-
Search Results
-
2ተኛው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን፣ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የ2012 ዓ.ም የ5 ቢሊዮን የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አርብ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀዋሳ ከተማ በታቦር ተራራ በይፋ ተጀምሯል።
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስጀመሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እየሠራች እንደሆነ ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 84 በመቶ መፅደቁን አስታውሰው፥ ዘንድሮ የታቀደውን 5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ግቡን ለማሳካት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ግቡን ማሳካት ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
በዘንድሮ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በደቡብ ክልል በ227 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 1.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፥ ወይራ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ እና የአበሻ ፅድ የመሳሰሉት ሃገር በቀል ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በዓለም ለ47ተኛ ጊዜ በሀገራችን ለ27ተኛ ጊዜ የሚከበረው የአለም የአካባቢ ቀንም (World Environment Day) “አካባቢን መጠበቅ የብዝሃ-ህይወትን በመጠበቅ ነው” በሚል መሪ-ቃል ከ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ጋር እየተከበረ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው መሪ ቃል “ለተፈጥሮ ጊዜ እንስጥ” (‘Time for Nature’) የሚል ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት “40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ቃል ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል አቅዳ 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞች ተተክሎ የዓለም ክብረ ወሰን መያዟ የሚታወስ ነው።
አምና 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በአጠቃላይ 4.7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከል የተቻለ ሲሆን 23 ሚሊዮን ሕዝብ መሳተፉም ይታወሳል። በቀጣም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በየዓመቱ የሚካሄድ ይሆናል ተብሏል።
ምንጭ፦ የግብርና ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ጉራጌ በክልል የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ የክልሉ መንግሥት በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠው የብሔሩ ተወላጆች ጠየቁ።
ኧዣ ወረዳ ፥ጉራጌ ዞን (ሰሞነኛ) – የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳው ከጉራጌ ማኅበረሰብ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጉራጌ ዞን ኧዣ ወረዳ በደሳለኝ ሎጅ ውይይት አካሄዱ። የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ጉራጌ በክልል የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብቱ በሰላማዊና በሰለጠነ መልኩ የክልሉ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ ጥሪ አቀረቡ።
በጠንካራ የሥራ ባህሉና ከየትኛውም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተግባብቶ፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር የቆየ ልማድ ያለው የጉራጌ ብሔር ባለፋት 27 ዓመታት በማኅበራዊ፣ በፓለቲካዊና በኢኮኖሚው ከፍተኛ በደልና ጭቆና ሲደርስበት እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ አሁን በመጣው የሀገሪቱ ለውጥ ፍትሃዊ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ተጠቃሚነቱ ሊረጋገጥለት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አክለውም ብዙ ጊዜ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሲነሳ ጉራጌ ክልል አያስፈልገውም የሚል አስተያየት የሚሰጥ መሆኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ፥ ክልል የማያስፈልግ ከሆነ አሁን ያለው የዞን አስተዳደር ለምን ያስፈልጋል፣ ጉራጌ በክልል ቢደራጅ ስጋቱ ምንድን ነው የሚል ጥያቄዎች ተነስተው በመድረክ አወያዮቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንደገለጹት፥ ዞኑ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ስትሆን መንግሥት እንኳ ባይኖር ሕዝቡ ራስ በራሱ መምራት የሚችልበት ቱባ ባህል፣ እሴትና እምነት እንዲሁም ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ያለው ነው ብለዋል።
የዞኑ ሰላም ለማስጠበቅ የሀይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች እየሠሩት ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት አቶ መሀመድ፥ በቀጣይም የሕዝቦች አንድነት ለማጠናከር በትኩረት ይሠራል ብለዋል። ጉራጌ በክልል የመደራጀት ጥያቄ የሚጠይቀው ለቅንጦት ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ስለሆነ መንግሥት አፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ አቶ መሀመድ ጠይቀዋል።
በክብር እግድነት የዞኑ ማኅበረሰብ ለማወያየት የመጡት የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ እንደተናገሩት፥ የጉራጌ ብሔር ለሥራ እንጂ ለግጭትና ለንትርክ ጊዜ የሌለው ከየትኛውም ብሔር ብሔረሰብ ጋር ተከባብሮና ተዋዶ በፍቅር የሚኖር ነው ብለዋል። ጉራጌ በክልል እንዲደራጅ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አሁን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ መልስ መስጠት እንደማይችሉና በቀጣይ በመመካከር ለህብረተሰቡ ምላሽ እንደሚሰጠው አቶ ሞገስ ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳው ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሳላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ እንደተናገሩት፥ በመስቃን ቤተ ጉራጌና በማረቆ መካከል የተፈጠረው ግጭት ለመፍታት ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑንና በአጭር ጊዜ መፍትሄ ያገኛል ብለዋል።
ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝቡ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሲመልሱ እንደተናገሩት፥ ጉራጌ በክልል የመደራጀት መብት እንዳለው ጠቁመው ጥያቄው የሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ በማያደናቅፍ መልኩ መሆን አለበት በማለት አቋማቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ የደቡብ ክልል የካቢኔ አባላት፣ ከአዲስ አበባ የመጡ አመራሮችና ተወላጆች፣ ባለሀብቶች፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ነበሩ ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ነው።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ሀገር የማዳን ጥሪ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሕዝብ ግንኙነትባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በሥርዓት አልበኞች በተወሰደ የጥፋት እርምጃ የማይተካ የዜጎቻችንን ሕይወት አጥተናል፣ የብዙዎች አካል ጎድሏል፣ ዜጎች ለፍተው ያፈሩት ንብረት ወድሟል እዲሁም በተዘጉ መንገዶች ምክንያት ዜጎች ተንገላተዋል፤ የሀገሪቷ የኢኮኖሚ እቅስቃሴም ተስተጓጉሏል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዜጎች ሕይወት ላይ በደረሰው ጥፋት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል። ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል። የተፈጸመውን ሕገ ወጥ እና አሳፋሪ ተግባር አጥብቆ ያወግዛል!
የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል ለመጫን የሚደረጉ የሥርዓት አልበኞች ሙከራዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ መጥቷል። የመንግሥት እነዚህን ሙከራዎች አስቀድሞ የመተንበይ፣ ሲከሰቱም አፋጣኝ እና ተገቢውን ምላሽ የመስጠት አቅሙ ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል እየታየበት አይደለም። በዚህም ምክንያት የዜጎች ሕይወት በተደጋጋሚ አደጋ ላይ ወድቋል፤ አሁንም እየወደቀ ይገኛል። በቁጥር ቀላል የማይባሉ ዜጎች በሀገራቸው ደኅንነታቸው ተጠብቆ በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ የመሥራት እና የመኖር መብታቸውን መጠቀም የማይችሉበት ብቻ ሳይሆን በማያቋርጥ ስጋት እና ጭንቀት ውስጥ ሕይወታቸውን እንዲመሩ የተገደዱበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ከዚህም አልፎ በዕምነት ተቋማት እና ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለመተማመን ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት እየሆነ ነው። ይህ ጉዳይ በአስቸኳይ የማይታረም ከሆነ የሽግግር ሂደቱ ተጨናግፎ ወደማንወጣው ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል።
መንግሥት የችግሩን ጥልቀት እና ሕግ የማስከበር ድክመቱን በሚገባ ፈትሾ በአስቸኳይ ክፍተቶቹን እንዲያስተካክል እና የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት የማስጠበቅ እና ጥፋተኞችን ሕግ ፊት የማቅረብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጥብቀን እናሳስባለን።
መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ የጋራ ሀገራችንን ከጥፋት አፋፍ ለማዳን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ የሚገባን ወቅት ላይ መሆናችንን ተገንዝበን ልዩነቶቻችንን አቻችለን በአንድነት እንድንቆም እና ሀገራችን ከተደቀነባት ከባድ አደጋ እንድንታደግ ከአደራ ጭምር ጥሪ እናስተላልፋለን።
የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት
ምንጭ፦ ኢዜማ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- ከኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ (ህወሃት እየፈጠረ ያለው ተግዳሮት)
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሸነር የእስረኞች ጉብኝት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
- “ባንዲራ ይዛችሁ ወጥታችኋል” በማለት ክርስቲያኖችን የሚያዋክቡ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ
- ጥፋተኞች ለሕግ ይቀርባሉ፤ ሰላምን ለማስፈን እንተጋለን ― አዲስ የተሾሙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው
- ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
አቶ ርስቱ ይርዳው በሹመት ንግግራቸው “ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ያጋጠሙ ውስብስብ ችግሮች መፍትሔ በሚሹበት ሰዓት ቢሆንም፤ የሕዝቦችን ኃላፊነት በመቀበሌ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።
ሀዋሳ (ሰሞነኛ) – የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዘጠነኛ መደበኛ ጉበኤው የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመሾምና ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በማጽደቅ ተጠናቀቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ ከገመገመ በኋላ የርዕሰ መስተዳድር ለውጥ እንዲደረግ በወሰነው መሠረት አቶ ርስቱ ይርዳው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እንዲመሩ ሾሟቸዋል።
በተጨማሪም ደኢህዴን ለ2012 በጀት ዓመት 40 ቢልዮን 56 ሚሊዮን 938 ሺህ 826 ብር አጽድቋል። በጀቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ3 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው።
የበጀቱ ምንጭ ከፌዴራል መንግሥት ድጎማ፣ ከውጭ እርዳታና ከክልሉ ገቢ እንደሚሰበሰብ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምራት ዲላ ገልጸዋል።
አቶ ርስቱ ይርዳው በሹመት ንግግራቸው ጥፋተኞችን ለሕግ ማቅረብና ሠላምን ማስፈን ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል። በመልዕክታቸው “ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ያጋጠሙ ውስብስብ ችግሮች መፍትሔ በሚሹበት ሰዓት ቢሆንም፤ የሕዝቦችን ኃላፊነት በመቀበሌ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።
ከደኢህዴን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጣሉባቸውን እምነት፣ ሁሉንም በእኩል ዓይን በማገልገል ለመወጣት ቅን ፍላጎት እንዳላቸው አቶ ርስቱ ይርዳው ገልፀዋል።
በክልሉ የተነሱ የክልልነትና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ለክልሉና ለደህኢዴን ከባድ ፈተና ስለመሆናቸው ያነሱት አቶ ርስቱ፥ የተፈጠሩትም ሁከቶች ከባድ ጉዳት ያደረሱና የአብሮነት ሕልውናን የተፈታተኑ ነበሩ ብለዋል።
በክልሉ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ ሰላም የማስፈንና ጥፋተኞችን ለሕግ ማቅረብ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ መሆናቸውንም አቶ ርስቱ ገልፀዋል።
አቶ ርስቱ በሹመት ንግግራቸው “የብሔር ፅንፈኝነትን፣ የሀይማኖት አክራሪነትን እና ሕገ ወጥነት ለመከላከል ጠንካራ ሥራ ይሠራል” ብለዋል።
የአመራር ማስተካካያዎችም በጥብቅ ትኩረት እንደሚከናወንም ነው አቶ ርስቱ በንግግራቸው ያስገነዘቡት።የኑሮ ውድነትንና ሥራ አጥነትን ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠራ የተናገሩት አቶ ርስቱ፥ ከባለሀብቶች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎት በመግለፅ፣ የእንደጋገፍ ጥሪ ለባለ ሀብቶቹ አቅርበዋል።
አቶ ርስቱ ይርዳው ከ1985 እስከ 2001 ዓ.ም. በክልሉ ጉራጌ ዞን ከወረዳ አመራርነት እስከ ዞን አስተዳዳሪነት ያገለገሉ ሲሆን፤ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ የደኢህዴን ሥራ አስፈፃሚ እና በፌደራል ደረጃ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለትምህርትና ጤና አገልግሎት የሚውል ከ452 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገ። የጃፓን መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ አራት ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና ለማስፋፋት ያስችላል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ (Daisuke Matsunaga) የፕሮጀክት ግንባታና ማስፋፊያ ከሚደረግላቸው ትምህርት ቤቶች ኃላፊዎች ጋር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ፕሮጀክቶቹ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የጉንችሬ እና እነሞር ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታና በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሀሮ ሾጤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ናቸው።
በተጨማሪም ለሻሻመኔ ከተማ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች የምግባረ ሰናይ መጠለያ ግንባታና ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የዩሮሎጂ እና ድንገተኛ ክፍል የህክምና መሣሪያዎች ግዥ የሚውል ነው።
እነዚህ አራት የትምህርት እና የጤና ፕሮጀክቶች ከአራት ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እንዳሉት አገራቸው ለኢትዮጵያ ልማት ተሳትፎ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች። ጃፓን በኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1989 ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ከ400 በላይ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገች ነው።
በትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በኢኮኖሚ ልማትና ሌሎችም መስኮች ድጋፍ ስታደርግም ቆይታለች።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽነር እርስቱ ይርዳው የተደረገው ድጋፍ የዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ድጋፉ በተለይም ትምህርት ቤት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መሆኑ የትምህርት ሽፋንን በማስፋት የመንግስትን ጥረት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የጃፓን ኤምባሲ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘውን የራስ መኰንን አዳራሽ ለማደስ የ85 ሺሕ 679 ዶላር (2,403,500 ብር) ዕርዳታ መለገሱን ሪፖርተር ጋዜጣ በእሁድ ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. እትሙ ዘግቧል።
አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር አህመድ ሐሰን (ዶ/ር) የእርዳታ ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን፣ ገንዘቡም የራስ መኰንን አዳራሽ ባህላዊና ታሪካዊ ዳራው ሳይጠፋ ለማደስ፣ የተበላሹ ክፍሎችን ለመጠገን፣ ውስጣዊ ክፍሉን ለማደስ እና አዳዲስ ቁሳቁስ ለማስገባት መሆኑ ታውቋል።
የጃፓን መንግስት ትምህርታዊ ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ የራስ መኰንን አዳራሽን ለማደስ መነሳቱ፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ኢትኖሎጂካል ሙዚየም በርካታ ጎብኚዎች እንዲስብ ያስችላል ተብሏል።
በሙዚየሙ ከአሥር ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚገለጹባቸው አልባሳትና ቁሳቁሶች አሉ፤ ይህም በአፍሪካ አንዱ ታዋቂ ሙዚየም እንዲሆን አስችሏል።
በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሕንፃ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜው በስሩ ያቀፋቸው ቤተ-መጻሕፍት፣ የኢትኖግራፊክ ሙዚየም የምርምርና የጥናት ማዕከልን ነው። በውስጡም መጻሕፍት፣ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት፣ የዳግማዊ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የድምፅና የምስል ቅጂዎች፣ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ድርሳኖች፣ ጆርናሎች፣ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍትንም ይዟል።
እንዲሁም እስከ 20 ሺሕ የሚደርሱ የኅትመት ክምችቶች ከቅድመ ምረቃ እስከ ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም. መስከረም ወር ከጃፓኑ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትምህርታዊ ልውውጥና የጥናት ትብብር ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ኢዜአ እና ሪፖርተር ጋዜጣ
Search Results for 'ርስቱ ይርዳው'
Viewing 6 results - 1 through 6 (of 6 total)
Viewing 6 results - 1 through 6 (of 6 total)