Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Viewing 15 results - 616 through 630 (of 730 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    የሚገነባው የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል በኢትዮጵያ በቀዳሚነት በግል ዘርፉ የሚመራ ሆኖ መንግስት ክበባዊ ሁኔታን የማመቻቸት ሥራ ይሠራል። መንግስት ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው የቦታ መረጣም ሆነ መሠረት ልማት በፍጥነት እንደሚያሟላም ተጠቁሟል።

    አዲስ አበባ (ኢ.ፕ.ድ)– የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል በኢትዮጵያ ለመገንባት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፍ ፖስታል ዩኒየን መካከል ስምምነት ተደርጓል።

    የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እና የዓለም አቀፍ ፖስታል ዩኒየን (Universal Postal Union) ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ቢሻር ሁሴን ስምምነቱን ተፈራርመዋል። ሚኒስትሩ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንግስት የቦታ አቅርቦትና መሠረተ ልማት የማሟላት ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፤ የዓለም አቀፍ ፖስታል ዩኒየን ደግሞ ሥርዓቱን የመዘርጋት ኃላፊነቱን ወስዷል።

    እንደ ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን ገለጻ፥ በአዲስ አበባ ይገነባል የተባለው ማዕከል በአፍሪካ ውስጥ ከሚገነቡ አራት ኢ-ኮሜርስ ማዕከላት አንዱ ሲሆን፥ ቀድሞ የምስራቅ አፍሪካ የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ኬንያ ናይሮቢ ሊገነባ ታቅዶ የነበረው ነው። ወደ አገራችን የመጣበት ምክንያት ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ እያደገች መምጣቷ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚያደርገው በረራ መበራከቱና የኢትዮጵያ መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት ዋንኞቹ ናቸው።

    ተመሳሳይ ዜና፦ Chinese giant e-commerce Alibaba Group & its affiliate Ant Financial entering Ethiopian market

    ማዕከሉ በኢትዮጵያ በቀዳሚነት በግል ዘርፉ የሚመራ ሆኖ መንግስት ክበባዊ ሁኔታን የማመቻቸት ሥራ ይሠራል። መንግስት ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው የቦታ መረጣም ሆነ መሠረት ልማት በፍጥነት እንደሚያሟላም ጠቁመዋል።

    የማዕከሉ መገንባት ከፍተኛ ሀገራዊና አህጉራዊ ጠቀሜታ አለው ያሉት ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን፥ ለ100ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል። የአፍሪካ ምርቶች ለማንኛውም ሀገራት በቀላሉ እንዲታዩ በማድረግ ገበያውን በቀላሉ እንዲቀላቀሉ ዕድል ይሰጣል ብለዋል።

    በኢትዮጵያ የገንዘብ ዝውውር በኤሌክትሮኒክ እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፥ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባና የገንዘብ ዝውውርን ለማቀላጠፍና የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመን ሚናውን ይወጣል። ዓለም በአሁኑ ወቅት በኤሌክትሮኒክ ግብይት በጣም ርቆ መሄዱን ተከትሎ በአፍሪካ ደረጃ አስፍቶና ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

    በዘርፉ ኢትዮጵያ ብዙም ተጠቃሚ እንዳልሆነች የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ዘመኑ የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ዓለም ነውና ከዓለም ጋር እኩል ለመጓዝ ማዕከሉን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። በዓለም ላይ እንደ አማዞን (Amazon)፣ አሊባባ ግሩፕ (Alibaba Group) እና የመሳሰሉ በኤሌክትሮኒክ ግብይት በዓመት እስከ አምስት ትሪሊን ዶላር እንደሚያንቀሳቅሱ ሁሉ በማዕከሉ አማካኝነት አገሪቱ ለማደግ የሚያስችላትን ተግባራት ሁሉ ትሠራለች ብለዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢ.ፕ.ድ) | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ኢ-ኮሜርስ ማዕከል


    Semonegna
    Keymaster

    ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የ2011ዓ.ም. አዲስ ገቢ ተማሪዎችን በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት መጨረሱን ገለጸ። ዩኒቨርሲቲ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ራሱን ለማስፋፋት ያስችለው ዘንድ መምህራንን እና ሠራተኞችን በስፋት እየቀጠረ ነው።

    አሰበ ተፈሪ (ሰሞነኛ) – ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የ2011ዓ.ም. አዲስ ገቢ ተማሪዎችን በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት መጨረሱን ገለጸ።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙክታር ሙሀመድ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በ2010ዓ.ም. ተማሪዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀብሎ ማስተማር የጀመረ ሲሆን፥ በማስፋፊያ ግንባታ መዘግየት ምክንያት በ2011ዓ.ም. የተመደቡትን ተማሪዎች እስካሁን ድረስ ጥሪ ያላደረገ አብራርተው በዚህ ወር መጨረሻ ግን ለተማሪዎቹ ጥሪ እንደሚያደርግ ገለጸዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ግርማ መኮንን በበኩላቸው የተማሪዎች የመኖሪያ ቤቶች (ዶርምተሪ) ግንባታ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ 15 ቀናት ውስጥ በማስታወቂያ ለተማሪዎቹ ጥሪ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

    የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጤና እና የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ 220 የጤና ባለሞያዎችን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማን በተገኙበት ዛሬ አስመርቋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ራሱን ለማስፋፋት፣ የትምህርት ክፍሎችን (ዲፓርትመንቶች) እና የተማሪዎችን ቁጥር ለመጨመር ያስችለው ዘንድ መምህራንን እና ሠራተኞችን በስፋት እየቀጠረ ነው።

    ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ዓመት በአካባቢው ያለውን የብዝሀ ሕይወት ለመንከባከብና ለመጠበቅ በሚል ዓላማ ከኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ጋር ተባብሮ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት መፈራረሙን መዘገባችን ይታወሳል።

    ምንጭ፦ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ


    Semonegna
    Keymaster

    ሐረር (ሰሞነኛ)–የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጤና እና የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ 220 የጤና ባለሞያዎችን ዛሬ አስመርቋል። በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማን ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች ዘርፉ የሚጠይቀውን ሥነ- ምግባር በመላበስ ኅብረተሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት “ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች የሙያውን ሥነ- ምግባር በመላበስ ኅብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት የማገልገል ኃላፊነት ተጥሎባችኋል” ብለዋል።

    “ከራስ ጥቅም ይልቅ ለወገን ቅድሚያ መስጠት፣ ብልሹ አሠራሮችን መከላከልና ውጤታማ ሥራን በማከናወን ለሌሎች አርአያ መሆን ይጠበቅባችኋል” ሲሉም አሳስበዋል።

    ◌ ቪዲዮ፦ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት በአጭሩ

    በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ የተመሠረተውን የአገሪቱን የጤና ፖሊሲ የሚያጠናክሩ አገልግሎቶችን መስጠትና ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ እንዲሁም በእናቶችና ህጻናት ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

    የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደዘገበው የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድ አቶ ኦርዲን በድሪ ዩኒቨርሲቲው በጤናው ዘርፍ የባለሙያዎችን እጥረት ለማቃለል እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ኮሌጁ በህክምና ሳይንስ ዘርፍ እያከናወነ ባለው የመማር፣ ማስተማርና ምርምር ሥራዎች በክልሉና አጎራባች አካባቢዎች እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ዘርፉን የሚያጠናክሩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የተማረ የሰው ኃይል የማፍራት ሥራውን እንዲያጠናክር የክልሉ ህዝብና መንግሥት ድጋፍ እንደማይለየው ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።

    የዩኒቨርሲቲው በሐረር ከተማ በሚገኘው ኮሌጁ በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር ካስመረቃቸው መካከል 173ቱ የህክምና ዶክተሮች መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የኮሌጁ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ያደታ ደሴ ናቸው። ቀሪዎቹ ተመራቂዎች በመጀመሪያ ዲግሪ በነርስነት የሰለጠኑ ናቸው። በተያያዘም ከአጠቃላይ ተመራቂዎች ውስጥ 38ቱ ሴቶች መሆናቸውንም ዶ/ር ያደታ ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ኮሌጁ በዚህ ዓመት በሕክምና ሳይንስ የቅድመ ምረቃ መርሐ ግብር በ11 ዘርፎች 2ሺህ 616 ተማሪዎች እያሰለጠነ ነው።

    ◌ ተመሳሳይ ዜና፦ Addis Ababa University’s School of Medicine graduates 288 medical doctors

    በዕለቱ በከፍተኛ የማዕረግ ዕጩ ተመራቂ ዶ/ር ምኅረት ለገሠ “የሙያ ሥነ- ምግባሩን በማክበር ኅብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ” ብላለች። የእናቶችንና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ፣ የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻልና በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል የተየዘውን ጤና ልማት ግብ ለማሳካት የበኩሏን እንደምትወጣ ገልጻለች።

    ዕጩ ተመራቂ ዶ/ር ቢሊሱማ ደገፉ በበኩሉ አገሪቱ የነደፈችውን የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቋል።
    የሐረማያ ዩኒቨርሲ ከአገሪቱ ቀደምት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ ቢሆንም፤ የህክምና ዶክተሮችን ሲያስመረቅ የአሁኑ ለሰድስተኛ ጊዜ ነው።

    ምንጭ፦ ኢዜአ | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ


    Semonegna
    Keymaster

    አርባ ምንጭ (ሰሞነኛ)– ከ875 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበት በ2007 ዓ.ም. በ6 ሄክታር መሬት የግንባታ ሥራው የተጀመረውና በ2 ዓመት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል በአገራዊ የገንዘብ ግሽበትና የእቃዎች ዋጋ መናር ምክንያት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ አለመቻሉን የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ገለጸ።

    የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝደንት ተወካይ ወ/ሮ ታሪኳ ወልደመድኅን እንደገለጹት ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማስጨረስ ዩኒቨርሲቲው በ2011 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከጠየቀው 450 ሚሊየን ብር በጀት በፌዴራል መንግሥት የተፈቀደው 166 ሚሊየን ብር ብቻ ሲሆን ይህም ገንዘብ ቢሆን በወቅቱ ሊለቀቅ አልቻለም። የበጀት ችግሩ እንዳለ ሆኖ ከተቋራጭ ድርጅቱ ጋር መግባባት በመፍጠር በተቻለ መጠን ሥራዎች አየተሠሩ መሆኑን ተወካይዋ ተናግረዋል።

    ከአገር አቀፍ የገንዘብ እጥረቱ በተጨማሪ የዲዛይን ሥራዎች እና በሆስፒታሉ ዙሪያ የድንበር ማካለሉ ሥራ ሙሉ ለሙሉ አለመጠናቀቅ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቅ ካደረጉ ምክንያቶች ዋናዎቹ ናቸው። ድንበር ማካለሉን አስመልክቶ በሆስፒታሉ ዙሪያ ከይዞታቸው ተነሺ ከሆኑ 60 መኖሪያ ቤቶች ለ47ቱ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ጋር በመሆን ተመጣጣኝ ተለዋጭ የመኖሪያ ቦታ ተመርጦ የዲዛይኑ ሥራ ያለቀ ሲሆን በዩኒቨርሲቲውና በከተማው ማዘጋጃ ቤት ትብብር ለነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለማከናወን በሂደት ላይ ነው። ለቀሪዎቹ ተነሺ ነዋሪዎችም ለመኖሪያ ቤት የሚሆን የቦታ መረጣ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

    ◌ ተመሳሳይ ዜና፦ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው ዘመንዊ የህክምና ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎችች ባለስልጣናት በተገኙበት ተመረቀ

    የሆስፒታሉን ግንባታ በማከናወን ላይ የሚገኘው ይርጋለም ኃ/የተ/የግል ማኅበር መሀንዲስ ይህደጎ ተስፋዬ እንደተናገሩት የግንባታ ሥራዎች በታቀደላቸው ጥራት በመከናወን ላይ ቢገኙም በዩኒቨርሲቲው በኩል የሚለቀቀው ገንዘብ ወቅቱን ጠብቆ አለመድረስ፣ በአማካሪው በኩል የዲዛይን ሥራዎች ሙሉ በሙሉ አለማለቅ እንዲሁም የድንበር ወሰን ማካለል ችግር ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዳይጠናቀቅ ምክንያቶች ሆነዋል። የጋዝና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሲስተሞቹ በሪፈራል ሆስፒታል ግንባታዎች ከተሰማራንባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ ዘመናዊነትን የተላበሱ ናቸው ያሉት መሀንዲሱ፥ በአጠቃላይ ሊገነቡ ከታሰቡት 11 ግንባታዎች የሪፈራል ሆስፒታሉ ዋና ህንፃ፣ የአካል ጉዳተኞች መወጣጫ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ብቻ ግንባታቸው ከ90% በላይ መድረሱን ገልጸዋል።

    አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ በማድረግ 7 የመወጣጫ ሊፍትና 400 አልጋዎች ያሉት ዘመናዊው ሆስፒታል በውስጡ መረጃዎች በዘመናዊ መልክ የሚደራጁበት ዳታ ሲስተም (Data System)፣ ህመምተኞች በቀላሉ የህክምና ባለሙያዎችን የሚጠሩበት ነርስ ኮል ሲስተም (Nurse Call System)፣ የሆስፒታሉን ደኅንነት የሚቆጣጠሩ ዲጂታል ካሜራ ሲስተም (Digital Camera System)፣ ታካሚዎችን የሚያዝናኑና በቂ መረጃን የሚሰጡ የቴሌቪዥን ሲስተም (TV System) እና መሰል ዘመናዊ ሲስተሞች የተገጠሙለት ነው።

    የዘመናዊውን የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የማማከር ሥራ የሚሠራለት ሲሆን ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለመማር-ማስተማር ሂደት አጋዥ ከመሆኑም በተጨማሪ ለምርምር ሥራ መዳረሻ እንደሚሆን ይሆናል።

    ምንጭ፦ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል

    Semonegna
    Keymaster

    የገቢዎች ሚኒስቴር የነደፈው ብሔራዊ የግብር ገቢ ንቅናቄ ዜጎች ግብር መክፈል ሀገራዊ ግዴታቸው መሆኑን በማስገንዘብ እና ከዜጎች የሚሰበሰበውን ግብር በመጨመር ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2025 የመካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ውስጥ ለመመደብ የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል ተብሎ ይጠበቃል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ጠንካራ የግብር ዘርፍ እንዲኖር ጠንካራ መሠረተ ልማት እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት “ግዴታዬን እወጣለሁ፣ መብቴን እጠይቃለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን ብሔራዊ የግብር ገቢ ንቅናቄ (National Tax Revenue Movement) ታህሳስ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በይፋ ሲያስጀምሩ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው እንዳሉት ቁሳዊ መሠረተ ልማቶችና ቁሳዊ ያልሆኑ እንደ ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ጸጥታና የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች እጅግ በጣም ወሳኝ ናቸው። “ዜጎች በሚከፍሉት ግብር መንግስት መሠረተ ልማቶች በማስፋፋት፣ የግሉ ዘርፉ ጠንካራና ተወዳዳሪ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል” ብለዋል።

    ጠንካራና ተወዳዳሪ የሆነ የግል ዘርፍም ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ከመፍጠር በላይ ትርፋማነቱን የሚያረጋግጥና ለመንግስትም ትልቅ የገቢ ምንጭ በመሆን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር (ቪዲዮ)

    በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሰፊ የዴሞክራሲ ግንባታ ለማስቀጠል ጠንካራና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

    “ያለበቂ ተሳትፎና ውክልና ግብር የመክፈል ግዴታ ሊኖር አይችልም” ያሉት ዶክተር ዐቢይ “ግለሰባዊ የመብት አያያዝ፣ ማኅበረሰባዊ ደህንነት፣ የዳበረ የፍትህ ስርዓት፣ የላቀ የዕውቀትና ጥበብ አቅም፣ በምግብ ራስን መቻልና መሠረታዊ ጤናን ለሁሉም የማዳረስ ብቃት ሳይቋረጡና ከደረጃቸው ሳይወርዱ ማዳረስ የሚቻለው ያለማቋረጥ ግብር ለመሰብሰብ የሚችል ስርዓትና አቅም ስንፈጥር ብቻ ነው” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ኢትዮጵያን ለማሳደግና ሰላም እንድትሆን ለዜጎችና ለነዋሪዎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብና ድህነትን በማሸነፍ ወደብልጽግና ለመገስገስ ከተፈለገ ስለግብር ያለው ደካማ አመለካከት መቀየር እንዳለበት ተናግረዋል።

    “ግብር የሚያጭበረብር ሰው እንደ አራዳ መቆጠሩ ቀርቶ አገርና መንግስትን እንደሚጠላ ብቻ ሳይሆን ስለራሱ ልጆች የዛሬና የወደፊት ህልውና ምንም የማይጨነቅ ሞኝ ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

    ዜጎችና ነዋሪዎች ግብር በመክፈል አገሪቱን፣ መንግስትንና ልጆቹን እንደሚወድ በይፋ የሚያሳይ ኩሩ ዜጋ መፍጠር እንደሚያስፈልግም አክለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደጠቀሱት ኢትዮጵያ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርቷ (GDP) የግብር ገቢዋ (tax revenue) የሚይዘው 10.7 በመቶ ብቻ ሲሆን፥ ይህም ከአፍሪካ ሀገራት አንጻር እንኳን በጣም ዝቅተኛ ነው።

    የገቢዎች ሚኒስቴር የነደፈው ብሔራዊ የግብር ገቢ ንቅናቄ (National Tax Revenue Movement) ኢትዮጵያውያን ለግብር ያላቸውን ዝቅተኛ ብሎም የተሳሳተ አመለካከት በመቀየር፥ ይልቁንም ግብር መክፈል ሀገራዊ ግዴታ እና ማንኛምው ገቢ የሚያገኝ ሰው መክፈል ያለበት ነገ መሆኑን በማስገንዘብ ከዜጎች የሚሰበሰበውን ግብር በመጨመር ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2025 የመካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ውስጥ ለመመደብ የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል ተብሎ ይጠበቃል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ብሔራዊ የግብር ገቢ ንቅናቄ

    Semonegna
    Keymaster

    የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታ 56 በመቶ ደርሷል

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከ986 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሚያስገነባው የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከልን በተያዘለት ግዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ተገለጸ።

    የሆስፒታሉ የምህንድስና ኢንጂነሪንግ ክፍል አስተባባሪ ኢንጅነር ሞቲ አሰፋ ለ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት እየተገነቡ ያሉት የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከላት መጀመሪያ አካባቢ ቶሎ ወደ ሥራ ያለመግባትና በብረት ዋጋ ንረት ምክንያት መዘግየት የታየበት ቢሆንም ግንባታው 56 በመቶ ደርሷል።

    የማዕከላቱ መሠረት በ12 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ባለ12 እና 10 ወለል ህንፃዎች ይኖሩታል ብለዋል። ህንፃዎቹ ከ600 በላይ የመኝታ ክፍሎች እንደሚኖራቸው ነው ኢንጂነር ሞቲ ያብራሩት።

    ከዚሁ ጎን ለጎን ከተጀመረ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረውና ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የእናቶችና ህጻናት ማዕከል ባለ 8 ወለል ህንፃም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

    በህንጻ ተቋራጩ እና ክትትል በሚያደርገው ተቆጣጣሪ ድክመት ምክንያት ተጓትቶ የነበረው ፕሮጀክቱ ባለሙያዎችን በመቀየር በአሁኑ ወቅት ሥራው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝና በዚህ ሳምንት ከፊሉን ሥራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።

    ◌ Ethiopia: Are Ethiopian hospitals constructed in environment-suitable and climate-friendly way?

    የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሜዲካል አገልግሎት ዋና ፕሮቮስት ዶ/ር ወንድማገኝ ገዛኸኝ በበኩላቸው ማዕከላቱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ በሀገሪቱ በካንሰርና በልብ ህመም ለሚሰቃዩ ዜጎች የሚሰጡት ጥቅም ከፍተኛ ነው ብለዋል። በተለይ ህክምናዎቹ የሚጠይቁት ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ አብዛኛውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት።

    ከሰባት ዓመት በፊት ሆስፒታሉ በቀን ከ500 ያልበለጡ ህሙማንን ብቻ ያስተናግድ እንደነበር የተናገሩት ዶክተር ወንድማገኝ፥ በአሁኑ ወቅት በየቀኑ ለሁለት ሺህ ሰዎች ህክምና አገልግሎት እያገኙ ነው ብለዋል።

    በአሁኑ በወቅት በወር ለ1 ሺህ 500 እናቶች የወሊድ አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን በግንባታ ላይ የሚገኘው የእናቶችና ህፃናት ህንፃ ሲጠናቀቅ በቀን ለ400 እናቶች የወሊድ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ጠቁመዋል።

    ህንፃው 15 የማዋለጃ ክፍሎች እንደሚኖሩት የጠቀሱት ዶ/ር ወንድማገኝ በቅርቡ አገልግሎቱን ለማስጀመር ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

    የሆስፒታሉ ሀኪም ዶ/ር ዮናስ ገብረጊዮርጊስ በበኩላቸው የሚገነቡት የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከላት በሀገሪቱ በመንግስት በብቸኝነት አገልግሎት እየሰጠ ካለው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተጨማሪ በመሆን ህብረተሰቡ የጤና አገልግሎቱን በአቅራቢያው እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።

    የማዕከላቱ መገንባት በሀገሪቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን የካንሰር ህመም ለመከላከል የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ዮናስ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

    ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ተነግሯል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከል

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለትምህርትና ጤና አገልግሎት የሚውል ከ452 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገ። የጃፓን መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ አራት ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና ለማስፋፋት ያስችላል።

    በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ (Daisuke Matsunaga) የፕሮጀክት ግንባታና ማስፋፊያ ከሚደረግላቸው ትምህርት ቤቶች ኃላፊዎች ጋር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።

    ፕሮጀክቶቹ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የጉንችሬ እና እነሞር ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታና በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሀሮ ሾጤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ናቸው።

    በተጨማሪም ለሻሻመኔ ከተማ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች የምግባረ ሰናይ መጠለያ ግንባታና ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የዩሮሎጂ እና ድንገተኛ ክፍል የህክምና መሣሪያዎች ግዥ የሚውል ነው።

    እነዚህ አራት የትምህርት እና የጤና ፕሮጀክቶች ከአራት ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።

    አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እንዳሉት አገራቸው ለኢትዮጵያ ልማት ተሳትፎ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች። ጃፓን በኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1989 ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ከ400 በላይ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገች ነው።

    በትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በኢኮኖሚ ልማትና ሌሎችም መስኮች ድጋፍ ስታደርግም ቆይታለች።

    በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽነር እርስቱ ይርዳው የተደረገው ድጋፍ የዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

    ድጋፉ በተለይም ትምህርት ቤት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መሆኑ የትምህርት ሽፋንን በማስፋት የመንግስትን ጥረት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

    ከዚህ ጋር በተያያዘ የጃፓን ኤምባሲ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘውን የራስ መኰንን አዳራሽ ለማደስ የ85 ሺሕ 679 ዶላር (2,403,500 ብር) ዕርዳታ መለገሱን ሪፖርተር ጋዜጣ በእሁድ ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. እትሙ ዘግቧል።

    አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር አህመድ ሐሰን (ዶ/ር) የእርዳታ ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን፣ ገንዘቡም የራስ መኰንን አዳራሽ ባህላዊና ታሪካዊ ዳራው ሳይጠፋ ለማደስ፣ የተበላሹ ክፍሎችን ለመጠገን፣ ውስጣዊ ክፍሉን ለማደስ እና አዳዲስ ቁሳቁስ ለማስገባት መሆኑ ታውቋል።

    የጃፓን መንግስት ትምህርታዊ ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ የራስ መኰንን አዳራሽን ለማደስ መነሳቱ፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ኢትኖሎጂካል ሙዚየም በርካታ ጎብኚዎች እንዲስብ ያስችላል ተብሏል።

    በሙዚየሙ ከአሥር ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚገለጹባቸው አልባሳትና ቁሳቁሶች አሉ፤ ይህም በአፍሪካ አንዱ ታዋቂ ሙዚየም እንዲሆን አስችሏል።

    በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሕንፃ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜው በስሩ ያቀፋቸው ቤተ-መጻሕፍት፣ የኢትኖግራፊክ ሙዚየም የምርምርና የጥናት ማዕከልን ነው። በውስጡም መጻሕፍት፣ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት፣ የዳግማዊ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የድምፅና የምስል ቅጂዎች፣ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ድርሳኖች፣ ጆርናሎች፣ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍትንም ይዟል።

    እንዲሁም እስከ 20 ሺሕ የሚደርሱ የኅትመት ክምችቶች ከቅድመ ምረቃ እስከ ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

    የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም. መስከረም ወር ከጃፓኑ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትምህርታዊ ልውውጥና የጥናት ትብብር ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ይታወሳል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ እና ሪፖርተር ጋዜጣ

    የጃፓን መንግስት

    Semonegna
    Keymaster

    የመንገዶች የመብራት አገልግሎት አለመስጠት ምክንያቱ ኃይል ያልተለቀቀላቸው በመኖራቸው፣ መሠረተ ልማቶች ስለሚዘረፉ፣ የምሰሶና የአምፖል ማርጀት እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጠቅሷል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ)–በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት መንገዶች ውስጥ የመብራት አገልግሎት እያገኙ ያሉት ከ40 በመቶ እንደማይበልጥ ያስታወቀው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እስከሚቀጥለው ዓመት ዘጠና በመቶ የከተማዋ መንገዶች መብራት እንዲኖራቸው ከአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ ጋር እየሠራሁ ነው ብሏል።

    የመንገዶች የመብራት አገልግሎት አለመስጠት ምክንያቱ ኃይል ያልተለቀቀላቸው በመኖራቸው፣ መሠረተ ልማቶች ስለሚዘረፉ፣ የምሰሶና የአምፖል ማርጀት እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጠቅሷል።

    የመብራት ምሰሶዎች በየመንገዱ ቢተከልም ከሁለት ዓመት ወዲህ አብዛኛዎቹ አገልገሎት እንደማይሰጡ የጠቀሱት የአፍንጮ በር ነዋሪ አወል አማን፥ በምሽት ወደ መስጊድ ሲሄዱና ከሥራ አምሽቶ ወደ ቤት ለመግባት ስጋት ፈጥሮብናል ብለዋል። አክለውም ምሰሶዎችና አምፖሎች ተሰባብረው እንደሚገኙ ያነሱት ነዋሪው አገልግሎት የማይሰጡ መብራቶች እንዲጠገኑ ጠይቀዋል።

    የጉለሌ አካባቢ ነዋሪ አቶ ፀጋዬ መኩሪያ መኪና አሽከርካሪ ሲሆኑ፥ መንገዶች የምሽት መብራት ከሌላቸው ለአሽከርካሪዎች ፈታኝ በመሆኑ የትራፊክ አደጋ ይከሰታል ብለዋል። አቶ ጸጋዬ እንደሚሉት ጉለሌ አካባቢ በርካታ መኪናዎችና እግረኞች የሚተላለፉበት ቢሆንም የምሽት መብራት የላቸውም፤ ብዙዎችም አደጋ እየደረሰባቸው ነው።

    ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስም ሆነ አሮጌ መኪናዎች ከሚገባው በላይ ውድ የሆኑበት ምክንያት ምንድን ነ?

    የላዳ ታክሲ አሽከርካሪ ማቲዮስ ታምር ሥራው በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲዘዋወር ስለሚያደርገው በርካታ መንገዶችን እንዳየና መብራት እንደሌላቸው ተናግሯል። ውስጥ ለውስጥና በዋና መንገዶች መብራት በብዛት አለመኖሩ መሪን ያለ አግባብ የመጠቀም ዕድል ስለሚኖር የመጋጨት አጋጣሚውም ሰፊ ነው ብሏል።

    ከስድስት ኪሎ ሽሮ ሜዳ፣ ከሰሜን ማዘጋጃ እንጦጦ፣ ከእንቁላል ፋብሪካ ዊንጌት ባሉ መንገዶች እንደሚሰሩ የገለፁት በአዲስ አበባ የጉለሌ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ቁጥጥር አባል ምክትል ኢንስፔክተር አያሌው በለጠ ከነዚህ መንገዶችም አብዛኛዎቹ መብራት የላቸው ብለዋል።

    መዲናዋ በተሽከርካሪዎችና በእግረኞች የተጨናነቀች በመሆኗ በጨለማ ወቅት መብራት አለመኖሩ የትራፊክ አደጋን አባብሷል ነው ያሉት ምክትል ኢንስፔክተሩ።

    መብራት ከሌለ አሽከርካሪዎች ረጅም መብራት የመጠቀም ዕድላቸው ሰፊ ነው ያሉት ረዳት ኢንስፔክተር መራጭ ድንጌቻ፤ ከፊት ለፊት የሚመጡ መኪናዎችን እይታ ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን ለአደጋ ያጋልጣል ብለዋል።

    “ከእንቁላል ፋብርካ እስከ ዊንጌት ብዙ ሆስፒታሎች ስላሉ ህሙማንን የያዙ ተሽከርካሪዎች ቀንና ሌሊት ይመላለሳሉ፤ ባለፈው ዓመት በዚያ መንገድ በርካታ ሰዎች ተገጭተዋል” ነው ያሉት።

    ምክትል ኢንስፔክተር አያሌው “ከዚህ ቀደም በአዲሱ ገበያ ዊንጌት በሚወስደው መንገድ አንዲት ሴት ተገጭታ መብራት ባለመኖሩ ምክንያት ሌሊቱን ሙሉ መኪና ሲመላለስባት አድሮ የገላዋ ዱቄት ነው የተነሳው” ሲሉ ያጋጠማቸውን አሳዛኝ ክስተት ነግረውናል።

    በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መብራት ክትትል ባለሙያ ኢንጅነር ደረጀ ኃይሉ የከተማዋ መንገዶች አንዳንዶቹ የመብራት አገልግሎት እንደሌላቸው ገልጸው “ከጉርድ ሾላ ኦቨር ፓስ፣ መገናኛ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ከስድስት ወር በፊት ተጠይቆ የዋጋ ግምት አልተመለሰልንም” ነው ያሉት።

    የቦሌ አራብሳ መንገድ ከሁለት ዓመት በፊት ለአገልገሎት ክፍት ሆኖ የመብራት ምሰሶ ቢተከልም መብራት እንዳልተለቀቀ የገለጹት ኢንጅነር ደረጀ ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ጉራራ ኪዳነምኅረት የምሰሶ ተከላና የገመድ ዝርጋታ የማሟላት ሥራ ተከናውኖ የኃይል ዋጋ ግምት እንዲላክለት ከአንድ ወር ወዲህ መጠየቁን ተናግረዋል።

    በባለስልጣኑ የድንገተኛና አንሰለሪ ጉዳዮች ቡድን መሪ አቶ ዘውዱ ባይህ በበኩላቸው መብራት ተቋርጦባቸው የነበሩ 37 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የቀለበት መንገዶች ባለፈው ዓመት ተጠግነው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

    ጨለማን ተገን አድርገው ዝርፊያ የሚፈጽሙ አካላት የመብራት ቁሳቁሶችን ከአገልግሎት ውጪ እያደረጉና እየዘረፉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዘውዱ ከዮሴፍ-ቦሌ ሚካኤል፣ ከአየር መንገድ አደባባይ-ኢምፔሪያል፣ ሸጎሌ ከጎጃም በር-እስከ ዊንጌት እንዲሁም 18 ማዞሪያ፣ ከ3 ቁጥር ማዞሪያ-አለርት ቁሳቁሶቹ በየጊዜው እየጠፉ ተቸግረናል በማለት አስረድተዋል።

    የተበላሹትን ወደ አገልገሎት ለመመለስ በራስ ኃይልና በጨረታ እየተጠገኑ መሆኑን ያነሱት ቡድን መሪው አሮጌ መብራቶችን ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

    በከተማዋ መንገዶች ከ40 በመቶ የማይበልጡ የመብራት አገልግሎት ያላቸው ሲሆን ባለሥልጣኑ 25 ሚሊዮን ብር በመመደብ ጥገና እየሠራ ነው፤ በዚህ በጀት ዓመትም ሽፋኑን 90 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ በበኩላቸው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ባለው ውል መሠረት ቆጣሪና ትራንስፎርመር እየገጠምን ነው ብለዋል።

    ሆኖም የሲቪል ሥራዎች በመንገዶች ባለስልጣን በኩል ባለመጠናቀቃቸውና የመንገድ ርክክብ ባለማድረጋቸው ምክንያት መብራት የማያገኙ መንገዶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

    “የካ አባዶ አንድ መንገድ፣ ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ጉራራ መንገድ ተገምቷል፣ ቦሌ አራብሳ እየተገመተ ነው፣ ጎሮ ቱሉ ዲምቱ ትራንስፎርመርና ቆጣሪ ተገጥሟል፣ ከሲኤምሲ አደባባይ እስከ ካራ ትራንስፎርመርና ቆጣሪ ቢገጠምም መንገዱን ርክክብ አላደረጉም፣ ከዊንጌት አደባባይ እስከራስ ደስታ ሆስፒታል ላለው መንገዶች ባለስልጣን ግምት አላመጣም፣ ዓለም ባንክ ቤቴል አየር ጤና ፍርድ ቤት ያሉት ያልተጠናቀቁ የሲቪል ሥራዎች ሲጠናቀቁ ኃይል ይለቀቅላቸዋል” ብለዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን

    Semonegna
    Keymaster

    ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ለተቀናጀ የግብርና-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ15 ሚሊዮን የአሜርካ ዶላር (420 ሚሊዮን ብር) ስምምነት ተፈራረሙ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ እና ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማቶችን በገንዘብ የሚደግፈው የአፍሪካ ልማት ባንክ ለተቀናጀ የግብርና-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ15 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ።

    የፋይናንስ ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ሲሆኑ በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል ደግሞ የባንኩ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አብዱል ካማራ (ዶ/ር) ናቸው።

    ዋና መቀመጫነቱ በአቢጃን ከተማ (አይቮሪኮስት) የሆነው የአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው በኢትዮጵያ በግብርና – ኢንዱስትሪ (agro-industry) ዙርያ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ነው። ድጋፉ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስታት ስር እየተገነቡ ላሉ አራት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን እንደሚውል ተገልፃል።

    ፕሮጀክቱ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን ለመደገፍ የሚውል ሲሆን በኢንዱስትሪ ፓርኮች መሠረተ-ልማትን ለማሳደግ፣ በዘላቂነት የግብርና-ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ እንዲኖር ለማሰቻል እና በፕሮጀክት አስተዳደርና አተገባበር ላይ ለአራቱ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት እና ለንግድ እና ኢንዱስትሪ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማከናውን ይውላል።

    African Development Bank Group approves US$123 million grant for Ethiopia’s Basic Services Transformation Program

    የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በፊርማ ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካለቸው የአፍሪካ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የተለያዩ መርሀ ግብሮችን ነድፋ እየተንቀሳቀሰች የምትገኝ ሲሆን፥ በተለይም ሁሉን አቀፍ እድገት እንዲኖር ማስቻል፣ ድህነት ቅነሳ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የማደረግ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
    የገንዘብ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ ልማት በስፋት ለመግባት እያደረገች ላለው ጥረት የአፍሪካ ልማት ባንክ እያደረገው ላለው ድጋፍ ምስጋናቸው አቅርበዋል።

    ባለፈው ወር የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ የዘረጋቸውን መሠረታዊ አገልግሎቶች ማሻሻያ መርሀ ግብር (Basic Services Transformation Program) ለመደገፍ 123 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

    ምንጭ፦ የገንዘብ ሚኒስቴር
    ——
    ተጨማሪ ዜናዎች፦

    የአፍሪካ ልማት ባንክ


    Semonegna
    Keymaster

    ታስረው ከነበሩ ሰዎች የተፈጸመውን ግፍ የሰማውና ጠንቅቆ የሚያውቀው ሕዝብ በሌሎችም በርካታ አጋጣሚዎች በዜጎች ላይ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲሰማ የኖረው ሕዝብ የከረረ ተቃውሞ ቢያሰማ አሻፈረኝ ቢል ምንም አይፈረድበትም።

    መሐመድ አማን (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–ከሰሞኑ በተለያዩ የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያዎች የቀረበው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘጋቢ ፊልም በሕዝብና በዜጎች ላይ የተፈጸመው ግፍና በደል መጠን የለሽ እንደነበር ያሳያል። ገራሚው ነገር እኩልነት በተግባር ተረጋግጧል በሚባልበት ሀገር ዜጎች በብሔራቸውና በጎሳቸው መነሻነት ተለይተው እጅግ ዘግናኝና በጭካኔ የተሞላ አረመኔያዊ ድርጊት የተፈጸመባቸው መሆኑ በእጅጉ አሳዝኗል። የት ሀገር ላይ ነበርንም ያሰኛል።

    ይህ ዓይነቱ ጸያፍ ድርጊት በዓለም ደረጃ ይፈጸም የነበረው በተለይ በናዚ ጀርመን የማሰቃያና የመግረፊያ በጋዝ መርዝ ሰዎች ይገደሉባቸው በነበሩ ካምፖች ነበር። በተለያዩ የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያዎች የተላለፈው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘጋቢ ፊልምም ድፍን ሀገርን በእንባ አራጭቷል።

    የግፉና የአረመኔያዊ ድርጊቱ ጫፍና ጣሪያ ከሚገመተው በላይ የሆነ በተለይም ዘርና ብሔርን ኢላማ ያደረገ መሆኑ ደግሞ እጅጉን ያማል። ሰው የሆነ ሰው፤ ቤተሰብ ልጅ እህት ወንድም ወገን ያለው ሰብዓዊ የሆነ ፍጡር እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ይፈጽማል ብሎ ለማመን ይከብዳል፤ ግን ደግሞ ሆነ፤ ተደረገም።

    ይህን በዘረኝነት ጥላቻ የተሞላ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ የፈሰሰን እጅግ አረመኔያዊ ድርጊት ለመግለጽ ቃላቶች አቅም ያጥራቸዋል። ሰው በአገሩ እንዲህ ዓይነት በደልና ግፍ በአረመኔነት ተሞልቶ ሲፈጸምበት ሀገሬ አይደለችም አላውቃትም ቢል አይፈረድበትም።

    የፍትህ ሰቆቃ ― አማርኛ ዘጋቢ ፊልም

    ከሥልጣኔና ከዕውቀት፣ ከመልካም ሥነ-ምግባር የተፋቱ ሰብዓዊነት የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው አረመኔ አውሬዎች ቀጣዩን ትውልድ እንዳይበክሉት መጠንቀቅ ለሕግና ለፍትህ ማቅረብ ግድ ይላል።

    ሕዝብና የሕዝብ ልጆችን ማሰቃየት፣ ብልታቸውን ማኮላሸት፣ ገልብጦ በእንጨት ላይ አንጠልጥሎ መግረፍ፣ ሰቅሎ ማቆየት፣ ዘርን ለይቶ መሳደብ ማንቋሸሽ፣ አፍ ላይ መጸዳዳት፣ ወንድ ላይ የግብረ ሰዶማዊነትን መፈጸም፣ ሴትን ልጅ እርቃኗን እያዩ መሳለቅ፣ ከዚያም አልፎ ወሲብ መፈጸም ሌላ ሀገር ሳይሆን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመ ድርጊት ነው። ያውም የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባና ፈጣሪውን የሚፈራ ሩህሩህ ሕዝብ አለበት በሚባል ሀገር።

    ይህ ሁሉ ድርጊት በኃይል፤ በጉልበት፤ በጠመንጃ አፈሙዝ አስገብሬና አስፈራርቼ እገዛለሁ በሚል የደንቆሮዎች እምነት መከወኑ ያሳፍራል። ጉዳዮቹ በጥብቅ ምስጢር ተይዘው ሲሠራባቸው የነበሩና የምስጢር ዘበኞቹም ራሳቸው ስለሆኑ ይህን ጉዳይ በአልፎ አገደም ከምንሰማው ውጪ እንዲህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ሰዎች አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን ለማሰማት የማይችሉባቸው በርካታ ሁኔታዎች ነበሩ። ቀን ሲፈቅድ ሁሉም ይሆናል እንዲሉ ሆነና ቀን በደሉን ግፉን አረመኔነቱንና ጭካኔውን ግፈኝነቱን እንዲህ በአደባባይ አሰጣው።

    ግፍ ሠርቶ መደበቅ፣ ዘርፎ መንደላቀቅ አይቻልም ― የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ

    ምስጋናው ለሰው ሳይሆን ለቀን ነው የሚሆነው። ለውጡን ላመጣው የሕዝብ ትግልና ለውጡን ከዳር ለማድረስ ሪፎርሙን እየመሩ ላሉት ሰዎች። ይህን ያህል ግፍ በጭካኔና አረመኔያዊነት በዘር ጥላቻ ላይ የተፈጸመ ሰቅጣጭ ድራማ በአገራችን ምድር ላይ ተፈጽሞ እናያለን ብሎ የገመተም የጠበቀም አልነበረም። ያለፈው (የደርግ) ሥርዓት እንዲህ ዓይነት እጅግ ነውረኛና ዘረኛ አረመኔያዊና ፋሽስታዊ ድርጊት በዜጎቹ ላይ ስለመፈጸሙ አልሰማንም።

    በፖለቲካ ልዩነት እንጂ በደርግ ዘመን እንኳን በዜጎቹ መካከል ልዩነትን ፈጥሮ ማጥቃት አልተስተዋለም፤ ብሔር እየመረጠ አልረሸነም፤ ብሔር እየመረጠም አልጠቀመም። የደርግ አምባገነናዊ ባህሪይው እንደተጠበቀ ሆኖ በእንዲህ መልኩ አሰቃቂ የግፍ ተግባራት ስለመፈጸማቸውም ያጠራጥራል። ይሁንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ክቡር ህይወታቸውን ገብረው ለሰብዓዊ መብት መከበር የከፈሉትን መስዋዕትነት ገደል የሚከት ተግባር በእነዚህ ጥቂት አረመኔዎች ተፈጽሟል። የሀገሬ ሰው እንደሚለው “ወንበሬን ማን ነክቶት አይሉም አይሉም፤ ሚስቴንስ ማን ዓይቷት አይሉም አይሉም፤ ቀን የፈቀደ ዕለት ይደረጋል ሁሉም” እንዲሉ ሁሉንም ይፋ ያወጣው ቀን ሆነ። በቀላሉ ይፋ የማይወጡ ሊታወቁ የማይችሉ ምስጢሮች ለአደባባይ በቁ።

    መቼም አንዱ ሄዶ ሌላው ሲመጣ አዲስ ለውጥና ሂደት ቢጠበቅም በዚህ ዓይነት ደረጃ መዝቀጥና መውረድ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም ነበር። እነዚህ ሰዎች የፈጸሙትን አረመኔያዊ ድርጊት የጀርመኑ አዶልፍ ሂትለር ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች በመፍጀት አሳይቷል። በማቃጠያና መግደያ ካምፖቹ ውስጥ በማስገባት በጋዝ መርዝ ጭስ ተሰቃይተው ከሞቱ በኋላ አስከሬናቸው ተፈጭቶ ወደ ሳሙናነት እስኪለወጥ ድረስ ሠርቷል። ይህን ዓይነቱን አረመኔያዊ ድርጊት በራሱ ዜጎች ላይ ግን አልፈጸመም።

    ሙሶሎኒ ፋሽስት ስለሆነ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመግዛት ቋምጦ በመጣውና መሪ በነበረው ግራዚያኒ አማካኝነት ኢትዮጵያ ውያንን በአካፋና በዶማ አስጨፍጭፏል። ቤት ውስጥ እንዲገቡ ካደረገ በኋላ እሳት ለኩሶ አንድዷቸዋል። የዘር ማጥፋት ፍጅት ፈጽሟል።

    የተላለፈው እጅግ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የተመለከተው ዘጋቢ ፊልም እነዚህ ሰዎች ከባሕላችን፤ ከእሴቶቻችን፤ ከሀይማኖታዊ እምነታችን በእጅጉ የራቁ፤ በዘረኝነት ጭፍን ጥላቻ የታወሩ፤ የክፍለ ዘመናችን ጥቁር ፋሽስቶች መሆናቸውን ደግሞ ደጋግሞ ያረጋግጣል።

    የራሳችን ሰዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ጸያፍ ሥራ ሲፈጽሙ እንደኖሩ፤ አገርንና ሕዝብን እንዳዋረዱ፤ ወደፊትም በዚሁ አሳፋሪ ሥራቸው ቀና ብለው ለመራመድ እንደሚቸገሩ በእርግጠኝነት ለመናገር ይቻላል። ታስረው ከነበሩ ሰዎች የተፈጸመውን ግፍ የሰማውና ጠንቅቆ የሚያውቀው ሕዝብ በሌሎችም በርካታ አጋጣሚዎች በዜጎች ላይ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲሰማ የኖረው ሕዝብ የከረረ ተቃውሞ ቢያሰማ አሻፈረኝ ቢል ምንም አይፈረድበትም።

    እንዲህ ዓይነቱ ፋሽስታዊ ድርጊት ከምድራችን ተነቅሎ እንዲጠፋ፤ ሕግና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፤ ሁሉም ዜጋ የየበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል። በመዲናዋ አዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች ህቡእ ከመሬት ስር ያሉ እስር ቤቶችን ከፍቶ ዜጎችን ማሰቃየት፣ መግረፍ፣ መግደል፣ የወንጀሎች ሁሉ የከፋው ወንጀል ከመሆኑም በላይ አስቸኳይ የሕግ ውሳኔን ይጠይቃል።

    ዋናውና ትልቁ ጥያቄ ይህ ሁሉ ግፍና በደል ሲፈጸም ዜጎች ሲደፈሩ፤ ግብረሰዶም ሲፈጸምባቸው፤ አፋቸው ላይ ሲጸዳዱ፤ ሴቶች እርቃናቸውን ሆነው መጫወቻ ሲሆኑ፤ መንግሥት ተብሎ የሚጠራው መንግሥት ምን ሲሠራ ነበር ብሎ መጠየቅ ይገባል። ሀገሬ የተፈጸመብሽ ግፍ አረመኔነት ጭካኔ ከጣሪያ በላይ ወጣ። የናቁሽ የረገጡሽ ያዋረዱሽ ሁሉ ውርደትን ሽንፈትን ውድቀትን ይከናነቡ ዘንድ ፍርዱ የአምላክም የሕዝብም ይሆናል። ይሁንና ከዚህ ልንማረው የሚገባው ጉዳይ ልክ እንደ ዘራፊዎች ጨካኞችም የትኛውንም ብሔር እንደማይወክሉና የሕዝብ ጠላቶች እንደሆኑ ነው። ሕዝባችንም ለእነዚህ ዓይነት ጨካኞች ምን ዓይነት የመደበቂያ ከለላ ሳይሰጥ የወገኖቼ ጠላቶች ናችሁ ብሎ ሊያወግዛቸው ብሎም ለፍርድ ሊያቀርባቸው ይገባል። ስህተት በሌላ ስህተት አይታረምምና መንግሥትም እነዚህ አካላት ከፈጸሙት ተግባር በተቃራኒው ሄዶ ሰብዓዊነትን የሚማሩበትን የፍርድ ሂደት ማከናወን ጊዜ ሊሰጠው የማይገባው ተግባሩ ሊሆን ይገባል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የሰብዓዊ መብት ጥሰት

    Semonegna
    Keymaster

    የዘንድሮው የፀረ-ሙስና ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበርያ ጽህፈት ቤት ዘግቧል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ እና በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ትብብር የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የፀረ-ሙስና ቀን “ሁለንተናዊ ሰላማችንና እድገታችንን ለማረጋገጥ በሙስና ላይ በጋራ እንዝመት፤ ጊዜው የተግባር ነው” በሚል መሪ-ቃል በፓናል ውይይት እሁድ ኅዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ተከብሮ ውሏል።

    በዕለቱም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታከለ ሉሊና ሙስና ተሸሞንሙኖ የሚጠራ ሳይሆን ሌብነት እንደሆነ ሁሉም ዜጎች ተገንዝበው መታገል እና ሙስና በዓይነቱም የተለያየ እንደሆነ በመግለፅ ሁላችንም ተረባርበን መከላከል አለብን ብለዋል።

    አቶ ታከለ አያይዘውም ከትንሽ ከህዝብና መንግስት ሰዓትና ንብረት ጀምሮ ትኩረት በመስጠት ያለአግባብ እናዳይባክኑ በቀጣይነትም ልንሠራ ይገባል፤ ለዚህም ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን ብለዋል።

    በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋው የፓናል መወያያ መነሻ ሃሳብ ላይም የኢፌዲሪ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የአዲስ አበባ ማስተባበሪ ቅርንጫፍ የሕግ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ከፋለ እንደተናሩት በርካታ የሙስና መገለጫዎች አሉ እነዚህንም እንደየዓይነታቸው ነጣጥለን መከላከል ያስፈልጋል፤ ህብረተሰቡም ሊያግዝ ይገባል በጉዳዩም ላይ ባለቤት ነኝ ይመለከተኛል ማለት ይገባል ብለዋል።

    ሙስና በአሠራር፣ በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት፣ በጥቅም ትስስር፣ በዝምድናና በመሳሰሉት የሚፈፀም በረቀቀና ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ የሚከወን በመሆኑ የኮሚሽኑን ስራም በተገቢው እንዳይወጣ ሲያደርግ እንደነበርም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    የአዲስ አበባ ከተማ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ችግሯን ለመፍታት አማራጮች እየተፈለጉ ነው

    አክለውም ሙስና ለአገር ዕድገት ፀር፣ ለዲሞክራሲ ጋንግሪን እንደሆነ በማስታወስ ለአንዲት አገር ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ውድቀት የሚያስከትል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ እንደሚመለከተው በማብራራት ይህን ለመከላከል ሁሉም ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።

    በመጨረሻም እንደአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ያለው የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በመሆኑና ብዙውን ጊዜ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚታዩ የሙስና ወንጀሎችን ለመቀነስ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

    የዘንድሮው የፀረ-ሙስና ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበርያ ጽህፈት ቤት (TPMO) ዘግቧል።

    የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሙስናን ለመዋጋት የተደረገው ስምምነት (United Nations Convention Against Corruption) እ.ኤ.አ ጥቅምት 31 ቀን 2003 ቀን መጽደቁን ተከትሎ በየዓመቱ ኅዳር 30 ቀን  “የፀረ-ሙስና ቀን” ሆኖ እንዲከበር ተወስኗል።

    ምንጭ፦ TPMO | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የፀረ-ሙስና ቀን

    Semonegna
    Keymaster

    ጅማ (ኢ.መ.ባ.)– የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በተገኙበት በይፋ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን (ኢ.መ.ባ) አስታወቀ።

    የአንድን ሀገር ልማት በማፋጠን ረገድ ጉልህ ሚና ካላቸው የመሠረተ ልማት ዘርፎች አንዱ መንገድ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እና በነደፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት የዘርፉ ዋነኛ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለተግባራዊ እንቅሰቃሴው ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

    የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የመንገድ ፕሮጀክት ነባሩ መንገድ ገፅታ

    • በጠባብ የአስፋልት መንገድ ደረጃ የነበረ፣
    • የ50 ዓመት አገልግሎት የሰጠ፣
    • በ5 ሜትር ስፋት እጅግ አስቸጋሪ የነበረው፣ እና
    • ለትራፊክ እንቅስቃሴዎች ምቹ ባለመሆኑ ለአደጋ ሲያጋለጥ የነበረ መንገድ ነው።

    የጅማ – አጋሮ – ዲዴሣ ወንዝ ድልድይ የመንገድ ፕሮጀክት አዲሱ መንገድ ገፅታ

    • የ2ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመንገድ ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር አንድ አካል ነው፤
    • የአገሪቱን ደቡብ አና ሰሜን ምዕራብ ክፍሎች ደረጃውን በጠበቀ የመንገድ መሠረተ ልማት ያስተሳስራል።

    መገኛ፦ ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት – ጅማ ዞን ጅማ ከአዲስ አበባ ምዕራባዊ – ደቡብ አቅጣጫ ወሊሶን አቋርጦ በሚያልፈው አስፋልት ኮንክሪት መንገድ 360 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት።

    መነሻ እና መድረሻ ፕሮጀክቱ የሚጀመረው ጅማ ከተማ ከሚገኘው “ሃኒላንድ ሆቴል” በመነሳት በዋናነት በጅማ ሰሜን – ምዕራብ አቅጣጫ አድርጐ ወደ አጋሮ እና ዴዴሣ ወንዝ ድልድይ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ከዚያም ከወንዙ እስከ መቱ ከተማ በሚዘልቀው በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኘው መንገድ ጋር ያገናኛል።

    የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ኮንትራት እና ውል

    የሥራ ተቋራጭ፦ ቻይና ሬል ዌይ 21ኛ ቢሮ ግሩፕ የተባለ አለም አቀፍ ድርጅት
    አማካሪ ድርጅት፦ ኦሜጋ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነሪንግ እና ፕሮሜ ኮንሰልታንትስ በጋራ
    የግንባታ ወጪ፦ ከ1.3 ቢሊዩን ብር በላይ
    የግንባታ ጊዜ፦ 41 ወራት
    የግንባታ ወጪ ሽፋን፦ የኢትዮጵያ መንግስት

    የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ሁለንተናዊ ፋይዳ

    ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤
    የተሽከርካሪ የጉዞ ወጪና ጊዜ ይቀንሳል፤
    የምርት እና የሸቀጥ ልውውጥን ያቀላጥፋል፤
    የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ በማውጣት የገበያ ተደራሽነትን ያቀላጥፋል፤
    የከተሞች የእርስ በርስ ትስስር ይፈጥራል፤
    የጤና ፣ የትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን ተደራሽነት ያጠናክራል፤
    የማኅበረሰቡን ኑሮና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል፤
    ቡናን ጨምሮ በግብርና ምርቶችና በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገውን አካባቢ ተጠቃሚ ያደርጋል።

    ምንጭ፦ ኢ.መ.ባ. | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የጅማ–አጋሮ–ዲዴሳ መንገድ ግንባታ

    Semonegna
    Keymaster

    ዩኒሴፍ ባወጣው መግለጫ መሠረት በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለስደተኞች ህጻናት የሚሆኑ ሦስት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ፣ ባለ 41 ክፍሎች ስምንት ሁለተኛ ደረጃ እና ባለ 84 ክፍሎች አራት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ። 

    አዲስ አበባ (ኢዜአ)– በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እና ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ሊገነቡ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) አስታወቀ።

    ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ኅዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ የሚከናወነው ”ትምህርት ቆሞ አይጠብቅም” በሚል መርህ ለትምህርት በተያዘው እና በመላው ዓለም በስደት ለሚገኙ እና ለአደጋ የተጋለጡ 12,000 የሚደርሱ ህጻናትን በትምህርት ለመደገፍ ከተያዘው የ15 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት ውስጥ እንደሆነ ታውቋል።

    ሦስት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ፣ ባለ 41 ክፍሎች ስምንት ሁለተኛ ደረጃ እና ባለ 84 ክፍሎች አራት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ የሚከናወን መሆኑን መግለጫው አትቷል።

    በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ጊሊያን ሜልሶፕ ”ይህ ፕሮጀክት በስደተኞች መጠለያ ጣቢያና የስደተኞች ተቀባይ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ የምናደርገው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

    ማንኛውም ታዳጊ በምንም አይነት ሁኔታ ቢገኝ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን ብሩህ ከሚያደርገው ትምህርት መራቅ የሌለበት መሆኑን ገልጸዋል።

    ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 3600 ታዳጊዎችን በሁለተኛ ደረጃ፣ 8400 ታዳጊዎችን በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተቀብሎ የሚያስተናግድ ይሆናል። ትምህርት ቤቶቹ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2019 እና 2020 ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚገመት ተገልጿል። ትምህርት ቤቶቹ በቁሳቁስ፣ በላቦራቶሪ፣ በቤተመጽሐፍት፣ በመምህራን ቢሮዎችና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች የተሟላ እንደሚሆኑም ተነግሯል።

    ዩኒሴፍ ያውጣውን መግለጫ ሙሉውን (በእንግሊዝኛ ቋንቋ) ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ዩኒሴፍ


    Semonegna
    Keymaster

    ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሽከርካሪ ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን በአዲስ አበባ እና በሌሎች የክልል ከተሞች የተመረጡ መንገዶችን ለሰዓታት ለተሽከርካሪዎች ዝግ በማድረግ እና በመንገዶቹም ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን የማድረግ መርሃ ግብር ተካሄደ።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን (non-communicable diseases/ NCD) በተመለከተ ግንዛቤ ለማስጨበጥና የእግር ጉዞ ልምድን ለማበረታታትና ባህል ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ በማድረግ (car free day) የጤናና አካል ብቃት ስፖርቶች ተካሄዱ።

    ህዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በመዲናዋ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ በማድረግ በተከናወነው የጤና የአካል ብቃት ስፖርቶች መርሃ ግብር የጤና ሚኒስትሩ አሚር አማን (ዶ/ር) እና የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ታዋቂ ግለሰቦች ተሳታፊ ሆነዋል።

    መርሃ ግብሩ በየወሩ የሚከናወንና በሌሎች የክልል ከተሞች የሚስፋፋ እንደሆነም ተጠቁሟል። በአዲስ አበባ የተጀመረውን መርሃ ግብር ተከትለው በዚሁ ዕለት ባህር ዳር፣ ጅማ፣ መቐለ፣ ሀዋሳ እና ጅግጅጋ “ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን” በሚል ተመሳሳይ ዝግጅቶችን ማዘጋጀታቸውን ዶ/ር አሚር አማን በማኅበራዊ ገጻቸው አስታውቀዋል።

    በመዲናዋ መርሃ ግብሩ ሲከናወን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አደባባዮችና ጎዳናዎች ዝግ ተደርገው ህብረተሰቡ በእግሩ እንዲጓዝ ተደርጓል።

    መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ የአዲስ አበባ መንገዶችን በወር አንድ ጊዜ የእግር ጉዞ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲደረግባቸው ለማስቻል እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል። በሚቀጥለው ዓመት 15 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ለእግረኛ እና ለብስክሌት መንቀሳቀሻ ምቹ መንገዶችን ለመስራት መታሰቡን ጠቁመዋል።

    በየወሩ መጨረሻ እሁድ በመላው አገሪቱ በእግር የመጓዝ ልምድን ለማበረታታትና ባህል ለማድረግ “ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን” በሚል መሪ ሀረግ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ እንደሚደረጉ ለማወቅ ተችሏል።

    ህዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በተደረገው መርሃ ግብር በርካታ ቁጥር ያላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ የእግር ጉዞና የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል።

    ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና አጋላጭ መንስዔዎቻቸውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ህብረተሰቡ የመመርመር ልምዱን እንዲያሳድግም ጥሪ ቀርቧል። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እ.ኤ.አ የ2016 ዓ.ም. መረጃን/ውሂብን ተገን አድርጎ በ2018 ዓ.ም. ባወጣው የሀገራት ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ከሚሞተው ሰው 39 በመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት እንደሆነ ያሳያል። ይህ አሀዝ በበሽታዎች ሲከፋፈልም፥ ከልብ ጋር የተያያዙ በሽታዎች (16 በመቶ)፣ የተለያዩ የካንሰር በሽታዎች (7 በመቶ)፣ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ በሽታዎች (2 በመቶ) እና የስኳር በሽታ (2 በመቶ) ሲይዙ የተቀረው 12 በመቶ ደግሞ በሌሎች የተለያዩ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንደሆነ ሪፖርቱ ያትታል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)

    ነፃ የሆኑ መንገዶች

    Anonymous
    Inactive

    የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተመረቀ

    ኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የጂቡቲ መሪዎች የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልን መረቁ።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር እና ከጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ ጋር በመሆን ነው ሆስፒታሉን ዛሬ የመረቁት።

    ሆስፒታሉ 800 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሲሆን በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው።

    እንዲሁም ለደቡብ ሱዳን እና አጎራባች አገሮች የህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የተገነባ ነው።

    ሆስፒታሉ ከጤና አገልግሎቱ ባሻገር የምርምር፣ የማስተማሪያና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ለመስጠት ያስችላል።

    መሪዎቹ የህክምና ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ 300 ተማሪዎችንም ይመርቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Viewing 15 results - 616 through 630 (of 730 total)