዎቻቸውን መሸፈን በማይችሉ አቅመ ደካማ ህፃናት እና አረጋውያን ስም አመስገነው ገንዘቡን ሙሉ በሙሉ ለታለመለት ዓላማ እንደሚያውሉ ከምስጋና ጋር ቃል ገብተዋል።

    በዝግጅቱ መጨረሻ ላይም የባንኩ ቀጣይ የንግድ ምልክት ወይም መለያ ምልክት ሆኖ የሚያገለግለውን አዲስ አርማ ለታዳሚያን ተዋውቆ የዕለቱ ዝግጅት በእራት መርሀ ግብር በደማቅ ሁኔታ ተገባዷል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ብርሃን ባንክ

    Semonegna
    Keymaster

    በኢትዮጵያውያን የኪነ ጥበብ አድናቂዎች ዘንድ ተወዳጅነት እያተረፈ የመጣው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል፣ አዲስ አበባ፣ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። ቁራኛዬ ፊልም ሦስት ሽልማቶችን ሲያገኝ፥ ድምጻዊ ቸሊና እና ዘመን ተከታታይ ድራማ ሁለት፣ ሁለት ሽልማቶችን አግኝተዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – በሀገራችን የሙዚቃ ታሪክ እጅግ መቀዛቀዝ፣ የሙዚቃ አልበምም ህትመት መፍዘዝ፣ ፊልም ሠሪዎችም ሥራዎቻችውን ተመልካቾች ፊታቸውን ባዞሩባቸው ወቅት እንደ አንድ የኪነጥበብ አባልና የሚዲያ ባለሙያ አቅማቸው በፈቀደ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማበርከት፣ እንዲሁም አድማጭ እና ተመልካቹን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለማነቃቃት በማሰብ ነበር ጋዜጠኛ ብርሀኑ ድጋፌ እና ባልደረቦቹ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ላይ “ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት” ሥነ ሥርዓትን የየጀመሩት።

    በእርግጥ ኪነ-ጥበብና ኢትዮጵያ ሀገራችን በባህላዊውም ሆነ በዘመናዊው መንገድ እጅግ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ቁርኝት ቢኖራቸውም ቅሉ የኪነ ጥበብ ሙያዉን እንደተከበረ ሙያ ባለሙያዉንም የተከበረ ሙያ እንዳለው ቆጥሮ ወቅት ጠብቆ በተገደበ የጊዜ ኡደት ለሙያውና ለባለሙያው ተገቢውን ዕውቅና፣ ብሎም ክብር የሚሰጥ ቋሚ ተቋም ባለመኖሩ ያለመኖሩን በማስገንዘብ የሥነ ስርዓቱ ሀሳብ ጠንሳሾች “ለምን እኛ የቻልነውን አናደርግም?” በሚል ነበር የኪነ ጥበብ ሰዎችን በዓመት አንድ ጊዜ እያሰባሰቡ ለማወያየት፣ በዓመቱ በሙያውና በሙያቸው ጉልህ አስተዋጽዖ ያደረጉትን “በጎ ሥራ ሠርታችኋል! ይበል!” ለማለት ለዛ የኤድማጮች ምርጫ ሽልማትን በ2003 ዓ.ም የጀመሩት።

    በ2003 ዓ.ም በተደረገው የመጀመሪያ ሽልማት ‘የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ’፣ ‘ምርጥ ተዋናይት’፣ ‘የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ’፣ ‘የዓመቱ ምርጥ ፊልም’ እና ‘የዓመቱ ምርጥ አልበም’ በሚሉ አምስት ዘርፎች (ዘውጎች) ኢትዮጵያውያን የኪነ ጠበብ ሰዎች ተመርጠው የተሸለሙ ሲሆን ሽልማቱም ያገኙትም ከያኒት ዘሪቱ ከበደ “አርቴፍሻል” በሚለው ነጠላ ሙዚቃዋ፣ ተዋናይት ሰሃር አብዱልከሪም “ያንቺው ሌባ” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣ ጋሽ አበበ ባልቻ “ሄሮሺማ” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየው ትወና፣ “ሄሮሺማ” ፊቸር ፊልም በምርጥ በፊልምነት፣ እንዲሁም ከያኒ ናትናኤል አያሌው (ናቲ ማን) በመጀመሪያው አልበሙ በአምስቱ የተዘረዘሩት ዘርፎች አሸናፊዎች ሆነው የሥነ ሥርዓቱ የበኩር ተሸላሚዎች ሆኑ።

    በዚህ መልኩ የተጀመረው ለዛ የአድማጮች ምርጫ በየዓመቱ ከጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ ሃምሌ ድረስ የሚወጡ የኪነ ጥበብ ሰዎችንና ሥራዎችን በአድማጮች ምርጫ አወዳድሮ ዕውቅና እየሰጠ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሳታፊዎችን እያበዛ፣ በባለሙያዉም፣ በመራጭነት በሚሳተፈውም ይሁን በየበይ ተመልካችነት በሚከታተለው ኢትዮጵያዊ ዘንድም ተወዳጅነት እያተረፈ ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል፣ አዲስ አበባ፣ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። በዘጠነኛው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች ሽልማት ያገኙት የሚከተሉት ናቸው።

    • ምርጥ ነጠላ ዜማ፦ “ቢልባ” (ጃንቦ ጆቴ) [ኦሮምኛ ሙዚቃ]፣
    • ምርጥ አዲስ ድምፃዊ፦ ቸሊና የሺወንድም (“ቸሊና” በተባለው የሙዚቃ አልበሟ)፣
    • ምርጥ የሙዚቃ አልበም፦ “ቸሊና” (ቸሊና የሺወንድም)፣
    • ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ፦ ከእሁድ እስከ እሁድ (ጎሳዬ ተስፋዬ)፣
    • ምርጥ ሙዚቃ/ዘፈን፦ “ሰርካለሜ” በድምጻዊ ዚጊ ዛጋ (በኃይሉ ታፈሰ)፣
    • ምርጥ ተዋናይት፦ የምስራች ግርማ ቁራኛዬ በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣
    • ምርጥ ተዋናይ፦ ዘሪሁን ሙላት ቁራኛዬ በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየው ትወና፣
    • ምርጥ ፊልም፦ ቁራኛዬ
    • ምርጥ ተዋናይት በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ ሀና ዮሐንስ (“ዘመን” ድራማ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን)፣
    • ምርጥ ተዋናይ በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ አበበ ባልቻ (“ዘመን” ድራማ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን)፣
    • ምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ ደርሶ መልስ በፋና ቴሌቪዥን፣ እና
    • “የ2010 ዓ.ም የኪነ ጥበባ በለውለታ” የክብር ተሸላሚ፦ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ደማቅ አሻራቸውን ያስቀመጡትን የቀድሞዎቹን አይቤክስ ባንድ እና ሮሃ ባንድ ከመሠረቱት አባላት አንዱ የሆኑት ጂዮቫኒ ሪኮ (Giovanni Rico)

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ቁራኛዬ


    Anonymous
    Inactive

    በአገራችን ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ በመከላከል እና ቢከሰቱም እንኳን የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸዉ በፊት በአፋጣኝና በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ረገድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዓይነተኛ ሚናን መጫወት ችሏል።

    አዲስ አበባ (ኢመደኤ) – የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ባሳለፍነዉ 2011 በጀት ዓመት በተለያዩ ቁልፍ የሀገሪቱ ተቋማት እና መሠረተ ልማቶች ላይ ሊፈጸሙ የነበሩ 791 የሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶችን (cyber-attacks) ማክሸፍ መቻሉን ገለጸ።

    በኢመደኤ የኢትዮጵያ ሳይበር የድንገተኛ ዝግጁነት እና ምላሽ ሰጪ ዲቪዥን (Ethiopian Cyber Emergency Readiness & Response Team – ETHIO CERT) ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም ገብረጻዲቅ እንደገለጹት፥ በአገራችን ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ በመከላከል እና ቢከሰቱም እንኳን የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸዉ በፊት በአፋጣኝና በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ረገድ ኢመደኤ ዓይነተኛ ሚናን መጫወት መቻሉን ገልጸዋል። ኃላፊዉ ጨምረዉ እንደገለጹት በ2011 በጀት ዓመት በአገሪቱ ላይ የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ መከላከል በመቻሉ ሊደርስ ከነበረው የደኅንነት እና የገንዘብ ኪሳራ በድምሩ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማዳን መቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ ከዚህም በላይ በገንዘብ የማይተመን ሰላምን እና ፍትህ ማስጠበቅ ተችሏል ብለዋል። በቀጣይ 2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት አገራዊ የሳይበር ጥቃትን የመከላከል ሽፋን በማሳደግ እና ዓለም አቀፍ ትስስርንና ቅንጅትን በማጠናከር የአገሪቱን ቁልፍ የሳይበር መሠረት ልማቶችን ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ እንደሚሠራም ኃላፊዉ ገልጸዋል።

    በኢመደኤ የኢትዮጵያ ሳይበር የድንገተኛ ዝግጁነት እና ምላሽ ሰጪ ዲቪዥን በኢትዮጵያ የሳይበር ሥነ-ምህዳር የሚገኙ የሳይበር መኃረተ ልማቶችን ከጥቃት ከመከላከልና ምላሽ ከመስጠት ባለፈ የሳይበር ደህንነት ክፍተት ትንተና (vulnerabilities) በማከናወን የሳይበር ጥቃት አስቀድሞ የመከላከል፣ የሳይበር ጥቃቶች ከመፈጠራቸው በፊት የማስቀረት፣ የተፈጠሩት ሳይበር ጥቃቶች ከጥቃቱ በፊት ይሠሩበት ወደነበረው ይዞታቸው የመመለስ እና በተመሳሳይ ጥቃት እንዳይጠቁ የደኅንነት ክፍተታቸውን እንዲደፈን የማድረግ፤ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የሳይበር ጥቃት መከላከያ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትስስር ሥራዎችን የሚሠራ ክፍል ነዉ።

    ምንጭ፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ኢመደኤ


    Anonymous
    Inactive

    ሴተኛ አዳሪዎች እና የእኔ ቢጤዎች (ለምኖ አዳሪዎች) ላይ መስተዳድሩ ሊወስድ ያሰበው እርምጃ ሰብዓዊነት የጎደለው እና መንግሥት ድህነትን ለማጥፋት በቅድሚያ ማከናወን የሚገባውን ሥራዎች ሠርቶ ሳይጨርስ በድሃ ላይ ለመዝመት ማሰቡ የአስተዳደሩን ብልሹ አተያይ ከወዲሁ የሚያሳይ ነው።

    ደሃን በማጥፋት ድህነትን መዋጋት አይቻልም!
    (ያሬድ ኃይለማርያም)

    የአዲስ አበባ መስተዳደር የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሹ በሚል የፈረጃቸውን የእኔ ቢጤዎች እና ሴተኛ አዳሪዎችን ከከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ለማወገድ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ሽር ጉድ እያለ መሆኑን እና ሕግ ያረቀቀ መሆኑን በቅርቡ ገልጿል። ህብር ሬዲዮ እንደገለጸው በመስተዳድሩ የከንቲባው ጽ/ቤት የፕሬስ ጉዳይ ሹም ከፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የአገሪቱን እና የከተማዋን መልካም ገጽታን የሚያበላሹት ከ50 ሺህ በላይ የእኔ ቢጤዎች እና 10 ሺህ የሚገመቱ ሴተኛ አዳሪዎች ከከተማው ጎዳናዎች የሚወገዱበት እርምጃ ሊተገበር ተቃርቧል” በማለት መግለጻቸውን ዘግቧል።

    ከ90 በመቶ በላይ ድሃ ሕዝብ የያዘች እና በዓለምም የድሃ ድሃ በሚል ማዕረግ የምትታወቅ አገር ድህነትን ለመቅረፍ ገና ረብ ያለው እርምጃ ሳትወስድ ድሃን ለማጥፋት መጣደፏ አጃይብ የሚያሰኝ ነው። ለነገሩ ለአንዳንድ ችግሮቻችን መስተዳድሩም ሆነ በአገር ደረጃ የሚወሰዱቱ እርምጃዎች እጅግ አስገራሚ እና በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች በመሬት ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር ምን ያህል ያህል ይተዋወቃሉ የሚለውን እንድንጠየቅ የሚያደርጉ ነገሮች ደጋግመን እያየን ነው። ለምሳሌ ያህል ሌብነት በእግረኛ፣ በሞተረኛ፣ በመኪና እና በሌሎች የተደራጁ ቡድኖች በአደባባይ በሚፈጸምባት መዲና፤ አዲስ አበባ ሌብነት ለመከላከል ተብሎ በሞተር አሽከርካሪዎች ላይ የተወሰደው የጅምላ እቀባ፣ ፈተና እንዳይሰረቅ በሚል የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናዎች ሲቃረቡ የኢንተርኔት አገልግሎት ለቀናቶች ማቋረጥ እና እነኚህን የመሳሰሉ አንዱን ችግር በሌላ ችግር የመቅረፍ አካሄድ ግራ ከማጋባት ባለፈ የአስተዳዳሪዎቹንም ብቃት እና ለሕዝብ ችግር ያላቸውንም ቀረቤታ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። የተደራጀው ሌብነት በመኪና ቢሆን የሚካሄደው ምን ሊደረግ ይሆን?

    ወደ ተነሳሁነት ዋና ጉዳል ልመለስና በልመና እና በሴተኛ አዳሪነት ሥራ በተሰማሩ የአገሪቱ ዜጎች ላይ መስተዳድሩ ሊወስድ ያሰበው እርምጃ ሰብዓዊነት የጎደለው እና መንግሥት ድህነትን ለማጥፋት በቅድሚያ ማከናወን የሚገባውን ሥራዎች ሠርቶ ሳይጨርስ በድሃ ላይ ለመዝመት ማሰቡ ደግሞ የአስተዳደሩን ብልሹ አተያይ ከወዲሁ የሚያሳይ ነው። እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለ የድሃ ደሃ አገር አይደለም በሰለጠኑት እና በሃብት በተትረፈረፉት አገሮች እንኳን የመንገድ ላይ ለማኝ እና ሴተኛ አዳሪ አይታሰርም፣ አይሳደድም ወይም ከከተማ እንዲወገድ አይደረገም። አንዳንዱ አገር ሴተኛ አዳሪነት እንደ ማንኛውም የንግድ ሥራ ጭምር ተቆጥሮ የግብር ከፋይ ኮድ ተሰጥቷቸው እና ፍቃድ ተሰጥቷቸው በአደባባይ እንደልባቸው እና ሙሉ ጥበቃ ተደርጎላቸው ይሰራሉ። እኛ ጋ ይህ ይሁን እያልኩ አለመሆኑ ይታወቅልኝ። ነገር ግን እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ከጎዳና ላይ ለማጽዳት ሕግ ከማርቀቅ እና ከመፎከር በፊት ዜጎችን ለልመና እና ለሴት አዳሪነት የሚዳርጉትን ዋና ዋና ምክንያቶችን በቅጡ ማጥናት እና ምንጩን ለማንጠፍ ማቀድ ይቀድም ነበር።

    የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማም ሆኑ አብረዋቸው ሃሳቡን የሚገፉ የመስተዳድሩ አካላት የሚያስተዳድሯትን ከተማ እና የሚመሩትን አገር ባህሪ በቁጡና በደንብ ያጠኑት እና ያወቁት አልመሰለኝም። የአዲስ አበባ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና ሴተኛ አዳሪዎች ለመስተዳድሩ ተሿሚዎች እና በቅንጦት ለሚኖረው የከተማዋ ነዋሪ የዓይን ቁስል እንደሆኑባቸው ግልጽ ነው። የአዲስ አበባን አውራ ጎዳናዎች ከእነዚህ ድህነት ገፎት አደባባይ ላይ ካሰጣቸው ዜጎች በማጽዳት ግን የኢትዮጵያን ድህነት ወይም የከተማዋን እውነተኛ ገጽታ መሸፈን አይቻልም። ከንቲባው ከጥቂት ወራቶች በፊት የአዲስ አበባን የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደ ተለያዩ የማኖሪያ ተቋማት ለማስገባት ዘመቻ ጀምሬያለው በማለት በየጎዳናው ላይ ሕጻናት ሲሰበስቡ የተነሱትን ፎቶ በየማኅበራዊ ድረ-ገጹ ለቀው እና ዜናውም በአገሩ ተናኝቶ አይቻለው። ያን ጅምራቸውን የት አድርሰውት ይሆን? በወቅቱ የተሰማኝ ነገር ነገርየው እጅግ ተገቢ እርምጃ ቢሆንም ከገጽታ ግንባታ የዘለለ መሆኑ ስጋት ፈጥሮብኝ ነበር። ዛሬም የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በመንገድ ላይ ተዳዳሪዎች እንደተሞሉ ናቸው። ያንን ፕሮጀት ፍሬውን ሳያሳዩን ድሆቹን ከመንገድ ለማጥፋት ሕግ ማርቀቅ መጀመራቸው የበለጠ ለገጽታ ግንባታ የሰጡትን ክብደት እንጂ ሰብዓዊነታቸውን አያሳይም።

    ወያኔም ይችን ድሃን ከጎዳና ላይ የማራቅ ስልት በከፋ ሁኔታ ደጋግማ ሞክራዋለች። አዲስ አበባ ከሚመጡ ዓለም አቀፍ እንግዶች አይን ድሃን ለማራቅ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የእኔ ቢጤዎች እና ሴተኛ አዳሪዎችን አፍሰው በሌሊት ከአዲስ አበባ አርቀው በመጣል እና ወደ ከተማዋ እንዳይመለሱ በማድረግ የጅብ እራት ያደረጓቸው ዜጎች ነበሩ። ይህ አስነዋሪ እርምጃ በወቅቱ በኢሰመጉ ተጣርቶ መግለጫ ወጥቶበታል። ዛሬ መስተዳድሩ ይህን አይነት አስነዋሪ ድርጊት ይፈጽማል ብዮ ባላስብም የእነዚህን መጠጊያ የሌላቸው ድሆች እንቅስቃሴ በሕግ ለመገደብ የጀመረው እንቅስቃሴ ግን አልሸሹም ዞር አሉ ነው የሚሆነው።

    የዛሬ ሃያ ዓመት ግድም በአዲስ አበባ ከተማ በልመና እና በሴተኛ አዳሪነት በተሰማሩ ዜጎች ላይ ያተኮረ እና አንድ ዓመት ተኩል ግድም በወሰደ ጥናት ላይ የመሳተፍ ዕድል ገጥሞኝ ነበር። በአዲስ አበባ ውስጥ እንኳን መንግሥት የከተማው ነዋሪ ጭምር የማያውቀው ብዙ ጉድ እንዳለ የታዘብኩበት እና እንደ ዜጋ እራሴም የተሸማቀቅኩበት ብዙ ገበናችንን አይቻለሁ። አዲስ አበባ ቢያጠኗት የማታልቅ የጉድ ከተማ ነች። በውስጧ ብዙ አይነት ሕይወትን የያዘች እና ብበዙ ድሃ ዜጎች ገበና ሸፋኝ ከተማ ነች። ችግሩ ገበናዋን አስተዳዳሪዎቿም ሆኑ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ አያውቀውም። የሚያስተዳድሯትን ከተማ የማያውቁ አስተዳዳሪዎች ታክተው ትተዋት እሲኪሄዱ የነሱንም ገበና ተሸክማ የምትቆይ ጉደኛ ከተማ ነች።

    በሴተኛ አዳሪዎች ላይ ያደረግነው ጥናት እና የሰማናቸው የህይወት ታሪኮች ቢጻፉ መጻህፍት ይወጣቸዋል። ከ14 ዓመት ህጻን ሴተኛ ዳሪ አንስቶ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ታናናሽ ወንድም እና እህቶቿን ለማስተማር እና ለማስተዳደር በአንድ ምሽት ከ24 ወንዶች ጋር በየተራ ግንኙነት አድርጋ በስተመጨረሻ እራሷን ስታ የወደቀችውን የጎጃም በረንዳ ወጣት ሴት ታሪክ ከራሳቸው ከባለታሪኮቹ አንደበት ሰምቻለሁ።

    ባለሥልጣናት በሚሊዮን ገንዘብ በሚቆጠር ወድ መኪኖች፣ በተንጣለሉ ቪላዎች፣ በውድ ሆቴሎች በሚንፈላሰሱባት እና ባስነጠሳቸው ቁጥር ከአገር ውጭ ውጥተው በአውሮፓ እና በአሜሪካ ህክምና እንዲያገኙ በምታደርግ አገር ውስጥ የኑሮ ዋስትና አጥተው ጎዳና ላይ የሚለምኑ እና ሰውነታቸውን የሚሸቅጡ ዜጎች (ሴተኛ አዳሪዎች) ቁጥር ቢበረክት ምን ይገርማል። እያንዳንዱ ዜጋ በአገሪቱ ሃብት እኩል የመጠቀም መብት እና ድርሻ እንዳለው ባልተቀበለች አገር ውስጥ የሺዎችን ድርሻ ለአንድ ድንቁርና ለተጫነው እና ሰብዓዊነት ከውስጡ ተንጠፍጥፎ ላወጣ ባለስልጣን ምቾት እና ድሎት የምታውል አገር በጎዳና ተዳዳሪ ዘጎች ብትወረር ምን ይደንቃል።

    ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከድህነት እና ከድሃ ጋር በተያያዘ የሚናገሩት ሁለት ቁምነገር ይህን እየጻፍኩ ወደ አዕምሮ ስለመጣ ላካፍላችሁ። አንዱ “ድሃ ባይኖር ኖሮ ሃብታም ተብድሎ አያድርም ነበር” የምትለዋ ነች። አዎ ማኅበራዊ ፍትህ በተጓደለበት፣ ሙስና ያለቅጥ በተንሰራፋበት፣ ግለኝነት በነገሰበት እና ለድሃ አሳቢ መንግሥት በሌለበት ስፍራ ሁሉ የሚሊዎኖች ድህነት የጥቂቶች የብልጽግና ምንጭ ይሆናል። ዘርፎ የበለጸገውን ባለሃብት እንተወው እና ለአንድ ባለሥልጣን ምቾት ተብለው የሚበጀት ገንዘብ ለስንት ድሃን የመኖር ዋስትና እና መሠረታዊ ነገሮች ሟሟያ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ለእናንተው እተዋለሁ።

    ሁለተኛው የፕሮፌሰር ምክረ ሃሳብ ድህነትን የመርሳት በሽታችንን የሚያሳይ ነው። ምን ይላሉ “እንደ ድህነት ቶሎ የሚረሳ ነገር የለም፤ እኔም ድህነቴን እንዳልረሳ ድሆች ያሉበት አካባቢ መኖርን እመርጣለሁ። ድህነቴን ካልረሳው ድሃንም አረሳም፤ ያለኝን በወር በወር ከድሃ ጋር እካፈላለሁ።” እያሉ ድህነታችንን ቶሎ እንዳንረሳ እና በድሃ ላይ እንዳንጨክን እና እንዳንከፋ ደጋግመው ያስተምሩን ነበር። ድሃ ሰው ድህነቱን ቢረሳ ኩነኔው ለራሱ ነው። በሌሎች ድሆች ላይ የሚያደርሰውም ጉዳት ያን ያህል ላይሆን ይችላል። ድሃ ሕዝብ የሚያስተዳድር ድሃ መንግሥት ድህነቱን ቶሎ ሲረሳ እና ከተማዋን የሀብታሞች ደሴት ለማድረግ እንቅልፍ ሲያጣ ግን አደጋው ብዙ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው ሕዝቧ ትልቁን ቁጥር በሚይዝበት አገር ድሃን ከመንገድ ለማራቅ መዳከር ውድቀትን መለመን ነው። በሞቀ ጎጇቸው ውስጥ እየሆሩ በድህነት አቅሙ የጣላትን ደሳሳ ጎቾ በላዩ ላይ አፍርሰው ሲያበቁ መንገድ ላይም ለምኖ እንዳያድር ሕግ የሚያወጡ እና ስልት የሚነድፉ ሹመኞች ጸባቸው ከድሃ እንጂ ከድህነት ሊሆን አይችልም። ባለፉት 27 የታከለ ኡማ ፓርቲ ኢህአዴግ መኖሪያ ቤታቸውን እያፈረሰ ለጎዳና ላይ ሕይወት የዳረጋቸውን ዜጎች የፈረሰው ቤት ይቁጠራቸው።

    የአዲስ አበባ መስተዳድርም ሆነ የአገሪቱ መንግሥት እንዲህ አይነት የዜጎችን መሠረታዊ መብት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እና በተለይም ድሃውን የአገሪቱን ሕዝብ የመኖር ዋስትና የሚያሳጡ እርምጃዎችን ለመውሰድ ከመሞከር በፊት ለዜጎች ድህነት እና ለጎዳና ሕይወት ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ለማንጠፍ ቢሰራ መልካም ነው። ይህ ደግሞ እንዲህ በጥድፊያ በአንድ ዓመት አይደለም በአምስት እና አስር ዓመትም ውስጥ የሚሳካ ነገር ስላልሆነ ቅድሚያ ድህነትን ለማጥፋት ይሰራ። ድሃነት መአረግ ስላልሆነ ማንም መርጦ የገባበት ህይወት አይደለም እና ድህነት ሲጠፋ ድሃም እቤቷ ትሰበሰባለች። ድሃ ላይ ያነጣጠሩ የጽዳት ዘመቻዎች ግን ‘ወጡ ሳይወጠወጥ…’ ነው የሚሆነው።

    በቸር እንሰንብት!

    (ያሬድ ኃይለማርያም)

    ሴተኛ አዳሪዎች እና የእኔ ቢጤዎችን ከአዲስ አበባ በማስወጣት ድህነትን መዋጋት አይቻልም!


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– አገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ (NEAEA) የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የፈተና ውጤትን ነሐሴ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ አደረገ።

    የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት፥ ወጤታቸን በመጠባበቅ ላይ ያሉ ተፈታኝ ተማሪዎች ውጤታቸውን በኤጀንሲው ድረ-ገጽ app.neaea.gov.et በመግባት ማወቅ ይችላሉ።

    የመፈተኛ ቁጥራቸውን አድሚሸን (Admission) በሚለው ሳጥንውስጥ በማስገባት ውጤታቸውን መመልከት ይችላሉ ብለዋል አቶ አርአያ።

    በሞባይል አጭር የፅሁፍ መለእክት (SMS) 8181 id በማለት የሚያዩበት አማራጭ መመቻቸቱንም ገልጸዋል።

    • የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ለማወቅ እዚህ ጋር ይጫኑ app.neaea.gov.et

    በ2011 ዓ.ም. የትምህረት ዘመን 319 ሺህ 264 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና የወሰዱ ሲሆን 59 ተማሪዎች ከ600 መቶ በላይ ውጤት አስመዝግበዋል።

    ዘንድሮ 645 ከፍተኛ ውጤት ሆኖ መመዝገቡም ታውቋል።

    የዘንድሮው ውጤት ካለፉት ዓመት ጋር ሲነፃፀር መካከለኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች 48 ነጥብ 59 በመቶ ናቸው።

    በፈተና ሥነ ስርዓት ጥሰት ምክንያት በቀረበባቸው ሪፖርት የ68 ተማሪዎች ውጤት መሰረዙንም አቶ አርአያ ገልጸዋል።

    ከአራት ክልሎች (አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ቤኒሻንጉል) የ864 ተማሪዎች ውጤት ለተጨማሪ ማጣራት እንዲያዝ ተደርጓል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት


    Anonymous
    Inactive

    ፓምፋሎን ብዙ ልታይ ልታይ የሚል ሰው አይደለም። ሙዚቃውን ለሕዝብ በሚያቀርብበት ጊዜ የአድማጮቹ ትኩረት በመልዕክቱ ላይ እንዲሆን እንደሚፈልግ ይናገራል። ለዚህም ነው ብዙ የሙዚቃ ክሊፖችን የማይሠራው።

    ቅድመ ነገር – ለምን የሙዚቃ ስሙን ፓምፋሎን ብሎ ሰየመው?

    የሁለት ሰዎችን ሕይወት የሚተርክ በልጆች መጽሐፍ ውስጥ ያለ ታሪክ ነው። አንደኛው ገፀ-ባሕሪ መንፈሳዊ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ዓለማዊ ነበር።

    መንፈሳዊው ከሰዎች እና ከዓለማዊ ኑሮ ርቆ ለሠላሳ ዓመታት ከፈጣሪው ጋር በመወያየት ቆየ። አንድ ቀን ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ ሳለ ለመንፈሳዊው ግለሰብ ፈጣሪ ይገለጥለትና ወደ ፓምፋሎን እንዲሄድ ይነግረዋል።

    ይህም ሰው ለመንፈሳዊ ጥያቄዎቹ እንዴት ወደ ፓምፋሎን እንደተላከ ሊገባው አልቻለምና ፈጣሪውን “ለምን ወደ እርሱ ትልከኛለህ?” ብሎ ሲጠይቅ “በሰዎች ዓይን ፓምፋሎን ዓለማዊ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን የሰው ልጅ መንፈሳዊነት በልቡ ያለ እንጂ በሰዎች የሚታይ አይደለም” ብሎ ይመልስለታል። “እኔም ለዚያ ነው የሙዚቃ ስሜን ፓምፋሎን ያልኩት” ይላል ፓምፋሎን።

    የፓምፋሎን ተረት በሩስያዊ ደራሲ የተፃፈ ቢሆንም ፓምፋሎን ግን ከልጅነቱ ጀምሮ በጀርመን ሃገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ነው። ያለ እናትና አባት ያደገው ፓምፋሎን ከ16 ዓመቱ ጀምሮ ነው ራሱን ማስተዳደር የጀመረው።

    ስለ ሕይወት ታሪኩ እና ወደ ጀርመን እንዴት እንደሄደ ሲጠየቅ “እሱን ሌላ ጊዜ በሌላ መልኩ ለሕዝብ ለማቅረብ ስለምፈልግ ለጊዜው ስለ ታሪኬ ለመናገር ዝግጁ አይደለሁም” ይላል።

    በየወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ የሚለው ፓምፋሎን ነገሮች ቢመቻቹለት ኑሮውን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያደርግ ይወዳል። ለጊዜው በሙዚቃ ስሙ ብቻ እንዲታወቅ እንደሚፈልግ ይናገራል።

    ወደ ሙዚቃ የገባው በተለያዩ ነገሮች ተገፋፍቶ ነበር። “የተለያዩ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የምጠቀምበት ስለሆነ ነው ሙዚቃ መሥራት የጀመርኩት። ጥበበኛ ነኝ ወይም ችሎታ አለኝ ማለትም አልፈልግም ምክንያቱም ለጊዜው ሙዚቃውን መልዕክት ማስተላለፊያ ነው ያደረግኩት” በማለት በትህትና ይናገራል።

    ፓምፋሎን ብዙ ልታይ ልታይ የሚል ሰው አይደለም። ሙዚቃውን ለሕዝብ በሚያቀርብበት ጊዜ የአድማጮቹ ትኩረት በመልዕክቱ ላይ እንዲሆን እንደሚፈልግ ይናገራል። ለዚህም ነው ብዙ የሙዚቃ ክሊፖችን የማይሠራው።

    “ለጊዜው የሙዚቃ ዓለሙን ተቀላቀልኩ እንጂ ወደፊት ሌሎች ነገሮችን የመሥራት ፍላጎት አለኝ” የሚለው ፓምፋሎን በሙዚቃዎቹ የተለያዩ ሰዎችን ንግግሮች ያካትታል። ከእነዚህም መካከል የማንዴላ፣ የማልኮም ኤክስ እና የዶ/ር አብይ አሕመድ ይገኙበታል።

    ለምን ብሎ ሲጠየቅም በአንድ ወቅት ንግግሮቹ ስሜቱን ከነኩት የሙዚቃውን መንፈስ ለአድማጮቹ ለማስተላለፍ እንደሚያስችሉት በማሰብ እንደሆነ ይናገራል።

    ገቢው በሙዚቃ ሥራዎቹ ላይ እንዳልተመሰረት የሚናገረው ኢትዮ-ጀርመናዊው ሙዚቀኛ “ሙዚቃዬ እያበላኝ አይደለም። የምተዳደረው በግራፊክ ዲዛይን፣ ፎቶግራፎችን በመሸጥ እና ሌሎች ነገሮች በመሥራት ነው” ይላል።

    የሕይወቱን ሦስት አራተኛ በጀርመን ስለኖረ አልፎ አልፎ በጀርመንኛ መልዕክቱን ለማስተላለፍ ይቀለዋል። ሆኖም ግን በአማርኛ ነው አልበሙን የሠራው። “ቋንቋ እንደአጠቃቀማችን ነው እና ጀርመንኛው ቀለል ይለኛል ግን ሆን ብዬ በሃገሬ ቋንቋ ነው ሙዚቃዬን የምሠራው ምክንያቱም የኢትዮጵያ ልጅ ነኝ” በማለት ይናገራል።

    አክሎም “በልጅነቴ የተለያዩ የራፕ ቡድኖችን ተቀላቅዬ በጀርመንኛ ራፕ አደርግ ነበር። ሳድግ ግን ምንድነው ማድረግ የምፈልገው ብዬ አሰብኩበት። መልዕክቴን ለኢትዮጵያ ማስተላለፍ እንደሆነ ሳውቅ በአማርኛ መሥራት ጀመርኩኝ” ይላል።

    የሚሠራቸውን የተለያዩ የጥብብ ሥራዎች በእኩል እንደሚመለከት የሚጠቅሰው ፓምፋሎን ቢገደድ እንኳን አንዱን ብቻ ለመመረጥ በጣም እንደሚከብደው የሚናገረው በመግለጽ እየሳቀ “ከሙዚቃውና ከፎቶግራፍ ምረጥ የሚለኝን ሰው እንደጠላት ነው የምቆጥረው” በማለት ይናገራል።

    “የግጥም አፃፃፌ እራሱ ከኢትዮጵያ ገጣሚያን የተለየ ነው። ብዙዎችም ለየት እንደሚል ይነግሩኛል” በማለት በሃገሩ ቋንቋ ሥራዎቹን ለሕዝብ ማቅረብ መቻሉ እንደሚያስደስተው ይገልፃል።

    ቢቢሲ አማርኛ ላይ ማንበብዎን ይቀጥሉ

    ፓምፋሎን


Viewing 15 results - 1 through 15 (of 25 total)