Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Viewing 15 results - 451 through 465 (of 730 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአምራች ድርጅቶቻቸው አድራሻና ምንጫቸው የማይታወቁ እንዲሁም የብቃት ማረጋገጫ የሌላቸውን የምግብ ምርቶች ገበያ ላይ እየዋሉ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ባደረገው የገበያ ቅኝት ማገኘቱን አስታወቀ።

    ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ድርጅቶች ተመርተው ወደ ገበያ በተሰራጩ ምርቶች ላይ በተደረገ የገበያ ቅኝት በብሔራዊ ደረጃ የተቀመጠውን መስፈርት ያላሟሉ፣ ምንም ዓይነት ገላጭ ጽሁፍ የሌላቸው፣ የአምራች አድራሻ እና መለያ ቁጥር የሌላቸው የሕፃናት ምግብ፣ የለዉዝ ቅቤ፣ የምግብ ዘይት፣ የምግብ ጨውና ማር ገበያ ላይ መገኘታቸው በተደረገው የቁጥጥር ሥራ የተገኘ ሲሆን ባለስልጣኑ አስተዳደራዊ እርምጃ ወስዷል።

    በመሆኑም ህብረተሰቡ ከታች ስማቸው የተገለጹትን የሕፃናት ምግቦች፣ የለዉዝ ቅቤ፣ የምግብ ዘይት፣ የምግብ ጨውና ማር ምርቶችን እንዳይጠቀማቸው እያሳሰበ፤ ተመሳሳይ ምርቶች በሌሎች አካባቢ የመገበያያ ስፍራዎች ሊኖር ስለሚችሉ ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ለሚገኝ የጤና ተቆጣጣሪ፣ ለፖሊስ አካላት ወይም በፌደራል ደረጃ ለባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በነጻ ስልክ መስመር 8482 በመጠቆም እንዲያሳውቅ ጠይቋል።

    በማያያዝም የክልል ተቆጣጣሪዎችና በየደረጃው የሚገኙ የቁጥጥር አካላት ምርቶቹን ከገበያ ላይ በአፋጣኝ የመሰብሰብ ሥራውን እንዲሠሩ ባለስልጣን መሥሪያቤቱ ጥሪውን አቅርቧል።

    ህብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው የተከለከሉ የምግብ ምርቶች ዝርዝር

    የሕፃናት ምግቦች
    1. ፍቅር ምጥን
    2. ማስ የሕፃናት ምግብ
    3. ተወዳጅ ኃይል ሰጪና ገንቢ የሕፃናት ምግብ
    4. ስሚ የሕፃናት ምጥን ገንፎ
    5. ፋሚሊ ኃይል ሰጪና ገንቢ የሕፃናት ምግብ
    6. አባድር
    7. ሂሩት ሕፃናት ሂሩት ባልትና
    8. አዩ ለልጆች የተዘጋጀ ምጥን ምግብ
    9. ምቹ 100% ተፈጥሯዊ ይዘቱን የጠበቀ የሕፃናት ምግብ
    10. ፍቅር ኑሪሺ ዩር ቤቢስ ፍቅር/Nourish your babies Fiker

    የምግብ ጨው
    1. ሸዋ የገበታ ጨዉ/Shoa table salt
    2. Greep iodized salt
    3. SNAME iodized table salt
    4. አባተ አዮዲን ጨው/ Abate iodized salt
    5. Refined and iodized Woef table salt
    6. ምርጥ የገበታ ጨዉ
    7. አቤት የገበታ ጨዉ

    የለዉዝ ቅቤ
    1. ኤደን የለዉዝ ቅቤ
    2. ጽጌ የለዉዝ ቅቤ
    3. ፀዬየ ለዉዝ ቅቤ
    4. ማቲፍ የለዉዝ ቅቤ
    5. ምሥራቅ የለዉዝ ቅቤ
    6. ታደለ ንጹህ የለዉዝ ቅቤ
    7. ምእራፍ የታሸጉ ምግቦች
    8. ህብረት የለዉዝ ቅቤ
    9. ደስታ የለዉዝ ቅቤ
    10. ሳራ የለዉዝ ቅቤ
    11. ሰን ናይት የለዉዝ ቅቤ
    12. አቢሲኒያ የለዉዝ ቅቤ

    የምግብ ዘይት
    1. ጸደይ የምግብ ዘይት
    2. ኑር
    3. ኦሜጋ
    4. ቅቤ ለምኔ
    5. ሰብር የኑግ ዘይት
    6. ያሙ የምግብ ዘይት
    7. ሜራ የኑግ ዘይት
    8. ፍፁም የተጣራ የኑግ ዘይት
    9. ቀመር የምግብ ዘይት
    10. ኔግራ የምግብ ዘይት
    11. ከበለመን የምግብ ዘይት

    ማር ምርት
    1. ሃበሻ ንጹህ የተፈጥሮ ማር
    2. ተርሴስ ማር
    3. ንጹህ ማር
    4. ኢትዮ ማር
    5. ማስ የጫካ ማር
    6. ራይት ማር

    ምንጭ- የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን/ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የተከለከሉ የምግብ ምርቶች


    Semonegna
    Keymaster

    እኛ ያሰባሰበን እግር ኳስ ነው፤ የሚያዝናናን እግር ኳስ ነው፤ የታገልነው ለእግር ኳስ ፍትህ ነው፤ ሌላ ዓላማ የለንም፤ እግር ኳስ ቋንቋችን ነው፤ ከዚህ ቋንቋ ውጪ መናገረ የማይችል ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች መሀል ባይገኝ ይመረጣል፤ ምክንያቱም መግባቢያችን እግር ኳስ እና እግር ኳስ ብቻ ነው።

    ከመጣንበት መንገድ በላይ የሚቀረን ይከብዳል!! (ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች)

    ከሊቅ እስከ ደቂቁ፣ ከመምህሩ እስከ ደቀመዝሙሩ፣ ከሹፌሩ እስከ ረዳቱ፣ ከገጠሩ እስከ ከተማው፣ ከገበሬው እስከ ሠራተኛው፣ ከአስተማሪው እስከ ተማሪው፣ ከፖለቲከኛው እስከ አክቲቪስቱ፣ ከመሪው እስከ ተመሪው… የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንድ ቃል ሲያነጋግር የነበረው 8 ውሳኔዎች የተለዋወጡበት በቀሽም ደራሲ ተደርሶ በቀሽም ተዋንያን ሲተወን የነበረው ተከታታይ ድራማ በመጨረሻም እውነትን ይዞ እስከ መጨረሻው ሲታገል የነበረው በሕዝባዊው ክለብ ኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቋል።

    ኢትዮጵያ ቡና ምንም ዓይነት ጥፋት ሳይገኝበት ‘ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ጋር በዝግ ተጫወት’ የሚለውን ቀልድ መሰል መራር ፍርድ ከመላው ደጋፊው ጋር በመሆን እና ሌሎች ለእውነት የቆሙ በርካታ አጋሮቹን አብሮ በማሰለፍ በምርቃና እየወሰኑ፣ በሞቅታ የሚሽረውን ከእግር ኳስ ዕውቀት ነጻ የሆነው የፌዴሬሸኑን [የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን] አድልዎ የተሞላበትን ዝርክርክ አሠራር በአደባባይ አጋልጠን ውሳኔውን በማስቀልበሳችን ደስተኛ ብንሆንም ደስታችን ሙሉ የሚሆነው የማክሰኞውን ጨዋታ በድል ተወጥተን በፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት ኢትየጵያ ቡና ብቻ ከፍ በማድረግ ደስታችንን ሙሉ በማድረግ ተወስኖብን የነበረው ፍርድ ምን ያህል ከእምነት የራቀ ፍርደ ገምድል ውሳኔ መሆኑን ማሳየት ይኖርብናል።

    ● SEMONEGNA on Social Media: FacebookTwitterInstagramPinterest | Video | Forum

    ውድ ደጋፊዎቻችን፥ ታግለን ካሸነፍነው እና ከመጣንበት መንገድ በላይ የሚቀረን መንገድ ከባድ እንደሆነ በማሰብ ሁሉንም በጥንቃቄ መከወን ይኖርብናል። በዚህ ጨዋታ ላይ ፌዴሬሽኑ የአደባባይ ውርደቱን ለማካካሰ እና የቅጣት ዶሴውን ለመምዘዝ ጥቂት ስህተት ብቻ ከእኛ እንደሚጠበቅ ለማወቅ ነብይ መሆን አያስፈልግም። የመጣንበትን መንገድ መመርመር ብቻ በቂ ነው። ስለዚህ ምዕራፍ ሁሉቱን በድል ለመወጣት ሁሉም ደጋፊ እንደቀድሞ በህብረት በመሆን ዘጠና ደቂቃ ስለ ክለባችኝ ኢትዮጵያ ቡና ብቻ በመዘመር በፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት ይህን ምዕራፍ መዝጋት ይኖርብናል።

    በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ስም እንዲሁም በቡኒው እና ቢጫው መለያ ስር ተደብቆ የተለየ ዓላማውን ለማራመድ ወደ ካንቦሎጆ የሚመጣ ሰው ካለ ኢትዮጵያ ቡና ማለት ለዚህ ደጋፊ ምን እንደሆነ ያልተረዳ ነውና ጥንቃቄ እንዲያደርግ እንመክራለን።

    እኛ ያሰባሰበን እግር ኳስ ነው፤ የሚያዝናናን እግር ኳስ ነው፤ የታገልነው ለእግር ኳስ ፍትህ ነው፤ ሌላ ዓላማ የለንም፤ እግር ኳስ ቋንቋችን ነው፤ ከዚህ ቋንቋ ውጪ መናገረ የማይችል ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች መሀል ባይገኝ ይመረጣል፤ ምክንያቱም መግባቢያችን እግር ኳስ እና እግር ኳስ ብቻ ነው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች


    Semonegna
    Keymaster

    ሐረማያ ከተማ (ሰሞነኛ) – ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በባቢሌ ወረዳ ለሚገኙና ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለነበሩ አርሶ አደሮች ከ750ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ 266 ኩንታል በአጭር ጊዜ የሚደርስ የተሻሻለ የቦቆሎና የማሽላ ዘሮችን በእርዳታ አከፋፈለ።

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምርጥ ዘሩን ያከፋፈለው ከኢትዮጵያ ሶማሌና ከኦሮሚያ ክልሎች ድንበር አዋሳኝ ዘጠኝ ቀበሌዎች ከ2 እስከ 8 ወር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የባቢሌ ንዑስ ምርምር ጣቢያና በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው ለነበሩ 964 ወደ ቄያቸው ተመላሽ አርሶ አደሮች ነው።

    ዩኒቨርሲቲው ያከፋፈለው የቦቆሎና የማሽላ ምርጥ ዘሮች በሦስት ወር ውስጥ የሚደርሱ በሽታንና ድርቅን የሚቋቋሙ ሲሆን ለገመቹ፣ ኤረር ጐዳ፣ ኢፋዶኒ፣ ቱላ፣ ሼካ አብዲ፣ አውሸሪፍ፣ ኤረር ኢባዳ፣ ራመታ ሠላማ እና አባዳ ገመቹ ለሚኖሩ 964 አባ እና እማወራዎች 241 ኩንታል መልካሣ-2 የተባለ የቦቆሎና 25 ኩንታል መልካም የተባለ የማሽላ ዘር ነው።

    የቱላ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪ የሆነችው ነኢማ ዑመር ቀደም ሲል ከቀዬዋ ተፈናቅላ በባቢሌ ስትኖር እንደ ነበርና አሁን ሠላም ወርዶ ወደ ቀዬዋ ብትመለስም የምትዘራው ዘር አጥታ ስትጨነቅ እንደነበርና አሁን ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያገኘችው ዘር እንደደረሰላት በመግለፅ ዩኒቨርሲቲውን አመስግናለች።

    ሌላው ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያነጋገራቸው የገመቹ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አብዱረህማን ሽኩር፥ በኢትዮ ሶማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ በተቀሰቀሰ ግጭት አጠቃላይ የቀበሌው ነዋሪ ከ8 ወራት መፈናቀል በኋላ በሀገር ሽማግሌዎች፣ በመከላከያ እና የፀጥታ ዘርፍ አመራሮች ጥረት በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል እርቅ ተደርጐ ወደ ቄያቸው ቢመለሱም ቀደም ሲል የነበራቸው ንብረት በመዘረፉ እና በመውደሙ የእርሻ ማሳቸውን አዘጋጅተው የመግስትን እርዳታ ሲጣባበቁ እንደነበር ጠቁመዋል። ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ምርጥ ዘር ለ700 አባና እማወራዎች እንደተከፋፈለና ይህም በ355 ሄክታር መሬት ላይ ለመዝራት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አቶ አብዱረህማን ገልፀው ምንም እንኳን ፍላጎቱ ከአቅርቦቱ ጋር ሲነፃፀር ብዙ ቢቀረንም ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ላዳረገው አስቸኴይ እርዳታ በራሳቸውና በቀበሌው አርሶ አደሮች ስም አመስግነዋል።

    በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የባቢሌ ወረዳ ተፈጥሮና ግብርና ልማት ፅህፈት ቤት ተወካይ አቶ ኢዳ አቦንሣ እንደገለጹት ተፈናቃዮችን ወደቄያቸው መልሶ ለማቋቋም በምናደርገው ጥረት ምርት አምርተው ለመኖር እንዲችሉ ለማድረግ የግድ ዘር በማስፈለጉ ይህንኑ ዩኒቨርሲቲው እንዲረዳን በደብዳቤ በጠየቅነው መሰረት ፈጣን ምላሽ በመስጠት ከመጋዘኑ ባይኖረውም ካለው በጀት ላይ 750000 (ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ) ብር የሚያወጣ ዘር በመግዛት በራሱ ትራንስፖርት ወረዳው ድረስ በማምጣት በዘጠኝ ቀበሌ ለሚገኙ 964 አባና እማወራዎች 266 ኩንታል የተለያዩ የተሻሻሉ ዘሮችን አከፋፍሏል። ላሣየው የህዝብ ወገንተኝነት ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል ብሏል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በያዝነው የ2011 ዓ..ም በጀት ዓመት ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ የሰብል፡ የአትክልት እና ፍራፍሬ፣ የእንቁላል ጣይ ዶሮ ፤ የቦሎቄ ዘሮችንና የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ለተጠቃሚዎች በነፃ ማከፋፈሉን ከዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ያገኘነው ማስረጃ ያሳያል ሲል ሲሣይ ዋቄ ለዩኒቨርሲቲው ዘግቧል።

    ምንጭ፦ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ (ኤፍ ኤም 91.5) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ


    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እንዳሳወቀው፥ የተጠናቀቁ የባቡር ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ለማስገባት የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር ጉልህ ችግር መፍጠሩንና፣ እየተከናወኑ ባሉ ፕሮጀክቶችና ታላላቅ ተግባራት ላይ መስተጓጎልን አስከትሏል።

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የተጠናቀቁ የባቡር ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ለማስገባት የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር እክል መፍጠሩን የኢትዮዽ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ ችግሩ ኮርፖሬሽኑ ለመሠረተ ልማት የሚያስፈልገውን ክፍያ ባለመፈጸሙ የተፈጠረ መሆኑን ገልጿል።

    በቱርኩ ሥራ ተቋራጭ ያፒ መርኬዚ እየተሠራ ያለውና ግንባታው ከ97 በመቶ በላይ የደረሰው የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት እየተጠናቀቀ ቢሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ የሙከራ ጉዞ ለማድረግ አለመቻሉን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ገልጸዋል።

    እንደ አቶ ደረጃ ገለጻ ያለቁት ፕሮጀክቶች ወደሥራ ቢገቡ ወደ ጅቡቲ ወደብ በሚደረገው ጉዞ የሚወስደውን ጊዜ ከ50 በመቶ በላይ በመቀነስ የወጪ ገቢ ንግድን ያቀላጥፋሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የባቡር መስመሩ የሚያልፍበት አካባቢ ኅብረተሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከፍ ይላል። ስለዚህም የኤሌክትሪክ ችግር ቶሎ እልባት ቢያገኝ መልካም ነው ብለዋል።

    የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው እንዳሉት፥ ድርጅታቸው መሠረተ ልማቱን ዘርግቶ ኃይል የማቅረብ ሥራ ይሠራል። ለመሠረተ ልማት ዝርጋታው የሚያስፈልገው ወጪ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይሉን በሚፈልገው ድርጅት የሚሸፈን ይሆናል። የኢትዮጵያ ምድር ባቡርም ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚሆነውን ክፍያ ባለመፈጸሙ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊያገኝ አለመቻሉን አቶ ሞገስ ገልጸዋል።

    የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ግን ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የበጀት እጥረት ሲገጥመው በመጨረሻ ያመጣው ሃሳብ እንጂ የቀድሞ አሠራሩ እንዲህ አልነበረም ብለዋል።

    እንደ አቶ ደረጀ ገለጻ፥ ‘በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ውሃ ስትፈልግ ከለገዳዲ ጀምረህ መስመር አትዘረጋም፤ ራሱ ድርጅቱ መሠረተ ልማቱን ይሰራልሃል። የኤሌክትሪክ ኃይልም ከዚህ የተለየ አይደለም፤ የመሠረተ ልማት ዝርጋታውንም ሆነ የኃይል አቅርቦቱን የሚያከናውነው ራሱ ነው’ ብለዋል።

    ምንጭ፡- አዲስ ዘመን / ኢቢሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን


    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ተወሰነ
    —–

    የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ለጊዜው እንዲቋረጥ ውሳኔ መተላለፉን ውድድሩ በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. አስታወቀ።

    የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ግንቦት 28 ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ በውድድሩ ከሚካፈሉ የእግር ኳስ ክለቡችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ፥ ውድድሮች በተገቢው መንገድ የሚካሄዱበት ዘላቂ መፍትሄ እስኪሰጥ ድረስ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ወሳኔ ላይ ደርሰዋል።

    የተደረገውን የአስቸኳይ ስብሰባ ውሳኔ ተከትሎ ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ ለጊዜው እንዲሰረዝም ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ለፌዴሬሽኑ የሚቀርቡ የተለያዩ ጥያቄዎች በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ የውድድር ደንብ መሰረት እንዲታዩ ውሳኔ ተላልፏል።

    ምንጭ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

    Anonymous
    Inactive

    የተከሰተውን የአተት ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ግብረ ሃይል ተቋቋመ
    —–

    በአምስት ክልሎች የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል መቋቋሙን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሰታወቀ።

    በአምስት ክልልች በተከሰተው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ወረርሽኝ እስከአሁን የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ ፡፡

    ወረርሽኙን በአፋጣኝ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የህክምና ግብአቶች በሁሉም ክልሎች ወደሚገኙ የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ መጋዘኖች መላካቸውንም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

    እስካሁን ድረስ በኦሮሚያ 138፣ በአማራ 198፣ በሱማሌ 33 እና በትግራይ 8፤ በድምሩ 377 ሰዎች በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ተይዘዋል ብሏል ኢንስቲትዩቱ።

    ምንጭ፦ ኢቢሲ

    Semonegna
    Keymaster

    በአሁኑ ጊዜ የግዕዝ ቋንቋን ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚሰጥባቸው መካከል መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ደሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዲ.ሪ.) ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከብሔራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ፣ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ቅዱስ ያሬድ ጥንታዊ ብራና ጽሑፎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ከሰኔ 1-2 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ “ግዕዝ እና ሥነ-ፈውስ” በሚል መሪ ቃል በመቐለ ከተማ ለሚካሄደው 5ኛውን የግዕዝ ጉባኤ ቀንን አስመልክቶ መረጃውን አስቀድሞ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጋዜጣዊ መግለጫ በሚኒስቴሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንቦት 26 ቀን 20011 ዓ.ም. ተሰጥቷል።

    ጋዜጣዊ መግለጫውን በጥምረት የሰጡት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቋንቋና የባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው፣ የብሔራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ቅዱስ ያሬድ ጥንታዊ ብራና ጽሑፎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሐጎስ አብርሃ ናቸው።

    እንደኃላፊዎቹ መግለጫ፥ በግዕዝ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶች በርካታ በመሆናቸው ልንማርበት፣ ልንጠቀምበትና ልትውልድ በማሸጋገር ወደ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ማምራት ይቻላል። በመሪ ቃሉ “ግዕዝ እና ሥነ-ፈውስ” ስንል እንደየባህሉ ሥነ-ልቦናን፣ ፀሎትን፣ ሥነ-ቃልን ለማወቅና መዳንን የሚያበረታታታ ሀገር በቀል ዕውቀት መሆኑንማወቅ ስላለብን፣ ብሎም ስለግዕዝ ያለንን ግንዛቤ ለማስፋት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

    እንዲሁም በሀገራችን በርካታ ጥንታዊ የጽሑፍ ሀብቶቻችን የምናገኝበት በግዕዝ ቋንቋ የተፃፉ በመሆኑ፣ ጥንታዊ የስልጣኔ መገለጫ ሆኖ የሚያገለግል ነው። በአሁኑ ጊዜ የግዕዝ ቋንቋን ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚሰጥባቸው መካከል መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ደሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በሀገራችን በግዕዝ ቋንቋ በተሠሩ ሥራዎች ላይ እስካሁን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት 750,000 በብራና ላይ የተፃፉ መጽሕፍት መኖሩ ታውቋል።

    ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    መቐለ ዩኒቨርሲቲ


    Semonegna
    Keymaster

    ለግንቦት 27 ቀን ተወስኖ የነበረውን የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ በድጋሚ ወደ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ ተወስኗል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ግንቦት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት ጨዋታ የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ሊያካሂዱት የነበረው ጨዋታ በጸጥታ ስጋት ምክንያት (የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባደረገው ውሳኔ መሰረት) ውድድሩ ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወቃል።

    የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ጨዋታ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውቆ ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የላከው መግለጫ (በዋና ሥራ አስኪያጁ በተፃፈ ደብዳቤ) እንደሚያመለክተው ፌዴሬሽኑ ለግንቦት 27 ያወጣዉን ፕሮግራም እንደሚቃወመው አስታውቋል። በተጨማሪም ክለቡ ደብዳቤ ላይ በ27ኛ ሳምንት በሜዳው ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር ያለዉን ጨዋታ በሜዳዉና በደጋፊው ፊት እንዲካሄድም ጠይቋል።

    የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውሳኔውን በዚህ ብቻ ሳያበቃ ግንቦት 26 ቀን ለመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ሆቴል ከቀኑ 9:00 ሰዓት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ክለቡ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ ስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (Court of Arbitration for Sport) እንደሚወስደዉም ይፋ አድርጓል።

    እንደገና ግንቦት 26 ቀን የዒድ አል ፈጥር በዓል ማክሰኞ ግንቦት 27 ቀን እንደሚውል ከታወቀ በኋላ ለግንቦት 27 ቀን ተወስኖ የነበረውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በድጋሚ ወደ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ ተወስኗል።

    የኢትዮጵያ ቡና የጻፈው ደብዳቤ

    ጉዳዩ፦ የተላለፈብንን ውሳኔ ስለመቃወም።

    ክለባችን በ25/09/2011 ከመቀሌ 70 እንደርታ ቡድን ጋር በሊጉ 27ኛ ጨዋታ ለውድድር ተዘጋጅቶ መቅረቡ ይታወቃል።

    ሆኖም በእኛ በኩል ምንም ዓይነት ጥፋት ሳንፈጽም የዕለቱ ውድድር ሳይጀምር መሰረዙ ተገልፆልናል።

    በማግስቱ ጨዋታው በወጣበት ፕሮግራም በአስተናጋጅነታችን፣ በሜዳችን የሚካሄድበት ፕሮግራም ይላክልናል ብለን ስንጠብቅ በ26/9/2011 ዓም ውድድሩ በ27/9/2011 በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም በዝግ ስታድየም እንደሚካሔድ የሚገልፅ ደብዳቤ ደረሰን።

    ከፍተኛ ወጪ አውጥተን ወደ መቀሌ በመጓዝና በከተማችንም ቡድናችን በማዘጋጀት ያወጣነው ወጪ ከግምት ሳይገባ የዚህ ዓይነት ውሳኔ መስጠቱ በእጅጉ አሳዛኝ ነው።

    በሌላ በኩ እኛ መቀሌ ለውድድር ሄደን የደረሰብንን በደለ በቃልና በተጨማሪም በፅሁፍ 3 ጊዜ ወሳኔ እንዲሰጠን ስንጠይቅ ምንም ሳይወሰን ዛሬ በእኛ ላይ በምሽት ስብሰባ ተደርጎ የተሰጠው ወሳኔ በእጅጉ ያሳዘነነ ከመሆኑም በላይ፥ ክለባችን ከሜዳው የሚያገኘውን ገቢ በማቋረጥ፣ ወደ አዳማ ጉዞ የምናወጣው ወጪ፣ የከተማዋን ነዋሪና ደጋፊ ሞራል የሚነካ ሁኔታን በመፍጠር ተጫዋቾቻችንን ላላስፈላጊ እንግልት ከመዳረግ በተጨማሪ የሞራልና አካል ድክመት የሚፈጥር በመሆኑ ክለባችን አይቀበለውም።

    ስለሆነም በጋራ ያቋቋምነው ፌዴሬሽን ለሊግ ኮሚቴ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ የዝግ ስታድየም ጨዋታ ውሳኔ መስጠት ያለበት የፍትህ አካል መሆኑ እየታወቀ፥ ሊግ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳነ ሕገ ወጥ ስለሆነ በአስቸኳይ ተሽሮ በሜዳችን፣ ለተመልካች ክፍት በሆነ ስታድየማችን እንድንጫወት ይደረግ ዘንድ እየጠየቅን፥ ከዚህ ውጭ ያለ አማራጭ ክለባችንን የሚጎዳ ስለሆነ የማንቀበለው መሆኑን እንገልፃለን።

    የክለቡ ማኅተም
    የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ፊርማ

    የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያሳለፈው አዲስ ውሳኔ

    የ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ ግንቦት 29/2011ዓ.ም ይካሄዳል።

    በ27ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ግንቦት 25/2011ዓ.ም ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ በጸጥታ ስጋት ምክንያት ጨዋታው መሰረዙ ይታወቃል፤ የሊግ ኮሚቴ ጨዋታው በጸጥታ ስጋት ምክንያት አለመካሄዱን ተከትሎ ግንቦት 27/2011ዓ.ም. በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ያለ ተመልካች /በዝግ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል፤ ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ውሳኔውን በመቃወም ደብዳቤ ያስገባ ሲሆን ጉዳዩን የተመለከተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀደም ሲል የተሰረዘው ጨዋታ ከመንግስት ጸጥታ ኃይል በደረሰ መረጃ የደኅንነት ስጋት በስታዲየም እንዳለ በማሳወቁ በመሆኑ እና አሁንም በድጋሚ በተደረገው ውይይት ይህ ጉዳይ በጥብቅ ሊታይ የሚገባው በመሆኑ እና የመንግስት የጸጥታ ሀይልም የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ባሉበት ጨዋታው መካሄድ የሌለበት መሆኑን በጥብቅ አስገንዝቦናል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታን ግንቦት 27/2011ዓ.ም. ለማካሄድ የዒድ አል ፈጥር በዓል ስለሆነ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሐሙስ ግንቦት 29/2011ዓ.ም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በ9 ሰዓት ያለ ተመልካች በዝግ ይካሄዳል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራሮች አሜሪካ ውስጥ በካሊፎርንያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር አዲስ በተቋቋመው ፓርቲ አጠቃላይ ሁኔታና የሀገራችን ኢትዮጵያን (የፖለቲካ) ነባራዊ ሁኔታን በተመለከተ ተወያዩ።

    የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ናትናኤል ፈለቀ በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ ሦስት ከተሞች ከሚያደርጉት ውይይቶች የመጀመሪያው በሆነው የሎስ አንጀለስ ውይይት፣ የፓርቲው አመሠራረት፣ ለመሥራት የታቀዱ ሥራዎች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በፓርቲው እና በአጠቃላይ ሀገሪቷ ውስጥ እንዲገነባ የሚፈለገው የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዴት ማገዝ እንደሚችሉ ውይይት ተደርጓል። በቪዛ መዘግየት ምክንያት ለስብሰባው መድረስ ያልቻሉት የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ የመክፈቻ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ኢዜማ ባደረገው በዚህ ውይይት፥ የሀገራችንን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችም የውይይቱ አካል ነበሩ። ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ “ሁለንተናዊ መሻሻል” ተብሎ የሚፈረጅ (reform) እንጂ አብዮት (revolution) አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት ያስተላለፉት የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ለውጡ ያልገባቸው (የሚያስጨንቃቸው) የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚፈጥሩት እንቅፋት፣ በየክልሉ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች እና ብዛት ያለው ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቁጥር የለውጡ ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንደሆኑ እና በየደረጃው መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

    በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኢዜማ እንቅስቃሴዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን የሚችሉበት አደረጃጀት (ቻፕተሮች) በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች የሚዋቀሩ ሲሆን በሀገራችን ዜግነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር እና ማኅበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን የሚፈልጉ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በነዚህ መዋቅሮች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ተላልፏል።

    ከፓርቲው ዜና ጋር በተያያዘ፥ የኢዜማ ግብረ-ኃይል በአምስት አቅጣጫ ተንቀሳቅሷል። ከአዲስ አበባ በመነሳት በአምስት አቅጣጫ መዳረሻውን ያደረገ ግብረ-ኃይል ግንቦት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. እንቅስቃሴ ጀምሯል።

    መነሻውን ከመስቀል አደባባይ ያደረገው ግብረ-ኃይል የኢዜማ ምክትል የፓርቲ መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌና የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በተገኙበት መሸኛ ተደርጎለታል።

    ግንቦት 24 ቀንጉዞውን የጀመረው ግብረ ኃይል፣ በኢዜማ ለተደራጁ ለ216 የምርጫ ወረዳዎች ጊዚያዊ የእውቅና ደብዳቤ፣ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ደረሰኝ፣ የአባላት ፎርም እና የድርጅት ጉዳይ መመሪያዎቹን ተደራሽ ለማድረግ በአምስት አቅጣጫዎች ጉዞ ጀምሯል። በየመጀመሪያው ዙር ጉዞ ተደራሽ የሚደረግባቸው፡-
    1. ከአዲስ አበባ – ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ወልዲያ መዳረሻውን ሰቆጣ
    2. ከአዲስ አበባ – ፍቼ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ባህር ዳር አድርጎ መዳረሻውን ጎንደር
    3. ከአዲስ አበባ – ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ፣ ጌድኦ፣ አለታ፣ መዳረሻውን አዶላ (ክብረ መንግስት)
    4. ከአዲስ አበባ – አምቦ፣ ነቀምት፣ ጊምቢ፣ ጅማ፣ መዳረሻውን ቤንች ማጂ
    5. ከአዲስ አበባ – አዳማ፣ አሰላ፣ ወላይታ፣ ሀዲያ፣ ዳውሮ፣ ወልቂጤ፣ መዳረሻውን ጉራጌ በማድረግ ሲሆን በቀጣይም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሌሎች አዳዲስ ቦታዎችንና ከተማዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ጉዞ እንደሚኖር ታውቋል።

    የሀገር መረጋጋትን ቀዳሚ ዓላማ አድርጎ የሚሠራው ኢዜማ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ ይህንኑ ዓላማ ተፈፃሚ ለማድረግ እንዲሠሩ በሁሉም አቅጣጫ የሚጓዙት የግብረ ኃይሉ አባላት አፅዕንዎት ሰጥተው የሚያስገነዝቡ ይሆናል። በየአካባቢው የሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የየአካባቢው ሕዝብ ለግብረ -ኃይሉ አባላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጥሪ ተላልፏል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ


    Semonegna
    Keymaster

    አውታር የተባለውን የሙዚቃ መተግበሪያ ለማዘጋጀት 5 ዓመታት የወሰደ ሲሆን ዕውቁን የሙዚቃ አቀናባሪ ኤልያስ መልካን ጨምሮ የተለያዩ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለሙያዎች በዝግጅቱ ላይ ተሳትፈዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች፣ መተግበሪያ በማዘጃጀት ላይ የተሰማሩ (app developers) እና ኢትዮ ቴሌኮም የረዥም ጊዜ ጥረት በኋላ በሞባይል ስልክ የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች ማግኘት የሚያስችል አዲስ መተግበሪያ ይፋ ተደርጓል።

    ኤልያስ መልካ፣ ጆኒ ራጋ፣ ዳዊት ንጉሡ እና ኃይሌ ሩትስ በጋራ የመሰረቱት አውታር መልቲ ሚዲያ ከሌሎች የሙዚቃ ባለሙያዎች እና ኢትዮ ቴለኮም ጋር በመሆን ጥቅም ላይ እንዲውል ያዘጋጁት አውታር የሙዚቃ መተግበሪያ (music app) ዓርብ፣ ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ ሥራ ጀምሯል።

    አውታር የተባለውን የሙዚቃ መተግበሪያ ለማዘጋጀት 5 ዓመታት የወሰደ ሲሆን ዕውቁን የሙዚቃ አቀናባሪ ኤልያስ መልካን ጨምሮ የተለያዩ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለሙያዎች በዝግጅቱ ላይ ተሳትፈዋል።

    በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉት ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ አውታር መተግበሪያ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘውጎችና ቋንቋዎች ይሸፍናል። ከመተግበሪያው ላይ አንድ ዘፈን ለማውረድ 4 ብር ከ50 ሳንቲም የሚጠይቅ ሲሆን አንድ አልበም ለማውረድ ደግሞ 15 ብር ያስከፍላል ተብሏል።

    የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ የማስፈጸሚያ ሰነድ እንደሚያስፈልገው ተጠቆመ

    “አዲሱ አመተግበሪያ ኢትዮጵያውያን የፈለጉትን ሙዚቃ በፈለጉት ጊዜና ቦታ በእጅ ስልኮቻቸው በኢንተርኔት አማካይነት ለመግዛት ያስችላቸዋል” ይላል ኤልያስ መልካ።

    መተግበሪያውን የሠሩት ባለሙያዎች እንደሚሉት የዚህ ሥራ ዋና ዓላማ ሙዚቃዎቹን በመፍጠር ሂደት ለሚሳተፉ ሁሉ ገቢን ለማሳደግ ነው።
    ገቢን ለማሳደግ ሲባል ለአንድሮይድ ስልክ ተጠቃሚዎች ከተዘጋጀው ከዚህ መተግበሪያ ላይ የሚወርዱትን ሙዚቃዎች ለሌሎች ማጋራት እንዳይቻል መደረጉም ታውቋል።

    ከሙዚቃ ሥራዋ በተጨማሪ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ የምታደርገው ድምፃዊት ፀደኒያ ገብረማርቆስ፥ አውታር የሙዚቃ መተግበሪያ ይፋ መደረግ እና የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን ለመሸጥ እንደ አማራጭ መቅርቡን በጽኑ ከሚደግፉት መካከል አንዷ ነች።

    ሰዎች ዘመናዊ ስልክ መያዝ በመጀመራቸው፣ ኢንተርኔት አጠቃቀማችንም ከፍ እያለ በመምጣቱ እንደዚህ ዓይነት የመሸጫ መንገድ ማስለመዱ መልካም መሆኑን ትገልፃለች።

    ከህመሜ እስከ ስደቴ ከጎኔ ላልተለየው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለመገናኘት አበቃን – አርቲስት ፋሲል ደመወዝ

    ድምጻዊት ፀደኒያ እስካሁን ሥራዎቿን ወደ አውታር ወስዳ በእናንተ በኩል ይሸጥልኝ ብላ ባትሰጥም፤ አገልግሎቱ ከተጀመረ ግን ይህንን ለማድረግ ዓይኗን እንደማታሽ ትናገራለች።

    ብዙ ሰዎች በአንድ ሲዲ ውስጥ ያሉ ሥራዎችን በአጠቃላይ ስለማይወዱት “እያለፉ ነው የሚያደምጡት” የምትለው ድምጻዊት ፀደኒያ፥ ግዴታ አስራ ምናምን ዘፈኖች መግዛት አይጠበቅባቸውም ትላለች።

    ይህ አዲስ መተግበሪያ አንድ ሰው የሚፈልጋቸውንና የሚመርጣቸውን ዘፈኖች ብቻ መርጦ የመግዛት ዕድል ስለሚሰጥ ተመራጭ መገበያያ መንገድ ነው ስትል ሀሳቧን ታጠናክራለች።

    መተግበሪያው የተሠራው ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ሲሆን ቴሌኮሙ የትርፍ ተጋሪ እንደሚሆንም ተነግሯል።

    ምንጭ፦ ቢቢሲ አማርኛ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Awtar አውታር


    Anonymous
    Inactive

    አቶ ነአምን ዘለቀ የኢሳት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል በግላቸው የሰጡት መግለጫ

    ሶሻል ሚዲያ ላይ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፦

    ኢሳትን በሚመለከት የውስጥ “መረጃ” በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ነገር ግን ከሃቁ፣ ከእወነታው ከሂደቱ የራቁ፣ ሕዝብን ለማወናበድ፣ ኢሳትንም ለማፍረስ ሆነ ተብሎ የተደረገ መሆኑ እንዲታወቅ እንወዳለን። የወጣው ስም ዝርዝር ከሀቁ የራቀ፣ መሰረተ ቢስ መሆኑን ለማሳወቅ እወዳለሁ።

    ማንኛውም ተቋም ገቢውን የሚያገኝበት ሁኔታ ሲለወጥ የማስተካከያ እርምጃዎች ይወስዳል። በእኔ በኩል ለአለፉት 4 ዓመታት አራት ሌሎች አባላት የሚገኙበት የኢሳት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሆነን ስንሠራ እንዳደረግነው ሁሉ ኢሳትን የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ የማዋቀርና የማስተካከል በርካታ እርምጃዎች ስንወስድ የቆየን ሲሆን አሁንም ተጨማሪና ተከታታይ እርምጃዎችን እንደሚወስድ በአፕሪል 18 ቀን 2019 (ሚያዝያ 10 ቀን 2011 ዓ.ም.) ለሕዝብና ለኢሳት ቤተስቦች ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

    በተጨማሪም ኢሳት ከለውጡ በፊት በነበረው አቅምና ሁኔታ ማስቀጠል እንደማይቻል ለኢሳት ባልደረቦች ስናሳስብና ለወራት ያህል ብዙ ዝርዝሮች የሚገኙበት ውይይቶች ስናደርግ ቆይተናል፤ መፍትሄዎችም ለማፈላለግ ብዙ ጊዜ በርካታ ስብሰባዎች ተደርገዋል። ካስፈለገ ሁሉንም ጉዳይ ከጅምሩ እስካሁን የነበረውን በተለያዩ ደረጃዎች የተደረጉትን ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ ለማድረግ እንደሚቻል መታወቅ አለበት።

    ይህ “መረጃ” ተብዬ የወጣው ኢሳትን ለማፍረስ በዚህም ተጠቃሚ ለመሆን በታቀደ መልኩ ሆን ተብሎ የተሠራና ከዶ/ር ብርሃኑም ሆነ ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በመሆን የተወሰነ የፓለቲካ አስተሳሰብ ያላቸውን ለማጥቃት የታለመ እንደሆነም የተሰራጨው “መረጃ” መሰረተ-ቢስ መሆኑን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማረጋገጥ እወዳለሁ።

    “ቅጥረኛ” በሚልም እኛን ለመወንጀል የደፈሩ ግለሰቦችም ሆነ “መረጃው”ን የሰጧቸው ሰዎች በዚህ ሸፍጥ የሚያሸንፉና ሕዝብን የሚያወናብዱ ከመሰላቸው ይህ እንደማይሳካላቸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማን ምን እንደነበር፣ ከየትስ እንደመጣ፣ መቼ ወደ ኢሳት እንደመጣ፣ ማንስ እንዳመጣው፣ እኛም ምን እንዳደረግን፣ ከየት ወዴት እንደተጓዝን፣ ሁሉንም እስካሁን ድረስ የተደረገውን ጉዞ ከማስረጃና ከሰነዶች ጋር ለማቅረብ ስለሚቻል ሕሊናቸውን እንዲመረምሩና ከዚህ የአደባባይ ነውር ቢታቀቡ የተሻለው መንገድ ነው በማለት በግሌ ሁሉንም ለማሳሰብ እወዳለሁ።

    እዩኝ፣ እዩን ስለተባለ ብቻ “እኛ ብቻ ጋር ሀቅም፣ እውነትም፣ የትግል ባለቤትነትም፣ ዕውቀትም፣ አልፎሞ አሁን ደግሞ ኢሳትም ‘የእኔ’ ብቻ ነው” ባዩ የበዛበት ዘመን ላይ ስለሆንን፣ ነውር ውስጥ እየገቡ እኛን ምላሽ እንድንሰጥ፣ ህዝብም እንዲያዝን የሚያስገድዱን ማናቸውም ወገኖች ሁሉ በድጋሚ፣ ባለፈው እንደሆነው ስም ወደማንሳትና ጭቃ መወራወር እንደተገባው እንዳይሆን በጥብቅ ለማሳሰብ በግሌ እወዳለሁ።

    እውነት ያወጣሀል እንደሚባለው ሃቁን፣ ሂደቱን፣ እውነቱን በዝርዝር ለማውጣት ምንም የምንቸገርበት፣ የምናፍረበትም፣ ለማንም ለምንም ኣንደማንመለስ፣ እንደ አንዳንዶች “ቅጥረኛ’ ሳንሆን 26 ዓመታት ለኢትዮጵያ ህዝብ ፍትህን፣ ነጻነት፣ ለማምጣት ሁለንተናዊ ትግል ያደረግን፣ ሁሉንም ነጋራችንን የሰጠን፣ ከማንም ምንም የማንፈልግ ግለሰቦች እንደምንገኝበት ለህሊናችን ያደርንና ይህንኑ ይዘን እስከ ዕለተ ሞታችን እንደምንቀጥልም ሆዳቸው የሚያውቁ፣ ነገር ግን ይህን ርካሽ ተግባር የትም የማያደርሳቸው ግለሰቦች እንዲያስቡበት፣ ወደ ህሊናቸው እንዲመለሱ በግሌ በጥብቅ ለማሳሰብ እወዳለሁ። ለሁሉም ጎራ ስናሳስብ፣ በግልም፣ በቡድንም፣ በአደባባይ ስም ሳይጠቀስም ለሁለት ሳምንታት እንደተጻፈውና ፣ ለበርካታ ወራት ኢሳት ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ስናደርግ እንደከረምነው።

    አቶ ነአምን ዘለቀ የኢሳት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል (በግል)

    Semonegna
    Keymaster

    ከኢሳት (ESAT TV) የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    ጉዳዩ፦የኢሳትን (ESAT TV) መዋቅርና አሠራር ማስተካከልን ይመለከታል

    ጊዜው ኢሳትን የመሰሉ የኢትዮጵያዊነትና የዲሞክራሲ ድምጾችን አገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የምትፈልግበት ነው። ኢሳትም (ESAT TV) ለዚህ አገራዊ ጥሪ መልስ ለመስጠት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ተጠናክሮ ለመሥራት ቃል መግባቱን በድጋሚ ለማስታወስ እንፈልጋለን።

    የኢሳት ቦርድ (ESAT TV Executive Board) ባለፈው ኤፕሪል ወር (April 2019) ውስጥ ይህንን ጥሪ በወጉ ለመመለስ በስድስት አስፈላጊ የሆኑ ኢሳትን የማጠናከሪያና የማሻሻያ አቅጣጫዎች ከተቋሙ ሠራተኛና የድጋፍ ኮሚቴ ተወካዮች ጋር በመመካር መወሰን እንደሚጀመር አስታውቆ ነበር። በዚህ መሰረት ሜይ 28፣ 2019 (ግንቦት 20 ቀን 2011 ዓ.ም.) ቦርዱ ከመላው ዓለም አቀፍ የኢሳት ባልደረቦች ጋር በመሰብሰብ የመጀመሪያውን ውሳኔ ይፋ አድርጓል።

    ይህ ውሳኔ ያተኮረው ኢሳት ኢንተርናሽናልን በባጀት፣ በሰው ኃይል፣ በፕሮግራሞች ይዘትና አቅጣጫዎች እንዲሁም በአስተዳደር አቅም ከዘላቂነት ጋር እንዲጣጣም ማድረግን ይመለከታል። ውሳኔው እንደማንኛውም ተቋማዊ የመዋቅር የማስተካከያ እርምጃ ጊዜያዊ ችግሮችን ሊፈጥር ቢችልም በዘላቂነት ግን ኢሳትን (ESAT TV) በሁሉም ዘርፍ አቅሙንና ሕዝባዊነቱን በማጠናከር የተመሰረበትን መሰረታዊ ዓላማ እውን ማድረግ ነው።

    ይህንን መሰረተ ሃሳብ በደንብ ተገነዘቦ በሚሠራ የኢሳት አስተዳደርና ባለሙያዎች የተወሰነን ውሳኔ የፖለቲካ ፉክክር ጨዋታ ውስጥ እያስገቡ መተርጎም ትክክል አይሆንም። ይህ ውሳኔ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሰሞኑን እንደሚወራው በኢሳት ውስጥ ያሉ የጋዜጠኞች የሃሳብ ልዩነቶች ጋር የተያያዘ አይደለም። ኢሳት የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም። በባለሙያዎቹ ውስጥ እንደማንኛችንም የህብረተሰብ አባላት የተለያየ የግል እምነትና የፓለቲካ አመለካከቶች እንደሚንጸባረቁ ግልጽ ነው። ሆኖም እንደ ሚዲያ ተቋም የኢሳት ሚና የመንግሥትን ወይም የማንንም አንድ ወገን ፍላጎትን መቃወም ወይም መደገፍ ሳይሆን ሙያዊ ብቃት ያለው አስተማማኝና የተጣራ መረጃ የሚያቀርብ የህዝብ ሚዲያ ሆና ማገልገል ነው።

    የኢሳት ግብ በነጻነት፣ በሙያዊ የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር፣ እንዲሁም በሕዝባዊ ዓላማ ላይ ተመስርቶ የሚዲያ ምርቶችን በማምረት፡ በፓለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና፣ ባህላዊ ርዕሰ ጉዳዮች እንዲሁም የተጣሩ መረጃዎች በማቅረብ ሕዝብን ማገለገል ነው። በተለይ አሁን ሀገራችን ባለችበት ሁኔታ ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ማበረታታት፣ የሀገሪቱም ችግሮችና ተግዳሮቶች በዲሞክራሲያዊ መንገድና በውይይት የመፍታትን ባህል እንዲስፋፋ መርዳት ነው።

    ይህንን መሰረተ ሃሳብ በደንብ ተገነዘቦ በሚሠራ የኢሳት አስተዳደርና ባለሙያዎች የተወሰነን ውሳኔ የፖለቲካ ፉክክር ጨዋታ ውስጥ እያስገቡ መተርጎም ትክክል አይሆንም። ዛሬ የተጀመረው የኢሳት ማጠናከሪያ በቅርቡም በቦርድ፣ በአስተዳደር፣ በኤዲቶሪያልና በአጠቃላይ የኢሳት አሠራር ላይ ይቀጥላል። ኢሳት በመጀመሪያ የሥራ ምዕራፉ ማለትም በሀገራችን ከ 27 ዓመታት በላይ የተሰራፋውን አፋኝና ዘረኛ ስርዓት በማስወገድ ሂደት ያበረከተውን አስተዋጽኦ በሚቀጥለውም የሀገርና የሕዝብ አንድነትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሥራ ምዕራፍ ውስጥም እንደሚቀጥል ጥርጥር የለንም። ለዚህም የኢሳት ቤተስቦችና የድጋፍ ኮሚቴዎች እንደወትሮው ኢሳት የህዝን ዓይንና ጆሮ ሆና እንዲቀጥል የበኩላችሁን እንድታደረጉ ትብብራችሁን በአክብሮት እንጠይቃለን።

    ጁን 1 ቀን፣ 2019 (ግንቦት 24 ቀን 2011 ዓ.ም.)፣ ዋሺንግተን ዲሲ
    የኢሳት (ESAT TV) ቦርድ ሥራ አስፈጻሚ
    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ኢሳት (ESAT TV)


    Semonegna
    Keymaster

    ፊቼ ጫምባላላ በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ከተመዘገቡ ቅርሶቻችን ውስጥ አንዱ ነው። የፊቼ ጨምበላላ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት በዓል መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ገልጸዋል።

    ሀዋሳ (ሰሞነኛ) – የሲዳማ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ፊቼ ጫምባላላ በሀዋሳ ከተማ በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉ ላይ ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡ የሲዳማ አባቶች የቄጣላ ሥነ-ስርአት አድርገዋል።

    በሀዋሳ ጉዱማሌ አደባባይ በልዩ ሁኔታ የተከበረው በዓል ላይ የሲዳማ ሴቶች በባህላዊ አለባበስ እና ባህላዊ የፀጉር አሰራር አሸብርቀው የበዓሉ ድምቀት ሆነዋል።

    በበዓሉ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተጋበዙ ልዑካንም የተገኙ ሲሆን፥ ከደቡብ ክልልም ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተውጣጡ ልዑካን ታዳሚዎች ሁነው ነበር።

    የፊቼ ጫምባላላ በዓል በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ከተመዘገቡ ቅርሶቻችን ውስጥ አንዱ ነው። የፊቼ ጨምበላላ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት በዓል መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ገልጸዋል።

    በዓሉ በጋራና በድምቀት እንዲከበር ዋጋ ከፍለው በዓሉን እዚህ ላደረሱት አባቶች ምስጋና አቅርበዋል – አቶ ሚሊዮን። አክለም በዓሉ በይቅርታና በፍቅር የምናከብረው በዓል በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፍቅር እንዲያከብረውም ጥሪ አቅርበዋል።

    የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፥ ፊቼ ጫምበላላ የኛም ባህል በመሆኑ ለማድመቅ ሳይሆን ለማክበር ነው ወደ ሀዋሳ የመጣነው ሲሉ ገልጸዋል። ባህሉ ተጠብቆ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲቆይ አባቶቻችን ታላቅ ሚና በመጫወታችሁ ምስጋና ይገባችሀል በማለትም ተናግረዋል።

    አቶ ሽመልስ መልዕክታቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት የሲዳማና የኦሮሞ ህዝብ አብሮ ብዙ መስዋዕትነትን የከፈለና ድል ያስመዘገበ ህዝብ ነው ሲሉም ገልጸዋል – አቶ ሽመልስ። እኩልነትን፣ ነፃነትንና ወንድማችነትን በማጠንከርና በማሳደግ የተገኘውን ድል ለማስቀጠል መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። ልዩነታችንን ጠብቀን አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ በመሥራት ለበለጠ ድል መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል። በዚህም የሁለቱም ወገኖች የሆኑት ኤጀቶና ቄሮዎች ተባብረው ለክልሎቻቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ እድገት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

    የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው፥ ባህሉ ከትውልድ ትውልድ ተጠብቆ እንዲተላለፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተገቢውን ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ከቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን የወረስናቸውን እንደ ፍቼ ጫምበላላ ያሉ ባህሎቻችንን ጠብቀንና ተንከባክበን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

    የፖለቲካ አክቲቪስትና የኦሮሚያ ሚድያ ኔትዎርክ (ኦ.ኤም.ኤን) ቴሌቭዥን ጣቢያ መሥራች የሆነው አቶ ጃዋር መሀመድ በበኩሉ፥ ፊቼ ጫምበላላ በዓልን ያለ አንዳች ችግር ማክበር መቻሉ እንደሚያስደስት ገልጿል። በዓሉ ቀደምት አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ እየተከበረ ያለ ቅርስ መሆኑን ተናግሯል። በዓሉ እንዲህ እንዲከበር ኤጀቶና ቄሮዎች ለሰላም ያደረጉት ትግል ውጤት መሆኑንም ገልጿል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ፊቼ ጫምባላላ


    Semonegna
    Keymaster

    ከዴሞክራሲና ከነጻነት ጋር የተቆራኙ እሴቶች
    (ነአምን ዘለቀ)

    ከዴሞክራሲና ከነጻነት መብቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸው እሴቶችና ከእነዚህ ጋር የተገናኙ ንድፈ ሃሳቦች ከፍልስፍና አኳያ መነሻቸው አንዱ የሰው ልጅ ክቡርነትና የግለሰብ ሉዓላዊነት መከበር ጋር የተጋመዱና የተያያዙ መሆናቸው ነው። ዴሞክራሲም ሆነ ነጻነት የሰው ልጆችን ክብር፣ የእያንዳንዱን ሰው ሰብዓዊ ክቡርነት (dignity) ከልብ ካልተቀበለ፣ አንዱ ሌላውን ሰው እንደመጠቀሚያ፣ ለአንድ ግብ ማስፈጸሚያ መሣሪያ (means to an end/instrument) የሚመለከት ከሆነ፥ ለምሳሌ በፓለቲካም ሆነ በሌላ “እገሌን ለዚህ ጉዳይ ተጠቀምኩበት” እንደሚባለው ከሆነ ስር የሰደደ የእሳቤው፣ የእሴቶች፣ እንዲሁም የፍልስፍናው ግንዛቤ ላይ ከፍተኛ እጥረት አለ ማለት ነው። ይህንንም በጥልቀት በንድፈ ሃሳብ (theory)፣ እንዲሁም በጽንሰ ሃሳብ (concept) ደረጃ በጥልቀት ማወቅ ቢቻልም፣ ከልባችን ጋር አልተዋሃደም (internalized አልሆነም) ማለት ነው።

    ሰዎችን የግብ ማስፈጸሚያ አድርጎ ማየት ብዙ ጊዜ የግራም ሆነ የቀኝ ርዕዮትን ያነገቡ በጣም ጨካኝና ጠቅላይ ከሆኑ (totalitarian) ርዕዮቶች/ፍልስፍናዎች ፣ የነዚህ ውላጅ ከሆኑ የፓለቲካ ስርዓቶችም የሚመነጭ ነው። በምዕራባውያኑ ዘንድ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በሰፊው የተጻፈበትና ልዩ ልዩ አመለካከቶች ያሉ ቢሆንም ከሊበራሊዝም አኳያ በርሊን፣ ከፕራግማቲዝም ሪቻርድ ሮርቲ (Richard Rorty)፣ ከሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ የማርክሳዊ ፍልስፍና አመለካከቶች እንደ ኤሪክ ፍሮም (Erich Fromm) እንዲሁም ሌሎችም ፈላስፎችና ሃያሲዎች የእነዚህ ጠቅላይ ርዮተ ዓለሞች ቅድመ መነሻ/መሠረት ከጥንታዊ ግሪክ ከፕሌቶ ፍልስፍና መሆኑን ተንትነውበታል። ነገር ግን የምዕራባዊ ስልጣኔና አካል ባልሆኑ፣ የእኛንም ማኅበረሰብ ጨምሮ ይህ አመለካከት በቅድመ ዘመናይ (pre-modern) ስርዓተ መንግሥታት የፓለቲካ፣ የባህልና ፣ ማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥም ሰፍኖ የነበረ መሆኑ ግልጽ ነው።

    በርካታና እጅግ አንገብጋቢ ሃገራዊ ጉዳዮች ቢኖሩም ቅሉ፣ አንዱ የችግሮቻችን ምንጭ ከአስተሳሰብ ጋር፣ ከአመለካከቶች ጋር የተያያዙ ጎጂ የአስተሳሰቦችና እሴቶች (values) መሆናቸው ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። የሰው ልጅ ውስብስብ ፍላጎቶች ያለን ፍጥረቶች ነንና ወደ ውስጥ መመልከትና የትኛው ፍላጎት ለምን አላማ የሚለውን ራስን መሞገት ወደ ተሻለ በበጎ የሞራል እሴቶች ላይ የተመሠረተ የፓለቲካ ማኅበረሰብ ለማጠናከር የራሱ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የፓለቲካ ጉዳይ ከስልጣን ጋር የተያያዘ መሆንና፣ በዴሞክራሲም ሆነ ዴሞክራሲያዊ ባልሆኑ የፓለቲካ ስርዓቶች ውስጥ ስልጣን (power) የሰው ልጆችን ‘ኮራፕት’ [corrupt] (በጥቅም ብቻ ሳይሆን ስልጣን ላይ ያሉትንም ሆነ ወደ ስልጣን የሚመጡትን ሰዎች የሞራል እሴቶን በማዳከም ጭምር) የማድረግ አቅሙ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ቢታወቅም፥ ፍትህ፣ ዴሞክራሲና ነጻነት በሀገራችን እንዲመጣ ከልብ ከተፈለገ ደግሞ ከነዚህ ዓይነት አመለካከቶች ለመጽዳት መሞከር አንዱ የቤት ሥራ መሆን አለበት ማለት ነው።

    የሰውን ልጅ ክቡርነት (dignity) ከልብ ማመን፣ ይህ እሴት እንዲዋሀደን ማድረግ፣ ለዲሞክራሲያዊ ባህል መስፈን፣ ፍትሃዊና ሰብአዊነት የነገሰበት ስርዓት እውን እንዲሆን ለማድረግ በጣም ወሳኝ ከሆኑ እሴቶች አንዱና ዋነኛው ነው። ቅዱሳን መጻህፍትም የሚሉት ‘በአንተ ላይ ሊደረግ የማትፈልገውን በሌላው ሰው ላይ አታድርግ’ ይመስለኛል። ፓለቲካው በርካታና አስፈላጊ የሞራልና የስነ-ምግባር እሴቶች ያስፈልጉታል የሚለው ዋናው ጭብጥ ነው – በተለይ በፓለቲካ ልሂቃን (political elites)። በቀጣይነት ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ይኖራሉ። በቸር ይግጠመን።

    አቶ ነአምን ዘለቀን ፌስቡክ ገጻቸው ላይ ይከተሏቸው (Like ያድርጓቸው)፦ Neamin Zeleke
    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ከዴሞክራሲ እና ከነጻነት ጋር የተቆራኙ እሴቶች


    Anonymous
    Inactive

    የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ ዓመት ተማሪ ሆሳዕና ከተማ ውስጥ ባልታወቁ ሰዎች ተገደለ
    —–

    ሆሳዕና (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የ2011 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን መማር-መስተማር ተግባር በሰላም እየተገባደደ ባለበት ወቅት፥ አንድ ያልተጠበቀ አሳዛኝ ክስተት ተከስቷል፡፡ ይኸውም በዩኒቨርሲቲው የምህንድስናና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የኤሌክትሪከል ምህንድስና ትምህርት ክፍል የ5ኛ ዓመት ተማሪ በሆነው ዓለሙ ባሣ ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. የደረሰው ድንገተኛ ህልፈተ ሞት ነው፡፡

    በተማሪው ላይ የሞት አደጋ የደረሰው ወጣቱ ከዩኒቨርሲቲ ውጪ በሆሳዕና ከተማ ከጓደኞቹ ጋር አምሽቶ ሲመለስ በመንገድ ላይ ባጋጠመው ግጭት መሆኑ ተዉቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሆሳዕና እና የሀዲያ ዞን ፖሊስ መምሪያ፣ ዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማኀበረሰብ ባደረጉት ብርቱ የተቀናጀ ትብብርና ክትትል ሁሉም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡ ምርመራው እንደተጠናቀቀም ለፍርድ እንደሚቀርቡ እምነታችን ነው፡፡

    በዚህ አጋጣሚ በተማሪ ዓለሙ ባሳ በደረሰው ድንገተኛ ህልፈተ ሞት ምክንያት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ስም እየገለጽን፥ ለውድ ቤተሰቦቹ፣ ለወላጅ ዘመዱና ለሚወዱት ጓደኞቹ ከፈጣሪ ዘንድ መጽናናትን እንመኛለን፡፡ እንደዚሁም በዚህ አስቸጋሪና አስደንጋጭ በሆነው ክስተት ወቅት ተማሪዎች ላሳዩት መረጋጋትና በሳል ስሜት፥ የዞንና፣ የሆሳዕና ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቶች ተጠርጣሪዎችን በማሰስና በቁጥጥር ስር በማዋል ለፈጸሙት ፖሊሳዊ ጀብድ፣ የአካባቢውና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ስላሳዩት ትኩረትና ትብብር ከልብ የመነጨ ምስጋናን ለመቅረብ እንወዳለን፡፡

    ምንጭ፦ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

Viewing 15 results - 451 through 465 (of 730 total)