-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴዎች ዙሪያና በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠረጥረዉ በቁጥጥር ስር እየዋሉ የሚገኙ አካላትን በተመለከተ ሚያዚያ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኃላ በጽሕፈት ቤታቸው ለመገናኛ ብዙኀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመንግስት ተቋማት እና ፕሮጀክቶች ላይ የተፈጸመ ከባድ የሙስና ወንጀልን በተመለከተ በተለይም የመንግስት ግዥ ንብረት አስተዳደርና ማስወገድ አገልግሎት፣ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንና በመድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲ በሦስቱም ተቋማት በበርካታ ሚሊየን የሚቆጠር የመንግስትና የሕዝብ ሀብት የመዘበሩ ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተደራጀዉ የምርመራ ቡድን በቂ ማሰረጃና መረጃ በመሰብሰብ 59 በወንጀሉ የተጠረጠሩ የቀድሞ የሥራ ኃላፊዎችና ግብረ-አበሮች በቁጥጥር ሥር በማዋል ዐቃቤ ሕግ ክስ ለመመሥረት ተጨማሪ የምርመራ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተደራጀ መልኩ በሙስና ወንጀል እጃቸው አለበት ተብሎ ከተጠረጠሩት መካከልም የቀድሞ የመንግስት ግዥ ንብረት አስተዳደርና ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግስቱ ከበደ፣ የመንግስት ግዥ ንብረት አስተዳደርና ማስወገድ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተሮች፣ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ አትክልት ተካ፣ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ፣ የመድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲ (PFSA) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ኃይለስላሴ ቢሆን፣ የመድሃኒት ፈንድ ኤጀንሲ ም/ዋ/ዳይሬክተር እና ሌሎች የነዚህ ተቋማት መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች በተጨማሪም በጥቅም የተሳሰሩ ሌሎች ግበረ-አበሮቻቸው እንደሚገኙ በመግለጫዉ ይፋ ተደርጓል።
በተያያዘም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሀኑ ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፥ ተቋሙ የሕግና የፍትህ ምህዳሩን ለማስፋትና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የቆመላቸው ዋና ዋና ዓላማዎች ማለትም ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማክበርና ማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የወንጀል ሕግን ማስከበርና የፌዴራል መንግስቱን እና የሕዝብን የፍትሀ ብሄር ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ተቋማዊ ለውጦችን ማከናወኑን ተናግረዋል።
በመደበኛ ሥራዎች ላይም ሰፋፊ ለዉጦች ማምጣት ጀምረናል ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ፥ በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎችና አተገባበር በማጥናትና የባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ለማሻሻል የሕጎቹን አተገባበር የሚገመግም ጥናትና በጥናቶቹ ግኝት ተከታታይ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኮች በማካሄድ ከተገኘው ግብዓት በመነሳት ረቂቅ ሕግ የማዘጋጀትና በረቂቅ ሕጎችም ላይ ግብዓት የማሰባሰብ ተግባር መከናወኑን አዉስተዉ አጠቃላይ የተሠሩ የሕግ ማሻሻያዎችን አፈፃፀምን በመግለጫቸዉ አንስተዋል።
በተጨማሪም በልዩ ሁኔታ ምርመራና ክስ እየተደረገባቸው ያሉ ጉዳዩችን በተመለከተ የሰብዓዊ መብት ጥስት ወንጀል ፈጽመዋል በሚል 42 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዉለዉ የወንጀል ምርመራ ሲጣራባቸው የነበረ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ በ10 የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት እንዲሁም በ9 የማረሚያ ቤት አመራሮች ላይ ክስ ተመሥርቶ በክርክር ሂደት ላይ ያለ ሲሆን፣ በ21 የደኅንነት አባላት ምርመራ ተከፍቶ ምስክር እየተሰማ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በተያያዘ መልኩም በተለያዩ ቦታዎች ከተፈጠሩ ሁከትና ብጥብጦች ጋር ተያይዞ በተከናወነ የምርመራ ሥራዎች በወንጀል ተግባራት የተሳተፉ አካላትን ለይቶ ለሕግ በማቅረብ በኩል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ለአብነትም በሐዋሳ ከተማ ከተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ፣ ሱማሌ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈጸመ ወንጀል፣ በኦሮሚያ ክልል ቡራዩና በአዲስ አበባ በተለያዩ በክፍለ ከተሞች ተነሰቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
በመጨረሻም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ አካባቢዎች ዓለማቀፍ ግንኙነት ያላቸዉና የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በዝግጅት ላይ የነበሩ አካላትን ሊያደርሱት የነበሩትን ጉዳት በመቆጣጠርና ቁጥጥር ስር ለማዋል ከብሔራዊ የመረጃ ደኅንነት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንና የምርመራው ሂደት እንደተጠናቀቀ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ካሉ በኋላ ሰላም የሁላችንም ሀብት በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከመንግስት ጎን በመቆም በጋራ ሊሠራ ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ መኖሪያ ቤታቸው ለፈረሱባቸው ዜጐች ተገቢዉን ድጋፍ እና ተመጣጣኝ ካሳ በአስቸኳይ እንዲያደርጉና በሠላም የመኖር መብታቸውን እንዲያስጠብቁላቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ጠይቋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ ለገጣፎ ከተማ፣ የዜጐች መኖሪያ ቤት መፍረሱ በእጅጉ እንዳሳሰበው የገለፀው የተባበሩት መንግስታት (ተመድ)፥ ጉዳዩን በትኩረት እንደሚመረምር አስታውቋል። በተባበሩት መንግስታት የመኖሪያ ቤት ምጣኔ ኃላፊዋ ለይላኒ ፋራህ (Ms. Leilani Farha) እንደገለፁት፥ በለገጣፎ 12ሺህ ቤቶች እንዲፈርሱ መወሰኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ቤት አልባ አድርጐ፣ ለእንግልት ይዳርጋል፤ ይህም ግልጽ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ብለዋል።
ስለ ቤቶቹ መፍረስ መረጃው ለተቋማቸው መድረሱን ያረጋገጡት ለይላኒ ፈራህ፥ በቀጣይ ጉዳዩ በልዩ መርማሪዎች ተመርምሮ፣ በዚህ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ወገኖች እንዲጋለጡ ይደረጋል ብለዋል። የዜጐችን መኖሪያ ቤት በዚህ መልኩ ማፍረስ በተባበሩት መንግስታት፣ ሀገራት ቃል ኪዳን የገቡለትን የማንኛውም ዜጋ፣ መጠለያ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት በእጅጉ የሚፃረር ነው ብለዋል – ኃላፊዋ።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) በለገጣፎ ዜጐች መጠለያ አልባ መደረጋቸውን በጽኑ አውግዞ፥ ቤት ለፈረሰባቸው ወገኖች፣ የፌደራል መንግስትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተገቢውን ድጋፍና ተመጣጣኝ ካሣ በአስቸኳይ እንዲያቀርብ እንዲሁም እየተካሄደ ያለው የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስና ዜጐችን የማፈናቀል ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በጉዳዩ ላይ ያወጣው መግለጫ የሚከተለው ነው።
ዜጐችን ማፈናቀል በአስቸኳይ ይቁም!!
በኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ዙሪያ ልዩ ዞን የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር በ01 እና 02 ቀበሌዎች፣ ጭላሎ፣ ወበሪ፣ ለገዳዲ ቄራ፣ ገዋሳ፣ እና በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን “ህገወጥ ግንባታዎች ናቸው፤ ለአረንጓዴ ልማት ይፈለጋሉ” በማለት ከየካቲት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በኃይል በማፍረስ ላይ ይገኛል። የከተማዋ ከንቲባ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፁትም በቀጣይም ከ12 ሺህ በላይ ቤቶችን እንደሚያፈርሱም አረጋግጠዋል። ሰመጉ ስለጉዳዩ የከተማዋን ከንቲባ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ሰመጉ ያነጋገራቸው ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው በርካታ ዜጐች እንዳስረዱት ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግስት ላይ እምነታቸውን ጥለው በተለያየ ወቅት በገዙት ቦታ ላይ የገነቡትን መኖሪያ ቤቶች በመገንባት እና አካባቢ በማልማት ከተማዋን ለእድገት አብቅተዋታል። በእነዚሁ ዓመታት ውስጥም የአካባቢው የመንግስት ኃላፊዎች እያወቁት የመብራት እና ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መሆናቸውን፣ ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን፤ በተለያዩ አስተዳደራዊና የልማት እንቅስቃሴ ላይ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አስረድተዋል። ይሁን እንጂ የከተማዋ አስተዳደር ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመተባበር ከነዋሪዎች ጋር በቂ ምክክር ሳያደርግ እና ሊመጣ የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ላይ ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ሳይኖረው ቤቶችን በማፍረስ ህፃናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች ሜዳ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል። በዚህም የዜጐችን ለኑሮ አመቺ በሆነ አካባቢ የመኖርን መብት፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃና ምግብ የማግኘት መብት፣ የአካል ደህንነት መብት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ መብቶች ተጥሰዋል።
የከተማው አስተዳደር የወሰደውን የኃይል እርምጃ ይበልጥ አስከፊ እና አጠያያቂ የሚያደርገው ከመኖሪያቸው በ7 ቀናት የማስጠንቀቂያ ጊዜ በኃይል እንዲፈናቀሉ ለተደረጉ ዜጐች ምንም ዓይነት አማራጭ የመኖሪያ ስፍራም ሆነ ጊዜያዊ የመጠለያ ስፍራ ያልተዘጋጀላቸውና ሰብዓዊ እርዳታም ያልተደረገላቸው መሆኑ ነው።
የፌዴራል መንግስትም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በዜጐች ላይ እየተፈፀመ ያለውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት፤ እየተካሄደ ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ማፍረስና ዜጐችን ማፈናቀል በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ፣ መኖሪያቸው ለፈረሱባቸው ዜጐች ተገቢዉን ድጋፍ እና ተመጣጣኝ ካሳ በአስቸኳይ እንዲያደርጉና በሠላም የመኖር መብታቸውን እንዲያስጠብቁላቸው ሰመጉ ይጠይቃል።
ምንጮች፦ አዲስ አድማ ጋዜጣ፣ ሰመጉ፣ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
“በርቱ! ባየሁት ነገር ተደስቻለሁ… የሥራ ፍላጎት ተነሳሽነት ለለውጥ ወሳኝ መሆኑን ከጴጥሮስ መረዳት እንችላለን” – የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኘተው የሥራ እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በቆይታቸውም የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በጋራ ያስገነቡትን የልብ ህክምና ማዕከል፣ በሀገሪቱ ብቸኛና የመጀመሪያ የሆነውን የተመረዙ ሰዎች የሚታከሙበት የቶክሲኮሎጂ ህክምና ማዕከል እንዲሁም የእናቶችና ህጻናት የህክምና ከፍልን ዋና ዳይሬክተሩ ጎብኝተዋል።
በሆስፒታሉ ፈጣን እድገት ተደስቻለሁ ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የልብ ህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩና በሀገሪቱ ካለው የህክምና እጥረት አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸው ብዙም ትኩረት ያልተሰጠበት የመመረዝ ህክምና በሆስፒታሉ መሰጠቱም ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።
◌ ቪዲዮ፦ የኢትዮጵያዊያን-አሜሪካዊያን ዶክተሮች ቡድን እያስገነባ ያለው ግዙፉ ዓለምአቀፋዊ ሆስፒታል በአዲስ አበባ
ሆስፒታሉ የሰሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) ህክምና ብቻ ይሰጥ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ቴዎድሮስ በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ መሠረታዊ የሆስፒታል አገልግሎቶችን መስጠት መጀመሩና የተወሰኑ የህክምና አገልግሎቶች ላይም የበለጠ ስፔሻላይዝድ ለማድረግ መሥራቱ በጣም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
ከዚህ ሌላም የሆስፒታሉ ሰራተኞች የሥራ ተነሳሽነትም በጣም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። ለሆስፒታሉ ፈጣን ዕድገትም ሁሉም የሆስፒታሉ ሠራተኞች ዋና ተዋናይ መሆናቸውን እንዳዩ ገልጸው በዚህም የሥራ ፍላጎት መኖር ለለውጥ ወሳኝ መሆኑን ከጴጥሮስ መረዳት እንችላለን ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በዚሁ ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ከመጎብኘታቸው በተጨማሪም ከየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) የጤና ሚኒስትር አሚር አማን (ዶ/ር) እንዲሁም ከኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ተገናኝትው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ከሰኔ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀን ጀምሮ ዋና መቀመጫው ጄነቭ፣ ስዊዘርላንድ የሆነውን የዓለም ጤና ድርጅትን (WHO) በዋና ዳይረክተርነት የሚመሩት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከዚህ ስልጣናቸው በፊት ከ ከኅዳር 20 ቀን 2005 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከጥቅምት 2 ቀን 1998ዓ.ም. እስከ ኅዳር 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ደግሞ የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ምንጭ፦ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የካንሰር ህክምና አገልግሎት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታ 56 በመቶ ደርሷል
- ከሆዱ 120 ሚስማር የወጣለት ታካሚ መዳኑ ተገለጸ ― የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርመራ በጋራ ለማከናወን ተስማሙ
- አዳማ ከተማ ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል ተገነባ
የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ያዘጋጁት የዘንድሮው ውድድር ለ2ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፥ በባለፈው ዓመት የተመረጠችው ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል በተካሄደው የቁንጅና ውድድር ላይ ተሳትፋ 3ኛ ደረጃ መውጣቷም ተገልጿል።
ደብረ ብርሃን (ሰሞነኛ)– በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ‹‹ቱሪዝም ለአካባቢ እንክብካቤና ለማኅበረሰብ አቅም መጎልበት›› በሚል መሪ ቃል ሲከበር የቆየው የቱሪዝም ሳምንት ጥር 24/2011 ዓ/ም የቁንጅና ውድድር በማካሄድ ተጠናቀቀ።
በውድድሩም ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ያብፀጋ አይነኩሉ ከሁለተኛ ዓመት የሎጅስቲክና ሰፕላይ ቼን ማኔጅመንት (Logistics and Supply Chain Management) ትምህርት ክፍል ተመርጣለች። በሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ኤልሳቤጥ ደስታ የ3ኛ ዓመት የባዮቴክኖሎጂ (Biotechnology) እና በሦስተኛነት ደረጃ ተማሪ ትንሳኤ ፀጋዬ አንደኛ ዓመት የሳይኮሎጂ (Psychology) ትምህርት ክፍል እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።
◌ VIDEO: The Yellow Movement AAU: Speaking up for women and girls – empowering women (Ethiopia)
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ተወካይ ዶ/ር ጌትነት አሸናፊ በፕሮግራሙ መዝጊያ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ከሳምንት በፊት ጀምሮ በዩኒቨርስቲው ግቢና ውጪ ያለውን አካባቢ በማጽዳት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ ተግባራት በማከናወን የቆዩ መሆናቸውን በመግለፅ ላደረጉት በጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።
የቱሪዝም ማኔጅመንት የትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አብርሃም ኪዳኔ እንደገለፁት የዘንድሮው ውድድር ለ2ኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፥ በባለፈው ዓመት የተመረጠችው ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል በተካሄደው የቁንጅና ውድድር ላይ ተሳትፋ 3ኛ ደረጃ በመውጣቷ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘች መሆኗን ተናግረዋል።
በመጨረሻም ለጓሳ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ መታሰቢያነት ‹‹ቱሪዝም ለአካባቢ እንክብካቤና ለማህበረሰብ አቅም መጎልበት›› በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የቱሪዝም ሳምንት 8 /ስምንት/ ተወዳዳሪዎችን ያሳተፈው የቁንጅና ውድድር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የወጡትን አሸናፊዎችን በመምረጥና እውቅና በመስጠት በዓሉ ተጠናቋል።
ምንጭ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ካምፓስ (በንሳ ዳዬ ካምፓስ) ተማሪዎችን በመቀበል በይፋ ሥራ ጀመረ
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርመራ በጋራ ለማከናወን ተስማሙ
- የአርሲ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ4ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 388 የህክምናና የጤና ተማሪዎች አስመረቀ
- አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገነባው የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ አይጠናቀቅም
- የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለቀረቡላቸው አማራጮች ፈንታ በከተማው ውስጥ ሁከት በመፍጠራቸው ከባህር ዳር እንዲወጡ ተጠየቀ
በአስር ሺህ ካሬ ሜትር ላይ በ58 ሚሊዮን ብር ወጪ በአዳማ ከተማ የተገነባዉ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል 10 ሺህ ኪሎ ግራም በሰዓት የማቃጠል አቅም ያለው ሲሆን፥ በሌሎች 7 ከተሞችም 500 ኪሎ ግራም በሰዓት ማቃጠል የሚችሉ ማዕከላትም በመገንባት ላይ ይገኛሉ።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በ100 ቀናት ዕቅድ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን እና የህክምና ግብአቶችን ማስወገጃ ማዕከል ገንብቶ አስመረቀ።
በአስር ሺህ ካሬ ሜትር ላይ በ58 ሚሊዮን ብር ወጪ በአዳማ ከተማ የተገነባዉ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል (incinerator) ምረቃ ሥነ ስርዓትላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን እንደተናገሩት፥ ማዕከሉ 10 ሺህ ኪሎ ግራም በሰዓት የማቃጠል አቅም ያለው ሲሆን፥ በሌሎች 7 ከተሞችም 500 ኪሎ ግራም በሰዓት ማቃጠል የሚችሉ ማዕከላትም በመገንባት ላይ ይገኛሉ ብለዋል። በቅርቡም ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምሩ ዶ/ር አሚር አክለው ተናግረዋል።
ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች እና ግብዓቶች ማስወገጃ ማዕከሉ ለሀገራችን የመጀመሪያ ሲሆን ከዚሀ ቀደም በየተቋሟቱ በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ የማይውሉ ወይም የተበላሹ መድኃኒቶችን በማስወገድ ረገድ ይገጥሙ የነበሩ ችግሮችን ከመሠረቱ እንደሚፈታ የገለጹት ሚኒስትሩ፥ የምለሳ ሎጂስቲክ (recycle logistic) ስርዓትን በመተግበር የማያገለግሉ የህክምና ግብአቶች እና በባኅሪያቸው ጎጂ የሆኑ ኬሚካሎችን በዘመናዊ መንገድ አካባቢን በማይበክል ሁኔታ በማስወገድ ከዚህ ቀደም አካባቢ የሚበከልበትን ሁኔታ እንደሚያስቀር ተናግረዋል።
◌ የኢትዮ-አሜሪካውያን ዶክተሮች ቡድን እያስገነባ ያለው ዓለም አቀፍ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው ሆስፒታል
ለዚህ ሥራ መሳካት ተባባሪ የሆኑ ያካባቢው ማኅበረሰብ አባላትና የአዳማ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤትን ያመሰገኑት ሚኒስትሩ፥ ማዕከሉ ለአካባቢ ነዋሪዎች ቅድሚያ ተጠቃሚ የሚያደረግ ስልጠናና የሥራ ዕድል በኤጀንሲው እንዲመቻችላቸውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬከተር ዶ/ር ሎኮ አብርሀም በበኩላቸው የአዳማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በሌላው ዓለም የሚተገበሩ ዘመናዊ አሠራሮችን በመቀመር የመድኃኒት እና የህክምና መገልገያ አቅርቦት እና ስርጭት የልህቀት ማዕከል ሆኖ ለሌሎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መማማሪያ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ተናግረው ለአካባቢው፥ ማኅበረሰብም የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሆነ እና በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ምንጭ፦ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው ዘመናዊ የህክምና ማዕከል ተመረቀ
- የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ዶክተሮችን ለስድስተኛ ጊዜ አስመረቀ
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታ 56 በመቶ ደርሷል
- ከሆዱ 120 ሚስማር የወጣለት ታካሚ መዳኑ ተገለጸ ― የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርመራ በጋራ ለማከናወን ተስማሙ
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ለተቀናጀ የግብርና-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ15 ሚሊዮን የአሜርካ ዶላር (420 ሚሊዮን ብር) ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ እና ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማቶችን በገንዘብ የሚደግፈው የአፍሪካ ልማት ባንክ ለተቀናጀ የግብርና-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ15 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ።
የፋይናንስ ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ሲሆኑ በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል ደግሞ የባንኩ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አብዱል ካማራ (ዶ/ር) ናቸው።
ዋና መቀመጫነቱ በአቢጃን ከተማ (አይቮሪኮስት) የሆነው የአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው በኢትዮጵያ በግብርና – ኢንዱስትሪ (agro-industry) ዙርያ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ነው። ድጋፉ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስታት ስር እየተገነቡ ላሉ አራት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን እንደሚውል ተገልፃል።
ፕሮጀክቱ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን ለመደገፍ የሚውል ሲሆን በኢንዱስትሪ ፓርኮች መሠረተ-ልማትን ለማሳደግ፣ በዘላቂነት የግብርና-ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ እንዲኖር ለማሰቻል እና በፕሮጀክት አስተዳደርና አተገባበር ላይ ለአራቱ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት እና ለንግድ እና ኢንዱስትሪ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማከናውን ይውላል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በፊርማ ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካለቸው የአፍሪካ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የተለያዩ መርሀ ግብሮችን ነድፋ እየተንቀሳቀሰች የምትገኝ ሲሆን፥ በተለይም ሁሉን አቀፍ እድገት እንዲኖር ማስቻል፣ ድህነት ቅነሳ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የማደረግ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ ልማት በስፋት ለመግባት እያደረገች ላለው ጥረት የአፍሪካ ልማት ባንክ እያደረገው ላለው ድጋፍ ምስጋናቸው አቅርበዋል።ባለፈው ወር የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ የዘረጋቸውን መሠረታዊ አገልግሎቶች ማሻሻያ መርሀ ግብር (Basic Services Transformation Program) ለመደገፍ 123 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።
ምንጭ፦ የገንዘብ ሚኒስቴር
——
ተጨማሪ ዜናዎች፦- አንበሳ የከተማ አውቶቡስ በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማቋረጡ ተገልጋዮች ለችግር ተዳርገዋል
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርመራ በጋራ ለማከናወን ተስማሙ
- የጅማ–አጋሮ–ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በተገኙበት በይፋ ተጀመረ
- ሐረር የሚኖሩ የጉራጌ ህብረተሰብ አባላት በመስቃንና ማረቆ ወረዳ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ100,000 ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
- የዱባይ አቡዳቢው ኤግል ሒልስ በአዲስ አበባ ለገሀር የተቀናጀ የመኖሪያ፣ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ሥራውን ጀመረ
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ የደረሱበት ስምምነት በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የፎረንሲክ ምርመራ ተከትሎ በህክምናና በሕግ ጉዳዮች ላይ መረጃን በወቅቱ ለማግኘት የሚያስችል ፈጣን አሠራር ለመዘርጋት ያለመ ነው።
አዲስ አበባ (ኢዜአ)– የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ህክምና ኮሌጅ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር የፎረንሲክ ምርመራን በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ኅዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የፎረንሲክ ምርመራ ተከትሎ በህክምናና በሕግ ጉዳዮች ላይ መረጃን በወቅቱ ለማግኘት የሚያስችል ፈጣን አሠራር ለመዘርጋት ያለመ ነው ተብሏል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ዋና ፕሮቮስት ዶ/ር ወንድማገኝ ገዛኸኝ ስምምነቱ በተፈረመበት ጊዜ እንደገለጹት፥ ከምረዛና ከአደጋዎች ጋር የተያያዙ የሞት መንስዔዎችና የጤና ጉዳቶች በመለየት ለሕግ አካላት መረጃን በወቅቱ በማቅረብ ረገድ በአገሪቱ ውስጥ ክፍተቶች አሉ። በዚህም ሆስፒታሉ በቅርቡ በጀመረው አጠቃላይ የፎረንሲክ ምርመራ ማዕከል ለሕግ አካላትም ሆነ ለመረጃ የሚጠቅሙ መንስዔዎችን የማጣራት ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ይህንን የፎረንሲክ ምርመራ በማጠናከር የወንጀል ምርመራን በፍጥነት በመለየት ከፌዴራል ፖሊስ በመተባበር ለመሥራት የሚያስችለውን ቅንጅታዊ አሠራር ማጎልበት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህን ሰነድ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል ዶ/ር ወንድማገኝ።
በስምምነቱ መሠረትም የአስክሬን ምርመራን ጨምሮ፣ የአስገድዶ መደፈር ጥቃት፣ የእድሜ ምርመራና የመኪና አደጋ በስምምነቱ የተካተቱ እንደሆኑ ተጠቁሟል። በዋናነትም ለፖሊስና ለሕግ ባለሙያዎች የፎረንሲክ ህክምናና ፎረንሲክ ሳይንስ ከተግባር ትምህርት ጋር ስልጠና የመስጠት ሥራ በሆስፒታሉ የሚከናወን እንደሆነና ምርመራውን የሚያግዙ መሣሪያዎችን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ሁኔታም በስምምነቱ ተካቷል።
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ተኮላ አይፎክሩ በበኩላቸው ወንጀልን መርምሮ ተጠያቂውን አካል ለፍርድ በማቅረብ ረገድ የፎረንሲክ ምርመራን ዘመናዊና ፈጣን በሆነ መልኩ ማከናወን አስፈላጊ ነው። ”ይህም ደግሞ በአገሪቱ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥና የዜጎችን ሰላም ለማስፈን ሚናው የጎላ ከመሆኑም ባሻገር ዜጎች በፍትህ አካላት ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ ይረዳል” ብለዋል።
ወንጀሎች በተፈጸሙባቸው አካባቢዎች ከሁለቱም ተቋማት የተውጣጣ የሙያተኞች ቡድን በስፍራው በመገኘት የማጣራት ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት የሚያስችል አሠራር መስምምነቱ መካተቱን ጀኔራል ተኮላ ጠቅሰዋል። ሌላው አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች ውስጥም ብሔራዊ የፎረንሲክ ተቋማትን ለመመስረት የሚያስችል አሠራር የሚዘረጋ እንደሆነና የጋራ የሆነ የስልጠናና የምርምር ፕሮግራሞች የሚካሄድ ይሆናልም ሲሉ አክለዋል።
በአሁኑ ወቅት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፎረንሲክ ማዕከል በቀን ከ25 እስከ 30 የሚሆኑ ምርመራዎችን እንደሚያከናውን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
(የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ጋዜጣዊ መግለጫ) – የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሰኞ ኅዳር 03 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ አሰቃቂ ድርጊት የሚፈጸምባቸው 7 ድብቅ እስር ቤቶች መገኘታቸውን፤ ከእነዚህም በተጨማሪ በማረሚያ ቤቶችና በፖሊስ ጣቢያዎችም ጭምር በተጠረጣሪዎች ላይ ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ እጅግ አሰቃቂ ድርጊቶች ሲፈፀሙ መቆየታቸውን ገልፀዋል። ከእነዚህ በሕግ ጥላ ስር በሚገኙ ዜጐች ላይ ከሚፈፀሙት የማሰቃየት ድርጊቶች መካከልም የታሳሪዎችን ሰውነት በኤሌክትሪክ ሾክ ከማድረግ ጀምሮ ብልት ላይ ውሃ የያዘ የፕላስቲክ ኮዳ ማንጠልጠል፣ብልትን በፒንሳ መሳብ፣ ጥፍር መንቀል፣ ከአውሬ ጋር ማሳደር፣ ሴቶች ታሳሪዎችን መድፈር፣ በወንዶች ላይ ግብረሰዶም መፈፀም፣ እንዲሁም ደብዛን ማጥፋት በጉልህ የሚጠቀሱ በሕግ ጥላ ስር በተገኙ ዜጐች ላይ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መሆናቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አረጋግጠዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ/ ሰመጉ) ባለፉት 27 ዓመታት ይህ ድርጊት በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፤ ሃሳብን የመግለፅ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሃሳባቸውን በነፃነት ሲያንሸራሽሩ በነበሩ ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች፣ እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰቡ አባላት ላይ እየተፈፀመ መሆኑን በማጋለጥ መንግስት የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ሲወተውት መቆየቱ ይታወሳል። መንግስት ለአመታት ለችግሩ ምላሽ መንፈግ ብቻ ሳይሆን የማሰቃየት ድርጊቶቹን ውጤት በመጠቀም የዜጐችን ሕገ-መንግስታዊ እና ሰላማዊ ጥያቄዎች በኃይል ሲያዳፍን ብሎም ንጹሃንን ሲያሸብር ቆይቷል። ይህንንም የማሸበር ድርጊት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ፊት በመቅረብ በግልፅ መናገራቸው እና ይቅርታ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው። እነዚህ የማሰቃየት ድርጊቶች ለዜጐች ከለላ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቅ ከነበረው ፍርድ ቤት የተደበቀ እንዳልሆነ በፍርድ ቤቶች ውስጥ የማሰቃየት ድርጊት ሰለባዎች ለችሎት ከሚያቀርቡት የቃል እና የፅሁፍ አቤቱታዎች በተጨማሪ፤ ልብሶቻቸውን በድፍረት በማውለቅ አካላዊ ጉዳታቸውን ቢያሳዩም በፍርድ ቤቶች በኩል የተወሰዱ እርምጃዎች አለመኖራቸው ታይቷል። በዚህም ፍርድ ቤቶች የዜጐችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማስከበር ግዴታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ዜጐች እምነት አጥተውበት ቆይተዋል።
ባለፉት 7 ወራት የመጣውን የመንግስት አስተዳደር ለውጥ ተከትሎ በመንግስት በኩል ሲወሰዱ የነበሩት እርምጃዎች በመልካምነታቸው የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይም ላለፉት 27 ዓመታት መንግስታዊ ኃላፊነትን ተገን በማድርግ በንፁሃን ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ በቆዩ የብሔራዊ ደኅንነት የሥራ ኃላፊዎች እና ድርጊቱን በቀጥታ ሲፈፅሙ በነበሩ ግለሰቦች ላይ እየተወሰደ ያለው ሕጋዊ እርምጃ የሚደገፍ ነው። እስካሁን ከተወሰደው የማጣራት ሥራ በተጨማሪም ተመሳሳይ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ እና ሲያስፈፅሙ የነበሩ ሌሎች የመንግስት ኃላፊዎችም ላይ እርምጃው እንዲቀጥል ሰመጉ ይጠይቃል።
የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፃሚዎች ላይ መውሰድ የጀመረውን ሕጋዊ እርምጃ በመደገፍ ረገድ፤ ከሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ሰለባዎች ያሰባሰባቸውን መረጃዎች ለሚመለከተው የሕግ አስከባሪ አካል መስጠትን ጨምሮ በማናቸውም መንገድ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል። በተጨማሪም የማሰቃየት ድርጊቶቹ ሰለባ የሆኑ ዜጐች የደረሰባቸው አካላዊ ብቻ ሳይሆን ስነ-ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት በቀላሉ የሚሽር እንዳልሆነ እሙን ነው። በመሆኑም ለተጐጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው ነፃ የህክምና፣ የስነ-ልቦና ምክር አግልግሎት እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሰመጉ ይጠይቃል።
በአጠቃላይ መንግስት በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በፍጥነት ለፍትህ ማቅረቡ ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው። ይህ የፍርድ ሒደት መንግስት ከበቀል በፀዳ መልኩ ሕግን ብቻ መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ በማድርግ ላይ መሆኑን የሚያሳይበት፣ ዜጐች በፍርድ ቤቶች ላይ የተሸረሸረ እምነታቸውን የሚያድሱበት እና የሕግ ልዕልና የሚከበርበት የፍርድ ሒደት እንዲሆን ሰመጉ ይጠይቃል።
ምንጭ፦ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በምንም ተአምር ለኢትዮያ ሕዝብ ውሸት አልነግርም። ዕድሜዬም፤ ሥነ ምግባሬም አይፈቅድልኝም። ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሕይወታቸው ያለፈው በሰው በደረሰባቸው ጥቃት አይደለም ― ኮሚሽነር ጄነራል ዘይኑ ጀማል
(ኤስ.ቢ.ኤስ ሬድዮ)–በሜልበርን ከተማ (አውስትራልያ) ተቀማጭነቱን ያደረገው ኤስ.ቢ.ኤስ ሬድዮ (SBS Radio) የአማርኛ ዝግጅት ክፍል ጋዜጠኛ ካሣሁን ሰቦቃ ኢትዮጵያ በነበረበት ጊዜ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፤ ኮሚሽነር ጄነራል ዘይኑ ጀማል ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር። የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሳም ቃለ ምልልስ አድርጎላቸው ነበር። ቃለ ምልልሱ የተደደረገው በሐዋሳ ከተማ ነበር – የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው በተመረጡ ማግስት።
ዋነኛ ርዕሰ ነገራቸውም ሕግና ሥርዓትን በአገር አቀፍ ደረጃ ማስፈንና ተዓማኒ የምርመራ ውጤቶችን በወቅቱ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ናቸው።
አቶ ዘይኑ፤ እንደ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራልነታቸው የሕግ የበላይነት ለዲሞክራሲ እስትንፋስ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለተጀመረው የለውጥ ሂደት እጅጉን ቀናዒ ናቸው።
“የሕግ የበላይነት ሳይከበር ዲሞክራሲ የሚታሰብ አይደለም። የዲሞክራሲ፣ የሰላምና የነፃነት ሀ ሁ የሕግ የበላይነት ነው” ይላሉ። ይህ ፅንሰ ሃሳብ ነው። ግብሩ የፖሊስ ኃይላቸው ፖለቲካዊ ሁከትን የመግታት ደረጃ ላይ አለመድረሱ ነው።
የጸጥታ ሥራ ያለ ሕዝብ ትብብር ዕውን እንደማይሆን ስለሚረዱም ፤ ሕዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን ቆሞ ሰላሙን እንዲያስከብር፤ ዲሞክራሲያዊ ሂደቱን እንዲታደግ ጥሪ ያቀርባሉ።
የሁከት ምንጮችን በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገር ውስጥ በገቡ ተፎካካሪ ድርጅቶች ላይ በጅምላ ማላከኩ ተገቢ አይደለም በማለትም ያስገነዝባሉ።
በሳቸው አተያይ ለአገረ ኢትዮጵያ የጸጥታ መደፍረስ ዋነኛ አስባቦች፡ –
• የሕግ የበላይነትን ጠንቅቆ ካለመረዳት የሚከሰቱ የእርስ በርስ ግችቶች፣
• ከነፃነት መግለጫ መንገዶች ጋር ተያያዥ የሆኑ የሕግ ግድፈቶችና
• ጥቅማቸው የተነካባቸውና ያኮረፉ ኃይላት ድርጊቶች እንደሆኑ በዋቤነት ይነቅሳሉ።የፌዴራል ፖሊስ የምርመራ ውጤች መጓተትን አስመልክተው “ጥፍር እየነቀልን ምርመራ ስለማናካሂድ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ጊዜ ይወስዳል” ባይ ናቸው፤ የፖሊስ ኃይሉ አቅም ደረጃም ታክሎበት።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለን አሟሟት አስመልክቶ መግለጫቸው በሕዝብ ዘንድ ሙሉ አመኔታን እንዳላሳደረ ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤
“በምንም ተአምር ለኢትዮያ ሕዝብ ውሸት አልነግርም። ዕድሜዬም፤ ሥነ ምግባሬም አይፈቅድልኝም። ኢንጂነር ስመኘው ሕይወታቸው ያለፈው በሰው በደረሰባቸው ጥቃት አይደለም”
በማለት በእርግጠኛነት ተናግረዋል።
ለወደመው ንብረት፤ ለባከነው ሐብትና ከኢንጂነሩ ሞት ጀርባ ተጠያቂ ስለሚሆኑ አካላት ሲመልሱ፤ “ከኢንጂነር ስመኘው ሞት ጀርባ ያሉትን ፖሊስ ለፍርድ ያቀርባል። ያ እስከሚሆን ድረስ ፖሊስ ዕንቅልፍ አይኖረውም” ብለዋል።
አንዱ አንኳር መልዕክታቸው “አንድም ሰው ቢሆን ጠብመንጃ ይዘናል ብለን ተኩሰን መግደል አንፈልግም። ግድያ፣ እስር፣ እንግልት ይበቃናል። ለዘመናት አይተነዋል። ለዘመናት ተሰቃይተንበታል። እዚህ ጋር ሊቆም ይገባል” የሚል ነው።
ኮሚሽነር ጄነራል ዘይኑ ጀማል ከጋዜጠኛ ካሣሁን ሰቦቃ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡ።
ዘጋቢ ካሣሁን ሰቦቃ ለኤስ.ቢ.ኤስ ሬድዮ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል
በፌዴራል ፖሊስ አባላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የሶስት ፖሊሶች ሕይወት ጠፋ ― የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ዛሬ [መስከረም 24 ቀን 2011 ዓም] ማለዳ በአዲስ አበባ ቦሌ ወሎ ሰፈር አካባቢ በፖሊስ አባላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የሶስት ፖሊሶች ሕይወት መጥፋቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
ምክትል ጀኔራል ኮሚሽነር መላኩ ፋንታ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት በፌዴራል ፖሊስ አባላቱ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት አንድ አባል በያዘው መሳሪያ በከፈተው ተኩስ ሁለት ፖሊሶችን ገድሏል።
ድርጊቱን የፈጸመውን አባል በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት ተደርጎ ባለመሳካቱ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ሲባልም እርምጃ ተወስዶበታል።
ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ ወደፎቁ የላይኛው ክፍል በመውጣት ላይ ሳለ በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ሲከታተሉት የነበሩትን ስድስት የስራ ባልደረቦቹን በመተኮስ አቁስሏቸዋል።
ለጥበቃ በታጠቀው ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ተኩሱን እንደከፈተ የተረጋገጠው ይህ የፖሊስ አባል አለቆቹን ከገደለ በኋላ ተጨማሪ መሳሪያ ከባልደረቦቹ በመቀማት ሊይዙት በመጡት የጸጥታ ሃይሎች ላይ እስከ ማለዳ ደረስ ሲተኩስ ቆይቷል።
አለመግባባቱ የተከሰተበት ስፍራ በርካታ ነዋሪዎች የሚገኙበት የመኖሪያ አፓርተማ በመሆኑ ፖሊስ በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረጉን ምክትል ጀኔራል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
”አባሉ በሥራ ቦታ ላይ መጥቶ ምድብ ቦታው ላይ ከነበሩ አባላት ጋር የሥራ ርክክብ ሲያደርጉ ግጭት ተፈጥሮ የከፋ ችግር እንዳያደርስ ምክር ቢሰጠውም መቀበል አልቻለም፤ በያዘው መሳሪያ የሥራ ጓዶቹ በሆኑ ሁለት ፖሊሶች ላይ የሞት አደጋ አድርሷል” ብለዋል።
በተደረገው መከላከል የከፋ አደጋ ሳይደርስ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ መደረጉንና ፖሊስ በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል ሥራ መሥራቱንም አክለዋል።
አባሉ ተደጋጋሚ የስነ-ምግባር ችግር ባይመዘገብበትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚደረግ የሥራ ግምገማ ሊያርማቸው የሚገቡ ጉዳዮችን እንዲያስተካክል ቢነገረውም ያልተቀበለው በመሆኑ የዛሬውን ችግር ሊፈጥር እንደቻለ ምክትል ጀኔራል ኮሚሽነር መላኩ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና ARTS TV
ለሶማሌ ክልል በድጎማ ከተመደበ በጀት ላይ ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ በቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድና በሌሎች ግለሰቦች መወሰዱን ጠቅሶ፣ ገንዘቡ እንዳይንቀሳቀስ ፖሊስ አሳገደ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በተለያዩ የምርመራ መዝገቦች ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ባቀረበው ማመልከቻ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) እና የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥ የነበሩት አቶ አብዱራህማን አብዱላሂን ጨምሮ፣ በ11 ሰዎች ለግል ጥቅም ተወስዷል ያለውን በአጠቃላይ 132.2 ሚሊዮን ብር እንዲታገድ ጠይቋል፡፡
የተሻሻለውን የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ (8) በመተላለፍ የተፈጸመና የተጠቀሰውን ያህል የብር መጠን ያለው ጉዳት፣ በመንግሥት ላይ የደረሰ መሆኑን በማስረዳት ገንዘቡ እንዲታገድ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የተጠቀሰው ገንዘብ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ እንዳይንቀሳቀስና ተጠብቆ እንዲቆይ፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎች ባንኮችም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ማንበብዎን ይቀጥሉ፦ በቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንትና በሌሎች ግለሰቦች ተወስዷል የተባለ 130 ሚሊዮን ብር ታገደ