ምርጫ በኢትዮጵያ ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ― ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች

Home Forums Semonegna Stories ምርጫ በኢትዮጵያ ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ― ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች

Viewing 15 posts - 1 through 15 (of 28 total)
  • Author
    Posts
  • #13377
    Semonegna
    Keymaster

    ምርጫ የሚደረግበት የመጨረሻ ቀን ወደፊት ይገለጣል፤ ጊዚያዊ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አይቻልም

    አዲስ አበባ (ዶይቸ ቬለ አማርኛ) – ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርጫ የሚደረግበት የመጨረሻ ጊዜ ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም.ን ጊያዊ የምርጫ ቀን ማድረጉን በቅርቡ አስታዉቆ ነበር። የቦርዱ ቃል አቀባይ ወ/ት ሶሊያና ሽመልስ ጥር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቁት ግን የመጨረሻዉ የምርጫ ቀን ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና “የሕብረተሰብ ክፍል” ካሏቸዉ ወገኖች ጋር ቦርዱ ከተወያየ በኋላ ይወሰናል። ቦርዱ ያስቀመጠዉ ጊዜያዊ የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ሳይጀመር የምረጡኝ ቅስቀሳ በሚያደርጉት ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በመመርመር ላይ እንደሆነም የቦርዱ ቃል አቃባይ ወ/ት ሶሊያና ሽመልስ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የዘንድሮዉ ምርጫና ዝግጅቱ የሚደረግበት ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ በቅርቡ ይፋ አድርጓል። በጊዜ ሰሌዳዉ መሠረት ካለዉ ታህሳስ 22 ቀን ጀምሮ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን እያደራጀ ነዉ። የቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜን ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ለማድረግ ጊዚያዊ ቀጠሮ መያዙንም ነው ይፋ የተደረገው የጊዜ ሰሌዳ የሚያለክተው።

    የምርጫ ቦርዱ ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳን ሕጋዊ እና ትክክለኛ በማለት ስምምነታቸውን የገለጹ የመኖራቸውን ያህል ምርጫዉ በከባዱ የክረምት ወቅት ይደረጋል መባሉ፣ በመንገድ መሠረተ ልማት እና የወንዞች ሙላት ምርጫው ያለ ችግር ስለመከናወኑ ጥርጣሬ የገባቸው እንዳሉም ታይቷል።

    የምርጫ ቦርድ በበኩሉ የመጨረሻ በሚለው የምርጫ ማስፈጸሚያ የጊዜ ሰሌዳ ለማውጣት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። ቀደም ሲል ለመነሻነት ይፋ ያደረገው የጊዜ ሰሌዳ ላይ አስተያየት እያሰባሰበበት ስለመሆኑም ነው የቦርዱ ቃል አቀባይ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስ ለዶይቸ ቬለ የተናገሩት።

    በኢትዮጵያ በየአምስት ዓመቱ ሀገራዊ ምርጫ መካሔድ እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል። በዚሁ በሥራ ላይ ያለው ሕገ- መንግሥት ሥራ ላይ ከዋለ ለስድስተኛ ጊዜ ሊካሄድ በጊዜያዊነት የተያዘለት ቀነ-ቀጠሮ ውዝግብ ማስነሳቱ ከሕግ አንጻር እንዴት ይታይ ይሆን?

    በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ እንደሚሉት የምርጫ ቦርዱ በሕግ የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ ከአሠራሩ ጋር በሚያመቸው መልኩ የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀት ይችላል በማለት ይናገራሉ። ቦርዱ ሕግን የሚተላለፍ ተግባር እስካልፈጸመ ድረስ በየትኛውም የአየር ጠባይ ውስጥ ቀጠሮውን የመያዝ ስልጣን ቢኖረውም ሁሉን ሊያስማማ ወደ ሚችል የውይይት መድረክ ቢያመራ የተሻለ ውጤት ሊገኝበት እንደሚችል እምነታቸው መሆኑን ያስረዳሉ።

    ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በጊዜያዊነት ይፋ ያደረገው የየምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ተግባራዊ መደረግ ባልጀመረበት አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እያደረጉ መሆናቸው ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ተገቢውን ቁጥጥር አላደረገም የሚል ወቀሳ እና ትችት ሲሰነዘር ይሰማል።

    የምርጫ ቦርድ ቃል አቃባይ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስ እንደሚሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተሰጣቸው ሕጋዊ የመንቀሳቀሻ መንገድ ወጥተው በሚገኙት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በቅድሚያ ተፈጸሙ የተባሉ የሕግ ጥሰቶች መመርመር አለበት ይላሉ።

    የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተዘጋጀላቸው የሕግ ማዕቀፍ ወጥተው ሲገኙ ይህንኑ ለማስተዳደር በወጣው ሕግ ሊዳኙ እንደሚገባ የሚያሳስቡት ደግሞ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ ናቸው። ከሰሞኑ ጀምሮ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጌቸው ጊዜያቸውን ያልጠበቁ የምርጫ ቅስቀሳዎች ወይም የቅስቀሳ ይዘት ያላቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎች ሕጋዊ መንገድን ሊከተሉ እንደሚገባም ነው የሚያሳስቡት።

    የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የ2012 ምርጫ ቀነ-ቀጠሮን ቁርጥ ባያደርግም የአዳዲስ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችን ግን መመዝገቡን ቀጥሏል። ቦርዱ ጥር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቀው ለአራት ፓርቲዎች የእውቅና ምስክር ወረቀትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ሰጥቷል። የእውቅና ምስክር ወረቀትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ የተሰጣቸው አራቱ ፓርቲዎች ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ ናቸው።

    ምንጭ፦ ዶይቸ ቬለ አማርኛ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ምርጫ የሚደረግበት የመጨረሻ ጊዜ

    #14035
    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የምርጫ 2012 ኦፕሬሽን እቅድ እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ የፈጠረውን ችግር ገምግሞ ያሳለፈው ውሳኔ መግለጫ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2012 ዓ.ም የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ ለማስፈፀም የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ሥራዎች ሲያከናውን ከቆየ በኋላ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ይፋ አድርጓል።

    በዚህ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫው ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲካሄድ ተወስኖ ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው የተገለጹ ተግባራትን በተያዘላቸው ጊዜ እያከናወነ ለሕዝብ እያሳወቀ እንደቆየ ይታወሳል። በዚህም መሠረት በያዝነው መጋቢት እና በሚመጣው ሚያዝያ ወራት 2012 ዓ.ም. መጠናቀቅ ያለባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ። መከናወን ካለባቸው ሥራዎች ዋና ዋናዎቹ የመራጮች ምዝገባ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ፤ ስልጠናና ስምሪት፤ የመራጮች ትምህርት፤ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ስርጭት የመሳሰሉት ናቸው።

    እነዚህን ሥራዎች በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ለማከናወን ቦርዱ ተገቢ ጥረት እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ባለፉት ሳምንታት በሃገራችን እና በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ አስገድዷል። ከዚሁ የወረርሽኝ ሥጋት የተነሳ በርካታ ሃገራት ምርጫን ጨምሮ መንግሥታዊ ዕቅዶቻቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል። በሃገራችንም መንግሥት ወረርሺኙን ለመከላከል የሰዎች ግንኙነትን የመቀነስ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በመወሰኑ የመንግሥት ሠራተኞች አብዛኛውን ሥራ ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ተደርጓል፡መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ ጥብቅ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በክልል መንግሥት መስተዳድሮች ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የውስጥና የአገር አቋራጭ የትራንስፓርት ገደቦች፣ የመሰብሰብ ገደቦችን የመሳሰሉ ጥብቅ ክልከላዎች ይፋ ሆነዋል።

    በመንግሥት ከተላለፉ የክልከላ ውሳኔዎች በተጨማሪ ለቦርዱ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለምአቀፍ አጋር ድርጅቶች አብዛኞቹ ሠራተኞቻቸው ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ሲደረጉ አንዳንዶቹ ደግሞ ጥቂቶቹን ብቻ በማስቀረት ሠራተኞቻቸው ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል። ከላይ የተጠቀሱት ድምር ሁኔታዎች በሚያዚያ ሊጀመር በታቀደው የመራጮች ምዝገባ እና ተያያዥ የዝግጅት ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል። ከዚህ የሚከተሉት ከችግሩ ማሳያ ከሚሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው።

    • በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጋዘን የሚገኙ የምርጫ ቁሳቁሶችን የማሸግ ሥራ በሁለት ሳምንት ዘግይቷል፤
    • የቀሪ ህትመት ውጤቶች ግዥ በቫይረሱ ምክንያት በተፈጠረ የአቅርቦት ሰንሰለት መደናቀፍ ምክንያት ተጓቷል፤
    • ለምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና ቁጥራቸው 1000 /አንድ ሺ/ በላይ የሚሆን አሰልጣኞችን ክክልሎች ወደ አዲስ አበባ በማምጣት የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት አልተቻለም፤
    • ለ150,000 (አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ) የምርጫ አስፈፃሚዎች በየክልሎቹ መሰጠት ያለበትን ስልጠና መጀመር አልተቻለም፤
    • ቦርዱ የሚሰጠው የመራጮች ትምህርት ኮቪድ-19 ቫይረስን አስመልክቶ በሚወጡ የማኅበረሰብ ጤና መልእዕቶች ሊዋጡ የሚችሉበት ዕድል ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

    የቫይረሱ ስጋት በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በአጠቃላይ በተለይም በአፋጣኝ መፈጸም ባለባቸው የመራጮች ምዝገባ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና፤ የመራጮች ትምህርት ተግባራት አፈፃፀም ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ አስመልክቶ ቦርዱ ከሕግ አውጪው አካል፤ በጉዳዩ ላይ ከሚሠሩ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የማኅበረሰብ ጤና ባለሞያዎች፣ ከዓለምአቀፍ አጋሮች እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጋር ተመካክሯል።

    ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት አብዛኞቹ ፓርቲዎች የችግሩን ግዝፈት እና በምርጫ ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ተገንዝበው ቦርዱ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተመካክሮ አማራጭ የአፈጻጸም ዕቅድ ሊኖረው እነደሚገባ መክረዋል። ይሁን እና በዚህ አግባብ የሚወሰደው እርምጃ ችግሩ ከሚጠይቀው በላይ የሆነ መዘናጋት እንዳያመጣ ቦርዱ በወረርሽኙ አፈጻጸማቸው የማይስተጓጎል ሥራዎችን እንዲያጠናቅቅ አሳስበዋል።

    ቦርዱ ለውሳኔው መሠረት የሚሆነው የዳሰሳ ጥናት በአማካሪ ባለሙያዎቹ ተሠርቶ እንዲቀርብለትም አድርጓል ። የተፈጠረው አጠቃላይ ሁኔታ ከታቀደው የምርጫ ምዝገባና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ባግባቡ ለመዳሰስ ያስችለው ዘንድ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ተመሥርቶ ቦርዱ ሁለት የቢሆን ሁኔታ ግምቶች (scenarios) ተመልክቷል።

    የመጀመሪያው የቢሆን ሁኔታ ግምት መሠረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት በኢትዮጵያ መንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለአራት ሳምንት ብቻ ማለትም እስከ ሚያዚያ 7 ሊቆይ ይችላል በሚል ግምት ላይ የተመሠረተ ነው። ክልከላው የአራት ሳምንት ብቻ የሚቆይ ከሆነ አሁን ባለው የጊዜ ሰሌዳ ዋና የሆነውን የመራጮች ምዝገባ ቢያንስ በአራት ሳምንት የሚገፋው ሲሆን ምዝገባው ቢከናወን የማኅበረሰቡ ተሳትፎ፣ የምርጫው ተአማኒነት ማግኘትን እና የኦፕሬሽን ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት ድጋፍን ሙሉ ለሙሉ ማግኘትን በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ያሳያል።

    ቫይረሱ በቁጥጥር ስር ካልዋለም የመራጮች ምዝገባን ማካሄድ የማኅበረሰብ ደኅንነትን አደጋ ውስጥ የሚጥል ከመሆኑም በተጨማሪ ከማኅበረሰብ የጤና ደኅንነት ከመጠበቅ አንጻር ጥቂት እንኳን ክልከላዎች የሚኖሩ ከሆነ ይህንን ዕቅድ ወደ ተግባር መለወጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

    በተጨማሪም በያዝነው ሳምንት መንግሥት ተጨማሪ እርምጃ እየወሰደ መቀጠሉ፣ እንዲሁም ቦርዱ ከጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ባደረገው ውይይት እስከ ሚያዚያ መጨረሻም ሁኔታው የመሻሻል ዕድል እንደሌለ የተገለጸለት በመሆኑ፣ በዚህ የቢሆን ሁኔታ ግምት በታየው መልኩ የመራጮች ምዝገባን በተያዘለት ጊዜ ማከናወን እንደማይቻል ቦርዱ መረዳት ችሏል።

    የዳሰሳ ጥናቱ ሁለተኛ የቢሆን ሁኔታ ግምት የሚያሳየው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ከሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ፤ በመሆኑም በመንግሥት የሚደረግ ማንኛውም ከአራት ሳምንት የበለጠ ክልከላ ቢኖር ምርጫውን በተያዘለት ሕገ-መንግሥታዊ የጊዜ ሰሌዳ ማከናወን እንዳይቻል ያደርገዋል፤ ስለዚህም ወረርሽኙን መቆጣጠር በሚቻል ጊዜ ቦርዱ ዕቅዶቹ ላይ የተለያዩ ማሻሻያ ሊደርግ ይገባል የሚል ነው።

    በመሆኑም ቦርዱ እነዚህን የቢሆን ሁኔታ ግምቶች መርምሮ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ካደረጋቸው ምክከሮች ያገኘውን ግብአት ታሳቢ በማድረግ የሚከተለውን ወስኗል።

    1. በተፈጠረው ሁኔታ የተነሳ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫውን ማካሄድ የማይቻለው መሆኑን በመረዳት ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ በሰሌዳው መሠረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ ወስኗል፤
    2. ቦርዱ የወረርሽኙ ሥጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደገና ግምገማ በማድረግ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን ዕቅድና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቀሴውን የሚያስጀምር ይሆናል፤
    3. ቦርዱ ባደረጋቸው ምክክሮችና የዳሰሳ ጥናት ላይ በግልጽ የተለዩ፣ በኮቪድ-19 የማይስተጓጎሉ፣ የቦርዱን የምርጫ አፈጻጸም ዝግጁነት የሚጨምሩ፣ ሁኔታው ተቀይሮ ተቋሙ ወደ መደበኛ ተግባሩ ሲመለስ በተገቢው ሁኔታ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያሥችል ሁኔታን የሚፈጥሩ ተግባራትን እያከናወነ መቆየት እንዳለበት ወስኗል።
    4. በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት በሥራ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ አጠቃላይ ምርጫውን ማድረግ የማይችል መሆኑን ምክር ቤቱ ተገንዝቦ፣ ከዚህ አንጻር የሚሰጠው ውሳኔ ቢኖር ለመነሻነት ያገለግለው ዘንድ ይህ ውሳኔ እንዲሁም ቦርዱ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ሰነድ ለሕዝብ ተወካዮች እንዲተላለፍለት ወስኗል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

    #14357
    Anonymous
    Inactive

    “የጃዋርና የልደቱ ትልቁ ችግር ሕዝብን በኪሳቸው እንደያዙት ሳንቲም ሲፈልጉ ሊያስቀምጡት፣ ሲፈልጉ ደግሞ አውጥተው ሊጠቀሙበት፣ ደፍነው ለጅምላ ግዢ፣ ዘርዝረው ለችርቻሮ ሊያውሉት የሚችሉት አድርገው መቁጠራቸው ነው።”

    ሕዝብ እኮ ስልጣን የራበው ሁሉ እየነቀለ የሚጥደው የቦና ጎመን አይደለም (በድሉ ዋቅጅራ)

    የጃዋርን እና የልደቱን ውይይት አየሁት፤ ሰማሁት። ላየው የቀሰቀሰኝ ዋና ነጥብ አንድ ላይ ያመጣቸውን ጉዳይ የማወቅ ጉጉት ነበር። አገኘሁት። ያቀረቡበት መንገድ ነው ልዩነቱ፤ የጃዋር በፖለቲከኛ (ብስለትና መሰሪነት)፣ የልደቱ በወታደር (ጉልበትና ማስፈራራት) ከመቅረቡ በስተቀር፤ ‹መስከረም 30 የመንግሥት ሕጋዊ ተቀባይነት ስለሚያበቃ፣ መንግሥት እኛ የምንለውን የማይቀበል ከሆነ ሕዝቡ ከእኛ ጋር ቆሞ መንግሥት እንዲቃወም፣ እንዲታገል› ነው።

    በጎው ነገራቸው ―
    “መንግሥት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሁኔታው ላይ መወያየትና መስማማት አለበት” የሚለው ነው። በእርግጥ መንግሥት ይህን ማድረግ አለበት፤ ይህ ሕዝብ በኮሮና ድቀቱ ላይ፣ በፖለቲካ ምክንያት የሚፈጠር ነውጥን የሚሸከም ትከሻ አይደለም፤ የሚሰማ ጆሮ የለውም።

    የጃዋርና የልደቱ ትልቁ ችግር ሕዝብን በኪሳቸው እንደያዙት ሳንቲም ሲፈልጉ ሊያስቀምጡት፣ ሲፈልጉ ደግሞ አውጥተው ሊጠቀሙበት፣ ደፍነው ለጅምላ ግዢ፣ ዘርዝረው ለችርቻሮ ሊያውሉት የሚችሉት አድርገው መቁጠራቸው ነው። ሕዝቡን እውን ቢያውቁት የትላንቱን ውይይታቸውን ይዘውለት ለመቅረብ ባልደፈሩ ነበር። በተለይ አዚህ ላይ የልደቱ ድፍረት ለከት አልነበረውም። ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት ስብሰባ እንኳን ለመምራት፣ መብት እንደሌለው ሲናገር፣ ስለራሱ ሀገር የሚያወራ ፈጽሞ አይመስልም፤ በወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ ስለተራዘመበት መንግሥት ሳይሆን፣ ሀገር ለቅቄ እወጣለሁ ያለበትን ቀን ስላላከበረ ቅኝ ገዢ የሚያወራ ነው የሚመስለው። የሚገርመው ከወራት በፊት ልደቱ “ተቃዋሚ ፖርቲዎችን 10 ሺህ ፊርማ እንዲያሰባስቡ መጠየቅ፣ ፓርቲዎችን ማዳከምና እንዳይመሠረቱ ማድረግ ነው…” ባለበት አፉ ዛሬ 100 ሚሊየን ሕዝብ ከጎኑ እንደሆነ በሙሉ ልብ ሲናገር መስማት ጤንነቱን ያጠራጥራል፤ .. ሕዝብ እኮ ስልጣን የራበው ሁሉ እየነቀለ የሚጥደው የቦና ጎመን አይደለም።

    ውይይታቸውን ልብ ላለ የልደቱና የጃዋር ልዩነት (ምንም እንኳን ጃዋር የፓርቲያቸውን የመፍትሄ ሀሳብ ግልጽ ባያወጣውም) ለችግሩ የሚያቀርቡት የመፍትሄ ሀሳብ ላይ ነው። በግሌ የጃዋር ፓርቲ የሽግግር መንግሥትን እንደመፍትሄ የሚያቀርብ አይመስለኝም። ዶ/ር መረራ እና ጃዋር እራሱ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪዎች በመሆናቸው እውቀታቸውን ተጠቅመው የተሻለ ሀሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ።

    የልደቱ “የሽግግር መንግሥት” ሀሳብ ግን እንዳለው ቀድሞም በቀዳማዊ ኢህአዴግ መውደቅ ፍትጊያ (2009/10 ዓ.ም.) የነበረ፣ ዛሬም ከኮረና ጋር ያለ ነው። ልደቱ ከፍተኛ የስልጣን ፍላጎት ያለው ይመስለኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የ97ቱ ምርጫ ሕዝባዊ ቅቡልነቱን እንዳወረደውና የሚፈልገውን የስልጣን እርካብ እንደማያስረግጠው ያውቃል። በመሆኑም ፓርቲዎች በመዋጮ የሚያቋቁሙት የሽግግር መንግሥት ነው ብቸኛ የማርያም መንገዱ። ይኸው ነው።

    በርካታ ሀገሮች በኮሮና የተነሳ ምርጫ አራዝመዋል፤ የትኛው ሀገር ነው የሽግግር መንግሥት የመሠረተው? የሽግግር መንግሥት የተወሰነ ጊዜ ተሰፍሮለት የሚመሠረት ነው። አሁን ያጋጠመው ችግር ወረርሽኝ ነው፤ 6 ወር ወይም ዓመት ሊወስድ ይችላል፤ አናውቅም።

    ለሁለቱም ―
    ፖለቲከኛ መሆን ካሻችሁ ሕዝቡን እወቁት፤ አክብሩት። አክብሮታችሁ ቀርባችሁ ከማወቃችሁ ይሁን። ሕዝብን የማያከብር ፖለቲከኛ ሕዝብን ሊመራ አይችልም። ሕዝብን አክብሩ። ሕዝብ ጉልበት ስትፈልጉ የምትገዙበት የሚስጢር ኪሳችሁ ሳንቲም፤ ስልጣን ሲርባችሁ እየነቀላችሁ የምትጥዱት የጓሮአችሁ ጎመን አድርጋችሁ አትኩጠሩት።

    በድሉ ዋቅጅራ

    የጃዋርና የልደቱ

    #14365
    Anonymous
    Inactive

    ከሚያዝያ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ተሰብስቦ የነበረው የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ባለ አምስት ነጥብ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

    ከህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

    የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በክልላችንና በሀገራችን እንዲሁም በንዑስ ቀጣናው የተከሰቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በስፋት በመመርመር የውሳኔ ሃሳቦችን አሳልፏል። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በክልላችን እየተከናወኑ ያሉ የሰላምና የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የክልላችንና የሕዝባችን ድኅንነት የመታደግ ሥራዎችን እንዲሁም የኮረናን ወረርሽኝ ለመመከት የተሠሩ ሥራዎች በሚመለከት በዝርዝር የተወያየበት ሲሆን፣ እስካሁን የታዩ ጥንካሬዎችን ጠብቆ ለማቆየትና የታዩ ጉድለቶችን ለማረም የተሠሩ ሥራዎችን በመመርመር ውሳኔዎችን አሳልፏል። በክልላችን ያሉ ወይም የሚኖሩ ፈተናዎች ለመመከት አሁንም ወሳኙ ውስጣዊ ጥንካሬያችን መሆኑን በድጋሚ በማረጋገጥ በዚህ ረገድ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል።

    የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በሦስት ቀን ስብሰባው በስፋት ከመከረባቸው ጉዳዮች ዋነኛው በሀገር ደረጃ በብልፅግና ፓርቲ እየተካሄደ መጥቶ አሁን በመጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰውን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የመናድ ዘመቻ የሚመለከተው አጀንዳ የጎላ ትኩረት የተሰጠው ነበር። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዝርዝር ተወያይቶ እንዳስቀመጠው የብልፅግና ፓርቲ ቀድሞውኑም ለማከናወን ሙሉ ፈቃደኝነት ያላሳየበትን ሀገራዊ ምርጫ የCOVID-19 ወረርሽኝ መከሰትን እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር በአንድ ሰው የሚመራ አምባገነን ሥርዓትን ለመትከልና ከሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ውጪ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ባለፉት ጥቂት ቀናት በግልፅ እንደታየው የፓርቲዎችን ሃሳብ ለመቀበል በሚል በተጠራ የይስሙላ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለቀለት ያሉትን ሃሳብ ማጠናቀቂያ ክፍል ምን ሊመስል እንደሚችል በግልፅ አመላክተዋል።

    የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይህ ያለበቂ ዝግጅትም ሆነ ያለግልፅ አጀንዳ የተጠራውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕግ ውጭ በሥልጣን ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩበት መድረክ ተከትሎ በፓርላማው የተጀመረውና ሕግን ያላግባብ በመተርጎም የብልፅግና ፓርቲን ሕገ-ወጥ የስልጣን ዕድሜ የማራዘም እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው በድጋሚ አስምሮበታል። አሁንም ሥልጣን ላይ ባለው ኣካል የተጀመረውና ሕገ-መንግሥትን መተርጎም በሚል ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የመናድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደተደረሰ ግልፅ ሆኗል።

    በዚህም መሠረት የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተሉተን ውሳኔዎች አሳልፏል።

    1. የብልፅግና ፓርቲ ሕገ-መንግሥቱን ለመተርጐም በሚል ሰበብ የተጀመረው ገሀድ የወጣ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆም። ሕገ-መንግሥታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልገው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ባስቀመጠው ግልፅ መስፈርት መሠረት አሻሚ ሁኖ ለተገኙ አንቀፆች እንጂ የአንድን ስብስብ የሥልጣን ዕድሜ ከሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ውጭ ለማራዘም ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ይህንን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ጥድፍያ በአስቸኳይ ቆሞ አሁንም የኮረና ወረርሽኝን በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልም ሆነ ሀገራዊ ምርጫን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው ማእቀፍ ውሰጥ በመሆን ለማከናወን በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሁሉም ፓርቲዎች በሙሉ የባለቤትነት መንፈስ እንዲሳተፉ ተደርጎ ሀገርን ከለየለት የጥፋት አደጋ ለመታደግ እንዲቻል መድረክ እንዲመቻች ይጠይቃል።
    2. የእንደዚህ ዓይነቱ መድረክ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የብልፅግና ፓርቲ ነፃና ግልፅ ምርጫ የመምራት ምንም ዓይነት ሞራላዊ ብቃት የሌለው በመሆኑ ይህንን ለማስፈፀም የሚችል የተለየ አደረጃጀት የመፍጠር አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ላይ ተደርሶ የሀገርን ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስከበር አስፈላጊነት በቂ ትኩረት በሰጠ መልኩ ምርጫውን ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እንዲጀመር ጥሪውን ያቀርባል።
    3. ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወትሮውኑም ገዢውን ፓርቲ በሕገ-ወጥ መንገድ አፍርሶ ራሱን በወራሽነት ያስቀመጠው የብልፅግና ፓርቲ ከመስከረም 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለው ጠባብም ቢሆን ዕድል የማይኖር በመሆኑ የሀገሪቱ ችግር ለመፍታት ወደሚከብድ ችግር የምትገባበት ዕድል መፈጠሩ የማይቀር ይሆናል። ህወሓት እንደዚሁ ዓይነቱ ክስተት ሊፈጥረው የሚችለውን ትርምስ ለማስወገድ በሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶች ውስጥ ድርሻውን በቀናነት ለመጫወት ዝግጁ ቢሆንም የትግራይ ሕዝብ በመስዋዕትነቱ በተከለው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የተረጋገጠለትን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደዋዛ እንዲጣልበት አይፈቅድም። ለዚህም ሲባል ከትግራይ ሕዝብና ለትግራይ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሙሉ ዕውቅና ከሚሰጡ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመሆን ክልላዊ ምርጫን ጨምሮ ይህንኑ የሕዝባችንን መብት ከትርምስ ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በክልል ደረጃ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ ወስኗል። ይህ እንቅስቃሴ የፀረ ኮረና ወረርሽኝ ዘመቻችንን እንዲሁም ተቀባይነት ያላቸውን ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎችን ባሟላ መልኩ የሚፈፀም ይሆናል።
    4. የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ህልውናቸው ያረጋገጠውን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በጠራራ ፀሀይ ለማፍረስ የሚደረገውን እኩይ ተግባር በማስቆም ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳቸውን እንዲያርቁ በዚህ አጋጣሚ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ጥሪውን ያቀርባል።
    5. በመጨረሻም ህወሓት ሆነ የትግራይ ሕዝብ የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓታችን ያረጋገጠውን ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለማዳን በሚደረገው ርብርብ መሰል አጀንዳ ከሚያራምዱ ብሔር ብሔረሰቦችም ሆነ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ለመታገል ዝግጁ መሆናችንን አሁንም በድጋሚ ማረጋገጥ እንፈልጋለን።

    የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ ጽ/ቤት
    ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም.

    ምርጫ በኢትዮጵያ ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ― ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች

    የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተሉተን ውሳኔዎች

    #14394
    Anonymous
    Inactive

    የምንሰጠው ሕጋዊና ፖለቲካዊ አማራጭ ከወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ የሚታደገን፣ ሀገረ-መንግሥቱን የሚያስቀጥልና ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ሽግግር የሚያግዝ ሊሆን ይገባል! ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባድ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ይታወቃል። ወረርሽኙ በሰዎች ጤና እና ደኅንነት ላይ ካደረሰው እና እያደረሰ ካለው ጉዳት ባልተናነሰ የዓለምን እና የሀገራትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች እና ሥርዓትን ከባድ አደጋ ውስጥ ከቷል። ወረርሽኙ በሀገራችን ኢትዮጵያ እስከካሁን ያስከተለው ጉዳት ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር አስከፊ የሚባል ባይሆንም የደቀነው አደጋ ግን ከፍተኛ መሆኑ እርግጥ ነው። በሌሎች ሀገር ከታየው ተሞክሮ አንፃር ወረርሽኙ ድንገት በከፍተኛ ቁጥር ዜጎችን ሊያጠቃ እና የጤና ሥርዓት ቀውስ ውስጥ ሊከተን የሚችልበት አደጋ አሁንም አለ። የጎረቤት ሀገሮች (ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት መዛመት የጀመረበትና በተለይ ከጅቡቲ ጋር ካለን የቀረበ የኢኮኖሚ ትስስር አንፃር በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ላይ የደቀነው ስጋት ከፍተኛ እንደሆነ ግልጽ ነው።

    ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፉት ጫና ከአሁኑ እየታየ ነው። ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርሰው ጫናም በወጪ እና ገቢ ንግድ ዘርፍ ላይ ጫና እያሳደረ ሲሆን ይህም በቶሎ ወደቀድሞ ሁኔታው የሚመለስ አይሆንም። የበረሀ አንበጣ በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ላይ እንደዚሁም የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም በኮሮና ምክንያት ከፍተኛ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና እስከ ሰኔ ድረስ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዋስትና የማጣት ስጋት/አደጋ እንዳንዣበበባቸው በቅርቡ ተገልጿል። በአጠቃላይ ቫይረሱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው መጠነ ሰፊ መቀዛቀዝና የአገራዊ ጥቅል አመታዊ ምርትና እድገት ማሽቆልቆል ሀገራችን ላይ የከፋ ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ ነው።

    በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የወረርሽኙ ተጽዕኖ ከኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጫና በተጨማሪ በፖለቲካው ዘርፍም በታሪካችን አጋጥሞን የማያውቅ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል።

    ከወረርሽኙ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የነበሩ የውስጥ ፖለቲካዊ ችግሮች እና በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባን ካለነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያየዘ ከሌሎች ሀገሮች የተደቀነብን አደጋ በፍፁም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይም ከግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ተጽዕኖ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊደረግ ታስቦ የነበረውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም አስታውቋል። ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለመቻሉ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ከተጠናቀቀ በኋላ ሀገርን ማን ያስተዳድራል የሚል ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ አስነስቷል። በዚህም ምክንያት የተለያዩ አካላት ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ነው የሚሉትን ሀሳብ እያቀረቡ ይገኛሉ።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዚህ ጉዳይ ላይ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በተለይም ከሕገ-መንግሥት ጠበቆች (constitutional lawyers) ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። ባለሙያዎቹ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ክፍተት በሕገ-መንግሥታዊ አግባብ እንዴት ሊፈታ ይችላል የሚለውን የወቅቱ ትልቅ ጥያቄ ጊዜ ሰጥተው እንዲመክሩበት የከፍተኛ የባለሙያዎች ጉባዔ (high level panel of experts) በማቋቋም ለአንድ ወር ያህል ጉዳዩን ሲያስጠናና ምክክር ሲያስደርግበት ቆይቷል። ኢዜማ ከገባንበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለመውጣት ልንከተለው የሚገባው የመፍትሔ ሀሳብ የሚከተሉትን ታሳቢዎች ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበት በጽኑ ያምናል፤

    1. አገራችን ከምትገኝበት የሕግም የፖለቲካ አጣብቂኝ በአጭር ጊዜ ለመውጣት የሚረዳ መሆን እንዳለበት፣
    2. ተቋማዊ አሠራሮችን ከማጎልበት አንፃር የተሻለ ዕድል የሚፈጥር መሆን እንዳለበት፣
    3. አጠቃላይ ችግሩ በአጭር ጊዜ ፈቶ አገራችን ወደተረጋጋ የምርጫ ሂደት ለመግባት የሚያስችል መሆን እንዳለበት፣
    4. ከወጪም ከጊዜም አንፃር አገሪቱን ብዙ ዋጋ የማያስከፍል የተሻለው አማራጭ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትና በፍጥነት የተቀያየሩት የአገራችንንና የቀጠናውን ጂኦ-ፖለቲካዊና የደኅንነት ስጋቶች በሚገባ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት።

    ኢዜማ ከላይ የገለፅናቸውን ሀገራዊ ፈተናዎች ለማለፍ ሕዝብን አስተባብሮ ሊመራ የሚችል ጠንካራ መንግሥት እንደሚያስፈልገን ያምናል። ለዚህም እንደፓርቲ ልንከተለው የሚገባን የመፍትሄ ሀሳብ ይህንን የሚያረጋግጥ መሆን እንደሚገባው በፅኑ ይረዳል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የፓርቲያችንን የሕግ ባለሙያዎች ጨምሮ በሌሎች አካላትም የቀረቡትን የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

    1. ከሕግ አማራጭ ውጪ የፖለቲካ መፍትሄ በሚል በተለያዩ አካላት የቀረበ የመፍትሄ ሀሳብ

    በዋናነት በዚህ ረገድ የቀረበው ሀሳብ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ዘመን ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የሚያበቃ በመሆኑ እና ሕገ-መንግሥቱም ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት መንግሥት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ሁኔታ ክፍተት ስለማይሰጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ንግግር ላይ የተመሠረተ የሽግግር መንግሥት ሀገሪቱን ሊመራ ይገባል የሚል ነው። ይህ መፍትሄ ሀሳብ አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነት እና የቁጥር ብዛት ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል ነው። ከዚህም በላይ እንደ ሀገር ያሉብንን ከላይ የጠቀስናቸውን ፈተናዎች ተጋፍጦ ለማለፍ የሚያስፈልገንን ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር የሚፈጥር አይደለም። ይህም የገባንበትን ችግር ከመፍታት ይልቅ ወደባሰ ሀገራዊ ቀውስ ሊከተን የሚችል አማራጭ ያደርገዋል።

    1. በሕገ-መንግሥቱ ማዕቀፍ ሥር ያሉ አማራጮች

    2.1. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 60/1 እና 3 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6 ወር ውስጥ ምርጫ ማድረግ፦ ይሄ አማራጭ በ6 ወር ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ እና ሕግ ማውጣት የሚያስፈልጋቸው ድንገተኛ የሀገር እና ሕዝብን ደኅንነት እና ጥቅም አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ሁኔታዎች ከግምት የማያስገባ፣ የፌደራል መንግሥትን እንጂ ሥልጣናቸው አብሮ የሚጠናቀቀውን የክልል ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ችግር ያላገናዘበ አማራጭ በመሆኑ የምንፈልገውን ጠንካራ መንግሥት የሚፈጥር አማራጭ ሆኖ አላገኘነውም።

    2.2. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እና ምርጫውን ማራዘም፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የተቀመጠ አንቀጽ አይደለም። አስቸኳይ ግዜ ማዋጅም በቀጥታ የመንግሥትን ሥልጣን ማራዘምን አያስከትልም። እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ስር የሚደረግ ምርጫን ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግ አይቻልም።

    2.3. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 83 እና 84 መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ከፌደሬሽን ምክር ቤት መጠየቅ፦ በዚህ አማራጭ መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ሥራ የሚሠራው የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሙሉ ነፃነት እና ያለማንም ጣልቃ ገብነት የተመራለትን ጉዳይ በመመርመር የውሳኔ ሀሳብ አቅርቦ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ ያ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። አሁን ካለንበት አጣብቂኝ ክብደት አንጻር ጉዳዩን መዳረሻ ውጤቱ አስቀድሞ በእርግጠኝነት ለማይታወቅ እና ምናልባትም መልሶ እዚህ ከተጠቀሱት አማራጮች መካከል አንደኛውን እንድንከተል ሊያደርግ ለሚችል ሂደት መስጠት ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም።

    2.4. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 104 እና 105/2 መሠረት የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ፦ ይህ አማራጭ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ የማስፈጸሚያ ሥነ ሥርዓት ያለው እና አሁን ለገባንበት አጣብቂኝ የማያዳግም ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል።

    ምንም እንኳን ኢዜማ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸው በርካታ አንቀጾች እንዳሉ በፅኑ ቢያምንም፥ አሁን ያለንበት ወቅት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አይደለም። አሁን ለገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝም ቀልጣፋ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም። በኢዜማ እምነት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ሀገራዊ መረጋጋት፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እና ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። እንዲሁም በከፍተኛ በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባው ሀገራዊ ጉዳይ በዚህ ወቅት ሊከወን አይገባም ብለን እናምናለን። ሆኖም አሁን የገጠመንን አጣብቂኝ ለመሻገር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58ን ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ ለማድረግ የማያስችል ድንገተኛ እና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ1 ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ምርጫውን ማራዘም እና ምርጫው እስኪደረግ ድረስ ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመከወን በከለከለ መልኩ የመንግሥትን ቀጣይነት በግልፅ የሚደነግግ አድርጎ በማሻሻል ቀጥተኛ፣ ሕገ-መንግሥታዊ፣ የማያዳግም እና ተቀባይነት ያለው መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።

    በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 105/2 ሀ እና ለ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ በ2/3ኛ ድምፅ ማሻሻያውን ሲያጸድቁ እንዲሁም ከክልል ምክር ቤቶች ውስጥ 2/3ኛ ክልሎች (6 ክልሎች) በአብላጫ ድምፅ ሲያጸድቁት በሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ 3 ስር ከሚገኙት እና አንቀጽ 104 እና 105 ውጪ ያሉትን የሕገ-መንግሥት አንቀጾች ማሻሻል እንደሚቻል ተደንግጓል። በዚሁ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58/3 ከላይ በተገለጸው መሠረት ማሻሻል የተሻለ መፍትሄ እንደሆነ እናምናለን።

    ይህ መፍትሄ ተግባራዊ ከተደረገ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግሥት ተከትሎ የሚፈፀም በመሆኑ ሕገ ምንግሥታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ አይሆንም። እንዲሁም በቅርቡ ልናደርገው ከምናስበው ምርጫ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንፃርም አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን። በዚህ አማራጭ ላይ በተለያዩ አካላት የሚነሳው ጥያቄ በዚህ የወረርሽኝ ወቅት በአንቀጽ 104 ድንጋጌ መሠረት ህዝብን ለማወያየት አያስችልም የሚል ሲሆን ይህንን ክፍተት ግን ሕዝቡን በወኪሎቹ አማካኝነትና በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በማወያየት መሸፈን ይቻላል።

    ከዚህ ቀደም በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የጋራ የታክስ እና የግብር ሥልጣንን የሚደነግገው አንቀጽ 98 እና የሕዝብ ቆጠራን በሚመለክት የሚካሄድበት የጊዜ ገደብን የሚደነግገው አንቀጽ 103/5 በሕገ-መንግሥቱ የተጠቀሰውን የማሻሻያ ሥነ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሳይከተሉ ለየብቻ በተለያየ ጊዜ ማሻሻያ ተደርጎባቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ አሁን መደረግ ያለበት ማሻሻያ ግን የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105/2 ያስቀመጡትን ድንጋጌዎች በሙሉ አሟልቶ ሊሆን እንደሚገባው እናምናለን።

    ይህ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ የክልል ምክር ቤቶችንና የፌድሬሽን ምክር ቤትንም የሥልጣን ዘመን በሚያራዝም መልኩ መተግበር አለበት።

    የፓርቲያችን እምነት የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 58/3 ማሻሻል የተሻለ አማራጭ ነው የሚል ቢሆንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ በተራ ቁጥር 2.3 ላይ የጠቀስነውን አማራጭ በመውሰድ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጥ 54/1፤ 58/3 እና 93 ላይ ትርጉም እንዲሰጥ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንደመራው ታውቋል። ምንም እንኳን ኢዜማ ይህንን አማራጭ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ባያምንም አማራጩ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ሕገ-መንግሥቱን በሚተረጉምበት ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ተግባሩን ማከናወን አለበት። የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚያጸድቀው ትርጉም የመንግሥትን ሥልጣን በማንኛውም መልኩ የሚያራዘም ከሆነ ማራዘሚያውን እጅግ ቢገፋ ከ1 ዓመት እንዳይበልጥ ማድረግ አለበት። ውሳኔው በዚህ የማራዘሚያ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመፈፀም እንዲቆጠብ የሚያስገድድ መሆንም አለበት።

    በአጠቃላይ እንደሀገር የሚወሰዱ ማንኛውም አማራጮች አሁን ያለንበትን አስቸጋሪ እና ፈታኝ ወቅት ከግምት ያስገቡ፣ የሀገር መረጋጋት፣ ሰለም እና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያስቀጥሉ እንዲሁም አሁን ከገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስወጡን መሆን እንዳለባቸው ኢዜማ ለማሳሰብ ይወዳል። በተጨማሪም በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የተለያየ አመለካከት ካላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ውይይት መዳበራቸው መፍጠር የምንፈልገውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድንለማመድ በር የሚከፍት እና ሁሉንም ኃይሎች የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በቂ እና ቀጣይነት ያለው ውይይት የምናደርግበት መድረክ እንዲመቻች ጥሪ እናቀርባለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም
    አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    #14398
    Anonymous
    Inactive

    ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ
    ስልጣንን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም የሚደረግ ሙከራ በአስቸኳይ ይቁም!

    ሀገራችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሆና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ግን የስልጣን ዘመኑን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም የሚያስችለውን ጥረት ለሕዝብ ይፋ ባልሆነ መንገድ እያደረገ ስለመሆኑ መረጃዎች እየደረሱን ነው። ገዥው ፓርቲ በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት ከተሰጠው ስልጣንና መብት ውጭ በሦስት አማራጮች ስልጣኑን ለማራዘም እየሞከረ እንደሚገኝ ታውቋል።
    እነዚህ አማራጮችም፤-

    1. በዓመቱ መጨረሻ ላይ የአገሪቱ ፓርላማ እንዲበተን ማድረግና በ6ወር ጊዜ ውስጥ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ፤
    2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደገና በማራዘም የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም መሞከር፤
    3. የአገሪቱን ሕገ-መንግሥት በማሻሻል የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለተወሰነ ጊዜ ማራዘም የሚሉ ናቸው።

    ከእነዚህ አማራጮች ውስጥ በየትኛው መንገድ የመንግሥትን ስልጣን ለማራዘም እንደሚቻልም ገዥው ፓርቲ ከራሱ መዋቅሮችና በዙሪያው ከሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች ጋር እየመከረ እንደሆነ ታውቋል።

    አብሮነት ከዚህ ቀደም ደጋግሞ ለመግለፅ እንደሞከረው ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ የሚገኘውን መንግሥት ዕድሜ ለማራዘም የሚያስችል ምንም ዓይነት ድንጋጌ በሀገራችን ሕገ-መንግሥት ውስጥ የለም። በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 58/3 እና አንቀፅ 72/3 መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ብቻ ስለመሆኑ በግልፅ ተቀምጧል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወይም ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥም የመንግሥትን ዕድሜ እንዴት ማራዘም እንደሚቻል ሕገ-መንግሥቱ ምንም ዓይነት ድንጋጌ አላስቀመጠም። ስለሆነም ብልፅግና ፓርቲ እንዲህ ዓይነት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑትን የሕገ-መንግሥቱን አርቃቂዎች እና ለሕገ-መንግሥቱ ክፍተት መታየት ምክንያት የሆነውን ኮሮና ቫይረስን “ከመርገም” ውጭ በሕጋዊ መንገድ የስልጣን ዘመኑን ለአንድም ቀን የሚያራዝምበት ምንም ዓይነት መብትና ስልጣን በሕገ-መንግሥቱ አልተሰጠውም።

    በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 60 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲያካሂዱ ስልጣን የተሰጣቸውም በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን አምስት ዓመት የመንግሥት የስልጣን ዘመን ለመጨረስ ነው እንጂ ከአምስት ዓመት በላይ የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም አይደለም። እንዲያውም በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 60/1 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ድጋሜ ምርጫ መካሄድ የሚችለው በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ብቻ ነው። ስለዚህ ይህ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ በሕግ የተሰጠን የሥራ ዘመን ለማጠናቀቅ ከመቻል ጋር እንጂ የሥራ ዘመንን ከማራዘምና የመንግሥት የሥራ ዘመን ካለቀ በኋላ ከሚካሄድ ምርጫ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም።

    በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 93/1፣ ሀ እና ለ ላይ በግልፅ እንደተደነገገውም የመንግሥትን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ተብሎ ሊታወጅ የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የለም። አሻሚና አከራካሪ ባልሆነ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምን ዓይነት ጉዳዮች ሊታወጅ እንደሚችል ሕገ-መንግሥቱ በዝርዝርና በግልፅ ስላስቀመጠ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማዎጅ ስልጣኑን ለአንድም ቀን ለማራዘም የሚያስችለው ሕጋዊ መብትና ስልጣን የለውም።

    እንደ ሦስተኛ አማራጭ እየታየ ያለው ሕገ-መንግሥቱን አሻሽሎ የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም መሞከርም ሕጋዊነትን የተከተለ አሠራር አይደለም። አንድ በስልጣን ላይ የሚገኝ መንግሥት የራሱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ሲል በሥራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግሥት የሚያሻሽል ከሆነ፣ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንደ አንዳንድ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች በዓለም ፊት መሳቂያ እና መሳለቂያ የሚያደርግ የአምባገነኖች ድርጊት እንጂ ሕጋዊ አሠራር ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ የስልጣን ዘመንን ለማራዘም ሲባል ሕገ-መንግሥትን ለማሻሻል የመሞከር እርምጃም ከሕግ መኖርና አስፈላጊነት መሠረታዊ መርህ ጋር የሚጋጭ ሕገ-ወጥ ተግባር ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ሂደትም ማንኛውም የፖለቲካ ኃይል የሕዝብ ቅቡልነት ሊያገኝ አይችልም። እንዲህ ዓይነቱን ከባድ ሀገራዊ ጉዳይ አሳታፊና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመወሰን መሞከርም ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ሁለንተናዊ የህልውና ፈተና ውስጥ እንደምትገኝ አለመረዳት ነው። ይህም እንደተለመደው የገዥውን ፓርቲ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የራሱን ስልጣን የማስቀደም ኃላፊነት የጎደለው ፍልጎት የሚያሳይ ነው።

    ስለዚህ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሕገ-መንግሥቱ አርቃቂዎች በሠሩት ስህተት እና በኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባት ምክንያት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የመንግሥት የሥራ ዘመንን አስመልክቶ ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ (constitutional crisis) መፈጠሩን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ በአንድ አገር ሲፈጠር ደግሞ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው በመደበኛ የሕግ አሠራር ሳይሆን ከመደበኛ የሕግ አሠራር ውጭ (extra-constitutional) በሆነ መንገድ ነው። እንዲህ ዓይነቱን መፍትሄ ለመስጠትም በተለየ ሁኔታ በሕግ መብት የተሰጠው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም መንግሥታዊ ተቋም ስለሌለ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ እንዴት እንፍታው? በሚለው ጥያቄ ተነጋግሮ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የምክከር ሂደት (national dialogue) መጥራት ያስፈልጋል። ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ በሀገራችን በሕጋዊም ይሁን በይስሙላ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት ስለማይኖር የወደፊቱን የአገሪቱን ዕጣ-ፈንታ በመወሰን ረገድ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ከማንኛችንም በአገሪቱ ከምንገኝ ፓርቲዎች የተለየ መብትና ስልጣን ስለሌለው በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ውሳኔ ብቻውን መወሰን አይችልም። ገዥው ፓርቲ ይህንን ማድረግ ከሞከረ በሀገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ እና ትርምስ ሊፈጠር እንደሚችል ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።

    ስለሆነም፦

    1ኛ. በአሁኑ ወቅት ዋናውና ቀዳሚው ትኩረታችን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠር መሆን ስላለበት ቢያንስ እስከ ነሃሴ መጨረሻ 2012 ዓ.ም. ድረስ ብልፅግና ፓርቲ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ በተመለከተ ምንም ዓይነት አጀንዳ ይዞ እንዳይነጋገርም ሆነ የተናጠል ውሳኔ እንዳያስተላልፍ፤

    2ኛ. የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በዘንድሮው ዓመት በተናጠል ምርጫ ለማካሄድ ማሰቡ ሕገ-መንግሥታዊ ውሳኔ አይደለም። በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ ብቸኛ መብት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መሆኑን በመገንዘብ የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ ህወሓት ከዚህ ዓይነቱ ሕገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፤

    3ኛ. ብልፅግና ፓርቲ ይህንን አጀንዳ በሚመለከት በድብቅ የሚፈፅማቸውን ተግባራት ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በንቃት እንዲከታተሉ፣ ገዥው ፓርቲ ይህንን አጀንዳ በተመለከተ ሕገ-ወጥ እርምጃ መውሰዱን የሚቀጥልበት ከሆነም ተቃዋሚ ፓርቲዎች አመቺ የመገናኛ መንገድ ፈጥረው በአስቸኳይ መመካከር እንዲችሉና በጉዳዩ ላይ የራሳቸውን አቋም እንዲይዙ፣ ከዚህ በኋላም በሀገራችን ጉዳይ አንዳችን ጋባዥ ሌላችን ተጋባዥ የምንሆንበት ምክንያት እንደሌለ ተገንዝበን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር የምናደርገው ማንኛውም ግንኙነትና ድርድር በእኩልነት መንፈስ ብቻ እንዲሆን የሚያስችል አቋም እንድንይዝ፤

    4ኛ. የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 29 ዓመታት በአፈናና በይስሙላ ምርጫ በስልጣን ላይ የኖረው ገዥው ፓርቲ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ ሊቀጥል የሚችልበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መብት የሌለው መሆኑን ተገንዝቦ በሕገ-ወጥ መንገድ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረገውን ጥረት አጥብቆ እንዲቃወም፣ መቃወምም ብቻ ሳይሆን የገዥውን ፓርቲ ሕገ-ወጥ እርምጃ በጠንካራ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ለማስቆም እንዲዘጋጅ አብሮነት ጥሪውን ያቀርባል።

    አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት)
    ሚያዚያ 21 2012 ዓ.ም
    አዲስ አበባ

    አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት

    #14411
    Anonymous
    Inactive

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ

    ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
    ለድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣
    ለመላው ኢትዮጵያውያን!

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 26 እና 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የሀገራችንን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ አውዶችን በጥልቀት በመገምገም፤ የአማራ ሕዝብን ወቅታዊ አቋምና ዘላቂ ጥቅሞችን፤ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ኃይሎች ፍላጎቶችን እና የቀረቡ አማራጮችን በፅሞና በመመርመር፤ በዚህም መሠረት፦

    • ለሰላማዊና ጠንካራ ሀገራትና መንግሥታት እንኳን የሚያዳግቱ ግዙፍና አሳሳቢ ብሔራዊ ተግዳሮቶች የተደቀኑብን መሆኑን በማመን፤
    • የዴሞክራሲያዊ ውድድር፣ የልሂቃን ውይይትና ድርድር ባህል ባልዳበረበት በጥልቅ በተከፋፈለ ብሔራዊ ማኅበረሰብ ውስጥ እንደምንገኝ በመገንዘብ፤
    • የኢትዮጵያ ቀጣይ ሁኔታ በምርጫ ወይም በይስሙላ ማሻሻያዎች ብቻ እንደማይወሰን፣ የአሸናፊዎችና የጉልበተኞች ጫናም ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣ በማመን፤
    • ከምንም ከማንም በላይ የአማራን ሕዝብ ሰላም፣ ደኅንነትና ዘላቂ ጥቅሞች መከበርና የሀገራችንን ህልውና ቀጣይነት በማስቀደም፤

    አብን እነዚህንና ሌሎችንም ተጓዳኝ ታሳቢዎችን በማድረግ ሀገራችን ከገባችበት አጣብቂኝ በአስተማማኝ ልትወጣ የምትችልባቸውን መንገዶች በተመለከተ የሚከተሉትን አቋሞች ወስዷል።

    1ኛ. የሽግግር ጊዜ (transitional period) አስፈላጊነት
    ንቅናቄያችን አብን ሌሎች በሀገራችን የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችና ተቋማት ላቀረቧቸው አማራጭ ሃሳቦች ክብር ያለው ቢሆንም አሁን ለገባንበት ፖለቲካዊ ቀውስ አዲስ የሽግግር መንግሥት (transitional government) መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት የለውም።

    ከዚህ ይልቅ የተወሰነ የሽግግር ጊዜ መፍጠር የተሻለ አማራጭ መሆኑን እንገነዘባለን። ምክንያቱም የሕዝባችንና የሀገራችን ዕጣፈንታ በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲቆም ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ነባራዊ ውጥረቶችና ክፍተቶች እንዲረግቡና የጥሞናና ውይይት መንፈስ እንዲሰፍን ያስችላል። የሽግግር ጊዜ ያላሰለሰ ሕዝባዊ ውይይት፣ ልሂቃዊ ምክክርና ድርድር እንዲደረግና ሊያሠራ የሚችል ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ዕድል ይሰጣል።

    2ኛ. የመንግሥት-መር (state-led) ሽግግር አስፈላጊነት
    አብን ከገባንበት ብሔራዊ አጣብቂኝ ለመውጣት የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት፣ የሕግን የበላይነት በማስከበር ረገድ ኃላፊነቱን በብቃት የሚወጣ አካል መኖር እንዳለበት ያምናል። አዲስ የሽግግር መንግሥት መፍጠር በሀገራችን ወቅታዊ የፖለቲካና የኃይል አሰላለፍ አውድ ሊሳካ እንደማይችል ይገነዘባል።

    ስለዚህም ምንም እንኳን ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ የታየው መንግሥት መሩ የለውጥ ሂደት የከሸፈና የማያሰራ እንደነበር ብንረዳም፣ ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መቆየትና የሽግግር ሂደቱን መምራት ለሕዝባችንና ሀገራችን ሰላምና ደህንነት ካሉት አማራጮች በአንፃራዊነት የተሻለው ነው ብለን እናምናለን።

    3ኛ. የመዋቅራዊና ሁሉን አካታች ሽግግር ሂደት አስፈላጊነት
    አብን የአማራ ሕዝብና የሌሎች ወንድም ህዝቦች መሠረታዊ ጥያቄዎች ሥርዓታዊና መዋቅራዊ በመሆናቸው በዋነኝነት የሚፈቱት በልሂቃን መካከል በሚደረግ ውይይትና ድርድር ከሚመነጭ ፖለቲካዊ መፍትሄ መሆኑን ያምናል።

    ብሔራዊ ፖለቲካችን ከጥሬ የስልጣን ትግል ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲሻገር ከታሰበ ከአጭር ፖለቲካዊ ትርፍ ይልቅ ዘላቂ የሀገርና የሕዝብ ጥቅምን ያማከለና አዲስ ቅርፅና አቅጣጫ ያለው ሰፊና የማያቋርጥ የድርድርና እርቅ ሂደት ያስፈልጋል። በተለይም የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥት ማሻሻል፣ አጠቃላይ መዋቅራዊና ተቋማዊ ለውጦችን ማድረግ ያሻል። ከሁሉም በላይ በአሳሳቢ ሁኔታ እየወደቀ የመጣውን ምጣኔ ሀብታችንን እንዲያንሰራራ ማድረግ የግድ ነው። ለዚህም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማኅበራትንና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላትን ያካተተና ለሕዝብ ተወካዮች ተጠሪ የሆነ የብሔራዊ ውይይት ኮሚሽን እንዲቋቋም ድርጅታችን አብን ይጠይቃል።

    4ኛ. መሠረታዊ የሕዝባችንን ጥያቄዎች በተመለከተ

      • ሀ. የኮቪድ-19 ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ በመሠረታዊ የሕዝቦች ጥያቄዎች ላይ ቅርፅ ያለውና ተቋማዊ የሆነ ብሔራዊ ውይይት (national dialogue) እንዲጀመር ለማድረግ ዋስትና እንዲሰጥ ንቅናቄያችን አበክሮ ይጠይቃል።
      • ለ. የሕዝብና ቤት ቆጠራን በተመለከተ፣ ንቅናቄያችን የ1999 ዓ.ም. ብሔራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሳይንሳዊ ያልሆነና ሸፍጥ የተሞላብት የሕዝባችንን ቁጥር በእጅጉ የቀነሰ በዚህም ፖለቲካዊ ውክልናውን እና ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነቱን ያሳጣ በመሆኑ ውጤቱ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ፤ ለተከሰቱት ጉዳቶች ፍትኃዊ ማካካሻ (restorative justice) እንዲደረግና ቀጣዩም ቆጠራ ሳይንሳዊና ገለልተኛ በሆነ ተቋም እንዲካሄድ ይጠይቃል።
      • ሐ. የሕገ መንግሥት ማሻሻያን በተመለከተ፤ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ሕዝባችንን የማይወክልና በሂደትም ቅቡልነትን ያላተረፈ፣ በአማራ ጠል ትርክት ላይ የተመሠረተ፣ ለሀገር አንድነትና ህልውና የማይበጅ፣ እንደዚህ ያለ ፈታኝ ወቅት ሲያጋጥም እንኳን በአግባቡ ሊያሻግር የማይችል በመሆኑ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት የሕገ-መንግሥት ለውጥ ወይም ማሻሻያ እንዲደረግ ይጠይቃል።
      • መ. የሀገራችንንና ሕዝባችንን የሰላምና ደኅንነት ዋስትና በተመለከተ፤ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሕግና ሥርዓት በማስከበር ረገድ ያሳየው ድክመት ተገቢ አለመሆኑንና በፍፁም መቀጠል እንደሌለበት በማመን፤ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር ከመንግሥት ግንባር ቀደም ኃላፊነቶች መካከል መሆኑን በመገንዘብ፤ ሀገራችን ባለችበት የስጋት ሁኔታ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የተለየ ዝግጁነት እንዲደረግ አበክሮ ይጠይቃል።

    አብን በሕዝባችን ትግል የተሸነፉ ቋሚ የአማራ ሕዝብና የኢትዮጵያ ጠላቶችና ግብረ አበሮቻቸው ሀገራችንን ለማተራመስና እንደገና የጭቆና መንበራቸውን ለመመለስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጥብቆ እንደሚታገለው በአፅንኦት ያረጋግጣል።

    ንቅናቄያችን ከላይ የገለፃቸውን አቋሞች በተመለከተ ከመንግሥትና ከተለያዩ የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ንግግሮችንና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን እያሳወቀ የተከበረው የአማራ ሕዝብ፣ የድርጅታችን አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በአሁኑ ወቅት የተደቀነብንን ብሔራዊ አደጋ በማጤን ላቀረብናቸው አማራጭ ኃሳቦች ስኬት ከጎናችን እንድትሰለፉ በአክብሮት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    አንድ አማራ ለሁሉም አማራ! ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ የሥራ ኮሚቴ
    አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
    ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም.

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    #14418
    Anonymous
    Inactive

    ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫን በተመለከተ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የሰጠው ወቅታዊ የአቋም መግለጫ
    የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት (Caretaker Government of Technocrats) ይቋቋም!

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት የምትሸጋገረውና መጪው ምርጫ ብሩህ ተስፋ የያዘ የሚሆነው አሳታፊ፣ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ጉባዔ በማድረግ ብቻ ነው። ጉባዔው በአንድ በኩል ሀገራችን ያንዣበበባትን የኮሮና ወረርሽኝን እንዴት ልታልፍ እንደምትችል ምክክር እንዲደረግ የሚያስችል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ቀጣዩ ምርጫ መቼ ይሁን? በምን ቅርጽ ይካሄድ? እስከ ምርጫው ድረስ ሀገራችንን ማንና እንዴት ይምራት? ለሚሉት አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ የሚገኝበት መድረክም ነው። ይህን ዓይነቱን ጉባዔ ፍሬያማ ለማድረግ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ዋና ዋና የፖለቲካና የሲቪክ ባለድርሻዎች እንዲሳተፉበት ማድረግ የግድ ይላል።

    ይሁን እንጂ፣ ገዢው ፓርቲ እንደዚህ ዓይነቱ ሀገራዊ ጉባዔ እንዲደረግ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ፥ በሀገራችን ውስጥ ተፅዕኖ ያላቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች በማግለል የተወሰኑ የፖለቲካ ድርጀቶችን ብቻ መርጦ ስብሰባ አድርጓል። በዚህ ሂደት ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን ጨምሮ፣ ሌሎች ለገዢው ፓርቲ ብርቱ ተፎካካሪ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳይሳተፉ አድርጎ፣ ቅንነትና ታማኝነት የጎደለው፣ ጠቃሚ ሃሳቦች በተሟላ መልኩ ያልተንሸራሸሩበት፣ ለሃቀኛ ሽግግር ያልቆረጠ ስብሰባ እንዲሆን አድርጎታል።

    በዚህም ሳቢያ በሀገራችን መጻኢ ዕድል ላይ ጥቁር ዳመና እንዲያንዣብብ እየሆነ ነው። ኢትዮጵያን ወደ ሚቀጥለው የተሻለ ደረጃ ከማስፈንጠር አንፃር ማንም ልጅ፣ ማንም የእንጀራ ልጅ ስላልሆነ፣ የማግለል አካሄድ ለሀገራችን ስለማይበጅ በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል።

    በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የመንግሥት የሥራ ዘመን 5 ዓመት ብቻ እንደሆነና፣ የስልጣን ዘመኑ ከማለቁ ከወራት በፊት [ብሔራዊ] ምርጫ መደረግ እንዳለበት የደነገገ ቢሆንም፥ በበሽታ፣ በጦርነት፣ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በሌላ እክል ምርጫውን ማካሄድ ሳይቻል ቢቀር ምን መደረግ እንዳለበት ምንም መፍትሄ አላስቀመጠም። ይህም አሁን ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫን በተመለከተ ትልቅ ሀገራዊ ተግዳሮት ፈጥሯል።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ በሚያዝያ 24 እና 25 ቀን 2012 ዓ·ም. ባደረገው አስቸኳይ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ፣ የምርጫውን መራዘም አስመልክቶ ገዢው ፓርቲ አግላይ በሆነው ስብሰባ ያቀረባቸውን 4 አማራጮች በጥልቀት ከሕግና ከፖለቲካ አግባብነት አንፃር እያየ መርምሯል።

    ኮሚቴው በገዢው ፓርቲ የቀረቡት አማራጮች ሀገሪቷን ከተጋረጡባት ተግዳሮቶች የማይታደጓት ብቻ ሳይሆኑ፣ በከፊል ሕጋዊ መሠረትም የሌላቸው መሆኑንም ተገንዝቧል። ስለሆነም፣ አማራጭ ሀገራዊ መፍትሄ ለማስቀመጥ ውይይትና ክርክር ከማድረጉ በፊት አራት መስፈርቶች እንደ ቅድመ-ሁኔታ አስቀምጧል። እነዚህም፡-

    1. የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት፣ ሠላምና ደኅንነት የሚያስቀጥል መሆን እንዳለበት፣
    2. መፍትሔው ሀገራዊ ተግዳሮቱን እንደ ክፍተት በመጠቀም የማንንም የስልጣን ጥም እውን ለማድረግና ለማስፈፀም መዋል እንደሌለበት፣
    3. ለዴሞክራሲያዊ ሽግግርና ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት መሆን እንደሌለበት፣
    4. የባልደራስን ጨምሮ ከማንኛቸውንም የፖለቲካ ድርጅት ፍላጎትና አመለካከት የፀዳ መሆን እንዳለበት፣
    5. ለመሰል ሀገራዊ ተግዳሮት ዓለም-አቀፍ ተሞክሮ ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት የሚሉት ናቸው።

    እነዚህን መስፈርቶች መመዘኛ አድርጎም፣ በገዢው ፓርቲ በኩል የቀረቡት «አማራጮች»ም ሆኑ በተቃራኒው ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚሹ ኃይሎች የተሰባሰቡበት ያቀረቡት «የሽግግር መንግሥት እንመሥርት» ጥያቄ ለሀገሪቱ እንደማይበጁ ጥርት አድርጎ ማየት ችሏል።

    በአንጻሩ በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካና በአፍሪካ ያሉትን መሰል ተሞክሮዎች ግምት ውስጥ ሲገቡ፣ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለኢትዮጵያ የሚበጃት «የባለሙያዎች የባለአደራ መንግሥት» ወይም በእንግሊዘኛ አጠራሩ “Caretaker Government of Technocrats” ነው ብሎ በፅኑ አምኗል።

    ይህ የባለሙያዎች የባለአደራ መንግሥት ከየዘርፉ በሚመለመሉ ምሁራንና ባለሙያዎች የሚቋቋም ሲሆን፣ አዋጪነቱም ተፈትኖ የታየ ብቻ ሳይሆን፣ ገዢው ፓርቲም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲዋች ሀገራዊ ተግዳሮቱን በመጠቀም ለስልጣን ሽሚያ እንዳይጋበዙና ሀገር እንዳትጎዳ ዋስትና ይሰጣል።

    የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት፡-

    1ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት በሕይወት ዘመናቸው የፖለቲካ ድርጅት አባላት ባልነበሩ ምሁራንና ባለሙያዎች የሚቋቋም ይሆናል፣
    2ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላትና ሹመኞች በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ገደብ የሚጣልባቸው ይሆናል፣
    3ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላትና ሹመኞች ከምርጫ በኃላ በሚቋቋመው መንግሥት የፖለቲካ ሹመት እንዳይሰጣቸው የአንድ የምርጫ ዘመን ገደብ የሚጣልባቸው ይሆናል፣
    4ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላት በፖለቲካ፣ በሲቪክ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ታዛቢነት የሚመረጡ ይሆናል፣
    5ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላት ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ካሉ ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል ይመረጣሉ፣

    የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት ኃላፊነት፡-

    1. የሀገር ሉዓላዊነትን መጠበቅ፣
    2. የሀገር ጸጥታን ለማስጠበቅ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር፣
    3. ለነጻ ምርጫ የሚያስፈልጉ ነጻ የመንግሥት ተቋማትን መገንባት፣
    4. የመንግሥትን የዕለት ተዕለት ሥራ መምራት፣
    5. ከምርጫው በፊት፣ ለሀገራዊ እርቅና መግባባት ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የሰላም ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣
    6. ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ ቃል ኪዳን (citizen’s covenant) እንዲገቡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣
    7. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት የሥራ ዘመን ከሁለት ዓመት ያልበለጠ ይሆናል።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ
    ሚያዚያ 26ቀን 2012 ዓ·ም.
    አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ!

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ

    #14452
    Anonymous
    Inactive

    “ሕግ አክባሪው የትግራይ ሕዝብ፣ የህወሓትን ውሳኔ አይቀበለውም” ― አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – ህወሓት የዘንድሮውን ምርጫ በክልል ደረጃ አካሂዳለሁ ብሎ ያወጣው መግለጫ ሕገ መንግሥቱን የሚጣረስ በመሆኑ ሕግ አክባሪው የትግራይ ሕዝብ በምንም መልኩ የማይቀበለው መሆኑን የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል አስታወቁ።

    የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፥ ምርጫ የማካሄድ ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሆኖ ሳለ ህወሓት በክልል ደረጃ ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚጥስ ከመሆኑም ባለፈ ሕግ አክባሪው የትግራይን ሕዝብ የማይመጥ ነው። ሕዝቡ ይህንን ሕገ መንግሥቱን የሚንድ ተግባር አይቀበልም።

    «የህወሓት መግለጫው ከሕገ መንግሥት ያፈነገጠ ብቻ ሳይሆን የምርጫ ቦርድ ኃላፊነትን የዘነጋና አልፎ ተርፎም እውቅና መስጠት ያልፈለገ መግለጫ ነው» ያሉት አቶ ነብዩ፥ ይህም ሕገ መንግሥትና አገርን መናድ በመሆኑ በወንጀል ሕጉ የሚያስጠይቅ መሆኑንን አስገንዝበዋል።

    የትግራይን ሕዝብ አስተዳድራለሁ የሚለው ህወሓት እያደረገ ያለው ተግባር ይህንን ጨዋ ሕዝብ ደረጃ የማይመጥንና የሥልጣንን ጥማትን ለማርካትና ወንበርን ለመጠበቅ ብቻ የሚሄድበት መንገድ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

    በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ ሥርዓት አለ ለማለት በጣም አስቸጋሪ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፥ በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ በሚል ዝግ የሆኑ የካድሬዎች ስብሰባ እየተካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህም ደግሞ በክልልም ሆነ በአገር ደረጃ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚጥስ መሆኑን አመልክተዋል። “ይህም የሚያሳየው ራሳቸው ላወጁት አዋጅ እንኳን ተገዢ አለመሆናቸውን ነው” ብለዋል።

    በሌላ በኩል እንደ አገር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ እያለ፤ በቫይረሱ የተየዙ ሰዎችን ውጤት እንደ አገር መረጃ እየተላለፈ ባለበት ሁኔታ የክልሉ ጤና ቢሮ በተናጠል መረጃ ማውጣቱ የህወሓትን አመራሮች ምን ያህል ለሕዝብም ሆነ ለአገር ደኅንነት የማያስቡ መሆናቸውን እንደሚያመላክት አስረድተዋል። “የትግራይ ሕዝብ እንዲህ ዓይነት የመንግሥት አገልግሎት አይመጥነውም፤ አይገባውምም” ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች መንገዶች የህወሓትን ተግባር እየኮነነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

    መንግሥትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ጊዜው ከማራዘም ባለፈ የሕዝብና የአገር ግዛት አንድነትን እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት አስታውሰው፤ ሕገ መንግሥቱን ለመናድና በአቋራጭ ወደ ሥልጣን ለመምጣት ብሎም አገር የሚበጠብጡ አካላትን ሕግን መሠረት በማድረግ እርምት የሚወሰድባቸው መሆኑን አስታውቀዋል። “የአገርና የሕዝብን ደኅንነትን በማስቀደም ሕጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ ይወስዳል” ብለዋል።

    ምንጭ፦ አዲስ ዘመን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል Nebiyu Sihul Mikael

    #14537
    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 27 ፓርቲዎችን ሰረዘ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በቀድሞ ሕግ የምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት) የነበራቸው እና በቀድሞው ሕግ ምዝገባ ጀምረው ለነበሩ 106 ፓርቲዎች በአዲሱ ሕግ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ በደብዳቤ ማሳወቁ ይታወሳል። ከቦርዱ ደብዳቤ ከደረሳቸው 106 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 76 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰነዶችን ያቀረቡ ሲሆን በሕጉ መሠረት ተሟልቶ የቀረበ ስለመሆኑ እየተመረመረ ይገኛል።

    ምርመራውም፦

    • ፓርቲዎቹ በደብዳቤ የተገለጸላቸውን ነጥቦች ሁሉንም ማሟላታቸውን ማረጋገጥ (የሕገ–ደንብ ለውጥ ጠቅላላ ጉባዔ ሰነዶች አቀራረብ፣ የመስራቶች ፊርማ… የመሳሰሉት)፣
    • የፖለቲካፓርቲዎችበሕጉመሠረትማሟላትየሚገባቸውንየመሥራችአባላትብዛትትክክለኛነትንለመፈተሽካቀረቡትየመሥራችአባላትዝርዝርናሙናየማውጣት፣
    • ናሙናዎቹበትክክልግለሰቦቹየተፈረሙመሆናቸውንወደተፈረሙበትቦታበመላክማረጋገጥ፣
    • የሕገ–ደንብለውጦችና፣የጠቅላላጉባዔሰነዶችበትክክልመያያዛቸውንማረጋገጥንያጠቃልላል።

    ይህ እንደተጠናቀቀም ሰነዶቻቸው ካስገቡት 76 ፓርቲዎች መካከል ምን ያህሎቹ መስፈርት እንዳሟሉ በቦርዱ ይፋ የሚደረግ ይሆናል። ነገር ግን የሚጠበቅባቸውን ሰነድ ማስገባት ያልቻሉ እና ጊዜ እንዲራዘምላቸው የጠየቁ 15 የፓለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ ከነዚህ ፓርቲዎች መካከል ከስር የተጠቀሱት የ13ቱ አጥጋቢ ምክንያት ባለማቅረባቸው እንዲሰረዙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወስኗል።

    የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ሳያገኙ የተሰረዙ ፓርቲዎች ዝርዝር የሚከተለው ነው፦

    1. የኢትዮጵያውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) – የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባዔ ያላካሄደ
    2. የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ) – የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
    3. የየም ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (የብዴን) – የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባዔ ያላካሄደ
    4. የደንጣ ዱባሞ ክችንችላ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት – የመሥራች አባላት ዝርዝርም ያላቀረበ፣ ጉባዔ ያላካሄደ
    5. የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ (ኮንግረስ) – የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
    6. የትግሪ ወርጂ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ትወብዴድ) – ጠቅላላ ጉባዔ ያላካሄደ
    7. የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) – የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባዔ ያላካሄደ
    8. የኢትዮጵያን አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢአዴድ) – ጠቅላላ ጉባዔ ያላካሄደ
    9. የመላው አማራ ሕዝብ ፓርቲ (መዐሕፓ) – የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
    10. የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) – የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
    11. የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ (ደቡብ ኮንግረስ) – የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
    12. የሸኮና አካባቢው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሸአሕዲድ) –ጠቅላላ ጉባዔ ያላካሄደ
    13. ነጻነትና ሰላም ለኢትዮጵያ ሕብረት ፓርቲ ( ነጻነትናሰላም) – የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

    በሌላ በኩል ሌሎች 14 ፓርቲዎች ደግሞ ከቦርዱ በተደረገው ጥሪ መሠረት ሰነዶቻቸውን ከነአካቴው ያላቀረቡ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መዋሃዳቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም የእነዚህ 14 ፓርቲዎች እንዲሰረዙ ቦርዱ ወስኗል። በመሆኑም ሰነድ ባለማምጣታቸው እንዲሰረዙ የተሰወኑት ፓርቲዎች የሚከተሉት ናቸው።

    1. የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ
    2. መላው ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
    3. የከምባታ ሕዝቦች ኮንግረስ
    4. የሐድያ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
    5. የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት
    6. የዲል ወቢ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ
    7. የቤንች ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት
    8. የስልጤ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
    9. የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ
    10. የሱማሌ አንድነት ፓርቲ
    11. ነፃነት ለአንድነትና ለፍትሕ ፓርቲ
    12. ብሔራዊ ተሀድሶ ለሰላም ልማት
    13. የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሕብረት
    14. የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ

    ሁለት ፓርቲዎች ሰነዶችን ማቅረብ አለመቻላቸው በፓርቲው የውስጥ ችግር የተነሳ መሆኑ ስለታመነበት ጠቅላላ ጉባዔያቸውን የኮቪድ ወረርሽን (COVID-19) በሚያበቃበት ወቅት አንዲያከናውኑ ቦርዱ ሲወስን ሌሎች ሰነዶቻቸው ግን ከላይ በተጠቀሰው መንገድ እየተገመገሙ ይገኛል። በልዩ ሁኔታ የሰነድ ካስገቡ ፓርቲዎች ጋር ሰነዶች እንዲታይላቸው የተደረጉ ፓርቲዎች፦

    1. ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)
    2. ወለኔ ሕዝቦች ፓርቲ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (NEBE)

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

    #14542
    Anonymous
    Inactive

    ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ

    አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት) ከግንቦት ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገራችን የተከሰተው “የለውጥ ሂደት” መሠረታዊ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት በሚያስችል አግባብ ያልተካሄደና የከሸፈ መሆኑን በመገንዘብ ሀገሪቱን ወደ አንድ አዲስና ጤናማ የሽግግር ሂደት የሚያስገባ አማራጭ ሃሳብ በረቂቅ ደረጃ አዘጋጅቶ ለሕዝብ ውይይት ማቅረቡ ይታወቃል።

    ከኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባት ጋር በተያያዘ በረቂቅ ሰነዱ ላይ በአሰብነው መጠን ሕዝባዊ ውይይቶችን ማካሄድ ባንችልም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ቀላል የማይባል የሕብረተሰብ ክፍል በረቂቅ ሰነዱ ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት ማድረግ ተችሏል። በአብሮነት አባል ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ መዋቅሮች በረቂቁ ላይ በስፋት እንዲወያዩበት የተደረገ ሲሆን፥ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ከተገኙ ግብአቶች በተጨማሪ ከ700 በላይ የሆኑ አስተያየቶች በኢሜል (email) አማካኝነት መሰብሰብ ተችሏል። የተለያዩ ምሁራንና የፖለቲካ መሪዎችም ሰነዱ እንዲደርሳቸውና ሃሳብ እንዲሰጡበት ማድረግ ተችሏል።

    እነዚህን ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተገኙ አስተያየቶች ባገናዘበ ሁኔታ የአብሮነት አባል የሆኑት ሦስቱ ፓርቲዎች በረቂቅ ሰነዱ ላይ ሰፊ ውይይትና ክርክር ካካሄዱበት በኋላ ገንቢ የሆኑ ማሻሻያዎችን በረቂቅ ሰነዱ ላይ በማድረግ ይህንን የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚጠይቅ ሰነድ የጋራ ሰነዳቸው እንዲሆን ተቀብለውታል። በይዘት ደረጃ ማሻሻያ የተደረገባቸው ጉዳዮችም ሁለት ናቸው።

    አንደኛ- ሀገር አቀፍ የሕዝብና የቤት ቆጠራ ጉዳይ አወዛጋቢ የፖለቲካ አጀንዳ እየሆነ በመምጣቱ የሽግግር መንግሥቱ አንዱ ኃላፊነት የሕዝብና ቤት ቆጠራ ማካሄድ እንዲሆን፤ ሁለተኛ- የሽግግር መንግሥቱ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ረቂቅ የማቅረብ ብቻ ሳይሆን በሕዝበ-ውሳኔ ሕገ-መንግሥት የማሻሻል ኃላፊነት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው። እነዚህንና ሌሎች መለስተኛ ማሻሻያዎችን በማድረግ ሰነዱ ከዛሬ ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሦስቱ አባል ድርጅቶችና የአብሮነት ኦፊሴላዊ ሰነድ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን፥ የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎችና ሕዝቡ ጥያቄውን እስከሚቀበሉት ድረስ ሰነዱ አንድ ቁልፍ የፖለቲካ የመታገያ አጀንዳችን ሆኖ እንዲቀጥል ተወስኗል።

    አብሮነት በወቅታዊው የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የረጅም ጊዜ ግምገማ አካሂዶ የደረሰበት አቋም “ሀገራችን ኢትዮጵያ ከእንግዲህ መዋቅራዊ ችግሮቿን በአስተማማኝ ሁኔታ ሊፈታ በሚችል ውጤታማ የሽግግር ሂደት ውስጥ ማለፍ እስካልቻለች ድረስ እንደተለመደው በየአምስት ዓመቱ የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ ወደ መዋቅራዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ልትሸጋገር አትችልም” የሚል ነው።

    በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ የሚገኘውና ከሁለት ዓመት በፊት ስልጣን ለመያዝ የበቃው ብልፅግና ፓርቲ በሀገሪቱ ውጤታማ ሽግግር ለማካሄድና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም ቃሉን ጠብቆ የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ መዋቅራዊ ዲሞክራሲ ማሸጋገር አልቻለም። ፓርቲው ለሕዝብ የገባውን ቃል ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል እውቀትና ልምድ ብቻ ሳይሆን ቅንነትና ፍላጎት የሌለው ኃይል በመሆኑ ምክንያት ሀገሪቱን ወደ በጎ አቅጣጫ ከመምራት ይልቅ የራሱን የፖለቲካ ስልጣን በማጠናከር ወደ ለየለት አምባገነናዊ ኃይልነት መቀየርን የመረጠ ይመስላል።

    ይህ ኃይል እራሱንም ሆነ ሀገሪቱን ወደ ከፍተኛና ውስብስብ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ከማስገባቱ በፊት፥ በሀገሪቱ የምንገኝ የፖለቲካ ኃይሎችና የሀገሪቱ ዋና ባለቤት የሆነው ሕዝብ ተባብረን በሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገባ ካላስገደድነው በስተቀር በአጭር ጊዜ ውስጥ በታሪካችን አይተነው ወደማናውቅ አምባገነናዊ ኃይል እራሱን ሊቀይርና ሀገሪቱንም ከባድ እና ውስብስብ ወደ ሆነ አደጋ ሊያስገባት ይችላል።

    አብሮነት ሀገራችንን ከእንዲህ ዓይነት አስፈሪ ጥፋት መታደግ የሚቻለው በቂ የሥነ-ልቦናና የመዋቅር ዝግጅት ያልተደረገበት ሀገራዊ ምርጫ በማካሄድ ሳይሆን፥ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ሁሉን አቀፍ የሆነ የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግሥት በማቋቋም ነው ብሎ በፅኑ ያምናል።
    መዋቅራዊ የሆኑ የፖለቲካ ችግሮቻችንን በአግባቡ ለመፍታት በሚያስችል የሽግግር ሂደት ውስጥ እስካላለፍን ድረስ ግን ላለፉት 29 ዓመታት በስልጣን ላይ በቆየው ገዢ ፓርቲ፣ በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግሥት እየተመራንና ከአለፉት አምስት ምርጫዎች ያልተለየ ስድስተኛ ዙር ምርጫ በማካሄድ የሀገራችንን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት አንችልም። እንዲያውም ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች የተለየና የተሻለ ማድረግ እስካልቻልን ድረስ ሀገራችን ህልውናዋን ወደሚፈታተን የእርስ በእርስ ጦርነት ወይም መንግሥት-የለሽ ሁኔታ ልትገባ ትችላለች የሚል ከፍተኛ ስጋት አለን። ይህንን የሽግግር መንግሥት ሰነድ ብዙ ተጨንቀንና ተጠበን እንድናዘጋጅ ያስገደደንም ይኸው ስለ ሀገራችን ህልውና መቀጠል የሚሰማን ስጋት ነው።

    ይህ ለሀገራችን ህልውና መቀጠል መድኅን የሚሆን የሽግግር መንግሥት መቼና እንዴት ሊቋቋም ይችላል? በማንና ለምን ሊቋቋም ይገባዋል? ሂደቱና የመጨረሻ ግቡስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በዝርዝር ለመመለስ በሚያስችል መጠን ተዘጋጅቶ ቀርቧል።

    ስለሆነም፦

    ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በሀገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ሀገራችን ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አካሂዳ በዘላቂነት ወደ መዋቅራዊ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር በምን ዓይነት የሽግግር ሂደት ውስጥ ማለፍ ይገባታል?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የየራሳቸውን ዝርዝር አማራጭ ለውይይት እንዲያቀርቡ፤

    የኮሮና ቫይረስን ስርጭት በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በማያስተጓጉል ሁኔታ መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያቀርቧቸው አማራጭ ሃሳቦች ዙሪያ ውይይትና ድርድር አካሂደው የጋራ መፍትሄ የሚያመነጩበት ሀገራዊ የምክክር ሂደት /national dialogue/ በፍጥነት እንዲያመቻች፤

    የኢትየጵያ ሕዝብም በአንድ ውጤታማ የሽግግር ሂደት ማለፍ ለሀገሪቱ ችግሮች በዘላቂነት መፈታት አስፈላጊና የማይተካ ሚና ያለው ቅድመ-ሁኔታ መሆኑን በመገንዘብ ሀገራዊ የምክክር ሂደት እንዲጠራ የራሱን ግፊትና ትግል እንዲያደርግ

    አብሮነት በአፅንኦት ይጠይቃል።

    ከዚህ ውጭ ገዢው ፓርቲ ላለፉት 29 ዓመታት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም “የሀገሪቱንዕጣ-ፈንታ መወሰን የሚገባኝ እኔ ብቻ ነኝ” በሚል መታበይ ወይም “እኔ አሻግራችኋለው” በሚል ያልተገባ ፍልስፍና በስልጣን ላይ የሚቀጥል ከሆነ ግን ሀገሪቱ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ አደገኛ የብጥብጥ አዙሪት ልትገባ የምትችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ሀገራችን ከዚህ ዓይነቱ አሳሳቢ ስጋት ወጥታ ወደ ዘላቂ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትሸጋገር ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በየበኩሉ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ አብሮነት ጥሪውን ያቀርባል።

    አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት)
    ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ

    ምርጫ በኢትዮጵያ ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ― ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች

    አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት)

    #14559
    Anonymous
    Inactive

    በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ የሰጠው መግለጫ

    ከሁሉ አስቀድመን በመቐለ ከተማ በጠራራ ፀሀይ ክልሉን እየገዛ ባለው ፓርቲ በታጠቁ ሀይሎች በጥይት ተደብድቦ በተገደለው ትግራዋይ ወጣት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን፤ ለቤተሰቦቹ ለወዳጆቹና ለአብሮ አደግ ጓደኞቹ እንዲሁም ለሰላም ወዳድ የትግራይ ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን።

    በአሁኑ ሰዓት አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተዉ ገዳይና አሰከፊ የሆነዉን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሕዝብ ጋር በመሆን የመከላከል እና ሕዝብን የማዳን ሥራ እተሠራ ይገኛል።

    በዚሁ ሁኔታ መንግሥትና ፓርቲያችን ዘርፈ-ብዙ የሆኑ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወንና በመተግበር ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ጉልህ ዘርፈ ብዙ አወንታዊ ዉጤቶች ባሻገር የተለያዩ ችግሮችና ተግዳሮቶች አብይ ፈተና ሆነዋል። በተለይም በግጭት አትራፊዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚፈጥሩትና በሚቀሰቅሱት ግጭቶችና ሁከቶች ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ሲቀጥፍ መመልከት እየተለመደ መጥቷል። ይህም ድርጊት ለሕዝቦች ሆነ ለሀገራዊ አንድነት የማይበጅ እንዲሁም አሳዛኝ ድርጊት ነዉ።

    ሕዝባችን በዚህ ፈታኝ ወቅት ያጋጠመውን ድርብ ፈተናና ችግር በማለፍ ወደሚፈልገውና ወደሚገባው የሰላም፣ የብልጽግና የመረጋጋት፣ የዲሞክራሲና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግሥት ሆነ በፓርቲ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የመንግሥት አመራሮችና ሠራተኞች ሕዝባዊነታቸው፣ የአመራር እሴቶቻቸውና ጥበባቸው የሚፈተንበት ታሪካዊ ጊዜ ላይ እንደምንገኝም ማስተዋልና መበርታት ይገባል።

    ሆኖም መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመሆን ችግሮችንና ተግዳሮቶችን በመለየትና ቅድሚያ በመስጠት እንዲሁም የስጋት ደረጃና መጠኖችን በመመርመርና በመፈተሽ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ፀረ ለውጥና ጸረ-ኢትዮጵያዊያን ኃይሎች ሆን ብለዉና አቅደዉ በተሳሳተ መንገድ ሕዝቡን በማደናገርና ወደ ጥፋት ጎዳና ለመምራት እየሠሩ ይገኛሉ።

    በተጨማሪም ይህንን አስቸጋሪ የታሪክ አጋጣሚ ለግላዊ ጥቅማቸዉና ፍላጎታቸው ለማሟላት ሕዝብንም ሆነ ሀገርን የሚጎዱ አስነዋሪና አጸያፊ ተግባሮችን በመፈፀም ላይ እንደሚገኙ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል።

    የትግራይ ሕዝብ የቅርብ ሆነ የሩቅ ታሪኩ እንደሚያሳየው፣ ጭቆናንም ሆነ አፈናን የሚፀየፍ ለኢትዮጵያ አንድነት መስዋዕት የከፈለ ሕዝብ ነው። በትግሉና በመስዋዕትነቱም ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች ጉልህ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የበኩሉን ድርሻ የተወጣና በመወጣትም ላይ ያለ ሕዝብ ነዉ። የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በአንድነት በመሆን ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በከፈለው መስዋዕትነት የሰላምና ዲሞክራሲ ብልጭታ የማየት ፍላጎቱ በቀረበው ቁጥር የሚሸሽበት ምናባዊ ዓለም ብቻ እየሆነበት መጥቷል። ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ከተማ የተከሰተው ለአንድ ወጣት ክቡር ሕይወት ህልፈትና ለሁለት ወጣቶች የመቁሰል አደጋ በክልሉ ዉስጥ የሰላምና ዲሞክራሲ እጦት ማሳያ ነዉ።

    በሰላም ወዳዱና እንግዳ አክባሪ በሆነዉ የመቐለ ከተማ ነዋሪ መሪር የሀዘንና ውጥረት ድባብ ዉስጥ ይገኛል። ይህ ክቡር የሰው ሕይወት የጠፋበትና ከባድ የመቁሰል አደጋ ያጋጠመበት ክስተትም ሰላምንና ፀጥታን በሕግ አግባብ ለማስጠበቅ ኃላፊነት በተሰጠው የፀጥታ አካል የተፈፀመ መሆኑ እጅጉን በጣም አሳዛኝ ያደርገዋል። ይህም ድርጊት ብዙ መስዋዕት ለከፈለ የማይገባዉ ነዉ። በመሆኑም የወጣቱ ግብረመልስም በክልሉ ሰላምና ዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ የኔ ጉዳይ ነዉ የሚል ከፍተኛ የሰላም፣ የልማትና የለውጥ ፍላጐቶችና ቁርጠኝነት እንዲሁም ዝግጁነት መኖሩን በግልፅ አሳይቷል።

    እንደሚታወቀዉ በአስቸኴይ ጊዜ አዋጅ የማስተዳደርና የማሰፈፀም አግባቦች ውስጥ የሰው ልጅን ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርና በሕግ የማስከበር ተግባር ላይም የፀጥታ አካላት የላቀ ሰብአዊነት፣ ታጋሽነትና፣ ፍፁም ሕዝባዊነትን የተላበሱ መሆን ይገባቸዋል። የዲሞክራሲና የተሻለ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ልምድ ጉዳይ ከአስተምህሮት ስርፀትና ግልፅ ተጠያቂነትን ከማስፈን አሠራር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ጉዳይ ሲሆን፤ ዜጎች በመንግሥታቸው የደኅንነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ቢሆንም እንደ አለመታደል ሆኖ በትግራይ ክልል በወቅቱ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ክስተቶች አፈናና ግልፅ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዳለ ማስተዋል ተችሏል። በተለይም እራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉ ወጣቶች ላይ መተኪያ የሌለውን ክቡር ሕይወታቸዉን እስከመቅጠፍ የደረሰ የኃይል እርምጃ በየትኛውም መለኪያ መወገዝ ያለበትና ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው እኩይ ተግባር ነው። ድርጊቱም በፍጥነት ተጣርቶ የተወሰደው እርምት እርምጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን።

    ይህ እኩይ ተግባር በተለይ በክልሉ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ፣ ይህን መሰል የአፈና ተግባር የክልሉ ወጣት ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መልኩ አጥብቆ እንዲታገለው የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጥሪውን እያቀረበ፤ በአጠቃላይ ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ላይ የነቃ ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማድረግ በክልሉና በሀገር ደረጃ የተደቀኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ፓርቲያችን ድጋፉ እንደማይለያችሁ ለመግለፅ እንወዳለን።

    “ወደ ሕዝብ የተኮሰ ውድቀቱን አፋጠነ” እንደሚባለው፣ የገዢዎች የውድቀት ምልክት የሚጀምረዉ ወደ ሕዝብ መተኮስ የጀመሩ ዕለት ነው። ስለሆንም በትግራይ ክልል በተለይ ደግሞ በመቐለ ከተማ ባጋጠመው ክስተት፣ በክልሉ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ የክልሉ ገዢ ፓርቲና መንግሥት አካሄዱን ቆም ብሎ እንዲመረምር አስገዳጅ ማንቂያ ደወል ነው። የትግራይ ብልፅግና ፓርቲም ጉዳዩን በአፅንኦት እንደሚከታተለውና ለሚመለከታችሁ ሁሉ በጥብቅ ያሳስባል።

    በዚህ አጋጣሚ ለሁሉም የትግራይ ወጣት እና ለውጥ ፈላጊ ኃይል ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጋር በመሆን የለውጥ ሂደቱን እንዲያፋጥኑ ከፓርቲያችን ጋር እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ፓርቲያችን የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሚገባዉን ጥቅም እንዲረጋገጥ እና ሃገራዊ አንድነቱ እንዲጠናከር ይሠራል። በጥቂት ገዥ የህወሓት ቡድን በተለይ በዝምድና እና ጥቅም ትስስር እንዲሁም በሥልጣን ጥማት ምክንያት ትግራይን ከሌሎች የሀገሪቱ ሕዝቦች ለመነጠል የሚደረግ ሥራም ሆነ ሴራ በጥብቅ የምንታገለዉና የምናወግዘዉ መሆኑን በጥብቅ እናሳዉቃለን።

    በመጨረሻም ለሟች የዘለዓለም እረፍት፣ ለቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ከልብ እንመኛለን።

    የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ
    ግንቦት 11ቀን 2012 ዓ.ም.

    የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ

    #14589
    Anonymous
    Inactive

    “የትግራይ ሕዝብ ህወሓትን በቃህ ሊለው ይገባል” አቶ ደረጀ በቀለ – የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሊቀመንበር

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የትግራይ ሕዝብ ህወሓትን (ህዝበ ወያኔ ሃርነት ትግራይ) በቃህ ሊለው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሊቀመንበር አስታወቁ። 45 ዓመታት የዘለቀው የህወሓት ትግል የጉዞ ምዕራፉ ወደመጠቃለሉ መቃረቡንም አመልክተዋል።

    ሊቀመንበሩ አቶ ደረጀ በቀለ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት፥ ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል የሚያደርገውን አካሄድ ተገንዝቧል፤ በቃህ ሊለው ይገባል። የትግራይ ወጣቶች፣ የትግራይ ምሁራን፣ በትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተው፣ ላለፉት 45 ዓመታት ያደረጋቸውን በማሰብ፤ የህወሓትን አመራሮች በቃችሁ ሊሏቸው እንደሚገባ አስታውቀዋል።

    የትግራይ ወጣት የህወሓትን ወቅታዊ አካሄድ እንደማይቀበለው መገንዘባቸውን የጠቆሙት አቶ ደረጀ፥ ሕዝቡ ከድህነት መውጣትን የሚፈልግ መሆኑን አመልክተዋል። ህወሓት የዘረፈውን ወደአውሮፓና መሰል አገሮች ከማሸሽ የዘለለ ለሕዝቡ የሰራለት ነገር እንደሌለም መታዘባቸውን ተናግረዋል። በተለይ በትግራይ ያለው የገጠር ሕዝብ ስለህወሓት መሰሪነትና ተንኮል በደንብ ይገነዘባል ያሉት ሊቀመንበሩ፥ የትግራይን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል የሚያደርገውንም አካሄድ ሕዝቡ መገንዘቡን አመልክተዋል። የትግራይ ተወላጆችና የትግራይ ሕዝብ ህወሓትን በቃህ ሊሉት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

    እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ የህወሓት አመራሮች በመቐለ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች ጭምር ከህንጻ እስከተሽከርካሪ የሚገለጽ ሀብት አከማችተዋል። በአንጻሩ በክልሉ የዕለት ጉርሱን፣ ጫማና ልብስ ማሟላት እንኳን ያቃተው ሕዝብ (በተለይ በገጠሩ) ተፈጥሯል። የህወሓት አመራሮች ለዚህ ሕዝብ ታግለንለታል ካሉ ሕዝቡ ነጻ መውጣት ነበረበት፤ ቢያንስ ትንሽ መሻሻልም ሊያሳይ ይገባ ነበር። ስለሆነም የትግራይ ሕዝብ፣ ልሂቃንና ሌላውም የሕብረተሰብ ክፍል የሚያደርጉትን ድጋፍ ማቆም አለባቸው ሲሉ መክረዋል።

    በየክልሉ ተበትነው ያሉና በውጭ አገራት የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችም ለህወሓት የሚያደርጉትን ድጋፍ ቆም ብለው እንዲያስቡ ጥሪ አቅርበዋል። በሚያደርጉት ድጋፍ በአገራቸው ለውጥ ስለመኖሩ መመልከት እንዳለባቸው፣ ህወሓት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲገዛና ሀብቱን እንደፈለገው ሲያሽከረክር ለትግራይ ሕዝብ ምን አደረገ? ብለው ሊያስተውሉ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።

    ችግር ሲመጣባቸው መቐለ ተሰበሰቡ እንጂ አካባቢውን እንኳን አይተው የማያውቁ ብዙዎች ናቸው ያሉት ሊቀመንበሩ፥ ክልሉን ባስጎበኟቸው ጊዜ አምባሳደር ስዩም መስፍን በተገኙበት የጉብኝት መርሐ ግብር የአምባሳደር ስዩም የትውልድ አካባቢ መመልከታቸውን አስታውሰው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች አምባሳደር ስዩምን ከዛን ዕለት በስተቀር እንደማንኛውም ሰው በቴሌቪዥን ከመመልከት ውጪ በአካል አይተዋቸው እንደማያውቁ እንደነገሯቸውም ነው የገለጹት።

    በክልሉ፣ በሌሎች ክልሎችና በውጭ አገራት የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ሕወሓት ለሕዝቡ ምን አደረገለት ወይም ምን አደረገበት ብለው ሊመረምሩ እና እነዚህን ግለኛ አመራሮች በቃ ሊሏቸው እንደሚገባ በመጠቆም፥ የትግራይ ሕዝብ እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ የሚፈልገውን ፓርቲ ደግፎ የነጻነት አየር መተንፈስ እንዲችል ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

    የትግራይ ሕዝብ ትክክለኛ አካሄድ የሚሄድ ኢትዮጵያዊ መሆኑን በመጠቆምም፤ የትግራይን ሕዝብ እገነጥላለሁ ብሎ የሚፎክረው ህወሓትም የግል ስሜትና ፍላጎቱን እንጂ የሕዝቡ ፍላጎትና ድጋፍ እንዳልሆነም ተናግረዋል። ሕዝቡ ለህወሓት ባዶ ፉከራ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊነቱ ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ኢትዮጵያዊነቱን እንደሚያከብር መገንዘባቸውንም አቶ ደረጀ ተናግረዋል። ህወሓት ለራሱ ጥቅምና ስልጣን ማስቀጠያ በሚያመች መልኩ እንጂ ለክልሉ ሕዝብም ሆነ ለክልሉ የተሻለ እድገት ሲል ያከናወነው ነገር አይታይም ብለዋል። በትግራይ ክልል እየሆነ ያለው የማግለል ተግባር ግን የህወሓት ሥራ ውጤት እንጂ የሕዝቡ ፍላጎትም ተግባር እንዳልሆነም አስታውቀዋል።

    የትግራይ ሕዝብ በድህነት ውስጥ የሚገኝ፣ በአፈና ውስጥ ያለ፤ ከስጋት ያልተላቀቀ መሆኑን ገልጧል። እንደሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ የፈለገውን የመደገፍ የሚፈልግ፣ ከተወሰኑ የህወሓት ቡድኖች አፈና መውጣትን የሚናፍቅ መሆኑንም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብም ለህወሓት ባዶ ፉከራ ሳይሆን ለዚህ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ የትግራይ ሕዝብ ጆሮ ሰጥቶ የሕዝቡን እውነት ማድመጥ እንደሚኖርበት ደረጀ በቀለ አመልክተዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አቶ ደረጀ በቀለ

    #14664
    Anonymous
    Inactive

    የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

    የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከግንቦት 15 እስከ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው በፍጥነት እየተለዋወጠ ያለው የዓለም፣ የአካባቢያችንና የሀገራችን ሁኔታ ጨምሮ የክልላችን ሰላምና ደኅንነት፣ የኮረና ቫይረስ በሽታ ስጋትና የመከላከል ሥራ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት፣ የድርጅትና የመንግሥት ሥራ አፈፃፀም እንዲሁም በአስተዳደር በኩል እየመጡ ያሉት ለውጦች አስመልክቶ ሰፊ ውይይት አካሂዷል።

    ኮሮና ቫይረስን ወይም ኮቪድ-19ን ተከተሎ እየመጣ ያለውን አዲስ ዓለማዊ ሁኔታ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር አስፈላጊነትንና ትክክለኛነትን የሚያረጋግጥ ነው። ቀድመውንም ቢሆን የመንግሥት ስልጣን ሽግግርን ለብቻ ተቆጣጥረህ ጠባብ ጥቅምህን ለማርካት፣ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለአፍታ እንኳን ግድ የሌለው ጥገኛ የብልፅግና ቡድን በተፈጠረው አዲስ ዓለማዊ ሁኔታዎችና ፈተናዎች ራሱን አስተካክሎ በሕዝባዊ ትግልና በሕዝብ ልጆች መስዋእትነት በግንቦት 20 የተመዘገቡ አስደናቂ የዴሞክራሲና የልማት ድሎች አጠናክሮ ከማስቀጠል ይልቅ የጥፋት መንገድ አጠናክሮ ቀጥሎበታል።

    በጊዜያዊ ጥቅም ወይም በጥላቻ የዚህ ሥርዓት መጠቀሚያ በመሆን ሙያቸውንና ስብዕናቸውን አሳልፈው የሰጡ አካላት ከፊት በማሰለፍ በግላጭ ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ስልጣን ላይ እንደሚቆይ ይፋ ያደረገው የብልፅግና ቡድን ለማስመስል እንኳን ውሳኔ ይሰጣሉ የተባሉትን ተቋሞች የሚሉትን እስከምንሰማ ድረስ እንኳን ሊታገስ አልቻለም። በእንደነዚህ ዓይነት ወደ ጥፋት የሚምዘገዘገው የብልፅግና ቡድን የሚያስተዳድረው መንግሥት ባላት ሀገር ሆነን መሠረታዊ ዓላማችንንና ልማታችንን ለማሳካትም ሆነ የገጠመንን የኮሮና ቫይረስ ፈተና ለመመከት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሁሉም ሊገምተው የሚችል ነው።

    የ‘ብልፅግና’ ቡድን ሉዓላዊነትና መሠረታዊ የሚባሉ የሀገር ጥቅሞች ለሽያጭ በማቅረብ፣ ሕገ መንግሥትንና ሥርዓትን እንዲሁም ሁሉም ዓይነት ከፊቱ ላይ የቆሙትን ሕጎችንንና ተገቢ የመንግሥት አሠራሮችን በመጣስ ስልጣን ላይ ለመቆየት ከመወሰን አልፎ ሥርዓትንና ሕግን አክብረው በሄዱት አካላት ላይ ይፋዊ ጦርነት ወደ ማወጅ ተሸጋግሮ ይገኛል። የዚህ ቡድን ፉከራዎችና ሴራዎች በአካሄዳችን ላይ ይሁን በሕዝባዊ ትግላችን ተጨማሪ ቁጭትና ወኔ ከመፍጠር አልፈው ሌላ ፋይዳ ያላቸው እንዳልሆኑ ግልፅ ቢሆንም ለጠባብ ፍላጎት ሲባል የሀገርና የመላ ሕዝቦች ጥቅም ወደ ገደል ገፍትሮ ለመጣል ‘ብልፅግና’ ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ ለሁሉም ግልፅ ሆኗል።

    ይሁን እንጂ ወትሮም ቢሆን ህልውናውንና ጥቅሙን በጠንካራ ክንዱና በትክክለኛ አስተሳሰቡ የተመሠረተ መሆኑን፤ ታሪኩንና ትግሉን በተጨባጭ አሳምሮ የሚያውቅ ሕዝባችን፤ የጥገኞች ቀጣይ በርካታ ጥቃቶችን ተቋቁሞና የመመከት ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠናል። ድርጅታችን ህወሓት ሕዝባችን እያካሄደ ላለውን ፍንክች የማይል ቀጣይነት ያለው ትግል ከፍተኛ ክብርና አድናቆቱን ይገልፃል። ወደፊትም ሁኔታዎች በጥብቅ እየገመገምን የምናሳልፋቸው ውሳኔዎች በንቃት እንደሚከታተልና እንደሚፈፅም የትናንትም የዛሬም ታሪካችን ምስክር ነው። እያካሄድን ያለነው የተፋፋመ ትግል በሁሉም የሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ አውዶች ተስፋ የሚያሰንቁና ለቀጣይ ድሎችም አመቺ ቦታ የሚፈጥሩ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም ሕዝባችንን ያላረካንባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ አሳምረን የምንረዳው እውነታ ነው።

    ከሕዝባችንና ከመሪ ድርጅታችን ፊት ለፊት መግጠም ከብረት ጋር መጋጨት የሆነባቸው ጥገኛ ቡድንና ተከታዮቹ በዋነኛነት በተቀናጀ የሚዲያ ዘመቻ የታገዘ ግልፅ ውሸት በመመሥረትና ባንዳዎችን በማዝመት ውስጣዊ ሰላማቻንን በማደፍረስና ልማታችንን በማደናቀፍ ወደ ድቅድቅ ጭለማ ሊያስገቡን እየሠሩ መሆናቸውን ሁሉም በተለይ ደግሞ ሕዝባችን የሚገነዘበው ጉዳይ ነው።

    በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ሆነን በአንድ እጃችን ሁለገብ የመመከት ሥራዎቻችን እያጎለበትን በሌላም በኩል ፈጣን የልማትና የመልካም አስተዳደር ማስፈን፣ ሕዝባችንንና መላ መዋቅራችንን እንዲሁም የሰላምና የልማት ወዳጅ የሆነ ኃይል ሁሉ ሊረባረብላቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው በማረጋገጥ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው ያሳለፋቸው ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን በማጽደቅና መሠረት በማድረግ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚከተሉትን ውሳኔዎችን አሳልፏል።

    1. የኮሮና ቫይረስ መከላከል ሥራ ከዚህ በፊት ሲደረግ እንደቆየው አዲስ ለውጦች፣ ተጨባጭ የክልላችን ሁኔታ እንዲሁም ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን መሠረት በማድረግ ሕዝባችንን ለማዳን እየተከላከልን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በሚቀንስ መልኩ እየተገመገመ በጥብቅ እንዲመራ ተወስኗል።
    2. የ‘ብልፅግና’ ቡድን ከድሃ ጉሮሮ እና ልማት ቀምቶ ያልተቆጠበ ሃብት በማፍሰስ ሀገር ከጫፍ እስከ ጫፍ ለማበጣበጥ፣ በዶክሜንተሪ ፊልሞች የታገዘ ዘር የማጥፋት ጥሪ እንዲካሄድና ሁሉም መብቶች እንዲረጋገጡ እያደረገ ያለው ጭፍን ፀረ-ሕዝብና ስልጣንን በገንዘብ የመግዛት ተግባር እንዲቆም ብቻም ሳይሆን ከጥፋት መንገድ ወጥቶ በሕገ-መንግሥት መሠረት የሚመለከተው ወገን ሁሉ ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ እና ወደ ምክንያታዊ ውይይት እንዲገባ እንዲሁም ጨርሶ ሳይረፍድ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ከማፍረስ እንዲቆጠብ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያሳስባል።
    3. ሙሉ ዝግጅትና የሕብረተሰቡን ጤና የመጠበቅ ሥራ በመሥራት በሕገ መንግሥት በተዘረጋው ሥርዓት መሠረት ሁሉንም እኩል ማየት የሚችል ኃይል የሚመራው ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ዳግም ያሳስባል።
    4. ምርጫ በሀገር-አቀፍ ይሁን በክልል ደረጃ በሺዎች መስዋዕትነትና ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ሕገ-መንግሥታዊ ዋስትና ያገኘ መብት እንጂ ገደብ የለሽ የስልጣን ጥማት ያለው ግልገል አምባገነን የሚሰጠው ወይም የሚከለክለው ችሮታ አይደለም። የትግራይ ሕዝብ ከድሮም ቢሆን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠ፣ በማንኛውንም ሁኔታ በራሱ ላይ ይሁን በሌሎች ሕዝቦች ላይ ባርነት እንዲነግስ የማይፈቅድ ሕዝብ ነው።

    የትግራይ ሕዝብ በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠው መብት በማንኛውንም ጊዜ እና ሁኔታ ወደ ድርድር እንደማይቀርብና የዚህን መብት ተግባራዊነት ወደ ኋላ መመለስ የሚችል ማንኛውም ምድራዊ ፖለቲካዊ ኃይል እንደሌለ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አስምሮበታል። ስለዚህም የፌደራል ስልጣን በአምባገነናዊ አኳኋን ተቆጣጥሮ ያለው ኃይል በተለመደው አካሄዱ የሕዝቦችን መብት እየደፈጠጠ መቀጠሉን አጠናክሮ እየገፋበት በመሆኑ ሕዝባችን በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠው እና የማንም ፈቃድ የማይጠይቅበት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተግባር ለመተርጎም በክልላችን ምርጫ እንድደረግ እና ይህንን ለማድረግ የተጀመሩ ዝግጅቶች ለማድረግ የተጀመሩ ዝግጅቶች በሕግ አገባብ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ወስኗል።

    የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በትግራይ ምርጫ እንዲካሄድ ሲወስን በ‘ብልጽግና’ ጥገኛ ባህርይ ምክንያት የተጀመረው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የማፍረስና ሀገር የመበተን ሂደት ወደ መጨረሻ ምዕራፍ እየደረሰ መሆኑን ይገነዘባል። አሁንም ቢሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና እና ሕዝቦች የሀገራችንን ሕገ-መንግሥት ያጎናፀፋቸው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዳያጡ ትግላቸው ማጠናከር እንደሚገባቸው ህወሓት ያምናል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይህንን ተገንዝቦ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    1. የ‘ብልፅግና’ ቡድን ምርጫ ላለማካሄድና የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም እየወሰዳቸው ካሉ ሕገ-ወጥ እርምጃዎችና ሴራዎች በተጨማሪ የድርጅታችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በትግራይ ክልል ሕግና ሥርዓት እንደሚቀጥልና ‘ብልፅግና’ ምርጫ ለማስቀረት እየሠራ በመሆኑ በትግራይ ደረጃ በሕግ መሠረት ምርጫ ለማካሄድ ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት የብልጽግና መሪ አሁንም መሠረታዊ የሕዝቦች ራስን በራስ የመወሰን መብት ክብር እንደሌለው በሚያሳይ መልኩ የጦርነት አዋጅ ይፋ አድርጓል። የትግራይ ሕዝብ በፉከራና የጦርነት ነጋሪት መጉሰም እንደማይደነግጥና መብቱን አሳልፎ እንደማይሰጥ የሚታወቅ ሃቅ ነው። ኃላፊነት በጎደለው አካሄድ እንዲሁም የ‘ብልፅግና’ ቡድን እና መሪው የሚመጣ ማንኛውንም ጥፋት ብቸኛው ተጠያቂዎች ራሳቸው መሆናቸው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ መገንዘብ ይገባቸዋል።
    2. በልማት ሥራዎች፣ የዴሞክራሲ ባህል እና አስተዳደር የተጀመሩ ለውጦች በጊዜ የለንም መንፈስ በበለጠ ፍጥነት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በየደረጃው ያለው አመራር በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ እንዲሠራው ተወስኗል። ይህ በእንዲህ እንዳለ መላው ሕዝባችንና ሁሉም የመንግሥትና የድርጅት መዋቅሮች ለርካሽ ዓላማቸው ሲሉ ከልማትና የዴሞራሲ ግንባታ ሃዲድ አውጥተው ወደ ብጥብጥና ጥፋት ሊያስገቡን የሚረባረቡ ብልጽግና ኃይሎች፣ አይዞህ ባዮችና እና ተላላኪዎቹ ለመመከት የተጀመረውን ትግል እንዲጠናከር ተወስኗል።
    3. የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ የሕዝባችን ደኅንነትና ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳዮች ላይ አብሮው ሊሠሩ ዝግጅ ከሆኑ የሀገራችንና የክልላችን የፖለቲካ ኃይሎች የተጀመረውን ዝምድና በፍጥነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገርና ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ ወደሚችልበት የሕዝባችን ደኅንነትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ሥራዎች እንዲገባ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ወስኗል። የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትንና መንግሥትን አስፈላጊነትና ቀጣይነት በአግባቡ ተረድታችሁ፣ ይህን ለማረጋገጥ የድርሻችሁ ሀገራዊ ግዴታ እንደምትወጡ እና ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሰያችሁን አጠናክራችሁ እንደምትቀጥሉ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያምናል።

    የትግል ጥሪ፤

    የተከበርክ የትግራይ ሕዝብ፥ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች ለመናድ ሕገወጡ የ’ብልፅግና’ ቡድን እየተከተለው ያለው የተቻኮለ አካሄድ እና የጦርነት አባዜ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል በማካሄድ ለመመከት የትግራይ ሕዝብ በተለይ ደግሞ የትግራይ ወጣቶች የትግል ዝግጁነታቸውና አደረጃጀታቸውንእንዲያጠናክሩ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።

    ኮሮና ቫይረስ በህልውናችን ላይ እና በጀመርነው የመመከት እንቅስቃሰያችን ለያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ በመረዳት፣ የባለሞያዎች ምክርና የመንግሥት መመሪያዎች በጥብቅ በመተግበር፣ ሕዝባችን ተገቢ ትኩረት በመስጠት እንዲመክተው ከከፍተኛ አደራ ጭምር ጥሪውን ያቀርባል። ህልውናችን፣ ሰላማችንና ልማታችን ለማረጋገጥ ደግሞ መላ ሕዝባችን የሚያጋጥሙትን ችግሮች ተሸክሞ፣ ምርቱና ምርታማነቱ ይበልጥ እንዲጠናክር በድጋሜ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    የተከበራችሁ የድርጅታችን ህወሓት አባላት፣ በየደረጃው ያላችሁ አመራሮች፥ አሁን ያለንበት መድረክ የሚጠይቀውን ፅናትና መስዋዕትነት በውል ተገንዝባችሁ፣ ሕዝባችን ለማዳን በሚደረገው ሁለንተናዊ ትግል ግንባር ቀደም ድርሻችሁ እንዲትወጡና አርአያነታችሁ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።

    የተከበራችሁ የክልላችን የሕዝብ ማኅበራትና ሲቪክ ተቋሞች፥ ዛሬም እንደትላንቱ ለሰላማችሁ፣ ለልማታችሁና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከእናንተ በላይ ሊቆረቆር የሚችል ኃይል እንደሌለ ተገንዝባችሁ በመመከት እንቅስቃሴ በጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ምርጫውን በድል እንዲጠናቀቅ በከፍተኛ ፍጥነት እንድቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    የተከበራችሁ የሀገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፥ የአፈና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ጭቆናና የተለያዩ በደሎች እንዲሁም ሁለንተናዊ ችግሮች የጀመራችሁት ትግል አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ለመሠረታዊ መብቶች፣ ፍትህና እኩልነት በምታደርጉት ትግል ህወሓት ዛሬም እንደትላንቱ ከጎናችሁ እንደሚቆም ያረጋግጣል።

    የተከበራችሁ የሀገራችን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፥ ሕገ-መንግሥቱን ለመናድ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ሊያስከትለው የሚችል ሀገር የማፍረስና እልቂት በውል ተገንዝባችሁ፣ ይህ ተግባር እንዲቆም ታሪካዊ ኃላፊነታችሁ እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    በሕገ-መንግሥት መሠረት የተዋቀራችሁ የሀገራችን የክልሎችና ተቋማት፥ ሕዝብ የሚያስቀድምና ሕገ-መንግሥቱን የሚያከብር መንገድ እንድትከተሉ እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በመናድ ላይ ከመሳተፍ እንድትቆጠቡ ጥሪያችን እናቀርባለን።

    የተከበራችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ ደግሞ በትግራይ ሕግ አክብራችሁ የምትንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አስተዋፅኦ ያላችሁ ኃይሎች፥ አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በጥሞናና በዕውቀት በመመርመር የብልፅግና ቡድን የያዘው የጥፋት መንገድ እንዲቆም ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ፣ ከሕግና ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳችሁን እንድታድኑ ጥሪ እናቀርባለን።

    የተከበራችሁ የትግላችን አጋር፣ የጎረቤት ሀገሮች ሕዝቦች በተለይ የኤርትራ ሕዝብ፥ አሁንም እንደ ትላንቱ የጋራ ችግሮቻችን ለመፍታት ትግላችንና ትብብራችን እንድናስቀጥልና ይበልጥ እንድናጎለብት ጥሪ እናቀርባለን።

    የተከበራችሁ የዓለማቀፍ ተቋሞች በተለይ ደግሞ ኢጋድ (IGD)አፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታችሁ አካላት፥ በኢትዮጵያ በለውጥ ስም እየተካሄደ ያለው ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፤ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን የመናድና ሀገሪቱን የማፍረስ እንቅስቃሴ በጠራ መረጃ እና ዕውቀት እንዲሁም በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ አወንታዊ ሚናችሁ እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    ዘለዓለማዊ ክብርና ሞገስ ለጀግኖች ሰማዕታት!
    ድልና ድምቀት ለ29ኛው የግንቦት 20 ድል በዓል!
    አሁንም መስመራችን አጥብቀን እንመክት!
    ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላይ ኮሚቴ
    ግንቦት 23 ቀን 2012 ዓ.ም.
    መቐለ

    የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ

    #14685
    Anonymous
    Inactive

    የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የሰጠውን መግለጫ በተመለከተ የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

    ሕዝባዊነት እና ዲሞክራሲያዊነት ከማያውቀው የህወሓት ገዢ መደብ፣ የተጎሰመው የሁከትና ብጥብጥ አቋቁሙኝ ነጋሪት መግለጫ ሰምና ወርቅ።

    የህወሓት ጥገኛ ገዢ መደብ የሰሞኑ መግለጫ ሰሙ በሕዝባዊነት፣ ሕጋዊነት፣ ሰላማዊነት፣ የዲሞክራሲያዊነትና የሀገራዊ አንድነት የተለበጠ አዛኝ ቅቤ አንጋችነት ባዶ ጩኸት ነው፤ ወርቁ ደግሞ በሴረኝነት፣ በቡድነኝነት፣ በሀገር ጠልነት እና በኢ-ዲሞክራሲያዊነት ሁሉን ፍጥረት በሚያስማማ ሕዝባዊ ቅቡልነት እጦት የተንሳፈፈን ኃይል በማንኛውም ኢ-ሰላማዊ መንገድ በመጠቀም የመተንፈሻ ድጋፍ በመስጠት ለመመለስ ያለመ የስሌት ችግር የሚስተዋልበት ኢ-ሞራላዊ የሁከት አታሞ ነው።

    የህወሓት የጥገኛ ገዢ መደብና ከተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች የተሰባሰቡ የኩርፍያ አድመኞች በቀድሞ የኢህአዴግ አወቃቀር በተለያዩ ግዜያት በተደረጉ ግምገማዎች የሥርዓትና የሀገር አደጋዎችን በመለየት ለማስወገድ በተዘጋጁ መድረኮች ሲናዘዙ ቆይተዋል።

    እንደ ኮሮና ቫይረስ ባሉ በማያከራክሩ ህልው ዓለማዊ፣ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታዎች ውስጥም ሆነን ጭምር ግላዊ ፍላጎቶቻቸው ሕዝብ ላይ ለመጫን እየሄዱበት ያለው አቅጣጫና ርቀት አሁንም አነጋጋሪና ዳግም የስህተት ታሪክ ሀወልትና ማፈርያ እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

    ይህ ለእኔ ስለኔ እና የእኔ ብቻ የሆነ የገዢ መደብ በሕዝባዊነት በዲሞክራሲያዊነትና በቀናኢ የኢትዮጵያዊ አንድነትም የማያምን መሆኑን አንዳንድ አባላቱ በድፍረት ባለፉት ሁለት ዓመታት በቀረቡበት ሚድያዎች ሁሉ ለሕዝብና ሕዝባዊነት ያላቸውን ቅጥ ያጣ ንቀት በገዛ አፋቸው ያለህፍረት መስክረዋል።

    አስተዋይና አርቆ አሳቢ የሆንከው መላው የሀገራችን ሕዝብ ሆይ፤ በዲሞክራሲ ስም እየማለ እና እየተገዘተ፣ ዲሞክራሲ ማዕከላዊነት በሚል ማሞኛ ፈሊጥ ለዓመታት እራስን በራስ ለማስተዳደርና ለሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማበብና መበልፀግ እንቅፋት ሆኖ፣ በምስለኔዎች የሞግዚትነት አሠራር የሀገራችን የፖለቲካ እድገት አቀጭጮ፣ በመጠላለፍ ሴራና በመከፋፈል ላይ የመሠረተውን ይህን የገዢ መደብ የጥፋት ሃሳብ በጥብቅ በማውገዝ ሰላምና አንድነትህን በንቃት በመጠበቅ እንድትታገለው ታሪካዊ ጥሪ ይድረስህ።

    በተለይም መላው የትግራይ ሕዝብ፥ አርሶ አደሩ፣ የመንግሥትና የግል ሠራተኞች፣ ምሁራን፣ ነጋዴዎች፣ ነባር ታጋዮችና ለፍትህና ለነፃነት አካላችሁን ያጎደላቹ ሀቀኛ የሕዝብ ልጆች፣ ወጣቶች፥

    • በሀገረ ኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ምሥረታ የትግራይ ሕዝብ ያለውን ጉልህ ታሪክና ጅግንነት ከካዱና ካሳነሱ፤
    • ላለፉት 29 ዓመታት የትግራይ ሕዝብ የታገለለትን አላማ ረስተው ለግልና ቡድናዊ ጥቅማቸው ካደሩ፤
    • ሕዝባዊ የልማት ተጠቃሚነትን በቡድናዊ ጥቅም ለውጠው በገዛ መሬትህና ሀገርህ ለዘመናዊ ባርነት የሽጥሁን፤
    • በኢትዮጵያዊ አንድነትህ የማትደራደረውንና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖችህ ጋር በሰላምና በመተሳሰብ ለዘመናት መኖርህ እንቅልፍ ነስቷቸው ሌት ተቀን የሚያሴሩብህን፤
    • “በምድር ላይ ያለ የፖለቲካ ኃይል እኔ ነኝ” በሚል ያነሰ አስተሳሰብ፣ በሺዎች ዓመታት የሚቆጠረውን ጅግንነትህን እና ታሪክህን ወደ አርባዎች አውርደው “ከኛ በላይ ለአሳር” የሚመስለውን ትምክህታዊና ሸውራራ የታሪክ ትርክታቸውን ‘በንቀት ለመጋት ከሚሞክሩ የዘመኑ አዋቂ ነን ባይ አላዋቂዎች፤
    • ለዓመታት በስልጣን ዘመናቸው በከተማ ሲንደላቀቁ፣ በመላው የትግራይ ገጠሮችና ከተሞች የንፁህ ውሃ እጦት እሮሮህ ለመስማትና ለመመለስ ጀሮ ዳባ ልበስ ካሉ፤
    • ከምንም በላይ የጥይት ባሩድ ለሰለቸህ፣ የጦርነት ኪሳራውን በተግባር በማወቅህ አጥብቀህ ሰላም ናፋቂና ፈላጊ መሆንህ የጎረበጣቸው፤

    እነዚህ የገዢ መደብ አለቆች ጠንቀኝነታቸውንና ተዘርዝሮ የማያልቀውን ጥፋታቸውን በጊዜው በመገንዘብ፥ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆነህ በድጋሚ እንቢተኝነትህን እንድታሳይና በሰላማዊ መንገድ ታግለህ ታሪክህን በድምቀት እንድታድስ ልዩ ጥሪ እናቀርብልሀለን።

    ለሕጋዊ፣ ሰላማዊ እና አስተዋይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች፥ በፖለቲካዊ አመለካክታችሁና አቋማቹ የቱንም ያህል ብትቃረኑ፣ ሕዝባዊነት፣ ሕጋዊነት እና ሰላማዊነትን ተላብሳችሁ የሚጠብቅባችሁን ታሪካዊ ድርሻ እንድታዋጡ አደራችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን።

    እንግዲህ “ከክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ አይጠበቅምና” መልዕክትና መልዕክተኛው የተቃረኑበትን ሰሞነኛ መግለጫው፣ ብሩህና አስተዋይ ለሆነው ሕዝባችን ሰምና ወርቁን እንደሚገነዘበው የሚያምነው የብልፅግና ፓርቲ፣ በየትኛውም ደረጃ ሕዝባዊ ተሳትፎን በመተማመን ከፊቱ የተጋረጠበትን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልን ቀዳሚ ትኩረቱ በማድረግ፣ ሕዝቡ ራሱንና ወገኑን እንዲጠብቅ በአፅንኦት ይገለፅፃል።

    ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
    የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ

    የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ

Viewing 15 posts - 1 through 15 (of 28 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.