-
AuthorSearch Results
-
August 13, 2020 at 11:53 am #15396
In reply to: የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
SemonegnaKeymasterበአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አፈጻጸም ወቅት የታዩ ክፍተቶች አፋጣኝ ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይገባል!
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ‹COVID-19› በኢትዮጵያ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ቁጥር 3/2012 ማወጁ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከታወጀ ወዲህ በመላው ሀገሪቱ ወጥነት ባለው መልኩ እየተተገበረ ካለመሆኑም በላይ የቫይረሱን ስፋት እና የስርጭት መጠን መሠረት በማድረግ በየጊዜው በአስፈጻሚው አካል የሚወጡ መመሪያዎችም በጥናት ያልተደገፉ እና ለሕግ አስከባሪው ኃይል የተለጠጠ የማስፈጸም ሥልጣን የሚሰጡ ሆነው ታይተዋል። በዚህም ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት አስር ሳምንታት የታዩት የዐዋጁ አፈጻጸም ሂደቶችም ሆኑ የመመሪያ አወጣጥ ሂደቱ ማሻሻያ ሊደረግባቸው የሚገቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በጽኑ ያምናል።
ዓለም-አቀፉ የጤና ድርጅት እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስን አስመልክተው በየጊዜው ይፋ ከሚያደርጓቸው መግለጫዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ቫይረሱ ገና በቅጡ ተጠንቶ ያልታወቀ ተለዋዋጭ ባሕርይ ያለው መሆኑ ነው። ከዚህ የተነሣ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንዲያስችሉን የምንወስዳቸው እርምጃዎች በበቂ ጥናት ላይ የተመረኮዙ መሆን ይኖርባቸዋል። ቫይረሱ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከታወቀበት ጊዜ አንሥቶ ፍ/ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው መቆየታቸው የዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብት እንዲገደብ ከማድረጉ በላይ ጉዳያቸው በአፋጣኝ ታይቶ በነጻ መሰናበት እንዲሁም በዋስ መለቀቅ የሚችሉ ዜጎች ያለ አግባበብ በእሥር እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል። በዚሁ ምክንያት አንዳንድ ማረፊያ ቤቶች በመጨናነቃቸው ዜጎች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ሆነዋል።
የዐዋጁ አፈጻጸም ሲገመገም የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ ከማንኛውም ጥቃት ነጻ-የመሆን፣ ፍትሕ የማግኘት፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቶች ላይ ያልተመጣጠነ ገደብ ያስቀመጠ በመሆኑ እነዚህ ጉዳዮች አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔዎችን የሚሹ መሆናቸውን ኢሰመጉ በጥብቅ ያምናል። ከዚህም በተጓዳኝ በቀጥታ በዐዋጁ ምክንያት ባይሆንም፤ የቫይረሱ መስፋፋት ባስከተላቸው ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች የተነሳ በጤና ባለሙያዎች፣ በሴቶች እና ሕጻናት፣ እንዲሁም በድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ላይ ዓይነተ-ብዙ የመብት ጥሰቶች እየደረሱ በመሆኑ ትኩረት እና መፍትሔ የሚሹ መሆናቸውን ኢሰመጉ ያምናል። እንዲሁም በዐዋጁ አፈጻጸም ወቅት እና በአጠቃላይ ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ ባሉ ጊዜያት ከታዩት ጉልህ የመብት ጥሰቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
በትግራይ ክልል ናዕዴር ዓዴት ወረዳ ቀደም ብሎ በክልሉ ታውጆ የነበረውን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ለማስከበር በሚል አንድ የፖሊስ ባልደረባ በወሰደው የኃይል እርምጃ መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም የአንድ ሰው ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ግንቦት 9 ቀን 2012 ዓ.ም መቐለ ከተማ ሰሜን ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው 05 ቀበሌ አካባቢ አንድ የፖሊስ ባልደረባ በወሰደው የኃይል እርምጃ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ተጨማሪ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ቆስለው ሕክምና ላይ ናቸው። በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ አንድ የባጃጅ ሹፌር በጸጥታ ኃይሎች በተፈጸመበት ጥቃት አንድ እጁ ላይ በጥይት ጉዳት ደርሶበታል።
በተለያዩ አካባቢዎች “የአፍ መሸፈኛ ጭምብል አላደረጋችሁም” በሚል ምክንያት ፖሊስ ተመጣጣኝ ባልሆነ እርምጃ በዜጎች ላይ ከፍተኛ እንግልት እና ለቫይረሱ አጋላጭ በሆነ መንገድ የጅምላ እስር ፈጽሟል። “ዐዋጁን ተላልፈዋል” በሚል ምክንያት ንግድ ቤቶች የሚታሸጉበት እና በሰዓት ገደብ እንዲዘጉ የሚደረጉበት ሂደት አንድ ወጥ አለመሆኑ አድሎአዊ እና ሕገ-ወጥ ለሆነ አፈጻጸም አጋልጧል።
ቫይረሱን ግንባር-ቀደም ሆነው እየተከላከሉ ላሉት የጤና ባለሙያዎች በቂ ራስን የመከላከያ ግብዓቶች እየቀረቡ ባለመሆኑ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ እንዲሰሩ በመደረጋቸው ለቫይረሱም ተጋላጭ ሆነዋል። በጤና ሚንስቴር ይፋ በተደረጉ መረጃዎች መሠረት እስከአሁን ድረስ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ተቋም ሠራተኞች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። “ንክኪ አላቸው” በሚል በየጊዜው ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የሚደረጉ የጤና ባለሙያዎች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ ነው።
በአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የሀገር ውስጥ በረራ ሊያደርጉ የነበሩ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች “ዓለም-አቀፍ በረራ አድርጋችኋል” በሚል ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ለአስራ ስድስት ቀናት ያህል እንዲገቡ፣ ለተወሰኑ ቀናትም ቤተሰብ ያሉበትን እንዳያውቅ ተደርጓል። ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም የቫይረሱን መከላከያ ሥራዎች ሽፋን በማድረግ በአባላትና አመራሮቻቸው ላይ ልዩ ልዩ ተጽዕኖዎች እየደረሱባቸው ነው። ለአብነት፥ ወደ ደቡብ ክልል ቁጫ ወረዳ ሰላም በር ከተማ ለቤተሰባዊ ጉዳይ የሄዱትን አንድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አባል ወደ ከተማዋ ለሚገቡ ሌሎች ሰዎች ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ በማይሆን አሰራር ከግንቦት 9 – 11 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጎ ተለቀዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲ ግንቦት 27 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኮልፌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች እርዳታ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ፖሊስ ጣልቃ በመግባት እንዲቆም ተደርጓል።
የቫይረሱ ስርጭት ባስከተለው ተጽዕኖ የዜጎች የሥራ ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ከመውደቁም በላይ፥ አንዳንድ አሰሪዎች ሠራተኞቻቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ ከሥራ ገበታቸው እንዲሰናበቱ እና አስገዳጅ ፈቃድ ያለክፍያ እንዲወጡ ተደርጓል።
የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ማኅበር ይፋ ባደረገው መረጃ በተለይም በጅቡቲ በኩል የሚገቡ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ከሚደርስባቸው መገለል በተጨማሪ በአንዳንድ ከተሞች የማደሪያ እና የምግብ አገልግሎት እንዳያገኙ፣ መኪና እንዳያቆሙ ክልክላ ይደረግባቸዋል።
መንግሥት ቀዳሚ ትኩረቱን በሽታውን በመከላከል እና ተያያዥ ሥራዎች በማድረጉ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ የቤት ውስጥ ጥቃቶች፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እና ያለ ዕድሜ ጋብቻን የመሳሰሉት ልማዳዊ ጎጂ ድርጊቶች እየተበራከቱ እና እየተስፋፉ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ ብቻ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት 101 ያህል ህጻናት የመደፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል። በተመሳሳይ መልኩ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም መሰል የመብት ጥሰቶች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በመሆኑም፥ ዐዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እና በየደረጃው ያለው ግብረ-ኃይል ለእነዚህ የመብት ጥሰቶች እና የአፈጻጸም ችግሮች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኙ በትኩረት እንዲሠራ ኢሰመጉ ያሳስባል። መንግሥት በዐዋጁ አፈጻጸም ምክንያት ሊጎዱ ለሚችሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች፣ በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊውን የምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እርዳታ እና ድጋፍ እንዲያደርግ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።
ቫይረሱን ከፊት ሆነው እየተከላከሉ ላሉ የሀገራችን የጤና ባለሙያዎች ቫይረሱ አሁን ካለበትም ደረጃ የከፋ የሚሆንበትም ጊዜ ሳይጠበቅ አስፈላጊ የሆነውን ራስን የመከላከያ ግብዓት በበቂ ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲያገኙ መንግስት እና የጤና ሚኒስቴር በትኩረት እንዲንቀሳቀሱ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ በለይቶ ሕክምና ላይ የሚገኙ ዜጎች የምግብ አገልግሎት፣ የመኖሪያ እና የንፅህና መስጫ ስፍራ ጽዳት፣ የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎችን ጨምሮ የሌሎች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አቅርቦትና የመሳሰሉ የአገልግሎት ችግሮች መኖራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች በመኖራቸው መንግሥት በትኩረት ችግሮቹን እንዲያስተካከል ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል። በየጊዜው ዐዋጁን በመተላለፍ ተይዘው እንደ ትምህርት ቤት ባሉ መሠረተ ልማቶች ውስጥ የታሰሩ ዜጎች የሚቆዩበት ሥፍራ እንደ ምግብ፣ አልጋ፣ መጸዳጃና የመሳሰሉት መሠረታዊ አገልግሎቶች ለመስጠት በሚያስችል መልኩ መደራጀታቸውን እንዲያረጋግጥ ኢሰመጉ ያሳስባል።
በዐዋጁ ድንጋጌ መሠረት የመንግስትም ሆነ የግል ትምህርት ተቋማት ተዘግተው ተማሪዎች እና መምህራን በአካል ተገናኝተው ትምህርት የሚሰጥበት ሂደት ተቋርጧል። ሆኖም ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው ትምህርት እንዲከታተሉ እየተደረገበት ያለው መንገድ ጥራቱን በጠበቀ፣ ተማሪዎች ትምህረቱን ለማስተላለፍ የሚረዱትን ነገሮች የማግኘት አቅማቸውን ታሳቢ ያደረገ እና የብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን ፍትሐዊ እድል ለመስጠት በሚያስችል መልኩ እንዲሰጡ መንግሥት እንዲያመቻች ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መርማሪ ቦርድም ሁኔታዎቹን በየጊዜው እየተከታተለ፣ በዐዋጁ ይዘት እና አፈጻጸም ላይ የሚሰጡ አስተያየቶችን በአግባቡ እንዲስተካከሉ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን። መንግሥት ቫይረሱን የመከላከል ሥራዎችን አስመልክቶ በየደረጃው የሚሠሩ ሥራዎች ለሕዝብ ይፋ እንዲሆኑ እና የሲቪል ማኅበረሰቡንም ሌላውን የሕብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል።
ከዚህ በኋላ የሚወጡ መመሪያዎች የበሽታውን ባህርይ ታሳቢ ያደረጉ፣ በበቂ ጥናት እና መረጃ ላይ የተመሠረቱ፣ ለሕግ አስከባሪ ኃይሎች የሚሰጡት ሥልጣን ውስን እንዲሆን፣ ብሎም ክልከላ የተደረገባቸውን ነገሮች በግልጽ የሚያመላክቱ እንዲሆን ኢሰመጉ በጥብቅ ያሳስባል። ዐዋጁን በማስፈጸም ወቅት የፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት ሚና የጤና ባለሙያዎችን የማገዝ እንዲሆን ቅጣት እንኳን አስፈላጊ ቢሆን ሕይወትን የማዳን ዓላማ እንጂ የባሰ አደጋ ውስጥ በማይከት ሁኔታ መሆን ስለሚገባው፤ ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ የሚያሳስብ ድንጋጌ በያዘ መልኩ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ኢሰመጉ ያሳስባል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረጉ የመሬት ወረራን ታሳቢ አድርገው የሚሠሩ የሕግ ማስከበርና የቤት ማፍረስ እርምጃዎች ያለንበት ወቅት ክረምት እንደመሆኑ እና ዜጎችን ለበሽታውም ስርጭት የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ በመሆኑ በጥንቃቄ እና ወጥነት ባለው እንዲታዩ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።
ሁሉም መብቶች ለሁሉም!!
ምንጭ፦ ኢሰመጉ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር አንቀጽ 1(ሀ) እና በኢትዮጵያ ፍትሐ-ብሔር ሕግ ቁጥር ከ404-482 በተጻፉት ድንጋጌዎች መሠረት መስከረም 29 ቀን 1984 ዓ.ም. በአባላት የተመሠረተ የመጀመሪያው መንግሥታዊ ያልሆነ ተሟጋች ተቋም ነው።August 11, 2020 at 7:17 pm #15371In reply to: የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveወላይታ ዞን ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም ሊቆጠቡ ይገባል!
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – ወላይታ ዞን ውስጥ በአንዳንድ ከተሞች ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረጉት ተቃውሞዎች የፀጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የወሰዱት እርምጃ ተመጣጣኝነት አጠያያቂ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
የተለያዩ ምንጮች እንደጠቆሙት የተቃውሞ ሰልፉ የተቀሰቀሰው ሰኞ ዕለት በፌዴሬሽኑ ውስጥ አዲስ የክልል መንግሥት መመሥረትን በተናጠል ለማወጅ በፈለጉ በርካታ ከፍተኛ የዞኑ ባለስልጣናት እስርን ተከትሎ ነው። የመንግሥት ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ግን ታሳሪዎቹ በአካባቢው አለመረጋጋት ለመፍጠር ሲያሴሩ ተይዘዋል ብለዋል።
የኮሚሽኑ የመረጃ ምንጮች እንዳስረዱት የባለስልጣናቱን እስር ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፈኞች በዞኑ ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ከተሞች ወደ ጎዳናዎች የወጡ ሲሆን፥ በዞኑ ዋና ከተማ በሶዶ አንድ ሰው እንዲሁም በቦዲቲ ከተማ አምስት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል ።
በሰኞው እስር ወቅት በጠቅላላው 178 ሰዎች የተያዙ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 28ቱ የዞኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት መሆናቸው እና በወላይታ ሶዶ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ውስጥ በቁጥጥር ስር የሚገኙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ እንደገለጹት፥ “የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሰልፎችን በሚቆጣጠሩበት ወቅት የሞት አደጋን የሚያስከትል የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ሊቆጠቡ ይገባል፤ እንደነዚህ ያሉ እርምጃዎች ቀድሞውኑን የነበረ ውጥረትን ያባብሱ እንደሆን እንጂ መፍትሔ አይሆኑም” ብለዋል።
አቶ አሮን አያይዘውም በግጭቱ ወቅት የተከሰተው የ6 ሰልፈኞች አሟሟትን እና የጸጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀምን አስመልክቶ ፈጣን ምርመራ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። እንዲሁም የታሳሪዎችን መብቶች ማክበርና በአፋጣኝ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለስረ-ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ከመፈለግ አንጻርም የፌዴራልና የክልሉ መንግሥታት በክልሉ ውስጥ ለተነሱት የክልልነት ጥያቄዎች ወቅታዊና ሰላማዊ መፍትሔ በሥራ ላይ እንዲውል ከፍተኛ ጥረትና ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።
ወላይታ ዞን ውስጥ በተቀሰቀሰው ግጭት የተከሰተው ምንድን ነው?
ባለፈው እሁድ (ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ መልስ አልተሰጠንም በሚል በተነሳ የተቃውሞ ሰልፍ፥ በነጋታው (ነሐሴ 4 ቀን) በተቃዋሚዎችና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት ቢያንስ የአስር ሰዎች ሕይወት ማለፉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የጠቀሳቸው የቦዲቲ ከተማ የጤና ቢሮ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተመስገን ሕሊና ነሐሴ 4 ቀን በቦዲቲ ከተማ ቢያንስ ስድስት ሰዎች የጸጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ መገደላቸውን ተናግረዋል። ለሌሎችም (ለተጎዱ ሰዎች) የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ መስጠታቸውን የተናገሩት አቶ ተመስገን፥ የጥቃቱ ሰለባዎች ጭንቅላታቸው፣ ሆዳቸውንና ደረታቸው ላይ መመታታቸውን ገልጸዋል። ከሞቱት መካከል የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት እንደሚገኝበትና የቆሰሉትም በቁጥር እንደሆኑ አክለው ተናግረዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የጤና መኮንን ደግሞ፥ በሶዶ ከተማ አራት ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ተተኩሶባቸው የተገደሉ ሰዎች ማየታቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ታደሰ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ 21 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ105 በላይ መቁሰላቸውን እንዳረጋገጡ ለዶይቼ ቬለ የአማረኛ ዝግጅት ክፍል ገልጸዋል።
-
AuthorSearch Results