Home › Forums › Semonegna Stories › ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
Tagged: አበበ ገላው
- This topic has 35 replies, 3 voices, and was last updated 1 year, 11 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
June 12, 2021 at 7:41 pm #19647AnonymousInactive
የሰሞኑ “ቃል በተግባር” የተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘጋቢ /ገላጭ/ ፊልም በሁለት ኢትዮጵያውያን አተያይ
[ቃል በተግባር ― በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ እና በአቶ ያሬድ ኃይለማርያም አተያይ]- ቃል በተግባር ― ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት
[በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)]
ኢትዮጵያን እንደሀገር ያገለገልኳት፣ ያፈቀርኳት በ1970ዎቹ መጨረሻ (1976-79) ባለው ጊዜ ነበር፤ በመጀመሪያው ዙር የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ዘመኔ። ከትምህርት ቤት በግዴታ ታፍሼ የገባሁበት የብሔራዊ ውትድርና ከሀገሬ ጋር ልብ ለልብ አስተዋወቀኝ፤ አፈቀርኳት።
ግዳጄን ፈጽሜ፣ ዩኒቨርሲቲ ተምሬ፣ በ1983 አ.ም. ወደ ሥራ ስሰማራ ኢትዮጵያን አጣኋት። በብሔር ፖለቲካ ሴራ የተካኑ፣ ስሟን መጥራ የሚዘገንናቸው መሪዎች እጅ ወድቃለች። ለጎሳና ቋንቋ ድንበር ከልላ፣ ባንዲራ [ሰንደቅ ዓላማ] ሰቅላ እሷ ፈዝዛለች።… ለብሔረሰቦችና ለቋንቋዎች እኩልነትና ለሰብዓዊ መብት መከበር ዝም ብዬ አላውቅም፤ እሟገታለሁ። ባንዲራቸው ሲከልላት፣ የምትተነፍሰው አየር ሲያጥራት፣ ኢትዮጵያን ሲረሷት ግን አዝናለሁ፤ ያመኛል።
ከረዥም ጊዜ በኋላ በትላንትናው ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት። ዘመንን መስላ፣ ተስፋ አዝላ አነበብኳት። በሦስት ዓመት፣ ያለጥላቻና ግጭት ዜና ነግቶ በማይመሽበት ሀገር፣ ‘የእኔ ሀሳብ ካልሆነ ሀገሬ ትበተን’ በሚል ጽንፍ ረገጥ ፖለቲካዊ መርገምት ውስጥ፣ እንኳን በልዕልና መሥራት፥ በትክክል ማሰብስ ይቻላል ወይ? ያውም ይህ ሁሉ ኃላፊነት ለተጫነበት መሪ?!
የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው!
አዎ፣ ሀገራችን የብሔር ፖለቲካው ካጣባት ደዌ አልተፈወሰችም። አዎ አሜሪካ ማእቀብ ጥላብናለች። አዎ ሱዳን ድንበራችንን ተሻግራ መሬታችንን ይዛለች። አዎ የትግራይ ወገኞቻችን በከፍተኛ ሰብዓዊ ችግር ላይ ናቸው። አዎ የኤርትራ ወታደሮች ከሀገራችን ጨርሶ አልወጡም። አዎ ሸኔና የጁንታው ርዝራዦች በሚሰነዝሩት ጥቃት አሁንም ዜጎች ህይወታቸውን እያጡ ነው። አዎ የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቷል።… ሀገራችን ውስጥ በርካታ ችግሮች፣ በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።
እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉ እነዚህ አስደናቂ ፕሮጀክቶች መሠራታቸው አግባብ አይደለም በማለት ሰዎች ለጥላቻቸው የሰበብ ድር ያዳውራሉ። እኔን የሚገርመኝ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ መሠራት መቻላቸው ነው።
መሠራት የነበረበት ያልተሠራ አለ። ካልተሠራው የበለጠ የተሠራው የወደፊት መንገዳችንን ያሳያል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሀገሪቱ ባጀት ሳይነካ፣ የተሸለመውን የግል ገንዘብ ሳይሰስት፣ ወዳጆቹን ለምኖ በሦስት ዓመት፣ ጥላቻና ዘለፋን ቁብ ሳይል ይህንን ሠራ። ባለቤቱ ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዲሁ ከሀያ በላይ ትምህርት ቤቶችን በገጠር ቀበሌዎች ገነባች። ለመሆኑ እነዚህን ሰዎች የማናደንቀው ከእነማን ጋር እያወዳደርናቸው ነው? እንኳን በሦስት ዓመት፣ በሦስት አስርታት ውስጥ የዚህን ግማሽ የሠራ መሪ ኖሮን ያውቃል?
እንደመሪ እነሱ ይህን ሠሩ፤ ያልመለሷቸው ችግሮችም አሉ። እኛስ! እንደ ዜጋ ባለፉት ሦስት ዓመታት ምን ሠራን? እኛ እንደዜጋ ያለነው የት ነው? የሠሩት በጎ ተግባር ወይስ ያልመለሷቸው ችግሮች አካል ነን? በዋናነት የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው። ሀገራችን በውስጥና ውጭ ችግር ተተብትባለች፤ ፈተና ላይ እንደሆነችም እናውቃለን። ዋናው፣ እያንዳንዳችን ማወቅ ያለብን ጉዳይ ግን ሀገራችንን የተበተባት ችግር፣ የተጋረጠባት ፈተና አካል አለመሆናችንን ነው። እና እንጠይቅ! እንደዜጋ የቆምነው የት ነው?!
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ደራሲና ገጣሚ ሲሆኑ፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሂዩማኒቲስ፤ የቋንቋዎች ጥናት የጆርናሊዝምና የኮሚኒኬሽን ኮሌጅ ውስጥ ደግሞ መምህር ናቸው። ከዚህ ቀደም ለህትመት ከበቁላቸው ሥራዎች ውስጥ የማይፃፍ ገድል፣ የራስ ምስል፣ ያልተከፈለ ስለት፣ የወይራ ስር ጸሎት፣ የማይጻፍ ገድል፣ የተስፋ ክትባት፣ እና ፍካት ናፋቂዎች የጠቀሳሉ። በተጨማሪም በብሔራዊ ቲያትር ቀርቦ በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው “ደብተራው” የተሰኘው የሁለት ገጸባሕርያት ቲያትር (two-handler theater) ደራሲ ናቸው።
- ቃል በተግባር ― እያደነቅን ስጋታችንንም እንገልጻለን፤ አቧራው መሬት ላይ ያለ ግፍ፤ ሃሜቱም ሃቅ ነው
[አቶ ያሬድ ኃይለማርያም]
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ የሠሯቸውን እና እየሠሯቸው ያሉ ድንቅ ነገሮችን አደንቃለሁ። ለዚህ ሥራቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ከሠሯቸው ሥራዎቹ አንዱ የሆነውን የእንጦጦ ፖርክን የመጎብኘት ዕድል ገጥሞኛል። የሚያስደምም ድንቅ ሥራ ነው።
ከትላንት መግለጫቸውም ሁለት ነገር መረዳት ይቻላል። አንደኛው ሀገር ለማልማት ብዙ እቅድ እና ህልም እንዳላቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ይህን ህልማቸውን እውን ለማድረግ አንባገነን እሰከመሆን የሚሄዱ መሆናቸውን ነው። አገሪቱ አሁን ያለችበትን ውጥንቅጥ እና አሳሳቢ ችግር፣ የተቃዋሚዎቻቸውን ቅሬታ እና በመንግሥታቸው ላይ የሚሰነዘሩ ቅሬታዎችን ‘አቧራ’ በሚል ገልጸውታል። “ሀሜት አቧራ እንጂ አሻራ መሆን አይችልም። አቧራውን ንቀን አሻራ ማኖራችንን እንቀጥላለን” የምትለዋ ንግግራቸው አለቃቸው የነበሩትን መለስን [የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን] አስታወሱኝ። ባጭሩ የመለስን የመታበይ ንግግር ነው የደገሙት። መለስ ‘ውሾቹ ይጮኻሉ፤ ግመሎቹም ጉዟቸውን ይቀጥላሉ’ ነበር ያሉት?
ታቃዋሚዎቻቸውን ውሻ አድርገው እና ተቋውሟቸውንም እንደ ውሻ ጩኸት ቆጥረው እሳቸው ከጉዟቸው ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል እንደማያስቆማቸው ሊያውም በፓርላማ ፎክረው ነበር። የመሠረት ድንጋይ ጥለው ያስጀመሩትን የሕዳሴ ግድብ መጨረሻ ለማየትና ሪባን ለመቁረጥ ግን አልታደሉም። ግመሎቹስ ዛሬ ወዴት አሉ? አብይም ያች በሽታ እየታየችበት ነው። ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ያፈጠጠ እና አሳሳቢ ችግር እንደ አቧራ መቁጠር መጥፎ መታበይ ነው። አቧራው እንዲሰክን የሚቀርቡ ምክርና ወቀሳዎችንም እንደ ሀሜት መቁጠር ሌላው አሳሳቢ የክሽፈት ምልክት ነው።
ሕዝብ እየተራበ ነው፤ የኑሮ ውድነት ሌላ የቀውስ ምንጭ ነው፤ ያልተረጋጋ ፖለቲካም የልማት ጸር ነው፤ ጦርነትም አውዳሚ ነው፤ የመብት ጥሰቶች መበራከት የአፈና ሥርዓት መሳለጫ ነው። እነዚህ ችግሮች አቧራ አይደሉም። በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ የሚቀርብብዎት ወቀሳና ነቀፌታዎች ሀሜት አይደለም። ልማቱን ግፉበት፤ መታበይዎን አቁመው ለዲሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰብዓዊ መብቶች እና ለፍትህ ቀናዕይ በመሆን እንደ ልማቱ አፋጣኝ መልስ ይስጡ። ካልሆነ ግን መካር እንደሌለው ንጉሥ… ይሆናሉ።
አቶ ያሬድ ኃይለማርያም መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia) የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
June 16, 2021 at 2:42 am #19678AnonymousInactiveእብለት የሌለበት ምስክርነቴ – ለዶ/ር ብርሀኑ ነጋ
(የትነበርክ ታደለ /ጋዜጠኛ/*)
በሀገራችን የዲሞክራሲ ትግል ውስጥ ትልቁ ፈተና ኢ-ዴሞክራሲያዊና አምባገነን መንግሥታት ብቻ አይደሉም፤ የሴራ ምሁራንም ጭምር እንጂ። በገዛ ራሳችን ምሳሌ “ቀና ቀና ያለች ማሽላ አንድም ለወፍ፥ አንድም ለወንጭፍ” እንደ ተባለው የሀገራችን የሴራ ምሁራን ከመካከላቸው ቀና ያለውን በማጥቃት ብዙ ፍሬ ያዘሉ ሰብሎቻችንን አምክነው ኖረዋል። በዚህ ድርጊታቸው ከአምባገነን መንግሥታት በላይ ሀገራችንን መከራ ውስጥ ጨምረዋል። ብርሀኑ ነጋ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የመፍትሄ ምንጭ እንጂ ጸረ-ኢትዮጵያዊ ወይም ጸረ-ኢትዮጵያ ተብሎ ለተከታታይ ዓመታት በአደባባይ የሚዘመትበት ሰው አልነበረም!!
ብርሀኑ…
ከጽንፈኛ ብሔርተኞችና ከአክራሪ ሀይማኖተኞች በሚወረወርበት ሾተል ጀርባው እየደማ የዜግነት ፖለቲካን የሙጥኝ ያለው ‘በኔ ጉዳት ኢትዮጵያ ትዳን’ ብሎ እንጂ ኢትዮጵያን ስለሚጠላ አይደለም!
እንዲህም ተባለ እንዲያ ዛሬ ያ መገፋቱ ፍሬ አፍርቶ እነሆ ከሦስት የጭለማ ዓመታት በኋላ ሀገር ኖራ፣ ምርጫም ኖሮ፣ ወደ ፊት ልንሻገር ነው ብለን የምናስብበት የተስፋ ጭላንጭል ላይ ደርሰናል።
‘ምርጫ አለ’ ያልነው ብርሀኑ ስላለ ነው! ኢትዮጵያ ያንን ሁሉ መከራ አልፋ ለምርጫ የደረሰችው ብርሀኑ ነጋ በፖለቲካ ስም ሀገር የመናድ የገመድ ጉተታው አካል ስላልነበረ ነው!
ዶላርና የጥይት አረር ታቅፈው ከውጭ የገቡ ተቃዋሚዎችና ሚሳኤል የታጠቀች ህወሓት “ሕገ-መንግሥቱን ትነኩትና” እያሉ በሚያስፈራሩበት በዚያ የሦስት ዓመት ጭለማ ክረምት ውስጥ ሕዝብ ብርሀኑን ሰምቶ “እውነት ነው፤ ጊዜው የሕገ መንግሥት ጥያቄ ማንሻ አይደለም” ብሎ ጋብ ባይል ኖሮ፤ “ይህ የምንፈልገው ሥርዓት አይደለም፣ ይሁን እንጂ ለሀገራችን ስንል እንደግፈው፣ ከችግሮቹ ይልቅ ጠንካራ ጎኖቹን እያሳየን ወደ ፊት እንግፋው” ብሎ ከመንግሥት ጎን ቆሞ “አለሁ!” ባይል ኖሮ የዛሬው የምርጫ ክርክር ቅንጦት በሆነ ነበር።
በእውቀቱ ልክ እያሰበ በሀገር ፍላጎት ልክ እየወሰነ ባይራመድ ኖሮ “በለው! በለው! ፍለጠው! ቁረጠው!” ባዮች ጋር በስሜት ጋልቦ ቢሆን ኖሮ… እንኳን አንግቦት የተነሳውን የዜግነት ፖለቲካ ለአካለ ምርጫ ማድረስ ይቅርና፥ ለሀገራችንም ጦስ በሆነ ነበር።
ይህ ሁሉ ለሕዝብ ግልጽ የሆነ ሀገራዊ አበርክቶው በሴራ ምሁራን ትንታኔ እየታጀለ ቀን ከሌት መዶስኮሩ ሰውዬው በእርግጥም ፍሬ ያዘለ ሰብል መሆኑን ከማሳየቱ በቀር እንደሚሉት ጥላቻ በልቦናው የተሸከመ ጸረ-ሕዝብና ጸረ-ሀገር መሆኑን ፈጽሞ አይመሰክርም!!
― ይድረስ ለብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ―
የመጨረሻ ውጤቱ፣ ጥራቱና መጠኑ ምንም ይሁን ምን፣ ዴሞክራሲን አዋልደሀል!! ጨቅላውን ዴሞክራሲ አንስቶ መሳም፣ አቅፎ ማሳደግ የኛ ድርሻ ይሆናል! ለዘመናት የተጫነብንን የዘር ፖለቲካ የምናራግፍበትን አንድ ዘዴ የሆነውን የዜጋ ተኮር ፖለቲካ አስተምረህ፣ አዋቅረህ፣ ከምርጫው ኮሮጆ አድርሰህልናል – ያለፈውን ጥፋት ላለመድገምና እንደ ቀሪው ዓለም በሀሳብ ላይ መሠረት ያደረገ ፖለቲካን መምረጥ የኛ ፋንታ ይሆናል። በብዙ መከራዎች መካከል ባለች ሀገር ውስጥ የሰከነ የተቃውሞ ፖለቲካን በማራመድ ሀገርና መንግሥት በፈለጉን ጊዜ አቤት እያልን በቀረው ደግሞ እየተቃወምንና እየተቸን መጓዝ የምንችልበትን የሰለጠን አስተሳሰብ አሳይተኸናል። ይህን መንገድ ተከትሎ ያለጩኸት እና ያለ ወከባ መንግሥት መቀያየርን መልመድ የኛ ተግባር ይሆናል።… በቀረው ደግሞ ምርጫው በሰላም ተጠናቆ ቢሆን በፓርላማው፣ ከዚያም ሲያልፍ በመንግሥት ስልጣን ላይ ሆነህ ቀሪ ህይወትህን ለዚህች ደሀ ሀገራችን የበለጠ እንድትሠራ መልካም ውጤት እመኝልሀለሁ! በቀረው ግን ውለታህ አለብን እንጂ ግዴታችን የሌለብህ ከሚጠበቅብህ በላይ ያገለገልከን ታላቅ ዜጋ ነህና እናከብርሀለን!!!
* አቶ የትነበርክ ታደለ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚጽፍ ጋዜጠኛ ሲሆን፥ በፌስቡክ ገጹ ሊያገኙትና ጽሁፎቹን ሊከታተሉ ይችላሉ።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
July 7, 2021 at 2:08 am #19856AnonymousInactiveህወሓት ጠቡ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው
በአቶ ዮሐንስ መኮንን
“ከማዕከላዊው የመንግሥት የሥልጣን ማማ ተገፍቼያለ” ብሎ ያኮረፈው የህወሓት ቡድን ከሦስት ዓመታት በፊት የጦርነት ዳርዳርታ በጀመረ ሰሞን መገዳደል ማንንም አትራፊ ስለማያደርግ የጦርነት ጉሰማውን እንዲተው በሀገር ሽማግሌዎች፣ በልኂቃንም ሆነ በተራ ዜጎች ሳይቀር ተለምኖ ነበር። የህወሓት ሰዎች ግን “ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው” እያሉ ያፌዙ እንደነበር ኢትዮጵያውያን ሁላችንም የምናስታውሰው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
የጦርነት ጉሰማው ድንበሩን አልፎ “የ45 ደቂቃ መብረቃዊ ጥቃት” ሲሉ በራሳቸው አንደበት በነገሩን አረመኔያዊ የክህደት እርምጃ ወገናቸው በሆነው የሀገር መከላከያ ላይ የፈጸሙት ጥቃት እና በማይ ካድራ ንጹሐን ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ ለህወሓት ሰዎች እና ደጋፊዎቻቸው ዛሬ ላይ “ጀብድ” ይምሰላቸው እንጂ የፈጸሙት ተግር በታሪክ ፊት አንገታቸውን የሚያሰደፋ የነውር ጥግ ነበር።
ይህንኑ የህወሓት አረመኔያዊ ተግባ ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊታችን በወሰደው የአጸፋ እርምጃ ዋንኛው ዓላማ ህወሓትን ከነመዋቅሯ መደምሰስ ቢሆንም ጦርነቱ በንጹሓን ዜጎች ይልቁኑም በሴቶች እና በሕጻናት ላይ ያደረሰው ጉዳት የሚያሳዝነን እና የሚያሳፍረን ክስተት ነበር።
ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጪ መንግሥታት ተጽእኖም ይሁን በጦርነቱ አክሳሪነት የተነሳ “የጽሙና ጊዜ ለመስጠት” የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ ከክልሉ ሠራዊታችን ማስወጣቱ ተገቢ እርምጃ ነው። ይህ ማለት ግን “ትግራይን የራሱ ሉዓላዊት ሀገር አካል መሆኗ አበቃ” ማለት አይደለም። በግልጽ ቋንቋ ለመግለጥ “ህወሓት ይሻለናል” ለሚሉ አባላቶቿ ደጋፊዎቿ “ዕድል ለመስጠት ያለመ” መሆኑን እገነዘባለሁ።
ይሁን እንጂ መንግሥት ተገፍቶ ሕግ ወደማስከበር ጦርነት ሲገባም ሆነ አሁን ትግራይን ለቅቆ ሲወጣ ጉዳዩን ያየዘበት መንገድ ሌላ ዘላቂ ሀገራዊ ችግር ተክሎብን እንዳያልፍ ሊጠነቀቅባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ ይሰማኛል። በምክንያት ላስረዳ፡
ህወሓት ያኮረፈውም ሆነ የተጣላው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንጂ ከአንድ ሕዝብ ጋር እንዳልነበረ የሚስተው ያለ አይመስለኝም። ጦርነቱ እንደተጀመረ ተደራጅቶ በቅርብ ርቀት ላይ ገኝ የነበረው የአማራ ልዩ ኃይል ቀድሞ የህወሓትን ተስፋፊ ጦር መመከቱ የሚያስመሰግነው ተግባር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሂደት ግን በዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ በአንዳንድ “ልኂቃን” ጭምር የህወሓት ጠብ “ከአማራ ልዩ ኃይል” ጋር አስመስለው መግለጻቸው ተገቢ ካለመሆኑም በላይ የአንድን ጠባብ ቡድን የእብሪት ጦርነት በሁለት ሕዝቦች መካከል የተደረገ ጦርነት አስመስሎ ማቅረቡ ጉዳቱ ውሎ አድሮ የሚያመረቅዝ ቁስል እንዳተርፈን ያሳስበኛል። በእርግጥ የመከላከያ ሠራዊታችን ከሁሉም ብሔሮች የተውጣጣ ጦር መሆኑ እየታወቀ ተደጋግሞ “አማራ ልዩ ኃይል” የጦርነቱ ፊት አውራሪ ተደርጎ መሳሉ የህወሓት ጠብ ከአንድ ሕዝብ ጋር አስመስሎታል።
በቀደም እለት ጠቅላይ ሚንስትሩ በፓርላማ ባደረጉት ንግግርም “የአማራ ሕዝብ ለህወሓት አይንበረከክም” የሚለው ንግገራቸው ምንም እኳን ሕዝቡን ለማጀገን እንደተጠቀሙበት ብረዳውም የአማራ ልዩ ኃይል ለሀገር አንድነት የከፈለውን መስዋእትነት ክልሉን ለመከላከል እንደተከፈለ መስዋእትነት አሳንሶ ወደማየት እንዳይተረጎም ያሳስበኛል።
ዛሬ ደግሞ የጀርመኑ ዶቼቬሌ ሂውማን ራይት ዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው ህወሓት “በአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች ተይዘውብኛል” የሚላቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመንጠቅ በርካታ ታጣቂዎቹን እያንቀሳቀሰ መሆኑን ሰምተናል። እንደዘገባው ከመጠለያ ካምፖች ሳይቀር ወጣቶችን በገፍ እየመለመለች ነው። (ህወሓት ሰንአፌ በረሃ አርቅቃ ኢትዮጵያ ላይ የጫነችውን “ሕገመንግሥት” ሳይቀር በተቃረነ መንገድ የአማራ ገበሬዎችን በማፈናቀል በወረራ የቀማቻቸውን ወልቃይት እና ሁመራን የመሳሰሉ ለም መሬቶች በግፍ መንጠቋ ይታወሳል)
የህወሓትን ትፍራፊ ጦር እንደ አመጣጡ ለመመለስ የአማራ ልዩ ኃይል የሚያንስ ባይሆንም ትንኮሳውን ማስቆም ያለበት ዋንኛው ፊትአውራሪ ጦር ግን የሀገር መከላከያ ኃይል ነው ብዬ በጽኑ አምናለሁ። የልዩ ኃይል ተሳፎ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም የአማራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች በመከላከያ ሠራዊት ሥር ታቅፈው ስምሪት ሊሰጣቸው ይገባል።
“ኢትዮጵያን ሳላፈርስ እንቅልፍ አይወስደኝም” ብሎ የማለውን የህወሓት ትርፍራፊ ጦር መመከት እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም መደምስ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የቅድሚያ ቅድሚያ ኃላፊነት ነው። ምክንያቱም የህወሓት ጸብ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው!
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
July 18, 2021 at 4:23 am #19942AnonymousInactiveይድረስ ለትግራይ ወገኖቼ!
በአቶ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ
የትግራይ ሕዝብ ከባለጌ ልጆቹ በላይ ሀገሩን የሚመርጥበት ጊዜ ደርሷል። በተለይም የትግራይ እናቶች እና አባቶች በራሳቸው ልጆች እኩይ ስምሪት ቀደምቶቻቸው ለአንድነቷ ሰማዕትነትን የተቀበሉላት ኢትዮጵያችን ክብሯ እንዲጎድፍ በዝምታ መተባበራቸውን ይበቃል ለማለት ትክክለኛው ወቅት አሁን መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል።
የዘመን ተጋሪዬ ለሆናችሁ የትግራይ ወጣቶችም “ጅብም ብሆን የወንዝህ ጅብ ስለሆንሁ፤ ልበላህ መብት አለኝ” የሚሉ ሀገር አጥፊዎችን በመተው ከሀገራችን ኢትዮጵያ እና ወንድሞቻችሁ ጎን እንድትቆሙ ወንድማዊ ጥሪዬን አቀርብላችኋለሁ።
የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጨዋው የትግራይ ሕዝብ በሀገር አፍራሽ፣ ዘር አጥፊና ዘራፊ ብኩኖች በኩል ዘላቂ መብቶቹ፣ ጥቅሞቹና ፍላጎቶቹ እንደማይከበሩለት አውቃችሁ፤ ሁለንተናው ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጋር የተሸመነውን የትግራይ ሕዝብ ታሪክ፣ ክብርና የወደፊት በጎ ተስፋ በሚመጥን ስምሪት እንድትገኙ ዝቅ ብዬ እለምናችኋለሁ።
ታላቁ የትግራይ ሕዝብ በሌባ አይወከልም! ከዘፍጥረት ጀምሮ እስካሁን ድረስም እናት ኢትዮጵያም ሆነች ወንድሙ የአማራ ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ የክብሩ ምንጭ የደኅንነቱ ደጀኖች እንጂ የስጋቱ ምንጮቹኘች ሆነው አያውቁም፤ አይሆኑምም። እንዴት ሀገር ገንቢው ትግራይ በሀገር አፍራሽ ይወከላል?
ትግራይ የምታሸንፈው ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ብቻ ነው፤ ትግራይ አንገት ደፍታ ኢትዮጵያ አትቃናም። በትግራይ ለቅሶ ፈገግታው የሚደምቅ አንድም ኢትዮጵያዊ አይኖርምም። ሌባና ዘራፊ፤ ባንዳና ሀገር አጥፊ ግን ከየትም ይሁን የትም የጋራ ጠላታችን ነውና በጋራ ልንደመስሰው ይገባናል። በባንዳ ሞት ደረት የሚደቃና ፊት የሚነጭ ሊኖር አይገባም።
እናም ለተከበራችሁ የትግራይ አባቶቼና እናቶቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ፥ ስለደማቁ የትናንት ትናንታችን ብቻ ሳይሆን ስለብሩህ ነጋችንም ብላችሁ ለኢትዮጵያችን ኅልውና እንዲሁም ለሕዝባችን ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት መረጋገጥ በአንድነት እንድንቆም ስል ጥሪዬን ደግሜ ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።
ሁሉም ችግሮች ከጋራ አቅማችን በታች ናቸው። ስንደማመጥ፣ ስንከባበርና ስንተማመን ከባዱ ቀላል ይሆናል። ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ሁላችንም እናሸንፋለን!
አቶ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ
አቶ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ በፌደራል የጤና ሚኒስቴር፥ የማኅበረሰብ ጤና ኤክስፐርት (public health expert) ሲሆኑ፤ በፖለቲካ እንቅስቃሴአቸው ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው። እርሳቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ወይንም በትዊተር ሃንድላቸው ሊያገኟቸው ይችላሉ።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
June 28, 2022 at 12:20 am #41750SemonegnaKeymasterየአማራን ሕዝብ ሰቆቃ እያየ እንዳለየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ…
ጋዜጠኛ አበበ ገላውየአማራ ሕዝብ በደለኝ የሚል ካለ ማስረጃውን ይዞ ይቅረብ። አንድም ሰው አይገኝም። የኦሮሞም ይሁን የትግራይ፣ የአፋርም ሕዝብ ይሁን የሲዳማ፣ የጋምቤላም ይሁን የሶማሌ፣ የጉራጌም ይሁን የወላይታ ሕዝብ… ፈጽሞ ማንንም በድለው አያውቁም። የትኛውም ሕዝብ በጅምላ ግለሰቦችንም ይሁን ቡድኖችን ሊበድል ፈጽሞ አይችልም። ስለዚህም ነው በዓለማችን ላይ እጅግ አሰቃቂው ግፍ በተፈጸመበት አውሮፓ ናዚዎች ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ አድርጎ ጀርመኖችን እያደነ የሚገድልና የሚያፈናቅል ቡድን ኖሮ አያውቅም። በእኛም ሀገር ሞሶሎኒ በመርዝ ጋዝ ሳይቀር ለፈጸመው ግፍ ንጹኃን የጣሊያን ዜጎችን አሳደንም ይሁን ጨፍጭፈን አናውቅም። እንዲህ ዓይነቱን አስነዋሪ ወንጀል ብንሞክረውም ግፍ እንጂ ፍትሃዊ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም።
በእኛ ሀገር በክፋት ህወሓት በዋነኛነት ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው መዋቅርና ቅርጽ የሰጠውን ተረት በማንገብ በጥንታዊ ነገሥታትና መንግሥታት ለተፈጸሙ በደሎች መላውን የአማራ ሕዝብ በነፍጠኛነት ፈርጆ ከምንም የሌሉበትን ምሲኪን ድሆች በጅምላ መግደል፣ ማሳደድ፣ ማፈናቀል፣ አፍኖ መውሰድ፣ አካላዊና ስለልቦናዊ ጥቃት መሰንዘር የተለመደ ክስተት ከሆነ አርባ አመታት ተቆጥረዋል። አብዛኛው የአማራ ተወላጅ ሀገሩ እንዳይፈርስ፣ ሕዝብ ለበቀል እንዳይነሳ እና ማለቂያ የሌለው እልቂትና ውድመት እንዳይደርስ በሚል የአስተዋይነት መንፈስና ባህል የሆዱን በሆዱ ይዞ በትዕግስት ህመሙን እና ሀዘኑን አፍኖ በኢትዮጵያዊነት ጨዋነት ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተቻችሎና ተከባብሮ ለመኖር የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል።
ይሁንና አሳዛኙ ሃቅ የሕዝቡን ትዕግስት እንደ ፍርሃት የቆጠሩ እኩይ ኃይሎች የአማራን ሕዝብ በጅምላ ዘውትር ከማሸማቀቅ አልፈው የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ግፍና ማፈናቀል ያለማቋረጥ እየፈጸሙበት ይገኛሉ። የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነትን የተረከበው “የለውጥ” ኃይልና መንግሥትም ከእነ መለስ ዜናዊ ባልተለየ ሁኔታ የአማራን ሕዝብ ሰቆቃ እያየ እንዳለየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ… ሕዝቡ በገፍ እያለቀና እየተሰቃየ ባለስልጣናቱ ሌላው ቀርቶ የረባ የሀዘን መግለጫ፣ ማጽናኛም ይሁን የአንዲት ሰከንድ የህሊና ጸሎት ነፍገውታል።
የዚህ ታጋሽ ሕዝብ ትግስት አልቋል። መንግሥት የሕዝብን ደህንነትና ሰላም በአግባቡ መጠበቅ ካልቻለና የዜጎቹ የጅምላ ሞት፣ ሰቆቃ መፈናቀል፣ የደም ጎርፍና እንባ ግድ የማይለው ከሆነ ሕዝቡ ሰላሙን፣ ደህነንቱና ዜግነታዊ መብቱን ሙሉ በሙሉ የሚያከብርለትና እኩልነትና አንድነትን የሚያረጋግጥለት መንግሥት እንዲመጣ አምርሮ ከመታገል ውጭ አማራጭ እንደማይኖረው ሊታወቅ ይገባል።
ጋዜጠኛ አበበ ገላው (facebook.com/agellaw)
[caption id="attachment_41752" align="aligncenter" width="600"] በጀርመን የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ሰላማዊ ሰልፍ ላይ[/caption]
January 28, 2023 at 2:10 pm #55737SemonegnaKeymasterመርገምት፤ ግንድ ግንዱን መገርሰስ
(ያሬድ ኃይለማርያም)በዘመነ ወያኔ የጀመረው ሀገራዊ ክሽፈት በብዙ እጥፍ አቅሙንና ፍጥነቱን ጨምሮ ኢትዮጵያን ቁልቁል እየነዳት እንደሆነ የቅርቡ በእስልምና እምነት ላይ አነጣጥሮ የነበረው ደባና ክፍፍል ጋብ ሲል በሰሞኑ ቆብ ያጠለቁ ነውረኞች ድራማ መተካቱ ጥሩ ማሳያ ነው። ወያኔ ስልጣን ከያዘች ጀምሮ ካደረገችው በርካታ ኢትዮጵያን የማዳከም እኩይ ሥራዎች መካከል የሀገሪቱን እድሜ ጠገብ ተቋማት ማፈራረስ፣ ሕዝቧን ያስተሳሰሩ ማኅበራዊ መስተጋብሮችን መበጣጠስ፣ እድሜ ጠገብ ሀገራዊ ትውፊቶችን ማራከስ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ክብርና ሞገስ ያላቸውን አውራዎች ማዋረድ፣ ማሸማቀቅ እና ሕዝብ እንዲንቃቸው ማድረግ ነበር። በወቅቱ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ‘ወያኔ ግንድ ግንዱን እየገነደሰች ነው’ ብለው ነበር።
አንጋፋ የሙያ ማኅበራትን አፍርሶ በተለጣፊ ካድሬዎች መተካት፣ ዓለም ያከበራቸው ምሁራንን በአደባባይ መዝለፍና ማዋረድ፣ ማሰርና ማዋከብ፣ የሀይማኖት ተቋማትን አናታቸውን ጨምድዶ በመያዝ የአፈናው መዋቅር አካል ማድረግና የፖለቲካ ምርኩዝ አድርጎ ምዕመናኑን ለማሸማቀቂያነት መጠቀም፣ ታሪክን በተዛባ ትርክት መቀየርና ጥራዝ-ነጠቅ ትውልድ መፍጠር የተሳካው የወያኔ ትልም ነበር። አንጋፋውን የመምህራን ማኅበር፣ የሠራተኞች ኮንፌደሬሽን፣ የነጻ ጋዜጠኞች ማኅበር እና አከርካሪያቸው ተመትቶ በካድሬዎችና በፖለቲካ ተሻሚዎች እጅ የወደቁትን የትምህርት ተቋማትና የጏይማኖት ቤቶችን ሁኔታ ልብ ይለዋል።
ይሄ ኢትዮጵያን ለማዋረድ፣ ታሪኳን ለማዛባት፣ ነጻና ጠንካራ ተቋም የሌላት ደካማ ሀገር እንድትሆን እና አዲስ የታሪክ ድርሳን ለመጻፍ በወያኔ የተጀመረው ግንድ ግንዱን የመደርመስ እኩይ ተግባር ዛሬም ወያኔ ባሰለጠነቻቸው መንደርተኛ ካድሬዎች አፍጥጦና አግጥጦ መምጣቱ፣ ምናልባትም እጅግ በከፋና አስፈሪ በሆነ መልኩ መከሰቱ ማንኛውንም ጤነኛና ቅን አሳቢ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንቅልፍ የነሳው ጉዳይ ይመስለኛል።
ወያኔ ከርክማና ኮትኩታ ያሰለጠነቻቸው የትላንት ጨቅላ ካድሬዎች፣ የዛሬ ሀገር መሪዎች በሰለጠኑበት መንገድ ኢትዮጵያን አውራ ግለስብ እና አውራ ተቋማት የማሳጣት የክሽፈት ምሪታቸውን ምንም ሳይሳቀቁና ያለ ምንም አፍረት ቀጥለውበታል። ኢትዮጵያ ዛሬ ማባሪያ በሌለው በመከራዎች ናዳ ከግራ ቀኝ እየተወገረች ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት እንኳ አጣዬና አካባቢዋ በዘር ፖለቲካ በተመረዙ አክራሪዎች በእሳት ቶን ውስጥ ሲለበለቡና ጥይት ሲያጓራባቸው፤ በተመሳሳይ ቀናት የብዙ ዘመናት ታሪክ ያላትና የጽናት ተምሳሌት የሆነችው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከጉያዋ በወጡ ባለቆብ ካድሬዎች ስትናጥ ከረመች። ለእኔ አጣዬ ለስንተኛ ጊዜ የተከሰተው በአክራሪ ታጣቂዎች ጥቃት ስር ውላ ለቀናት በእሳት መንደድና የቤተክርስቲያን በተመሳሳይ ጊዜ የተኩላ ለምድ በለበሱ ሰዎች በነገር እሳት መለብለብ ውላቸውም ሆነ ምንጫቸው አንድና አንድ ብቻ ነው። ሀገራዊ የፖለቲካ ክሽፈት ያስከተላቸው ችግሮች ናቸው። መዳረሻ ግባቸውም እንዲሁ አንድ ነው። አክተሮቹም ግብራቸው ቢለያይም፣ ውሏቸውና የተሰማሩበት ግንባር ቢራራቅም ከጀርባ ሆነው ነገሩን ለሚያቀነባብሩትና ለሚመሩት ሰዎች ግን አንድ ግብና አንድ መዳረሻ ነው ያላቸው፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ግንድ ግንዱን የመገርሰስ ስልቶች አካል ናቸው። ባጭሩ ኢትዮጵያን አዳክሞ የዛሬ ክልሎችን የነገ ራስ-ገዝ ሀገር የማድረግ ጭንጋፍ የሆነ የፖለቲካ ንድፍ ማሳለጫዎች ናቸው።
እስኪ በዚህ 30 ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተዋከበ፣ ያልተዋረደ፣ ክብሩ ያልተገፈፈ፣ በካድሬዎች ጭንጋፍ እሳቤ ያልተጨናገፈ፣ ያልተዘረፈ ተቋም ጥሩልኝ? በጭንጋፍ እሳቤ ሀገር የማጨንገፉ እኩይ ሥራ በብዙ መልኩ ለመሳካቱ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ጥሩ ምስክር ነች። እስኪ እንደ ሕዝብና እንደ ሀገር ያልከሸፍንበትን ጎናችንን ንገሩኝ? በትምህርት ጥራት መቀመቅ መውረዳችንን የትምህርት ሚኒስትሩ ትላንት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ውጤት ሲናገሩ አብረው አርድተውናል፤ የሀይማኖት ተቋማቶቻችን የጨነገፉ ካድሬዎች መፈንጫ ከሆኑ ዘመናት ተቆጥሯል፤ አንጋፋ የሚባሉ ተቋማትች ገሚሱ ፈርሰዋል፤ የተቀሩት ካለመኖር ባልተሻለ ሁኔታ ተዳክመዋል፤ ለሀገር ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ምሁራን ከነመኖራቸው ተረስተዋል፤ ምሁራኖቹ ያደራጇቸው የትምህርት ተቋማት ከሳይንሳዊ ምርምር ይልቅ የብሔር ፖለቲካ ሰለባ ሆነዋል፤ የሀገር ባለውለታ የሆኑ አውራዎች ለበጎ ሥራቸው የስድብና የጥላሸት ካባ በላያቸው ተደፍቶ እንዲሸማቀቁ ተደርጓል።
ዛሬ መከራው በብዙ እጥፍ ቢበረታም ቢያንስ ቁጭ ብለን የሃፍረት፣ የክሽፈት፣ የስጋትና የምሬት እንቆቋችንን እየተጎነጨን የምንቆዝምበት ምርጥ ምርጥ ፖርኮች ተሠርተውልናል። አንድነት በሌላት ሀገር ውስጥ በአንድነት ፖርክ ውስጥ ቁጭ ብለን ለምን አንድነት እንዳጣን ማሰላሰል እንችላለን።
ለማንኛውም ሀገርን አውራ በማሳጣትና ግንድ ግንዱን እየገነደሱ በደረቅ ጭራሮ ሀገርን ለማቆምና ለማጽናት እንደማይቻል የመጣንበት ረዥም እርቀት ጥሩ ማሳያ ነው። ጭራሮ ተሰብስቦ ቢታሰር እንኳ ችቦ ይሆናል እንጂ ግንድ ሊሆን አይችልም። ሀገር የሚጸናው በጠንካራ ተቋማት፣ በደፋርና እውነተኛ ምሁራን እና ቅን አሳቢና በጎ ራዕይ ባነገቡ የፖለቲካ ልሂቃን ነው። ፖለቲከኛውም፣ ቄሱም፣ ሼሁም፣ ምሁሩም፣ ተማሪውም እኩል በከሸፉበት ሀገር ግን አውራና ግንድ አይኖርም። ጭራሮ ብቻ እንጂ። አውራ ያጣ ሕዝብ ቀፎው ጠፍቶበት እንደተበተነ የንብ መንጋ ነው። ለራሱም ለሌላም ስጋት ነው። ወደ ቀልባችን ቶሎ ተመልሰን አውራዎቻችንን ከፊት ካላስቀደምን፣ ሀገር ጸንታ እንድትቆም ግንድ የሆኑንን ተቋማትና ግለሰቦች ጨርሰው ሳይጠፉ ካልደገፍናቸው እና ሁሉን ነገር ለጭራሮዎች ከተውን እንደ ሀገርም፣ እንደ ሕዝብም ተረት የምንሆንበት ዘመን እሩቅ አይሆንም።
- ቃል በተግባር ― ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.