ስምንተኛው የበጎ ሰው ሽልማት የእጩዎች ጥቆማ የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ይጀመራል

Home Forums Semonegna Stories ስምንተኛው የበጎ ሰው ሽልማት የእጩዎች ጥቆማ የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ይጀመራል

Viewing 3 posts - 1 through 3 (of 3 total)
  • Author
    Posts
  • #13541
    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ለሀገር እና ለሕዝብ አርአያነት ያለው ታላቅ ተግባር ያከናወኑ ኢትዮጵያውያንን በየዓመቱ ዕውቅና የሚሰጠው የበጎ ሰው ሽልማት በ2012 ዓ.ም. ለሚያካሄደው ስምንተኛው መርሐ-ግብሩ የእጩዎችን ጥቆማ ከየካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. አንስቶ ከሕዝብ መቀበል እንደሚጀምር መርሐ-ግብሩን የሚያዘጋጀው የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት አስታውቋል።

    ለስምንተኛው የበጎ ሰው ሽልማት መርሐ-ግብር ከየካቲት 1 እስከ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በአስር ዘርፎች እጩዎችን እንደሚቀበል ድርጅቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ያሳወቀ ሲሆን ዘርፎቹም፥ መምህርነት፣ ሳይንስ (ሕክምና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ምህንድስና፣ ኬሚስትሪ፣ አርክቴክቸር፣ ወዘተ)፣ ኪነ ጥበብ/ሥነ-ጥበብ (በወግ ድርሰት)፣ በጎ አድራጎት (እርዳታና ሰብዓዊ አገልግሎት)፣ ቢዘነስና ሥራ ፈጠራ፣ መንግሥታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት፣ ቅርስና ባህል፣ ማኅበራዊ ጥናት፣ ሚዲያና ጋዜጠኝነት፣ እና ለኢትዮጵያ እድገት አስተዋጽዖ ያበረከቱ ዳያስፖራዎች ናቸው።

    ካለፈው ዓመት ሰባተኛው የበጎ ሰው ሽልማት አንስቶ በሽልማት ዘርፎች ውስጥ የተካተተው ለአገራችን እድገት አርአያነት ያለው አስተዋጽኦ ያበረከቱ ዳያስፖራዎች እውቅና የሚያገኙበትን ዘርፍ ጨምሮ እስካሁን ሥራ ላይ ባዋልናቸው ዘርፎች በሙሉ ጥቆማ ማድረግ ይቻላል።

    በተለይ የማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት በቂ እጩዎች ባለመጠቆማቸው ሽልማቱ ስላልተካሄደ፣ በዚህ የሙያ ዘርፍ ያሉ ደርዝ ያለው ሥራ የሠሩ ኢትዮጵያውያንን ለማክበርና አርአያነታቸውን ለማጉላት ሕዝቡ በተለይም ለሙያው ቅርብ የሆኑ ሁሉ ጥቆማቸውን እንዲያቀርቡ ድርጅቱ ጠቁሟል። እንዲሁም በኪነ-ጥበብና ሥነ-ጥበባት ዘርፍ በዘንድሮው መርሐ-ግብር ከሥነ-ጽሑፍ መስኮች አንዱ በሆነው የወግ ድርሰት ላይ ትኩረት ይደረጋል። የወግ ድርሰት ኢ-ልቦለዳዊ በሆነ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ የሚመደብ፣ ጥበባዊ በሆነ የአጻጻፍ ብቃት የሚቀርብ ሲሆን፥ በርካታ አንጋፋና ወጣት ደራሲያን የድርሰት በረከታቸውን አቅርበውበታል። ስለዚህ የዘርፉን ጥበባዊነት ለማጉላትና ደረሲያኑንም ለማበረታታት የዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት የኪነ-ጥበባት ዘርፍ የሙያ መስክ ተደርጎ ተመርጧል።

    ባለፉት ሰባት የሽልማት ወቅቶች፤ አገራችን የምትኮራባቸውና የላቀ አርአያነት ያለው ተግባር ያከናወኑ ሰዎችን እውቅና የተሰጣቸው ከሕዝብ በቀረቡ ጥቆማዎች መሰረት ነው። የበጎ ሰው ሽልማትን ለዚህ ያበቃውም በሽልማቱ ሂደት በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሕዝብ ተሳትፎ በመኖሩና ይህም ከዓመት ዓመት እያደገ በመሄዱ ስለሆነ ይህ ተሳትፎ አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድርጅቱ ጠይቋል። ጠቋሚዎች እጩዎችን በሚጠቁሙበት ጊዜ እጩው ግለሰብ ለአገርና ለሕዝብ ያከናወኑትን ተግባር በዝርዝር እንዲገልጹልንና የሚገኙበትንም አድራሻ መጠቆም እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

    ስለዚህ ይህን የበጎ ሰው ሽልማት ዓላማን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከላይ በተገለጹት መስኮች ለጥቆማ በተመደበው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ሽልማት ብቁ ናቸው የሚላቸውን እጩዎች እንዲጠቁሙ ጥሪ ተደርጎላቸዋል። ጥቆማ የምንቀበለው በስልክ፣ በቫይበር (Viber)፣ በቴሌግራም (Telegram)፣ በኋትስአፕ (WhatsApp)፣ በኢ-ሜይል (email) እና በፖስታ ነው። አድራሻዎቹም፦

    ስልክ፦ 0977-23-23-23 (ቫይበር፣ ቴሌግራምና ኋትስአፕን ጨምሮ)
    ኢሜይል፦ begosewprize@gmail.com
    ፖስታ፦ 150035፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ናቸው።

    የበጎ ሰው ሽልማት ዓላማ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ መልካም የሚሠሩ፣ ሀገራዊ ተልዕኳቸውን በብቃትና በልዩ ልዕልና የሚወጡ፣ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ለውጥ አምጪ ተግባር የፈጸሙ፤ በብዙ ሰዎች የማይደፈረውን ተግባር በተነሣሽነት የከወኑ፣ ለድጋፍ ፈላጊ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነት ወስደው የሠሩ፣ የሀገሪቱ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል፣ እንዲጠበቅ፣ የሀገሪቱ ሥልጣኔ ከፍ እንዲል የሠሩ ኢትዮጵያውያንን በማበረታታት፣ ዕውቅና በመስጠትና በመሸለም ሌሎችን በጎ ሠሪዎች ለሀገራችን ማፍራት ነው።

    ከሕዝብ የሚቀርበው ጥቆማ ከተጠናቀቀ በኋላ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ፣ ለመጨረሻው ውድድር ተመርጠው ስማቸው ለዳኞች የሚላከውን እጩዎች ማንነት፣ ሕዝብ እንዲያውቀው ለማድረግ፤ አውቆም ለሀገርና ለሕዝብ ባበረከቱት አስተዋጽዖ እንዲያከብራቸው ዝርዝራቸውን በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ይፋ ይደረጋል።

    የመጨረሻውን የየዘርፎቹን የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ምርጫ የሚያደርጉት ለእያንዳንዱ የሽልማት ዘርፍ በዳኝነት የተመረጡ ባለሙያዎች ናቸው። ዳኞቹ በእውቀታቸውና በሙያቸው አንቱ የተባሉ፣ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውና በታማኝነት ምርጫውን ያከናውናሉ ተብለው የታመነባቸው ናቸው። ለእያንዳንዱ ዘርፍም አምስት ዳኞች ተመርጠው ምርጫውን ያከናውናሉ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የበጎ ሰው ሽልማት

    #15464
    Anonymous
    Inactive

    ስምንተኛው የበጎ ሰው ሽልማት በልዩ ሁኔታ እንደሚካሄድ ተገለጸ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – ስምንተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ሥራ ጋር ለሕዝብ አርዓያነት ያለው ተግባር ላይ ያተኮረ ሆኖ በልዩ ሁኔታ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

    ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ የሚካሄደውን የበጎ ሰው ሽልማት መርሃ ግብር አስመልክቶ ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የበጎ ሰው የሽልማት በጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፥ ወቅታዊ ሁኔታውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት በዘርፎች ላይ ሳይሆን በሁለት ወቅታዊ እና ሀገራዊ አንኳር ጉዳዮች ላይ ልዩ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ኢትዮጵያውያን የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል።

    እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ምክንያት በዓለም ላይም ሆነ በሀገሪቱ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የተነሳ ሽልማቱን በተለመደው መንገድ ለመስጠት አይቻልም፤ በመሆኑም የዘንድሮውን መርሃ ግብር በተለየ መንገድ ለማከናወን ተወስኗል፤ በበሽታው ምክንያት ከሰዎች ንክኪና ግንኙነት ነጻ በሆነ መንገድ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሽልማቱ ከዚህ ቀደም ከተለመደው በተለየ ሁኔታ ይካሄዳል።

    የበጎ ሰው ሽልማት በጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ጸሐፊ አቶ ቀለመወርቅ ሚዴቅሳ በበኩላቸው፥ ድርጅቱ በየዓመቱ በአስር ዘርፎች በየሙያቸው ለሀገራቸው የላቀ ተግባር ላከናወኑ ኢትዮጵያውያን በሕዝብ ፊት ዕውቅና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፥ “በጎ ሰዎችን በማክበርና ዕውቅና በመስጠት ሌሎች በጎ ሰዎችን እናፍራ” በሚል መሪ ሃሳብ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሽልማቱ ሲከናወን መቆየቱን ጠቁመዋል።

    የዘንድሮውን ሽልማት ለማከናወንም ከየካቲት 1 እስከ መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሁለት መቶ በላይ ዕጩዎችን በመቀበል ታሪካቸውንና አበርክቷቸውን የማጥናት ሥራ መሰራቱንም አመልክተው፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመቀስቀሱና በሀገሪቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ስርጭቱ እየተባባሰ በመምጣቱ በዕቅዱ መሠረት እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ መሥራት ባለመቻሉ የዘንድሮው ሽልማት በልዩ ተሸላሚ ሥነ ሥርዓት እንዲካሄድ በቦርዱ አባላት በተወሰነው መሠረት የሚከናወን መሆኑን አቶ ቀለመወርቅ አስታውቀዋል።

    አቶ ቀለመወርቅ ሁለት ወቅታዊና አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮች መመረጣቸውንና ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና በኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ሥራ ለሕዝብ አርዓያነት ያለውና የላቀ ተግባር ላከናወኑ ግለሰቦችና ተቋማት በልዩ ሁኔታ የዘንድሮው በጎ ሰው ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ተናግረዋል።

    የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሳካ፣ ለመጀመሪያው ዙር ውሃ ሙሌት እንዲበቃና በሕዝቡ ዘንድ ብሔራዊ ኩራት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ በጎ ሰዎችና ድርጅቶች የዘንድሮው የበጎ ሰው ተሸላሚ ይሆናሉ ብለዋል።

    የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገሪቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በሕዝብ ላይ የሚደርሰውን የጤና ችግር ለመከላከል፣ በበሽታው መስፋፋት የተነሳም በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ እና በተለያዩ መንገዶች ለተጎጂ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ የተጉና አርዓያነት ያለው ተግባር የፈጸሙ ኢትዮጵያውያን የሚመሰገኑበት እንደሚሆንም አክለዋል።

    በሁለቱ ጉዳዮች ዙሪያ ለሀገራቸው የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ስምንት ኢትዮጵውያን ግለሰቦችና ድርጅቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና የጤና ተቋማት ደንብን ባከበረ መንገድ በተመጠኑ ታዳሚያንና በቀጥታ የሚዲያ ስርጭት በመታገዝ ጳጉሜ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚካሄድ መርሃ ግብር የዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት የሚከናወን ይሆናል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    ስምንተኛው የበጎ ሰው ሽልማት

    #15741
    Anonymous
    Inactive

    8ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ስምንት ግለሰቦችንና ተቋማትን የዓመቱ በጎ በማለት ሸልሟቸዋል

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በልዩ ሁኔታና መስፈርት ጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም በኢንተርኮንቲነንታል አዲስ ሆቴል የተከናወነው 8ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ስምንት የተለያዩ ግለሰቦችን፣ ድርጅቶችንና ማኅበራትን በጎ ተሸላሚዎች በማለት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

    የዘንድሮውን የስምንተኛውን ዙር የበጎ ሰው ሽልማት እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ በተለመዱት በአስሩ ዘርፎች እና በተለየ ድምቀት እንዳይካሄድ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) የሽልማቱ አዘጋጆችን እንደገታቸው ጋዜጠኛና የሥራ አመራ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ ሕሊና አዘዘ በመግቢያ ንግግሯ ላይ ገልጻለች።

    የዚህን ዓመት ሽልማት ለማከናወን ከየካቲት 1 እስከ መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ከ200 በላይ የዕጩዎች ጥቆማ ከሕዝብ መቀበላቸውን እና የሽልማት ድርጅቱ የሥራ አመራር ቦርድ የዕጩዎቹን ታሪካቸውንና አብርክቷቸውን በማጥናት ላይ እያለ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመከሰቱ ምክንያት የተሟላ ዝግጅት ሊያደርጉ አለመቻላቸውን ጋዜጠኛ ሕሊና ጠቅሳለች።

    የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዲ.ሪ) ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ፣ እንዲሁም የበጎ ሰው ሽልማት የበጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም የአግዮስ መጻሕፍት ሥራ አስኪያጅ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኘተዋል።

    የ8ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚዎች የሚከተሉት ናቸው፡-

    1. አቶ ካሊድ ናስር

    የመጀመሪያ ልዩ ተሸላሚ ባለፉት አምስት ወራት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገዛ መኖሪያ ግቢያቸውን ሳይቀር በመስጠት፣ መጠለያ የሌላቸውን (የጎዳና ተዳዳሪዎችን) በመደገፍ የበጎ አድራጎት ሥራ የሠሩት አቶ ካሊድ ናስር ናቸው።

    1. አቶ ኪሮስ አስፋው

    አቶ ኪሮስ አስፋው ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያለማቋረጥ መቶ ጊዜ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ የገዙ እና በደም መፍሰስ የሚሞቱ እናቶችን ለመታደግ ለ21 ጊዜ ደም የለገሱ ግለሰብ ናቸው።

    1. አቶ ብንያም ከበደ

    የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን መሥራች ጋዜጠኛ ብንያም ከበደ የ8ኛው የበጎ ሰው ሽልማት 3ኛ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል። ጋዜጠኛ ብንያም ከበደ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ልጆች በየቤታቸው ሲሆኑ የሚመለከቱት የሚመጥናቸውና በተለያየ ቋንቋ መሰናዶዎች የሚቀርብበት የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቭዥንን ከመክፈት ጀምሮ ያደረጉት አስተዋጽዖም የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ አድርጓቸዋል።

    1. ጋዜጠኛ መሀመድ አል-አሩሲ (محمد العروسي / Mohammed Al-Arousi)

    በአረብኛ ቋንቋ የኢትዮጵያን ሀሳብና እውነት (በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ) በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲያስረዳና ሲከራከር የቆየው አቶ መሐመድ አል-አሩሲ (محمد العروسي / Mohammed Al-Arousi) የዘንድሮ የበጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ ሆኗል። ከኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች በሳዑዲ አረቢያ የተወለደው መሐመድ አል አሩሲ፥ የሕዳሴ ግድብን በሚመለከት ስለኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሙግት በማድረግ ይታወቃል።

    1. ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ

    በሕዳሴ ግድብ ላይ እንዲሁም በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ባላት የልማት ተጠቃሚነት ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉትና በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ስለሕዳሴ ግድብ ተግተው በመሞገት የሚታወቁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ የዘንድሮው የበጎ ሰው ተሸላሚ ሆነዋል።

    1. ኢትዮ ቴሌኮም

    ኢትዮ-ቴሌኮም በዓመቱ ውስጥ በተለይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል መልዕክት በማስተላለፍ፣ ማዕድ በማጋራት፣ እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሠራቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎቹ የ2012 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ሆኗል። ድርጅቱን በመወከል የተገኙት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ሽልማቱን ተረክበዋል።

    1. የሕክምና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች

    የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችን ከተከሰተ ጀምሮ ራሳቸውን አደጋ ላይ ጥለው የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ከፊት የተሰለፉ የጤና ባለሞያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የ2012 ዓ.ም የዓመቱ የበጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በመድረኩ የጤና ባለሞያዎችንና የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን በመወከልም ሽልማቱን ተቀብለዋል።

    1. የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሠራተኞች በሙሉ

    የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጸጥታውን የሚቆጣጠሩ የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፓሊስ አባላት፣ እንዲሁም የሕዳሴው ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ከመጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በጉባ በሥራ ላይ የሚገኙ የግድቡ ሠራተኞች የ2012 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። በጉባ የሚገኙ ሠራተኞችን ወክለው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ክፍሌ ሆሮ ሽልማቱን ተረክበዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    8ኛው የበጎ ሰው ሽልማት

Viewing 3 posts - 1 through 3 (of 3 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.