ምርጫ በኢትዮጵያ ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ― ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች

Home Forums Semonegna Stories ምርጫ በኢትዮጵያ ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ― ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች

Viewing 13 posts - 16 through 28 (of 28 total)
  • Author
    Posts
  • #14689
    Anonymous
    Inactive

    የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር በምንም ምክንያት እና በማንኛውም ጊዜ ለድርድር የማይቀርብ ነው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) «ሕግን ከማስከበር ባሻገር» በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ሁለት አካባቢዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ዘርዝሯል። በዘገባው ውስጥ በፀጥታ አስከባሪዎች እርምጃ በአሰቃቂ እና ከሕግ ውጪ በሆነ ሁኔታ የዜጎች ሕይወት መጥፋቱን፣ ሴቶች መደፈራቸውን፣ በማቆያ ካምፖች ውስጥ ሰቆቃ መፈፀሙን፣ ከሕግ አግባብ ውጪ እስር መፈጸሙን፣ ዜጎች ከሚኖሩበት እንደተፈናቀሉ እና ንብረታቸው እንደወደመ ተዘርዝሯል። በተጨማሪም በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የእርስበርስ ግጭት ሲከሰት የአካባቢ አስተዳዳሪዎች እና ፀጥታ ኃይሎች የዜጎችን ደኅንነት ከማስጠበቅ ይልቅ በግጭቱ ውስጥ እንደተሳተፉ እንዲሁም ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ እንዳልተወጡ ተጠቅሷል። እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ በአካባቢው ይፈፀማሉ ብሎ ካወጣው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ዘገባ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።

    በዘገባው ውስጥ የተጠቀሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ዘገባውን በሠራው ተቋም ምላሽ ወይንም ማብራሪያ ከተጠየቁ የፌደራል እና የክልል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች መካከል የአማራ ክልል የሰላም እና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ብቻ መልስ እንደሰጠ ዘገባው ጠቅሷል። በሁሉም ደረጃ ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተሰማሩበት የኃላፊነት ዘርፍ የተከሰቱ ችግሮችን በተመለከተ የሚቀርብላቸውን የማብራሪያ ጥያቄዎች በቀናነት መቀበል እና ምላሽ መስጠት ግዴታቸው እንደሆነ እናምናለን። የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በርን ክፍት አድርጎ መቀበል እና ግልጽነት የተሞላው ምላሽ መስጠት፣ እንዲሁም የተሠሩ ስህተቶችን ለማረም ዝግጁ መሆን በሂደት ለምንገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ እሴቶች ናቸው። በዚህ ረገድ የአማራ ክልል ሰላም እና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ላሳየው አርኣያ የሚሆን ተግባር ያለንን አክብሮት መግለጽ እንወዳለን። የፌደራል መንግሥቱን ጨምሮ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አካላት በተለይ ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች እና ጥቆማዎች ከዳተኝነት እና ተጠያቂነትን ለመሸሽ ከሚደረግ ማንኛውም ሙከራ በመታቀብ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

    የአምነስቲ ዘገባ በሁለት የተወሰኑ ቦታዎች እና ውስን ክስተቶች ላይ ያጠነጠነ መሆኑ ተከሰቱ የተባሉትን ጥሰቶችም ሆነ ሌላ በሀገራችን የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሙሉ በሙሉ ለመረዳትም ሆነ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ በቂ መረጃ የያዘ ነው ተብሎ ባይወሰድም በውስጡ የያዛቸው የከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰለባ የሆኑ ዜጎች ስም፣ የተፈጸመበት ቦታ እና ጥሰቱን እንደፈጸሙ የተጠቀሱት ተቋማት በግልጽ መቀመጥ ግን የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጣራት ቀላል ከማድረጉም በላይ ተጨማሪ ምርመራ ተደርጎ የተጠቀሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው ከተረጋገጠ የእርምት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ከበቂ በላይ አመላካች ናቸው። በአምነስቲ ዘገባ ያልተካተቱ በየጊዜው ለዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደል፣ ከመኖሪያቸው መፈናቀል፣ የተማሪዎች መታፈን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መታሰር እና መንገላታትን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ይፋ የተደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳሉም ይታወቃል።

    በመሆኑም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ ውስጥ የተካተቱትን ጨምሮ የለውጡ አስተዳደር ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በፌደራል እና የክልል መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ የፖለቲካ ዓላማ ባነገቡ ታጣቂዎች እንዲሁም በየአካባቢው በተደራጁ ኢ-መደበኛ ቡድኖች ዜጎች ላይ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ልዩ ቡድን በአስቸኳይ እንዲያቋቁም እና ምርመራ አድርጎ ውጤቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለክልሎቹ ምክር ቤቶች እና ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ እንጠይቃለን። በዘገባው በተጠቀሱ እና ከዛም ውጪ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው በሚታወቁ (በሚጠረጠሩ) ቦታዎች የተከሰቱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በቦታው ድረስ በመገኘት ከተጎጂዎች እና ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ በጊዜው በአካባቢው ግዳጅ ላይ ከነበሩ የፀጥታ አስከባሪዎች፣ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎችን በማግኘት ሰፊ ምርመራ እንዲደረግ እንጠይቃለን።

    የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይህንን ኃላፊነት እንዲወስድ ማድረግ እና አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት የሀገራችንን ችግሮች አውድ በበለጠ የሚገነዘብ እና በዜጎች ዘንድ ያለው ተዓማኒነት በሂደት እያደገ የሚሄድ ሀገር በቀል የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋም እንዲሆን እንዲሁም የተቋሙን አቅም በሂደት በመገንባት ለምናደርገው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በጎ አስተዋፅዎ እንደሚያደርግ እናምናለን።

    የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በዜጎች ዘንድ ያላቸው አመኔታ እና የሕዝብ ወገንተኝነት ስሜት መገንባት ለምንፈልገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት በሚደረግው ምርመራ ውስጥ ኃላፊነታቸውን የሚመጥን ትብብር እንዲያደርጉ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመው በሚገኙበት ጊዜ ሁሉ ጥፋቱን በቀጥታ የፈፀሙ፣ እንዲፈፀም ትዕዛዝ የሰጡ እና ዜጎችን ከአደጋ የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በማንኛውም መንገድ ያልተወጡ አባሎቻቸው ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ ወስደው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሕዝብ ወገተኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ አንጠይቃለን።

    በዚህ አጋጣሚ በተለይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገራችንን ድንበር እና ሉዓላዊነት ለማስከበር እና በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመቆጣጠር እና መፍትሄ ለመስጠት እየከፈለ ላለው መስዕዋትነት ከፍተኛ አድናቆት እና ክብር እንዳለን ለመግለጽ እንወዳለን። ሠራዊቱ በመደበኛነት ሥልጠና ከወሰደበት የግዳጅ ዓይነት የተለየ እና ሰላማዊ ዜጎች በሚኖሩበት ቦታዎች የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚወስዳቸው ግዳጆች የሚፈልጉትን ተጨማሪ ሥልጠናዎች በአግባቡ ማግኘት እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን። ነገር ግን የሠራዊቱን መስዕዋትነት እና ያለበትን ኃላፊነት በፍፁም በማይመጥን መልኩ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ላይ ጥቃት እንዳደረሱ የተረጋገጡ እና በምንም መልኩ እጃቸው ያለበትን አባላቱ ላይ አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ የሕዝብ አለኝታነቱን እንዲያረጋግጥ አጥብቀን እንጠይቃለን።

    ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ግልጽ እንዳደረግነው፣ ምንም ሕገ መንግሥታዊ መሰረት የሌለው የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀት የዜጎችን ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ እራሱን የአንድ ወገን ጠባቂ እና ተከላካይ አድርጎ በመቁጠር ለዜጎች ደህንነት ስጋት ሆኖ መቀጠሉን የሚያሳዩ ተደጋጋሚ ማስረጃዎች እያየን ነው። ስለዚህም መንግሥት ይህን በየክልሉ የተደራጀ ልዩ ኃይል ወደክልሎቹ መደበኛ የፖሊስ ኃይል አልያም የፌደራል ፖሊስ እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዲቀላቅል አሁንም ደግመን እናሳስባለን።

    የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር በምንም ምክንያት እና በማንኛውም ጊዜ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን እና ዜጎች ላይ ጥፋት የሚያደርሱ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ መገንባት ለምንፈልገው ሥርዓት ያለውን ከፍተኛ ዋጋ በመረዳት ለዜጎች ደህንነት እና ሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያለውን ቁርጠኝነት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለሚያደርገው ልዩ ምርመራ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ እና በምርመራው ውጤት ላይ በመመስረትም አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ ቁርጠኝነቱን በድጋሚ እንዲያረጋግጥ እናሳስባለን።

    የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እና በየጊዜው የሚከሰቱ ጉዳዮችን ሰበብ በማድረግ የሀገር መረጋጋትን እና ሰላምን እንዲሁም የዜጎችን ደህንነት አደጋ ውስጥ ሊጥል ከሚችል የፖለቲካ ትርፍን ዓላማ ካደረገ ማንኛውም እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ አጥብቀን እንጠይቃለን።

    የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት
    ግንቦት 25 ቀን 2012 ዓ.ም

    የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር

    #14811
    Anonymous
    Inactive

    ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መሠረታዊ፣ የምንደግፈው እና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት መብት ነው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    አንኳር

    • ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ሥራዎች የሕዝብ ፈቃድ ያላገኘ አስተዳደር የሕዝብ ፍላጎት ሳይታወቅ በዚህ የሽግግር ወቅት ሊተገብር እንደማይገባ በጽኑ እናምናለን።
    • ገዢው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር/ምደባ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግሥት ሕገ-ወጥ የሆነ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት በመድገም ተመሳሳይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሄ ለመቅረፍ ደግሞ የሚሞክር (የትልቁን ደቡብ ችግር ትንንሽ ደቡቦች በመፍጠር ለመፍታት)፣ ከባለፈው ችግር ትምህርት ያልወሰደ ሂደት ነው።
    • በዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና ጥንቃቄ በሚፈልግ ወቅት በደቡብ ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር የቀረቡ ግልጽ ጥያቄዎችን በፍፁም መመለስ የማይችል፣ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት ዓላማ ያደረገ ጥረት አመፅ እና ብጥብጥ ለማንሳት ለሚሞክሩ ኃይሎች ስንቅ እንደማቀበል የሚቆጠር ነው።
    • ከሕብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ሲገባ ጊዜያዊ እና የሕዝቡን ጥያቄ የማይፈቱ አማራጮችን በማቅረብ የሕዝብን እውነተኛ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ማፈን ተገቢ አይደለም።
    • ገዢው ፓርቲ ከሕግ አግባባ ውጪ በሆነ የመብት ሰጪ እና ነሺነት የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም ኢዜማ አጥብቆ ያሳስባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ምክንያት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዩን እየገፋ ያለው ገዢው ፓርቲ እንደሚሆን በግልፅ መታወቅ አለበት።

    ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መሠረታዊ፣ የምንደግፈው እና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት ጥያቄ ነው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ የአምባገነን ሥርዓቶች መፈራረቅ እና ሥርዓቶቹን አስወግዶ ሕዝብን እውነተኛ የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ከተደረገ የብዙዎችን መስዕዋትነት የጠየቀ ትግል በኋላ ወደእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ለማደርግ የሚያስችል ዕድል ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት አግኝታለች። ለ27 ዓመታት ሀገራችንን ዘውግን መሠረት ባደረገ አምባገነናዊ ፖለቲካዊ ሥርዓት ሲመራ የነበረው አገዛዝ ውስጥ የነበሩ የለውጥ አይቀሬነትን የተረዱ ግለሰቦች ለረጅም ጊዜ ሲደረግ የነበረውን ትግል በተወሰነ ደረጃ አግዘው ስልጣን መያዛቸው የሚታወስ ነው። እነዚህ ኃይሎች ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት ለተፈፀሙ ጥፋቶች ይቅርታ ጠይቀው ሀገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ማድረግ እንዳለባት እንደሚያምኑ እና ይህንንም ሽግግር ጠንካራ መደላድል ላይ ለማስቀመጥ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጠቅሙ የመንግሥት ተቋማት ጠንካራ እና ገለልተኛ ሆነው እንዲዋቀሩ እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማነቆ የሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩን ያጠበቡ ሕጎችን እና አሠራሮችን ለመቀየር (ለማሻሻል) ቃል ገብተው ነበር።

    ሥርዓቱን ለመቀየር ትግል ሲያደርግ እና መስዕዋትነት ሲከፍል የነበረው ሕዝብ እና አብዛኞቹ የፖለቲካ ኃይሎችም ይህንን ዕድል በአጭር ጊዜ የፖለቲካ ስሌት ከማየት ይልቅ ስልጣን ላይ የወጣው ኃይል ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር የሚያግዙ ሥራዎች ለመሥራት ቃል እስከገባ እና ይህንን ቃል የሚጠብቅ እስከሆነ ድረስ በረጅም ጊዜ ቀስ በቀስ የሚገነባ ሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከፉክክር ውጪ በሆነ መልኩ ማገዝ እንደሚያስፈልግ አምኖ ምንም እንኳን ስልጣን የያዙት ከሕዝብ ውክልና ውጪ ቢሆንም እስከ ምርጫው ድረስ ስልጣን ላይ እንዲቆዩ ዕድል መስጠትን መርጧል።
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህም (ኢዜማ)ከተመሠረተ ጀምሮ ለሀገር መረጋጋት እና ሰላም ቅድሚያ በመስጠት የፉክክር ጉዳዮችን ምርጫው ለሚደረግበት ጊዜ አቆይቶ ለሁላችንም የሚበጀውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ከሚፈልጉ አካላት ሁሉ ጋር በትብብር መንፈስ ሲሠራ ቆይቷል። በኢዜማ እምነት ቀጣዩ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ያለው የሽግግር ወቅት በዋነኛነት ሀገርን ለማረጋጋት እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ለማድረግ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ማከናወኛ ነው። ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ሥራዎች የሕዝብ ፈቃድ ያላገኘ አስተዳደር የሕዝብ ፍላጎት ሳይታወቅ በዚህ የሽግግር ወቅት ሊተገብር እንደማይገባ በጽኑ እናምናለን።

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካሳወቀ በኋላ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ባስቀመጠው የአምስት ዓመት ገደብ ውስጥ ምርጫው መደረግ ስላልቻለ ምርጫ ተደርጎ የሕዝብ ውክልና ያለው መንግሥት እስኪኖር ድረስ ሀገራችንን ማን ያስተዳድር የሚል ጥያቄ መነሳቱ ይታወሳል። ይህን ጥያቄ ተከትሎ ከነበሩት አማራጮች መካከል በድንገተኛ እና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ማድረግ ሳይቻል ሲቀር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራሱን እና የአስፈጻሚውን አካል ስልጣን የዜጎችን ደህንነት፣ የሀገር ሉዓላዊነትን እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ከማድረግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ብቻ ገድቦ ምርጫውን እስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ማራዘም የሚያስችለውን ስልጣን ሕገ-መንግሥቱን በማሻሻል እንዲሰጠው ምክረ-ሀሳብ አቅርበን ነበር። ነገር ግን መንግሥት በወሰደው የሕገ-መንግሥት ትርጉም አማራጭ የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ያቀረበለት ምክረ-ሀሳብ ላይ ተመሥርቶ የኢፌዴሪ ፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜም ሆነ የመንግሥትን ስልጣን ያልገደበ ውሳኔ አሳልፏል። የፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜ በወረርሽኙ ምክንያት ክፍት አድርጎ የተወው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወረርሽኙ ባይጠፋም እንኳን በተጨማሪ ጥንቃቄ፣ ጊዜ እና በጀት ምርጫውን ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ (scenario) እንዳለ ለሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ከገለፀ በኋላ እና ምርጫው ያለገደብ እንዲራዘም የመጨረሻ ውሳኔ የሰጡት የምክር ቤቱ አብዛኛዎቹ አባላት «ምርጫው በቶሎ እንዲካሄድ እፈልጋለሁ» ብሎ በይፋ የተናገረው ገዢ ፓርቲ አባል መሆናቸው ውሳኔው የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን ግልፅ ያልሆነ ዓላማ እንዳነገበም እንድንጠራጠር አድርጎናል።

    ይህ የ«ሕገ-መንግሥት ትርጉም» ለመንግሥት ያልተገደበ ስልጣን በሰጠ ማግስት በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ ዞኖች ካነሱት ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ መንግሥት አስጠናሁ ያለውን ክልሉን ወደ አምስት የሚከፍል ምክረ-ሀሳብ ለመተገበር እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ተረድተናል።

    ገዢው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር/ምደባ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግሥት ሕገ-ወጥ የሆነ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት በመድገም ተመሳሳይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሄ ለመቅረፍ ደግሞ የሚሞክር (የትልቁን ደቡብ ችግር ትንንሽ ደቡቦች በመፍጠር ለመፍታት)፣ ከባለፈው ችግር ትምህርት ያልወሰደ ሂደት ነው። ከሁሉ በላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ ጭራሹንም የረሳ ነው።

    ሀገራችን በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ባለው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መያዛቸው የተረጋገጡ እና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ የሚገኝበት፣ ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለመግፋት የተገደድንበት፣ የንግድ እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ የተቀዛቀዘበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። ከዚህ በተጨማሪ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚመጣብንን ጫና ለመቋቋም ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ አንድነት የሚያስፈልግበት እና ጫፍ የረገጠ ፅንፈኛ አመለካከት ያላቸው ኃይሎች ምርጫው መራዘሙን እንደሽፋን በመጠቀም ብጥብጥ ለማስነሳት ቀጠሮ በያዙበት ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ ወቅት ላይ እንገኛለን።

    በዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና ጥንቃቄ በሚፈልግ ወቅት በደቡብ ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር የቀረቡ ግልጽ ጥያቄዎችን በፍፁም መመለስ የማይችል፣ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት ዓላማ ያደረገ ትልቁን ደቡብ ክልል ወደ አነስተኛ ደቡብ ክልሎች ለመቀየር የሚደረግ ጥረት አመፅ እና ብጥብጥ ለማንሳት ለሚሞክሩ ኃይሎች ስንቅ እንደማቀበል የሚቆጠር ነው።

    በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 47 ንዑስ አንቀፅ 2 መሠረት የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ከሁለት አስር ዓመታት በላይ በተግባር የተፈተሸው ሕገ-መንግሥት ያረጋገጠው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት አስከብራለሁ ብሎ ካስቀመጠው ተቃራኒ የሕዝቦች መብት ከመከበር ይልቅ የብሔራዊ አንድነት፣ ሰላም እና የሕዝቦች አብሮ መኖርን አደጋ ላይ መጣሉን ነው። ይህ ሕገ-መንግሥት በስልጣን እስከቆየ ድረስ ሀገራችን ኢትዮጵያ ተረጋግታ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ብሎም ሕዝቦቿ በነፃነት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው የሚከበርበት መንገድ እንደሌለ በተግባር ተፈትኖ ግልጽ ሆኗል። ይልቁንም የተለያዩ አጀንዳ ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ይህንን የሕገ-መንግሥት ክፍተት ተጠቅመው ወደማያባራ እና መጨረሻ ወደሌለው የማንነት፣ የክልልነት እንዲሁም የሀገር እንሁንነት ጥያቄዎችን ሊያስከትል ይችላል።

    ሕገ-መንግሥቱ በራሱ ምሉዕ ካለመሆኑም በተጨማሪ ከፍተኛ የአፈፃፀም ጉድለት አለበት። በስልጣን ላይ የነበረው መንግሥት እራሱ ባረቀቀው ሕገ-መንግሥት ውስጥ ከተቀመጡት አካሄዶች ባፈነገጠ መልኩ የተወሰነ ቡድን ፍላጎትን ለማሟላት እና በፖለቲካ ጥቅም አሳዳጅነት ብሎም ለሕዝብ እና ለሀሳቡ ካለው ንቀት በሕዝብ ቁጥር አነስተኛ የሆኑ አካባቢዎችን በክልልነት ሲያካልል እና እውቅና ሲሰጥ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸውን አካባቢዎች በመጨፍለቅ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልልን መሥርቷል። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት መሠረት አሁን ለፌደሬሽን ምክር ቤት «ክልል እንሁን» የሚል ጥያቄ ያስገቡት ዞኖችን ክልል እንዳይሆኑ ለመከልከል ምንም ሕጋዊም ሆነ የሞራል ምክንያት የለም።

    ከምሥረታው ጀመሮ በብዙሃን ቅቡልነት ያልነበረው የዚህ ክልል አደረጃጀት ክልሉ ከተመሠረተ በኋላ ሲተገበሩ በነበሩ አግላይ ፖሊሲዎች፣ የሀብት እና የስልጣን ከፍፍል ኢ-ፍትሃዊነት እናም የመልካም አስተዳደር እጦት በብዙ የክልሉ ማኅበረሰብ ዘንድ የክልልነት ጥያቄዎች እንዲነሱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። ለዚህም ከሕብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ሲገባ ጊዜያዊ እና የሕዝቡን ጥያቄ የማይፈቱ አማራጮችን በማቅረብ የሕዝብን እውነተኛ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ማፈን ተገቢ አይደለም።

    በኢዜማ እምነት ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ መሠረታዊ፣ የምንደግፈው እና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት ጥያቄ ነው። በእርግጥ አሁን በሥራ ላይ ባለው የፌደራል አወቃቀር መሠረት ዘውግን መሠረት አድርጎ የሚደረግ የአስተዳደር አከላለል ራስን በራስ ከማስተዳደር ይልቅ አካባቢውን ለዘውግ ማንነት የባለቤትነት ካርታ መስጫ መንገድ እንደሆነ ግልጽ ነው። ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በክልል ወይም በዞን ደረጃ ብቻ የሚመለስ አለመሆኑንም በጽኑ እናምናለን። በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን የወለደው የተዛባው ሕገ-መንግስታዊ የመስፈርት አጣብቂኝ፣ በሌብነት የተዘፈቀ ሥርዓት፤ ፍትህ ማጣት፤ የሀብት ክፍፍል ኢ-ፍትሃዊነት፤ እንደልብ ተንቀሳቅሶ ሰርቶ ሀብት በማፍራት የንብረቱ ሕጋዊ ባለቤት የመሆን ብሎም በሰላም የመኖር መሠረታዊ መብት መነፈግ እና የመሳሰሉት አስተዳደራዊ በደሎች ጥርቅም መሆኑን እንረዳለን። አሁን የተጀመረው እንቅስቃሴ ችግሮቹን ማከፋፈል እና ማሰራጨት እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል ስላልሆነ ከበደሎቹም ባሻገር የወደፊት መጪ ስጋቶች ፍንትው ብለው እየታዩ ነው። ወደፊት ሀብት የሚፈስባቸው ከተሞች ባለቤትነት እና በሕዝብ ስም የሚፈፀሙ የበጀት ምዝበራዎች ከስጋቶቹ መካከል ዋነኞቹ ናቸው። በራስ የሚተዳደደር ክልል እና ዞን መሆንን መፈለግ የእነዚህ በደሎች እና መጪ ስጋቶቸ ውጤት መሆኑን በቅጡ እንደሚረዳ ፓርቲ አሁን ለመሄድ እየታሰበበት ያለው መንገድ ለበደሎቹም ሆነ ለስጋቶቹ መፍትሄ እንደማይሆን ጠንቅቀን እናውቃለን።

    እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሕዝቦች በየትኛውም ደረጃ ያለ የስልጣን እርከን ባለቤትነት መረጋገጥ ቁልፍ እርምጃ ነው። ይህ ደግሞ ሊሳካ የሚችለው እያንዳንዱ ዜጋ ከታችኛው የስልጣን እርከን ጀምሮ የሚያሰተዳድሩትን አመራሮች መምረጥ ሲችል ነው። መሰል የዜጎች ሕጋዊ የስልጣን ባለቤትነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በየትኛውም ቦታ የሚካሄድ የትኛውም ዓይነት ዘላቂ ውጤት ያለው ውሳኔ የዜጎችን መሠረታዊ ጥያቄ መልስ መስጠት የሚችል እንዳልሆነ ፍንትው ያለ ሃቅ ነው።

    ዛሬም ቢሆን በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ከሚነሳው፤ እኛም እንደ ሀገራዊ ፓርቲ ካሉን መዋቅሮች ከሚደርሱን መረጃዎች እንደተገነዘብነው ትላንት አፋኝ እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ከሆነው ሥርዓት ጋር ተባባሪ በመሆን በሕዝባቸው ላይ ለደረሰው መከራ ቀዳሚ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ካድሬዎች በውሳኔ ሰጪነት ስልጣን ላይ ናቸው። ለውጥ እንዲመጣ ዋጋ የከፈሉ፣ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንዲሁም ለሕዝባቸው እኩል ተጠቃሚነት የታገሉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በየደረጃው ባሉ የመንግሥት ውሳኔዎች ላይ ሀሳባቸው ሊሰማ ሲገባ ዛሬም በእነዚህ የመንግሥት አካላት ተፅዕኖ እየደረሰባቸው እንደሆነም ጭምር የምንረዳው ሃቅ ነው።

    ገዢው ፓርቲ ይሄን ያልታደሰና የመለወጥም ፍላጎት እያሳየ ባልሆነው የካድሬና የባለሥልጣናት መዋቅሩ በደቡብ ክልል እየቀረበ ያለውን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለማፈን እያደረገ ያለው ሩጫ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄ የማይመልስ ብቻ ሳይሆን ፓርቲው እያሳየ ያለውን የመብት ሰጪ እና ነሺነት ፍላጎትንም የሚያሳይ ነው። ይህ በየግዜው ከለውጡ አጠቃላይ መንፈስ እየራቀ የመጣው የገዢው ፓርቲ ፍላጎት በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍም ጭምር ነው።

    ገዢው ፓርቲ በአንድ በኩል በኮቪድ-19 ወረርሸኝ እና ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ባለው ጫና እግር ከወረች ተይዣለው በማለት ስድሰተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ላልተወሰነ ግዜ እያራዘመ በሌላ በኩል በዚሁ ጭንቅ ጊዜ ዘላቂ ውጤታ ያላቸው ትልልቅ ሥራዎችን ያለሕዝብ ምክክር እና ውሳኔ በራሱ እያከናወነ ይገኛል። ገዢው ፓርቲ ከሕግ አግባባ ውጪ በሆነ የመብት ሰጪ እና ነሺነት የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም ኢዜማ አጥብቆ ያሳስባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ምክንያት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዩን እየገፋ ያለው ገዢው ፓርቲ እንደሚሆን በግልፅ መታወቅ አለበት።

    በደቡብ ክልል የምትኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፥ ኢዜማ ደቡብ ክልል የሕዝቡን ፍላጎት ባሟላ መልኩ እንደገና እንዲዋቀር እንደሚፈልግ እንድትረዱ እና ለምታነሱት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ትክክለኛ እና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አሁን ያለንበት ጊዜ እንደማይፈቅድ እና የእናንተን ፍላጎት የሚያስፈጽሙ በእናንተው የተመረጡ ወኪሎቻችሁ ሳይኖሩ እኔ አውቅልሃለው በሚሉ ካድሬዎች ሊከወን የሚቻል እንዳልሆነ በመረዳት፣ ቀጣዩ ምርጫ ተደርጎ ፍላጎቶቻችሁን የሚያስፈጽሙ ወኪሎቻችሁን እስክትመርጡ እና በጥያቄያችሁ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጋችሁ በሕዝበ-ውሳኔ መወሰን የምትችሉበት ሁኔታ እስኪመቻች በተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና ትዕግስት እንድትጠብቁ አበክረን እንጠይቃለን። ይህንን ተረድታችሁ ለጋራ ሀገራችን መረጋጋት እና ሰላም በማሰብ ጥያቄዎቻችሁን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ለምታሳዩት ትዕግስት ከወዲሁ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የከበረ ምስጋና ያቀርባል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.

    ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ

    #14819
    Anonymous
    Inactive

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕግ ትርጉም ሽፋን ያስተላለፈውን የፖለቲካ ውሳኔ በመቃወም የተግባር እርምጃ ስለመውሰድ
    ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የወጣ የአቋም መግለጫ

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፥ 6ኛው ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በውል ላልታወቀ ዘመን እንዲራዘም እና እድሜያቸው መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚያበቃላቸው ሁሉም ምክር ቤቶች በስልጣናቸው እንዲቀጥሉ መወሰኑን መሠረት አድርጎ፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰፊ ምክክር አድርጓል።

    ከመነሻው፥ ገዢው ፓርቲ ለሀገራችን የሚጠቅም የፖለቲካ አማራጭ ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሙሉ በሙሉ ከሂደቱ እና ከውሳኔው አግልሎ፣ የሥርዓቱ መጠቀሚያ በሆነው የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ እና ለአዲስ አበባ እና ለድሬደዋ ውክልና በነፈገው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ብቻውን የሰጠው ውሳኔ፣ ሀገራችን ያለችበትን ውስብስብ ወቅታዊ ሁኔታ በቅጡ ያላገናዘበ እና በቀጣይም ከባድ አደጋ የሚጋብዝ አካሄድ እንደሆነ ፓርቲያችን ተገንዝቧል።

    ባለፉት ሁለት ዓመታት ዳግም እያቆጠቆጠ የመጣውን የገዢው ፓርቲ አምባገነናዊነት፣ ህሊናቸውን በሸጡ የፍትህ ሥርዓቱ ቀለብተኞች እና ምሁራን ተብዬዎች ዲሞክራሲያዊና ህጋዊ ገጽታ እንዳለው አስመስሎ ለማስቀጠል የተሞከረ ቢሆንም፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የተጀመረው ሂደት የመጨረሻ ውጤት ተረኛ ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት የሚፈጥር ነው። የተወሰነው ውሳኔ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መንግሥት፣ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት እንደታየው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኃይል ስልጣን ላይ እንዲቆይ የሚያስችለውን መደላደል የሚፈጥርለት እርምጃ ነው።

    1. የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔና እንደምታው
      • ወቅታዊው የኮረና ወረርሽኝና የአባይ ጉዳይ የፈጠረው ችግር
        የሕዝባችንን ህልውና ለዘመናት ሲፈትኑ በነበሩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ላይ ወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ የፈጠረው ችግር፣ ምርጫን በጊዜው ለማድረግ የማያስችል ከባድ ሁኔታ መፍጠሩን ፓርቲያችን ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ፣ ሀገራችን ባነሳችው ፍትሃዊ የአባይ ውሃ አጠቃቀም መብት ጋር በተያያዘ ብዙ ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች እንደተደቀኑብን ምስክርነት የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም።እነዚህን መጥፎ አጋጣሚዎች ተጠቅሞ፣ የዜጎችን መብት የማያከብር አምባገነናዊ ሥርዓት ለመፍጠር በገዢው ፓርቲ እየተወሰደ ያለው እርምጃ፣ የሀገራችንን ልማትም ሆነ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በእጅጉ የሚያቀጭጭ እና ወደ ግጭት የሚያመራ፣ አስተዋይነት የጎደለው አካሄድ ነው።
      • የሀገራችንን አንድነትና ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች
        ይህ ሕገ-ወጥ ውሳኔ፣ ዶሮ “ካልበላሁት ጭሬ ላፍሰው” እንዳለችው፣ የሀገራችንን አንድነት እና የሕዝብን ሰላም ለማይፈልጉ ኃይሎች ‘ሠርግና ምላሽ’ በመሆን ለብጥብጥና አለመረጋጋት በሩን ወለል አድርጎ የሚከፍት ነው። ገዢው ፓርቲም የሚቀርቡበትን እውነተኛ የሕዝብ ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ፣ ችግሮችን ውጫዊ በማድረግ የሀገሪቷን የመለወጥ ዕድል የሚያጨልም የጥፋት ጉዞ ላይ ይገኛል። ይህም ሕዝብ ታግሎ የጣላቸውን ያለፉትን ሥርዓቶች ታሪክን ከመድገም ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።
    2. የመፍትሄ ሃሳቦች
      ስለሆነም፣ የመንግሥት ሥልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ በፊት ሁሉንም ኃይሎች ያሳተፈ፣ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክር ጉባዔ /ኮንፈረንስ/ ያስፈልጋል ብሎ ያምናል። በባልደራስ እምነት፣ ኢትዮጵያ በቀጣይነት የሚያስፈልጋት የባለሙያዎች ባለአደራ መንግሥት ነው። ነገር ግን ከዚያ አስቀድሞ ሁሉም ኃይሎች በሀገራቸው ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ ያላቸውን አማራጭ ይዘው በአንድነት ሊመክሩና ሊወስኑ እንደሚገባ ፅኑ እምነታችን ነው።አሁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሰጠው ውሳኔ ግን በሕግ ትርጉም የተላለፈ የፖለቲካ ውሳኔ ነው። ፓርቲያችን ይህን ፖለቲካ ውሳኔ በጽኑ ይቃወማል። ኢትዮጵያን በፍጥነት ወደ ብሔራዊ መግባባት መድረክ ማምጣት ያስፈልጋል። ከዚህ በተቃራኒው የሀገሪቱን መፃኢ ዕድል ገዢው ፓርቲ ሌሎችን የፖለቲካ ኃይሎች አግልሎ በብቸኝነት እወስናለሁ የሚል ከሆነ፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ሕጋዊና ሰላማዊ እርምጃዎችን ይወስዳል።በአጠቃላይ ፓርቲያችን የሀገራችንን ህልውና ለማስቀጠልና ወደ ሀቀኛ ዲሞክራሲ ለመሻገር የሚከተሉትን አቋሞች ይዟል፡-

      • የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔንና ጽንፈኞችን በመቃወም ሕጋዊ ሰላማዊ ሰልፍ ስለማድረግ
        የአንድ ፓርቲ አምባገነናዊ ሥርዓት እንዲያበቃ እና ሕዝቡ መስዋዕትነት የከፈለለት የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ፓርቲያችን ሰላማዊ እና ሕጋዊ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል። በዚህም ሕገ-ወጡን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እና ሀገሪቷን ለማፍረስ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ጽንፈኛ ኃይሎችን በመቃወም፣ የመንግሥት የሥልጣን ዘመን ከሚያበቃበት መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ሕጋዊና ሰላማዊ ሰልፍ እንዲካሄድ ጥሪ የሚያደርግ ይሆናል። የሰላማዊ ሰልፉ ጥሪው የኮረና ወረርሽኙን፣ የሀገሪቱን አንድነትና ሰላም በዋናነት ግምት ውስጥ ያስገባ ይሆናል።
      • የአንድነት ኃይሎችን ትብብርና ቅንጅት በሚመለከት
        ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው፣ እየተጠናከረ ያለውን አምባገነናዊ ሥርዓት በጋራ ለመታገል፣ የአንድነት ኃይሎች በሙሉ ወደ ትብብር እንድንመጣ ፓርቲያችን ልባዊ ጥሪውን ያቀርባል።
      • በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን
        በውጭ ለምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የዚህ ሀገርን የማዳን ትግል ተካፋይ እንድትሆኑ ፓርቲያችን ልባዊ ጥሪውን ያስተላልፋል።
      • የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ
        የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትየአፍሪካ ሕብረት፣ የሀገራችን ወዳጅ የሆናችሁ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አጋር ሀገራት፣ ኢትዮጵያና እና የአፍሪካ ቀንድ ሊገቡበት የሚችለውን ሁሉን አቀፍ ቀውስ በመገንዘብ፣ በገዢው ፓርቲ ላይ ጫና በማድረግ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች አሳታፊ የሚያደርግ ውይይት እንዲደረግ ድጋፍ እንድታደርጉ ፓርቲያችን የአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ
    ሰኔ 9/2012 ዓ.ም. ፣ አዲስ አበባ

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቅርቡ ያጸደቃቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ ባልደራስ ያወጣው የአቋም መግለጫ

    #14947
    Anonymous
    Inactive

    የትግራይ ክልል ምክር ቤት የምክር ቤት ምርጫ እንዲፈጸምለት ለቦርዱ ያቀረበውን ጥያቄ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    የትግራይ ክልል ምክር ቤት “ኮቪድ-19ን እየተከላከለ 6ኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ የወሰነ በመሆኑ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በሚያዘው መሠረት ቦርዱ ውሳኔውን ተቀብሎ ምርጫውን እንዲያስፈጽም፣ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልግ የሰው ኃይል እና ሎጂስቲክስ ዝግጅት እንዲያደርግ እና ውሳኔውን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቀን” ሲል ጥያቄ አቅርቧል።

    በመላ ሀገሪቱ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የሚደረጉ ምርጫዎችን የማስፈጸም ስልጣን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 102 (1) ላይ ተደንግጓል። ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ የቦርዱን ሥልጣን እና ኃላፊነት የወሰነው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 በአንቀጽ 7.1 ይህ የቦርዱ ሥልጣን በሀገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ምርጫዎች እና ሕዝበ ውሳኔዎችን በሙሉ እንደሚሸፍን በተብራራ ሁኔታ ገልጾታል።

    በተጨማሪም የቦርዱን የሥራ ኃላፊነቶች በተለያየ ሁኔታ በዝርዝር በሚገዙት ሕጎች ማለትም በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 እና በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እንደተደነገገው፥ በማንኛውም የምርጫ ዑደት የሚፈጸሙ ዋና ዋና ክንዋኔዎች ማለትም የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣ ለምርጫ የሚወዳደሩ የፓለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠር እና ማስተዳደር፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን መልምሎ ማሰማራት፣ ጣቢያዎችን ማቋቋም፣ ምርጫውን ከተፅዕኖ ነፃ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማስፈጸም በመጨረሻም የውድድሩን ውጤት አረጋግጦ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እና የመሳሰሉት ከማንኛውም የመንግሥት ተቋም በተለየ ለቦርዱ የተሰጠ እና ከማንም አካል ጋር የማይጋራው ሕጋዊ ስልጣኑ ነው።

    ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ላይ እያለ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሀገራችንም በመከሰቱ ምርጫውን ለማስፈጸም ሲያካሂዳቸው የነበሩት ሥራዎች እንደተስተጓጎሉ ይታወቃል። ወረርሽኙ በኢትዮጵያ መከሰቱ እንደተረጋገጠ ሁናቴውን መገምገም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ቦርዱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ካደረገ በኋላ 6ኛውን ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ቀደም ሲል ቦርዱ ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ማካሄድ የማይቻል በመሆኑን ወስኖ ይህንኑ ውሳኔ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። ምክር ቤቱም የቀረበለትን የቦርዱን ውሳኔ ተቀብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት መወሰኑ ይታወሳል።

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ ምርጫውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ባለበት ሁኔታ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ የፌዴራል እና ክልል ምክር ቤቶች የሥልጣን ዘመን እንዲቀጥል እንዲሁም አጠቃላይ ምርጫው ሥልጣን ያላቸው አካላት ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበት ጀምሮ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ እንዲካሄድ ወስኗል።

    ስለሆነም፤

    1. ስድስተኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ እንዲራዘም ምክንያት የሆነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታ እንደገና ተገምግሞ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ እስኪረጋገጥ ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየትኛውም የሀገሪቱ ክልል ምርጫ አያካሂድም።
    2. በተጨማሪም ከላይ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠር እና ማስተዳደር፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣ የምርጫውን ከተፅዕኖ ነፃ እና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ማስፈጸም ስልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳን፣ አፈጻጸምንም ሆነ ተያያዥ ሁኔታን የሚወስነውም ቦርዱ ብቻ ነው። በመሆኑም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ 6ኛውን ዙር የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም ቦርዱ ይህንን ውሳኔውን ተቀብሎ ሊያስፈጽም ይገባል የሚልበት ሕጋዊ መሠረት የለውም።

    በመሆኑም ቦርዱ ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የትግራይ ክልል ምክር ቤት የክልል ምክር ቤት ምርጫን አስመልክቶ የሰጠውን ውሳኔ እንዲያውቅለትም ሆነ ምርጫ እንዲያስፈጽምለት ያቀረበውን ጥያቄ ያልተቀበለው መሆኑን፣ የተጠየቀውን የሰው ኃይል፣ የሎጂስቲክስ እና የቁሳቁስ አቅርቦት የሚሰጥበት የሕግ አግባብ አለመኖሩን ያሳውቃል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

    ምርጫ በኢትዮጵያ ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ― ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች

    የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫ ለማካሄድ ላቀረበው ጥያቄ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    #15248
    Anonymous
    Inactive

    የትግራይ ክልል ለምርጫ የጀመረውን ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳሰበ

    አዲስ አበባ (ኤፍ.ቢ.ሲ) – የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምርጫ ለማካሄድ የጀመረውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እንቅስቃሴ በአፋጣኝ እንዲያቆም ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳሰበ።

    ምክር ቤቱ ለትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት በላከው ደብዳቤ፥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ያቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ የሕገ-መንግሥት ትርጉም እንደተሰጠበት አስታውሷል።

    በዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ሕገ-መንግሥት ምርጫን በወቅቱ ለማካሄድ ከአቅም በላይ የሆነ እክል ሲያጋጥም ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ባለመደንገጉ እና ሕገ-መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ክፍተቱን በሕገ-መንግሥት ትርጉም መሙላት ተገቢ መሆኑን በማመን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲራዘም መወሰኑንም አስታውሷል።

    ይሁንና የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ይህን ውሳኔ ወደጎን በመተው በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ወስኖ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አረጋግጠናል ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት በፌዴራል እና በክልል ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኛነት ማካሄድ የሚችለው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ እንደሆነና፥ በክልል ደረጃ የሚቋቋም ምርጫ ቦርድ አለመኖሩን ጠቅሷል።

    በመሆኑም የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የትግራይ ክልል ምርጫን በሚመለከት የወሰነው ውሳኔና የራሱን የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ጭምር እያካሄደ ያለው እንቅስቃሴ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ያሳለፈውን ውሳኔ ያላከበረ ከመሆም ባሻገር ግልጽ የሆነ የሕገ-መንግሥት ጥሰት ነው ብሏል ምክር በቤቱ በደብዳቤው።

    በተጨማሪም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) መነሻ በማድረግ፥ ማንኛውም ክልል ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 12 መሠረት፥ በአንድ የክልል መንግሥት ተሳትፎ ወይም እውቅና ሕገ-መንግሥቱን ወይም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ በግልጽ መደንገጉን ጠቅሷል።

    በመሆኑም የትግራይ ክልል ምርጫን ለማካሄድ የጀመረው እንቅስቃሴ ሕገ-መንግሥቱን የሚቃረን፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና የኢትዮጵያን የፌዴራል ሥርዓት የሚጎዳ አካሄድ ነው ብሎታል።

    በተጨማሪም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 50 (8) መሠረት፥ ለፌደራል መንግሥት የተሰጠው ስልጣን በክልሎች መከበር ያለበት መሆኑና የሕገ-መንግሥት የበላይነት በሚደነግገው የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9 (1) መሠረት፥ ማንኛውም ሕግ ወይም የመንግሥት አካል ውሳኔ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ታውቆ የክልሉ መንግሥት ሕገ-መንግሥ ቱንና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲያከብር እና የጀመረውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እንቅስቃሴ በአፋጣኝ እንዲያቆም ሲል ምክር ቤቱ አሳስቧል።

    ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት

    #17545
    Anonymous
    Inactive

    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚያደርገውን ዝግጅት አስመልክቶ የጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱ፥ እንዲሁም የተለያዩ ተግባራትን ለማከናውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከዚህም መካከል የምርጫ ጸጥታን ማረጋገጥ እንዲሁም የምርጫ ክልል እና የዞን ቢሮዎችን ለመክፈት መሥራት ይገኙበታል። በዚህም መሠረት ቦርዱ በተለያዩ ወቅቶች ከክልል መስተዳድር ኃላፊዎች ጋር ውይይቶችን ያከናወነ ሲሆን፥ በእነዚህ ውይይቶች ላይ የምርጫ ኦፕሬሽን መዋቅር እና የክልል መስተዳድሮች የሚጠበቁ ሚናዎችን በዝርዝር አቅርቧል። በውይይቶቹ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ቦርዱ የሚከተሉትን ዋና ዋና ትብብሮች ከክልል መንግሥታት የጠየቀ ሲሆን እነሱም በዋናነት፦

    1. የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር – 33 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 3 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    2. የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል መንግሥት – 22 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 3 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    3. ድሬደዋ ከተማ መስተዳድር – 47 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 1 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    4. ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት –72 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 11 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    5. ጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 14 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 3 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    6. ደ/ብ/ብ/ህ ክልላዊ መንግሥት – 113 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 16 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    7. ሃረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 3 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 1 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    8. አፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት –32 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 5 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    9. አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 138 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 12 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    10. ሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት –19 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 1 ዞን ማስተባበሪያ ቢሮ እና የስልጠና ቦታዎች
    11. ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 179 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 20 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች

    ናቸው። ቦርዱም በጥያቄው ለክልሎች ለዕቅድ እና ለአፈፃፀም ያመቻቸው ዘንድ የምርጫ ክልሎች ዝርዝር እና ቢሯቸው የሚቋቋምባቸው ከተሞች ዝርዝር፣ የዞን ማስተባበሪዎች ዝርዝር እና ቢሯቸው የሚቋቋምባቸው ከተሞች ዝርዝር እንዲሁም ቦርዱ ያወጣውን ረቂቅ የምርጫ ሰሌዳ ቅጂ (copy) አብሮ አቅርቧል።

    ይሁንና ለክልሎች ይህንኑ ለቢሮ መከፈት የሚያስፈልግ ዝግጅት በደብዳቤ በመጠየቅ ለጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲያሳውቁ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም፥ እስከአሁን ድረስ ይህንን ዝግጅት አስመልክቶ ምላሽ ያቀረበ የክልል መስተዳድር የለም። በመሆኑም በደብዳቤ የተገለጹት አስፈላጊ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ለመክፈት የሚያስፈልጉ ትብብሮች ለምርጫው ሂደት አስፈላጊነታቸውን በመገንዘብ ክልሎች ትብብራቸውን እንዲፋጥኑ እንዲሁም በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 161 የተቀመጠውን የመተባበር ግዴታቸውን እንዲወጡ እናሳስባለን።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም.

    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    #18021
    Anonymous
    Inactive

    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የአመራሮች ክፍፍልን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቋቋመበት አዋጅ 1133/2011 በምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በሥነ ምግባር አዋጅ 1162/2011 በተሰጠው ስልጣን መሠረት ፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ እና ቁጥጥር የሚያደርግ ተቋም ነው። በዚህም መሠረት በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ አመራሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ሕጋዊ እና ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል።

    በዚህም መሠረት፦

    1. የፓርቲው የተወሰኑ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ነሐሴ 01 ቀን 2012 ዓ.ም. በተጻፈ እና በድርጅቱ ምክትል ሊቀ-መንበር በተፈረመ ደብዳቤ የድርጅቱን ሊቀ-መንበር መታገዳቸውን ለቦርዱ አሳውቀው እንደነበር፤ ከዚህም በተጨማሪ የድርጅቱ አመራር ላይ ተከታታይ አቤቱታዎች አስገብተው እንደነበር ይታወሳል። በሌላ በኩል የድርጅቱ ሊቀ-መንበር መስከረም 02 ቀን 2013 ዓ.ም. ድርጅቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ አድርጎ የፓርቲውን ምክትል ሊቀ-መንበር፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እስከሚቀጥለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ድረስ ከኃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ እንደወሰነ ለቦርዱ አሳውቀዋል።
    2. ፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል አለመግባባት ሲከሰት እና ለቦርዱ አቤቱታ ሲቀርብለት በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ 6 መሠረት ጉዳዩን ተመልክቶ የውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርብ የባለሙያዎች ጉባዔ ለማቋቋም በተሰጠው ስልጣን መሠረት በማድረግ የሁለቱንም ቡድኖች ደብዳቤዎች እና አቤቱታዎች፣ እንዲሁም የውስጥ ሕጎች የሚያይ የባለሞያዎች ኮሚቴ ለማቋቋም ውሳኔ አሳልፎ እንደነበርም ይታወሳል። በዚህም መሠረት በእነ አቶ አራርሶ በኩል ባለሞያ ቢመድቡም፥ በእነ አቶ ዳውድ በኩል ባለሞያ ለመመደብ ፍቃደኛ ካለመሆናቸውም በላይ የፓርቲው የውስጥ ደንብ መሠረት መጠናቀቅ ያለበት ጉዳይ ነው በማለት መልስ በመስጠታቸው የባለሙያዎች ጉባዔ ማቋቋም ሳይሳካ ቀርቷል።
    3. በኦነግ አመራር መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተደረገው የመጀመሪያው የቦርዱ ጥረት ባለመሳካቱ ጉዳዩን ከባለሞያዎች ጉባዔ ይልቅ በራሱ ሊያየው ተገድዷል። በዚህም መሠረት ከሁለቱም ወገን የገቡትን እገዳዎች በማየት እና የገቡ ሰነዶችን በመመርመር፥ እንዲሁም ከሁለቱም ቡድን አመራሮች ጋር እንዲሁም ከሥነ ሥርዓት እና ቁጥጥር ኮሚቴ አመራር አባላት ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። በውይይቱም ወቅት ፓርቲው አመራር ቀውስ ውስጥ እንደገባ፣ ለአባላቱ አመራር መስጠት የሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ፣ በተለይም ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች ያቀረቧቸው እገዳዎች ሕጋዊ እንዳልሆኑ ቦርዱ ወስኗል። በዚህም መሠረት የሁለቱም ወገን እገዳ የቀረበባቸው አባላት በነበራችው ሕጋዊ ኃላፊነት ላይ እንደሚቆዩ ወሰነ።

    በተጨማሪም ሁለቱም አካላት ሕጋዊ ሂደቱ የተሟላ ሰነድ ባለማቅረባቸው፣ ፓርቲው ያለበት የአመራር ቀውስ ለመፍታት አለመቻላቸውን በመረዳት ቦርዱ የአመራር መከፋፈሉን  ጠቅላላ ጉባዔ በማከናወን የፓርቲው አባላት መሪዎቻቸውን እንዲመርጡ ታኅሣሥ 08 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ከመወሰኑም በተጨማሪ፥ የጠቅላላ ጉባዔውን ለማመቻቸት ኃላፊነቱንም እንደሚወስድ አሳውቆ እንደነበር ይታወሳል።

    1. ከላይ በተጠቀሰው ውሳኔ መሠረት ለሁለቱም አመራር ቡድኖች ቦርዱ ውሳኔ በደብዳቤ ደርሷቸው የመጀመሪያውን ውይይት በቦርዱ አመቻችነት በጋራ ለማከናወን የመጀመሪያውን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ጥሪ ቢደረግላቸውም በድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ የሚመራው የሥራ አስፈጻሚ ቡድን ቦርዱ በጠራው ስብሰባ ላይ ሲገኝ፥ በአቶ ዳውድ የሚመራው ቡድን ግን “ቦርዱ ይህንን የማመቻቸት ሕጋዊ ሚና የለውም” በማለት በውይይቱ ላይ አልገኝም በማለታቸው በቦርዱ የተደረገው ጥረት አሁንም ሊሳካ አልቻለም።
    2. ይህ ሂደት በዚህ ላይ እንዳለ ሁለቱም ወገኖች የተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ሚመለከቱ ማመልከቻዎችን ለቦርዱ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።
    3. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው የቦርድ አመራር አባላት ስብሰባ በኦነግ ሥራ አስፈጻሚ መከፈልን አስመልክቶ እስከአሁን የተደረጉ ጥረቶችን እና ለመፍታት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በዝርዝር መርምሯል። በዚህም መሠረት ቦርዱ እጁ ላይ ባሉት የሕግ እና የአስተዳደር መሣሪያዎች በመጠቀም ሊያግዝ የሚችልበት ተጨማሪ አሠራር አለመኖሩን ተረድቷል።
    4. በዚህም መሠረት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት፣ የተለያዩ የድርጅቱ መዋቅሮች እና አመራሮች ለችግሩ መፍቻ ሊሆን የሚችለውን ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርጉ ቦርዱ ማሳሰብ እንደሚገባው ወስኗል። በመሆኑም ፓርቲው በመሀከሉ ያለውን አለመግባባት በሥራ አስፈጻሚ አመራሮቹ ሊፈታ ባለመቻሉ የተለያዩ የድርጅቱ መዋቅሮች እና አባላት አውቀው ጠቅላላ ጉባዔ እነዲከናወን የሚያደርጉባቸውን ማንኛውንም መንገዶች እንዲጠቀሙ ቦርዱ በጥብቅ ያሳስባል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም.

    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የአመራሮች ክፍፍልን አስመልክቶ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    #18107
    Anonymous
    Inactive

    በብልፅግና ሰልፎች ላይ ፓርቲዎች የሚመሩባቸው ሥነ ምግባሮች ተጥሰዋል
    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ለብልፅግና ፓርቲ ድጋፍ ለማሳየት የተለያዩ ሰልፎች መካሄዳቸው ይታወቃል። እነዚህን ሰልፎች ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) “ፓርቲያችን ያለአግባብ ተወንጅሏል፤ ይህም ፓርቲዎች የፈረሙትን የጋራ የሥነ ምግባር ደንብ የጣሰ ነው” ሲል አቤቱታውን ለቦርዱ አቅርቧል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ከአቤቱታው በተጨማሪ በዕለቱ የተደረጉ የተለያዩ ሰልፎችን በሚዲያ ክትትል ክፍሉ አማካኝነት ክትትል በማድረግ በአሜሪካ ድምጽ፣ በዋልታ፣ በፋና፣ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ እንዲሁም በእነዚሁ ሚዲያዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች በቀጥታ የተላለፉ መልእክቶችን በማየት፦

    • ሠልፎቹ በዋልታ ቴሌቪዥን እና በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በቀጥታ መተላለፋቸውን እንዲሁም የመንግሥት አመራር አካላት፣ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች እና ደጋፊዎች መሳተፋቸውን ተረድቷል፤
    • ከሚዲያዎቹ በቀጥታ ከመተላለፉም በተጨማሪ የተለያዩ የመንግሥት አመራር አባላት በሰልፎቹ ላይ ያደረጓቸውን ንግግሮች ተመልክቷል፤
    • በሰልፎቹ የተለያዩ መፈክሮች፣ በተወሰኑ የመንግሥት የዞን፣ የከተማ አስተዳድር አመራር አካላት እና ብልፅግናና ፓርቲ ኃላፊዎች ንግግሮች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ እና የምርጫ ምልክቶቻቸውን የመረጡ ፓርቲዎች በአሉታዊ መልኩ መነሳታቸውን ተገንዝቧል።

    እነዚህ ሰልፎች ላይ የተነሱ ንግግሮች እና መፈክሮች በሕጋዊነት ተመዝግበው፣ በፖለቲካ ፓርቲነት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ማለትም አማራ ብሔራዊ ንቅናቄባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በአመፃ ተግባር በመሳተፍ ከምርጫ ቦርድ ከተሰረዘው ጁንታ በማለት ከሚጠሩ ህወሓት ፓርቲ ጋር አንድ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው ብሎ በመፈረጅ እና ሕገ ወጥ ናቸው በማለት የምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ሕግ 1162/2011 ላይ ያሉ ድንጋጌዎችን ጥሰዋል።

    ቦርዱ ሰልፎቹ ላይ የተንጸባረቁት ንግግሮች እና መፈክሮች በአዋጁ አንቀጽ 132 ንዑስ 2(ሀ) ላይ የተጠቀሰውን ስም የሚያጠፋ ንግግርን ክልከላ ድንጋጌ አንዲሁም በዚሁ ሕግ አንቀጽ 143 (2) ላይ የተጠቀሰውን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳያሰራጩ ስጋት እና ፍርሀት የመፍጠር የሥነ ምግባር ጥሰት ፈጽሞ አግኝቶታል። ከዚህም በተጨማሪ ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ በጋራ ተስማምተው በፈረሙት የቃልኪዳን ሰነድ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የተጠቀሰውን “የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችል የዓላማ፣ የሃሳብ ወይም የዘር ልዩነትን፣ ወይም ሌላ ምክንያት መሠረት በማድረግ የሌሎች ፓርቲዎችን መብቶች የሚፃረሩ ወይም የሚያጣብቡ ድርጊቶችን ከመፈፀም የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው” የሚለውን አንቀጽ የሚጥስ ተግባር ነው።

    ይህ ተግባር በተለይ ቦርዱ የመጨረሻ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ የምርጫ ተግባራት በይፋ መፈጸም ከጀመረ በኋላ በምንገኝበት የምርጫ ወቅት መከሰቱ በምርጫ ውድድር ላይ ፓርቲዎች በእኩልነት የመወዳደር መብታቸውን ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ ቦርዱን በእጅጉ አሳስቦታል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየደረጃው ያሉ የገዥው ፓርቲ አመራሮች እና በየአስተዳደር እርከኑ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች በተመሳሳይ ተግባራት ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ ያሳውቃል።

    ለወደፊትም በተመሳሳይ በምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ሕግ 1162/2011 እና ተያያዥ መመሪያዎች መሠረት የፓርቲዎች የቅስቀሳ የንግግር እና ሌሎች ለሕዝብ የሚያሰራጯቸውን መልዕክቶች ላይ ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን እስከእጩ መሠረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያሳውቃል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም.

    በብልፅግና ሰልፎች ላይ ፓርቲዎች የሚመሩባቸው ሥነ ምግባሮች ተጥሰዋል ― ምርጫ ቦርድ

    #18367
    Semonegna
    Keymaster

    የምርጫ ክርክር ለማዘጋጀት ፍላጎት ላላቸው የሲቪል ማኅበራት እና ሚዲያዎች የተደረገ ጥሪ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል፤ በዚህም መሠረት የተወሰኑ ተቋማት በተወዳዳሪዎች መካከል የምርጫ ክርክር ለማከናወን ከቦርዱ ፍቃድና አቅጣጫ ለማግኘት ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

    ይህንን፥ እንዲሁም ሌሎች ልምዶችን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባ ተጠናቆ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከታወቁ በኋላ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክር ሂደትን ለማስተባበር ይፈልጋል። በመሆኑም ከዚህ በፊት ጥያቄ/ ማብራሪያ ያስገባችሁም ሆነ በዚሁ ጉዳይ ላይ ፍላጎት ያላችሁ መንግሥታዊ ያልሆናችሁ ተቋማት እና ሚዲያዎች በተናጠል ወይም በጋራ የምርጫ ክርክር ዝርዝር የፍላጎት መግለጫ ወረቀት (expression of interest) ለቦርዱ እንድታቀርቡ ጥሪ ያቀርባል።

    የፍላጎት መግለጫ ማካተት የሚገባቸው ዋና ዋና ሃሳቦች

    ማንኛውም የምርጫ ክርክር ለማከናወን የሚያስብ ተቋም የሚመለከቱትን ዋና ዋና ነገሮችን ያሟላ የፍላጎት መግለጫ ሊያቀርብ ይገባል።

    • ሊያከናውኑት ያቀዱት የምርጫ ክርክር ግልጽ ዓላማ፣
    • ሊያከናውኑት ያቀዱት ክርክሩ የሚከናወንበት መንገድ (mode of engagement)፣
    • ሊያከናውኑት ያቀዱት የክርክሩ ሥነ-ምግባር ደንብ (code of conduct)፣
    • የክርክሩ ቁጥር ብዛት፣ የተሳታፊዎች ሁኔታ፣ ለሕዝብ የሚቀርብበት ሁኔታ፣
    • የአከራካሪ አመራረጥ ሂደት፣ መስፈርት እና መመዘኛ፣
    • ክርክሩ ለሕዝብ የሚቀርብበት መንገድ፣
    • በጀት እና የገንዘብ ምንጭ፣
    • ክርክሩን የሚከናወንባቸው ቋንቋዎች እና የመሳሰሉት፣

    ከላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ጉዳዮች በተጨማሪ ምክረ-ሃሳብ የሚያስገቡ ተቋማት አስፈላጊ ነው የሚሉትን ዝርዝር ዕቅድ በምክረ-ሃሳባቸው ውስጥ አካተው ማቅረብ ይችላሉ። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ክርክሩን በማመቻቸት ብሔራዊ ክርክር መከናወንን ከማመቻቸት በተጨማሪ ለክርክር ዝግጅት የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ አያደርግም።

    የፍላጎት መግለጫ ወረቀት እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ (በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ) በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት በግንባር ወይም በ media@nebe.org.et ኢ-ሜይል አድራሻ ሊቀርብ እንደሚችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

    ከምርጫ ቦርድ መግለጫ ሳንወጣ፥ ቦርዱ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የእጩዎች ምዝገባን እያከናወነ ባለበት በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ ዙር የእጩ ምዝገባ የሚከናውንባቸው ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ማለትም፦

    • የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር
    • የድሬደዋ ከተማ መስተዳድር
    • የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል
    • የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል
    • የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል
    • ሃሪሪ ብሔራዊ ክልል ለእጩዎች ምዝገባ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሠረት የካቲት 08- 21 ድረስ እንደሚከናወን ማሳወቁ ይታወቃል።

    ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ሂደትን በመገምገም የምርጫ ክልል ቢሮዎች ለመከፈት በመዘግየታቸው፥ የትራንስፓርት መጓተት የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ላይ የምዝገባ ቀንን በማራዘሙ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች እጩዎችን ለመመዝገብ ችግር ስላጋጠመን ይራዘምልን ብለው ጠይቀዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከላይ የተጠቀሱትን አሳማኝ ምክንያቶች በማየት የመጀመሪያ ዙር ምዝገባ በጀመሩት ከላይ በተጠቀሱት ክልሎች/የከተማ መስተዳድሮች ላይ የሚካሄደው የእጩዎች ምዝገባ ለ4 ቀናት ያህል እስከ የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን አስታወቋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

    የምርጫ ክርክር

    #19894
    Anonymous
    Inactive

    “በዚህ ሀገራዊ ምርጫ የፈጠርነው አሸናፊና ተሸናፊን ሳይሆን፣ ጠያቂና ተጠያቂ ያላበት የዲሞክራሲ ሥርዓትን ነው። በዚህ ደግሞ ያሸነፉት በምርጫው የተሳተፉት ሁሉም አካላት ናቸው።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስድስተኛው የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ውጤትን ያስተላለፉት መልዕክት

    የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት፥

    ላለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመናት፣ የሀገራችን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በነጻ ፈቃዱ የመረጠው መንግሥት እንዲኖረው ብዙ ሙከራዎች ሲደረጉ ቢቆዩም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሲሰናከሉ ነበር። በሂደቱ አያሌ ተማሪዎችና ወጣቶች፣ ገበሬዎችና የቤት እመቤቶች፣ ምሁራንና መለዮ ለባሾች፣ መላው የሀገራችን ሕዝብ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ካለፈ ልምዳችንና ባልተሳኩ ጉዞዎች ጠባሳ ሰበብ፣ የአሁኑም ምርጫ ዴሞክራሲያዊነቱ ተጠብቆ ባይጠናቀቅስ በሚል ስጋት፣ ያለፉትን ወራት እንደ ሀገር በፍርሃት ተወጥረን መክረማችን ሊካድ አይችልም። ኢትጵያውያን ግን ጨዋ ብቻ ሳይሆኑ አርቆ አሳቢ መሆናቸውን ዛሬም አስመስክረዋል። የተሰጋውን ሳይሆን የሚፈልጉትን ማድረግ እንደሚችሉ በግብር አሳይተዋል። ዝናብና ፀሐይ ሳይገድባቸው፣ በረጃጅም ሰልፎች ሳይሰለቹ፣ እስከ እኩለ ሌሊት ታግሰው ፍላጎታቸውን በካርዳቸው ገልጸዋል። እንደ እኛ እምነትም በዚህ ምርጫ አሸናፊ የሆነው ሕዝባችን ነው። ከሕዝባችን በመቀጠል፣ በብዙ ውሱንነቶች ውስጥ አልፈው በዲሞክራሲና በሕዝብ ድምፅ ላይ ባላቸው ጽኑ እምነት፣ ሀሳብና ፖሊሲያቸውን ለሕዝብ አቅርበው ብርቱ ውድድር ያደረጉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ድል አድራጊዎች ናቸው።

    ይህንን ምርጫ ልዩና ታሪካዊ የሚያደርጉት ብዙ ጉዳዮች አሉ። በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተጽዕኖዎች በተላቀቀ የምርጫ ቦርድ ዳኝነት ያደረግነው ምርጫ መሆኑ አንደኛው ነው። የምርጫ ቦርድ ዳኝነት እንዲሳካ ደግሞ ቁጥራቸው የበዙ የግልና የመንግሥት ሚዲያዎች፣ የሲቪል ተቋማት፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ፍርድ ቤቶችና ሌሎችም ተቋማት በግልጽ የተከታተሉት መሆኑ ሂደቱን ከመቼም ጊዜ በላይ ተአማኒና ዲሞክራሲያዊነቱ የተጠበቀ ምርጫ ያደርገዋል። ምርጫው ዴሞክራሲን የመትከል ግባችንን አንድ እርምጃ ያስኬደ በመሆኑ፣ ፓርቲያችን ከምንም በላይ ቀዳሚ ድሉ አድርጎ ይቆጥረዋል። በታሪካዊው ምርጫ ተሳታፊ መሆን በራሱ የሚፈጥረው ደስታ እንዳለ ሆኖ፣ ፓርቲያችን በሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ ሀገር ለማስተዳደር መመረጡ አስደስቶናል። በውጤቱም ከአሸናፊነት ይልቅ ኃላፊነት፣ ከድል አድራጊነት ይልቅ ታላቅ የሆነ ሀገራዊ አደራ እንዲያድርብን አድርጎናል።

    መንግሥት የሚመሠረተው በሕዝብ በተመረጡ ፓርቲዎች ቢሆንም ሀገርን መምራትና ማስተዳደር ግን ለተመረጡ ፓርቲዎችና መሪዎች ብቻ የሚተው አይደለም። ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸውም እስከሚቀጥለው ምርጫ በመንግስት አስተዳድርና ሕዝብን በማገልገል ሂደት ውስጥ ሚናቸው ሰፊ ሊሆን እንደሚገባ ለማስታወስ እወዳለሁ። በቀጣይ ወራት ብልጽግና በሚመሠርተው መንግሥት ውስጥ በአስፈጻሚው አካልም ሆነ በፍርድ ቤቶች፣ በሌሎችም የፌደራልና የክልል ተቋማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው፣ በዘንድሮው ምርጫ በኃላፊነትና በብቃት የተወዳደሩ የሕዝብ አለኝቶችን ከዚህ በፊት ካደረግነው በእጅጉ ከፍ ባለና አዎንታዊ ለውጥ በሚፈጥር መልኩ እንደምናካትታቸው ለመግለጽ እወዳለሁ። በተጨማሪም እስከሚቀጥለው ምርጫ የበለጠ ተጠናክረውና ተቋማዊ አቅማቸው ደርጅቶ ብርቱ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም። በዚህ ምርጫ የፈጠርነው አሸናፊና ተሸናፊን ሳይሆን፣ ጠያቂና ተጠያቂ ያላበት የዲሞክራሲ ሥርዓትን ነው። በዚህ ደግሞ ያሸነፉት በምርጫው የተሳተፉት ሁሉም አካላት ናቸው።

    ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፥

    በምርጫ ካርዳችሁ ስትመርጡን በዕቅድና በፖሊሲ የያዝናቸውን የብልጽግና ግቦች እንድናሳካ የድፍረትና የጥንካሬ ስንቅ እንደሚያቀብለን ሁሉ፣ እኛና እናንተን ያስተሳሰረው ቃል ኪዳን ተጠብቆ እንዲቆይ ነገሮች አልጋ በአልጋ እንደማይሆኑን እንገነዘባለን። ቢሆንም ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትከሻችንን አስፍተን፣ ኢትዮጵያን ከሚወዱ አካላት ጋር ሁሉ በትብብር ዐቅማችን አማጥጠን ለመሥራት ቆርጠን እንደተነሣን ሳበስራችሁ ደስ እያለኝ ነው። በቀጣይ ዓመታት ሀገራችን በእውነትም በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ከፍ የምትልበት ዘመን ይሆናል። ይህ እንዲሳካ የሐሳብና የሞራል ስንቅ እንደምታቀብሉን፣ መንገድ ስንስት እንደምትመልሱን፣ ስናጠፋም እንደምታርሙን ተስፋ በማድረግ ነው።

    በሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን እንዲሆን በቀጣዩ አምስት ዓመት ፈር ጠራጊ እንሆናለን የምንለው፣ በዙሪያችን ባሉና ብልጽግና በሚቀላጠፍባቸው አራት ማዕዘኖች መሐል ቆመን ነው። የመጀመሪያው ማዕዘናችን የመሠረተ ልማት ግንባታ ሲሆን፥ ሀገራችን እንድትበለጽግ በኢኮኖሚውም ሆነ በማኅበራዊና ፖለቲካ ዘርፎች ዘላቂ መሠረት የሚሆኑ፣ በፍጥነት የሚጠናቀቁ፣ ጥራታቸው የተጠበቁ፣ ከብክነት ነጻ የሆኑ እና የምንፈጥራቸውን ተቋማት መሸከም የሚችሉ ትውልድ ተሻጋሪ መሠረተ ልማቶችን መገንባታችንን እንቀጥላለን። ጥቂትም ቢሆኑ ባለፉት 3 ዓመታት አመርቂ ሥራዎችን ለመሥራታችን ምስክሮቹ እናንተው ናችሁ።

    ሁለተኛው ማዕዘናችን የተቋማት ግንባታ ሲሆን፣ በጥቂት ግለሰቦችና ነጠላ ተቋማት ላይ ከማተኮር ባለፈ ሀገራችንን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆሙ ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጉናል። ዘመን ተሻጋሪ ሥርዓት ለማጽናት የሚስችሉ ገለልተኛና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚያገለግሉ ተቋማትን መገንባት ላይ ትኩረት ይደረጋል። ይሄ ማሕቀፍ ከፌደራል እስከ ክልል የሚገኙ ተቋማትን የሚያካትት ይሆናል።

    በሦስተኛ ደረጃ እንደ ሀገር የሚያስተሳስሩን የጋራ አመለካከቶችና የጋራ ትርክቶች ላይ ትኩረት ሰጥተን ልንሠራባቸው ይገባል። እርስ በእርስ የሚቃረኑና የሚጠፋፉ ትርክቶች ምን ያህል ለጠላቶቻችን ተመችቷቸው እኛን ደካማ እንዳደረገን ያሳለፍናቸው ዓመታት ሕያው ምስክሮች ናቸው። ስለዚህ ክፍተቶቻችንን በሚደፍን መልኩ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር አጠንክረው በሚያቆሙን እሴቶች ላይ የተመሰረተ፣ ገዢና ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርግ ትርክት ለመገንባት ጠንክረን እንሠራለን።

    በአራተኛ ደረጃ የሞራል ልዕልናና ግብረገባዊነት ተመጣጣኝ ትኩረት አግኝተው እስካልተሠራባቸው ድረስ በሀገራችን ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ቁጥር እየቀነሰ፣ በተቃራኒው ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች እየተስፋፉ እንዲመጡ በር ይከፍታል። ይኼንን ችግር የመቅረፍ ኃላፊነት መንግሥትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ላይ ብቻ የሚጣል ሳይሆን፣ ከግልና ከቤተሰብ ጀምሮ የሚሠራ ሥራ ነው። ሁሉም አካላት ተረባርቦ ሀገርና ትውልዱን እያቆሸሹ ያሉ መጥፎ ተግባሮችን ጠርጎ ሊጥላቸው ይገባል። በቀጣይ ዓመታት በሞራል ንጽህና የተገነቡ ተቋማትንና መሪዎችን አንጥረን የምናወጣበት እንዲሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

    ውድ የሀገሬ ዜጎች፥

    ባለፉት ሦስት ዓመታት በከፍተኛ ጥንቃቄ የቀረጽነው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለተግባራዊነቱ በጋራ ከተጋን ያለ ጥርጥር ቀጣዩቹ ዓመታት ለሀገራችን ብልጽግና እንደ ወሳኝ የመታጠፊያ ኩርባ ይሆናል። ዕምቅ ዐቅሞቻችን ምንድን ናቸው? ምን ዓይነት የመበልጸግ ዕድል እጃችን ላይ አለ? ምን ብናደርግ ኢኮኖሚያችን መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣል? የሚሉትን በሚገባ ፈትሸን ያረቀቅነው ዕቅድ ነው።

    በሀገራችን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። በፍጥነት የምግብ ፍላጎታችንን በማሟላት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከውጭ የምግብ ድጎማ መላቀቅ አለብን። ምግብ ለእኛ ቅንጦት መሆን አይገባም። ጠግቦ መብላት ቅንጦት የሆነበት ሕዝባችንን መርጦ መብላት እንዲጀምር ለማድረግ ቆርጠን መነሳት አለብን። በብዝኃ ዕጽዋትና በብዝኃ እንስሳት የምትታወቅ ሀገራችን የእንስሳት ተዋጽዖና ፍራፍሬዎች ለገበታችን ከቅንጦትነት ወደ አዘቦትነት መለወጥ አለባቸው። ዶሮና ዕንቁላል፣ ወተትና ቅቤ፣ ተርፎን ለገበያ የምናቀርባቸው እንጂ ለዓመት በዓል አይተናቸው የሚሰወሩ የሩቅ እንግዳ መሆናቸው ሊያከትም ይገባል።

    እዚህ ጋር አንድ መታወቅ ያለበት ሀቅ አለ። መንግስትና ሕዝብ እጅና ጓንት ሆነው እስካልሠሩ ድረስ ሕልማችን ይሳካል ማለት ዘበት ነው። በቀጣይ 5 ዓመታት ተባብረን በተለይ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ ጠንክረን መስራት አለብን። ከዚህ ቀደም ጀምረናቸው ውጤት እያመጡ ያሉ ተግባራት አሉ። የበጋ ሰብሎችና ፍራፍሬዎች ላይ ለውጥ ለማምጣት ከተጀመሩ አነስተኛ መስኖዎች ባለፈ፣ ዝናብ አጠርነት ለመዋጋት በቴክኖሎጂ አማካኝነት ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ልምምዳችን እያደገ ይገኛል። በቅርቡም ምርትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመን ችግሮቻችንን ወደ ዕድል መቀየር ጀምረናል።

    አየር ንብረታችንን የሚያስተካክለውና የብዝኃ ዕጽዋትና የብዝኃ እንስሳት ሀብታችንን በእጅጉ ያሳድጋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብራችን እንዲሁ ተጠቃሽ ነው። በቁጥር ግንባር ቀደም ያደረጉን የቀንድ ከብቶቻችን ከመቀንጨር ወጥተው ምርታማ እንዲሆኑ ያደርጋል። ወደየጎረቤት ሀገሩ የሸሹ የዱር አራዊትም ተመልሰው፣ ከታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ጋር የተዋደደ ተፈጥሮአዊ መስህብ በመሆን የቱሪስት ፍስትን እንዲጨምርና ኢኮኖሚያችን መስፈንጠር እንዲችል መደላድል ይሆናል ብዬ አምናለሁ።

    የሀገራችን ሕዝብ ሆይ፥

    ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረታችንን ሰቅዘው ከያዙት ጉዳዮች መካከል ሌላኛው የሕዳሴ ግድብን የተመለከተ ጉዳይ ነው። የዴሞክራሲ ጥያቄን አንድ ምዕራፍ ለማሳደግ የምርጫችን መሳካት ወሳኝ እንደነበረው ሁሉ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግራችንን ለመቅረፍና ለዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መቀላጠፍ ጉልህ አስተዋጽዖ ከሚያበረክቱ ፕሮጀክቶቻችን መካከል አንዱና ወሳኙ የሕዳሴ ግድብ ግንባታችን እንደሆነ ይታወቃል።

    የሕዳሴ ግድብ አጀንዳ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከግድብም፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭነትም በላይ ነው። ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባለፈ ዳግም የመነሣታችን ተምሳሌት ነው። በራስ ዐቅም የመቆም፣ በራስ ፍላጎት የመመራት፣ የሉዓላዊነታችን ምልክት፤ የሀገራዊ አንድነታችን ገመድ ነው። በሕዳሴ ጉዳይ ብዙ አይተናል፣ ብዙ ተፈትነንበታል። በራሳችን ዐቅም መቆማችን የሚያስደነግጣቸው፣ በፍላጎታችን መመራት መጀመራችን የሚቆጫቸው ብዙ ጋሬጣዎችን ሲጥሉብን ነበር። “ሚስማር አናቱን ሲመቱት ይበልጥ ይጠብቃል” እንዲሉ ሆኖ፤ በዓባይ ጉዳይ በገፉን ቁጥር እየቆምን፣ በተጫኑን ቁጥር እየበረታን፣ ባዋከቡን ቁጥር ይበልጥ እየጸናን አሁን የደረስንበት ቦታ ላይ ቆመናል። በቅርቡ ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት አድርገን፣ በምርጫው ስኬት የተደሰትነውን ያህል፣ በሕዳሴያችንም ሐሴት እንደምናደርግ አልጠራጠርም።

    በሕዳሴ ግድብ ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚነታችን እንዲጠበቅልን እንጂ መቼም ቢሆን ሌሎች ሀገራትን የመጉዳት ፍላጎት ኖሮን አያውቅም። አሁንም ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ደግመን ማረጋገጥ የምንፈልገው ሐቅ፣ የዓባይ ወንዝ እንደሚያስተሳስራቸው ወንድም ሕዝቦች በእናንተ ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ የመፍጠር ፍላጎት የለንም። ዛሬም ሆነ ወደፊት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ለመመካከር በራችን ክፍት ነው። እኛንም ሆነ እናንተን ነጥሎ ተጎጂ ወይም ተጠቃሚ በሚያደርጉ አካሄዶች ላይ እንድንሳተፍ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን አይፈቅም።

    ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከዚህ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን የሚቀዳ ነው። በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ለመሥራት ሁሌም ዝግጁዎች ነን። የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላሙ እንዲጠበቅ፣ የጋራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር፣ በትብብርና በመግባባት እንድናድግ ኢትዮጵያ ትፈልጋለች፤ ጥሪም ታቀርባለች።

    የተከበራችሁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፥

    የሀገራችን መጻኢ ጊዜ ብሩህ ለማድረግ በተገቢው መወጣት ከሚገቡን የቤት ሥራዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችንን በሠለጠነ መንገድ መምራት ነው። ከላይ በመግቢያዬ እንደገለጽኩት ይኼ ኃላፊነት በመንግሥትና በተመረጠው ፓርቲ ላይ ብቻ የሚጣል አይደለም፤ አንድ አካል ልሥራው ብሎ ቢነሣ እንኳን በአግባቡ የሚወጣው ጉዳይ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አይተናል። እንኳንስ የሠለጠነ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባትን የሚያህል ነገር ይቅርና፣ አንድ ዙር ምርጫን ዴሞክራሲያዊ አድርጎ ለማጠነቀቅ ብዙ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው ካለፍናቸው ምርጫዎች በሚገባ ተረድተናል። የዘንድሮውንም ምርጫ ካለ እናንተ ድጋፍና ትብብር ፍትሐዊና ዴሞራሲያዊ በሆነ መንገድ ማከናወን ባልተቻለ ነበር።

    በቀጣይም ዓመታት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደታችን መሬት እንዲረግጥ የተለመደ ትብብራችሁና በየምዕራፉ ያላሰለሰ ድጋፋችሁ እንደሚያሻን ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ። በሀገራችን የብልጽግና ጉዞ ውስጥ የሚኖራችሁ ድርሻ ወሳኝ እንደሆነ እናምናለን።

    የፖለቲካ ልዩነቶቻችን እንዳሉ ሆነው፣ ለሀገርና ለሕዝባችን በሚጠቅሙ ማናቸውም የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ ከእናንተ ጋር በመግባባት ለመሥራት ዝግጁዎች ነን።

    ምርጫውን ስኬታማ ያደረጋችሁ ውድ የተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች፣

    ይህ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን የምርጫ ቦርድ አመራሮችና ሠራተኞች፣ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ሁሉ ከደም መሥዋዕትነት በመለስ ያለ ከፍተኛ ዋጋ ከፍላችኋል። ከግራ ከቀኝ የሚመጡትን ጫናዎች ተቋቁማችሁ በውጣ ውረዶች ሳትበገሩ ለሀገራችን የማይደበዝዝ የዴሞክራሲ አሻራ አትማችኋል፤ በዚህም ታሪክ ስማችሁን አድምቆ ይጽፈዋል።

    የጸጥታ አካላት፤ ምርጫው ሰላማዊ እንደሆን ጉልህ ሚና ተጫውታችኋል፤ እናንተ ዕንቅልፍ አጥታችሁ ሥጋቶቻችን ሁሉ እንደ ጉም እንዲተንኑ ስላደረጋችሁ ክብር ይገባችኋል። በተመሳሳይ፣ ፈጣንና ሚዛናዊ መረጃን ወደ ሕዝቡ በማድረስ በኩል የግልና የመንግስት ሚዲያዎች፤ እንዲሁም አጭር የጽሑፍ መልዕልት ስርጭት በኩል የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ሠራተኞች፣ ላበረከታችሁት አስተዋጽዖ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች።

    ውድ የፓርቲያችን አመራሮችና አባላት፥

    በዚህ ምርጫ ሕዝቡ ያስተላለፈውን መልእክት በሚገባ መረዳት የወደፊቱን መንገዳችንን ቀና እንደሚያደርገው እናምናለን። ሕዝቡ በአብላጫ ድምጽ እኛን የመረጠው ፓርቲያችን እንከኖች ስለሌሉበት አይደለም፤ ከነስሕቶቻችንን ዕድል ሰጠን እንጂ ድል አላደረግንም። ሕዝብ የመረጠን በአንድ በኩል ያጠፋናቸውን እንድናርም፣ በሌላ በኩል መልካም ጅማሮዎቻችንን እንድናስቀጥል፣ ከሀገር ግንባታ አንጻር በወሳኝ ደረጃ ላይ ያሉ የለውጥ ሥራዎችን በቀጣይ ጊዜያት ፈጽመን እንድናሰረክብ ነው። ሕዝባችን ጉድለቶቻችንን በሚገባ ያውቃል። ከስርቆት ዓመል ያልተላቀቁ፣ ለሰው ነፍስ ግድ የሌላቸው፣ ሕግን የማያከብሩ፣ ኃላፊነታቸውን የማይወጡ አመራሮች በመካከላችን መኖራቸውን ጠንቅቆ ያውቃል። ድምፁን ሲሰጠን ታረሙ፣ ውስጣችሁን አጥሩ እያለን ጭምር ነው። እኛም በተግባር ሆነን ማሳየት አለብን። ይኼን ማድረግ ካልቻልን ከአምስት ዓመት በኋላ በካርዱ እንደሚቀጣን እናውቃለን።

    በአሁኑ ምርጫ መምረጥ ያልቻላሁ ወገኖቻችን በሙሉ፥

    በልዩ ልዩ የጸጥታና የደኅንነት ምክንያቶች፣ እንዲሁም በሎጅስቲክና በተለያዩ ውሱንነቶች ምርጫው በተያዘለት ክፍለ ጊዜ መሠረት ከተቀረው ሕዝብ ጋር አብራቸሁ ድምፅ ባለመስጠታችሁ ታላቅ የሆነ ቅሬታ ፈጥሮብናል። ይኼ የሆነው ባልተጠበቁ ምክንያቶች እንደሆነ ግንዛቤ ትወስዳላችሁ የሚል ግምት አለን። ሁኔታዎች ተስተካክለው የምርጫ ቦርድ በወሰነው ቀን ምርጫው እንደሚደረግ እምነቴ ነው።

    ትግራይን በተመለከተ የትግራይ ሕዝብ በሚፈልገው መንገድ ከተደራራቢ ችግር የሚወጣበትን፣ ተያያዥ ሀገራዊ ችግሮች የሚፈቱበትን እና ሰላምና ደኅንነት የሚረጋገጥበትን የመፍትሔ አቅጣጫ እንከተላለን።

    በመጨረሻም፣ ከለውጡ ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ስለ ሀገር አንድነትና ስለ ሕዝባችን ተጠቃሚነት ቀና ቀናውን በማሰብ በመንገዳችን ሁሉ ድጋፍ ሲያደርጉልን የነበሩ አካላትን ከልብ ሳላመሰግን አላልፍም። ኢትዮጵያ በታሪክ ለውጥ ላይ ናት። በዚህ የለውጥ ሂደት ተሳፍረን የተሻለች ሀገር እንገነባለን። በዚህ ምርጫ ኢትዮጵያችን አሸናፊ ስለሆነች በድጋሚ ለመግለጽ እወዳለሁ። ቀጣይ ዘመናችንን ብሩህ ያድርግልን፤ ሁላችንም እንኳን ደስ አለን።

    ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
    ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
    ሐምሌ፣ 2013 ዓ.ም

    • በስድስተኛ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫዎችን ማሸነፉን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 3 ቀን  2013 ዓ.ም. አስታውቋል። ዝርዝሩን ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ
    • የስድስተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ውጤት መታወቅን ተከትሎ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ “ኢትዮጵያ ሀገራችን ተከብራ የምትኖረው ስንቻቻል፣ ስንደማመጥና የሌላውን ሃሳብ ስንቀበል ብቻ ነው” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
    • ይህ ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ትልቁን ሚና የተጫወተውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የሚመሩት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ “ሀገራዊ ምርጫው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት በይፋ የታየበት ነው” ብለዋል።

    ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ

    #19898
    Anonymous
    Inactive

     ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ውጤት

    ሰኔ 14 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የተካሄደው የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጤት ይፋ ተደረገ። ይህ ውጤት የሚገለፀው ባገኙት ወንበር ልክ ሲሆን በዚህም መሠረት፦

    • የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር
      – መስተዳድሩ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 23
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 23
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 22
      □ የግል ተወዳዳሪ ያገኘው መቀመጫ: 1
    • የአፋር ብሔራዊ ክልል
      – ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 8
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 6
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 6
    • የአማራ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 138
      – ሰኔ ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 125
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 114
      □ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 5
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 5
    • የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 9
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 3
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 3
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 2
    • የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር
      – መስተዳድሩ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 2
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 2
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 1
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
    • የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 3
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 3
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 3
    • የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 178
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 170
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 167
      □ የግል ተወዳዳሪዎች ያገኙት መቀመጫ: 3
    • የሲዳማ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 19
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 19
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 19
    • የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 104
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 85
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 75
      □ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 4
      □ የጌዴኦ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት: 2
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 3

    በዚህ ሐምሌ 3 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመቀመጫ ብዛት በአጠቃላይ 484 ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ በስልጣን ላይ የሚገኘው ብልፅግና ፓርቲ 410 መቀመጫ አሸንፏል። ይህም ውጤት ፓርቲውን መንግሥት ለመመሥረት ያስችለዋል።

    ይህን የምርጫ ውጤት እና የፓርቲያቸው ማሸነፍን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስተላለፉትን መልዕክት ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ

    የምርጫ ክርክር የምርጫ ውጤት

    #48240
    Semonegna
    Keymaster

    ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የኢዜማ መሪ ሆነው ስለተመረጡ እንኳን ደስ ያለዎት!
    አቶ አንዱዓለም አራጌ

    ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አያሌ ኪሎ ሜትሮች አቆራርጣችሁ ለሁለት ቀናት በዚህ ታላቅ ጉባዔ ላይ የታደማችሁ፣ የተከበራችሁና የተወደዳችሁ የጉባዔ አባለት፥ አንደኛ መደበኛ ጉባዔያችንን በአማረና በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ በመቻላችን እንኳንም ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ ያለን ለማለት እወዳለሁ።

    ኢዜማ ለሀገራችን እንግዳ የሆነዉን የዴሞክራሲ ባህል ናሙና በጓዳዉ ሲጠነስስ ጀምሮ የፓርቲያችንን መፈረካከስ የሚሹ፣ ፓርቲያችንን የሚደግፉና የፓርቲያችን አባላት ሳይቀሩ ተመሳሳይ ድምፀት ያለዉ ሀሳብ ሲያስተላልፉ ሰምተናል፤ ኢዜማ ይፈረካከሳል የሚል። ይህ ታላቅ ጉባዔ በአካሄደዉ ጥብብ የተሞላ ዉይይት ኢዜማ ከመሰነጣጠቅ ይልቅ ተጠናክሮና ፈርጥሞ እንዲወጣ ለማድረግ በመቻሉ በድጋሚ እንኳን ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ።

    ዴሞክራሲን አምጣ ለመዉለድ ባልቻለችዉ ሀገራችን ማህፀን የተፈጠረዉ ኢዜማ በራሱ ጓዳ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ እዉነተኛዉንና መሠረታዊዉን የዴሞክራሲ ችግኝ በመትከል ታሪክ ሠርቷል። ይህ በኢዜማ ጓዳ ዉስጥ የተፈላዉ የዴሞራሲ ችግኝ ነገ አባጣ ጎርብጣዉን የሀገራችንን የፖለቲካ መልክዐ-ምድር በመሸፈን፣ ሀገራችንን ለዘመናት እያቆረቆዛት የመጣዉን ዘመን ጠገብ የፖለቲካ ስብራት ለመፈወስ የመሠረት ድንጋይ እንዳስቀምጥን አማናለሁ።

    የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዚህ ጉባዔ አባለት፥ አንድ ከዚህ ወጣ ወደ አለ ጉዳይ ልዉስዳችሁ። ይህን ሰሞን የምርጫ ቅስቀሳ አድርጌ ስመለስ ልጆቼ አንድ ቀልድ ይቀልዱብኝ ነበር፤ ልክ እዚህ መድረክ ላይ የተገኙ በማስመሰል የምርጫዉን ዉጤት በድራማ መልክ ያሳዩኝ ነበር –እንዲህ እያሉ “እባካችሁ ከሦስት ተወዳዳሪዎች አራተኛ ለወጣዉ ለአንዱዓለም አራጌ ሞቅ ያለ ጭብጨባ አድርጉለት” በማለት ሲቀልዱብኝ ነዉ የሰነበቱት። ዛሬ ሟርታቸዉ ሰምሮ በምርጫዉ በመሸነፌ ጥሩ አለንጋ ገዝቼ ወደ ቤት በመግባት ብስጭቴን እንደምወጣባቸዉ ቤቱ እንዲያዉቅልኝ እፈልጋለሁ። ዛሬ እነርሱን አያድርገኝ!

    ወደ ፍሬ ሀሳባችን ልመልሳችሁ፤ ኢዜማ ሲጠነስስ ሀሳብ ነበር። ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ ድርጅታዊ ዉቅሩን አስቀምጠናል። ከዚህ አንደኛ መደበኛ ጉባዔያችን ቀጥሎ ደግሞ መሬት የቆነጠጠና፣ ሰንጥቆ መዉጣት የሚችል ድርጅት እንዲሆን ስጋ የማልበስ ሥራችንን እንቀጥላለን። ግዙፉን መዋቅራችንን አስፈላጊ የሆኑ አካላዊና ርዕዮታዊ ትጥቆችን በጥንቃቄ ካስታጠቅነዉ ከፊታችን በሚመጡ ዓመታት ለኢትዮጵያችን ፖለቲካዊ ተዓምራቶችን መሥራት የሚችል ድርጅት ይሆናል ብዬ አምናለሁ። አብዛኛዎቻችን በመርከብ ተጉዘን የምናዉቅ አይመስለንም ይሆናል። ነገር ግን መለስተኛ ከተማን የሚያክል መርከብ፣ በባህር ላይ ሲንሳፈፍ ብዙዎቻችን በቴሌቪዥን መስኮት [ሳናይ] አንቀርም። ብዙዎቻችን ይህንን ግዙፍ አካል አንድ ካፒቴን ሺህ ማይሎችን እንዴት ሊያንሳፍፈዉ እንደቻለ እያሰብን እንደመም ይሆናል፤ ነገር ግን መርከቡ ሁለንተናዊ ጤንነቱ ተጠብቆ እንዲንሳፈፍ የሚያስችሉትን አያሌ ቴክኒሽያኖች እንዘነጋለን። በአንድ ቴክኒሽያን ስህተት አንድ ኤሌክራቲካል ወይንም ሜካኒካል ክፍሉ ቢበላሽ ካፒቴኑ ምንም መፈየድ እንደማይችል የምናስተዉል ስንቶቻችን እንሆን?

    ኢዜማን የሚያክል ግዙፍ ድርጅትም ያስመዘገባቸዉን በጎ ዉጤቶች ሁሉ ያስመዘገበዉ ሁለንተናቸሁን ለትግሉ ሰጥታችሁ በየአከባቢያችን ኢዜማን ባቆማችሁ ያልተዘመራለቸሁ ጀግኖች ትልቀ ተጋድሎ ጭምር እንጅ በጥቂት አመራሮች ብቻ አልመሆኑን በአንክሮ እገነዘባለሁ። እናንተን ከመሰሉ ጀግኖች ፊት ስቆም ከአክብሮት በላይ ከልቤም ዝቅ የምለዉ ለተጋድሏችሁ ካለኝ ክብር የተነሳ ነዉ። የምርጫዉንም ዉጤት የምቀበለዉ ለእናንተ ካለኝ ትልቅ አክብሮትና ከፍ ያለ ትህትና ጋር ነዉ። ከአንድ ደሃ የገበሬ ቤተሰብ ብገኝም ሁልጊዜም የነፃነትና እኩልነት ጉዳይ ሕይወቴ የሚሾርበት ምህዋር ነዉ። ዴሞክራሲ ስንል አሸንፎ መደሰት ብቻ ሳይሆን ሽንፈትን በፀጋ መቀበልንም ያካትታል። በሂደቱ ግን ከምንም በላይ ድርጅታችን አሸናፊ አድርገናል። በቅስቀሳ ወቅት ቃል እንደገባሁላችሁ ቃሌን እጠብቃለሁ። በማያሻማ ቋንቋ ፕ/ር ብርሃኑ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እንዲመሯችሁ መርጣችኋቸዋል፤ ምርጫችሁን ተቀብያለሁ። ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ የመርጣችኋቸዉ የእናንተ ብቻ ሳይሆኑ የተፎኮካርኳቸዉ እኔና እኔን የመረጡ የጉባዔ አባላትም መሪ መሆናቸዉን ለመግለፅ እወዳለሀ! በዚህ አጋጣሚ ፕ/ር ብርሃኑን እንኳን ደስ ያለዎት እያልኩ፥ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸዉ ከልብ እመኛለሁ!!

    የምርጫ ዘመቻ ቡድኔን፣ በገንዘብና በምክር የረዳችሁኝ ዜጎች ሁሉ ከልብ እያመሰገንኩ፥ ለሽንፈታችን ተጠያቂዉ እኔና እኔ ብቻ እንደሆኑኩ ለመግለፅ እወዳለሁ!

    ዘመኑ የፈተና ነዉ፤ ዘመኑ የትግል ነዉ። በድል የሚወጣዉ ደግሞ በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመና አንድነቱን በብርቱ የሚያስጠብቅ ድርጅት ነዉ። ሁላችንም ከዚህ ሰዓት ጀምሮ እጅ ለእጅ በመያያዝ ትግላችንን እንድንቀጥል አደራ እላለሁ!

    ፍትህ እንደ ቀጥር ፀሐይ፣ ፍቅር እንደ ኃይለኛ ጅረት፣ ወንድማማችነት እንደ አበባ ጉንጉን በኢትዮጵያ ላይ ለዘላለም ይንገስ!!

    [caption id="attachment_48242" align="aligncenter" width="600"]ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ አንዱዓለም አራጌ ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ አንዱዓለም አራጌ[/caption]

    #53297
    Semonegna
    Keymaster

    የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ይከናወናል – የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልነት ጥያቄ ላይ የሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ቦርዱ በተገቢው መንገድ ኃላፊነቱን ይወጣል ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናገሩ።

    በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኙ የጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዲኦ፣ ኮንሶ፣ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ፣ እና አሌ ልዩ ወረዳዎች የሚካሄደውን ሕዝበ ውሳኔ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚከናወን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

    የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በሰጡት መግለጫ፥ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከጊዜ ወደጊዜ አሠራሩንና ደረጃውን እያሳደገ በመሆኑ ሕዝብ ውሳኔውም በተሻለ ሁኔታ እንዲከናወን ያደርጋል ብለዋል። ሕዝብ ውሳኔው ሰላማዊ፣ ነጻና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ቦርዱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ይወጣል ሲሉ ዋና ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

    ሕዝበ ውሳኔው ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ከሚደረጉ ዝግጅቶች መካከል የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ምልመላ ሥራ እንደሚገኝበት ብርቱካን ሚደቅሳ ገልጸዋል። ለምልመላ በሚቀርቡ እያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚ ላይ ቅሬታ አለኝ ያለ አካል ሪፖርት ማድረግ የሚችልበት አሠራር መዘርጋቱን አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም በፖለቲካ ፓርቲ፣ በሲቪክ ማኅበራትና በተቋማት ካልሆነ በቀር በግለሰብ ደረጃ በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ቅሬታ የሚቀርብበት አካሄድ እንዳልነበር አስታውሰዋል። በሕዝብ ውሳኔው ላይ ግን በምርጫ አስፈጻሚዎች ሥነ-ምግባርና ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ አለኝ የሚል ማንኛውም ግለሰብ በማስረጃ በተደረፈ መንገድ ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

    በእስካሁኑ የአስፈጻሚዎች ምልመላ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የተሳተፉ ዘጠኝ ሺህ አስፈጻሚዎች በደቡብ ኢትዮጵያ የሕዝበ ውሳኔ ላይ በድጋሚ ለማገልገል ፍቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ፥ በአጠቃላይ 18,750 የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች እንደሚያስፈልጉ አስረድተዋል።

    ቀሪዎቹን የምርጫ አስፈጻሚዎች ለመመልመል ቦርዱ የቅጥር ማስታወቂያ እንደሚወጣ ገልጸዋል። እንደ ብርቱካን ሚደቅሳ ከሆነ፥ ከምልመላ ሥራው ባለፈ ለሕዝበ ውሳኔው መሳካት የሚረዱ የውይይት መድረኮች ከሲቪክና ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከማኅበረሰቡና ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር ተካሂደዋል።

    በእስካሁኑ የዝግጅት ሥራ የሕዝበ ውሳኔው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በአርባ ምንጭ ከተማ ተቋቁሟል። በዞንና በልዩ ወረዳዎች መከፈት ያለባቸው 11 ጽሕፈት ቤቶች እስከትናንትናው ዕለት ድረስ አልተከፈቱም ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የየአካባቢው አስተዳደሮች በወቅቱ አስፈላጊውን ትብብር ባለማድረጋቸው የተፈጠረ በመሆኑ አስተዳደሮቹ አስፈላጊውን ትብብር በወቅት እንዲያደርጉ ዋና ሰብሳቢዋ ጥሪ አቅርበዋል።

    በደቡብ ብሔሮች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እንዲሁም አምስት ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ዜጎች ደቡብ ኢትዮጵያ በሚል አዲስ ክልል እንመስርት፤ አሊያም በነበረው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልነት እንቀጥል በሚል ሕዝብ ውሳኔውን ያደርጋሉ።

    ለሕዝበ ውሳኔው በመራጭነት ሊመዘገቡ የሚችሉ ግምታዊ መራጮች ሦስት ሚሊዮን 106,585 ሰዎች መሆናቸውን ቦርዱ አሳውቋል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ 410.1 ሚሊዮን ብር ከመንግሥት ተፈቅዷል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት 

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ

Viewing 13 posts - 16 through 28 (of 28 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.