AnonymousInactive
ትግራይ ክልል – የሲቪል ሰዎችን ሁኔታ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል
አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 21 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ የግንኙነት መሰመሮች በመቋረጣቸው፣ በክልሉ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሁኔታ እንደሚያሳስበውና መንግሥት የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ እርምጃዎች በአፋጣኝ ሊወስድ እንደሚገባ ገለጸ። በክልሉ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስና በትግራይ ክልል ስላለው ተጨባጭ የፀጥታ ሁኔታና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በቂ መረጃ መስጠት፣ በዚህ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለማረምና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ለመፍጠር ቀዳሚ እርምጃዎች ናቸው።
ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት አስፈላጊነት እንደተጠበቀና በክልሉ ለሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥበቃና ለተደራሽነቱ ትብብር እንደሚቀጥል መገለጹ የሚበረታታ ሆኖ፣ የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በአሁኑ ወቅት በአብዛኛዎቹ የትግራይ አከባቢዎች የመብራት፣ የስልክ እና የውሃ አገልግሎት በመቋረጡ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከባድ የኑሮ ጫና እያስከተለ ይገኛል። የባንክ አገልግሎት መቋረጥና የጤና አገልግሎት አቅርቦትና ተደራሽነት ውሱንነት ችግሩን አባብሶታል።
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሀገራዊና ዓለምአቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የኤሌክትሪክ እና የስልክ አገልግሎት መቋረጥን ጨምሮ የሌሎች አቅርቦቶች እጥረት የሰብዓዊ ድጋፉን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳውና በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ስለሚገኙበት ሁኔታ ማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ፣ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታ ኮሚሽኑ በመከታተል ላይ ይገኛል። ይህም በነዋሪዎች ላይ ማንነትን በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይሆን ስጋት የሚያሳድር ነው።
በተጨማሪም፥ በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ወጣቶች ወላጆችና ቤተሰቦች ተማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ስለሚገኙበት ሁኔታ ተገቢው ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የነዋሪዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግሥት ግዴታ መሆኑን አስታውሰው፥ “በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች ስላሉበት ሁኔታ የተገቢው መረጃ ማነስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደመጡ ዘገባዎችና ንግግሮች ጋር ተዳምሮ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ የሚጥል ነው። የተኩስ አቁሙ በሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ በነበሩ ወገኖች ሁሉ በቁርጠኝነት መከበር እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መመለስ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን ለማሻሻል፣ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ፣ እንዲሁም ሰብዓዊ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው። በተጨማሪም ማንኛውም አይነት እስር ሁልጊዜም ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ሁሉ ሁኔታውን የሚያባብሱ፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና ጥርጣሬን ሊፈጥሩ ከሚችሉ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፦ ኢሰመኮ
AnonymousInactive
ከትግራይ ክልል ሁኔታ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች አያያዝ
አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እና የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው እስር ቤት የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በመገኘት በታሳሪዎች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል አድርገዋል።
በጉብኝቱ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙትን እነ ዶ/ር አብረሃም ተከስተ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ አቶ ስብሀት ነጋ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ፣ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ፣ ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ፣ ሜ/ጀነራል ይርዳው ገብረመድኅን፣ ሜ/ጀነራል ገብረመድኅን ፍቃዱ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋን ጨምሮ በአጠቃላይ 21 ታሳሪዎች የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ ጎብኝተው ታሳሪዎችን አነጋግረዋል። እንዲሁም ከፖሊስ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በጉብኝቱም ታሳሪዎቹ በጥሩ አካላዊ ደኅንነት ላይ እንደሚገኙ፣ የሚገኙበት አካባቢና ክፍሎች ንፁህ እና ብዙም ያልተጨናነቁ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን ያላቸው መሆኑንና አጠቃላይ ሁኔታው ተቀባይነት ያለው መሆኑን ኮሚሽኑ ተመልክቷል። ሁሉም ከላይ የተጠቀሱት ታሳሪዎች ወደ ፌዴራል ፖሊስ እስር ቤት ከመጡ ወዲህ ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩንና ፖሊሶች በተገቢው የሙያ ሥነ ምግባር የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። የህክምና አገልግሎት ባለው አቅም እያገኙ እንደሆነ፣ ከቤተሰባቸው ተገናኝተው አቅርቦት እንደሚቀበሉ እና ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት መቻላቸውን አስረድተዋል። የተወሰኑ ታሳሪዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል በበረሀ ውስጥ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በሰብአዊ እንክብካቤ መያዛቸውን እና የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ከድንገተኛ አደጋና ጥቃት እንደጠበቋቸው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን፣ በትግራይ ክልል ከመቀሌ ከተማ ሸሽተው ሲሄዱ በተያዙበት ጊዜ ስድብ፣ ድብደባ፣ ማስፈራራት እና ተኩስ እንደነበረና የአካል መቁሰል እንደደረሰባቸው፣ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም ነፃ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጋፋ መልኩ በሚዲያ አሰልፎ የማቅረብ እና የማንኳሰስ ሁኔታ እንደነበረ ያነሱ ታሳሪዎች አሉ። አብዛኞቹ ታሳሪዎች የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ በተናጠል አለመቅረቡን እና የምርመራ ሂደቱ በአፋጣኝ አለመታየቱን ገልጸው አቤቱታ አቅርበዋል። ታሳሪዎቹ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከጠበቆች ጋር የሚገናኙበት ጊዜ ማጠሩን አንስተዋል። በተጨማሪም የተወሰኑ ታሳሪዎች የራሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ ሒሳብ በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹ የሚገኙበት የአያያዝ ሁኔታ በተገቢው ደረጃ መሆኑን በማረጋገጥ፣ በታሳሪዎች የተነሱ አስተዳደር ነክ ጥያቄዎች ላይ ከእስር ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጓል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የወንጀል ምርመራውን በተቻለ ፍጥነት ማጠናቀቅ እና የሕግ አግባብ በሚፈቅደው መልኩ በዋስትና ሊለቀቁ የሚገባቸውን ታሳሪዎች መለየት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
ምንጭ፦ ኢሰመኮ
AnonymousInactive
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ትግራይና አማራ ክልል፡ የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመራ ይችላል
አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እና ድጋፍ ሊቀርብ ይገባል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ፣ በቦታው ያሉ የሲቪል ሰዎች ደኅንነት እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቦታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በአሳሳቢና ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመራ በሚችል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገለጸ። ኮሚሽኑ ከታኅሣሥ 6 እስከ ታኅሣሥ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በጎንደር እና በዳንሻ በመገኘት እንዲሁም፣ ከታኅሣሥ 22 እስከ ታኅሣሥ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ በትግራይ ክልል፣ ደቡባዊ ዞን፣ ጨርጨር ወረዳ በሚገኙት ኡላጋ እና ቢሶበር መንደሮች በመጓዝ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም ተጎጂዎችና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ያደረገውን ክትትል ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
በተጨማሪም የኮሚሽኑ ባለሞያዎች ከጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለተጨማሪ ዙር የመስክ ምልከታ ወደ መቀሌ ከተማ እና ሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች በመንቀሳቀስ፥ በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረውን የሰብዓዊ ቀውስ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በመመርመር ላይ የሚገኝ ሲሆን ሥራው እንደተጠናቀቀ ተጨማሪ ሪፖርቱን ይፋ የሚደረግ መሆኑን ኮሚሽኑ አክሎ አሳውቋል።
የአሁኑ ክትትል በዋነኛነት በተካሄደባቸው በዳንሻ፣ በሁመራ፣ በቢሶበር እና በኡላጋ ጦርነቱ የሲቪል ሰዎችን ሞትና አካላዊ ጉዳት አስከትሏል፤ የሲቪል ሰዎችን መኖሪያና የንግድ ቦታዎች ለዝርፊያና ለተለያዩ ጉዳቶች አጋልጧል፤ እንዲሁም በመሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ውድመትና የኤሌክትሪክ እና የውሃ የመሳሰሉ አገልግሎቶች አለመመለስ፣ በአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እና በተፈናቃናዮች ላይ የበለጠ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል የሚያሰጋ ነው። በቢሶበር እና በኡላጋ 31 ሲቪል ሰዎች ሞተዋል፤ 104 መኖሪያ ቤቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል፤ እንዲሁም የአካባቢው ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በሁመራ እና በዳንሻ የሲቪል ሰዎች ንብረት የሆኑ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶችን ጨምሮ የአካባቢው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ውድመት እና ዝርፊያ ደርሷል። ሲቪል ሰዎች በብሔራቸው ምክንያት ወይም በአካባቢዎቹ የፀጥታ መጓደል ምክንያት ለደኅንነታቸው እንደሚሰጉ ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። በአጠቃላይ በእነዚህ አራት ከተሞች ያለው የፀጥታ ስጋትና የፍትህ አካላት ወደ መደበኛ ሥራቸው አለመመለስ፣ የሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅና የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ጥበቃ ለማረጋገጥ አዳጋች አድርጎታል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ጉዳቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ሲያስረዱ፥ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ምርመራውና ክትትሉ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ፣ የነዋሪዎቹንም ሆነ ከትግራይ ክልል ወደ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን ሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት እንዲጨምርና የመቋቋም አቅማቸውን በአስከፊ ሁኔታ እንዲፈተን አድርጓል” ብለዋል። የኮሚሽኑ ምርመራ ቡድን የጎበኟቸው ተጎጂዎች በአብዛኛው በአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ እርዳታ የተደረገላቸው አሊያም አንድ ዙር ብቻ እርዳታ የተደረገላቸው መሆኑን በሪፖርቱ እንደተመለከተ ጠቅሰው፥ “በአካባቢዎቹና በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት የሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት ከፍተኛና አፋጣኝ ርብርብ የሚጠይቅ ነው” በማለት ገልጸዋል።
ሙሉውን ሪፖርት እዚህ ጋር (ማስፈንጠሪያ) በመጫን ማግኘት ይቻላል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
AnonymousInactive
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ
ኦሮሚያ ክልል ― የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ተከስቷል፤ አጥፊዎቹ ሕግ ፊት መቅረብ አለባቸው
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ አካባቢዎች በተከሰተ የፀጥታ መደፍረስ የተሳተፉ ሰዎችና ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ ያደረሷቸው ጥቃቶች በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ባህርያትን የሚያሟሉ መሆናቸውን በምርመራ ሪፖርቱ አመለከተ።
ኢሰመኮ ከሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩ ሦስት ተከታታይ ቀናት በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የባለሙያ ቡድኖቹን ወደ 40 የክልሉ አካባቢዎች የላከ ሲሆን፥ የምርመራውን ግኝቶች ታኅሣሥ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።
በ59 ገጽ ሪፖርቱ እንደተመለከተው፥ በዚህ መጠነ ሰፊ ጥቃት የተሳተፉት ብዙ ቁጥር ያላቸው እና ከቦታ ቦታ በቡድን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች ሲሆኑ፤ በጩቤ፣ በድንጋይ፣ በእሳት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ፣ በዱላ፣ በዶማ፣ በገጀራ እና በመጥረቢያ ተጠቅመው ሰዎችን ደብድበዋል፤ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፤ ፍጹም ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በማሰቃየት እና በማረድ ጭምር ሰዎችን ገድለዋል። በጥቃቶቹ የ123 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ 500 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
በአብዛኛው በቡድን የተደራጁ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ፣ በብሔርና በሀይማኖታቸው ተለይተው የተመረጡ ሲቪል ሰዎችን፣ ቢያንስ በ40 የተለያዩ ቦታዎች በተስፋፋና ለሦስት ቀናት በቆየ ሁከት ማጥቃታቸው፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንደሚያደርገው የኮሚሽኑ ግኝቶች ያመላክታሉ።
ምንም እንኳን የፀጥታ ኃይሉ በየቦታው የገጠመውን መጠነ ሰፊ የፀጥታ መደፍረስ ችግር እና የፀጥታ አባሎቹንም የሕይወት መስዋዕትነት በሚጠይቅ ሁኔታ በመሰማራታቸው ኃላፊነታቸው እጅግ ፈታኝ የነበረ መሆኑን መገንዘብ ቢቻልም፤ በተወሰኑ ቦታዎች የኃይል አጠቃቀም ተመጣጣኝነት ከፍተኛ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል። በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ፥ ሰልፍ ውስጥ ያልነበሩ፥ በመንገድ ወይም በቤታቸው በር ላይ የተገደሉ፣ ለማሸማገል ጣልቃ የገቡ የአገር ሽማግሌዎችን እና የአዕምሮ ህመምተኛ ጭምር እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ‘በኢትዮጵያ የሚታየው የግፍና የጭካኔ ወንጀሎች መደጋገም፣ የችግሩን ስር መሠረት ለመፍታት የሚያስችል የተሟላ ብሔራዊ የግፍና ጭካኔ ወንጀል መከላከያ ስትራቴጂ ነድፎ በአፋጣኝ በሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ የሚያሳይ መሆኑን’ ገልጸዋል።
ሙሉ ሪፖርቱ “መንግስት ያለ አይመስልም ነበር፡ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ሪፖርት” በሚል ርዕስ እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።
AnonymousInactive
ማይካድራ ውስጥ ሲቪል ሰዎች ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ የግፍና ጭካኔ ወንጀል ነው ― ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ
ትግራይ፡ የማይካድራ ሲቪል ሰዎች ጭፍጨፋ የግፍና ጭካኔ ወንጀል ነው
የተጎዱትን ማቋቋም እና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ ይገባል
በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በምትገኘው ማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅቱ በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን የተፈጸመው ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል (atrocious crime of massacre against civilians) መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
ይህ የተገለጸው ኮሚሽኑ ከሕዳር 5 እስከ ሕዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀ ጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጐንደር ከተሞች ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን ግኝቶች ይፋ ባደረገበት የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርት ነው። ይህ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) እና የጦር ወንጀል (war crime) ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ስለሆነ፥ ኮሚሽኑ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑን አሳውቋል።
በቀዳሚ ሪፖርቱ እንደተመለከተው፥ በአካባቢው የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር በፌዴራሉ ሀገር መከላከያ ሠራዊት እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበርና በመተባበር በተለይ “አማሮችእና ወልቃይቴዎች” ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፣ በስለት በመጥረቢያ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል፤ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፤ እንዲሁም ንብረት አውድመዋል። ኢሰመኮ ከአካባቢው ምንጮች እስከ አሁን ባገኘው መረጃ በአነስተኛ ግምት እስከ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥም እንደሚችል በሪፖርቱ ተመልክቷል።
ሳምሪ የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጅች የሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተ ክርስቲያን እና በእርሻ ቦታ ደብቀው በመሸሸግ ሕይወታቸውን እንዳተረፉላቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ምስክሮች አረጋግጠዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “በማይካድራ ከተማ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ እጅግ ዘግናኝ ኢ-ሰብዓዊ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል፤ ስለ ወደፊት በሰላም አብሮ መኖርም ተስፋ ይሰጣል” ብለዋል። አክለውም “የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመጠገን በተጨማሪ፥ በዚህ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ብለዋል።
የኮሚሽኑን የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርትን እዚህ ጋር በመጫን ማግኘት ይቻላል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም.
AnonymousInactive
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ኦሮሚያ ክልል፡ የዋስትና መብትን በተቀላጠፈ መንገድ ስለማረጋገጥ
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበታ ልዩ ችሎት ለአራት ወራት ያህል በእስር በቆዩት በአቶ ለሚ ቤኛ እና በአቶ ዳዊት አብደታ ጉዳይ የዋስትና መብታቸውን በማረጋገጥ የሰጠውን ትክክለኛ ውሳኔ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እውቅና እየሰጠ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሥራ አስፈጻሚና የፍትሕ አካላት በተመሳሳይ መልኩ የሌሎችንም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት መከበሩን እንዲያረጋግጡ ጥሪ ያቀርባል።
ኢሰመኮ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፥ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸውና የዋስትና ሁኔታውን አሟልተው ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጠላቸው ሰዎች በእስር እንዲቆዩ መደረጉ ፍትህን የሚያጓድልና ሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ ተግባር መሆኑን በመግለጽ፥ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተከብሮላቸዉ በእስር ላይ የነበሩ ሰዎች በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ ማሳሰቡ ይታወሳል።
በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ስለሚገኙ ሰዎች ሁኔታ ሊወሰድ የሚገባውን እርምጃ ለሚመለከታቸው የክልሉ ኃላፊዎች በማሳወቅ ክትትሉን የቀጠለ ሲሆን፤ በተለያዩ ቦታዎች አበረታች አርምጃዎች የተወሰዱ ቢሆንም አሁንም ድረስ በተለይ የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው በእስር የሚገኙ ሰዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል የአቶ ልደቱ አያሌው እና የዶ/ር ሁሴን ከድር ጉዳይ አፋጣኝ እልባት የሚሻ መሆኑን ኮሚሽኑ ያሳስባል።
ከሐምሌ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ በእስር ላይ ለሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ክስ የተመሠረተባቸው ሲሆን፤ አሁንም በድጋሚ ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ መሰጠቱ ይታወቃል። በኢሰመኮ ምርመራ መሠረት በአቶ ልደቱ ላይ የቀረቡት ክሶች የዋስትና መብት የማያስከለክሉ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ኢሰመኮ የተመለከተው የጤንነታቸው ሁኔታ ማስረጃዎች የዋስትና መብት ጥያቄውን በአፋጣኝ ተግባራዊ ማድረግን አስፈላጊነት ያስረዳል። ስለሆነም የአቶ ልደቱ አያሌው የዋስትና መብት በአስቸኳይ ሊፈቀድ የሚገባ ነው።
በሌላ በኩል ከሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሁሴን ከድር የአጋርፋ ወረዳ ፍርድ ቤት ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. የዋስትና መብት ፈቅዶላቸዉ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ከመስጠቱም በተጨማሪ፥ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከፖሊስ በቀረበለት የተጠርጣሪው የምርመራ መዝገብ ላይ በሰጠው ውሳኔ ክስ ለማቅረብ የሚያበቃ ማስረጃ አለማግኘቱን ጠቅሶ የምርመራ መዝገቡን ዘግቷል። ይሁንና ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ ፖሊስ ለኮሚሽኑ እንዳሳወቀው በተጨማሪ ወንጀል በመጠርጠራቸው አሁንም በእስር ላይ ናቸው፡፡ ዶ/ር ሁሴን ከድር አብዛኛውን የእስር ጊዜ የቆዩት በአጋርፋ እስር ቤት ሲሆን፤ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ከተማ ተወስደው አሁንም በኦሮሚያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ኢሰመኮ የተረዳ ቢሆንም፤ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ወዲህ ከቤተሰቦቻቸው አለመገናኘታቸው ኮሚሽኑን አሳስቦታል። ስለሆነም ዶ/ር ሁሴን ከድር በአስቸኳይ በቤተሰባቸው ሊጎበኙ የሚገባ ከመሆኑም በተጨማሪ፤ ሊያስከስስ የሚችል አሳማኝ ክስ ካለ በአፋጣኝ ሊቀርብ፣ አሊያም ከእስር ሊለቀቁ ወይም የዋስትና መብታቸው በአስቸኳይ ሊከበር ይገባል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት “የዋስትና መብት በሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የተረጋገጠ መሠረታዊ መብት እንደመሆኑ፥ በሕግ በግልጽ ከተመለከቱ ሁኔታዎች በስተቀር የዋስትና መብት በተቀላጠፈ አሠራር ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው ነው።” አክለውም “በዚህ ረገድ ፍርድ ቤቶች የተከሳሾችን የዋስትና መብት የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን እየወሰኑ መሆናቸው የሚበረታታ ተግባር ነው” ብለዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን
AnonymousInactive
የፖሊስ የዘፈቀደ እስር በአስቸኳይ ሊቆም እና የታሰሩትም ሊለቀቁ ይገባል
Police Should Immediately Stop Arbitrary Arrests and Release those Detained
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን) – [በትላንትናው ዕለት (ግንቦት 5 ቀን 2012 ዓ.ም.)] በአዲስ አበባ ከተማ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የተገኙ ሰዎች በፖሊስ እየታሰሩ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ በሚዲያዎች የወጡ ዘገባዎችንና ለኮሚሽኑ የቀረቡ አቤቱታዎችን ተከትሎ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሚከተለውን ብለዋል።
“የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል አስፈላጊ የጤና መመርያ ሲሆን ሕብረተሰቡም ሊከተለው የሚገባ ነው። በእርግጥም የአስቸኳይ ጊዜ ደንቡ ማንኛውም ሰው እንደ ገበያ ቦታዎች፥ ሱቆች ፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ባሉ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች እና በሌሎች ሕዝብ በሚበዛባቸውና የአካል መራራቅን መጠበቅ በማይቻልባቸው አካባቢዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል። ከዚህ ውጪ ግን በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የተገኙ ሰዎች ላይ ሁሉ የሚደረግ የዘፈቀደ እስር ከሕግ ውጭ ከመሆኑም በላይ ለነገሩ ሁኔታ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ እና የታለመለትን አላማ የሚቃረን በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፤ በዚህ ሁኔታ የታሰሩ ሰዎችም በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል።”
[የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በመጋቢት ወር 20212 ዓ.ም. የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ለአምስት ወራት ተግባራዊ እየሆነ እንደሚቆይ ተነግሯል።]
ADDIS ABABA (Ethiopian Human Rights Commission) – Responding to media reports and complaints of arrests by police in the city of Addis Ababa on 13th May 2020 for not wearing face masks, Chief Commissioner of the Ethiopian Human Rights Commission (EHRC) Dr. Daniel Bekele said:
“Covering nose and mouth are recommended health measures to prevent the spread of COVID-19 and the public needs to follow these critical health directives. Indeed, the Emergency Regulations impose an obligation to wear face covering in public service areas such as markets, shops, transport services or other public spaces with large number of people where social distancing is not possible. Otherwise, arbitrary arrest of people on the streets is outside the regulation, disproportionate and counter-productive measure which should stop immediately and all those detained should be released immediately.”
[In the first week of April 2020, Ethiopia has declared a state of emergency in the country to help curb the spread of the coronavirus pandemic. The state of emergency is reported to stay in action for five months from its declaration.]
Semonegna.com
AnonymousInactive
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ጋዜጣዊ መግለጫ
አዲስ አበባ፥ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሸነር የእስረኞች ጉብኝት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን ስር በአደራ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ተጠርጣሪ ታሳሪዎችን ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጐብኝተዋል።
ዋና ኮሚሸነሩ በዚህ ጉብኝታቸው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተማ ከተከሰተው የፖለቲካ ግድያ ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች በቁጥጥር ስር ከሚገኙ እስረኞች ውስጥ፥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር እና አባሎች ውስጥ እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ በለጠ ካሳን፤ ከባልደራስ ባለአደራ ምክር ቤት ንቅናቄ አባሎች ውስጥ እነ አቶ ኤልያስ ገብሩ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኰል እና አቶ መርከብ ኃይሌን፤ ከኢትዮጵስ ጋዜጣ ባልደረቦች አቶ ምሥጋና ጌታቸው እና አቶ አዳሙ ሁጁራን (አቶ አዳሙ በተጨማሪም የባልደራስ ባለአደራ ም/ቤት ንቅናቄም አባል ናቸው)፤ እንዲሁም «የተጠለፈው ትግል›› ከሚለው መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘም በእስር የሚገኙትን አቶ ፍሬው በቀለ፣ አቶ ሳሙኤል በቀለ፣ አቶ መለሰ ማሩ፣ አቶ ጋዲሳ ዳንኤል እና አቶ አማረ ተፈራን፤ በተጨማሪም የሟች ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋንና ሌሎች በርካታ ታሳሪዎችን በማነጋገር ጉዳያቸው ያለበትን ደረጃ እና የእስር ሆኔታቸውንም ተመልክተዋል።
ዋና ኮሚሸነሩ ‹‹የሴቶች እስር ክፍሉ በአንፃራዊነት የተሻለ እና የጽዳት ደረጃው የተጠበቀ ሲሆን በሌላ በኩል ከ300 በላይ ታሳሪዎችን የያዘው የወንዶች እስር ቦታ እጅግ የተጨናነቀ፣ በውሃ መቋራረጥ እና በታሳሪው ብዛትም የጽዳት ደረጃው ዝቅተኛ ነው» ያሉ ሲሆን ታሳሪዎቹ በየእለቱ ከቤተሰብ፣ ወዳጅ እና የሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እንደሚችሉም ለማወቅ ችለዋል።
በሌላ በኩል “ታሳሪዎቹ ከ 3–4 ወር ያህል የፖሊስ ምርመራን ለማጠናቀቅ በሚል በእስር የቆዩና በአሁኑ ወቅት በሕግ የሚፈቀደው የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በአብዛኛው የተጠናቀቀ እና ቀሪውም በመጠናቀቅ ላይ ያለ በመሆኑ ከዚህ በላይ ታሳሪዎቹ በእስር ሊቆዩ ስለማይገባ እንደየአግባቡ በዋስ ወይም ያለዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ተዓማኒ የሆነ ክስ በመደበኛው የወንጀል ሕግ መሰርት ሊቀርብ ይገባል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
“ከአንድ መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘ የመጽሐፉ ፀሐፊ ነው ተብሎ ከተጠረጠረ ግለሰብ አንስቶ፣ የማታሚያ ቤቱ ባለቤት፣ የመጽሐፉ የፊት ገጽ ዲዛይን የሰራ ግለሰብ፣ የመጽሐፉ አከፋፋይ እና የመጽሐፉ የጐዳና ላይ ቸርቻሪ ሻጭ ሳይቀር እንዲሆም ሌሎች ታሳሪዎች ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጌዜ ፎቶ አንስተሃል በሚል የተያዘ ጋዜጠኛ ጭምር ለዚህን ያህል ጊዜ በእስር መቆየታቸው አሳሳቢ ሁኔታ በመሆኑ አፋጣኝ እልባት እና የዋስትና መብት መከበር ያስፈልገዋል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ክቡር ዋና ኮሚሽነሩ በተጨማሪም ለጉዳዮቹ ሁሉ ሕጋዊ እልባት ለማግኘት ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር በመነጋገር ኮሚሽኑ ክትትሉን እየቀጠለ መሆኑን አሳውቀዋል።
ጉብኝቱ በዓለም ዓቀፍ የእስር ቤቶች ጉብኝት ደረጃ መሠረት ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የተደረገ ሲሆን የፖሊስ ኮሚሸኑ አመራሮች እና የጥበቃ ክፍል ኃላፊዎች ለዋና ኮሚሸነሩ ጉብኝቱ በማመቻቸት ኃላፊነታቸውን በመወጣታቸው ዋና ኮሚሸነሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ምንጭ፦ የኮሚሽኑ ፌስቡክ ገጽ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆኑ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም የኖቤል ሽልማት ለመቀበል የበቁት ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመታት የዘለቀው አለመግባባት በሰላም በመቋጨታቸውና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ባበረከቱት አስተዋጽኦ መሆኑ ሽልማቱን የሚሰጠው ኮሚቴ ገልጿል።
በሐምሌ 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉብኝት ዓለምን ያስገረመና ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ያልተቀመጠለት የቅርብ ወዳጅ ዘመድ ጥየቃ ዓይነት ቃና የነበረው ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎ ሁለት ዓይነት ሀሳቦች ቢስተናገዱም ሚዛን የሚደፋው ጉብኝቱ ሰላምን ለማምጣት መሠረት የተደረገ መሆኑ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአገር ውስጥና በአጎራባች አገሮች እያመጡ ያለውን ጉልህ ለውጥ ተከትሎ ‘ሽልማቱ ይገባቸዋል’ የሚሉ ድምጾች አሸናፊነታቸውን ቀድመው እንዳወጁላቸው ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጠቃላይ በጎረቤት አገሮች መካከል ሰላምንና አብሮነት ለማስረጽ ባደረጉት ጥረት የዘንድሮው የሰላም ኖቤል አሸናፊ ሆነው ተመርጠዋል።
ኖርዌይ ላይ አሸናፊው ይፋ ሲደረግ በኮሚቴው እንደተገለጸው፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት እውቅናና ማበረታቻ ያስፈልገዋል።
በእንግሊዝ ኪል ዩኒቨርሲቲ (Keele University) የህግ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢትዮጵያዊው አወሎ አሎ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ገጭት እንዲያበቃ በማድረጋቸው ሽልማቱ ይገባቸዋል” ማለት ግጭቱ በሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳስከተለና የማይተካውን ብዙ ህይወት እንደቀጠፈም ተናግረዋል።”
ከኤርትራ ጋር የወረደው ሰላም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍ ያለ ሙገሳ ያስገኘላቸው ሲሆን ለሁለቱ አገሮች ወንድማማች ህዝቦች ደግሞ ትርጉሙ ከዚህ የላቀ ነበር። በተለይ ተለያይተው የነበሩ ቤተሶች ሲገናኙ ያፈሰሱት የደስታ እምባ ሰላም ምን ያህል ዋጋ እንዳላት በተጨባጭ የመሰከረ ነው።
- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአገር ውስጥ የጀመሯቸው የለውጥ ማሻሻያዎች የፖለቲካ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን በመልቀቅ ተጀምሮ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው አስከመቀበል የዘለቀ ነው።
- ኢትዮጵያና ኤርትራ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት በቀጠናው የሰላም አየር እንዲነፍስ መሠረት ጥሏል።
- በሱዳን የተነሳውን የለውጥ ፍላጎት ከዳር ለማድረስ የተጀመረው ተቃውሞ በሰላም እንዲጠናቀቅና ተቃዋሚዎች ከወታደራዊ ቡድኑ ጋር ሰላም እንዲያወርዱ ያደረጉት አስተዋጽኦ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሱዳናውያን ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። በተለይ በሰኔ 2011 ዓ.ም ወደ ሱዳን በማቅናት ሁለቱን አገሮችለማስማማት የጀመሩትን ጥረት ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬት እንዲደግፉት በማድረግ ለውጤት እንዲበቃ አድርገዋል።
- ከዚህ ባለፈ ኤርትራና ጂቡቲ ጀርባ የተሰጣጡበትን አለመግባባቶች በሰላም እንዲቋጩና ለጋራ እድገት በጋራ እንዲነሱ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።
- በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር በአፍሪካ ቀንድአገሮች መካከል የኢኮኖሚ ህብረት እንዲኖር ያደረጉት ጥረት ለሰላምና ወንድማማችነት ያላቸውን ክፍት ልብ ያሳየ ነው።
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስና ሁሉንም ያማከለ እንዲሆን የማይደፈረውን ደፈረው ተንቀሳቅሰዋል።
- በዚህም ከዚህ በፊት በተቃዋሚነት ተፈርጀው ለእስር የተዳረጉትን አቶ ዳንኤል በቀለን የአገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አድርገው የሾሟቸው ሲሆን ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ደግሞ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር አድርገዋቸዋል።
- በተጨማሪም ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት በአገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ ውይይት ማድረጋቸው ሌላው ስኬታቸው ነው። በውጭ አገር ተቀምጠው የአገሪቱን ፖለቲካ ለመዘወር ሲጥሩ ከነበሩት ተቃዋሚዎች ጋርም ሰላም በማውረድ አገራቸው ገብተው እንዲታገሉ ሜዳውን ከፍተውላቸዋል።
- የደህንነቱንና የፍትህ ዘርፉንም ተአማኒ ለማድረግ በሩን ክፍት በማድረግ ተቋማዊ ለውጥ እንዲያመጡ እያገዙ ነው።
- በአገሪቱ ወደ ኋላ የቀረውን የሴቶች ተሳትፎ ከነበረበት አዘቅት በማውጣት ሴቶች በአመራርነት ቦታ ላይ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸውም አድርገዋል።
- በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ መስተካከል ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል። በዚህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አብሮነቱንና ዕውቅናውን ሰጥቷቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል ሽልማት 100ኛው አሸናፊ ናቸው። የኖቤል የሰላም ሽልማትን የሚያሸንፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች 900 ሺ ዶላር የሚሰጣቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመጪው ታህሳስ ወር በኦስሎ ሽልማታቸውን ይወስዳሉ።
በአጠቃላይ 301 ዕጩዎች ለዚህ ታላቅ ክብር ታጭተው የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከል 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶች ይገኙበታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ