-
Search Results
-
ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ ላይ ጉዳት አድርሰውብኛል በሚል በመሠረተው የ174.6 ሚሊዮን ብር ክስ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ።
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን ጋዜጣ) – የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ (HERQA) እንዲሁም አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ በድርጅቱ ላይ ላደረሱትና ለሚደርሰው ጉዳት የ174.6 ሚሊዮን ብር ተከፍሎ እስከሚያልቅ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር ክስ እንዳቀረበባቸውና ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ፍርድ ቤት እንደቀርቡ ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ጥምረት ለተሻለ ጤና) /ABH Partners/ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፥ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከማምራቱ በፊት ኤጀንሲው የድርጅቱን መልካም ሥምና ዝናን በማጠልሸቱ ይቅርታ እንዲጠይቅና ችግሩን እንዲያርም ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም።
በዚህም ድርጅቱ ነሐሴ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ-ብሔር ስድስተኛ ምድብ ችሎት የመዝገብ ቁጥር 241863 ክስ ለመመሥረት ተገዷል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴን ጨምሮ አምስት የሥራ ኃላፊዎችም ተከሰዋል።
ኤጀንሲው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) ጋር በጥምረት የሚሠሩትን ሥራ እንደማያውቀው ቢያስተባብልም፤ ሁለቱ ተቋማት ውል ተፈራርመው ሥራውን ሲጀምሩ በወቅቱ የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በቦታው ተገኝተው መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተው እንደነበር ዶ/ር ማርቆስ አስታውሰው፤ “ይህም መንግሥት አያውቀውም የሚለውን ሐሳብ ትክክል እንዳልሆነ አመላካች ነው። ከወራት በፊት ትምህርት የሚሰጥበትን ቦታ ተገኝተው የጎበኙ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታዎች ግን ‘ሥራው የዩኒቨርሲቲውን አቅም ለማዳበር ያገዘ ነው’ ሲሉ አሞካሽተውታል። ለጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመስጠት የመምህራን ፍልሰት እንዲቀንስ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱንና ለትምህርት ጥራት እንዲተጋ የሚያግዙ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ሚኒስቴሩ ምስክርነቱን በደብዳቤ ሰጥቷል” ብለዋል።
ሚኒስቴሩ፥ የዚህ መሰል የግሉ ዘርፍና የመንግሥት አጋርነት ለትምህርት ጥራትም ሆነ ተደራሽነት ሚናው የላቀ መሆኑን በመግለጽ፥ ለዚህ ሊበረታታ ለሚገባው ድርጅት አገራዊ ፋይዳውን በማየት የግንባታ መሬት በመስጠት ትብብር እንዲደረግላቸው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የትብብር ደብዳቤ እንደፃፈላቸውም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴሩ ለዩኒቨርሲቲውና ለድርጅቱ ምስክርነት በመስጠት ከመንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ሲያደርግ፥ ኤጀንሲው ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 ከሰጠው ሥልጣን ውጪ “ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ በአዲስ አበባ የሚሰጠው ትምህርት ዕውቅና የለውም፤ ሕጋዊም አይደለም” በማለት እግድ ማስተላለፉ “ባለፉት ሰባት ዓመታት የት ነበረ?” የሚል ጥያቄንም የሚጭር እንደሆነ ዶ/ር ማርቆስ አብራርተዋል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሥራውን ሊሰራ፤ አማካሪ ድርጅቱ ደግሞ አስተዳደራዊ ድጋፍ ሊሰጥ በገቡት ስምምነት መሠረት ዩኒቨርሲቲው አዲስ አበባ ባለው ካምፓስ ምንም ዓይነት የመንግሥት ድጋፍ ሳይደረግለት ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሙሉ ድጋፍ በማድረግ ለመማር-ማስተማሩ አስፈላጊ ግብዓቶችን አሟልቶ በውሉ መሠረት ግዴታውን ሲወጣ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ ማስተማርም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር መሥራት እንደማይችል ኤጀንሲው ቢገልጽም፣ በዩኒቨርሲቲው እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 ግን ዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ከሚገኝበት ጅማ ከተማ ውጪ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን እንዲሁም የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ሊያቋቁም እንደሚችል ተደንግጓል።
በተመሳሳይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸውን ለማሟላት ድጋፍ ሊሰጣቸው ከሚችል ከማንኛውም ተቋም ጋር መሥራት እንደሚችሉ ይደነግጋል። በዚህም በአዋጁ ያልተከለከለን ሥልጣን ኤጀንሲው በደብዳቤ መሻሩ ተገቢነት እንደሌለው ዶ/ር ማርቆስ ገልፀዋል። በመሆኑም ለቀጣይ የትምህርት ዘመን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንና ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች በሁኔታው መደናገጥ እንደማይገባቸው ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ (ቁጥር 650/2001) አንቀጽ 93፣ ንዑስ አንቀጽ አንድ አገልግሎት በሌሎች ወገኖች እንዲሰጥ ስለማድረግ ይደነግጋል። በዚህም ማንኛውም የመንግሥት ተቋም ተገቢና ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ሆኖ ሲያገኘው የድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን በሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች እንዲሰጥ ሊያደርግ እንደሚችል አስቀምጧል።
በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ (ቁጥር 240/2003) በአንቀጽ ሦስት መሠረት የዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ጅማ ከተማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን፣ የምርምርና የሕብረተሰብ አገልግሎት ማዕከሎችን ሊያቋቁም እንደሚችል ተቀምጧል።
ባለፉት 15 ቀናት ኤጀንሲው “የትብብር ሥልጠና ትክክል ባለመሆኑ እንዲያቆሙ” በሚል ሚኒስቴሩ በደብዳቤ ማሳወቁን መግለጹ ይታወሳል። በዚህ መልኩ ሲሠሩ የነበሩ የጅማ፣ የደብረ ማርቆስ፣ የባህር ዳር እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች እንደታገዱ አሳውቋል።
ሆኖም ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሥራቸውን በመቀጠላቸው “አደብ ሊገዙ ይገባል” ብሎም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ኤጀንሲው በተቋማቱ በመማር ላይ ያሉትን ተማሪዎች ዝርዝር እንዲላክለት የጠየቀ ሲሆን፤ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ ግን ቀጣይ ውይይት እንደሚያስፈልገው አሳውቆ ነበር።
ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲና የክልል ትምህርት ቢሮዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ላይ ውሳኔ ላይ ከመደረሳቸው በፊት በፈተናው ያጋጠመውን ችግር ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲመረምር መቆየቱን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ውሳኔ አሳለፈ።
ሚኒስቴሩ በተፈተኞች ወጤት መሰረት እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ባደረገው ጥናት ማረጋገጡንም አስታውቋል።
የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ (NEAEA) እና የክልል ትምህርት ቢሮዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ በፈተናው ያጋጠመውን ችግር ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲመረምር መቆየቱን ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት በተፈጥሮ ሳይንስ (natural science) እና ማኅበራዊ ሳይንስ (social science.) መስኮች ሰኔ 6 እና 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ፈተናቸው የተሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ታሳቢ የተደረጉ ሲሆን ሰኔ 10 እና 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡ ፈተናዎች ውጤቶች ግን ተሰርዘዋል።
ሰኔ 6 እና 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ እንዲያገለግሉ የተወሰነው ሂሳብ፣ እንግሊዝኛ፣ ፊዚክስ፣ አፕቲትዩድ እና ጂኦግራፊ የትምህርት ዓይነቶች ናቸው።
ሰኔ 10 እና 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡ ፈተናዎች ከግምት ውስጥ ያልገቡት እጅግ የጋሸበ ውጤት የተመዘገበባቸው በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- NEAEA: የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ይፋ ሆነ
- አሶሳ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ የትምህርት ዘመን ሰላማዊ ለማድረግ ተዘጋጅቷል
- ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
- አድማስ ዩኒቨርስቲ አይ ኤስ ኦ የምስክር ወረቀት (ISO Certificate) ለማግኘት የሚያስችል ሥራ እየሠራ መሆኑን ገለጸ
- የአስረኛ ክፍል አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንደሚቀርና የሁለተኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ይሆናል
Topic: 7ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ሥነ ሥርዓት ተካሔደ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ዘንድሮ ለሰባተኛ የተለያዩ ኢትዮጵያውያንን የሸለመው የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት ሥነ ሥርዓት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ (ካዛንችስ፣ አዲስ አበባ) ተካሂዷል።
በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማንን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
ለዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት በዘጠኝ ዘርፎች 291 ሰዎች ከሕዝብ ዘንድ ተጠቁመው የነበረ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 27ቱ ተመርጠው ለመጨረሻ ዕጩነት (በዘጠኝ ዘርፎች፣ በእያንዳንዱ ዘርፍ ሦስት ሦስት ዕጩዎች) ቀርበው ኢትዮጵያውያን አሸናፊዎችን እንዲመርጡ ተደርጎ ነበር።
ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በእያንዳንዱ ዘርፍ ከቀረቡት ዕጩዎች ውስጥ የመጨረሻ ተሸላሚዎች ይፋ ተደርገዋል። በዚህም መሠረት አሸናፊዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
በመምህርነት ዘርፍ
- ወ/ሮ ህይወት ወልደመስቀል
በሳይንስ (ህክምና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ምህንድስና፣ ኬሚስትሪ፣ አርክቴክቸር፣ ወዘተ)
- ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሴ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በ አትክልት ምርምር ፕሮፌሰር፣ የጎለሌ ዕፅዋት ማዕከል የበላይ ኃላፊ፣ በሀገረ እንግሊዝ የተከበረው KEW International ሜዳል ተሸላሚ)
በኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ እና በፎቶ ግራፍ ዘርፍ
- አቶ በዛብህ አብተው (ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የስፖርት ፎቶግራፍ አንሺ)
በበጎ አድራጎት (እርዳታ እና ሰብዓዊ አገልግሎቶች)
- አቶ አብድላዚዝ አህመድ
በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ
- አቶ ነጋ ቦንገር (የነጋ ቦንገር ሆቴል፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ የንግድ ተቋማት ምሥራች እና ባለቤት)
በመንግሥታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት
- አቶ ግርማ ወንዳፍራሽ
በቅርስና ባህል ዘርፍ
- አቶ አብዱልፈታህ አብደላ (የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የባህላዊ ዳኝነትና የፍትህ ሥርዓቶችን በመጻፍ የሚታወቁ)
በሚዲያና ጋዜጠኝነት
በኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች
- አቶ ኦባንግ ሜቶ (ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) መሥራች እና ሊቀ-መንበር)
የሰባተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ የክብር ተሸላሚዎች
- የጋሞ ሽማግሌዎች (በቡራዩ የተከሰተውን ግድያ በመቃወም በአርባ ምንጫ የተቃውሞ ሠልፍ ላይ፣ በቁጣ ንብረት ለማውደም የቃጡ ወጣቶች እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ አንደ አካባቢው ባሕል ሣር ይዘው በአካላቸው ቆመው ንብረቱን ከጥፋት የተከላከሉት የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ነበሩ።)
በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚዎችን እንኳን ደስ አላቸሁ ብለዋል። ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ የምትገነባ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቷ፥ የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚዎች ለነገው ትውልድ ተረካቢዎች አርዓያ የሚሆን ሥራ በመሥራታቸው ሊደነቁ ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በ2005 ዓ.ም. በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተቋቋመው የበጎ ሰው ሽልማት ዋና ዓላማ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵይውያን በጎ ሥራን የሠሩ እና ለሌሎች አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ማበረታታት እና ዕውቅና መስጠት ነው።
አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የ2012 ዓ.ም. ነባርም ሆነ አዲስ ተማሪዎች ላይ በጠቅላላ የመማር-ማስተማር ሂደት ሰላማዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎችን በማሳተፍ ውይይት እንደሚካሄድ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት አስታውቀዋል።
አሶሳ (ኢዜአ) – አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የመማር-ማስተማር ሒደቱን ሰላማዊ ለማድረግ የሚረዱትን ቅድመ ዝግጅቶች ማጠናቀቁን አስታወቀ።
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲው በ2011 ዓ.ም. የትምህር ዘመን በተከሰተ ግጭት የሶስት ተማሪዎች ህይወት ሲያልፍ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ይታወሳል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ከማል አብዱራሂም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለፁት፥ ከዚህ በፊት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎችን በወቅቱ ምላሽ አለመስጠት ለግጭት መፈጠር ምክንያት ተደርጎ ይጠቀስ ነበር።
በደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጥፋት የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በእጅጉ ማዘኑን የገለፁት ፕሬዝዳቱ፥ ችግሩ እንዳይደገም በመምህራንና በተማሪዎች ቅንጅት የሚተገበር ጠንካራ ዕቅድ አዘጋጅቷል።
በዕቅዱ መሠረት የዩኒቨርሲቲው የ2012 ዓ.ም. ነባርም ሆነ አዲስ ተማሪዎች ላይ በጠቅላላ የመማር-ማስተማር ሂደት ሰላማዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎችን በማሳተፍ ውይይት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
ተማሪዎች በግጭት ላለመሳተፍ ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው የጋራ መግባቢያ ሰነድ ላይ እንደሚፈራረሙም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ባለፈው የትምህርት ዘመን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን (social media) የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት በዩኒቨርሲቲው ግቢ ግጭት እንዲባባስ የሚጥሩ በርካታ መምህራን ነበሩ።
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ፖለቲካን ከትምህርት የመነጠል ሥራ ጀምረናል ያሉት ዶ/ር ከማል፥ ይህንን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ከችግሩ የተነካኩ አንዳንድ መምህራን በፈቃዳቸው የዝውውርና የሥራ መልቀቂያ እያቀረቡ ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው ውስጣዊ ችግር ምክንያት ግጭት ዳግም ይከሰታል ብለን አናምንም የሚሉት ዶክተር ከማል፥ የተማሪዎች መማክርት አደረጃጀት፣ ምግብ፣ መኝታ፣ ኢንተርኔትን መሠል የተማሪዎችን ጥያቄዎችን መመለስ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።
ከሠላማዊ የመማር ማስተማር ተግባር ባሻገር አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት (research and community services) እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ማስጠብቅ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው የክረምት ትምህርት እየተከታተሉ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል በኬሚስትሪ የ1ኛ ዓመት የክረምት ተማሪ ለማ ታገሰ በሰጠው አስተያየት የዩኒቨርሲቲ የጸጥታ የተረጋጋ ነው። አልፎ አልፎ የምግብ አቅርቦት ችግር እንዳለበት ጠቅሶ የመጸዳጃ ቤትና ተያየዥ አገልግሎቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ጠቁሟል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አቶ ርስቱ ይርዳው በሹመት ንግግራቸው “ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ያጋጠሙ ውስብስብ ችግሮች መፍትሔ በሚሹበት ሰዓት ቢሆንም፤ የሕዝቦችን ኃላፊነት በመቀበሌ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።
ሀዋሳ (ሰሞነኛ) – የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዘጠነኛ መደበኛ ጉበኤው የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመሾምና ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በማጽደቅ ተጠናቀቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ ከገመገመ በኋላ የርዕሰ መስተዳድር ለውጥ እንዲደረግ በወሰነው መሠረት አቶ ርስቱ ይርዳው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እንዲመሩ ሾሟቸዋል።
በተጨማሪም ደኢህዴን ለ2012 በጀት ዓመት 40 ቢልዮን 56 ሚሊዮን 938 ሺህ 826 ብር አጽድቋል። በጀቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ3 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው።
የበጀቱ ምንጭ ከፌዴራል መንግሥት ድጎማ፣ ከውጭ እርዳታና ከክልሉ ገቢ እንደሚሰበሰብ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምራት ዲላ ገልጸዋል።
አቶ ርስቱ ይርዳው በሹመት ንግግራቸው ጥፋተኞችን ለሕግ ማቅረብና ሠላምን ማስፈን ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል። በመልዕክታቸው “ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ያጋጠሙ ውስብስብ ችግሮች መፍትሔ በሚሹበት ሰዓት ቢሆንም፤ የሕዝቦችን ኃላፊነት በመቀበሌ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።
ከደኢህዴን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጣሉባቸውን እምነት፣ ሁሉንም በእኩል ዓይን በማገልገል ለመወጣት ቅን ፍላጎት እንዳላቸው አቶ ርስቱ ይርዳው ገልፀዋል።
በክልሉ የተነሱ የክልልነትና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ለክልሉና ለደህኢዴን ከባድ ፈተና ስለመሆናቸው ያነሱት አቶ ርስቱ፥ የተፈጠሩትም ሁከቶች ከባድ ጉዳት ያደረሱና የአብሮነት ሕልውናን የተፈታተኑ ነበሩ ብለዋል።
በክልሉ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ ሰላም የማስፈንና ጥፋተኞችን ለሕግ ማቅረብ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ መሆናቸውንም አቶ ርስቱ ገልፀዋል።
አቶ ርስቱ በሹመት ንግግራቸው “የብሔር ፅንፈኝነትን፣ የሀይማኖት አክራሪነትን እና ሕገ ወጥነት ለመከላከል ጠንካራ ሥራ ይሠራል” ብለዋል።
የአመራር ማስተካካያዎችም በጥብቅ ትኩረት እንደሚከናወንም ነው አቶ ርስቱ በንግግራቸው ያስገነዘቡት።የኑሮ ውድነትንና ሥራ አጥነትን ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠራ የተናገሩት አቶ ርስቱ፥ ከባለሀብቶች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎት በመግለፅ፣ የእንደጋገፍ ጥሪ ለባለ ሀብቶቹ አቅርበዋል።
አቶ ርስቱ ይርዳው ከ1985 እስከ 2001 ዓ.ም. በክልሉ ጉራጌ ዞን ከወረዳ አመራርነት እስከ ዞን አስተዳዳሪነት ያገለገሉ ሲሆን፤ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ የደኢህዴን ሥራ አስፈፃሚ እና በፌደራል ደረጃ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በአገራችን ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ በመከላከል እና ቢከሰቱም እንኳን የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸዉ በፊት በአፋጣኝና በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ረገድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዓይነተኛ ሚናን መጫወት ችሏል።
አዲስ አበባ (ኢመደኤ) – የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ባሳለፍነዉ 2011 በጀት ዓመት በተለያዩ ቁልፍ የሀገሪቱ ተቋማት እና መሠረተ ልማቶች ላይ ሊፈጸሙ የነበሩ 791 የሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶችን (cyber-attacks) ማክሸፍ መቻሉን ገለጸ።
በኢመደኤ የኢትዮጵያ ሳይበር የድንገተኛ ዝግጁነት እና ምላሽ ሰጪ ዲቪዥን (Ethiopian Cyber Emergency Readiness & Response Team – ETHIO CERT) ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም ገብረጻዲቅ እንደገለጹት፥ በአገራችን ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ በመከላከል እና ቢከሰቱም እንኳን የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸዉ በፊት በአፋጣኝና በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ረገድ ኢመደኤ ዓይነተኛ ሚናን መጫወት መቻሉን ገልጸዋል። ኃላፊዉ ጨምረዉ እንደገለጹት በ2011 በጀት ዓመት በአገሪቱ ላይ የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ መከላከል በመቻሉ ሊደርስ ከነበረው የደኅንነት እና የገንዘብ ኪሳራ በድምሩ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማዳን መቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ ከዚህም በላይ በገንዘብ የማይተመን ሰላምን እና ፍትህ ማስጠበቅ ተችሏል ብለዋል። በቀጣይ 2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት አገራዊ የሳይበር ጥቃትን የመከላከል ሽፋን በማሳደግ እና ዓለም አቀፍ ትስስርንና ቅንጅትን በማጠናከር የአገሪቱን ቁልፍ የሳይበር መሠረት ልማቶችን ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ እንደሚሠራም ኃላፊዉ ገልጸዋል።
በኢመደኤ የኢትዮጵያ ሳይበር የድንገተኛ ዝግጁነት እና ምላሽ ሰጪ ዲቪዥን በኢትዮጵያ የሳይበር ሥነ-ምህዳር የሚገኙ የሳይበር መኃረተ ልማቶችን ከጥቃት ከመከላከልና ምላሽ ከመስጠት ባለፈ የሳይበር ደህንነት ክፍተት ትንተና (vulnerabilities) በማከናወን የሳይበር ጥቃት አስቀድሞ የመከላከል፣ የሳይበር ጥቃቶች ከመፈጠራቸው በፊት የማስቀረት፣ የተፈጠሩት ሳይበር ጥቃቶች ከጥቃቱ በፊት ይሠሩበት ወደነበረው ይዞታቸው የመመለስ እና በተመሳሳይ ጥቃት እንዳይጠቁ የደኅንነት ክፍተታቸውን እንዲደፈን የማድረግ፤ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የሳይበር ጥቃት መከላከያ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትስስር ሥራዎችን የሚሠራ ክፍል ነዉ።
ምንጭ፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት) – ኤሌክትሪክ ለአንድ ሃገር ሁለንተናዊ የዕድገት እንቅስቃሴ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ይሁን እንጂ ይህንን መሠረታዊ የሆነውን ዘርፍ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ለማዳረስና ተጠቃሚ ለማድረግ እየተደረገ ባለው ጥረት፤ በኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቱ ላይ የሚደረሱ አደጋዎችና ስርቆቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል።
የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት አውታሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጓጉዞ ደንበኞች ጋር የሚደርስበትና ደንበኛው የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የሚረዱ ግብዓቶች ቢሆኑም፤ በሚደርስባቸው ጉዳትና ስርቆት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት (ተቋም) የተጠቃሚውን የኃይል ፍላጎት ለሟሟላት እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድረጎታል።
ትራንስፎርመር ደግሞ ከእነዚህ ግብዓቶች አንዱና መሠረታዊ ነው። ለደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማሰራጨት ሚናው ከፍተኛ ሲሆን፤ የኃይል ፍላጎት ሲጨምር የትራንስፎርመሩን አቅም ለማሳደግ ካልሆነ በስተቀር መነካካት፣ ለማንሳት ወይም ለማንቀሳቀስ መሞከር እጅግ አደገኛ ከመሆኑ በላይ ለንብረትና ህይወት መጥፋት መንስዔ ይሆናል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን ችላ በማለት የስርጭት ትራንስፎርመር ስርቆት በስፋት እየተከናወነ መጥቷል። በዚህም በተቋሙ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰና የአብዛኛው ደንበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት እያስተጓጎለ ይገኛል። ለዚህ ማሳያ ሰሞኑን በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳትና ስርቆት መጥቀስ ይቻላል።
በአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስር በሚገኙት አራት ዲስትሪክቶች መካከል በደቡብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት ሁለት ትራንስፎርመሮች እንዲሁም በምስራቅ አዲስ አበባ ዲስትሪክት 3 ትራንስፎርመርመሮች እና ሌሎችም በርካታ ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሆኑ እና ለሰፊው የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ንብረቶችን ኃላፊነት በጎደላቸው እና የራሳቸውን ኪስ ከመሙላት ባለፈ ለሀገራቸው በማያስቡ ጥቂት ግለሰቦች ተዘርፈዋል።
ዝርፈያው የተፈፀመው ጨለማን ተገን በማድረግና በመስመሩ ላይ ኃይል በማይኖርበት ወቅት በመጠቀም ነው። ይህ በተቋምና ህዝብ ንብረት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ የሚያደርስ ህገወጥ ተግባር ሲሆን፤ ህብተረሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል በአግባቡ እንዳያገኝም የሚያደረግ ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንን አውቆ በአካባቢው የሚገኙ የተቋሙ ብሎም የሀገር ንብረቶች የሆኑቱን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት አውታሮች እንደራሱ ንብረት ሁልጊዜ በንቃት እንዲጠብቅ ተቋሙ ይጠይቃል።
ጥገና የሚያከናውኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋም ባለሞያዎች በመምሰል ንብረቱን የሚነካኩ፣ የሚበጥሱ፣ የሚቀይሩ እና ሌሎች ሕገ-ወጥ ተግባሮችን የሚፈፅሙ ግለሰቦች ሲመለከት ህብረተሰቡ ሊከላከላቸው ይገባል።
የተቋሙ ሠራተኞች ቢሆኑም እንኳን ሕጋዊ መታወቂያ መያዛቸውን፣ መለያ ባጅ (badge) ማድረጋቸውንና የደንብ ልብስ መልበሳቸውን ማረጋገጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግም ያስፈልጋል። እንዲሁም የሚያጠራጥር ሁኔታ ካለ በተቋሙ 905 ነፃ የጥሪ ማዕከል በማሳወቅ፣ በአካባቢው በሚገኝ የተቋሙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በመጠቆምና ከሚመለከተው የህግ አካላት ጋር በጋር በመተበባር ማስቆም እንደሚገባ ተቋሙ ያሳስባል።
የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገዙና የህዝብ ሃብት የፈሰሰባቸው በመሆናቸው፣ ሁሉም ህብረተሰብ እንደራሱ ንብረት ሊጠብቃቸው ይገባል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ሥርዓት አወቃቀር ላይ በሚደረገው ለውጥ ከ1ኛ-6ኛ ክፍል የአንደኛ ደረጃ፤ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል መለስተኛ እንዲሁም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንደሚሰጥ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
አዲስ አባባ (ዶይቼ ቬለ ሬድዮ) – ከመጪው የትምህርት ዓመት (2012 ዓ.ም.) ጀምሮ የአስረኛ ክፍል አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንደሚቀር የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌጤ ተናገሩ።
በአዲሱ የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ-ካርታ መሠረት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው አሠራር ለስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ ፈተና ይሰጣል ተብሏል። የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ነሐሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በትምህርት ፍኖተ-ካርታ ላይ ረዘም ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተብሎ የሚጠራው እና አስረኛ ክፍልን ለሚያጠናቅቁ ተማሪዎች ይሰጥ የነበረው አገር አቀፍ ፈተና ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ እንደማይኖር መናገራቸውን የአዲስ አበባው የዶይቼ ቬለ ሬድዮ ወኪል ዘግቧል።
ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ ይሰጥ በነበረው አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በአብዛኛው ተማሪዎች ዘጠኝ የትምህርት ዓይነቶች ሲፈተኑ ቆይተዋል። በአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አማካኝነት የሚሰጠውን ይኸን ፈተና ያለፉ ተማሪዎች ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ወደ መሰናዶ ትምህርት (preparatory) ይሻገራሉ።
በኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ሥርዓት አወቃቀር ላይ በሚደረገው ለውጥ ከ1ኛ-6ኛ ክፍል የአንደኛ ደረጃ፤ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል መለስተኛ እንዲሁም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ይሰጣል።
በዚህም መሠረት መጀመሪያ ደረጃ አንደኛ ሳይክል (ከ1ኛ ክፍል እስከ 4ኛ ክፍል)፣ መጀመሪያ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል (ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል)፣ ሁለተኛ ደረጃ አንደኛ ሳይክል (9ኛ እና 10ኛ ክፍል) እና ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት (11ኛ እና 12ኛ ክፍል) ተብሎ ሥራ ላይ የነበረው አወቃቀር ይቀየራል።
በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት በክልላዊ መንግሥታት የሚሰጥ የስድስተኛ ክፍል ፈተና እንደሚኖር ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት «መጀመሪያ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል» ተብሎ በሚጠራው ምዕራፍ መጨረሻ ለ8ኛ ክፍል ተማሪዎች በክልሎች የሚሰጠው የሚሰጠው ፈተና ሀገር አቀፍ ይሆናል ተብሏል።
ምንጭ፦ ዶይቼ ቬለ ሬድዮ
“የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ፈተና በገለልተኛ አካል ከሁሉም ክልል ተውጣጥቶ ውጤቱ ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ ሊደረግና የማያዳግም የእርምት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። አንዳንድ ክልሎች ማኅበር አቋቁመው ፈተናው ሠርተው እንደሰጡ ግልፅ መረጃዎች እየወጡ ነው።” ባይቶና ፓርቲ
አዲስ አበባ – የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት በድጋሚ ከሁሉም ክልሎች በተውጣጣ ገለልተኛ አካል ተጣርቶ ይፋ እንዲደረግ እና ከፈተናው ውጤት ጋር በተያያዘ ስህተት በፈፀሙ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የታላቋ ትግራይ ብሄራዊ ኮንግረስ (ባይቶና) ፓርቲ የጠየቀ ሲሆን የክልሉ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ፤ በውጤቱ ላይ ያለውን ቅሬታ አቅርቧል፡፡ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮም ቅሬታ ማቅረቡ ታውቋል።
የዘንድሮ የ12ኛ ከፍል መልቀቂያ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከ350 ነጥብ በላይ ያመጡት 49 ከመቶ መሆናቸውን ገልጾ ውጤቱን ይፋ ያደረገው በትምህርት ሚኒስቴር አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ኤጀንሲ (NEAEA)፤ በዋናነት በስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ፈተና እርምትና ውጤት አሰጣጥ ላይ ስህተት መፈጠሩን ተገንዝቦ፣ እርምት ማድረጉን የገለፀ ሲሆን በሌሎች የትምህርት ዓይነት ውጤቶች ላይ ‹‹ስህተት የለም፤ ቅሬታ ያለው በግል ያቅርብ›› ብሏል።
በርካታ ተማሪዎች የጠበቁትን ውጤት እንዳላገኙ በማመልከት ውጤታቸው በድጋሚ እንዲታይ ቅሬታ ማቅረባቸውንም ምንጮች ለአዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ የጠቆሙ ሲሆን፥ ብሔራዊ የምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በበኩሉ፤ ኮሚቴ አዋቅሮ ቅሬታዎችን መሠረት በማድረግ እያጣራ መሆኑን ገልጿል።
የውጤት አገላለፁን ተከትሎ ቅሬታውን በይፋ ያቀረበው የትግራይ ትምህርት ቢሮ፥ ፈተናው በተሰጠበት ወቅት በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች፣ የፈተና አሰጣጥ ሥነ ምግባር ጉድለት እንደነበርና ይህንንም በወቅቱ ለሚመለከተው አካል መጠቆሙን አስታውቋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ኢንጅነር ገብረመስቀል ካህሳይ፥ ‹‹በክልላችን ፈተናው ሲካሄድ የፈተና አወሳሰድ ሥነ ምግባርን ጠብቆ ነበር፤ ይሁን እንጂ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሥርዓቱን የጠበቀ አይደለም›› ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ይህንን ቅሬታም ለኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር አሳውቀው እንደነበርና ቅሬታው ምላሽ ሳይሰጠው ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል:: ይሄም ኃላፊው፤ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ጠይቋል።
ከወራት በፊት መሠረቱን በትግራይ አድርጎ የተቋቋመው ‹‹ብሄራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ›› (ባይቶና) (‹‹የታላቋ ትግራይ ብሄራዊ ኮንግረስ››) የተሰኘው የፖለቲካ ድርጅት ‹‹ዘንድሮ የተለቀቀው የ12ኛ ክፍል ውጤት ከፍተኛ ብልሽት፣ ዝርክርክ አሰራርና የታየበት ስለሆነ ተቀባይነት የለውም፤ ውጤቱ በድጋሚ በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ ይደረግ ኃላፊዎችም በሕግ ይጠየቁ›› ሲል አሳስቧል።
ባይቶና ከ12ኛ ክፍል የፈተና ውጤት ጋር በተያያዘ የሰጠውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ
ምንጭ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Topic: ደሃን በማጥፋት ድህነትን መዋጋት አይቻልም!
ሴተኛ አዳሪዎች እና የእኔ ቢጤዎች (ለምኖ አዳሪዎች) ላይ መስተዳድሩ ሊወስድ ያሰበው እርምጃ ሰብዓዊነት የጎደለው እና መንግሥት ድህነትን ለማጥፋት በቅድሚያ ማከናወን የሚገባውን ሥራዎች ሠርቶ ሳይጨርስ በድሃ ላይ ለመዝመት ማሰቡ የአስተዳደሩን ብልሹ አተያይ ከወዲሁ የሚያሳይ ነው።
ደሃን በማጥፋት ድህነትን መዋጋት አይቻልም!
(ያሬድ ኃይለማርያም)የአዲስ አበባ መስተዳደር የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሹ በሚል የፈረጃቸውን የእኔ ቢጤዎች እና ሴተኛ አዳሪዎችን ከከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ለማወገድ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ሽር ጉድ እያለ መሆኑን እና ሕግ ያረቀቀ መሆኑን በቅርቡ ገልጿል። ህብር ሬዲዮ እንደገለጸው በመስተዳድሩ የከንቲባው ጽ/ቤት የፕሬስ ጉዳይ ሹም ከፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የአገሪቱን እና የከተማዋን መልካም ገጽታን የሚያበላሹት ከ50 ሺህ በላይ የእኔ ቢጤዎች እና 10 ሺህ የሚገመቱ ሴተኛ አዳሪዎች ከከተማው ጎዳናዎች የሚወገዱበት እርምጃ ሊተገበር ተቃርቧል” በማለት መግለጻቸውን ዘግቧል።
ከ90 በመቶ በላይ ድሃ ሕዝብ የያዘች እና በዓለምም የድሃ ድሃ በሚል ማዕረግ የምትታወቅ አገር ድህነትን ለመቅረፍ ገና ረብ ያለው እርምጃ ሳትወስድ ድሃን ለማጥፋት መጣደፏ አጃይብ የሚያሰኝ ነው። ለነገሩ ለአንዳንድ ችግሮቻችን መስተዳድሩም ሆነ በአገር ደረጃ የሚወሰዱቱ እርምጃዎች እጅግ አስገራሚ እና በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች በመሬት ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር ምን ያህል ያህል ይተዋወቃሉ የሚለውን እንድንጠየቅ የሚያደርጉ ነገሮች ደጋግመን እያየን ነው። ለምሳሌ ያህል ሌብነት በእግረኛ፣ በሞተረኛ፣ በመኪና እና በሌሎች የተደራጁ ቡድኖች በአደባባይ በሚፈጸምባት መዲና፤ አዲስ አበባ ሌብነት ለመከላከል ተብሎ በሞተር አሽከርካሪዎች ላይ የተወሰደው የጅምላ እቀባ፣ ፈተና እንዳይሰረቅ በሚል የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናዎች ሲቃረቡ የኢንተርኔት አገልግሎት ለቀናቶች ማቋረጥ እና እነኚህን የመሳሰሉ አንዱን ችግር በሌላ ችግር የመቅረፍ አካሄድ ግራ ከማጋባት ባለፈ የአስተዳዳሪዎቹንም ብቃት እና ለሕዝብ ችግር ያላቸውንም ቀረቤታ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። የተደራጀው ሌብነት በመኪና ቢሆን የሚካሄደው ምን ሊደረግ ይሆን?
ወደ ተነሳሁነት ዋና ጉዳል ልመለስና በልመና እና በሴተኛ አዳሪነት ሥራ በተሰማሩ የአገሪቱ ዜጎች ላይ መስተዳድሩ ሊወስድ ያሰበው እርምጃ ሰብዓዊነት የጎደለው እና መንግሥት ድህነትን ለማጥፋት በቅድሚያ ማከናወን የሚገባውን ሥራዎች ሠርቶ ሳይጨርስ በድሃ ላይ ለመዝመት ማሰቡ ደግሞ የአስተዳደሩን ብልሹ አተያይ ከወዲሁ የሚያሳይ ነው። እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለ የድሃ ደሃ አገር አይደለም በሰለጠኑት እና በሃብት በተትረፈረፉት አገሮች እንኳን የመንገድ ላይ ለማኝ እና ሴተኛ አዳሪ አይታሰርም፣ አይሳደድም ወይም ከከተማ እንዲወገድ አይደረገም። አንዳንዱ አገር ሴተኛ አዳሪነት እንደ ማንኛውም የንግድ ሥራ ጭምር ተቆጥሮ የግብር ከፋይ ኮድ ተሰጥቷቸው እና ፍቃድ ተሰጥቷቸው በአደባባይ እንደልባቸው እና ሙሉ ጥበቃ ተደርጎላቸው ይሰራሉ። እኛ ጋ ይህ ይሁን እያልኩ አለመሆኑ ይታወቅልኝ። ነገር ግን እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ከጎዳና ላይ ለማጽዳት ሕግ ከማርቀቅ እና ከመፎከር በፊት ዜጎችን ለልመና እና ለሴት አዳሪነት የሚዳርጉትን ዋና ዋና ምክንያቶችን በቅጡ ማጥናት እና ምንጩን ለማንጠፍ ማቀድ ይቀድም ነበር።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማም ሆኑ አብረዋቸው ሃሳቡን የሚገፉ የመስተዳድሩ አካላት የሚያስተዳድሯትን ከተማ እና የሚመሩትን አገር ባህሪ በቁጡና በደንብ ያጠኑት እና ያወቁት አልመሰለኝም። የአዲስ አበባ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና ሴተኛ አዳሪዎች ለመስተዳድሩ ተሿሚዎች እና በቅንጦት ለሚኖረው የከተማዋ ነዋሪ የዓይን ቁስል እንደሆኑባቸው ግልጽ ነው። የአዲስ አበባን አውራ ጎዳናዎች ከእነዚህ ድህነት ገፎት አደባባይ ላይ ካሰጣቸው ዜጎች በማጽዳት ግን የኢትዮጵያን ድህነት ወይም የከተማዋን እውነተኛ ገጽታ መሸፈን አይቻልም። ከንቲባው ከጥቂት ወራቶች በፊት የአዲስ አበባን የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደ ተለያዩ የማኖሪያ ተቋማት ለማስገባት ዘመቻ ጀምሬያለው በማለት በየጎዳናው ላይ ሕጻናት ሲሰበስቡ የተነሱትን ፎቶ በየማኅበራዊ ድረ-ገጹ ለቀው እና ዜናውም በአገሩ ተናኝቶ አይቻለው። ያን ጅምራቸውን የት አድርሰውት ይሆን? በወቅቱ የተሰማኝ ነገር ነገርየው እጅግ ተገቢ እርምጃ ቢሆንም ከገጽታ ግንባታ የዘለለ መሆኑ ስጋት ፈጥሮብኝ ነበር። ዛሬም የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በመንገድ ላይ ተዳዳሪዎች እንደተሞሉ ናቸው። ያንን ፕሮጀት ፍሬውን ሳያሳዩን ድሆቹን ከመንገድ ለማጥፋት ሕግ ማርቀቅ መጀመራቸው የበለጠ ለገጽታ ግንባታ የሰጡትን ክብደት እንጂ ሰብዓዊነታቸውን አያሳይም።
ወያኔም ይችን ድሃን ከጎዳና ላይ የማራቅ ስልት በከፋ ሁኔታ ደጋግማ ሞክራዋለች። አዲስ አበባ ከሚመጡ ዓለም አቀፍ እንግዶች አይን ድሃን ለማራቅ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የእኔ ቢጤዎች እና ሴተኛ አዳሪዎችን አፍሰው በሌሊት ከአዲስ አበባ አርቀው በመጣል እና ወደ ከተማዋ እንዳይመለሱ በማድረግ የጅብ እራት ያደረጓቸው ዜጎች ነበሩ። ይህ አስነዋሪ እርምጃ በወቅቱ በኢሰመጉ ተጣርቶ መግለጫ ወጥቶበታል። ዛሬ መስተዳድሩ ይህን አይነት አስነዋሪ ድርጊት ይፈጽማል ብዮ ባላስብም የእነዚህን መጠጊያ የሌላቸው ድሆች እንቅስቃሴ በሕግ ለመገደብ የጀመረው እንቅስቃሴ ግን አልሸሹም ዞር አሉ ነው የሚሆነው።
የዛሬ ሃያ ዓመት ግድም በአዲስ አበባ ከተማ በልመና እና በሴተኛ አዳሪነት በተሰማሩ ዜጎች ላይ ያተኮረ እና አንድ ዓመት ተኩል ግድም በወሰደ ጥናት ላይ የመሳተፍ ዕድል ገጥሞኝ ነበር። በአዲስ አበባ ውስጥ እንኳን መንግሥት የከተማው ነዋሪ ጭምር የማያውቀው ብዙ ጉድ እንዳለ የታዘብኩበት እና እንደ ዜጋ እራሴም የተሸማቀቅኩበት ብዙ ገበናችንን አይቻለሁ። አዲስ አበባ ቢያጠኗት የማታልቅ የጉድ ከተማ ነች። በውስጧ ብዙ አይነት ሕይወትን የያዘች እና ብበዙ ድሃ ዜጎች ገበና ሸፋኝ ከተማ ነች። ችግሩ ገበናዋን አስተዳዳሪዎቿም ሆኑ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ አያውቀውም። የሚያስተዳድሯትን ከተማ የማያውቁ አስተዳዳሪዎች ታክተው ትተዋት እሲኪሄዱ የነሱንም ገበና ተሸክማ የምትቆይ ጉደኛ ከተማ ነች።
በሴተኛ አዳሪዎች ላይ ያደረግነው ጥናት እና የሰማናቸው የህይወት ታሪኮች ቢጻፉ መጻህፍት ይወጣቸዋል። ከ14 ዓመት ህጻን ሴተኛ ዳሪ አንስቶ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ታናናሽ ወንድም እና እህቶቿን ለማስተማር እና ለማስተዳደር በአንድ ምሽት ከ24 ወንዶች ጋር በየተራ ግንኙነት አድርጋ በስተመጨረሻ እራሷን ስታ የወደቀችውን የጎጃም በረንዳ ወጣት ሴት ታሪክ ከራሳቸው ከባለታሪኮቹ አንደበት ሰምቻለሁ።
ባለሥልጣናት በሚሊዮን ገንዘብ በሚቆጠር ወድ መኪኖች፣ በተንጣለሉ ቪላዎች፣ በውድ ሆቴሎች በሚንፈላሰሱባት እና ባስነጠሳቸው ቁጥር ከአገር ውጭ ውጥተው በአውሮፓ እና በአሜሪካ ህክምና እንዲያገኙ በምታደርግ አገር ውስጥ የኑሮ ዋስትና አጥተው ጎዳና ላይ የሚለምኑ እና ሰውነታቸውን የሚሸቅጡ ዜጎች (ሴተኛ አዳሪዎች) ቁጥር ቢበረክት ምን ይገርማል። እያንዳንዱ ዜጋ በአገሪቱ ሃብት እኩል የመጠቀም መብት እና ድርሻ እንዳለው ባልተቀበለች አገር ውስጥ የሺዎችን ድርሻ ለአንድ ድንቁርና ለተጫነው እና ሰብዓዊነት ከውስጡ ተንጠፍጥፎ ላወጣ ባለስልጣን ምቾት እና ድሎት የምታውል አገር በጎዳና ተዳዳሪ ዘጎች ብትወረር ምን ይደንቃል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከድህነት እና ከድሃ ጋር በተያያዘ የሚናገሩት ሁለት ቁምነገር ይህን እየጻፍኩ ወደ አዕምሮ ስለመጣ ላካፍላችሁ። አንዱ “ድሃ ባይኖር ኖሮ ሃብታም ተብድሎ አያድርም ነበር” የምትለዋ ነች። አዎ ማኅበራዊ ፍትህ በተጓደለበት፣ ሙስና ያለቅጥ በተንሰራፋበት፣ ግለኝነት በነገሰበት እና ለድሃ አሳቢ መንግሥት በሌለበት ስፍራ ሁሉ የሚሊዎኖች ድህነት የጥቂቶች የብልጽግና ምንጭ ይሆናል። ዘርፎ የበለጸገውን ባለሃብት እንተወው እና ለአንድ ባለሥልጣን ምቾት ተብለው የሚበጀት ገንዘብ ለስንት ድሃን የመኖር ዋስትና እና መሠረታዊ ነገሮች ሟሟያ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ለእናንተው እተዋለሁ።
ሁለተኛው የፕሮፌሰር ምክረ ሃሳብ ድህነትን የመርሳት በሽታችንን የሚያሳይ ነው። ምን ይላሉ “እንደ ድህነት ቶሎ የሚረሳ ነገር የለም፤ እኔም ድህነቴን እንዳልረሳ ድሆች ያሉበት አካባቢ መኖርን እመርጣለሁ። ድህነቴን ካልረሳው ድሃንም አረሳም፤ ያለኝን በወር በወር ከድሃ ጋር እካፈላለሁ።” እያሉ ድህነታችንን ቶሎ እንዳንረሳ እና በድሃ ላይ እንዳንጨክን እና እንዳንከፋ ደጋግመው ያስተምሩን ነበር። ድሃ ሰው ድህነቱን ቢረሳ ኩነኔው ለራሱ ነው። በሌሎች ድሆች ላይ የሚያደርሰውም ጉዳት ያን ያህል ላይሆን ይችላል። ድሃ ሕዝብ የሚያስተዳድር ድሃ መንግሥት ድህነቱን ቶሎ ሲረሳ እና ከተማዋን የሀብታሞች ደሴት ለማድረግ እንቅልፍ ሲያጣ ግን አደጋው ብዙ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው ሕዝቧ ትልቁን ቁጥር በሚይዝበት አገር ድሃን ከመንገድ ለማራቅ መዳከር ውድቀትን መለመን ነው። በሞቀ ጎጇቸው ውስጥ እየሆሩ በድህነት አቅሙ የጣላትን ደሳሳ ጎቾ በላዩ ላይ አፍርሰው ሲያበቁ መንገድ ላይም ለምኖ እንዳያድር ሕግ የሚያወጡ እና ስልት የሚነድፉ ሹመኞች ጸባቸው ከድሃ እንጂ ከድህነት ሊሆን አይችልም። ባለፉት 27 የታከለ ኡማ ፓርቲ ኢህአዴግ መኖሪያ ቤታቸውን እያፈረሰ ለጎዳና ላይ ሕይወት የዳረጋቸውን ዜጎች የፈረሰው ቤት ይቁጠራቸው።
የአዲስ አበባ መስተዳድርም ሆነ የአገሪቱ መንግሥት እንዲህ አይነት የዜጎችን መሠረታዊ መብት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እና በተለይም ድሃውን የአገሪቱን ሕዝብ የመኖር ዋስትና የሚያሳጡ እርምጃዎችን ለመውሰድ ከመሞከር በፊት ለዜጎች ድህነት እና ለጎዳና ሕይወት ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ለማንጠፍ ቢሰራ መልካም ነው። ይህ ደግሞ እንዲህ በጥድፊያ በአንድ ዓመት አይደለም በአምስት እና አስር ዓመትም ውስጥ የሚሳካ ነገር ስላልሆነ ቅድሚያ ድህነትን ለማጥፋት ይሰራ። ድሃነት መአረግ ስላልሆነ ማንም መርጦ የገባበት ህይወት አይደለም እና ድህነት ሲጠፋ ድሃም እቤቷ ትሰበሰባለች። ድሃ ላይ ያነጣጠሩ የጽዳት ዘመቻዎች ግን ‘ወጡ ሳይወጠወጥ…’ ነው የሚሆነው።
በቸር እንሰንብት!
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– አገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ (NEAEA) የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የፈተና ውጤትን ነሐሴ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ አደረገ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት፥ ወጤታቸን በመጠባበቅ ላይ ያሉ ተፈታኝ ተማሪዎች ውጤታቸውን በኤጀንሲው ድረ-ገጽ app.neaea.gov.et በመግባት ማወቅ ይችላሉ።
የመፈተኛ ቁጥራቸውን አድሚሸን (Admission) በሚለው ሳጥንውስጥ በማስገባት ውጤታቸውን መመልከት ይችላሉ ብለዋል አቶ አርአያ።
በሞባይል አጭር የፅሁፍ መለእክት (SMS) 8181 id በማለት የሚያዩበት አማራጭ መመቻቸቱንም ገልጸዋል።
- የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ለማወቅ እዚህ ጋር ይጫኑ app.neaea.gov.et
በ2011 ዓ.ም. የትምህረት ዘመን 319 ሺህ 264 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና የወሰዱ ሲሆን 59 ተማሪዎች ከ600 መቶ በላይ ውጤት አስመዝግበዋል።
ዘንድሮ 645 ከፍተኛ ውጤት ሆኖ መመዝገቡም ታውቋል።
የዘንድሮው ውጤት ካለፉት ዓመት ጋር ሲነፃፀር መካከለኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች 48 ነጥብ 59 በመቶ ናቸው።
በፈተና ሥነ ስርዓት ጥሰት ምክንያት በቀረበባቸው ሪፖርት የ68 ተማሪዎች ውጤት መሰረዙንም አቶ አርአያ ገልጸዋል።
ከአራት ክልሎች (አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ቤኒሻንጉል) የ864 ተማሪዎች ውጤት ለተጨማሪ ማጣራት እንዲያዝ ተደርጓል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓመታዊው የበጎ ሰው ሽልማት ከግንቦት 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዕጩዎችን ሲጠቁሙ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህ በተጠቀሰው የጊዘ ገደብ ውስጥም በ አጠቃላይ 291 ሰዎች ተጠቁመው 27 ዕጩዎች ለዳኞች ውሳኔ ቀርበዋል ለመጨረሻው የዳኞች ውሳኔ መቅረባቸውን የበጎ ሰው ሽልማት አስተባባሪዎች በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
እንደወትሮው ሁሉ በሽልማቱ ዕጩዎች የተጠቆሙባቸውና ሽልማት የሚያሰጡት አስር የተለያዩ ዘርፎች ናቸው። በእያንዳንዱ የሽልማት ዘርፍ የቀረቡት ዕጩዎች የሚከተሉት ናቸው።
በመምህርነት ዘርፍ
- ፕሮፌሰር ሽታዬ ዓለሙ ባልቻ (ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ)
- ወ/ሮ ህይወት ወልደመስቀል
- ዶ/ር መስከረም ለቺሳ ደበሌ (ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርት እና ሥነ-ባህሪ ኮሌጅ)
በሳይንስ (ህክምና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ምህንድስና፣ ኬሚስትሪ፣ አርክቴክቸር፣ ወዘተ)
- ፕሮፌሰር ለገሰ ነጋሽ
- ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሴ
- ዶ/ር ታደለች አቶምሳ
በኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ እና በፎቶ ግራፍ ዘርፍ
- አቶ ሚካኤል ፀጋዬ
- አቶ በዛብህ አብተው
- አቶ ዳኜ አበራ
በበጎ አድራጎት (እርዳታ እና ሰብዓዊ አገልግሎቶች)
- ዶ/ር ጀምበር ተረፈ
- አቶ አብድላዚዝ አህመድ
- አቶ ላሌ ለቡኮ
በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ
- አቶ ዳንኤል መብራቱ
- አቶ ክቡር ገና
- አቶ ነጋ ቦንገር
በመንግሥታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት
- አቶ በትሩ አድማሴ (ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የቴሌኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር የነበሩ)
- ዶ/ር አሚር አማን (የአሁኑ የጤና ሚኒስትር)
- አቶ ግርማ ወንዳፍራሽ
በቅርስና ባህል ዘርፍ
- አቶ አብዱልፈታህ አብደላ (የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የባህላዊ ዳኝነትና የፍትህ ሥርዓቶችን በመጻፍ የሚታወቁ)
- አርሶ አደር አቶ አድማሴ መላኩ (በምስራቅ ጎጃም ዞን በጮቄ ተራራ አካባቢ የሚገኘውን ‹‹አባ ጃሜህ›› ደን ለ52 ዓመታት በግል ተነሳሽነት ሲጠብቁና ሲንከባከቡ የነበሩ)
- ሳሙኤል መኮነን (ከጎንደር)
በሚዲያና ጋዜጠኝነት
- አቶ በልሁ ተረፈ
- አቶ አማረ አረጋዊ
- ወ/ሮ አንድነት አማረ
በኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች
- አቶ ኦባንግ ሜቶ
- አርቲስት ታማኝ በየነ
- ፕሮፌሰር ፀጋዬ ታደሰ
በተጠቀሱት የሽልማት ዘርፎች ከእያንዳንዳቸው አንደኛ ሆነው የሚመረጡት ዕጩዎች በተመረጡበት ዘርፍ የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ተብለው ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል (ካዛንችስ፣ አዲስ አበባ) አዳራሽ ውስጥ በሚደረገው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ይሸለማሉ።
Topic: ፓምፋሎን ― ኢትዮጵያዊው ቦብ ማርሌ?
ፓምፋሎን ብዙ ልታይ ልታይ የሚል ሰው አይደለም። ሙዚቃውን ለሕዝብ በሚያቀርብበት ጊዜ የአድማጮቹ ትኩረት በመልዕክቱ ላይ እንዲሆን እንደሚፈልግ ይናገራል። ለዚህም ነው ብዙ የሙዚቃ ክሊፖችን የማይሠራው።
ቅድመ ነገር – ለምን የሙዚቃ ስሙን ፓምፋሎን ብሎ ሰየመው?
የሁለት ሰዎችን ሕይወት የሚተርክ በልጆች መጽሐፍ ውስጥ ያለ ታሪክ ነው። አንደኛው ገፀ-ባሕሪ መንፈሳዊ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ዓለማዊ ነበር።
መንፈሳዊው ከሰዎች እና ከዓለማዊ ኑሮ ርቆ ለሠላሳ ዓመታት ከፈጣሪው ጋር በመወያየት ቆየ። አንድ ቀን ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ ሳለ ለመንፈሳዊው ግለሰብ ፈጣሪ ይገለጥለትና ወደ ፓምፋሎን እንዲሄድ ይነግረዋል።
ይህም ሰው ለመንፈሳዊ ጥያቄዎቹ እንዴት ወደ ፓምፋሎን እንደተላከ ሊገባው አልቻለምና ፈጣሪውን “ለምን ወደ እርሱ ትልከኛለህ?” ብሎ ሲጠይቅ “በሰዎች ዓይን ፓምፋሎን ዓለማዊ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን የሰው ልጅ መንፈሳዊነት በልቡ ያለ እንጂ በሰዎች የሚታይ አይደለም” ብሎ ይመልስለታል። “እኔም ለዚያ ነው የሙዚቃ ስሜን ፓምፋሎን ያልኩት” ይላል ፓምፋሎን።
የፓምፋሎን ተረት በሩስያዊ ደራሲ የተፃፈ ቢሆንም ፓምፋሎን ግን ከልጅነቱ ጀምሮ በጀርመን ሃገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ነው። ያለ እናትና አባት ያደገው ፓምፋሎን ከ16 ዓመቱ ጀምሮ ነው ራሱን ማስተዳደር የጀመረው።
ስለ ሕይወት ታሪኩ እና ወደ ጀርመን እንዴት እንደሄደ ሲጠየቅ “እሱን ሌላ ጊዜ በሌላ መልኩ ለሕዝብ ለማቅረብ ስለምፈልግ ለጊዜው ስለ ታሪኬ ለመናገር ዝግጁ አይደለሁም” ይላል።
በየወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ የሚለው ፓምፋሎን ነገሮች ቢመቻቹለት ኑሮውን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያደርግ ይወዳል። ለጊዜው በሙዚቃ ስሙ ብቻ እንዲታወቅ እንደሚፈልግ ይናገራል።
ወደ ሙዚቃ የገባው በተለያዩ ነገሮች ተገፋፍቶ ነበር። “የተለያዩ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የምጠቀምበት ስለሆነ ነው ሙዚቃ መሥራት የጀመርኩት። ጥበበኛ ነኝ ወይም ችሎታ አለኝ ማለትም አልፈልግም ምክንያቱም ለጊዜው ሙዚቃውን መልዕክት ማስተላለፊያ ነው ያደረግኩት” በማለት በትህትና ይናገራል።
ፓምፋሎን ብዙ ልታይ ልታይ የሚል ሰው አይደለም። ሙዚቃውን ለሕዝብ በሚያቀርብበት ጊዜ የአድማጮቹ ትኩረት በመልዕክቱ ላይ እንዲሆን እንደሚፈልግ ይናገራል። ለዚህም ነው ብዙ የሙዚቃ ክሊፖችን የማይሠራው።
“ለጊዜው የሙዚቃ ዓለሙን ተቀላቀልኩ እንጂ ወደፊት ሌሎች ነገሮችን የመሥራት ፍላጎት አለኝ” የሚለው ፓምፋሎን በሙዚቃዎቹ የተለያዩ ሰዎችን ንግግሮች ያካትታል። ከእነዚህም መካከል የማንዴላ፣ የማልኮም ኤክስ እና የዶ/ር አብይ አሕመድ ይገኙበታል።
ለምን ብሎ ሲጠየቅም በአንድ ወቅት ንግግሮቹ ስሜቱን ከነኩት የሙዚቃውን መንፈስ ለአድማጮቹ ለማስተላለፍ እንደሚያስችሉት በማሰብ እንደሆነ ይናገራል።
ገቢው በሙዚቃ ሥራዎቹ ላይ እንዳልተመሰረት የሚናገረው ኢትዮ-ጀርመናዊው ሙዚቀኛ “ሙዚቃዬ እያበላኝ አይደለም። የምተዳደረው በግራፊክ ዲዛይን፣ ፎቶግራፎችን በመሸጥ እና ሌሎች ነገሮች በመሥራት ነው” ይላል።
የሕይወቱን ሦስት አራተኛ በጀርመን ስለኖረ አልፎ አልፎ በጀርመንኛ መልዕክቱን ለማስተላለፍ ይቀለዋል። ሆኖም ግን በአማርኛ ነው አልበሙን የሠራው። “ቋንቋ እንደአጠቃቀማችን ነው እና ጀርመንኛው ቀለል ይለኛል ግን ሆን ብዬ በሃገሬ ቋንቋ ነው ሙዚቃዬን የምሠራው ምክንያቱም የኢትዮጵያ ልጅ ነኝ” በማለት ይናገራል።
አክሎም “በልጅነቴ የተለያዩ የራፕ ቡድኖችን ተቀላቅዬ በጀርመንኛ ራፕ አደርግ ነበር። ሳድግ ግን ምንድነው ማድረግ የምፈልገው ብዬ አሰብኩበት። መልዕክቴን ለኢትዮጵያ ማስተላለፍ እንደሆነ ሳውቅ በአማርኛ መሥራት ጀመርኩኝ” ይላል።
የሚሠራቸውን የተለያዩ የጥብብ ሥራዎች በእኩል እንደሚመለከት የሚጠቅሰው ፓምፋሎን ቢገደድ እንኳን አንዱን ብቻ ለመመረጥ በጣም እንደሚከብደው የሚናገረው በመግለጽ እየሳቀ “ከሙዚቃውና ከፎቶግራፍ ምረጥ የሚለኝን ሰው እንደጠላት ነው የምቆጥረው” በማለት ይናገራል።
“የግጥም አፃፃፌ እራሱ ከኢትዮጵያ ገጣሚያን የተለየ ነው። ብዙዎችም ለየት እንደሚል ይነግሩኛል” በማለት በሃገሩ ቋንቋ ሥራዎቹን ለሕዝብ ማቅረብ መቻሉ እንደሚያስደስተው ይገልፃል።