Search Results for 'የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ'

Home Forums Search Search Results for 'የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ'

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 40 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    በሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ዜጎች በንቃት እንዲሳተፉ በቂ አትኩሮት ይሰጠው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተላለፈ ወቅታዊ መልዕክት

    በሀገራችን ኢትዮጵያ በየዘመኑ የነበሩትን፣ ከፖለቲካው ሥርዓት የሚመነጩ ችግሮችን ለመፍታት እና ወደተሻለ ሀገራዊ ሁኔታ ለመሸጋገር የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማንበር እቅስቃሴ ማድረግ ከተጀመረ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።

    እነዚህ እንቅስቃሴዎች የሥርዓት ለውጥ ከማምጣት ተሻግረው የዴሞክራሲን ፍሬ ከማፍራት ይልቅ ሀገራዊ ችግሮቻችንን በአይነትና በብዛት እየጨመሩ እና እየተወሰሳሰቡ እንዲመጡ በማድረግ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያችን ህልውና እና ቀጣይነት ላይ ከፍተኛ አደጋ ለመደቀን በቅተዋል።

    ምንም እንኳ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም፤ የኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተደቀነው አደጋ በዋነኛነት የሚመነጨው፣ ከሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓቱ ነው። ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓቱ በተለያዩ ፍላጎቶች፣ ጥቅሞች፣ ስሜቶች፣ ተስፋዎች እና ስጋቶች በመወጠሩ፤ እርስ በእርስ አለመተማመን፣ ሰላም ማጣት፣ መፈናቀል፣ አለመረጋጋት . . . ወዘተ ተፈጥሮ መዋቅራዊ ቅራኔ ውስጥ እየዳከርን መገኘታችን የአደባባይ ሀቅ ነው።

    ይህ አደገኛ ሀገራዊ ሁኔታ ሳይረፍድ እና ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣታቸው በፊት በጋራ አንድ መፍትሔ ካልተበጀለት፤ እርስ በእርሳቸው እየተሳሳቡ ጫፍ እና ጫፍ የቆሙትን የተለያዩ ፍላጎቶች፣ ጥቅሞች፤ ስሜቶች፤ ቡድኖች እና ድርጅቶች በሙሉ ጠራርጎ፣ ማንኛችንም አሸናፊ ወደማንሆንበት ምድራዊ ሲኦል ውስጥ የመግባት እድል እንዳለን መገንዘብ ይኖርብናል።

    ይህንን ሁላችንም ላይ የተደቀነ ሀገራዊ አደጋ ለማስወገድ፣ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በተለይ በፖለቲካው ሂደት ውስጥ ከተሞከሩት እንዲሁም ሀገራዊ ሁኔታውን ከማባባስ እና ከማወሳሰብ ይልቅ ምንም አይነት መፍትሔ መስጠት ካልቻሉት የፖለቲካ አካሄዶች ውጭ ባለ ሂደት፣ መፍትሔ የማፈላለጉ ጥረት አማራጭ የሌለው አካሄድ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል።

    ሀገራዊ ምክክር ያስፈለገውም የሀገራችን አንኳር ችግሮች በመደበኛው የችግር አፈታት ሂደት መፍትሔ ማግኘት በማይቻልበት ደረጃ በመድረሳቸው እና በመቀጠልም፣ የበለጠ እየገዘፉና እየተወሳሰቡ ሄደው ሀገርን የማፍረስ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ሀገርን ለማዳን እንዲያስችል ነው።

    በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት ኮሚሽን ተቋቁሞ የተጀመረውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት በተመለከተ አሁን በደረስንበት ደረጃ ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት በሀገራችን ህልውና እና ቀጣይነቷ ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለአንዴም ለሁሌም እንዲወገድ ማድረግ ነው። ለዚህ ሊረዳን የሚችል ስምምነት ላይ ለመድረስ ደግሞ በምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላትን በሂደቱ ላይ በቀናነት እንዲሳተፉ የማሳመን ሥራ በስፋት ሊከናወን ይገባል።

    የሀገራዊ ምክክሩ ቁልፍና ወሳኝ ባለድርሻዎች ምክክሩን ለመቀበል እና እንዲነቃቁ ለማድረግ፣ በመጀመሪያ መደረግ ያለበት፣ በሀገራዊ ምክክር ምንነትና እና በሀገራችን ሁኔታ ያለውን አስፈላጊነት አስመልክቶ ግልጽ የሆነ አረዳድ እንዲኖር ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የተለያዩ ባለድርሻዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ማሳየት ነው።

    ሀገራዊ ምክክር በመደበኛ አሰራሮች ሊፈቱ የማይችሉ መዋቅራዊና ጊዜያዊ ቅራኔዎችን በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ ለመፍታት የሚያስችል በመሆኑ፤ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው። ሀገራዊ ምክክር በአግባቡ ከተጠቀምንበት ልዩነቶችን በማስታረቅ ሀገራዊ የፖለቲካ ቀውስን ለማስቀረት፤ ፖለቲካዊ አጣብቂኞችን ሰብሮ ለመውጣት እና ውጥረትን ለማርገብ፤ በትጥቅ የታገዘ አመፅ እንዳይፈጠር አስቀድሞ ለመከላከል ያስችላል። በተጨማሪም፤ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ከዚህ ቀደም ለተፈፀሙ በደሎች እና ወንጀሎች እንዲሁም የፍትህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ይረዳል። በውጤቱም ከተፈጠሩ ፖለቲካዊ ቀውሶች ፈጥኖ በማስወጣት በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል መተማመንን ይፈጥራል። በፖለቲካዊ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ ለሚያነሱ አካላትም በሀገራዊ ምክክር ላይ በመሳተፋቸው በሀገር ጉዳይ ላይ የባለቤትነት ስሜትን በማጎልበት ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት የመፍታት ባህል በማዳበር እንዲሁም ሀገራዊ ቀጣይነት እና መረጋጋትን በማረጋገጥ፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መደላድሎችን ይፈጥራል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከዚህ ቀደም በተለያየ መልኩ ሲገልፅ እንደቆየው፤ ሀገራዊ ምክክሩ በዚህ ወቅት ለአጠቃላይ ማህበረሰባዊ ደህንነታችን የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ስለሆነ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ሀገራዊ አጀንዳ ነው። ነገር ግን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለዚህ ሀገራዊ ክንውን እየሰጡት ያለው ትኩረት በጣም አነስተኛ መሆኑ ፓርቲያችንን በእጅጉ አሳስቦታል።

    ከሁሉም በላይ መንግሥት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ብዙ እርቀት ተጉዞ አስተዋፅዖ ማድረግ ሲጠበቅበት፤ በምክክሩ ላይ ሊፈቱ የሚገባቸውን ጉዳዮች አስቀድሞ በመወሰን እንዲሁም ግጭቶች እንዲቀንሱ በትጋት ከመስራት ይልቅ በመንግሥታዊ መዋቅሮች ያልተገባ ውሳኔ ምክንያት ተጨማሪ ግጭቶች እየተፈጠሩ መሄዳቸው እንድንሰጋ አድርጎናል። በኢዜማ እምነት መንግሥት አስተባባሪ እንጂ አፍራሽ፤ ጠቃሚ እንጂ ጎጂ፤ ጠንካራ እንጂ ልፍስፍስ፤ ሕግ አስከባሪ እንጂ ሕግ የሚጥስ ሆኖ መገኘት የለበትም። በመንግሥት በኩል የሚከናወኑ አፍራሽ አካሄዶች አደጋቸው ለሁላችንም ነውና ሊወገዱ ይገባል።

    መንግሥት የሀገራዊ ምክክሩን ሂደት የሚያበላሹ ተግባራትን ማከናወኑ እንዲሁም የምክክሩን ሂደት ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሚና በአግባቡ እስካሁን አለመወጣቱ ትክክል እንዳልሆነ መረዳት ይጠበቅበታል። ለአብነትም፤ ኢዜማ ከዚህ ቀደም ባወጣቸው መግለጫዎች ላይ እንደገለፀው መንግሥት መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸውን ሀገራዊ የፖሊሲ ጉዳዮች፤ የሕገ-መንግሥት አንቀፆች፤ አዋጆች እና ሌሎች ውሳኔዎችን ከሀገራዊ ምክክሩ አስቀድሞ መወሰኑ የምክክር ኮሚሽኑን በማቋቋም ያሳየውን በጎ ተስፋ የሚያጨልም ነው።

    ከመንግሥት በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ልሂቃን፤ የሙያ ማኅበራት፤ የሲቪክ ማኅበራት፤ መገናኛ ብዙሃን፤ የሃይማኖት ተቋማት እና ሰፊው ሕዝብ እስካሁን ባለው ሂደት ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ አልተወጡም። ሀገራዊ ምክክር ለተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ተቋማት ብቻ የሚተው ሳይሆን የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የነገ ህልውና፤ ደህንነት፤ ሰላም፤ ልማት እና ተጠቃሚነት የሚወስን ጉዳይ መሆኑን አለመገንዘብ ሁላችንንም ለውድቀት የሚዳርግ መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል። በሀገር ዕጣፈንታ ላይ የሚወሰንበትን ክንውን ትኩረት አለመስጠት ማኅበራዊ ኪሳራ እንደሆነ እያንዳንዱ ዜጋ ማወቅ አለበት።

    ፓርቲያችን ኢዜማ ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ትኩረት እንድትሰጡት እያሳሰበ የሚከተሉት ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል ብሎ ያምናል።

    1. መንግሥት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሊሠራ የሚችላቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች በተደጋጋሚ ተላልፎ ምክክሩ ላይ ጫና መፍጠሩን በአስቸካይ እንዲያቆም፤ እንዲሁም ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅበትን መንግሥታዊ ሐላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ፤
    2. ምክክር ኮሚሽኑ ለዜጎች መድረስ ያለባቸው መረጃዎች በአግባቡ መድረሳቸውን እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጣቸው ማድረግ ላይ በአትኩሮት እንዲሰራ ብሎም ክንውኖቹን፤ እቅዶቹን እና የሀገራዊ ምክክሩን አስፈላጊነት በተመለከተ በመገናኛ ብዙሃን እየቀረበ በአግባቡ መልዕክቶችን ለማኅበረሰቡ ወቅቱን ጠብቆ እንዲያደርስ ራሱን የቻለ የአየር ሰዓት እንዲመደብለት
    3. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም እና ምርጫ ቦርድ እንዲሁም ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት እየሠሩት ያለውን ጅምር በጎ ሥራ ምሳሌ በማድረግ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በተሰጠው ስልጣን ልክ ተግባሩንና ታማኝነቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ እንዲያደርግ፤ በኮሚሽኑ ውስጥ የሚያገለግሉ ግለሰቦችም ታማኝነታቸውን ለህሊናቸው እንዲያደርጉ
    4. የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ልሂቃን፤ የሙያ ማኅበራት፤ የሲቪክ ማኅበራት፤ መገናኛ ብዙሃን፤ የሃይማኖት ተቋማት እና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሚና በአዎንታዊነት እንዲወጡ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ።

    በአጠቃላይ፤ ሀገራዊ ምክክር እንደስሙ ሀገራዊ መሆን አለበት። ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ያለምንም ተጽዕኖ እንዲሳተፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል። እንደ ሀገር ያሉንን ልዩነቶች ለማስታረቅ ሁላችንም ከልባችን በእውነተኛነት መስራት አለብን። በጋራ ለአደጋ እንደተጋለጥነው ሁሉ፤ አደጋውንም በጋራ ለመጋፈጥና በጋራ ለመወጣት መትጋት ይጠበቅብናል። በኢዜማ በኩል የሀገራዊ ምክክር አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም አባላትን እንዲሁም ማኅበረሰቡን ለማንቃት የሚችለውን ሁሉ እያከናወነ ሲሆን፤ በቀጣይም ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ማረጋገጥ ይወዳል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ጥር 02 ቀን፥ 2015 ዓ.ም.

    Semonegna
    Keymaster

    “በኢዜማ እምነት አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ባለበት እስከቀጠለ ድረስ እንኳን ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መገንባት ይቅርና እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችንም ቢሆን አደጋ ላይ የወደቀ ነው!!”
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሀገራችን ላይ እውን እንዲሆኑ ከሚታገልላቸው የፖለቲካ መሠረቶች አንዱ እና ዋነኛው የዜጎች እውነተኛ የስልጣን ባለቤትነትንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነው!!

    ፌደራሊዝም “የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ሕዝብ ነው” የሚለውን ትልቅ የዴሞክራሲ መርህ ሰፋ ያለ ትርጉም በመስጠት፥ “ሕዝብ በሚኖርበት አከባቢ ራሱን በራሱ ማስተዳደር አለበት” የሚለውን መርህ ተግባራዊ የሚያደርግ የአስተዳደር መዋቅር ነው።

    ፓርቲያችን ኢዜማ ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ የቆዳ ስፋት፣ ከአንድ ቦታ ሁሉን ማስተዳደር የማይመች መልከአ ምድር፣ በተለያየ ደረጃ ያለ ኢኮኖሚ በየአካባቢው ባለበት፣ ብዝኀ ማንነት ማለትም ብዙ ዘውግ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት አንፃር ያልተማከለ ሥርዓት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል። ካልተማከሉ የፖለቲካ ሥርዓቶች ውስጥ ደግሞ የመጀመርያው ምርጫ ፌደራሊዝም ነው።

    እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ፌደራሊዝም ተመራጭ የሚሆነው በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ነው። አንደኛው ሕዝብ በአካባቢው ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲችል ሙሉ መብትና ስልጣን የሚሰጥ የመንግሥት ሥርዓት ስለሆነ ሲሆን፤ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ፌደራሊዝም ከአሐዳዊ መንግሥት በተሻለ ብዝኀነትን ማስተናገድ መቻሉ ነው።

    ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት የተከተለችው የፌደራሊዝም ሥርዓት፤ ፌደራል ሥርዓቱን የፈጠረው ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ ከመዋሉ አስቀድሞ በነበሩ ሂደቶች ብዙኃኑን ያላሣተፈ መሆኑ ዴሞክራሲያዊነቱን አሳጥቶታል። ከዚያ በተጨማሪ የፌደራሊዝም ዋና ጥቅም ለሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በመስጠትና በዘውግና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ ተመስርተው የሚነሱ ግጭቶችን ማስወገድ ሆኖ እያለ፤ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ግን ራሱ የተመሠረተው በዘርና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ ስለሆነ ማስወገድ የሚገባውን ችግር ጭራሹኑ አባብሶታል። በተለይ የፌደራል ሥርዓቱ ማንነትንና የመሬት ባለቤትነት በሕገ መንግሥት ደረጃ እንዲያያዝ በማደረጉ ከዚህ ቀደም በመካከላቸው የሚለያያቸው ወሰን ባልነበረ ኩታ ገጠም በሆኑ ወረዳዎች በሚኖሩ የዘውግ ማኅበረሰቦች መካከል ደም ያፋሰሱ በርካታ ግጭቶች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኗል። አሁንም መሆኑን ቀጥሏል።

    በኢዜማ እምነት አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ባለበት እስከቀጠለ ድረስ እንኳን ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መገንባት ይቅርና እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችንም ቢሆን አደጋ ላይ የወደቀ ነው ብሎ ያምናል።

    ይህንን አደጋ ለማስወገድ የፌደራል ሥርዓቱ እንዴት መመሥረት አለበት? ክልሎች እንዴት መዋቀር አለባቸው? በክልሎችና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? የሚሉና ከፌደራል መንግሥትና ከክልል መንግሥታት ማን የበለጠ ስልጣን ይኑረው? ለሚሉት ጥያቄዎች እና ሌሎች ሀገሪቱን አደጋ ላይ ጥለዋታል የሚባሉ የሕገ መንግሥቱ ክፍሎችን አንድ በአንድ ነቅሶ በማውጣት ከፊታችን ሀገራችን ታደርገዋለች ተብሎ በሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ ማቅረብ የግዴታ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።

    ኢዜማ ለዚህ ምክክር ጠንካራ አማራጭ ሀሣቦችን ይዞ ለመቅረብ ሀገራዊ ምክክሩ ላይ ብቻ ትኩረትን ሰጥቶ የሚሠራ ኮሚቴ በማዋቀር እየሠራ ሲሆን ዝግጅቱንም አጠናቆ የመድረኩን መጀመር እየተጠባበቀ ይገኛል።

    ባለፉት ጥቂት ዓመታት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የ “ክልል ወይንም ዞን እንሁን” የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት እየተደመጡ ነው። ይህንንም ተከትሎ ሁለት ሕዝበ-ውሳኔዎች ተደርገው ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ ከነበሩት ዘጠኝ ክልሎች ሁለት ተጨምረው የክልሎች ቁጥር ወደ 11 ከፍ ብሏል።

    አንዳንዶቹ የክልልነት ጥያቄዎች የሚቀርቡት ሕዝብ በወከላቸው እንደራሴዎች ሳይሆን ስልጣን ላይ ባሉ አካላት የግል የፖለቲካ እና ሌሎች ጥቅሞችን የማግበስበስ ፍላጎት መነሻነት መሆኑን ፓርቲያችን በተደጋጋሚ ገልጾ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ጥሪ አስተላልፏል። አሁንም በዚህ ተግባር የተጠመዱ ስልጣን ላይ ያሉ አካላት ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።

    ማኅበረሰቡም ለእነዚህ ጥቅመኛ ግለሰቦች የግል ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣርያ ከመሆን ይልቅ ከታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ጀምሮ ያጋጠሙትን አስተዳደራዊ በደሎች ለመፍታት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይደረጋል ተብሎ በሚታመነው የአካባቢ፣ የቀበሌ እና የወረዳ ምርጫ በንቃት በመሣተፍ በአግባቡ ሊያስተዳድሩት የሚችሉ ግለሰቦችን እንዲመርጥ ጥሪ እያስተላለፍን፤ የሀገራዊ ምክክሩንም ሂደት በተመሣሣይ እንዲሁ በአንክሮ እንዲከታተል እንጠይቃለን።

    ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት የፌደራል ሥርዓቱ ያሉበት እንከኖች ሳያንስ ያለ ሕዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ እንዲሁም አማራጭ ሐሣቦችን ሣይመለከት “የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስትን በክላስተር ለማዋቀር” ብቸኛው አማራጭ አድርጎ ይዞ መምጣቱ ፈጽሞ ትክክል አለመሆኑን እና ሀገራዊ ምክክሩ ላይ አጀንዳ ሆኖ ይቀርባል ተብለው ከሚታመንባቸው አንዱ የሆነውን የፌደራል አወቃቀር ከወዲሁ በመነካካት ሀገራዊ ምክክሩ ላይ እምነት እንድናጣ ከማድረግ ሊቆጠብ ይገባል።

    ኢዜማ ፌደራሊዝም ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሕዝቡ ራሱን ለማስተዳደር መፈለጉ በራሱ ችግር አለመሆኑን ይገነዘባል፡፡

    የዞን እና ክልል የመሆን ጥያቄ ያላቸው ማኅበረሰቦች ምንም እንኳ አሁን ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47(2) መሠረት ጥያቄዎችን የማንሳት ሕገ መንግሥታዊ መብት ቢኖራቸውም፤ ክልል የመሆን ጥያቄዎች ከዘውግ ይልቅ ዜግነትን መሠረት ያደረገ እና ሁሉንም ማህበረሰብ ባቀፈ መልኩ መቅረብ እንዳለባቸው ኢዜማ ማስገንዘብ ይወዳል፡፡ ይህም ለጋራ የወደፊት ዘላቂ ሰላም እና ልማታችን  ቁልፍ መሆኑን ያምናል፡፡

    ኢዜማ በአራቱም አቅጣጫ ላለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላቂ ሰላም እና ልማት የሚጠቅመው በጥናት ላይ የተመሰረተ እንዲሁም የህዝብን ከታች እስከ ላይ ባሉ መዋቅሮች ራስን በቀጥታ የማስተዳደር መብት የሚያጎናጽፈው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም መሆኑን ያምናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ከፍተኛ በጀት ፈሰስ ተደርጎበት በአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የተጠናው የአስተዳደር ክልሎች እንዴት ይዋቀሩ የሚለው የጥናት ውጤት ለሀገራዊ ምክክሩ እንደ ግብአት ሆኖ እንዲቀርብ እንጠይቃለን።

    የዞን እና ክልል የመሆን ጥያቄ ያላቸው አካላት ቀጣይ ሀገራችን ታካሂደዋለች ተብሎ የሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ ተነስተው መፍትሄ ያገኛሉ ተብለው የሚጠበቁ ጉዳዮች ላይ ከወዲሁ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ማድረግ ምክክሩ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ መሆኑን ተረድተው ከጊዚያዊ አካባቢያዊ ጥቅም ይልቅ የትልቋን ኢትዮጵያ ምስል በማየት ለነገ የጋራ ጥቅማችን አስቦ አጀንዳውን በማሳደር፤ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ በሰከነ እና የሀገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ በተረዳ መልኩ ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ ሀሳቦችን ከመመዘን እስከ ሕዝባዊ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።

    ሀምሌ 28 ቀን፥ 2014 ዓ.ም
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ

    ኢዜማ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠየቀ

    Anonymous
    Inactive

    በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ የተደቀነውን አደጋ የመመከት ኃላፊነት በዋነኛነት የፌደራል መንግሥቱ ነው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    መንግሥት በትግራይ ያለው ግጭት ቆሞ ለሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር እና ሌሎች ምክንያቶችን ጠቅሶ የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባወጣው የ‘ቢሆንስ’ ትንተና ሊሆን ይችላል ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (scenario) መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የትግራይ አማጺዎች ግጭቱን ለማስፋት የሚያደርጉት ሙከራ ቀጥሎ ግልፅ አሸናፊ የማይኖርበት ሁኔታ ይከሰታል የሚል ነበር። ይህም ከቀጠለ በክልሉ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር አዳጋች መሆኑ የሚፈጥረውን አጋጣሚ በመጠቀም ዘረፋዎች ሊበራከቱ እንደሚችሉ፣ የዕለት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ሳያገኙ ቀርተው ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ፣ መሰረታዊ ለኑሮ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች እና ግብዓቶች (የውሃ፣ የመብራት፣ ህክምና) ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር የሚጋለጥበት ሁኔታ ሊበራክት እና ለረጅም ጊዜ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ አገልግሎት ሊያገኝ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እና የዚህ ዓይነት የማያቋርጥ ግጭት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ብዙ ችግሮችን ስቦ በማምጣት (ኢንቬስትመንት ይቀንሳል፤ ቱሪዝም ይቀንሳል፤ በዚህም የሥራ አጥ ቁጥር ይጨምራል) በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም አለመረጋጋትን ሊያስከትል ይችላል የሚል ትንተና አስቀምጠን ነበር። በትንተናችን ውስጥ ይህ ቢሆንስ (scenario) የመሆን ዕድሉ ከሌሎቹ የበለጠ መሆኑን ጠቅሰን በክልሉና ባጠቃላይ በሀገራችን ከብሔር ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የመጣውን አደጋ በዘላቂነት የማይፈታ፣ ሀገሪቱን ቀስ እያለ ውስጧን እንደሚበላ በሽታ ከመግደሉ በፊት መፍትሄ የሚፈልግ እንደሆነ ገልፀን ነበር። በተጨማሪም በዚህ ሁኔታ ውስጥ መረጋጋትን ማስፈን ስለማይቻል የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ከፍተኛ ግጭት ማምራቱ እንደማይቀር በትንታኔያችን ውስጥ አስቀምጠን ነበር።

    የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በይዞታው ስር የነበሩ ቦታዎችን ለቆ ከወጣ በኋላ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያስተዋልነው እንቅስቃሴ በቢሆንስ (scenario) ትንተናችን ውስጥ ከሁሉም የተሻለ የመከሰት ዕድል አለው ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (scenario) እውን እየሆነ እንደሆነ የሚያመላክት ነው።

    በእርግጥ ከላይ በጠቀስነው ትንተናችን ውስጥ ህወሓት የሚያደርሳቸውን ትንኮሳዎች በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እየተመከቱ እና እየከሸፉ ሊሄዱ ይችላሉ የሚል ግምታችንን ብናስቀምጥም በተግባር ያየነው ግን የፌደራል መንግሥት ህወሓት ግጭቱን ለመቀጠል የወሰዳቸውን እርምጃዎች በግንባር ቀደምነት አመራር እየሰጠ ለማክሸፍ ከመሞከር ይልቅ ግጭቱን በክልሎች መካከል ያለ ግጭት እስኪመስል የወሰደው ግልፅ ያልሆነ አቋም እጅግ አስደንጋጭ ሆኖ አግኝተነዋል።

    ከዚህም በላይ ግጭቱን በተመለከተ በፌደራል መንግሥቱ በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች የተጣደፉ እና በቅጡ ያልታሰበባቸው መምሰላቸው በአጭር ጊዜ ከህወሓት የተደቀነውን አደጋ በማንኛውም መንገድ ከማክሸፍ ባለፈ እርምጃዎቹ ለሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት የሚኖራቸውን አንድምታን ያልገመገሙ ስለመሆናቸው አመላካች ሆነው አግኝተናቸዋል።

    መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎችን በተመለከተ ጊዜውን የጠበቀ እና ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ ባለማድረሱ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥ ከመፍጠሩም ባለፈ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ህወሓት ያደረሳቸውን ወንጀሎች እና የሚፈጽማቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ከተራ ክስ ባለፈ በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ ለዜጎች እና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንዲደርስ ማድረግ ላይ ከፍተኛ ክፍተት እየተስተዋለ ይገኛል። እነዚህ ክፍተቶች በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀላቸው ችግሩን የበለጠ እያባባሱት እንደሚሄዱ እናምናለን።

    መንግሥት በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ተመስርቶ ለህወሓት የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማስቆም እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ያለበትን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የምንደግፍ ቢሆንም በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ህወሓትን ትደግፋላችሁ በሚል ምክንያት የሚወሰዱ እርምጃዎች ማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ከመሆን ይልቅ እንዲሁ በጅምላ የሚወሰዱ መሆናቸው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጋፉ እና በትግራይ ያለውን ችግር የበለጠ የሚያወሳስቡ ድርጊቶች ናቸው። ለአብነት በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቻ በተመሳሳይ ወቅት ቢያንስ 60 የንግድ ተቋማት/ሱቆች ከግጭቱ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ታሽገው ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተዘግተው ቆይተዋል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር እና ጥቃት በአፋጣኝ መቆም እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መጠየቁ ይታወሳል።

    ከላይ የተጠቀሱትን መሰረት በማድረግ የሚከተሉት ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲደረጉ እንጠይቃለን፥

    1. በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የፀጥታ አስከባሪዎች ህወሓት የደቀነው አደጋን ለማክሸፍ እያደረጉ ያሉትን መረባረብ በከፍተኛ አክብሮት እናደንቃለን። ህወሓት የፌደራል መንግሥቱን በበላይነት ይቆጣጠር በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ላይ በሙሉ ግፍ ሲፈጽም እንደነበረ ሁሉ አሁንም የደቀነው አደጋ በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ እንጂ በአንድ ወይንም በጥቂት ክልሎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልሆነ በመረዳት አደጋውን ለመከላከል የሚወሰደው እርምጃ አንድ ወጥ የዕዝ ሰንሰለት ኖሮት በፌደራል መንግሥት እና በኢፌደሪ መከላከያ ሠራዊት አመራር ሰጪነት ብቻ እንዲወሰድ፤
    2. በትግራይ ክልል ያለውን ችግር አሁን ከፊታችን ህወሓት ከደቀነው አደጋ እንፃር ብቻ በማየት ህወሓትን ማሸነፍን ብቻ ዓላማ ያደረገ የአጭር ጊዜ ስልት ይዞ ከመንቀሳቀስ ባለፈ በዘላቂነት ክልሉ ወደተረጋጋ ሰላም እና ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ሊመለሱ የሚችሉበት እንዲሁም ግጭቱ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተቋጭቶ የሀገር ህልውና እና አንድነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻልበት ስልት የአካባቢውን ተወላጆች በማሳተፍ እንዲነደፍ እና ተግባራዊ እንዲደረግ፤
    3. አሁን ያለው ግጭት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የምትገኙ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ልሂቃን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የምታስፈልጉበት ወቅት ላይ መሆናችሁን ተረድታችሁ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ፤
    4. የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚደረገው ጥረት አሁን ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ በክልሉ ለሚኖሩ ዜጎች እንዲዳረስ የሚያደርገውን ጥረት በግልፅ እንዲያሳውቅ፤ እንዲሁም በዚህ ተግባር የሚሳተፉ የሰብዓዊ ድርጅቶች በግልፅነት እንዲንቀሳቀሱ ተገቢው ክትትል እንዲደረግ፤
    5. የተለመዱ መንግሥትን የሚያሞግሱ የፕሮፖጋንዳ ሥራዎችን እየደጋገሙ ሕዝብን ከማሰልቸት ይልቅ መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ እንዲደረግ እና ህወሓት የሚፈፅማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እና ታዳጊዎችን በወታደርነት መመልመል እና በጦርነት ማሳተፍን የመሳሰሉ ወንጀሎችን በተገቢው ፍጥነት በተጨባጭ ማስረጃዎች እያስደገፉ ይፋ የማድረግ ሥራ ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ፤
    6. ዜጎች ለህወሓት የሚደረግ ማንኛውም የሞራልም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ በሕዝብ ሠላም፣ በሀገር ደህንነት እና ሕይወቱን ለመሰዋዕትነት አዘጋጅቶ በተሰለፈው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ላይ የሚደረግ ክህደት መሆኑን በመረዳት ከተመሳሳይ ድርጊቶች እንዲታቀቡ፤
    7. ህወሓትን ደግፋቹኻል በሚል በጅምላ የሚወሰዱ እርምጃዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙ እና እስካሁንም በዚህ መልኩ የተወሰዱ እርምጃዎች አፋጣኝ ማጣራት ተደርጎ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም አሁን ያለውን ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የግል ጥቅም ለማግኘት ዜጎች ላይ እንግልት የሚፈፅሙ የመንግሥት እና የፀጥታ ሠራተኞች ላይ አስፈላጊው ማጣራት በአስቸኳይ ተደርጎ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤

    በመጨረሻም የሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት ተረጋግጦ የሁሉም ዜጎች መብት እኩል የሚከበርበት እና እኩል ዕድል የሚሰጥበት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ የምናዋጣበት አሳሳቢ ወቅት ላይ እንዳለን እያስታወስን ሁላችንም ኃላፊነታችንን ከምር ወስደን እንድንወጣ እናሳስባለን።

    ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ

    የፌደራል መንግሥቱ

    Anonymous
    Inactive

     ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ውጤት

    ሰኔ 14 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የተካሄደው የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጤት ይፋ ተደረገ። ይህ ውጤት የሚገለፀው ባገኙት ወንበር ልክ ሲሆን በዚህም መሠረት፦

    • የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር
      – መስተዳድሩ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 23
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 23
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 22
      □ የግል ተወዳዳሪ ያገኘው መቀመጫ: 1
    • የአፋር ብሔራዊ ክልል
      – ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 8
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 6
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 6
    • የአማራ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 138
      – ሰኔ ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 125
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 114
      □ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 5
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 5
    • የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 9
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 3
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 3
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 2
    • የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር
      – መስተዳድሩ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 2
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 2
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 1
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
    • የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 3
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 3
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 3
    • የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 178
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 170
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 167
      □ የግል ተወዳዳሪዎች ያገኙት መቀመጫ: 3
    • የሲዳማ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 19
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 19
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 19
    • የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 104
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 85
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 75
      □ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 4
      □ የጌዴኦ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት: 2
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 3

    በዚህ ሐምሌ 3 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመቀመጫ ብዛት በአጠቃላይ 484 ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ በስልጣን ላይ የሚገኘው ብልፅግና ፓርቲ 410 መቀመጫ አሸንፏል። ይህም ውጤት ፓርቲውን መንግሥት ለመመሥረት ያስችለዋል።

    ይህን የምርጫ ውጤት እና የፓርቲያቸው ማሸነፍን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስተላለፉትን መልዕክት ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ

    የምርጫ ክርክር የምርጫ ውጤት

    Anonymous
    Inactive

    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
    (ድኅረ ምርጫ 2013)

    ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም

    የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን መሠረት ለመጣል የሚጠይቀው መስዋዕትነት እጅግ ረጅምና መራር ነው። በተለይም እንደ አፍሪካ ውስጥ ባሉ በበርካታ ውስብስብ አሠራሮች በተተበተቡ አገሮች ውስጥ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ጥበት፣ ከፍተኛ የሥልጣን ጉጉትና የመሳሰሉት እንቅፋቶች የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ቀይደው ይይዙታል። ድህነቱ፣ ኋላቀርነቱ፤ የዜጎች የፖለቲካ አረዳድ ወዘተ ችግሮቹን ይበልጥ ያባብሱታል።

    በተለይም በዘውግና በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የሀገራችን የፖለቲካ ትርክት ላለፉት 30 ዓመታት ከአንድነት ይልቅ ልዩነቶቻችንን አግዝፎ በትውልዱ ላይ ቁርሾን ዘርቷል። ዛሬም ከዚህ የማንነት የፖለቲካ አዙሪት ለመላቀቅ አልቻልንም። ከዚህ የችግር አረንቋ ውስጥ ለመውጣት የዜግነት ፖለቲካው ብርቱ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም ነገም ብቸኛው አማራጭ መሆኑ ሊታመን ይገባል።

    ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ በተለያዩ የመንግሥት ቅርጽና የፖለቲካ ፍልስፍና በየጊዜው ሥልጣን ላይ በወጡ ኃይሎች ስትመራ መቆየቷ ይታወቃል። ላለፉት 30 ዓመታት እስከ 6ኛው ዙር ምርጫ ድረስ በምርጫ ብቻ ሥልጣን ለመያዝ የተሞከረው ሒደት ተስፋ ሰጪ ባይሆንም ዜጎች የምርጫ ተሳትፎ ማድረጋቸው አንድ ጥሩ እርምጃ ነው ሊባል ይችላል።

    ሰኔ 14 ቀን 2013 የተደረገው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሂደቱ እና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ የተገለፀ ባይሆንም በብዙ ግልጽ ችግሮች የታጀበ ነበር። ለዚህ ምርጫ ሰላማዊነትና የአገሪቱን የነገን ቀጣይነት በምርጫ ለማረጋገጥ፣ ዜጎች በምርጫው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ኢዜማ የበኩሉን ድርሻ በኃላፊነት ተወጥቷል የሚል የፀና እምነት አለን። ከምንም በላይ ለሀገር መረጋጋትና ለሕዝብ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነትም በተግባር አስመስክሯል።

    በመሆኑም ለቀጣይ የኢዜማ መዋቅር አደረጃጀት ለፓርቲያችን ደጋፊዎች፣ አባላትና በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች የሚከተሉትን ማሳወቅ ይኖርብናል።

    1ኛ/ ሰኔ 14 ቀን 2013 የተደረገው የ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት እስከሚገለጽ የምንጠብቅ ሲሆን ቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ኢዜማ በተወዳደረባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች ያጋጠሙትንና በየሰዓቱ ለምርጫ ቦርድ ያሳወቅናቸው በርካታ ተግዳሮቶችን በአጽንኦት ተመልክቶ ውሳኔ የማይሰጥባቸው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍትህ አካላት ይዘን የምንሔሄድበትን ሁኔታ ቀድመን ለሕዝብ የምናሳውቅ ይሆናል።

    2ኛ/ ኢዜማ የምርጫ 2013 አጠቃላይ የፓርቲውን የምርጫ እንቅስቃሴ የሚያስተባብር የምርጫ ስትራቴጂክ ማኔጅመንት ኮሚቴ ከአመት በፊት አዋቅሮ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ይታወቃል። ይህ ኮሚቴ አጠቃላይ የምርጫውን ሂደት በተመለከተ ከሚያዘጋጀው የግምገማ አጠቃላይ ሪፖርት፣ በድርጅት በኩል፣ በብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተቋቋመ ቡድንና ከፓርቲው ውጪ በተመረጡ ገለልተኛ አካላት ከሚቀርበው ግምገማ ተነስተን አጠቃላይ ሁኔታውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንገልጻለን።

    3ኛ/ እንደሚታወቀው የፖለቲካ ፓርቲ ሰላማዊ ትግል ቀጣይነት ያለውና ከምርጫ በኋላም ቢሆን ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ እሙን ነው። በዚህ ረገድ ኢዜማ ጊዜያዊ ፓርቲ ሳይሆን ገና ከመነሻው ከምርጫ ወረዳ ጀምሮ ሲዋቀር ሩቅ ተጓዥና ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ሆኖ ነው። ከዚህ አንጻር በምርጫው ሒደት ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች በሕግ አግባብ እየጠየቅን ከዚህ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የድርጅቱን መዋቅር ይበልጥ በማጠናከር ወደ ሥራ የገባን መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።

    4ኛ/ ኢዜማ በተቋቋመ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከየትኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ በላቀ መልኩ በመላው አገሪቱ 455 የምርጫ ወረዳ መዋቅሮችን አደራጅቶ በጥንካሬ እየተንቀሳቀሰና በምርጫ 2013 ገዢውን ፓርቲ በብርቱ የሞገተ ፓርቲ ነው፤ ሕዝባዊ መሠረቱም ሰፊና ጠንካራ ነው።

    ከዚህ አንጻር የፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች በምርጫ ሂደት የተገኘውን ውጤት፣ ልምድ፣ የሰው ኃይል፣ ልዩ ልዩ ግብዓቶች እና ወዘተ የመሳሰሉትን ፓርቲውን ይበልጥ ለማጠናከር መጠቀምና ድርጅቱን በጥንካሬ ለመምራት በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ከዚህ ምርጫ ማግስት ጀምሮ ብርቱ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና በቀጣይ ለሚያጋጥሙን ሀገራዊ ጉዳዮችና ሰላማዊ ለሆኑ የትግል እንቅስቃሴዎች ራሳችንን እንድናዘጋጅ የከበረ ጥሪ ማስተላለፍ እንሻለን።

    ኢዜማ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለይም ከምርጫ መቃረብ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መፍትሄ ሰጪ ፖሊሲዎችን የነደፈ፣ ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ ለሕዝብ ያሳወቀ፣ የምርጫ ቅስቀሳዎችን በሰለጠነ መንገድ ያካሄደ፣ ማኅበራዊ ፍትህ ለማስፈን መሠረቱን ዜግነት ላይ ያደረገ ፓርቲ መሆኑንና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ላይ የራሱን ተሳትፎ እንዳደረገ እናምናለን።

    በመጨረሻም ነገም ኢትዮጵያ ሀገራችን ሉዓላዊ ግዛቷና የሕዝብን ደህንነት ተጠብቆ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሳት ጠንካራ ሀገር እንድትሆን ኢዜማ ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ሆኖ በጥንካሬ እንደሚቀጥል እየገለጽን በፀሐይና በዝናብ ወስጥ፤ ቀንና ለሊት ተሰልፋችሁና በብርቱ ጫናና መዋከብ ውስጥ ሆናችሁ ድምጻችሁን ለኢዜማ የሰጣችሁትን ከልብ እያመሰገንን ያልመረጣችሁንንም ውሳኔያችሁን የምናከብር መሆኑን እንገልጻለን።

    ምንጭ፦ ኢዜማ

    ኢዜማ

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠየቀ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በቅርቡ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን እና ተግባራት ላይ ማብራሪያ ይሰጠኝ ሲል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ጠየቀ።

    ኢዜማ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በላከው ደብዳቤ፣ በተለያዩ መንግሥታዊና የግል ሚዲያዎች ‹‹የፊንፊኔ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት›› በይፋ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ በማለት የተሰሩት ዘገባዎች፣ በሕገ-መንግሥቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የተሰጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን የሚጋፋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል።

    የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኩመላ ቡላን ጠቅሶ በሰራው ዘገባ «…በፊንፊኔ ከተማ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችም ሕገ-መንግሥታዊ መብታችውን በመጠቀም በዚህ ፍርድ ቤት በቋንቋቸው የመዳኘትና ተደራሽ የሆነ የፍትህ አገልግሎት የማግኘት መብትም ያገኛሉ ብለዋል።» በማለት መዘገቡን ያስታወሰው ኢዜማ፣ ይህንን ዘገባ ተከትሎ አዲስ የተከፈተው ፍርድ ቤት ሥልጣንና ተግባራት ላይ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠይቋል።

    የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 49 (2 እና 3) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው ተጠሪነቱም ለፌደራል መንግሥት አንደሆነ በግልጽ ደንግጓል ያለው ኢዜማ፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ ያስተዳድራል ሲባል ከተማው የራሱ ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ ይኖረዋል ማለት መሆኑን ጠቁሞ፤ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥት ነው ማለት ደግሞ በአዲስ አበባ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ የመወሰን ሥልጣን ያለው አካል የፌደራል መንግሥቱ ብቻ ነው ማለት ነው ሲል አመላክቷል።

    የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለሚገጥማቸው ማናቸውም ጉዳይ የትኛውም ብሔር ጀርባ ቢኖራቸውም የመዳኘት ሥልጣኑ የከተማ መስተዳደሩ ፍርድ ቤቶችና የፌደራል ፍርድ ቤቶች መሆኑን የጠቀሰው ኢዜማ፣ አንድ ክልል የዚህ ብሔር ተወላጆችን ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም የመዳኘት ሥልጣን ይኖረኛል ማለቱ በሕገ-መንግሥቱ ለፌደራል መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣን የሚጋፋ፤ በአዲስ አበባ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989 እንዲሁም እሱን ያሻሻለው አዋጅ ቁጥር 361/1995 የአዲስ አበባ አስተዳደር ራስ ገዝ ከመሆኑም ባሻገር በፌደራሉ መንግሥት የዳኝነት ፈቃደ ሥልጣን ሥር በማይወድቁ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች አና የቀበሌ ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ብቻ ሥልጣን እንደሚኖራቸው ተብሎ የተደነገገውን በግልጽ የሚቃረን ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል።

    አሁን ለተቋቋመው ፍርድ ቤት የሕግ መሰረት ተደርጎ የተጠቀሰው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አደረጃጀት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 216/2011 በአንቀጽ 24 ላይ ከተዘረዘሩት የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸው ሥልጣን እና ተግባራት ላይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ጉዳይ የማየት ሥልጣን እንዳላቸው ባልጠቀሰበት ሁኔታ፣ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ጉዳይ የማየት የዳኝነት ፈቃደ ሥልጣን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አላቸው ተብሎ መገለጹ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ እና ምንም ዓይነት የሕግ መሰረት የሌለው ነው ያለው ኢዜማ፣ በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የብሔር ማንነታቸው ላይ በመመስረት የተለያየ የዳኝነት መብት ይኖራቸዋል ብሎ ፍርድ ቤት መክፈት የዜጎቸን በሕግ ፊት በእኩልነት የመታየት ሰብአዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብትን የሚጥስ ከመሆኑም ባለፈ የዜጎችን ተከባብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽር ነው የሚል እምነት እንዳለው ኢዜማ በደብዳቤው ገልጿል።

    በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የብሔር ማንነታቸው ላይ በመመስረት የተለያየ የዳኝነት መብት ይኖራቸዋል ብሎ ፍርድ ቤት መክፈት የዜጎችን በሕግ ፊት በእኩልነት የመታየት ሰብዓዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብትን የሚጥስ ተግባር መሆኑን የጠቀሰው ኢዜማ፣ ይህ ዓይነቱ ድርጊት የዜጎችን ተከባብሮ የመኖር ዕሴት ይሸረሽራል ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።

    የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት በአፋጣኝ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያውን እንዲሰጠው የጠየቀው ኢዜማ፣ ‹‹ጠቅላይ አቃቤ፣ ይህንን ከሕገ-መንግሥት ማዕቀፍ ውጪ የሆነ ኢ-ሕገ-መንግስታዊ ተግባር እንዲያስቆም ሲል ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ በላከው ደብዳቤ ጥያቄውን አቅርቧል።

    ምንጭ፦ ኢዜማ

    ኢዜማ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠየቀ

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ለምርጫ አስፈፃሚነት ከተመለመሉት ሰዎች መሀከል ጥያቄ ያነሳባቸውን ለምርጫ ቦርድ አመለከተ

    ‘የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ አስፈፃሚነት የመለመላቸው የምርጫ አስፈፃሚዎች ገለልተኛ ናቸው ወይስ አይደሉም?’ የሚለውን ለማጣራት ለሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች የአስፈፃሚዎቹን ስም ዝርዝር በመላክ ማጣራት እያካሄደ ነው። ቦርዱ አስፈጻሚዎችን ከመለመለ በኋላ የተመለመሉትን አስፈጻሚዎች ስም ዝርዝር ለፖለቲካ ፓርቲዎች በመላክ ፓርቲዎች ገለልተኝነታቸው ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ እንደሚያደርግ መናገሩ የሚታወስ ነው። በዚህም መሠረት በመጀመሪያው ዙር ወደ 750 ምርጫ አስፈጻሚዎች ስም ዝርዝር የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ደርሶታል።

    የተላኩላቸውን ምርጫ አስፈጻሚዎች የፓርቲውን መዋቅር በመጠቀም ገለልተኝነታቸውን ለማጣራት ሙከራ እንዳደረጉ ለዜጎች መድረክ የገለፁት የኢዜማ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፥ ዜጎች መድረክ ከዚህ ቀደም የምርጫ አስፈፃሚዎቹን ስም ዝርዝር ይዞ ለማጣራት አቅም አላችሁ ወይ ብላ ጥያቄ አንስታላቸው እንደነበር አስታውሰው፤ የፓርቲውን መዋቅር በመጠቀም ምርጫ ቦርድ የመለመላቸውን ምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኝነት ማጣራት መቻላቸውን ተናግረዋል። በማጣራት ሂደቱም አንዳንዶቹ የምርጫ አስፈፃሚዎች ከዚህ ቀደም የኢሕአዴግ አባል የነበሩ አሁን ደግሞ የብልፅግና አባል መሆኑን እንደደረሱበትና ይህንንም በማስረጃ በማስደገፍ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መላካቸውን ለዜጎች መድረክ አስታውቀዋል።

    “የእኛ መዋቅሮችም የብልፅግና አባል የሆኑትን ሰዎች አጣርተው ከእነ ስም ዝርዝራቸውና ከመቼ ጀምሮ የብልፅግና አባል እንደሆነ ጠቅሰው ስማቸውን ልከውልናል። አንዳንዶቹ ሰዎች ለብልፅግና ፓርቲ የአባልነት መዋጮ የከፈሉበትን ደረሰኝ ጭምር አያይዘው ልከውልናል። ይህንንም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገቢ አድርገናል” ብለዋል።

    ምርጫ ቦርድ በሁለተኛ ዙር የሌሎች ሰዎችን ስም ዝርዝር የላከላቸው መሆኑን የጠቀሱት ድርጅት ጉዳይ ኃላፊው፥ ይህንንም የሚያጣሩ መሆናቸውንና ተገቢውን ማጣራት ካደረጉ በኋላ ለቦርዱ ምላሻቸውን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

    አንዳንድ ቦታዎች ላይ በምርጫ አስፈጻሚነት እየተሳተፉ ያሉ ሰዎች በግልፅ ወገንተኝነት የታየባቸው ናቸው ያሉት ዋሲሁን ተስፋዬ፣ ዋናው የአስፈጻሚነት ሚና ገለልተኝነት መሆኑን ጠቅሰው፥ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ አስፈፃሚዎችን ገለልተኝነትን በጥንቃቄ ሊመረምረው ይገባል ብለዋል። ቦርዱ፣ ፓርቲያቸው የገለልተኝነት ጥያቄ ያነሳባቸውን ሰዎች ዝርዝር በመመልከት ሌሎቹ አስፈጻሚዎች እንዴት ነው የተመለመሉት የሚለውን ያጣራል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

    ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፥ ለምርጫ አስፈጻሚነት የመለመላቸውንና ገለልተኝነታቸው ላይ ጥያቄ ያነሳንባቸውን እነዚህን ሰዎች በሌሎች ሰዎች ይቀይራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ መቀየርም ይኖርበታል ብለዋል አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ።

    ኢዜማ በገለልተኝነታቸው ላይ ጥያቄ ያነሳባቸውና ስም ዝርዝራቸው ለምርጫ ቦርድ የተላከው የምርጫ አስፈፃሚዎች፣ ሲፈርሙባቸው የነበሩ የደሞዝ መክፈያ ሰነድና የብልፅግና አባል መሆናቸውን የሚያሳይ የአባልነት መዋጮ የከፈሉበት ደረሰኝ በማያያዝ ለምርጫ ቦርድ ገቢ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል።

    ሰነድ ማስረጃ ያልተገኘባቸው ደግሞ የሰው ማስረጃ በማቅረብ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በደብዳቤ እንዲደርሰው መደረጉን የፓርቲው መጽሔት “የዜጎች መድረክ” መረዳት ችላለች።

    ኢዜማ፥ በመንግሥት ሥር ያሉ እንደ ሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ዓይነት ተቋማት፣ ምርጫ አስፈጻሚ መሆን የምትፈልጉ ሰዎች መመዝገብ ትችላላችሁ የሚል ማስታወቂያ ለጥፎ ምልመላ ሲያካሄዱ ደርሶበት ይህንን ከእነ ሰነድ ማስረጃው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማቅረብ፣ ከቦርዱ ውጪ የትኛውም አካል ምርጫ አስፈፃሚዎችን የመመልመል ስልጣን እንደሌለው ማስታወቁ አይዘነጋም።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    ኢዜማ ለምርጫ ቦርድ ያመለከተው

    Anonymous
    Inactive

    የሀገር ሰላም እና አንድነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደው እርምጃ በፍጥነት ተጠናቆ ሙሉ ትኩረታችንን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ላይ እናድርግ!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    በሀገራችን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መንግሥታዊ ድጋፍ አግኝቶ በተግባር ላይ የቆየው ማንነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ በዜጎች እና ማኅበረሰቦች መካከል የጥላቻ እና ያለመተማመን ስሜት እንዲሰፍን ማድረጉ የሚታወቅ ነው። በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረው አገዛዝ በስልጣን ላይ ለመቆየት የጥላቻ እና አለመተማመን መስፈኑን እንደአንድ መሣሪያ ሲጠቀመው ቆይቷል። ይህን ለረጅም ጊዜ በመንግሥት መዋቅር ጭምር እየተደገፈ የተሠራው ማንነትንን መሠረት ያደረገ መከፋፈል፣ የጥላቻ እና የእርስ በርስ አለመተማመን አሁንም ድረስ በየአካባቢው ተንሰራፍቶ፤ ዜጎች በሀገራቸው በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው ደህንነታቸው ተጠብቆ የመኖር፣ የመሥራት እና ሀብት የማፍራት ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና ያለውን ሰብዓዊ መብታቸውን እየገፈፈ ነው።

    ይህ መከፋፈል፣ የእርስ በርስ ጥላቻ እና አለመተማመን ከሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ውጪ የፖለቲካ አመለካከታቸውን በኃይል ለመጫን የሚፈልጉ ኃይሎች ዓላማቸውን ለማሳካት እንደአጋጣሚ ወስደው እየተጠቀሙበት እንደሆነ ግልፅ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት መዋቅርም ሙሉ በሙሉ ከዚህ ችግር ያልጸዳ ብቻ ሳይሆን አደጋ በደረሰባቸው ቦታዎች የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች ከአጥፊዎች ጋር በትብብር እየሠሩ ከአደጋ መጠበቅ የሚገባቸውን የንፁሃን ዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ እየጣሉ ይገኛል።

    የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና የሀገር ሰላም እንዲሁም አንድነትን የማስከበር ኃላፊነት ያለባቸው የደህንነት መዋቅሮች የደህንነት ስጋት ያለባቸው ቦታዎችን በአግባቡ ተንትኖ ደረጃቸውን መለየት እና በዚያም ልክ ተዘጋጅቶ የንፁሃን ዜጎችን ሕይወት እና የሀገርን ሰላም ማስጠበቅ ላይ በተደጋጋሚ ክፍተት እንዳለባቸው አይተናል። የንፁሃንን ሕይወት የቀጠፉ እና ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ጥቃቶች መደጋገማቸው ከተፈፀሙ በኋላ የሚወሰዱ የእርምት እርምጃዎችም አጥጋቢ እንዳልሆኑ በግልፅ የሚያሳዩ ናቸው። እነዚህን ጉድለቶችን ሙሉ ለሙሉ ማረም እና አስተማማኝ የሆነ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የረጅም ጊዜ ከባድ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም፥ ክፍተቱ እያስከተለ ያለው የንፁሃን ዜጎች ሕይወት ጥፋት የማስተካከያ እርምጃዎች ከማንኛውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ትኩረት ቅድሚያ ተሰጥቶዋቸው እንዲሠሩ የሚያስገድድ ነው።

    ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ የቆየው ኢሕአዴግ አባል የነበሩ ሰዎች በሀገር እና ዜጎች ላይ ላደረሱት ጥፋት ሁሉ ይቅርታ ጠይቀው፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊያንም ተቀብሎት፤ ሀገር አቀፍ ለውጥ ሂደት ጅማሮ ውስጥ መግባታችን ይታወቃል። የነበረውን ስልጣን የበላይነት ያጣው ህወሓት በተለያየ ጊዜ የወሰዳቸው እርምጃዎች ከአጠቃላይ የለውጡ መንፈስ ውጪ ከመሆን አልፈው፤ የሀገር ሰላም እና አንድነትን በተደጋጋሚ አደጋ ላይ የሚጥሉ ነበሩ። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የፌደራሉን መንግሥትና የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በቀጥታ በመቃወም ራሱ አስመራጭ፣ ተመራጭ፣ ታዛቢ እና ቆጣሪ የነበረበት ሕገ-ወጥ የክልል ምርጫ አድርጓል። በዚህም የተነሳ የፈደራል መንግሥት ከክልሉ ጋር ያለዉን ቀጥተኛ ግንኙነት ማቋረጡን እናስታውሳለን። “ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም!” የሚል አደገኛ ቅስቀሳ በማድረግ በሀገራችን ውስጥ ፍፁም ሥርዓት አለበኝነት እንዲነግሥ በባለስልጣናቱ እና በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል። በሀገሪቱ በተለያየ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖችን ቢያንስ በእርግጠኝነት የምናውቀውን የሚዲያ እና የሞራል ድጋፍ በማድረግ የብዙ ንጹሀን ሕይወት እንዲቀጠፍ ተባባሪ ሆኗል።

    በሀገራችን የመከላከያ ሠራዊት ላይም በተደጋጋሚ ሥራዉን የማደናቀፍ እና የሚገባዉን ክብር የመንፈግ ድርጊቶች ፈጽሟል። የሠራዊቱ የተለያዩ ክፍሎች ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ መንገድ በመዝጋት እና በማዘጋት እንዲሁም በመከላከያ ሕግ እና ደንብ መሠረት የሚፈጸሙ የከፍተኛ የጦር ኃይል አመራር ሹመቶችን ባለመቀበል አስተጓጎሏል። ህወሓት የፖለቲካ ዓላማውን ለማሳካት በሰላማዊ መንገድ ከመንቀሳቀስ እና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የትግራይን ሕዝብ እንደከለላ በመውሰድ እና ያከማቸውን ገንዘብ እና የኃይል አቅም በመጠቀም በማንአለብኝነት የፈፀማቸው ድርጊቶች እያደር የብዙ ዜጎችን ሕይወት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነት የበለጠ አደጋ ውስጥ እየከተቱ መጥተው መንግሥት ያለውን ኃይልን ተጠቅሞ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና የሀገር ሰላም እና አንድነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተገደደበት ደረጃ ላይ መድረሱን እንገነዘባለን።

    ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እራሱን ለመከላከል እና ለሀገር አንድነትና ሰላም ከፍተኛ እና ተደጋጋሚ ስጋት ሲደቅን የነበረው ህወሓት ላይ መውሰድ የጀመረው እርምጃ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎችም ኃይልን ተጠቅመው የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነት ላይ አደጋ በመጣል የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በሙሉ ሥርዓት የሚያሲዝ እና ከአሁን በኋላ የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካት ከሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ውጪ ለመንቀሳቀስ ያሉ አማራጮችን በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚዘጋ መሆን ይኖርበታል።

    በሁሉም አካባቢዎች ችግር ሲያጋጥም አሰስፈላጊውን መስዕዋትነት እየከፈለ የሚጠብቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን በዚህ ወቅት ከውጭ ጠላቶች ሀገርን የመከላከል እና ከሀገር ውስጥ የጥፋት ኃይሎች ሀገርን የመታደግ ድርብርብ ከባድ ኃላፊነቶችን እንደተሸከመ እንረዳለን። ምንም እንኳን ተደራራቢ እና አስቸጋሪ ኃላፊነት ቢሆንም የተቋቋመበት ኃላፊነት እና የተሰጠው ሕገ-መንግሥታዊ ግዳጅ በመሆኑ እንደሚወጣው እናምናለን። በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን አንድነት እና ሰላምን ለማስከበር የሚወስዳቸው እርምጃዎች የኢዜማ አባላት እና አመራር ሙሉ በሙሉ ከጎኑ እንደሚቆም ለማረጋገጥ እንወዳለን።

    በመሆኑም፦

    1. መከላከያ ሠራዊቱ እና ሌሎች የመንግሥት የፀጥታ ተቋማት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወስዷቸው እርምጃዎች የሁሉንም ዜጎች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያከበረ እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች በተለይም ሕፃናት፣ ሴቶች እና በዕድሜ የገፉ አረጋውያን ማንኛውም ጉዳት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ እንዲደረግ ልናሳስብ እንወዳለን። የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላምን እና አንድነትን ለማስከበር የሚወሰደው እርምጃ በተቻለው አቅም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ በሁሉም አካባቢዎች መደበኛ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የሚቀጥልበት ሁኔታም ሊመቻች ይገባል።
    2. የትግራይ ሕዝብ አሁን እየተወሰደ ያለው እርምጃ የሀገር ሰላም እና አንድነትን የማረጋገጥ እርምጃ መሆኑ በማወቅ ለረጅም ጊዜ የስጋት ድባብ በመፍጠር እንደሽፋን እየተጠቀመ ሲበዘብዘው እና በስሙ ሲነግድ የነበረው ህወሓትን በፍፁም ሳይተባበር ከአብራኩ ከወጣው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ለሀገር ሰላም እና አንድነት ከአባት እና እናቶቹ የወረሰውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያረጋግጥ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
    3. የትግራይ ክልል ፖሊስ እና ልዩ ኃይል አባላት ህወሓት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እንዲደርስ በማድረግ በኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት ላይ መዳከም እንዲፈጠር በሚያደረገው ሀገርን የማፍረስ ዘመቻ ላይ እንዳይሳተፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። የትግራይ ክልል ፖሊስ እና ልዩ ኃይል በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆምም ሕዝቡን ከስጋት እና ከአደጋ እንዲጠብቅ እንጠይቃለን።
    4. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚወሰደው እርምጃ የዜጎችን ደህንነት እና የሀገር ሰላም እና አንድነት ለማረጋገጥ መሆኑን በመረዳት አብሮነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ እና ለሰላም እና ደህንነት እንቅፋት የሚሆኑ ማንኛውንም እንቅስቃሴዎች ከማድረግ እንዲቆጠብ፣ በሁሉም አካባቢ ስጋት የገባቸውን ሰላማዊ ዜጎች ከለላ እና ማበረታቻ በመስጠት እንዲሁም አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ ለሰላም እና ደህንነት መከበር ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ትብብር እንዲያደርግ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
    5. አሁን እንደ ሀገር የተደቀነብን አደጋ ማንንም ከማንም የማይመርጥ የህልውና አደጋ መሆኑን በመገንዘብ ይህንን አደጋ የሚመጥን መፍትሄ በማፈላለግ ረገድ የተማረው ማኅበረሰብ ሚና ትልቅ እንደሆነ እሙን ነው። የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ከዳር ቆሞ አስተያየት ሰጪና ተቺ ከመሆን ወጥቶ ወደመሀል በመግባት ሊመጡ የሚችሉ የፖለቲካ መፍትሄዎችን በመጠቆም፤ እንዲሁም በቀጥታ ድጋፉን የሀገር አንድነትን እና ሰላምን ከሚፈልጉ ኃይሎች ጎን በማሰለፍ ያለበትን ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት እንዲወጣ በዚህም በታሪክ ከሚመጣበት ወቀሳ እንዲድን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
    6. አሁን እየተተገበረ ላለው ሀገራዊ ግዳጅ ጥሪ ተደርጎላችሁ የምትሳተፉ ኃይሎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ ስር ብቻ ተልኮውን እንድትፈፅሙ እና በተሰጣችሁ ሀገራዊ ግዳጅ ላይ ብቻ እንድታተኩሩ እናሳስባን። ኢዜማ ለሀገራዊው ጥሪ በፍጥነት ለሕይወታችሁ ሳትሳሱ ምላሽ ለሰጣችሁ ሁሉ ምስጋናውን እያቀረበ በዚህ ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት በይፋ ከመንግሥት ከተሰጠ ተልዕኮ ወጪ የሆነ ለሀገር ሰላም እና አንድነት የበለጠ እንቅፋት የሚሆን ተግባር እንዳትፈፅሙ ስንል እናሳስባለን። በተለይም ኢ-መደበኛ በሆነ አደረጃጀት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የገባንበትን ችግር የበለጠ የሚያወሳስብ እጅግ አደገኛ ተግባር እንደሆነ ልናሳስብ እንወዳለን። ስለዚህም አሁን የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነትን ለማስከበር የተገባው በሀገራዊ ግዳጅ ላይ ብቻ አተኩረን በመንቀሳቀስ በፍጥነት የሕዝብን ጭንቀት በመቋጨት ሌሎች የዴሞክራሲ እና የይገባኛል ጥያቄዎች በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገዶች ወደፊት የሚፈቱበት መንገድን እንድናመቻች በአፅንዖት እናሳስባለን።
    7. ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተፅእኖ ያላገገመው የኢኮኖሚ እንቀውሰቃሴ የአንበጣ መንጋ ጥቃት ተጨምሮበት ኅብረተሰባችን ምን ያህል ጉዳት ውስጥ እንደሚገኝ ለመገመት የሚከበድ አይደለም። በዚህ አስቻጋሪ ሁኔታ የተቀሰቀሰው ግጭት ሊፈጥር የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በመክተት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ የእርዳታ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ዜጎች ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ ከወዲሁ ታሳቢ በማድረግ እንዲንቀሳቀሱ ለማሳሰብ እንወዳለን።
    8. በተደጋጋሚ እንደገለፅነው የዜጎችን ደህንነትና ያለስጋት የመኖር መብት የማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነት የመንግሥት ነው። መንግሥት በተደጋጋሚ ይህን ኃላፊነቱን መወጣት ሳይችል በመቅረቱ ዜጎች ውድ የሆነውን ሕይወታቸውን ሲያጡ ቆይተዋል። በሀገር ውስጥ የሚፈፀሙ በተለይም ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በማንም ይፈፀሙ በማን የማስቆም እና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት በመሆኑ መንግሥት ከተጠያቂነት ነፃ ሊሆን አይችልም። ጠመንጃ ደግነው ጥይት ተኩሰው ሰው ከሚገድሉት ነብሰበላዎች እኩል እነዚህን ኃይሎች በተለያየ መንገድ የሚያበረታቱ ከጎናችሁ ነን የሚሉ በተለይም በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች እና በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ጭምር ንፁሃን ላይ ለሚደርስ ጥቃት ድጋፍ ሲሰጡ የሚታዩ ኃይሎች ላይ መንግሥት አስተማሪ የእርምት እርምጃ በመውሰድ እንዲያስቆም እናሳስባለን። ምንም እንኳን ሰላምን የማረጋገጥ ኃላፊነት በዋናነት የመንግሥት ቢሆንም መንግሥት ብቻውን የሚፈፅመው አይደለም። ማኅበረሰቡን ያላስተባበረ እና ያላካተተ የሕግ ማስከበር እርምጃ ውጤታማ እንደማይሆን በተደጋጋሚ ታይቷል። ስለሆነም መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን መላውን ማኅበረተሰብ ባሳተፈ መልኩ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ በየቀበሌው የፀጥታና አካባቢ ጥበቃ ሥርዓት እንዲዘረጋ ለማሳሰብ እንወዳለን። በተለይም መንግሥት በተደጋጋሚ በመግለጫ ጭምር የችግሩ አካል እንደሆኑ የሚገልፃቸው የመንግሥት ስልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦችን ወደ ተጠያቂነት በማምጣት ራሱን እንዲያጠራ አፅንኦት ሰጥተን እናሳስባለን። ለዚህም ኅብረተሰቡን የመፍትሄው አካል ማድረግ ወሳኝ ነው። መንግሥት በቅርብ ጥቃት የተፈፀመባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወደመደበኛ ሕይወታቸው የሚመለሱበት ሁኔታን በአፋጣኝ እንዲያመቻች እንዲሁም ሌላ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ እንዳለበት ለማስታወስ እንወዳለን። ተመሳሳይ ማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች ሊፈጸሙ የሚችሉባቸው ቦታዎችን አስቀድሞ በመለየት በልዩ ትኩረት ጥበቃ እንዲደረግም እናሳስባለን። በተለይም የክልል አስተዳደሮች በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ የመጀመሪያ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
    9. ኢዜማ በክልል የተደራጀው ልዩ ኃይል በምንም መስፈርት ሕጋዊ ነው ብሎ እንደማያምን እና ለዴሞከራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚሆን በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል። ይህ አደረጃጀት በሀገር አንድነት ላይ ሊያስከትለው የሚችለው ተጨባጭ አደጋ ማሳያ በትግራይ ክልል ሰሞኑን የተከሰተው ክስተት አንዱ እና ዋነኛው ነው። በዘውግ ላይ የተመሠረተው የሀገራችን ፖለቲካ አንዱን የዘውግ ማንነት ከሌላው ለመከላከል ወይም ሌላውን ለማጥቃት በሚዋቀረው የልዩ ኃይል እየተደገፈ የሀገራችንን ሕዝብ ወደበለጠ ስቃይ እና የጭንቅ እየከተታት ይገኛል። ሕዝቡም እርስ በእርሱ በጠላትነት እንዲተያይ የሚያደርግ እኩይ አደረጃጀትም መሆኑን በተደጋጋሚ በተግባር ለማየት ችለናል። ስልዚህም በየክልሉ በስፋት የተደራጀውን ልዩ ኃይል ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ ወይንም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሚቀላቀልበትን አሠራር እንዲዘረጋ እንጠይቃለን።
    10. በሁሉም አካባቢ የምትገኙ የኢዜማ አባላት እና ደጋፊዎች በተለመደው ሥነ-ምግባር በየአካባቢያቹ ሰላም እና ደህንነትን ለማስከበር በንቃት ማኅበረሰቡን በማስተባበር እና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እንድትሠሩ እናሳስባለን።

    በመጨረሻም የሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት የሚጠበቀው የሁሉም ዜጎች እኩል መብት የሚከበርበት እና ለሁሉም ዜጎች እኩል ዕድል የሚሰጥ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲመሠረት እንደሆነ በፅኑ እናምናለን። የሀገራችን አንድነት እና ሰላም ተጠብቆ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሠረት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር አንድነት እና ሰላም ተባብረው ለመሥራት ፈቃደኛ እና ቁርጠኛ መሆን አለባቸው። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ ተቀራርበው እንዲሠሩ የሚያስችል ከምር የሚወሰድ የውይይት መድረክ መዘጋጀት አለበት። ይህ ውይይት ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ኃይሎች ግን ሁሉም የሕግ የበላይነትን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የፈረሙትን የቃልኪዳን ሰነድ የሚያከብሩ መሆን አለባቸው። የደህንነት እና የፍትህ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት መቻላቸው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት ውጤታማ እንዲሆን የማይተካ ሚና ይኖረዋል። በመሆኑም መንግሥት ኃይልን የመጠቀም ብቸኛ ስልጣኑን አረጋግጦ እውነተኛ እና ለውጥ ማምጣት የሚችል ውይይት እንዲጀመር መንገድ የመጥረግ ሥራውን በአፋጣኝ አጠናቆ ሁላችንም ትኩረታችንን ወደዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንድናዞር አበክረን ጥሪ እናደርጋለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም

    የሀገር ሰላምና አንድነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደው እርምጃ በፍጥነት ተጠናቆ ትኩረታችንን ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ እናድርግ!

    Anonymous
    Inactive

    ምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመውን ግድያ በጽኑ እናወግዛለን
    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)

    ከትላንት በስትያ ህዳር 1 ቀን 2020 [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ከመገናኛ ብዙሃን የሰማን ሲሆን፥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ይህንን የግድያ ተግባር በጽኑ እያወገዘ፤ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘንም ይገልጻል።

    መንግሥት ነኝ የሚለው አካል ከአሁን ቀደም እንደለመደው ይህንን ግድያ የፈጸሙት ህወሓት እና ኦነግ-ሸኔ ናቸው በሚል ገልጿል። ኦነግ-ሸኔ በሚል የሚታወቅም ይሁን በዚህ ስም እራሱን የሚጠራ ድርጅት ግን አላገኘንም። ለኢትዮጵያ ሕዝቦችም ይሁን ለዓለም ማኅበረሰብ በዚህ ስም የሚከሰሰው ድርጅት ማንነት ግልጽ አይደለም።

    ይህ የግድያ ድርጊት እና ሌሎች መሰል ድርጊቶች ሁሉም ነጻና ተዓማኒነት ባለው ገለልተኛ አካል በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጣርተው ለተጎጂዎችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥ እንዲሁም ለዓለም ማኅበረሰብ ግልጽ እንዲሆኑ እንጠይቃለን። ከዚህ ባሻገር ሁሉም አካላት ሕዝቦችን የሚያጋጩና በብሔሮች መካከል መጠራጠርን የሚፈጥሩ ማናቸውንም ዓይነት መረጃ ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።

    በመጨረሻም ዜጎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ያለው ቀውስና የደህንነት ችግር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሄ ካልተበጀለት፥ ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድ ኦነግ በመግለጫው ሲያሳስብ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን እያየን ያለነውን አደጋ ለማስቀረት እና ኦሮሚያና ዜጎችን ከባሰ ቀውስ ለመታደግ ያለው ብቸኛው መፍትሄ የኦሮሚያ ሽግግር መንግሥት ማቋቋም በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪያችንን በድጋሚ እናድሳለን።

    በድጋሚ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በምዕራብ ኦሮሚያ በዜጎች ላይ የተፈጸመውንና ካሁን ቀደምም በተመሳሳይ መልኩ የተፈጸሙ ግድያዎችን ሁሉ በጥቅብ እንደሚያወግዝ እያሳሰበ፥ ለሟች ቤተሰቦችና ዘመዶች እንዲሁም ሰላም ወዳዶች ሁሉ መጽናናትን ይመኛል።

    ድል ለሰፊው ሕዝብ!
    የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)
    ህዳር 3 ቀን 2020 ዓ.ም

    ምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመው ግድያ

    Anonymous
    Inactive

    የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ

    • የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት
    • የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መልዕክት
    • የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጋዜጣዊ መግለጫ
    • የብልጽግና ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ
    • የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መልዕክት
    • የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ
    • የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መግለጫ

    የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ።

    የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ማምሻውን ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እንዳሉት፥ በጥቃቱ የተነሳ የተፈናቀሉ 200 ያህል አባወራዎችን የማረጋጋትና ሥራ እየተሠራ ነው።

    በተፈጸመው ጥቃት 23 ወንድ እና 9 ሴቶች በድምሩ 32 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የገለጹት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፥ 10 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

    በጥቃቱ የመኖሪያ ቤቶችና አንድ ትምህርት ቤት እንደተቃጠለ ተናግረው፥ ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር በመተባበር መልሶ የማቋቋም ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

    የጥቃት ድርጊቱን የፈጸመው አካል ኦነግ ሸኔ መሆኑን ገልጸው፥ ከጀርባ በመሆን የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እየደገፈው እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተለይም ቡድኑ የታጠቃቸው እንደ ስናይፐርና ብሬል ያሉ የጦር መሳሪያዎች ህወሓት ያስታጠቀው እንደሆነ ገልጸዋል። ከኦነግ ጀርባ በመሆን ህወሓት በህብረተሰቡ ላይ ጥፋት እያደረሰ እንደሆነም አክለዋል።

    ጥቃት የተፈጸመበት ቀበሌ ከወረዳ ከተማ በ75 ኪሎ ሜትር የሚርቅ መሆኑን ገልጸው፥ ህወሓት በብሔሮች መካከል ግጭት ለመፍጠር በስሌት የፈጸመው ተግባር ስለመሆኑ ተናግረዋል።

    ከድርጊቱ ፈጻሚዎች መካከል የተወሰኑት መያዛቸውን ተናግረው ቀሪዎቹን ለመያዝ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸም ከሕብረተሰቡ ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    • የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት

    በተያያዘ ዜና፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ከምንጩ ለማድረቅ መንግስት የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት ምሁራንና ሌሎችም የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት እንደሚከተለው ይነበባል።

    “በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልፃለሁ።

    የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ “ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም” ብለው ተነሥተዋል። ለዚህም የጥፋት አቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው።

    ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የማያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው። ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ ርምጃ እንዲወስድ የታለመ ነው።

    መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም።

    የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ ነው። ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል።

    ይህ ግን ከመንገዳችን ወደኋላ፣ ከግባችን ወደ ሌላ አያደርገንም። ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፣ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም። ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሣ ያደርገናል እንጂ።

    መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል። የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል። ርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል።

    ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ ምሁራንና ሌሎችም፧ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።”

    • የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መልዕክት

    የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል። አቶ ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት የሚከተለውን ብለዋል።

    “በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማኝን ሀዘን እየገለፅኩ፥ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን እመኛለሁ።

    በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀደም ሲል ብሔርን፣ ሀይማኖትን እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የማድረስ ዓላማ ያላቸው ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል። በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል።

    በተለይ የአማራን ማኅበረሰብ ትኩረት ያደረገና በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ ፍፁም አረመኔያዊና በፍጥነት መቆም ያለበት እኩይ ድርጊት ነው። ድርጊቱ አስቀድሞ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ሲዘራ የቆየ በመሆኑ፥ ችግሩን የሚመጥን መፍትሄ በዘላቂነት ለማበጀት አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ከሁሉም አቅጣጫ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት የመንግሥትና ሕዝብ ቅንጅታዊ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል።”

    • የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጋዜጣዊ መግለጫ

    ይህንን ጥቃት ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፉት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል ብሏል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር በመጫን ያንብቡ።

    • የብልጽግና ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ

    የብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ፥ ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን እንደማይችል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።

    • የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መልዕክት

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) “በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በዜጎች ላይ ማንነትን መሠረት ባደረገ ጥቃት በተገደሉት እና ጉዳት በደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን የተሰማንን ሀዘን እንገልፃለን” በማለት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል መልዕክቱን አስተላልፏል።

    ፓርቲው በዚሁ መልዕክቱ፥ ኢትዮጵያውያን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በአንድነት በመቆም የዘውግ ፖለቲካ ያመጣብንን በሕይወት የመኖር እና እንደ ሀገር የመቀጠል አደጋ ልንታገለው እንደሚገባና፤ ኢዜማ አጠቃላይ የሀገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ በቀጣይ ቀናት መግለጫ እንደሚሰጥ አመላክቷል።

    በማስከተልም፥ በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ማንነትን መሰረት አድርጎ የተፈፀመው ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሐዘን ሲሆን፤ የጥቃቱ ዓላማም ሀገርን የማፍረስ መሆኑን ተረድተን ሀዘናችንን በጋራ በመግለፅ በአንድነት እንድንቆም እንጠይቃለን ሲል መልዕክቱን ቋጭቷል።

    • የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ

    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ካወገዘ በኋላ፥ መንግሥት ጥቃቱን ያደረሱት ህወሓትና ኦነግ ሸኔ ናቸው ማለቱን በከፊል በማስተባበል፤ ይልቁንስ ኦነግ ሸኔ የሚባል ቡድን በአካል እንደሌለ ገልጿል። የኦነግን ሙሉ መግለጫ እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።

    • የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መግለጫ

    የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ደግሞ በሰጠው መግለጫ፥ በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ዘር-ተኮር ጥቃት የፌደራል መንግሥቱን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ  ግንባር ቀደም ተጠያቂ እንደሆነ አትቷል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር ያገኙታል።

    በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር

    Anonymous
    Inactive

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎችን ለማድረግ ጥሪ አደረገ

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎች እንደሚደረጉ አስታውቋል። አብን ስለሰላማዊ ሰልፎቹ እና በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ከዕለት ወደ ዕለት ያልተቋረጠ በደል እየደረሰበት መሆኑን ያመላከተበት ትንታኔ የሚከተለውን ይመስላል።

    ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
    ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች፣
    ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ !

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግሥታዊና ሥርዓታዊ ጭቆና እና የዘር ጥቃት ያንዣበበትን የአማራን ሕዝብ ከህልውና ስጋት ለመታደግና በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በፍትህና በወንድማማችነት የሚኖርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የቆመ ድርጅት ነው።

    አብን ባለፉት ሁለት ከመንፈቅ ዓመታት ሕዝባችን በከፍተኛ መስዋዕትነት ያስገኘው የለውጥ ተስፋ እንዳይመክን፣ በትግላችን የተንበረከኩ አማራ-ጠል ኃይሎች ዳግም እንዳያንሰራሩና የሀገር እና የሕዝብ ህልውና በድጋሚ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጓል። የአማራ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዎንታዊ የመረጋጋት፣ የመቻቻልና የግንባታ ሚና እንዲኖረው ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።

    ይሁን እንጂ ተስፋ የተጣለበት “ለውጥ” እያደር መስመሩን በመሳቱ አዲሱ አገዛዝ የአምባገነንነትና የአንድ ቡድን ፍላጎት አስፈፃሚነት አዝማሚያ ማሳየቱ ገሃድ ወጥቷል። በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ጥቃት እየተባባሰና አድማሱን እያሰፋ በቅርቡ እንኳን በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ጉራ ፈርዳ ተከታታይ ለሆኑ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ የዘር ማጽዳትና የማፈናቀል ጥቃቶች ሰለባ ሆኗል።

    አብን በሕዝባችን ላይ ስልታዊ፣ የተደራጀ፣ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ቅስቀሳ የተደረገበት ዘመቻና በመንግሥት መዋቅር ጭምር የተደገፈ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመበት መሆኑን በመግለጽ መንግሥት ችግሩን እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ወትውቷል። እንደ ሕዝብም መቻቻልና ሀገር ወዳድነት ትርጉም እስኪያጡ ድረስ ታግሰናል። ነገር ግን ብልፅግና-መራሹ መንግሥት የሕዝባችንን ሆደ-ሰፊነትና አስተዋይነት እንደ ዓይነተኛ ድክመት በመቁጠር፥ ንቅናቄያችን ለሀገር ህልውና ሲባል የሰጠውን ይሁንታ በሰፊው በማጓደል ዛሬም አማራው መንግሥት-አልባ ሕዝብ መሆኑን አረጋግጦልናል።

    አብን በሕዝባችን ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ቀንደኛው ተጠያቂ ማዕከላዊ መንግሥት መሆኑን ያምናል። መንግሥት ‹‹የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል›› የሚባለውን የዘር ማጥፋትን በመከላከል፣ በማስቆምና ዘላቂ መፍትሄ በመፈለግ ረገድ የረባ ሚና አልተጫወተም። እንዲያውም የዘር ጥቃቶችን “ግጭት” እያለ ለማድበስበስ፣ መረጃዎችን ለማፈንና ሰለባዎችን ጭምር ለመወንጀል ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ ተስተውሏል። መንግሥት በአማራ ላይ የተፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ልዩ ጠባሳ የሆነውን የጉራ ፈርዳ ጥቃት መሪ አቀናባሪ የነበረውን ግለሰብ ለዳግም ሹመት የመምረጡን አንድምታ እንረዳለን፤ አሁን የሚፈፀመውን ካለፈው የሚያስተሳስር ረጅም ክር አለው።

    በሁለተኛ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ፍጅት በተፈፀመባቸው ክልሎች ያሉ መንግሥታት በተለያየ ደረጃ ኃላፊነታቸውን ካለመወጣት አልፈው፥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በሕግ፣ በመዋቅር፣ በመሣሪያና በገንዘብ ጥቃቶችን መደገፋቸውና ማቀናበራቸው በገሃድ ይታወቃል። ከጥቃቱም በኋላ የየክልሎቹ የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች በሕዝባችን ላይ በየፊናቸው በማንአለብኝነት የሚያደርጉት ዛቻና ማስፈራሪያ በድርጊቱ አለመጸጸታቸውንና ችግሩን ለማረም ፈቃደኝነት እንደሌላቸውም ያረጋግጣል።

    ሦስተኛው ተጠያቂ “የአማራ ብልፅግና” የሚባለው ነው። ለአማራ ሕዝብ ብልፅግናውን ቀርቶ ህልውናውንም ሊያስጠብቅለት አልቻለም። ቀድሞ ከነበረው አጠቃላይ አቋም መሻሻል አላሳየም። ንቅናቄያችን አማራው እንደ ሕዝብ በአንድነት እንዲቆም ለማስቻል ለሁለት ዓመታት ያክል “የአማራ – ብልፅግናን” ለማግባባት ያደረገው ሰፊ እና ያላሰለሰ ጥረት ፍሬ አላፈራም። የአማራ ሕዝብንም፣ አብንንም በተደጋጋሚ ያሳዘነ ሲሆን፤ ከታሪክ ተጠያቂነትም አያመልጥም።

    አብን በማዕከልም ሆነ በክልል ያሉ መንግሥታት የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ውጤቱ በአማራው ሕዝብ ተገድቦ እንደማይቀር በውል እንዲጤን ይሻል። መንግሥት መሠረታዊ መብቶቹን የማያስጠብቅለትን ሕዝብ ማናቸውንም የሞራልም ሆነ የሕግ ግዴታ ሊጥልበት አይቻለውም። በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ማኅበራዊ ውልም ክፉኛ ይናጋል።

    አብን በአማራው ላይ የሚደረገው የዘር ማጥፋት ድርጊት ዞሮ ኢትዮጵያን እንደሀገር ዋጋ እንደሚያስከፍልም ይገነዘባል። ንቅናቄያችን እስካሁን የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ተስፋ እንዲቆርጥና ወደ አመፅ እንዲያመራ የሚደረገውን አሉታዊ ጥረት ሲታገል ቆይቷል። ሆኖም ከእንግዲህ ወዲያ የሕዝባችን ህልውና በምንም መልኩ ለድርድር እንደማይቀርብ ለማረጋገጥ ይወዳል።

    አብን የአማራ ሕዝብ ሆደ ሰፊና አስተዋይ በመሆኑ ተፈጥሯዊ መብቱንና ነፃነቱን በልቅሶና በልመና ሳይሆን በተደራጀ ትግል እንደሚያስከብር ይተማመናል። ይህን ታላቅ ታሪካዊ ኃላፊነት በመምራት ከግብ ለማድረስ ድርጅታችን ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል።

    አብን መንግሥት ችግሩን በአስቸኳይ ከማስቆም በተጨማሪ ጥቃቱን እንዲያምንና በስሙ እንዲጠራ፣ ጉዳዩን የሚያጣራ ገለልተኛ አካል በፍጥነት እንዲሰይም፣ ወንጀለኞችን አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብና ለተጎጂዎችም ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል በጥብቅ ይጠይቃል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መሠረታዊ ምንጭ የሆነው አማራ-ጠል ሕገ-መንግሥት የሚሻሻልበትን አግባብ በአስቸኳይ እንዲያመቻች ይጠይቃል።

    አብን መንግሥት የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር አለመቻሉንና በተደጋጋሚ የአማራ ተማሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ችላ ማለቱን በማጤን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያደረገው የትምህርት መጀመር ጥሪም ያሳስበዋል። ብዙ ሽህ የአማራ ተማሪዎች በፅንፈኞች ጥቃት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉ፣ ሲደበደቡና ሲታገቱ በአሳፋሪ ሁኔታ አልታደጋቸውም። አሁንም ለተማሪዎች አስተማማኝ ጥበቃ እንዲያደርግ በጥብቅ እንጠይቃለን።

    የአብን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጥቅምት 14 እና 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በወሰነው መሠረት በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ያንዣበበውን ከፍተኛ የደህንነት ስጋት በመቀልበስ፤ የሕዝባችንን ህልውና ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸውን ሰላማዊና ሕጋዊ የትግል ጥረቶችና ስልቶች ለሕዝባችን ለማሳወቅ የፊታችን ረቡዕ ጥቅምት 18 በአማራ ክልል ከተሞች፤ እሁድ ጥቅምት 22 በአዲስ አበባ ታላላቅ ሕዝባዊ ትዕይንቶች ይደረጋሉ።

    በእነዚህ ሰልፎች ላይ መላው የአማራ ሕዝብ ማናቸውም ልዩነት ሳይገድበው እንዲሳተፍ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የተለያዩ የአማራ የሲቪክ አደረጃጀቶች በወገናችሁ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል እንድትቃወሙ ጥሪ እናደርጋለን።

    አብን በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የተጠሩት የተቃውሞ ሰልፎች ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆኑና ሊከተሉ የሚችሉ አላስፈላጊ ረብሻዎችንና ጥቃቶችን ለማስቀረት ሕዝቡ የራሱን ደህንነት በንቃት እንዲጠብቅ ያሳስባል።

    ሰልፉን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች፣ በሰልፉ ላይ የሚተላለፉ መልዕክቶችና መፈክሮች በማዕከል ተዘጋጅተው በፓርቲያችን ይፋዊ ገፅ የሚለጠፉትና ለየአካባቢው የሚላኩት ናቸው።

    ጉዳዩ የሕዝብ ህልውና ጥያቄና የራሱ ሰልፍ በመሆኑ የሀገር መከላከያና አጠቃላይ የደህንነት ኃይሉ የሕዝቡ ሰልፍ የተሳካ እንዲሆን ተገቢውን የፀጥታ ሥራ እንዲያከናውን ጥሪ እናደርጋለን።

    በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ አማሮች እሁድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚደረገው ሰልፍ ጋር በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ድምፃችሁን እንድታሰሙ አብን ጥሪውን ያቀርባል።

    ሰልፉ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ በጥንቃቄ እንዲካሄድ እያሳሰበ፥ ሕዝባችን በየአካባቢውና በየቤተሰቡ በገጠመን ፅኑ ወቅታዊ ችግር ላይ ውይይት እንዲያካሂድ፤ በቀጣይም ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ አብን ዓለምአቀፍ የመላው አማራ ሕዝባዊ ውይይት መድረኮችን እንደሚያመቻች መግለጽ ይወዳል።

    በአዲስ አበባም ሆነ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የማናለብኝነትና የተረኝነት አካሄድ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ጉዳት በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወንድሙ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ግፍና በደል በመቃወም አብሮ እንዲሰለፍ አብን ጥሪውን ያቀርባል።

    አብን ከእንግዲህ ጉዳዩ የማያዳግም እልባት እስከሚያገኝ ድረስ ማናቸውንም የሰላማዊ ትግልና የሕዝባዊ እምቢተኝነት ስልቶችን በየደረጃው የሚተገብር በመሆኑ ሕዝባችን ከወዲሁ እንዲያውቀውና ወትሮ ዝግጁ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
    ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም
    ሸዋ፥ አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ!

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    Anonymous
    Inactive

    በአዳራሽ ስብሰባ ለማድረግ ፈቃድ ከልክሎ በአደባባይ ቢልቦርድ እንዲሰቀል እንዴት ፈቀዳችሁ?
    አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ

    “መስከረም 30 መአት ይወርዳል” ከሚሉት ጋር የማልስማም መሆኔን አስረድቻለሁ። መስከረም 30 በአዲስ አበባ ጎዳና ወጥተው የተመለከትኩት፥ በየአደባባዩ የተሰቀለው የማስታወቂያ ሰሌዳ (billboard) ግን አንድ ነገር አስታዋሰኝ። የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚቴ (ኢሠፓአኮ) ማብቂያው ደርሶ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ሊመሠረት ዋዜማው ላይ በከተማቸን የምናየው መፈክር ሁሉ፥ “ከጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም አመራር ጋር ወደፊት!”፣ “ብልሁ፣ አስተዋዩ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም…” ወዘተ… የሚሉ ነበሩ። አልቀረልንም… ከዝሆን እና አንበሳ ምረጡ ተባለና ዝሆን ተመረጠ፤ አለቀ ደቀቀ። ይህ በሁለት የአንድ ፓርቲ አባላት መካከል በሚደረግ ምርጫ ዝሆን ቢመረጥ፣ አንበሳ ወይም ሚዳቋ ብዙ ትርጉም የለውም። ኢሠፓ ያለውን መንግሥቱን መርጧል።

    ዛሬም ብልፅግናዎች ዐቢያቸውን “ብልሁ መሪ” የማለት መብታቸውን አከበራለሁ። ያላቸውን የመምረጥ መብት አላቸው። በአጠቃላይ ለሀገሩ እና ለከተማው ነዋሪ ይህን በግድ መጫን ግን መብታቸው አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ቅስቀሳ ሳይጀመር ምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ሌላውን በቢሮ ለሚደረግ ውይይት ፍቃድ ሰጪና ነሺ የሆነ መንግሥት፥ በትራፊክ መንገድ አዘግቶ “ዐቢይ ለዘላለም ይኑር!” መፈክር ተገቢና ትክክል አይደለም። ይህ መንገድ የመንግሥቱ ኃይለማርያም መንገድ ነው። ብልፅግና ኢሠፓአኮን/ኢሠፓን መሆን ካማረው ሕጉን ይለውጥና ምርጫ ቦርድን ዘግቶ መጫወት ይችላል። የሚከተለውን ለመቀበል መዘጋጀት ብቻ ነው የሚጠበቅበት።

    አስገራሚው ዛሬም በየቀበሌና ወረዳው በዚህ ደረጃ ወርደው የሚያዋርዱ ካድሬዎች መኖራቸው ነው። “ታላቁ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም!”፣ “ታላቁ መሪ ዐቢይ አህመድ!” ብሎ ለመፃፍ ልብ የሚያገኙ ካድሬዎች እንዴት ነው ማፍራት የተቻለው? መክሸፍ ማለት ይህ ነው፤ ከታሪክ መማር ያለመቻል። የሀገርን መሪ በሕዝብ ድምፅ ቢቻል በቀጥታ ድምፅ ይሰጥ የምንለው አብዛኛው ይሁንታ የሰጠው እንዲመራን እንጂ፥ ካድሬ እንዳይመርጥልን ሰለምንፈልግ ነው። ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአዲስ አበባ ተመራጭ አይደሉም፤ በቀጣይ አዲስ አበባም የሚወዳደሩ ከሆነ በወረዳቸው ይህን ማድረግ ይቻላል። ግን ገና ለገና መስከረም 30 መንግሥት የለም ካሉት ጋር ብሽሽቅ ለመግባት የዚህን ያህል መውረድ አያስፈልግም። የዚህ ዓይነት ድርጊቶች ሳይቃጠል በቅጠል ካልተባለ፥ ምርጫ ሲጀመር በየወረዳው ኃላፊነት ላይ ያሉት የብልፅግና ሰዎች መላወሻ ሊከለክሉን ግድ አይሰጣቸውም። ይህ መስመር ግን በወረዳ የብልፅግና ካድሬዎችንም ቢሆን አይጠቅምም፤ አያኗኑርም ብሎ መመከር ደግ ነው።

    የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ወዘተ… በዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ የማረሚያ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። የአዲስ አበባ መስተዳደር ለዚህ ጉዳይ ፈቃድ የሰጠ መሆኑን ጋዜጠኞች እባካችሁ አጣሩልን። ሥራችሁን ብትሠሩ ጥሩ ነው። ‘በአዳራሽ ስብሰባ ከልክሎ በአደባባይ እንዴት ፈቀዳችሁ?’ በሉልን፤ የዚህ ዓይነት ድርጊት “ብልግና” ነው በሏቸው።

    ግርማ ሰይፉ ማሩ

    አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራር አባል (የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ አባል) ሲሆኑ፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በቸኛው ተቃዋሚ አባል በመሆን አገልግለዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ

    Anonymous
    Inactive

    የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ሃሳብ ሊደገፍ የሚገባው ነው
    የሺዋስ አሠፋ

    ወ/ሮ ሙፈሪሃት የፌደራል መንግሥቱን (ብልፅግና) እና የትግራይ ክልል አስተዳደርን (ህወሓት) መካረር በተመለከተ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የገለፁትን አይቼ በግሌ ጥሩ ጅምር ነው – ይበርቱ ብያለሁ። ስድብ፣ ፉከራ እና ይዋጣልን ሀገርን እና ሕዝብን ምስቅልቅል ውስጥ ከመክተት ውጭ ምንም ፋይዳ የለውም። “እልህ ምላጭ ያስውጣል” እንዲሉ ለራሳችሁም ቢሆን ውስጣችሁን የሚቆራርጥ ከሚሆን በስተቀር አይጠቅምም። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቋራጭ መንገድ የለውም፣ ውይይት/ድርድር ብቻ! በጉልበት/በጠመንጃ የሚሆን ቢሆን ኢትዮጵያን የሚቀድም ባልነበረም ነበር። ልብ በሉ ለውይይት አሻፈረኝ የሚሉ ወገኖች በስተመጨረሻ ቢፈልጉ አያገኙትም፤ ምክንያቱም አይበለው እንጂ ጦርነትም ቢሆን መቋጫው ውይይት/ድርድር ነው።

    በ2009 ዓ.ም ራሳቸው ወ/ሮ ሙፈሪሃት የነበሩበትን የፓርቲዎች ውይይት/ድርድር (ስያሜው ራሱ አወዛጋቢ ነበር) ባስታውሳቸው ጠቃሚ የሚሆን ይመስለኛል። ሙከራው የተቀጨው ከጅምሩ ነበር። የቀድሞ ገዢ ፓርቲን ጨምሮ 22 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት ውይይት/ድርድር የመሀል ዳኛ (mediators) ያስፈልጋሉ/አያስፈልጉም በሚለው የጦፈ ክርክር ተደርጎ ኢህአዴግ እና ሌላ አሁን ስሙን የማላስታውሰው አንድ ፓርቲ አያስፈልግም ሲሉ 20 ፓርቲዎች ያስፈልጋል ብለን በከፍተኛ ቁጥር አሸነፍን፣ mediators ሊሆኑ የሚችሉትን ወገኖች የሥራ ልምድና የትምህርት ደረጃ መግለጫ (ማለትም፥ CV) እና ዝርዝር ማዘጋጀት ጀመርን።

    በዚህ የተናደዱት የሂደቱ ፊትአውራሪ የነበሩት የተከበሩ አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ [የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል] ለሳምንት እንደገና እንየው ብለው በተኑት። በሳምንቱ ራሳቸው አጀንዳውን አንስተው mediators ያስፈልጋሉ/አያስፈልጉም እጅ አውጡ ሲሉ ጠየቁ። ከመድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ውጭ ሁሉም አያስፈልጉም አሉ። በሳምንት ልዩነት 20 ለ 2 ውጤቱ ሲገለበጥ ወ/ሮ ሙፈሪሃት እጃቸውን በአፋቸው ጭነው ይታዘቡ ነበር።  እኔም በጣም ተበሳጭቼ “የተከበሩ አቶ አስመላሽ! ሳምንቱን ሙሉ ሲደልሉና ሲያስፈራሩ ሰንብተው ውጤቱን በጉልበት አስቀየሩት! ይሄ ጉልበት ግን አይቀጥልም፤ ነገ በሌላ ጉልበት ይሰበራል!” ብዬ ትቻቸው ወጣሁ። ሂደቱም ተጨናግፎ ቀረ (በወቅቱ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ዘግቦታል)። ከ3 ዓመታት በኋላ እነአቶ አስመላሽን ወክለው አቶ አዲስዓለም ባሌማ ሁሉን አካታች ውይይት/ድርድር እናድርግ ብለው ሲጠይቁም፣ ያልተገባ ምላሽ ሲሰጣቸውም በተራዬ በትዝብት ተመለከትኩ።

    ዛሬ የመንግሥት አካል ከሆነው የሰላም ሚኒስትር መፍትሄው ውይይት/ድርድር ነው የሚል ተነሳሽነት ሲመጣ አያስፈልግም ብሎ መታበይም ሆነ ተለመንኩ ብሎ ማጣጣል አይገባም። ሚኒስትሯ እንዳሉት፥ ከስሜት ወጥቶ፣ ሰከን ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። በእኔ እምነት ይሄ ትልቅ እርምጃ ነው፤ ቀጣዩን ታሪክ ለመሥራት መሽቀዳደም ለኢትዮጵያ ውለታ ነውና ማን ይሆን ፈጥኖ ወደ መቀሌ ከተማ ወይም ወደ ወለጋ ጫካዎች ነጭ ባንዲራ ይዞ የሚዘምተው? (የኬንያው Building Bridges Initiative (BBI) ጥሩ መማሪያ ይሆነናል) ወይም ወደአዱ ገነት የሚመጣው? የወጣቶቻችንን ህይወት ከመቀጠፍ፣ የእናቶቻችንን እንባ ከመፍሰስ የሚታደገው? ከፌደሬሽን ምክር ቤት? ከሰላም ሚኒስትር? ከሀይማኖት አባቶች? ከእርቀ-ሰላም ኮሚሽን? ከሀገር ሽማግሌዎች? ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች? ከአባ ገዳዎች? ከጋሞ አባቶች? እናቶች? ከወጣቶች? ከህፃናት?… ማን ይሆን በሞራል ልዕልና እና በመንፈስ ከፍታ ቆሞ ከኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የሚጥመለመለውን የጥላቻ አውሎ ነፋስ ገስፆ የሚያስቆመው? እስኪ “እኔ አለሁ” በሉ! (እኔ እንዳልሞክር ፓርቲ ውስጥ መሆን ይሄን ነፃነት አይሰጥም) ግን ኢትዮጵያ የሰው ድሃ አይደለችምና ፍጠኑ። ሰላም!

    የሺዋስ አሠፋ

    አቶ የሺዋስ አሠፋ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)  ሊቀ መንበር ሲሆኑ፤ ከዚያ በፊት ደግሞ የቀድሞው ሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ነበሩ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ የሺዋስ አሠፋ

    Anonymous
    Inactive

    የምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል!
    ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫ

    በኢትዮጵያ ሕዝብ የረዥም ጊዜ መራራ ትግል 2010 ዓ.ም ላይ የመጣው ለውጥ ሕዝቡ ከነበረው ተስፋ በተቃራኒ የመክሸፍ አደጋ አጋጥሞታል።

    ከእንግዲህ በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን፣ የዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፥ በእርግጠኝነት ደጋግሞ ቃል በመግባት ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረው የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ለሕዝብ የገባቸውን ቃሎች ሁሉ በማጠፍ የለየለት አምባገነናዊ መንግሥት መሆን ጀምሯል።

    በዚህም ምክንያት የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ክፉኛ የሚፈታተንና የሀገሪቱን አጠቃላይ ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረትና ቀውስ በሀገራችን ተከስቷል። በብዙ ዜጎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ መክሸፉና ሀገሪቱ ተመልሳ በሌላ አምባገነናዊ ሥርዓት ስር መውደቋ እጅግ ልብ የሚሰብር አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም፥ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሀገራችንን ከውድቀት ለማዳን ዛሬም ዕድሉ በእጃችን ነው ብሎ ያምናል።

    ይህ ከውድቀት የመዳን እድል እውን ሊሆን የሚችለውም በአንድ ገዥ ፓርቲ የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት፣ ወይንም ባለፉት 27 ዓመታት ያየነው ዓይነት ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ አይደለም።

    በኢዴፓ እምነት ከዚህ አሳሳቢ የህልውና አደጋ ወጥተን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመሸጋገር ቢያንስ የሚከተሉት አራት ተጨባጭ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ብለን እናምናለን፤

    1. በሀገራችን የሕግ የበላይነት የመጥፋት ችግር እጅግ አሳሳቢ ወደ ሆነ የከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው። በኢዴፓ አመራር በአቶ ልደቱ አያሌው እና በሌሎችም የፖለቲካ ሰዎች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲሆን እንደታየው ሰዎች በፈጠራ ክስ ያለአግባብ የሚንገላቱበትና የፍርድ ቤቶች ውሳኔና ትዕዛዝ የማይከበርበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ያለ ፍርድ ቤት ነፃነት በአንድ ሀገር ላይ የሕግ የበላይነት ሊከበር ስለማይችል ፍርድ ቤቶችን ለፖለቲካ ጉዳይ ለመጠቀም፤ እና የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመጣስ እየተፈፀመ ያለው ሕገ-ወጥ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም አለበት።
    2. በአሁኑ ወቅት የኢዴፓ/አብሮነት፣ የኦፌኮ፣ የኦነግና የባልደራስ ከፍተኛ ዓመራሮች፣ እንዲሁም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች /በተለይም በኦሮሚያ ክልል/ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ስለሚገኙ በሀገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ነግሷል። ይህ አሳሳቢ ውጥረት ወደ ሌላ አሳሳቢ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ሁሉም ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው።
    3. ሀገራችን በዚህ ዓይነት የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ሆና በፍፁም ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ መታሰብ የለበትም። ከአሁን ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሀገራዊ ምርጫ ድረስ ሀገሪቱ እንዴት ትተዳደር? ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ምን ዓይነት ውይይት እና ድርድር ይካሄድ? ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ያለው የፖለቲካ ውጥረት እንዴት ይርገብ? ሀገሪቱ ቋሚ መንግሥት እስከሚኖራት ድረስ የኢኮኖሚ ደህንነቷን የሚያስጠብቅ ምን ዓይነት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል? ያልለየለትን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በተመለከተ ምን ልናደርግ ይገባል? በሚሉትና በመሳሰሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መፍትሄ ማመንጨት የሚያስችል አንድ ሁሉን አቀፍ የውይይትና የድርድር ሂደት /national dialogue / በአስቸኳይ መጀመር አለበት።
    4. በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል እየታየ ያለው ተገቢ ያልሆነና አሳሳቢ ፍጥጫ በአስቸኳይ መቆም አለበት። ጉዳዩ ከሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ እንደምታ ያለው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በውይይትና በድርድር መፈታት አለበት።

    በአጠቃላይ እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ሳይችሉ ከቀሩና በሀገሪቱ ላይ የሚታየው ውጥረት የበለጠ ተባብሶ በዜጎችና በሀገር ላይ ለሚደርሰው ለማንኛውም የከፋ ጉዳት ዋናው ተጠያቂ ብልፅግና ፓርቲ መሆኑን እንገልፃለን። ከማንም በላይ የጉዳዩ እና የሀገሪቱ ባለቤት ሕዝቡ ነውና ከፍ ሲል የዘረዘርናቸው ጥያቄዎች በአስቸኳይ ተገቢ ምላሽ አግኝተው ሀገራችን ከውድቀት እንድትድን ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በብልፅግና ፓርቲ ላይ ሕጋዊ እና ሰላማዊ ተፅዕኖ እንዲያደርግ ኢዴፓ ጥሪውን ያቀርባል።

    የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
    ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
    አዲስ አበባ

    የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)

    Anonymous
    Inactive

    በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ ይቆጠራል
    አንዱዓለም አራጌ

    ከዚህ ቀደም በጣም በአመዛኙ የፓርቲዬን አቋም ካልሆነ በስተቀር እምብዛም የግል አቋሜን አንፀባርቄ አላውቅም።

    ብዙውን ጊዜ ተቋሞቻችን ሕጸጻቸውን እያረሙ ሁላችንም የምንደገፍባቸው ተቋማት እንዲሆኑ እድልም ሆነ ጊዜ መስጠት ተገቢ መሆኑን አምናለሁ። ይሁን እንጂ፥ ትናንት የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፍስና በስጋው ተወራርዶ መራር ሕዝባዊ ትግል ያደረገው ዝቅ ብለን የምንመለከተውን ዓይነት ግፍ ለማስተናገድ አለመሆኑ እሙን ነው።

    በ1993 ዓ.ም በጊዮርጊስ የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት በተለያዩ ሁለት ችሎቶች፣ በተመሳሳይ ዕለት፣ በተመሳሳይ ሰዓት የተፈፀሙ ሁለት ውሳኔወችን ለማስታወስ እወዳለሁ። አንደኛው ችሎት በሀቪየስ ኮርፐስ (habeas corpus) ክስ አማካኝነት፣ እነአቶ ታምራት ታረቀኝን ካሰረበት አምጥቶ ለፍርድ ቤቱ ያቀርብ ዘንድ ፓሊስን ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ቢያዝም፥ ትዕዛዙ ባለመፈፀሙ በወቅቱ የፍትህ ሚንስትር የነበሩት አቶ ወረደወልድ ወልዴ ታስረው እንዲቀርቡ ባዘዘው መሠረት ታስረው ቀረቡ። ፍርድ ቤቱም የአንድ ወር እሥራት ፈረደባቸው። በሌላ ደግሞ የዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ችሎት አቶ ስዬ አብርሃ ቀርበው የወ/ት ብርቱካን ችሎት አርነት ሰደዳቸው። ይሁን እንጂ ለቤታቸው ሊበቁ የተገባቸው አቶ ስዬ አብርሃ በአፈሙዝ አስገዳጅነት ወህኒ እንዲወርዱ ተገደዱ። ሚኒስትር ወረደወልድ ወልዴ ደግሞ ሳይገባቸው ለሞቀ ቤታቸው በቁ።

    ይህን የሃያ ዓመት ታሪክ ያለምክንያት አላነሳሁትም። ከእልህ አስጨራሽ ሕዝባዊ ትግል በኋላ የለውጥ ሽራፊ ለማየት ብንጓጓም ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ለከት ያጣ ግፍ እያስተናገድን ነው። በ”ለውጡ” የመጀመሪያ ወራት ሕዝቡ የተራበ አንጀቱን አስሮ ይስቅ የነበረው፣ ድጋፉንም የቸረው ከእንግዲህ በፍትህ፣ በእውነትና በእኩልነት የምጠግብበት ዘመን ጠባ ብሎ በማመኑ ይመስለኛል። ከፈጣሪ በታች ተስፋችን በእጃችን መሆኑ የቀትር ያህል ግልፅ ቢሆንም፣ ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ የፍትህን መጨንገፍን ሳይ ጥልቅ ሀዘን አልተሰማኝም ብል ግን እውነቱን አልናገርም።

    በቅርቡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሥራ አስፈፃሚ አባል ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ ፍርድ ቤት የዋስትና መብቷን ቢያከብርላትም፥ ፓሊስ ላለመልቀቅ ያሳየውን ዳተኝነት እናስታውሳለን። በተመሳሳይ የአሥራት ቴሌብዥን ጋዜጠኞችንም እንዲሁ በመከራ መልቀቁ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

    ዛሬ ብዕሬን እንዳነሳ ያደረገኝ ጉዳይ የአቶ ልደቱ አያሌው ጉዳይ ነው። ስለአቶ ልደቱ ከእኔ በላይ ብዙ ነገሮችን አጣቅሶ ማቅረብ የሚችል ሌላ ማን እንዳለ በእውነት አላውቅም። በፓርቲዬም ላይ ቢሆን በተደጋጋሚ ምን ያደርጉ እንደነበር ፈፅሞ ዘንግቼው አይደለም። አቋማቸው ከአቋሜ ስለገጠመም አይደለም። ይልቅስ አቶ ልደቱ እራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት በዚህ ሁኔታ አንዳች አሉታዊ ጉዳይ አንስቼ እሞግታቸው ዘንድ ፈፅሞ ህሊናዬ አይፈቅድልኝም።

    በተወሰነ መልኩ የቀደመውን ለአንባቢ ያስታወስኩትም ቢሆን፥ የቆምኩበትን የሀሳብ ማዕዘን ለማሳየት ይረዳኝ ዘንድ ግድ ሆኖብኝ እንጂ ምቾት ተሰምቶኝ አይደለም። ይልቅስ ከላይ ከፍ ብዬ ከጠቀስኳቸው ወገኖቻችንም በከፋ ሁኔታ የ“ፓሊስ ጢባጢቤ” መጫወቻ ሆነው ሳይ፥ እርሳቸውን የወጋ ጦር እኔንም እንደወጋኝ ተሰምቶኛል። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር እንዲለቀቁ ቢያዙም በፓሊስ እንቢተኝነት ግን በእስር ላይ ይገኛሉ። ውርደቱ፣ መረገጡ፣ ንቀቱና ኢፍትሃዊነቱ፣ የኢፍትሃዊነትን ስቃይ ለምናውቅ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ነው። በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ የሚጠራጠር ካለ እርሱ ፍፁም ማስተዋል የጎደለው ነው።

    በኢትዮጵያችን እየታየ ያለው ለከት ያጣ ግፍ ቅስም የሚሰብርና በምንም ዓይነት መንገድ ልንታገሰው የማይገባ ኢፍትሃዊ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ያዋረደ ወደር-አልባ የነውረኝነት ተግባርም ነው።

    በፈጣሪ እንደምትታመኑ ደጋግማችሁ የነገራችሁን ወገኖች፥ በሚፈፀመው ግፍ ፈጣሪ የሚደሰትበት ይመስላችኋል? የሚሠራውን ኢፍትሃዊነት በአስቸኳይ እስካላስቆማችሁ የፈጣሪም ሆነ የሕዝብም ቁጣ እሩቅ እንደማይሆን ለመናገር ነቢይነትን አይጠይቅም።

    Free Lidetu Ayalew
    አንዱዓለም አራጌ

    አቶ አንዱዓለም አራጌ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምክትል መሪ ሲሆኑ፤ ከዚያ በፊት ደግሞ የቀድሞው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ፕሬስ ሴክሬተሪ ነበሩ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ አንዱዓለም አራጌ

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 40 total)